Sunday 5 February 2023

ኦርቶዶክስ ተዋህዶን መናዱ፣ ከሦስቱ ግንዶች አንዱ!

 ኦርቶዶክስ ተዋህዶን መናዱ፣ ከሦስቱ ግንዶች አንዱ!



እንግዲህ ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ ...
ብሎ የጀምራል የዮሐንስ ራዕይ መዕራፍ 2 ቁጥር 5!

 ወንድሙ መኰንን፣ እንግላንድ 05/02/2023

መግቢያ

ዘረኞች ካሉ ማን በሰላም ተኝቶ ያድራል? ዘሮኞች ሥልጣን ላይ ከወጡማ፣ አያድርስ ነው። የጎጠኝነትን ጠንቅ በሩዋንዳ አይተናል። የአንድ አገር ልጆች በጎሳ ተከፋፍለው፣ ተጨፋጨፉ፣ ተገዳደሉ። ያሸነፈው አሸንፎ፣ ተሸናፊው በጄኖሳይድ ተክሶ እስከዛሬ ይወቀሳል። ከስህተቱ የተማረ የሩዋንዳ ህዝብ ዛሬ፣ ስለዘር ማውራት በሕግ የተከለከለ ነው። ዘረኝነት በዚያ አገር ዛሬ ዕርም (ታቡ) ቃል ነው። “የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም” ይላል ያገሬ ሰው። ኢትዮጵያውያን ግን ከሩዋንዳ መማር አልቻልንም። ትላንት መጥፎ ጊዜ አሳልፈን ነበር። ዛሬም ህዝባችን አሣሩን እየበላ ነው። ሕዝባችን ተገፍቶ ከድጡ ወደማጡ ገብቷል። ነገስ?

የኢትዮጵያ ዘረኞች ጥምድ አድርገው የያዙትና በየጊዜው የሚያቆረቁዙ፣ የዘረኝነት ስሜት ያልነበረውን መንዜውን፣ ጅሩዬውን፣ መርሀቤቴውን፣ ቡልጌውን፣ ተጉለቴውን፣ ወሎዬውን፣ ጎጃሜውን፣ ጎንደሬውን “አማራ” እያሉ ነው። ይኸን አማራ፣ በምናባቸው ጭራቅ አድርገው ስለው ቀን ሲያናውዛቸው ውሎ ማታ ሲያቃዣቸው ያድራል። ይኸን ምስኪን ሕዝብ ያለጥፋቱ ጥፋት ፈጥረውለት፣ (ለምሳሌ የአኖሌ የሌሌ ታሪክ) ጠብ ያለሽ በዳቦ እያሉ ይጨፈጭፉታል። ዓላማቸው ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው። ሌላው የኢትዮጵይዊነት ትልቁ ግንድ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና ነው። የአንድነት ተምሳሌቱን ከሦስቱ አንዱን ግንድ መገንደስ ማለት የኦርቶዶክስ ሀይማኖትን ማጥፋት ነው። ለነገሩ ደግ የማይመኙልን እንድ ባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ (Baron Roman Prochazka)[i] እና ጄምስ ኤድዊን ባውም (James Edwin Baum)[ii] የተባሉ የነጩ ዓለም ጸሐፊዎች፣ እንዲሁም የአሜሪካ ስቴትስ ዴፓርትመንት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ሄነሪ ኪሲንጀር ኢትዮጵያ ከበለጸገች ለነጩ ዓለም አደጋ ስለምትደቅን ሦስቱን አምዶቿን ማፈራረስ እንደ ረዥም ዕቅዳቸው (ስትራተጂያቸው) ነድፈው ቁጭ ቁጭ አድርገውልናል። አንዱ አንድ የሚያደርጋትን የዘውድ ሥርዓቷን መገርሰስ ነው። ያንን የደርጉ ሥርዓት አሳክቶላቸዋል። ሀለተኛው የኦርቶዶክስ ሀይማኖቷን ማጥፋት ነው። ደርግ ሞክሮ ሳይሳካለት ለዘረኞቹ ትቶት ጠፍቷል። ሦስተኛው፣ አማራ የሚባለውን ህዝቧን ከሌሎች ጎሳዎች ጋር አጋጭቶ፣ ማስጨፍጨፍ ነው። የወያኔው ኢህአዴግ ለ27 ዓመታት ሂዶበት አሁን ደሞ የኦህዴዱ ብልጽግና ላለፉት አራት ዓመታት እያከናወነላቸው ነው። ፕሮጄክታቸው፣ ገና አላለቀም።

በከንቱ ልፉ ብሏቸው ነው እንጂ፣ ኢትዮጵያስ አትጠፋም። ኢትዮጵያ ምርጥ የእግዚአብሔር ርስት ናት።

የዘርኝነት ፖሊቲካ በኢትዮጵያ

ዘረኝነትን ሲያሰማምሯት የኢትዮጵያ ዘረኞች “ብሔር ብሔርሰቦች ህዝቦች” ብለው ጠሯት። የፖሊቲካ ቀለም ሲቀቧትም “ፌዲራሊዝም” አሏት። ድንቄም ፊዴራሊዝም! ዓላማቸውን ለማሳካት ህዝቡን በቋንቋ ከልለው፣ “በአፍ መፍቻህ ቋንቋህ ተማር” አሉት። እንዳይግባባ እኮ ነው! ትልቁ ከፋፍሎ የመግዛቱ ፍቱን ዘዴ የህዝቡን መግባቢያ በቋንቋ አጥፍቶ መደበላለቅ ነው። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት የምትለየው አንዱ የራሷን ፊደል መጠቀም ነው። ህዝቡን የጋራ እሴት እንዳይኖረው አንድ ፊደል እንኳን እንዳይጠቀም፣ ኩቤ የሚባል የላቲን የፊደል ሾርባ ሾርበው ጋቱት።

ታላቋ የተዋጣላት ፌዴራሊስት አገር ብትኖር የተባበረችው አሜሪካ (United States of America – US) ናት። ከዚህ በኋላ እንዲቀለን፣ አሜሪካ እንበላት። እንደ አገሪቱ የሕዝብ ቆጠራ ስታቲስቲክስ ጽሕፈት ቤት፣ በአሜሪካ 350 ቋንቋዎች ይነገራሉ። ከንግሊዝኛ ሌላ፣ ከሦስቱ ሁለቱ የአሜሪካዊ የሚናገረው ስፓኒሽ ነው። የፌዴራሉ ቋንቋ ግን እንግሊዝኛ ነው። ትምህርቶቹም በቀደምትነት የሚሰጡት በእንግሊዝኛ ሲሆን፣ ተጨማሪ ቋንቋ እንደፍላጎቱ በትምህርት ቤትም በዩኒቨርሲቲም ይሰጣል። ግዕዝም ሳይቀር። በዚህ የተነሳ ከሎስ አንጀለስ እስከ ኒው ዮርክ ከተሞች፣ ሕዝቡ በአንድ ቋንቋ ይናገራል፣ ይግባባል፣ ይነጋገዳል፣ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ ይሠራል። አስተርጓሚ አያሻውም። አገሪቷ፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢኮናሚ በልጽጋ፣ ልዕለ ኃያል ህናለች። እነዚህ እንግዲህ በእውነቱ የተዋህዱ ሀምሳ አገራት ናቸው። እኛስ? አቦ ተወና!

ዘረኝነት የተጠናወታቸው የሕወሀት ሊሂቃን ተደራጅተው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን ተዋዶ፣ ተፋቅሮ፣ እና ተጋብቶ ተዛምዶ ከሚኖርበት፣ በዘር በታተኑት። በለስ ቀንቷቸው ለ27 ዓመታት በሕዝቡ ልብ ውስጥ ዘረኝነትን ዘሩት። ኢህአዴግ የሚባል ካባ ደርበው፣ የዘረኞች ካድሬ አሰልጥነው ሕብረተሰቡን በዘረኝነት  መርዝ በከሉት። የዘረኛ ሕገ-መንግስትም ቀርጸው አከናነቡት። የዘሩት የዘረኝነት ዘር፣ ዛሬ ላይ በቅሎ አብቦ፣ ፍሬው ጎመራ። ዘረኝነትን ይጸየፍ የነበረውም ”ከሌላው በምን አንሼ፣” በሚል ስሜት ዘረኛ ሁኖ ቁጭ አለ። ታዲያ በአገራችን ፍሬው የጎመራው ዘረኝነት ውሎ አድሮ መልሶ ፈጣሪውን የትግራይ ጽንፈኛን ቀረጠፈው። ጄኖሳይድ እያለ ቢጮህ ማን ይሰማዋል? ሥራ ለሠሪው እሾህ ላጣሪው ይባላል። ሌላ የራበው ዘረኛ ተነሳለታ! ለሕዝቡም ተረፈለት። ለኃጢያን የመጣ ለጻድቃንም ይተርፋል ይባል የለ? መቅሰፍቱ እሱን ብቻ ይዞ በጠፋ! አማራውንና አፋሩን ረፈረፈው።

በወያኔ ሥር ተኮትኩቶ አድጎ ለቁምነገር በቅቶ፣ ጊዜ ጠብቆ፣ የሕዝቡን ብሶት ተጠቅሞ፣ አሳዳጊዎቹ ላይ በብልሀትና በዘዴ አምጾ፣ በተለይ አማራውን አግባብቶና አወናብዶ (convince and confuse)[iii] የአራት ኪሎን ወንበር የነጠቀው ተረኛው ዘረኛ የኦሮሞ ጽንፈኛ ሁኖ ተገኘ። ኮቱን ገለበጠና “ብልጽግና” ነኝ አለ እንጂ ያው እህአዴግ ነው። ያው የዘረኝነት እንጂ ሌላ ሥርዐት እኮ አያውቅማ። ለውጥ መጣልን ብለን አሸሻ ገዳሜ ያልን ሁላ ካለንበት ወርደን ከድጡ ወደ ማጡ ወድቀን እየዳከርን ነው።

እርካቡን ረግጠው መንበሩን የተቆጣጠሩት ዶር ዐቢይ

አንድ ዲራአዝ የተባለ ጸሐፊ በደረሰው “እርካብና መንበር" የተባለ ድንቅ መጽሐፍ ክፍል አንድን፣ በአልበርት አንስታየን አባባል እንዲህ ሲል ይጀምራል፡ “ችግሩን በፈጠረው አስተሳሰብ፣ ችግርን መፍታት አይቻልም” ይላል። ድንቅ ጥቅስ ነው። አንድ ዘፋኝ እንዲህ ይላል።

በሀሰት ስትምዪ፣ ምላስሽ ልስልስ ነው፤
ቅርሽም እንደ አፍሽ፣ ቢሆንልኝ ምነው?

ዶክተር ዐቢይ የመጡልን (ዋ! የመጡብን አላልኩም፣ ነገሬን አታጣምሙብኝ) የወያኔ የዘር ፖሊቲካ ከገማና ከገለማ በኋላ ነው። እሳቸውም የሄዱበት መንገድ በዚያው ፍልስፍና ነው። ሕዝቡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ፣ በግፍ ሰንሰለት ታስሮ የጭቆና አስተዳደሩ ብሶት አንገብግቦት ምድሪቱን ቀውጢ አደረጋት። ኦሮሞው በቄሮ ተደራጅቶ መትረየስና ቦምብ የታጠቀውን በዶ እጁን ከአናቱ በላይ አጣምሮ ተጋፈጠ። የሚችሉትን ያህል ገደሉ። ቆራጡ አማራ በፋኖ ተደራጅቶ፣ ሀምሳ ቢሞትበት አሥሩን እየደፋ፣ ተመመ። “በከንቱ ኦሮሚያ ውስጥ የሚፈሰው የኦሮሞ ደም ደሜ ነው” ብሎ ሲያውጅ፣ የወያኔ የዘረኛ መንበር ተነቃነቀ። ጉራጌው ዘርማ በሚል የወጣት ክንፍ ተጋፈጠው። ደቡቡ ነብሮ ብሎ ተነሳበት። ጥግ ይዘው ተራቸውን ይጠባበቁ የነበሩት፣ ብልሀተኛ የኦሮሞ ሊሂቃን ተመካከሩና፣ “ኢትዮጵያ ሱሴ ናት”ን  እየዘመሩ ዐባይን ተሻገሩ። “ትግሬ ከፋፈለን እንጂ አንድ እኮ ነን” ሲሉ አማራው እጁን ዘርግቶ እንባውን እየረጨ፣ አርባ ጉጉን ረስቶ፣ በደኖን ረስቶ፣ ወተርን ረስቶ ... አቅፎ ተቀባላቸው። ካባ አለበሳቸው። ኢትዮጵያዊነት በደም ሥሩ የሰረጸው አማራ፣ ያለምንም ማቅማማት፣ በውሸት ትርክት ጭራቅ ሁኖ መሳሉን ረስቶ፣ የተቆረጠ ጡት ባልዋለብት እሱ እንደቆረጠው ተቀርጾ የቆመውን ሐውልት እንኳን ዞር ብሎ ሳያይ፣ “ኦሮማራ” በሚል ወጥመድ ገባላቸው። ዶር ዐብይ “በሬ ሆይ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” የሚሉት ይኸንን ነው። ከሁለቱ እርካብ አንዱ ሆነላቸውና ለዶክተር ዐብይ ወደ መንበር መወጣጫ ተመቻቸላቸው።

ዶክተር ዐብይ ልዩ ስጦታ ያላቸው ተናጋሪ (ኦራቶር) ናቸው። እንደመጡ ልባችንን መርምረው ስለሚያውቁት የምንፈልገውን እየነገሩን፣ በፍቅር አናወዙን። “ኢትዮጵያዬ” ስሉን፣ ዓይናችን ጭልምልም ልባችን ስልምልም አለላቸው። ተነጠፍንላቸው። የትግሬው ዘረኛ ገዥ መንበሩን ጥሎላቸው ወደመቀሌ ነጎደ። የኦሮሞው ገዥ መደብ በዶክተር ዐብይ እየተመራ ወደ አራት ኪሎ ሂዶ መንበሩ ላይ ጉብ አለ! የበሻሻው አራዳ፣ ዶር ዐብይ ሆዬ፣ ተቃዋሚውን “ና ግባ” ብለው ቀይ ምንጣፍ አስነጠፉለት። ከኦሮሞ ነጻ አውጪ ሠራዊት በስተቀር እያንዳንድዱ ተቃዋሚ መሣሪያውን ቁጭ አድርጎ ገባላቸው። እሳቸውም፣ “ከዚህ በኋላ ስምህ "ተፎካካሪ” እንጂ “ተቃዋሚ” አትባልም አሉት። ጌታ እየሱስ ሳናስበው በአቋርጭ ተመልሶ መጣ እንዴ ያልንም ነበርን። ሁሉም አዚም አንዳዞሩብት በያለበት በፍቅር ገበረላቸው። ተቃዋሚውን በዚህ መንገድ እሹሩሩ ብለው አስተኙት። ፈርንጆች እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ “hypnotic stupor”  ይሉታል። አፈዝ አድንግዝ እንበለው? እስረኞችን፣ የሞት ፍርድ ላይ ያሉትን ሳይቀር ፈቱልን። ከዚህ በኋላ አንድ ሰው ወንጀሉ ሳይጣራ አንሳርም። አስረን አንመረምርም አሉን። ዘፈን ተዘፈነላቸው። የጉራጌ ምስኪን እናቶች አታሟቸውን (ዲቤያቸውን) እየደለቁ፡

