“ወደ ፈተና አታግባን ”
ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ
ሐምሌ ፳፻፮ ዓ.ም.
መግቢያ
በዚህ ሰሞን ራሴን ከራሴ ያጣሁት መሰለኝና መፈለግ ጀመርኩ። በእንቅልፍ ላይ የነበርኩም መሰለኝ። ሰውነቴን ለመቀስቀስ ጎተጎትኩት፤ ከሰመመኔ ለመላቀቅ እየታገልኩ ተንጠራራሁ። ራሴንም ወዘወዝኩ። ሙሉ በሙሉ ሳልነቃ በመንፈሴ እኔነቴን ታቅፌ ወደ ተወለድኩባት መንደር፤ ፊደል ወደ ቆጠርኩባት ደብር፤ በየደረጃው ለመማር የዞርኩባቸውን ታላላቅ የጉባዔ መካናትንና መምህራንን ቃኝሁ።
ኢትዮጵያን ለቅቄ በወጣሁበት ጊዜ ከዓለም ሸሽተው የዘጉትን፤ በዓለም ላይ አኩርፈው በዝምታ ላይ የነበሩትንና፤ በሕዝብ መካከል የሚንቀሳቀሱትን ሊቃውንት ተመለከትኩ። ሁሉም የሉም። ድምጻቸው ግን ይሰማኛል። የሚሰማኝ ድምጽ የኑዛዜ ድምጽ ሆነብኝ። የስቅለት ዕለት እየሰገድን የምንተነፍሳት፤ ሥርዐተ ቁርባኑን የምንደመድምባት “አቡነ ዘበሰማያት ኢታብአነ እግዚኦ ውስተ መንሱት” የምንላትን በሰመመን እየወደኩ እየተነሳሁ ማንጎራጎር ጀመርኩ። ከዚያም መጥምቁ ዮሐንስ ትዝ አለኝ። እመቤታችን ቅድስት ድንግልም የተናገረችው፤ ከሷም በኌላ “ይእቲ ሥጋ እንተ ነስአ መድኅን እማርያም” እያሉ ያንጎራጉሩ የነበሩ ሊቃውንት ከፊቴ ተደረደሩብኝ። ዛሬ ኢትዮጵያውያን ከያሉበት ሆነው ከሚያስተጋቡት ጩኸት ጋራ ተገጣጠመብኝ። ታዲያ ከኔ በፊት የነበሩ የኢትዮጵያውያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አበው ዛሬ ቢኖሩ ምን ይሉ ነበር? ይህችን ወቅትስ እንዴት ይመለከቷት ነበር? የሚል ጥያቄ ተፈጠረብኝና ይህችን ጦማር በ፯ አንቅጽ ለማቅረብ ተገደድኩ።
፪ኛ፦“ወደ ፈተና አታግባን። ከክፉ አድነን እንጅ”
፫ኛ፦መጥምቁ ዮሐንስ የተናገረውን
፬ኛ፦የጸሎተ ማርያም ትርጉም
፭ኛ፦ይህች ሥጋ (ሰብአዊነት)
፮ኛ፦ የኪዳን የቃዳሴ የማህሌቱ ይዘት ይለወጣል
፯ኛ፡የጽዋዕ ማኅበራት
ከ፩ እስከ ተራ ፯ የረዘርኴቸውን አንቀጾች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ግንዛቤ እያሳጠርኩ ለማቅረብ በኑዛዜ እጀምራለሁ።
፩ኛ የኑዛዜ ድምጽ
“ሥርዓቱሰ ለዘይመውት ጽንእት ይእቲ እስመ ኢትበቁዕ አመ ሕያው ውእቱ ዘሠርዓ”( ዕብ ፱፡፲፯) በጸና ህማም ላይ ያለ ሰው ሞቱን ለመቅደም የሚናዘዘው ኑዛዜ ከሞት ተርፎ ቢድን፤ ኑዛዜውን ሊለውጥ ይችላል። ከሞተ ግን ኑዛዜው የጸና ነው።” የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስን ቃል ተመርኩዘው ብዙ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት ተናግረዋል። ጽፈዋል። ከብዙወቹ አንዱ”ኩሎሙ ነብያት ዘተናገሩ በበዘመኖሙ ወበበ ነገዶሙ ዘነበቡ በመንፈስ ቅዱስ ዘመለኮት በኩሉ ጊዜ ነአምን እስመ ኩሉ ዘነበቡ ጽድቅ ውእቱ“ (ሃ. ም. 70፡ 33)ብሎ የተናገረው ቅዱስ ቄርሎስ ነው። ይህን የሚተረጉሙ አባቶች፤ “ባንተ ሀሳብ ብቻ አትገታ፤ ባካባቢህ ያሉትን ሰዎች ሁሉ ጠይቅ፤ በሕይወት ያሉ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሀሳባቸውን ይለዋውጣሉና በነሱም አትወሰን። ሐሳባቸውን ሳይለዋውጡ ይህችን ዓለም ያቋረጡትን የነ ቅዱስ አትናቴዎስን ዮሐንስ አፈወርቅን ምክር ጥለውልህ በሄዱት መጻሕፍቶቻቸው
እንደገና ሀሳብህን ለካው” ብለው የሰጡኝን ምክር አስታወስኩ።
ያወረሱንንም መጻሕፍት ማገላበጥ ጀመርኩ። የቅዱስ ጳውሎስን መጽሐፍ ይመረምር የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ስለ ኑዛዜ “አልቦ ዘይሤኒ እምቃለ ኑዛዜ ምስለ ገቢር”(ድ ር ፳፩፡ ፱)። ብሎ የተናገረውን ተመለከትኩ። ማለትም፦በምትለዋወጠው ዓለም ሀሳባቸውን ሳይለዋውጡ ሳይሰርቁ ሳይዋሹ፤ ከከፈን በቀር የሚይዙት ጓዝ ለማስከተል በማይችሉባት ቅጽበት በሞት አፋፍ ላይ ሲደርሱ የሚናዘዟትን ቃል ጠብቀው ህይወታቸውን ለመፈጸም ከሚጥሩ ሰዎች በቀር የተሻለ ሰላምና ጸጋ ያለው ሰው የለም።” የሚሉትን ተመለከትኩ።
በመቀጠልም ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ “ኢትፍቅዱ ቃለ ኑዛዜ እምኀበ ካልዕ።” ነፍሳችሁ ከሥጋችሁ በምትላቀቅበት ቅጽበት የምትናገሯትን የኑዛዜ ቃላችሁን የሚያላቅቅ ሀሳብ አትቀበሉ። ካለ በኋላ፤ “ለሊክሙ አርአያ ወኑዛዜ ኩንዎሙ ለካልአን” በእድሜ በልምድ በእምነት ከናንተ በታች ላሉ ሰዎች በማትቀይሩት የኑዛዜ ቃላችሁ ምሳሌ ሁኗቸው (ድ ር ፳፩፡ ፵፩)። እያለ የተናገረውን አስተዋልኩ። እውነትም “የማይጨበጡ ነፋሳት” ተብሎ ከመከሰስና ከመወቀስ መዳንን ከመሰለ የሚልቅ ጸጋና ክብር እንደሌለ ተገነዘብኩ።
ሰሞኑን በህገ አረሚ የሚመሩት ወያኔዎች በነአቶ አንዳርጋቸው ላይ የፈጸሙትን አድኖ የመብላት ዜና ስሰማ፤ ያንዳርጋቸውንና ካንዳርጋቸው በፊትና አሁንም ካንዳርጋቸው ጋራ ወያኔ የበላቸውን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ውጬ ለማሻገር፤ ሰውነቴ ዮናስን ያስተናገደው የአንበሪው ከርስ በሆነላቸው ብየ ተመኘሁ። ኢትዮጵያ ወደ ባህር በተለወጠች፤ የእነ አንዳርጋቸውን ሰውነት ወደ ዓሣነት፤ እኔን ወደ አሳነባሪነት መለወጥ ቢቻል ኑዛዜየ በጸና ብየ ተከዝኩ። የማይሆን ኑዛዜ ሰመመን ሆነብኝ። የማሰብ አቅጣጫየን ቀይሬ፤ የስቅለት ዕለት በጾምና በማክፈል በስግደትም በመውደቅ በመነሳት “ለከ ኃይል” የምንላትን ለማለት ተሰማኝ። ከዚያም ለቅዳሴ የተሰማሩ አምስቱ ልኡካን በየመስመራቸው የሚያከናውኑትን ተልእኮ ፈጽመው ድርገት ወርደው ሲመለሱ፤ ቅዳሴያችን በምንደመድምባት ”ኢታብአነ እግዚኦ ውስተ መንሱት” በምትለው የኑዛዜ ቃል ትንፋሸን ገታሁ።
፪ኛ “ወደ ፈተና አታግባን (ኃይል አልሀቂተ ኩሉ)
“ወደ ፈተና አታግባን” የምትባለው ጸሎት “ኃይል አልሀቂተ ኩሉ” የተባለችውን ረቂቅ መንፈሳዊት ኃይል ያዘለች ናት ብለው አባቶች አስተምረውናል። ይህችውም የስነ ተፈጥሮ ሊቃውንት “reflex is negative feedback system that helps maintain homeostasis” የምትባል ሰውነት የምትወጋ እሾህ ስትወጋን ድንገት ብልጭ የምትል ሰውነትን ለመከላከል ድንገት የምትተኮሰው ነርቭ አለችን እያሉ ካስተማሩን ጋራ የምትነጻጸር ናት። የቁምጥና በሽታ ያጠቃው ነርቭ ከተሸከመ አካል በቀር፤ ሰውነት በእሾህ በተወጋባት ቅጽበት እሾሁን ከሰውነት ለመንቀል፤ ወይም ከእሳት ወላፈን ለመሸሽ ለማሰብና ለማሰላሰል ነርቫችን የሰከንድ ፋይታ አይሻም። በዚያችው ቅጽበት የወጋውን ከሰውነቱ ይነቅላል። ኢትዮጵያዊነታችን በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። ህዝባችን ቤተ ክርስቲያናችንና ባጠቃላይ ኢትዮጵያ አገራችን የገቡበት ፈተና ዶክተር አረጋዊ በርሄ፦ ስለወያኔ አጥፊ መርሆ በገለጹበት መጽሀፋቸው፦
“የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር በ1979 አመተ ምህረት አስተሳሰብ ለዋጭ የፕሮፓጋንዳ መርሀ ግብር ለሚመለምላቸው ቀሳውስት ዘረጋ። የማሰልጠኑ ዓላማ ቤተ ክርስቲያኗን ከህዝብ ለይቶ በመምታት ስፋቷን ማጥበብና በትግሬአዊነት ላይ ብቻ የተመሰረተ ስሜት በትግራይ ተወላጆች ጭንቅላት መክተት ነው። ቤተ ክርስቲያኗ ለረዥም ዘመናት በህዝቡ አዕምሮ ላይ ስትተቀርጸው የኖረችውን ብሄራዊ የኢትዮጵያነትን ስሜት ከትግራይ ህዝብ አዕምሮ ጠራርጎ በጠባቡ ትግሬአዊነት ስሜት በመተካት የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዘት እያጠበቡ ራሷን ቤተ ክርስቲያኒቱን መምታት ነው።” ሲሉ የገለጿት ናት።
ወያኔዎች ኢትዮጵያ አገራችንና በቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ከላይ በተገለጸችው መርኋቸው መመራት ከጀመሩባት ቅጽበት ጀምሮ፤ ኢትዮጵያውያን ወደፈተና የገቡበት እና ከክፉ ነገር ላይ የወደቁበት ዘመን ነው። ይህች መርሆ የተፈጠረችባት ሰአት በኦረሞ ባማራ በአፋር በኦጋዴ በጉራጌ ልጆች ላይ በየገዳማቱ በሚኖሩት አበው መነኮሳት ላይ በትግራይ ወገኖቻችን ስም የተሰነዘረችው፤ በእነአቶ
አንዳርጋቸው ሰውነት ላይ የተከከለችው ሾተል ተጸንሳ የተወለደችባት ቅጽበት ናት።
ኢትዮጵያውያን ህጻናት እናቶችና አዛውንት በረሀብ እያለቁ፤ ወያኔ በስማቸው በሚሰበስበው ገንዘብ ሰላይ በመግዛት የውጭ ዜግነት ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን እያደኑ መብላታቸውን ስናስብ፤ ክርስቶስ “በርጡብ እጽ ለእመ ኮነ ከመዝ እፎ በይቡስ” (ሉቃስ ፳፫፡ ፴፩) ማለትም “መለኮታዊነት በተወሐደው አካል ላይ ግፉና መከራው እንዲህ ከጠነከረ፤ በተራ ሰውነት ላይማ ምን ያህል የከፋ ይሆን?እንዳለው፤ በእጃቸው ላይ በወደቀችው ኢትዮጵያ ውስጥ በገጠር በከተማ፤ በየአድባራቱና በየገዳማቱ ባሉት ወገኖቻችንማ የሚፈጽሙትን መከራና ግፍ ስናስበው አካላችን ይፈርሳል። አቶ መለሰንና አቡነ ጳውሎስን በተመሳሳይ ቅጽበት ኢትዮጵያን እንዲለቁ የፈረደ አምላክ የት አለ? እንድንል ያደርገናል። ሰውነታችንን ይዘገንነዋል። እንቅልፋችን ሰመመን ይሆናል። የቆምንበት ይጠፋናል። አፋችንን ደምደም ይለናል። ይህች ወቅት የከበሮ ሽብሸባ (ማህሌት) መዝሙር ይቅርና ወደፈተና ከመግባታችን በፊት
የምንጸልያትን “ወደ ፈተና አታግባን” የምትለውን አጭር ጸሎት ለመጸለይ ያለንባት ቅጽበት ፋታ ነፍጋናለች።
አባቶቻችን “ወደፈተና አታግባን። ከክፉ ሁሉ አድነነ እንጅ” ሳትሉ ሰአተ መዐልቱንም ሰአተ ሌሉትንም አትጀምሩ” ብለው በአጽንኦ ይመክሩን የነበረው፤ ለእንደዚህ ያለች ቀውጢ ሰአት በቅተን ለመገኝት እንድንችል ነበር። ሳይታለም ድንገት ሚገጥሙ ፈተናወችን በቅጽበታዊት ውሳኔ ማሸነፍ የሚቻለው “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ። መንፈስ ተዘጋጅታለች። ሥጋ ግን ደካማ ነው”(ማቴ ፳፡፵፩) ብሎ ክርስቶስ የተናገረውንተገንዝቦ በሚኖር ስሜት ብቻ ነው። ሥጋ ደካማ ናትና በደካማ ሥጋቸው ድንገት ከፈተና ቢገቡም፤ ፈተናው ሳይጥላቸው ማሸነፍ የሚችሉት፤ በተረጋጋ ጊዜ ወደ ፈተና አታግባን የምትለው ሀረግ ባዘለችው
ያንድምታ ትርጓሜ ውስጣዊ መንፈሳቸውን በሞራል እና በእምነት ያስታጠቁ ሰዎች ብቻ ናቸው።
ጌታችን “ወደፈተና አታግባን ከክፉ አድነን እንጅ” ብላችሁ ጸልዩ ብሎ ያስተማረውም፤ በቅጽበታዊ ነገር ላይ ለማሰብ፤ በቅርብ ካለ ሰው ጋራም ለማመከር ላማቀድ ቅጽበት በሌለበት አጋጣሚ መጸለይ አለመቻሉን ለማሳየት ነው። ይህች ያዘቦት ጸሎት በደህና ጊዜ “ወደፈተና አታግባን“ በማለት የምትጸለየው አማራጭና ፋታ የነፈገች ቀውጢ ቅጽበት ስትከሰት፤ የምንወስናትን ቅጽበታዊት ውሳኔ፤ አቅጣጫ የምታሲዝ ቅጽበታዊት “ኃይል አልሀቂተ ኩሉ” ናት።
“እስመ አኮቴቶሙ እረፍቶሙ። ወእስመ እረፍቶሙ አኮቴቶሙ”እንዲል ከህገ አራዊት የተላቀቁ ሰዎች፤ በቅጽበት በሚገጥሟቸው ክስተቶች ወቅት ብቻ ወደ ፈተና አታግባን እንላለን በማለት ሳይዘናጉ ከፍጡርና ከፈጣሪ ጋር የማይጋጨው በየሰአቱ የሚያከናውኗቸው ተግባራቸው ሁሉ ጸሎት ነው። በዓይን የሚታዩ የጎሉ ግላዊም ሆነ ህዝባዊ ፈታኝ ነገር ሲገጥሟቸው በደህና ጊዜ “ወደ ፈተና አታግባን” በሚለው መንፈሳዊት ትጥቅ ወደ ተግባር ይገሰግሳሉ እንጅ፤ ስብከት እንስማ፤ እናስቀድስ፤ በከበሮ እናሸብሽብ አይሉም። የመጥምቁ ዮሐንስን እንቅስቃሴ እንመልከት።
፫ኛ መጥምቁ ዮሐንስ፦
“የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትን ወደ ጻድቃን ጥበብ በመመለስ በኤልያስ መንፈስና ኃይል መሄድ ነበር (፲፯) እንደተባለው፤ የዮሐንስ ተልእኮ የተበታተነውን መንፈስ ለመሰብሰብ ቅጽበታዊ ርምጃ ለመውሰድ የተዘጋጀች ቅጽበታዊት ተልእኮ ነበረች። ይህች የዮሐንስ ቅጽበታዊት ተልእኮ፤ አክአብን “ክፉ ለማድረግ ራስህን ለክፋት ሸጠሀል (ቀ ነ ፳፡፲፯_᎗ ፳፮)። በማለት እየዘለፈች፤ ንብረቱን ርስቱን በመጨረሻም ህይወቱን ከተነፈገው በወቅታዊት ችግር ላይ ከወደቀው ከናቡቴ ጋራ የተሰለፈች ቅጽበታዊት ርምጃ ነበረች። መጥምቁ ዮሐንስም በኤልያስ መንፈስና ወኔ በመመራት “ተራራው ዝቅ ኮረብተው ከፍ ይባል ጉርጓዱአዘቅቱ ይሙላ፤ ንስሀ በማይገባ አንገት ላይ ምሳር ተሰንዝሮባታል” እያለ በዚያች አጣብቂኝ ፈታኝ ቅጽበት ወደ ህዝብ ብቅ አለ። እየጸለየ እየዘመረ ወደ ህዝብ አልመጣም። ሰውነትን ከሰውነት፤ ወቅትን ከወቅት፤ ተልእኮን ከተልእኮ ጋራ ስናነጻጽር፤ መጥምቁ የቀረባቸው ሰዎች “ወደፈተና አታግባን” የምትለውን ቃል በሉ እየተባልን እንዳደግን እንደኛ በመድገም አላደጉባትም። በሰውነታቸው ላይ ለምትደርሰው ቅጽበታዊት ፈተና በደማዊት ስሜታቸው (ነርቫቸው)ቅጽበታዊት መፍትሔ ከሚወስዱ በቀር ፤ እንደኛ “ወደፈተና አታግባን” የምትለውን ቃል ሰምተዋት አያውቁም። ስለዚህ “ኃይል አልሀቂተ ኩሉ” የተባለችው ትጥቅ
አልነበረቻቸውም።
የሰውነትን ተፈጥሮ የሚያጠኑ መምህሮቻችን ሰውነታችንን ቅጽበታዊት እሾህ ስትወጋን ቅጽበታዊት ርምጃ የምትወስድ “reflex the negative feedback system” የምትባል ነትቭ አለችን እያሉ እንዳስተማሩን ሁሉ፤ እምነታችንን ሞራላችንን ኢትዮጵያዊነታችንን የምትወጋ እሾህ ስትገጥመን ድንገት ብልጭ የምትል “From the time immemorial Ethiopia has played an important part and often the leading role in the affairs of the world. The Bible as well as Secular history 5
confirms this fact (pa 100 ) ተብላ የተመሰከረችልን “ኃይል አልሀቂተ ኩሉ” የተባለቸው አለችን እያሉ አባቶቻችን አስተምረውን ነበር።
ዛሬ ያባቶች ልብ፤ ያባቶች ወኔ፤ ያባቶች እምነትና ተስፋ ከኛ የራቀበት፤ ለእውነት ከመታዘዝ የፈረጠጥንበት ዘመን በመሆኑ፤ አባቶቻችን አገራችንን ጠብቀው ያቆዩባት “ኃይል አልሀቂተ ኩሉ” የተባለችው ጥበብ፤ እምነት ተስፋ የጠፋችበት ወቅት በመሆኗ፤ ብዙዎቻችን ከዘራፊዎች ከአካባውያን ጋራ በመተባበር ህዝቡን ከሚደበድቡበት የኢትዮጵያውያንን ሰውነት እየቆራረጡ በመብላት ላይ ካሉት ወያኔዎች ጋር ለመተባበር ራሳችንን ለንዋይ የሸጥንበት ዘመን ነው።
ዮሐንስ የተመራባት “ኃይል አልሀቂተ ኩሉ” የተባለችው የኤልያስ መንፈስ፤ ሐዋርያት ከክርስቶስ፤ ሊቃውንት ከሐዋርያት፤ ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ከሊቃውንት እየተቀባበሉ ኢትዮጵያዊነታቸውን ሞራላቸውን አንድነታቸውን የጠበቀኡባት ለቀውጢ ጊዜ ፈጥና ደራሿ ቅጽበታዊት ውሳኔ እንደ ጢስ በመትነን የጠፋችበት ሰአት ናት።
ምሥጢርን ምሥጢር ስቦ በሚያመጣው ያንድምታ ትርጓሜያቸው ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት “በሬ ጌታውን፤ አህያ መሰማሪያውን አወቀ። ህዝቤ ግን አላወቀም”(ኢ፩፡፫) ብሎ ነቢዩ የተናገራትን ሐረግ አንድም እያሉ ሲተረጉሙ ስበው የሚያመጧት ምሳሌ የሰፈነችበት ዘመን ትመስላለች። ውሾች በሚከረፋ ሽንታቸው ይተባበራሉ። አንዱ ቀድሞ የሸናውን እያሸተቱ በላው ላይ ለመሽናት ይምበረከካሉ። ዘመን ሲከፋ ሰው ዘመኑን ዘመነ_ ከልብ ያደርገዋል። ተገቢ አለመሆኑን እያወቀ እምነት በሚንድ ሰው በሚጎዳ አገርን በሚበደል ነገር ላይ ይተባበራል።” ይላሉ። እንዳሉትም፤ እነ አቶ መለሰ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በሸኑት ሽንት፤ እነ አቶ ኃይለ ማርያም ተምበርክከው እሸኑበት ነው።
ቀሳውስት፤ ጳጳሳት፤ መነኮሳትና ሰባኪዎች ሁሉ፤ በወንድሞቻችሁ ጀርባ ላይ የምትሰነዝሩት ጅራፍ፤ በኢትዮጵያውያን አንገት ላይ የሰነዘራችሁት ምሳር፤ እጀታው ወደ ምትደበድቡት ህዝብ ፤ስለቱ ወደ ራሳችሁ አንገት ተንሸራቶ መግባቱን ተመልከቱ!እያልን ለወያኔዎች አለመንገራችን ሲያስገርም፤ በዝሙት በዘረፋ የሰው ትዳር በሚያፈርስ ተግባር መሰማራታችን “ወደፈተና አታግባን” የምትለውን ሀረግ ትርጓሜዋን ቀርቶ ጥሬ ቃሏን ሰምተናት የማናውቅ መምሰላችን እጅግ የሚያሳዝ ነው።
“በህዝብ ላይ የምትፈጽሙት አስከፊና አስቀያሚ ተግባራችሁ ሸተተን፤ ከረፋን፤ ቤተ መቅደሳችን ይጽዳ” ብለው የሚጮኹትን ምእመናን፤ የሚቃወሙላቸውን፤ የሚሳደቡላቸውን፤ የሚደበደቡላቸውን፤ ሰዎች አዘጋጅተዋናል። በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሆኖ ሂዱ! ያዙ! የሚላቸውን በመስማት ብቻ እንደ ተናካሽ ውሽ ለመናከስ የሚጣደፉ ወገኖች፤ ወደ ሰውነታቸው ህሊና ተመልሰው በቤተ መቅደሱ የቆመው ማነው? ምንድነው የሚካሄደው? ብለው ራሳቸውን ከመጠየቅ ይልቅ፤ ከዘራፊዎች፤ ካታላዮች፤ ከሸተቱትና ከከረፉት ግለ ሰቦች ጋራ በመተባበር በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ እልል የሚሉ ጉዶች ሆኑ።
በዚህ ዘመን ያለን ቀሳውስት፤ መነኮሳት፤ ሰባኪዎችና ጳጳሳት በህዝብ በቤተ መቅደስ ላይ ወያኔ የሚያደርገውን የከረፋ ነገር እያሸተትን እንደ ማያስቡ እንስሳት፤ የእኛንም አስከፊ ነገር ለመደርብ በህዝብ እና በየቤተ መቅደሱ ተንበርክከናል። የቆሎ ተማሪዎች አፋቸውን የፈቱባት የጸሎተ ማርያምን መልእክት ሳንረዳ ዘው ብለን ወደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክህነታዊት አገልግሎት መግባታችን ገሀድ እየሆነ ነው።
፬ኛ ጸሎተ ማርያም
እመቤታችን “ትእቢተኞችን በልባቸው ሀሳብ በትኗቸዋል። ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዷል ትሁታንን ከፍ አድርጓል የተራቡትን አጠገባቸው። ባለ ጠጎችን ባዷቸውን ሰዷቸዋል”( ሉቃ ፩፡፶፩᎗፶፬) ብላ የተናገረችው ቃል ሰላም በጠፋበት፤ ህይወት በደፈረሰበት ቅጽበት የመንፈስ የሞራልና የእምነት ስንቅና ትጥቅ እንድትሆነን እንደግማታለን እንጅ ጸሎት አይደለችም።ጸሎተ ማርያም ብለን በምንደግማት አንቀጽ ወያኔን የመሳሰሉ ቡድኖች በተለያዩ ዘመናት እንደሚከሰቱ እመቤታችን ተናግራለች። እመቤታችን የተናገረቻት ይህች አንቀጽ፤ “ከሳምራዊው ቅጽበታዊ ውሳኔ ጋራ ትስማማለች“ ይላሉ ሊቃውንት አበው።
በሉቃስ ወንጌል ምዕ ፲፡ ከቁ ፳፱᎗፴፯ ተመዝግቦ እንደምናነበው፤ ካህኑና ሌዋዊው የተነቀፉት በዚያች ቅጽበት ከችግር ላይ ለወደቀው ሰው እንጸልይልህ፤ ወይም ንስሀ ግባ፤ ወይም እመን ብለው ስላስበኩት አልነበረም። በዚያች ቅጽበት በሰውነቱ የገባቸውን እሾህ ሊነቅሉለት ባለመሞከራቸው ነበር። ሳምራዊው የተደነቀው ስለጸለየለት ወይም ሃይማኖት ስለሰበከለት አይደለም። በሰውነቱ የተተከለችውን ቅጽበታዊት ሾተል ስለነቀለለት ብቻ ነበር። ክርስቶስ “እንዲሁ አድርጉ” ያለውም ሳምራዊው ለቁሰለችው
አዳማዊት ሰውነት ያደረጋትን ቅጽበታዊት ውሳኔ ነው። ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የቆሰለች ሰባዊት አካል ሲገጥማቸው ይነቅሉላታል። በሩቅ አሻግረው ለሚያዩዋት “ይእቲ ሥጋ” እያሉ ይተክዛሉ። ወቅታዊት ናትና እንመልከታት።
፭ኛ ይእቲ ሥጋ
በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነገረ መለኮት ትምህርታችን፤ በዚህች ቁሳዊት ዓለም ውስጥ ስንኖር ከማይለቅ መከራ በመሸሽ ለመዳን መሞከር፤ የመከራውን ዘመን ከማራዘም በቀር መፍትሄ አይደለም። መለኮት ዓለምን ያዳነው ከእመቤታችን ከፍሎ በተወሀዳት ሥጋ ሰባዊነትን ለብሶ ነው። ተግባር በተለየው ጸሎት ብቻ ፤ በሩቅ ሆኖ በሪሞት ኮንትሮል ለመዳን የሚደረገውን ሙከራ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነገረ መለኮት አይቀበለውም። በጸሎት ብቻ መዳን ቢቻል ኖር፤ ክርስቶስ “አባቴ ይህች የመከራ ጽዋዕ ከኔ ትለፍ” ባለው ብቻ በዳን ነበር። ከሰው ተለይቶ ወደ ገዳም የገባው የመጀመሪያው መነኩሴ እንጦንስ እንኳ ሰባዊት አካል ስትወጋ መወጋትን ለመሳተፍ ከሸሸበት ገዳም ወጥቶ ከህዝብ ጋራ ተቀላቀለ። ይህች ሥጋ ማንም ያዳም ዘር የሆነ ሁሉ በክርስትና ቢያምንም ባያምንም የሚጋራት ሰባዊት ቅንጣ ናት። አንዲት ሰባዊት አካል ስትወጋ ሰወ የሆነ ሰው ሁሉ ሊሰማው ይገባል። እግዚአብሔር በአርያው አክብሮ ሰራት፤ ስትርቀውም ተከተላት፤ አቀፋት ተወሀዳት፤ ቁስሏን፤ ግርፋቷንና ስቅላቷን ተጋራት ተሳተፋት እያሉ ይገልጿታል።
ዮሐንስ አፈወርቅ “ከመ ብእሲ ዘተሐጥአ ፍቅሩ ወሮጸ ለኃሢሶቱ እስከ ረከቦ ወነሥኦ፤ ከመዝ ህላዌ ዚአነ ዘተኃጥአት እምግዚአብሄር ወርህቀት እምኔሁ ጥቀ ሮጸ ድህሬሃ እስከ ረከባ ወነሥኣ ወይእቲኒ ተወክፈቶ። ወክሡተ ግብሩ እስመ ውእቱ ገብረ ዘንተ በአፍቅሮቱ ኪያነ” (ሃ አ ፷፫፡፭) አለ። ማለትም፦
የሚወደው ሲጠፋው እስኪያገኘው ድረስ ፋታ እንደሌለው ሰው፤ ክርስቶስ የሚወደው በአርአያው አክብሮ የፈጠረው ህላዌ ዚአነ (ሰውነት) ስትጠፋበት ከፍቅሩ የተነሳ ፈለጋት ተከተላት አገኛት። ሰውነትም ህላዌ ዚአነ ተቀበለችው። ይህን ያደረገው እኛነታችንን (ሰውነታችንን) በመውደዱ ነው። “ይእቲ ሥጋ” ይህች ሰውነታችን የተወደደች የተከበረች ናት። “አባይ ሲደፈርስ ሲመስል እንቆቆ፤ ጋሬጣው ጎጃሜ ገባ ባጭር ታጥቆ “ እንደተባለው የሰው ህይወት ሲደፈርስ ይህች ሥጋ ስትጎሰቁል ክርስቶስ ባጭር ርቁመት በጠባብ ደረት ሰውነትን ታጥቆ በደፈረሰው ሰባዊነት ገባባት። አቡነ ጴጥሮስ አደረጓት። ዛሬም እናዳርጋቸው ደገሟት።
ቄርሎስ “ወነሲኦ አርያ ገብር እማርያም ድንግል ኮነ በአርያ ሰብእ ወተረክበ በአምሳለ ዕጓለ እመሕያው (፸፭፡፳፱) ክርስቶስ ከእመቤታቸው በለበሰው ሥጋ የቆሰለውን ሰውነታችንን በሚቆስለው ሰውነት ለማዳን የምትቆስል ሰውነታችን ተወሀዳት። ለማዳን የሚታደገውን ጩኸት የሚቆስለውን ቁስል የሚቀበለውን መከራ መቀበል አለበት በሪሞት ኮንትሮል ወይም ተግባር በተለየው ጸሎት ብቻ መፍትህ የለም።
ሰለስቱ ምዕት “ገአረ በህማሙ ወጸርሀ ኀበ አቡሁ አድነነ ርእሶ. . . . እንዘ ሀሎ ህየ ጸርሀ ሀበ አዳም አቡሁ ወገብሩ፤ ወሀበ ኩሎሙ ደቂቁ።” (ሰለስቱ ምእት ከቁ ፺፯᎗፺፱) እንዳሉት፤ ክርስቶስ ይህችን ሰባዊነት በመልበስ ሰባዊነትን ከተወሀደ በኋል የህዝቡን መከራና ስቃይ በመካፈል በመለኮትነቱ ለባህርይ አባቱ፤ በሰባዊነቱ ራሱ ለፈጠረው ለምድራዊ አባቱ ለአዳምና ሰባዊነትን ለለበሰ ሰውነትን ለሚጋራው ሁሉ በመስቀል ላይ በነበረባት ቅጽበት ድምጹን አሰማ።
ቅዱስ ዮሐንስ “እስመ ነፍስ እምከመ ረከበት ዘይሳተፍ ምስሌሃ በውስተ ምንዳቤ ተዐርፍ ወትረክብ ጽማዌ (ድ ር ፳፪፡፲፫) እንዳለው፤ ይህች ሥጋ በደረሰባት ቅጽበት ጸሐይ ሲጨልምባት ጨረቃም ደም ስትለብስ የሚካፈላት ትሻለች። እረፍትና የጥሞና ጊዜ ትናፍቃለች። ዛሬም ያልሰረቀች፤ ያልቀማች። የሰው ድንበር ያላፈረሰች፤ በተለየ አካል ባንዳርጋቸው ስም የምትታወቀው ንጽህት አዳማዊት ኢትዮጵያዊት ሥጋ ድምጿን እያሰማች ነው። ለአንዳርጋቸውና ለመሳሰሉት ጀግኖች ጸሀይ እንደጨለመች፤ ለጊዜው ለሁላችንም ጨልማለች። ጨረቃ ደም እንደሆነች። አፋችንንም ደም ደም ብሎታል።
ቄርሎስ “እስመ ደቂቅ ተሳተፍዎ በሥጋ ወደም ወውቱኒ ዓዲ ተሳተፈ እሎንተ ከመዝ ከመ በሞቱ ያብጥል ዘበእዴሁ ሙአተ ሞት፤ ዘውእቱ ሰይጣን ወይፈውስ እለ ታህተ ፍርሀተ ሞት እሱራን ለቅንየት በኩሉ መዋዕለ ሕይወቶሙ” (ሃ አ ፸፭፡፳፯) አርያውን በማሳተፍ የተፈጠረ አዳማዊ ሰውነት ሰይጣን ካዘጋጀው የሞት ቀውስ ያላቅቀው ዘንድ መለኮት ሰውነትን ተሳተፈ።“ እንዳለው በኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ነገረ መለኮት ግንዛቤ ስንመለከተው፤ ወያኔ በየገዳማቱ በየአድባራቱ በየጠረፉ በየከተማው በየገጥሩ ለነጻነቱ ለክብሩ ላንድነቱ በሚታገለው ህዝብ ላይ የሚያነደውን እሳት የነክቡር አንዳርጋቸውን ስጋ ተሳተፉት። የነ አንዳርጋቸውን ጸሐይ አጨልመናታል።
ያንዳርጋቸውን ጨረቃ ወደ ደም ለውጠናታል” በሚለው ፉከራቸው የጨለመብን ቢስልም። አፋችንን ደም ደም ቢለንም “የፎከረ በደም ተነከረ” የሚለው ኢትዮጵያዊው ብሂላችን “ታራሚወችን ያዝናቸው” እያሉ በሚፎከሩ ግብዞች መከሰቱ አይቀርም። ከነሱ ጋራ በመተባበር ከበሮ ተሸክመው በማሸብሸብና ታራሚወች እያሉ ከሚሳለቁት አስመሳይ ካህናት ከተሰበሰቡበት አካባቢ በቀር፤ ቅዳሴያችንና ማህሌታችን ሳይቀሩ የሚለወጡባት ቅጽበት ናት።
፮ኛ በመከራ ጊዜ ቅዳሴያችንና ማህሌታችን ይለወጣሉ።
አዳማዊት የክርስቶስ ሥጋ በህገ አራዊት በሚመሩ ሰዎች ከምትወጋባት ከእለተ ስቅለት በፊት ባሉት ሳምንታት ከበሮ የለም። ሽብሸባ የለም። በጭብጨባ የታጀብ ዕልልታም የለም። ይህም የሚያሳየው ሰባውነትን የምትወከል ያልሰረቀች ያልቀጠፈች ሁላችንንም የምትወክል ኢትዮጵያዊት አካል ስትታሰር ስትገረፍ፤ በጦርና በሾተል ስትወጋ “አብጥሎ ለዘያሜክረነ ወስድዶ እምኔነ ወገስጽ ሁከታቲሁ ዘተከለ ዲቤነ ወብትክ እምኔነ ምክንያተ እንተ ትወስደነ ውስተ ኃጢአት ወባልሀነ በሃይልከ ቅዱስ በኢየሱስ እግዚእነ ጎርጎ ፹፭ የሚፈታተነን አስወግድልን። በመካከላችን የተከለውን የጥላቻ መጋረጃ ቀዳደህ ጣልን። ጠላት በዘረጋት ወጥመድ ተጎትተን ለወያኔ ጥፋት መሳሪያ እንዳንሆን እርዳን” የሚለው ጸሎት ወደ ቅጽበታዊት ውሳኔ ለማሻገር በንባብ ትታወጃለች።
ቅዱስ ጎርጎርዮስ “ንኡ ትርአዩ ዘንተ ቅስፈተ እለ ትሳተፉ ህማመ ቢጽክሙ፤ ወእለ ትትዌከፉ ህማመ ፍቁራኒክሙ”(ጎርጎ ቅዳ ገጽ ፪፻፸፭፡ቁ ፵” እንዳለው፤ ማለትም፦ “ወገናዊ፤ ሰባዊ ፍቅርና ርህራሄ የሚሰማችሁ በወንድማችሁ ላይ የሚካሄደውን ግፉንና ግርፋቱን መከራውን ቀርባችሁ ተመልከቱ።” እንዳለው፤ ሥጋ ለባሽ ሁሉ የቆሰለችውን ሥጋ እንዲመለከት ቅዳሴያችን የሚጣራ ይሆናል። በዚህ ምንባብ ላይ አባቶቻችን ባንድምታ ትርጉማቸው የሚተርኳትን ልጥቀሳትና ወደ ማህሌታችን እሻገራለሁ።
“ብዙ ሰዎች በመርከብ ተሳፍረው ሲሄዱ ፤ ከተሳፋሪዎች አንዱ፤ ሰው በማይደርስበት እቃ ክፍል ውስጥ ገብቶ በመዶሻና በምሮ መርከቡን መቅደድ ሲጀምር ከተሳፋሪዎች አንዱ ደረሰበት። የሰው ሁሉ መስመጥ ታይቶት የዘገነነው ሊያስቆመው ቢሞክር አላቆምም በማለት መርከቡን ማፍረስ ቀጠለ። ተከላካዩ ሰው ባንድ እጁን መዶሻውን በሌላው እጁ ምሮውን እንቅ አርጎ ያዘበት። ትግል ገጠሙ። ምሮው ባፍራሹ መዶሻው በተከላካዩ እጅ ቀረና ከጨበጣ ትግላቸው ተላቀቁ። አፍራሹ ከዚያ ላይ አላቆመም። በእጁ ላይ በቀረው ምሮ ተከላካዩን ለሞት በማያበቃው አካል ላይ ወጋው። ተከላካዩ በፈላ ደሙ በወሰደው አጻፋ ከጁ በነጠቀው መዶሻ አናቱን መታው ሞተ።”
በዚህ ሁኔታ ለሚጠፋው ህይወት ማነው ተጠያቂው? ለሚለው ጥያቄ፤ አባቶቻችን “ወትወርድ አመጻሁ ዲበ ድማሁ” ብለው በሚደግሙት ዳዊት ይመልሱታል።
ማህሌታችን፤ ሽብሸባችንና ዘፈናችን ከዚህ በታች በተገለጹት ቅዱሳት መጻህፍት መሰረት ይለወጣሉ። በከበሮ የሚደረገውን የማሸብሸብ ባህል የጀመረችው የሙሴ እህት ማርያም ናት። ያደረገችውም “ቀኝህን ዘረጋህ ምድርም ዋጠቻቸው በማይለወጥ ፍቅርህ የተቤዠሀቸው ህዝብህ መራሀቸው ወደ ቅዱሱ ማደሪያህ መራሀቻው” (ዘጸ ፲፭፡፲፫) ብላ የገለጸችው ቃል እንደሚያሰየው፤ ከድል በኋላ ነው። በከበሮ በጭብጭባ በይባቤ በዕልልታ የሚቀርብ መዝሙር፤ ማህሌትና ሽብሸባ ኢትዮጵያዊው ባህላችን
እንዲደረግ የሚፈቅደው ከድል በኋል ከሰላም አድማስ ሲደረስ ብቻ ነው።
ዳዊት በትዝታ በስቃይ በሀዘን በልቅሶ ወቅት የዝማሬ መሳሪያወችን በአኽያ ዛፍ ላይ ሰቀልን እንዳለው (መዝ ፻፴፮ )። ኢትዮጵያውያንም የባቢሎውያን ባህርይ ባላቸው ቡድን ጭካኔ፤ ምድራዊ ኑሮ እንደ እንቆቆ ሲመር እንዚራቸውን መሰንቋቸውን በኩሀት ዛፍ ላይ ይሰቅላሉ። በነገራችን ላይ፤ “ኵሀት” የሚባለው ዛፍ ጠንካራና ፈጥኖ የሚበቅል ነው። በዘመኑ የደረሰበትን መከራ መሸከምና ሀላፊነቱን ለመወጣት የተዘጋጀውን ትውልድ የሚገልጽ መሆኑን በቅኔ ትምህርታችን ለሰምነት እንጠቀምበታለን።
ኢትዮጵያ በችግር ላይ ስትወድቅ “በከበሮ የሚደረገው ዘፈንና ማህሌት ጸጥ ይበል። የጨፋሪዎች ጫጫታ ያብቃ። ደስ የሚያሰኘው በገና ረጭ ይበል።” (ኢሳይያስ፳፬፡ ፰) ካለው ከነቢዩ ኢሳይያስ ጋራ ባህላችን ይስማማል። በዚህ ዘመን ያሉ የጥንታዊት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ምእመናን በኢትዮጵያዊነት ሰውነት ላይ የተጋረጠችው የወያኔን ሾተል የምታደርሰውን ህመም ስቃይ ለማዘናጋት፤ አወናባጅ አደናቋሪና አደንዛዥ አዚም አድርገው የሚጠቀሙበትን ዝማሬ፤ የሚደበደበውን የከበሮ ድምጽ ሊቀበሉትና ሊሰሙት አይገባም። ለዚህ መሳሪያ የሚሆኑት የሚሰርቁ የሚዘሙቱ ለትዳር መፍረስ ምክንያት የሆኑ ጳጳሳት፤ ካህናት፤ ሰባኪወችና ቀሳውስት ናቸውና፤ እነሱን አቅፎ መያዝ እጅግ መረገም ነው። ራሳቸው እየዘሞቱ እየሰረቁ እየዘረፉ ”ንስሀ ግቡ አትስረቁ አትዘሙቱ” እያሉ የሚለፈልፉትን መስማትና መቀበል የመከራውን ጊዜ ማረዝም ይሆናል።
ኢዮብ ሰውነቱ በቁስል በተመታ ጊዜ “አጥንቴ ከትኩሳት የተነሳ ተቃጠለች። ስለዚህ መሰንቆየ ለሀዘን እምቢልታየም ለሚያለቅሱ ቃልና ድምጽ ይሁንላቸው (፴፡፴፩ ) እንዳለው፤ ኢትዮጵያዊው ባህላችን አማራው ኦሮሞው ጋምቤላው አፋሩ ኡጋዴው ተራ በተራ ኢትዮጵያን በወረራት የቁስል በሽታ (ወያኔ) ሲመታ ፤ በገና ለሀዘን፤ እምቢልታም ለልቅሶ መቃኘት አለበት።
ትላንት ባገር ውስጥ ከሚደበደቡት ወገኖቻቸው ጋራ ተቀላቅለው መከራውን በመካፈል ላይ ያሉት ክቡር አንዳርጋቸውን የመሳሰሉ ጀግኖች እንደ ወያኔወች ሲሰርቁ፤ የሰው መሬት ሲነጥቁ ድንበር ሲያፈርሱ ተይዘው አይደለም። ምጊዜም የማይቀረውን ሞት ሲሞቱ ሥጋቸውን ሲቀበር ለመብላት የተሰለፉትን የመቃብር ትሎችን በመሻማት ወያኔዎች ሥጋቸውን በመብላት አጥንታቸውን በመቆርጠም ደማቸውን በመጠጣት ላይ እንዳሉ እናውቃለን።
ቅዱስ ዮሐንስ “በእንተ ዘሀደጉ ህገ አይሁድ ወአረሚ። ወገብኡ ሃበ ህገ ትሩፋት። ወመነኑ አዝማዲሆሙ። ወተወክፉ ምንዳቤ ወሥቃይ እምነ አዕርክቲሆሙ እነዘ አልቦ ዘይረድኦሙ”(ድር ፳፩፡፳፰) እንዳለው፤ በህገ አራዊት የሚመሩ አረመኔዎች የሚፈጽሙባቸውን መከራና ስቃይ አስቀድመው በማወቅ የገቡ ጀግኖች ቢሆኑም፤ ወደውና ተዘጋጅተው ስለገቡበት ከራሳቸው ይልቅ በሚወዷቸው ቤተሰባቸው፤ ልጆቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ላይ የሚደርሰው ስቃይና ሰቀቀን በነሱ አካላት ላይ
ከሚደርሰው ሥቃይ እጅግ የከፋ ነው።
ከራሳችው ሞራል ጽናትና ከፈጠሪ በቀር በዚህች ቅጽበት የሚያካፍሉትና ሚታመኑት የላቸውም። ለሰው የሚያካፍሉትን ጨርሰዋል። ቢኖሩም ሁሉት ነገሮች ናቸው። አንደኛው የድምጻቸውን ማሚቶ እንዲያስተላልፍላቸው ላየሩ ለጫካውን ለዱሩ ድምጻቸውን ማሰማት ነው። ሌላው የቤተ ክርስቲያናችንን ድምጽ የሚያውቁና የተረዱ፤ ለጽድቅ፤ ለእምነትና ለሰው ልጅ ክብር ሲሉ የተሰደዱ ከዚህ በታች የጠቀስኳቸውን መጻሕፍት የተረዱ የእግዚአብሔር ካህናት ብቻ ናቸው።
የስደተኞች ካህናት ድምጽ
“ንህነሰ እለ ተሰደድነ በእንተ ስምከ ወኮነ ሕብልያነ እምኀቤሆሙ ለዕልዋን ረዐየነ በሣህልከ ከመ ነሀድፍ ልቦሙ ለመሃይምናን” አትና ፻፴፰ ማለትም፦ በስደት ላይ ያለን ላሳዳጆቻችን ተበዝባዦች ሆን። በስደት ላይ ሆነው በመበዝበዝ በመቁሰል ላይ ያሉትን እንድናጽናና በምህረትህ ጽናቱን ብርታቱን ስጠን” ብለን ድምጻችንን ከፍ በማድረግ እንድንጮህ ቅዳሴያችን ያዝዘናል።“በእንተ ስዱዳን ናስተበቁዕ። ከመ እግዚአብሔር የሀቦሙ ትእግስተ፡ ወትምህርተ፡ ሠናየ ወጸጉ ጻማሆሙ(ሥ ቅ ገ ፵፫፡፺፩) ስደት የትእግስትን እና የልምድ ትምህርት ቤት ነው። የተሰደደ ሰው፤ ካልተሰደደ ሰው ይልቅ ስለዓለም ብዙ ያውቃል፤ የሚሰደደውም ጩኸቱ የሚሰማበት ተራራ ለመፈለግ ነው። በስደት ያለ ሰው ካልተሰደደው ካልተሻለ፤ ቀሪውን ህዝብ ወክሎ ለመመስከር ድፍረቱ ትእግስቱና እውቀቱ ከሌለው፤ ለሆዱና ለራሱ ምቾት ሲል ብቻ ከመነኩሰ አታላይ ሰው የተሻለ አይሆንም። አገሩ መንደሩን ወገኑን ትቶ የተሰደደ ሰው፤ ስለ ህዝቡ ስለወገኑ ምስክርነቱን ከነፈገ አግብቶ እንዳልወለደ ሰው፤ መንኩሶ እንዳልጸደቀ መነኩሴ መሆኑ ነው።
ሰው በተለይም ካህናት አገራቸው በህገ አራዊት እጅ በምትወድቅበት ጊዜ የሚሰደዱት፤ “ተዘከር እግዚኦ ለዛቲ ሀገር ወኩሎን አህጉር ወበሀውርት ወደሰያት ወአዕጻዳት ወምኔታት ወእለ በርትዕ ሃይማኖት ወኩሎሙ እለ የሀድሩ ውስቴቶን” ባስል ፶፬ እያሉ በተወለዱባት አገር ያሉትን በየወረዳዎች አውራጃዎች፤ ገዳማትና አድባራት ላይ የሚደርሰውን መከራ እያሰቡ በየደረሱበት እንዲመሰከሩት የውዴታ ግዴታ ሳይሆን፤ የግዴታ ግዴታቸውን ለመወጣት ብቻ ነው።
ሰብሮ ገቦች የመንፈስ ዲቃላወች ካልሆን በቀር፤ በእውነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነገረ መለኮት መምህራን ጉባኤ የተዳሰሰን ከሆን፤ ቀኑ በህዝቡ ላይ ሲመሽ፤ ሸክሙ ሲከብደው፤ ሰባዊነቱ ሲናድበት “ኢትግድፉ እንከ ሞገስክሙ እንተ ባቲ ትረክቡ ብዙኀ እሴትክሙ”( ድ ቅ ዮ ፳፩፡፵፱) ተብሎ የተሰጠንን ክህነታዊና ሰባዊነት ሀላፊነት፤ በሉቃስ ወንጌል እንደተ ጠቀሱት ካህንና ሌዋዊ ገሸሽ በማድረግ፤ እንዳላየን ሆነን ለማለፍ ለህሊናችን እረፍት አይሰጠውም።
“ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና ስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ ቀንም በድንገት እንዳይመጣ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ”(ሉቃ ፳፩፡፴፬) ብሎ ክርስቶ ያስጠነቀቀውን ረስተን በጥላቻ በቂምና በነፍሰ ገዳይነት ከተመረዘው ወያኔ ጋራ በመተባበር፤ የመረረችውን የመርዝ ጽዋዕ ህዝባችንን ተራ በተራ ለማጠጣት ወያኔ ጠንስሶ የደፈደፈውን መራራውን ጽዋዕ ባለወር ባለሳምንት እያልን አካፋዮችና አቀባባዮች እንዳንሆን የምናስብባት ወቅት ናት።
፯ኛ ከወያኔ ጋራ የጽዋ ማህበርተኛነታችሁን አቁሙ
ወያኔ በመሰረተው የጽዋ ማህበር የሚካሄደውን ስርአት የሚቃወሙትን ንጹሐን ዜጎች “ታራሚወች” በማለት ቃለ መርገም የሚያሰራጩ፤ የዝሙት የስርቆትና የማታለል ልምድ ያላቸውን ሰዎች ቀሳውስት መነኮሳት ቆሞሳት ጳጳሳት በመካከላችን እንደሰገሰጉብን ተደጋግሞ ተነግሯል። ታይቶም ተረጋግጧልም። “ቤተ ክርስቲያኗ ለረዥም ዘመናት በህዝቡ አዕምሮ ላይ ስትተቀርጸው የኖረችውን ብሄራዊ የኢትዮጵያነትን ስሜት ከትግራይ ህዝብ አዕምሮ ጠራርጎ በጠባቡ ትግሬአዊነት ስሜት በመተካት የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዘት እያጠበቡ ራሷን ቤተ ክርስቲያኒቱን መምታት” እና “ኢትዮጵያዊነትን ከትግራይ ህዝብ ጭንቅላት አጥቦ ማውጣት።” ነው። በማለት ወያኔ ያቀደውን ዶ/ር አረጋዊ በርሄ እንደገለጹት በኢዛናና በነ አብርሃ አጽብሀ ልብ የተተከለችውን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከአኩስም ነቃቅሎ በማስወገድ እና፤ በትግራይ ህዝብ ልብ ላይ ደግሞ በራሱ ታሪክ እንዲዘምት የሚያደርግ አዚም የተከለ፤ በትግራይ ህዝብ ስም ኢትዮጵያዊነትን ለመደምሰስ የተዘጋጀ የጽዋዕ ማህበር እንደሆነ በትግራይ ልጆች በነ አቶ ገብረ መድህን አርአያ ተደጋግሞ ተገልጿል።
Jonathan Fox እና Shmuel Sandler የተባሉ የ social science ሊቃውንት የሚነድፈውን በመፈለግ እንደሚቀነዘነዘው እንደቀትር እባብ፤ ወጥመድ የሚያዘጋጁበትን ሰው የሚነድፉበትን መርሆ የሚቀርጹትን፤ በቀረጹት መርሆም ሰው እየነደፉ የሚገሉትን ለመግለጽ “policy makers from other states can undermine policy by branding them as against religious precepts as well as use religion to mobilize their own population against the policy” እንዳሉት፦የወያኔ አመራር ከመጀመሪያ ጀምሮ የዘረጋው መርሆና የተጓዘበት መንገድ እነዚህ ሊቃውንት ከተናገሩት ጋራ እጅግ
የተመሳሰለ ነው።
እርቅ ሳይፈጸም የፓትርያርክ ምርጫ እንዳይደረግ እየተባለ አቡነ ማትያስን ለመክተት እነ አቶ ስብሀት ነጋ የተዋደቁት “የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዘት እያጠበቡ ራሷን ቤተ ክርስቲያኒቱን መምታት ነው።” ብለው በቀረጹት መመሪያቸው ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲመቱ፤ ህዝቡን ሲያንገላቱ የሚተባበራቸውን ግለ ሰብ ለማስቀመጥ ነበር። “የስልጠናውም ይዘት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጠቅላላ መዋቅራዊ አስተዳደር በትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት ባለሟሎች መተካትና በቤተ ክርስቲያኒቱ አካባቢ የትግርኛ ቋንቋ እንዲሰፍን ማድረግ ነው።” ብለው የቀረጹት የትግራይንም ህዝብ ጭምር ይዞ የሚጠፋውን መርሆ ቤተ ክርስቲያናችን እንዳትቃወማቸው ለማፈን ነበር። እንደነ አቶ አንዳርጋቸው ያሉት ለቁርጥና ለፈታኝ ቅጽበታዊት ችግር ቅጽበታዊት መፍትሄ ለመስጠት ሲነድፉና፤ በአገር ውስጥም ያለውን ዜጋ ሁሉ እንደ ዘንዶ ውጠው እስኪጨርሱ የሚታዛባቸው እንዳይኖር ነው።
ሆኖም ከላይ ጀምሮ እስከ ታች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሰገሰጔቸው ሰዎች፤ በህዝቧ ላይ የሚፈጽሙትን ግፍ ቤተ ክርስቲያናችን እንዳትናገር ቢያፍኗትም፤ “Given all of this, playing the religion card can backfire on a policy maker.” እንዳሉት፤ የሚቃወመው ህዝብ ሲነቃና አማራጭ ሲያጣ ወያኔዎች የሚያደርጉትን ለማድረግ ከዳር እስከደር ከተነሳ ችግሩ የሚከብደው በራሳቸው ላይ ነው። “polisy makers must be aware that others may play the religion card against them.” እንዳሉት፤ የብዙኃኑን እምነትና ባህል መሳሪያ በማድረግ ብዙኃኑን ለማጥፋት የሚያስቡ ሰዎች፤ ብዙሀኑ እነሱ ያደረጉትን ተንኮል ከራሳቸው ተምሮ በነሱ ላይ መገልበጡን አለማጤናቸው፤ በገደል አፋፍ ላይ ያለውን ሳር ብቻ በማየት ገደል ከሚገባው እንስሳ ያልተለዩ እንስሳት ሊሆኑ አይገባቸውም ነበር።” ለነጻነታቸው ለአገራቸው በሚታገሉት የኢትዮጵያውያን ላይ ወያኔዎች ታራሚ የሚል ቅጽል በመስጠት የሚፈጽሙትን ደባ እነ አባ ማትያስ ከመደገፍ ይልቅ፤ በራሳቸው መገልበጡን በማስገንዘብ ወያኔዎች
የሚፈጽሙትን ደባ እንዲያቆሙ በገሰጿቸው ነበር።
“አባት እንድሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ ህዝብ መረጠኝ” የሚሉት አባ ማትያስ፤ መረጠኝ የሚሉትን ህዝብ የሰበሰበች ቤተ ክርስቲያን ህዝቧ አሁን የገጠመውን መሳይ ፈታኝ ቅጽበት ሲገጥመው እንዲመራበት “ወአንኂ ለኩላ ነፍስ ዕጽብት ወእለ እሡራን በመዋቅህት ወእለ ሀለው ውስተ ስደት ወጼዋዌ። ወእለ እኍዛን በቅኔ መሪር አምላክነ አድህኖሙ በምህረትከ” ብላ በቅዳሴያችን ላይ የመዘገበችውን መሰረት በማድረግ፤ መረጠኝ የሚሉትን ህዝብ ከማጽናናትና ወያኔን ከመገሰጽ ይልቅ፤ ወያኔ ጽፎ የሰጣቸውን አራዊታዊ መመሪያ በመከተል ላይ ናቸው። ወያኔ የተጠቁትን ኢትዮጵያውያን ለማስጠላት ታራሚና አሸባሪ የሚል ሸፍጠኛ ቅጽል እሳቸውም ተቀብለው በማጽደቅ ለዓለም በማስተጋባት ላይ ናቸው።
እነ አባ ማትያስ እስካሁን የሄዱበትን ተቃራኒ መንገድ የማይለወጡ መሆናቸው ከታወቀ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በተለይም በስደት ያለን ካህናት “ወደ ፈተና አታግባን” የምትለው የዘወትር የጸሎት የተሸከመችውን ሀተታ ከዘወትሩ አመለካከታችን በተለየች መንገድ የምንተረጉምባት ቅጽበት ላይ መሆናችንን መረዳት አለብን።
በዚህ ወቅት በስደት ላይ ያለን ካህናት ቅዱስ ጎርጎርዮስ “ንኡ ትርአዩ ዘንተ ቅስፈተ እለ ትሳተፉ ህማመ ቢጽክሙ፤ ወእለ ትትዌከፉ ህማመ ፍቁራኒክሙ”(መ ቅዳ ገጽ ፪፻፸፭፡ቁ ፵” እንዳለው፤ ማለትም “ወገናዊ፤ ሰባዊ ፍቅርና ርህራሄ የሚሰማችሁ በወንድማችሁ ላይ የሚካሄደውን ግፉንና ግርፋቱን መከራውን ቀርባችሁ ተመልከቱ።” እያልን በወያኔ ግርፋት ላይ ያለችውን ሰባዊት አካል እንዲመለከት ለሚጋራት ሁሉ ደቂቀ አዳም ጥሪያችንን እንድናቀርብ፤ ክህነታችን፤ ሰባዊነታችን፤ ዜግነታችንና ስደተኞች መሆናችን ያስገድዱናል።
ቄርሎስ “እስመ ደቂቅ ተሳተፍዎ በሥጋ ወደም ወውቱኒ ዓዲ ተሳተፈ እሎንተ ከመዝ ከመ በሞቱ ያብጥል ዘበእዴሁ ሙአተ ሞት፤ ዘውእቱ ሰይጣን ወይፈውስ እለ ታህተ ፍርሀተ ሞት እሱራን ለቅንየት በኩሉ መዋዕለ ሕይወቶሙ” (ሃ አ ፸፭፡፳፯) እንዳለው፦ አምላክ አርያውን በማሳተፍ የፈጠረው አዳማዊ ሰውነት ሰይጣን ካመጣበት መዘዝ (የሞት ቀውስ) ያላቅቀው ዘንድ ሰው መሆንን ተሳተፈ። ይህን መሰረት በማድረግ በኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ነገረ መለኮት ግንዛቤ፤ ችግርን ማስወገድ የሚቻለው በተሳትፎ ግብር እንጅ በጸሎት ብቻ አለመሆኑን ከመቼውም በበለጠ ግንዛቤ ተርጉመን ለህዝባችን እንድናቀርባት ይህች ቅጽበታዊት ወቅት ታስገድደናለች።
ከጾም ከጸሎቱ ጋራ መጥምቁ ዮሐንስ የወሰዳት ቅጽበታዊት ርምጃ። እመቤታችን የተናገረችውን ቃል እንዳዘቦቱ ቁጭ ብለን የምንደግምበት ወቅት አይደለም። ከላይ እንደገለጽኩት መርከበኛው ተከላካይ፤ በያዘው መዶሻና መሮ መርከቡን ይቀድ በነበረ ሰው ላይ እንደወሰዳት ቅጽበታዊት ርምጃ፤ ወያኔ በዚህ መርሆው አገራችንና ቤተ ክርስቲያናችንን አፈራርሶ ሁላችንንም ለማስመጥ የያዘውን መሮና መዶሻ ለመንጠቅ ወቅቱ እየጋበዘን ነው። ወያኔዎች በነ አንዳርጋቸው አካላት ላይ እየተከሉ ያሉት ሾተል ነርቫችንን
እየቀደደው ነው። “ወደ ፈተና አታግባን” የምትለውን የዘወትር የጸሎት የተሸከመችውን ሀተታ ከዘወትሩ አመለካከታችን በተለየች መንገድ የምንተረጉምባት ቅጽበት አሁን ናት። በከበሮ በጭብጨባ በዕልልታ የምናቀልጠውን ሽብሸባና ማህሌት ቀይረን በመሰቃየት ያሉትን ሁሉ ወገኖቻችንን በማሰብ “ይእቲ ሥጋ” እያሉ በመንፈሳቸው እንደ አንጎራጎሯት አባቶችችን፤ እኛም በዚህች ቅጽበት ልናንጎራጉራት ይገባናል።
እኛ ካህናቱም ተገልጋዩ ምእመናንም ከላይ የተገለጸውን ቤተ ክርስቲያናችን ጽፋ ያስቀመጠችልንን መመሪያ በአዕምሯችን ይዘን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሂድ! ካህናቱ ከጥንታዊት ቤተ ክርስቲያናችን መርሆና ነገረ መለኮት ጋር የተጋጩ መሆናቸውን ለመመዘን ለመታዘብና ትግላችንን ከነሱና ከራሳችን ለመጀመር ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሂድ። ወያኔዎች የዓለምን ቀልብ ስበው ከኛ ስሜት ጋራ ያዋሀዱትን እነ አንዳርጋቸውን ከበሉ፤ በገጠር በከተማ በየገዳማቱና በየደብሩ ያሉትን ዓለም ያላወቃቸውን ስንቱን
እንደበሉትና እየበሉትም መሆናቸውን በአቶ አንዳርጋቸው ቁስል ለዓለምም ለማሳየት አሁን ያለን እድል ከመቸውም የበለጠ ነው።
ወደ ቤተ ክርስቲያናችን የምንሄደው እንደቀድሞው በልማድ ከግብር የተለየ ቅዳሴ ለመስማት፤ የነ መጥምቁ ዮሐንስን ቅጽበታዊት መልእክት የሚሸፍነውን አደናቋሪ ከበሮና ስብቀት ለማዳመጥ አይሁን። በቤተ ክርስቲያን ያደጉ በመምሰል ግእዙ የተሸከመውን ምስጢር ሊረዱ ይቅርና፤ ተነሹንና ወዳቂውን ለማወቅ የሚያግዘውን ውርድ ንባባ ያልተማሩ፤ የዘመናችን ሰባኪወች፤ ዘመኑ ያበቀላቸው ነጋዴና ጥራዝ ነጠቆች፤ በማያውቀው ህዝብ ፊት፤ አዋቂ መስለው በመቆም አንዳንድ ግስ በመቀላቀል መስለው የገቡ
ከሚዘሙተው፤ከሚሰርቀው ጳጳስ ጋራ ተስማምተው ህዝቡን በራሳቸው ጩኸት የሚያደነቁሩ መሆናቸውን ተገንዘቡ! ተመልከቱ! ታዘቡ! አወቅንባችሁም በሏቸው!
እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ! የዘመናችን ሰባኪ፤ ጳጳስ፤ ቄስ በፊታችሁ ቆመው በሚቀላምዱት አትታለሉ፤ ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያናችን ምን ትላለች? ምን ጽፋለች? ወደ ሚለው ተሻገሩ? ቤተ መቅደሱ የወያኔ መርሆ ማስተጋቢያ፤ ከበሮው ማደናቆሪያ፤ ማህሌቱ ማፍዘዣ፤ ቅዳሴው ማደንዘዣ፤ በመሆን ላይ እንዳሉ ተገንዘቡ። የሰውነትን ተፈጥሮ የሚያጠኑ መምህሮቻችን ሰውነታችንን ቅጽበታዊት እሾህ ስትወጋን ቅጽበታዊት ርምጃ የምትወስድ “reflex the negative feedback system” የምትባል ተፈጥሯዊት ነርብ አለችን ከሚሏት ጋራ፤ “ወደ ፈተና አታግባን” የምትለውን መንፈሳዊት ስሜታችንን በማዋሀድ ወያኔ አገራችንንና ቤተ ክርስቲያናችንን የወጋበትን ጦር፤ በሰውነታችን ላይ የተከለውን ሾተል ለመንቀል ይህች ቅጽበት ታስገድደናለች። እርስ በርሳችን ከመጠራጠር፤ ከምንጠረጥራቸውም ጋራ አብሮ ከመተሻሸትና ከመድበስበስ ይልቅ አስመስለው ገብተው የሚያደነቁሩትን ለመለየት ይህችን ጦማር እያባዛችሁ በፊታችሁ ቆመው እንቀድስላችሁ! በከበሮ በእልልታ በጭብጨብ እንዘምርላችሁ! ወንጌል እንስበክላችሁ ለሚሉት ስጧቸው። ከቻሉ ይንቀፉት ይተቹት። ካልቻሉ “ወደ ፈተና አታግባን” የምትለው ሀረግ በተሸከመችው አንድምታ እየተመሩ ከወያኔ ጋራ ያላቸውን የጽዋ ማህበር አቁሙው፤ ከተጠቃው ዜጋቸው ጋራ ይሰለፉ!
ይቆየን
የቀሲስ አስተርአየን ጦማሮች ለማንበብ ከፈለጉ ከዚህ ቀጥሎ ወደ ተገለጸው ድረ-ገጽ ይሻገሩ::
http://www.medhanialemeotcks.org/