Friday 4 May 2012

የዋልድባ መነኮሳት እሪታ በለንዶን ተስተጋባ


ከወንድሙ መኰንን፣ ለንዶን ግንቦት ፳፬ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም
በዛሬው ዕለት፣ ኢትዮጵያውያን፣ ከጎንደር፣ ከጎጃም፣ ከወሎ፣ ከሸዋና ከሌሎቹም የኢትዮጵያ ክፍላተ አገር ወደ ዋልድባ ሲተምሙ፣ በለንዶን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ካህናትና ምዕምናንም ደግሞ ወደ ብርቲሽ ፓርሊያመንት በመጉረፍ የምነኮሳትን እሪታ በጸሎት፣ በዝማሬ እና መፈክር በማሳማት አስተጋብተዋል። 

ዋልድባ፣ በጣም የመንፈሳዊ ቦታ በመሆኑ፣ ስሙ እንኳን በኢትዮጵያው ክርስቲያን መሀል እንደዋዛ አይነሳም። እንዲያው ላነጋገሩ፣ “አንዳንዴ በዋልድባም ይዘፈናል” ሲባል ከመስማት በአሻገር፣ ስለዋልድባ፣ በሀይማኖት የጠለቀ አማኝ ካልሆነ እንጂ እንዲሁ ተራው ሰው አያውቀውም። ማወቅም አይኖርበትም። ዋልድባ የመናንያን ገዳም ነው። ዋልድባ፣ የጸሎት ስፍራ ነው። ዋልድባ፣ ከክብሩ መግነን የተነሳ፣ እህልም አይዘራበትም፡ ዓለማዊ ምግብም ወደገዳሙ ፈጽሞ አይገባም። መነኮሳቱ የሚበሉት፣ ቋርፍ የተባለ ምግብና የተቀቀለ ሙዝ ብቻ መሆኑን እንሰማለን። “ቋርፍ” ሲባል እንጂ፣ ስር ይሁን ምን እንደሆነ ብዙዎቻችን አናውቅም። እነዚህ በሺህ የሚቆጠሩት መናንያን፣ በሕቡዕና በግልጽ፣ የሚኖሩበት፣ ሰላም የሰፈነበት፣ የዚህ ዓለም ግርግር የራቀበት መንፈሳዊ ስፍራ እንደነበር በዓይነ ሕሊናችን እንቃኘዋለን። በልባችን እናስበዋለን።
ከዚህ በፊት የነገሡት የኢትዮጵያ ነገስታት፣ እንዲህ ዓይነት ትዕቢት በተሞላበት ቅዱሳት ገዳማትን መድፈር ቀርቶ፣ ደግ ነገር እንኳን ለነዚህ መናኒያን አባቶች ለማድረግ መጀመሪያ በአማላጅ፣ በትህትና፣ አስጠይቀዋችው፣ አስፈቅደው ነው። መናንያኑ፣ በፍጹም ዓለማዊ ድሎት ሾልኮ ገብቶ ከረቂቅ አጋንንት ጋር የሚያደርጉትን መንፈሳዊ ውጊያ እንዳያበላሽባቸው፣ አንዳችም ለሥጋ የሚበጅ ነገር እንዲመጣባቸው አይፈልጉም። መጋደላቸው “ከደምና ከሥጋ ጋር” ሳይሆን “ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር፣ በሰማያዊውም ሥፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ። (ኤፌሶን ፮፡፲፪)። ታዲያ ውጊያቸውን እንዲሰምር የዚህን ዓልም ቅንጦት እርግፍ አድርገው ትተው የሰማዩን ስለያዙት፣ ነገሥታቶቻን በሙሉ ያለፈቃዳቸው የሚበጃቸውን እንኳን ሊያድርጉላቸው አልደፈሩም። በአምባገነንነት ስሙ በዓለም ገንኖ የተነገረለት የደርግ መንግሥት እንኳን መጥቶ የነዚህን አባቶች ሰላም አላደፈረሰባቸውም። ዋልድባችን፣ ከኢየሩሳሌሞ ገዳመ ቆሮንቶስ የማይተናነስ ታላቅ ስፍራ ነው።
የመነኮሳት ሬሳ ከመቃብሩ እየታረሰ ሲወጣ አቅመ ቢሶቹ ቋሚ መነኮስታ በአንክሮ ሲመለከቱ
 ለአገር ባህል፣ ታሪክ፣ ሀይማኖት እና ደኅንነት ደንታ ቢሱ ወያኔ ግን፣ እህል እንኳን የማይዘራበትን የዋልድባ መሬትን፣ ለዔፈርት ድርጅቱ ገንዘብ ማግበስበሻ ለስኳር ማምረቻ ሸንኮር አገዳ ሊያመርትበት መሬቱን በትራክተር አረሰው፣ ወንዙን በግሬደር ቆፍሮ ሊገድበው ታጥቆ ተነሳ። ጫካውን ከመመንጠሩ አልፎ፣ በጾም በጸሎት ጊዚያቸው አብቅቶ ያንቀላፉትን የሙት መናንያንን አጥንት ከየመቃብራቸው እየተጎረጎረ አውጥቶ፣ ከ50,000 - 75,000 ሄ/ር መሬት ቀምቶ የሸንኮራ አገዳ ለመትከል ትራክተሮቹን ማስጓራቱን በማናልብኝ ተያያዘው። ያንቀላፉት አባቶቻቸው ሬሳ እየተመዘዘ ሲወጣ ለመከላከል፣ ምንም ዓይነት አቅም የሌላቸው መነኮሳት እንባቸውን እንደጅረት እያፈሰሱ፣ በዝምታ ተመለኩቱት:: መናንያኑ በዝምታ ሲያለቅሱ፣ አንዳንዶቹ ግን፣ በዓለም ላይ የሚደረገውን ምንም ባያውቁም፣ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ መንግሥት አለ ብለው የሚደረገው ጥፋት እንዲቆም ወደ አዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ ሂደው እሪ ለማለት ሞከሩ። ድምጻቸውን ሊሰማ የፈለገ አልነበረም።
የዋልድባ መቃብር ቆፋሪ ማን ሆነና ነው የሚሰማቸው።
ወደ ፓትሪያርኩ አቤት ለማለት ሂዱ። ማን አድርሶአቸው። ወደ ሲኖዶሱ ሊጮኹ ሄዱ። ሲኖዶሱ፣ የታጋይ ፓውሎስ ፎቶግራፍ፣ እንደመድኀኒታችን እንደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስና እንደ እመቤታችን ማርያም፣ እንደመላዕክቶቹ በየቤተክርስቲያኑ ሲሰቀል ማስነሳት ያቃታቸው፣ የታጋይ ጳዎሎስ ሀውልት ተሠርቶ መቆሙ በሀይማኖታችን ትክክል አለመሆኑን አስረድተው፣ እንዲነሳ ወስነው ለማስነሳት አቅም ያነሳቸው፣ የወልድባን ገዳም ከወያኔ ትራክተር ማዳን ፈጽሞ የማይታለም እንደሚሆንባቸው ለመነኮሳቱ ማን በነገራቸው። ታዲያ አንዳንድ ቆራጥ መነኮሳት ኢትዮጵያ ውስጥ ድምጻቸው ቢታፈን፣ በአንዳንድ አገር ቤት ባሉ በጣት የሚቆጠሩ የግል ጋዜጦችና፣ እንዲሁም ቁጭት በተሰማቸው ወገኖች ዕርዳታ፣ ለአሜሪካን ድምጽ ሬዲዮ የአማርኛው ፕሮግራም እንዲናገሩ ዕድል አግኝተው፣ ዋልድባን እንድንታደግ አቤቱታቸውን ለኢትዮጵያውን ሁሉ አሰሙ። የመለስ አሽክሮች እነዚህን ጀግና የሀማኖት አባቶቻችንን እያደነ አሰራቸው። ድምጻቸው ግን ከአጽናፍ እስካጽናፍ ተሰማ። ኢትዮጵያዊው እነሆ ከየክፍላተ ሀገሩ፣ ለዕምነቱ፣ ለሀይማኖቱ፣ ለአንድነቱ ስንቁን በአህያው፣ ዓመሉን በጉያው ከቶ፣ ለአንድ ዓላማ ወደ ዋልድባ እየተጓዘ ነው። የጸለምት ኗሪዎች፣ በወታደር እንደተከበቡ እንሰማለን። እስካሁን ወያኔ ወደ ዋልድባ የሚጓዘውን ኢትዮጵያዊ ማቆም አልቻለም። በየዓለም ዳርቻ የተበተኑትም ኢትዮጵያውያን የነዚህን ምስኪን አባቶቻችንን ድምጽ ሰምተው በያሉበት ብሶታቸውን እያስተጋቡ ነው። የሚከተለውን ቪዲዮ ይመልከቱ

