Wednesday 5 October 2011


ሰንደቅ ዓላማችን
ከወንድሙ መኰንን፣ ኤልስበሪ፤ ኢንግላንድ፣ መስከረም ፳፬ ቀን ፪፼፬ ዓ. ም
ወያኔ ወደ ሥልጣን የመጣው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እያጋየ ነበር። የጨው መቋጠሪያ ጨርቅም አድርጎት ነበር፡፡ በመጣም በነጋታው ሕገ-መንግሥቴ የሚለውን መጨቆኛ መሣሪያ ለማጽደቁ ኑ ብሎ በጠራቸው የሱ ብጤ ዘረኞች ስብሰባ ላይ ሰንደቅ ዓላማችን፣ ሲዋረድ፣ ሲብጠረጠር እንደነበር ለታሪክ ዩ-ትዩብ በተባለው የዘመኑ የድምጽና የተንቀሳቃሽ ስዕል ማሳያ የድረ ገጽ ማሳያ ላይ ለሕብረተሰቡ ለዕይታ በቅቶ ይገኛል።
ያንን ጉድ ስንሰማ ስንቶቻችን በገንን።
ሰንደቅ ዓላማችን እንዳገራችን እራሷ ባለታሪክ ናት። ሰንደቅ ዓላማችን፣ እነሱ እንዳሏት “ጨርቅ” ብቻ ሳትሆን ስንት ደም የፈሰሰባት ወድቃ የተነሳች ልዩ የታሪካችን መዘክርና የማንነታችን ማብሰሪያ ሰንደቅ ናት። በነገራችን ላይ በተለምዶ “ባንዲራ” ትባል እንጂ ትክክለኛው አጠራሯ “ሰንደቅ ዓላማ” ነው። ባንዲራ በጠላት ወረራ ጊዜ እንድንቀበለው ወራሪዎች የዶሉብን ወይም የተበከልንበት “አልለቅ” ያለን የጣሊያን ቃል ነው። ጠላት ወርሮን አራዳን “ፒያሳ”፣ አዲስ ከተማን “መርካቶ” እንዳላትና ለሌሎቹም ካክዛንቺስ፣ ፖፖላሬ፣ ባምቢስ ብሎ ሰይሞ ተጣብቀውብን እንደቀሩት የቦታ ስሞች እንደማለት ነው። ባህር ምድርንስ ኤርትራ ብሎ ሰይሞ አይደል ጉድ ያፈላብን!
ከአምስቱ ዓመታት የጠላት ወረራ በስተቀር ይኽች ሰንደቅ ዓላማ ለብዙ መቶ ዓመታት ዓርማችን ሁና አገልግላለች። ቀይና አርንጓዴው ቦታ ቢቀያየሩም፣ ብጫው ከመሀል ሁኖ ከኛ ጋር የኖረች አርማችን ናት።
ሰንደቅ ዓላማችን ከ ፲፰፻፸፫ (1881)[1]  እስከ ፲፰፻፹ (1887) ዓ.ም. ድረስ ይኸን ስዕል እንደምተመስል ከታሪክ መዘክር ማውቅ ችለናል።










በአጼ ምኒልክና በንግሥተ ነገስታት ዘውዲቱ ምኒልክ ዘመን መንግስታት ከ፲፰፻፹ (1887) እስከ ፲፱፳፰ (1936) ዓ. ም. ሰንደቅ ዓላማችን፣ ምንም ዓይነት ምልክት ያልተለጠፈባት ሁና እንደሚከተለው ተሽሞንሙና እናገኛታለን።













ይኸች ሰንደቅ ዓላማ ነበረች፤ አደዋ ድረስ ዘምታ በአሸናፊነት ወደ አዲስ አበባ የተመለሰችው። ይኽችን ሰንደቅ ዓላማ መሆን ነበረባት ዘርዓይ ድረስ በጁ ጨብጦ የብዙ ጣሊያኖችን አንገት በጎራዴ ሮም ላይ የቀላው። መሰረቷ ሶስቱ ቀለማት ናቸው።
መቸም ታሪካችን ውጣ ውረድ የሞላበት ነው። ጠላት በ፲፱፳፰ (1936) ዓ.ም. ሲወረን፣ ሰንደቅ ዓላማችንን እንደወያኔዎቹ አብጠልጥሎ ሳይሆን በክብር አውሮዶ አታጥፎ ካስቀመጠ በኋላ፣ የራሱን፣ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ እና የሶማሌ ውሁድ የምስራቅ አፍሪካ ጣሊያን ኤምፓየር ብሎ ሰይሞ “ባንዲራ” ሠርቶ አንጠለጠለላት። የኛ ሰንደቅ ዓላማ “ወደቀች” የሚባለው በዚህ የአምስት ዓመት የጠላት ወረራ ነበር። ዕውነቱ ግን ጠላት ሰንደቅ ዓላማዋን ከጃንሆይ ግቢ አውረዳት እንጂ አልወደቀችም። ሰንደቅ ዓላማዋ አርበኞችን ተከትላ በረሀ ገባታ ተዋጋች እንጂ አልተጣለችም። ሰንደቅ ዓላማችንም እንዳባቶቻችን እራሷን ችላ አርበኛ ናት! ያችን ሰንደቅ ዓላማ ያከበረና የያዛት ሁሉ በአሸናፊነት እንደሚወጣ የተመሰከረላት በዚህን የችግር ጊዜ ብሩህ ተስፋ ነበረች። የሚከተለውን የምሥራቅ አፍሪካና “ባንዲራ” የነመለስ አያት እና መሰሎቻቸው ባንዳዎች ያጎበድዱላት ይሆን ይሆናል እንጂ የኛዋስ በየዱር ገደሉ ስትውለበለብ ነበር። "ባንዲራ" ማለት ይኽች ናት። በቃሉም ውስጥ “ባንዳ” ይገኝበታል። ሌላም አስጸያፊ ቃል በውስጧ ይገኝባታል።። አልለውም ግን። 
-

በየአደባባዩ ከሞቅዲሾ እስከ አሥመራ ይኸንን “ባንዲራ” ብላ ጣሊያን ብታውለበልበውም፣ የኛ ዕውነተኛ ሰንደቅ ዓላማ ግን አርበኞቹ ባሉበት ሁሉ፣ ሲንቀሳቅሱ ከፍ አድርገው ተራ በተራ ሲሸከሟት፣ ሲያርፉ፣ በየእንጨቱ እያውለበለቧት በየዱር በየገደሉ ተሟሟቱባት። በቆላ በደጋ ለአምስት ዓመታት ተዋግተው ነጻነታቸውን ሲያስመልሱ፣ ኦሜዴላ ላይ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተወለበለበች ሰንደቅ አሸናፊዋ ዓላማችን አረንጓዴ፣ ብጫ፣ ቀይ የሆነች ሌጣ መለያችን ይኽች ነበረች። ቀዩና አረንጓዴው ቦታ እንዴት እንደተቀያየሩ ለታሪክ ባለሙያዎች ትቼዋለሁ።



















በኋላ ላይ ግን ያው ዘውዱን የጫነ አንበሳ ተቀምጦበት ኦፊሴላዊ በሆነ ቦታ ላይ ሲውለበለብ፣ በየመሥሪያ ቤቱ፣ በየትምሕርት ቤቱ ይወጣና ይወርድ የነበረው የግድ ዘውድ ያያዘ አንበሳ ያለበት ሳይሆን መሠረታዊው አርንጓዴ ብጫና ቀይ ሰንደቅ ነበር። መሠረቱ ምንጊዜም ሶስቱ ቀለማት ናቸው። ንጉሡም ሆኑ ባለሟሎቻቸው የሚያውቋት ያችኑ በአረንጓዴ ብጫ ቀላማት ያንቆጠቆጠችውን ሰንደቅ ዓላማችንን ነበር። ትርጉሙም፣ አርንጓዴ ልምላሜንና ዕድገትን፣ ብጫው ዕምነትን (በእግዚአብሔር ማመንን) እና ቀዩ ኢትዮጵያዊው ሁሉ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ጉራ ጊሚራ፣ ወላይታ፣ አደሬ፣ ሲዳማ ትግሬ፣ እስላም ክርስቲያን ሳይል በአንደነት ደሙን አፍሦ፣ አጥንቱን ከስክሶ የወጃትን አገራችንን የሚያወሳ መሰዋዕትነትና ጀግንነትን ነው። አንድም ሰው፣ “ወድቆ በተነሳቸው ሰንደቅ ዓላማችን” ሲባል፣ ቀጥ ያላል። ሰንደቅ ዓላማችን የራሷ የሆነ ልዩ ክብርና ልዩ ፍቅር ሕዝባችን ዘንድ ነበራት።

እያንዳንዱ ሕብረተሰብና እያንዳንዱ ቤተሰብ ጋ ይኸች ሰንደቅ ዓላማ የየበተሰቡ እንደ አንድ አባል ሁና ነበር የኖረችው። ዛሬም አለች። በትግራይ፣ አንድ ትልቅ ሰው ሲሞት ክብሩ የሚለካበት፣ ሬሳው ሰንደቅ ዓላማ ለብሶ ወደ ቤትክርስቲያን ሲሄድ ነው። ያንን እንኳ ወያኔዎች አልተገነዘቡትም! ታዲያ ዘውድ የግድ ያለበት አልነበረም፣ አይደለም። ዘውድ ያለበት የሚውልበለበው ኦፊሴል በሆነ ንጉሡ ወይም እንደራሴአቸው ባለበት ብቻ ነው። ይኸች ሰንደቅ ዓላማ ከ፲፱፳፰ (1936) እስከ ፲፱፻፷፮ (1974) ኦፊሴላዊ በሆነ ቦታ ቻ ከዘውዱ ተውለበለበች። በየትምሕርት ቤቱ ሲትወጣ፣
ደሙን ያፈሰሰ ልቡ የነደደ፣
ባርበኝነት ታጥቆ ጠላት ያስወገደ፣
ንጉሡን አገሩን ክብሩን የወደደ
ነጻነቱን ይዞ መልካም ተራመደ፡፡
ገናናው ክብራችን ሰንደቅ ዓላማችን፣
ያኮራሻል አርበኝነታችን፡፡

እየተባለ እየተዘመረ ትወጣ ነበር። የሚሄድ ሁሉ በያለበት ይቆማል።
ሲትወርድ ደግሞ

ተጣማጅ አርበኛ በአገር መውደድ ቀንበር፣
ገዳይ ድል አድራጊ ደም አፍሳሽ ወታደር፣
አንቺን እያሰበ ይጓዛል ሲፎክር፣
ሰንደቅ ዓላማችን የነጻነት አገር

እየተባለ ሲዘመር አሁንም የሚንቀሳቀስ ሰው ቀጥ ይላል፣ የተቀመጠ ተንስቶ ቀጥ በተጠንቀቅ ይቆማል።

በ፲፱፻፷፮ (1974) ደርግ ሥልጣን ስይዝ፣ እስከ ፲፱፻፷፯ (1975) ዘውዱን አውርዶለት በኦፊሴል ሲጠቅም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ግን ሌጣው እንዳለ ሕዝቡ ይጠቀምበት ነበር። ትንሽ ቆይቶ ደርግ ኦፊሴሊያዊ በሆነ ቦታም ጭምር በየስብሰባው ያለ ዘውዱ አንበሳውን ያስቀምጥበት ጀመር