በአማርኛ ውሀ፣ በእንሊዝ ወተር
ዐቢዬን የጠላ፣ ሆዱን ይተርተር

 ብለው በሚጣፍጥ አማርኛቸው ዘፈኑላቸው። ባሀሩን የሚያሻግረን ሙሴ መጣልን ተባለ። ሱዳን ሂዱና ጃንሆይ እንዳደረጉት፣ የሱዳን ተቃዎሚዎች አገሪቱን ከማያበራ የእርስ በርስ ጦርነት አፋፍ መለሱት። ወደኤርትራ ሳይጋበዙ ሂደው የኢሳይያስን ልብ ብልት አድርገው፣ ወያኔ አልጀርስ ላይ የፈረመላቸውን ባድሜ አስርከቡት። ምን መጣ ተባለ! አሜሪካ ሰተት ብለው ሂደው፣ ስደተኛ የኦርቶዶክስ ፓትሪያርኩን አግባብተው ወድ ኢትዮጵያ መልሰው ከአባ ማትያስ ጎን አስቀመጧቸው። ዐብይ ማኒያ አሉት ፈረንጆቹ።

ኖርዊይ የኖቤል የሰላም ሽልማት ቸረቻቸው። አሜሪካ ሂደው የወያኔ ባልሥልጣናትን ያዋክብ የነበረውን ዲያስፖራ እሹሩሩ ብለው አስተኙት። ጀርመን ሂደው፣ የአውሮፓውን ዲያስፖራ አፍዘውት በድል ተመለሱ። መንበራቸው የጸና መሰለ! ህወሃት ኢህአዴግን እንዲያገለግል እንደፈጠረችው ሁሉ፣ ኦህዴድ እንዲያገላቸው ብልጽግና መሠረቱ። የኔ ቃል አይደለም። የሽመልስ አብዲሳ ቃል ነው።

ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ መልክት አለኝ! ሰው እንዳማረበት አይሞትም። ዛሬ ከሕገወጡ መፈንቅለ ሲኖዶስ የፈጸመው፣ የኦሮሚያ ሲኖዶስ ነኝ ላለው “በቋንቋዬ ልቀድስ ብሎ መነሳቱ ትክክል ነው” በማለት ዕውቅና ሰጥተውታል። በዚያ ምክንያት የኦሮሞ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ በየቦታው የኦርቶዶክስ ምዕምናን ሕይወት ቀጥፎ ቤተክርስቲያን ሰብሮ ገብቶ ለህገወጦቹ አስረክቧል። አንዱ እርካባቸው ተበጥሷል። መንበራቸውም ተነቃንቋል። አንድ እርካብ አይስተማምንም። የደርግና የወያኔ እጣ ይጥብቃቸዋል።

ባለጊዜዎቹ! ያሁኑ ይባስ!

ቀድም ብዬ፣ ሁሉም ተቃዋሚ መሣሪያውን አስቀምጦ አዲስ አበባ ተመልሶ ጎዝጉዞ ሲተኛ፣ የኦነግ ሠራዊት ብቻ ነበር ከነትጥቁ በአሶሳ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የገባው። ብልጽግና ለምን ሸኔ እንደሚለው አትጠይቁኝ። አላውቅም። ሞጋሳ ሲችሉበት! ለምሳሌ፣ አብሮ አደግ ኦሮሞ ጉደኞቼ፣ ሁንዴ ጦሬ እያሉ በአንድ ስፖርተኛ ስም ይጠሩኝ ነበር። በፍቅር ነው ታዲያ! እንግዲህ ይኽ የኦነግ ሠራዊት፣ በመጀመሪያ ሥራ ላይ ባዋለው ዕቅድ ወያኔ “ኦሮሚያ” ብሎ ጠፍጥፎ ከሸለመው ክልል ኦሮሞ ያልሆኑትን ዘሮች መንጥሮ ማጽዳት ነው። አማራ የተባለውማ አይወራ። በደኖ፣ አርባ ጉጉ፣ ወተር፣ አረካ፣ አሰቦት ገዳም የጀመረውን ዕልቂት ክግቡ ማድረስ ነበረበት። ይኸን ቆሻሻ ሥራ ሲሠራለት፣ የቀድሞ ኦህዴድ ዝም ብሎ ያያየዋል። ወለጋ የደም መሬት ሆነች። ስለዚህ ወለጋ ውስጥ ደርግ ያሠፈራቸውን ብቻ ሳይሆን ከጥንት፣ አንዲያው ቢያንስ ቢያንስ ከአጼ ዮሐንስ ዘምነ መንግሥት ጀምሮ የነበሩትን አማሮች ማረዱን ቀጥሎበታል። ለዚያ ደሞ፣ የቀድሞ ኦህዴድ የአሁኑ የኦሮሞ ብልጽግና መቶ በመቶ እየተደገፈና እየታጠቀ ደማቸውን ደመ-ክልብ አደረጎታል። ማን ከልካይ፣ ማን እ-ሽ ባይ አለበትና። ከአማራው በተጨማሪ፣ አዲስ አበባ ጠጋ ብለው፣ ቡራዩ ላይ በሰላም የሚኖሩትን የጋሞ ተወላጆችን አረደ! ማን ነክቶት? የጨፈጨፈውን ያህል ጨፍጭፎ ከሄደ በኋል መከላከያ ደረሰ አሉን። ጀብ ከኼደ ውሻ ጮኸ ይሉሀል። ያ ወደዚያ ሂዶ የነበረው የታጠቀ ሠራዊት፣ የሚያደርገው ነገር ሲያጣ፣ ወደ ቤተ መንግሥት ጎራ ብሎ ደሞዝ ጭማሪ ለመጠየቅ ሲመጣ፣ ጠቅላይ ሚንስትራችን አባብለውት ፑሽ አፕ አሠርተውት ሸኙት።

በዚያ አላቆመም። አንድ እነሱ “ዓይናችን” የሚሉት ፖሊቲከኛ “ጥበቃ ተነስቶብኝ ተከብቤያለሁ” ብሎ በነበረው የሬዲዮና የማኅበራዊ ሚዲያ ሲያስተጋባ፣ ከዳር ዳር የኦሮሞ ሕዝብ ግር ብሎ ወጥቶ፣ አማራ ነው ብሎ የገመተውን ሁሉ በሜንጫ ጨፈጨፈው። የጉዲሳ የልጅ ልጅ የሆኑትን የራስ መኰንን ሐውልት ሐረር ላይ ፈነገለው። ናዝሬት ላይ፣ አንዱን ምስኪን ዘቅዝቀው ሰቅለው ገደሉት። ጉራጌዎችም አልተረፉም።

