Tuesday 21 May 2013

አስታራቂዎቹ መጡ! ከአበባ አመዴ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን።

ወረት በሌለው ፍቅሩ ለዘላለም ሕይወት ለመረጠን ለክርስቶስ ኢየሱስ ውድ ቤተሰቦችና ለመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የቃል ኪዳን ልጆች እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!!

እንባችንን ካይኖቻችን የሚያብስ የሰማይና የምድር ንጉስ እሱ እንደ ወደደ እየመራ፤ መዋል ባለብን ቦታ እያዋለ፤ ማደር ባለብን ቦታ ሲያሳድረንየእድሜ ባለጠጋ ሲያደርገን ከማዬት የበለጠ ምን መልካም ነገር አለስለሆነም መንጋውን እየሰበሰበ፣ ቃሉን እየመገበ፣ ሰይጣንን እያሳፈረ፣ ልጆቹን እያከበረ እውነትም ልዩ ትንሣኤ ፤እውነትም ልዩ ሞገስ ሆነልን። በቸርነቱ አክብሮ ውስጣችንን በሀሤት አንደበታችንን በዕልልታ፤ በትንሣዔው ተሥፋ  ሞላን እንጂ፤ ህዝበ ክርስቲያኑማ በየቤቱ ሲያነባ ነው የከረመው።

አስታራቂዎቹ መጡ!

የፀሎተ ሐሙስ  ዕለት ወደ ከስዓት አካባቢ ስልኬ አቃጨለ። አማሞኝ ስለነበር ብዙም ለወሬ አልጓጓሁም። የሚጮኸውን ስልክ ዝም አልኩኝና፤መሬት  ላይ ደላድዬ በተኛሁበት እንደተሟሟቅሁ ወደ ግራ ጎኔ ተገላብጨ ተኛሁ። አሁንም ስልኩ ደግሞ አቃጨለ፤ ዝም። ለሶስተኛ ጊዜ ሲጮህ መተኛት እንደማልችል ገባኝ፤ አነሳሁት።

ሀሎ!  ምነው  በደህና ነው? ስልክ የማታነሽው!”
ሀይ ደህና አደርሽ? ብዬ ጥያቄውን በሰላምታ ከፈትኩ።
ያንቺስ በዛ ! በጠራራው ፀሐይ ገና  ደህና አደርሽ ትያለሽ?” አለችና ስንፍናዬን ጠቆም አረገችኝ። 
ምነው?  አንቺስ በደህና ነው? እንዲህ የምታሳድጂኝ? አልኩኝ እኔም አጸፋውን።
ምን ደህንነት አለ!  ይልቁንስ የሠላም ጥሪ እየተላለፈ ነው፤ አያምልጥሽ!አለችኝ።
የምን የሰላም ጥሪ?” መልሸ እኔም ጠየቅኳት፤
የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ የነበሩት የሰላም ጥሪ እያስተላለፉ ነው። ተመልከችው። በኋላ እናወራለንአለችና ስልኩን ድርግም አደረገችው።

የስልኩ በጆሮዬ ላይ መዘጋት አናደደኝ። ቅድም ደጋግማ ስትደውል ላለማንሳት እንደዛ የተግደረደርኩት ሴትዮ፤ አሁን ወሬውን እንደ ልቤ እስክጠግብ ሳታቅመኝ ተካልባ በመዝጋቷ ቅር ተሰኘሁ።

የተነገረኝን ወሬ የት እንደማገኘው ባላውቅ መልሸ ወደ እሷው መደወሌ አይቀሬ ነበር። ግን ይመስለኛል በደመ ነፍስም ቢሆን የሁሉም ሰው ጭንቀት ስለሆነ ወሬው የሚገኝበትን በዳሰሳም ቢሆን ማንም ፈልጎ እንደማያጣው አስባለሁ። ወዲያው አይ ፓደን  ከፈትኩና ወሬ ለማፈንፈን ሁለመናዬን እያቁነጠነጥኩ የጠረጠርኩትን ቤት ሁሉ ከፈት ዘጋ ከፈት ዘጋ እያደረኩ ፈላለኩኝና አገኘሁት። 

