ሕዳሴ ግድብ፣ ዓባይ፣ ኦርቶዶክሳዊት
ቤተ ክርስቲያን:-እሬትና ማር
ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ
nigatuasteraye@gmail.com
ጥቅምት ፮ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም.
(October 16, 2025)
መግቢያ
ኢትዮጵያ ያቋረጠቻቸው ረዥም ዘመናት በውስጣቸው ያሉት ዓመታት፣ ወራትና እለታት የሚገጥሟቸውን ክስተቶች እየደመሩ የሚሽከረከሩባት
እንዝርት ናት፡፡ እየተሽከረከሩ በመስከረም ወር ላይ በሚገጥሙት ዓውደ ዓመት የሚታወሱ
በዓለት ድርብርቦችና ድምሮች ናቸው፡፡ የመደመር ባህላችንን ተከትሎ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዑደቱን ለመቀጠል ለመጀመሪያ ጊዜ በደመራ ላይ ተደምሮ ብቅ አለ፡፡
በሰውነታችን ውስጥ ያሉት ሴሎች እያንዳንዳቸው የትዝታ መዛግብት እንደሆኑ፡ በኢትዮጵያ ታሪካዊ የሕይወት ጉዞ እያንዳንዳቸው
ቀናት የትዝታ መዛግብት ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ድርብ (ድምር) እንጂ ነጠላ በዐል የልንም፡፡ ኢትዮጵያ ባቋረጠችትባቸው ዘመናት እስከ ግድቡ ፍጻሜ ድረስ ከመሰቀሉ በዐል
ሌሎች በራሱ በደመራ ላይ የተደመሩ ከዓባይ ራቅ ላለው ሕዝብ ያልተገለጹ ብዙ ክስተቶች አሉ፡፡
ኢትዮጵያ ክመከስቷ በፊት የነበረና ኢትዮጵያ ከተከሰተችበት ዘመን ጀምሮ በወገቧ እንደ መቀነት ተጠምጥሞ ይኖር የነበረው
ዓባይ፡ እስከ ዓለም ፍጻሜ ሲከበር የሚኖረውን ታላቁን
የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ደምሮ በዚህ ዓመት ተከሰተ ፡፡ የወገቧ
መቀነት ሆኖ የኢትዮጵያ ሽንጥና ዳሌዋ ሲታይባት የኖረውና የማንነቷ መነበቢያ አትሮኑስ ሆኖ የኖረው ዓባይ የኢትዮጵያን ባሕርይ
ቀይሮ እያስነበበ ብቅ አለ፡፡
ባዓባይ ሲገለጽ የኖረው የኢትዮጵያ ውበት ይነበብበት (ይገለጽበት) የነበረው አትሮኑስ ጎጃም ነው፡፡ “ውሀን ከምንጩ፣ ነገርን ከሥሩ እንዲሉ” ጎጃም ደስታውንም፣ ሐዘኑንም፣
ስሜቱንና ሁለመናውን የሚገልጸው በአባይ ወንዝ (ናይል) ነው፡፡ ስነ ጽሑፉ ግጥሙና ቅኔው ሁሉ የሚመነጨው ከዚያው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከመከሰቷ በፊት
ጀምሮ ግድቡ እስኪፈጸም ድረስ ስለ አባይ የቀረቡት ቅኔወች ፉከራወችና ግጥሞች ብዙ ናቸው፡፡ ሁሉንም አምቆ በመሸከም ሲፈስ የኖረው
የዓባይ ግድብ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲከበር የቀረበው ቅኔ በጎጃም ሊቃውንት ሲታሰብ ስድ ንባብ ሆኗል፡፡
የቀረቡትን ስድ ንባቦች ባደግኩበት የቅኔ ስልት ፈተሽኳቸውና ስሜቴን ዳሰሰኩት፡፡ ካንድ ወጃጄ
ጋራ የተላለፉትን ግጥሞች አንስተን ተነጋገርንና “አንተን በጎጃሙ ቅኔ ተቀኝ ቢሉህ እንዴት ትቀኝ ነበር?” ብሎ ጠየቀኝ፡፡ “እንዴት
ትቀኝ ነበር?” የሚለው ጥያቄ፦ ባንድ ወቅት ካነበብኳቸው መጻሕፍት መካከል ባንድ መጽሐፍ ያገኘሁትን ተመሳሳይ ነገር አስታወሰኝ፡፡
በነገረ መለኮትና በሰባዊ ተፈጥሮ ተማሪወች መካከል:- በወንድና በሴት መካከል ስላለው አካላዊና ስሜታዊ መሳሳብ ውይይት ተጀምሮ
ክርክሩ ጦፈ፡፡ ክርክሩን እንዲዘጋ አንድ ሰው የመቋጫ ሐሳብ ተጠየቀ፡፡ የተጠየቀው ሰው “ከሳይንሱ ማሕጸን ገብቼ ስዋኝ የሴቱን ማሕጽን ረሳሁት
እንጅ በወንድና በሴት መካከል ያለውን መሳሳብ ከኔ የበለጠ የሚገልጸው አልነበረም” ብሎ የሰጠው መቋጫ ትዝ አለኝ፡
የኢትዮጵያ ልጆች እርስ በርስ የሚተላለቁበት፤ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት የሚቃጠሉበት፤ መነኮሳት
ቀሳውስት ሕዝበ ክርስቲያን እየታደነ የሚገደልበት ዘመን ሆኖ በልቅሶና ዋይታ ላይ ተጣደንና ፋታ አላገኝንም እንጅ፦ ዐባይ በሚከበው
በጎጃም ምድር ካልተወለደ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተጠምቆ ካላደገ ሰው ሁለንተና ገላጭ የሆነ ቅኔ የሚጠበቅ አይመስለኝም፡፡ በተስፋ ሲጠበቅ የኖረው የዓባይ ግድብ ፍጻሜ ቢያስደስትም፡
ዓባይ ልጆች ላይ በመካሄድ ያለው ዘግናኝ ጭፍጨፋ በመደመሩ ከጎጃም
ሊቃውንት የሚፈልቀውን ቅኔ እሬትና ማር ያደርገዋል፡፡
ሆኖም “እንዴት ትቀኝ ነበር?” የሚለው ጥያቄ ጭንቅላቴን እረፍት ነሳውና መቁነጥነጥ ጀመረ፡፡ ኢትዮጵያዊት
ቅኔ በድሮው አነጋገር በጨለማ በምትበራ ጧፍ ትመሰላለች፡፡ በዘመኑ አነጋገር በእጅ ባትሪም ልትገለጥ ትችላለች፡፡ የቅኔ ሰው ጧፍ
ወይም ባትሪ ይዞ ወደማያውቀ ጨለማ ቤት የሚገባ ሰው ይመስላል፡፡ ባትሪ ወይም ጧፍ የጨበጠ ሰው ወደማያውቀው ጨለማ ቤት ሲገባ
በቤቱ ውስጥ ተካቶ ያለውን ሁሉ ያያል፡፡ በጨለማው ተጋርዶ ማየት ለተሳነው ያሳያል፡፡ የቅኔ ሰውም በወቅትና በኩነቶች ተጠቅልለው
ተፍታተው ለሰሚ ወዳልቀረቡት ሐሳቦች የሚገባው፦ ለማየትና ለመስማት ጉጉት ላለው ሰው ለማሳየትና ለማሰማት ነው፡፡ ለማየትና ለመስማት
የሚጓጓ ሰው ከሌለ ለማነው የምቀኘው? ብሎ ማሰቡን ይተዋል፡፡ እኔም ! ይቅርብኝ! ብየ ልተወው ሞከርኩ፡፡
በኢትዮጵያዊው ቅኔ ስልት የተገራ ጭንቅላት ያየውን ላለመግለጽ አፍኖ መያዝ አይችልም፡፡ ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል፡፡ እንዳልተገራ
ግልገል ፈረስ ይቁነጠነጣል፡፡ በሚቁነጠነጠው ጭንቅላቴ በደመራ ላይ ተደምሮ ስለተከበረው የዐባይ ግድብ የቀረቡትን ግጥሞችና ስድ ንባቦች እንደገና ልቃኛቸው ግድ ሆነብኝ፡፡ ጠቅላይ ምንስቴር ዐቢይ አሕመድ በመደመር ርዕስ
አቀናብረው በተደጋጋሚ ባቀርቧቸው መጻሕፍት ላይ በተለያዩ ተችወች የተሰጡትን የምርምር ትችቶችንም ሰማሁ፡፡ መጻሕፍቱን አግኝቼ ባላነባቸውም
በጥልቅ ትኩረታቸው ያነበቧቸው ሰወች ባቀረቧቸው ትችቶች አማካይነት የመጻሕፍቱን መንደርደሪያ በመጠኑ ተረድቻለሁ፡፡ በጎጃሞች ላይ
ለሚከሰቱት ደግና ክፉ አጋጠሚወች መገለጫና የስነ ባሕርያትም መተርጓሚያ ሆኖ በየደብሩና በየመንደሩ ሲነገሩ የኖሩ ናቸው፡፡ መደመርም
በታሪካችን፣ በባህላችን በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናችን እንግዳ አይደለም፡፡
የውጭ ወራሪና የውስጥ ተቀጣሪ ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ ሲበትኗትና ሲከፋፍሏት አባቶቻችን መልሰው ሲገነቡባቸው ከነበሩት
