Wednesday, 13 June 2018

የወርቅ ዕንቁላል የምጥለውን ዶሮህን አትረዳት


የወርቅ ዕንቁላል የምትጥለውን ዶሮህን አትረዳት

ወንድሙ መኰንን፣ ሰኔ 5 ቀን 2ሺ10 ዓም (12 June 2018) ኢንግላድ

የምታውቁትን ተረት ልድገምላችሁ። አንድ በዶሮ ዕርባታ ብቻ የሚተዳደር ድሀ ገበሬ ነበረ። ጫቹቶቹን እያስፈለፈለ አውራዎቹን እየሸጠ፣ እንስቶቹን ግን እያኖረ አንዳንዴም ዕንቁላላቸውን እየለቀመ ሽጦ ኑሮውን ያሸንፍ ነበር። አንዴዲት የምትገርም እንስት ዶሮ ተፈለፈለች ገና ከጫጩትነቷ ጀምራ የተለየች (unique), እንደአውራዎቹ የሚያብረቀርቅ የላባ ቀለም ነበራት። አንዳንዴም እንደ ቆቅም ያደርጋታል። ለየት ያለች ስለሆነች ገበሬው ከሌሎቹ አብልጦ ይወዳት ነበር። ለአቅመ ዶሮ ከደረሰች በኋላ ብዙ ጊዜ ዕንቁላል ሳትጥል ዘገየች ቢጠብቅ፣ ቢጥብቅ ዕንቁላል አልጥል ስላለች፣ “ይኽቺ መልኳን አሳምራ የማትረባ ዶሮ!” ብሎ ከአውራዎቹ ጋር ሊሸጣት ሲያቅማማ፣ አንድ ቀን ሳይታሰብ አሽካክታ የሚያብረቀርቅ ዕንቁላል ጣለች። ገርሞት ዕንቁላሉን ሲያነሳው ሲል ለየት ባለ ሁኔት እንደ ድንጋይ ከበደው። እንዲያው እያፈረ፣ እየፈራ እየተሸበረና እየተሸማቀቀ፣ ወደ ርቅ ቤት ወስዶ ባለሙያዎቹ እንዲመረምሩለት ጠይቃቸው። የወርቅ ቤቱ ባለሙያ ሙሉ በሙሉ ዕንቋላሉ የወርቅ ትልቅ እንክብል መሆኑን አረጋገጠለት። ከዚያም ያንን የወርቅ ዕንቁላል ወስዶ በብዙ ብር ሽጦ ከድህነቱ ተላቀቀ። ላሞች ገዛ፣ በሬዎች ገዛ፣ ፈረሶች ገዛ፣ በቅሎዎች ገዛ ....። ያችን ባለውለታ ዶሮ በእንክብካቤ ያዛት። “ዕንቋላል ብትጥል ባትጥል ምን ቸገረኝ? በአንድ ጊዜ በጣም ሀብታም አድርጋኛለች፣ ባለውለታዬ ናት!” ብሎ ከእጁ እይበላች ለማዳ (pet) ሆነች። ኑራ ኑራ፣ ቆይታ ቆይታ፣ አንድ ቀን አሽካክታ ሌላ የወርቅ ዕንቋላል ለችለት። አሁንም ወስዶ ያንን ከባድ ንጹህ ወርቅ ሽጦ ሀብት በሀብት ሆነ። ቤቱን በዕብነ በረድ ሠራ። ዉድ መኪና ገዛ። በሰፈሩ እሱን የሚያክል ሀብታም አልነበረም። ታዲያ ምንም ሳይጎድለው አንድ ቀን አንድ ሰይጣናዊ ሀሳብ ብልጭ አለበት።ለምን እኔ ወቅቷን ጠብቃ አንድ የወርቅ ዕንቁላል እስክትጥል አስጠበቀኝ። አርጄአት በውስጧ ያለውን ወርቅ በሙሉ ሙልጭ አድርጌ ወስጄ ለምን በበለጠ በአንዴ የናጠጠ ኃብታም አለሆንም?” ብሎ ተሰገበገበ ወሰነ ምንም ያልጠረጠርችው ዶሮ እንደልማዷ ከእጁ ልትበላ ስትቀርበው ምንም ሳታሰበው ይዞ አረዳት። በጉጉት ሆዷን ሰንጥቆ ሲከፍታት በውስጧ ምንም ወርቅ አልነበረም። ከዚያ በኋላ የሚሆነውን አንባቢ ይገምተው።

ይኸን ታሪክ እዚህ ለመድገም ነሳሳ የሰሞኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለመሸጥ የኢትዮጵያ ገዢዎች የወሰዱት እርምጃ አስደንግጦኝ እና አሳስቦኝ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር 30 December 1945 (ታኅሣስ 21 ቀን 1938) ዓ.ም፣ ልክ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳለቀ፣ ትራንስወርልድ ኤር ላየንስ በተባለ የአሜሪካ አየር መንገድና በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግስት የጋራ የሽርክና ንግድ ተመሠረተ። በዚያን ጊዜ አምስት DC-3 በተባሉ ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት የተረፉ የአሜሪካ የጦር ማጓጓዣ አይሮፕላኖች የጀመረው ድርጅት፣ ዛሬ በኢትዮጵያ ልጆች ጥረት ከውስጥ በራሱ አድጎ (organic growth) እና ተመንድጎ፣ የ22 ቦይንግ ድሪምላይነር (Boeing 787 Dreamliner))፣ 16 ቦይንግ 777 (Boeing 777)፣ 6 ቦይንግ 767 (Boeing 767)፣ 2 ቦይንግ 757 (Boeing 757)፣ 23 ቦይንግ 737 (Boeing 737)፣ 9 ኤርባስ (Airbus A350)፣ እና የ22 ዲሀቫላንድ ካናዳ ዲኤችሲ-8-400 (De Havilland Canada DHC-8-400)፣ በጠቅላላው የ100 ዘመናዊ በራሪ አይሮፕላኖች ባለቤት ሁኗል። ዛሬ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የማይበርበት የዓለም ክፍል የለም። አንዲት አውስትራሊያ ብቻ ነበረች የቀረችው፣ እሷም ባለፈው ሳምንት በውል ተጠናቀቀች።



From here to here

አየር መንገዱ፣ ከማንኛውም ከበለጸጉት አገራት ባላነሰ፣ ደረጃውንና ጥራቱን የጠበቀ ቴክኒካል ሰርቪስ አለው። ከራሱ አልፎ ተርፎም ቴኪኒካል ሰርቪሱ የሌሎች አገሮች አይሮፕላኖች እየጠገነ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል። ከብዙ አገሮችም ወጣቶች እየመጡ የቴክኒካል ሙያን ይማሩበታል። ያም ሌላው የወጪ ምንዛሪ የገቢ ምንጭ ነው። የራሱ የፓይሌቶች ወይም አብራሪዎች ማሰልጠኛ አለው። እጹብ ድንቅ የተባሉ አብራሪዎቻችን ከዚያ ነው የሚመረቁት። የኔልሰን ማንዴላን መጽሐፍ ያነበበ ኢትዮጵያውያን ፓይሌቶች የመጀመሪያዎቹ አፍሪካውያን አውሮፕላን አብራሪዎች መሆናቸውን መገንዘብ ይችላል። ይኸ ሁሉ ሲኬታማነት የተገኘው በኢትዮጵያ ልጆች ወዝና ላብ ነው። ሌላ ሲከስር አየር መንገዳችን የሚያተርፈው ከሌሎች ሲወዳደር ሠራቶኞቹ ከሌሎች አገሮች ባነሰ ደሞዝ ድንቅ ሥራን ሲሊሚሠሩ ነው። ያ ምንጊዜም መካድ የለበትም።

ሰዶ ማሳደድ ካማረህ ዶርህን በቆቅ ለውጥ አለ ያገሬ ሰው!

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ብቸኛው ተውዳዳሪ የማይገኝለት አትራፊ አየር መንግድ ነው። በየጊዜው የተፈጠሩ፣ እንደ ኢስት አፍሪካን ኤርዌይስ ያሉ አየር መንገዶች ከሥረው ከገቢያ ሲወጡ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያተረፈ ለአገሪቱም የማይደርቅና የማያቋርጥ የውጭ ምንዛሪ የሚያመጥላት ብቸኛው የተሳካለት ድረጅት ነው። እንዲያው በአጠቃላይ ሲነገር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየጊዜው ወርቅ ዕንቁላል የምትጥለውን ዶሮ ነው የሚመስለው። ሥራ “ሀ” ብዬ የጀመርኩት በዚህ ድርጅት ውስጥ ስለሆነ፣ ዛሬም ቢሆን ወገንተኝነት ይሰማኛልና አትፍረዱብኝ።

የኢትዮጵያ ገዢዎች እንደሆኑ የውጪ ምንዛሪ ሁሌ እንዳጠራቸው ነው። በሚሊዮን የሚቆጠር የውጪ ዕርዳታ ቢጎርፍላቸውም፣ ቋታቸው ምንም ጠብ አትልም። ምነው ቢባል፣ ከዚህ በፊት 11 ቢሊዮን ዶላር ገብቶላቸው፣ አስራ አንዱም ቢሊዮን እንዳወጡ አንብበን ጉድ ብለናል። ወያኔ ሥልጣን ከያ ጀምሮ እስከዛሬ ዩኤስ አሜሪካ ብቻ $30 ቢልዮን እንደሰጠች ይታወቃል። ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግን አንዳዲት ቤሳ ቢሲት አልደረሰውም። ለሕዝባችን “40 ቢታለብ ያው በገሌ” ያለችው ድመት ብጤ ነው። እንዳልኳችሁ የኢትዮጵያ ገዢዎች ቋት ጠብ አትልም። በየጊዜው ያው የውጪ ምንዛሬ እጥረት እዬዬ እንደቀጠለ ነው። ማቆሚያ የለውም። ታዲያ ያንን የውጪ ምንዛሪ ጥማት ለመቁረጥ  የኢትዮጵያ ቅርሶች እይተቸበቸቡ አልቀዋል። የዚህ የውጭ ምንዛሪ ጥም የኢትዮጵያ ገዢዎችን ያላስቧጠጣቸው ግድግዳ የለም። Daily Mail የተባለው ጋዜጣ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2010 እንዲህ የሚል ጽሑፍ አስፍሮ ነበር፡

... a corrupt London Police stood to gain 2 million ($3.13 million) by brokering the sale of Ethiopian embassy in London for £24 million ($37.5 million).

የንጉሠ ነገሥቱ ነፍስ በሰማይ ቤት ይማርና፣ ሕንጻው የምማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ አንጡራ ሀብት (Heritage) አድርገው በፍርድ ቤት አስወስነው ስለነበር ሺያጩ ሳይሳካላቸው ቀረ እንጂ ዛሬ የሎንደኑ ኤምባሲአችን 17 Princess Gate መሆኑ ቀርቶ የሆነች ጭርንቁስ ስቶክዌል ውስጥ የኪራይ ቤት ውስጥ ተወሽቆ በተገኘ ነበር።

ይኸው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነበር መሬትን ከገበሬ ቀምቶ ለውጪ ባለሀብቶች በውጪ ገንዘብ (hard currency) መቸብቸብን ያመጣውና መንግሥት ተቢዬውን ከሕዝብ ያጋጨው። የውጪውን ምንዛሪ ቢሰበሰብ ቋቱ እንደሆን ጠብ አይል፣ እንዲያው ምን አለፋቸው!

እስቲ በውጪ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ዛሬ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽ፣ የኢትዮጵያ የንግድ መርከቦች ... ወዘተ ተሸጡ እንበል። የውጪ ምንዛሬዋንም አገኟት። ወያኔ እጅ የገባ የውጭ ምንዛሪና እሳት ውስጥ የወደቀ ቅቤ አንድ ነው። እንደገባ ነው የሚወጣው። ነገም እኮ ያው ነው! ያቺ ስትሟጠጥስ ምን ሊሸጡ ነው? ያች የውጭ ምንዛሪ እንቁላል የምትጥል ዶሮ እንደሆነች የለች። አየርመንገድ ከሌለ ወርቁ ከየት ሊመጣ ነው? 

ሌላም የማይታይ ጣጣ አለ። አንድ ያስተዋልኩትን ምሳሌ ልጥቀስላችሁ። ሪያል ማድሪድ የተባለው የእስፓኒሽ የፉትቦል ቲም የማያውቅ አለ? ሲብዛ ሀብታም ነው። ብዙም ያሸንፋል። የሚገርመው የትም አገር ይሁን፣ የትም ቡድን ውስጥ ኮከብ የተባሉ ተጫዋቾች ሲፈጠሩ፣ እያሳደደ ይገዛቸዋል። ኮከብ በኳክብት የተሞላ ቡድን ነው። አንዱ ዓላማው በነዚህ ኮከብ ተጫዋቾች ተጫውቶ ዋንጫ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ ኮከብ ተጫዋቾች ለሌላ ክለብ ተጫውተው ድል እንዳይነሱት፣ በብዙ ሚሊዮን ዶላር ገዝቶ ከጨዋት ውጪ ማድረግ ነው። ለወራት፣ለዓመታት ቤንች ላይ ያስቀምጣቸዋል። የማንቸስተሩ ዩናይትዱ ኮከብ ተጫዋች ዴቪድ ቤካም ወደ ማድሪድ ተዛውሮ ነው የጨዋታ አኪሩ የጠፋው። የሊቨርፑሉ ማይክል ኦዌን በማድሪድ ተገዝቶ ቤንች ሲያሞቅ ኑሮ ነው ኮከብነቱ የደበዘዘው። ተምልሶም ሰው አልሆነ። በተመሳሳይ ዓላማም ታዲያ ሌሎች የታወቁ አየር መንገዶች፣ እንደሉፍታንዛ፣ ብሪቲሽ ኤርዋይስ፣ አሊታሊያ ያሉት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ገዝተው የራሳቸው ካደረጉ በኋላ፣ የአይር መንገዱን መሥመሮች በሙሉ እጃቸው አስገብተው ከጨዋታ ውጪ ሊያድርጉት እንደሚችሉ ታስቦበት ይሆን? ዶሮ ባትበላ ጭራ ታፈሳለች አሉ አበው።

የኢትዮጵያ መንግስት ልብ ግዛ። የወርቅ ዕንቁላል የምትጠለውን ዶሮህን አትረድ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ  አንድ በድሀ አገር ብቻውን ተመዞ የወጣና በእግሩ የቆመ ድርጅት ብቻ ሳይሆን፣ እንደአትሎቶቻችን ስማችንን በጥሩ ገጽ ያስጠራ ድርጅት ነው። ስኬታማ መሆኑ ሊያስሸጠው ከሆነ ያቺን ያለችንን አንድ ዓይን እንድማጥፋት ነው። በድንብ በጥንቃቄ ይታሰብበት እላለሁ። ባይሆን የአንበሳውን ድርሻ፣ ይኸ በዶክተር ዓቢይ የሚመራው ቡድን ለኢትዮጵያ የሚያስብ ይመስላልና፣ መንግሥት ያስቀረው።

ያለውን የወረወረ ፈሪ አይባልም። ሀሳቤን ወርውሬአለሁ!

1 comment:

  1. በእጅጉ እውነት ነው፡፡ሆኖም የአባት ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ ሆኖባቸው ነው፡፡ኢትዮጵያ ታርዳ ተጥላ ተንጋልላ እንደፍሪዳ በሬ ምነው አይሻሙ ህወሃት ብቻ አይደለም ሁሉም ዘነጠሏት እንጂ፡፤አይደርስ መስሉዋት በቁዋት .......

    ReplyDelete