ቶሎ አልጀምር አለኝ፤ ኢጭ! የኔ ቤት ደሞ እንደ እኔው መስመሩም የደበዘዘ ነው።
ይኸ ኔት ወርክ ወደ እኔ ቤት ለመድረስ ምን ሆኖ እምደሚያዘግም አይገባኝም። ቤትሽ ኔት ወርክ የለውም እያለ የመጣው ሁሉ ይወቅሰኛል። እነዚህ የኔት ወርክ ባለቤቶች ለእኔ በአየር ሳይሆን በኤሊ እየጫኑ ነው ሁሉንም ነገር የሚልኩልኝ።
በግድ እየተጎተተ ብቅ አለ።


መጀመሪያ እንደማስታወቂያ በአየር ላይ እያማተቡ ሁለት ካህናት ብቅ ጥልቅ፤ ብቅ ጥልቅ እያሉ አለፍ አለፍ አሉ። ቀጠሉና አንድ በጣም ብጭጭ ብለው ከመንጣታቸው የተነሳ ፈረንጅ የመሰሉ ካህን በግዕዝኛ ሲያማትቡ፤ ድምጻቸው የማውቀው ሆኖ ፊታቸው ቢበጭጭብኝ ደንግጨ መነጽሬን ፍለጋ ተነሳሁ። እሳቸው ግን ማነብነባቸውን አላቋረጡም ነበር።

ተመልሸ መነጽሬን አይኔ ላይ ደነቀሬ አይፖዱን በአውራ ጣቴና በሌባ ጣቴ ጨምቅ አርጌ ይዠ፤ ብልጥጥ ሳደርገው የበለጠ ተናጋሪው ወደ እኔ እየቀረቡ መጡና በራሴው ላይ ያፈጠጡብኝ መሰለኝ።

እሳቸው አይናቸውን ከወዲያና ከወዲህ አዲስ ዔበረድ ድንጋይ እንደገባለት ባትሪ በላዬ ላይ እያንቦገቦጉ አንድ ጊዜ ወጋ አንድ ጊዜ ከኔ ላይ ደሞ ነቀል እያደረጉ አካባቢውን እያማተሩ፤ እኔም እሳቸው ላይ ፍጥጥ ብዬ ገትሬ ያዝኳቸው።

አይ!  ይኸ ቴክኖሎጂ አንዳንድ ጊዜስ ሰውን ጂል ያደርጋል ልበል?

ብቻ መገረም አይሉት መደንገጥ አንድም የተናገሩትን ቃል ከልቤ ሳልጥፈው፤ እንደዛ ምን ብጭጭ አድርጎ ፈረንጅ እንዳስመሰላቸው ግራ ተጋባሁ። በጸሎት ባምላካቸው ፊት ተደፍተው ከርመው የአምላኬ ጸጋ በሙላት ፈሶባቸው ይሆን? ብዬ ሳስብ ፤በደቂቃ ልቤ ወደ መጽሐፍ ቅዱሴ ተሰረቀ።

እንዲህም ሆነ ሙሴ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ሁለቱ የምስክር ጽላቶች በሙሴ እጅ ነበሩ። ሙሴም ከተራራው በወረደ ጊዜ፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለተነጋገረ የፊቱ ቁርበት እንዳንፀባረቀ አላወቀም ነበር።አሮንና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ሙሴን ባዩ ጊዜ፤ እነሆ የፊቱ ቁርበት አንጸባረቀ፤ ወደ እርሱም ይቀርቡ ዘንድ ፈሩ .ዘጽ.34 29-31

አዎ! የፈጣሪ ክብር በባሪያዎቹ ላይ ሲገለጥ፤ ከእግዚአብሔር ክብር የተነሳ፤ ባሪያዎቹን ማንም የኔ ቢጤ ደካማ በድፍረት ሊያፈጥባቸው ቀርቶ ቀና ብሎ ማዬትም እንደማይችል አምናለሁ።
የኔው ደግሞ ግራ የሚያጋባ ሆነብኝ። እሳቸው ይቁለጨለጫሉ እኔም አፍጥጨባቸዋለሁ።
ቃሉ በልቤ እየተመላለሰ ለማረጋገጥ ልቤ በጣም ቋመጠ። ከተሳሳትኩ ድፍት ብዬ በአምላኬ ፊት በድያለሁ ለማለት።

ግን ደግሞ ትክክል ባልሆነና ባልተረጋገጠ ነገር ንስሀ መግባት ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት ነውና ከዚህ ይልቅ ለማጣራት፤ መነጸሬን በደንብ ጥርግ አድርጌ፤ ፍጥጥ ብዬ ማዬቴን ቀጠልኩ።
የእሳቸው ንጣት ግን፤  የአባቴ ሙሴ አይነት ሆኖ በፍርሀት እንድንቀጠቀጥ አላረገኝም። ይልቁንም ነጭ ዱቄት የተቀቡ መሰለኝ።ተገረምኩ!  መቸም እንደ ዘመኑ የፊልም አክተሮች ሜክ አብ ያደርጋሉ ብዬ አልገምትም። ያውም መለኩሴ!። ማነውስ ደፋሩ የሳቸውን ፊት ሜካብ ሊያደርግ ቡርሹን አንከርፍፎ ወደ መስታወት እየጎተተ የሚወስዳቸው? እንጃ እኔስ እንጃ!  ግን ምን እንዲህ አነጣቸው? ለራሴው ያልተመለሰ ጥያቄ ሆነብኝ። ደሞስ ድሎት ነው ብሎ ለማሰብ ይኸ ሁሉ ህዝበ ክርስቲያን በየቤቱ በሀዘን እና በእንባ እየታጠበ ምን አይነት ድሎት ልበል? በመጠረሻ የተናገሩትን ነገር ልብ ብዬ አደመጥሁ።

ከተናገሩት ነገር በልቤ ውስጥ የተሰነቀረው ነገር ደግሞ ሁለት ጳጳሳት ከኢትዮጵያ ሊመጡ ነው። ቤተክርስቲያኑ ነገ ለስቅለት ይከፈታል፤ የሚለው ነገር ነበር።

አቤቱ ምህረትህን አሳዬን፤ አቤቱ መድሐኒትህንም ስጠን። እግዚአብሔር አምላክ የሚናገረውን እሰማለሁ፤ ሰላምን ለህዝቡና ለቅዱሳኑ ልባቸውንም ወደ እርሱ ለሚመልሱ ይናገራልና።መዝ. 84(85)7-8

እግዚአብሔር አምላክ የሚናገረውን እሰማለሁ፤ እያለ የሚናገረው ልበ አምላክ ዳዊት ነው። እግዚአብሔር ደግሞ ሰላምን ለህዝቡና ለቅዱሳኑ፤ ልባቸውንም ወደ እርሱ ለሚመልሱ ሁሉ ይናገራልና፤ ምን አልባት በነዚህ መጡ በተባሉ ጳጳሳቶች እግዚአብሔር መፍትሄ ልኮ ይሆን ብዬ ልቤ በጉጉት ጆሮየም ለሚመጣው መልካም እና ሰላማዊ ዜና ለመስማት እያለከለከ ሰነበተ።
መቸም ሕዝበ ክርስቲያኑ በድኑ በየቦታው ይንቀሳቀሳል እንጂ ነፍሱ በዚያው በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ተቆልፎበታል። አቤቱ አምላክ ሆይ እባክህ ነፍሳችን ከስጋችን ተመልሳ በሰላም እናመልክህ ዘንድ ይቅርታህ ፈጥና ታግኘን።

ጌታ እግዚአብሔር የተጠጉትን የማይጥል አምላክ ትንሳዔውን በክብር እንድናሳልፍ እረዳን።
ከትንሳዔ በኋላ አንድ ቪድዮ ክሊፕ ከጳጳሳቱ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ ተለቀቀ ሲባል ሰማሁና፤ እየተስገበገብኩ ስልኬን ሁሉ አጠፋፍቸ ለማዳመጥ ቁጭ አልኩኝ።

እንዳልኳችሁ የኔት ወርክ ጉዳይ ለኔ ያው ትግል ነው። ቢሆንም በትግስት ብዛት፦
Speech by His Holiness Abune Gebreal and His Holiness Abune Qostos. ይላል።
አቡነ ገብሬዔል  እንዲህ አሉ፦ቅዱስ አባታችን  ስድስተኛው ባትርያርክ አቡነ ማትያስ ልከውን ነው።መለያዬቱን በውይይት ለመፍታት።

