Thursday, 1 January 2015

እውነትን ፈልጓት፤ ታገኟታላችሁም!

እውነትን ፈልጓት፤ ታገኟታላችሁም!

አሰፋ ምን ተስኖት

ክፍል አንድየተከበራችሁና የተወደዳችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ሆይ፤ እትብታችሁ ስለተቀበረባት የምትወዷት ሀገራችሁ ኢትዮጵያም ሆነ ስለ ሃይማኖታችሁና ስለ ቤተ ክርስስቲያናችሁ ስታስቡ ሁሌም አስተዋይ፤ አርቆ አሳቢ፤ ብልህና ንቁ ሁኑ እንጂ ባማሩ ቃላት በመሳብም ሆነ ልብሰ ተክህኖና ግርማ ሞገስን በማየት የተንኮልና የሃሰት ሰለባ እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ።
“የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ፤ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች፤ ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነብቢያት ተጠንቀቁ” ተብሏልና (የማቴ. ወ. ም. ፯ ቁጥር ፩፭)

በለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ሁሉም የሚያውቀው ነው፤ መንስኤው ማን እና ምንድን ነው ከተባለ ደግሞ እውነተኛው መልስ ሥጋዊ ጥቅምን በማስቀደም ለሥልጣን፤ ለንዋይና ለዝና ያደሩ ጥቂት ካህናት የፈጠሩት ችግር መሆኑ የተረጋገጠ ነው።

እነዚህ ችግር ፈጣሪ ጥቂት ካህናት ልብሰ ተክህኖውን ለብሰው፤ የጌታን መስቀል በመያዝ ካህን መስለው ለመታየት ይጥራሉ እንጂ አንዳችም ለካህን የተገባ ሥነ ምግባር የሌላቸው ፍሪሃ እግዚአብሔር የሚባል ነገር ጨርሶ የራቃቸው፤ በማንኛቸውም ስፍራና ቦታ ያለምንም ፍርሃትና ሰቀቀን በድፍረትና በጭካኔ የሚዋሹና የሚክዱ ናቸው።

ውሸታቸው እንደታወቀባቸው ሲረዱ ደግሞ ሃሰትና ክህደታቸውን ወደማያውቀው ህብረተሰብ ዘንድ በመሄድ ነገ ቅጥፈቴ ይታወቅብኛል የሚለው ሳያስፈራቸው የለየለትንና ዓይን ያወጣ ሃሰትን እውነት አስመስለው በሕዝብ ውስጥ በማሰራጨት በነሱ ሃጢአትና ችግር ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲጣላና እንዲፋጅ ሌት ተቀን ይደክማሉ።

ሕዝበ ክርስቲያኑም ነገሮችን አጣርቶ እውነቱን እንዳይረዳ የራሳቸው የሆነ የብረት አጥር በመሥራት ዋሽተውና ደልለው ከጎናቸው ያቆሙት ሕዝበ ክርስቲያን ወደ ሌላው ጎራ እንዳይሔድ አንዱ በሌላው ላይ ጥላቻን አብቅሎ በጠላትነት እንዲተያይ የሚችሉትን የተንኮል ሥራ ሁሉ ሳይታክቱ ያከናውናሉ።

ይህንን ከፈጸሙ በኋላ ራሳቸው የፈጠሩትን ችግር በምእናን መከፋፈልና መጠላላት የተነሳ አስመስለው በማቅረብ ራሳቸውን እንደ ጲላጦስ ከደሙ ንጹሕ ነኝ በማለት ያለ ሃፍረት ይለፍፋሉ።

መቸም የሚገርም ነው፤ ምእመኑን ጣቱን የሚጠባ ህጻን አደረጉት አሁንስ። ትላንት ሲዋሹና ሲያታልሉት ሳያውቅ በየዋህነት፤ አውቆም በይቅር ባይነት ባለፋቸው ዘለዓለም የውሸት ናዳ እየጫኑበት የሚገዙት መስሏቸዋል።

በቅርቡ በእነዚሁ የእግዚአብሔርን መኖር በረሱና የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ባረከሱ ጥቂት ካህናት ተዘጋጅቶ በፌስ ቡክ ላይ የተለጠፈ ጽሑፍ ሲታይ አሁንም ሌላ ሕዝብን የማታለሊያና የማደናገሪያ ሃሰትን በመንዛት ሕዝብን አሳስቶ አንዱን ክርስቲያን በሌላው ክርስቲያን ወገኑ ላይ በማስነሳት በተከፋፈለው ሕዝበ ክርስቲያን ተጠቅመው የጓጉለትን ስጋዊ ዓላማ ለማሳካት ከመጣር አለመቆጠባቸውን የሚመሰክር ነው።

ከቶ ሕዝበ ክርስቲያኑ እነሱ እንደሚያስቡትና ዝቅ አድርገው እንደሚያዩት በእነሱ ውሸትና ተንኮል እየተነዳ እውነትን አጥቷት ይኖር ይሆን? አይምሰላቸው ይህ በዚህ አይቀጥልም፤ እውነት ትዘገያለች እንጂ መምጣቷ መች ይቀራል። ደግሞስ መቸ እውነት በውሸት ተሸንፋ ሞታና ተቀብራ ታውቅና፤

ብትቀበርም ከመቃብር ትወጣለች። የጌታችን የመድሐኒታችን የእየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤም የሚያረጋግጥው ይህንኑ ነው።
ጽሑፉ “በለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ላለፉት 2 እና 3 ዓመታት እልባት ሳያገኝ “ምህመናትን” ለሁለት ከፍሎ የሚገኘው አለመግባባት ዛሬ ቤተ ክርስቲያኗ ደጃፍ ላይ ድንኳን ጥለው የሚገለገሉት “ምህመናን” ቤተ ክርስቲያኗን ላለፉት 20 እና 30 ዓመታት የተጠቅምንባት እኛ ምህመናን ቤተ ክርስቲያኗ እኛ ነን ሻይ፤ ቡና እንጀራ የመሳሰሉትን ሸጠን የገዛነው፤ እኛ ይህንን ስላደረግን ልናዝባት የሚገባን እኛ ነን፤ ሃገረ ስብከትም ሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ አያገባውም፤ የሚለው ሃሳብና ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየተገለገሉ ያሉት ምህመናን ደግሞ እያሉት ያሉት የምንተዳደረው በቅዱስ ሲኖዶስ የመበላይነትና በአገረ ስብከቱ ስር በመሆን ሲሆን ምንም እንኳን ለቤተ ክርስቲያኑ ግዢ እንጀራም ሆነ ሻይ ቡና ብንሸጥም፤ ያልችንን ገንዘብ ብንለግስም የቤተ ክርስቲያኑ ፈላጭ ቆራጭ መሆን አንችልም በማለታችው ነው....” እያለ ያትታል።

“አዕምሮአቸውም በጠፋባቸው፤ እውነትንም በተቀሙ እግዛብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነሲህ ካሉት ራቅ” ፩ኛ ጤሞቲ.፮፤፬-፮።

ከላይ የተጠቀሰው ጽሑፍ ከእነዚሁ እግዚአብሔርን የማይፈሩና ሕዝብን ከሚንቁ ጥቂት ካህናት የተሰራጨ ነጭ ውሸት ሲሆን ሕዝብ ያወቀው ፀሐይ የሞቀው መሠረታዊ ሃቅ ግን የችግሩ መንስዔና ምክንያት አዲስ በተረቀቀ የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ የአባ ግርማን በገንዘብ ላይ እንዳሻቸው የማዘዝ፤ ደምወዝ የመጨመር፤ ጉርሻ የመስጠትና ሳይተኩና ሳይለወጡ ለዘለዓለም ስልጣን ላይ እንዲቆዩ የሚያደርጋቸውን ማሻሻይ ረቂቅ አባ ግርማ ካሳደሟቸው ጥቂት ካህናት ጋር ሆነው በማቅረባቸው በዛ ምክንያት በተነሳ ውዝግብ ነው። በእርግጥ ከዛ በኋላ ለዚህ መሠረታዊ ችግር የተለያየ ሽፋን እየተሰጠው ሕዝብን ለማወናበድ ሲሞከር ተቆይቷል።

አባ ግርማ ሥልጣናቸው ከሚነካ ቤተ ክርስቲያን ብትፈራርስና ሕዝበ ክርስቲያኑ እርስ በእርሱ ቢጨራረስ እንደሚመርጡ ያላቸውን ቁርጠኝነትና ጭካኔ በተግባር አስመስክረዋል።
ከዓመት በፊት የተፈጸመውን የሩቁን ትተን፤ በቅርቡ በራሳቸው ደጋፊዎችና ተከታዮች መካከል የተነሳውን ውዝግብ ማጤን ያሻል። አቅሌሲያ በሚባለው ስብስብ አማካኝነት የአባ ግርማን ከአስተዳዳሪነት ሥፍራ ዞር የማድረግ ነገር ሲነሳ የአባ ግርማ ምላሽ ምን ነበር? ምንስ አደረጉ? ምንስ በማድረግ ላይ ናቸው? ይህንን ስልጣኔን አትንኩ ጸብ የሲኖዶስና የሃገረ ስብከት ጉዳይ ነው በማለት የሃሰት ሽፋን ሊሰጡት አይችሉም። አይኑን አፍጥጦ የመጣው አሁንም የእሳቸው ሥልጣን ጉዳይ በመሆኑ በድጋሜ እንደ ፌንጣ ሊያዘልላቸው ችሏል።

አንዱን ክርስቲያን በሌላው ወገኑ ክርስቲያን ላይ አነሳስቶ እርስ በእርሱ ለማቃቃርና ለማፋጀት በማሰብ አዳዲሶቹ መላዕክት የመሳሰሉ ወጣቶች፤ ተብለው በአባ ግርማ እና በመሪ ጌታ ዓለማየሁ የተሞካሹትን ወጣቶች ስብስብ መጠሪያ የሆነውን አቅሌሲያ “አቅለቢስ” በውስጡ ያሉትንም እንዳላወደሱና እንዳልካቡ “በሀጢአት ተወልደው በሃጢያት የኖሩ” በማለት ሃዘኔታ የሌለው እጅግ አፀያፊ ስድብን ያዘለ ጽሑፍ ያሰራጨባችውስ ማን ነበር? ሊንኩን በመጫን ጽሑፉን ያግኙ።

http://www.tigraionline.com/letter-of-petition-london-debrestion.pdf

ቀድመው ነገሩን የተረዱት የቤተ ክርስቲያኑ አባላት ገና ከጅምሩ ለአባ ግርማ ተከታዮች ለማስረዳት የሞከሩት ይህንኑ ሃቅ ነበር። መታወቅ ያለበት ነገር እነዚህ ዛሬ ወጣቶቹን በመላዕክት የተመሰላችሁ እያሉ የሚያሞካሿቸው ካህናት ትላንትና አዛውንቱንና ልዩ፤ ልዩ ሙያ ያላቸውን ምእመናንን መንፈስ ቅዱስ እየመራችሁ የምትሰሩ መላዕክትን የመሰላችሁ እያሉ ሲክቧቸውና ከፍ ከፍ ሲያደርጓቸው ነበር የኖሩት፤ በኋላ ግን የሥልጣንና የንዋይ ጉዳይ ሲመጣ ነው አናውቃችሁም ብለው በመካድ ይባስ ብለው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ እቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ እንዳትደርሱ በማለት በደብዳቤና በሴኩሪቲ ሊያባርሯቸው የሞከሩት።

አሁንም ወጣቶቹን መጠቀሚያ ካደረጉ በኋላ እነሆ የማትቀረዋ እውነት ከሃሰት ተለይታ ጎልታ መታየት ስትጀምር አናውቃችሁም ማለት ጀመሩ፤ ቀጥለውም ከቻሉ ቤተ ክርስቲያን እንዳትደርስ የሚል ማዘዣ ማውጣታቸው የማይቀር ነው ርህራሄ የላቸውምና፤
አባ ግርማ የሥልጣን መነካት ጉዳይ ከአቅሌሲያ ሲመጣባቸው ከለንደን ዘለው አዲስ አበባ በመሄድ የተለመደ ውሸትን በድፍረት እውነት አስመስሎ የመናገር ባህሪያቸው ተጠቅመው የሚሉትን ብለው በመመለስ እዚህ የሚንጫጩትን ጸጥ አድርጌአቸዋለሁ እያሉ በመፎከር ላይ ይገኛሉ። ድል አድራጊነታቸውንም ለማሳየት ሲሉ ተደርጎ በማይታወቅ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያኑ መዝጊያዎች ላይ ስማቸውንና ሥልጣናቸውን የሚገልጽ በቀለም ያሸበረቀ ማስታወቂያ አስለጥፈዋል።

አባ ግርማ ወደ አዲስ አበባ ባደረጉት ዘመቻ ተሳክቶላቸውም ይሁን በሌላ አይታወቅም በአማራጭነት ቀርበው የነበሩት አዲስ መጤው መነኩሴም ወደ አዲስ አበባ እንደሄዱ ሳይመለሱ የውሃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል ይባላል።

ሌላው በጽሑፉ ላይ ችግሩ ሁሉ የምእመናን፤ ሃጢአተኛና በደለኛውም ምእመን እንጂ ካህን በችግሩ ውስጥ ጨርሶ የሌለ ተደርጎ ተመልክቷል። እውነቱ ግን በተቃራኒው ነው፤ እነዚህ ሃሰተኛና ፈሪሃ እግዚአብሔር የራቃቸው ጥቂት ካህናት ችግሩን ባይፈጥሩትና ባያመጡት ምእመኑ እግዚአብሔርን ለማገልገል ሲሉ በሃቅ ከቆሙ ከጥቂት እውነተኛ ካህናት ጋር በመሆን ያላንዳች ችግር ፈጣሪውን እያመለከ ሃይማኖቱንና ቤተ ክርስቲያኑን በከፍተኛ ደረጃ ባሳደገና ባስፋፋ ነበር።

“አንተ ግብዝ፤ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፤ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ” (ማቴ. ፯፤ ፭)

ከዚህ በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያኑን እንጀራና ሻይ ቡና ሸጠን የገዛነው ነው.... በሚል በጽሑፉ ላይ የታተተው ምእመኑ ለሃይማኖቱን ለቤተ ክርስቲያኑ ሲል የጣረውንና የደከመውን ድካም ለማጣጣል ሲባል የተጠቀሰ የእብሪተኞች አገላለጽ እንደሆነ በግልጽ ይታያል።

እነ አባ ግርማ የካህናቱንና የምእመኑን ጥረትና ድካም ለማጣጣልና ለማርከስ ቢጥሩም ምእመኑ ሳይተርፈው ከራሱ ቀንሶ፤ ከልጆቹ አፍ ነጥቆ፤ የሚሰራው ከውስኗ ደምወዙ፤ በድጎማ የሚኖረውና ጡረተኛው ደግሞ ለህይወቱ ማኖሪያ ተብሎ ከሚሰጠው ቀንሶ የገንዘብ አስተዋጽኦ በማድረግ፤ ተረባርቧል። ሴት እናቶችና እህቶች፤ እንጀራና ዳቦ ጋግረው፤ በእሳት ተጠብሰው ወጥ ሰርተው፤ ሻይና ቡና አፍልተው፤ ተሸክሞ በማምጣት በበረዶ፤ በዝናብና በጸሐይ መከራ አይተው ሸጠው ፈንድ ሬዝ በማድረግ፤ ወንዶች አባቶችና ወንድሞች ጉልበታቸውን፤ እውቀታቸውንና ጊዜአቸውን ሰውተው የነጻ አገልግሎት በመስጠት ተረባርበው በእግዚአብሒር ተራዳኢነት በስደት ሃገር ቅድስት ማርያምን የቋሚ ርስት የህንፃ ቤተ ክርስቲያን ባለቤት በማድረግ ለትውልድ የሚተላለፍ ታሪክ መስራታቸው እነ አባ ግርማ ሊያጣጥሉት ቢሞክሩን በእግዚአብሔር ቀርቶ በሰውም ዓይን ሊታይና ሊዳሰስ የሚችል ሃቅ ነው።

ይህንን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈሉት ደግሞ በድንኳን ውስጥ የሚጸልዩት ብቻ አይደሉም፤ በቤተ ክርስቲያን ውስጥም አባ ግርማን ደግፈውም ይሁን እውነትን ማየት ተስኗቸው፤ ወይንም ደግሞ ቤተ ክርስቲያን እስከተከፈተ ድረስ ገብቼ ልጆቼን አቆርባለሁ፤ ክርስትና አስነሳለሁ በሚል የዋህነት በተንኮል በተከፈተ የቤተ ክርስቲያን በር ውስጥ ከሚገቡት ውስጥም ተመሳሳይ አስተዋጾ ያደረጉ እንደሚኖሩ ማንም ሊክደው አይችልም።

ነገር ግን እውስጥም የገቡት ይሁኑ እውጪ በድንኳን ውስጥ የሚጸልዩት ለሃይማኖታቸውና ለቤተ ክርስቲያናቸው፤ ሲሉ ቤተ ክርስቲያኗ የእግዚአብሔር ቤትና እግዚአብሔርን የማምለኪያ ቦታ እንድትሆን እንጂ የራሳቸው ሃብትና ንብረት በማድረግ ፈላጭ ቆራጭ ሊሆኑባት እንዳልሆነ ከአባ ግርማና መሰሎቻቸው በስተቀር ማንኛቸውም ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው ሊዘነጋው እንደማይችል እነ አባ ግርማ ማወቅ ይኖርባቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ ሕዝብ ክርስቲያን ሃብትና ጉልበቱን አስተባብሮ በእግዚአብሔር ተራዳኢነት የገዛው ህንፃ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ የመኖሪያ ቤት (ቪካሬጅ) የእግዚአብሔር ማደሪያ የእመቤታችን የቅድስት ማርያም ሃብትና ንብረት እንጂ አባ ግርማ ለፖሊስና ለካውንስል (This is my Property) እንዲሚሉት የሳቸው የግል ንብረት እንዲሆን በውጪ የሚጸልዩትም ሆኑ እውስጥ የገቡት ጨርሶ ሊቀበሉት የሚችሉት ጉዳይ አይደለም።

ትውልድን ለመተካት የህፃናት ት/ቤትና ጽህፈት ቤት እንዲሆን የተደረገውም የቪካሬጅ ህንፃ ለተመደበለት አገልግሎት እንጂ የአቡነ እንጦስ መኝታ ቤትና ሳሎን እንዲሆን የሚፈቅድ የለም።

ይህም በመሆኑ የእነ አባ ግርማን መከፋፈያ ዘይቤ እውስጥ ገብተው የሚገኙትም ቢሆኑ ሊቀበሉት እንደማይችሉ አጠራጣሪ አይሆንምና እንደው ከንቱ ውዳሴ ሆኖ ይቀራል እንጂ አባ ግርማ እንደሚያስቡት በዚህ ሕዝብን ሊከፋፍሉና እንደ ልማዳቸው ሊያበጣብጡበት እንደማይችሉ ከወዲሁ ሊረዱት ይገባል። ይቀጥላል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

Friday, 19 December 2014

ድንቄም ጠቅላይ ሚኒሴቴር!

ድንቄም ጠቅላይ ሚኒሴቴር!

ወንድሙ መኰንን፣ ከብሪታኒያ 19 December 2014

ብዙ ተብሏል። እኔም አንድ ነገር ልጨምርና ልገላገለው። “የጊዮርጊስን መገበሪያ የበላ ሲለፈልፍ ይኖራል” ነው የሚባለው? ተናግሮ ከሚያናግር ይሰውራችሁ! ውሀን ምን ነበር የሚያናግረው? ድንጋይ! የሰውም ድንጋይ እራስ አለ! ይቅርታ አንጀቴ አርሮ ነው!

ሦስት መንግስታትን የማየት ዕድል አጋጥሞኛል። ተወልጄ፣ አድጌ፣ ተምሬ ለዩኒበርሲቲ የበቃኹት በንጉሠ ነገሥቱ ዘመነ መንግሥት ነበር። ዕውነቱን እንናገር ከተባለ፣ ንጉሡ ሲናገሩም ሆነ ሲራመዱ፣ የርዕሰ ብሔርነት ግርማ ሞገስ ነበራቸው። “በንጉሥ መገዛቱ ጊዜ ያለፈበት፣ ያረጀ ያፈጀ፣ ገበሬውን በገባርነት ጠፍንጎ የያዘ፣ አገሪቱ በዕድገት ወደፊት እንዳትራመድ ያገዳት፣ ኋላ ቀር የፊውዳል ሥርዓት ነውና ወደሶሻሊዝም እንለውጣት” የሚሉ ድምጾች ከተማረው ክፍል አካባቢ እያየሉ መጡና እኛንም እንደጎርፍ ይዘውን ነጎዱ። ተከተልናቸው። “መሬት ለአራሹ እያልን” ተማሪዎች በጠበጥን። እንዳጋጣሚ ሆኖ በ፲፱፷፮ ዓ/ም የጠና ረሀብ በወሎ በመከሰቱ ሕዝብ በረሀብ እየረገፈ ፹ ዓመታቸውን “ድል” ባለ ድግስ አከበሩ የሚል በተማሪዎች የተጀመረው ርብሻ በመምሕራን (ሴክተር ርቬው)፣ በታክሲዎች እና በሠራተኞች ሥራ ማቆም አድማ ተቀጣጥሎ ለወታደሩ “መንግሥት የመገልበጥ” እድል ተፈተለት። የሥርዓቱ ጠባቂ የነበረው የወታደሩ ክፍል አመጸና የንጉሡን መንግሥት አፈረሰው። አዝጋሚ ዕድገት ላይ የነበረች ኢትዮጵያ የባሰውኑ በወታደራዊ ደርግ ተጠፈነገችና ወደ ኋ ተወረወረች። የንጉሡ ሥርዓት በአምባገነን ወታደሮች ተካ፣ ሶስት መኰንኖች ተፈራረቁባት። ርዕሰ ብሔርነቱም መጀመሪያ ለጥቂት ወራትም ቢሆን (ከመስከረም እስከ ኅዳር ፲፱፻፷፯) ሌፍትናንት ጀኔራል አማን አንዶም፣ ቀጥሎም ትንሽ ውረድ ብሎ ለጥቂት ዓመታት (ከኅዳር ፲፱፻፮፯ - ጥር ፲፱፷፱) ብርጋዴር ጄኔራል ተፈሪ በንቲ፣ ቀጥሎ በጣም ወርዶ-ወርዶ፣ ለብዙ ዓመታት (ጥር ፲፱፻፷፱ - ግንቦት ፲፱፻፹፫) ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም (በኋላ ኮሎኔል) በመጨራረስ ተተካኩ። ሲምሩ በሰደፍ፣ ከፈለጉም በእሥራት፣ ከጨከኑም በጥይት ሕዝቡን በጅምላ እየረሸኑ፣ ለአሥራ ሰባት ዓመታት በወታደር ፌሮ ጭንቅላታችን ላይ ቁመው ወታደሮቹና ጀሌዎቻቸው ቀጠቀጡን።  ግድያው እሥራቱ ያደነዘዘው ሕዝብ፣ “የባሰ አይመጣም” በማለት፣ ገንጣይ አስገንጣይ ዘረኞች ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግሱ፣ ዝም ብሎ አያው። እንዲያውም አንዳንዱ መንገድ እየመራ ወደ አዲስ አበባ አደረሳቸው። ይኸውና በወያኔ የሚመራው የዘረኞች ቡድን ከዚያች ከተረገመች ከግንቦት ፳ ቀን ፲፱፻፹፫ ዓ/ም ጀምሮ፣ ያላንዳች ርኅራሔ፣ ቀጥቅጦ እየገዛን ነው። ያም ብቻ አይደለም። መሬታችንን እየሸነሸነ፣ ነዋሪውን እየፈነቀለ በርካሽ እየቸበቸበው ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ንጉሡ ለደርግ ከአስረከቧት እጅግ አንሳ ትገኛለች። መሪዎቹም፣ ከበፊተኞችም እጅግ ወርደው የወረዱ ቀትረ ቀላሎች ሆኖብን። መጀመሪያ መለስ ዜናዊ ለሀያ አንድ ዓመታት (ከግንቦት ፳ ቀን ፲፱፻፹፫ - ከግንቦት ፳ ቀን ፳፻፬)፣ ፏልለውብን ሞት ገላገለን። መለስ ዜናዊን የተኩት ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ድቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር ናቸው


እንግዲህ እኔ እስካሁን የኖርኩት ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እስከ ኃይለማርያም ደሳለኝ መሆኑን ተገንዘቡልኝ። ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በ፲፱፻፳፰ ዓ/ም በሊግ ኦፍ ኔሺን ላይ ያደረጉትን[i] ንግግር፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ፣ ሰኔ ፳፪ ቀን ፲፱፻፺፱ ዓ/ም ካደረጉት አሳፋሪ ንግግር[ii] እና የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ሰሞኑን የስልጤ ዞን ዋና ከተማ፣ ወራቤ የተመሠረተችበትን አሥረኛ ዓመት ለማክበር ተግኝተው ከተናገሩት አሳፋሪ ንግግር[iii] ብናወዳድር፣ “እንዴት ወርደን እዚህ ደረሰን” ያስብላል

መለስ ዜናዊ ለሰው ስሜት የማይጨነቁ፣ በአራዳ አነጋገር ሁሉንም የሚዘረጥጡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ስቃይ ነበሩ። ሙት ወቃሽ ላለመባል፣ ያሉትን አስነዋሪ አባባሎች “ሾላ ብድፍን” ብለን እናልፈዋለን። አሽቃባጮችም ነበሯቸው። ብልግና በተናገሩ ቁጥር፣ መላው የፓርላማ አባላቸው፣ የሚያቅለሸልሽ ታሪክ እንኳን ቢሆን፣ ከት ብሎ የሚስቅላቸው ቷቸው ነበር። እሳቸውን የተኩት ጉድ እንደሳቸው መሆን ቢያምራቸውም፣ የተለዩ ፍጡር ናቸው። ወላጆቻቸው፣ “ኃይለ ማርያም”ብለው ስም ሲያወጡላቸው፣ ለመሆኑ ምን ታይቶአቸው ነው? በዚህ ስማቸው መጨረሻ ላይ እደምደማለሁ መልካም ንባብ

ኃይለማርያም፣ ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሳይሆኑ፣ የወያኔ ባለአደራ ሁነው የጠቅላይ ሚኒስቴርነቱ ቦታ ጠባቂ ናቸው። አልጋ ጠባቂ እንበል?! አልመሆናቸውን ገና በጠዋቱ፣ የሟቹ የመለስ ሚስት፣ ደፋሯ አዜብ ጎላ (መስፍን) አስመስክራለች። “የምኒልክን ቤተ መንግሥት አልለቅለትም” ብላ ጎዳና ተዳዳሪ ልታደርጋቸው ምንም አልቀራትም ነበር። ደንቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር!

ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የራሳቸው ሰው ባለመሆናቸው፣ የወያኔ መሣሪያ መሆናቸውን ለማስመስከር፣ አራዳው መለስ የተናገሩትን አነጋገር ቃል በቃል፣ አንዲት ቃል ሳይጨምሩ - ሳይቀንሱ፣ እንደበቀቀን ሲደግሙት ተሰምተዋል። የእነ አቤ ቶኪቻው መሳቂያ መሳለቂያም ሁነዋል። ከኦሪጂናሌው መለስ ላለማነስ፣ ብዙ ነውሮችን ካፋቸው ዘርግፈዋል። አዪዪ! ምናለ በተማሩት የውሀ ማጣራት ሙያ ቢሰማሩ ኑሮ! ከሰውም ሞገስን፣ ከእግዚአብሔርም በረከቱን ባገኙ ነበር። ለጠማው ንጹሕ ውሀ ማቅረብ በሰማይም ባጸደቃቸው በምድርም ባስከበራቸው!
ያለቦታው ገብቶ፣ ያለ ሰገባው
አሳዛኙ ልቤ፣ የተንገላታው

ነበር ያለው አፍቃሪ! ያለቦታቸው ገብተው፣ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ አገር የመምራቱን ኃላፊነት አምቦጫረቁት የቢቢስን እና የሲኤንኤንን ገዜጠኞች በሽብርተኝነት ሊያስሯቸው እንደሚችሉ አስፈራርተዋል። አራዳ ሳይሆኑ፣ እንደመለስ ጮጋ ለመሆን የሚያደርጉት መፍጨርጨር የመጨረሻው ፋራ መሆናቸውን፣ አጋልጦባቸዋል። አይ የኛ ነገር። ወርደን ወርደን እዚህ ደረስን? እንዲያው ኢትዮጵያውያን ፈጣሪን ምን ያኽል ብንበድለው ነው፣ ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ ጉዶች አሳልፎ የሰጠን? ነገራችን ሁሉ፣ከድጡ ወደ ማጡሆኖብናል። ሕዝባችን መገድሉ፣ መታሰሩ፣ መሰደዱ፣ መራቡ፣ መጠማቱ፣ መታረዙ ሳያንስ፣ እነዚህ መዥገሮች በየቀኑ እየተነሱ የሚመርጉበት ስድብ፣ የባሰ የሚያስመርር ደረጃ ላይ አድርሶታል።ጠቅላይ ሚኒስቴርኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ድንቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር!

የታኅሣሥ ፪ቱን (11 December 2014) ኢሳት ሬዲዮ ፕሮግራም እንደኔ ያደመጠ ሁሉ መቼም ሆዱ በንዴት ድብን እንደሚልበት አልጠራጠርም። ጨጓራ የሚልጥ የአልሰርን በሽታ ያስንቃል። ከአንደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቀርቶ፣ አንድ እራሱን ከሚያከብር፣ አባትና የቤተሰብ ኃላፊ ነኝ የሚል ሰው፣ እንዲህ የወረደ ንግግር አያደርግም። ምን አለ አሁን እንዲህ ዓይነት ቅሌት ቢቀርባቸው? ዲያ! ዲያል ወዲያ! ምን ዓይነቱ ለዛው ሙጥጥ ናቸው? እኔ ስለሳቸው አፈርኩ። ሰውዬው ያልበላቸውን ነበር የሚያኩት። ወራቤ፣ የስልጤዋ ዋና ከተማ፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር መስለዋት አሥረኛ ዓመቷን ልታከበር፣ የወያኔ ባላደራውን ጠርታ፣ መከበሯ ቀርቶ ተዋረደች። ጠቅላይ ሚኒስቴር ተብዬው፣ እንዲህ ነበር ያሉት፣ ዲንቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር!

፩ኛ፡ አሜሪካ ተሰደው ስለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን

“አንዳንድ ጌዜ አሜሪካን አገር ውስጥ የሆነ መርቸዲስ፣ ማለት፣ መኪና ተደርድሮ ባለበት ፎቶግራፍ ይነሱና ከዚያ በኋላ ወደቤተሰብ ይልኩና፣ ይኼ የኔ መኪና ነው ይላሉ። ማንን እንድሚያታልሉ ግን አይገባም።”

ያጣ ወሬ! እንዴ! ጠቅላይ ሚኒስቴር ተበዬው እኮ በሥፍራው የተገኙት የወራቤን ከተማን አሥረኛ ዓመት ምስረታ ለማክበር ነበር። አሜሪካ የሚኖሩት ስደተኞችናና የወራቤ ከተማ ምን አገናኛቸው? ከተደረደሩት መኪናዎች ጋር ተደግፈው የተነሱትን ፎቶ የት ቁመው ያዩት? ሰውዬ ለምን ያልበላቸው ቦታ ያካሉ? ለመሆኑ፣ አሜርካን ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንቱ የተባሉ ስንት ኢትዮጵያውያን ምሑራን እንዳሉ ያውቁ ይሆን? አሜሪካን ሆስፒታሎች ውስጥ ስንት እውቅ ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች እንዳሉ ማን በነገራቸው። አሜሪካ የምርምር ማዕከላት ውስጥ፣ ናሳ ሳይቀር፣ ስንት ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶች እንዳሉ የሚያስብ ጭንቅላት አላቸው ልበል? ኢትዮጵያን ለማንቋሸሽ እራሳቸው ቆሽሸው አረፉት! ይሁን! ይህ ቀን እኮ ታልፋለች። ማርቸዲስ ለኃይለማርያም ብርቅ ይሆን ይሆናል እንጂ፣ ወጪ አገር ማርቸዲስ ታክሲ ነው። ፈራሪም፣ ሎተስም፣ ቤንትሌይም፣ ሮልስ ሮይም ማለት እኮ አንድ ነገር ነበር። ድንቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር!

፪ኛ፤ በጀርመን ተሰደው ስለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ

“... ለልጆቼ ዶሮ ይዘህ ሂድ አሉኝ። እሺ ብዬ ጀርመን አገር ዶሮ ወጥ ተሸክሜ ሄድኩኝ። ከሄድኩ በኋላ፣ በተሰጠኝ ስልክ ብደውል፣ ብደውል፣ ልጆቹን ማግኘት አቃተኝ። ምንድነው ሲባል፣ ስልኩን ለጓደኞቼ፣ ለጀርመናዊ ለጓደኞቼ አሳየኹዋችወ፣ ኧረ! ይኸማ ሀይም(?) ውስጥ እኮ ነው አሉኝ። ምንድነው ሀይም አልኳቸው። ሰው የሚሰቃይበት እስር ቤት ዓይነት ነገር ነው አሉኝ። ዶሮ ወጡን ይዤ እዚያ ሀይም ሄድኩ። ስደርስ ኮንቴነር ውስጥ ነው ያሉት። እዚያ ዱቄት ይሰጣሉ፣ ዱቄቱን እያቦኩ፣ ዱቄት ብቻ ነው የሚበሉት። እቃውን አስረከብኩላውና፥ “ታዲያ ያ ሁሉ ፎቶግራፍ የላካችሁት፣ ከየት የመጣ ነው?” አልኳቸው። ብዙዎቻችን እናውቃለን፣ ውጭ አገር ሰው እንዴት እንደሚኖር።“

ደግሞ “ጀርምናዊ ጉደኞቼ ይላሉ! አያፍሩም? ለመሆኑ፣ የማን ደፋር እናት ናት፣ እንደተራ ሰው፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒቴራችንን ዶሮ አሸከማ ጀርመን አገር ድረስ የምትልክ? “የማይመስል ወሬ፣ ለሚስትህ አትንገር” ነው የሚባለው? እንዴ! የወራቤ ነዋሪ ላለፉት አሥር ዓመታት ያደረገውን ጉዞ እንዲገመግሙለት እንጂ፣ ጀርመን ውስጥ ስለሚኖ ስደተኛ ወሬ ጠምቶአቸው ነው እንዴ የጋበዟቸው? በነገራችን ላይ፣ ጀርመን አገር አዲስ የመጡት ስደተኞቹ፣ ምናልባት ጉዳያቸው እስከሚጠናቀቅ በዚያ ዓይነት አኗኗር ለጊዜው ይኖሩ ይሆናል፣ ለመሆኑ፣ አዲስ አባባ ስንት የጎዳና ተዳዳሪዎች እንዳሉ የሚያይ አይን ተተክሎላቸው ይሆን?

፫ኛ፣ በአረብ አገር ተሰደው ስለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ

“እኛ እህቶቻችንን ለማየት አቻልንም። ሳውዲ ሂደን፣ ማየት አልቻልንም።... ይኸ የዚያ አካባቢ የሀይማኖትዊ ሥነ ሥርአት ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ሂጄ ማየት ስላልተቻለኝ፣ የፈቀዱልኝስ እንድሄድ ነበር። ለምንድነው፣ ማየት የማይፈቀድልኝ፣ የሀይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ሊሆን ይችል ይሆናል ግን በእዚያ ደግሞ ቦታ ስንሄድ፣ መንገድ ላይ እንደአበደ ውሻ የሚኖሩ እህቶቻችን አየን። ከዚያ ቦታ ስንሄድ፤ በምባሲ በራፍ፣ ወደ ሺ የሚጥጉ፣ አንድ ላይ ተኰልኵለው  በዚያ ሙቀት ውስጥ ኤር ኮንዲሺነር በሌለበት ታጭቀው ሲሰቃዩ አየሁ። ከዚያ በኋል ግን፣ ምን ትዝ ይለኛል፣ ቢያንስ እዚህ ገጠር ውስጥ በእግራቸው ተጉዘው በልተው ጠግበው እኮ ይኖራሉ።

ድንቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር! ወያኔ አገሪቱን መቀመቅ ውስጥ በመጨመሩ፣ ኢኮኖሚዋን ማድቀቁ፣ እና እንደ ኃይለማርያም ደሳለኝ ያሉ አሽከሮቻቸው በልተው በልተው ሆዳቸው ተወጥሮ ሲነፋፋ፣ ቤተሰቦች የሚበላ የሚቀመስ ሲያጡ፣ ወጣት ሴቶቻችን ገና በሎጋ ዕድሜአቸው፣ትምሕርታቸውን አቋርጠው፣ ሴተኛ አዳሪ ከመሆን፣ በጉልበታቸው ሠርተው ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት የሚያደርጉትን መፍጨርጨር፣ ከእብድ ውሾች ቆጥረዋቸው አረፉ? ደግሞ ሰለ አረቦች ግርድና አፋቸውን ሞልተው ተናግረዋል። ለመሆኑ የግርድና ንግዱን የሚያካሄዱት የሕወሀት አባላት መሆናቸውን የሚረዳ ጭንቅልታ ማን ባዋሳቸው! አፋቸው ተበላሽቷል። ታዲያ ምን ያደርጋል! በቅቤ አሽተው አይመልሱት ነገር። ድንቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር!

፬ኛ፣ ድንጋይ ይወረውራሉ ስለሚሏቸው የስልጤ ወጣቶች

“አንድ እኛ እዚህ ግድም የሚያሳዝነን፣ አብዛኛው እዚያ መርካቶ አካባቢ ደንጋይ የሚወረውረው ወጣት የዚህ ዞን ወጣት መሆኑ ነው። በሙስሊምነት ከሆነ፣ ትልቁ ሙስሊም፣ ኦሮሞ ነው፣ ኦሮሚያ ነው። ነገር ግን ድንጋይ የሚወረውረው ግን የሥልጤ ወጣት ነው። ምን ማለት ነው ይኼ? ምን ማለት ነው? አባቶች በተለይ እስቲ ይታያችሁ የናንተ ልጆች ድንጋይ ሲወረውሩ፣ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ መስኮት ሲሰብሩ፣ መኪና ሲሰብሩ፣ እናንተ እዚህ ሁናችሁ ሲታዩ እንዲያው በአጠቃላይ፣ ይኸ ምን ማለት ነው? ይኸ አደብ መግዛት አለበት። ትላንት ከዚህ ሞባይል ገዝቶ፣ መርካቶ የገባ ሰው ድንጋይ እያነሳ ንብረትና ኃብት ማውደም ማለት፣ ይኽ ንቀት ነው። በምንም ምልኩ! ድንጋይ ወርውሮ መስኮት ሰበረና መኪና ከሰበረ በኋላ ሲታሰር ደግሞ በኃይማኖት ምክንያት ታሰርኩ ካለ፣ ድንጋይ የሚያስወረውር ሀይማኖት የለም። እንደዚያ ነገር ድንጋይ የሚያስወረውር ሀይማኖት የለም ...።”

ለዛው ሙጥጥ! ወይ ጉድ! ከክብር እንግዳ ተሳዳቢ እግዚአብሔር ይሰውራችሁ። የሥልጤ ሕዝብ የጋበዛቸው፣ የወራቤን ከተማ መቆርቆር አሥራኛ ዓመት ሲያከብሩ፣ ከጠቅላይ ሚኒስቴራቸው ጋር አብረው በክብር ተደስተው ቀኑን ለማሳለፍ ነበር እንጂ፣ ሊሰደቡ፣ ሊዋረዱ፣ ልጆቻቸው ላይ የሚቃጣውን ማስፈራሪያ ሊያዳምጡ ነበር እንዴ! የስልጤን ሕዝብ አዋረዱት! ምንኛ ሕዝቡ ልቡ ይቁሰል! ድንቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር! 

፭ኛ፣ ስለሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሞቴ

አፋጣኝ የፍርድ ውሳኔ ለምን አይሰጥም ተብሎ የተጥየቁ ግለሰቦችን በተመለከተ በመጀመሪያ ደረጃ እኛ ሰዎቹ የሙስሊሙ ኮሚቴ ተወካዮች ነን ሊሉ ይችላሉ። ይኸ መብታቸው ነው። ማንም አይከለክላቸውም።  ግን መንግሥት ተወካይ ለመሆናቸው ምንም ማስረጃ የለውም። ሙስሊሙን እነሱን እንዴት እንደወከለ አናውቅም። ስለዚህ ስለማናውቅ ጉሕጋዊ ወኪሎች ስለመሆናቸው ማስረጃ የለንም ነው የምንለው። ሕጋዊ ወኪሎች አይደሉም። እነዚህ ግለሰቦች ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው በሀማኖታቸው ምክንያት ወይም ዕምነታቸው ምክንያት ወይም በሚያራምዱበት ዕምነት ምክንያት አይደለም የታሰሩት። የታሠሩት ሀይማኖታቸውን እና እምነታቸውን ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ከማካሄድ አልፈው ሂደው ከምንግሥትና ከሕዝብ ጉዳዮች ላይ ወንጀል በመፈጸማቸው ነው የታሰሩት።

የምን ወንጀል? ሰው ገደሉ? ዕቃ ሰበሩ? በቃ ወያኔ አስተዳዳሪአቸው “ወንጀለኞች” ናቸው ካለ እንደበቀቀን ተከትለው፣ የኛ “ጠቅላይ ሚኒስቴር” ረዱባቸው ማለት ነው? ወያኔ ከሳሽም፣ ምስክርም፣ ዳኛም ነው። አገሪቱን ጠፍንጎ ይዞአል። ምን ዓይነት ጭንቅላት ቢኖራቸው ነው፣ ወያኔ እንዲህ የሚጫወትባቸው? አይ ሆድ! ለሆዱ ያደ አንጎሉ አይሠራም። ይህቺን አጥብቃችሁ ያዙልኝ! ሕግ የሚሠራው ሁሉም ሲገዛለት ነው። ወያኔ ሕግን የሚጠቀመው ሌላውን ጠፍንጎ ለመያዝ ነው። ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ዕውቀታቸው ወሀ ማጣራት ነው አንጂ ሕግ አይደልምና የተማሩት፣ የሕጉን ነገር ባያጨማልቁት ጥሩ ነበር።  ከዚያ አልፈው ተርፈው፣ እስካሁ ፍርድ ያልተሰጠበትንም ምክያት ሲደረድሩ፣ የተከሳሾቹ ጥፋት እንደሆነ ሊነግሩን ከጅሎአቸዋል። ኧረ ምን ከጀላቸው፣ ወጀሏቸው እንጂ! ጥፋተኛ ላለመሆናቸው፣ አራት መቶ ገደማ ምስክሮች በማቅረባቸው፣ ያንን ለማዳመጥ የዘገየ ፍርድ ነው ብለውን አርፍዋል። ድንቁርና አንዳንዴ ጡሩ ነው። ከሒሊና ቀሳ ያድናል።በድፍኑ፣ ወያኔ ወንጀለኛ ነው ብሎ የፈረጀው ሁሉ ወንጀለኛ መሆን ስላለበት፣ እራሱን መከላከል የለበትም ሊሉን ምንም አልቀራቸውም! በቃ! ወያኔ ከእግዚአብሔር በታች ትልቁ አማላካቸው ነው። ድንቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር።

፮ኛ፣ ወላይታን ሕዝብ በጅምላ ሰድቡ

“እኔ የተወለድኩበት ብሔር፣ ብዙ ሰው ነው እዚህ ጋ የሚያሰፋው። ያኛውን ለመምሰል ሲል ነ። ትንሽ ቀላ ካለ፣ ያኛውን እመስላለሁ ለማለት ይኸንን አሰፍቶ፣ እራሱን ለውጦ፣ እራሱን ለመሸ የምንሸቃቀጥበት ነው የኛ ትውልድ።

ኧረ በሕግ አምላክ! እኚህን ሰው አንድ በሉልን! የወላይታ ሕዝብስ እራሱን እንደሸቀጥ አልሸጠም። ይልቁንስ ከኩሩውና ከርህሩሁ የወለይታ ሕብረተሰብ ተፈጥሮ ሒሊናውን ለቁራሽ እንጀራ የሸጠ ማን እንደሆነ እናውቃለን። የሥነ አዕምሮ ሐኪም ጋ የሚወስዳቸው ዘድ የላቸውም? ወያኔ ምን ጭንቅላታቸውን ብታዞራቸው ነው ጃል፣ እራሳቸውን እንዲሰድቡ የለወጠቻቸው? ደግሞ የወላይታን ባላዊ ጠባሳ ለመሸፈን መሰፋትን፣ ከወራቤ አሥረኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ጋር ምን አገናኛቸው? ስድብ ርቦአቸዋል? ስድብ ጠምቶአቸዋል? የእሳቸውን አዕምሮ ነው ወያኔ ግጥም አድርጋ የሰፋችባቸው እንጂ፣ እኔ የማውቀው የወላይታስ ሕዝብ ባሕሉን አክባሪ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ነው። ድንቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር!

በመጨረሻ፣ ጠቃላይ ሚኒስትሩ፣ ለምንድነው ዲያስፖራውን የሚጠሉት? ምክንያት አላቸው! በፈረጆቹ አቆጣጠር፣ 2011 ላይ ወያኔ ገንዘብ ከዲያስፖራው ለመለምን ወሰነች። እሳቸው የአሜርካውን ልክ እንዲመሩ ተላኩ። ሁሉም በሄዱበት ተመሳሳይ ዕድል ገጠማቸው። ከሄዱበት ሁሉ ዲያስፖራው ምድረ ወያኔን ባዶ እጃቸውን ስደዳቸው። ለንደን ላይ ለምሳሌ፣ ከኢምፔሪያ ኮሎጅ አሳደናቸው አባረን፣ እምባሲ ከተናቸዋል[iv]፣ አንዲት ሳንቲም ሳይሰበስቡ ተመለሱ። አሜርካ ላይ እንዲሁ አዳራሻቸው ተረሾባቸው፣ ኪሳራ በኪሳራ ሆነው፣ ቤሳ ቤሲትን ሳይሰብበሰቡ ተመለሱ ታዲያ በዚህ የበሸቁት ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ሚያዝያ ፲፭ ቀን ፳፻፫ (23 April 2011) በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ፣ እንዲህ እያሉ ነበር የተሳደቡት!

“ከሁለት ሺ በላይ ሕዝብ በሚሰበሰብበት አካባቢ፣ ከ20 እስከ 150 ሰዎች፣ የተቃውሞ ሰልፍ ቢወጡ፣ ምንም የሚገርም አይደለም። እነሱም፣ የቀደሞ የደርግ ሥርዓት ርዝርዦችና፣ በሽብር ተግባር ላይ የተሰማሩ የአማጺ ቡድኖች አባላት ናቸው። እነዚህ ሰዎች፣ በበርካታ ዓመታት ሲጮሁ ኑረዋል። ኢትዮጵያ ግን ወደፊት እየገሰገሰች ትገኛለች። እነሱ እየጮሁ ይኖራሉ፣ ምናልባትም፣ አርጅተው እስኪሞቱ ድረስ የሚጮሁ ይኖራሉ። ሬሳቸው አገር ቤት ሊቀበር ይመጣል... እኛም እንቀጥላለን። ይልቁንስ፣ በዚህ ታሪካዊ ወቅት እራሳቸውን በእሳት ባያስለበልቡ የሚሻል ይሆናል”።

አርጅተው እስኪሞቱ ድረስ የሚጮሁ ይኖራሉ። ሬሳቸው አገር ቤት ሊቀበር ይመጣል” ነበር ያሉት? ይኸንን የተናገሩት ሚያዚያ ፲፭ ነበር። ከነዚያ ሰላማዊ ሰልፈኞች እስከአሁን ሙቶ ወደ አገር ቤት የተመለሰ ሬሳ የለም። እግዚአብሔር ይመስገን። ዳሩ ግን እንደ ጣዖት የሚያመልኳቸው አሳዳሪ ጌታቸው፣ መለስ ዜናዊ፣ ነሐሴ ፲፭ ቀን 2004 ዓ/ም ብራሴልስ ሆስፒታል ሙተው ወራት ከከረሙ በኋላ ለቀበር፣ አዲስ አበባ ሬሳቸው ገብተውላቸዋል። በእግዚአብሔር የሚያምን ሰው ግፍ አይናገርም። አንዳንዴ እግዚአብሔር ቅርብ ነው። ስሙ የተመሰገነ ይሁን!

ሰውዬው የዞረባቸው ናቸው። ጠቅላላ ሰብዕናቸው፣ ውጥንቅጡ የወጣባቸው የሚናገሩትንም ሆነ የሚያደርጉትን የማያውቁ ጉድ ናቸው። ወይ አያምሩ ወይ አያፍሩ! እንኳን ለጠቅላይ ሚኒስቴርነት፣ የአንድ መስሪያ ቤት ዴፓርትመንት እንኳን ለመምራት ብቃት ያንሳቸዋል። እንኳን ሠርተው፣ ተናግረው ስሜት የማይሰጡ አሳፋሪ ሰው ናቸው። ለወያኔ መሣሪያነት ያበቃቸው ይኸው ቅደመ ሁኔታ ነው።

አንድ ለብዙ ጊዜ አምቄው እስከዛሬ ያቆየሁትን ልበልና ልሰናበታችሁ።

ደንታ-ቢስ ከሀዲ፣ አድር-ባይ ሆድ-አደር
ወገኑን የሸጠ፣ የወያኔ አሽከር፣
ስብዕናውን ገድሎ፣ ከሒሊናው የራቀ
ስሙ ኃይለ-ማርያም፣ እሱ ጸረ-ማርያም፣ የተዘባርቀFriday, 12 December 2014

ውይ! አምባሳደሩ ተናገሩ!

ውይ! አምባሳደሩ ተናገሩ!
ወንድሙ መኰንን፣ ብሪታኒያ
የዛሬ 30 ዓመት ገደማ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሒሣብ መዝገብ አያያዝ ትምሐርት አስተምር ነበር። ዛሬም በሱው ነው እንጀራዬን በስደት ዓለም ከስቃይ ጋር እንደወጥ እያጣቀስኩ የምበላው። ታዲያ ያኔ፣ የመምሕራን ካፌቴሪያ ለምሳ በየጠረጴዛው ዙሪያ በቡድን በቡድን እየተሰበሰብን አንዳንድ ክፍል ውስጥ ያጋጠሙን ገጠመኞች እያነሳን እንስቅ ነበር። አንድ ዕውቅ የኢኮኖሚክስ መምሕር ነበሩ። እግዚአብሔር ይመስገንና፣ ዛሬም በሕይወት አሉ። ስማቸውን ግን አልጠቅስም። ታዲያ አንድ ቀን ከጎናችን ካለው ጠረጴዛ ላይ ሁነው ምሳ እየበሉ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በዕለቱ ያጋጠማቸውን አስቂኝ ክስተት ሲገልጹ፣ ጆሮዬን ጣል አድርጌ እንደዋዛ እሰማቸው ነበር። ነገሩ እንዲህ ነው። አንዳንድ ጠጠር ያሉ የኢኮኖሚክስ ጽንሰ-ሀሳቦችን አንስተው ሲያስተምሩ፣ አንድ ወጣት ተማሪ ነገሩ ከብዶት ነው መሰል፣ ሳያስበው እንቅልፍ ይዞት ለሽ ይላል። ያንን ያዩት ዕውቁ የኢኮኖሚክስ ባለሙያ፣ ድምጻቸውን በድንገት በጣም ክፍ በማድረግ፣ ጮክ ብለው ማስተማር ይጀምራሉ። እንቅልፉን ይለጥጥ የነበረው ተማሪ በርግጎ ተነስቶ ይቆማል። መምሕር ትኵር ብለው አይተውት፤ “ይቅርታ! ቀሰቀስኩኽ እንዴ? ምን ላድርግ ብለኽ ነው። እንጀራ ነው የሚያስጮኸኝ።” አልኩት ብለው ሲናገሩ ጠረጴዛቸው ዙሪያ የተኮለኮሉት በሳቅ አውካኩ። እኔ ባልስቅም፣ ነገሩን ልብ ብዪ ከጎናቸው ከነበረው ጠረጴዛ እሰማቸው ስለነበር እስካሁን አስታውሰዋለሁ። ታዲያ፣ ዛሬ ይኸንን ምን አስታወሰህ ትሉኝ ይሆናል። አምባሳደር “ብርሀኑ” ከበደ፣ ለሪፖርተር ጋዜጣ የሰጡትን ቃለ-ምልልስ[i] አንድ ወንድሜ ከአገር ቤት አካባቢ አንብቦት እኔም እንዳነበው ስለጋበዘኝ፣ አንብቤ ስጨርስ፣ “ምስኪን! እንጀራ ሁኖባቸው ነው የሚጮኹት” ብዬ እርፍ።

አምባሳደር “ብርሀኑ” ከበደን፣ ባልተረዱት ነገር ገብተው፣ አሳዳሪ ጌቶቻቸውን ለማስደስት አንዴ ጀርመን ሬዲዮ ድረስ ደውለው፣ ሌላ ጊዜ፣ ቪኦኤ የአማርኛ ዝግጅት ድረስ ደውለው[ii]፣ የሆነውን አልሆነም እያሉ ሲቀሉ ሰምቼአቸው፣ የወንድምነቴን ያክል፣ “ይኸ ነገር አይስማማዎትም። ባይሆን፣ ለመዋሸት - ለመዋሸት፣ ወያኔ ከትግራይ ያስመጣልዎትን ታኮዎች ይጠቁሙና፣ እነሱ ይዋሹልዎት። እርስዎ ምን በወጣዎት” ብዬ መከሬአቸው ነበር። በኔ ሞት፣ ያኔ የጻፍኩትን ምክር፣ ከላይ ያለውን ማጣቀሻ፣ ወይም የግርጌ ማስታወሻው ጠቁመው፣ ወንድማዊ ምክሬን አንብቡልኝ። እንደማይከፉ ቃል እገባልዎታለሁ። ታዲያ ወያኔ ካልሆኑ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ በዛሬ ጊዜ አሁን ማን እንዲህ ያለ ገንቢ ምክር ይለግሳል? ያውም ለባላንጣችን ታማኝ አገልጋይ አሽከር! ያንን ምክሬን ሰምተው፣ ለብዙ ጊዜ ዝም በማለታቸው ከእንዲህ ዓይነት ቅሌት እራሳቸውን ቆጥበው ሥራቸውን ብቻ በመሥራት ላይ ነበሩ ብዬ አምኜ ነበር። ምን ያደርጋል! “ድመት መንኵሳ፣ ዓይጧን አትረሳ” ነው የሚባለው? ጠፍቶኝ እንዳይመስላችሁ! አውቄ አጣምሜው ነው።

አምባሳደር ብርሀኑ፣ ከደርግ ዘመን ጀምረው ቀጣሪዎቻቸውን በማስደስት በሥራ የታወቁ ናቸው። የቤልጀየሙ ሥራቸው እንዳለ ሁኖ፣ ለንደን ከመጡ በኋላ፣ ለወያኔ የሠሩትን ውለታ፣ በአውሮፓ ያሉት የወያኔ ጉዳይ አስፈጻሚዎች የሠሩት በሙሉ ተሰብስቦ ቢደመር የለንደኑን አያክልም። ስለዚህ እራሳቸው እንዲህ እያሉ ስለራሳቸው ይመሰክራሉ።

“ለዓለም ገበያ ለሽያጭ የቀረበውን ቦንድ በተመለከተ በውጭ የተሸጠ በጣም ጠቃሚ እንኳን ባይባል፣ የአውሮፓ አጠቃላይ ተደምሮ የዚህ የእንግሊዝ ይበልጣል፡፡ ወደ 1.4 ሚሊዮን ዶላር ቦንድ ሸጠናል፡፡” (ሪፖርተር ታኅሳስ ፩ ቀን ፳፻፯)
ጎበዝ ደላላ! አሻሻጭ! የጠባ የጠነባውን የወያኔ የዘር ፖሊቲካ፣ በአፍዝ አደንግዝ ኪስ ማውለቅ ፕሮፓጋንዳ ሕዝቡን አታሎ ገንዘቡን መሞሸልቅ! መሸጡን ደኅና አድርገው ተክነውበታል። ሥራዎስ ድሮም መሸጥ አይደል? ኧረ እኛም ምስክር ነን። በዚሁ በሪፖርተር ቃለ ምልልስ፣ የእንግሊዝን መንግሥት በማግባባቱ ሥራና የፈጸሙትን ጀብዱ እንዲህ ሲሉ ያስረዳሉ።

ትልቁ ነገር ግን በኢትዮጵያ ኢንቨስት የሚያደርጉ ኢንቨስተሮች ትልልቆች ናቸው፡፡ ለአብነት ለመጥቀስ ዲያጆ የሚባለው በኢትዮጵያ ውስጥ 225 ሚሊዮን ዶላር ሜታ ቢራ ፋብሪካን ገዝቷል፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ 100 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርጓል፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ 325 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት አለው ማለት ነው፡፡ ዩኒሊቨር የሚባለው ትልቁ የመልቲላተራል ኩባንያ በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመርያ የኢንቨስትመንት ኦፕሬሽን እየጀመረ ነው ያለው፡፡ ሦስተኛ ፒተርድ የሚባለው የቆዳ ውጤቶች አምራቾች ድርጅት ለሰባ ዓመታት ጥሬ ቆዳ ይገዛ የነበረው በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ሦስት ፋብሪካዎች ሠርቶ 1,500 እስከ 2,000 ሠራተኞች ቀጥሮ እያሠራ ይገኛል፡፡ ይኼም የታወቀ ብራንድ ስለሆነ የቆዳ ውጤቶቹ ብሪቲሽ ኤርዌይስ የሚጠቀምበት ትልልቅ ሱቆች ውስጥ እየገባ ነው፡፡ ሌላ በማዕድን ፍለጋ ስንሄድ ታሎ በነደጅ ፍለጋ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ካምፓኒ ነው፡፡

አሁንም ይሄ የሚያሳየው ሰውዬው በተሰለፉበት ሥራ ውጤታማ መሆናቸውን ነው። ነገር ማበላሸት የሚጀምሩት፣ ጋዜጠኛው ወደማይሸጠው የወያኔ ፖሊቲካ ሲመራቸው ነው። እኔ እሳቸውን ብሆን፣ “እዚህ ጋ ወራጅ አለ” ብዬ ዱብ እል ነበር።

ሪፖርተር፡ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ መንግሥት በቁጥጥር ሥር የዋሉት የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸውን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ በተመለከተ የእንግሊዝ መንግሥት ስሜት ምንድን ነው? ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን (በግላቸው) ለኢትዮጵያ መንግሥት የመማፀኛ ደብዳቤ መጻፋቸው ይነገራል፡” ለሚለው ጥያቄው መልስ ሲሰጡ፣  “ጉዳዩ ይህን ያህል ትልቅ ጫና የለውም፡፡ ነገር ግን ግለሰቡ የእንግሊዝ ዜጋ እንደመሆኑ መጠን በእንግሊዝ መንግሥት የሆኑ ዕርምጃዎች መወሰድ አለባቸው የሚሉ አሉ፡፡  ሰውየው ለምን ታሰረ የሚል አይደለም፡፡ በሕግ ይዳኝ የሚል ነገር ነው፡፡” ሲሉ አቃለው ተናግረዋል። አንዳርጋቸውንም ሲከሱ፣ ያላንዳች ሀፍረት እንዲህ ብለዋል።

 ይኼ ሰውዬ የሽብር ተግባር ላይ ገብቷል፡፡ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከሚፈልጉ ኃይሎች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ይሠራ ነበር፡፡ ሦስተኛ ራሱም ይህንን አምኗል፡፡ ብዙ ጊዜ እጅ ከፍንጅ የተያዙና የታሰሩ ሰዎች እሱ እንደሚያሠለጥናቸውና የቡድኑ መሪ እንደሆነ፣ ከኤርትራ መንግሥት ጋር አብሮ እንደሚሠራ በግልጽ ያስቀመጠው ነገር አለ፡፡ እሱ እንደተያዘ ግንቦት ሰባት የሚባለው ድርጅት ራሱ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጦርነት ነው ያወጀው፡፡ 

አዪዪዪ! “አይ አለማወቅሽ፣ አገርሽ መራቁ" አለ ነው የሚባለው ሰውዬው! ለመሆኑ፣ የወያኔው ወኪል፣ አሳዳሪ ጌታቸው እራሱ ወያኔ፣ ትላንትና ከሻዕቢያ ጋር አብሮ ኢትዮጵያን ሲያደሙ እንደነበሩ ጠፍቶአቸው ነው? እንዴታ! በድንብ ነው እንጂ! የኤርትራን “ናጽነት” ዕውን ለማድረግ የስንት ኢትዮጵያዊን ደም አብረው እንዳአፈሰሱ ዘንግተውታል ማለት አይቻልም። የደርግ ዲፕሎማት በነበሩበት ጊዜ የወያኔና የሻዕቢያን አደገኛ አካሄድ የሀገር ክህደት መሆን ሲያብራሩ አልነብሩምን? ለመሆኑ ዛሬዎቹ ወያኔ ባለሥልጣናት እና ሞት የገላገለን የኢትዮጵያ ጠቅልላይ ሥቃይ አልነበሩም፣ “የተገነጠለችውን የኢትዮጵያን ጠቅላይ ግዛት እንደ ነጻ አገር ዕወቁልን” ብለው በአፍሪካ አንድነትና በተባበሩት መንግሥታት ኮሪዶሮች ኮሮጆ ተሸክመው ሲሯሯጡ የነበሩት? እሱ ድርጊት ነው በታሪክ ዓይን የአወጣ የአገር ክህደት፣ ወዳጄ ልቤ! በዚህ ወራዳ ድርጊታቸው የዓለም መንግሥታትን አስደምመው አልነበረም? የራሱን አገር ገንጥሎ አስገንጥሎ "እውቋት" ብሎ ሲሯሯጥ ወያኔ በታሪክ የመጀመሪያው ነው፣ የመጨረሻውም ከሀዲ ሳይሆን አይቀርም። ለመሆኑ ኢትዮጵያን ያለወደብ ያስቀራት ከሀዲ መንጋ፣ አንዳርጋቸው ነው ወይስ የወያኔ ዘረኛ ወራሪ? አምባሳደሩ፣ ምን አለ ቁስል ያለበትን ቦታ እየመረጡ ባይነካኩን? ሻዕቢያን በተመለከተ፣ ወያኔ የሞራል ብቃት የለውም ማንንም ለመወንጀል። ነገሩ፣ የወያኔ እንዲህ መፍጨርጨር፣ “የትላንትናውን የወንጀል ባልደረባዬን አትቀሙኝ” ወይንም “ባሌን አትቀሚኝ” ዓይነት ቂመኝነት ነው፣። ትላንት ከሻዕቢያ ጋር “በአንድ አልጋ ካልተኛን፣ በአንድ ጉድጓድ ካ...” ብለው እነፕሮፌሰር አሥራትን የመሰሉትን ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች ያስገደሉ ገንጣይ አስገንጣይ አገር ሻጮች፣ ዛሬ ደርሰው ከኤርትራ ጋር የተጎዳኘን ሁሉ “ዓይንህን ላፈር” ማለት ሌብነት እንጂ ምን ሊባል ነው? አምባሳደር እዚያ አካባቢ ወያኔን የረከሰ ፖሊቲካ ለመሸጥ ባይሞክሩ ጥሩ ነበር። ለምን ቢሉኝ፣ ሰውየው “እናቴን ያገባ ሁሉ አባቴ ነው” እንዳለው ሁሉ፣ ነገም ዴሞክራሲያዊ የሆነ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ በግድም ሆነ በውድ ቢቋቋም፣ በተማሩት ሙያና በአካበቱት ልምድ ገዢዎቹን ሳይሆን ኢትዮጵያን ሊያገለግሉ ይቻላሉና፣ እንዳናምርርብዎት፣ የብዙዎቻችንን ቆሽት ከሚያድብን ንግግር ራቅ ቢሉ ነገም የመሥራት ዕድል ይኖርዎት ነበር።

ሰውዬው ከዚያም አልፎ ተርፎ፣ እነ አመንስቲ ኢንተርናሽናል፣ እነ ሕይማን ራይትስ ዎትች አልቀሩአቸውም። እንዲህም እስከማለት በቅተዋል።

“ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ድርጅቶች አሉ፡፡ እነ ሂውማን ራይትስ ዎች እና እነ አምኒስቲ ኢንተርናሽናል አሉ፡፡ እነሱ በመንግሥት ላይ የሚቀሰቅሱት ውንጀላ ይቀጥላል፡፡ ውንጀላቸው መሠረት የለውም፡፡ ዲሞክራሲ በአንድ ሌሊት የምትፈጥረው አይደለም፡፡ የእንግሊዝ ወይም የኖርዌይ ዓይነት ካልሆነ ብለህ ዲሞክራሲ አይደለም ብለህ ልትፈርጅ አትችልም፡፡

“አወቅኩሽ ናቅኩሽ” አለ አሉ ሰውዬው። እነዚህ ግዙፍ ድርጅቶች በዓለም ዙሪያ በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነታቸውና ተአማኒነታቸው እንደ ሐውልት የተተከሉ ናቸው። እነዚህን የትም አይደርሱም፣ አሉታዊ ተጽዕኖም አያደርሱም ማለት ጅልነት ነው። እነዚህ ድርጆቶች እኮ ናቸው ደርግ በጥይት ሐሩር ሲያራውጣቸው በዓለም ጥብቅና ቁመውላቸው ሲሟገቱላቸው የነበሩት። ያኔ ወያኔዎች ሲሰደዱ፣ ወዳጆቻቸው ነበሩ። ዛሬ እነሱ አሳዳጆች ሲሆኑ፣ ከጠላት ቆጠሩአቸው? ዓለም ተለዋዋጭ ናት። እንኳን እነዚህ በ17 መርፌ የተጠቀመ ቡቲቶ ለብሰው ልሥልጣን የበቁ ወንበዴዎችና፣ የሮም መንግሥትም ወድቋል። የማይበገር የሚመሰለው የሶብየት ሕብረትም መንግሥት ፈራርሷል። አሳዳጆቹ በተራቸው እንደሚሰደዱ ጥርጥር የለንም። የጊዜ ጉዳይ ነው። ያቺ ቀን እንደገና ብቅ ስትል፣ ዓይናቸውን በጨው አጥበው፣ “ጥብቅና ቁሙልን” ሊሉ ነው እነዚህ ዓይን አውጣዎች። የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግሥታት ወያኔ የጸረ-ሽብር ዘመቻ የቃል ኪዳን አጋራቸው ስለሆነች እነዚህን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ጩኸት ቦታ እንደማይሰጡአቸው ተናግረዋል። እንግሊዝን በተመለከተም እንዲህ ብለዋል።

“የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የመጣ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ውስጥ አንደኛ ደረጃ ይዛ ትገኛለች፡፡ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግንኙነቱ ዘርፈ ብዙ እየሆነ ነው የመጣው፡፡ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ዕርዳታ እንግሊዞች ‹‹Value for Money›› [ገንዘብን ለታሰበለት ዓላማ ማዋል] በሚል መርህ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰጠው ዕርዳታ ለትክክለኛ ዓላማው እየዋለ መሆኑንና የሕዝብን ሕይወት በመለወጥ ተግባራዊ እየሆነ መሆኑን በደንብ አስቀምጠዋል፡፡ እንደ ምሳሌም ይጠቅሱታል፡፡

ይኸ እንግዲህ፣ “እኛ አሽከራቸው እስከሆን ድረስ ንዋዩን ያለምንም ጥያቄ ያፈሱልናል” የሚል የሚመስል ድምዳሜ ነው። ግን አምባሳደሩም ሆነ የሪፖርተር ዘጋቢ አንድ ነገር ረስተዋል። በየዓመቱ የሚወጣው የዩኤስ ስቴት ደፓርትመንት የሰብዓዊ መብት ረገጣ በኢትዮጵያ ዘገባ[iii]፣ አለማንሳታቸው አይግርምም? ዘንድሮም ተመሳሳይ ዘገባ በዪኬ መንግሥት ወጥቱአል[iv]። የአውሮፓ ሰብዓዊ መብት ኮሚሺን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሰፕቴምበር 24 ቀን 2014[v] የተወያየበት የወያኔ አፈና፣ የአንዳርጋቸው ጠለፋ፣ የጋዜጠኞች መታፈን፣ “የጸር-ሽብርተኝነት ሕግ”፣ የጋዜጠኝነት ሕግ፣ የመያድ ሕግን በተመለከተ፣ ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት ሳይሆን ጋጠ-ወጥ የሆነ ማፊያ ቡድን ኢትዮጵያን የሚያስተዳድር እስኪመስል ተወያይቶባታል። “እኔ አላይም” ለማለት ካልሆነ፣ እንደሰጎን አንገትን አሸዋ ውስጥ ቀርቅሮ፣ አደጋ ሲመጣ መሸሸግ መላ ሰውነትን ከሞት አያድንም። አምባሳደር “ብርሀኑ” ከበደ፣ ጸሐይ የሞቀውን፣ ዓለም ያወቀን የሰብዓዊ መብት ረገጣ በኢትዮጵያ “የለም” ብሎ ድርቅ ብሎ መሸፋፈን አይቻልምና፣ ያንን ለመከላከል መሞከር ትዝብት ላይ ይጥላል። አምባሳደር! 23 ዓመት እኮ አንድ ሌሊት አይደለም። ደግሞ ዴሞክራሲ በአንድ ሌሊት አይሠራም እያሉ የዘባነኑብናል። የሰው ልጅ መብት ረገጣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከደርግ ዘመን በላይ አሁን ብሶበታል!

ሌላው በጣም የገረመኝ አንድ ነገር፣ ሳይጠየቁ የዘበዘቡት፣ የኛ ዲያስፖራ የተባልን፣ “የጥቂቶቹ” ወያኔ ቁጥጥር ሥር አንውልም ብሎ አሻፈረኝነት ጉዳይ ነው። አምባሳደር ሆዬ “አገር ቤት የሚካሄዱትን አዎንታዊ ለውጦችን፣ ልማቶችን ማየት አለባቸው” ካሉ በኋላ እንዲህ ነበር ያሉት። 

ልንታሰር ይሆናል የሚል ፍርኃት ያላቸው አሉ፡፡ ኢሕአዴግ 90 ሚሊዮን ሕዝብ የሚመራ ድርጅት ነው፡፡ እገሌ ወጣ እገሌ ገባ ብሎ ለመቆጣጠር ጊዜም የለውም፡፡ አንድም የተሳሳተ አመለካከት ነው አልያም ለራስ የሚሰጡት ግምት ነው፡፡ ሰው ከገደሉ ወይም ሌላ ወንጀል ከፈጸሙ ኢሕአዴግም ማንም አያድናቸውም፡፡ ሕግ ነው የሚመለከታቸው፡፡ ኤርፖርት ላይ እንደሚታነቁ የሚያምኑ ሰዎች አሉ፡፡ ኢሕአዴግ ግን ስለመኖራቸውም አያውቅም፡፡ 

ወቸ ጉድ! ከተናግሮ አናጋሪ ይሠውራችኹ! ሪፖርተር ይኽቺን ‹‹ኤርፖርት ላይ እንደሚታነቁ የሚያምኑ ሰዎች ቢኖሩም ኢሕአዴግ ግን ስለመኖራቸውም አያውቅም›› የምትለዋን ሐረግ መዝዞ ነው እንደ አርዕስት የተጠቀመባት። አይ አምባሳደር! እሶም እንደ አሳዳሪ ጌቶችዎ እንደ ጅል ይቆጥሩን ገቡ እንዴ? እኛ እኮ ከዚያ በላይ ነቄ ነን! ለመሆኑ ወያኔ ሚሊዮን ዶላር አፍስሶ፣ እንደሌባ ሸምቆ፣ ኢትዮጵያ ኤርፖርት ሳይሆን፣ ሰናዓ ኤርፖርት ድረስ መሽጎ፣ ወንድማችንን አንዳርጋቸው ጽጌን የጠለፈው[vi] አለመኖሩን ባለማወቁ ኑሯል? ጃታኔ አሊን ኬኒያ ድረስ ቅጥር ነፍሰ ገዳይ ልኮ ሲያስረሽን፣ ውጪ የምንኖረው፣ ተቃዋሚ ዲያስፖራ መዘንጋቱ ነበር። የኢትዮጵያን ኤርፖርት ተውት፣ ከኬኒያ ስንቶቹ ስደተኞች ናቸው እየተፈኑ የተወሰዱት[vii]? አቶ ሱሉብ አህመድና አቶ ዓሊ ሁሴን[viii] እኮ ከኬኒያ የተጠልፉት በዚህ ዓመት ጃኑዋሪ 26 ቀን መሆኑን ዘንግተውት ይሆን? ለመሆኑ፣ US$23,000,000 ከፍለው የበፊቱን የጋምቤላ አስተዳዳሪ የነበሩትን ኦኬሎ አክዩዪን ከጁባ የጠለፉት አፋኞች[ix]፣ ማንንስ ይምራሉ! ክቡር አምባሳደር! ለመሆኑ ስንት የደኅንነት አባል ነው፣ የራስዎ ለንደን የሚገኘው ቢሮዎ የሚያሰማራብን? እነዚህ ጆሮ ጠቢዎች፣ ምን ለመሥራት ይሆን የዘመቱብን? እንዲያው እራስዎ ጅል ሁነው አያጃጅሉን ጃል!

አንድ መርዶ ለአምባሳደር ብርሀኑ ከበደ ልንገራቸው። አንዳርጋቸው ጽጌን መጥለፋችሁ ትልቅ ስሕተት ነው። እስክንድር ነጋን፣ ርዕዮት ዓለሙን፣ አንዱዓለም አራጌን፣  ውብሸት ደሳለኝን፣ ናትህናኤል መኰንንን፣ ምትኩ ዳምጠን፣ የሺዋስ ይሁናለምን፣ ኪንፈሚካኤል ደበበን፣ ኦልባና ሌሊሳን፣ የእስልምና ጉዳይ ተከታታዮችን ወያኔ ሲያስር ለጊዜው ተናደን ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተን ነበር፣ ግን እንደአሁን አላመረርንም። ገንዘብ ልመና የመጡትንም ባለሥልጣኖቻችሁን አሳፍረን መልሰናቸው ነበር፣ ግን አልቀጠልንበትም። አንዳንድ ሆዳሞችን በየማሕበረሰባችን እያስሰረጋችሁ አስገብታችሁ፣ ቤተክርስቲያናችን ሳይቀር በሆዳደር ልማታዊ መንኰሳት ልትቀሙን ስትነሱ እሱን ለማስጣል፣ በተለይ ለንደን ውስጥ ጌቶችዎ የሚሠሩትን ወንጀል ከማጋለጥ ትንሽ ረገብ ብለን ነበር። ወንድማችንን አንዳርጋቸውን ከየመን ያንን ሁሉ ገንዘብ አፍስሳችሁ ስትጠልፉት፣ የተዳፈነውን እሳት ቆስቁሳችሁ አነደዳችሁት። ያውላችሁ ትግሉ ተቀጣጥሎላችኋል። አሁን ሆይ-ሆይ ተበሎ ይብርዳል ብላችሁ እየጠበቃችሁ ነው። እንደ ቋያ እሳት እይተንቀለቀል፣ ነበልባሉ እየጦፈ ነው። እነዚህ “ጥቂት” የሚሉአቸው ሰዎች ናቸው ሎንዶን ላይ 5th September 2014 ከአውሮፓ ሁሉ ተሰብሰበው መንገዱን ያጨናነቁት። ከሁለት ወር በኋላ፣ 7th November 2014 እነዚህ ጥቂት ናቸው፣ የብራሰልሱን Schuman Square ቀውጢ ያደረጉአት! የድሮ መሥርያ ቤትዎ ባልደረቦች፣ ወያኔ እምባሲ ውስጥ የሚሠሩት ሠራተኞች አለንገሩዎትም እንዴ ምን እንደሆነ። ሆ ብሎ ያ ሁሉ ሰልፈኛ ወደ ኤምባሲው ሲተም፣ ተደናግጠው፣ ባለአምባሻውን የወያኔ ባንዲራ ከተሰቀለበት አውርደው፣ እዚያ መሬት ላይ ጥለው ነበር ሩጠው ቤት ውስጥ ገብተው በራቸውን ዘግተው የተቀረቀሩት! “ድኃን አትናቁ፣ ድኃ እንዴት ይናቃል፣ ትኋን እንኳን በአቅሙ፣ አልጋ ያስለቅቃል!” ሲባል አልሰሙም እንዴ!

እሳቱ ገና አልቆመመ። በዚህ ብቻ መች አባርቶ! እነዚህ “ጥቂት” የሚሉአቸው ሰዎች ናቸው ባለሥልጣኖቻችሁን በአሜሪካና በአውሮፓ ከተሞች ሲያሯሩጡአቸው የነበሩት። ዋሽንግተን በየሁለቱ ሳምንት ሰኞ ሰኞ የእንግሊዝ ኤምባሲ ይሸበራል፣ በኢትዮጵያ ሰላማዊ ሰልፎች! በየሁለቱ ሳምንት፣ ዓርብ ዓርብ የለንድን የውጭ ጉዳይ መሥርያ ቤትን በሰላማዊ ሰልፍ ይናወጣል። “የጎዳና ነውጥ ነው የምትሉት? “ምንም ለውጥ” አያመጡም፣ ያሉት፣ እኛ በፈጠርነው ማዕበል እኮ ነው የዩኬ መንግስት £2 ሚሊዮን ፓወንድ[x] የወያኔ ባለሥልጣኖች የሚሰለጥኑበትን ገንዘብ የያዘባችሁ። £20 ሚሊዮን ፓወንድ የደኅንነቶች[xi] ስልጠና ፕሮግራማችሁን የተሰረዘው እኮ በድምጻችን ነው!  የኛ እኮ ግፊት ነው፣ ትላልቅ ጋዜጦች፣ እንደ Independent[xii], The Guardian[xiii], and The Daily Mail[xiv] የመሳሰሉት ጋዜጦች መንግሥታቸውን በጥያቄ እንዲያጣድፉ የተገደዱት! በኛና፣ እነዚያ ምንም ለውጥ አያመጡም ያሉአቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ተሟጋቾች፣ እንደ Amnesty International[xv], Human Rights Watch[xvi], the Frontline, Pen International, Reprieve, Redress መሆኑን የሚረዳ ጭንቅላት አለዎት? አስተዳዳሪ ጌቶችዎ ካዝና ውስጥ ያለውን የብር ምንዛሪ ደርቆባቸዋል። ለእርስዎና ውጪ ለበተናቸው የደኅንነት ወፈሰማይ የሚከፍለው ደሞዝ አይነሮውም። ያንን መርዶ የዓለም ባንክ ሰሞኑን ነግሮናል[xvii]። ከዚህ በፊት እንደመከርኩዎት፣ ከስዎ በፊት እንደነበረው አምባሳደር ፍሰሀ አዱኛ፣ እርስዎም አገር ፈልገው ቢኮበልሉ ከአሁኑ ይሻልዎታል። ዕድሜዎ እየገፋ ነው። እየጨለመብዎት ነው። አሁንም ጨለማው ከበደ። ካረጁ አይበጁ!