ትንሽ ቆይተው፣ አማራውን የሚገድሉበትን ምክንያት ሲጠፋቸው፣ ተወዳጅ የነበረውን የራሳቸውን የኦሮሞ ዘፋኝ ሀጫሉ ሁንዴሳን ገድለውት፣ “አማራ ገደለው ብለው” አማራውን በተገኘበት፣ በባሌ፣ በሸዋ፣ በሐረር፣ በወለጋ ጨፈጨፉት። ዝዋይ ላይ ከአንድ ቤተሰብ አምስት ሰዎች በአንድ ቤት አረዷቸው። የሻሻምኔን ከተማ ዶጋመድ አደረጓት። አንድ ምስኪን ባለ ልኳንዳ ቤት ጉራጌ አርሲ አግኝተውት ገድለውት በድኑን ከሥጋው ጋር ሰቅለው ሂዱ። እናንተ ባለጊዜዎች፣ ተው ሕዝቡን አታስመርሩት!

ይኸ ሁሉ የአማራ፣ የጋሞ፣ የጉራጌ ግዲያ ሲደረግ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እንዳላየ ሁነው ማለፋቸው ነው የሚገርመው። በክልላቸው የባሰውኑ፣ ጭፍጨፋ በተፈጸመ ቁጥር፣ እሳቸው፣ ወይ አበባ ወደመትከል፣ ወይ ዛፍ ወደመትከል፣ ወይ ወደእርሻ ይኸዱ ነበር። በአንድ ወቅት፣ አንዱ እንዴት ሰው አልቆ እስዎ ወደ ዛፍ ተከላ ይኸዳሉ ቢባሉ፣ “ምናለበት ባይሆን ዘመዱ የሞተበት፣ ዛፍ ጥላ ሥር ተቅመጦ ያዝናል” ብለው አሾፉ። አማራው ክልል፣ አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር ቅጠልያ የጦር ልብሳቸው ለብሰው ክቸች ማለታቸው ለተመልካች ግርም ይላል።

መስሏቸው ነው እንጂ የኦሮሞ ጽንፈኛ፣ ለሳቸውም አይተኛ። ከዚህ በፊት በመስቀል አደባባይ ሊግድላቸው ነበር። አንዱ የተጠመዱበት ትልቁ ነገር፣ ለምን አዲስ አበባን ከሌሎቹ ብሔር ብሔርሰቦች አጽድተው ለኦሮሞ አልስጡም የሚል ነው። የአፍሪካም ዋና ከተማም ስልሆነች ከአፍሪካኖችም መጽዳት ነበረባት ባዮች ናቸው መሰሉኝ። ፊንፊኔ እያሉ ፊን ፊን ይላሉ። ፊንፊኔ አማርኛ መሆኑን ማን በነገራቸው!

እንደመሰለኝ ከሆነ፣ ሁለት ዓይነት የኦሮሞ ብሔርተኞች ያሉ ይመስለኛል። አንዱ ወገን፣ ከኢትዮጵያ ተገንጥለው፣ የሚችሉትን ያህል መሬት ነጥቀው ታላቋን ኦሮሚያን መመሥረት ይመስለኛል። እየመረቀኑ በሳሏት ካርታ፣ እራሳቸውን ለጥጠው ከትግራይ ጋር አገናኝተዋል። ልብ ዕንቅርት የመኛል አሉ፣ አባቶች። ሌሎቹ ግን፣ እንደትግሬዎቹ የበላይነቱን ይዘው፣ ኢትዮጵያን እንደፈልጉት መግዛት ነው። ሁለቱም ወገኖች፣ የኦሮሚያን ኦሮሞ ካልሆኑት ማጽዳትና፣ ኬኛ የሚሏቸው ግዛቶች ጠቅልሎ መያዙ ላይ ልዩነት የላቸውም። አዲስ አበባንም የመውረር ሕልም አላቸው። ሁሌ የሚገርመኝ፣ የኦሮሞ ጽንፈኞች፣ አዲስ አበባ ዋጠችን እያሉ ሲጮሁ፣ አሁን ደሞ፣ አዲስ አበባን ካልዋጥናት ያዙን ልቀቁን ማለታቸው ነው። አብዛኛው ኦሮሞ ዝም ማለት ከትግሬ ጋር እያመሳሰለው መጥቶብኛል።



ሰሞኑን ኦነግ ከዚህም የባሰ ስፋት እንደሚይዝ ነግሮናል። ጠቅልይ ሚኒስትሩ፣ ይኸን ሁሉ የጽንፈኛ ኦሮሞን መቧረቅ እያዩ እንዳላየ መሆን፣ ይሁንታቸውን መስጠታቸውም ነው የሚያረጋግጠው። አንዳንዴም ድጋፋቸው በግልጽ ነው የሚያስቀምጡት። ሰንደቅ ዓላማውን በየትምህርት ቤቶች ሊሰቅል ሞክሮ፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ “ወዲያልኝ ወዲያ!” ሲል፣ የአዲስ አበባ ህዝብ ኦሮሞ ጠሊታ ነው ብለው በአደባባይ ተናገሩ። በውቅቱ እንደማይባል ለማለት ሞክሬያለሁ[iv]። ትምሀርት ቤት ባንዲራችን ካልተሰቀለ፣ መዝሙራችን ካልተዘመረ፣ በቁቤ በየትምህርት ቤቱ ኦሮሚኛ ካልተሰጠ ብለው ያዙን ልቀቁን፣ ሲሉ፣ የመንግሥት ጽጥታ ጠባቂዎች ሕጻናትን እያነቁ እሥር ቤት ማጎራቸውን ዝም ብሎ ማየት ወገናዊነት ነው።

በነገራችን ላይ፣ ዶር ዐብይን የሚገለብጠው ወይ በብብታቸው የያዙት የኦሮሞ ጽንፈኛ ነው፣ አለበለዚያም ሚሊታሪው ነው።ይኸ ሀቅ መነገር አለበት። አማራው እሳቸውን ለመገልበጥ ፍላጎቱም፣ አቅሙም የለውም። እራሱን ለመከላከል ብቻ ነው የሚፍጨረጨረው። በዝምታ እንደበግ ግን አይታረድላቸውም። “ኦኛን ያስቸገረን የኦሮሞ ሸኔና የአማራ ሸኔዎች ናቸው፣” ያሉት ግን ምንኛ ፍርደ ገምድል መሆናቸውን ያሳያል። ገዳዩንም፣ ሟቹንም በአንድ ላይ መደባለቅ የመደመር ፍልስፍናቸው ይሆን? አጣዬ 9 ጊዜ ስትነድ፣ ያነደዳት አማራ ነው? ሸዋ ሮቢትን ያጋያት አማራ ነው? ደራን ወሮ ደም ያፈሰሰው አማራ ነው? በየቦታው ከተማ እይወረረ ወንጀለኞችን ከእሥር ቤት የሚያስመልጠው አማራ  ነው? ከዳንጎቴ የሲሚንቶ ፋብሪካ ሰዎችን እያፈነ እየወሰደ ማስለቀቂያ ግንዘብ የሚቅበለው፣ አማራ ነው?

የኦሮሞ ብልጽግና ከኦነግ ሠራዊት ጎን ሁኖ አገሪቷን እያሸበረ ነውና፣ መንግሥት በመንግሥትነት ለመቀጠል ከፈለገ በመጀመርያ ደረጃ፣ የዶክተር ዐብይ መንግሥት፣ አበባ መትከሉን፣ ለአትክልተኞች፣ ስንዴ ማምረቱን ለግብርና ሚኒስቴር፣ ፓርክ ማሠራቱንና አዲስ ቤተመንግሥት መሥራቱን ለመሀንዲሶችና ሥራ አከፋፍለው ወይም ደሊጌት አድርገው፣ እሳቸው የሕዝብ ደኅንነትና ሰላም ላይ አጥብቀው መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

የዘር ፖሊቲከኞቹ ለመንበር ጦርነት

“When the elephants fight, the grass gets trampled.ዝሆኖች ሲጣሉ ሣሩ ነው የሚረጋገጠው!

ከመንበሩ ተፈናቅሎ መቀሌ ላይ የመሸገው የትግሬ ጽንፈኛ ቡድን፣ ይጠብቀው የነበረውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተኛበት እምሽክ አድርጎት፣ ለዳግመኝ ንግሥና ጎዞውን ከመቀሌ ጀመረ። ዳሩ ግን፣ ከዚህ በፊት ርስቱን ቀምቶ፣ በጭራቅነት ስሎ በነበረው የአማራ ሕዝብ መሬት ውስጥ ማለፍ ነበረበት። አማራው ተነሳ። ጎንደሬው አላርምድ አለው። በብልጽግና የሚዘወረው የዶክተር ዐብይ ጦር ከሰማይ በአይሮፕላንና በድሮን ሲያጋየው፣ የትግሬዎቹ ዘረኛ ገዢዎች የሞቱት ሙተው መቀሌን ለቀው ወደ ተምቤን በረሀ ሸሹ። መቀሌም ከ20 ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ወደቀች። የመከላከያ ጦሩ በድንገት መቀሌን ለቆ ወደ መሀል አገር ሲሂድ፣ የብልጽግና መንግሥት ወያኔን ለእርቅ ልመና ገባ። አማራውን ለወያኔ ትቶ ማለት ነው። “የምን ዕርቅ” አለች የዘረኝነት ፈላስፋዋ ወያኔ!

ወያኔዎች የልብ ልብ ተሰምቷቸው ዳግም ጉዟቸውን ጀመሩ። የጎንደር ፋኖ ደሙን ዘርቶ እየተዋደቀ፣ ያስመለሰውን የወልቃይት ሁመራን ርስቱን እንደያዘ አላነቃንቅ አላቸው። እሱን ትተው በአፋርና በወሎ በኩል፣ አሜሪካና መዕራብ አውሮፓውያን እየረዷቸው ጉዞ ጀመሩ። አፋርም ተጨፈጨፈ። ፋኖ አማራውና ሚሊሺያው በወሎ በኩል ረገፈ። ቆቦም፣ ላሊበላም ተያዘች ወልዲያም፣ ደሴም ኮምፖልቻም ወደቁ። ወያኔዎች ሸዋ ሮቢት ደረሱ። እንደገና ዶር ዐብይ የሸሚዛቸውን እጄጌ ስብስበው ለ15 ቀናት ወደ ውጊያ ገቡ። ህዝቡም ዘር ሀይማኖት ሳይለይ፣ “ተመልከት ዓላማህን፣ ተከተል አለቃህን!” በሚባለው ከአባቶቹ በወረሰው ጀግንነት መሪውን ተከትሎ ሆ ብሎ ተነሳ። የዐብይ ዝና በአገሪቱ እንደገና ገነነ። ዐብይ እንደቀድሞ መሪዎች፣ እንደአባቶቻቸው ጦር ሜዳ ገቡዋ! ውጭ ያለነውም ተጠናክረን የአውሮፓና የአሜርካ ከተሞችን ቀወጥናት። የምዕራባውያንም የውሸት ሚዲያ ተጋፈጥን። ከውስጥም ከውጭም ተረባረብን። ወያኔ በሚይስደንቅ ፍጥነት ቀኟ ኋላ ዙራ ፍርጥጣ በ15 ቀን ውስጥ ሬሳዋንም መሣሪያዋንም እያዝረከረከች፣ አላማጣን አልፋ ኮረም ደረሰች። የመከላከያ ሠራዊት ትግራይ ገብቶ ይጫርሳታል ብለን ስንጠብቅ ጦራችን ዋጃ ላይ እንዲቆም ተደረገና፣ ወያኔን ለሁለተኛ ጊዜ ለዕርቀሰላም ልመና ተገባ።

እንደመሰለኝ ከሆነ ይኸ ሁሉ ውሀ ቅዳ ውሀ መልስ፣ የኦሮሞ ብሔርተኞች፣ የትግራይን ብሔርተኞች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አከርካሪያቸውን መምታት፣ እንደሞት የሚፈርቱን አማራውን ያጠናክራል ብለው የፈሩ ይመስላል። ከላይ የትግሬ ጽንፈኞች አማራውንና አፋሩን ሲጨፈጭፉ፣ መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሠራዊት በወለጋና በሌሎች ቦታዎች የሚኖሩትን መጨፍጨፉን አልገታም ነበር። የሁላችንም አዕምሮ በሰሜኑ ጦርነት ላይ አትኩሮ ስለነበረ፣ እስከዛሬ ስንት አማራ በኦሮሚያ እንድተገደለና አንድተሰደደ ገና ቁጥሩን አላወቅንም። የኦሮሞው መንግሥት የድፍረቱ ድፍረት ስንት መስዋዕትነት ተከፍሎ በህይወት የተያዙትን ቆንጮ የሕወትሀት መሪዎች፣ እነስብሀት ነጋን ሲፈቱ፣ ያኔ ነበር ለኔ የበቁኝ።

ወያኔ ትንሽ እፎይታ ከወሰደች በኋላ፣ የተሰጣትን የዕርቀሰላም ዕድል ረግጣ 3ኛ ዙር ወረራ ጀመረች። የፈረደብትን ቆቦን በቀናት ውስጥ ብትይዝም፣ ወልዲያን መያዝ አቃታት። አማሮቹ፣ ከተወሰኑ መከላከያዎች ጋር ገትረው ያዟት። እንደበፊቱ መንገዱ አልጋ በአልጋ አልሆነላቸውም። መከላከያው ወያኔዎች ባላሰቡት መንገድ ከኋላ መታቸው። የትግራይ ከተሞች አንድ በአንድ እየወደቁ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መቀሌ ደጃፍ ደረሰ። ወያኔ አድኑኝ ብላ ወደ ጌቶቿ፣ ወደ አሜሪካና አውሮጳ ለቅሶ ገባች። የወያኔም ጦር ከቆቦና፣ ከዋጃ፣ ከአላማጣ ፈርጥጣ ወጣች። ወያኔም “የምን ዕርቅ” ስትል የነበረችው፣ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ እንቀበላለን ብላ አወጀት። ወያኔም ወደ ፕሪቶሪያም አሜሪካኖት መሪዎቿን ወስደው፣ አስታረቅን ብለው፣ መቀሌን ታደጓት። እንግዲህ ወያኔና ብልጽግና፣ እንደገና አሸሻ ገዳሜ ፍቅር ላይ ናቸው። በአማራ ግን፣ ፋኖውን መሣሪያ ለማስፈታት ማሳደዱና በጅምላ ማሠሩ ቀጥሏል። ስሞኑን የኦሮሞ ጽንፈኞች ቤተክርሲያናችንን ከውስጥ ሲነድሏት፣ እኔጌታቸው ረዳ የመጡት ዶ/ር ዐብይን እንኳን ድስ አለዎት ሊሉ ነው?

አሁን በዓይኔ መጣሽ!

የሰሞኑ፣ የኦሮሞ “ሆንዱምቱ ኬኛዎች”፣ ዓይን ያወጣ ድርጊት ፈጽመዋል። የማይነካውን ነክተዋል። በኦርቶዶክ ቤተክርስቲያን ላይ ያደረጉት፣ ጽንፍ የረገጠ ሕገ ወጥነት ዓይናውጣነትና፣ በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘረ ወንጀል ነው። የጠቅላይ ሚኒስቴሩ፣ አቋም የመንግሥታቸው እጅ በዚህ ወራዳ ሥራ መኖር ከሚናገሩትና የጽጥታ ክፍላቸው ከሚውስደው እርምጃ፣ ይታወቃል። ምናልባት መንግሥቱ ኃይለማሪያም ነባሩን ፓትርያርክ ገድሎ፣ የራሱን ፓትርያርክ እንደሾመ፣ መለስ ዜናዊ መንበር ላይ የነበሩትን እንዲሰደዱ ካደረግ በኋላ የእርሱን ፓትርያርክ እንደሾመ፣ እሳቸውም በተራቸው፣ የራሳቸውን ፓትርያርክ መሾም አምሯቸው ይሆን? አባ ሳዊሮስ ወይም አቶ አካለወልድን መደገፋቸው ያን አይመስልም? የማስፈራሪያ ንግግራቸው በጣም የኦርቶዶክስ ዕምነትን ተከታዮችን ያሳዘነ ነው። የሚግርም ነገር ነው የምንሰማው። በጦርነት ላይ እያለን፣ “የትርግራይ ኦርቶዶክስ ቤትክርስቲያንና የእስልምና ሀይምኖት ጽህፈት ቤቶች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተለይቻለሁ ስትል፣ ምንም አላላችሁም። ይኸ ኦሮሞ ጠሊታነት ነው” ለማለት ሞክረዋል። “እኛ እኮ፣ እንደ ደርግም ፓትርያርኩን አልገደልንም፣ ወይም እንደወያኔ አላሳደድንም፣ ምናለ ፓትርያርኩ እንዳሉ እነዚህ እራሳቸውን ከቀኖና ውጪ እራሳቸውን ፓትርያርክ አድርገው የሾሙትን ሳዊሮስና ጳጳሳችን በእርቅ አብራችሁ ጎን ለጎን አትሆኑም ዓይነት ነግግር አደረጉልን። መሠረታቸውም፣ ሁለት ፓትርያርክ በአንድ ጊዜ መንበር ላይ ነበሩ፣ ለማለት ዳድቷቸዋል። ያንን ለቤተክርስቲያኗ ልተውና፣ የዶክተር ዐብይ መንግሥት እጅ በመፈንቅለ ሲኖዱሱ አንዳለ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። ሁሉም ድርጊታቸው ያንን ነዋ የሚያመለክተው።

ስለነዚህ ሰዎች እስቲ ትንሽ እንበል። ስለ አባ ሳዊሮስ ብዙ የሚነገር ነገር ቢኖርም፣ አሉባልታን ትቼ፣ በአንድ የአሜሪካ ቤተክርስቲያን ውስጥ “ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ኦሮሚያ ውስጥ ተቀባይነትን የላትም” ሲሉ ሰምቼ አዝኜባቸዋለሁ። ስለዚህ ጸረ ኦርቶዶክስ እንደሆኑ ነው የሚሰማኝ። እንዲያው ትኩር ብዬ ሳያቸው፣ ምንም የፓትሪያርክነት ሞገስ የላቸውም። የሆኑ ጎረምሳ እኮ ናቸው። አንድ ጳጳስ ሲናገሩ፣ ሀገር ስብክታቸውን ትተው አዲስ አበባ ሲያውደለድሉ ነው የሚውሉት አሉ። አይ ጵጵስና! እንዲህ ተዋረዶ አረፈው። አዲስ አበባ ገዳም መሆኑ ነው?

ስለአባ ዜና ማርቆስ በተጨባጭ የማውቀ ነገር ስለሌላ ምንም ማለት አልችልም። ከዚህ በፊት አላውቃቸውም።

ከቆሙስነት ስለተሾሙት ጳጳሳትና ኤጵስ ቆፖሳት ብዙ ማለት ይቻላል። የሆኑ ጎረምሶች ናቸው። ከመሀላቸውም፣ በፍጹም የመንኩሴነት ማዕረግ ያልነበራቸው፣ እንዳሉበት መረጃ በገፍ እየደረሰን ነው። እግዚኦ መሀረነ ክርስቶስ። ሳይበቁ መመንኮስ፣ ሳይገባቸው መጰጰስም ይቻላል ለካ።

ሌላው ቆብ የጫኑ ነውረኛ ሰው፣ አባ ኤውስጣቲዎስ የተባሉት ግለሰብ ናቸው። ከ10 ዓመት በፊት የአባ ኢዎስጣቴዎስን አስነዋሪ ድርጊት ከሜሪካ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን (The Orthodox Church in America) በቅዱስ ቲኮን ሰሚናሪ (St Tikhon’ Seminary) በሚማሩበት ጊዜ ሁለት የሴት ጉደኞችን እያፈራረቁና፣ ከሊሎችም ጋር ፍትወት እንደሚፈጽሙ ተረጋግጦ እንደተባረሩ፣ እንዲሁም እኚህ ሰው፣ አስገድዶ የመድፈርን ያካተተ የወሲብ ቀበኛ (sexual predator) በመሆናቸው ሴቶች አካባቢ እንዳይደርሱ የሚያስጠነቅቅ ለአቡነ ዘካሪያስ፣ የኒው ዮርክ አገረ ስብከት የተጻፈ ደብዳቤ ደርሶኝ ነበር። ሲኖዶሱ እርምጃ ይወስዳል ብዬ ስጠብቅ ጭራሹኑ ብጹዕ ወቅዱስ ብሎ ሾመቻቸው። ሰሞኑን እኚሁ ሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ቤተክርሲያን ከውስጥ ከነደሏት ሶስት “መነኮሳት ነን” ባዮች አንዱ ሁነው ተገኙ።

ምስኪን የኦሮሞ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች እነኚህ በሞራል የዘቀጡ ሰዎች እንምራቸው ብለው በጉልበት ሲመጡባቸው ምን ይሰማችሁ ይሆን?



በመንግሥት የጸጥታ ጠባቂዎች አጃቢነት፣ ወለጋ ውስጥ፣ አንድ የቤተክርስቲያን ቁልፍ ሰብረው ገብተው በእንሊዝኛ ሲያስተምሩ በቪዲዮ አንዱን ጳጳስ ነኝ ባይ አይቼ፣ የወለጋ ምዕምናን እንግሊዚኛ ነው እንዴ የሚናገሩት ብዬ ጉድ አልኩ። በአረቢኛም እንዲሁ ሲያስተምሩ አየሁ። እንደጴንጤዎቹ በልሳን መናገራቸው ይሆን?

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማንም የካቢኔ አባል መሀላቸው እንዳይገባ ሲሉ ቀጭን ትዕዛዝ ሲያስተላፉ ሰማኋቸው። ይገርማል። ሕገወጦቹን ግን የጸጥታ ጠባቂዎቻቸው በሙሉ ጥበቃ እያጀቧቸው፣ ቤተክርስቲያን ሲያሰብሩ አይተናቸዋል። ጂማ ደብረ መዌዕ በድኃኔዓለም እና እንዲሁም የሻሻማኔው ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የኦሮሞ ብልጽግና “የጸጥታ ጠባቂዎች” ተብዬዎች ቁልፎቹን ሰብረው ቤተክርስቲያኖቹን ለሕገ ወጡ መፈንቅለ ሲኖዶስ ወንጀለኞች ሲአስረክቡ ምዕምኑ በዕንባ እየተራጨ ተመልክቷል። በሻሻማኔ የጸጥታ ጥበቃቸው ዛሬ ቤተክርስቲያናቸውን ለመጠበቅ ከወጡት የመንግሥት ስናይፐሮች ብዙ ምዕምናን በጭካኔ ገድለዋል። ደማቸውን ከብልጽግና እጅ እንጠይቃለን። በአርሲና በተለያዩ ቦታዎች ያሉትን የሕጋዊ ቤተክርስቲያኗ ተሿሚዎችን እያፈኑ ሲያስዷቸውና ሲያዋክቧቸው እያየን ነው። መንግሥት ጭሬም ልደታማሪያም መእምናን በጪስ አፍነው ተኩስ ከፍተውባቸዋል። አቡነ ያሬድ፣ ሊቀ ሕሩያን ታምራት ወልዴ፣ ሊቀ ልሳናት ቀሲስ ወንድወሠን ጥላሁን፣ መምህር ሰሎሞን ዘገየ፣ አቡነ እስጢፋኖስ፣ መጋቢ ጸጋዘአብ አዱኟ... በዛሬው ዕለት ደሞ ሻሻሻማኔ የመንግሥት ጸጥታ ኃይል ተወስደዋል። ምናልባት፣ ካቢኒያቸው  በጸረ ኦርቶዶክስ የተጠቀጠቅ ካልሆነ፣ በዝምታ ማለፉ ከወንጀለኞች ጋር መተባበር ነው። ሌላ የእርስ በርስ ጦርነት ጠብቁ። ዝም ብሎ የሚሞትላቸው የለም። መከልከያ ውስጥ ብዙ ዘመዶቻቸው የሚገደሉባቸው መኖራቸውን መርሳት ሞኝነት ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስን በዚህ መልኩ መናድ፣ ማለት ለኔ በግሌ በዓይኔ እንደመጡብኝ ነው የምቆጥረው። ቁጭ ብሎ ማየት ማንም አይችልም። ፕሮቴስታንቱም፣ እስላሙም፣ ነግ በኔ ብሎ ድምጹን እያሰማ ነው። ያንን ድምጽ ማፈን አይቻልም። እንደወያኔ ያንን ለማፈን መግደል ማንግላታት፣ የወያኔ ጽዋ ለመቀብል ሕዝቡን ማመቻችት ማለት ነው። በዓይናችን መጥታችኋል። ስትነቁርን ዝም አንላችሁም። ታረሙ!

በነገራችን ላይ፣ እነዚህ ቆብ የደፉት፣ ነውረኞች፣ ለኦሮሞ ብቻ አልነበረም፣ ጳጳስ ሾምን የሚሉት። ለጉራጌ ሶዶ ሀገርስብከት ቆሙስ አባ ወልደገብሬል ዮሐንስ የሚባሉትን አቡነ ጢሞቲዎስ ብለው ሹመውላቸዋል። ለካምባታ ሀገረስብከት ቆሙስ አባ ሚካኤል ገብረማርያም ይባሉ የነበሩትን ብጹእ አቡነ ኤልሳ ብለው ሹመውላቸዋል። ለካፋ ሀገረስብከት፣ ቆሙስ አባ ኃይለ እየሱስ መንግሥቱ የሚባሉትን አቡነ እዝራ ብለው ሹመውላቸዋል። ለሃዲያ ሀገረስብከት ቆሙስ አባ ጳውሎስ ከበደ ይባሉ የነበሩትን አቡነ ዳኒኤል ብለው ሹመውላቸዋል። ለዳውሮ ኮንታ ሀገር ስብከት ቆሙስ አባ አብርሀም መስቀሌ ይባሉ የነበሩትን አቡነ ኒቂዲሞስ ብለው ሹመውላቸዋል። ለጊዴዎ ገርጂ አማሮ ዞን ሀገረስብከት ቆሙስ አባ መርሀጽድቅ ኃይለማርያም የነበሩትን አቡነ ልብሲዮስ ብለው ሹመውላቸዋል። ለጎፋ በስኬቶ አገረ ስብከት ቆሙስ አባ ገብረማርያም ገብረመድኅን የተባሉትን ብጹዕ አቡነ ኡራኤል ብሎ ሹሞላቸዋል።

ይኸ በወጣ ሰዓታት ውስጥ ኦነግ፣ የማህበራዊ ደረ-ገጽን ፕሮፋየል (አርማ እንበለው) በዚህ መልኩ ቀይሮታል። ምን ችግር አለ። አባቱ ዳኛ፣ ልጁ ቀማኛ!



ማጠቃለያ

የማጠቃልለው ደሜ ከደማቸው ለተደባለቀው ለኦሮሞ አባቶችና እናቶች፣ እንዲሁም ወንድሞች እህቶች ነው። ጽንፈኞቹን የሠራችሁትን ነውር ነው አቁም በሏቸው። በናንተ ስም ወንጀል እየተሠራ ነው። አንድ ነገር ልበል። በአድዋ ጦርነት ጊዜ የኦሮሞ የጦር መሪዎች አኩሪ ገድል ፈጽመው፣ ጣሊያንን እንዳባረሩና እንዳዋረዱ ታሪክ የመሰክራል። ያንን ታሪክ የሚያረክስ አጥንታቸው ይወጋቸዋል። ከአሥራ ሁሉቱ ዋና ዋና የአድዋ ጦር መሪዎች ሰባቱ ዕውቀን ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲናግዴን ጨምሮ ኦሮሞዎች ነበሩ። ያንን አኩሪ ተጋድሎ ያየ ጣሊያን፣ ከ40 ዓመት በኋላ፣ ጦሩን በዘማናዊ መልክ አድራጅቶ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ አጥንቶ፣ ትልቅ ታክቲክና ስትራተጂ ነድፎ በ1928 ሊዘምትብን ሲናሳ፣ ከታሪክ እንዳነበብኩት፣ ኦሮሞዎችን በአማራው ላይ አስነስቶ በጎኑ ለማቆምና የክህደት ወንጀል በሰፊው እንደፈጽሙ  ማነሳሳት ነበር። ከትግራይ ተባባሪዎች አንዳንድ እንደ ኃይለሥላሴ ጉግሳና፣ የመልስ ዜናዊ አያት እንደባሻ አስረስ ያሉትን መመልመል ቢችልም ከኦሮሞ ግን አልቀናውም ማለት ይቻላል። ብዙ የኦሮሞ አርበኞች ጣሊያንን ዛፍ ያጣ ጉሬዛ አድርገውት ነበር። ከነዚህ የኔ ጀግና ደጃዝማች ገረሱ ዹኪ ነበሩ!

አይጎነጎንም፣ የፈረሱ ጭራ፣
ለሰንደቁ ታማኝ፣ ገረሱ አባ ቦራ።

ተብለው የተወደሱ! ደጃዝማች ገረሱ ኪ፣ አምስቷን ዓመት ጣሊያንን መግቢያ መውጫ ያሳጡት፣ ገድላቸው በወርቅ ቀለም ተጽፎ ከትውልድ ትውልድ ሲዘከር ይኖራል። አዲሱ የኦሮሞ ትውልድ፣ ያንን ገድል እንዳያቆሽሽ አባቶች ልጆቻችሁን ምከሯቸው!

ከሰላሌ፣ እነአቢቹ የሚመሩት፣ እስከመጨረሻዋ ሰዓት ድረስ ወጣቶችን አሰልፈው፣ ሲፋለሙት፣ ዓምስቷን አመት ጨርሰው፣ የአበሻ ጀብዱ ተብሎ በፈረንጆቹ ሳይቀር ተምስክሮላቸዋል። አዲሱ ትውልድ፣ የአቢቹ አጽም እንዳይወጋህ፣ ከክህደት እራስህን አርቅ። ጄኔራል ጃከማ ኬሎን ቅርብ ቀን ነው ያጣናቸው። በታሪካችን ግን ወጣትነታቸው የሰው ታላቅ የኦሮሞ ኢትዮጵያዊ አርበኛና የጦር ጄነራልን መካድ አይቻልም።

 የእነ ኮሎኔል አብዲሳ አጋማ ገድል መቼ ተውስቶ ያልቃል። የበረሀው ተኩላ ተብለው፣ በአውሮጳ ምድር እነማርሻል ቲቶን እየመሩ የኢትዮጵያን ጀግንነት አስመስክረዋል።

ከጥሩ ዘር አንዳንድ እንክርዳድ እንደማይጠፋ፣ ከኦሮሞ መሀል፣ አንድ ከሀዲ ብቻ እንዳገኙ ጣሊያኖቹ በሮም ወመዘክር ጽፈው አስቀምጠዋል። ጣሊያኖች ጂማ ሲገቡ፣ የተቀባላቸው፣ አባ ጆቢር ወይም አባ ጆቢራ የተባለ ባላባት ነበር። ታርኩን፣ ወልቃይቴው የታሪክ ተመራማሪ አቶ በሪሁን ከበደ፣ እንዲህ ሲሉ ጽፈው አስቀምጠዋል።

ጅማ ጣሊያን እንደገባ፣ የጅማ ባላባት አባ ጆቢራ አብዱላሂ፣ የአማራን አንድ አንገት ቆርጦ ለአቀረበ 30 የጠገራ ብር ይከፈለዋል ብሎ ስለአወጀ 30 የአማራ አንገት ተቆርጦ ቀርቦለታል።[v]

በኢዮጵያ ታሪክ፣ የኦሮሞን አንጸባራቂ ሚና፣ ተውስቶ አያልቅም። በየአንዳንዱ፣ ኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘሩትን ጥቃቶች ለመመክት፣ ከወለጋ፣ ከኢሉባቦር፣ ከባሌ፣ ከሐረር ለኢትዮጵያ ደማቸውን ያፈሰሱና አጥንታቸውን የከሰከሱ፣ ጀግኖች ሞልተውናል። በቅርቡ እንኳን፣ ሞፈርና ቀንበሩን ሰቅሎ፣ ከወለጋ ገስግሦ ሚሊሺያውን ተቀላቅሎ፣ ሶማሌ ላይ አኩሪ ድል ያስመዘገበውን የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳሊያ ተሸላሚ፣ አሊ በርኬን እናስታውሳለን። ያ ሁሉ በጦር ሜዳ ጀብዱ ነው። በኃይማኖታችንስ? በሀይማኖቻን መጠንቀቅ የሚኖርብን ትልቅ ግዝት አለብን። ግዝቱም ከታላቁ፣ ሰማዕት አባታችን ከአቡነ ጴጥሮስ ነው። አቡነ ጴጥሮስ ከመጀመሪያዎቹ አራቱ የኢትዮጵያ ጳጳሳት አንዱ ነበሩ። ሰማዕቱ አባታችን፣ ብጹዕ ወቀዱስ አቡነ ጴጥሮስ በ1885 ዓመት ምህረት በፊቼ ነበር የተወለዱት። ዓለማዊ ስማቸው ማጋርሳ በዻሳ ነበር።



ሕዝቡ የፋሺስት ጣሊያንን አገዛዝ እንዲቀብሉ እንዲስብኩና ከመሞት እንዲተርፉ ሲጠይቃቸው እኚህ አባታችን ወደ ህዝቡ ዙረው ፋሺሽቶች የአገራችንን አርበኞች ሽፍታ ቢሉ እውነት እንዳይመስላችሁ። ሽፍታ ማለት ያለአገሩ መጥቶ የሰውን አገር የሚወር ይህ በመካከላችሁ የሚገኘው አረመኔው የኢጣሊያ ፋሺሽት ነው! የኢትዮጵያ ሕዝብ ለርሱ እንዳይገዛ ውጉዝ ነው! የኢትዮጵያ መሬት እንዳትቀበለው የተገዘተች ትሁን!” ብለው ደረታቸውን ለጥይት ሰጥተው ተሰውተዋል። የሰማዕቱ የአቡነ ጴጥሮስ የሞቱላትን ቤትክርስትያንና ሀገርን ለሚክድ ትልቅ ውግዘት አለበት። በረከታቸው በላያችን ላይ ይደር።

ስለዚህ፣ የኦሮሞ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አባቶች፣ ሕዝባችሁን ከመሳሳት እንድትመክሩ እለምናለሁ። ሲኖዶሱ፣ ያደረገው ትክክል፣ ይመስለኛል። በአንደኛው ቆሮንጦስ፣ ምዕራፍ 5 ቁጥር 13 ላይ ባለው መሠረት “ክፉውን ከመካከላችኹ አውጡት።” እነዚህ ሲኖዶሱን ከውስጥ የነደሉት ሰዎች፣ ክፉ ሥራ ሠርተዋልና፣ በጊዜውም ንሰሀ ገብተው አልተመለሱምና፣ ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ መንገድ መፈንቅለ ሲኖዶስ አድርገዋልና፣ መወገዛቸውና መወገዳቸው ትክክል  ነው ብዬ እንደ አንድ ምዕምን አምንበታለሁ።

ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን።

“.., ንስሐም ካልገባህ መቅረዝህን ከስፍራው እውስድብሀለሁ::” ብሎ ይጨርሳል የዮሐንስ ራዕይ መዕራፍ 2 ቁጥር 5

 

 



[i] Abyssinia: The Powder Barrel, 1935

[ii] Savage Abyssinia, 1928

[iii] የሺመልስ አብዲሳ ቃል

[v][v][v][v][v] የአጼ ኃይለሥላሴ ታሪክ፣ በሪሁን ከበደ፣ አዲስ አበባ 1993 ገጽ 804