Friday 4 April 2014

ወፈ-ግዝት


የምንኩስናን ሥርዐት ያጎደፉ፣ ጣምራ የቀበሮ ባኅታውያን
  ወፈ - ግዝት!

 ወንድሙ መኰንን፣ ከብሪታኒያ

መግቢያ

ወያኔ የማትሞክረው የለም። አንዳንዴ አቅሟን አታውቅም ልበል? በዚያን ሰሞን፣ ቺፍ ሳጂን ዘመድኩን የተባለ የወያኔ ጉደኛ የፖሊስ ባለጊዜ፣ የቮኤውን ጋዘጠኛ፣ ሰሎሞን ክፍሌን በስልክ ሲያስፈራራ፣ “ዋሺንግተን አይደለም፣ ሰማይ ቤት ብትሆን መጥቼ እወስድሀለሁ” ነበር ያለው[1]። የወያኔ ካድሬ ጉዶች፣ በለስ አንዴ ከቀናቸው፣ ሁሌ የሚቀናቸው ይመስላቸዋል። ከኢትዮጵያው ውጪም፣ የኢትጵያውያንን ሕልውና ለመቆጣጠር ያምራቸዋል። ሲያምራቸው ይቅር። ኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጽሙት ግፍ አንሶአቸው፣ ባህር ማዶም የቁጥጥራቸውን መረብ አሻግረው ለመዘርጋት የኢትዮጵያን ገንዘብ እንደ ጉድ ይረጩታል። ኬኒያና ጂቡቲ ቀንቶአቸው ይሆናል። እንግሊዝ ግን፣ ኬኒያም፣ ጂቡቲም አይደለችም። ሆድ-አደሮችን ወያኔ ትቆጣጠራቸው እንደሆን እንጂ ሌሎቻችን ዕምነታችንንም ሆነ መብታችንን አናስነካም። ለዚያ ከደርስንማ፣ ሙተናታላ! እምቢዮው!

ወያኔ፣ የቀበሮ ባህታውያንን በእንኩቤተር በረሀ ላይ ፈልፍላ፣ ወደየቤተክርስቲያናችንና ጋዳማቶቻችን እንደበተነች ውስጥ አዋቂዎች በሚገባ ነግረውናል። የዶክተር አረጋዊ በርሄን መጽሐፍ ያነበበ፣ ወያኔዎች እንዴት አድረገው ገዳም እንደገቡ፣ ከዚያም ገዳማትን በሙሉ እንዴት እንደተቆጣጠሩና፣ እንደምሽጋቸው እንደተጠቀሙባቸው ያስረዱናል። እነዚያ አክሴማ ለብሰው ሙሉ በሙሉ ያኔ እንደዋዛ የትግራይን አቢያተ ክርስቲያናትን የመቆጣጠር ዕድል የገጠማቸው አሳሳቾች፣ አልፈው ተርፈው፣ በጠቅላላው በኢትዮጵያም ያሉትን የዕምነት ተቋሞችን ሙሉ በሙሉ፣ በአስመሳይ መነኰሳት አዝማችነት እንደተቆጣጠሯቸው እንረዳለን። በነገራችን ላይ፣ ጀለቢያም ለብሰው እስላሞችን እንደተቆጣጠሯቸው ገድላቸው ይመሰክራል። ዛሬ እስላሞችንም የሚያሙሷቸው፣ በዚሁ ዘዴ የተተኩሉባቸው፣ አውቆ ሰላሚ የወያኔ ተጋደልቲዎች ናቸው። ስለዚህ፣ ጎበዝ የመነኵሴን ልብስ ለብሶ፣ አጎንባሽ ካህን ባይ ሁሉ  እውነተኛ እረኛ እንዳይመስልህ። ጠርጥር! ተጠንቀቅ! የበግ ለምድ የለበሰ ተኵላ ነው። አገር ቤት ያ ዕቅዳቸው ተሳክቶላቸዋል። ሕጋዊውን ፓትርያርክ ፈንግለው፣ የራሳቸውን አሻንጉሊት ፓትርያርክ ጎልተው፣ በታጋይ ጳውሎስ አዝማችነት ቤተክርስቲያናችንን ምስቅልቅሏን አውጥተዋል። ሕገ-ወጡ ፓትርያርክ፣ አሽመድምደዋት ነው የሞቱት። ሕጋዊው ፓትርያርክም ወደመንበራቸው ተመልሰው፣ ቢችሉ እንዲቀጥሉ፣ ባይችሉ መንበረ ፕትርክናውን በሰላማዊ መንገድ መንፈስ ቅዱስ ለሰየመው በሰላም እንዲያተላለፉ ዕድሉ ሲገኝ፣ የወያኔ ባለሥልጣናት፣ እነ ዓባይ ጸሐየና ስብሐት ነጋ፣ እንቅፋት ፈጥረው፣ ይኸውና የውስጥና የውጪ ሲኖዶስ ተለያይቶ፣ ምዕምኑም ጎራ ለይቶ የጎሪጥ ይተያያል! እንግሊዝ አገር እየኖርን ግን እኛን ለመቆጣጠር የሚደረገው መፍጨርጨር አቅምን አለማወቅ ነው። ከዚህ በፊት ሞክረው ከሽፎባቸው ተዋርደው ሂደዋል፣ አሁንም ይደገማል! “እምቢ!” በል ወገኔ! እምቢዮው!

እንዳሸን የፈሉ ወፈ-ግዝቶች

ሎንደን ውስጥ፣ “አባ” እንጦንስ፣ የመጀምሪያዋን ድንጋይ ለመወርወር ቀዳሚ ሆነዋል! ድሮ-ድሮ፣ ግዝት ቀላል አልነበረም ሲባል እንሰማ ነበር። “አባ” እንጦንስ፣ ግዝትን የሚያክል ነገር እንዲህ አምቦጫረቁት! ስንት ተጠንቶ፣ ተውጥቶ ተወርዶ፣ ሽማግሌ ተልኮ፣ ላለመገዘት ሁሉ መንገድ ተሞክሮ፣ ታስሦ፣ መኬድ የነበረባቸውን ሥርዓቶቹን ሁሉ አሟልተው ነበር ለዚህ ውሳኔ ላይ የሚደረሰው። “አባ” እንጦንስ፣ ግዝትን የሚያክል ነገር የልጅ ጨዋታ አድርገውት አረፉ! እርሳቸው ምንም አላጠፉም። ለወያኔ ጌቶቻቸው ለመሥራት ነበር ድሮም የተመልምልረ ገዳም የገቡት። ግዴታቸውን ተወጡ። ነገሩ የጠፋው ከላይ ከአናቱ ነዋ!

አሁንም ሥነ-ምግባር ሲበላሽ ተጠንቅቀው የሀይማኖት ግዝት የሚገዝቱ አባቶች መኖራቸውን እናውቃለን። አንድ እንደ እንጦንስ “አባ” ነኝ የሚሉ ዳሩ ግን ያፈረሱ ቄስ፣ ታደሰ ሲሳይ የተባሉ ግለሰብ፣ የራሳቸውን ሚስት ፈትተው፣ የሰው ሚስት አማግጠው፣ የቨርጂኒያን ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን ከምዕምኑ በመቀማት፣ ሕዝቡን ቁም-ስቅሉን ስላሳዩት፣ አቤቶታው ከልክ ስላለፈ፣ የቤተክርስትያኗ ስም እንደካቶሊኮች በዓለም የብዙሐን ሜድያ ከመዳረሱ፣ የአመጸኛውን ምግባረ-ብልሹነት ሶስት ካህናት መርምረው፣ ሕዝቡ በተሰበበት እንደሥርዓቱ እንዳወገዟቸው ሰሞኑን አንብበናል። ያ የሀይማኖት ግዝት ነው። የ“አባ” እንጦንስ ግዝት ግን፣ ከወፈ-ግዝትም ወርዶ፣ የፖሊቲካ ግዝት ነው። አሁን በሞቴ፣ “አባ” ተባዩ እንጦንስ፣ ምን “ከባድ ነውር መልአከ ብርሀን ቀሲስ ብርሀኑ ብሥራት ላይ አየሁበት” ብለው ነው፣  የውግዘት ናዳ ያወረዱት? ዳሩ ምን ያደርጋል፣ የዘመኑ የወፍ ግዝታችሁ የሀቀኞቹን፣ ሥርዓቱን ተከትለው መገዘት ያለበትን ነውረኛ የሚገዝቱት ግዝትን፣ እንደናንተ ባሉት ምግባረ ብልሹ ሰርጎ-ገብ ወያኔዎች ድካማቸው ሁሉ መና ቀረ። ዛሬ-ዛሬ፣ ለገዢዎች ያደሩ እንደ እንጦንስ ያሉ የወያኔ አገልጋዮች፣ ለሥርዐቱ ያላጎበደዱትን የእግዚአብሔር ካህናትን አፋቸውን ሞልተው “ገዝተናችኋል” ሲሉ በአርምሞ ታዝበናቸዋል። ሀቀኞቹም መልሰው “እኛም ገዝተናችኋል” ሲሏቸው፣ ግዝት ከሰማይ መሬት ወርዳ ክስክስ! የካህን ግዝት መሬት ላይ ካላሰረችማ፣ ሰማይ ላይ እንዴት አርጋ ልታርግ? በወያኔ ግፊት፣ ቤተክርስትያናችን ውስጥ መወጋገዝ በሽበሽ ሁኗል። በዚህ የተነሳ፣ ግዝቱ በሙሉ ዋጋ በመጣቱ፣ በሥነ-ሥርዓት ጉድለት ምክንያት የተወገዘውም ችላ ስለሚለው፣ ግዝትን ማንሳትም አላስፈለገውም። በወያኔ ግፊት የተገዘተውም ግዝት ተገዛች፣ በትክክል የተገዘተውም ማሠሪያው ላልቶ፣ አላስር ብሏል። ነገርዮውስ የተጀመረው፣ በደርግ ዘመን ነበር። እንዳነበብነው ከሆነ አቡነ ማትያስ፣ በአቡነ ተክለሀይማኖት ተገዘተውና ተውግዘው ክህነታቸው ተይዞባቸው ነበር እኮ። አቡነ ማትያስ የአቡነ ተክለሀይማኖትን ግዝት ችላ ብለው “ተግባር እንደወትሮው” (business as usual) አሉ። የአቡነ ተክለሀይማኖት ግዝት “አባ” ማትያስን አላሰራቸውም ማለት ነው። ቀድሰው ሲያቆርቡ ኖሩ። አሜሪካ ያቋቋሟቸውም አቢያተ ክርስቲያናት አሉ። አቡነ ተክለሀይማኖት ግዝታቸውን ሳያነሱ ሞቱ። ዛሬ አቡነ ማትያስ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ናቸው። እንግዲህ ማንን አይተን እንደሀይማኖታችን ሥርዐት በግዝት እንታሠር?

ወያኔ የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያው ሲኖዶስ፣ ሕጋዊውን ፓትርያርክ፣ አቡነ መርቆርዮስንና እሳቸውን ተከትለው የተሰደዱት ጳጳሳት፣ በውጪ ያተቋቋሙትን የኢትዮጵያን ኦርቶዶክ ሲኖዶስ አባላት፣ እንዳሉ አወገዛቸው። ስደተኛውም ሲኖዶስም በበኵሉ፣ “የወያኔ ፖሊቲከኛ ሲኖዶስ ገዘተኝ” ብሎ ቀድሶ ማቁረቡን አላቆመም። ዲያቆናትን፣ ካህናትን አና ኤጲስ ቆጶሳትን መሾሙን እንደወትሮው ቀጠለ። ማን ከወፍ-ግዝትም ወርዶ ለፖሊቲካ ግዝት ሊንበረከክ? እንዲያውም ስደተኛው ሲኖዶስ በተራው፣ ወያኔ የሚቆጣጠረውን ሲኖዶስ ፓትርያርክ በሕይወት እያለ ሌላ ፓትርያርክ ሹሟልና ቀኖና በማፍረሱ አውግዞታል። ተወጋዡም የወያኔ ሲኖዶስ፣ ግዝቱን ከቁብም አልቆጠረውም። አንድ አንደበተ ርቱዕ ወንድም ሲናገሩ፣ “እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች፣ አባቶቻችን በሙሉ ስለተወጋገዙ ብንሞት እንኳን ፍትሐት የሚደርሱልን ያልተገዘቱ የነፍስ አባቶች የሉንም እኮ” ነበር ያሉት። ትክክል! እንደዚያማ ከሆነ፣ አንድ ቄስ ነኝ ባይ ያፈረሰ ካህን “ውሀ ቀጠነ” ብሎ ካወገዘን በሰማይም ላይፈታልን ነው???! ውግዘት እንዴት ወረደች ጃል! እኛስ የሎንደኖቹ ክርስትያኖች፣ ለወያኔው ወኪል “ለአባ” እንጦንስ፣ የፖሊቲካ ወፈ-ግዝት ልንገዛ ያምራቸዋል? ለመሆኑ ለመገዘት የግብረ-ግብ ብቃቱስ አላቸው? ሲያምራቸው ይቅር። እምቢዮው!

ወያኔዎች የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያንን ከተቆጣጠሯት በኋላ፣ ግዝትን የሚያክል ተልቅ ነገር፣ አውርደው የልጆች የዕቃ-ዕቃ ጨዋታ አድርገውብናል። እንዲያው ተንቦጫርቋል በሉት! እኚህ የለንደኑ “የወያኔ ሊቀ ጳጳስ” እራሳቸው፣ የተወገዙ ውግዝ ከመ አርዮስ ናቸው። በእሳቸው ብሶባቸው የእግዚአብሔርን በጎች ሰብስበው ወንጌልን እያስተማሩ፣ ከመበታተን ያዳኑንን አባት፣ መልአከ ብርሀን ቀሲስ ብርሀኑ ብሥራትን መጋቢት ፲፬ ቀን ፪ሺ፮ (23 September 2014) “ገዘትኩ” አሉ። ሥልጣን ሳይኖራቸው፣ ሕግ ባለበት አገር ሕግ አፍርሰው ቤተክርስትያናችን ገብተው ተከረቸሙ (ስኳተረር ይሉታል ፈረንጆቹ)። እኛን ባለቤቶቹን ውጪ ውርጭ ላይ አቁሙን። በራሳችን አውደ ምሕረት ላይ ቁመው፣ የራሳችንን ካህን አፋቸውን ሞልተው፣ “ክህነቱን ይዤበት ገዝቼዋለሁ” አሉ። ወገኛ!

“አባ” እንጦንስ በዚያም አላባሩም! “መጥተህ እግሬ ሥር ወድቀህ ይቅርታ ካልጠየቅከኝ ምንጊዜም እንዳትቀደስ፣ እንዳታቆርብ፣ እንዳትጸልይ፣ ወንጌል እንዳትሰብክ ገዝቼሀለሁ” ብለውት እርፍ! ወያኔ ሁሉ ግን “ይቅርታ ጠይቁኝ” የሚል አባዜ ከደደቢት በረሀ ነው የተጠናወተው? ገድሎም እኮ ሟቹን ይቅርታ ሳይጠይቀው በመሞቱ ይናደዳል! አይ አቅምን አለማወቅ! “አባ” እንጦንስ የት የሚኖሩ መሰላቸው? ወያኔ ረግጦ የሚገዛት ኢትዮጵያ? እንዲያውም፣ በምድር ያሰርኩት በሰማይም አይፈታም ለማለት ዳድቷቸዋል። ደንቄም! ዕውነትም የልጆች የዕቅ-ዕቃ ጨዋታ! ተንቦጫረቁት አይደል! እንዲህ ያለውን፣ ፈር የለቀቀ የአምባ ገነንነት ግዝት ሲከስት፣ የቤተክርስቲያናችን ሊቆች “ወፈ-ግዝት” ቢሉትም፣ እኛ ልጆቻቸው ይቅርታ እየጠየቅን የፖሊቲካ ወፈ-ግዝት ብለን አሻሽለንላቸዋል። አይ መውረድ! ሲሆን ሲሆን፣ እንደ መልአክ ብርሀን ቀሲስ ብርሀኑ ብሥራት ያሉ ጥቂት ዕውነተኛ አባቶች፣ ጨለመም በራም፣ ዘነበም አባራም፣ ከመንጋው የማይለዩትን ሀቀኛ እረኞች፣  የጌታን በጎች ሰብስበው አውሬ እንዳይነጥቃቸው ነቅተው በመጠበቃቸው፣ በመብራት ተፈልገው መሾም መሸለም ነበረባቸው እንጂ በምን ዕዳቸው ይወገዛሉ? ለነገሩስ፣ ሽልማቱ ከምድር ሳይሆን ከመንጋው ባለቤት ያገኙታል። ይብላኝ ለቀበሮ ባኅታውያን፣ እንዲህ ዓይነቱን ወፈ-ግዝት ለመገዘት ለደፈሩት! የምጽዓት ቀን እነሱን አያድርገኝ። የፖሊቲካ ወፈ-ግዝት ካሰረንማ፣ ክርስቶስም ላይሰበክ ነው! አይ “አባ” እንጦንስ፣ የመጀመሪያዋን ድንጋይ ለመውርወር ደፍሩ! ከሰማይ የሚወርድብዎትን ናዳ ባዩ!

የቀበሮ ባኅታውያን አዘራር፣  አበቃቀልና መስፋፋት

ውሀ ክጥሩ ነገር ከሥሩ ይባል የለ? የሎንደኑ ይሁዳው፣ የክርስቶስን በጎች ለጥቅማቸው አሳልፈው የሸጡት፣ አቶ (ብትፈልጉ “አባ” በሏቸው) ግሩም ከበደና “አባ” እንጦንስ የለየላቸው፣ ከሁለት አቅጣጫ ጎርፈው በአንደ ወቅት ገዳሞቻችንን የበከሏቸው፣ የቀበሮ ባህታውያን ናሙናዎች ናቸው። ሁለቱም ገዳም አገባባቸው የተለየዩ ዓላማዎችን አንግበው ይሁን እንጂ፣ ለነፍሳቸው አልነበረም የመነኑት። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ ዓላማቸው የማይጣጣም፣ ሁለቱም የማይታረቁ ጠላቶች ነበሩ። ጥላቸው ግን በወደቀ ጥንብ ላይ እንደሚጣላ የጅብ ዓይነት ጥል እንጂ መሠረት አልነበረውም። “እኔ እበላ!  እኔ እበላ!!” አፈር ይብሉ! አሁን አንድ ያደረጋቸው ያው ከተፈጥሮ የወረሱት “የክሕደት” ባሕርያቸው ነው። ሀለቱም ሀሳዊ መንኰሳት ለመሆናቸው፣ መሬት ላይ የሚገኘው የአመነኳኮሳቸው ጭብጥ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ተግባራቸው ሳይቀር ይመሰክርባቸዋል። የፊተኛው በዘመድ አዝማድ ርዳታ፣ በሚሊሺያነት ከመመልመል ለማምለጥ አክሴማ አጥለቀው፣ ቆብ ደፍተው በፊት በር ገዳም ሲገቡ፣ ሁለተኛውን ወያኔ ፊደል የቆጠሩ ተጋደልቲዎችንና ሥራ-ፈት የመንደር አውደልዳዮችን በምንኵስና አሰልጥኖ፣ አሾልኮ አሽሎክልኮ በጓሮ ቀዳዳ ሰርስሮ ወደ ገዳም ያገባቸው የዘረኝነት ሐዋርያት ናቸው። ሁለቱን የሚያመሳስላቸው ለጥቅማቸው አሯሯጣቸው ነው። ለጥቅማቸው ሲሉ ነፍስ ከመግደል አይመለሱም። “አባ” ግርማን አያችሁ አይደል? እንደነዚህ ያሉት ናቸው የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ዛሬ እያመሷት የሚገኙት። ያድህነነ ከመዓቱ፣ ይሰውረነ! አባ እንጦንስ፣ ዕውነተኛውን ጠባቂ እረኛ ለማውገዝ፣ የመጀመሪያዋን ድንጋይ ወረወሩ? እኛስ ለእንደእኚህ ዓይነቱ የቀበሮ ባሕታዊ የፖሊቲካ ወፈ-ግዝት እጃችንን አንሰጥም! ሞኛቸውን ይፈልጉ! አይሠራም። እምቢዮው! እስቲ ክርስትናየን ሲነጥቁብኝ አያለሁ!

የቀበሮ ባሕታውያን የሎንደን ወረራ

ከሁለቱም ቡድን አጭበርባሪዎች ለንደን ላይ ከትመውልናል። መከተማቸው ብቻ ሳይበቃ፣ ከመጀመሪያ ቡድን የፈለቀው የቀበሮ ባህታዊ፣ “ቀጥቅጬ ካልገዛኋቸሁ፣ በረቂቅ ሕገ-ደንቡ ውስጥ ገዳማዊ መነኵሴ አስተዳዳሪ ይሁን ብላችሁ ካልከተታችሁልኝ (ዋ! አልተባለም ትሉና አስራ ዘጠኝ ገጹን ጉዳችሁን ነው ለዓለም ሕዝብ የምዘከዝክላችሁ)፣ የሥልጣኔን ዘመን ዕድሜ ልክ ካላደረጋችሁልኝ፣ ቤተክርስቲያናችሁን ለምትጠሉት ለወያኔ ማስረከቤ ነው” ብለው በወለድ አግድ ያገቱን አራጠኛ ግሩም ናቸው። እነሆ ከመጋቢት ፩ ቀን ፪ ሺ5 (10/03/2013) ዓቢይ ጾም በገባ ማግስት ጀምረው ቤተክርስቲያናችንን ዘግተው፣ ምዕምኑን ውጪ በውርጭ ላይ በትነውናል። “ምነዋ!” ቢባሉ፣ ትንሽ እንኳን ሳይፍሩ፣ “እነዚህ፣ ንጉሳችንን የገደሉ! ፓትርያርካችንን የገደሉ! አገራችንን ገድለው እዚህ ድረስ የመጡ እኛን ቢገድሉ አይደንቀንም”! እያሉ፣ ባልሰራነው ኃጢአት፣ ባልዋልንበት ሜዳ ስማችንን አጠፉ! በዚህ ድር-ገጽ http://www.youtube.com/watch?v=otlM6x8mzWk ወያንኛ አነጋገራቸውን ተከታተሉ። ድንቅ ነው። መልሶ መላልሶ መደመጥ ያለበት የጥላሁን ዓይነት ቀረርቶ ነው። እኛ አይደለንም የቀረጽነው። ወያኔ የመደበላቸው ጉደኛ ካድሬ ነው። እኔ እሳቸውን ብሆን እንዲህ ዓይነቱን ንግግር፣ ነገ በሔድኩበት ጣት የሚስጠነቁልብኝ ዕብደት፣ ተቀርጾ ባደባባይ ከሚታይ፣ እንዲደበቅልኝ ነበር የምማጸነው። አፍ ሲያመልጥና ጸጉር ሲመልጥ አይተአወቅም ነው የተባለው? ጸጉራቸው ቢመለጥ እንኳን በቆቡ ይሸፍኑታል፣ ካፋቸው የወጣውን ጉድ ምን ያደርጉታል?

ግሩም፣ በድንፋታም አልቀሩም። ከሌሎች ከመሰል የወያኔ ቡችሎች እርዳታ አምጥተው እነሆ እስከዛሬ አግተው ይሞግቱናል። መርታት ሲያቅታቸው፣ ከሁለተኛው ባለሥልጣን፣ ከበረሀ ለተቀላቀለው ቡድን፣ የቤተክርስቲያናችንን ቁልፍ አስረክበው፣ “አሁን ትግሉን፣ በኔና በሕዝቡ መሆኑ ቀረና፣ በነሱና በመንግሥት መሀል አድርጌ አረፍኩት” ብለው ይፎክራሉ። ክሕደት ጀብዱ ሁኖ! አይ የቀበሮ ባሕታዊ! ከፍርዱ የሚያመልጡ መሰለዎት! ወያኔም ከነግሳንግሱ ይምጣ! ችግር የለም። ይሸነፋታል! ትዝብት ነው ትርፉ እንጂ፣ ዕድል አገኘን ብላችሁ ከነኮተታችሁ “ብትኳትሩብን” (squaters)፣ እናንተም ሆናችሁ ግሩም፣ ከነግሳንግሳችሁ ነገ በሕግ ተጠራርጋችሁ ተዋርዳችሁ ትወጣላችሁ። ሕገ-ወጡ የወያኔ የቀበሮ ባህታዊ ጳጳስ፣ ለጥቅምዎ ሲሉ ለሕዝቡ ወንጌል እንዳይሰበክ፣ ከሕዝብ ወገን የቆሙትን አንድ የዋህ አባት ላይ ፖሊቲካዊ ወፈ-ግዝትዎን እንዲያው በከንቱ አባከኑ። ማን የቀበሮ ባሕታዊን ግዝት ከመጤፍ ቆጥሮ! የእርስዎ ግዝት በኛ ላይ አይሠራም!

የግል ሕይወታቸው ሲታይ - “አባ” ግርማ የተባሉት ግሩም

የመጀመሪያው ሀሳዊ መነኵሴ፣ አጨበርባሪው፣ ስማቸውን ከግሩም ወደ ግርማ ቀይረው የበበቱ (ባሕታዊ የሆኑት) የቀበሮ ባኅታዊ ናቸው ብዬአችኋለሁ። ስለሳቸው ከዚህ በፊት፣ “አባባሱባት[2]“ከድጡ ወደማጡ[3] በተሰኙት ጽሑፎቼ ቁልጭ አድርጌ ከነማስረጃው መንኵስና ሊላበሱ ቀርቶ፣ ከዓለማዊ ሰዎችም ሺህ ጊዜ የወረዱ፣ ለሥጋዊ ፍላጎታቸው የተገዙ መሆናቸው አሳይቼአችኋለሁ። የምንኵስና ሥርዐት መሐይም በመሆናቸው፣ ወጣቶቹን ሴቶች ልጆች እንደራስፑቲን እያሻሹ አስለምደዋቸው፣ ወጣቶቹ ከመነኵሴ መዳራት ነውር የሌለበት እየመሰላቸው፣ መነኰሳትን፣ በተለይ ጳጳሳት ባዩ ቁጥር፣ ሩጠው ደረታቸው ላይ ልጥፍ! በምስጢር ቢሆን እንኳን ደግ። ፎቶአቸውን በየፌስ ቡክ እዩልኝ እያሉ ማሳየት አመጡ! እኛ ተራዎቹ ምዕምናን ነን፣ “ኡ! ኡ! ኡ! የምንኵስና ስም ጎደፈ። መነኵሴ እንኳን ሴት ደረቱ ላይ ተለጥፋና፣ ድምጿንም መስማት አልተፈቀደለትም!” ብለን በመጮኻችን፣ ወጣቶቹ እየተነጫነጩ ከፌስ ቡካቸው ላይ ያነሱት። ግሩም ምንኩስናን ያስሰደቡ ሰው ናቸው። እኚህን አመጸኛ ሆድ አደርን አጋለጥክ ብሎ የሚጠላኝ ካለ፣ ሺህ ጊዜ ይራገም። ወጣት ሴቶቻችን አሁን አደብ ገዝተዋል። ያን ሥነ-ሥርዓት ነው ማስያዝ የምንፈልገው። መነኵሴ፣ እንደ ግሩም ሥጋዊ አይደለም። የምንኵስናን ሕይወት ለመጪው ትውልድ በትክክል ለማውረስ እያንዳንቻችን ኃላፊነት አለብን። እኚህ ሰው ዓለማዊ ናቸው። አሁን ላጋጠመን መከራና ስቃይ ያጋለጠን በምድርም በሰማየም አንድ ቁጥር ተጠያቂ ናቸው። “እዚያ ሂዶ ይበጥብጥልኝ” ተብለው፣ በታጋይ ጳውሎስ የተላኩብን መዘዘኛ!  ሎንዶንን ለማመስ የተመረጡ መሣሪያ! እኚህ የቀበሮ ባሕታዊ፣ እኛ ጋ ሲደርሱ ሁኔታውን አይተው፣ ታክቲካቸውን ቀይረው፣ ሕዝበ ክርስቲያን ልብ ውስጥ ለመጎዝጎዝ የተጠቀሙበት ዘዴ ለየት ያለ ሰይጣናዊ አሳሳች አካኼድ ነበር። ወያኔንና የሾሟቸውን ታጋይ ጳውሎስን
ለይስሙላ እየተቃወሙ ነበር የተቀላቀሉን። አንዳንድ ጥቂት ቆቆች ከመጀመሪያው፣ የዋሁ፣ ቄሲስ ብርሀኑ ላይ ሲያሳድሙ ደርሰንባቸው ነቅተንባቸው ተቃውመናቸው ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል፣ እንደራስፑቲን የማረኳቸው ሴቶችና ወጣቶች ተሰለፉብን። ሕዝብ ጠባቂ ካህን፣ መልአክ ብርሀን ቀሲስ ብርሀኑን ቁም-ስቅላቸውን አሳይተዋቸው ከአገር ሲያሳድዷቸው፣ በዓይናችን እያየን ተሸንፈን ዝም አልን። ደጋፊዎቻቸው በመብዛታቸው አንገታችንን ደፍተን ተገዛንላቸው። በዚያም አላቆሙም፣ ስደተኛውን መስለው፣ ወያኔን እያወገዙ፣ የገዳማትን መደፈር እየተቃወሙ፣ ከነዶክተር ብርሀኑ ጋር ፎቶ እየተነሱ፣ ገንዘብም እየሰጡ፣ ለነወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ አድናቆታቸውን በአደባባይ እየቸሩ፣ ሰላማዊ ሰልፍ እየወጡ፣ ሰንደቅ አላማችንን እየለበሱ፣ እኛንም ተጠራጣሪዎቹን ሳንቀር ሁላችንንም አንድ በአንድ እግራቸው ሥር አነጠፉን። ተበልጠን ተበላን!

እኚህ የቀበሮ ባሕታዊ፣ ዕውነተኛው ተልኮአቸው የተጋለጠው፣ ታጋዩ የወያኔ ፓትርያርክ፣ ፓውሎስ  ሲያርፉ፣ ባፈሰሱት ዕንባና “ሥራዐተ-ፍትሐት ላድርግላቸው” ብለው ከምዕምኑ ጋር በፈጠሩት ግብግብ ነበር። እስከዚያች ቀን ድረስ፣ “አባ” ግርማ ኃይለኛ ናቸው እንጂ፣ ተንኰል የለባቸውም፣ ለወያኔም አይገብሩም” እያልን፣ ከኔ ጀምሮ፣ እንከራከርላቸው ነበር።ይባስ ብለው ዓቢይ ጾም በገባ ማግስት የቤተክርስቲያኗን በር ምዕምኑ ላይ ጥርቅም አድርገው ከርችመው ዘግተው፣ ለብርድና ለውርጭ ያገለጡን አረመኔ ሰው ናቸው። ኧረ አረመኔ አቅል አለው! እኚህ የይሑዳም ይሑዳ ናቸው እንጂ። በብር በተለበጠ ሰታቴ ሳህን (silver platter) ዘርግፈውን ለሰው በላዎቹ ጠላቶቻችን አስረከቡን። ጲላጦስና ሄሮዶቱስ በእየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ላይ አልነበር የታረቁት? “አባ” እንጦንስና “አባ” ግርማም እንዲሁ!። ደግነቱ፣ የጅብ ፍቅር እስኪቸግር!

አቶ ግሩም/“አባ” ግርማ እንደፈለጉት ግን አልሆነላቸውም። ተቋቋምናቸው ነው የሚባልው!!! ማስፈራራቱ፣ በደብዳቤ ማባረሩ አላዋጣ ሲላቸው፣ ለአቤቶታ፣ ወደ ጌቶቻቸው፣ ወደ ወያኔዎች፣ ወደ አዲስ አበባ ነጎዱ! “ከቅንጅት፣ ከግንቦት ሰባት፣ ከደርግ መኰንኖች እጅ፣ መንግሥት ይታደገኝ” ብለው እንደተማጸኑ እሳቸው እራሳቸው ዜና ቤተክርስቲያን[4] በተባለው፤ጋዜጣ ላይ ተናዘዙ። አኼኼ!!! እንዴት ተሳስተን ኑራል ጃል! አይ “አባ” ግርማ! ገብረው ስለገቡ ወያኔ በየሳምንቱ ለነፍሳቸው ጠባቂ ዘበኛ በሺህ የሚቆጠር ፓወንድ እያፈሰሰ አቆመላቸው። እንዲያም ሁኖ፣ ልባቸው ብር ብር ማለቷን አልተወችም። ሲሲቲቪም በብዙ ሺ
ፓውንድ ገዝቶ ወያኔ ተክሏል። ይኸ ሲሲቲቨ ከርቀት በአይፎን (iPhone) ሳይቀር ለመቆጣጥር የሚያስችል ቴክኖሎጂ አለው። አይ መደደብ! ወያኔዎችን እንፈራቸው ይመስል፣ በየቀኑ እንደ “አባ” ተባዩ ያሉ ሆዳደሮችን እየመረቁ ኤምባሲአቸው ውስጥ ተጎልተው ሲቀዱን ይውላሉ። “አህያም የለኝ ከጅብ አልጣላ” ነበር ያለው ሰውዬው?! (ጅሎች! እንኳን ሲሲቲቪ፣ መትርየስም ብትደግኑ፣ ይኽ የዕምነታችን ጉዳይ ነውና፣ ከዓላማችን ዝንፍ እንደማንል፣ ማን በነገራችሁ! እንዲሁ ነው ገንዘባችሁን የምትከሰክሱት።) የቀበሌው ባለሥልጣናት “ያለፕላን የተተከለውን ሲሲቲቪ አንሱ” ሲሏቸው የጌቶቻቸውን ዲፕሎማሲያዊ ጡንቻ በመተማመን ይመስላል፣ “አባ” እና ደንገጡሮቻቸው፣ አሻፈረኝ ማለትን መረጡ። የካውንስሉን ትዕዛዝ ጣሱ። እስቲ ፍርድ-ቤት ስንደርስና ይኸ ጉዳይ እንዴት እንደሚታይ እናያለን። ልብ በሉ! ሸፍጠኛው መንኵሴ ነኝ ባይ ጉደኛ፣ ያኔ-ያኔ ድሮ-ድሮ እንደመጡ፣ “ስደተኛ ነኝ” ብለው እጃቸውን ለእንግሊዝ መንግሥት መስጠታቸውን አትርሱ። “ወያኔ አሳደደኝ፣ ቆረጠኝ፣ ፈለጠኝ፣ አሰቃየኝ” ባሉበት አፋቸው፣ ያንኑ ወያኔ “አድነኝ” ብለው የሙጥኝ ያዙ። የፋራ አጭበርባሪ! ዛሬ ለጠበቃ የሚከፈለውን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ የሚሸፍንላቸው ወያኔ ነው። ከጎናቸው ቁሞላቸው የሚሟገተን ወያኔ ነው። የወያኔ ዓይን ያለው፣ የቤተክርስቲያናችን ቁልፍ ላይ ነው። ተቀብለው ለበለጠ ታማኛቸው፣ ለሁነኛቸው የግል ሥልጡን የቀበሮ ባኅታዊ፣ “ለአባ” እንጦንስ አስረከቡ። ግሩም፣ ድሮም ሳይበቁ መነኑ። ሳይገባቸው ከነኑ (ካህን ሆኑ)። ሳይፈልጉ መነኮሱ። የመነኵሴ አክሴማ ቢያጠልቁና፣ በጌታ በጎች መሀል ቢመላለሱ፣ የበግ ለምድ ለባሽ ተኵላነት እንጂ፣ እረኝነት ሲያላፍም አልነካካቸውም! መቼም ቢሆን ግሩም መንፈሳዊ ሰው አይምሰሏችሁ! ዓለማቸውን ከማንም በበለጠ ያጣጥሟታል። ዓለማዊውን ሥራ በሙሉ እየሠሩ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይልላቸውን ወንጀል ፈጸሙብውብናል። ሁሉንም አሥርቱን ትዕዛዛት፣ ከመግደል በስተቀር ጥሰዋል። እነሆ ፍርድ ቤት ከወያኔ ባለሥልጣናት ጋር አጋትረውን ለወሮታቸው ሹመታቸውን እየተጠባበቁ ነው። ግድ የለም። የበጎቹ ባላቤት፣ ውሸታሙን እረኛ፣ ግሩምን፣ ጌታ እግዚአብሔር በፍርዱ ቀን፣ ዙፋኑ ላይ ተሰይሞ የፋረዳቸዋል (ሮሜ ፲፪፡፲፱)። ይኸን የምላችሁ መቶ በመቶ በእግዚአብሔር በመተማምን ነው! ድል የኃያሉ የእግዚአብሔር ነው። የሚደርስባቸውን አስቀድመው ለማወቅ፣ ራዕየ ማርያምን እንዲያነቡ አጥብቄ እመክራቸዋለሁ። እሱንም ቢሆን ቢያምኑበት ነው። ቢያምኑማ ኑሮ የእግዚአብሔርን መንጋ ለመበተን ባልሞከሩ! እግዚአብሔር በዚህ ፈተና ሰዓት ከኛ ጋር ነው።

አባ እንጦንስ

ሁለተኛውን የሐሳዊ መንኵኮሳት ቡድን አመጣጥ በአጭሩ እንይና ከዚያ ውስጥ ወደ ሎንደን የተመደቡልንን ጉድ ጥቂት እንመርምር! ይኽ የቀበሮ ባህታዊ ቡድን፣ በጊዜው በቦታው የነበሩ፣ ዶክተር አረጋዊ በርሀ (2008)[5] እንደጻፉት ቤተክርስቲያናችንን የወረሩት የወያኔ ውሪዎች ናቸው። እረኛ መስለው፣ በበግ መንጋ መሀል ተመላላሽ፣ ሌሎች የበግ ለምድ ለባሽ ተኵላዎች! ዶክተር አረጋዊ እንዲህ ይላሉ!

To weaken church authority, an intelligence group was formed under Sibhat Nega to in filtrate the well - established monasteries in Tigrai, such as Debre Damo, by planting TPLF members camouflaged as monks and influencing church activities in the interests of the TPLF 3 . (p 302)

ከነዚህ መሀል፣ ዛሬ አብዛኞቹ በወያኔው ፓትርያርክ፣ በሟቹ በታጋይ ጳውሎስ እስከ ጵጵስና ማዕረግ ተሰጥቶአቸው ቤተክርስትያናችንን ከላይ እስከታች ያተራሷታል የአሁኑ ፓትርያርክ፣ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ነገሩ ሳይገባቸው ቀርቶ ሳይሆን፣ የእሳቸውም ፕትርክና እራሱ በነዚህ ሰዎችና በወያኔ በጎ ፈቃድ በመሆኑ፣ እያዩአቸው የሚያደርጉትን አጥተው እጃቸውን አጣጥፈው ቁጭ ብለው የሚመለከቷቸው ይመስለኛል። አባ ማቲያስ ብልህ ሰው ናቸው። ታጋይ ፓውሎስን ሲታገሉ ቆራጥነታቸውን አይተናል። አሁን ግን የመንበራቸው ጉዳይ ሆኖባቸው ዝም ብለዋል! ይኸን ጉድ እያዩ ምን ይሉ ይሆን። የሎንደኑ ትንቅንቅ ወሳኝ የሀይማኖት ቁርጠኝነት የሚታይበት አውደማ ነው። ፈረንጆቹ “Make or Break” የሚሉት ዓይነት ማለት ነው። የአቡነ ማትያስን አስተያየት በትዕግስት እንጠብቃለን። ዝምታ ከክፋት ጋር ሕብረት ነው።

እኛን ሎንደን የምንኖረውን ስደተኞች ከምልምል ተጋደልቲ መነኵሴዎቿ መሀል፣ ወያኔ የመደበችልን ታማኝ ካድሬዋንአባእንጦንስ (Anthonios) የተባሉትን ነው።አባእንጦንስ ጉደኛ ናቸው። የሳቸው ጉድ ተከድኖ ይብሰል ቢባል ይቀላል። ዕሑድ ዕለት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የጠበቆች የዲሲፕሊን-ጉባዔ ስብሰባ ቃለ ጉባዔ፣ የመዝገብ ቁጥር 64/2006 የተጻፈ ዶሴና ሌሎችም ደጎስጎስ ያሉ መዘገቦች እጄ ገብተዋል። ጉድ! ጉድ! ጉድ! አንዷን ሐረግ ብቻ ልምዘዝላችሁ።

በኮልፌ ቀራንዮ የመጀመሪያ ደረጃ /ቤት ላይ እማሆይ ምግቤ ታከለ የተባሉ ከብጹዕ አቡነ እንጦንስ ጋር እንደባልና ሚስት ኖረዋል በማለት በጠበቆቻቸው አማካኝነት የንብረት ጥያቄ ክስ አቅርበው ...”   

የሚል ሀተታ ሳነብ፣ ሳልጨርሰው ደንግጬ አማተብኩኝ። ወዬው! ወዬው! ወዬው እምነቴ! ዕውነትም ቀሲስ አስተራየ አንዴ እንዳሉት፣ከገዳም የወጣ መነኵሴና ከዙ ያመለጠ አውሬ አንድ ናቸው።ነገሩ እንኳን አባ እንጦንስ ገዳም የገቡት መንነው
አይመስለኝም። ቢሆንም...  ይኸን ቦምብ፣ ባፈነዳሁ ደስ ባለኝ።  ሥጋቴ፣ አባ እንጦንስን ለማጋለጥ ስል ከፍርድ ቤት ያገኘሁትን ጉድ እንዳለ ብዘከዝክ ቤተክርስቲያኔን ገጽታ በድንገት እንዳልጎዳ ሳስቼ፣ ለጊዜው አቆይቼዋለሁ። ምን ይታወቃል፣ ምናልባት ለቤተክርስትያናቸውም ባይሆን ለራሳቸው ስም፣ ትንሽ እንኳን የሚሳሱ ሰዎች በአካባቢአቸው ካሉ፣ ተሯሩጠው የጀመሩትን ሰይጣናዊ ግዝት ማስጣል ከቻሉ፣ ግልግል ሌላውን  ፍርድ ቤት ይፈታዋል። ካልሆነ ግን ምን አደርጋለሁ። መቼም መትረየስ ተሸክሞ ሰው አይሞት ነገር። ነገሩ ከከረረ በኋላ ላይ እመለስበታለሁ። እራሱን የቻለ አንድ መጽሐፍ የሚወጣው ጉድ የጉድም ጉድ ነው። ጉድ ነው! ጉድ ነው! ጉድ ነው ብዬአችኋለሁ። እንዲህ ዓይነት የገማ የገለማ ታሪክ ይዘው ነው፣ እኚህ ሰው፣ የተከበሩትን የእግዚአብሔር ካህን፣ መልአከ ብርሀን ቀሲስ ብርሀኑ ብሥራትን የሚገዝቱት?! እነዚህ ጉደኞች ቤተክርስቲያናችንንና፣ ሀይማኖታችንን አጎደፏት! ከመጀመሪያውም የቅዳሴ ሥርዓቱን ሸምድደው እንጂ ዕምነቱ አልነበረባቸውም። የቅዳሴውንም ሥነ-ሥርዐት ግሩም እዚሁ ሎንደን አይደል የተማሩት? እግዚአብሔር ከእንደነዚህ ያሉ አስመሳይመነኮሳት ይታደጋችሁ? በኃጢአት እየተጨማለቁ እያየን፣ እኛስ ከማን የእግዚአብሔርን ነገረ መለኮት፣ እንማራለን? ቤተክርስቲያኒቱን የሌባና የወንበዴ ዋሻ አደረጓት። ወይ ክርስትና! ወይ ምንኵስና! ወይኔ ተዋህዶ ሀይማኖቴ! በእንደዚህ ያሉ የቀብሮ ባሕታውያን ሥር ትወድቂ?! እኛስ እምቢዮው! ለሌቦችና ለአጭበርባሪዎች አንታዘዝም!

“አባ” እንጦንስ የዛሬ ሰባት ዓመት ገደማ ሲመጡ፣ የለንደን ደብረ ጽዮን ቅደስት ማርያም አስተዳዳሪ ሁኜ ተሹሜአለሁ፣ ተቀበሉኝ” ብለው ነበር የላኩብን። ከሌሎች የሌቦች ካምፕ ቀድመው የደረሱ፣ “አባ” ግርማ  ነገሩ አልጣማቸውም። “አባ” ግርማ፣ መሪጌታ መርሀጽድቅ፣ መሪጌታ ሀዲስ፣ ቄስ ዳዊት፣ ዲያቆን ድርሻዬ የተባሉ የደብረጽዮን ካህናትና፣ ም/አስተዳዳሪው ታዬ “አባ” እንጦንስን በጊዜው ሂደው አነጋግረው ነበር። “አባ” ግርማ የዋዛ ሰው ስላልነበሩ፣ ሥልጣናቸው ከሌላ አቅጣጫ በመጣ ተቀናቃኝ ወንበዴ እንዳይነጠቅ፣ ሕዝብ አስተባብረው እዚያች በር እንዳይረግጡ በደብዳቤ አገዷቸው። ስልጡኑ የቀበሮ ባኅታዊ፣ ጦርነት ላለመፈለግ፣ “የማርያም ቤተክርስቲያን መስዋዕት አያርግም” እዚያ አትሄዱ ብለው፣ “የአባ ጳውሎስ ስም እንዴት አይጠራም አላችሁ” ብለው በሌላው ከትግራይ በመጡ ጳጳስ፣ አቡነ ሙሴ ወደተመሥረተው አፍቅረ ጳውሎስ ሥላሴ ገቡ። ልብ በሉ፣ የገዘቱት ቤተክርስቲያኗን እንጂ፣ የቀበሮ ባህታዊውን “አባ” ግርማን አልነበረም። ነገሩ፣ “አንተም ሌባ እኔም ሌባ፣ ምን ያጣላናል በሰው ገለባ” ይመስላል። ሌባ ለሌባ ስለሚተዋወቁ፣ ሁለቱ የቀብሮ ባህታዊያን አልተወጋገዙም። አልተገዛዘቱም። ብቻ በዓይነ-ቁራኛ ይጠባበቁ ነበር። ድሮውንስ ጅብ ለጅብ ተባብሮ ይዘነጥል እንደሆነ እንጂ፣ መቼ ተባብሮ አብሮ በልቶ ያውቃል? ደካማው፣
ለጉልበተኛው ለቆ፣ ጉልበተኛው እስኪጠግብ ድረስ ተራውን ጥግ ይዞ መጠበቅ ልማዱ ነው። “አባ” እንጦንስም ያደረጉት ያኑን ነበር። ቀናቸው እስኪደርስ አደፈጡ። ከሥላሴ በተቻላቸው መጠን ወያኔን ማገልገል ቀጠሉ። ሎንደንን መቆጣጥር ከባድ መሆኑን ተረድተው፣ ተወልደ ወልደማርያም ከሚባል የጎጣቸው ተወላጅ ጋር ሁነው፣ በወያኔ አሽቃባጮቻቸው ታጅበው፣ የአውሮፓ አገረ ስብከት[6] የሚባል የወያኔን የመቆጣጠሪያ መሣሪያ አቋቋሙ። ይኸ እርምጃቸው፣ ጸርሐ ጽዮንንም (የጀማይካዎቹን) በቁጥጥራቸው ሥር አዋለላቸው። አውሮፓን ለመቆጣጠር ቻሉ። ዘረኝነትን አስተማሩበት። “አባ” እንጦንስ አንድ ቀን ወያኔ ኤምባሲ ድግስ ሊበሉ ሊገቡ ሲመጡ ልጆቻችን ከበሩ ላይ ቀልበዋቸው ጥይቄ በጥያቄ አጣደፏቸው። ታሪኩን በግርጌው ያገኙታል[7]

እንግዲህ በዚህ መልክ ነበረ፣ ወደኛ ደብር አንዲት ቀን እንኳ ዝር ሳይሉ ሰባት ዓመት ሙሉ አድፍጠው ያሳለፉት። ከሥላሴም ሌላ፣ አንዳንዴም ለትግርኛ ተናጋሪዎች ብቻ ተብሎ በተመሠረተው ቅዱስ ገብርኤል ጎራ ብለው ድምጻቸውን ያሰሙ ነበር። አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል እንደሚባለው፣ “አባ” ተባዩ ግርማ (ግሩም) የነበራቸው ክብርና ፍቅር አልበቃቸው ብሎ ከሕዝብ ተጣሉና ሰማይ ምድሩ ሲዞረባቸው ለአንድ ቁጥር ጠላታቸው “ለአባ” እንጦንስ ገብረው ገብተው ሸጡን። ወደተፈጥሮ የክህደት ባህርያቸው ተመለሱና፣ የ“አባ” እንጦንስን እግር ስመው፣ ይቅርታ ጠየቋቸውና ከጎናቸው ሊያሰልፏቸው ቻሉ። ጉደኛዋ ቪዲዮዋም፣ ይኽቻትና! እዩአትማ ሲሸጡን! እንዳታመልጣቸሁ!  http://www.youtube.com/watch?v=Y_AiNCXCl90&feature=youtu.be

አበስኩ-ገበርኩ! “ውሻ ወደትፋቱ ይመለሳል”(፪ ጴጥሮስ ፪፡፳፪) ሲባል አይገባኝም ነበር። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን በሚገባ እየገባኝ መጣ። መጀመሪያ ጋዜጠኛ ንጉሴ ወልደማርያም አስደነገጠኝ። ቀጥሎ ሰሎሞን ተካልኝ! አሁን ደግሞ አባባሱባት! ግሩም ማሩኝ ብለው የ“አባ” እንጦንስ እግር ላይ ወደቁ! ለወያኔም እራሳቸውን ምርኮኛ ሲያደርጉ፣ ቤተክርስቲያናችንን ለእጅ መንሻ መስዋዕት አድርገው አቀረቡ! አይ “አባ” ግርማ! መነኵሴ እንዲህ ነው እንዴ?

መልአከ ብርሀን ብርሀኑ ብሥራት!

እዚህ ጋ የሕዝብ ወገን ስለሆኑት ስለመልአክ ብርሀን ቀሲስ ብርሀኑ ብሥራት ተጋድሎ ትንሽ ማለት እፈልጋለሁ። ሳውቃቸው ፲፯ ዓመት ሞልቶኛል። የነፍስ አባቴ ናቸው። የዳሩኝም እሳቸው ናቸው። ለነገሩስ፣ አባ ግርማም ሥነ-ሥርአቱ ላይ ነበሩ። ቀሲስ ገብረ-ጊዮርጊስም እንደዚሁ! በነገራችን ላይ ቀሲስ ገብረ-ጊዮርጊስ፣ የገብርኤል ካህን ናቸው። ማርያምን የተዋት፣ የታጋይ ጳውሎስን ስም አንጠራም ተብሎ ውሳኔ በመተላለፉ ነው። ከዚያ ባሻገር፣ አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል እንደሚባለው ብሂል ካልተወነጀሉ በስተቀር፣ እኚህ ካህን አንድም ቀን ሕዝቡን የሚያስቀይም ንግግር ከመናገር የተቆጠቡ ናቸው። ስናገኛቸውም ጨዋነት በተሞላበት ነው ሰላም የምንላቸው። ከከሐዲው ግሩም ይልቅ ቀሲስ ገብረ-ጊዮርጊስ የላቀ ክብር አለኝ። ለነገሩስ፣ እያየናቸው አልነበር ከኛው ጋር ሲያገለገሉ የኖሩት?

ወደ መልአከ ብርሀን ልመለስ። መልአከ ብርሀን ቀሲስ ብርሀኑ፣ ከሕዝቡ ተለይተው አያውቁም። እንደመልካም እረኛ ሕዝቡ ወደሔደበት ነው ተከትለው የሚሄዱት። አቡነ ዮሐንስ (አባ አረጋዊ) ታኅሳሥ 15 ቀን 1990 (24 December 1997) ሲያርፉ እንዳባት የሰበሰቡን እሳቸው ናቸው። ታጋይ ጳውሎስ ክፍተት አገኘሁ ብለው አንድ አንደበታቸው ያልተገራ ሊቀ-ካህናት ብርሀኑ ወልደአማኑኤል የተባሉ ካህን ልከውብን ሎንደንን ለማንበርከክ አጉል ሞክረው ነበር። እኚህ ሰው በደብረ ዘይት ዕለት ድንገት ዱብ ብለው፣ “ንብረቱን አስረክቡኝ። ከሲኖዶስና ከፓትርያርኩ ነው የተሾምኩት” ሲሉን፣ የማነህ ጥጋበኛ ብለን ኩም አደረግናቸው። ደብረ ዘይትን ልብ በሉልኝ። ከሆድ-አደር ሙሉጌታ አሥራተ ካሣና ከመሪጌታ ዓለማየሁ (ዛሬ ሊቀጠበብት፣ የይሑዳው የቀበሮ ባኅታዊው የግሩም ቀኝ እጅ) ጋር ሆነው በዳግማዊ ተንሳዔ ዕለት ቤተክርስትቲያናችንን እሽግ አደርጉብን። የመንግሥተ ሰማያት፣ በር “እሽግ” ትበልባቸው! ለማስቀደስ ስንመጣ፣ ልክ እንደዛሬው ከቀሲስ ብርሀኑና ወጣት ዲያቆናት ጋር ውጪ ቀረን! ምን የዞረበት ሰይጣን ነው ቤተክርስቲያንን በእንደዚህ ያለ ታላቅ የበዓል ቀን የሚያሽግ? የእንግሊዝ ባለሥልጣናት? አያደርጉትም! ቀሲስ ብርሀኑ በተርጋጋው ድምጻቸው አበረታተውን፣ ወደ ግሪን ፓርክ መሩን። እዚያ እንደደረስን ምሕላና ጸሎት አደረሱልን። ዝናብ ዘነበብን። ዝናቡን ከጽድቅ ነበር የቆጠርነው። ግሩምና ሊቀ-ካህናት ተብዬው የቄስ ካድሬ፣ ለሎንደን አንድ ላይ ነበር የተሾሙት። ግሩም ግን ሁለት ሳምንት ዘግይተው ነበር የደረሱት። ለወንጌል ስብከት (ድንቄም) ተሹመው ነበር የመጡት። ታዲያ አራዳው ግሩም ሊቀ-ካህናት ብርሀኑ ወልደአማኑኤል ላይ የደረሰውን ውርደት ሲያዩ፣ ታክቲካቸውን (አቋማቸውን) አስተካክለው “የጳውሎስ ተቃዋሚ ነኝ” አሉን። ያ ጣጣ የተጀመረው በአውሮፓ አቆጣጠር መጋቢት 1998 ነበር። ዓቢይ ጾም ጊዜ መሆኑን ያዙልኝ። ፲፭ ዓመት ጠብቆ፣ ያ ታሪክ መጋቢት ፩ ቀን ፪ሺ፭ ዓ. ም.(March 2013) ተደገመ። ባለፈው ዓመት ዓቢይ ጾም በገባ ማግስት፣ ቤተክርስቲያናችንን፣ “አባ” ተባዩ ሲጠረቅሙብን ከሕዝብ ጋር ማን ቀረ? አሁንም መልአክ ብርሀን ቀሲስ ብርሀኑ ብሥራት፣ መሪጌታ ሀዲስና፣ ወጣት ዲያቆናት!

“አባ” ተባዩና ደንገጡሮቻቸው መንጋውን ሲከፍሉት፣ ቀሲስ ብርሀኑ ለአራት ሳምንታት ክፍፍሉን ለማስወገድ ያላደረጉት ጥረት አልነበረም። አንዴ እነሱ ጋ ሂደው ሲጸልዩ፣ ሌላ ጊዜ ሕዝቡ ጋ ሂደው ምሕላ ሲያደርሱ፣ ሲመክሩ ቆዩ! ማን ሰምቷቸው! ከአራት ሳምንታት በኋላ በደብረ ዘይት ዕለት ግን፣ በሚከተለው ቪዲዮ እንደምታዩት፣ ጀግና የሆነች ትንሿ ሴት ልጃቸው እየጠበቀቻቸው፣ አንደነብር ዓይኗን ከግራ ቀኝ እያማተረች እያጀበቻቸው፣ ለሁለቱም አማካይ ቦታ፣ ቁመው ስለዕለቱ ታላቅነት አስተምረው ጸለዩልን። ሕዝቡ ፊቱን ወደሳቸው አዙሮ፣ አሜን ይላል። ያባ ደንገጡሮች፣ ዳር ቁመው ይመለከቷቸው ነበር። የቀበሮ ባህታዊው፣ ግሩም፣ ሊቀ-ጠበብታቸውን አስከትለው እየተንጎማለሉ ከቸች! ቀሲስ አየት አድርገዋቸው ጸሎታቸውን ቀጠሉ። ሁለቱ ነፍሰ በላዎች፣ ወደ አማካዩ ቦታ ሳይሆን፣ ቀሲስን ለብቻቸው ትተዋቸው ወደ ደንገጡሮቻቸው ሂደው፣ ጸሎት አይሉት ትንኮሳ፣ ኢ-ሀይማኖታዊ ማነብነብ ጀመሩ። ድርጊታቸው ቀሲስን ብግን አድርጎአቸው፣ “መነንኩ” ባዩን የቀበሮ ሐሳዊ መነኵሴና፣ እኛን በየጊዜው እንደይሑዳ ለተሾመ ሁሉ ሲሸጡን የኖሩትን መሪጌታ (አሁን ሊቀጠበብት) አለማየሁን በቀጥታ ሂደው ሕዝብ እንዳይከፋፍሉ ቢጠይቋቸው፣ የግሩም ደንገጡሮች አንጓጠጧቸው። ቀሲስ እንደ ጀግና ሰማዕት፣ የክርስቶስ በጎች በቆራጥርነት ከተኵላ በቆራጥኘት ጠባቂ ነበር የተጋፈጡአቸው። ዕውነተኛ በክርስቶስ የተመረጠ እረኛ እንዲህ ነው። http://www.youtube.com/watch?v=QhkmxF0bcH8&feature=youtu.be። ዕውነቱን ለመናገር፣ እዚህ ቪዲዮ ላይ እንደምታዩት፣ ከግሩም፣ ከሊቀጠበብቱና ደንገጡሮቻቸው ይልቅ፣ ነብሪቱ፣ የቀሲስ ትንሿ ሴት ልጃቸው፣ ታስፈራ ነበር። “አባ” ግርማን ትኵር ብላቸው እዩአቸውማ፣ አርዮስ ምስጋና ይንሳው! ይሑዳ እንኳን ተጸጽቶ፣ እራሱን ገድሏል። አባ ግርማ ከሆዳቸው በስተቀር ሒሊና አልተፈጠረባቸውም! መጥኔ! ለዚህ ነው ለቀበሮ ባሕታዊ ከዚህ በኋላ የማንበረከከው? እምቢዮው!

የእንጦንስ ትንኮሳ

የፈረደባት ሎንደን ደብረጽዮን፣ ከሁሉት የቀበሮ ባኅታዊያን የጋራ ግንባር ተወጥራለች። ላለፉት ፲፫ ወራት ሕዝባችን በስደት መኖሩ ሳያንሰው፣ አንጡራ ገንዘቡን አፍስሶ የገዛትን ቤተክርስቲያን ሊቀሙ በተደረገብን የተቀነባበረ የግሩም፣ የእንጦንስ እና የወያኔ ኤምባሲ ዘመቻ (ሙሉጌታ አስራተ አሁንም ዋነኛው አራጊ ፈጣሪ)፣ በአምላክ እርዳታ ሳንበገር በተባበረ ክንድ ስንመክት አንድ ዓመት አለፈ። ሕግ ለማክበር ስንል፣ በረዶውን፣ ውርጩን፣ ጸሐዩን ተቋቋምነው። ቤተክርስቲያናችንን በማስረከብ የተባበሩትን የከሀዲ ክንዶችን በቆራጥነት መክተን መለስን። ታዲያ “አባ” ግርማ ገብረው የገቡላቸው፣ “አባ” እንጦንስ፣ በድፍረት ማርያምን የሸጡ ከሀዲዎችን እንደጀግኖች፣ በወያኔ ሽልማት በሽልማት አንበሸበሿቸው። እኚሁ እራሳቸው ተቀቀሎ ዓይናቸው ሳይበስል ያመለጠ የትግራይ አራዳ፣ አንድ ቀን በጸሐይ ላይ ቁመን ምሕላ ስናደርስ፣ በሰባት ዓመታቸው ለምን ዓይኖቻቸውን በጨው ታጥበው ማርያም ግቢ ከቸች አይሉ መሰላችሁ! ዕለቱ ነሐሴ ፳፮ ቀን ፪ሺ፭ ዓ.ም. (1 September 2013) ነበር። ወይ ድፍረት! ሌባ እንዲህ ደፋር ነው እንዴ! ሕዝቡ ተናደደ! በገነ! ሆ ብሎ ሊውጣቸው ምንም አልቀረው። ልባሞቹ በሕዝብ የተመረጡ፣ መሪዎቻችን ግን ሕዝቡን አረጋጉ። ሥነ-ምግባር በሞላበት አኳኋን ከዚያ እንዲሄዱ በአረጋውያን ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው። የሚከተለው ቪድዮው የሚያሳየው፣ ከሀዲዎችን ሲሸልሙና እኛ ጋ መጥተው በነገር ሲተነኩሱን፣ ወደመጡበት እንዲመለሱ የሕዝብ ተወካዮች ስያስጠነቅቋቸው ነው። https://www.youtube.com/watch?v=nKcwMneQZ9A
አቡነ ገብርኤል ሁለቴ ሎንደን ተመላለሱብን። አንዴ አቡነ ቀውስጦስን አምጥተው አስደነፉብን። የግሩም ወጣት ሴቶች ያንን ዕድል ተጠቅመው በሁለቱም ደረት ላይ ተለጠፈው ፎቶአቸውን በፌስ ቡክ ለቀቁት። ሌላ ጊዜ አቡነ ያዕቆብን ይዘው መጥተው፣ በአካል ቤተክርስቲያናችንን ለመንጠቅ ሞክረው ከሸፈባቸው። ሽንጣችንን ገትረን ለዕምነታችን ዘብ ቆምን። በተለይ ኦክቶበር 12-13 ቀን 2013 ወንድሞችና እህቶች ያደረጉት ተጋድሎ ምንጊዜም አይረሳኝም! (http://ethioforum.org/wp-content/uploads/2013/10/%E1%8B%88%E1%8B%AD-%E1%88%88%E1%8A%95%E1%8B%B0%E1%8A%95-1.pdf)።

ይኸን ሕዝብ ለማንበርከክ፣ “አባ” እንጦንስ አንድ ሰይጣናዊ ዘዴ ተከሰተላቸው። ከሕዝብ ጎን የቆሙትን መልአከ ብርሀን፣ ቀሲስ ብርሀኑን በየጊዜው በደብዳቤ ማስፈራራት። “ሕዝቡን ትተህ ከካህናት ወንድሞችህ ጎን ካልቆምህ፣ ክርስቶስን ዳግመኛ ካለወገርክ፣ ከሹመትህ አወርድሀለሁ” የሚል ዓይነት መልዕክት ሁለት ጊዜ ላኩባቸው። (ጉድ እኮ ነው! እሳቸው የሾሟቸው ይመስል) አሁን እንዲህ ዓይነት ማስፈራሪያ ምን ይባላል? ጉድ እናያለን ብለን ዝም አልን።

ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ


ታጋይ ጳውሎስ እኮ እዝህች ከተማ ዱላ ቀምሰው ሂደዋል! በእንደዚህ ዓይነት ማስፈራራት፣ በጉልበት፣ የሎንደን፣ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን ለማንበርከክ መሞከር ጅልነት ነው። ይኸ ነው አልገባ ያላቸው። በሰላሙ ጊዜ ተኮራርፈን የማንነጋገር፣ የአገር ልጆች፣  በዚህን ጊዜ ነው እንደእናት ልጅ የምንፋቀረው። ይኸ አይበገሬነታችን ነው ወያኔንም ሆነ ቡችሎቻቸውን ያልተዋጠላቸው። የቀበሮ ባኅታዊያኑ፣ ሁለቱ ጣምራ የክርስቶስና የሕዝቡ ባላንጦች፣ ግሩምና እንጦንስ እኛን መስበር ሲያቅታቸው፣ ተያይዘው ለዱለታ አዲስ አበባ በረሩ። እሱም የሰላም መንገድ አልሆነላቸውም። ከሄትሮ ተነሰተው ቦሌ እስኪደርሱ
ድረስ በዓይነ ቁራኛ ነበር ግሩምን የተከተልናቸው። በመጀመሪያ ቀን ከአይሮፕላን ወረዱ። ሕዝቡን እንዳልሄዱ ከመቅጽበት አስታወቅን። በነጋታው እንደ ዓይጥ ተደብቀው ተሳፈሩ። ቦሌ ላይ፣ የኛ ሰዎች ጠብቋቸው፣ በካሜራ ፎቶግራፎቻቸውን ገጥግጠው በዘመናዊ የመገናኛ ዘዴ በደቂቃ ውስጥ ናኙላቸው።  አንዱ ይኸው! ከዚያ በኋላ የት እንደገቡ መከታተል አቃተን። አንድ ጊዜ ብቻ “ለዓባይ” ቦንድ ሽያጭ በተደረገው ስብሰባ ላይ ተጎልተው በቲቪ ታዩ ተባለ።  ከወያኔ አለቆቻቸውና ከሲኖዶሱ ጉያ ተውሽቀው ቤተክርስቲያናችንን እንዴት መቀማት እንደሚቻል ሸር ሲሸርቡ ሰንበቱ። በስተመጨረሻም፣ ሁለቱም የቀበሮ ባሕታውያን በጋራ “ዜና ቤተክርስቲያን[8]” ለሚባለው የወያኔ የቤተክርስቲያን ጋዜጣ ተናዘዙ። ግሩም የተለመደውን ፖሊቲከኞችና የደርግ ባላሥልጣናት አሳደዱኝ ብለው አቤቶታቸውን ደረደሩት። እንጦንስ ያስቸገሯቸው፣ የቅንጀት፣ የግንቦት ሰባት፣ የደርግ ባለሥልጣናትና ምሑራን መሆናቸውን ተማርረው ሲያስረዱ፣ እግረመንገዳቸውንም፣ እስከዛሬ የረዳቸውን የወያኔን (የኢትዮጵያን) ኤምባሲ ከልባቸው አመስግኑ። ኤጭ!

ቤቴክርስቲያችን በሕገወጦች ተያዘች

ከዚያ መልስ፣ በወያኔ እምባሲ ውትወታ፣ የእንግሊዝን መግሥት ለጊዜው አወናብደው ከእንግሊዝ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስቴር ትዕዛዝ እስከ አፍ ጢማቸው የታጠቁ 5 መኪና ሙሉ ፖሊሲችን አሰማርተውብን፣ ሌላ 15 የሚሆኑ ነፍሰ በላ ቦዲ ጋርድ ወይም ባውንሰርስ (የጥበቃ ጓድ)፣ በሰዓት ብዙ ሺ ፓወንድ እየገበሯቸው አቁመው፣ እሑድ ታኅሣስ ፳ ቀን ቤተክርስቲያኗን በጓሮ ገብተው፣ “አባ” ተባዩ እንጦንስ በገዛ አንጡራ ኃብታችን የገዛናት ሕንጻ ዉስጥ በቤተክስቲያናችን ገብተው ተከረቸሙ (squatters)። ከሥላሴ፣ ከገብሬል እና ከጸርሐ ጽዩን (የጀማይካኖችን ቤተክርስቲያን) በመጡ ምዕምናኖች ታጀቡ። አይ ለወገን ደንታ ቢስነት! ይኽቺ ቀን ታልፍና ታስተዛዝበናለች! እኛ በአንጡራ ገንዘባችን የገዛናት የሕንጻ፣ ባለቤቶቹ ውጪ ቁመን ወንጀለኞቹ እናታችን ማርያምን ጠለፏ። “ስንት ዓመት የተመኝናት ማርያም፣ ሳንወጣ ሳንወርድ የኛ ሆነች” ብለው ሰይጣንን አብረው አመሰገኑ። ጠለፋ እኮ በዚህ ዘምን ቀርቷል። ገብተን ድምጥማጣቸውን አጥፈተን የተያዘው ሰው ተይዞብን፣ የተጎዳ ሰው ተጎድቶብን፣ ከዚያ ማስወጣት አቅቶን አልነበረም። ዳሩ ግን፣ ለልጅ ልጆቻችን ውርስ ትሆናለች ብለን የገዛናት የሎንዶኗ ቤተክርስትያናችንን፣ ረብሻ ዳግመኛ ተነስቶ፣ ለዘለዓለመ ዓለም ያገሩ መንግስት እንዳይዘጋብን ሳሳን። እነሱ ምን ቸገራቸው። ሳንቲም አላወጡም። በነጻ ለነሱ እስካልሆነች ድረስ ዶጋመድ ብትሆን ደንታቸው አይደለም። ምን ገዷቸው። የነሱ ከሆነችላቸው ደግሞ በጀ! እንደማትሆን ስለሚያቁም፣ “ዶሮ ባትበላ ጭራ ታፈሳለች” ፍልስፍናን ተከተሉ። እኛ ግን፣ የመጽሐፈ ነገስት ቀዳማዊ፣ ምዕራፍ ፫ ከቁጥር ፲፮ እስከ ፳፰ ታሪክ ሆነብንና፣ ለጊዜው ተውናቸው። ተጎድተንም ቢሆን ሕጉን ማክበርን መረጥን። እነሱማ ከዚያም አልፈው ተርፈው፣ ወደውስጥ ካልገባን፣ ከአካባቢዋ ሊያባርሩን ሁሉ ሞክረው ነበር። ልብ ዕንቅርት ይመኛል! ፖሊሶቹ ያ ማድረግ፣ ሕዝቡን ወደ አመጽ መገፋፋት መሆኑ ገባቸውና የማይቻል መሆኑን ነግረዋቸው፣ ሕዝቡ በግቢው ገብቶ እንዲጸልይ ተደረገ። ቅጠረኛ ነፍሰ ገዳይ የጥበቃ ዘብኞቻቸው ቀስ ብለው ቀስ ብለው እንዲያስፈራሩን ተነግሯቸው ሊያባርሩን ሞክረው ነበር። ስንጋፈጣቸው አፍረው ወደ ጫማቸው ተሸማቀቁ! ከዚያ በኋላ በየሳምንቱ፣ ከዚያ ሕዝቡን አባርረው ሙሉ በሙሉ ቤተክርስቲያኗን ለመቆጣጠር ያደርጉት ሙከራ በጠቅላላው ስለከሸፈባቸው፣ ተስፋ ቆረጡ። የሕዝቡ ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየተመነደገ፣ የነሱ ቁጥር ቀን በቀን እየመነመነ ሄደ። የኛ ሕዝብ እንደዚያም ሁኖ፣ ሁሌ ደስተኛ፣ ሁሌ ፍቅር ነበር። አንድ ነገር ልመስክርላችሁ። ዝናቡ ወርዶ ወርዶ፣ በረዶው ወርዶ ወርዶ፣ እሑድ ሲመጣ ቀጥ ይላል። እግዚአብሔር ጥላውን ዘረጋልን። የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን! አሜን

ተከርቻሚው እንጦንስ እና ከሥላሴ ያመጧቸው ምዕምናን፣ በፖሊስ ኃይልና በነፍሰ-በላዎቹ በቅጥር ዘበኞች ዕርዳታ በእጃቸው በአጋጣሚ በገባው ቁልፍ በቤተክርስቲያኑ ለጊዜው መገልገላቸውን ገፉበት። ደፋሩ የወያኔ ቅጥር ጳጳስ፣ ለልጆች ትምሕርት ቤት ብለን ፮፻ሺ ፓውንድ  (£600,000) አዋጥተን የገዛነውን ቪካሬጅ ሕንጻ፣ ከነኮተታቸው ገብተውበት (squatter) “መኖሪያዬ ይኸ ነው” ብለው ዕርፍ! በየትኛው ሒሳብ? ሳንቲም ሳያዋጡ? አንድ ቀን ተጋብዘው ሳይቀድሱበት? እሳቸው የሚያገለግሉት፣ ወያኔ የሚቆጣጠረው ሲኖዶስ፣ “እንዳትሸጡላቸው” የሚል ደብዳቤ ጽፎ ለሻጮቹ የላከብን ሕንጻ? ኧረ የሕግ ያለህ! ሕግ በሰፈነበት አገር ሕጉ ስለተጓተተብን ሰይጣን ፈነጨብን። “እግዚኦ በሉ” ክርስቲያኖች! “አባ” ጉልቤውን ጳጳስ ነኝ ባይ የቀበሮ ባሕታዊን ዝም ብለን ለማየት ተገደድን! ነገሩ፣ “በገዛ ዳቦዬ፣ ልብ ልቡን አጣሁት” ሆነብን። የነሱን ትንኰሳ ችላ ብለን ሕጉ ተጓትቶ፣ ተጓትቶ እስኪደርስልን ምሕላችንና ጸሎታችንን በሰላም ደንኳናችንን እየተከልን ማድረስን መርጠን። ይኸ ሁሉ ሲሆን መልአከ ብርሀን ቀሲስ ብርሀኑ ብሥራት አንድም ቀን ከጎናችን ተለይተው አያውቁም። የአዋቂዎች አዋቂ የሆኑ የጥበብ ባለቤት፣ መሪጌታ ሀዲስና እና ዲያቆናት የዕለት ተዕለት፣ የእሑድ-ተእሑድ የመጋቢነት ኃላፊነታቸውን በደስታ በሚገባ ተወጡት። የጌታ መንጋ እረኛ በመሆናቸው፣ እንዳንበተን፣ እንዳንቅበዘብዝ፣ ነጣቂ ተኵላ እንዳይቦጭቀን አንዲት ነፍስ ሳታጠፋ ጠብቀውን ሁላችንም በአንድነት ዛሬን ደረስን። ፍቅራችን ከምንጊዜውም የበለጠ አደገ፡ ተመነደገ። ሕዝበ ክርስቲያኑ፣ አስቀድሶ መቁረቡ ቀረበት እንጂ፣ በጸሎት፣ በምሕላ ቀሲስ ብርሀኑን ይዞ ሌላ የዚህ ዓመቱን አቢይ ጾምን አገባደደው። ተአምረኛዋ ደብረ-ዘይት ዓመቷን ጠብቃ፣ ከቸች አለች! ሰይጣን ቅናቱን አይተውም አይደል? ደብረ ዘይት ነዋ! ጌታንስ ተፈታትኖት የለ! ደፋር! እኛ ድንኳናችን ውስጥ ሁነን፣ ደብረዘይትን በጾም፣ በጸሎትና በምሕላ ስናስታውስ፣ ጣምራ የቀበሮ ባህታውያን የጌታ ጠላቶች፣ በገዛ ቤተክርስቲያናችን አውደ ምሕረት ቁመው ላይ እንዴት ቀሲስ ብርሀኑን ጭጭ እንደሚያደርጓቸው የምትዶልት ደብዳቤ ተናበቡ። “እረኛውን ምታ፣ መንጋው ይበተናል” አይደል መጽሐፉ የሚለው? በደብረ ዘይት ዕለት!!!! እንዴት ቸኰሉ! ጌታ እየሱስ ክርስቶስ በዚህን ጊዜ አካባቢ አልነበር፣ አርባ ቀንና ሌለት ጹሞ፣ ስይጣን የደፈረው! እኛም እንዳቅማችን፣ የጌታን ፈተና መቋደሳችን በረከት ነው! ተባርከናል ወንድሞችና እህቶች! ተቀድሰናል! ከጌታ ጽዋ አንድ ሺህኛውን ቀምሰናል! ደስ ይበላችሁ! እንግዲህ፣ ግሩምና እንጦንስ፣ ተሰባስበው፣ መልአክ ብርሀን ቀሲስ ብርሃኑ ብሥራትን፣ “ስቅሎ! ስቅሎ!” ብለው በድብራችን አውደምሕረት ላይ ተንጫጩቸው!

ቅድስት ማርያማችን፣ በዕውነትም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መመለኪያ አጸድ ናት። እኔ ይኸችን የእንግሊዝ መዲና ከረገጥኩ ጀምሮ አንድም ቀን ዓቢይ ጾም በመጣ ቁጥር ሳትፈተን ያለፈችበትን ጊዜ አይቼ አላውቅም። ብቻ ጌታ ማዕበል-ሞገዱን በሰላም ሲያሻግረን ምስክር ለመሆን አብቅቶኛል። የአሁኗ ፈተና ከረር ያለች ናት። በጌታ ኃይል እናልፋታለን! የጌታችን፣ የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ለዘልዓለም ይባረክ! አሜን!

መልካም እረኛ ነፍሱን ስለበጎቹ ያኖራል

እነዚህ ከአይሑዶችም የባሱ ጨካኞች፣ ደብዳቤውንም በየድረ-ገጹ ያንኑ ሌሊት በተነው አደሩ! “ጭር ሲል አልወድም” ባዮቹ፣ የቀበሮ ባኅታውያን፣ የዚህ ዓለም የሰይጣን ግብራቸውን ሲወጡ፣ እንዲሁ ለፉ። አባ እንጦንስ በመተት “ጸሐይ ጨልሚ!” ሲሉ ድርግም እንደምትል፣ “ጨረቃ ተደበቂ” ሲሉ ስውር እንደምትል! “ክዋክብት ርገፉ!” ሲሉ እንደ እምቧይ ዱብ-ዱብ የሚሉ ይመስሏቸዋል መሰለኝ። ያንን ስልጣን ክርስቶስ የሰጠው ላፈረሱ ጳጳስ ሳይሆን ለጻድቃን ሰማዕታት መሆኑን ማን በነገራቸው! ልብ እንቅርት ቢመኝ፣ መብቱ ነው። ያ ሥልጣን ቢኖራቸው ኑሮ፣ እማሆይ ምግቤ ታከለን “ጭጭ ምጭጭ” ባሰኙ ነበር። ወዲያ ክሏቸው! አሁንስ ናቅኳቸው!

“ምህላ እንዳታደርስ፣ እንዳትቀድስ፣ እንዳታቆርብ፣ ክህነትህን ይዤብሀለሁ፣ ገዝቼሀለሁ፣ አውግዤሀለሁ” የሚል ዝባዝኬ፣ የያዘ ደብዳቤ በአድራሻቸው ዓለም ቀድሞ ካወቀው አንድ ቀን በኋል በነጋታው ለቀሲስ ደረሳቸው። እስቲ ተመልከቱ፣ በትንሹ፣ 500 የሚሆን ምዕምን አንድ ቄስ፣ አንድ ትምህርታቸው ተሰምቶ የማይጠገብ መሬጌታ ሀዲስ፣ እና ወጣት ዲያቆናትን ይዞ ነው ለሀይማኖቱና ለመብቱ የሚከራከረው! አሁንም ሌሎች ዲያቆናት ድምጻቸውን አጥፍተው በመሕላችን እንዳሉ አወቅናል። “የአባ” እንጦንስ መቀላመድ፣ አንዱን የተደበቀውን ዲያቆን ስሜት ፈንቅሎበት ወጥቶ እሑድ ዕለት ለምን አይዘምርልን መሰላችሁ! አስቀድሰን መቁረብ ካቆምን 13 ወራት አልፎናል። “እግዚኦ ማረን ክርስቶስ” ብሎ ምሕላ የሚያደርስልንና፣ አይዞአቸው እምባችሁን አምላክ ይጠርገዋል ብሎ የሚያጽናናን እረኛ “በዛባቸው” ብለው ነው እንጦንስ ደብዛችን እንዲጠፋ ለተኵላና ለጅብ የተመኙን? እንዴት የእግዚአብሔርን ዓይን ለመጠንቆል ደፈሩ እኚህ የቀበሮ ባሕታዊ!! እንዴ! እንዴት ተቀልዷል ጃል! እኚህ የቀበሮ  ባህታዊ ጳጳስ ነኝ ባይ ዘማዊ፣ ለመሆኑ፣ በየትኛው የሞራል ብቃታቸው ነው ይኸን ማድረግ የሚችሉት? እራሳቸው ውግዝ ከመ-አርዮስ፣ የተወገዙት ውግዘታቸው ሳይነሳላቸው “ገዝቼሀለሁ” የሚሉት በየትኛው ስልጣናቸው ነው? ግዝቱስ ቢሆን፣ የትኛው ቀኖና ፈርሶ ነው? ቀሲስ ብርሀኑ እንደነሱ ለወያኔ ስላላደሩ?

ገብረሔር!


መጋቢት ፳፩ ቀን፣ ዓቢይ ጾም ከገባ፣ ስድስተኛው እሑድ ነው። አይግርምም? ይኸኛው እሑድ ገብረሔር እንደሚባል፣ ዲያቆን ደረጀ አስተማረን። ቃለ ሕይወት ያሰማልን! መልካም አገልጋይ ማለት መሆኑን አወቅን። መክሊታችንንም በዚህ አጋጣሚ ተቀብልን። ወይ አጋጣሚ! እግዚአብሔር እኮ ይኽ እንዲሆን የፈቀደበት ምክንያተ ነበረው! አይ አለማወቃችን! እንደተለመደው ለጸሎታችንና ለምሕላችን ሁላችን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ዕምነት ተከታይ ክርስቲያኖች ግልብጥ ብለን ወደ ቤተክርስቲያናችን ግቢ ሄድን። ውስጡንማ ተከርቸመው ገብተውበት አርክሰውታል። የድንኳን ተከላ አገልጋዮቻችን በጠዋት ሂደው ድንኳናችንን ተክለው አሰማምረው ጠበቁን። በድኳኑ መግቢያ በር ላይ “መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል የሚል፣ የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የዮሐንስ መልዕክት ተጽፎ ከጎኑ የመልአከ ብርሀን ቀሲስ ብርሀኑ ብሥራት ፎቶ ተለጠፎበት ስናገኝ ልባችን በደስታ ተዋጠ ደቂቀ እንጦንስና ግሩም የጠበቁን፣ ዕንባ-በዕንባ ስንራጭ ለማየት ነበር። ቀኑም ተግባሩም ተገጣጠመልን። አይ አለማወቃቸው። ቀኗን እንኳን አሳልፈው ቢወስኑ ምን ነበረበት። ልባቸው እንደፈርዖን በደነደነ ቁጥር አዕምሮአቸው ይዘጋል። ይደፈናል። የዕምነት መሀይሞች! በጾም ሰዓት ሱባኤ እንጂ፣ የትኛው መልአክ ነው ሰውን ማሳዘን መልካም ሥራ ነው ብሎ ያስተማራቸው? እነዚህ መሠርይ የቀበሮ ባሕታውያን፣ በሐኬት ባሕር ውስጥ ስንዋኝ ምንኛ ልባቸው ይደማ! መጥተው ከዚያ አይበትኑን ነገር! መትረየስ የላቸው አይረሽኑን ነገር። ፖሊስ እንደሆነ ክፋታቸውን ተርድቶላቸዋል፣ አንዳችም ነገር ሊያደርግ አይሞክርም። እንደከዚህ በፊቱ የተገዙትን የጫት ዕብድ ወጣቶች በማስዘመት አያስደበደቡን ነገር! ቢሞክሩ፣ እነሱው የጠሩት ፖሊስ አጉኖ፣ አጉኖ አንቆ ውህኒ ይወረውራቸዋል። እኛ ደግሞ አንጀታችን ጭክኗል።  ዲያቆናት፣ ቀሲስን አጅበው መጡ! አይ አባ እንጦንስ! የወፍ ግዝታቸው ውስጥ አንድ ነገር ረሱ። “ይኽቺን ግቢ እንዳትረግጥ ገዝቼሀለሁ” የምትል ሐረግ!

መልአከ ብርሀን፣ ቀሲስ ብርሀኑ ብሥራት፣ በፍቅር ዓይን እያንዳንዳችንን እያዩ ፈገግ ብለው፣ “አይዞአችሁ አምላካችሁ አለላችሁ” ሲሉን አንዳንዶቻችን የፍቅር ዕንባ ዓይናችን ውስጥ ግጥም አለ። መልካም እረኛ መቼ ጠባቂ እንዴሌለው መንጋ በትኖህ ሆዱን ሊሞላ ይሄዳል! የእግዚአብሔርን በጎች፣ ለመጠበቅ ነበርና የተሾሙት፣ ያንን አደራ ዘንግተው፣ ንጹሐን አባቶች የሰጧቸውን ሹመት ችላ ብለው፣በቀበሮ ባሕታዊ ተገፍተው የትም እንደማይሄዱ ከሁኔታቸው ስንረዳ በደስታ ፈነደቅን። እልልልልልልልልልልልል! የዕለቱ ወንጌል ተነቦ፣ የጸጋ ነአኵቶ ተደርሶ፣ እግዚኦታችን ወደ ፈጣሪአችን አርጎ፣ ለላፉት 13 ወራት እናደርግ የነበረው አንዱም ሳይጎድልብን ምሕላችንን አድርሰን የተቀመጠ ተቀምጦ፣ የቆምነው ቁመን የዕለቱን ትምሕርት ተጠባበቅን። አንደበተ ርቱዑ ዲያቆን ደረጀ ሞገስ፣ ተነሳ! መጽሐፉን ተነተነው! ስለቸሩ እረኛ በጣም ልብ በሚነካ አኳኋን አስተማረን! ትምሕርቱ ልባችን ላይ ተዘራ። ጭንቻ የነበረው ልባችን፣ መልካም አፈር ሆነ! የጌታ ቃል በውስጣችን ገብቶ በቀለ! እያንዳንዱ አገልጋይ የተሰጠውን መክሊት ነግዶበት ለጌታው ካላተረፈበት ወየውለት! ከዳተኛው ተነጥቆ ብዙ ላለው እንደሚሰጠው ገባን። ምን ጎደለን! ሰይጣን አፈረ! እነሱ ከኳተሩበት አዳራሽ፣ የኛ ጭንቅንቅ ያለች ድንኳናችን በመንፈሳዊ ፍቅርና፣ በጌታ ፍቅር ብርሀን ተንቦገቦግች! ዕውነቱን ለመናገር ከዚያች ድንኳን “ውጡ ውጡ” አይልም ነበር።

ከትምሕርቱ በኋላ፣ ስሜታቸው የገፋፋቸው አባላት እየተነሱ የተሰማቸውን ተናገሩ። ለት ገጣሚዎች (አንድ አባትና አንድ እናት) ልብ የሚማርክ ግጥም ገጠሙ። ወጣት ሰዓና ገጣሚ ሳምራዊት ተሰማ (የነጋድራስ ተሰማ እሼቴ የልጅ-ልጅ-ልጅ) ከኢትዮጵያ ጥንታዊ ቤተክርስቲያኖች ጣርያ ላይ በዓይኖቿ ያየችውን አስታውሳ ሌሊቱን ሙሉ ስትስል አድራበት፣ መንፈሳ ሥዕል ለመልአክ ብርሀን ሸለመቻቸው። መልአከ ብርሀን ልባቸው በሐሴት ተሞላ ድሮም ብዙ ብዙ ያሳለፉ አባት ናቸውና፣ ለሳቸው የቀበሮው ባህታዊ የወፍ ግዝት አላሳሰባቸውም። ጨርሶም ትዝም ያላቸው አይመስሉም። መንፈሳዊው መርሀ ግብር እንዲህ እንዳያልቅ እየፈልግን ጊዜው ገሠገሠ። ለሥጋችን ደግሞ ቆም ቆም ብለን እህል እንድንቀምስ ተጋበዝን። የሎንደን ክርስቲያን እህቶቻችን ልዩ ናቸው። እግሬ እስኪላጥ እንደዚህ ዓይነት እህቶች የማገኝ አይመስለኝም። ወንዶቹ ስንደክም ግንባር ቀደም ተዋግተው የሚያነቃቁን እኮ እነሱ ናቸው። አንዴ፣ “አባ” ግርማ ወደ አቡነ ኤሊያስ ወስደው ያስቀሰሱት አባተ ሲያስተምር፣ “የነሱ ሴቶች እኮ ከወንዶቹ ቀድመው ስለሚጋፈጡ፣ ወንዶቻቸውን ስለሚከላከሉላቸው፣ ፖሊሶች አይነኳቸውም። የኛም ሴቶች እንደነሱ አድርጉ እንጂ!” አለ አሉ። ኽምምምም! የኛ ሴቶች እኮ ለወንዶቹ አስበው አይደለም ያንን ተጋድሎ የሚያደርጉት። ለዕምነታቸው እንደ እቴጌ ጣይቱ እናታቸው መዋደቃቸው ነው። በአድዋ በዓል ላይ፣ ለካንስ ብዙዎቹ፣ የአድዋ አርበኞች ልጆችና የልጅ ልጆች ኑረዋል። የአባቶቻቸውናን የአያቶቻቸውን የምኒልክ ኒሻኖችን ልጆቻቸው ደረት ላይ ሰከተው አላመጡ መሰላቸሁ? የኛ ሴቶች እኮ፣ በደምም በግብርም፣ የጣይቱ ልጆች ናቸው። የወያኔ ሴትማ በየትኛው በኩል ነው፣ የጣይቱን መንፈስ የምትላበሰውና ግንባር ቀደም ተዋጊ የምትሆነው! ወዲያልኝ ወዲያ! አሰድናቂዎቹ እህቶቻችን፣ በሰባት ሰባት ቤተሰብ ተራ ገብተው የምንበላውንና የምንጠጣውን አሳጥተውን አያውቁም። እንዲያውም ከቤተ ክርስትያኑ ውስጥ እየወጡ እኛ ጋ ሲመጡ እንጀራ ያበላናቸው ብዙ ወጣቶች አሉ። አንዷ የ’ኦርቶድክስ ዕምነት ተከታይ ፈርንጅ፣ እነሱ ጋ እየሄደች አስቀድሳ፣ ነገሩ ስላልገባት እኛ ጋ እየመጣች ጣፋጭ የጾም ወጥ እና እንጀራ እየብላች ሰነበተች። ለምን ቤተክርስትያኑ ውስጥ ጥቂት ሰዎች፣ ሜዳ ላይ ገን ብዙ ሰው እንዳለ ግራ ገብቷት፣ አንዷን እህት ስትጠይቃት፣ እህታችን ቀስ ብላ ስታስረዳት፣ ደንግጣ፣ ሁለተኛ እዚያ ሙትቻ ብቻ የበዛበት ghost houseላትገባ ምላ ደንኳናችንን ተቀላቅለች። ማጋነኔ እንዳይመስላችሁ። ያየሁትን ነው የማካፍላችሁ! የገብረ ሔር ዕለት ባለተረኛ መጋቢዎቻችን ከምንጊዜውም የበለጠ፣ ዝግጅት አድርገው ነው ግብር ያገቡን። እንጀራው፣ ቅንጬው፣ የሽምብራ አሹቁ፣ ሽሮው፣ ክኩ፣ አልጫው፣ የሱፍ ፍትፍቱ፣ ተልባው፣ ጎመኑ ... ስንቱን ዘርዝሬ እዘልቀዋለሁ። ድግስ በድግስ ነው ያደረጉት። የትም ሬስቶራንት ሄጄ ይሁን እቤቴም እንዲህ የሚጣፍጥ ምግብ ብልቼም አላውቅጠላና ጠጅ ብቻ ቀርን እንጂ፣ ድል ያለ ድግስ ነው ያበሉንጠላውና ጠጁንም ለማምጣት ባልቸገራቸው ነበር፣ ሁዳዴ ጦም ሁኖ ቀረ እንጂ! የኛን “እዬዬው” ለቅሶ ለማየት ጓጉተው የነበሩት የቀበሮ ባሕታውያን ደንገጡሮች፣ ነገር ዓለሙ ተላብጦባቸው አፈሩ። እኛ መንፈስ ሞል፣ ስጋችንንም በሚጣፍጡ የጾም ምግቦች ገንብተን፣ በመዝሙርና በዜማ ቦታውን ስናቀልጠው፣ አላፊ አግዳሚው እንግሊዛዊ በአድናቆት ሲያየን እየተቃቀፍን እየተሳሳቅን በደስታ ያንን ሁሉ ያደረገልን አምላካችንን ስናመሰግንከየቦታው ተጠርተው ቤተክርስትያናችንን የወረሩት ውሪዎች ግን እንደሌባ ሹክክ ብለው ገብተው፣ ሹክክ ብለው ወጥተውአልፎ-አልፎ እናያቸው ነበር። እግዚአብሔር ከኛ ጋር ነው። መሪጌታ ሀዲስ አንዴ እንዳስተማሩን፣ እነዚህ የቀበሮ ባህታውያን የማይበቅል፣ የማያፈራ የተቀቀለ ዘር ይዘው ነው የሚዞሩት! 

እግዚአብሔር ያከበረውን ካህን፣ ሰይጣን ሲያዋርደው አይታችሁ ታውቃላችሁ? ሰይጣን ለጊዜው ሊደንስ ይችላል። እዮብንም እንዲፈትነው ተፈቅዶለት ነበር። ጌታ እየሱስን እንኳን በድፍረት ተፈታትኖታል። የማታ የማታ ወዳቂ ነው። የቀበሮ ባሕታውያንም የማታ ማታ የሚጠብቃቸው ይኸው ነው። እንዲህ ዓይነት ምንኵስና ታይቶም አይታወቅ!

የዘመኑ መነኰሳት ነን ባዮች የቀበሮ ባሕታውያን፣ አክሴማ እየለበሱ፣ በየሥርቻው ልጅ እየወለዱ ሳያሳድጉ ከኃላፊነታቸው እየሸሹ ከሚኖሩት አስመሳዮች፣ በትዳርና በቤተሰብ ኃላፊነት የሚኖሩ እናትና አባት ክርስቲያኖች፣ ከነዚህ ኃይማኖት ሸቃጮች ይሻላሉ። የበለጡ የእግዚአብሔር ሰዎች መሆናቸውን የሎንዶኖቹ ወንድሞችና እህቶች ከገባቸው 13 ወራት አልፎአቸዋል። ብዙ ሰዎች በዕለቱ ብጫ ልብሰው ሳያቸው የተሰማኝ፣ የቀበሮ ባሕታውያን የምንኵስናን ገጽ በማጉደፋቸው ቆሽታቸው አርሮባቸው “ምንኵስናችሁ እንዲህ ነው እንዴ” ለማለ“እናንተ ወንጀል እየሠራችሁ መንኰሳት ነን ካላችሁ፣ እኛ ልብሱን ብንለብስ በበለጠ ያምርብናል፣ ከናንተም የተሻልን የእግዚአብሔር ልጆች ነኝ” የሚል መልዕክት ለማስተላልፍ መስሎኝ ነበር። ለካንስ ነገሩ ሌላ ነበር።  

ደስ አይሉም? እንደዚያ ብረዳውም አይፈረድብኝም አንድም “ከናንተ ዘማውያን እኛ ብንለብሰው እናስደስተዋለን” የሚሉ መስለውኝ ነበር። ለምን ቢባል ጌታን ከልባው እንደሚያፈቅሩትና አክብረው እንደሚያስከበሩት ስለማውቅ ነው። ግብራቸው ከቆሸሸ የሎንደኖቹ ጣምራ የቀበሮ ባህታውያን፣ እነሱ ቢለብሱ፣ እግዚአብሔር ይከበራል። ነገሩ ከእንግሊዝ እንጂ ከደብረ-ሊባኖስ አልመጣ! እነሱ እርግጥ እንደሱ አላሉም። እኔ ነኝ እንደሱ የገባኝ። ገጣሚ እሰይተ እንዳስረዱት፣ በዕለቱ የተለበሱብጫ ልብሶች ትርጉም ሲነግሩን፣ ለጌታ እግዚአብሔር እራሳቸውን ያገለሉትን ገዳማዊ መነኰስታን ለማስታውስና የተገዙትን፣ ልብሶች አስፈላጊ ቁሳቁሶች፣ ዋልድባ ለሚገኙት የወያኔ ሰለባ ለሆኑት ሐቀኛ አባቶች፣ ልከው፣ “አይዞአችሁ! እኛ የመንፈስ ልጆቻችሁ ከጎናቸው ነን” ለማለት ታስቦ መሆኑን ነግረውን፣ ሌሎችም ለዚህ የተቀደስ ተግባር ለመሰለፍ የምንፈልግ እንዳለን፣ እንድነተባበራቸው አሳስበውናል። ደስ አለን። ለንደን ውስጥ የሚኖሩትን የቀበሮ ባህታውያንን፣ አወቅናቸው ናቅናችውበዋልድባና በሌሎች የአገራችን ገዳሞች የሚኖሩትን የእግዚአብሔር መነኮሳትን፣ በገብረ ሔር እሑድ አስታወስናቸው! አከበርናቸው።

ለማንኛውም፣ “አባ” ተባዮቹ በአደረጉት የወፍ ግዝት እነሱ አፈሩ እንጂ እኛስ በእግዚአብሔር ታማኝ አገልጋይ ቀን ተደስተን፣ በቅዱስ ፈስ ተሞልተን ሐሴት አድርገንወንጌልን ቃል ትርጉም ተምረን፣ ከመራገም ይልቅ፣ “ልቦና ይስጣቸው” እያልን መርቀናቸው ወደየቤታችን በሰላም ተመልሰናል

“አባ” እንጦንስና አባ ግርማ የሠሩት ወንጀል፣ በታሪክ ተጽፎ ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ ኃጢአት ነው። ደጋግ አባቶች መኖራቸው በጀን እንጂ፣ የነሱ ሥራስ ሰው አገር እየኖርን የምንወልዳችው ልጆች፣ “ኦርቶዶክስ እምነት እንዲህ የሰው መብት የሚጋፋ ነው እንዴ” ብለው ቢጠይቁን መልስ ባጣን ነበር። ጥሩ መልስ ካጣን ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን ጥይቄ ውስጥ ሊያገቡብን ሊሆን ነው። እነዚህ በጣምራ ከሁለት አቅጣጫ፣ ገዳሞቻችንን የወረሩት አስመሳይ ባሕታውያን፣ ምነው የቀድሞውን ምንኩስና መሥራች የዕውነተኛውን የአባ እንጦንስ[9] ታሪክ ቢማሩ። እርግጠኛ ነኝ፣ በዚህ ለሥጋ ሟች ባሕሪያቸውን ይዘው፣ በውሸት መንኵሰው የማይመስል ትርዒት ከመከወን በታቀቡ ነበር። ፣ ምንኵስናን ባላሰደቡ ነበር። የአባቶችን ሥርዓተ ምንግኵስና ቅጣ አንባሩን ባላሳጡት ነበር። የምንኩስናን ሰናየ ምግባር ባላቆሸሹት ነበር። እግዚአብሔር ሙሴን እንደገና አስነስቶ እነዚህ ሸፍጠኞችን ጠርጎ ጠራርጎ ከዕውነተኞቹ መነኰሳት ማኅበር ለይቶ ወደ ጨላማው ካልጣለልን በስተቀር፣ ምንኵስና ሳይወጡና ሳይወርዱ መከበሪያ የቁጭ በሉዎች ሙያ ወይም ፕሮፌሽን እንዳይሆን ያሰጋል። ሳይመንኵሱ እኮ እግዚአብሔርን ማገልገል ይቻላል። ጳውሎስ ለእግዚአብሔር ተለየ። ጽድቅ ሁኖ ተቆጠረለት። ጴጥሮስ ሚስቱንና ቤተሰቡን ይዙ ክርስቶስን በፍቅር ተከተለው። ጌታ የመንገሥተ ሰማያትን ቁልፍ አስረከበው። ከመነኰሳችሁ እንደመነኵሴ ኑሩ። ካልመነኮሳችሁ ድግሞ አግቡና በዝታችሁ ተባዙ! አታጭበርብሩን ነው የምንላችሁ፣ የቀበሮ ባሕታውያን!

ብጹአን አባቶች! እንደ ግሩምና እንጦንስ ምግባረ ብልሹ የቀበሮ ባሕታዊያን ስማችሁ እየጎደፉ፣ መልካሙ ገጻችሁ እያበላሹ ነውና አንድ ነገር በሉ! ዝም አትበሉ! አለመሞቅም፣ አለመቀዝቀዝም፣ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት የለውም (ራዕይ ፫/፲፶-፲፯)።  ወደላይ መናገሬ አይደለም፣ ያ ቢሆን “ልጅ እናቷን ምጥ አስተማረች” ይሆንብኛል። ዝምታን ከመረጣችሁ እነዚህ የቀን ጅቦች የእግዚአብሔርን በጎች ልክ ሎንደን እንደተፈጠረው፣ እንደሚያስነጥቁ አትርሱ! እንደ አቡነ ጴትሮስ ለዕውነት ሰማዕትነትም አንድ ነገር ነው። በዚህ በኩል የካናዳውን አቡነ መቃርዮስን ላመሰግን እወዳለሁ!

መደምደሚያ

“አባ” እንጦንስና ጎረምሳው ግሩም፣ ዛሬ፣ ቀሲስ ብርሀኑን፣ ያለምንም ጥፋት ሕዝቡን እንዳያገለግሉ ለመገዘት ሞክረዋል። ቀሲስ ብርሀኑ፣ በዕውነት አቤት የሚሉበት ቦታ የላቸውም። የአገር ቤቱ ሲኖዶስ፣ ሌቦች ልጆቹን ሊቀጣ የተዘጋጀ አይመስልም።  አቡነ ገብርኤልና አቡነ ቀውስቶስ አድርገውን የሄዱትን ጉድ ስናስብ፣ “አይዞአቸው በሸፍጡ ቀጥሉበት የሚሉና የሚያበረታቷቸው ይመስላሉ። ወደውጪው ሲኖዶስ አቤት አይሉ፣ ምክንያቱም እኚህ የቀበሮ ባሕታዊውን አቡነ መርቆርዮስ አልሾሟቸውም። በመሀል ዕውነት አፈር ዲሜ ጋጠች። አባቶቻችን የወፍ ግዝትን የሚፈታ ቀመር ወይም ፎርሙላ ቢተውልንም፣ “የወፍ ግዝት” መሆኑን የሚናገረን ጀግና አባት እንፈልጋለን። ይኸውም መሆን ያለበት እኛ ጠይቀን ሳይሆን፣ የክርስቶስ ፍቅር ያቃጠላቸው አባቶች በራሳቸው ተነሳሽነት መሆን አለበት። ግዝት ችላ ተብሎ፣- ተግባር እንደድሮው (Business As Usual) የሚባልበት ዘመን ላይ ደርሰናል። 

ንደን ውስጥ እንበል፣ ቄስ ብርሀኑ ተገዝተዋልና እቤታቸው ቢቀመጡ፣ እኛ ምዕምናኑ ዝም ብለን ልንቀመጥ ነውን? ያልተገዘተ ካህን ፈልጉ እንባል ይኾናል። ጥሩ! ነገ ከሆነ ቦታ ያልተገዘተ ቄስ ፈልገን አምጥተን ምሕላ እንዲደረግልን ማድረግ ምናልባት ለጊዜው እንችል ይኾናል። ትግላችንን ግን ማቆም አንችልም። ክፋት የሚነግሰው እኮ በደጋጎቹ ዝምታ ነው። አይደል እንዴ? ታዲያ አንድ የወያኔ ወፈፌ ካድሬ ካህን ነኝ ባይ ውሀ ቀጠነ ብለው ካህናችንን ቢገዝቱብን ሌላ ካህን ደግሞ ፍለጋ ልንንከራተት ነው? እንደዚያማ ከሆነ፣ ከማንወጣው አዙሪት ገብተን ስንሽክረከር ሳይጣን በደስታ ለፈነድቅብን ነው። ንጹሐን አባቶች፣ የቀበሮ ባሕታውያንን መረን የለቀቀ ግዝት ዝም ብላችሁ አንዳታዩ። ለንደን ላይ የተፈጸመው ጉድ የምትወስዱት እርምጃ፣ ለቤተክርቲያናችን የወደፊት ዕጣ ዕጣ-ፈንታ ፍረንጆች make or break የሚሉት ዓይነት የማይዳግም ወሳኝ ዕርምጃ መሆን አለበት። ግሩምና እንጦንስ፣ በዕወነቱ መወገዝ ያለባቸውና፣ ከቅዱሳን ማኅበር መባረር ያለባቸው ምግባረ ብልሹ የቀበሮ ባኅታዊያን ናቸው። ይኸን ጉድ እያዩ ዝም ማለት፣ የክፋት ልጅ አድጎ ተመንድጎ፣ ከዚህ የበለጠ ወንጀል ሠርቶ እንደካቶሊኮቹ ቤተክርስቲያን፣ “ጉዳችንን እንሸሽግ” እየተባለ ይከርምና አደባባይ ሲወጣ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተውህዶ ዕምነት የዓለም መሳቂያና መሳለቂያ ልትሆን ነው። አንድ ነገር አድርጉ። በዕርግጠኝነት የምናገረው፣ ሁልቱም የሎንደኖቹ የቀበሮ ባህታዊያን፣ ወያኔዎች ናቸው። ወያኔን አትፍሩ። ሥጋችሁን እንጂ መንፈሳችሁን መግደል አይችልም።

መልአከ ብርሀን ቀሲስ ብርሀኑ ብሥራት፣ የሥርዓት ሰው ናቸው። እነዚህ የወያኔ አገልጋዮች ሊቆጣጠሩን በጳጳስ ነኝ ባዩ እንጦንስ ያስተላለፉትን ወፈ-ግዝት እንዴት እንደሚያዩት በጣም ግራ ገብቶአቸው ነበር። ከብዙ ሰዎችም ምክር ተቀብለዋል። ግዙቱን ተቀብለው፣ ተግባራዊ ለማድረግም አውጥተው አውርደዋል። ግዝቱን ተቀብለው ተግባራዊ  ማድረግ ማለት፣ ዕድሜ ልካቸውን ቀድሰው ያቆረቧቸውን ልጆቻቸውን መበተን ማለት ነው። ማንን ለማስደሰት? ቤተክርስቲያናችንን በግዝት አስሮን ሊቀማን የቆመውን የበግ ለምድ ለባሽ ተኵላ? አማራጭ ቄስ እንኳን ቢኖር ፍርድ እስኪያገኙ ድረስ፣ እጃቸውን አጣጥፈው እቤታቸው በተቀመጡ ነበር። ለመንፈስ ልጆቻቸው እንክብካቤ፣ ሌላ በቅስና ማዕረግ ያለ ካህን የለንም። በእንደዚህ ሁኔታ ምንድነው የሚደረገው? ስለነዚህ ሁለቱ ሌቦች ውሳኔ ተጨንቄ ሳይሆን፣ ዕምነታችንን የሚሸረሽር ስሕተት እንዳንሠራ ነው። ሕዝባችን የማይጎዳበትን፣ የማይበተንበትን፣ ከእግዚአብሔር የታያችሁን ምክር ብትለግሱን፣ ከሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያስደስተን ስጦታ ነው።

እኛ በየዓቢዩ ጾም የቀበሮ ባሕታውያን እያሰናከሉን፣ ጾምን ብለንም አንመጻደቅም። አሁን በዚህ ሰዓት የቀበሮ ባህታዊያን እንዲህ ዓይነት ውጥንቅጥ ውስጥ ባይጥሉን፣ በዚህ በሱባዔ እንዲህ ያለ ጽሑፍ ለመጻፍ ባልተገደድኩ። ሱባዔ በገባሁ። እነዚህ ሰይጣን እንደመጋጃ ጭኖ የሚጋልባቸው የቀበሮ ባሕታዊያን፣ እኛ ታናናሾችን እያሰናከሉን ተቸግረናል። ሱባዔአችን በአስመሳይ መነኰሳት ለተጨናገፈብን ምዕምን ክርስቲያኖች እና ከኛ ጋር ለዕውነት ለቆሙት ካህናት ሱባኤ እንድትገቡልን እንጠይቃለን፣ ነገሩ የገባችሁ፣ እግዚአብሔር ከናንተ ጋር መሆኑን የምታውቁ ብጹዓን አባቶች፣ ከሥጋና ከወተቱ ታቀብን እንጂ፣ ትግል ውስጥ ሁነን ጾሙን ጾምን አንልም። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በያሉበት ሲጽልዩልን እናንተ ደግሞ አባቶቻችን ፍቱን!

ይኸንን ጽሑፍ በጽሞና ያነበባችሁ ወንድሞችና እህቶች፣ በያላችሁበት የእግዚአብሔር ጸጋ ይብዛላችሁ። ቀሪውን የጾም ጊዜ፣ የሰላሙ ጌታ፣ ስላማዊው አባታችን፣ እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፣ በሰላም ያስፈጽምላችሁ። ሎንደን ላይ ከደረሰው መከራ ይሠውራችሁ!

ስብሐት ለእግዚአብሔር!

በሚቀጥለው ገጽ፣ መልአክ ብርሀን ቀሲስ ብርሀኑ ብሥራት ለ“አባ” እንጦንስ የመለሱትን መልስ ልግንዛቤአችሁ እንድታዩት ስላያያዝኩት፣ እንድታነቡት እጋብዛችኋለህ። አንብቡት። ዳኛኝነቱን ለሕሊናችሁ ትቼዋልሁ። እግዚአብሔር ያሳያችሁ!





[1] https://www.facebook.com/EthiopianReview/posts/10202561267408308
[2] http://www.ethiomedia.com/addis/ababasubat.pdf
[3] http://ecadforum.com/Amharic/archives/8778/
[5] Berhe, Aregawi (2008) A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopia, Amsterdam,  PhD Thesis.