ሌላው ቀርቶ በዚህ በአሜሪካን ሀገር እንኳን ተጀምሮ የነበረው ሶስት አራት ጊዜ ስብሰባ የተደረገበት የሲኖዶስና የሲኖዶስ አባላት ጉባዔ፤ ሁሉም የሲኖዶስ አባላት በዬ ነው የምለው፤ ሲኖዶስ አንድ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ አባላት ከኢትዮጵያም ሄዱ እዚያም ሄዱ፤ ሁሉም ያንድ ሲኖዶስ አባላት ናቸው።  ውይይት፤ አድርገው ነበር ለጊዜው እንቅፋት ቢገጥመውም ውይይቱ እንደሚቀጥል ተስፋ ነው የምናረገው። አንደየ ፤ሁለተየ ቢከሽፍም ይቀጥላል። ምክንያቱም መጽሐፉስባዕ ይወድቅ ጻድቅ፤ ወስባዕ ይትነስዓ፤/ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል ሰባት ጊዜ ይነሳል/ ይላልና፤ ብዙ ጊዜ ሙከራ ሙከራ ይባላልና ሙከራው ይቀጥላል ብዬ ነው የምገምተው። አባቶቻችን እና እኛ ተለያይተን መቅረት የለብንም።ይህ የሲኖዶሱ አባላት ድምጽ ነው። የሁሉም ድምጽ ነው። ሲኖዶስ አንድ ነው። ሲኖዶሱም አንድ ነው።
ምኑን ከምኑ ገጣጥሜ ለማዳመጥ ተቸገርኩኝ። ሊገባኝ አልችል አለኝ። ከዚህ በላይ ማዳመጥም ሆነ መልሸ እናንተን ማሰላቸቱ ጠቃሚ ስላልመሰለኝ ቀንጨብ አደረኩት።  ግን የአሜሪካው ውይይት ይቀጥላል ሲሉን ምን ለማለት ፈልገው ነው?

ከላይ ቤት ከታች ቤት ስትይ አገኝ አገኝ፤
ጅብ አህያ ለምዷል እኔ አንቺን አያርገኝ

ይላል ያገሬ ሰው! አንጀቱ ሲያር። እንዲህ በእግዚአብሔር ህዝብ ላይ ስታላግጡ ፈጣሪ ጽዋው የሞላ ቀን ምን ይውጣችሁ ይሆን? የእግዚአብሔር መንግስት መቸም በገንዘብ የሚገባበት እንዳልሆነ ከናንተ አይሰወርም።  ለመሆኑ እኛ በእናንተ ቤት ጣታችንን የምንጠባ ንፍጣሞች ነን ማለት ነው?
ደግሞስ እኛን ለማስታረቅ ከመጣችሁ የሲኖዶሱ ጉዳይ መጀመሪያ ምን በቀዳሚ አጀንዳነት አስነሳው? ምነው በሰው ስነ ልቡና ባትጫወቱ! የለንደን ደበረጽዮን የነበረባት/ያለባት/ ችግር የአስተዳደር ብልሽት ነው።  በተረፈ ስለ ሲኖዶሱ ግን  የሁሉም ድምጽ ነው ከተባለ፤ እኔም እንደ ቤተክርስቲያን አባልነቴ ስለሚመለከተኝ የሌለሁበትን ያልደገፍኩትን በግድ ተቀብለሻል ተብዬ መብቴ ሲደፈር ገረመኝ። እኔ ነዋሪነቴ በእንግሊዝ ሀገር ነው። ስለ ሰው መብት ማወቅ ብቻ ሳይሆን በተግባርም የሚተገበርልኝ ስለሆነ ማንንም በመብቴ ላይ እንዲያዝ ለሰከንድ እድል አልሰጠውም። ጳጳስም ቢሆን!! ግን አላከብርም ማለቴ አይደለም።

አቡነ ቀውስጦስ  እንዲህ አሉ፦በቅዱስ ሲኖዶሱ ታዘን ነው የመጣነው በፓትርያርኩ። የመጣንበት ምክንያት ለሁሉም ግልጽ ይመስለኛል። ደብረጽዮን ቤተክርስቲያን ተዘጋ፤ ምዕመናን እያዘኑ ነው። ምክንያቱን አናውቅም ተብለን ነው የመጣነው። አመጣጣችንም ለማቀራረብና ለማስታረቅ ነው።
ቤተክርስቲያኗ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሆና ሳለች ከኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለመለየት አንዳንድ ሰዎች ይጥራሉ።

