ራስፑቲን: ደብረ-በጥብጥ ሐሳዊው መነኵሴ
በወንድሙ መኰንን፡ (ኢንግላንድ 11/03/2013)
ራስፑቲን በ19ኛው መጨረሻና በ20ኛው መጀመሪያ መቶ ክፍለ ዘመናት የኖረ፣ የውሸት ራሻዊ መንኵሴ ነበር። በጣም አስገራሚና አሳሳች የቀበሮ ባሕታዊ ነበር። የሱን የሕይወት ታሪክ መዳሰስና ማወቁ፣ በዘመናችን ዳግማዊ ራስፑቲኖች ካሉ ለየቶ ለመጠንቀቅ ይረዳናል። በጽሞና አንብቡልኝ።
የራስፑቲን ትውልድና የልጅነት ዘመን
ግሪጎሪ ኤፊሞቪች ራስፑቲን (Григорий Ефимович Распутин) በ22 January 1869 ከአንድ የጭሰኛ ገበሬ ቤተሰብ፣ ቱራ ወንዝ አጠገብ በምትገኘው ፖክሮቮስኮየ በምትባል መንደር፣ በምዕራብ ሳይቤሪያ፣ ራሽያ ውስጥ ተወለደ። ገና ከሕጻንነቱ ጀምሮ በጣም አስግራሚና በጥባጭ ልጅ ነበር። ሲያልቅስ፣ የሕጻን ለቅሶ ዓይነት አባቢ ድምጽ ሳይሆን፣ ሰቅጣጭ፣ አስደንጋጭና አስፈሪ ድምጽ ይወጣው ነበር። በዚህ ምክኒያት፣ አልቅሶ ጎረቤት እንዳይረብሽ አና ቤተሰቦቹን እንዳያስጨንቅ፣ የሚፈለገውን ሁሉ በጥንቃቄ ያላንዳች ማንገራገር ወላጆቹ ያደርጉለት ነበር። በዚህ ላይ በጣም አስፈሪ ዓይኖች ነበሩት። ተናዶ፣ ከብለል፣ ከብለል ካደረጋቸው፣ የእሳት ፍም ከመምሰል አልፈው፣ ጨረር አፍልቀው ነበልባል የሚተፉ ይምስሉ ነበር። ታዲያ ገና ዳዴ እንኳን ሳይል፣ በጉልበቱ፣ ወላጆቹን አስገድዶ የሚፈልገውን እያገኘ፣ሲቀማጠል ለማደግ የበቃ አመጸኛ ነበር። በእግሩ ቁሞ ድክ-ድክ ማለትማ ሲጀምር፣ ሥራው ሁሉ “አይወራ” ጉድ ሆነ። ለሎች እኩዮቹን ሕጻናት ወንዶች ሲመታና ሲያደማቸው፣ ሕጻናት ሴቶች ልጆችን ጸጉራቸውን እየጎተተ፣ ቀሚሳቸውን እየግለበ ያስለቅሳቸውና ያንጫጫቸው ነበር። እሱ ለጨዋታ ከወጣ፣ ከሱ ጋር በሰላም ሊጫወት የሚችል ሕጻን በሙሉ፣ የሱን የበላይነት ተቀብሎ ጀሌው ለመሆን የተዘጋጀ ብቻ መሆን አለበት። አለበለዚያ የአባ ጉልቤውን ክርን ይቀምሳል። ሲፈልግ በጀሌዎቹ ያስደበድባል፣ ካልሆነም እራሱ ይደቁሰዋል። እንዲህ እንዲህ እያለ ጎርቤት እየበጠበጠ ማደግ አይቅርምና፣ ከፍ ከፍ ማለት ጀመረ።
ወላጆቹ ጢሰኛ ገበሬዎች በመሆናቸው ከፍ እያለ ሲኸድ እንደሰፈሩ ልጆች ወላጆቹን ለመርዳት በፍጹም ፈቃደኛ አልነበረም። ወላጆቹም ልጃቸው በመሆኑ “እንደፈቀደ” እያሉ ስድ ለቀቁት። ታዲያ መንደር ለመንደር ሲያውደለድል ይውል ነበር። ሥራው ሁሉ የተንኮል እንጂ አንዳችም የሚረባ አልነበረም። የሚገርመው ታዲያ ‘እህ” ብሎ ለሚሰማው ተናግሮ የማሳመን ችሎታው ልዩ ነበር። ትምሕርት የሚባል ነገር አልቀመሰም። ይልቁንም ሴቶችን መልክፍ ሥራዬ ብሎ ስለተያያዘው፣ በአካባቢው በወሲባዊ ስሜት የሚመራ አለሌ ይሉት ነበር። በመሆኑ በሰፈሩ ግሪጎሪ ተብሎ በራሱ ስም ከመጥራት ይልቅ “ራስፑቲን” በማለት ሕዝቡ ይጠራው ነበር። ራስፑቲን ማለት ትርጉሙ፣ የስሜቱ ባሪያ (debauchery) ማለት ነው። ታዲያ ኮረዳ ሲያሽኮረምም ነበር የሚውለው። እንደሱ ብዙ አውደልዳይ ተከታዮችም ነበሩት። ሥራው ሁሉ የተንኰል ነበር። ሰዉነቱም ያለዕድሜው የገዘፈ ነበር። የፈረጠሙ ባቶችና ክንዶች ነበሩት። ወጣቱ ራስፑቲን በፍጥነት፣ አደጎ ተመነደገ። በግዙፉ ሰውነቱ በተጨማሪ፣ ጢሙንና ጸጉርን መላጨት ወይም መከርከም አቆመ። እራሱንም ከወጣት የሀማኖት አባቶች ጋር ገና ከጠዋቱ አመሳስሎ ቁጭ አለ።
