Thursday 1 January 2015

እውነትን ፈልጓት፤ ታገኟታላችሁም!

እውነትን ፈልጓት፤ ታገኟታላችሁም!

አሰፋ ምን ተስኖት

ክፍል አንድ



የተከበራችሁና የተወደዳችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ሆይ፤ እትብታችሁ ስለተቀበረባት የምትወዷት ሀገራችሁ ኢትዮጵያም ሆነ ስለ ሃይማኖታችሁና ስለ ቤተ ክርስስቲያናችሁ ስታስቡ ሁሌም አስተዋይ፤ አርቆ አሳቢ፤ ብልህና ንቁ ሁኑ እንጂ ባማሩ ቃላት በመሳብም ሆነ ልብሰ ተክህኖና ግርማ ሞገስን በማየት የተንኮልና የሃሰት ሰለባ እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ።
“የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ፤ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች፤ ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነብቢያት ተጠንቀቁ” ተብሏልና (የማቴ. ወ. ም. ፯ ቁጥር ፩፭)

በለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ሁሉም የሚያውቀው ነው፤ መንስኤው ማን እና ምንድን ነው ከተባለ ደግሞ እውነተኛው መልስ ሥጋዊ ጥቅምን በማስቀደም ለሥልጣን፤ ለንዋይና ለዝና ያደሩ ጥቂት ካህናት የፈጠሩት ችግር መሆኑ የተረጋገጠ ነው።

እነዚህ ችግር ፈጣሪ ጥቂት ካህናት ልብሰ ተክህኖውን ለብሰው፤ የጌታን መስቀል በመያዝ ካህን መስለው ለመታየት ይጥራሉ እንጂ አንዳችም ለካህን የተገባ ሥነ ምግባር የሌላቸው ፍሪሃ እግዚአብሔር የሚባል ነገር ጨርሶ የራቃቸው፤ በማንኛቸውም ስፍራና ቦታ ያለምንም ፍርሃትና ሰቀቀን በድፍረትና በጭካኔ የሚዋሹና የሚክዱ ናቸው።

ውሸታቸው እንደታወቀባቸው ሲረዱ ደግሞ ሃሰትና ክህደታቸውን ወደማያውቀው ህብረተሰብ ዘንድ በመሄድ ነገ ቅጥፈቴ ይታወቅብኛል የሚለው ሳያስፈራቸው የለየለትንና ዓይን ያወጣ ሃሰትን እውነት አስመስለው በሕዝብ ውስጥ በማሰራጨት በነሱ ሃጢአትና ችግር ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲጣላና እንዲፋጅ ሌት ተቀን ይደክማሉ።

ሕዝበ ክርስቲያኑም ነገሮችን አጣርቶ እውነቱን እንዳይረዳ የራሳቸው የሆነ የብረት አጥር በመሥራት ዋሽተውና ደልለው ከጎናቸው ያቆሙት ሕዝበ ክርስቲያን ወደ ሌላው ጎራ እንዳይሔድ አንዱ በሌላው ላይ ጥላቻን አብቅሎ በጠላትነት እንዲተያይ የሚችሉትን የተንኮል ሥራ ሁሉ ሳይታክቱ ያከናውናሉ።

ይህንን ከፈጸሙ በኋላ ራሳቸው የፈጠሩትን ችግር በምእናን መከፋፈልና መጠላላት የተነሳ አስመስለው በማቅረብ ራሳቸውን እንደ ጲላጦስ ከደሙ ንጹሕ ነኝ በማለት ያለ ሃፍረት ይለፍፋሉ።

መቸም የሚገርም ነው፤ ምእመኑን ጣቱን የሚጠባ ህጻን አደረጉት አሁንስ። ትላንት ሲዋሹና ሲያታልሉት ሳያውቅ በየዋህነት፤ አውቆም በይቅር ባይነት ባለፋቸው ዘለዓለም የውሸት ናዳ እየጫኑበት የሚገዙት መስሏቸዋል።

በቅርቡ በእነዚሁ የእግዚአብሔርን መኖር በረሱና የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ባረከሱ ጥቂት ካህናት ተዘጋጅቶ በፌስ ቡክ ላይ የተለጠፈ ጽሑፍ ሲታይ አሁንም ሌላ ሕዝብን የማታለሊያና የማደናገሪያ ሃሰትን በመንዛት ሕዝብን አሳስቶ አንዱን ክርስቲያን በሌላው ክርስቲያን ወገኑ ላይ በማስነሳት በተከፋፈለው ሕዝበ ክርስቲያን ተጠቅመው የጓጉለትን ስጋዊ ዓላማ ለማሳካት ከመጣር አለመቆጠባቸውን የሚመሰክር ነው።

ከቶ ሕዝበ ክርስቲያኑ እነሱ እንደሚያስቡትና ዝቅ አድርገው እንደሚያዩት በእነሱ ውሸትና ተንኮል እየተነዳ እውነትን አጥቷት ይኖር ይሆን? አይምሰላቸው ይህ በዚህ አይቀጥልም፤ እውነት ትዘገያለች እንጂ መምጣቷ መች ይቀራል። ደግሞስ መቸ እውነት በውሸት ተሸንፋ ሞታና ተቀብራ ታውቅና፤

ብትቀበርም ከመቃብር ትወጣለች። የጌታችን የመድሐኒታችን የእየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤም የሚያረጋግጥው ይህንኑ ነው።
ጽሑፉ “በለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ላለፉት 2 እና 3 ዓመታት እልባት ሳያገኝ “ምህመናትን” ለሁለት ከፍሎ የሚገኘው አለመግባባት ዛሬ ቤተ ክርስቲያኗ ደጃፍ ላይ ድንኳን ጥለው የሚገለገሉት “ምህመናን” ቤተ ክርስቲያኗን ላለፉት 20 እና 30 ዓመታት የተጠቅምንባት እኛ ምህመናን ቤተ ክርስቲያኗ እኛ ነን ሻይ፤ ቡና እንጀራ የመሳሰሉትን ሸጠን የገዛነው፤ እኛ ይህንን ስላደረግን ልናዝባት የሚገባን እኛ ነን፤ ሃገረ ስብከትም ሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ አያገባውም፤ የሚለው ሃሳብና ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየተገለገሉ ያሉት ምህመናን ደግሞ እያሉት ያሉት የምንተዳደረው በቅዱስ ሲኖዶስ የመበላይነትና በአገረ ስብከቱ ስር በመሆን ሲሆን ምንም እንኳን ለቤተ ክርስቲያኑ ግዢ እንጀራም ሆነ ሻይ ቡና ብንሸጥም፤ ያልችንን ገንዘብ ብንለግስም የቤተ ክርስቲያኑ ፈላጭ ቆራጭ መሆን አንችልም በማለታችው ነው....” እያለ ያትታል።

“አዕምሮአቸውም በጠፋባቸው፤ እውነትንም በተቀሙ እግዛብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነሲህ ካሉት ራቅ” ፩ኛ ጤሞቲ.፮፤፬-፮።

ከላይ የተጠቀሰው ጽሑፍ ከእነዚሁ እግዚአብሔርን የማይፈሩና ሕዝብን ከሚንቁ ጥቂት ካህናት የተሰራጨ ነጭ ውሸት ሲሆን ሕዝብ ያወቀው ፀሐይ የሞቀው መሠረታዊ ሃቅ ግን የችግሩ መንስዔና ምክንያት አዲስ በተረቀቀ የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ የአባ ግርማን በገንዘብ ላይ እንዳሻቸው የማዘዝ፤ ደምወዝ የመጨመር፤ ጉርሻ የመስጠትና ሳይተኩና ሳይለወጡ ለዘለዓለም ስልጣን ላይ እንዲቆዩ የሚያደርጋቸውን ማሻሻይ ረቂቅ አባ ግርማ ካሳደሟቸው ጥቂት ካህናት ጋር ሆነው በማቅረባቸው በዛ ምክንያት በተነሳ ውዝግብ ነው። በእርግጥ ከዛ በኋላ ለዚህ መሠረታዊ ችግር የተለያየ ሽፋን እየተሰጠው ሕዝብን ለማወናበድ ሲሞከር ተቆይቷል።

አባ ግርማ ሥልጣናቸው ከሚነካ ቤተ ክርስቲያን ብትፈራርስና ሕዝበ ክርስቲያኑ እርስ በእርሱ ቢጨራረስ እንደሚመርጡ ያላቸውን ቁርጠኝነትና ጭካኔ በተግባር አስመስክረዋል።
ከዓመት በፊት የተፈጸመውን የሩቁን ትተን፤ በቅርቡ በራሳቸው ደጋፊዎችና ተከታዮች መካከል የተነሳውን ውዝግብ ማጤን ያሻል። አቅሌሲያ በሚባለው ስብስብ አማካኝነት የአባ ግርማን ከአስተዳዳሪነት ሥፍራ ዞር የማድረግ ነገር ሲነሳ የአባ ግርማ ምላሽ ምን ነበር? ምንስ አደረጉ? ምንስ በማድረግ ላይ ናቸው? ይህንን ስልጣኔን አትንኩ ጸብ የሲኖዶስና የሃገረ ስብከት ጉዳይ ነው በማለት የሃሰት ሽፋን ሊሰጡት አይችሉም። አይኑን አፍጥጦ የመጣው አሁንም የእሳቸው ሥልጣን ጉዳይ በመሆኑ በድጋሜ እንደ ፌንጣ ሊያዘልላቸው ችሏል።

አንዱን ክርስቲያን በሌላው ወገኑ ክርስቲያን ላይ አነሳስቶ እርስ በእርሱ ለማቃቃርና ለማፋጀት በማሰብ አዳዲሶቹ መላዕክት የመሳሰሉ ወጣቶች፤ ተብለው በአባ ግርማ እና በመሪ ጌታ ዓለማየሁ የተሞካሹትን ወጣቶች ስብስብ መጠሪያ የሆነውን አቅሌሲያ “አቅለቢስ” በውስጡ ያሉትንም እንዳላወደሱና እንዳልካቡ “በሀጢአት ተወልደው በሃጢያት የኖሩ” በማለት ሃዘኔታ የሌለው እጅግ አፀያፊ ስድብን ያዘለ ጽሑፍ ያሰራጨባችውስ ማን ነበር? ሊንኩን በመጫን ጽሑፉን ያግኙ።

http://www.tigraionline.com/letter-of-petition-london-debrestion.pdf

ቀድመው ነገሩን የተረዱት የቤተ ክርስቲያኑ አባላት ገና ከጅምሩ ለአባ ግርማ ተከታዮች ለማስረዳት የሞከሩት ይህንኑ ሃቅ ነበር። መታወቅ ያለበት ነገር እነዚህ ዛሬ ወጣቶቹን በመላዕክት የተመሰላችሁ እያሉ የሚያሞካሿቸው ካህናት ትላንትና አዛውንቱንና ልዩ፤ ልዩ ሙያ ያላቸውን ምእመናንን መንፈስ ቅዱስ እየመራችሁ የምትሰሩ መላዕክትን የመሰላችሁ እያሉ ሲክቧቸውና ከፍ ከፍ ሲያደርጓቸው ነበር የኖሩት፤ በኋላ ግን የሥልጣንና የንዋይ ጉዳይ ሲመጣ ነው አናውቃችሁም ብለው በመካድ ይባስ ብለው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ እቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ እንዳትደርሱ በማለት በደብዳቤና በሴኩሪቲ ሊያባርሯቸው የሞከሩት።

አሁንም ወጣቶቹን መጠቀሚያ ካደረጉ በኋላ እነሆ የማትቀረዋ እውነት ከሃሰት ተለይታ ጎልታ መታየት ስትጀምር አናውቃችሁም ማለት ጀመሩ፤ ቀጥለውም ከቻሉ ቤተ ክርስቲያን እንዳትደርስ የሚል ማዘዣ ማውጣታቸው የማይቀር ነው ርህራሄ የላቸውምና፤
አባ ግርማ የሥልጣን መነካት ጉዳይ ከአቅሌሲያ ሲመጣባቸው ከለንደን ዘለው አዲስ አበባ በመሄድ የተለመደ ውሸትን በድፍረት እውነት አስመስሎ የመናገር ባህሪያቸው ተጠቅመው የሚሉትን ብለው በመመለስ እዚህ የሚንጫጩትን ጸጥ አድርጌአቸዋለሁ እያሉ በመፎከር ላይ ይገኛሉ። ድል አድራጊነታቸውንም ለማሳየት ሲሉ ተደርጎ በማይታወቅ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያኑ መዝጊያዎች ላይ ስማቸውንና ሥልጣናቸውን የሚገልጽ በቀለም ያሸበረቀ ማስታወቂያ አስለጥፈዋል።

አባ ግርማ ወደ አዲስ አበባ ባደረጉት ዘመቻ ተሳክቶላቸውም ይሁን በሌላ አይታወቅም በአማራጭነት ቀርበው የነበሩት አዲስ መጤው መነኩሴም ወደ አዲስ አበባ እንደሄዱ ሳይመለሱ የውሃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል ይባላል።

ሌላው በጽሑፉ ላይ ችግሩ ሁሉ የምእመናን፤ ሃጢአተኛና በደለኛውም ምእመን እንጂ ካህን በችግሩ ውስጥ ጨርሶ የሌለ ተደርጎ ተመልክቷል። እውነቱ ግን በተቃራኒው ነው፤ እነዚህ ሃሰተኛና ፈሪሃ እግዚአብሔር የራቃቸው ጥቂት ካህናት ችግሩን ባይፈጥሩትና ባያመጡት ምእመኑ እግዚአብሔርን ለማገልገል ሲሉ በሃቅ ከቆሙ ከጥቂት እውነተኛ ካህናት ጋር በመሆን ያላንዳች ችግር ፈጣሪውን እያመለከ ሃይማኖቱንና ቤተ ክርስቲያኑን በከፍተኛ ደረጃ ባሳደገና ባስፋፋ ነበር።

“አንተ ግብዝ፤ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፤ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ” (ማቴ. ፯፤ ፭)

ከዚህ በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያኑን እንጀራና ሻይ ቡና ሸጠን የገዛነው ነው.... በሚል በጽሑፉ ላይ የታተተው ምእመኑ ለሃይማኖቱን ለቤተ ክርስቲያኑ ሲል የጣረውንና የደከመውን ድካም ለማጣጣል ሲባል የተጠቀሰ የእብሪተኞች አገላለጽ እንደሆነ በግልጽ ይታያል።

እነ አባ ግርማ የካህናቱንና የምእመኑን ጥረትና ድካም ለማጣጣልና ለማርከስ ቢጥሩም ምእመኑ ሳይተርፈው ከራሱ ቀንሶ፤ ከልጆቹ አፍ ነጥቆ፤ የሚሰራው ከውስኗ ደምወዙ፤ በድጎማ የሚኖረውና ጡረተኛው ደግሞ ለህይወቱ ማኖሪያ ተብሎ ከሚሰጠው ቀንሶ የገንዘብ አስተዋጽኦ በማድረግ፤ ተረባርቧል። ሴት እናቶችና እህቶች፤ እንጀራና ዳቦ ጋግረው፤ በእሳት ተጠብሰው ወጥ ሰርተው፤ ሻይና ቡና አፍልተው፤ ተሸክሞ በማምጣት በበረዶ፤ በዝናብና በጸሐይ መከራ አይተው ሸጠው ፈንድ ሬዝ በማድረግ፤ ወንዶች አባቶችና ወንድሞች ጉልበታቸውን፤ እውቀታቸውንና ጊዜአቸውን ሰውተው የነጻ አገልግሎት በመስጠት ተረባርበው በእግዚአብሒር ተራዳኢነት በስደት ሃገር ቅድስት ማርያምን የቋሚ ርስት የህንፃ ቤተ ክርስቲያን ባለቤት በማድረግ ለትውልድ የሚተላለፍ ታሪክ መስራታቸው እነ አባ ግርማ ሊያጣጥሉት ቢሞክሩን በእግዚአብሔር ቀርቶ በሰውም ዓይን ሊታይና ሊዳሰስ የሚችል ሃቅ ነው።

ይህንን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈሉት ደግሞ በድንኳን ውስጥ የሚጸልዩት ብቻ አይደሉም፤ በቤተ ክርስቲያን ውስጥም አባ ግርማን ደግፈውም ይሁን እውነትን ማየት ተስኗቸው፤ ወይንም ደግሞ ቤተ ክርስቲያን እስከተከፈተ ድረስ ገብቼ ልጆቼን አቆርባለሁ፤ ክርስትና አስነሳለሁ በሚል የዋህነት በተንኮል በተከፈተ የቤተ ክርስቲያን በር ውስጥ ከሚገቡት ውስጥም ተመሳሳይ አስተዋጾ ያደረጉ እንደሚኖሩ ማንም ሊክደው አይችልም።

ነገር ግን እውስጥም የገቡት ይሁኑ እውጪ በድንኳን ውስጥ የሚጸልዩት ለሃይማኖታቸውና ለቤተ ክርስቲያናቸው፤ ሲሉ ቤተ ክርስቲያኗ የእግዚአብሔር ቤትና እግዚአብሔርን የማምለኪያ ቦታ እንድትሆን እንጂ የራሳቸው ሃብትና ንብረት በማድረግ ፈላጭ ቆራጭ ሊሆኑባት እንዳልሆነ ከአባ ግርማና መሰሎቻቸው በስተቀር ማንኛቸውም ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው ሊዘነጋው እንደማይችል እነ አባ ግርማ ማወቅ ይኖርባቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ ሕዝብ ክርስቲያን ሃብትና ጉልበቱን አስተባብሮ በእግዚአብሔር ተራዳኢነት የገዛው ህንፃ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ የመኖሪያ ቤት (ቪካሬጅ) የእግዚአብሔር ማደሪያ የእመቤታችን የቅድስት ማርያም ሃብትና ንብረት እንጂ አባ ግርማ ለፖሊስና ለካውንስል (This is my Property) እንዲሚሉት የሳቸው የግል ንብረት እንዲሆን በውጪ የሚጸልዩትም ሆኑ እውስጥ የገቡት ጨርሶ ሊቀበሉት የሚችሉት ጉዳይ አይደለም።

ትውልድን ለመተካት የህፃናት ት/ቤትና ጽህፈት ቤት እንዲሆን የተደረገውም የቪካሬጅ ህንፃ ለተመደበለት አገልግሎት እንጂ የአቡነ እንጦስ መኝታ ቤትና ሳሎን እንዲሆን የሚፈቅድ የለም።

ይህም በመሆኑ የእነ አባ ግርማን መከፋፈያ ዘይቤ እውስጥ ገብተው የሚገኙትም ቢሆኑ ሊቀበሉት እንደማይችሉ አጠራጣሪ አይሆንምና እንደው ከንቱ ውዳሴ ሆኖ ይቀራል እንጂ አባ ግርማ እንደሚያስቡት በዚህ ሕዝብን ሊከፋፍሉና እንደ ልማዳቸው ሊያበጣብጡበት እንደማይችሉ ከወዲሁ ሊረዱት ይገባል። ይቀጥላል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!