ልብ አርጉልኝ! የጅብን ጥርስ በአጥንት ይፈሩታል እንዲሉ። እንግዲህ ከና ገጅምሩ የሚሉት ነገር ይሰቀጥጣል።

የሰዎችን ልብ በፍቅር እንጅ በቃላት ውርጅብኝ መስበር እንደሚያራርቅ እንደት ይህ ከእነሱ እንደተሰወረ አልገባ ያለኝ ጥያቄ ነው። 
  
አቡነ ቀውስጦስ ደገሙና እንዲህ አሉ፦ ተጠሪነቱ ለመንፈስ ቅዱስ የሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ አለ። ለቤተክርስቲያናችን ከእግዚአብሔር በታች። ሀይማኖት አለኝ የሚል ሁሉ ቤተክርስቲያንን አይዘጋም። ሀይማኖት አለኝ የሚል ሁሉ በቤተክርስቲያን ፀብ ንትርክ አይፈጥርም። ምንድን ነው ምክንያቱ የፖለቲካ ጉዳይ አለበት? ፖለቲካና ሀይማኖትስ ምን ግንኙነት አለው?
ካህናቱ እግዚአብሔር ቀርቧቸዋል። መጥተው ቃል ገብተዋል።እኛ ቤተከርስቲያናችን ያለ ሲኖዶስ ብቸኛ ሌላ መልክ እንድታወጣ አንፈልግም። የምትመራው በሲኖዶስ ነው። ፓትርያርክም አለን።በዚያ ነው ወደፊት ከዛሬ ጀምሮ’  የሚል ቃል ገብተዋልአሉ።

ልብ በሉ ካህናት እግዚአብሔር የቀረባቸው። ምዕመኑ ግን ርኩስ የሆነ። ደግሞም እንደ ጋሪ የሚጎተት። ሲፈልጉ የሚያባርሩት፤ ሲፈልጉ የሚያንጓጥጡት ፤ሲፈልጉ በብርድ ላይ ያለ ርህራሄ የሚያንከራትቱት የሜዳ አህያ ማንም የሚወግረው ደደብ አርገውት አረፉ።

አቡነ ቀውስጦስ  በመጨረሽም እንዲህ ሲሉ ተሰምቷል፦ አሁን በውጭ አሉ የሚባሉትን ! ቀጠሮ ይዘናል ለነገ። ምን አልባት እንደነሱ ጠይቀናቸው እምነቱ በሚያዘው በቀኖና ቤተክርስቲያን መሰረት እንጓዛለን ካሉ አስታርቀናቸው ወደ ሀገራችን እንመለሳለን።

ቀኖና በሚፈቅደው መሰረት ሂዱ ስንላቸው ሌላ ነገር ካመጡ፤ የኛ እንዳልሆኑ ነው የምናውቀው። ሲኖዶሱ ያለው ኢትዮጵያ ነው ከዚያ ሆኖ ይመራታል። የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን አንፈልጋትም። ሌላ ስም ሰጥተን እንመራታለን፤ቢሉ አይችሉም!!! አይችሉም። በጭራሽ!! አይችሉም። በዚህ መንገድ የሚመጡ ካሉ አይችሉም!! የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ናት። አዎ! ይኸንን ገንጥሎ ሌላ ስም እንሰጣለን የሚል ካለ ይኸ  የእምነቱ ተከታይ አይደለም ማለት ነው። ይኸ ደሞ ቤተክርስቲያኗን ተረክቦ እመራታለሁ ቢል ዘበት ነው!! በምንም አይነት። ሕግ አለ። ብለው እርፍ።

ካነጋገር ይፈረዳል፤ ካያያዝ ይቀደዳል። አሉ።

አሁን በእውነት እነዚህ ሰዎች ሊያስታርቁ ወይስ ሊያተናንቁ ነው የመጡት።
እግዚአብሔር በቁም ነገር ስለሚናገር፤ እውነተኛ አምላክ ስለሆነ እውነተኛ የሆኑ ሰዎችንም ስለሚፈልግ፤ ለሚናገረንም ቃል ዋጋ ሳንከፍል፤ ሳንታዘዝለት፤ እንዲሁ እንደ ተራ ነገር ሰምተነው የምንሄድበት እንዳልሆነ ስለሚገባኝ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ከእኔ የሚፈልገውን ነገር ለማወቅ ተስፋ አድርጌ፤  ስለ ማንም ሰው ለመስማት ሳይሆን ለራሴ ብቻ እንዲናገረኝ እና በመታዘዝም ለይቅርታም ሆነ ለንስሀ እራሴን አዘጋጅቸ ነበር፤  በብዙ ድካም ተጉዘው ከኢትዮጵያ ድረስ ለፍተው የመጡትን ጳጳሶች ለማዳመጥ በተከፈተ ጆሮና በማስተዋል ለመስማት የተዘጋጀሁት።

ከሁለቱም ጳጳሳት አንደበት አንድም የእግዚአብሐርን ቃል ጠቅሰውወንጌልን ወንጌል ለተጠማው ወገን ሳያሰሙ፤ እንደ ወንጌል አገልጋይነታቸው አደራቸውን /ስራቸውን/ሳይወጡ፤ ከእነሱ የማይጠበቅ ዛቻና ማስፈራራት፤ ካህናት እግዚአብሔር የቀረባቸው ፤ምዕመን ግን እንደ እርጉስ ተቆጥሮ፤ጭራሽ መኖራችንን እንኳን እርግጠኛ ባለመሆን እነዚህ በውጭ አሉ የሚባሉት ብለው ሲናገሩከመጡበት አላማ ጋር እንደሚጋጭ እንኳን እንደት አልተረዱም?።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን 450 ሺህ በላይ ካህናት አላት ብለው ሲናገሩ፤ እነዚህ ሁሉ ካህናት ለወንጌል አገልግሎት ያላቸው አመለካከት እንደዚህ ከሆነ፤ ለእግዚአብሔር ቤት ከጠቃሚነታቸው ይልቅ ሸክም ሆነው መቀመጣቸው የሚያሳዝን መስሎ ታዬኝ።
ዛሬ ወንጌል እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ በዓለም ዙሪያ በአራቱም አቅጣጫ እግዚአብሔር ህዝቡን ከተበተኑበት በቃሉ እየጠራ ያለበት ስዓት ነው።

ዛሬ በቤቱ የተቀመጡ አገልጋዮች ከፈጣሪ ክብር ይልቅ ለሥጋዊ ምኞት እያደሉ በልባቸው ቢክዱትም፤ እግዚአብሔር እራሱ፤ መጽሐፍ ቅዱስን/ ወንጌልን/ ለባሪያዎቹ ይገልጣል።
ቢሆንማ ቤተክርስቲያንም ሆነ ካህናት፤ የመኖራቸው ምንጭና ዋና ምክንያት የሚቆሙበትም መሰረታቸው፤ አለታቸውም፤ በዚህ በተበከለው ዓለም ውስጥ ካለው ትርኪ ምርኪ ነገር ሕዝቡን ለይተው እና በወንጌል ነፃ አድርገው፤ የጽድቅን ነገር እንድንለማመድ እና እንድንተነፍስ፤  የህይወት ባለቤት የሆነውን ጌጋችንን አና መድሐኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወታችን ዋልታና መሰረት አድርገን እንድንጨብጥ ባደረጉን ነበር።

እግዚአብሔር በቸርነቱ ባይጠብቀን እንደ እነሱ ቢሆንማ ስንቶቻችን አሰፍስፎ ወደሚጠብቀን የጠላት ወጥመድ ሮጠን በተመሰግንበት ነበር። ግን የማያንቀላፋ አምላክ ተግቶ እየጠበቀን እስካሁን አለን። የቸርነቱን እና የታላቅነቱን ጉዳይ በረከሰ አንደበቴ እንኳንስ እኔ ቅዱሳን መላዕክትም ገልጸው የሚጨርሱት አይመስለኝም። የፍጡራን ባለቤት እግዚአብሔር ከባሕርይውም ይሁን ከክብሩ፤ ወንጌላዊ የሆነ አምላክ ነው። የመጀመሪያው የወንጌል ሰባኪ ብዬ ሳስብ ማንም ሳይሆን እራሱ እግዚአብሔር አምላካችን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። በመጀመሪያ ወንጌል በማንም ሰው አንደበት አልተሰበከም። ምክንያቱም፦

በገላትያ፦38-9 መጽሐፍም፦እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያፀድቅ አስቀድሞ አይቶ፦ በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ።እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ።