የመንፈሳዊ ትምሕርት ቤት ተማሪ
እሱ ባደገበት ዘምን፣ ጊዜው የጦርነት ዘመን ነበርና፣ የራሻያ መንግሥት እንደራስፑቲን ያሉትን ሥራ-ፈት ወጣቶችን እየጠራረገ ለወታደርነት ያሰለጥን ነበር። ራስፑቲን አውደልድሎ እያምታታ መብላት እንጂ እንኩዋን ወታደርነትና ግብርናም እንክዋን አይወድም ነበር። በዚህ ምክኒያት የቀሳውስትን ቀሚስ እየለበሰ፤ ወደ ኦርቶዶክሳዊት በተክርስቲያን እያዘወተረ፣ ለቄሶቹ እየተላላከ፣ ሲያስፈልግም እንጨት እየፈለጠ፣ ዘኬውን ሆዱ እስኪወጠር እየበላ እዚያው መኖር ጀመረ። ዳሩ ግን፣ ቤተክርስቲያን ለመሳልም በየእሑዱ የሚመጡትን ምዕምናን ሴቶችን መልከፉን አልተውም። የምታንገራግር ሴት ካጋጠመችውም፣ ምንም ሳያፍር አፍ አውጥቶ፣ “ምነው አንቺ! ቀሚስ ብለብስ ሴት መሰልኩሽ እንዴ!” ማለት ይወድ ነበር። በየጊዜው ግን፣ ሥራውን ሰምተው እንዳያባርሩት ፈርቶ ወደ አባቶች እየቀረበ ያለበትን ድክመት እየተናዘዘ ከዚያ ክፉ የወሲብ ጥማት እንዲገላገል እንዲጸልዩለት ይማጠናቸው ነበር። ታዲያ እንደዚያ ሲያገልጋላቸው ያዩት አባቶች አዝነውለት ምናልባት ባለመማሩ ነው እነዚያን ስሕተቶች የሚሠራው ብለው አስበው በቨርኾቱርየ ገዳም (Verkhoturye Monastery) ውስጥ በሚገኘው “ሰሚናሪ” በተባለው የሀይማኖት ትምሕርት ቤት ገብቶ እንዲማር ሥፍራ አመቻቹለት።
በተወለደ በ18 ዓመቱ ተማሪ ለመሆን በቃ። የውትድርና ግዳጅም ቀረለት። የሚገርመው ታዲያ፣ ተምረው ሊሞነኵሱ ሰሚናሪ የገቡ ወጣቶት ተማሪዎች በራስፑቲን አነጋገር፣ በሁኔታው በመመሰጥ በአንድ ጊዜ ከበቡት። ሶስት ወራት ባልሞሉ የተማሪነቱ ጊዜያት ውስጥ ታዋቂ (popular) ለመሆን በቃ። ተከታዮቹ በዝናው እየተማረኩ እንደ አሸን ፈሉ። ወጣቶቹ መነኰሳት ከመምሕራናቸው ይበልጥ፣ ራስፑቲንን ማዳመጥ መረጡ። ከዓለም የመጣ ዓለማዊ ሰው ስለነበረ፡ በዓለም ስለሚገኙት ጣፋጭ ነገሮች እየነገራቸው ወጣት አዕምሮአቸውን ግብረ-ገብነት በጎዳላቸው የዚህ ዓለም ከንቱ ድርጊቶች ምኞት በከላቸው። ለያንዳንዱ ተማሪ ችግር፣ ራስፑቲን መፍትሄ እንደነበረው ታምኖ በሰፊው ተወራለት። ታዲያ ይኽቺን በአጭር ጊዜ የተገኘችውን ዝና፣ ታዋቂነትና ተወዳጅነት ተጥቅሞ ወጣት መነኰሳትን እያሳደመ ማሳመጽ ጀምረ። ወጣቶቹ መነኰሳት፣ ከዚያ በፊት ተሰምተው የማይታወቁትን ጥያቄዎች እያነሱ፣ አባቶችን ያፋጥጡ ጀመር። ጥያቄዎቻቸውም አንዳንዴ ግራ የሚያጋቡ ነበሩ። በራስፑቲን መሪነት “ምግብ ይሻሻልልን” በማለት፣ በሰላም ሳይሆን በረብሻ ጀመሩ። ራስፑቲን፣ ስለአባቶችም ብዙ ብዙ መጥፎ ነገሮች ለወጣቶቹ እየነገረ ማሳደምና ሰይጣናዊ ሥራዎችን ማድረግ የዕለት ተዕለት ተግብሩ አደረገው። መንፈሳዊ ትምሕርት ቤቱን ብጥብጥ አደረገ። አንዳንዴም መኖሪያችን ይሻሻል፣ ዘመዶቻችን እንዲጠይቁን ይፈቀድልን፣ እኛም ቤተሰቦቻችን ቤት እየሄድን ለወራት ሰንበትበት እያልን ጠይቀን እንመለስ የሚሉ ጥያቄዎችን እንዲደረድሩ አነሳሳቸው። አንዳንዴም ትምሕርቱ በዝቶብናልና ይቀነስልን እስከማለትም ደረሱ። ከዚያ በሁዋላማ፣ የገዳሙ አስተዳዳሪዎች እና ነባር መነኰሳት ምን መጣብን ብለው ነገሮችን መመርመር ጀምሩ። በፊት ተሰምቶ የማይታወቀውን አድማና ረብሻ በሰላሙ ቦታ እንዲፈጽሙ ወጣቶቹን መንፈሳውያን ማን እንዳሳሳተቸው ነቅተውበት ሶስተኛውን ወር እንደጨረሰ በጅምላ ተነስተው በመቆሚያቸው እያንቆራጠጡ፣ ከመንፈሳዊው ትምህርት ቤት አሽቀንጥረው አውጥተው ጣሉት።
አጅሬ ከመንፈሳዊ ትምሕርት ቤት ከተባረረ በኋላ ብዙ ቀናት ሳይፈጁበት፣ በአካባቢው በቁንጅናዋና በግብረ-ግብነቱዋ የታወቀችውን ወጣት ልጃገረድ፣ ፕሪስኮቪያ ፊዩድሮቭና (Proskovia Fyodorovna) በእጅዋና በእግርዋ ገብቶ ልብዋን ውልቅ አድርጎ፣ አላስቆም አላስቀምጥ ብሎ፣ አባብሎ፣ አግባብቶ አገባት። አከታትሎም ሶስት ልጆች (ሁለት ሰቶችና አንድ ወንድ) አስወልዶ አስታቀፋት። በአካባቢው ራስፑቲንን የሚያውቁ ሰዎች፣ “አሁን ይኸ መተተኛ ዕውነት አግብቶ አርፎ ሊኖር ነው?” እያሉ ጥያቄ ማቅረባቸው አልቀረም። የፈሩት ደረሰ። ፕሪስኮቪያ ሶስተኛውን ልጅዋን እንደወለደች፣ ራስፑቲን ሚስቱን፣ ልጆቹንና ቤቱን ጥሎ፣ የዓለም ልብሱን አውልቆ፣ የመነኮሳትን አክሴማ አጥልቆ፣ እሱ “መንፈሳዊ ጉዞ የሚለውን”፣ አገር ጥሎ ኮበለለ።
ከተማ መናኙ “መነኩሴ”
ጅብ የማያውቁት አገር ሂዶ ቆዳ አንጥፉልኝ ይላል አሉ የአገራችን ሰዎች ሲተረቱ። ራስፑቲን የፖክሮቭስኮየን (Pokrovskoye) መንደር ጥሎ ከቤቱ ከኮበለለ በሁዋላ፣ መነኩሴ ነኝ እያለ፣ በየደብሩ እያደረ፣ እግረ መንገዱን አንዳንድ ተጨማሪ ተንኮሎችን እየተማረ፣ እየጠነቆለ፣ የታመሙትን አድናለሁ እያለ፣ እያጭበረበረ፣ እጁን በሽተኞች ላይ እየጫነ፣ ጉዞውን ወደ ደቡብ አቀና። በዓመታት ውስጥ ድንበር ተሻግሮ፣ በኮንስታንቲኖፕል (ቱርክ – የዛሬዋ ኢስታንቡል) አድርጎ፣ አቴና (ግሪክ ደረሰ)። ቀንቶት፣ ከሳይበሪያ ጀምሮ፣ እስከ አቴና በመንገዱ ሁሉ፣ የነበሩት አቢያተ ክርስቲያናት በሙሉ የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች ስለነበሩ፣ በየደብሩ ጎራ እያለ፣ በመንፈሳዊ ጎዞ ላይ ያለ (piligrimage) መነኵሴ መሆኑን እየስረገጠ፣ የታመሙትን እየጎበኘና እጁን እየጫነ፣ ተንኰሎቹን ሁሉ እየሠራ ሳይነቃበት ማለፍ ቻለ። አቴና ከተማ ምን ሲሠራ እንደቆየ ባይታወቅም፣ ለብዙ ጊዜ ወደ ከተማዋ ሲገባና ሲወጣ እንደነበር፣ አንዳንድ ጽሑፎች ያስረዳሉ። ግሪክ አገር በዙ ዓመታት ሲኖር ቋንቋውንም ተምሮ መናገር ችሎበት ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር፣ ወደቅድስቲቱ ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ብቅ ማለት የቻለው።
ቅድስቲቱ ከተማ ከገባ በሁዋላ፣ መንኵሴ መስሎ በየደብሩ እየዋለ ያድር ነበር። በቅድስቲቱ ከተማ የነበሩ የጊዜው አቢያተ ክርስትያናት፣ “የበቁ” አባት የመጡ መስለዋቸው ተንከባከቡት። “አባ ራስፑቲን” እያሉም አከበሩት። አጅሬ ያቺን ዕድል ተጠቅሞ፣ ምንኵስናውን ሕጋዊ ሊያደርግ ምንም አልቀረውም ነበር። አንዳንድ አባቶችን አግባብቶ፣ የቆሙስነት ማዕረግ ሊቀበል ተዘጋጅቶ ነበር። በጊዜው የነበሩት በቅድስቲቱ ከተማ የራሺያ በተክርስቲያናት አስተዳዳሪ አቡን፣ እንደ ዛሬዎቹ በፖሊቲካ ተመርጠው የተጀበኑ
ሳይሆኑ በመንፈስ ቅዱስ የታነጹ ነበሩና፣ የሰውዬውን ተክለሰውነት አይተው፣ በመንፈስ ቅዱስ ተምርተውና ተመርኩዘው፣ “የለም
ልጄ! በጣም ወጣት ነህ! ገና ብዙ ይቀርሀል። ባይሆን ገዳመ ቆሮንቶስ ግባና አንድ አሥር ዓመት መንነህ በድንብ በቅተህ ና! ያኔ እናቆምስሀለን” ብለው ወሰኑበት። እንኳን ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ አሥር ዓመት መቀመጥና አሥር ቀናትም ለመቆየት ፈቃደኛ ያልነበረው ራስፑቲን፣ ከቅድስቲቱ ከተማ፤ ሰው ሳይሰማ ሹልክ ብሎ ጠፍቶ ግርግር ወደበዛባት ወደ አቴና ተመለሰ። አቴና ውስጥ፣ አንዳንድ ተጨማሪ ተንኰሎችን፣ የጥንቆላ ዘዴዎችን ከተማረ በኋላ፣ ባጋኛቸው ጥራዝ ነጠቅ ዕውቀቶችን አንግቦ፣ ወደ ራሺያ ለመመለስ ወሰነ። ከዚያም በመጣበት አኳኋን፣ በመጣበት መንገድ ወደ ኮንስታንቲኖፕል ተመለሰ።
ኮንስታንቲኖፕል ውስጥ የሚገኙትን ገዳማትና ካታኮምቦች ጎብኝቶ፣ የዕነተኛ መነኵሴዎችን አኗኗር በደንብ አጠና። ኮረጀ።
ከውጭ አገር፣ ወደ ራሺያ እናት አገር
ኮንስታንቲኖፕል ጥቂት ወራት ሲያውናብድ ከቆየ በሁዋላ ድንበር አቋርጦ፣ ወደኦዴሳ ከተማ ተሻገረ። ኦዴሳ፣ ጥቁር ባህር ላይ ያለች የዩክሬን የወደብ ከተማ ናት። ኦዴሳም ሰንበትበት ብሎ፣ ኪቭ ገባና ትንሽ አመታት እዚያው ሲያምታታ አሳለፈ። ኪቭ የዩክሬን ዋና ከተማ ናት። ከጥቂት ዓመታት በሁዋላ፣ ጎዞውን ወደ ሞስኮ ከተማ አቀና። ሞስኮ ከተማ ከገባ በሁዋላ፣ ክረምሊን ቤተመንግሥት ውስጥ ባለችው ቅዱስ ባሲል ቤተክርሲቲያን እየገባ ያስቀድስ ጀመር። ልቀድስ ብሎ ደፍሮ ባይገባም፣ ዳሩ ግን እንደ አንድ ታላቅ መነኵሴ ተከብሮ፣ እውስጥ ተቀምጦ፣ ለቡራኬ ብቻ ተነስቶ አንዳንድ ያጠናቸውን ነግሮችን ይል ነበር። በሆነ ተአምር፣ የሞስኮ ወይዛዝርት ታዲያ በዚህ በወሲብ ያበደ ሀሳዊ ምነኩሴ ፍቅር እፍ – ብን አሉ። ተራ በተራ ብቻ እየገቡ “መባረክ” ሆነ ውሎአቸው። ቀጠሮዋን ጠብቃ “አባን” የጎበኘች ሴት፣ በቃ የፈለገችው ሁሉ ይሟላላታል እየተባለ ዝናው ተናኘለት። ልጅ ያጣች ሚስት ከባል ተደብቃ “አባ” ጋ ገብታ ከወጣች፣በዓመቱ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ዱብ ታደርግ ገባች። ታዲያ ልጁ የባል ይሆን የራስፑቲን የታውቀ ነገር አልነበረም። ብቻ፣ የራስፑቲን ጻዲቅነትና የማዳን ተሰጥዖ በሞስኮ ከተማ እየገነነ መጣ። የሴቱ ሳያንስ ታላላቅና ሀብታም የተባሉ፣ ባለርስት፣ ባለኩባንያ የነበሩ ወንዶች ሁሉ፣ ለምክር፣ ለጥንቆላና ለመተት ራስፑቲን መኖሪያ ቤት ይጎርፉ ገቡ። የራሱ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሱም አተረጓጎም ነበረው። አዋቂ መሰለ። ብርድልብስ የሚጋፉት ሰቶች ሳይቅሩ፣ ጻዲቅ አለመሆኑን እንዳያዩ ዓይናቸው በፍቅር ተጋረደባቸው። ይኽ በዚህ እንደዳለ አንድ ችግር ፔትሮግራድ ከተማ አካባቢ እንደተከሰተ ተሰማ።
በጊዜው የራሺያን ኤምፓየር ይገዙ የነበሩት፣ ንጉሠ ነገሥት (ጻር ወይም ዛር) ዳግማዊ ኒኮላስ እና እቴጌ አሌክሳንድራ (Tsar Nicholas II and Tsarina Aleksandra ነበሩ። ንጉሡና ንግሥቲቱ አራት ሰቶች ልጆች ነበሯቸው። አልጋ ሊወርስ የሚችል ግን ወንድ መሆን ስለነበረበት ወንድ ለመውለድ ሁለቱም በትልቅ ጭንቀት ላይ ወደቁ። አምላክ ባርኮአቸው አምስተኛ ልጃቸውን ሲወልዱ ወንድ ልጅ ሁኖ ተገኘ። ስሙም አሌክሴይ ኒኮላየቪች (Aleksei Nikolayevich) ይባል ነበር። አልጋ ወራሽ አሌክሴይ በመወለዱ የተደሰቱት ወላጆች፣ ውሎ ሳያድር ክፉ ፈተና ገጠማቸው:: አልጋ ወራሹ ሕጻን ለሞት የሚያበቃ ሂሞፍሊያ (hemophilia) የተባለ በሽታ ነበረበት። ሂሞፊሊያ የያዘው ሰው፣ ሰውነቱን ትንኝ እንኳን ብትሸነቁረው አንዴ መድማት ከጀምረ፣ ደሙ ከውስጡ ፈስሦ እስኪያልቅ ድረስ አይቆምም። በቃ፣ ሰውነቱ ከተሸነቆረ፣ ከመሞት በስተቀር ለላ ምርጫ የለውም። ነገሩ የአሌክሴይን ወላጆቹ ስላስደነገጣቸው ነጉሠ ነገሥቱና ንግሥቲቱ፣ ያላማከሩት ሀኪምና፣ ያላዩት ጠንቅዋይ አልነበረም። በራሺይ አሉ የሚባሉ፣ ስር ማሽ ቅጠል በጣሽ የሆኑ “አዋቂ” መተተኞች ሁሉ እየተጋበዙ መጡ። አንድም ሰው አሌክሴይን ማዳን አልቻለም። አንድ ጊዜ ታዲያ አካሉ ትንሽ ተሸንቁሮ የመዳን ተስፋው ተሙዋጥቶ፣ አባትና እናት እጆቹን ይዘው ተስፋ ቆርጠው ሞቱን ይጠባበቁ ነበር። ታዲያ ይኽች ዜና ለምን ራስፑቲን ጆሮ ጥልቅ አትል መሰላችሁ! ይኽችን አጋጣሚ ለመጠቀም፣ ግሪጎሪ ራስፑቲን ሆዬ ብድግ ብሎ ወደ ፔትሮግራድ ጉዞውን አመራ።
ፔትሮግራድ ወይም ፒተርስበርግ (በኮሙኒዝም ጊዜ ለኒንግራድ ተብላ የነበረችው) የታልቁ ነጉሠ ነገሥት ጴጥሮስ (Peter The Great - Пётр Вели́кий) መናገሻ ከተማ ናት። ታልቁ ጴጥሮስ ነገረ ሥራው ሁሉ የኛኑ ተዎድሮስ ይመስላል። ይኸ ታልቁ ጴጥሮስ ማለት፣ ኢትዮጵያዊው ልዑል፣ አብርሀም ሀኒባል[i]፣ ገና በሕጻንነቱ በቱርኮች ተማርኮ፣ የተሸጠለት ገናናው የራሽያ ንጉሠ ነገሥት ነበር። ታዲያ ይኸ ታላቅ ነጉሥ፣ (የጻር ኒኮላስ አያት መሆኑ ነው) ልዑል አብርሃምን ሲያየው ወደደው። እንደባሪያ ሳይሆን፣ እንደልጁ አድርጎ አሳደገው። ስሙንም አብርሀም ሀኒባል ፔትሮቪች አለው። ፔትሮቪች ማለት የጴትሮስ ልጅ ማለት ነው። አብርሀም፣ ከልዑላን መሀል እንደ አንዱ ሁኖ አደገ። ፈረንሳይም ድረስ ሂዶ እንዲማር ተከፍሎለት ትምሕርቱን አጠናቀቀ። ሲሚለስም፣ ስመጥሩ የራሺያ ጦር ጀኔራል ሆነ። ከታላላቅ ባላባቶች መሀል፣ የአንዱ ልጅ ተዳረችለት። የታላቁን የራሺያ ገጣሚን፣ የአለክሳንደር ፑሽክንን እናት ወለደ። እንግዲህ፣ ራስፑቲን ሞስኮ ነገር ሲያማስል ነበር፣ ፑሽክን በሽጉጥ ተገዳድሮ በሰው እጅ የተገደለው።
ወደራስፑቲን ታሪክ እነመለስ። አንድ ጠዋት ግርግር አለክሳንደር ቤተመንግስቱ በር ላይ ተነሳ። ጫጫታው በጣም በዛና ወላጆቹ የአሌክሴይን ቀኝና ግራ እጁን በየቡኩላቸው ይዘው ነብሱ እስኪትወጣ ሊሰናበቱ ሲጠባበቁ በነበሩበት ክፍል ድረስ ተሰማ። ጫጫታው አልቆም ሲል፣ እቴጌ አሌክሳንድራ ተረበሸችና ወደመስኮቱ ሂዳ መግቢያው ላይ የሚካሄደውን ትርምስ አየች። ብዙ ወታደሮች ብቻ ሲተራመሱ ነበር የታያት። ነገሩ ምን እንደሆነ እንዲያጣራ ከታማኝ ክብር ዘበኞቻቸው አንዱን ላከች። ክቡር ዘበኛው በር ድርሶ ዜናውን ይዞ ተመለሰ። “ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም። ብቻ አንድ ፊየል-ፊየል የሚሸት ወጠምሻ መነኩሴ ወደ ውስጥ ገብቼ አልክሴይን ካላየሁ ብሎ ነው ከወታዶርቹ ጋር ግብ ግብ የፈጠረው። እንዳይገድሉት፣ መነኩሴ ሆነባቸው። እንዳይተውት ሀይለኛ በመሆኑ፣ ሰባት ወታደሮች ታግለው እንኳን ሊጥሉት አልቻሉም፤” አላት። ነግስቲቱ አሰብ አሰብ አረገችና “ተውት፣ አስገቡት” የሚል ትዕዛዝ አስተላለፈች። ወታደሮቹ እያጀቡት፣ ወደ አሌክሴይ መኝታ ክፍል አመጡት። ራስፑቲን፣ ንጉሡንም፣ ንግስቲቱንም ዝግት አድርጎ በቀጥታ ወደ ሕጻኑ ሄደና እጁን ያዘው። ልክ ጌታ እየሱስ ክርስቶስ የሞተችውን ልጅ እጅ ይዞ “ጣሊታ ቁሚ” (“Talitha, koum!” - טליתא, קום!) ብሎ እንዳስነሳት፣ ራስፑቲንም የአሌክሴይን እጅ ይዞ በሆነ እንግዳ ቋንቋ መናገር ሲጀምር፣ አሌክሴይ ዓይኑን ከፈተ። በሚያስገርም ሁኔታም ተነስቶ አልጋው ላይ ቁጭ አለ። ከዚያ እጁን ዘርግቶ ራስፑቲን አንገት ላይ ተጠመጠመ። ንግሥቲቱና ነጉሡ የሆነውን ባዩ ጊዜ፣ ራስፑቲን ጻዲቅ የእግዚአብሐር መልአክ መስሎአቸው ሩጠው እግሩ ሥር ተነጠፉ። በቃ! አበቃ! የራስፑቲን የዘላንነት ሕይወት ከዝያች ቀን ጀምሮ አከተመ። የቤተመንግስት ፈላጭ ቆራጭ የመሆን ዕድል በሩ ወለል ብሎ ተከፈተለት።
ራስፑቲን አሌክሴይን ከሂሞፊሊያ በሽታ ከዳነባት ከዚያች ሰዓት ጀምሮ በታላቁ ጴጥሮስ ቤተመንግሥት ውስጥ እንደፈለገው ፈነጨበት። የንጉሡም የግል አማካሪ ሁኖ ተሾመ። የፈለገውን አስሾመ። የፈለገውን አስሻረ። የፈለገውን አስገደለ። የፈለገውን አሳሰረ። የፈለገውን አሰደደ። ንጉሡ፣ አብረውት ስንት ውጊያ ላይ ያሳለፉትን፣ አንገታቸውን ለሱ ሊሰጡ የማሉትን፣አዋቂ አማካሪዎቹን በሙሉ አባርሮ፣ የራስፑቲንን ምክር ብቻ ይሰማ ጀመር። ይኸ እንግዲህ የመጀመሪያው የታልቁ ጴጥሮስን፣ የሮማኖቭ ሥረወ መንግሥት (dynasty) ከሥሩ መንግሎ ለመጣል የውድቀት ምክኒያት ነበር። ራስፑቲን አንዳች ደግ ነገር ንጉሡን አያማክርም ነበር። “ንግሥናህ የመጣው ከእግዚአብሐር ስለሆነ አንተ ፈላጭ ቆራጭ ነህና ውሳኔህ እንደእግዚአብሔር መሆኑን አትዘንጋ” ይለው ነበር። ሕዝቡ እንዲፈራው እንጂ፣ እንዲወደው መጨነቅ እንደሌልበት ይመክረው ነበር። ለተጨቆኑት ለተበደሉት ንጉሡ እንዳያዝን ይመክረው ነበር። ማስተዳደር ያለበት በዲሞክራሲ ሳይሆን በተዎክራሲ መሆን አለበት እያለ ከግሪክ የሰማትን ጥራዝ-ነጠቅ ይነግረው ነበር። ይኸ ለምን ሆነ ብለው የሚጠይቁትን በወታደር እንዲደፈTጥ ይመክረው ነበር። የራሺያ ባለሥልጣናት በሙሉ፣ ንጉሡ እንደነሱ የተማሩትና የተመራመሩትን፣ በሳይንስ፣ በተክኖሎጂ፣ በአስተዳደር፣ በሚሊታሪይ ሳይንስ፣ ክራሺያም አልፈው ውጭ አገር ሁሉ ተልክው፣ ከታወቁት ከፈረንሳይ፣ከእንግሊዝ ዩኒቨርሲቲዎች በታላቅ ማዕረግ የተመረቁትን፣ መኳንንት (aristocrats)[ii] ትቶ ከዚህ መሀይም የገባር ገብሬ ልጅ ምክር መቀበሉ አስቆጣቸው።
ራስፑቲን ግን ለማንም ቁጣ ደንታ ሳይሰጥ፣ ይልቅ እንደዓይናቸው ብሌን የሚመለከቱትን የመኳንንት ሚስቶች ተራ በተራ “ለበረከት” እየጠራ፣ እያማገጠ ከመጨረሱም አልፎ ተርፎ፣ በቤተመንግሥቱ የተወለዱትን የንጉሣውያን ቤተሰብ ወጣት ሴቶች ልጆች፣ ልዕልቶችን በሙሉ እየስመጣ ይጨረግዳቸው ጀመር። ንግስት አሌክሳንድራም እንደነብስዋ ትወደው ስለነበረ፣ ንጉሡ ከቤት ሲወጣላት፣ ሹልክ እያለች ራስፑቲን ጋ እየሄደች እንደ ማናቸውም ሴቶች ትስተናገድ ነበር። በዚህ አስቀያሚ የማይረካ የወሲብ ጥማቱ የተነሳ፣ በአንድ ቀን ከብዙ ሴቶች ጋር መማገጥ መቻሉ ያስገረማቸው ዜጎች፣ የራሺያ “የፍቅር ባቡር” (love machine) የሚል የቅጽል ስም አወጡለት። ብዙ ሴቶቹ ቀሚሳቸውን ጥለውና አንጠልጥለው ያብዱለት ነበር። የሚያስደንቀው ነገር አለመቀናናታቸው ነው። ተራቸውን በትዕግስት እየጠበቁ ይስተናገዳሉ። የሚገርመው ታዲያ እሁድ እሁድ ቤተመንግስት ውስጥ በምትገኘው ቤተክርስቲያን እየሄደ ያስቀድሳል። የክብር ቦታ ይቅመጥና፣ አንዴ ወይም ሁለቴ ተነስቶ በሚያስገመግም ድምጹ፣ “እግዚአብሐር የሀሎ ምስለ ኩልክሙ” (Бог с тобой все) ብሎ ተመልሶ ይቀመጣል። ያንን የሚያስገመግም ድምጽ ሲሰሙ፣ አድናቂ ሴቶቹ ልባቸው ወከክ ትርክክ ይላል። ወንዶች ግን በንዴት ብግን ይሉ ነበር። ምንም ዓይነት ክህነት ሳይቀበል እጁን አንስቶ ሲባርክ፣ ትንሽ እንክዋን አይሰቀጥጠውም። አንዳንዴ ሲያሰኘውም፣ “ዋ! እንዳልደግምብህ!” እያለ እየዛተ፣ የተቃወመውን ያርበደብዳል። በመጠጥና በወሲብ ፍላጎት ያበደ ዕብድ “መነኩሴ” ነኝ ባይ መተተኛ እስከመቼ እንደሚጫወትባቸው ባለማወቃቸው መኳንንቱ ልባቸው አረረ። ንጉሡንም አማረሩት። ይኸን መተተኛ ጉደኛ ዕብድ መነኵሴ ግን ለመገላገል ተማምለው ቆርጠው ተነሱ።
ራስፑቲንን
መገላገል፣ ለመኳንንቱ ቀላል ሥራ አልሆነላቸውም። በተለይ ንግስቲቱ በጣም ስለምትወደው፣ ቤተመንግሥት ውስጥ ለዘልዓለም ቢኖር ፍቃድዋ ነውና፣ በምንም መልኩ ከዚያ እንዳይርቅ ትከላከልለት ነበር። ራስፑቲንን በክፉ የሚተናኮለውን ከማጥፋትም አትመለስም ነበር። ነጉሡም ዓይኑ ተጋርዶበት አንዳችም የራስፑቲን ጥፋት አልታየው አለ። እንዲያውም በራስፑቲን ላይ ክፉ የሚያስበውን በሙሉ አይምሩ ቅጣት ነበር የሚቀጣቸው። በዚህ የተነሳ፣ መኳንንቱ፣ የንጉሡን ሥረወ-መንግስት ለማትረፍና እናት ራሺያን መቅመቅ ውስጥ ከመውረድ ለማዳን ሲሉ፣ የሚገደልበትን መንገድ ማሰላሰል ጀምሩ። መኳንንቱ፣ ጭርሶ ይኸን ሰው ከውጭ ምንም ማድረግ ስለማይችሉ፣ ከቤተመንግሥት ውስጥ የሚረዳቸውን ሰው ያፈላልጉ ጀመር። ፈሊክስና (Felix) እና ዩሱፖቭ (Yusupov) የተባሉ አንጀታቸው በራስፑቲን ያረረ የንጉሳውያን ቤተሰብ ተገኙ። የራስፑቲን የመጠጥና የፍትወት ፍቅሩ የአደባባይ ምስጢር ነበር። በዚያ ዙሪያ ሊያጠምዱት ወሰኑና በጥንቃቄ ወጥነው ተባባሪዎችን አዘግጁ። ፈሊክስ በአንዲት ማሪይ ጎሎቪና (Maria Golovina) የምትባል ሴት
በኵል ተወዳጀውና (ሌላም ነገር ይወራል) ዕምነቱን አገኘ። ሁለቱ ልዑላን በአንደኛቸው ቆንጆ ሚስት ወጥመድ ሊያጠምዱት ወሰኑ። በጥይት ደብድበው ሊገድሉት አስበው ነበር፣ ዳር ግን ጥይት ሲተኮስ ስለሚሰማ በቀላሉ በግድያው ሊያዙ እና ሊጠፉ እንደሚችሉ ተገነዘቡት። ከተያዙ ነጉሡና ንግሥቲቱ እንደማይምሩአቸው ያውቁ ነበር። በመርዝ ሊገድሉት ወሰኑ። ዕቅዳቸውን በዝርዝር ማወቅ የሚፈልግ ሰው ካለ ሮዘንበርግ (Jennifer
Rosenberg) “The Murder of Rasputin” ብላ የጻፈችውን
በሁለተኛው ተራቁጥር የተመለከተውን ድረ-ገጽ በመጨረሻው ገጽ ግርጌ ጠቁሞ ዝርዝሩን ማየት ይቻላል[iii]።
የራስፑቲን መጨረሻ
ክፉ ሰው መቼም ቢሆን፣ ይዘገይ እንደሆነ እንጂ፣ መጨረሻው አያምርም። ባጭሩ፣ ዲሰምበር 16 አልቆ ዲሰምበር 17 ቀን 1916 ሊገባ እኩለ ሌሊት ላይ ሳይናይድ (cyanide) መርዝ ተዘጋጀለት። ልክ በታቀደው መሠረት፣ ራስፑቲን መጠጡን ሊገሽር፣ የተዘጋጀለት ግብዣ ጥርግርግ አድርጎ ሊበላና፣ ከፈሊክ ሚስት ከኢሪና ጋር ሊዳራ ልብሱን ለባብሶ፣ ሽቶውን ተቀብቶ፣ መጣ። ለነገሩ፣ ኢሪና በዚያ ግድያ ተንኰል አልተባበረችም ነበር። ገዳዮቹ አስቀድመው ምግቡንና መጠጡን ሳይናይድ መርዘው አስቀመጡለት። ሳይናይድ ማለት፣ እንክዋን ተውጦና፣ ድንገት በስሕተት የሰው ቆዳ እንኳን ቢነካ ወዲያው ድብን የሚያደርግ መርዝ ነው። አጅሬ ራስፑቲን ግን፣ እላይ ቤት ድንገተኛ እንግዶችን እያስተናገደች ነው ተብሎ የተነገረውን፣ የኢሪናን መምጣት በጉጉት እየተጠባበቀ የተመረዘችውን ፓስቲኒዋን ጥስቅ አድርጎ በልቶ፣ ወይንዋንም ግጥም አድርጎ ጠጣት። ፈሊክስ፣ የተመረዘው ራስፑቲን ወዲያው ወድቆ ተፈራግጦ ይሞታል ብሎ ቢጥብቅ፣ ሰውዬው አንዳችም ፍንክች አላለም። መርዙ በራስፑቲን ላይ ሳይሠራ ቀረ። ምርጫ ሲያጡ፣ ገዳዮቹ ያልፈለጉቱን ማድረግ ነበረባቸው። በጥይት ደበደቡት። በጥይትም ተደብድቦ፣ ሞተ ብለው ሬሳውን ወስደው ሊጥሉት ሲሞክሩ ተነስቶ ሮጠባቸው። ተከታትለውም በሌሎች ጥይቶች ደጋግመው መቱት። ወደቀ። ግን አልሞተም። ከነነብሱ ወስደው ማላያ ነቭካ ወንዝ (Malaya Nevka River) ውስጥ ጣሉት[iv]። ሬሳው ከወንዝ ወጥቶ፣ የሀኪም መረጃ እንዳሳየው ከሆነ፣ ወደ በረዶነት ከተለወጠው ወንዝ ውስጥ ለመውጣት ሲፍጭርጨር እያታገለ ደሙ ረግቶ በመጨረሻው እንደሞተ ነበር።
ይኸ
ሀሳዊና መተተኛ አስመሳይ መነኵሴ ከሞተም በሁዋላ ዝናው አልሞተም። ቦኔ ኤም (Boney M) የተባሉት ዝነኞቹ የ70ዎች የሮክ ሙዚቃ አቀንቃኞች ስለዚያ ሞገደኛው መነኵሴ ነኝ ባይ በዓለም በአንደኝነት የተወደደላቸውን ዘፈን አቀንቅነውለታል። መስማትም የሚፈልግ፣ ዘፈኑን http://www.youtube.com/watch?v=kvDMlk3kSYg
መስማት ይቻላል። አንዳንድ የጨዋታ ሶፍትዌር ኩባንያዎች ዛሬም ራስፑቲን ከመቃብሩ እንደክርስቶስ ትንሳዔ ሙታን አንድርግዋል ብለው ያዘጋጁት ጨዋታና በዙ ሚሊዮን ዶላር የተሸጠላቸውን ዜና በ http://en.wikipedia.org/wiki/Grigori_Rasputin_(Hellboy)
ማየት ይቻላል።
መደምደሚያ
ራስፑቲን
የተከሰተው በራሺያ የኦርቶዶክስ በተክርስቲያን ውስጥ ነው። በአሁኑ ዘመን ዲያብሎስ ከገሀነም አምልጦ በየአድባራቱ እየገባ የጌታን በጎች ሲያምስ ይገኛል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥም ብዙ ራስፑቲኖች እንደተሰማሩባት ይስተዋላሉ። እስቲ አካባቢአችሁን ቀስ ብላችሁ ቃኙ! ራስፑቲን በየአድባራታችሁ የላችሁም?
[i] Frances Somer Cocks:
Abraham Hannibal and the Raiders of the Sands, 2003.
[ii]
http://history1900s.about.com/od/famouscrimesscandals/a/rasputin.htm
[iii] 1. Edvard Radzinsky,
The Rasputin File Trans. Judson Rosengrant (New York: Doubleday, 2000)