Tuesday 17 April 2012

የፋሲካ ለታ!


             (ለሜትር አርቲስት የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ መታሰቢያ - ከመኰንን ወዳጄነህ
ወገኖቼ ሁሉ፣ ለዚህ ታላቅ በዓል፣
እንኳን ደረሳችሁ፣ በሰላም በጤና፣
ሁሉም የሚታየው፣ በመኖር ነውና!!

አንደናንተ እንደኔ፣ ትናንት የነበሩት፣
በሁዳዴው ታመው፣
በሕማማቱ አርፈው፣
በቅዳሜሹር ለት፣

አፈር የቀመሱት፣ጌታቸውን መስለው፣
ጌታቸው ሲነሳ፣ እሱን ተከትለው፣
ይነሱ እንደሁ ብዬ፣ ሊቀ ጠቢባኑ፣ አርቲስት አፈወርቅ፤
ለቅሶኛው ሲመለስ፣ከቤቴም  ሳልዘልቅል፣
ጦሜንም ሳልፈታ፣ ሁዳዴውም ቢያልቅ፣
የፋሲካ ለታ፣ መቃብራቸውን፣ ዋልኩኝ ስጠብቅ። 
እንዲህስ ማደረጌ፣  መላው ቢጠፋኝ ነው፣
አቻ የለው ሆኖ፣ በፈጠራ ሥራው፣
ነጐድጓድ ተብሎ፣ ሙሉ ዓለም ቢያደንቀው፣
ተስኖኝ አይደለም፣በልማድ ሳላውቀው፤
ሸክላው አካላችን፣እንዲፈርስ በጊዜው።
የሰው ልጅ ጉብዝናው፣ ብርታቱ እሚታየው፤
ከፈጣሪው ሳይሆን፣ እውቀቱን ከሰጠው፣
ከመሰሉ ሰው ጋር፣ ፍልሚያ ሲገጥም ነው።
ተማርልን ብለው፣ከሰው መሃል መርጠው፣
ፈረንጅ አገር ልከው፣ አላፈሩበትም፣ ኮሩ በምርጫቸው፣
ትዛዝ አክባሪ ነው፣ ጽኑ ነው መንፈሱ፣
አልነገራቸውም፣ ፎቅ አይቼ መጣሁ፣ ብሎ ለንጉሡ፣
እንደተጠበቀው፣ ጥበብ ቀስሞ መጣ፣በቡሩሽ በርሳሱ።

ቧልተኞች ልጅ የለው፤ ብለው ሲያናፍሱ፣
ባለም የታወቀ፣ ልጅ ወለድን ብለው፤
እናትና አባቱ፣ እንዳልነበር ኮርተው ፣
አንደ ‘አደይ አበባ’ እጅግ የተዋቡ፣ መንፈስ የሚያድሱ፣
ደመግቡ ልጆች፣  እማይሞቱ እንደሱ ፣እንደሱ እማይፈርሱ።
የ መኝታ ቤቱ፣ ስላነሰ ቁጥሩ፣
ባለማችን ዙሪያ፣  በየመዘክሩ፣ አዳራሽ የሚያድሩ፣
እጅግ ብዙ ልጆች፣
ባእምሮው አርግዞ፣ በጣቶቹ ወልዶ፣በለጣቸው እሱ፣

ደህና ሁን አፈወርቅ፣
ገናና ታሪኳን፣ይበልጡን ለማድመቅ፣
 ‘እማማዬ’ ኢትዮጵያ፣ብለህ እያሞገስህ፣
ስትስላት፣ ስትኩላት፣ ባቻምየለው ጣትህ፣
የኖርክላት አገር፣ አፈሯ ይቅለልህ፤

የወገንክን ሕይወት፣ ምስጢር የቋጠረ፣
አላመች ብሎት፣ ሰሌዳ እየጫረ፣እየሞነጨረ፣
ልግባ ልውጣ እያለ፣ ሲታገል የኖረ፣
ያልጨረስከው ሥዕል፣ በውጥን የቀረ፣
ቁጭቱ አንገብግቦህ፣ቆሽትህ እያረረ፣
ባዲሱ ‘ቪላ አልፋ’፣ ብቻህን ቁጭ ብለህ፤
ታነባ እንደሆነ፣እየባባ  ሆድህ፣
እማማ ኢትዮጵያ፣ በጉያዋ ይዛ፣
እሹሩር ትበልህ፣ታጽናናህ፣ ታበርታህ።

እኔ እንደሚመስለኝ፣አንተ ጨርሰሃል፣ አብቅቷል ወር-ተራህ፣
ባይሆን፣  ይቺ እናትህ፣ ሊበልጥህ ባይበቃ፣ የሚስተካከልህ፣
ጣተ መልካም ህጻን፣ ወልዳ ትተካልህ።
መንገደኛው በዝቷል፣ዘንድሮስ ለጉድ ነው፣
አያጣም አንግዳ፣ እንዳንተም ያለ ሰው ።
ነጎድጓድ አፈወርቅ፣ስዕላዊ ትዝታህ፣
እስካለን ይኖራል፣ ባእምሮችን ጓዳ፣
እንደብጤታችን፣ እኛን ተወንና፤
ይልቅ አዲሱን ቤት፣ አርገው ቀባ ቀባ፣ አርገው ሰንዳ ሰንዳ!
______________________________________________________________________
ሚያዚያ 2 ቀን 2004 ዓመተ ምሕረት ክዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት ለሜትር አርቲስት የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ወርቃማ የፈጠራ ሥራ ዘመን መታሰቢያ።         
 Other precious works of Makonnen Wedajeneh can be fiewed at: