Tuesday 23 July 2013

ውግዘት: በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ባህል ውግዘት ሰይፈ ነበልባል ነው!




 

 


nigatuasteraye@gmail.com

                  ሐምሌ ፳፻፭ ዓ.ም

 

 

መግቢያ


 

በዚህ ርዕስ ይህችን መልእክት እንዳዘጋጅ ያስገደደኝ ለኢሳት ሶስተኛ አመታዊ በዓል ላይ በተገኘሁበት ሳምንት ቬርጂኒያ ላይ የገጠመኝ ነገር ነው። ከስብሰባው በኋላ በበነጋው ዓርብ ኢሳት ስራውን የሚያካሂድበትን ቢሮ ለመጎብኘት ወደ ቬርጂኒያ ሄድኩ። ጎብኝቼ ስመለስ፤ ለዚህች መልእክት ምክንያት የሆነው ከባድና አስቸጋሪ ነገር ገጠመኝ። የገጠመኝን ችግር ከቦታው ለመግለጽ ከዚህ ላይ ገትቼ፤ ይህ ችግር የቤተ ክርስቲያናችን መመሪያ እንዴት ሊፈታው ይችላል? ብየ በማሰብ አዕምሮየን ወደጠመዘዝኩበት አቅጣጫ ልሻገር። ኢሳት ባዘጋጀው ላይ እንድናገር የተሰጠኝ ርእስ ባለመኖሩ፤ በወያኔ ዘመነ መንግሥት  ኢትዮጵያንና: ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ትክርስቲያንን የቆሎ ተማሪ እንዴት ይመለከታቸዋል? ብየ  ባሰብኩበት መንገድ ይህንንም ችግር በዚያው መንገድ ተመለከትኩት። [ለኢሳት ያቀረብኩትን ሙሉ ሀሳቡን ለማግኘት ይህን ሰንሰለት ይጫኑ፦ የቆሎ ተማሪና ኢትዮጵያዊነት]

ኢትዮጵያውያንና የኦርቶዶክስ የዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የገጠማቸውን ችግር ለመፍታት የሚሞክሩት በኦርቶዶክሳዊው ነገረ መለኮት እና በኢትዮጵያዊው ባህል ነው። ነገረ መለኮቱም ሆነ ባህላችን ቅዱሳን ንጹሀን በመሆናቸው ከሥጋዊ ፈቃዳችን፤ ከሥጋ ዝምድና ሽፋን፤ ከጓደኛ ግርዶሽ እና ከግል ጥቅማ ጥቅም አላቀን ብንጠቀምብቻው፤ ሲሆን ለሰው ልጅ ክብርና መብት ከሚጠነቀቅ ምድራዊ ህግ በላይ፤ አለዚያም የሚስማሙ የሚጣጣሙና የማይቃረኑ በመሆናቸው ለችግራችን ዘላቂ መፍትሄ በሰጡን ነበር። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችን በቨርጂንያ ቤተ ከርስቲያን የገጠማትንና ወደፊትም የሚገጥማትን  ይህን አይነት ችግር በእምነታችን በባህላዊው ውግዘታችን  ለመፍታት ብንሞክር  ላንድ እና ለመጨረሻ ጊዜ ትምህርት ሰጭና ዘላቂ መፍትሄ መስጠት የሚቻል መሆኑን ለመጠቆም ይህችን ጽሑፍ አዘጋጀሁ። በኢትዮጵያዊው አርቶዶክስ ተዋህዶ ነገረ መለኮት አተረጓጎም መንገድ ውግዘት ቆራጥ ውሳኔ ሰጭ ሰይፈ ነበልባል ነው

ክፍል ፩፦ሰይፈ ነበልባል


“ወአውጽኦ እግዚአብሔር ለአዳም እምገነተ ተድላ . . . . አዘዞሙ ለኪሩቤል ወለሱራፌል  ዘውስተ እደዊሆሙ ሰይፈ እሳት እንተ ትትመያየጥ ከመ ይዕቀቡ ፍኖተ ዕጸ ህይወት”(ዘፍ ፫፡፳፬)  ይህም ማለት “አዳም በገነት ውስጥ በተድላና በደስታ ሲኖር ያልተፈቀደለትን ቆርጦ በጥሶ በመብላት ስህተት ላይ ወደቀ። ቆርጦ በጥሶ በበላት በለሰ ሰውነቱን ጠቅልሎ በዚያው በገነት ውስጥ ተደብቆ ለመኖር ፈለገ።እግዚአብሔር አውግዞ ከገነት አስወጣው። ለመቁረጥ ለመበጠስ ነበልባላዊ ስለት ያላትን የምትገለባበጥ ሰይፈ ነበልባል  በእጃቸው የያዙትን ሱራፌልንና ኪሩቤልን የህይወት መንገድን እንዲጠብቁ አዘዛቸው።” የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሊቃውንት አበው ይህች አንቀጽ የጸነሰቻቸውን ዓበይት ቁም ነሮች ባተረጓጎም ዘይቤአቸው እየፈለፈሉ ለማቅረብ አንድም እያሉ ይመላለሱባታል። ከዓበይት ቁም ነገሮች አንዱ፤ በበደልና በኃጢአት ጉድጓድ ስንወድቅ ዓይነ ህሊናችን ፈዞ እዝነ ህሊናችን ደንዝዞ ያካባቢያችን ህዝብ ወቀሳና ክስ መስማት ሲያቅተን፤ የሰመመን አዚም ሲጫነን በስለቱ ጫፍ ወግቶ በግራና በቀኝ ሾተሉ አጣብቆ እና አስጨንቆ የሚቀሰቅሰን ሰይፈ ነበልባል ውግዘት ነው። ውግዘት ኃጢአትን ከጽድቅ  ለመለየት የሚሰነዘር ሰይፍ ነው። ቅዱስ ጳውሎስም የመዳን ሰይፍ ብሎታል (ኤፌ ፮፡፲፯)

በሰይፍ ባህርይ የተገለጸው ውግዘት የእግዚአብሔር መመሪያ ነው። ሰይፍ ይቆርጣል ይፈልጣል ይወጋል ይስላል። በቃሉ የተመሰረተው ኢትዮጵያዊው መንፈሳዊው እና ባህላዊው ውግዘትም “በኃይል፤ በዓቢይ ስብሀት፤  ይቀጠቅጥ አርዘ፤ ይመትር ነደ እሳት፤ ያጸንኦሙ ለኀያላን፤ ያድለቀልቅ ገዳም፤ ለሀቅለ ቃዴስ፤ ወይሁቦሙ እግዚ ኃይለ ለህዝቡ”(መዝ ፳)፡ እንዳለው ዳዊት፤ “ይመክራል ያስተምራል ይገስጻል ይስላል አመጸኛውን ከህዝቡ ቆርጦ ይለየዋል። ክብሩን ማእረጉ ይገፈዋል። እግዚአብሄር አዳምን ገዝቶ ከገነት ሲያስወጣው ያደረገው ይህን ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ትርጓሜ የህይወት በር የተዘጋችባት ተገለባባጭ ሰይፈ ነበልባል ዘላለማዊት አይደለችም። የገነት በርም በአዳም ላይ ለዘላለም ተዘግታ የምትኖር አይደለችም። ይህ ነገር በጥንቃቄ እና በአጽንኦ እንድናስተውላቸው ከሚገቡን ነገሮች አንዱ እና የመጀመሪያው ነውና ላብራራው።

በመጀመሪያም እግዚአብሔር አዳምን አውግዞ ከገነት ከማስወጣቱ በፊት፤ የገነትንም በር ከመዝጋቱ በፊት፤ “ናሁ አዳም ኮነ ከመ ፩ዱ እምኔነ” (ዘፍ ፫፡፳፪) አለ። ማለትም፦ “አዳም ከእኛ እንዳንዱ ሆነ” በሚል የተስፋ ቃል የተዘጋው በር እንደሚከፈት፤ እንዲያውም እራሱ አምላክ ዳግማዊ አዳም (አማኑኤል) ሆኖ፤   የህይወት መግቢያ በር እንደሚሆንለትም ከውግዘቱ በፊት ለአዳም ጥንቃቄ አስቀድሞለታል። በቅድመ ውግዘት ጥንቃቄውም፤ እግዚአብሔር አዳም በቃሉ ተገዝቶ እንዳይኖር፤ የግዝቱን ቅንበር ፈልጦና ቆርጦ ለማስወገድ የግዝቱን ዋጋ ለመክፈል ቃል ሥጋ ሆነ። በአምላክነቱ የተወሀደውን ሥጋችንን በኛ ፈንታ ቀጣው። በሰውነቱ ከፈለው። የተወሀደውን ደማችንንም አፈሰሰው

እነ ቅዱስ ጎርጎርዮስ  “አርኀወ ለነ ኆህተ ገነት ዘተአጸወ በጌጋየ አዳም።  ወአግኀሦ ለኪሩብ ዘየአቅቦ ለዕጸ ሕይወት ወአዕተተ እምኔሁ ኩናተ እሳት ወአብጽሀነ ውስተ ሕይወት ወተመጦነ እምፍሬሁ  (ሃ.አበው ም ፴፮፡ቁ ፴፰) እንዳሉት፤ “ክርስቶስ በአዳም በደል የተዘጋውን በር ከፈተው። የሚገለባበጠውን የኪሩቤን ሰይፈ ነበልባል አስወገደው ወደ ህይወት መግቢያ አደረሰን የተከለከልነውንም ፍሬ ተመገብን::”  

እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያኖች ሁል ጊዜ በቅዳሴያችን “በከመ ምህረትከ አምላክነ ወአኮ በከመ አበሳነ” እያልን በውግዘቱና በይቅርታው የምናደንቀው ከዚህ ምሥጢር በመንደርደር ነው። እኔም አባ ማትያስ ከንሳስ ላይ መጥተው ያወጁትን እምነትና የሰነዘሩትን እገዳ ከላየ ላይ ገፍፌ እራሳቸውን መልሼ እንዳከናንባቸው፤  የራሳቸውን እምነት ገላልጨ እንዳየው፤ ጵጵስናቸውን እና አሁን ደግሞ ፓትርያርክነታቸውን ገፍፌ ለህዝብ እንዳቀርበው የረዳኝ  ቤተ ክርስቲያናችን ያስታጠቀችኝ ይኸው የመንፈስ ሰይፍ ነው።  

ውግዘት ቅዱስ ጳውሎስ “የመዳን ሰይፍ” (ገላ ፭፡፲፯_ ፳፩) እንዳለው፤ ከሚያድነው ቃሉ ጋራ የተያያዘ አዳኝ ነው። አውጋዡ ያወገዘው ከተወገዘበት ስህተቱ እስኪመለስ ድረስ በፍቅር በትእግስት ይጠብቀዋል። ተወጋዥም ተኝቶ ከሚያንቀላፋበት እንቅልፉ ፈጥኖ መንቃት አለበት። በህሊና በሽታ ታሞ የተኛበትን አልጋ በንስሀ እና በጸጸት ፈጥኖ ተሸክሞ ለመነሳት እባብ አሳተኝ፡ ሄዋን አሳተችኝ የሚል ሽባ ምክንያት መፍጠር የለበትም። ማውገዝም መወገዝም ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍሉ እጅግ አስፈሪዎችና የተከበሩ ናቸው።በግዝት ከተቀደሰው ቦታ እንደወጡ መቅረት የለም።  ውግዘት በኃጢአትም ተጠቅልሎ ላለመኖርና አካባቢውን ከብክለት የሚያድን የሚያጸዳ እና የሚቀድስ ከኃጢአት እትብት እና ሰንኮፍ ቆርጦ የሚያላቅቅ ሰይፈ ነበልባል ነው። ስለ ዉግዘት ተጨማሪ ሀሳብ ለማግኘት  “እንዲህ ያለ ፓትርያርክ አይተን አናውቅም” በሚል ያቀረብኩትን ሰንሰለት ይጫኑ፦አባ ማትያስ: “እንዲህ ያለ ፓትርያርክ አይተን አናውቅም] 

በኦርቶዶክስ ክርስትና ግንዛቤ፤ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በውስጣዊ የህሊና ውግዘት ከነዚህ ባህርያት ተቆራርጦ፤ በቅድስና በንጽህና ለመኖር መታገል ይኖርበታል። በጉባኤ የምናከናውነው ቅዳሴያችን ደጋግሞና አጥብቆ የሰጠንን መመሪያም ይህኸው ነው።  እንመልከተው።

ክፍል .፦መጽሐፈ ቅዳሴያችን


የሰጠ መመሪያ


 

ሥጋውን ደሙን ከመቀበላችን በፊት “እምኩሉ አበሳ ወመርገም ወእምኩሉ ጌጋይ ወክህደት ወመሀላ በሀሰት ወእምኩሉ ግዘት ወእምተደምሮ  በዕልዎት ወርኩስ ምስለ ዓላውያን ወአረማውያን ( ፻፪፡፹፮) ማለትም፦ “ውግዘትን ከሚያስከትሉ ከሀሰት ከስርቆት ከዝሙት ህሊናን ከሚያርክሱ ነገሮችና እነዚህን ከሚፈጽሙ ሰዎች ጋራ ከመቀላቀል ሰውረን” እያለ ካህኑ ምእመናኑ እንዲሰሙት  ከፍ ባለ ድምጽ ያነባል። የተዘረዘሩትን ክፉ ተግባራት ሁሉ ከህሊናችን የምንቆርጥበትን የመንፈስ ሰይፍ  ከእኛ እንዳይርቅብን “ጸግወነ እግዚኦ ጥበበ ወኃይለ ልበ ወልቡና ወአዕምሮ። ከመ ንርሀቅ ወንጉየይ እንከ እስከ ለዙሉፉ እምኩሉ ምግባራቲሁ ለሰይጣን ዘያሜክር” እያለ በሚሰማ ድምጽ በንባብ መልክ ያነባል። ቀጥሎም “ሀበነ እግዚኦ ንግበር ፈቃደከ ወሥምረተከ በኩሉ ጊዜ” እያለ ይጸልያል (፻፫፡፹፯᎗፰)።“እውነትን ፈቃድህን እንድንፈጽም ሃይሉንና ጥበቡን ሰጠን” እያለ ንባቡን  ሲጨርስ፤ በንቃተ ህሊና የቆመው ዲያቆን “ነጽር”(፻፫፡፹፱)” ይለዋል። ይህም ማለት፦ “አንተ ካህን ሆይ! ለህዝበ ክርቲያኑ እያሰማህ ባነበበከው ጸሎት ለራስህም መንፈሳዊ መስጠንቀቂያ ነውና ራስህን እና ህዝበ ክርስቲያኑ ተመልከት” ማለት ነው።

ካህኑም ከዲያቆኑ የቀረበለትን የማስጠንቀቂያ መልእክት በመቀበል “ቅድሳት ለቅዱሳን” (፻፫፡፺) ብሎ ይመልስለታል። ይህም ማለት፦  “የተቀደሰው ሥጋና ደም ለቅዱሳን እንደሚሰጥ አውቃለሁ እረዳለሁ እጠነቀቃለሁ” ለማለት ነው።  ሁሉንም በእግዚኦታ ወደ አምላክ ይመራ ዘንድ፤ ህዝቡ ሁሉ በዲያቆኑና በካህኑ መካከል የተደረገውን ልውውጥ፤ “፩ዱ አብ ቅዱስ ፩ዱወልድ ፩ዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ (፺) በማለት፦ በተባበረ ድምጽ ስምምነቱን በአሜንታ ያስተጋባል። በአንቅሆና በተሰጥኦ ቅብብሎሽ የሚከናወነው ይህ የአምልኮት ስርዓት፤ ሁሉንም በሀለፊነት አዋህዶ እና አስተሳስሮ በእኩል ለሀላፊነት እና ግዴታ የሚያሰልፍ ነው። መጽሐፈ ቅዳሴያችን ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ለሊቃውንቱ ለካህናቱ ለዲያቆናቱ ለጠቅላላ ህዝበ ክርስቲያኑ ያለውን የጋራ ኃላፊነት እንዴት እንደገለጸው ከዚህ በታች እንመልከተው።

ክፍል .ሀ፦ ለቅዱሳን አበው ሊቃውንት የተሰጠ መመሪያ


 በረዥሙ እድሜያቸው፤ በብዙ ልምዳቸው፤ ዓለምን የታዘቡ፤ ብዙ ትውስታ ትዝታ የተሸከሙ፤ ለታሪክ ለባህል ለስነ ልቡና ምስክርነት የበቁ፤ በየምንደሩ ፤በየጎጡ ፤በየደብሩና በየገዳሙ ለሚኖሩ ለቅዱሳን አበው ሊቃውንት የተሰጠ መመሪያ

 “ኦ ቅዱሳን አበው እለ ትመስሉ አእማደ ወርቅ ንጹሕ ዘቅውም ዲበ ዕብነ ሰንፔር ብጹአን ለክሙ”(፺፰) ማለትም፦ “ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነታችሁ  ጸንታችሁ፤የተሳሳተውን ለመምከር ለመገሰጽ ምሳሌነታችሁን ለማሳየት  በጽኑዕ እና ቆራጥ አቋማችሁ በያላችሁበት እንደወርቅ የምትፈልቁ ናችሁና ብጹአን ቅዱሳን መባል ይገባችኋል።” ይህ ኦርቶዶክሳዊ ስነ ትምህርት፤ በሩቅ ዘመን ልምድና በጥሞና ለበሰሉ ሁሉ ኦርቶዶክሳውያን አባላት የተሰጠ የማነኛውም አገር ህግ የማይገሰው፤ የሰባዊ ባህርይ መለኪያ የማይታጠፍ ኃያል ሰይፍ ነው። በየቦታው ተጀምረው አገልግሎት በመስጠት ላይ ባሉት ቤተ ክርስቲያኖቻችን ‘ዕብነ ሰንፔር” የተባለው ጽኑእ እምነትና  አቋም ያላቸው እምነት ሲፋለስ ባህል ሲደመሰስ በዝሙት በዘረፋ ስሜት በተለከፉ መነኮሳት፤ ቀሳውስትና ጳጳሳት ቤተ ክርስቲያን ስትወረር ተባብረው እና ጸንተው በመቆም ትክክል አይደላችሁም ብለው የተናገሩ  አዛውንቶች እናቶች አሉ?  

ክፍል .ለ፦ ለካህናቱ የተሰጠ መመሪያ


“ኦ ካህናት አንትሙ ውእቱ አዕይንተ  እግዚ ብሩሃት። ተናጸሩ በበይናቲክሙ ፩ዱ ምስለ ካልዑ። ህቱ እምውስተ ህዝብክሙ በአበይኖ፤ ኢይቁም ወኢይህበር ምስሌክሙ በጸልዮ ኢዘማዊ ወኢቀታሊ ወዘያጣዑ ኢሰራቂ ወኢሀሳዊ ዘውእቶሙ ፭ቱ አክላባት እለ በአፍአ ይትኬነኑ”( ፰)  ማለትም፦ “እናንት ካህናት የእግዚአብሄር ዓይኖች ናችሁ። ከጓደኝነት ከጥቅም ንክኪ ከሚመነጭ መከባበርና መፈራራት ርቃችሁ እርስበርሳችሁ ተፈታተሹ። በህዝባችሁ መካከልም የኃጢአት አዘቅት ተፈጥሮ፤ ብክለት እንዳይከሰት በሚዛናዊ ፍርድ ምእመናኑን መርምሩ።  በነፍሰ ገዳይነት፤ ገንዘብ በመዝረፍ ከሚከሰስና ከሚወቀስ፤ በዝሙትም ከሚታማ፤ ከሚዋሽ እና ከኦርቶዶክስ አምልኮት ውጭ በሌላ አምልኮ ከተሰማራ በአክላባት ባህርያት ከተበከለ ሰው እራቁ!

 አክላባት የተባሉት አምስቱ ባህርያት ያሏቸው ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን እንዲወጡ ቅዳሴው ይፈርድባቸዋል። በተለይም “በህዝባችሁ መካከልም  የሚበክል ኃጢአት ተፈጥሮ ብክለት እንዳይከሰት በሚዛናዊ ፍርድ ምእመናኑን መርምሩ” የምትለዋ ሀረግ የማነኛውም አገር መንግስት ህግ ከፍ ያለ ክብር የሚሰጠውና አቀባበል የሚያደርግለት ነው። ለዚህ ቅዱስ ክህነታዊ አገልግሎት ስለተሰለፉት ካህናት መጽሐፈ ቅዳሴያችን “ኦ ካህናት ሥዩማን ክብር ለክሙ ሶበ ትትከሀኑ ምስለ እግዚአ ሰማያት ወምድር (፪፻፳፱፡፺፮) ይላል። ማለትም፦ “ከአምላክ ፈቃድ ዝንፍ ሳትሉ ለተሰለፋችሁለት ነገረ መለኮት በታማኝነት ጸንታችሁ የቆማችሁ፤ የክህነቱን አገልግሎት ለማከናወን መንፈሰ ሰይፍ የታጠቃችሁ እናንት ካህናት ሆይ! ክብርና ምስጋና ይገባችኋል” ይላቸዋል። በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያናችን ነገረ መለኮትን ባዛቡ፤ በዝሙት በዘረፋ በሚወቀሱ፤ ሰዎች ስትታመስ ራሳችን ባናደርገውም፤ ባለመቃወማችን እና፤ በዝምታችን የጥፋት ተካፋዮች አርጎ መመሪያችን ስለሚመድበን በበመሪያችን መሰረት ካህናት ነን ለማለት የበቃን አያደርገንም። 

ክፍል .ሐ.፦ ለዲያቆናቱ የተሰጠ መመሪያ


 “ኦዲያቆናት ኅሩያን እለ ትመስሉ አስራበ ወርቅ ፍስሐ  ለክሙ ሶበ ትሬእዩ  ምሥጢረ  ዕጹበ” (፺፯) ማለትም፦እንደ ወርቅ መርገፍ ድምጻችሁ ያመረ  የተመረጣችሁ ዲያቆናት የሚያስደንቀውን ምሥጢር ተረድታችሁ ለምታከናውኑት ተልእኮ ደስ ሊላችሁ ይገባል። ይህንንም ተልእኮ “ኦ ዲያቆናት ማህቶተ ቤተ ክርስቲያን ወላእካኒሃ ምልኍ እምውስቴታ ኢየሀሉ ተኩላ ምስለ ብግዕ፤ አንቄ ምስለ ርግብ ክርዳድ ምስለ ስርናይ”(፲፩) ብሎ ገልጾታል። ማለትም፦ የቤተ ክርስቲያን ብርሃንና ጉዳይ አስፈጻሚዎች የሆናችሁ ዲያቆናት ሆይ! ከምታገለገሉበት ምእመናን መካከል ተኩላዎችን ጭልፊቶችንና እንክርዳዶችን  ጠራርጋችሁ አስወግዱ” ያሜሪካም ሆነ የእንግሊዝ  የማነኛውም አገር ህገ መንግስት ዜጋውን  ከሰው መሳይ ተኩላዎች እና ከሰው መሳይ ጭልፊቶች ለመከላከል የተዘጋጀ ሰይፈ ነበልባል ነውና ከዲቁናችን ተልእኮ ጋራ ይስማማል። መመሪያችን ዲያቆናትን የሚለካቸው በዚህ መስፈርት ነው። ታዲያ በየቦታው ያሉት ዲያቆናት ይህን ተምረውት አውቀውት የገቡ ናቸው? መታረም ያለበት ነገር ስለሆነ በትዝብት አቆይተን ራሱን በቻለ ርእስ ብንመለስበት የሚሻል ይመስለኛል።  

ክፍል .መ፦ ለምእመናኑ የተሰጠ መመሪያ


“ኦ ኩልክሙ መሃይምናን እለ ትመስሉ ከዋክብተ ብርሃን ዕበይ ለክሙ (፺፱) ማለትም፦  በሞራላችሁ በቅድስናችሁ በስነ ምግባራችሁ እንደ ሰማይ ከዋክብት በሩቅ ስትፈልቁ የምትታዩ ሁላችሁ ሴቶችም ወንዶችም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና እምነት ተከታዮች ሆይ! ክብር ልእልና የተጎናጸፋችሁ ናችሁ። “አንትሙሰ ህቱ እንተ አፍአ ወአኮ እንተ ውስጥ፤ ወእንተሰ ውስጥ እግዚአብሄር የአምር ወይፈትን በማህቶተ ዚአሁ”(፲፪) ማለትም፦ “በአፋዊ ዓይናችሁ የምታዩትን፤ በአፋዊ ጆሯችሁ የምትሰሙትን ሁሉ መርምሩ ርምጃም ውሰዱ።ተብለው የታዘዙት አማኞች ሁሉ ናቸው። መጽሀፈ ቅዳሴያችን የሰጠን ይህ መመሪያ፤ክርስቶስ  ሰርግ ለብስ ሳይለብስ የገባውን እንደምሳሌ በመጥቀስ “እጁንና እግሩ አስራችሁ አውጡት”(ማቴ ፳፪፡፲፩_፲፬) ብሎ በሰጠው መመሪያ ላይ የተመሰረተ ነው

በራሳቸው ባህል ቋንቋ የሚያመልኩትን ህብረተ ሰቦች በኛ ስርአተ አምልኮ እና ቋንቋ ካላመለካችሁ በማለት መተቸት ተገቢ አለመሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ ለመግለጽ “ውጭ” የምትለዋን በመጥቀስ “አትፍረዱ፤ የዚያን ፍርድ ለአምላክ ስጡ” ካለ በኋላ፤ በመካከላችን ሆኖ ስህተት የሚፈጸመው ግን የመቃወም የማስወጣት ሀላፊነት እንዳለብን “ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡ! በማለት አዝዟል።( ፩ኛ ቆሮ ፭፡፲፪)  

የቤተክርስቲያኒቱ አካላት ሁሉ በቤተ ክርስቲያናቸን ስም ንብረት እየሰበሰበ ያልሆነ ነገር እየሰራ እያየን እየሰማን ሳለን፤ በስሙ መዝግቦ የፈቀደለትን ያሜሪካ መንግስት እያማረርን ዝም ብለን ልንመለከተው አይገባም። ግለ ሰቡ ተጸጽቶ ከስህተቱ  እስኪመለስ ድረስ ሳንታክት መቃወም አለብን። ህዝቤን ሞራል ባህል እምነት ቋንቋ አስተምራለሁ ብሎ ለጠየቀ ሁሉ የአሜሪክ መንግስት  ፈቃድ ቢሰጥም፤ በቋንቋችንና በባህላችን ተሸፍኖ የሚደረገው ስህተት ለማወቅ አምላክነት የለውም። ለሞራል እና ለስነ ምግባር መከላክያ ሆኖ የኖረውን መንፈሳዊ ሰይፋችንን (ውግዘት) በተሳሳተው ላይ መዘን ማሳየት የኛ ፋንታ ነው።

ቅዱስያዕቆብ “ዘየአምራ ለሠናይት ወኢይገብራ ኃጢአተ ትከውኖ “( ያዕ ፬፡፲፯) እንዳለው፤ ማለትም፦ እውነትን አውቆ መመስከር ሲገባው ደብቆና ሸሽጎ የያዘ ሰው፤ የግዝቱ ሰይፍ በደሉን ከፈጸመው ሰው ጋራ ደርቦ ይመታዋል። በሰለስቱ ምእት የተዘጋጀው መጽሀፈ ቅዳሴያችንም “እመቦ ዘይትናገር ውስተ ቤተ ክርስቲያን ነገረ ከንቱ ወስላቅ እስመ ጌጋዩ ይከውን ላዕለ ካህን ዘይትለአክ።  ወአኮ ዘይኤብስ ባህቲቱ ዘይትኬነን አላ ዘሂ ይትፌሳህ  በኃጢአቱ ይትኴነን ወአኮ ውእቱ ዘአበሰ ወዳእሙ ዘሠምረ በኃጢአተ ዝኩ ወናሁ ተሣተፎ በኃጢአቱ ወበ አሐቲ ኩነኔ ይትኴነኑ ( ሃ ፳፪፡፬) ይላል። ማለትም፦ዝርፊያ ዝሙት ይቅርና ውሸት የሚናገረውን ሰው ዝም አትበሉት። ይህ አይነት ባህርይ እንዳለው እያወቃችሁ ዝም ካላችሁ በሰውየው ላይ የሚደርሰው ፍርድና ኩነኔ እናንተንም ይጨምራችኋል ይላል። መመሪያችን መባህን በመሰዊያ ላይ ብታቀርብ ከዚያም ወንድምህ አንዳች ባንተ ላይ እንዳለው ብታስብ መባህን በመሰዊው ትተህ ሂድ። አስቀድመህ ከወንድምህ ጋራ ታረቅ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ” (ማቴ ፮፡፳፫፳፮) ይላል እንጅ ከዓለማዊ ዳኛ ውሳኔ ጠብቅ አይልም ዲያቆኑ ጻኡ ንኡሰ ክርስቲያን” (፸፬፡፡፩) ለማለትም  የመንግስትን ውሳኔ መጠበቅ አለበት ማለት ነው። መጽሐፈ ቅዳሴያችንእስመ ቤተ ክርስቲያን አኮ መካነ ነገር ዳእሙ መካነ ጸሎት”(ስቅ ፳፫፡፸፩) ቤተ ክርስቲያን የጸሎት እንጅ የነገርና የሀሜት ቦታ ስላይደለች፤ ነገረ መለኮቱን የሚያስተምር ስርአቱን የሚያስከብረው ካህኑ ይቅርና ማነኛውም አባል በዝሙት በስርቆት በስስት ከተከሰሰ ንስሀውን ጨርሶ እስኪመለስ ከቤተ ክርስቲያን መራቅ አለበት። በተለይ በዝሙት የተወነጀለ ካህን ወቀሳና ክስ በተሰማባት ቀን ከክህነታዊ አገልግሎት መገለል አለበት። በዓለማዊ ዳኛም ሆነ በሽማግሌ ጉዳዩ እስኪጣራ የተቀደሰውን ክህነታዊ አገልግሎት እየሰጠ እንዲጠብቅ መመሪያችን አይፈቅድለትም። ታዲያ፤ መመሪያችን ለሥጋው እና ደሙ  ቅድስና ክብርና ጥንቃቄ በመስጠት የሚያዝዘውን በተግባር ለማዋል፤ ስንቱ አማኝ ነው ተባብሮ የቀመው?

ክፍል ፫፦ዝሙት


 


በሁለት ተቃራኒ ጾታወች ህጋዊ ጋብቻ ላይ ያልተመሰረተ ሩካቤ ሥጋ ዝሙት ነው። ሩካቤ ሥጋ አምላክ ቀድሶ አክብሮ በፍጥረቱ ባህርይ ያስቀመጠው የዘር ማብዣ የህይወት መፍለቂያ ምንጭ፤ የዓለም መሙያ መሳሪያ አርጎ በህግ በተሳሰሩ ሴትና ወንድ መካከል ብቻ እንዲፈጸም ያዘጋጀው ረቂቅ ምሥጢር፤ ከክህነት በፊት የነበረ ክህነት ነው።  ይህም ረቂቅ ምስጢር በጋብቻ ከተወሰኑት ሰዎች ውጭ እንዳይፈጸም በጥብቅ የተከለከለ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል። የተፈታችውን የሚያገባም ሁሉ ያመነዝራል”(ማቴ ፮፡፴፩) እንዳለው፤ በመካከል ከሚፈጸም ዝሙት በቀር ሊያፈርሰውና ሊያናውጸው የሚችል ኃይል የለም። የዚህን መሰረታዊ ታላቅነት የሰሙ ሐዋርያት “የባልና የሚስት ስርዓት እንዲህ ከሆነ መጋባት አይጠቅምም” ብለው ጌታችንን በጠየቁ ጊዜ፤ ሳያገቡ ለሞኖር “ለተሰጣቸው ነው እንጅ ለሁሉም አይደለም” ብሎ መለሰላቸው። (ማቴ ፲፱)  ይህም ማለት በተአምርም ሆነ በተፈጥሮ፤ ከሰባዊ ባህርይ ውጭ በመሆን በህብረተ ሰብ መካከል የሚከሰቱ ሰዎች አሉ ማለት ነው። ይህ የክርስቶስ ንግግር የምናያቸው መነኩሴዎች ሁሉ በዚህ ባህርይ የመጡ ናቸው ማለት እንዳንችል ያደርገናል። ምክንያቱም  የምናየው መነኩሴ ሁሉ በዚህ ክስተት የመጣ ቢሆን ኖሮ፤ ኢትዮጵያ እጅግ በተቀደሰችና በለንደንና ባሜሪካ የሚሰማው መታወክ ባልተፈጠረ ነበር

ይልቁንም “ከዝሙት ሽሹ! ሰው የሚፈጽመው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው። ዝሙትን የሚሰራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ  ኃጢአትን ይሰራል”(፩ኛ ቆሮ ፮፡፲፰) የሚለውን የዘነጉ ሰዎች ካህናት ጳጳሳት ሰባኪዎች እየሆኑ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ገብተዋል። የዚህች ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባላት የሆን ሁላችን እስቲ ለሰከንድ ትንፋሻችንን አቁመን ባንዲት ሳንቲም ላለመበለጥ በየሱቁ  የምናደርገውን ነቅተን መጠበቅና መከራከር እናስብ! እውነት ሃይማኖታችንን የምናከብር ባህላችንን የምንወድ ከሆን፤

*    ሲካብ የኖረው የባህል እና የታሪክ ክምችት ሲናድ፤

*     የመንፈስ የእምነት የሞራል ሰንሰለቱ ሲበጠስ፤

እየሰማን እያየን፤ በህሊናችን እየታዘብንና እየፈረድን፤ ምላሳችንን ጎርሰን አፋችንን አፍነን፤  አይናችንን ጨፍነን፤ ጆሯችንን ደፍነን እኔ ምንቸገረኝ በማለት መቀመጥ፤ የፈጣሪን ቁጣና መቅሰፍት  ስህተቱን ከፈጽመው ሰው ጋራ መጋራትና በቀሚጥለው ትውልድ ላይ መዝመት አይደለም?   

ይህ ርኩስ ልማድ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር እንዳይቀንስ  የተቀደሰውን ኢትዮጵያዊ ባህል እንዳያዛባው ማስተማር የሚገባቸው ፤ጳጳሳቱ መነኮሳቱ ቀሳውስቱ የዝሙት መምህራን ሆኑ እያለ ህዝቡ በማዘን ላይ ሳለ፤ ጠቃሚ ቢሆንም የሀገሪቱ ባለሙያወች አጥንተው ገና ያልተስማሙበትን “የወያኔ መንግስት ግዙ የሚለውን ቦንድ ያልገዛ ራሱን ከዜግነት የሰረዘ ነው” ብለው ጳጳሳቱ ሰበኩ ተብለው ሲወቀሱ መስማት እጅግ አሳፋሪ ነው። ህዝበ ክርስቲያኑ እያዘነባቸው ላሉ እምነቱን የሚጎዱ ቤተ ክርስቲያናችንን የሚንዱ ዝሙትን የመሳሰሉ ስህተቶች የሚታረሙበትን መፍትሄ ለማግኘት መጣር ሲገባቸው፤ ስለ ማያውቁት ቦንድ እያነሱ ለዚህ ያልተባበረ ከዜግነት ውጭ የሆነ ነው እያሉ መስበክ የሚያስጠይቅና  ከእምነትም አውጥቶ የሚጥል ታላቅ ስህተት ነው

ክፍል .፦ውግዘት በኢትዮጵያዊዩ


ባህላችን ግንዛቤ


ውግዘት በስነ መለኮት ትምህርት፤ አዳም ከገነት የወጣበት እና በምትገለባበጥ   ሰይፍም ከእጸ ህይወት የተከለከለበት መሆኑን እንዳየነው፤  በባህላችንም ውግዘት  የሚያከናውነው ትልቅ ሚና አለው።  አሁን በየቦታው መነኮሳቱ ካህናቱ ጳጳሳቱ ፈጸሙት የሚባለው ውድቀት ይቅርና፤ በህብረተ ሰቡ መካከል አንድ ሰው ከባህል ጋራ የተጋጨ ነገር ከፈጸመ ተጸጽቶ እስኪመለስ ድረስ ሌላ ቀርቶ እሳት እንዲጭር (ትንሽ ርዳታ) አይፈቀድለትም ነበር። ይህን በመሳሰሉ ባህላውያን ውግዘቶች (ገደቦች) ህዝባችን ተጠብቆ ቆይቷል።            

ውግዘትን የሚያስከትል የህሊና ጉድፈት (guilty conscious) ነው። በህብረተ ሰብ መካከል በህሊና ጉድፈት የሚኖር ካለ ተጸጽቶ እስኪመለስ ከህብረተ ሰቡ ተቆርጦ እንዲቆይ የማዕቀብ ሰይፍ በሱና በማህበረ ሰቡ መካከል እንዲሰነዘርበት ባህላችን ያዝዘናል። ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ብራውን የሚባሉት አሜሪካዊት ሊቅ “Guilt is an inside alarm that signals the need to change course. Once a person determines to change, he or she can look back on the past and learn from it.”(Elizabeth B. Brown, Living Successfully with screwed- up people pp. 173) እንዳሉት ማለት ነው።

ኢትዮጵያዊው ባህል፤ የህሊና ጉድፈት የሚያስከትለው ውግዘት ጊዜአዊ ጉዳት እና ዘላቂ ጥቅም ካለው ከምጥና ከእትብት መቆረጥ ጋራም ያመሳስለዋል። ጊዜአዊ ጉዳት በኃጢአት የተሰጸነሰውን ለማዋለድ የሚካሄደ ምጥ እና እትብቱን ቆርጦ ለመገላገል የሚደረገው ትግል ነው። ዘላቂው ጥቅም ደግሞ ብርሃን ለማየት ለተሻለ ህይወት ለማዘጋጀት ነው።

በባህላችን በስህተት በተንኮል በምቀኝነት በአድማ በሀሰት ማውገዝ ወይም ማእቀብ ማድረግ፤ የበለጠ ስርየት የሌለው በደል ነው። ይሁን እንጅ በሀሰትም ቢሆን  የተወገዘ ሰው፤ውግዘቱ  ከላው ላይ እስኪወድቅ ድረስ  ውግዘቱን ተቀብሎ ከቆመበት መስመር ዘወር ማለት አለበት። በእውነት ላይ የተመሰረተ እና ህሊናው የሚያውቀው ከሆነ ውግዘቱን በትህትና ተቀብሎ ውግዘቱ ለሚጠይቀው ዋጋ ክፍያ ታዛዥና ዝግጁ መሆን አለበት። በፈቃዱ በትህትና ስህተቱን አምኖ ለንስሀ ተዘጋጅቻለሁ ካለ ንስሀውን ከፈጸመ በኋላ ወደ ቦታው በክብር ይመለሳል። በማይረታበት  ስህተት ክዶ ከተከራከረ ክርስቶስን ዳግመኛ መስቀል ነውና፤ በበደል ላይ በደል እንደጨመረ ተቆጥሮ በቅኔ ከቀደመ ክብሩ ዝቅ እንዳለ ይቀራል። ይህ እምነታችንም ባህላችም የሚያዝዘን መመሪያችን ነው።

“ከመ ኢያዕቢ ልቦ እምአኀዊሁ ወከመ ኢይህድግ እምትእዛዙ ለእግዚአብሔር”(ዘዳ ፲፯፡፲፱) ይህም ማለት፦ ውግዘት የሚያስከትሉ ተግባራት ከትእቢት የሚፈልቁ ከህዝብ እና ከፈጣሪ ጋራ የሚያጋጩ ናቸው። ህብረተ ሰቡ የሚወስነው ውግዘት ተወጋዡን ከሁሉም ጋራ ለማስታረቀ ስለሆነ፤ ውግዘቱን ጥሶ ና አቃሎ በክፉ ተግባሩ  ሲቀጥል፤ ሌላውም አብሮ ተስማምቶ እንዲቀጥል የሚረዳ ካለ፤ ግለ ሰቡ ተሎ እንዲመለስ ለመርዳት የሚደረገውን ረደኤት መስበር ነው። ይህን የሚያደርጉትን ሰዎች ህብረተ ሰባችን ማሟለግና መሟለግ ነው ብሎ ይጸየፋቸዋል።

በዝሙት በመከሰስና በመወቀስ ላይ ካለ ካህን ጋራ ኪዳን የሚያደርሰውንና  የሚቀድሰውን ከዚህ በከፋ ሁኔታ ይጸየፈዋል።

በዝሙት ላይ ሆነህ ንስሀ ሳትገባ መቀደስህን አቁም በመባል ላይ ያለ ሰው ይቅርና  ሁለት ሰዎች ለመጋደል በሚያደርስ ጸብ ውስጥ ሲገቡ፤ አቅም የሌላት እቤርት (የእድሜ ባለጸጋ እናት) በእግዚአብሄር ይዣችኋለሁ አቁሙ! የሚለው ድምጿ እንደ ሚቆርጥ እንደ ሚበጥስ ሰይፍ ይፈራ ይከበር ነበር። ከደካማዋ እናት የሚወጣው የውግዘት ድምጽ በዙፋን ተሰየሞ ከሚፈርድ ዳኛ በላይ ስልጣን ነበረው።

ለእምነት ለሞራል ለስነ ልቡና ለታሪክ እንደ ምንጭ በምትታየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ስህተት በሚፈጥር ሰው ይቅርና፤

·       በመንደር አጥር የጣሰ

·       ድንበር ያፈረሰ

·       ሴት የደፈረ ነው ከተባለ፤

ተጸጽቶ እስኪመለስ ድረስ ዘመድ አዝማድ ሳይቀር እሳት እንዳይጫጫር (ትንሽ እርዳታ) ማግኘት እስከ ማይችል ድረስ እንደ ሰይፈ ነበልባል የሚፈራው ውግዘት ይሰነዘርበት ነበር።  

ይህን ኢትዮጵያዊ ውግዘት  በባህላችን  እንደነበረና እንዳለ እን መኖሩን የማናውቅ ካህናት ስለበዛን፤ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ የታጠቀውን ሰይፈ ነበልባል ተገፎ በወገቡ ላይ የሰይፉ ማፉዳ (አፎት) ብቻ ተንጠልጥሎ እንዲቀር ሆኗል። ይህም ማለት የወያኔ መንግሥት ሁላችንንም እብጠት የማይፈውስ “ያበጠ ምላጭ” አድርጎናል። በዚህ ምክንያት በቨርጂንያ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን የተከሰተውን ችግር በዚያው በቨርጂንያ፤ በዲሲ፤ በሜሪላንድ አካባቢ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ካህናትና ምእመናን መፍታት አልቻሉም

 

ክፍል .፦የቨርጅንያ ኪዳነ ምህረትን ቤተ ክርስቲያን የገጠማት ችግር


ከመግቢው ላይ በቦታው እገልጸዋለሁ ብየ ያለፍኩትን ችግር እንደሚከተለው ለመግለጽ እሞክራለሁ። ኢሳት ሶስተኛ አመቱን ባከበረበት እለት ተገኝቼ ወደቤቴ ከመመለሴ በፊት በኢሳት ውስጥ ተሰባስበው የሚያገለግሉት ወገኖች እያደረጉ ያሉት ስራ የነብያት እና የካህናት ስራ በመሆኑ ለማየትና ይህን የተቀደሰ ተግባር የሚያከናውኑበትን ቦታ ለመጎብኘት  ሄድኩ። ቢሯቸው ከኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ህንጻ ባጥር የተለየ ሆኖ አየሁት። ሁለቱንም የኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያንን ቄሶች ስለማውቃቸው፤ እግር ጥሎኝ ከደረስኩ ተሳልሜ እነሱንም ሰላም ብየ ልለፍ ብየ የወሰዱኝን ሰዎች በመኪናቸው እንዲቆዩኝ ጠይቄ፤ ለመሳለም ሄድኩ። የቤተክርስቲያኑ ህንጻ በር ተዘግቷል። በውጭ እየተሳለሙ የሚሄዱ ሰዎች አየሁ።

  በስተጀርባ የተቀመጡ ሰዎች አግኝቼ ከቄሶች ጋራ እንዲያገናኘኝ ጠየኩ። በሳብ የደቀቀ  የሚመስል ወጣት ከተቀመጠበት ካንድ ሽማግሌ ጎን ተነስቶ ወደኔ መጣና ሁለቱም ቄሶች እዚህ ነበሩ ብሎ  ወደቢሯቸው መራኝ። ሳንኳኳ እጃቸውን በወጣነታቸው ዘመን በጥቁራት ያስጌጡ፤ ማርያም መግደላዊትን መስለው አንዲት ቀይ እናት ብቅ አሉ። “ማንን ይፈልጋሉ?” አሉኝ። “ሁለቱን ቄሶች ነው” አልኳቸው። “ቄስ ሀብቴ ሌላ ስራ ጀምረዋል። አባታችንም (ቄስ ታደሰ) ማለታቸው ነው። “አሁን ወጣ አሉ” አሉኝ። “ማን ይባላሉ ?” ብለው ጠየቍኝ። “አስተርአየ” ብያቸው ምልስ ስል፤ ሁለት ሰዎች ከኋላየ ተከትለው መጥተው አስቆሙኝ። “ማን ይባላሉ? ብለው ጠየቁኝ። “አስተርአየ” አልኳቸው።

“ይህን ስም ለሴትዮዋ ሲናገሩ ሰምተናል” በሌሎች ቄሶች ላይ እንደምናየው ያጠለቁት ቀሚስ የተከናነቡበት ክንብንብ ባናይም በለበሱት ልብስ በያዙት መስቀል የኦርቶዶክስ ካህን ይመስላሉ? ሌላ የሚጠሩበት የማእረግ ስም የለዎትም?” ብለው ጠየቁኝ። ከቄስ የበለጠ ምን ማእረግ አለ? አልኳቸው። “ቀሲስ አስተርአየ የሚባሉት ነዎ?”  ብለው ጠየቁኝ። “አዎ ነኝ”አልኳቸው። ጥያቄ ቢኖረን መጠየቅ እንችላለን?” አሉኝ። ‘ደስ ይለኛል። ግን በችኮላ ላይ ነው ያለሁት። እንደምታዩዋቸው በዚያ መኪና ውስጥ ያሉ ሰዎች እየጠበቁኝ ናቸው” አልኳቸው። “የሚቸኩሉበት ጉዳይ ከሌለዎ  እነሱን ያሰናብቷቸው እና እኛ ከሚፈልጉበት ቦታ እናደርሰዎታለን” አሉኝ። አብረውኝ ከነበሩት መካከል አንዱ በኢሮፕ የሚኖር ነው። ይመለሳል። እኔም ወደ ቦታየ ነገ እመለሳለሁ። ለብዙ ዘመን ተለያይተን ከኖርን በኋላ፤ እንዳጋጣሚ በኢሳት ስብሰባ ላይ ስለተገናኝን ከሱ ጋራ ያለኝን የናፍቆት ጊዜ አልጨረስኩምና ይቅርታ አድርጉልኝ” አልኳቸው። “እንግዲያውስ ፈቃደዎ ከሆነ የስልክ ቁጥረዎን ይስጡን” ብለውኝ፡ ሰጥቻቸው ተለያየን። 

ወደ ማታ ደወሉና የሚቀጥለውን ጠየቁኝ። “አንድ ሰው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ስም በሰበሰበው ገንዘብ በስሙ ህንጻ ተከራይቶ በቅዳሴው በታቦቱ ራሱን ሸፍኖ የራሱን ሥጋዊ ፍላጎት እያረካበት እንዲኖር ቤተ ክርስቲያናችን ትፈቅዳለች? ብለው ጠየቁኝ። “ቤተ ክርስቲያን የእምነት የቅድስና የሞራል ምንጭ ናት። ይህን የሚያደርጉ ካህን ካሉ “ንዑስ ክርስቲያን ተብለው ውጣ መባል ያለባቸው ናቸው” ብየ መለስኩላቸው።

እነሱም መለሱና፤ “ከቤተ መቅደስ ይውጡ ብንላቸው ሆን ብለው ለዚህ ዓላማቸው  አስቀድሞ በመዘጋጀት ማንም እንዳይጠይቃቸው በእሜሪካ ህግ ህንጻውን በራሳቸው ስም አስመዝግበው ራሳቸውን በመሸፈናቸው ልናስቆማቸው አልቻልንም አሉኝ። “የጌታችን ክርስቶስን ትእዛዝ በመከተል፤ መጀመሪያ  በጥሞና በፍቅር ቄሱን አነጋግሯቸው። ከሰሟችሁ መልካም ነው። ካልሰሟችሁ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ሁለት ሶስት ሰዎች ይዛችሁ ምከሯቸው። ከሰሟችሁ መልካም ነው። ካልሰሟችሁ ለመላው ህዝበ ክርስቲያን አሳውቁ” አልኳቸው። “አሳውቀናል’ አሉኝ። “በዲሲ ዙሪያ ያሉት ካህናት ይህንን ያውቃሉ?” ስላቸው “አዎ በራዲዮ ሳይቀር ደጋግመን  ነግረናል። እንዲያውም የልጆቼን እናት እነዚሁ ቄስ ወሰዱብኝ ከኔም ከልጆቼም ለዩዋት ትዳሬም ፈረሰ እያለ በራዲዮ ሳይቀር ለህዝብ የተናገረ ሰው አለ። አሉኝ።

 “እናንተ ኃላፊነታችሁን ተወታችኋል ሸክም የለባችሁም። ሸክሙ ስህተቱን በሚጸሙት ካህን እና፤ ይህን ወቀሳና ክስ እየሰሙ በቅዳሴና በጸሎት የሚተባበሩ በመላው ካህናት ላይ ነው። ይህን እየሰማ በቄሱ እጅ በሚቆርበው እና በሚገለገለው ህዝብ ላይ ጭምር ነው” አልኳቸው። “ብዙ ምእመናን እየተጎዱ በእምነቱ ላይ ጥያቄ እየፈጠሩ ናቸው። ለዚህ ዓይነት ችግር ቤተ ክርስቲያን ምን ጽፋለች ምንስ የምትለው አላት? አሉኝ” “እንደነገራችሁኝ ንብረቱን በስማቸው ይዘውታል። መንግስት እስኪነቃባቸው ድረስ በንብረቱ የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ። ነገር ግን እንደ  ወጥመድ የሚጠቀሙበት በስማቸው ያስመዘገቡት ንብረት ብቻ ሳይሆን፤ ሁላችንም የምንጠቀምበት መጽሀፈ  ቅዳሴያችንና ያገልግሎቱ ስርአት የጋራችን ስለሆነ በነገረ መለኮት ትምህርታችንና በስርአተ ቤተ ክርስቲያናችን ስርአትና ደምብ ማስቆም መብት አለን።” አልኳቸው። ሁላችንም ሳንከፋፈል ተባብረን ለመንግስት በማስረጃ ካቀረብነው  ንብረቱንም ቢሆን ያሜሪካ መንግስት “ bogus ወይም spurious” በሚለው ፈርጆ ሊነጥቃቸው ካሜሪካ ምድርም ሊያስወጣቸው ይችላል” አልኳቸው። ይህን በጽሑፍ አርገው ሊያቀብሉን ይችላሉ? ብለው ጠየቁኝ። “የቤተ ክርስቲያናችን መመሪያ ስለሆነ፤ ለናንተ ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያናችን አካል የሆነ ሁሉ እንዲመለከተው  በሚዲያወች አማካይነት ላቀብላችሁ እችላለሁ” ብየ ተሰናበትኳቸው።

በገባሁት ቃል መሰረት ለማቀርበው ጽሑፍ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት፤ በቄሱ ትዳሬ ፈረሰ የሚለውን አቶ ቴወድሮስ የተባለውን  በስልክ  አነጋገርኩት። የቤተ ክርስቲያናችንን መመሪያ በመከተል፤ የሚፈጽሙትን የዝሙት ተግባር ያቁሙ። የሚያካሄዱትንም የክህነት ተግባር አቁመው ንስሀ ይግቡ ብሎ  እንደመከራቸው፤ ምክሩን ባለመቀበላቸው ጉዳዩን ለህዝብ እንዳቀረበው ነገረኝ። ባባ ማትያስ ለሚመራው ሲኖዶ ወኪል ለአባ ፋኑኤልም ሳይቀር ካህኑ የፈጸሙትን ስህተት አቅርቦላቸው በዓለማዊ ዳኛ ክሰስ ብለው  እንደሸኙት ነገረኝ።

በዲሲ ዙሪያ ካሉት  ካህናት እንደተረዳሁት አባ ፋኑኤል ከቄስ ታደሰ ጋራ ጥብቅ ግንኙነት እንዳለቻው አብረውም እንደሚቀድሱ  በዓልም አብረው እንደሚያከብሩ ነገሩኝ። አባ ፋኑኤልም ማህበረ ካህናቱን አፍርሰው፤ ወደ አቡነ ጳውሎስ በመቅረባቸው ጵጵስናው እንደ ሽልማት ተሰጣቸው እንጅ፤ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ለጵጵስና የሚበቃ ሙያ መንፈሳዊነትና ብቃት እንደሌላቸው በሰፊው ሲነገር ስለምሰማ፤ቤተ ክርስቲያኑንም በስማቸው በማስገመዝገብ ከህዝብ ጋራ ተሟገቱ የሚባል ነገርነ ገርም ስላለ፤ ግንኙነት ባይኖረኝም፤ ስለዚህ ጉዳይ  ለምሰጠው ምስክርነት ሙሉ ሀሳብ ለማግኘት በስልክ አነጋገርኳቸው። የነገሩኝ ነገር ለአቶ ቴወድሮስ ከሰጡት መልስ ጋራ ተመሳሳይ ነው።

አባ ፋኑኤል ከዚህ ቀደም በምን ምክንያት እንዳወገዙ ባይገባኝም አንድ ሰው አውግዣለሁ በማለታቸው የተጻጻፉት ነገር እንደነበረ ትዝ ብሎኝ ከኮንፒውተር ገልጨ ተመለከትኩት።  [የተያያዥ ደብዳቤን ሙሉሳቡ ለማግኘት ይህን ሰንሰለት ይጫኑ፦ደብዳቤው]:: ግለ ሰቡን ያወገዙበት ምክንያት በቤተ ክርስቲያናችን መርሆ ሲመዘን፤ በቨርጂንያ አካባቢ ተፈጸመ ከተባለው ስህተት ጋራም ሲነጻጸር፤ አባ ፋኑኤል ውግዘትን የግል ስሜት መፈጸሚያ የሚፈልጉትን የሚከላከሉበት የማይፈልጉትን የሚገሉበት ጠበንጃ እንዳደረግት ተረዳሁ።

በሊቀ ጳጳስነት የክፍሉ ሃላፊ ነኝ ብለው በሚመሩት ሀገረ ስብከት ይህ ሁሉ ጉድ ሲፈጸም ዝም ማለታቸው ይልቁንም አብረው መቀደሳቸው እሳቸውም ይህን ነገር ተቀበለውታል፤ ወይም ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ምንም ግንዛቤ ሳይኖራቸው ጵጵስናውን በገንዘብ ገዝተውታል ማለት ነው። ይህችን ቤተ ክርስቲያን የማያውቃት ጉድ ከላይ እስከታች እንደወረራትም ደመደምኩ። ያለነዚህ አመራር አትጸድቁም የተባለ ይመስል እነዚህን ብጹዕ አባታችን እያለ የሚጠራቸው ህዝብም በጨለማ ውስጥ እንዳለም ተረዳሁ።

የነገረ መለኮቱ ትምህትቻን ስላልተማሩ ሊከብዳቸው ይችላል፤ ባህላችንንም ሊረሱት ይችሉ ይሆናል፤ ለመሆኑ ቤተ ክርስቲያኑን ሲጀምሩ ምን ብለው አስመዝግበውት ይሆን? ብየ ራሴን ጠየኩ። ራሴ የተጓዝኩባቸውንም ወደ ኋላ መለስ ብየ ለማስታወስ ሞከርኩ፦

ለምሳሌ፦

፩ኛ፦ ወደ ዲስ እንድመጣ ከጋበዘኝ  ከዋሸንግተን መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ መተዳደሪያውን  ሲቀርጹ ከነ አቶ ክፍሌ ወዳጆ ወልደ ጊዮርጊስ አንዳርገህ በላቸው ኮረኔል አስፋው ዶ ክተ አክሊሉ ከመላከ ገነት ውቡና አቶ ጌታነህ ጋራ ተሳትፌአለሁ። ይህም  ከእምነቱ በተጨማሪ ባህል ታሪክ ሞራል ፊደል እናስተምራለን የሚል ነው።  

፪ኛ፦ ከአቡነ ማትያስ ከተለየሁ በኋላም በቅዱስ ብርኤል ስም ኮሎምብያ እና 14ኛ መንገድ በሚገኘው በቅዱስ ጊዮርጊስ አንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ህንጻ የጀመርነው ከነ አቶ ቀናው፤ ዝናቧ፤፤ ማርታ ኢየሩሳሌም፤ ከሚባሉት ጋራ የጀመርነው እኛ ነበርን።

፫ኛ፦ የስያትል ማኑዔልንም ቤተ ክርስቲያንን ባይሎም የመጀመሪያው ቄስ እኔው ስለነበርኩ መመሪያው በውስጡ የያዘውን አስታውሳለሁ  

፬ኛ፦ ከቅዱስ ገብርኤል የጽዋ ማህበር አባላት እና ከሌሎችም በከተማው ከሚኖሩት  ሰዎች ጋራ ተባብረን መሰርተን ከሁለት አመታት በኋላ ለአቡነ ዜና ያስረከብኳቸውን   ስያትል ቅዱስ ብርኤል ቤተ ክርስቲያን የሰራነውን የመተዳደሪያ ደንብ አስታወስኩ።  

፭ኛ፦ የሴንት ሉስ ቤተ ክርስቲያንንም እንደዚሁ፤

፮ኛ፦የከንሳስ ዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ያባ ማትያስን የተሳሳተ እምነትና ትምህርት ተቀብላ በተሳሳተ መንገድ መጓዝ ከመጀመሯ በፊት ትመራበት የነበረውን  መተዳደሪያ ደንብ አብሬ የሰራሁት ስለሆነ አስታውሳለሁ።

፯ኛ፦አሁን ያለሁበትን የከንሳስ ድኃኔ ዓለምን ቤተ ክርስቲያን ካስመዘገቡትም አባላት ጋራ አብሬ ስላለሁ አውቀዋለሁ። አባ ማትያስ ካመጡት አይነት የተሳሳተ  ትምህርት እምነት ለመከላከል “በሊቃውንቱ መጻህፍት ተብራርቶ ከተሰጠን በብሉያት በሀዲሳት ከተገለጸው ነገረ መለኮት ውጭ አዲስ እምነትና ትምህርት አንቀበልም። ከየኦሬንታል አብያተ ክርስቲያ ናት ጋራ አንድ ነን። ያባ ማትያስን እምነት ትምህርት ከማያወግዙ። ቀጥተኛውን ነገረ መለኮት  ከማይቀበሉና ተቀብለውም ከማይመሰክሩ  ከዘመናውያን ቄሶች መነኩሴዎችና ጳጳሳት፤ እንዘምራለን ከሚሉ አሸብሻቢዋች ጋራም አንድነት የለንም” የሚል ከመጨመራችን በቀር ሞ ራል ታሪክ ባህል እናስተምራለን  የሚለው ለስድስቱ አብያተ ክርስቲያናት መተዳደሪያ ደንቦች ጋራ ይመሳሰላል።

የቨርጂኒያዋን ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያንም  ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነገረ መለኮቱ ባሻገር ኢትዮጵያዊውን ባህል ታሪክና ሞራል ስነ ምግባር ፊደል እናስተምራለን የሚለውን ሳይጨምሩ እንደማያስመዘግቡ እርግጠኛ ነኝ። ታዲያ እንዲህ ከሆነ እናካሂዳለን ብለው ካስመዘገቡት ከተቀደሰው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትና ስርአት እየተጋጩ እየደለምን?  ባስመዘገቡበት መመሪያቸው ለመፈጸም የገቡትና ቃል እያፈረሱ እራሳቸው ካዘጋጁት መመሪያ ጋራ በመጋጨት ያማሪካውንስ ህግ ቢሆን እያታለሉ አይደለም? መጀመሪያ ሲያስመዘገቡት እንፈጽማለን ብለው የገቡትን ትተው በተቃራኒው አባላቱ የማይፈልጉትን ከመመሪያቸው ጋራ የሚጋጭ ነገር የሚፈጽመውን ስህተት ያሜሪካ ህግ ይቀበለዋል? ብየ ራሴን ጠየኩ።ከሞላ ጎደል መረዳት ይኖረኝ ዘንድ ይህችን ጽሁፍ ከማዘጋጀቴ በፊት የሚመለከታቸውን ሰዎች እንዳነጋገርኩ፤ በቨርጅንያ የተከሰተውን ውዝግብ አሜሪካስ እንዴትይመለከተዋል? በማለት በመጀመሪያ በነበሩት ተወላጆች መካከል እና በኋላም ከኢሮፕ በመጡት ሰዎች መካከል የነበረውን ባህላዊ ውዝግብ ፍጭትና መጣጣም አቅሜ የፈቀደውን ለመረዳት ሞከርኩ።

ክፍል .፦አሜሪካ ይህን ውዝግብ


እንዴ ይመለከተዋል?


Colin G. Calloway  የተባሉ ስለ አሜሪካ ያጠኑ ምሁር “Europeans also imported blackflies, cockroaches ,rats, and house mice  “They also, inadvertently, imported new weeds, dandelions ,thistles, stinging nettles, chichweeds mayweeds,  nightshades, and plantain, which Indians called “Englishman’s Foot ,”because it seemed to spring up wherever  the newcomers  “have trodden, & was never known before the English came into this country .”(13- 14 ) እንዳሉት፤ ማለትም፦ የአገሪቱ ተወላጆች አውሮፓውያንን “ጥቁር ዝንብ፤ በረሮ፤ አይጠ ሞገጥ፤  የቤት አይጥ እና አሳማ ሁሉ አመጡብን።ይህም ብቻ አይደለም።  ወደ አሜሪካ ከመምጣቸው በፊት በምድራችን አይተናቸው ረግጠናቸው የማናውቃቸውን የአረም አይነቶች አመጡብን” እያሉ ወቅሰዋል። ይሁን እንጅ  “funneled into Indian an inventry of munfuctured goods ….. and shirts jackets በማለት በበጎ ጎናቸው ደግሞ የሚጠቅሙ ነገር ይዘውልን መተዋል እያሉ አውሮፓውያንን አመሰግነዋቸዋል። እየሰከኑ ከመጡ በኋላ እየሆነ ያለውንም ደግሞ  “defines ethnicity not as something  static and constant but as “a dynamic relation between different cultural groups,”who continually modify their understanding of themselves in light of shifting relationships with others.”(2) ብለው ይህም ማለት “ዘር እና ነገድ መጋረጃ ሳይሆን የተለያዩ ባህሎች ባሏቸው ነገዶች መካከል ጠንካራ ግንኙነት እያዳበረ እርስበርስ ለመዛመድ ለመማማር የማወቅ ችሎታቸውን ወደ በለጠ ግንዛቤ ለማሻገር ግንኙነት በመቀያየር ብርሃን በዚህ መንገድ ተገነባች” እያሉ  የአሜሪካን ስነ ህይወት ገልጸውታል።

እንደነ Dinesh የመሳሰሉት ወደ ዚህ አገር መጥተው ተምረው ከጨረሱ በኋላ፤ በአገራቸው ጥለውት በመጡት ህዝባቸው አይን አሜሪካን ዘወር ብለው ለማየት ወደ ወገናቸው እየተመለሱ የራሳቸውን ወገን “Why are you so eager to come to America? (ለምን ወደ አሜሪካ መምጣት ፈለክ?) ብለው ጠይቀው “Because I realy want to live in a country where the poor are fat.”(77) (ድሆች የሚወፍሩባት አገር ስለሆነች ነው።”ብሎ የመለሰላቸውን ተመለከትኩ።

እኛም ብዙወቻችን በተለይ ካህናት ይህን እያሉ ከመጡ ሰዎች በተለየ መንገድ የመጣን አይደለንም። እንግሊዞች ዝምብን አረምን እና አሳማን አመጡብን ተብለው ቢወቀሱም በቴክኖሎጃቸው ክሰዋቸዋል። ኧረ እኛ ምን ይዘን መጣን?። ያለን የምንታወቅበት ቅርሳችን ስነ ልቡና፤ የሞራል ልእልና፤ የነጻነት ታሪክ ነበር። ለመጣንበት ላሜሪካ ይህን የነበረንን በማካፈል አስተዋጽኦ ማድረግ ሲገባን፤ ይልቁንም ከቅርብ ወዲህ ከወያኔ መንግስት የቀሰምነውን  ውሸት ማታለል ዝሙት በራሳችን ልጆች በማሪካ ዜጎች ላይ መነስነስ ጀመርን፤ በተቀደሰችው በቤተ ክርስቲያናችን ስም መሆኑ ደግሞ አውሮፓውያን ይዘውብን መጡ ብለው ያገሪቱ ተወላጆች ከከሰሱበት ካይጡ፤ ከሞገጡ፤ ከበረሮው፤ ካሳማው ከኩርንችቱ ከእሾሁ እና ካረሙ እጅግ የከፋ የሰው አዕምሮ የሚደመስ ነው። አውሮፓውያን አረምና ዝምብ ይዘውብን መጡ ተብለው ቢወቀሱም፤ ይዘውት በመጡት ቴክኖሎጃቸው ክሰዋል። እኛ ከወደቅንበት ትዝብት በቀር አሜሪካን የምንክስበት ምን አለን? በቨርጂንያ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን የሚካሄደውን ውዝግብ የጎረጥ በማየት ዝም ያልክ ቄስ መነኩሴ ጳጳስ ነኝ የምትል ሁሉ መልስ!

ክፍል .፦ ኢትዮጵያን የሚውቁ  የዉጭ አገር ሰዎች ትዝብት


አንድ የአርመን ተወላጅ የሆኑ ቄስ ወዳጄ እንደነገሩኝ፤ ኢትዮጵያም medieval history እንደሚገልጻት የዛሬይቷን አሜሪካ ትመስል ነበር። “ለመካከለኛው ምስራቅ ለክርስቲያኑም ለእስላሙም የምትናፈቅ እንሂድባት እኑንርባት በመባል የሚመኟት ነበረች። ወላጆቻችን ይህን ይነግሩን ነበር።ያ ተለውጦ ዛሬ ሁላችንም አሜሪካን መጥተን ተማርን። ከናንተ ቀደም ብለን ወደ አሜሪካ መጥተን ማህበረ ሰባችንን አደራጅተን፤የቤተ ክርስቲያናችን አዳብረን የተረጋጋ ኑሮ በጀመርንበት ዘመን እናንተ መጣችሁ። ወላጆቻችሁ ለወላጆቻችን ያደረጉትን መልካም መስተንግዶ ለመመለስ ተዘጋጅተን ሳለን፤ እርስ በርሳችሁ በመራወር የምትፈነካከቱበት ድንጋይ እንዳይመታን እራቅ ብለን እንድንመለከታችሁ ተገደድን” አሉኝ።

አባ ማትያስ “ተፈስሂ ድንግል ንጽህት ዘወለድኪ ለነ ብርሀነ ጽድቅ፤  ምክሐ ዘመድነ” እየተባለች ስትወደስ የኖረችውን የእመቤታችንን የተፈጥሮ ሰባዊ ባህርይዋን የሚያጠያይቅ ከሰው ባህርይ ውጭ የሚያደርጋትን የተዋህዶ ነገረ መለኮት ምስጢረ ትስብእቱን የሚንድ ነገር፤ ከንሳስ ላይ ይዘውብን በመጡ ጊዜ ተወግዘው ይለያሉ ብሎ ከምስራቅ እና ከኦሬንታል ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት መከከል ያልጠበቀ አልነበረም። ከዚያ ወዲህ “ወደ ኢየሩሳሌም ተዛወሩ” ሲባል ሁሉም አዘኑ። አሁን ደግሞ “እንዲያውም ፓትርያርክ ሆነው ተሰየሙ” ሲባል፤ ይህች ቤተ ክርስቲያን ከጥፋት ወደ ባሰ ጥፋት በመሄድ ላይ እንዳለች ደመደሙ። ይህ ሲካሄድ ዝም ብሎ  እየተቀበለ የሚያስተናግደውም ህዝብ ችግር እንዳለበት ተገነዘቡ። “ለመሆኑ የከንሳሱ ቄስ ምን አለ? ምንስ ተሰማው? እንደተባባሉም ነገሩኝ። “አሁንም ዝም አልልም” ብየ ለነሱ ጥያቄ በሰጠኋቸው መልስ ይህችን ጽሑፍ እደመድማለሁ።


 

ክፍል ፰.፦ዝም አላልኩም፤ አልልምም


እንደሚታወቀው፤ ከዚህ ቀደም ህዝባቸውን ለማገልገል በተዘረጉት ድረ ገጾች አማካይነት ደጋግሜ ባቀረብኳቸው ጽሑፎች ፵፩ ሚሊዮን ህዝብ በመምራት ባለችው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ከመግለጽ ዝም አላልኩም።

ለምሳሌ ፩ኛ፦ከዚህ ቀደም አንድ ሊቀ ጳጳስ በዝሙት ተከሰው እራሳቸው አምነው ኮሌጁም በያዘው ማስረጃ በወሰደው ርምጃ ደንግጨ፤ ኮሌጁንም አነጋገርኩ በቤተ ክርስቲያናችን ዙሪያ በግንባር ለማገልገል ተሰልፈናል የሚሉትንም ሁሉ አነጋገርኩ። [በጳጳሱ ላይ ኮሌጁ የጻፈውን  ደብዳቤ ሙሉሳቡ ለማግኘት ይህን ሰንሰለት ይጫኑ፦ኮሌጁ በጳጳሱ ላይ የወሰደዉን እርምጃ የተጻፈ ደብዳቤ ]::  አንዳንዶቹ ሰው የፈለገውን የሚያደርግበት ነጻ አገር ስለሆነ  ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ነገሩኝ። ራሳቸውንም ሰውየንም ጠየኩ። “ኮሌጁ በኔ ላይ የግል ጥላቻ ስላለው ስሜን ለማጥፋት ያደረገው ነውና በህግ እፋረደዋለሁ አሉኝ።” እስከዚያ ገለል የሚሉበት ቦታ ተዘዘጋጅቶላቸው ቢጠየቁ አልተቀበሉትም። “ስሜ በከንቱ ጠፋ ብለው” ከሰውና ረተው  ነጻነታቸውን ይዘው እስኪመጡ ድረስ በቤተ ክርስቲያናችን መመሪያ መሰረት በአውደ ምህረት ላይ ቆመው መናዘዝ መባረክ ቀርቶ የሚለብሱትን ልብስ የጨበጡትን መስቀል ማስቀመጥ አለባቸው። ይህን ከማድረግ አልፈው ባንዳንድ ቦታ እየተዘዋወሩ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንዳሉ ሰማሁ። ይህን የሚደርጉ ከሆነ ከሰሩት ስህተት በላይ የበለጠ ስህተት ነው። አገልግሎታቸውን የሚቀበሉም ሰዎች ከሳቸው የባሱ እንደሆኑ በራሳቸው እየመሰከሩ ናቸው።  

ለዚህች መልእክት ምክንያት የሆኑትንም ሰው አነጋሬአለሁ። በዋሸንግተን ዲሲ ዙሪያ ያሉትን ካህናትና በተለይም በዚያ ቦታ በዝሙት ከሚወቀሱት ካህን ጋራ የቅርብ ጓደኝነት አላቸው የሚባሉትን አባ ፋኑዓልን አነጋሬአለሁ፤ በኒወርክ ከተማ ያሉትን አቡነ ዘከርያስንም አነጋግሬአለሁ። የቨርጂንያዋ ቤተ ክርስቲያን በሲኖዶሳቸው ዘርፍ የተያያዘች ባትሆንም ጠቅላላዋን ቤተ ክርስቲያን ዝቅ የሚደርግ ይህን ለመሰለ ነገር መፈጸሚያ ስትሆን ዝም ማለቱ ተገቢ መስሎ ስላልታየኝ አቡነ መልከ ጼዴቅንንም አነጋግሬአለሁ።

አባ ማትያስ የተሳሳተውን እምነት ከንሳስ ላይ ሲያውጁ፤ በዜግነት በቋንቋ በባህል በመልክአ ምድር ከኛ ጋራ የማይገናኙት፤ በነገረ መለኮት ብቻ ከኛ ጋራ አንድ የሆኑት የኦሬንታል አብያተ ክርስቲያናት ከከንሳስ ክርስቲያኖች ጋራ በመቆም በጽሁፍና በመካከላችንም በመገኘት ትክለኛውን የኦርቶዶክሱን እምነትና ትምህርት የመሰከሩት በሲኖዶሳቸው ስር በመታቀፋችን አይደለም። “ወድልዋኒክሙ ንበሩ ከመ ታውስኡ ቃለ ለእለ ይሴአሉክሙ በእንተ ዛቲ ተስፋክሙ” (፩ኛ ጴ ፫፡፲፭) ተብሎ የታዘዘውን በማክበር ለነገረ መለኮቱ እና ለጋራ እምነታችን ቅድሚያ በመስጠት ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ነገረ መለኮትና ቀኖና የሚመለከታችውም እውነተኛ የቤተ ክርስቲያችን አካላት ሁሉ በዚህ ዓለም እስካለን ንድረስ ከውስጥም ከውጭም የሚገጥሙን ፈተናወች ብዙ መሆናቸውን ከኔ የበለጠ ታውቁታላችሁ። ታዲያ የኦሬንታል አብያተ ክርስቲያናት ከንሳስ ላይ የተወጡን ሃላፊነት እንደ ምሳሌ ለመውሰድ መድኀኒታችን ክርስቶ “ቅድመ ህጽቦ ለጻህል ወለጽዋዕ እንተ ውስጡ፤ ከመ ይኩን ንጽሀ እንተ አፍአሁ” (ማቴ ፳፫፡፳፮) “የውጩ ንጹህ ይሆን ዘንድ አስቀድማችሁ የውስጣችሁን አጽዱ” እንዳለው  ምስክርነታችን ቀጥ ያለና ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ፤ ከራሳችን ህሊና ጀምሮ በካባቢያችን ያለውን ጉድፍ ለማስወገድ  እየታገልን፤ የቦታን ርቀትና መከፋፈሉን በመጠቀም በቬርጂንያ በመፈጸም ላይ ካሉት ስህተቶች የሚመሳሰሉትን የሚፈጽሙትን ሰዎች በቤተ ክርስቲያናችን መመሪያ ለመግታት በትክክል ከተሰለፉት ጋራ መሰለፍ ግዴታችን ይመስለኛል። ከመበታተን ሊሰበስበንና ሊያገናኘንና ወደ አንድነት የሚያመጣንም ይህ ይመስለኛል። በቬርጂንያ ኪዳነ ምህረት ዝሙት ፈጽመዋልና ከቤተ መቅደስ ይውጡ እየተባሉ በመወቀስ ላይ ያሉት ቄስ ታደስ፤ ገንዘብና ጥቅም ፈላጊ ካልሆኑ ለቅድስት ኦርቶዶክሳዊት እምነትና ለቤተ ክርስቲያናችን ክብር ሲሉ የሚወቀሱበትን የዝሙት ተግባር ባይፈጽሙትም በቤተ ክርስቲያናችን ስርአትና በባህላችን ወግና ማእረግ ሲሉ ምእመናኑ ያቀረቡለዎትን ጥያቄ ተቀብለው መቅደሱ ገለል ሊሉ ይገባል።

በዚህ አይነት ወቀሳና ክስ እርሰዎ ብቻ ሳይሆኑ  ሌሎችም የሚወቀሱና የሚከሰሱ እርሰዎ የሚውቋቸው ካህናት እንዳሉ ነግረውኛል። ይሁን እንጅ እስካሁን ባሜሪካ አገር ምን ትላለህ ብሎ የጠየቀኝ እና ልክ አለመሆኑን ነግሬ የተናገርኩትን በጽሑፍ እንድገልጸው ቃል ያስገባኝ  የለም። እኔ የምጠነቀቀው ለጠቅላላዋ ቤተ ክርስቲያን እንጅ ለግለ ሰብ አይደለም። እርሰዎም ይህን መርሆ አድርገው ይህን አደረጉ የሚሏቸውን ሰዎች  ለመፋለም ማስረጃ ይዘው ወደፊት የሚቀርቡ ከሆነ አብሬዎ እንደምሰለፍ ቃል እገባለወታለሁ።

እርሰዎ ግን “ተናጸሩ በበይናቲክሙ ፩ዱ ምስለ ካልዑ” ማለትም፦ ከስህተት ለመውጣት ወደ ስህተት ላለመግባት እርስ በራሳችሁ ለቅድስና ለተሸለ ምግባር ተወዳደሩ ተራረሙ እንጅ፤ አንዱ የፈጸመውን ኃጢአት አንተም ለማድረግ ተወዳደር ማለት እንዳልሆነ ተረድተው የቀረበበዎትን ክስና ወቀሳ  ተቀብለው ስሜ በከንቱ ጠፋ ብለው ያቀረቡለት አካል ነጻ ነዎ እስኪለዎና ህዝቡም ተስማምቶ እስኪቀበለዎ ድረስ በመመሪያችን መሰረት የሚያከናውኑትን ክህነታዊ ተግባር ሊያቆሙ ይገባዎታል።

በእምቢታዎ  የሚቀጥሉ ከሆነ ግን፤ ያቁሙ ብየ ሳንጋግረዎ  “እኔ ብቻ አይደለሁም። ሌሎችንስ ለምን አቁሙ አላሉም” ባሉኝ ጊዜ፤ ከርሰዎ ጋራ በዚህ ግብር የሚተባበሩ እንዳሉ ተረድቻለሁ። ሆኖም ጥቂትም ቢሆኑ ለቤተ ክርስቲያናቸው ክብርና ቅድስና ለመቆም ፈቃደኛ የሆኑትን ካህናት “ይትነስኡ ላዕሌሁ በጽድቅ።ወኢይህድግዎ ይትዐደው ሃበ አባግአ ክርስቶስ” (ፍ . አንቀጽ ፭፡ ቁ ፻፹፭)  በሚለው መመሪያችን መሰረት ያቁሙ እያሉ ከሚጮሁት ምእመናን ጎን ተባብረን  እንድንቆም እጠይቃለሁ። ከቦታው ድረስ መጥቼም ያስመዘገቡትን መመሪያወትን እንዲያከብሩ ያቁሙ ብለው ከሚጠይቁት ምእመናን ጋራ በመሰለፍ ፈቃድ የሰጠዎትን መንግስት የተቀደሰውን ክህነታዊ ተግባር በባህላችን መሰረት ጥያቄያችንን ተቀብሎ  ለማስቆም እንዲተባበረን ወደ መጠየቁ እንሻገራለን።

ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት  የቤተ ክርስቲያናችንን መርሆ  የህዝቡንም ጥያቄ አክብረው ገለል ቢሉ ራሰዎንም ሁሉንም ይጠቅማሉ። ባያደርጉት ግን ተናግሬ ዝም አልልምና፤ ብታቆም አቁም ባታቆም  “ይብህሰከ ረጊጽ ውስተ ቀኖት በሊህ”(የሐ ም ፱፡ )ማለትም በሰይፍ ላይ መቆም ላንተ ይብስብሀል” ብሎ ክርስቶስ ሳኦልን ባስቆመበት ውግዘት የህዝቡን ድምጽ ጥሰው የቀጠሉትን ክህነታዊ ስራ አሁኑኑ እንዲቆሙ አሳስበዎታለሁ። ለሚወስዱት የተቀደሰ እርምጃ እግዚአብሔር ይርዳዎ!

 

ይቆየን::

ለሌሎች ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ጦማሮች የሚከተለዉን ድህረ-ገጽ ይመልከቱ::