እሴቶቻችን መካከል መደመር አንዱና ዋናው ነው፡፡ ጠ/ ምንስቴሩ ነባራዊ እሴትነቱን ሳያሳዩ አዲስ ፍልስፍና አድርገው ማቅረባቸው
እሴቶች እንዲዘነጉ ከተደረጉባቸው ብዙ አዘናጊወች አንዱ የሆነ ስለመሰለኝ በጠቅላይ ምንስቴሩ የቀረበው መደመር “እሬትና ማር” ሆኖብኛል፡፡ መደመርን ጠ/ ምንስቴሩ ከገለጹበት
መንገድ ለየት ያለውን አዘግይቼ፦ በኢትዮጵያውያን እይታ ለማቅረብ ኢትዮጵያን ባጭሩ ገልጬ በሁለት ጡቶች ስለ ተገለጹት ስለ ኦርቶዶክስ
ቤተ ክርስቲያንና ዐባይ ከዚህ በታች ለማቀረብ ሞክሬአለህ፡፡
ኢትዮጵያ
አባቶቻችን የዓባይን ተፈጥሯዊ ቀዳሚነቱን ሳይረሱ በንግግራቸው ሁሉ ከዓባይ በፊት የሚያስቀድሟት ኢትዮጵያን ነው፡፡
ምሳሌ አርገው የሚከተሉት ጌታችን ክርስቶስ በተወለደበት ጊዜ በበረት የተከሰተውን ነው፡፡
የሰማይ ሠራዊት ከሰማይ የወረዱት መለኮቱን ተከትለው እንጅ ሥጋውን በመከተል
አይደለም (ሉቃ 2፡13)፡፡ ምድራውያን እረኞችም ክርስቶስን በበረት ያዩት በሥጋው እንጅ በመለኮቱ አይደለም፡፡ የጥበብ ሰወችም
ያዩት እመቤታችንና ሰውነቱ በግርግም ተኝቶ፣ ተጥቅልሎ ነው (ማቴ 2፡7-12)፡፡
የቀደሙ ሊቃውንት አባቶቻችን ምድራውያን
እረኞችንና የጥበበ ሰወች ምሳሌ በማድረግ ከክርስቶስ በፊት የሚገልጿት ቅድስት ድንግል ማርያምን ነው፡፡ ይህን ምሳሌ በመከተል ዓባይ
ከኢትዮጵያ ቀድሞ ቢታወቅም አስቅድመው የሚናገሩት ስለ ኢትዮጵያ ነው፡፡
እኔም ከዓባይ በፊት ኢትዮጵያን የሚገልጽልኝ
ምሳሌ ስፈልግ “እናንት የኢየሩሳሌም ቆነጃጅት እኔ ጥቁር ነኝ ግን ከሁላችሁም የተዋብኩ ነኝ” (ማሕ 1፡5)
እያለች በዐለም አደባባይ ራሷን ስትገልጽ የኖረችውን ኢትዮጵያን በማሕሌት ሲራክ ደምግባት አየኋት፡፡ እንደ ጠመኔ ያልገረጣ፤ እንዳረረ
ከሰል ያልጠቆረ እንደ ጎመራ የወይን እሸት ከሩቅ በሚጋብዘው ደም ግባቷ ማሕሌት ሲራክ ኢትዮጵያን ገለጥችልኝ፡፡
በቅኔ ትምህርታችን ያለባለቤቱ ፈቃድ ሰውን መጥቀስ ይቅርና የሰውን ሐሳብ
ሳያስፈቅዱ ከራስ እንደወጣ አርጎ መናገር ስሕተት ነውና የኢትዮጵያዊቷን ሱላማጢስ አባት ፈቃዳቸውን ጠየኳቸው፡፡
የማሕሌት አባት ኢትዮጵያንና ኦርቶዶክሳዊት
ቤተ ክርስቲያንን “አንች ውብነሽ በዐይነ ርግብ መሸፈኛሽ ውስጥ ዓይኖችሽ እንደ ርግብ ናቸው” (ማሕ 4፡1) እያሉ ሲያወድሱ ያደጉ ያቋቋም
መምህር ናቸው፡፡ ለሚወዷቸው ለሁለቱም ለኢትዮጵያና ለቤተ ክርስቲያናቸው የሚያቀርቡትን ውዳሴ ከአብራካቸው በፈለቀችው ማህሌት የደመደሙ
ያቋቋም መምህር የሰሎሞን ምክሼ ሲራክ ናቸው፡፡ “መኃልየ መኃልይ” ማለት የዜማወች መደምደሚያ የመጨረሻው ጽንፍ ማለት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ካሉን
ማሕሌቶች በላይ ስሜት የሚቀሰቅስ በእንቅስቃሴና ውዝዋዜ ተመስጦ የሚቀርብ አቋቋም የሚባለው ክፍል ነው፡፡ የማሕሌትን አባት የጠቀስኳቸው
ማሕሌት ብቅ ስትል የማናት በሚል አነጋገሪያነቷ እንደማይቀርና ተመልሶ እንዳይመጣብኝ ለመግታት ብየ ነው፡፡
በማህሌት ሲራክ የገለጽኳት ኢትዮጵያ
የአካሏ ቅርጽ እስከተዛባበት ስሟ እስከተዘነጋበት እስከ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ዘመን ድረስ የነበሩት ጥንታውያን የቅኔ ሰወች አንች ሱላማጢስ “ቁመናሽ እንደ
ዘንባባ ዛፍ መለል ያለ ነው፡፡ ጡቶችሽም እንደ ወይን ዘለላ ይመስላሉ”( 7፡8) እያሉ ሲቀኙላት ኖረዋል፡፡ ሻብያና ወያኔወች ቁመናዋንና ቅርጿን እስኪቀይሩባት ድረስ “እኅቴ ሙሽራየ
የታጠረች የአትክልት ቦታ ዙሪያዋ የተከበበች ምንጭ የታተመችም ፏፏቴ ነሽ”(ማሕ 4፡12) እያሉ አወዳድሰዋታል፡፡ የቀርብ አባቶቻችን እነ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፡
እነ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬም “ሁለቱ ጡቶሽ መንታ እንደተወለዱ በሱፍ አበባ መካከል እንደሚሰማሩ
እንደ ሚዳቋ ግልገሎች ናቸው” (ማሕ 4፡5)
እያሉ ኢትዮጵያን የገለጹባቸው ቅኔወቻቸው በታላላቅ አድባራት በደብረ ኤልያስ፣ በዲማ፣ በብቸናና
ደብረ ሊባኖስ ገዳም መምህራን እየተነገረን አድገናል፡፡
የሰባዊ ተፈጥሮን ውበት መግለጫ ሰምና
ወርቅ ቅኔያችን የሚያስደንቅ ነው፡፡ በሚያስደንቀው ቅኔያችን የለሴቶችን
ወርቅነት የምንገለጻባቸው ሰሞች ብዙ ናቸው፡፡ ሴቶች በውርቅነት የሚገለጡባቸው በደረታቸው የበቅሉት ሁለቱ ጡቶቻቸው
ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ቁንጅና ለመግለጽ ዓባይንና ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን በኢትዮጵያ ደረት ላይ የበቀሉ ሁለቱ
ጡቶች ብለዋቸዋል፡፡ ዓባይና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ደረት ላይ የበቀሉ የማይነጥፍ ወተት በማምንጨት
የማይነጥፈውን ተተካኪ ትውልድ የሚያጠቡ ናቸው፡፡
ከላይ እንዳልኩት ምንም እንኳ ዐባይ በተፈጥሮ ቀዳሚ ሆኖ ኢትዮጵያን ቢቀድማትም፦
ልጇ ከፈጠራት በኋላ ከሱ በሥጋ ቀድማ የታየችው ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ በሰምና ወርቅ ቅኔያችን አባይንና ኦርቶዶክሳዊት
ቤተ ክርስቲያንን እያስከተልን ኢትዮጵያን በማስቀደም ሳንዳስሣት የምናልፋቸው እለቶችና ቅኔወች ጥቂቶች ናቸው፡፡
በመጽሐፈ መኃልይ ከሱላማጢስ ጋራ
የተጠቀሱት ሶስቱ፦ ሚዳቋ፡ ግልገሎቿና የሚፈነጩባቸው የሱፍ አበባወች
የኢትዮጵያን ሁለንትና የሚገልጹ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የሰው አገር እያደኑ በሚውጡት ቅኝ ገዥወች ተከባ መኖሯን ለመግለጽ በአራዊት እየታደነች ምትበላዋ ሚዳቋ ሲገልጿት ኖረዋል፡፡ ግልገሎቿ የሚፈነጩባቸው
የሱፍ አበበች የተባሉትም በዓባይ ተፋሰስ አካባቢ የሚኖረውን ተተካኪውን ትውልድ ይገልጹበታል፡፡ በሁለቱ ጡቶቿ ዐባይንና ኦርቶዶክሳዊት
ቤተ ክርስቲያን ይገልጿቸውል፡፡ አንዱ ጡት ጠልና ልምላሜ አመንጭ የሆነው ዓባይ ሲሆን፦ ሁለተኛይቱ የውበት መግለጫ ቅኔ፤ ስነ ጽሑፍና ሙዚቃ ስታመነጭ የኖረችውን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን
ናት ይላሉ፡፡
ሁለቱ ጡቶች:- ዓባይና ኦርቶዶካዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን
የኢትዮጵያ ተክለ ሰውነት ውበት ከላይ በተገለጸበት አንቀጽ ላይ ለረዥም ዘመናት ሲጥቀሱ የኖሩት ዓባይና የኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ ሁለቱም በኢትዮጵያ ደረት ላይ የበቀሉ የማይነጥፍ ወተት በማምንጨት የማይነጥፈውን
ተተካኪ ትውልድ የሚያጠቡ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በማይነጥፉት በሁለቱ ጡቶቿ በሩቅና በቅርብ ያሉትን ስታጠባ ኖራለች፡፡ ባንዱ ጡቷ
(ዓብይ )ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉትን ሱዳናውያንና ግብጻውይንን የመሳሰሉትን በጠለልምላሜ እያጠባች፦ በሌላዋ ጡቷ (ኦርቶዶክሳዊት ቤተ
ክርስቲያን) በጉያዋ ያሉትን ኢትዮጵይውያንን በቅኔዋ በስነ ጽሑፏ ስታጠባ ኖራለች፡፡ የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንን ጡትነት
ከዐባይ ጡትነት በማስቀደም ከዚህ በታች ለመግለጽ እሞክራለሁ፡፡
ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በሚዳቋ ግልገሎች ከተገለጡት ከሁለቱ ኢትዮጵያ ጡቶቿ አንዷ ናት፡፡ “የታተመች ምንጭ ፏፏቴ ነሽ” ተባለች፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን፣
ቅኔውን፣ ስነ ጽሑፉን የትወልዱን ስሜት በመመገብ ላይ ያለው ለአራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች:- አንቺ ሆየ፣ ባቲ፣ ትዝታና አምባሰል
የፈልቀባቸውን ያሬዳዊ ዜማ ያመነጨች ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን በግዕዙ ቋንቋችንና ፊደላችን ትውልድ የሚቀባበለውን ታሪካችንን፣ እምነታችንን
ባህላችንን የምታፈስ በኢትዮጵያ ደረት ከበቀሉት አንዷ ጡት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን ናት፡፡
በሙዚቃ ትምህርት ርቀው የዘለቁት ሊቃውንት እንደሚሉት የኢትዮጵያ የዘፈን አይነቶች ባንቺ ሆዬ፡ በትዝታ፡ በአምባሰልና
በባቲ በአራቱ ቅኝቶች የተመሠረቱት በቤተ ክርስቲያን ዜማወች ቁሜ፣ አጫብር ፣ቤተ ልሔም በሚባሉት ላይ ነው፡፡
የቤተ መቅደሱ ሰለልኩላ ደብር ዐባይ የሚባለው የቅዳሴ ዜማ ሌላው ማእዘን ነው፡፡ ከላይ የተገልጸው አቋቋም የሚባለው አራቱን ማለትም፦
ተክሌ፡ ጎንደር፡ ሳንኳና ፋኖ
የሚባሉትም ለዓለማውያን ሙዚቃወቻችን (አጣፋጮች) ቅላጼወች ናቸው ይሏቸዋል፡፡ የራሳቸውን እምነት ይዘው ከውጭ የመጡት
የሃይማኖት ሰባኪወች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የራሳቸው ዜማ ጥለው ነው፡፡ ስብከታቸውን
ከራሳቸው አገር ዜማ ሳይነጥሉ ቢመጡ ኖሮ የሚከተላቸው ኢትዮጵያዊ አይኖርም ነበር ይላሉ፡፡
መናፍቃን (ከፋፋዮች) የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ጥሰው በገቡባቸው ወቅቶች ሁሉ እነ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ “እኔ ተኝቻለሁ ልቤ ግን ነቅቷል” (ማሕ 5፡2) እያሉ የመከላከያ መልዕክት ያስተላልፉ
ነበር፡፡ ይህ የኛ ዘመን ነቢዩ ኤርምያስ የነበረበትን ዘመን ይመስላል፡፡ የሀገሩ ጠላቶች የትውልድ አገሩን ለማፍረስ አጋጣሚ እድል
ሲጠብቁ ኖረው እድሉ በገጠማቸው ጊዜ “ጠላቶሽ ሁሉ በአንድ ላይ አፋቸውን በኃይል ከፈቱ፡፡ ጥርሳቸውንም
አያፋጩ ውጠናታል! የናፈቅነው ጊዜ ይህ ነበር፡፡ ኖረንም ልናየው ነው”(ሰቆቃ ኤር 2፡16) አሉ ብሎ ኤርምያስ የተናገረው በኢትዮጵያ ላይ የደረሰ ይምስላል፡፡
የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለመበታተን ሲጠብቁ የኖሩ ጠላቶች ግማሾች ቆቡን እየለበሱ ወደ ውስጥ በመግባት፡ ግማሾቹ
ቆቡን ሳያወልቁ ከውጭ ሆነው በተሐድሶ ጎራ ተሰልፈዋል፡፡ “በአንድ ላይ አፋቸውን በኃይል ከፈቱ” እንዳለው ነገረ መለኮቱንና ነገረ ማርያም ያልተረዱ ከባእድ ከወረሱት ስህተት ጋራ
ቀላቅለው በድፍረት ለመናገር ታጥቀው የተሰለፉበት እንደዚህ ዘመን የከፋ ዘመን ቤተ
ክርስቲያናችንን ገጥሟት የምታውቅ አይመስልም፡፡
ነቢዩ ኤርምያስ “ጠላቶችም ሆኑ ወራሪወች የኢየሩሳሌምን በሮች ጥሰው ይገባሉ” እንዳለው፦ ከፓትርያርኩ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያናችንን ቀኖና ነገረ መለኮት ሳይጥስ
የገባ ማን አለ? “ከነብያት ኃጢአት፣ ከካህናቷም መተላለፍ የተነሳ ሆኖአል” እንዳለውም ከፓትርያርኩ እስከ ተላላኪው
ድረስ በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ በደልና ክህደት ያልፈጸመ ማን አለ? “በውስጧ የጻድቃንን
ደም አፍሠዋል”(ሰቆ 4፡13)፡፡ እንዳለውም አሁን ያሉት ጳጳሳት በአርሲ፣ በባሌ፣ በወለጋ፣ በሐረር፣ በሸዋ፣ በጎጃምና
በወሎ ለፈሰሰው ደም በዝማታቸው የተሳተፉበት እንደዚህ ዘመን የከፋ
ዘመን ቤተ ክርስቲያናችንን ገጥሟት ያውቃል? ከዚህ ቀጥየ ፏፏቴ ወደ ተባለችው ሁለተኛዋ ጡቷ ወደ ዓባይ እሻገራለሁ፡፡
ዓባይ
ከላይ እንደጠቀስኩት በነገረ መለኮትና በሰባዊ ተፈጥሮ ተማሪወች መካከል የተነሳውን ክርክር እንዲዘጋ የተጋበዘ ሰው
“ከሳይንሱ ማሕጸን ገብቼ ስዋኝ የሴቱን ማሕጽን ረሳሁት እንጅ በወንድና በሴት መካከል ያለውን
ፍቅር ከኔ የበለጠ የሚገልጸው አልነበረም”
እንዳለው፦ ስለ ዓባይ ሲነሳ በሊቃውንቱና በባለአገሩ
ይነገር የነበረው ሁሉ ትዝ አለኝ፡፡
የሕዳሴው ግድብ የወገንን እልቂት ለማይመለከቱ ወገኖች ደስታቸውን እጥፍ ድርብ አድርጎላቸዋል፡፡ አታሞዋን ይዛ በዐባይ
ግድብ መደሰት የነበራባት ጎጃሜዋ እናት ነበረች፡፡ ዳሩ ምን ያድርጋል ግድቡ ሲፈጸም፣ የልጅ አባቷ ሞቶ፣ ልጇ በመከላከል ላይ
ሆኖ ቤቷ ፈርሶ በልቅሶ ላይ መሆኗ “የዐባይን እናት ውሀ ጠማት” ሲባል የኖረው ትንግርት የተፈጸመበት
ይመስላል፡፡
የዓባይ ተፋሰስነት እንደ አራቱ ወቅቶች ተለዋዋጭ ነው፡፡ በበጋ፣ በክረምት፣ በመጸውና በጸደይ የፍሰቱን ጠባይ ይቀያይራል፡፡
ከላይ የዝናም ከታች የጎርፍ ማእበል በሚበረታበው በክረምት ይቆጣል፤ ይደፈርሳል፡፡ የዓባይን ውሀ የሚጠጡ ጎልማሶች ወቅቱን ተከትሎ
እንደሚቀያየረው እንደ ዐባይ በኢትዮጵያ ላይ ክፉ ዘመን ሲከሰት፣ የውጭ ወራሪወች የውስጥ ባንዳወች መከራ ሲያከብዱባቸው ሕይወታቸው
ይደፈርሳል፤ ኑሮ እንደ እንቆቆ ይመራል፡፡
“አባይ ሲደፈርስ
ሲመስል እንቆቆ
ጋሬጣው ጎጃሜ
ገባ ባጭር ታጥቆ” የተባለው የዘመናችንን አደፍራሽ ለመግለጽ
ነው፡፡ መንደሩ ፈርሶ፣ ህዝቡ ታምሶ ሳለ ባጭር ታጥቆ ለመከላከል ከተሰለፈው ከጋሬጣው ፋኖ ጎን ከመሰለፍ ይልቅ በመወላወል
ላይ ያለውን ፈሪ፦ “ማደሪያ የሌለው ዐባይ ግንድ ይዞ ይዞራል” እየተባለ ተገስጾበታል፡፡
ወራሪ ጠላት ድንብር ጥሶ ዓባይን ተሻግሮ ሲመጣ “አባይም ቢሞላ፡
መሻገሪያው ሌላ” እያለ ከውጭ የሚመጣ ጠላት ባልጠበቀበት ኬላ በመጋረጥ ኢትዮጵያን ያሻግራታል፡፡ ጠላት ከየአቅጣጫወች ከበባ ሲጀምር፦ ምንጩን በመጋራት እየጠጡ ያደጉ
ጎልማሶች እርስ በርሳቸው ይጠራራሉ፡፡ የጎጃም ፍኖ ለጎንድር፣ ለሸዋና ለወሎ ፋኖወች ጥሪ ያስተላልፋሉ፡፡ የጎንድር የወሎ የሸዋ
ፍኖወች ደግሞ ለሚያዋስኗቸው ኢትዮጵያውያን ጥሪውን ያቀበላሉ፡፡
“ካባይ ወዲያ
ማዶ አንድ ሰው ተጣራ፣
ወዲህ ማዶ
ሆኖ አንድ ሰው አቅራራ፣
ወዲህ ማዶ
ሆኖ ሌላ ሰው ወይ አለው፣
ጎበዝ ተጠንቀቁ
ይህ ነገር ለኛ ነው።” የተባለውም የመላ ኢትዮጵያንን የርስ በርስ ጥሪ ለማንጸባረቅ ነው፡፡ በየዘመናቱ ኢትዮጵያን ፈታኝ ቀን
ሲገጥማት ፈሪና ጀግና ተለይቶ የሚታወበት ነው፡፡ ፊሪው ፈርቶ ሲርበተበትና ወደ ኋላ ሲያፈገፍግ፡ ደፋሩ እየፎከረ ይገባበታል፡፡
ይህን ለመግለጽ፦
“ፈሪ ሲርብርተበት
ተጠቦ ተጨንቆ፣
ያባይ ልጅ
ጎጃሜው ሄደበት ሰንጥቆ” ተብሎ ተዘፈነለት፡፡
ፈሪና ደፋር አብረው ተስልፈው ፈሪው ሸሽቶ ይሮጣል ይፈረጥጣል፡፡ እንደ በላይ ዘለቀ ያለው ጀግና በጀግንነቱ በመዝለቅ
ድልን ይቀዳጃል፡፡ ይህንን ለመግለጽ፦
“ያኛው ቁልቁል
ሲሮጥ ፈር እየለቀቀ፣
ዐባይ ያሳደገው
ያ በላይ ዘለቀ።”
ተብሎ ተዘፈነለት፡፡
የበላይ ቅኔ ጀግንነት ነው፡፡ የበላይን ጀግንነት ያልተለማመደ ባንዳውን መቋቋም አይችልም፡፡ በባንዳ ይሸነፋል፡፡ ይህን ለማመልከት፦
“መቀኘት ካቃተው
የበላይን ቅኔ፣
ባንዳን ለማሸነፍ
አያገኝም ወኔ።” የሚለው ተዘፈነ፡፡ የጎጃም ቆነጃጅቶችና
ድረገቦች በላይ በመፋለም ሳለ በሸሸቱ ወንዶች ላይ፡
“ፈርተህ አትንሳፈፍ
እንደ በሀር ኩበት፣
እንደ ዘለቀ
ልጅ ፎክረህ ግባባት።” ብለው ዘፈኑ፡፡
ወንድ ልጅ ለአገሩና ለወገኑ መከታም
ጋሻም ነው፡፡ በመከታነቱና በወንድነቱ ካልተጠቀመበት
“በወንድነቱ
ወንድ ካልተጠመቀበት፣
ላኩት ወደ
በረት አበት ይዛቅበት።” ተብሎ ይዘፈንበታል፡፡
ጀግኖች በመዋደቅ ላይ ሳሉ መሰለፉን
ትቶ መንደር ለመንደር እየዞረ በሚሰርቀው ዘራፊ ላይም
“የበላይን
ቅኔ መቀኘት ካቃተህ፣
ዘራፊ እንዳትሆን
ተጠንቀቅ አደራህ።” ተብሎ ተዘፈነበት፡፡
ከላይ የተገለጹት ግጥሞች የሚገልጹት ያባይን ምንጭ እየጠጡ እየዋኙ በመከራ በደስታ ዘምን ያቋረጡትን አሁን በመሞትና
በመከላካል ያሉትን ነው፡፡ ከምንጩ ራቅ ብለው የተወለዱ በገባር ወንዞች አማካይነት ለዓባይ ግድብ ባእዳን ባይሆኑም እንደ ጎጃሞች
ፉከራውና እስክስታው ፦
“አሳ አበላሻለሁ ዓባይ ዳር ነው ቤቴ፣”
ደሮ መረቅማ
ክወዴት አባቴ።”
ኢያሉ በመዝፈን ሊያደምቁት አይችሉም፡፡
ዓባይ እንደ አራቱ ወቅቶች ተለዋዋጭ ነው፡፡ በበጋ በክረምት በመጸው በጸደይ የፍሰቱን ጠባይ ይቀያይራል፡፡ በክረምት
ከላይ የዝናም ከታች የጎርፍ ማእበል ሲበረታ ይቆጣል፡፡ ይደፈርሳል፡፡ የዓባይን ውሀ የሚጠጡ ጎልማሶች ወቅቱን ተከትሎ እንደሚቀያየረው
እንደ ዐባይ ይቀያየራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ላይ የመከራው ደመና ሲያንዣብብ የማእበሉ ክብደት ሲያይልባት የጎጃም ጎልማሶች ስሜት ይደፈርሳል፡፡
ሕይወት እንደ እንቆቆ መራራ ይሆንባቸዋል፡፡ ያንዣበባቸውን መሪር
አገዛዝ አሸንቅጥረው ለመጣል ወስነው ይሰለፋሉ፡፡ ይህን ቆራጥ ውሳኔ ለመግልጽ
“አባይ ሲደፈርስ
ሲመስል እንቆቆ፣
ጋሬጣው ጎጃሜ
ገባ ባጭር ታጥቆ።” ብሎ ባለቅኔው ተቀኘ፡፡
የዐባይ ምንጭ አሳ እንጅ ባህርዩን
ቀይሮ ለመታረድ አንገቱን የሚሰጥ ዶሮ አይታቀፍም፡፡ ያባይ ዳር ልጆችም ከመጣው ሁሉ ጋራ በመተባበር ራሳቸውን ቀይረው ለጠላት
የሚታረድ ዶሮ አይሆኑም፡፡ ይህን ለመግለጽ
“አሳ አበላሻለሁ
ዓባይ ዳር ነው ቤቴ፣”
ደሮ መረቅማ
ክወዴት አባቴ።”
የተባለው ተዘፈነ ይባላል፡፡
ጎጃምን በሚያዋስኑት ካዓባይ ወዲህና ወዲያ ማዶ በሚባሉት ሸለቆወች ባሉት ብዙ ገዳማት አድባራትና መስጊዶች ኢትዮጵያውያን
ሲቀበሩ ኖረዋል፡፡ ዓባይ ሲያስገብራቸው በኖሩት በ14 ገባር ወንዞች በመላ ኢትዮጵያ ሲቀበሩ የኖሩትን ሁሉ ዐባይ እያጋዘ ለሱዳንና
ለግብጽ በማቀበሉ “ዘራፊ” የሚል የቅጽል ስም ነበረው፡፡
“እናት ኢትዮጵያ
የገባቸው እዳ፣
ስትወቀስ ኖረች
ዘራፊ ልጅ ወልዳ።” እየተባለች ኢትዮጵያ
በጎጃሞች ስትወቀስና ስትከሰስ ኖራለች፡፡ የሰው ዘር መኖር ከጀመረበት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሲቀበሩ የኖሩትን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ግድቡ ተፈጽሞ በቆላ በደጋ የተቀበረው
ሰውነታችንን ዓባይ ማጋዙን እስኪያቆም ድረስ በቅኔያችን እይታ በሕይወት ስንኖር እንጅ ስንሞት ኢትዮጵያውያን አልነበርንም።
በምንጭነቱና በፈሳሽነቱ የጎጃሞች ባህርይ ሲገለጠበት የኖረው ዓባይ ሲገደብ፡ ምንጩን እየጠጡ ባደጉትና ኦርቶዶክሳዊት
ቤተ ክርስቲያን ባጠመቀቻቸው ልጆች ላይ አሁን ዛሬ እየተፈመባቸው ያለው ጭፍጨፋና መታረድ ባይኖር ኑሮ፡ አሁን ከቀረበው ዲስኩር
ይልቅ የመጠቀ የረቀቀ ቅኔ ይቀርብበት ነበር፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል! በዓባይ ልጆች ላይ ስደቱ መፈናቀሉ መገደሉና መታረዱ በሚፈጸምበት
ወቅት ስለ መደመርም ስለ ግድቡም ሲነገርና ሲተረክ የተሰማው ሁሉ “እሬትና ማር” የተቀላቀለበት ባዶ ዲስኩ ሆነ፡፡
በሕዳሴው ግድብ እንደማነኛውም ተወላጅ ደስ ብሎኛል፡፡ በጠ/ ምንስቴሩ የቀርበው የመደመር ፍልስፍና ግን፦ የነበሩትን እሴቶች እንዲሸፈኑና
እንዲዘነጉ ከተደረጉባቸው ብዙ አዘናጊወች አንዱ ስለመሰለኝ በግድቡ ደስ ቢለኝም እሬትና ማር
ሆነብኝ፡፡ ጠ/ምኒስቴሩ በዲስኩራቸው ሊነኳቸው ያልደፈሯቸውን
ኢትዮጵያ ስትደመርበት የኖረችባቸውን እሴቶች ለመግለጽ ባዘጋጅኋት ጦማር እንገናኝ፡፡
ይቆየን
No comments:
Post a Comment