Saturday 28 May 2011

ግንቦት ሀያና ሀያ የሰቆቃ ዓመታት በኢትዮጵያ

ዘረኛውና ጨቋኙ የወያኔ አምባገነን ገዥ በታሪክ አጋጣሚ በለስ ቀንቶት አዲስ አባባን ከተቆጣጠረ፣ እንሆ ሀያ ዓይመታት ደፈነ። በነዚህ ሀያ

ዓመታት፣ ይኸ የማፊያ መሰል ቡድን፣ ኢትዮጵያን ሲገነጣጥላትና ሕዝቧን በዘር ከፋፍሎ ሲያምሳት፣ በሽህ የሚቆጠሩትን ዜጎቻችንን ያለርሕራሔ ሲጨፈጨፍና፣ ሲያስጨፌጨፍ፣ በመቶ ሺ የሞቆጠሩትን እስር ቤት አጎራቸው፣ በሚሊዮን የምንቆጠረውን ዘመድ አዝማድ፣ ቤት ንብረታችንን፣ ተወልደን ያደግንባትን ቄዬዎቻችን ትተን፣ አገር ጥለን እንድንሰደድ አደረገን። ያቺን አዲስ አበባን የተቆጣጠሩባትን ከይሲ ዕለት ወያኔና ግብረ አብሮቹ በከበሮ፣ በእምቢልታና በጭፈራ ለማክበር ሲዘጋጁ፣ ዘጠና ከመቶው ኢትዮጵያውያን ግን ዘረኝነትና ፈላጭ ቆራጭ የነገሠበትን ዕለት በሀዘን፣ በለቅሶ በዋይታና በቁጭት አስታውሰናት እንውላለን


ከታሪካዊ አስክፊ ተግባሮቹ መሀል፣ ከሽዕቢያ ጋር አብሮ፣ ተባብሮ ኢትዮጵያውን ወግቶ፣ አድምቶ ገንጥሎ ማስገንጠሉ፣ ምንጊዜም ቢሆን ከታሪክ ተወቃሽነት አያድነውም። ለዚህ እኵይ ዓላማ ተዋግቶ ሕይወት ከማጥፋቱ፣ ደም ከማፍሰሱ ባሻገር፣ በተባበሩት መንግሥታትና በአፍሪካ አንድነት ድርጅቶች ኮሪዶሮች ኮሮጆ ተሸከሞ ተገንጣይዋን የኢትዮጵያ አካል፣ ኤርትራን እንደ ነጻ አገር ዕወቁልኝ ብሎ የተሯሯጠው የክሕደት ወንጀል ምንጊዜም የማይፋቅለት በደም የተጻፈ በደል ነው። ወያኔ ምንጊዜም ባለሁለት ወደብ ባለቤት የነበረችውን ኢትዮጵያን ወደብ አልባ ያደረጋት ከሀዲ ገዢ መሆኑ ምንጊዜም ተመዝግቦ ለታሪክ ይተላለፍላታል። ይኸ ሁሉ አሳፋሪና አሳዛኝ ድርጊት በወያኔ መፈጸሙን ቢረዱ፣ ሕሊና ቢኖራቸው አሻቃባጮቹ አገልድመው የሚያዝኑበትና የሚያለቅሱበት፣ አንገት የሚደፉበት እንጂ ሊያከብሩት፣ ሊጨፍሩብት፣ ባልተነሱም ነበር። ወያኔ ያ ሁሉ ወንጀል ሳያንሰው፣ ከላይ ከትግራይ እስከታች ጋሞ ጎፋ ድርስ የወረደውን 1600 ኪሎ ሜትር ርዝመት እስከ 30 እና 50 ወደውስጥ የገባ ጥልቀት ያለውን፣ መሬት ለሱዳን በነጻ ማስረከቡ፣ በታሪክ ፊት የሚያስጠይቀው ወንጀል ነው። አሁን አሁን እንኳ፣ ኗሪውን ከቀዬው እየፈነቀለ ለውጭ ቱጃሮች የሚቸረችራቸው የእርሻ ለም መሬቶች ከዚህ በፊት በታሪካችን በማንም ርዕሰ ብሐሮች የልተፈጸመ አሳፋሪና አሳዛኝ ወንጀል ነው።
ወያኔ ሥልጣን ሲይዝ፣ ከፎከረባቸው አንዱ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀን ሶስቴ የሚበላበትን ሁኔት ፈጥሮ ከረሀብ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚገላገልበትን ባዶ ቃል ኪዳን ገብቶ ነበር። የሚናገረው አንድ ነገር፣ የሚሠራው ሌላ! መለስ ያኔ የሚያወራው ስለምግብ መስሎን ነበር። ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀን ሶስቴ አበሳውን ይበላል። ምግብማ ከየት ተገኝቶ! ረሀቡ፣ ጠኔው ከዛሬ ሀያ ዓመት ሁኔታ በሶስት ዕጥፍ ጨምሮ፣ ዛሬ እስከ 15 ሚሊዮን ሕዝብ ጦሙን የሚያድርባት አገር ስለሆነች በየጊዜው የተባበሩት መንግስታትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከሚያወጡት መግለጫ መረዳት ይቻላል። ዛሬማ፣ ነጻ ገበያ ብሎ የፎከረብን ነጻነት ተረስቶ የዘይትና የስኳር ዋጋ እስከመቆጣጠር ገብቷል። የሚላስ የሚቀመስ የጠፋበት አገር አስታቅፎናል።

ወያኔ ስልጣን እንደጨበጠ፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋትን እንደሚያመጣላት ቃል ገብቶ ነበር። እንኳን ሰላምና መረጋጋት በአገሪቱ ሊሰፍንና ሽታውም ዝር አላለባትም። እንዲያውም አገሪቱ ከዚያን ጊዜ ጅምሮ ወይ በእርስ-በርስ ዕልቂት፣ ወይ በጎረቤት አገር ጦርነቶች ውስጥ ጥልቅ ባይነት ትንጣለች። ከዚያች ሥልጣን ከቶቆጣጠረባት ዕለት ጀምሮ እነሆ እስከዛሬ ለአንዲት ቀን እንኳን አገሪቷ ከጦርነት አርፋ አታውቅም። የጎሳ ፖሊቲካው ሆን ተብሎ በሕዝባችን ላይ ተጭኖ፣ በሰላም አብሮ ለብዙ ዓመታት የኖረው ሕዝባችን ኦሮሞውና አማራ እንዲጨራረስ ተገፋፋ። በአርባ ጉጉ፣ በአሰላ፣ በወተር፣ በበደኖ የተከሰተው እልቂት የዚያ ውጤት ነው። በጉጂና በጌደዎ መሀል ሆን ተብሎ የተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ዕልቂት የዚያ ውጤት ነው። በሸከቾና በመዠንግር ብሔረሰቦች መሀል ተቀስቅሶ በመቶዎች የሚቆጠሩ መዠንግሮች: ሕጻናትና እርጉዝ ሴቶች ሳይቀሩ የተጨፈጨፉብት ሆኔታ ተመዝግቦ ተቀምጧል። እንዲሁ በወላይታና በሲዳማ መሀል የተፈጠረው አለመግባባት የዚያ ውጤት ነው። ኧረ ስንቱ ተወስቶ ያልቃል! ወያኔ በ1985 ዓመት ምሕረት ያለርህራሔ የጨፈጨፋቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ በ1990 በመንገድ ላይ የገደላቸው እነ አቶ አሰፋ ማሩ፣ ጉዲሳ እንሳ፣ ተስፋዬ ኩምሲሳ፣ ተረፈ ቁምቢ፣ በየጊዜው ሕይወታቸውን ያጡ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች፣ እነ ግዛቸው መንግሥቱ፣ ተስፋዬ ታደሰ፣ ወርቁ መኰንን፣ አባይ ኃይሉ፣ ኩምሳ ቡራዩ፣ በቀለ መኰንን ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው። ከ1990 ዓመተ ምሕረት እስከ 1993 የዘለቀው በሁለቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቶች በወያኔና በሻዕቢያ መሀል ተቀስቅሶ የ70 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት የቀጠፈው ጦርነት፣ ወያኔ ጦረኛ እንጂ የሰላም እርግብ አለመሆኑን ነው የሚያስረዳው። በዚያ ጦርነትም፣ ያ

ሁሉ መስዋዕት ተክፍሎ የተገኘውን ድል አልጄርስ ላይ የእጅ መስጠት ያህል ውል ተዋውሎ የዓለም መንግሥታት ያወቁላትን መሬታችንን ኢግላን ሳትቀር “አንጠይቅም” በማለት እንደተወላቸው ሲታውቅ በባድሜ ምክንያት እነሆ እስከዛሬ ሁለቱ ጦሮች እንደተፋጠጡ የጦርነት አታሞ እንደተመታ ነው። ወያኔ ጦሩን አሰልፎ ሶማሊያ ገብቶ በውርደት መውጣቱ የሚያሳፍር እንጂ የሚያስፎክር ባልሆነ። ለመሆኑ ጋምቤላ ውስጥ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ በዓለም አቀፍ የዘር ማጥፋት ድርጅት ተመዝግቦ መቀመጡ ምን መሆኑ ይመስላቸው ይሆን? እንግዲህ በቅርቡ በምርጫ 97 በግፍ የተጨፈጨፉት ወገኖቻችን ዕልቂት የሰላምና መረጋጋት ምልክት ነው ወይስ የብጥብጥ? ኧረ ለመሆኑ ኦጋዴን ውስጥ የሚንቀለቀለው የጦርነት እሳት የሰላም ምልክት መሆኑ ነው?

ወያኔ ዴሞክራሲን በአገሪቱ እንዳሰፈነ ይለፈልፋል። ድንቄም ዴሞክራሲ። እኛ አገር ወያኔ ያመጣው “ዴሞክራሲ”፣ ከለሎቹ፣ ጋዳፊ ሊቢያ ውስጥ ያመጣው፣ ሳዳም ሁሴን ኢራቅ ውስጥ ያሰፈነው “ዴሞክራሲ”፣ ሙጋቤ ዚምባብዌ ውስጥ ያመጣው “ዴሞክራሲ” እና የደቡብ አፍሪካ ውስጥ አፓርታይድ ለጥቁሮቹ ያመጣው “ዴሞክራሲ” ምስጋና ይንሳው ያሰኛል። ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ከአፓርታይድ የከፋ የፕሬስ ሕግ ተደንግጎ ከግድያ፣ ከእስራት የተረፉ ጋዜጠኞቿ እንዳሉ ወደ ስደት የተዳረጉባት አገር ውስጥ የምን ዴሞክራሲ ነው ለማውራት የሚቻለው? አሁን አሁንማ፣ መለስ ዜናዊ እርቃኑን መቅረቱን ተረድቶ፣ “ከዴሞክራሲ በፊት ልማት” ማለት ጀምሯል። የዴሞክራሲማ ነገር አይነሳ። ዲሞክራሲ ያበበላቸው፣ ምናልባት እንደፈለጉ እንዲገድሉ፣ እንደፈለጉ እንዲያስስሩ፣ እንደፈለጉ የሚሳደቡ የወያኔ ባለሥልጣናትና አጫፋሪዎቻቸው ብቻ መሆን አለባቸው። አለበለዚያማ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች ወገኖቻችን እስር ቤት በታጎሩባት አገራችን፣ አማሮች በዘር ተለይተው እንዲጠሉ የሚለፈፍባት አገር ምን ዓይነት ዲሞክራሲ አለ ተብሎ ሊወራ ነው?
ለመሆኑ፣ ዓለም ጉድ ያለው የ1997ቱ አሳፋሪ የምርጫ ማጭበረበር እንዳለ ሁኖ፣ በ2002ቱ ምርጫ ተቃዋሚውን ሁሉ አፋቸውን ለጉሞ 99.6% አሸነፍኩ ብሎ አንድ ገዢ ባወጀባት አገር የምን ሀያኛው ዴሞክራሲ የሰፈነበት ዓመት ማክበር ነው የሚወራው? ወያኔዎች ምን ዓይነት ዓይን አውጣ ፍጡሮች ቢሆኑ ነው፣ በብርሀን የሚታየውን ገሀድ ሊሸውዱን የሚሞክሩት?
የዘንድሮውን ግንቦት ሀያ፣ የምናስታውሰው እስከ አሁን ያልተገላገልነውን ሀያውን የስቃይና የሰቆቃ ዓመታትን ከል ለብሰን እያዘን ነው። ወያኔ አገሪቱን ወደ ከፋ ቀውስና የማንወጣው አዘቅት ይዟት እየነጎደ ነው። የዘንድሮውን ግንቦት ሀያ የምናስታውሰው ይኸንን ዘረኛ፣ ጨቋኝና አፋኝ ቡድን ለመገላገል በቁርጠኝነት ታጥቀን ለመታገል በአንድነት ለመነሳት ቃል እየገባን ነው። ግንቦት ሀያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ የሀዘን ዕለት ነው።

በተባበሩት ልጆቿ ክንድና በአምላክ ኃይል ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

Wednesday 18 May 2011

TORNOTO MEETING OF 14 OCTOBER 2011


Toronto.Meeting.Report.For.Media.Release -