መሠረታዊውን አረንጓዴ ብጫ ቀዩን ግን ማንም ሊደፍር አልሞከረም። እንዲያውም መስከረም ፪ ቀን ፲፱፻፷፯ (1975) አምበሳውንም እስካናካቴው አነሳውና ሌጣ አርንጓዴ ብጫ ቀይ ኦፌሰሊያዊ ለሆነ ስብሰባ ሁሉ ሳይቀር የሚውለበለብ ተደርጎ መጠቀም ተጅምሮ ነበር።


ወዲያው፣ ትንሽ ቆይቶ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት፣ "የሕብረሰብዓዊት ኢትዮጵያ ጊዚያዊ ወታደራዊ መንግሥት" አርማ ቀርጾ መህል አስቀመጠና ኢፊሴሊያዊ በሆኑ ቦታዎች ይጠቅም ነበር፡፡ ሕዝቡም ሆነ መሥሪያ ቢቶች ግ ን ልሙጡን ከመጠቀም የሚያስገድዳቸው ሕግ አልነበረም፡፡



በኋላ ላይ ደርግ “ሕብረተሰባዊት ኢትዮጵያ”ን ሲያውጅ አንድ ያንን የሚያንጸባርቅ አርማ አስቀምጦበት ነበር። ልብም ያለው የለም። እነሱም ሆኑ ሕዝቡ ግን ያው ምንም ዓርማ ያልነበረበትን ነበር ይጥቀሙ የነበሩት።
በኋላ ላይ በ፲፱፻፸፯ (1985) ዓ.ም ላይ “የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት” መሰረትኩ ሲል አርማውን ቀየረ።


ሌጣው ግን ምንጊዜም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማነቱን እንኳን መከራከርና የጠየቀም አልነበረም። እንዴት ተደርጎ! ሁሉም አረንጓዴ ብጫውን አቅፎ በየቤቱ በየበዓላቱ ያውለበልብ ነበር።

በታካችን ሰንደቃላማችን የተዋረደችው ከወራሪው ጣሊያን በበለጠ በዚህ በወያኔ ዘመነ ፍዳ፣ ዘመን ኩነኔ ነው። አንደኛ፣ ከበረሀ ጀምሮ ቤተመንግሥት እስኪደረስ ድረስ ሰንደቅ ዓላማችን ወያኔ እንዳቀጠለና፥ እንደቀደደ፥ እንደረገጠ ነበር። አዲስ አበባን ሲቆጣጠር በሰላም የመከላከያ ሚኒስቴርን ሲረከብ እንደወራሪ ሰንደቅ ዓላማዋን ወዲያው እንደማይሆን አድርጎ አውርዶ የወያኔን ሰንደቅ ዓላማ በቦታው ተካ። ሰው እሪ ብሎ ሲጮኽበት ተገዶ በቦታው መለሰው። ይኸ ከሀዲ ቡድን ሕዝባችንን ልብ አያውቀውም እንበል? ከዚያ በኋላ ሰንደቅ ዓላማውን ለመቀየር ያልሸረበው ደባ፣ ያልፈተለው ተንኰል አልነበረም። በብዙ ሰው ትግል አረንጓዴ ብጫ ቀዩ ተረፈ። በ፲፱፻፹፬ (1992) የዘረኞች መንጋ ተሰብሰቦ ከመጀመሪያ በዩቲዩቡ ፊልም ላይ እንደታየው ዶልቶ፣ “የብሔር-ብሔረሰብነትን እኵልነት የሚያበስር” ብሎ በ፲፱፻፹፰ (1996) ላይ በክብ ሰማያዊ ኣምባሻ መሰል ዙሪያ ውስጥ የተሠራ ኮከብን ለጠፎበት “ህንካችሁ ትክክለኛው ባንዲራችሁ ይኽች ናት” ሊለን ሞከረ። የሆዳችንን በሆዳችን ይዘን ዘግተነው ትክክለኛውን መጠቀሙን ሕዝቡ ቀጠለ።


ቆዩኝማ! ማን ነበር ያ ስም አይጠሬ ይኸን ኮከብ ግንባሩ ላይ የለጠፈው? 
ማንም ክፍል ሥልጣን ሲይዝ የራሱን አርማ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ መለጠፉ የተለመደ እየሆነ መጥቷልና እሱስ መሆኑ ባላስገረመም ነበር። የነሱ አምባሻ አሽታሮት ብዙም ባልደነቀን ነበር። ዳሩ ግን፣ እየቆዩ በሄዱ ቁጥር ሌጣውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የያዘ ሁሉ የነሱን ኮከብ ካላስቀመጠበት ለነሱ ሰጥ ለጥ ብሎ አለመገዛቱ እየመሰላቸው መወንጀላቸው ነው።
ይኸ ሰንደቅ ዓላማ የአባቶቻችን ደም የፈሰሰበት፣ አጥንታቸው የተከሰከሰበት ነው። ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎበታል። በዚህ ምክንያት ማንም ሰው ተነስቶ የሚቀልድበት ወይም የፈለገውን ለጥፎበት ሊያርክሰው አይችልም። ወያኔ ሰንደቅ ዓላማችንን እንዳጎደፋት፣ መጥቶ ዛሬም በጉልበት ሥልጣን ጨብጦም እንዳዋረዳት ይገኛል። የሱ አሽታሮት የሌለበትንም “ባንዲራ” ሳይሆን አርንጓዴ ብጫ የያዘውን ሁሉ ወንጀለኛ በማድረግና በማሰር ሕዝባችንን ማሰቃየት ጀምሯል። ይኸንንም ከሚከተለው የአሜሪካን ድምጽ ሬዲዮ ቃለ መጠይቅ በመኢአዱ መሪ በእንጅነር ኃይሉ ሻውልና በአንድ የወ በወያኔ አፈቀቀላጤ ኃብታሙ ሚሚ በሚባለው መሀል የተካሄዱትን ክርክሮች በመስማት መረዳት ይቻላል።
ኮከብ የሌለው ባንዲራ ከዚህ ሥርዓት ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ባንዲራ ነው። ያ ሥርዓት ፈርሷል። በብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ትግል ፈርሷል! በሚገባ ለመስቀመጥም የጨቋኝ ሥርዐት ምልክት ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችና ወደዘር ጭቆና ዳግም ላለመግባት በጋራ ቃል ገብተው ነው ... አንድነታቸውን ለማጠናከር እየሠሩ ያሉት። ... ስለዚህ ከዚህ አንጻር ስናይ አንደኛ ባንዲራ እንደሚታወቀው ሰንደቅ ዓላማ ከስሙ እንደሚገለጸው የአንድን ሥራዓት አላማ ነው የሚገልጸው። የኛ የፌዴራል ሥራዐታችን ዓላማ የፌዴራሉ መንግሥት ባንዲራ ኮከብ ያለው ነው። ያኛው ሥርዓት የራሱ ዓላማ የነበረውና የወደቀ ሥርዓት ነው። ዳግመኛም የማይመለስ ሥርዐት ነው። ... እንግዲህ ያንን ሰንደቅ ዓላማ አውለበልባለሁ ብሎ ማለት ጸረ-ሕዝብነት በወንጀልም የሚያስጠይቅ ነው። ከዚያም ባሻገር በኢትዮጵያ ብሔር ብሐረ ሰቦች መበቶች እንደማመጽ የሚቆጠር ነው። ያንን ለስቀል መሞከር ሕገ-ወጥነት ነው። ሕገ መንግሥቱንም መተላለፍ ነው።
ኃብታሙ ሚሚ እንደዛተውም የወያኔ ኮኮብ የሌለበትን ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልበውን ሁሉ የጨቋኝ ሥርዐት አራማጆች እያለ ማሳደዱን ቀጥሏል። ወያኔ ታሪካችንን እያጎደፈ፣ ባሕላችንን እያቆሸሸ፣ አንድነታችንን እያፈረሰ፣ አገራችንን እየሸጠ ይኽ ምልክት ያለበትን ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብና “የባንዲራ ቀን እያለ” ማሾፍ ጅምሯል።

በቅርብ ቀን የወያኔ ቅልቦች ውጭ አገር ድረስ እጃቸውን አስረዝመው የተረገመችውን “ባንዲራቸውን” ስደተኛው እንዲቀበለው ማስገደድ ጅምረዋል። የወያኔ ተንኰል ያልገባቸው ወጣት ኢትዮጵያውን የስደተኛ ሊጆች ወያኔ በረሀብ ለሚፈጀው ሕዝባችን ገንዘብ ለማሰባሰብ፣ አባቶችን፣ እናቶችን፣ ወንድሞችን፣ እህቶችንና ጓደኞቻቸውን ለንዶን ውስጥ ለማሰባሰብ ሞክረው ነበር። የወያኔ ሰዎች በራሪ ወረቆቶቹ ላይ የነበረውን ሰንደቅ ዓላማ አይተው “ያ ትክክለኛ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሳይሆን የቅንጅት ሰንደቅ ዓላም ነውና በኢትዮጵያ ስም ይኸን ሰንደቅ ዓላማ መጠቀም አትችሉምና ትክክለኛው ይኸ ነው” ብለው አስፈራርተው እንዳይስቀየሩአቸው ደርሰንበት በግነናል።
ስደተኛው ኢትዮጵያዊ ሕብረተሰብ ይኸን ድፍረት መመከት ይገባዋል። ወያኔ ለአረንጓዴ፣ ብጫ ቀዮ ሌጣ ቀለም ተገቢውን ክብርና ቦታ እስካልሰጠው ድረስ ማንም ይኸንን የዘረኝነት ዓላማ የተንጸባረቀበትን የግድ መቀበል የለበትም። ወጣቶቹስ ምንም አያውቁምና አይፈረድባቸውም። ለትላልቆቹ ግን ትልቅ መልዕክት ማስተላለፍ ይጠበቅብናል። እሱም፣ ይኸንንም “ባንዲራ” ይዞ የተገኘ አዋቂ፣ የሟቾቹ አባቶቹና እናቶቹ አጥንት ይውጋው ብለን መርገም አለብን። እርጉም የተረገመ ይኹን! አሜን።[2] ወያኔ መሠረታዊውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እስካላከበረ ድረስ ከሱ ጋር ያበረ፣ ከሱ ጋር የተባበረ፣ ከሚተባበረውም ጋር የዋለ፣ የፕሮፌሰር ጌታቸውን ቃል ልዋስና፣ እሱም እራሱ ወያኔ ስለሆነ የተረገመ ይሁን። ይኸን የወያኔ የዘረኛ አርማ “ባንዲራ” የያዘ ሁሉ ጥቁር ውሻ ይውለድ በሉና ርግሙት። ዕውነተኛው ሰንደቅ ዓላማችን፣ ያልተበረዘች፣ ያልተለወጠች፣ በድል አድራጊነት ዛሬ ላይ የደረሰች አርንጓዴ ብጭ ቀይ አርማችንን ከፍ አድርገን እናውለብልባት።





[1] በቅንፍ ውስጥ የሚታዩት የአውሮፓ ወይም የግሪጎራውያንን አቆጣጠር ነው።
[2] ነሐሴ ፴ ቀን ፲፱፻፩ ዓ. ይኸንን በተመለክተ የተጻፈችውን የእንግሊዝኛ ግጥሜን ብሎጌ ላይ ማንበብ ይችላሉ። http://wondimumekonnen.blogspot.com/2010_06_01_archive.html