Saturday 31 March 2012

“ ሞት የሚፈራ ሙት ”


 ሞት  የሚፈራ  ሙት                የጐንቻው!

ከሰው ተራ ወርዶ ክብሩ ሲንኳሰስ፤

የሰብ ስብዕናው ቃል-አቡ ሲጣስ፤

ማተቡ ግማዱ ከአንገት ሲቦጠስ፤

የእምነቱ መሰረት ታቦቱ ሲረክስ፤

ስርዎ ስሪቱ ተክሉ ሰው ሲፈርስ፤

የሞተው ሞት ፈርቶ ገዳዩን ሲያነግስ፤

ደመ ነፍስ ይኖራል የማይላወስ።



በእራሱ መቃብር የሚንከላወስ፤

ሞት ኑሮ ሆነና የማይኰስኩስ፤            

ወዶ እሚጋቡበት የአደባብባይ ዳስ፤

ተዝካር መጠራሪያው የሰርጉ ድግስ፤

በድን ያሸለበው ‘አስከሬኑ ነፍስ’፤

ሞትን ሙጥኝ ብሎ ኑሮ ዋቢ ቢስ፤

በግፍ በበደሉ እንዳይከሰስ፤እንዳይወቀስ፤

ዳኛና ህሊና ሙት እሚያስጨርስ፤

ሙቶ የሸፈተው ወንጀለኛ ነፍስ፤

ቢጠሩት አይሰማ ቢወጉት ደንደስ።



ጥቃት፤ስቃይ፤ሊያመልጥ ማደንዘዣ ፈውስ፤

የሞት ሞቱን ሙቶ፤ቁም እሚያስለቅስ፤

ኑሮን ሙቶ ሊሸሽ ምሽጉን ሲምስ፤

ትንሹን ሞት፤ሊሞት የሚልወሰወስ፤

ለቀን ጆሞራዎች እርካሽ በለስ፤

ምናል? ፍራት ገድሎ፤ጀግና ቢወደስ።



በአገር ባድባራችን ገዳማት፤ሲያፈርስ፤

የጻድቃኖች አጽም ቆፍሮ እሚምስ፤

‘ገነት ፍሬ’ አማሎ ‘ሸንኮራ እጽ-በለስ’፤

ለእሸትም አይበቃ ለአውድማም አይደርስ፤

ለአንዳችንም አይበጅ የባዕዳን ድግስ፤

‘ደም እየጠጁልን’ እንዳንጫረስ፤

አያቀባብርም በግፍ ሞት ሲነግስ።



ጥፋተኛው ልማት የሺህ ዘመንት ጦስ፤

ደን መንጥሮ ችግኝ ቀጠና ሊያውርስ፤

አረብ ጨው ያጋጠው ግራኙ መለስ

ቀኝ እጁ ‘አላሙዲ’ ‘የዮዲት’ ጥንስስ፤

የንጉሡ ጥዋ ሞልቶ አገር ሲፈስ፤

አድባራት ሊያከትም ገዳማት ሊያፈርስ፤

‘መስቀል የቆረጠ’ ‘ጨረቃው ንጉስ’፤

መነኩሴ ሊያጠምቁ ‘ዋልድባ’ ድፍርስ፤

ከቀያቴው አፈር ሥጋ ደም ልውስ፤

ሞትን ድል በመቱ መነኰሳት ነፍስ፤

በአምላክ አገልጋዮች በንቁ መንፈስ፤
ሞትን እንግደለው ምዕመናን ተነስ።   

የጐንቻው!    yegonchaw@yahoo.co.uk

Tuesday 13 March 2012

በአደባባይ መዘባረቅ መብት አይደለም! ቁልቁለቱን ለብቻ

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም

ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ወዲህ የመጡት ገዢዎች የታሪክ አዋቂዎች ለመምሰል የሚጥሩ ናቸው፤ ምክንያቱን በኋላ እናየዋለን፤ በቅርቡ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትግላችን የሚል ትልቅ መጽሐፍ አሳትሞአል፤ እዚህ ደሞ አቶ ስብሐት ነጋ አክሱም ለተንቤንና ለአጋሜ ምኑ ነው በማለት አዲስ የኢትዮጵያ ታሪክ ነግሮናል፤ የጎሠኛነት አስተሳሰብ እየጠበበና እያጠበበ መሄዱ የታወቀ ነው፤ እስቲ ስብሐት ተናገረ የተባለውን ፍሬ-ገለባነትን ትተን ያስተሳሰቡን አድማስ ቆንጠር አድርገን እንየው፡፡
‹‹ታሪክና የፖለቲካ አቋም ይለያያል፡፡ የተናገርኩት እኔ የማውቀውን ታሪክ ነው፡፡ ታሪክ አውቃለሁ የሚል ደግሞሊ ያጣራው ይችላል፡፡ ታሪክ የፖለቲካ አቋም ስላልሆነ ተነቦ ሊስተካከል ይችላል፡፡እኔ እንደሚመስለኝ የአክሱም መንግሥት በመጀመሪያ ደረጃ የ ከተማ   መንግሥት  ይመስለኛል፡፡እንደነ አቴንስ እንደነ እስፓርታ የከተማ መንግሥት ይመስለኛል፡፡›› ሰንደቅ የካቲት 14 2004

እነዚህ ስድስት ዓረፍተ ነገሮች አቶ ስብሐት ነጋ በተጠቀሰው ጋዜጣ ላይ የተናገራቸው ናቸው ተብለው የወጡ ናቸው፤ ዛሬ ሁለት ሳምንት ሊሆነው ነው፤ ስብሐት ነጋ አላስተባበለም፤ አንዳንዱን ዓረፍተ ነገር ለየብቻው እንየው፤--

1. ታሪክና የፖለቲካ አቋም ይለያያል፡ ፡ እስማማለሁ፤ ምንም ቅሬታ የለኝም፡፡


2. የተናገርኩት እኔ የማውቀውን ታሪክ ነው፡፡ ችግር አለ፤

ሀ)ስብሐት ነጋ የሚያውቀው ታሪክ ወላጆቹ ከሚያውቁትና እኛ ከምናውቀው ታሪክ እንዴት ተለየ? እኛ ተማሪ ቤት አልሄድንም፤ ወይ እሱ ተማሪ ቤት አልሄደም፤ ወይ የእኛ እውቀት በልፋት የተገኘ ሲሆን የእሱ በመንፈስ ኃይል የተገለጠለትና የታየው ነው፤ ወይ ስለጉዳዩ የተጻፉትን መጽሐፍት አላነበበም፤

ለ)የተናገርሁት እኔ የማውቀውን ነው ማለት ምን ማለት ነው? አንድ ሰው አራትና አራት ስድስት ነው ከአለ በኋላ የተናገርኩት እኔ የማውቀውን ሂሳብ ነው ቢለን ምን እንለዋለን? ድንጋይ ቢበሉት ያጠግባል ብሎ ከተናገረ በኋላ የተናገርኩት እኔ የማውቀውን ነው ቢለን ምን እንለዋለን?

3. ታሪክ አውቃለሁ የሚል ደግሞ ሊያጣራው ይችላል፤ አውቃለሁ ያለው ስብሐት ራሱን መጠራጠር የጀመረ ይመስላል፤ በታሪክ እውቀት ከስብሐት የሚበልጥ ሰው ከአለ ጉዳዩን እንዲያጣራው ፈቃድ ይሰጣል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው ከአነበበና ከተመራመረ ስብሐት ወደደረሰበት መደምደሚያ ሊያደርስ ይችላል ማለቱ ይሆናል፡፡

4. ታሪክ የፖለቲካ አቋም ስላልሆነ ተነቦ ሊስተካከል ይችላል፤ የአስተሳሰብ ችግሩ ምንጭ እዚህ ላይ ነው፤ ይህ ዓረፍተ ነገር በቅርጹም በይዘቱም ፉርሽ ነው፤ ሊስተካከል የሚችለው ታሪክ ነው? ወይስ የፖለቲካ አቋም? በስብሐታዊ አስተሳሰብ የፖለቲካ አቋም አይነቃነቅም፤ አይለወጥም፤ ታሪክ ግን ሊለወጥ ይችላል፤ በስብሐታዊ አስተሳሰብ የፖለቲካ አቋም ሃይማኖት መሆኑ ነው፤ ስለዚህ አይለወጥም፤ ይችላል፤ ለስብሐት ከራራንለት ስለታሪክ የሚያነብ ሰው የበለጠ ሲያውቅ ራሱን ያስተካክላል ብለን እንተረጉምለታለን፤ ለስብሐት ካልራራንለት ደግሞ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት የሆነውን ታሪክ እናስተካክለዋለን ማለቱ ስለሆነ ልክ አይደለም እንላለን፤ በሌላ አነጋገር ታሪክ በስብሐት አስተሳሰብ ይስተካከላል፤ በጣም ግልጽ ለማድረግ፣ ስብሐታዊ አስተሳሰብ የሚለው ያለፈውን፣ ያላየነውንና በቀጥታ የማናውቀውን መለወጥ እንችላለን፤ የወደፊቱን፣ ያልደረስንበትን፣ እኛ ራሳችን እየሰራን ያለነውን ግን ልንለውጠው አንችልም!

5. እኔ እንደሚመስለኝ የአክሱም መንግሥት በመጀመሪያ ደረጃ የከተማ መንግሥት (City state) ይመስለኛል፤ እዚህ ላይ ታሪክን ወደተረት የመለወጥ ዝንባሌ መጣ፤ አክሱምን እንደነገሩ እንኳን የማያውቅ ሰው ባሕር ተሻግሮ ስለአቴንስና ስለስፓርታ እንደነገሩ እንኳን የማያውቀውን ቢጨምርበት ወደታች እንጂ ወደላይ የሚወስድ መንገድ አያገኝም፤ የየጁ ደብተራ ቅኔ ቢጎድልበት ቀረርቶ ሞላበት እንደሚባለው የማይገናኙ ነገሮችን ማገናኘት ነው፤ ወይም በአፈር ቡኮ ቂጣ ለመጋገር አይቻልም፡፡)

አንድ ሰው እንኳን ሳይገደድ ተገዶስ ቢሆን የማያውቀውን ነገር ለምን ይናገራል? አንድ ጊዜ ግቢ በአስቸኳይ ድረስ ተብዬ ሄድኩና ጃንሆይ ፊት እጅ ነሥቼ ስቆም፣ ‹‹የት›› ስለሚባል ኦጋዴን ውስጥ ያለ መንደር ጠየቁኝና እንደማውቀው ከተናገርሁ በኋላ በ‹‹የት›› የሚገኘው የውሃ ጉድጓድ በቀን ስንት በርሜል ውሃ ይወጣዋል? ብለው ጠየቁኝ፤ ‹‹ጃንሆይ አላውቅም፤›› አልሁ ደጋግመው ግምት ጠየቁኝ መልሴ ያው አላውቅም ሲሆንባቸው ‹‹ሂድ ውጣ!›› አሉኝ፤ የማላውቀውን ለምን ልዘባርቅ የኢትዮጵያን ታሪክ አጥርቶ ሳያውቅ ጭራሹኑ ወደማያውቀው ወደ ጥንቱ የግሪክ ታሪክ ምን አስኬደው!

ታሪክ በአጥንትና በደም የተገነባ መቅደስ ነው፤ ታሪክ የስንትና የስንት ትውልዶች የተጋድሎ፣ የፍቅርና የቃል ኪዳን፣ የኩራትና የክብር፣ የመብትና የግዴታ ገድል ነው፤ ታሪክ መዝገብ ነው፤ ምስክር ነው፤ ታሪክ የህልውና መሠረት ነው፤ ማንነት ነው፡፡

በአለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ታሪክ ከፋሺስት ኢጣልያ ዘመን ያላነሰ ውርደት ደርሶበታል፤ አምባ-ገነኖች ታሪክን የሚያነሡት የወደቀውን ለመቅበርና ሁልጊዜም በግልጽ እንደሚሉት ‹‹በመቃብሩ ላይ ለመቆም›› ነው፤ ከዛሬ በፊት የነበረውን ሁሉ በማራከስ፣ በማጥላላት፣ በማናናቅ፣ በማፍረስ ታሪክ ነገ እንደሚጀምር የተስፋ ዳቦ መጋገር ለአለፉት አርባ ዓመታት የተለመደ ሆኖ እያሰለቸን ነው፤ የትናንቱ ታሪክ በትንንሽ ሰዎች እንደማይደመሰስ ሁሉ የነገውም ታሪክ በትንንሽ ሰዎች አይገነባም፡ ፡

ትናንትን ያላግባብ እያራከሰ ለመቅበር የሚጥር ሁሉ ዛሬን ትናንት ያደርገዋል፤ ትናንትንና የትናንትን ኃይል ከነድካሙ በትክክል ያልተገነዘበ የሚቆምበት መሬት አያገኝም፤ የሚንደረደርበትም ሆነ የሚንደረደርለት ዓላማ የለውም፤ ከሆዱ በቀር የሚሞትለት ወይም የሚሞትበት ዕዳ የለውም፤ እንደእውነቱ ከሆነ ግን ሁላችንም የታሪክ ዕዳ አለብን፤ ጥንት ከተለያዩ ቄሣራውያን ኃይሎች ጋር አባቶቻችንና እናቶቻችን የፈጸሙትን ተጋድሎ እንርሳው፤ ከሰባ አምስት ዓመት በፊት ከፋሺስት ኢጣልያ ጋር ለተደረገው ትግል የተከፈለውን መስዋዕትነት እንርሳው፤ ለመቋቋም የተከፈለውን መስዋእት እንርሳው፤ የቅርቡን የባድመን እንዴት ልንረሳው እንችላለን? በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የጅብና የአሞራ ምግብ ሆነው የቀሩት በእውነት ለቁራጭ መሬት ብቻ ነው? የአድዋ ክብርና ኩራት፣ የማይጨው ውርደት የለበትም? እንደስብሐት ነጋ ያለ በትልቅ የኃላፊነት ቦታ ላይ ያለው ሰው ይህንን ይስታል ለማለት ያስቸግራል፤ ስሕተት ካልሆነ ታሪክን በጎሣ ማጥበብ ዓላማው ምንድን ነው? አደጋ ሲመጣ እንኳን ከተምቤንና ከአጋሜ ጋር ከቦረናና ከኦጋዴንም ጋር የታሪክ ዝምድና መቁጠር አስፈላጊ ይሆናል፡፡
በወላጆቻችን የምናፍርበት ምክንያት ቢኖርም መንፈሳዊ ወኔያችንን አጠንክረን ህመማችንን ልንጋፈጠው ይገባል እንጂ ታሪካችንን በሙሉ በማራከስ ከሐፍረታችን አንድም፤ የአንድ ሰው ታሪክ የአንድ ሰው ታሪክ ነው፤ የአንድ ቤተሰብ ታሪክ የአንድ ቤተሰብ ታሪክ ነው፤ የአንድ አገር ታሪክ ደግሞ የተለየ ነው፤ የሁሉም ነው፤ ኩራትና ክብሩ የጋራ ነው፤ ውርደትና ሐፍረቱም የጋራ ነው፤ የግል ቁስልን አክካለሁ ብሎ አገርን ማቁሰል ተገቢ አይደለም፡፡

ትናንት ለዛሬው ሕይወት የሕይወት ዋጋ የተከፈለበት ነው፤ ዛሬ የትናንትን ውለታ ተሸክሞ የቆመ ነው፤ ይህ ሸክምና ውለታ ለእንደ ስብሐት ነጋና መሰሎቹ አይሰማቸውም፤ እነሱ የሚያውቁት የዛሬውን ምቾትና ጉልበተኛነት ነው፤ እነሱ የሚያውቁት የዛሬውን ማናለብኝነት ነው፤ አቶ ስብሐት ስለአክሱም ታሪክ የተናገረው (መናገሩን የማውቀው ባለማስተባበሉ ነው፤) በትምህርትም ሆነ በንባብ ያገኘው ነው ለማለት ይከብዳል፤ አለማወቁን የነገረን ስለአክሱም ብቻ ሳይሆን ስለከተማ ሀገረ-መንግሥቶችም (City state) ነው፤ በእርግጥ ለስብሐት አዲስ የሚባል ነገር ተናግሮአል፤ የተለየ ነገር የሚያውቁ ካሉ ያስተምሩ፤ ይናገሩ፤ በማለት ፈቅዶአል! ስለዚህ ልንጨክንበት አይገባም፤ ነገር ግን አንድ ጥያቄ ለመጠየቅ እንገደዳለን፤ ከመጠምጠም ትምህርት ይቅደም፤ የሚባለውን ስብሐት ሳይሰማ አይቀርም፤ ስለዚህ የማያውቀውንና እርግጠኛ ያልሆነበትን ዓቢይ የአገር ታሪክ ሞሽልቆ ራቁቱን አስቀርቶ በአደባባይ በጋዜጣ ለመናገር እንዴት ደፈረ? የማያውቁትን ነገር ለማወቅ መድኃኒቱ መጠየቅ ነው፤ ጥያቄ በመጠየቅ የሚወቀስ የለም፤ የማያውቁትን በአደባባይ መዘባረቅ ግን ከማስወቀስ አልፎ ያስንቃል፡፡

የአክሱምን ሀገረ-መንግሥት የአረብ፣ የኢጣሊያ፣ የፈረንሳይ፣ የእንግሊዝ፣ የሩስያ… ሊቃውንት ለረጅም ጊዜ አጥንተው ጽፈውበታል፤ እኔ በእጄ ስላሉ የጥናት ውጤቶች ለመናገር ነው እንጂ በጀርመንና በሌሎችም ቋንቋዎች ጥናቶች ይኖሩ ይሆናል፡፡

ታሪክ የቡና ቤት ወሬ አይደለም፤ ማን ጠያቂ አለብኝ በማለት አፍ እንዳመጣ እየተናገሩ ታሪክን ማወላገድ ለወጣቶችና ለትንንሾቹ ልጆች አለማሰብ ነው፤ አንድ ሰው ስለአክሱም ሀገረ- መንግሥት የምን ያህል ጊዜ ጥናት አድርጎ፣ የእነማንን ጥናት አንብቦ የአክሱምን ታሪክ በድፍረት ለመናገር ቻለ የሚለውን ጥያቄ ማንሣቱ ዋጋ የለውም፤ ምክንያቱም አንድ ነገር ወይም አንድ ሰው ከባሕርዩ ውጭ ሌላ ሊሆን አይችልም፤ ታሪክ ሰዎችን ለማስደሰት ወይም ለማዝናናት የሚነገር ተረት አይደለም፤ ምን ዓይነት ጥላቻና ጎሠኛነት ነው በድንጋይ ላይ የተጻፈውን ታሪክ ለመካድ የሚያስገድድ? እንደስብሐት ሥልጣንን እውቀት አድርገው ለሚገምቱ ሰዎች በ1996 በታተመው የክህደት ቁልቁለት መጽሐፍ ውስጥ የተለያዩ ሊቆች፣ የፈረንሳይና የአረብ፣ የኢጣልያም ሆነ የእንግልጣር ሳይቀር፣ ስለአክሱም የጻፉትን ጠቅሼ በአራት ገጾች ላይ ጽፌ ነበር፤ ሌላው ሁሉ ቀርቶ ያንን እንኳን ያላነበበ ሰው አንብቦ ስለማጣራት ይነግረናል፤ በተለያዩ ምክንያቶች የተጠቀሱትን መጽሐፍት ለማንበብ የማይችል ሰው ባይሆን ጥቅሶቹን አንብቦ ሌላውን ከማሳሳት መዳን ይችል ነበር፤ ሥልጣን አለኝ ተብሎ አለማወቅን በአደባባይ ማወጅ፣ ሕዝብን፣ በተለይም ወጣቱን ከጥንት ታሪኩ ጋር ለማቆራረጥ መሞከርና ማሳሳት ሊያሳፍር ይገባል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጣን በእውቀት ላይ ያለውን የበላይነት በግልጽ የሚያሳየን ከሠላሳ ሁለት ዩኒቨርስቲዎች (ዶር. ዳኛቸው እንዳለው ይህንን ያህል ካሉ) ውስጥ አንድም የታሪክ ሊቅ ለሙግት ብቅ አላለም፤ ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያ መካነ ጥናትም ትንፍሽ ሲል አልሰማሁም! ሁሉም በሆዱ ተሰንጎአል! እዚህ ላይ የስብሐት ድፍረት ይጠቅማል፤ ስብሐት ቢጠየቅ ስለጳጳሳቱ ያለውን ስለሊቃውንቱ ይደግመው ነበር፤ በመሀከላቸው አንድ ሰውም የለባቸውም እንደሚል አልጠራጠርም!

Monday 12 March 2012

የአንዱአለም አራጌ ቃል - ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት - ፍትህ ጋዜጣ

አንዱአለም አራጌ ቃል - ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት - ፍትህ ጋዜጣ

  በዚህ በቃሊቲ ወህኒ ቤት በእኔ ላይ የደረሰውን የግድያ ሙከራ አስመልክቶ በተከበረው ጋዜጣዎ መዘገቡን ሰማሁ፡፡ በቅድሚያ ጋዜጣዎ እውነቱን ለማሳወቅ ስለአደረገችው ጥረት ከልብ እንዳመሰግን እንዲፈቀድልኝ እጠይቃለሁ፡፡ እነሆም ፍቃድ ከጠየቁኝ ዘንዳ ምስጋናዬን አቀርባለሁ!
በዚህ ለኑሮም ሆነ ለማሰብ ፍፁም በማይመች ሁኔታ ለዛውም ከተፈፀመብኝ አሰቃቂ ድብደባ ሳላገግም ብዕርና ወረቀት እንዳገናኝ የጐተጐተኝን ጉዳይ ከዚህ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡ ባለሁበት ወህኒ ቤት ጋዜጦችን ቀርቶ መፃህፍትንም ማስገባት ባለመቻሌ እናንተ የምትኖሩበት ‹‹ዓለም›› ከሚያቀርበው የመረጃ ማዕድ መቋደስ አልችልም፡፡ ሆኖም እንደሌላው እስረኛ ሁሉ በህገ-መንግስቱ መሰረት እንዳልጠየቅ አሳሪዎቼ ቢከለክሉም እንዲጠይቁኝ ከተፈቀደላቸው ሁለትና ሶስት ቅርብ የቤተሰብ አባሎች አልፎ አልፎ ወሬ መቃመሴ ግን አልቀረም፡፡ እናም ይህን በመሰለው ሁኔታ ውስጥ ወህኒ ቤቱ በእኔ የደረሰውን የግድያ ሙከራ አስመልክቶ የሰጠውን ምላሽ ይዘት በመስማቴ ቀደም ሲል በጉዳዩ ላይ የመናገር ፍላጐት ባይኖረኝም በቀጥታና በዝርዝር ማስረዳት እንደሚገባኝ ከራሴ ጋር ስምምነት ላይ ደረስኩ፡፡
ስለሆነም አሁን ካለሁበት የእስር ሁኔታና ከገጠመኝ የጤና መቃወስ አንፃር ሃሳቤን በወጉ ለማደራጀት መቸገሬን ግንዛቤ ውስጥ አስገብተው ሃሳቤን በሚከተለው አኳኋን እንዳቀርብ መልካም ፍቃድዎ እንዲሆን በአክብሮት በድጋሚ ጠይቄ ወደ ዋናው ጉዳይ እገባለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብና አለም እንደሚያውቀው ለሁለት ወራት ገደማ በማዕከላዊ እስር ቤት ከቆየው በኋላ ወደ ቃሊቲ ወህኒ ቤት መዛወሬ ይታወሳል፡፡ ቃሊቲም እንደገባው ከሌሎች በአንድ መዝገብ ከተከሰስን ሰዎች ተነጥዬ፣ አሰቃቂ ወንጀል ፈፅመው የታሰሩና በተደጋጋሚ እያመለጡ ያስቸገሩ እስረኞች ወደሚታሰሩበት (የቅጣት ቤት) ተወሰድኩ፡፡ እናም ለምን ወደዚህ አይነት ቦታ እንደተወሰድኩ ለሰሚው ግራ እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡ መቼም በወህኒ ቤቱ ውስጥ ግማሽ ቀን እንኳን ባልቆየሁበት ሁኔታ ‹‹ለአያያዝ አስቸግሮኝ ልዩ ጥበቃ (Maximum security zone) ውስጥ አስገባሁት›› ሊል አይችልም፡፡ ይህ ውሳኔ ቀደም ሲል መከሰስ እንዳለብኝ ከወሰኑት አሳሪዎች እንደተላለፉ መገመት የሚከብድ ጉዳይ አይደለም፡፡
አሳዛኙ ጉዳይ ግን በዚች እጅግ በጣም ጠባብና አራት ማዕዘን ሰማይ ብቻ በሚታይባት እስር ቤት ተወርውሬም የአሳሪዎቼ የበቀል በትር ያልታለየኝ መሆኑ ነው፡፡ በዚች የጭንቅ ማማ ሁለት ወራትን እያገባደድኩ በነበርኩበት አንድ ምሽት ድብደባውን የፈፀሙብኝ አቶ ይባስ አስፋው እንዲቀላቀሉኝ ተደረገ፡፡ አብረውኝ ከነበሩት ከኦፌዴኑ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ጋር በመሆኑ እንደሁላችን ጐናቸውን ያሳርፉበት ዘንድ ወለሉን ካመቻቸንላቸው በኋላ፣ ቤት ያፈራው ቀማምሰን የእስር ህይወታችን ቀጠልን፡ ፡ በመታሰሪያ ክፍላችንም የተከሰስንበትን ሁናቴ ጨምሮ ቀደም ሲል ያለንን የእስር ተሞክሮና አንዳንዴም ግለታሪካችንን መጨዋወታችን አልቀረም፡፡ እናም ከአንደበታቸው በተደጋጋሚ እንደሰማነው በበርካታ የነፍስ ማጥፋትና ከባድ የዘረፋ ወንጀል ምክንያት እንደታሰሩ ገለፁልን፡፡ አክለውም ከዶ/ር ታዬ ወልደሰማያት፣ ከአቶ ታምራት ላይኔና ከአቶ ስዬ አብርሃ ጋር እንደታሰሩ አጫወቱን፡፡ ‹‹ለምን እኒህ ሰው ተለይተው ከእነዚህ ፖለቲከኞች ጋር ታሰሩ?›› የሚለውን ጥያቄ ግን መመለስ አልቻልንም፡፡ በሂደት ለረጅም ጊዜ የሚያውቋቸው እስረኞች የማረሚያ ቤቱ ሰላይ በእነርሱ አገላለፅ ‹‹ወሬ አቀባይ›› መሆናቸውን አስረዱን፡፡ እርሳቸው ግን ሌላውን ታሪክ ባይነግሩንም አሁን ያለንባት ጠባብ ክፍል ውስጥ ከታሰሩ የመጀመሪያ እስረኞች አንዱ ስለመሆናቸው ገለፁልን፡፡
ቃሊቲ ውስጥም ሆነ ውጭ ትክክል ነው ብዬ የማምንበትን ነገር ፊት ለፊት መናገር ወይንም መተግበር ከጉዳቱ ጥቅሙ እንደሚያመዝን አምናለሁ፡፡ ከ1998-1999 ባለው ጊዜ በአብዛኛዎቹ የቃሊቲ ወህኒ ቤት ዞኖችና በከርቸሌ ጨለማ ቤት ድረስም ስታሰር የተከተልኩት ዘይቤ ይኽኑ ነው፡፡ በሂደቱም ከአንድም እስረኛ ጋር የሃይል ነገር ቀርቶ፣ ሃይለ-ቃልም ተለዋውጬ አላውቅም፡፡ ‹‹ቦዘኔ›› ክልል ተብሎ ይታወቅ በነበረው ዞን እንኳን ይኽንን የመሰለ ነገር አልፈፀምኩም፡፡ በጊዜው አብረውኝ የታሰሩ ጓደኞቼ እንደሚያስታውሱት አልፎ አልፎ ፀቤ ከፖሊስ ጋር ነበር፡፡ ከፖሊስም ጋር ቢሆን የነበረኝ አለመግባባት ‹‹ለምን የእስረኛ መብት አይከበርም? ለምንስ እስረኛ ይደበደባል?›› በሚል እንጂ በሌላ ምክንያት እና በግል ጉዳዬ አልነበረም፡፡ ይኽንንም በግልጽና በአክብሮት ከመግለፅ ውጭ የተለየ አቀራረብ ኑሮኝ አያውቅም፡፡ አቶ ይባስ አስፋውም ለረጅም ዓመታት የታሰሩና የኤች አይ ቪ ታማሚ በመሆናቸው ከማክበርና ከመንከባከብ ውጭ አንዳች ቅር የሚያሰኝ ነገር ተናግሬያቸው ወይንም ፈፅሜ አላውቅም፡፡
ነገር ግን ገና አንድ ሳምንት ሳይሞላቸው ጀምሮ በጋዜጣ ላይ ሊገለፁ የማይችሉ አያሌ ፈታኝ ነገሮችን ያደርሱብኝ ጀመር፡፡ መዘለፍ የእለት ተእለት ህይወቴ ሆነ፡፡ እንደ ድመት በጥፍሬ ቆሜ መውጣት መግባት የዘወትር የአኗኗር ዘይቤዬ ሆነ፡፡ ከአለፈው የእስር ተሞክሮዬ በመነሳት ያረጋጋቸዋል ብዬ የማስበውን ነገር ሁሉ ባደርግም አልተሳካልኝም፡፡ ያለአንዳች ማጋነን ክብራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከተናካሽ ውሻ ጋር ከመታሰር ፈፅሞ የተለየ አልነበረም፡፡ ጊዜው እየገፋ ሲሄድ ተራ ስድብ እየተሰደብኩም ሁሉንም በፀጋ ከመቀበል ባለፈ ሌላ አማራጭ አላገኘሁም፡፡ አስቀድሜ እንደገለፅኩት ያለሁበት እስር ቤት ከወህኒ ቤቱ አቅም በላይ የሆኑ እስረኞችና በሌሎች የወህኒ ቤቱ ዞኖችም አደገኛ የተባሉ እስረኞች ለቅጣት የሚመጡበት ቤት ነች፡፡
ታዲያ ሰውየው እኔና ሌሎች በእጣት የምንቆጠር እስረኞች ወዳለንበት ቅጥር ለምን መጡ? ከቀደመው የእስር ቤት ቆይታዬ እንደተረዳሁት እስረኞችን እንዲሰልሉ የሚመደቡ እስረኞች አሉ፡፡ ስለደብዳቢዬ ከታሳሪዎች ከተረዳሁትም በላይ በተለያየ ወቅት ከተለያዩ ፖለቲከኞች ጋር መታሰራቸው ለምን ይሆን? የሚለው ጥያቄ እየተመላለሰ ሳያሳስበኝ አልቀረም፡፡ መጀመሪያ ሞት፣ ከዛም በኋላ በይገባኝም እድሜ ልክ የተረደባቸው እስረኛ በመሆናቸው ለ16 ዓመታትም እንደሚሉት የታሰሩ በመሆናቸው ክፍለ ሀገር በዝውውር ቢሄዱ ኑሮ እስከአሁን ሊፈቱ ይችሉ እንደነበር በማንሳት ይቆጫሉ፡፡ የወህኒ ቤቱን ሃላፊዎች ከረጅም ቆይታቸው የተነሳ እስከ ቤተሰብ ድረስ እንደሚያውቋቸውና የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሊያስረዱን ሞክረዋል፡፡ ከድብደባው 10 ቀናት በፊት ወደ ዋናው የወህኒ ቤቱ ኃላፊ ቢሮ እያሉ በየቀኑ ማለት በሚቻል ሁኔታ በጥበቃ ፖሊሶች አማካኝነት ይመላለሱ ነበር፡፡ ሁኔታው ለሁላችንም ግልፅ ነበር፡፡ የስለላ ስራ እየሰሩ እንደሆነ፡፡ እናም በዚያ ወቅት በእኔ በኩል በወንጀለኛ መቅጫ አንቀጽ 148 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት ለፍርድ ቤት ለማቅረብ በመፃፍ ላይ ነበርኩ፡፡ ወረቀቱንም ልነጠቅ እንደምችል የራሴን ግምት ወስጀጃለሁ፡፡ የተለየ አማራጭም ሆነ የሚደበቅ ጉዳይ ባለመኖሩ የመጣው ይምጣ ብዬ መፃፌን ቀጠልኩ፡፡ የኔ ሀሳብ የነበረው ወህኒ ቤቱ በፍተሻ ሰበብ ይወስድብኛል የሚል ነበር፡፡ የተፈጠረው ግን ከዚህ ፈፅሞ የተለየ ነበር፡፡
ግለሰቡ በ6/6/2004 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ እንደተለመደው ዋና አስተዳዳሪው ቢሮ ውለው መጡ፡፡ እንደመጡም ፍራሻቸውን አሁን ወዳሉበት ዞን ለመላክ ሲሞክሩ ግራ ከመጋባት በዘለለ የተለየ ሀሳብ አልያዝኩም፡፡ መፃፌን ግን ቀጥያለሁ፡፡ በዚያው እለት ማታ ሽንት ቤት ገብተው ሲወጡኩ ‹‹ቧንቧ ባለመዝጋታችሁ ውሃ ፈሰሰብኝ›› በማለት ‹‹እናንተ ትንንሾች›› ሲሉ ሶስታችንንም በጅምላ ሰደቡን፡፡ አሰዳደባቸውና ሁናቴአቸው ከሌላ ጊዜ የከረረና እንደምንም ምክንያት ፈልገው አካላዊ ግጭት ውስጥ ለመግባት የመፈለግ ፍላጐት ይነበብባቸው ነበር፡፡ ሶስታችንም ለመሃላ እንኳን አንዳች ሳንተነፍስ ምሽቱም እየገፋ ነበርና እንደተገረፉ ህፃናት ትንፋሻችንን ውጠን ወለሉ ላይ እንደ አስከሬን ተገግጠን አንቀላፋን፡፡ በማግስቱ የግድያ ሙከራ ባደረጉብኝ ቀን አርፍደው ከእንቅልፍ ነቁ፡፡ አቶ በቀለ ገርባ ያነባል፡፡ እኔ አሁንም እየፃፍኩ ነው፡፡ አቶ ይባስ እንደተነሱ በመጮህ ያዘጋጁትን በሶ ‹‹ትጠጣላችሁ አትጠጡም›› አሉ፡፡ ሁለቱ የእንርሱን ድርሻ መጠጣታቸውን ሲገልፁ እኔ መጠጣት እንደማልፈልግ ገለፅኩላቸው፡፡ ይኽ የሆነው ከቀኑ 5 ሰዓት ገደማ ነው፡፡ ስምንት ሰዓት ተኩል ሲሆን በፀጥታ የተቀመጥንባት ክፍል በር በሃይል ተከፈተ፡፡ ደብዳቢዬ ለረጅም ሰዓት ከቤት ውጭ ቆይተዋል፡፡ ሃሳባቸው ሌሎቹ እስረኞች ሲወጡ ጠብቀው ውሳኔያቸውን ለመፈፀም እየተጠባበቁ እንደነበር ነው ከድርጊታቸው በኋላ የተረዳሁት፡፡ በአጋጣሚ ሁላችንም በስራ በመጠመዳችን ከተቀመጥንበት አልወጣንም፡፡ ጊዜ እየመሸባቸው ስለነበር ያላቸው አማራጭ ባለው ሁኔታ እርምጃውን መውሰድ ነበርና በሩን እንደከፈቱ ተንደርድረው በመግባት አሳልፈው ይሰጡብኛል ብዬ የሰጋዋቸውን ወረቀቶች ከሌሎች ወረቀቶች እየለዩ ጉዳዩን ይከታተሉ ስለነበር ከያሉበት ለቀሟቸው፡፡ ከማስታወሻ ደብተሮቼም በተጨማሪ 40 ገጽ ወጥ ፅሁፍና ሌሎችንም ሰነዶችን በእጄ ላይ የነበረውን ጨምረው ነጠቁኝ፡፡ ይኼ ነገር እንደሚመጣ በተወሰነ መልኩም ቢሆን እጠብቀው ነበርና ዝምታን መረጥኩ፡፡ በበኩሌ ከማንም ሰው ጋር ቢሆን ግብግብ መግጠም አልፈልግም፡፡ ስለዚህም ዝም አልኩ፤ ሆኖም ዝምታዬ መፍትሄ አልሆነም፡፡ እናም ከተቀመጥኩበት ተንደርድረው ከኮንክሪት ግድግዳ ጋር አጣብቀው ጭንቅላቴን ረገጡኝ፡፡ ተንሸራትቼ በቀኝ ጐኔ የሲሚንቶው ወለል ላይ ተነጠፍኩ፡፡ አሁንም አልበረዱም፡፡ ከወለሉ ላይ ጭንቅላቴን ሶስት ጊዜ እንደረገጡኝ አቶ በቀለ መሃል በመግባት ለማስጣል ሲሞክሩ በሰመመን ውስጥ ሆኜ እሰማለሁ፡፡ ‹‹እገለዋለሁ! ብገለው 6 ወር ብቻ ነው ካቴና የሚገባልኝ›› ይላሉ፡፡ አቶ በቀለንም ዘወር ካላለ እንደሚደበድቡት ይዝታሉ፡፡ ነገር ግን አቶ በቀለ ‹‹ደብድበኝ እንጂ ስትጨርሰው ዝም ብዬ አላይህም፡፡›› እያለ ግብግብ ገጥሟል፡፡ ከዚህ በኋላ ሌሎች እስረኞችም በመጨመራቸው ወለሉ ላይ እንደወደኩ ደብዳቢዬን ገፋፍተው አስወጧቸው፡፡ ትንሽ ራሴን ማወቅ ስጀምር ጭንቅላቴ ላይ ድብደባ ስለተፈፀመብኝ ህክምና የማገኝበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹልኝ ፖሊሶችን ጠየኩ፡፡ የተከበሩ የጋዜጣው አዘጋጅ እስካሁን የገለፅኩልዎ ሁሉ እውነት ስለመሆኑ በፈጣሪ ስም አረጋግጥልዎታለሁ፡፡
ከፍ ብዬ አጠቃላይ ሂደቱን ልገልፅልዎ ሞክሬያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ የወህኒ ቤቱ አስተዳዳሪ ሁኔታውን አስመልክቶ በጋዜጣዎ ባወጣው ምላሽ ላይ የእኔን እምነት እንድገልፅ ፈቃደዎንና ትግስትዎን በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ እውነቱን ለመናገር የእኔ ጉዳይ በአሳሪዎቼ በእነአቶ መለስ እጅ እንጂ በወህኒ ቤቱ አሊያም በፍርድ ቤቱ እጅ ነው የሚል አንዳች ብዥታ ኑሮኝ አያውቅም፡፡
ስለዚህ ከወህኒ ቤቱ አስተዳዳሪዎችም ሆነ ከፖሊሶች ጋር ከወንድማማችነትና ከአክብሮት ውጭ ሌላ የተከልኩት መንገድ ኑሮ አያውቅም፡፡ ደብዳቢዬ አስተዳዳሪው ቢሮ ሲመላለሱ ግን ምን እየተነጋገሩ እንደነበር ለማሽተት ብዙ አስቸጋሪ አልነበረም፡፡ የግድያ ሙከራውም ቢሆን አሳሪዎቼ የወህኒ ቤት አስተዳደሩን በመጠቀም ሊወስዱብኝ ያሰቡት እርምጃ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስለዚህም ከዚህ በታች የማነሳቸው ነጥቦች የግድያ ሙከራው በአሳሪዎቼ እንጅ በደብዳቢዬ የግል ፍላጐት ላለመፈፀሙ አስረጅ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡
1ኛ. ከሌሎች እስረኞች ተነጥዬ ከመጀመሪያውም እንዲህ አይነት ቦታ የገባሁት ይኽን መሰል እርምጃ ለመውሰድ ያመች ዘንድ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
2ኛ. እስከአሁን በነበረው የወህኒ ቤቱ አሰራር በእስረኛ ላይ የግድያ ሙከራ የሚያደርግ ቀርቶ ግጭት እንኳን ቢፈጥር አስተዳደሩ በአፋጣኝ በካቴና አስሮ ማማ ስር በማስገባት ቅጣት ይፈፅም ነበር፡፡ እኔን ለመግደል የሞከሩት እስረኛ ግን ሊቀጡ ቀርቶ ከሶስት ሳምንታት በላይ አንዳች ተግሳፅ እንኳን ሳይደርስባቸው እኛ ካለንበት በእጅጉ በተሻለ ቦታ ታስረው ይገኛሉ፡፡
3ኛ. ችግሩ እንደተፈጠረ ተጠርተው የመጡት የአስተዳደሩ አባላት ለአቶ ይባስ የጀግና አቀባበል ነበር ያደረጉላቸው ማለት ይቻላል፡፡ ‹‹አንተ ፖሊስ ወይንም የአስተዳደሩ አባል ባለመሆን ቀድሞውንም መንጠቅ አልነበረብህም፣ አሁንም በአስቸኳይ መልስ›› ማለት ሲገባቸው፣ ሰነዶቹን በፈገግታ ተቀብለው ሰውየውን ወደ ተሻለ ማረፊያ ቤት እኔን ደግሞ ባለሁበት ቅጣት ቤት እንድቀጥል አድርገዋል፡፡
4ኛ. ተጐድቼ ወደ ህክምና እንዲወስዱኝ በምጠይቅበት ሰዓትም ቢሮ አስገብተው ወረቀቱን የነጠቁኝ የእርሃብ አድማ ለማድረግ ሃሳብ ላይ መሆኔን ስለደረሱብኝ መሆኑንና የወህኒ ቤቱ አስተዳደርም ይኽኑ እንደሚጠረጥሩ ገለፁልኝ፡፡ በእኔ በኩል የሚባለው ነገር ፍፁም ሀሰትና ነገሩን ለማድበስበስ ተብሎ የቀረበ መሆኑን ገልጬ የግድያ ሙከራው ባለቤቶች እነርሱ መሆናቸውንና ንብረቴን ከእነርሱ እንደምጠብቅ አስረዳሁ፡፡
5ኛ. በደረሰብኝ ከፍተኛ ድብደባ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ብሆንም ተገቢውን የህክምና ክትትል ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ሌሊትም ሆነ ቀን ከፍተኛ የስቃይ ስሜት ሲሰማኝ በጥበቃ ላይ የሚገኙ ፖሊሶችና በጤና ጣቢያው ያሉ የህክምና ባለሙያዎች የቻሉትን ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉም ግልፅ በሆነ የአቅም ውስንነት ምክንያት ጊዜያዊ ማስታገሻዎችን ከማድረግ ባለፈ ከስቃዬ ሊታደጉኝ አልቻሉም፡፡ ይህም ሁኔታ በውል እየታወቀ የተሻለ የህክምና ክትትል በድንገተኛ እንኳን እንዳገኝ አለመደረጉ ያልተፈለገው ህይወቴ ይቀጥል ዘንድ ባይፈለግ ነው የሚል ከፍተኛ ስጋት አለኝ፡፡
6ኛ. ክስ የምመሰርት ከሆነ በአስተዳደሪዎቹ ተጠይቄ ነበር፡፡ ግለሰቡ በራሳቸው ተነሳሽነት አደረጉት ብዬ እንደማላምን በመግለፅ ፈቃደኛ አለመሆኔን ገለፅኩ፡፡ አክለውም ምስክሮች እንዳሉኝ ጠይቀው እነርሱ የራሳቸውን እርምጃ እንደሚወስዱ ገልፀው ቢሄዱም፡፡ በጉዳዩ ላይ እዚህ ግባ የሚባል ነገር ሳያደርጉ አያሌ ቀናት አልፈዋል፡፡ ይኽም የእውነት በግለሰቡ የተፈፀመ ቢሆን ኑሮ ጉዳዩ በዚህ ሁኔታ በቸልተኝነት እንደማይያዝ መረዳት አያስቸግርም፡፡
7ኛ. የወህኒ ቤቱ አስተዳደሮች የተወሰዱብኝን ሰነዶች ሙሉ በሙሉ እንዲመልሱልኝ ብጠይቅም ቀደም ብለው በጋራ እያየን የሚመለስ ካለ እንደሚመለስ የማይመለስም ካለ ለምን እንደማይመለስልኝ እንደሚገልፁልኝ ነግረውኝ ነበር፡፡ በአጋጣሚ አደጋው ከተፈጠረ በኋላ ተቀይረው የመጡት አስተዳደሮችም በተገለፀው መሰረት ይፈፅሙልኛል ብዬ ባስብም አልተሳካም፡፡ ከወሰዷቸው ሰነዶች የፍርድ ቤት የክስ ወረቀቴንና አንድ የተገነጠለ የደብተር ሽፋንና የተቀደዱ አንዳች ነገር ያልተፃፈባቸው የተቀደዱ ወረቀቶችን መለሱልኝ፡፡ ብዙ የደከምኩባቸው ፅሁፎች የውሃ ሽታ ሆኑ፡፡ በሁኔታው ማዘኔንና አዲስ እንደመሆናቸውም ከእነርሱ ጋር እሰጣ- ገባ ውስጥ መግባት እንደማልፈልግ ገልጬ መብቴን እየገፈፉ ግን በዝምታ እንደማልቀጥል ስገልፅላቸው ደብዳቢዬ ወረቀቶቹን ከሰጡአቸው እንደሚጠይቋቸው ካልመለሱላቸው ግን ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ገለፁልኝ፡፡ ‹‹ዶሮን ሲያታልሏት…›› የሚባለው በእንዲህ ያለ ጊዜ ነው፡፡ አንድ እስረኛ ከወህኒ ቤቱ አቅም በላይ እንደሆነ ማን ሊያምን ይችላል? ሰነዱንስ ቀደም ብለው ሊመልሱልኝ፣ የማይመለስም ካለ ለምን የሚለውን እንደሚያስረዱኝ ተገልፆልኝ እንደነበር ዘንግተውት ወይንስ…?
8ኛ. እየተፈፀመብኝ ያለው ግፍ ሳያንስና ጥዋትና ማታ ከሞት ጋር ግብግብ በገጠምኩበት ሁኔታ የወህኒ ቤቱ አስተዳደር በጋዜጣዎ ላይ ነገሩን ተራ ጉዳይ ተራ ግጭት አስመስሎ ለማቅረብ መሞከሩ ሀዘኔን አክብዶታል፡፡ ስቃዬንም አብዝቶታል፡፡ ከፍ ሲል እንኳ ለመከላከል እጄን እንዳላነሳው በሚገባ እየተረዱ ጉዳዩን የግድያ ሙከራ ሳይሆን ግጭት ለማስመሰል መሞከራቸው ከበደል ሁሉ የከፋ በደል ነው፡፡ በሰውነት ከተቸረኝ ክብር ውጭ የምጠቅሰው ሌላ ክብር የለኝም፡፡ ነገር ግን የወህኒ ቤቱ እርምጃ እኔን ተራ አምባጓሮ ፈጣሪ በማስመሰል ለማብጠልጠል የታቀደ እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡ ለመሆኑ ምንስ የሀሳብ ልዩነት ቢኖረኝ ሰውነቴን ይጠራጠራሉ? ወይንስ ኢትዮጵያዊነቴን? ከእስር አያያዜ ጀምሮ ከፍ ብዬ እስከ 7ኛ ተራ ቁጥር የገለፅኳቸው በደሎች ሳያንሱ እኔን እንደ ምግባረ-ብልሹ አድርገው ለአንባቢ ለማቅረብ ይመቻቸው ዘንድ ‹‹ጉዳዩ ተጣርቶ ጥፋተኛው ተለይቶ እርምጃ እንወስዳለን፡፡›› የሚል ምላሽ መስጠታቸው እውነት ልጅ ያወጣላቸው ይሆን? ወይንስ ክብር ያጐናፅፋቸው ይሆን? በአጠቃላይ ወህኒ ቤቱ በጉዳዩ ዙሪያ እያሳየ ያለው ነገር በገሃድ የሚያሳየው የጉዳዩ ባለቤት አሳሪዎቼ መሆናቸውንና ያንንም ለመሸፈን ሲል ከፍ ያለ ውጥረት ውስጥ መግባቱን ነው፡፡ ነገር ግን ይኼን መሰሉ ተግባር ለተቋም ግንባታም ሆነ ለወንድማማችነት መልካም ሁኔታዎችን ሲፈጥር አይታየኝም፡፡ የፓርቲዬ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህም ዓላማም፣ እንዲህ አይነት የሸፍጥና የመጠፋፋት አዙሪት ቆሞ ፍትህ፣ ዴሞክራሲ፣ ነፃነትና ወንድማማችነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ማየት ነው፡፡
ክቡርነትዎ እንዲረዱልኝ የምፈልገው ይኽንን የመሰለ ደብዳቤ ስፅፍ ማንንም ለመበቀል ወይንም ለማንቋሸሽ ሳይሆን እውነቱ ፍንትው ብሎ እንዲወጣ፣ ወህኒ ቤቱም እንደተቋም ህዝብ የሚያምነውና የሚያከብረው እንዲሆን ከማሰብና ጉዳቴንና ስቃዬንም ህዝብ እንዲያውቅልኝ ከመሻት የተነሳ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ባነገብኩት እውነት ደስተኛ ነኝ፡፡ ለዚህ እውነት ደግሞ ግራና ቀኛቸውን ለይተው ከማያውቁ ልጆቼ ተለይቼ ዘመኔን በሙሉ በውርደት ለመጨረስ ብቻ ሳይሆን፣ ለመሞትም ዝግጁ መሆኔን አሳዳጆቼም እንዲያውቁት እወዳለሁ፡፡
መቼን እኔ ባለሁበት ሁኔታ ያለ ሰው ነገር ቢያበዛ ቅር እንደማይሰኙ በተመተማመኔ ነገሬን ዘለግ ማድረጌን ይረዱልኝ፡፡
ስለትብብርዎ በቅድሚያ እያመሰገንኩ እውነቱን የማሳወቅ ጥረትዎ እንዲሳካ እምኛለሁ!!
አክባሪዎ!
(የማይነበብ ፊርማ)
አንዱዓለም አራጌ
የህሊና እስረኛ
የካቲት 25/2004 ዓ.ም.
ከቃሊቲ ወህኒ ቤት