http://www.youtube.com/watch?v=e5dhKLk0Nzc&feature=share

ጩኸታቸው ለንዶን ድረስ ተስምቶ፤ በዛሬው ዕለት በርዕሰ አድባራት ለንዶን ደብረጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ ዋና አስተባባሪነት፣ በደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ጽዮን ቆሞስ አባ ግርማ ከበደና በደብሩ ካህናት ግንባር ቀደም መሪነት በብርቲሽ ፓርላማ የተዘመተውም፣ ይኸንኑ ጉዳይ ለብሪታኒያ መማክርት አባላት ለማስረዳት ነበር።
ከዛሬ በፊት፣ ባለፈው ሳምንት፣ የደብሩ ሰበካ አስተዳደር ጉባኤ አባልት፣ የሀይማኖት አባቶችና የምዕምናን ተወካዮች በፓርሊያመንቱ በመገኘት፣ የተከበሩ አለን ሚካኤል፣ የደቡብ ካርዲፍን የምክር ቤት አነጋግረው፣ በገዳማትና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ ገዢው አካል በማድረስ ላይ የሚገኘውን ጥፋት፣ ስቃይና ሰቆቃ አስረድተዋል። በዚሁም፣ የሁሉም መማክርት ስብስብን (All Parliamentary Group), በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳይ ሃላፊውን፣ እንዲሁም የሀውስ ኦፍ ሎርድስን ተወካይ በቅርብ ጊዜ አግኝተው ጉዳያቸውን እንዲያስረዱ ተነጋግረው ወስነዋል።
በዛሬው ዕለት በምክር ቤቱ አደባባይ (Old Palace Yard SW1, Westminster Parliament) የተገኙት ኢትዮጵያውያን፣ ቤተክርስቲያናትን ማውደም ይቁም፣ ገዳማቱን መድፈር ይቁም! የታሠሩት ይፈቱ፣ ከዋልድባ ገዳም፣ ትራክተሮቻችሁን ይዛችሁ ውጡ! ዋልድባን የከበበው የጦር ሠራዊት ይነሳ!” የሚል መፈክር ሲያሰሙ ተደምጠዋል።
ይኽ በዚህ እንዳለ፣ የተከበሩ አለን ሚካኤል ረዳት የሆኑት ሚስ ሊዝ ስሚዝ ከምክር ቤቱ ወጥተው፣ ተሰላፊውን ካነጋገሩ በኋላ ደብዳቤአቸውን ከደብሩ የሰበካ አስተዳደር ጉባኤ ተወካዮች ከዋና አስተዳዳሪውና ከጸሐፊው ተቀብለው፣ ለአለን ሚካኤልና ለሚመለከቱአቸው እንደሚያደርሱ ቃል ገብተዋል::

መፈክር ከማሰማትም አልፎ፣ ተሰብሳቢው በመዘመርና በመጸለይ አላፊ አግዳሚውን አሰደምሟል። በአካባቢው የሚያልፉ ቶሪስቶችና እንዲሁም የለንዶን ነዋሪዎች የተያዙትንና በራሪ ጽሑፎች በማንበብ በበለጠ በሁኔታው በማዘን ቀርብ ብለው ተሰላፊውን በመጠየቅ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደውን የበተክርስቲያን ቃጠሎዎችን፣ የገዳማት መሬቶችን መቀማትና መታረስ፣ እንዲሁም የመቃብሮችን መደፈርና የአባቶቻችን መነኮሳትና መናንያን አጽም እየተቆፈሩ መውጣት እጅግ አሳዛኝ ታሪክ ለመረዳት ችለዋል። ይህ ፣ ለሰው ልጅ መብት ቀናዒ የሆነውን የለንዶን ሕብረተሰብን፣ ስለኢትዮጵያ አምባ ገነን ግዢዎች ማስረዳት ተችሏል።
በጣም የሚገርመው፣ ይህ የኢትዮጵያን ገዳማት አፍራሹ፣ አድባራት አቃጣዩ፣ ደን አውዳሚው፣ ኗሪውን ከቄየው እያፈናቀለ መሬቱን ለባዕዳን ሻጩ፣ የወያኔ ገዢ ቁንጮ ወይም ርዕስ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሥቃይ፣ መልስ ዜናዊ፣ የአፍሪአካ ከባቢ አየር ጉዳይ ኃላፊ ሆኖ መሾም ነው። የኤርትራው ኢሲይያስ አፈርቂ እየተንክባከበ ያሳደገልን አምባ ገነን፣ ዛሬ ታሪክ ከማበላሸት አልፎ፣ የኢትዮጵያን ንብረት ከመመዝበር አልፎ፣ መሬት ቆርሶ ለጎረቤት በስጦታ መልክ ከመለገስ አልፎ፣ ቤተክርስትያናችንን እያወደማት ነው። ኢትዮጵያዊ ሁሉ በያለበት ይኸን ማውገዝና፣ ልክ ወገኖቻችን ቤቶቻቸውን፣ ንብረቶቻቸውን ትተው ቅዱሳን አባቶችን ከወያኔ መንጋ ለመከላክል ተጠራርተው ዋልድባ እንደወረዱ ሁሉ፣ በስደት የምንኖር ኢትዮጵያውያንም ተጠራርተን በውጭ አገር የነዚህ ሰሚ ያጡ ወገኖቻችን ደጀን እንድንሆን ከወዲሁ ጥሪአችንን እናስተላልፋለን።
እግዚአብሔር ሀይማኖታችንን፣ ሀገራችንን፣ አባቶቻችንንና ወገኖቻችን ኢትዮጵያውያንን ይጠብቅልን!

ማስታወሻ
የሰላማዊው ሰልፍ ተንቀሳቅሽ ስዕሎች በሚከተሉት ድረ-ገጾች ይመልከቱ