Monday 19 June 2023

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶስ ዉሳኔ ቀሳውስቱንና ምእመናንን በተግዳሮት ላይ ጣለን!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶስ ዉሳኔ ቀሳውስቱንና ምእመናንን በተግዳሮት ላይ ጣለን!

ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ nigatuasteraye@gmail.com


        የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶሳችን ቀሳውስቱንና ምእመናንን ከተግዳሮት (ፈተና ) ላይ ጥሎናል፡፡  “ሀሉ አንተ እንበለ ሐሜት ከመ ኢይትዐቀፍ በእንቲአከ አሐዱሂ ወህዝባዊ ያስተሐምም በነፍሱ አንተሰ ጾርከ ጾረ ክቡደ . .. .. . ብከ ዐቢይ ኩነኔ ለእመ ተሐከይከ በእንቲአሁ”( አ ፍ 5፡120)፡፡ ማለትም፦ “በትዳር ውስጥ ያለ ህዝብ ለትዳሩ ለልጁ በሚያስበው ተጽእኖ ለጥፋት የሚመጣበትን መከራ አርቆ የማያት ትኩረት ሊያጥረው ይችላል፡፡ አንተ ግን በህዝብ ላይ የሚያከሰትለውን መከራ አስቀድመህ ማየት እንድትችል ከትዳር፣ ከልጅ ሸክም ተላቀሀል፡፡ ያንዣበበውን መከራ አስቀድመህ የማየት እጽፍ ድርብ ግዴታና ሐላፊነት አለብህ” የሚለው ቃል የሚያተኩረው በመነኮሳት፣ ይልቁንም መንኩሰው ወደ ጵጵስና በመጡ በሲኖዶሱ አባላት ላይ ነው፡፡

        በዚህ ቃልኪዳን ውስጥ የገቡት በሲኖዶሱ ውስጥ የተሰበሰቡት ከትዳር የተገለሉ፣ ለሚስት፣ ለልጅ የማይጨነቁ ለዕለት ጉርስ፣ ለዓመት ልብስና ለመጠልያ፣ ለሞተው ሥጋቸው የማያስቡ ናቸው፡፡ የዘወትር ትኩረታቸውና ጭንቀታቸው በፈቃደ እግዚአብሔር እና በህዝብ ሁለንተና ደህንነት ላይ ብቻ እንዲሆን ለዕለት ጉርሳቸው ለዓመት ልብሳቸው አያርሱም፣ አይቆፍሩም፣ አይነግዱም፡፡ ከምድራዊ ሀሳብ ተላቀው መንፈሳዊ ልዕለ አዕምሮ እርክን ላይ በመድረሳቸው “ይትረኀዋ አዕዛነ ልብ ወይትከሰታ አዕይንተ ልብ ዘውስት ወአኮ እለ ትኩላት ብአፍአ” (አ ቁ 14)፡፡ ይህም ማለት “በሸፍጠኛ አደንቋሪ አንደበተኛ ጩኸትና ጫጫታ አትታለሉ፤ መከራ እየመጣባችሁ ነው፤ ንቁ ራሳችሁን ለመከላከል ተዘጋጁ፤ እያሉ ለሚመሩት ሕዝባቸው መመሪያ የመስጠት ብቃት ያላቸው ብጹዐን ናቸው ተብሎ ይታመንባቸዋል፡፡”

        በመንግሥትነት የተሰለፉ ቡድኖች በአፈሰፊ ካድሬወቻቸው ድንፋታና የቃላት ጋጋት ህዝቡን ባቀረቡለት የተሳሳተ ሐሳብ እንዲወሰን እያደረጉ፤ በስህተት የወሰነውን ወደ ተግባር ለማምጣት ህዝብ ወስኗል እያሉ የሚያደርጉትን ሽንገላ የሲኖዶስ አባል በብጽዕና ብቃቱ የማክሸፍ ሀለፊነትና ግዴታ ነበረበት፡፡ ሲኖዱሱ የሐሰት ፕሮፓጋንዳውን በማጋለጥ፣ መግሥትን ማሸማቀቅና ማሳፈር፣ ሕዝቡን የማንቃት ግዴታ ነበረበት፡፡ ሲኖዶሱ “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋል የእግዚ ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” (1ኛ ዮሐ 2፡16) የሚለውን ቃል በመከተል የቅዱስ እስጢፋኖስንና የሐዋርያትን ትውፊታዊ ምሳሌነት መከተል ነበረበት፡፡ ግን ሲኖዶሱ ሠረዘው፡፡ የተሰረዘውን ሐዋርያዊ ምስሌ ከዚህ በታች እንመልከት፡፡

እስጢፋኖስ የተመረጠለት ሥራ ለእለታዊ ምግብ አከፋፋይነት ነበር፡፡ ከተሰለፈለት አገልጎሎት ይልቅ ባካባቢው በነጻ አውጭነት ስም እየተሰበሰቡ የሚተበትቡት ሸፍጥ በሕዝብ ላይ የሚያስከትለውን አደጋ አርቆ ተመለከተና ወደ ጉባኤያቸው ጥሶ ገባ፡፡ “እናንት አንገተ ደንዳኖች አረመኔወች ልባችሁና ጆሯችሁ ያልተገረዘ ሁልጊዜ እንደ አረማውያን ፖለቲከኞች አባቶቻችሁ ሊቃውንቱን የምትገሉ የሚገስጿችሁን የምታሳድዱ ንጹሐንን ለሞት አሳልፋችሁ የምትሰጡ” (የሐዋ 7፡51_53) ብሎ በሙሉ ልብና ድፍረት ፖለቲከኞችን ገሰጻቸው፡፡

        ሲኖዶሱ- የእስጢፋኖስን ምሳሌ በመከተል በጠ/ሚ ዓቢይና በአቶ ጌታቸው ረዳ ቡድኖች ወደተሰበሰቡበት ጉባዔያት ገብቶ “እናንት አንገተ ደንዳኖች የአረመኔ ልብ ያላችሁ፣ ጆሯችሁ ያልተገረዘ እናቶችንና ሕጻናቱን የምትገሉ፣የሚገስጿችሁን የምታሳድዱ፣ ንጹሐንን ለሞት አሳልፋችሁ የምትሰጡ፣ ባጠመቅናቸው ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ሥጋና ደም የኢትዮጵያን ገጸ ምድር እንዲጨቀይ ያደረጋችሁ፤ ከወገን ደም ጋራ የተቀላቀለውን ውሀ እንድጠጣ፤ ያደረጋችሁ፣ በኢትዮጵያ የሚነፍሰው ነፋስ ትቢያ የሆነውን የወገንን ሥጋ ባፍንጫችን እየጋታችሁ እንዲያስነጥሰን ያደረጋችሁ፤ የወገን አካል ከመሬት እየጠራረገ በላያችን ላይ በመበተን በቁማችን እንድንቀበር ያደረጋችሁ" በማለት በድፍረትና በቁጣ መናገር ነበረበት፡፡ አላደረውም፡፡ እንዲያውም ፊደል ቆጣሪ ሆኖ በፖለቲከኞች እግር ስር ተቀመጠ፡፡

        ከሲኖዶሱ አባላቱ አንዱ አቡነ ሳዊሮስ ርሰዎ ባይርቁን ኖሮ ቤተክርስቲያናችን ከዚህ ላይ አትወድቅም ነበር በማለት ሲኖዶሱ በጠቅላይ ሚ. ዐቢይ አመራር እንዲቀጥል ተማጸኑ፡፡ ዓቢይም ሳዊሮስ በከፈቱላቸው በር ወደ ሲኖዶሱ ሰምጠው በመግባት የመለመሏቸውን ካድሬወች በሐምሌው ስብሰባ እንዲሰየሙ ትእዛዝ ሰጡ፡፡ ሲኖዶሱም ትእዛዙን ተቀብሎ በትህትና (በውርደት) ተሰናበተ፡፡ ሐዋርያት በሕዝቡ ላይ ያንዣበበውን መቅሰፍት እንዳያዩና የሚወገድበትን ዘላቂ መፍትሄ እንዳይፈልጉ ፈሪሳውያን ከወቅታዊ ችግር የራቀና፤ ችግር ባልሆነው በግዝረት ላይ እንዲያተኮሩ በማድረግ ትኩረታችውን ለመጥለፍ በሞከሩ ጊዜ፤ መንፈስ ቅዱስ በቃኘው አዕምሯቸው ለወቅታዊ አደጋ አጋላጭ ያልሆነውን ግዝረትን ገለል አድርገው ሕዝቡን ለከፍተኛ አዳጋ ባጋለጡት በሚቀጠሉት ነገሮች ላይ ብቻ አተኮሩ፡፡

1ኛ፦ ለጣዖት የተሰዋ መብላት

2ኛ፦ ሳይባረክ ወድቆ የተገኘ የእንስሳ ሥጋ መብላት፤

3ኛ፦ደም መጠጣት

4ኛ፦ዝሙት

        ህዝቡን ለእልቂት በሚዳረጉት በነዚህ በአራቱ አደገኞች ላይ ተነጋግረው ወሰኑ፡፡ “በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ተመርተን የወቅቱን ችግር ከሚፈታ ውሳኔ በቀር ሌላ ጫና እንዳንጭንባችሁም ተጠነቀቅን፤ ሁላችን ባንድ ልብ ባንድ ሐሳብ የወሰነውን ወደናንተ እንዲያደርሱላችሁ ራሳቸውን ለእውነት ያሰለፉ ሰወች ከመካከላችን መረጥን ላክንላችሁ” (የሐው 15፡28)፡፡ ሐዋርያት ከውጭ የቀረበላቸውን ሐሳብ ወርውረው የመፍትሔውን ውሳኔ መወሰናቸው ብቻ ሳይሆን ውሳኔውን የሚያደርሱት ልዑካን ለተልእኳቸው ታማኞችና እስከሞት ድረስ የሚዘልቁ መሆናቸውን መረዳታቸው የሚያስገርም ምሳሌ ነው፡፡

        የዘመናችን ሲኖዶስ የሐዋርያትን ምሳሌ በመከተል፦ መንግሥት ከፋፋይ እቅዱን የሚያስፈጽሙለትን በጎሳ በቋኗና በክልል እንዲሾሙ መልምሎ ያቀረበለትን አጀንዳ ገሸሽ አርጎ፦

1ኛ፦የግድያውን እቅድ ዘርግቶ እርስ በርሱ ያዋጋው፡ ያገዳደለውና አሁንም በማገዳደል ላይ ያለው ባስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርብ

2ኛ፦እርስ በርስ በሚጋደለው ሕዝብ መካከል ገብቶ እኔን ገድላችሁ ተጋደሉ በማለት መገዳደሉን እንዲያቆም ማድረግ

3ኛ፦ለመከፋፈልና ለእርስ በርስ ግዳያ ምክንያት የሆነውን ሕግ ባስቸኳይ እንዲታረም ለማስደረግ ተጽእኖ መፍጠር ነበር፡፡ አላደረገውም፡፡

        የገደሉ ያስገደሉ ወንጀለኞች በሕዝብ ስም ራሳቸውን ለራሳቸው ይቅርታ እየጠቁ ራሳቸው ለራሳቸው ይቅርታ እየሰጡና ራሳቸውንም ይቅርታ ተቀባዮች በማድረግ እንደገና ከቀድሞው ይልቅ በተጠናከረ ጭካኔ ግድያውን ለመቀጠል ያለ ሐፍረት በድፍረት ራሳቸውን ሰይመው ሲቀርቡ ሲኖዶሱ ባለመቃወሙ ቀሳውስቱንና ምእመናኑ በተግዳሮት ላይ እንዲወድቁ አደርጓል፡፡ በተግዳሮት ላይ የወደቁት ቀሳውስት ቀድሞ የማየትና የመስማት ተላልፎም የመሞት ሐላፊነት የሲኖዶሱ ቢሆንም፡ ቀሳውስት በልጆቻቸው፣ በሚስቶቻቸው፣ በራሳቸው በሁለንተናቸው ከሲኖዶሱ ይልቅ ለህዝቡ የሚቀርቡ ሕዝባውያን ናቸው፡፡ በህዝቡ መካከል የሚካሄደውን የሚፈጸመውን ከጳጳሳት ይልቅ ቀድሞ የሚደርሰው ለቀሳውስቱ ነው፡፡ በህዝቡ ላይ የሚደርሰው ሞቱ፣ ስደቱ፣ ረሀቡ፣ ጽማቱ፣ እርዛቱ፣ ግርፋቱ በቀሳውስቱና በልጆቻቸውም ላይ እኩል ይደርሳል፡፡

        በህዝቡ ላይ እየመጣ ያለውን መከራ ቀሳውስቱ ለሲኖዶሱ የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ ሲኖዶሱ ቀሳውስቱን የማይሰማቸውና የማይቀበላቸው ከሆነ አትናቴወስ ”እስመ አኅለቁ ሥጋሆሙ በዝሙት” (አት ቁ 82) ሲል እንደተናገረው በሥጋዊ ፈቃድ መሸነፉን መንፈሳዊ ኃይሉ መገፈፉን በዝሙት በመብላትና በመጠጣት መደንዘዙን ቀሳውስት መረዳት አለባቸው፡፡

        የደነዘዙ ጳጳሳት ክምችት የሆነው ሲኖዶስ ለድንዛዜው ምክንያት “ኢታብአን ውስተ መንሱት” የሚለው ነው፡፡ ይህ ቃል በፈተና ስንገባ በሰላም ጊዜ የሚጸለይ ነው፡፡ ከፈተና ከተገባ በኋል እጅን አጣጥፎ በመቀመጥ “ኢታብአን ውስተ መንሱት” እያሉ መጸለይ ብቻ ተፈጥሮንና ፈጣሪውን መካድ ነው፡፡

        ጠቢቡ ሲራክ “እንዘ ይጻላሀው መፍቅደ ሀገሮሙ ወጽሎቶሙኒ ከመ ይጠበቡ በውስተ ኪኖሙ”(ሲራ 38፡34)፡፡ በሚለው ቃሉ ሀገራቸው ከሚሻው ውጭ እንጸልያለን የሚሉ ሰዎች ከመፋለሙ መስክ የማምለጫ ደካማ ዘዴ ነው ብሎ ይህን የመሰለ የላሸቀ ሐሳብ ያላቸውን ደካሞች እንዳጋለጣቸው ቀሳውስት መገንዘብ አለባቸው፡፡

        በዚህ ዓይነት እንቅልፍ ላይ ያሉት ጳጳሳት “ወሎሙኒ ኖሙ ረሲ አክናፈ መላእክት ይክድኖሙ ክበደ ንዋም ኢያስጥሞሙ ዘውእቱ አምሳሊሁ ለሞት” ( ዘሥሩ ቁ 86) እንዲል ከምንግሥት በሚያገኙት ድፍጋፍ ከህዝብ በሚዘርፉት ገንዘብ በሥጋ ፈቃዳቸው ተውጠዋል፡፡ በቁማቸው ሞተዋልና አንቃቸው ቀስቅሳቸው እያሉ በህዝብ ፊት የሚያነቡትን ቀሳውስት ተገንዝበው ሲኖዶሱ በተግዳሮት ውስጥ እንደጣላቸው መገንዘብና በገጽ ለሚያገለግሉት ሕዝብም መግለጽ አለባቸው፡፡

በተግዳሮት ላይ የወደቁት ምእመናን

        ኢትዮጵያ ተጠብቃ የኖረችው በዳዊት ደጋሚ አርበኞች እንጅ በሲኖዶስ አልነበረም፡፡ ምእመናን በዘመኑ ሲኖዶስ ድክመት ወደ ተግዳሮት የገቡት የቀደሙ አባቶቻቸውን ፈለግ በመርሳታቸው ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በፓትርያርክ በሚመራ ሲኖዶስ ከመመራቷ በፊት በእጨጌና በሊቃውንቷ በዳዊት ደጋሚ አርበኞቿ ትመራ በየነበረችበት ጊዜ የነበራትን ንቃትና ትጋት የውጭ ሰዎች ይመኙት ነበር፡፡

        ይህን አጉልተው ከጻፉት ውስጥ፦“The majlis, perhaps the first manifestation of modern Cptic life, was the embodiment of the educated youth’s desire to be accepted by modern Egyptian society. In time this modern waing of the Coptic community would develop its own Ethiopian ideas, quite different from those of the patriarchate, the Holy Synod, and the Coptic Church establishment” (The Cross and the Riverpage page 68) በማለት የነበረውን እያደነቁ ከብዙ ጸሐፊወች Haggai Erlich የተባሉት አንዱ ናቸው፡፡ 

        ጠቢቡ ሲራክ “እቀብ ተግሳጾሙ ለአዕሩግ እስመ እሙንቱሂ ተምሕሩ እም አበዊሆሙ”(ም 8፡9) ማለትም፦ እነሱም ማለትም አባቶቻችሁ ከቀደሙ አባቶቻቸው የተማሩት ነውና የአባቶቻችሁን ምክርና ተግሳጽ ጠብቁ፡፡ እያሉ ያብነቱ መምህራን አባቶቻችን በአጽንኦ ይንገሩን ክነበረው ምክራቸው ጋራ የ Erlich አባባል እጅግ የተቀራረበ ነው፡፡

        ቀሳውስቱም ሲኖዶሱም ድርሻቸውን ካልተወጡ በማለቅ ላይ ያለው ሕዝብ ራሱን ለመከላከል ዓይኑን ከጳጳሳቱ አንስቶ ቅዱስ አትናቴወስ እንዳለው በክርስቶስ ላይ ማተኮር አለበት፡፡ ቅዱስ አትናቴወስ “ኦ ኩልክሙ መሃይምናን እለ ትመስሉ ከዋክብተ ብሩሃነ ዕበይ ልክሙ ሶበ ትሬእይዎ ለእግዚእክሙ ይቀንት ወያንሶሱ ምስሌክሙ ወይሜጥወክሙ ዘዚአሁ ሀብታተ”(አ ት ቁ 99) ያለው በተመሳሳይ

ተግዳሮት ለወደቁት ምእመናን ነው፡፡ ይህም ማለት እናንት ሁላችሁ በጨለማው ዓለም እንደ ሰማይ ከዋክብት ደምቃችሁ የምትፈልቁ ምእመናን ሆይ እናንተን ለማዳን ከለሜዳ ታጥቆ በመስቀል ላይ የቆመውን ክርስቶስን ተመልከቱ፡፡

ይህ አባባል ክርስቶስ መስቀሉን በሥጋው ቢሸከመውም በመለኮቱ ውህደት ነው፡፡ ክርስቲያኖች ሸሽተው የማያመልጡ ተደብቀው የማያሳልፉት የሚመጣባቸውን መከራ የሚሸክመት ክርስቶስ “ዓለም እንዳሸንፍኩት እናንተም በጽኑእ እምነታችሁ በርቱ” ባለው ቃል ተደግፈው እንጅ ከቀቢጸ ተስፋ በራቀ ስሜት አይደለም፡፡ ሮጠው የማያመልጡት ሸሽተው የማያሳልፉት አንዣቦ የመጣ መከራ ሲገጥማቸው “ብሞትም በሕይወት ብኖርም በእግዚአብሄር እጅ ነኝ” ብለው እንዲገቡበት ይገደዳሉ፡፡ ቢሞቱም የማይቀረውን ሞት ነው፡፡ በህወት ቢኖሩም ድሉ የክርስቶስ ነው፡፡ ብለው በተጋድሎው ይገቡበታል፡፡

        ምእመናን አስቀድመው እንዲያዩ እንዲያስቡ እንዲከላከሉ እግዚአብሔር ያስታጠቃቸውን ትጥቅ በተስፋ ሳይጠቀሙ የሚሞቱትን ሞት “እግዚአብሔርሰ ኢገብረ ሞተ አላ ረሲአን ጸውዕዎ ወአርከ አምሰልዎ”(ጥ. ም 1፡18 ) ብሎ ገልጾታል፡፡ ማለትም ሸሽተው የማያመልጡትን በፍርሀትና በእምነት ጉድለት እየሸሹ መገደል ኃጢአት እንጅ ጽድቅ አይደለም፡፡ ምእመናን በሲኖዶሱና በቀሳውስቱ ቸልተኝነት የመጣባቸውን አረማዊ ገዳይ ለመከላከል ቆርጠው ከተሰለፉ፡ ዳዊት “ወአሰሰልኩ ጽዕለተ እምደቂቀ እስራኤል” እንዳለው ራሳቸውንና ቤተ ሰባቸውን አድነው ዘላለማዊ ውርደትን ከህዝባቸውና ከሀገራቸው እንዲያስወግዱ እግዚአብሔር ሊያግዛቸው የታመነ ነው፡

        ይቆየን