ልብ በሉ! የመጀመሪያው የወንጌል ሰባኪ እግዚአብሔር እራሱ ነው። ወንጌልን የዘራ፤ የተናገረ፤  ሰዎችን ስለ ሐጢያታቸው የሚወቅስ፤  ሰለ በደላቸው የሚናገር፤ የሰዎችን እንደ ድንጋይ የጠጠረ ልብ በሕያው ቃሉ የሚያፈርስ፤ የሚያለዝብ ለንስሐ የሚያዘጋጅ፤ የሚያሰናዳ፤ ወንጌልን እንዲቀበሉ ቃሉን እንዲጠሙ ሰለ በደላቸው እንዲያነቡ የሚያደርግ እርሱ ራሱ ነው።

እግዚአብሔር ወልድም ይኽን የፍቅር ወንጌል በመለኮታዊ አሰራር ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ሆኖ ይዞ እንደመጣ፦ በዕብራ. 1.1-3 ላይ ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፦ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዘመናትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን። እርሱም የክብሩ መንጸባረቅ እና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ ኃጢያታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ።

አዎ! መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ ወንጌልን አስተማሪያችን፤ ከሐጢያት ከበደል እንድንርቅ የሚመክረን የሚገስጸን ነው። ታዲያ በእውነት ይህን የመለኮት አሰራር በእኛ ቤተክርስቲያን ቦታ ሰጥተነው ተቀባይነት አግኝቶ እየሰራ ይሆንየእግዚአብሔር ቃሉም ሆነ ቤቱ አይዘበትበትም።

The Vatican says the Scottish Cardinal who resigned as Archbishop after Admitting to Sexual Misconduct will leave Scotland for several Months of PRAYER AND ATONEMENT.

የራሴን ቤተክርስቲያን ጉዳይ እያሰላሰልኩ በመጻፍ ላይ እያለሁአንድ ጆሮዬ ይኽንን ዜና ስሰማ፤ የጀመርኩትን ቆም አድርጌ ዜናውን መከታተል ጀመርኩ። ልቤ በጣም ተመሰጠ። ሁሉ ኃጢያትን ሰርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጎሎአቸዋል። ይላል የእግዚአብሔር ቃል። በእርግጥ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ከኃጢያት የነጻ አይደለም። ልዩነቱ ግን ለራስ ክብር ሲባል የሰሩትን ኃጢያት በሚያንጸባርቅ ልብስ ጀቡኖ ይዞ ከተቀመጡበት ወንበር አልለቅም ብሎ እግዚአብሔርን እየደጋገሙ የመበደሉ ላይ ነው።

እነዚህ ሰዎች በእውነት እምነት የላቸውም ብለን ልንኮንናቸው እና እኛ የተገላቢጦሽ አማኞች ነን እያልን ልንኮፈስ ይገባን ይሆን? ይህ እና ይህንን የመሰለ ዜና በዚችው ባለንበት ሐገር እናያለን እንሰማለን ።እንኳንስ በሀይማኖት ደረጃ ያሉት ሰዎች ቀርተው፤ በፖለቲከኞች ደረጃ ያሉትም ቢሆኑ በጥፋተኝነት ተጠርጥረው ከተወቀሱ ቀድመው እራሳቸውን ከተከበሩበት ስራቸው በመልቀቅ ሕዝብን ባደባባይ ይቅርታ ይጠይቃሉ እራሳቸውን ለሕዝብ እና ለሀገር ሲሉ ያዋርዳሉ። የእኛ ዜጎች ግን እንኳን አይተን ልንማር፣ እና እራሳችንን ለሀገርና ለወገን ዝቅ ልናደርግ ቀርቶ እራሳችንን ከእግዚአብሔርም በላይ አድርገን ተንሰራፍተን እንገኛለን።ታዲያ ይህን የተጠናወተንን የትዕቢት በሽታ ለማላቀቅ ሲነገረን ካልሰማን ፤አይተን ካልተማርን፤ እንደ ቫይታሚን በኪኒን መልክ ማን ለኢትዮጵያኖች በሰራልን!!

አቤቱ አምላካችን ከሞተ የህሊና ሥጋ ስራ እንዳንተባበር እርዳን። ከተሰወረ ኃጢያት ያንፃን!! አሜን።

ከንደን ደ/ጽዮን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክርስቲያን
አበባ አመዴ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር።