Saturday 14 June 2014

በሳጥናኤል መንገድ ነጎዱ!

በሳጥናኤል መንገድ ነጎዱ!

ሕዝበ ክርስቲያን በጰራቅሊጦስ መንገድ ሲሄዱ፤ፓትርያርክ፤ሊቃነ ጳጳሳት፤መነኮሳትና ቀሳውስት በሳጥናኤል መንገድ ነጎዱ።




ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ
nigatuasteraye@gmail.com
ሰኔ ፳፻፮ ዓ.ም.

ማሳሰቢያ፦
የዚህች ክታብ አላማ ነገረ መለኮት ለማስተማር አይደለም። ሆኖም አብዛኛዎቻችን ኢትዮጵያውያን እምነታችሁ ምንድነው ስንባል መልሳችን ክርስቲያን ነና! ነው። እንዲያውም ብዙዎቻችን በኩራት በልበ ሙሉነት ከዘመኑ ክርስትና በፊት በነበረችው በኦርቶዶክስ ተጠምቄ ያደኩ ነኝ እንላለን። በተለይም በአውደ ምህረት ላይ ቆመን እግዚአብሄር ይባርክ ለማለት ተክነናል የምንል ሰዎች፤ ስንጠየቅ ለክርስትናየ ደግሞ ምን ጥያቄ አለው! እንዲውም ባይደንቅህ ልብሴን ተመልከት! የጨበጥኩትንም መስቀል እይ! በደረቴ ያንዘረገኳቸውን ክርስቲያን ነክ ጌጣ ጌጦች ተመልከት የዚህች ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ቄስ፤ መነኩሴ፤ (ጉዳችን አያልቅምና በአቡነ ጳዎሎስ ዘመን የተለቀቀ ቆሞስ)፤ ጳጳስ ነኛ! እንላለን። በእምነት በታሪክ በባህል መኩራት ተገቢ ነገር ነው። የሚኮሩበትን ሳይጠበቁ መኩራራት ብቻ ግን ዝናብ የለሽ ባዶ ደመና መሆን ነው።
መጠበቅ መቻላችን የሚመዘንበት ጰራቅሊጦስ ነው። በሱ እየተመዘን ፤ እሱ ከሚጠላቸው ከዝሙት፤ ከሀሰት፤ ከስርቆት፤ ከስስት፤ ከክህደት ተጠብቀና፤ ህዝቡንም፤ ጰራቅሊጦስ ከማይወዳቸው ነገሮች ሁሉ ራቁ እያልን፤ ራሳችንን ምሳሌ አድርገን እናስተምራለን። እግዚአብሄርን እንቀድሳለን፤ ህዝቡንም እናስቀድሳለን ቄስ፤ ቆሞስ ( መረን የተለቀቀ)፤ ጳጳስ ነን የምንል በወያ ዘመን ያለን ካህናት፤ ከምን ላይ እንዳለን ማሳየት እችል ዘንድ፤ የጰራቅሊጦስን ሚዛንነት ለመግለጽ ወደ ነገረ መለኮቱ ገባ ብየ ለመውጣት እገደዳለሁና ለትእግስታችሁ ይቅርታ።

መግቢያ


ለዚህች ጦማር መፍለቅ ምክንያት የሆነው ባለፈው እሁድ ሰኔ ፩ ቀን ፳፻፮ ዓ/ ም ያከብረነው ጰራቅሊጦስ የሚባለው ዓመታዊ በዓል ነው። በዚህች ቀን ጰራቅሊጦስ (እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ) ቤተ ክርስቲያንን በምድር ላይ የመሰረተበትን ዓላማና ተግባር እናጤናለን። 

ዓላማው፤ ሐዋርያት ከክርስቶስ ጋራ በቆዩበት ጊዜ የተማሩትንና የሰሙትን እንዳይረሱ፤ በጥበብ በማስተዋል በቅድስናና በድፍረት ሰውን ከሀሰት ወደ እውነት፤ ከክህደት ወደ እምነት፤ ከበደል ወደ ደግነት፤ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፤ ከግለኝነት ወደ ህዝባዊነት፤ በጠቅላላው ከዲያብሎስ ወደ ክርስቶስ ለማምጣት ነው። እነዚህን ነገሮች በተግባር የሚያውሉት ሰዎች ክርስቲያኖች ተባሉ። ከክርስቲያኖች መካከል በእውቀታቸው፤ በችሎታቸውና በመንፈሳዊነታቸው ተመርጠው በአመራር ላይ ያሉ ደግሞ ጳጳሳትና ቀሳውስት ተባሉ። የነዚህ ሁሉ ክምችት ቤተ ክርስቲያን ተባለች። ይህች ቤተ ክርስቲያን በምድር ያለች “ትምጣ” እያልን የምንመኛትን በሰማይ ያለችውን መለኮታዊት መንግሥት የምታንጸባርቅ ምሳሌና ምልክት የሆነች ድርጅት ናት።

ይህችን ድርጅት በመጀመሪያ ተቀበሉት ተብለው ከሚነገርላቸው ህዝቦች መካከል ኢትዮጵያውያን አሉበት። በዚህም ምክንያት ያብነት መምህራን ኢትዮጵያውያንና የሚኑሩባትን ምድር እንደሚከተለው ይገልጿቸዋል። ኢትዮጵያውያን ፊደሎች ናቸው። ኢትዮጵያ ደግሞ የፊደል ገበታቸው ናት። ኢትዮጵያውያን ታቦቶች ናቸው። ኢትዮጵያውያን የሚኖሩባት ምድር ለኢትዮጵያውያን መንበራቸው ናት።ከፊደል ገበታ ያልተሳተፈ መጽሐፍ ማንበብ እንደማይችል፤ ከኢትዮጵያዊነት  ስሜት መንፈስ ያልተሳተፈ ኢትዮጵያን አያውቃትም። በኢትዮጵያዊነት ያልተቀረጸም፤ ኢትዮጵያን መንበሩ ሊያደርጋት አይችልም ይላሉ።  

 ስለ በዓለ ጰራቅሊጦስ አጭር መግለጫ ከሰጠሁ በኋላ፡ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውን የፊደል ገበታቸው፤ የተቀመጡባት መንበራቸው እንደሆነችና፤ ቤተ ክርስቲያን በመሬት ከተመሰረተችባቸው አገሮች አንዷ እንደሆነች ለመግለጽ እሞክርና፤ በዘመናችን በተለይም በወያኔ ዘመን ያየናቸውን መንፈሳውያን መሪዎች በየትኛው መንገድ ላይ እንዳሉ በንጽጽር ለማሳየት፤ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት አንቀጾች ይህችን ጦማር አቅርቤያታለሁ።

፩ኛ፦ጰራቅሊጦስ
፪ኛ፦ እነማን ነበሩ
.የጻድቃን ቀጠሮ
.ሰዎች የመጡባቸው አገሮች        
ሐ. ማስረጃዎች
፫ኛ፦የጰራቅሊጦስ ሥራ የተገለጸባቸው ስድስት ጥቅሶች
፬ኛ ንጽጽር
፭ኛ፦የዘመናችን መሪዎች የውድድር መስክ
ክፍል ፩ ቅድመ ወያኔ
ክፍል ፪ ዘመነ ወያኔ
ሀ. በሲኖዶስ መካከል                                   
ለ. በለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን
. በዋሸንግተን ርእሰ አድባራት ቤተ ክርስቲያን                   
መ. በቨርጅንያ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን
ሠ. በሚኒሶታ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን           
. በሱዳን የታየው የጰራቅሊጦስ ስራ

ኛ፦ጰራቅሊጦስ ምንድነው? ማነው?


ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት እነ ቅዱስ ቴዎፍሎስ “ኢሀሎ አብ ግሙራ ዘመነ እምነ አዝማን ዘእንበለ ወልድ፤ ወኢወልድ ዘእንበለ መንፈስ ቅዱስ። አላ ህልዋን በኩሉ ዘመን እንበለ ጥንት ወተፍጻሜት በ፫ቱ አካላት ፍጹማነ ገጽ ወመልክእ እንዘ ኢይትዌለጡ፡ ወኢይትፋለሱ”(ሃይ ፷፱፡፭) እያሉ እን ገለጹት፦

አብ ያለ ወልድና ያለ መንፈስ ቅዱስ፤ ወልድም ያለ አብና ያለ መንፈስ ቅዱስ፤ መንፈስ ቅዱስም ያለ አብና ያለ ወልድ ብቻውን የነበረበት ቅጽበት የለም። አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በገጽና በአካል በስምና በግብር ሶስት ሲሆኑ፤ በመለኮት፤ በባህርይ፤ በስልጣንና በፈቃድ አንድ እግዚአብሔር ነው። ሱኑትዩ የተባለው ሊቅም “ወሶበሂ ንቤ መለኮት፤ አው እግዚአብሔር፤ ንብል በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ህላዌ ዘኢተፈጥረ ኢሥግው ዘኢያስተርኢ ወዘኢይትገመር ዘአልቦቱ ጥንት ወኢተፍጻሚት (ሃይ አበው ም ፻፲፡፰) ” አለ። ማለትም፦መለኮት ወይም እግዚአብሄር ስንል ስለ ሶስቱም ማለታችን ነው። ጰራቅሊጦስ (መንፈስ ቅዱስ) በተለየ አካሉ ሶስትነቱን ሳይለቅና ሳይፋለስ በመለኮቱ እግዚአብሔር (አምላክ) ነው። ክርስቶስም በተለየ አካሉ ከሶስቱ አንዱ ነው። አዮክንድዮስ የተባለው ሊቅም“ኢያምጽአ ሥጋ ምስሌሁ እምሰማያት ወመለኮቱሂ ኢኮነ እምድር አላ አምላክ ውእቱ(ሃ አ ፵፬፡፪” እንዳለው፤ ቃል የለበሰውን ሥጋ ከሰማይ አላወረደውም። እኛን ለማዳን ሰማያዊ አምላክነቱን ከምድራዊ ሰውነታችን ጋራ አዋሀደው። በዚህ መልክ  አምልኮታችንን “እግዚአብሔር አብ፤ እግዚአብሔር ወልድ፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተወከፍ መስዋዕተነ” እያልን በማምለክ፤ በቅዳሴያችን (በአምልኮታችን) እንገልጸዋለን።

ከሥላሴ አንዱ እግዚአብሄር ወልድ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ማለቴ ነው፤ በኛ ሥጋ የሰራውን እቅድ ከፈጽመ በኋላ “ወደ ላከኝ እሄዳለሁ” ብሎ ለሐዋርያት ሲነግራቸው “ሀዘን በልባቸው ሞላ”። “እኔ ባልሄድ ጰራቅሊጦስ ወደናንተ አይመጣምና ብሄድ ይሻላችኋል”( ዮሐን ፲፮፡፯) እያለ አጽናናቸው። ከሐዋርያትና እነሱም ምድራዊ አገልግሎታቸውን ፈጽመው ካለፉ በኋላ፤ እስከ ዓለም ፍጻሜ ከሚነሱት ክርስቲያኖች ጋራ በጰራቅሊጦስ በኩል እንዴት እንደሚሰራ ነገራቸው። እሱን ወክሎ ከሐዋርያት ጋራ ከሚሰራው ከጰራቅሊጦስ ጋራ መገናኘት ስላለባቸው እንዴት እንደሚያገኙት “አባቴ የሰጠውን ተስፋ (ጰራቅሊጦስ) ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ” ሉቃ ፳፬፡፵፱) ብሎ ነገራቸው። በሌላ በኩል ደግሞ፤ በኦሪት እምነት ውስጥ የነበሩትን ሰዎች ከሚኖሩበት አጎራባች አገሮች ሰበሰባቸው። ይህች ቀን የማይተዋወቁ ያልተቀጣጠሩ ጻድቃን የተገናኙባት ቀን ነበረች።
 በዚህች ቀን የሰው ልጅ ሊገልጸው በማይችለው ትንግርት ጰራቅሊጦስ በሐዋርያት ላይ በአምሳለ እሳት ፈሰሰ (የሐዋ ፪፡፩-፲፯)። በ፴፫ መተ ምሕረት ማለት ነው። ቤተ ክርስቲያን ተመሰረተች። በዚህች ቀን ሐዋርያትና ከተለያዩ አገሮች ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች ከጰራቅሊጦስ ጋራ ለመስራት ኃላፊነቱን ተረከቡ። የተረከቡትን የስራውን ጠባይ ከመግለጼ በፊት፤ ከሐዋርያት ጋራ የነበሩትን ሰዎች ከየት እንደነበሩ፤ እኛን ኢትዮጵያኖችንም ይጨምራልና መግለጽ ተገቢ ይመስለኛል።

፪ኛ፦ ክርስቲያንን በምድር ላይ ለመመስራት ጰራቅሊጦስ በተከሰተበት ቦታና ሰዓት እነማን ነበሩ

ቤተ ክርስቲያን በተመሰረተችበት ሰአትና ቦታ እኛም ነበርንበት። ኢትዮጵያውን ከጥንታውያን አገሮች አንዷ ከሚያደርጓት ታሪካውያን ምስክሮች አንዱ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ነው። አገራችን ኢትዮጵያ በዘመናችን ታሪኳን በሚደመሰስ፤ ህልውናዋን በሚፈታተን ቡድን እጅ ላይ ስለወደቀች፤ ጥንታዊነቷን የሚገልጹ አጋጣሚዎች ሲከሰቱ፤ የኢትዮጵያን ጥንታዊነት ሳይገልጹ ማለፍ ከዘመቱባት ጠላቶች ጋራ መተባበር ይመስለኛል።

ክርስቶስ በተነሳ በ፶ኛዋ ቀን የተከሰተው አስደናቂ ነገር ታሪካዊ አመጣጥ አለው። በዚያ ቦታ የተሰበሰቡት በኦሪቱ ስርዓተ አምልኮ የነበሩ ሰዎች ናቸው። በዚህች ቀን እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠውን ቃል ኪዳን ይዘው በዓለም ዙሪያ የተበተኑት ሁሉ ከተበተኑበት በኢየሩሳሌም በየዓመቱ እየተሰበሰቡ እንዲያከብሩት ራሱ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት አዝዞ ነበር (ዘዳ ፲፪፡፭)። በዚህ ባህላዊ እምነትና ትምህርት ውስጥ ያሉ ሁሉ በትእዛዙ መሠረት ከያሉበት አገር ተሰበሰቡ።ሐዋርያትም “አባቴ የሰጠውን ተስፋ (ጰራቅሊጦስ) ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ” ሉቃ ፳፬፡፵፱) ተብለው በታዘዙት መሰረት፤ ባንድ ቤት ተሰብስበው ቆዩ።

ክርስቶስ በተነሳ በ፶ኛው፤ባረገ ባ፲ኛው ቀን ሀዋርያት በተሰበሰቡበት ቤት አስደናቂ ተአምር ተከሰተ። ይህች ቀን ይህች ቅጽበት “ሚመጠን ግርምት ዛቲ እለት፡ወዕጽብት ዛቲ ሰአት፡ እነተ ባቲ ይወርድ መንፈስ ቅዱስ እመልዕልተ ሰማያት” እየተባለች በቅዳሴያችን የምትደነቅ ናት። ይህች ቀን የጻድቃን ቀጠሮ የተከናወነባት የሰው ቋንቋ ሊገልጸው በማይችለው ትንግርት በሐዋርያት ላይ ጰራቅሊጦስ በአምሳለ እሳት የፈሰሰባት ቀናት (የሐዋ ፪፡፩-፲፯) ይህችም ቀን የጻድቃን ቀጠሮ (ቤተ ክርስቲያን) የተከሰተችባት አሰደናቂ ቀን ነበረች።

ሀ. የጻድቃን ቀጠሮ

የጻድቃን ቀጠሮ የተባለችበት ምክንያት፤ ጻድቃን ሳይቀጣጠሩ ይገናኛሉ። በተገናኙባት ቅጽበት፤ ተቀጣጥረው ሊሰሩት ካሰቡት በላይ እጅግ  የላቀና ያልተጠበቀ ስራ ይፈጽማሉ። አባቶቻችን እንዲህ የመሰለ አስደናቂ ስራ የምትከናወንበትን ቅስበት፤ የጻድቃን ቀጠሮ ይሉታል። ይህች ቃል ከዚህ ታሪካዊ ትንግርት እንደሰረጸች ሊቃውንት መምህሮቻችን አስተምረውናል።

በሐዋርያት ላይ የወረደውን የጰራቅሊጦስኃይል አይተው፡ የተነገረውን ሰምተው ወደሀገራቸው ከተመለሱት ሰዎች መካከል በዚህች በጻድቃን ቀጠሮ እኛ ኢትዮጵያንም ነበርንባት። አባቶች ይህን ሲሉ በብሄራዊነት ኩራት ተጽእኖ የተናገሩት እንዳልሆነ ከሚደግፏቸው ብዙ ማስረጃዎች ጥቂቶችን እንመልከት።

ለ. በዚህ ሰዓትና ቦታ ኢት፡ዮጵያዉያን መኖራችንን የሚደግፉ ማስረጃዎች

ባህሉን ለማድረስ ከተለያዩ አገሮች የመጡትንና፤ ከኢየሩሳሌም ሳይወጡ ባንድ ቤት ተስብስበው የነበሩትን ሐዋርያት ስቦ ያገናኘ ጰራቅሊጦስ (divine magnetic power) ነበር። ጰራቅሊጦስ፤ ሊሰሩት ሊያደርጉት የሚገባቸውን በራሳቸው ቋንቋ በልባቸው ቀርጾ በህሊናቸው አስርጾ ድፍረትን፥ ጀግንነትን፡ እውቀትንና ዕዉነትን አስታጥቆ ወደየ መጡበት አገሮቻቸው ከመለሳቸው ሰዎች መካከል እኛም ነበርንበት።

ቅዱስ ሉቃስ በዚያች ቅጽበት ሰዎች ከየት እንደመጡ በገለጸበት በ (ሐዋ ፪፡፱᎗፲) ላይ፤ ሰፊዋን ኢትዮጵያን ባይጠቅስም፡ በበዓሉ ተገኝቶ ሊሰግድ የሄደው ኢትዮጵያዊ ወደ አገሩ ለመመለስ መንገድ ጀምሮ ሳለ፤ “መላከ እግዚአብሄር ቅዱስ ፊልጶስን ተነስተህ ወደ ጋዛ በሚወስደው መንገድ ሂድ” ብሎ ጃንደራበው ሳያመልጠው ተከታትሎ ደርሶበት አስጨብጦ ወደ መጣበት እንዲልከው አዘዘው። ትእዛዙን ተቀብሎ በጃንደረባነት የተገለጸውን ኢትዮጵያውን አግኝቶ፤ አጥምቆ እንደሸኘው በሌላ አንቀጽ፤ “ጃንደረባው ደስ እያለው ወደ አገሩ ለመመለስ የጀመረውን ጉዞ ቀጠለ”(የሐዋ ፰፡ ፴፱) ሲል ገልጾታል። ይህ ኢትዮጵያዊ በዚህች በጻድቃን ቀጠሮ ተገኝቶ፤ ፊልጶስ ካጠመቀው በኋላ “ደስ ብሎት መንገዱን ሄደ”፴፱” ይላል። ቅዱስ ሉቃስ ጃንደረባው ተመልሶ የገባበትን መንደር በታሪኩ ያልገለጸበት ምክንያት፤ “መንደሮች ተለዋዋጮች ናቸው። ቀደም ብለው የነበሩት መንደሮች በወራሪወች ይፈርሳሉ። ነዋሪዎች ይፈልሳሉ። ያልነበሩ ወራሪዎች ይሰፍራሉ። ይሁን እንጅ በጃንደረባው የተቀረጸችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በማይፈልስ፤ በማይፈርስ፤ በማይቀየረው ኢትዮጵያዊነት ላይ መመስረቷን ያሳያል” ይላሉ አባቶች።

ይሁን እንጅ በመልክአ ምድር አገላለጽ፤ ጃንደረባው ከየት መንደር ወረዳና አውራጃ እንደሆነ ቅዱስ ሉቃስ ባይገለጸውምለመረዳት የሚጥሩ ሊቃውንት እንደሚሉት፤ ለባህላዊው በዓል ወደ ኢየሩሳሌልም በመሄዱ የኦሪት እምነት ተከታይ በመሆኑንና፤ የኢትዮጵያ ንግሥት ጃንደረባነቱን በመግለጹ ዜግነቱን ጠቁሟል። በዚያ ዘመን ይዋሰኑ የነበሩት አገሮች የተገለጹባቸውን መጻፍት ስንመረምር ስለ ኢትዮጵያዊነቱ ከግምትነት አልፈን እርግጠኞች ያደርጉናል” ይላሉ።

ለምሳሌ፡- Runoko Rashidi የተባሉ የታሪክ ሊቅ “Meluhha’s precise geographical location has frequently been attached by modern scholars to either the African Ethiopia, or the Indus valley (Harappan ) region of Pakistan and western India. Both regions were lands of black men, but Harappan, whose civilization was larger in area than ancient Mesopotamia and Egypt combined, was much closer to Summer than African Ethiopia” (African Presence in Early Asia, Page 165). ብለዋል፡፡ ማለትም፡- እነዚህ አገሮች የጥቁር አገሮች ሲሆኑ Harappan ይባል የነበረው አገር በስልጣኔ ዳብሮ የቅርብ ግንኙነት ከነበራቸው አገሮች ከመስፖታምያና ከግብጽ ይልቅ የሰፋ ነበር፡፡ ከአፍሪካዊት ኢትዮጵያ ይልቅ Sumer ለምትባለው ቦታም በጣም ቅርብ ነበር፡፡ የMeluhha ግልጽ መልክአ ምድር ከአፍሪቃዊት ኢትዮጵያ ወይም ከህንድ ሸለቆ (Harappan) እና Pakistan አውራጃ እና ምዕራባዊው ህንድ ጋራ ፈጣን የሆነ ግንኙነት እንደነበረ ዘመናውያን ሊቃውንት ይናገራሉ።” ይህ አገላለጽ በዚያ ዘመን የኢትዮጵያን ስፋት የሚገልጽ ነው።” ብለዋል።

ታሪክ መዝጋቢው ወንጌላዊው ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፪ ላይ ብዙወቹን ወረዳዎችና አውራጃወች ሲጠቅስ ታላቋን ኢትዮጵያን ባይጠቀስም፤ ግልጽ በሆኑ ምክንያቶች ኢትዮጵያውያን በዚህ ታላቅ በዓል ላይ አልነበሩም ማለት አይቻልም። በተለይም በምዕራፍ ፰ ላይ የተጠቀሰውን ጃንደረባ ወደ ኢየሩሳሌም የሄደው እምነቱ ከሚያዝዘው ከበዓለ ፶ው ባህላዊ ክብር ለመሳተፍ ነበር። ከዚህም ጋር የጃንደራባው አድራሻ ኢትዮጵያ ላይ ለመሆኑ፤ እሱን ወደ ኢየሩሳሌም የጎተተውን እምነት እስካሁን ያለቀቁ ኢትዮጵያውያን ቤተ እስራኤሎች መሆናቸው ነው። (በዘመናችን ወደ ኢየሩሳሌም የሄዱት እምነቱን አንለቅም ብለው ወደ ክርስትና ባለመምጣቸው ብቻ ከኛ ተለዩ እንጅ፤ፍጹም ኢትዮጵያውያን ናቸው።  ከቀረነው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጋራ  በሥጋ በደም አንድ ናቸ) የጃንደረባን ትውፊት ጠብቀው እስክ ደርግ መንግስት ድረስ በነገታት ዘመን የነበሩት ጃንደረቦችም ተጨማሪ ማስረጃዎች ናቸው።

የቀሩት የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች፤ በኦሪቱ ዘመን የተጀምረውን ልማድ ወደ ክርስቲያናዊ ስሜት በመቀየር እስካሁን ድረስ በየአመቱ ወደ ኢየሩሳሌም የሚያደርጉት ጉዞም ተጨምሮ ሲገመት፤ኢትዮጵያውያን በዚያ ቀን በበዓሉ ላይ አልነበሩም ከሚያሰኘው ሩቅ ግምት ይልቅ፥ ነበሩ የሚለው አባባል የሚቀርብ ይሆናል።” ይላሉ።

በዚያ ቀን በኢየሩሳሌም የተሰበሰቡት በሥልጣኔና በስፋት ድንበር ከሚያዋስናቸው ከታላላቅ አገሮች ሥር የነበሩ ትንንሽ ከተማዎች ነበሩ። “ሉቃስ ታላላቅ አገሮች አንዳልጠቀሰ፤ታላቋን ኢትዮጵያን በዚህ ምዕራፍ ከጠቀሳቸው ትናንሽ አገሮች ጋራ አልጠቀሳትም፤ በማለት ብቻ ይህን ሁሉ መረጃ መጣል ታሪካዊ ግድፈት መፍጠር ነው” ይላሉ

ከሁለት ሽ አመታት በፊት የነበረችውን የኢትዮጵያን ስፋትና ጥበት እንተወውና፤ በቅርቡ የጅቡቲንና የኤርትራን ከታላቋ ኢትዮጵያ መለየት፤ እንደገና ደግሞ ሌላውም ኢትዮጵያ የሚለውን ስም አንፈልግም እንገንጠል የሚለውን ስንመለከት Paul Connerton የተባሉ ሰው “We experience our present world in a context which is causally connected with the past events, and hence with reference to events and objects which are not experiencing when we are experiencing the past” (pag 2) እንዳሉት፤ በዚያ ዘመን የነበረውን ኢትዮጵያዊ መልክአ ምድራችንን ስፋት እንድንገምት ይረዳናል።

መገመት ብቻ ሳይሆን፤ አገራችን ኢትዮጵያ እንደ እነ አቶ መለሰ ያሉ ልበ ጎደሎዎች የጠላት አሽከሮች ሲፈጠሩባት እንደ ጨረቃ የምትሸረ፥ ልበ ሙሉ መሪዎች ሲፈጠሩባት ደግሞ እንደ ጨረቃ የምትሞላ አገር እንደሆነች መረዳት ያስችለናል። ይህችን አንቀጽ ለማጠቀለል የኢትዮጵያ ኦርቶቶድክስ ቤተ ክርስቲያን በጃንደረባው አማካይነት የበቀለችባት ኢትዮጵያ ከጥንታውያን አገሮች አንዷ እንደነበረች የሚያሳየውን አባባል እዚህ ላይ ገትቼ፤ ኢትዮጵያዊት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከጰራቅሊጦስ ጋራ ልትሰራው የተረከበችውን አደራ ከዚህ በታች እገልጻለሁ።

፫ኛ:-የኢትዮጵ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እንድትፈጽማቸው ከጰራቅሊጦስ የተረከበቻቸው አደራዎች።


ጰራቅሊጦስ ወደ ሐዋርያት የመጣበት ምክንያት ክርስቶስ በአካል ሲለያቸው፤ ክርስቶስን ተክቶ ከሐዋርያት ጋራ ለመስራት ነው። ከ፩ እስከ ፮ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ቁም ነገሮች ከሞላ ጎደል በክርስቲያኖች፣ በተለይም በምሳሌነት በተሰለፉ በቀሳውስትና በጳጳሳት ላይ ጎልተው መታየትና መንጸባረቅ አለባቸው። እነዚህም ቁም ነገሮች በዮሐንስና በማቴዎስ ወንጌል ላይ የሰፈሩት ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ናቸው

፩ኛ፦ዮሐ ፲፡፳፯-፴

በዚህ ቁጥር የተካተቱት ሀሳቦች ክርስቲያኖች በተለይም የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አስተማሪዎች ነን የምንል ሰዎች በውስጣችን ይዘን ልንመራባቸው የሚገቡ ክርስቶስ የሰጣቸው መመሪያዎች ናቸው።
ሀ. ድምጼን ይሰማሉ                 ለ. እኔም አውቃቸዋለሁ
ሐ. እነሱም ያውቁኛል                መ. የዘላለም ህይወት እሰጣቸዋለሁ
ረ. ለዘላለም አይጠፉም               ሠ. ከእጄ ማንም አይነጥቃቸውም
         
አስተውል አንባቢ! ለመሆኑ በዚህ ዘመን በአውደ ምህረት ላይ ቆመን ህዝቡን እንምራህ እናስተምርህ የምንል ብዙዎቻችን ቀሳውስት ሰባክያን መነኮሳትና ጳጳሳት ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን፤ የክርስቶስን ድምጽ እንሰማለን? ክርስቶስን እናውቃለን? ክርስቶስስ ያውቀናል? በእውነት የዘላለም ህይወት ልንቀበል ቀርቶ እንዳለስ እናውቃለን? ምእመናን፤ እንናተው መልሱ።

፪ኛ(ዮሐን ፲፬፡፳፮)
ሀ. ሁሉን ያስተምራችኋል፤           
ለ. የነገርኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል

ሁሉን ማለት የተሰወረውንና የተገለጸውን፤ የሚዳሰሰውንና የማይዳሰሰውን፤ ከመንፈስ ቅዱስ ትማራላችሁ። የነገርኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል፤ ማለትም፦ ባለፉት ቅዱሳን አድሮ የሰራውን፤ በታሪክ፤ በስንክሳር፤ በገድልና በተአምር የተከናወኑትን ትንግርቶች ሳይቀር ጰራቅሊጦስ ያሳስባቸዋል። ታዲያ አሁን የሚታየው እንደዚህ ነው? ከማነው እየተማርን ያለነው? የምናስበው ምንድነው? አሳሳቢያችንስ ማነው? አስተውል አንባቢ!
        ፫ኛ፦(ዮሐ ፰፡፵፬)
ሀ. እናንተ ካባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ።      ለ. ያባታችሁን ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ፤
ሐ. እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ።      መ. እውነትም በእርሱ የለም።
ሠ. በእውነት አልቆመም።                      ረ. ሀሰት ሲናገር ከራሱ ይናገራል
ሰ. ሀሰተኛ የሀሰት አባት ነውና

ከማን ጋራ ነው ያለነው? በሰማይ ያለህ አባታችን እያልን በከንፈራችን ከምንጠራው ከእግዚአብሔር ጋራ? ወይስ ከነፍሰ ገዳዩ ከሳጥናኤል? እውነትን ከማያውቃት፤ በእውነት ቆሞ ከማያውቀው፤ በሀሰት ተጸንሶ፤ በሀሰት አድጎ፤ በሀሰት ከሚሞተው ጋራ? ተግባራችን ይመስክር! “በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በአመጽ ድስ የሚላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ ሀሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሄር የስህተትን አሰራር ይልክባቸዋል”(፪ ተሰ ፪፡፲፪) የሚለው በኢሀደግ ዘመን በተሰለፍነው ካህናት ሰባኪዎች በተለይም በጳጳሳት ላይ ያነጻጸር አይመስልምን?

፬ኛ፦ዮሐ ፲፬፡ ፳፯

ሀ. ሰላሜን እተውላችኋለሁ፡                   ለ. ሰላሜን እሰጣችኋለሁ።
ሐ. እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም

ክርስቶስ የሰጠንና የተወልን ሰላም ከዓለም ከሚመነጭ ከሹመትና ከገንዘብ ጋራ የተገናኘ ሰላም አይደለም። ታዲያ በቤተ መቅደስ እጃችንን ዘርገትን ከሰማይ የወረደ መላክ መስለን “ሰላም ለኩልክሙ” የምንለው ከየት የተቀበልነውን፤ ማን የሰጠንን ሰላም፤ ለማን ለማቀበል ነው? “በኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ነግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዟችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ”(ዮሐ ፲፮፡፴፫) ብሎ ከተናገረው ከክርስቶ ስ የተቀበልነው ሰላም ነው? ከክርስቶስ የሰማነው የተቀበልነው ቢሆንማ ኖሮ፤ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለው፤ “ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፤ሰላምህ እንደወንዝ ጽድቅህም እንደ ባህር ሞገድ በሆነ ነበር (፵፯፡፲፰)” አንባቢ ተመልከት! አሁን የሚታየው የክርስቶስ ሰላም ነውን?

ኛ፦ዮሐን ፲፮፡፲፪-፲፭

ሀ. ወደ እውነት ይመራችኋል፤       ለ. ከኔ የሚሰማውን ይነግራችኋል፤
ሐ. ስለ ጽድቅ ዓለምን ይወቅሳል።   መ. ስለ ፍርድ ዓለምን ይወቅሳል።    

አንባቢ ታዘብ! ማነው መሪያችን? ክርስቶስ ወይስ ሳጥናኤል? የሚነገረንና የምንሰማው ምንድነው? ወዴትስ እየተመራን ነው? ። የምንናገረው ስለ ጽድቅ (እውነት) ወይስ ስለ ሀሰት?፤ ፍርድ አጣመው የርዱትን ፈራጆችን እየወቀስን ነው? ወይስ በተዛባ ፍርድ ዜጎችን ታራሚዎች እያለ በግፍ ከሚፈርደው ጋራ በመተባበር፤ እኛም ታራሚዎች እያልን እየፈረድንባቸው ነው? ቤተ ክርስቲያናችን “ወአንሂ ለኩላ ነፍስ ዕጽብት፤ወእለ እሡራን በመዋቅህት ወእለ ሀለው ውስተ ስደት ወጼዋዌ”(ቅዳሴ ፺፡፲፱)” ብላ በጸሎት መልክ እንድንናገረው የምታዝዘንን ነው? ማለትም፦ “የተጨነቁትን ሁሉ ከጭንቀታቸው አውጣቸው። በሰንሰለት የታሰሩትን በስደት ያሉትን ታደጋቸው” እንድንል የታዘዝነውን እየተናገርን ነው? ወይስ በምደረ ኢትዮጵያ የታሰረ እንደሌለ ለማስመሰል ወያ በማጧጧፍ ላይ ነኝ የሚለውን  ልማት  እኛም ተቀብለን እያስተጋባን ነው።  አስተውል አንባቢ! [ይህን በተመለከተ ከዚህ በፊት ያቀረብኩትን ጽሑፍ ሙሉእን ለምንባብ ከፈለጉ የሚቀጥለውን ሰንሰለት ይጫኑ  ልማታዊ ፓትርያርክ ]

፮ኛ፦ማቴ ፲፡፱።

ከዚህ በታች ከሀ እስከ ሸ ተራ ፊደል የተዘረዘሩት ከሥጋ የሚመነጩ ሥጋውያን ናቸውና ጰራቅሊጦስ አይቀበላቸውም። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው።
ሀ. ብር  መውደድ                    ለ. ወርቅ  መውደድ
ሐ. ናስ   መውደድ                            መ. ከረጢት መውደድ
. ሁለት እጀጠባብ መውደድ                  .  ጫማ  መውደድ
. ብትር መውደድ

እነዚህን የሚወድ ለሥጋው ቅድሚያ የሚሰጥ ሰው ነው። ለሥጋው ቅድሚያ የሚሰጥ ስው ለእግዚአብሔር ህግ አይታዘዝም። መገዛትም ይሳነዋል። ስለዚህ ስለ ሥጋቸው ቅድሚያ በመስጠት የሚያስቡ እግዚአብሄርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም። ከእግዚአብሔርጋራ የተጣሉ ናቸው(ሮሜ ፰፡፭᎗፱)” ይላል። ሥጋውን በመውደድ ላይ ያለውን በምን ማወቅ ይቻላል? የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል። መልሱ፤“ጮማና ክትፎ እየበሉ አይከሱ፤ እየጾሙ አያገሱ” እንዲሉ። በተገለባባጭ ቃላችን፤ ሊፈነዳ በደረሰው ሰውነታችንና የሚቀዳ በመሰለው ወዛችን ነዋ! ከዚህ የበለጠ ምን ማስረጃ ያስፈልጋል?

አብ በስሙ ለሚልከው ጰራቅሊጦስ መሳሪያ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎች ከ፩ እስከ በቀረቡት አናቅጽ ላይ የተዘረዘሩትን ባህርያት የሚያንጸባርቁ ሰዎች ናቸው። ነገር ግን በ፮ኛው አንቀጽ ላይ እንዳየነው፤ ከ እስከ ሸ የተዘረዘሩት ነገሮች ለመንፈስ ቅዱስ ስራ ፈጽመው ተቃራኒዎች ናቸው። “እነዚህን መውደድ የክፋት ስሮች ናቸው። እነዚህን የተመኙ ሁሉ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ(፩ጢሞ ፮፡፲)። እንደታበለው፤ ከነዚህ ፍላጎት ያልተላቀቁ ሰዎች፤ በቤተ ክርስቲያን አመራር ላይ ሊሰለፉ ይቅርና፤ ራሳቸው በሰይጣን ሰኬዛ ተወግተው የወደቁ ናቸው።

ቅዱስ ጳውሎስ “ስለምናገለግለው ስጦታ ማንም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን (፪ኛ ቆሮ ፰፡፳) እንዳለው፤ ከነዚህ እንቅፋቶች ባንዷ ተሰናክለው ለህዝብ እንቅፋት እንዳይሆኑ የጰራቅሊጦስን ስጦታ የተቀበሉ መንፈሳውያን መሪዎች፤ እጅግ ይጠነቀቃሉ። ለክርስቲያኖች ከኃጢአት በቀር “ሁሉ ተፈቅዷል” ይሁን እንጅ ክርስቲያኖች ከተፈቀደላቸው በቀር ሌላ ሊያደርጉ ይቅርና “የተፈቀደው ሁሉ ግን አይጠቅመኝም”፩ኛ ቆር ፭፡፲፪) በማለት ራሳቸውን የመግታት መንፈሳዊ ሃይል ሊኖራቸው ይገባል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መጀመሪያ ጰራቅሊጦስን ከተቀበሉ አንዷ በሆነችው ውስጥ ነንና፤ መንፈስ ቅዱስ ከሚጠላቸው ከተዘረዘሩት ጠባያት ለመሸሽ፤ የሚወደውን ለመከተል ምሳሌ ልንሆን ይገባናል።

ቅሊጦስ ካዘዛቸው ባህርያት ጋራ የሚጋጩትን ካህናት ጳጳሳት ቀሳውስት እያለ ወደ ህዝብ የሚልከውንና ተላኪውን መቀበል ቀርቶ ህዝበ ክርስቲያኑ እያወገዘ እንዲያባርራቸው፤ የቤተ ክርስቲያናችን መመሪያ “ለኩሉ ዘዐለወ፤ ወተቃረነ ንባበ መንፈሳዌ፡ ወተግህሰ እምነ ጽድቅ፡ውስተ ኩሉ ሃበ ሀለወ፡ ወለኩሎሙ ከሀድያን ወሰብእ እኩያን፡ወሕጉላን፡ እለ አልቦሙ ሃይማኖት ወዘዐለው ሃይማኖተነ ወእለ ሤሙ ላዕሌሆሙ መገብተ ከሐድያነ ንኴንኖሙ በግዘት በኩሉ መዋዕል (ሃይ ምዕ ፻፩፡፳፫) ብሎ ያዝዛል። ተመልከት አንባቢ! ይህም ማለት፦ የቨርጅን ኪዳነ ምህረት ህዝበ ክርስቲያን በተሳሳተው ግለ ሰብ ላይ እንደወሰደው ያለ ርምጃ ማለት ነው። በዚህ ስርአት የተወገዘውን ሰው ደግፎ የሚልክ እንደ አባ ፋኑዔል ያለ አዲስ ተክል ይጠንቀቅ። [ስለ አዲስ ተክል ከዚህ ቀደም የተጻፈውን ለማንበብ ከፈለጉ ይህን ሰንሰለት ይጫኑ።  አባ ፋኑኤል አዲስ ተክል ናቸው]

ክርስቶስ ካስተማረው ጋራ የተጋጨ፤ እምነተ ጎደሎ፤ ከእውነት ራሱን ያገለለ፤ ስህተት ነው ብሎ ጰራቅሊጦስ በፈረጀው ውስጥ የተካተተ ሁሉ፤ እየሰየመ የሚልክም ሆነ እየተሰየመ የሚላክም አብረው ከቤተ ክርስቲያን መወገድ አለባቸው” ላኪና ተላኪ ተያይዘው አንድ ላይ የመወገዳቸው ሁኔታ፤ በላኪው በአቶ መለሰና በተላኪው በአቡነ ጳውሎስ ላይ የተፈጸመው አንድ ላይ መወገድ፤ የጰራቅሊጦስን ተግባር በገሀድ ገልጾታል። አሁን ወደ ንጽጽር እሻገራለሁ።

፬ኛ፦ ንጽጽራችን ወይም ውድድራችን ከማን ጋር ነው? በምን ነው? የትስ  ለመድረስ ነው?

ክርስቲያን በተለይም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና መምህራን፤ ቅዱስ ጳውሎስ “ኢንትሀበል ናጥብእ ነሐሊ ርእሰነ ለሊነ ከመ እለ ይንእዱ ርእሶሙ በዘአመከሩ ወአየኑ ለሊሆሙ ወኢያእመሩ ፍካሬሁ ዘለሊሆሙ ይነቡ ( ፪ቆሮ ፲፡፲፪)። እንዳለው፦ ማለትም፦ እራሳቸውን ከገዛ ራሳቸው ጋራ እያነጻጸሩ እኛ ብቻ በማለት እራሳቸውን እያገነኑ ከተግዳሮት እንደወደቁ ሰዎች አንሁን። ራሳቸውን ከራሳቸው ጋራ የሚያነጻጽሩ ሰዎች የሚናገሩትን አያውቁም” ብሎ ያስጠነቀቀውን ባለመርሳት፤ ለቅድስና መወዳደርና መነጻጸር እጅግ አፈላች ናቸው።  የቤተ ክርስቲያናችንን የመጀመሪያው አቡን አባ ሰላማን መክሮና አስተምሮ ክኖ የላከው ቅዱስ አትናቴዎስ “ተናጸሩ በበይናቲክሙ ፩ዱ ምስለ ካልዑ” እርስ በርሳችሁ ተወዳደሩ ብሏል።

ውድድራችን ግን በንብረት በሹመት በልብስና በማነኛውም ሥጋዊ ነገር ላይ መመስረት የለበትም። ለምሳሌ፦በዘመናችን ያሉ አንዳንድ ሰባኪዎች፤ ቀሳውስቶች፤ መነኮሳትና ጳጳሳት የህዝቡን ስነ ልቡና ተቆጣጥረው የሚፈልጉትን ለማግኝት ሲሉ፤ የማይጠቀሙት አስመሳይ ፈሊጥ የለም። እርስ በርሳቸው በሚደርጉት ሽኩቻ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነገረ መለኮት ራሳቸው እየሳቱና ህዝቡንም እያሳቱ ናቸው።

ይህ በዘመናችን የሚካሄደው ውድድር፤ ጸድቆ ለማጽደቅ ሳይሆን፤ ከማዳመጥ በቀር የምትናገሩትን ሁሉ ከየት አመጣችሁት? ብሎ ህዝቡ እንደማይጠይቃቸው ተረድተው፡ በተደበላለቀ ጩኸት ህዝቡን አፍዝዘውና አደንዝዝዘው ገንዘቡን ለመዝረፍ የሚያደርጉት ጥረት ነው። የውጭ ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ይታደሳል”(፪ቆር ፬፡፲፮)“ ያለውን ጭራሽ ረስተው፤ የሚወዳደሩት ለዚህ ዓለም ንብረት እንጅ፤ የውስጥ መንፈስን እምነትንና ሞራልን ማደስ በሚችሉት ላይ አይደለም።

እንድንወዳደር የጉባዔ ሊቃውንት አበው ያስተማሩንና የመከሩን እንደ ሐሀዋርያት “ይረትእኑ በቅድመ እግዚ ኪያክሙ ንስማእ ወአኮ ለእግዚ” ((የሐዋ ፬፡፲፱)እንድንል ነበር። ማለትም ” እግዚአብሔርን እንጅ የቤተ ክርስቲያንን አቅጣጫ የሚያስቱ ባለ ስልጣናትንና መናብርትን አንታዘዛችሁም። አንሰማችሁም ማለት ለሚያስችል ሞራልና እምነት ነበር። እናንተን ሰምተን በተድላ በደስታ ከመኖር “በብዙ መከራ ወደ እግዚአብሄር መንግሥት እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል” (የሐዋ ፲፬፡፳፪) እንድንል ለሚያስችል ቆራጥነት ነበር።

“በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሄርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ተጠንቀቁ ። ከሄድኩህ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ ደቀ መዛሙርትን ወደ ኋላ ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገረን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሱ እኔ አውቃለሁ” ( የሐዋ ፳፡፳፰᎗፴) እያልን ወደፊት የሚከሰተውን ሳይቀር እየተናገርን እንደ እነ ቅዱስ ጳውሎስ፤ ያለፈውን ካለው ጋራ እያነጻጸርን፤ ዘመናችንን እየዋጀን፤ የሚመጣውንም እየገመትን፤ የተኩላ ባህርይ ካላቸው ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን በትጋትና በቅድስና ለመጠበቅ ነበር። ቅኔ በማመሥጠር ቅዱሳት መጻህፍትን በመመርመር፤ ሊቃውንት አበው ቀምረው ካስቀመጡልን አኀት አብያተ ክርስቲያናት ከሚመዛዘኑበት ነገረ መለኮት ይዘትና ቅጽ ላለመውጣት በሚደረግ ውድድር ነበር። አሁን በዘመናችን ያለው ውድድር በልብስ በቤት ግዥ፤ በገንዘብ ክምችትና ከህዝበ ክርስቲያኑ የተሰወር የገንዘብ መሰብሰቢያ ድርጅት መፍጠር። ምእመናኑን በዚያም በዚህም አምታቶ የቤተ ክርስቲያንን ሙዳይ ምጿት መዝረፍ እንጅ ቀድሞ የነበሩት የተቀደሱ ውድድር አይነቶች በመካከላችን አሉ? ይህማ ቢኖር ኖሮ፤ ማርያማዊ ህገ ሃይማኖት በሚል ርእስና “ክርስቶስ ፍጡር ወይስ ፈጣሪ?” እያለ በሚጠለስም ነጋዴ ደፍተራ ሃይማኖታችን ሲቃወስ ዝም ባልተባለ ነበር። በዘመናችን የተከሰቱትን በቅድመ ወያኔና በዘመነ ወያ የተካሄዱትን ንጽጽሮች (ውድድሮች) እንመልከት።

በዘመናችን ያየናቸው የውድድር ሂደቶች

ክፍል ፩ ቅድመ ወያኔ

በታሪክ የሰማናቸውን እንደነ አቡነ ጴጥሮስ የነበሩትን ሰማእታት ሳንረሳ፤ በዘመናችን ተከስተው ባይናችን ያየናቸውን እንመልከት።

ለምሳሌ፦ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በ፬ቱ ዓመታት ዘመነ ፓትርያርክነታቸው በሳቸው ላይ በተንጸባረቁት በችሎታቸው፤ በሙያቸውንና በትእግስታቸው በውጭም በውስጥ የተደነቁ ናቸው። እንዲገደሉ ለሞት አሳልፈው የሰጧቸው የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች እንኴን ከማይካዷቸው ለሰማእትነት ውድድር ከሚያበቋቸው ተግባሮቻቸው ሶስቱን ብቻ እጠቅሳለሁ።

፩ኛ፦ዘመናውያን ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያንን ከስርዓተ ዘውዱ ጋራ ጨፍልቀው የሚከሱበት ምክንያት በመሬት ይዛታ ነበር። የኮምኒስት ስርዓት ተከስቶ ከመሳፍንቱ ስርአት ጋራ ቤተ ክርስቲያንን አብሮ ከመደሰሱ በፊት፤ የሚመጣውን ቀድመው በማየታቸው፤ ከመሳፍንቱ ስርዓት ጋራ ቤተ ክርስቲያን የተሳሰረችበትን ስርዓተ መሬት የሚያፈርሰውን የሰበካ ጉባዔ መተዳደሪያ ደንብ (ቃለ ዓዋዲ) በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን በማወጅ የደርግን አዋጅ ቀደሙ። በዚህም ምክንያት በመሬት ከበርቴዎችና ባልገባቸው ታላላቅ ካህናት ዘንድ ጥላቻን አተረፉ። የመናፍቅነት ስምም ተሰጣቸው። ተከሰሱ። የሚጠፉበት አጋጣሚም ተፈለገላቸው። ደግ ነገር እያደረጉ በከንቱ ጥላቻ ሞት ከተፈረደባቸው ታላላቅ ሰዎች አንዱ ሆኑ።

፪ኛ፦ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ “ይረትእኑ በቅድመ እግዚአብሔር ኪያክሙ ንስማእ ወአኮ ለእግዚአብሔር” (የሐዋ ፬፡፲፱) እንዳሉት ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ በደርግ የተሰየሙትን እነዶክተር ክነፈ ርግብ ዘለቀን አላውቃችሁም ወግዱ ብለው ተጋፈጡ። የምሰማው እግዚአብሔርን እንጅ፤ የቤተ ክርስቲያንን አቅጣጫ የምታስቱ እናንተን የደርግ ተላላኪዎች መናብርትን አንታዘዛችሁም። አንሰማችሁም። እናንተን ሰምተን በተድላ በደስታ ከመኖር ይልቅ፤“በብዙ መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል” (የሐዋ ፲፬፡፳፪) ብለው በሙሉ ልባቸው በመጋፈጥ፤ እንደ ሐዋርያት በአረመኔዎች እጅ ተሰቃይተው መሞትን መረጡ።

፫ኛ፦በመጨረሻም ሰሞኑን ሐራ ዘተዋህዶ [ሙሉውን ዝርዝር ለማንበብ አዚህ ላይ በመጫን ያንብቡ ]

“ከጊዜያዊ ጉባኤው ጋራ ያልተግባቡትና የማሻሻያ መዋቅሩን ያልተቀበሉት ቅዱስነታቸው በወርኃ የካቲት ፲፱፻፷፰ .ጊዜያዊ ጉባኤው ለደርጉ ባቀረበው የክሥ ሪፖርት ‹‹ሲጠበቅ የቆየ ፍርድ›› በሚል ዐዋጅ ከመንበረ ፕትርክናው ተገፉ፡፡ በቅዱስ ሲኖዶሱና በጊዜያዊ ጉባኤው መካከል ሽኩቻ የተካሔደበት ቀጣዩ የፕትርክና ምርጫ በጊዜያዊ ጉባኤው በኩል ታጭተው የቀረቡትን ሐዋርያዊውን ባሕታዊ አባ መላኩ ወልደ ሚካኤልብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በመንበሩ ሠየመ፡፡ ብሎ እንደገለጸው፤ በሰማእትነት ይህችን ዓለም ለቀቁ።የተሰየመለትን ተልእኮ ፈጽሞ “መልካሙን ገድልተጋድያለሁ ሩጫየንም ጨርሻለሁ ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ ወደፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል” በማለት ይህችን ዓለም የለቀቀውን ቅዱስ ጳውሎስን መሰሉ።


ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በዚህ ታማኝነት ይህችን ፈታኝ ዓለም የለቀቁበት ምሳሌነታቸው ቢያኮራንም፤ ቅዱስ ጳውሎስ “መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጅ ለኔ ብቻ አይደለም” (፪ኛ ጢሞ ፬፡፯ - ፱) እንዳለው፤ ጻድቅ ፈራጅ ለሳቸው ያዘጋጀውን የጽድቅ አክሊል ለመቀበል ፈቃደኛ ሆኖ የጰራቅሊጦስን ግብር ለመግለጽ ከሳቸው በኋላ የተከሰተ ባለመኖሩ; የዘመኑን መንሱትነት ገልጾታል።  [ስለ ዘመነ መንሱት ከዚህ ቀደም የተጻፈውን ለማንበብ ከፈለጉ ይህን ሰንሰለት ይጫኑ። ዘመነ መንሱት)  ማለትም ከሳቸው ወዲህ በወያኔ ዘመን በቦታው የተተኩ ሁሉ እንደሳቸው አልሆኑም።

ክፍል ፪ ዘመነ ወያኔ

"የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር በ1979 አመተ ምህረት አስተሳሰብ ለዋጭ የፕሮፓጋንዳ መርሀ ግብር ለሚመለምላቸው ቀሳውስት ዘረጋ። የማሰልጠኑ ዓላማ ቤተ ክርስቲያኗን ከህዝብ ለይቶ በመምታት ስፋቷን ማጥበብና በትግሬአዊነት ላይ ብቻ የተመሰረተ ስሜት በትግራይ ተወላጆች ጭንቅላት መክተት ነው። ቤተ ክርስቲያኗ ለረዥም ዘመናት በህዝቡ አዕምሮ ላይ ስትተቀርጸው የኖረችውን ብሄራዊ የኢትዮጵያነትን ስሜት ከትግራይ ህዝብ አዕምሮ ጠራርጎ በጠባቡ ትግሬአዊነት ስሜት በመተካት የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዘት እያጠበቡ ራሷን ቤተ ክርስቲያኒቱን መምታት ነው።” [ከአሁን በፊት ‘የኔ ፋሌቅ ወጥመድ’ በሚል ርእስ የጻፍኩትን ጦማር ሙሉን ለማንበብ የሚቀጥለውን ሰንሰለት ይጫኑ::   የነ ፋሌቅ ወጥመድ ] የሚል መመሪያ ወያኔ ዘርግቶ፤ኢትዮጵያን በመንግስት ደረጃ መምራት ከጀመረበት ዘምን ጀምሮ እስካሁን፤ እያየሉ በመሄድ ላይ ያሉት፤ ለጰራቅሊጦስ ፈቃድ ተቃራንያን የሆኑት በ፮ኛው አንቀጽ ከሀ ተራ ፊደል እስከ ሸ የተዘረዘሩት የሥጋ ፈቃዳት ናቸው። በነዚህም ፈቃዳት ላይ ተመስርተው የተፈፈጹምትን እንመልከት።

ለምሳሌ፦
·        እርቅ እንዲፈጸም በስደት ያሉትም፤አቡነ ጳውሎስም ሁሉም ተስማምተው በአስፈጻሚ ቡድን ድርድሩ ተጀመሮ ሳለ፤ አቶ ስብሀተ ነጋ እርቅ የሚሹ ይገደሉ አሉ። አሁን የዲያብሎስን ሥራ አንድ በሉ።
·       
  ፕሬዝደንት ግርማ አቡነ መቅርቆርዮስ ተመልሰው በመንበሩ ይቀመጡ ካሉ በኋላ፤ በዚያው ሳይገፉ የኢሀደግ ፈቃድ አይደለም በለው ቃላቸውን አጠፉ። ሁለት በሉ

·         የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት እርቁ ሳይፈጸም የፓትርያርክ ምርጫ ቢደረግ ለተጀመረው እርቅ እንቅፋት ይሆናልና ምርጫ እንዳይደረግ እያሉ፤ በእነ አቶ ስብሀት ነጋ አመራር ሰጭነት ለመመረጥ አቡነ ማትያስ በደስታ ቀረቡ። ሶስት በሉ።

·         በተለይም እርቁ እንዲፈጸም አምኖ ወዲያ ወዲህ ይል የነበረ እንደ አባ ማትያስ ያለ ሰው፤ እርቁ ሳይፈጸም ምርጫ ቢደረግ፤ ለእርቁ እንቅፋት እንደሚሆን በግልጽ ያወቃሉ። [ይህን አስመልክቶ የተጻፈውን ሙሉን ለማንበብ ቀጥሎ ያለውን ሰንሰለት ይጫኑ:: “ጭንጋፍ (ምቱር) ፓትርያርክ” ]:: “ሲያጥረኝ ብቀጥልሽ፤ ሲመቸኝ ባነሳሽ” እየተባለ እንደሚጫወቱት የገበጣ ጨዋታ፤ የቆረጠቱን የኢትዮጵያዊነትን ዜግነት ቀጥለው፤ ያነስቱን ያሜሪካ ዜግነት ጥለው፤ ዘው ብለው በመንበሩ ላይ ጉብ ማለታቸው፤ አራት በሉ። 

በህወት እያሉ ወያ ቢለወጥ፤ የትኛውን ዜግነት ቆርጠው፤ የትኛውን ይቀጥሉ ይሆን?

·         በመንበሩ ላይ ጉብ ካሉ በኋላ፤ ሲያደርጉ የምናየውን፤ ሲናገሩ የምንሰማውን ስህተቶች፤ አምስት በሉ። በፈቃዳቸው፤ ወይም በህዝበ ክርስቲያን ትግል፤ ወይም በጸጸት መለወጥ፤ ወይም ፈጽሞ ባለመኖር እስኪገቱ ድረስ አሁን በመጓዝ ላይ ባሉበት መንገድ ገና ይቀጥላሉ።

በሲኖዶስ መካከል

እርቅ ለመፍጠር ወዲያ ወዲህ ይሉ የነበሩ ሰዎች፤ በራሳቸው ፍላጎት ሳይሆን በጰራቅሊጦስ መሪት ቢጀምሩት ኖሮ፤ አልታረቅም ያለውን ክፍል እያወገዙ እስከ መጨረሻ ይቀጥሉ ነበር እንጅ፤ በአቶ ስብሀት ፉከራ አይቆሙም ነበር። ፕሬዝደንት ግርማም በመጀመሪያ የተናገሩት በእምነትና በሞራል ላይ የተመሰረተ ቢሆን ኖሮ ፤ በኢሀደግ ትእዛዝ ባላቆሙት ነበር።

ትላንት አባ ማትያስ ለፓትርያክነት አይበቁም፤ ችሎታው የላቸውም፤ የተዋህዶውን እምነት አያውቁትም፤ እያልን ስንናገር ከሳቸው ጋራ ተሰልፈው፤ በኛ ላይ የዘመቱ ብዙዎች ነበሩ [ ይህን አስመልክቶ የተጻፈውን ሙሉን ለማንበብ ቀጥሎ ያለውን ሰንሰለት ይጫኑ:: አባ ማትያስ : “እንዲህ ያለ ፓትርያርክ አይተን አናውቅም” ]

አልፈው ተርፈው በ፲፬ አመታቸው የቅኔ መምህር ሆኑ፤ ሀዲሳቱን ሊቃውንቱን ተማሩ፤ እንግሊዘኛውን እብራይስጡንም አፍሰው ይናገራሉ፤ እያሉ በማያውቃቸው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ አልሰበኩላቸውምን? ዛሬ ደግሞ ተገልብጠው እንዲህ ሆኑ እያሉ የሚናገሩት እውነት ቅዱሳንን በመራቸው በጰራቅሊጦስ በመመራት የሚናገሩት ነውን? ይህን ስል አቡነ ማትያስ ከአቡነ ጳውሎስ ይሻላሉ እያላችሁ ስታወሩ የነበራችሁ ወገኖች አሁንም ወደፊትም በሲኖዶስ አካባቢ በሚነሱ ነገሮች ላይ መነጋገር ያለብን፤ በማይለወጠው ሞታችን ላይ ሆነን እንጅ ከዘር፤ ከፖለቲካ፤ ከጎሳና ከጊዜያዊ ጥቅም ጋራ በተገናኘ መልክ መሆን የለበትም

እስካሁን እንደታየው ዛሬ አለ እየተባለ የለሚነገርለት ሲኖዶስ በነ አቶ ስብሀት የሚመራ ነው። እነ አቶ ስብሀት ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ “ኢንትሀበል ናጥብእ ነሐሊ ርእሰነ ለሊነ ከመ እለ ይንእዱ ርእሶሙ በዘአመከሩ ወአየኑ ለሊሆሙ ወኢያእመሩ ፍካሬሁ ዘለሊሆሙ ይነቡ ( ፪ቆሮ ፲፡፲፪)። እንዳለው፦ ማለትም፦ እራሳቸውን ከገዛ ራሳቸው ጋራ እያነጻጸሩ እኛ ብቻ በማለት እራሳቸውን እያገነኑ ከተግዳሮት የወደቁ ሰዎች እንደሆኑ ግልጽ ነው። ይህ ሲኖዶስ፤ “ራሳቸውን ከራሳቸው ጋራ የሚያነጻጽሩ ሰዎች የሚናገሩትን አያውቁም” ተብሎ በሀዋርያው የተሰጠውን ተግሳጽ በማያውቀው በወያኔ መንግስት በመመራት ላይ ስላለ ለቅድስና፤; ለሞራል፤ ለእምነት፤ ለወገንና ለሀግር መስዋዕት ለሚጠይቁ ነገሮች ንጽጽርና ውድድ የሚቀርብ አይደለም።

ይልቁንስ እያንዳንዳችሁ የቤተ ክርስቲያናቱ አባላት የሆናችሁ ሁሉ፤ ነገረ መለኮቱን ጠልቀው ባልተገነዘቡት ግለ ሰቦች በመመራት፤ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነገረ መለኮት በማፈንገጥ ከአቻወቿ አኀት አብያተ ክርስቲያናት ቤተ ክርስቲያናችሁን ለመቁረጥ የምታደርጉትን ስህተት አቁሙ እያልኩ፤ ከጰራቅሊጦስ መርሆ ማፈንገጥ ወደ ተከሰቱባቸው ከብዙ አብያተ ክርስቲያናት ጥቂቶችን ለምሳሌ ያህል ከዚህ በታች ጠቅሳለና፤አስተውል አንባቢ! ።     


አስተውል አንባቢ! ለንደን ላይ ባለችው ቤተ ክርስቲያን፤ መነኮሳት እና ጳጳሳት ባንድ ወገን፤ ካህናትና ምእመናን በሌላ ወግን ሆነው በመታገል ላይ እንዳሉ እየሰማን ነው።

አቡነ እንጦንስ የሚባሉት ሰው እንኴን መነኩሴ ጳጳስ ሊያደርገው፤ ማንም ክርስቲያን ቢያደርገው የሚያስወግዘውን፤ ካላገቧት እህታችን ወልደዋል ተብለው ከነ ህጻኑ ፎቷቸውን ሁሉም እያየው ነው። ለመሆኑ የሚጠሩበት እንጦንስ የሚለው የማን ስም እንደሆነ ያውቃሉ? ይህ ስም ከገዳም የወጣ፤፤ ምንኩስናውን ክዶ፤ ወልዶ የተወቀሰ ሰው የሚጠራበት አይደለም። ምንኩስናቸው የራሳቸው ነው። ለምን ጣሉት ብለን እንዳንወቅስ በመጻህፍት ክልክል ነው። ይሁን እንጅ በሁለት ነገሮች ከጰራቅሊጦስ ጋራ ተጋጭተው ከቤተ ክርስቲያናችን የወጡ መሆናቸውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በሰጠችን መብትና እውቀት መናገራችንን እንቀጥላለን።

፩ኛ፦ምንኩስናውን መሸከም አለመቻላቸውን እያወቁ፤ ከወለዱት ልጃቸው ጋራ እስኪጋለጡ ድረስ ህዝበ ክርስቲያኑን እያታለሉ መቆየታቸው ትልቅ በደል ነው።

፪ኛ፦ክህነት የህዝብ መገልገያ ህዝባዊ ንብረት እንጅ የግላቸው አይደለም።እሳቸው ግን የነበራቸውን የጵጵስና ተልእኮ ከላይ በተዘረዘሩት ድካማቸው ሰባብረው በመጣላቸው ማፈርና ንስሀ መግባት ሲገባቸው፤ ህዝባዊ አገልግሎት ሰጭ የሆነውን ህዝባዊ ክህነት አውግዣለሁ በማለታቸው፤ ከጰራቅሊጦስ መርሆ ውጭ ናቸው።

ዋሸንግተን ዲሲ ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም

በዲሲ ማርያም የሚካሄደውን እንመልከት፦ በመጀመሪያ በቅዱስ ገ ብርኤል ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ በአባ መዓዛ ላይ አድማ አነሳስቶ አንድ አካል የነበሩትን አብያተ ክርስቲያናት እንዲከፋፈሉ አደረገ። ቀጠለና ”ክርስቶስ ፍጡር ወይስ ፈጣሪ”በሚል ወ/ሮ አስቴር ተክለ አረጋይ በሚባሉ እናት ስም ጠልስሞ ያቀረበው፤ “ማርያማዊ ሕገ ሃይማኖት በሚል ርእስ ከጠለሰመው የከፋ ክህደት ነው። እነዚህ ሁሉ ተደጋጋሚ ስህተቶቹ [ ይህን አስመልክቶ የተጻፈውን ሙሉን ለማንበብ ቀጥሎ ያለውን ሰንሰለት ይጫኑ::  “የሰይጣን ቤተ መቅደስ”] የሚል ርእስ ቤተ መቅደሷን የሚነካ ጦማር እንዲዘጋጅ ምክንያት መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። ጊዜ በማጣት አልሄድበትም እንጅ “ማርያማዊ ሕገ ሃይማኖት” በሚል ርእስ ከጠለሰመው ክህደት ይልቅ፤ ”ክርስቶስ ፍጡር ወይስ ፈጣሪ” በሚል ርእስ የጠልሰማት የተሸከመችው ክህደት፤ እጅግ የከፋውን ክህደት የተሸከመች ናት።

ይህ መስሎ የገባ አሸብሻቢ ከሀዲ ደፍተራ፤ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አእማድ የምንላቸውን እነ ያዕቆብ ዘስርጉን፤ እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን እያንቋሸሸ፤ የእምነታችን መጠበቂያ ናቸው ብለው ሊቃውንት ያስተማሩንን መጻህፍትንም መቀበል የለብንም እያለ፤ የነቀፋቸውን ቅዱሳት መጻህፍት በመጠቀም ገብቶ ሲቀድስ አቁም የሚለው ባለመኖሩ ተመልካች እጅግ አዝኖ ሳለ፤ በሌላ ጉዳይ ራሱ በፈጠረው እጽፍ ድርብ በደል ከቦርዱ ጋራ በመጋጨት ከቤተ ክርስቲያን ወጥቷል። መንፈሳዊውን ሀላፊነት ወስዶ ከቤተ መቅደስ የሚያሰወጣው ሲጠፋ፤ መንፈስ ቅዱስ ሌላ መንገድ ተጠቅሞ፤ ራሱ በፈጠረው ስህተት ከቤተ መቅደስ አስወገደው ማለት ይቻለል። ጰራቅሊጦ ተአምር ሰራ።

 ይሁን እንጅ ይህ ግለ ሰብ ከቤተ መቅደስ በአካል ቢወገድም፤ ጨለማ የለበሰ፤ የራሱን ስም ከራሱ የሰረቀ፤ ለራሱ ስም ያልታመነ ሌባ የሆነ ሰው፤ ሰይጣን የሀሰት ተሸካሚ አርጎ እባብን እንደተ ጠቀመ፤ እሱም ወረቀትን የሀሳቡ ተሸካሚ እባብ አርጎ ርኩስ መንፈስ በማሰራጨት፤ የነካውን ሁሉ ለመመረዝ ቤተ ክርስቲያኒቱን አሁንም እየታገላት ነው። የዋሸንግተን ርእሰ አድባራት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አባላት የሆናችሁ ሁሉ፤ አንብቡ! ታዘቡ! አስተውሉ! ከዚህ ቀጥየ ወደ ቨርጅንያ ኪደነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን እሻገራለሁ።

ቨርጅንያ ሐመር ኖኅ ኪዳነ ምህረት


የቨርጅንያ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ነኝ ይል የነበረ ሰው የልጆቹን እናት ፈትቶ፤ የራሱን ትዳር አፍርሶ ሲቀድስ አቁም ያለው አልነበረም። የሚሰራው ስህተት እጅግ በዝቶ በቅርብ የታዘቡ ክርስቲያኖች ተቆጥተው ተነሱ። ለሌላው ትዳር መፍረስም ምክንያት በመሆኑ፤ የታዘቡ ምእመናን “አእትቱ እማእከሌክሙ እኩየ” በሚለው ሐዋርያዊ መርሆ፤ “ለክህነቱ ለቤተ መቅደሱ ምሳሌነትህ ብቁ አይደለህምና ገለል በል” ማለት ጀመሩ። ነገሩ ተረጋግጦ ንስሀ መግባት ሲገባው፤ ንስሀ ግባ ያሉትን ክርስቲያኖች ሚሊዮን ብር ካሳ ክፈሉኝ ብሎ ከሰሰ። በዘበኛም ማባረር ጀመረ።

የሃይማኖቱ ተቆርቋሪዎች የሆኑ ሽማግሌዎች እምነቱ ያገናኛቸዋልና፤ የግለ ሰቡን ወላጅ እናት በማያዝ፤ ለቤተ ክርስቲያን ክብር ሲባል ጸቡ በባህላዊው ሽምግልና በሰላም እንዲያልቅ ሞከሩ። ማንም ሰው እሰራበታለሁ ብሎ መተዳደሪያ ቀርጾ የአሜሪካን መንግሥት ፈቃድ ቢጠይቅ፤ ህግ ሳትጥስ ከቀረጽከው መመሪያ ጋራም ሳትጋጭ፤ ህዝብ ሳትጎዳ የምታምነውን አድርግ ብሎ የአሜሪካ ህግ ይፈቅዳል። ህዝበ ክርስቲያኑ ይህን ግለ ሰብ፤ በተግባር አውላለሁ ያልከውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የምታዝዘውን መመሪያዋን ደምሰሰሀል፤ ከህጋችን፤ ከባህላችን እና ከቀኖናችን ጋራ እየተጋጨህ ነውና ቁም! ያሉትን ምእመናን፤ ይህን ድንቅ አሜሪካው ህግ በመጠቀም ሊፋለማቸው ሞከረ። ለሞራል ውድቀትና ለማጭበርበር ሽፋን ሰጭ በማስመሰል ማስፈራሪያም አደረገው።

ይሁን እንጅ ህዝቡ በሶስት ካህናት አመራር ሰጭነት አወገዘ። የህዝቡንም ውግዘት ካህናቱ አጸደቁት። [ የውግዘቱን ውሳኔ ሙሉ ቃል አዚህ ሰንሰለት ላይ በመጫን ያንብቡ:: ] ውዝግቡ ሲካሄድ ምንድነው ያላሉ ወይም ታረቁ ያሉ ሰዎች፤ የተወገዘው ሰው ንስሀ እንዲገባ ከመርዳት ይልቅ፤ ቀሳውስት ማውገዝ አይችሉም በሚል ሰበብ የተወገዘው ሰው በክህነቱ አገልግሎት ይቀጥል በማለት ከያሉበት ብቅ ብቅ አሉ። ይህን ለሚሉ ሰዎች ቤተ ክርስቲያናችን የሰጠችንን ባለመረዳት ባይታወሮች መሆናቸውን ተረድተን፤ ቢያስፈለግ አስተማሪ የሆነ ቋሚ መልስ ለመስጠት የሚቻል መሆኑን በማሳሰብ፤ የመንፈስ ቅዱስ ስራ ጎልቶ የሚታየው በየትኛው ጎራ ነው? በተወጋዡ ጎን? ወይስ በህዝቡ ጎን? አስተውል አንባቢ! ወደ መኒሶታ እንሻገር።

ሚኒሶታ ደብረ ሰላም መድኃንያለም ቤተካርስቲያን  

 በተከበሩ አዛውንት አባታችን በአቶ ታየ ረታና፤ በሊቀ ጳጳስ ማርቆስ መካከል የተካሄደውን ትግል እንመልከት። ማነው የዋሸው? የተከበሩ አቶ ታየ? ወይስ ሊቀ ጳጳስ መርቆስ? አቶ ታየ የተናገሩትም የጠየቁትም ኮ፤ ራሳቸው የጠፋባቸው አቡነ ዘካርያስ የተናገሩትን ነው። አቶ ታየ ለጠየቁት መመለስ የነበረባቸው አቡነ ዘካርያስ ነበሩ። ይሁን እንጅ ያልተጠየቁት ሰው የራሳቸውን ማንነት በራሳቸው አንደበት ጰራቅሊጦስ ይገልጣቸው ዘንድ በማቀዱ የሚከተሉትን ጸያፍ ንግግሮች ዘረገፉ። [ አቡነ ማርቆስ የተናገሩትን ሙሉን ቪድዮ ለመመልከት ቀጥሎ ያለውን ሰንሰለት ይጫኑ:: የአቡነ ማርቆስ ጸያፍ ንግግሮች]
ሀ. ድሮ ውሻ አባረረኝ። አሁን የሰው ውሻ አባረረኝ፤     ለ. ፕሮቴስታንት ናቸው።
ሐ. በቤተ ክርስቲያኑ አህያ አሳማ ይሰሩበት፤
መ. “ኢትዮጵያ ቢሆን እናሳያቸው ነበር” የመሳሰሉትን ከተራ ሰው አንደበት የማይጠበቁትን ነገሮችን መናገር ጀመሩ።

ያባ ማርቆስ ንግግር የመንፈስ ቅዱስ ነውን? ውሸት ያልተናገሩትን ምእመናን በውሻ መመሰል ተገቢ ነው። የጠፋው ገንዘብ ነዋየ ቅድሳት ነውና ይመለስ በማለታቸው ፕሮቴስታንት ያሰኛቸዋልን? ይህ አባባል ፕሮቴስታንት እውነት ተናጋሪ ኦርቶዶክስ ዋሾ ማድረጋቸው አይደለምን? ኦርቶዶክሶችን ፕሮቴስታንት ማለት ወደዚያ መሸኘት አይደለምን? “ቤተ ንጽህ ቤተ በረከት” እየተባለ አምላክ የሚመሰገንበትን ሥጋው ደሙ የሚታደልበትን ቅዱስ ቦታ “አሳማ አህያ ይሰሩበት” ማለት ተገቢ ነውን? ይህ የመንፈስ ቅዱስ ስራ ነውን? እኒህ ግለ ሰብ የጵጵስና ቆባቸውን ተገፈው መባረር የነበረባቸው አይደሉምን? ያባ መርቆስን ንግግር ሰምቶ፤ እንደ መመሪያም ተቀብሎ እንደተቀደሰ አመራር ቆጥሮ ከነ አቶ ታየ ረታ አቋም የተለየ ካለ፤በጰራቅሊጦስ መንገድ ሳይሆን በተሳሳተ መንገድ በመጓዝ ላይ እንዳለ ያስተውል።

መደምደሚያ

አቡ ማትያስ  ጀምሮ ከላይ የተገለጹት ሁሉ ባየነው ጎዳና ጅው ብለው ሲነጉዱ፤ በለንደን፤ በዋሸንግተን፤ በቨርጅንያ፤ በሚኒሶታና በሱዳን ባለቸው እህታችንና በሌላም ቦታ ያሉ ምእመናን እውነትን ሳይለቁ ከጰራቅሊጦስ ጋር የሚያደርጉትን ጉዞ እየተመለከትን ነው። “እስመ በጽሀ ጊዜሁ ለፍዳ ዘያቀድም እምነ ቤተ ለእግዚአብሔር ወእመሰ ኮነ እምኀቤነ አቅድሞቱ፡ ምንተ እንከ ይከውን ደሀሪቶሙ ለእለ ይክህደዎ ለወንጌለ እግዚአብሄር። ወሶበ ጻድቅ እምእጹብ ይድህን ኃጥዕ ወአማጺ በአይቴ ያስተርኢ ሀለዎ” (ያዕ ፬፡፲፯) የሚለውን ቃል አንድም እያሉ የተረጎሙት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ቀና ብለው አሁን ያለነው አንዳንድ ቀሳውስት፤ ጳጳሳት፤ መነኮሳትና፤ ሰባኪዎች የሚፈጸመውን ቢያዩት እንዴት እንደሚጸየፉት መገመት ይከብዳል።

ቅዱስ ያዕቆብ “የፍርድ ቀን ቀርቧል። ፍርድ በእምነት ቤት ውስጥ ባሉት ላይ መንደድ ከጀመረ፤ በማያምኑት ላይማ የሚነደው የፍርድ እሳት እንዴት የከፋ ይሆን?” እያለ እንደጠየቀው፤ ይህ የምንገኝበት ዘመን እጅግ አስፈሪና አስደንጋጭ ጥያቄ ይቀሰቅሳል። እምነቱና ችሎታው ሳይኖራቸው ከቦታው ጋራ የተገናኘውን ክብርና ጥቅም ለመሰብሰብ ሲሉ እየዘለሉ በገቡ ሰዎች ላይ የሚመጣው ፍርድ እጅግ በጣም ያስፈራል።

ነቢዩ “ተመልሰው እንዳልፈውሳቸው የዚህ ህዝብ ልብ ደንድኗል፤ ጆሯቸውም ደንቁሯል፤ ዓይናቸውንም ጨፍነዋል” እንዳለው፤ ልባቸው ባይደነድን፤ ጆሯቸው ባይደነቁር፤ ዓይናቸውንም ባይጨፍኑ፤ በማያምነው ባቶ መለሰና፤ ሳያምኑ አምናለሁ ወይም እምነታቸውን በካዱት በአቡነ ጳውሎስ ላይ የነደደውን ፍርድ አይተው መመለስ እንዴት ይሳናቸዋል? እኛ ሁላችንም ማየት ያለብን፤ በነሱ ላይ የተከሰተውን ሁላችንም በተራችን የምንሞተውን ሞት አይደለም። መመልከት ያለብን በማሟተቸው ላይ የተከሰተውን ትንግርት ነው። ከእምነት ቤት ውጭ የነበሩት አቶ መለሰ፤ በእምነት ቤት ውስጥ የነበሩት አቡነ ጳውሎስ ተጠራርተው እንደመጡ፤ በሞት ተጠራርተው ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን መልቀቃቸውን ነው። “የጌታን መንፈስ ትፈታተኑ ዘንድ ስለ ምን ተስማማችሁ? እነሆ! ባልሽን የቀበሩት ሰዎች እግር በደጅ ነው አንችንም ይቀብሩሻል”(የሐዋ ፭፡፱) ተብሎ በሐናንያና በሰጲራ ላይ የተፈጸመው የጰራቅሊጦስ ፍርድ በነሱ ላይ ተፈጸመ። በአቶ መለሰና በአቡነ ጳውሎስ እግር የተተኩት ሰዎች፤በነሱ ላይ የደረሰውን ተአምር ቆም ብለው ከመመልከት ይልቅ፤ ቅጣቱ በተፈጸመባቸው በአባ ጳውሎስና በአቶ መለሰ መርሆ እንቀጥላለን ማለታቸው፤ ምን ያህል በኃጢአት ስካር እንደፈዘዙና እንደ ደንዘዙ አጢኖ የተመለከተውን ሁሉ እያስገረመው ነው።

ነፍሶቻቸውን ይማርና፤ በአቶ መለሰና በአቡነ ጳውሎስ ላይ የነደደው እሳት እያስፈራን ሳለ፤ በለንደን፤ በዋሸንግተን ቅድስት ማርያም፤ በቨርጅንያ ኪዳነ ምህረት፤ በሚኒሶታ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንና በሌሎች ሁሉ ምእመናን በተለይም በሱዳን ባለቸው እህታችን ላይ እየጦፈ ያለውን የጰራቅሊጦስ ስራ ስንመለከት የቀዘቀዘውንና የዛለውን መንፈሳችንን እየቀሰቀሰው ነው። ሐዋርያት ላይ ፈስሶ የዓለምን ስሜት እንደ ማግኔት የሳበው የጰራቅሊጦስ እሳት፤በዚሁ ወቅት ሱዳን ላይ ባለችው በእህታችን በMariam Yahya Ibrahim ላይ ቦግ ብሎ በዓለም ዙሪያ መታየቱ፤ በተጠቀሱት ቦታዎች ሁሉ የታዩትን የዲያብሎስ ስራዋች ደምስሷቸዋል፤ ሰሪወችንም አጋልጧቸዋል። እጅግ እጹብ ድንቅ ነው።

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደምንረዳው ከሀዋርያት በኋላ በዚያው በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን Vibia Perpetua የምትባል ክርስቲያን Felicitas ከምትባል ጓደኛዋ ጋራ በክርስትና እምነታቸው ብቻ ታሰሩ። ለሁሉም ሰይፍ ወይስ ህይወት የሚል ምርጫ ቀረበላቸው። ሁለቱም እምነታቸውን ክደው ከመኖር ሰይፉን መረጡ።  Felicitas ስለ ምትባለው ጸሀፊው እንዲህ ይላሉ። “She was very distressed that her martyrdom would be postponed because of her pregnancy ; for it is against the law for pregnant women te be excuted . She feared she would have to survive her Christian companions and alone endure a later execution along with criminals.” ያረመኔ መንግስት ህግ በጽንስ ያለች እናት ቢፈረድባትም መግደል አይፈቅድምና እስክትወልድ ድረስ በመቆየቷ አዘነች። ሞት አይቀርምና ተራ ሞት ወይም ከወንጀለኞች ጋራ መሞቷ አሳዘናት፤


Vibia Perpetua ስለምታበለውም Elian Pagels የተባሉ ጸሐፊ እንደገለጹት ወደ ምትሰየፍበት ስትወሰድ፤ “She was fresh from childbirth, with milk still dripping frpm her breast.” “አራስ ነበረች ያጋተችው ወተት ይፈስ ነበር” ብለው ገለጹት። (Adam Eve and the Sepent page 35 by) እህታችን ቅድስት Mariam Yahya Ibrahim ይህን ታሪክ ደገመችው። ስለ እህታችን ማርያም ያህያ ኢብራሂም፤ RUSSELL D. MOORE የተባሉ, ተመልካች የመዘገቡላትን ከዚህ በታች እንመልከት።


የዘመናችን ቅድስት Mariam Yahya Ibrahim እምነቷን ክዳ ከመኖር ሰይፉን መረጠች። ካሉ በኋላ፤ “When we see a heroine such as Mariam standing up for Jesus, even in chains, we are not simply seeing her. We are seeing the Spirit who blows where he wills, giving the kind of faith that fears not the one who can kill the body, the kind of faith that seeks first the kingdom of God.”
ለእምነቷ በመቆሟ፤ ማርያም ያሃያ ኢብራሂምን እጇ በሰንሰለት ገብቶ ስናይ፤ እምናየው እሷን ሳይሆን፤ በፈቀደው ቦታ ሰአትና ሰው ላይ፤ ቦግ የሚለውን የመንፈስ ቅዱስን እሳት ነው። ይህን የመሰለ እምነት እየሰጠ፤ ሰውነትን መግደል በሚችል ኃይል ፊት ያለ ፍርሀት አጽንቶ ማቆሙንና፤ ከሁሉ አስቀድሞ ለእግዚአብሔር ክብር መስጠትን የሚያስችል እምንቷን ነው ” ታዛቢው ይቀጥሉና  

“Mariam is not just fighting for her life. She's fighting against hell itself. And how does she do it? She does it with the only weapons that work: the blood of the Lamb and the word of her testimony, for she loves not her life even unto death (Rev. 12:11).”ይላሉ።ማለትም፦

“ማርያም እየታገለች ያለችው ለራሷ ጥቅም ክብር አይደለም። እንዴት ማድረግ ቻለች?። ሊሰራ በሚያስችል መሳሪያ ሰራቸው። ያም በፈሰሰላት በክርስቶስ ደም በመታመንና በሰጠችው የምስክርነት ቃል ነው። ይህን የመሰለ እስከሞት የሚያደርስ ፈተና ቢገጥማትም ራሷን አልወደደችም።” እያሉ RUSSELL D. MOORE, የተባሉ ጸሐፊ በመቀጠል፦ “who just gave birth in prison chains, is condemned to die for "apostasy," that is violating Sharia law by becoming a Christian. She's also charged with "adultery," because her marriage to a Christian man isn't recognized. As we pray for her, I'd like us to reflect on what we see in her” በማለት ስለሷ አስደናቂ ምስክርነታቸው ገለጹ።

“በዚህ ታማኝነቷ በሰንሰለት ታስራ ወህኒ በነበረችበት ጊዜ ወለደች። እስልምናን ክዳለች፤ ክርስቲያን ባልም በማግባቷ የሻርያን ህግ ጥሳለች” ተብላ ተሰይፋ እንድትሞት ተፈረደባት።” እያሉ ስለሷ ከመሰከሩ በኋላ፤ ወደኛም ዘወር ብለው “ስለሷ መጸለይ ብቻ አይደለም። እያንዳንዳችን ከሷ ያየነውን በራሳችን ለማንጸባርቅ እንሞክር” የሚል ምክራቸውን ሰጥተዋል። ቃለ ህይወት ያሰማዎ መባል ያለባቸው ይህን የመሰለ ምስክርነትና ምክር ለሚሰ ሰዎች ነው። እኒህ ጸሀፊ በእህታችን በማርያም ያሃያ አንጻር “ ሕዝበ ክርስቲያኑ በጰራቅሊጦስ መንገድ ሲሄዱ፤ አንቱ ፓትርያርክ፤ ሊቃነ ጳጳሳት፤መነኮሳትና ቀሳውስት በሳጥናኤል መንገድ አትንጎዱ እያሉ ነው።

ይቆየን
ለሌሎች ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ጦማሮች የሚከተለዉን ድህረ-ገጽ ይመልከቱ::


No comments:

Post a Comment