Thursday, 26 February 2015

የዓለምዬ!


የዓለምዬ!


Wednesday 25 February 2015

ብርሀኔ ጨለመ፣ ዓይኔ ደም አነባ
የዓለሜን ሸኝቼ፣ ባዶ ቤት ስባ።
የዓለም መከታ፣ የቤቴ ምሰሶ
ባዶ ሜዳ ቀረኹ፣ ግንቡ ተደርምሶ።
ጸጥታው አስፈሪ፣ ግራ የሚያጋባ
ዝምታን መረጠች፣ ባለቅስ ባነባ።
ከጎኔ ስትለይ፣ አልሄድ ነገር ወደሷ
አሁን ማን ይበለኝ፣ “ወንድምዬ!” እንደሷ።
አይቼአት በመጣኹ፣ እንደ ንሥር በርሬ
ባዶነት ተሰማኝ፣ የዓለሜን ቀብሬ።
“እወድህአለሁ!” እያለች፣ ሆዴን ስታባባ
ኬንሳል ግሪን ተኛች፣ የኔ ውብ አበባ።
ጥላኝ ብትሄድም፤ አድርጋኝ ብቸኛ
የዓለም መከታ፣ እህቴ ናት ጓደኛ!
ሁለመናዬ የሷ፣ አዕምሮዬ ርስቷ
ልቤ ሁኖላታል፣ የዘልዓለም ቤቷ።
“እህህን" በሆዴ ይዤ ፣ ሳልተኛ ፈዝዤ፤
“ኑሮ” ጀምሬአለሁ፣ ትዝታዋን ይዤ!



መግቢያ

የዓለምዬ  ለዚች ከንቱና አስቀያሚ ዓለም ለብቻዬ ትታ ከተሰናበተች፣ ዛሬ 40 ቀ ሞላት። 40 ቀናት አዘንኩላት! 40 ቀናት አነባኹላት። ግን ከማትመለሰው ቦታ የመኼዷን ተገንዝቤ፣ በዚህች ቀን የነጠፈውን ብዕሬን በሷ ትዝታ ለጀምር አነሳኹ። ከሌላ ጌዜ አጻጻፌ የተለየ ቢሆንም፣ ፍቅርን አግኝቶ ማጣት እንዴት እንደሚከብድ የሚገባችሁ፣ የዓለምዬን የምታውቋትና የምትወዱ ሁሉ እንድታነቡልኝ እጋብዛለሁ።


 ማውጫ

1)    የዓለምዬ አጭር የግል ትዝታዬ
2)   የዓለምዬ አጭር የሕይወት ታሪክ
3)   የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ መልዕክት (ኒው ዮርክ)
4)   የወንድም ደጀን ግጥም
5)   የወይዘሮ ሒሩት መስፍን መልዕክት ከሎንደን
6)   የወይዘሪት የጎንደር ጌጥ ግጥም
7) የጋዜጠኛ ደረጀ በጋሻው ግጥም
8)  የወንድማችን ሳሙኤል አድማሱ እና የእህታችን የወይዘሮ ዙርያሽወርቅ ለየዓለምዬ ማስታወሻ

 1)    የኔዪቱ የዓለም መከታ

የዓለምዬ፣ ክብር ያቀዳጀችኝ የሕይወቴ አጥር ነበረች። የዓለም መከታ፣ እንደስሟ መከታዬ ነበረች። መመኪያዬ ነበረች። ብርሀኔ ነበረች። እህቴ ነበረች! የእናቴ ምትክ ነበረች። መተኪያ የማይገኝላት የሕይወቴ ሙላት ነበረች። የዓለም መከታ ጋርዳቸው፣ በጣም ስለምትወደኝ፣ የቤተሰቧን ስም (family name or surname) ሳይቀር በኢትዮጵያውያን ዘንድ ባልተለመደ አኳኋን በሥነ-ሥርዓት ወደ “መኰንን” የቀየረች ግማሽ አካሌ ነበረች። ይኽቺ ፍቅሬ ከጎኔ በሞት ስትለየኝ፣ ግማሽ ሰውነቴ ተገምሶ እንደሄደብኝ ነበር ያመመኝ። ባዶነት ነበር የተሰማኝ። መያዢያ መጨበጫ ነበር የጠፋኝ። ሰማይና ምድሩ ነበር የተገለባበጠብኝ። እሷ ቀድማኝ ጥላኝ በመሄዷ መኖርን ነበር ያስጠላኝ። ያም ሆኖ ግን፣ በእግዚአብሔር ዕምነቴና የወገኖቼ ክብብ-ክብብ ማድረግ ይኽቺን አስቀየሚ 40 ቀናት ልዘልቃት ቻልኩ።

የዓለምዬና እኔ አብረን በእግዚአብሔር ፊት “ሞት ካልለያየን አንለያይም” ብለን ቃል ተጋብተን የኖርንባቸው 12 ዓመታት ከሰባት ወራት፣ በጣም ጣፋጭ ጌዜያት ነበሩ። እኔ እንደሚስቴ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ እናቴ፣እንደ እህቴ እና ከሁሉም በላይ እንደጓደኛዬ ነበር የማያት። በዚህ ላይ፣ ለኢትዮጵያ አገራችንና ለሕዝቧ ነጻነት ለምናደርገው እንቅስቃሴ፣ የትግል ጓደኛዬ ናት። ወደሥራ ካልሄድን በስተቀር ለደቂቃ እንኳን አንለያይም ነበር። በአጭሩ ዓለሜ ነበረች፣ ዓለሟ ነበርኩኝ።

የዓለም መከታና የኔ ትዳር፣ ብዙውን ጌዜ ሳቅና ጨዋታ የሞላበት ነበር። ያ ማለት አንጋጭም፣ አንጯጯህም ማለት ዓይደለም። ግን ዝም ብሎ አንዳንዴ እንዲህ አድርጊ፣ እንዲህ አድርግ ዓይነት ንግግር ነው እንጂ የከፋ አልነበረም። ከኹሉ ከኹሉ ኹለት ጊዜ የተጯጮኽናቸው ነገሮች አይረሱኝም። አንድ ጊዜ አንድ ትንሽ ጥፋት አጠፋኹና ያለወትሮዋ ንዝንዝ አደረገችኝ። “ይቅርታ” ብጠይቃት አልሰማ አለችኝ። እንዲያውም እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ከዚህ በኋላ ካሳየኸኝ ጥዬ ነው የምሄደው አለችኝ። ዝም ብላ ለአፏ እንደምትለው ስለማውቅ ዝም አልኳት። እሷ ግን ቀጠለች። “አሁን እዚህ ጉልት አድርጌህ ብሄድ፤ ምን ትኾናለህ?” አለቺኝ እየተምሰከሰከች። ቀና ብዬ አየኹአትና፣ “አይ ምንም አልንም የዓለምዬ” ብዬ፣ በዘሪቱ ከበደ ዜማ፡ “በቃ ቁጭ ብዬ ‘አትሂጂብኝ፣ ወደ ደዴሳ፣ እንዳይበላሽ አዞና አንበሳ’ እያልኩ አጎራጉርልሻለኹ” አልኳት። ሆዷን እስኪያማት ድረስ መሬት ላይ ወድቃ በሳቅ አወካች። ሳቁ ሲበርድላት፣ “በቃ አንተን ማናደ አይቻልም ማለት ነው?” ብላኝ ምግብ ልታመጣልኝ ወደ ጓዳ ገባች። ሌላ ቀን ደግሞ፣ ያለምንም ምክንያት ከመሬት ተነስታ ትነዘንዘኝ ገባች። ዪኝ ብላት አላቆም አለችኝ። ያለወትሮዬ ተበሳጨና፣ እንደብራቅ ጮኹኩባት። በጣም ደንግጠች። ዓይኗን ቁልጭ ቁልጭ ቁልጭልጭ አደረገች። “ወንድምዬ! እኔ በሰው ላይ ስጮ እንጂ ሰው በኔ ላይ ሲጮኽ እኮ አልወድም!” ብላኝ አረፈችው! ሆዴን ይዤ እኔም በተራዬ በሳቅ አወካኹ። የኔ ምስኪን፣ የኔ የዋህ! እንግዲህ፣ የኛ ኑሮና ትዳር ይኸን ይመስል ነበር። የዓለም መከታ፣ ለኔ ያላትን ፍቅር ማንም ወንድ የሚመኘው ነው። ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ወደደችኝ። ፍቅሯ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻው ሳይቀዘቅዝ፣ እስከወዲያኛው ወደደችኝ። እኔም እንደዚኹ።

የዓለምዬና እኔ ብዙ አገሮችን አብረን ጎብኝተናል። ከነዚህ መሀል፣ እስራኤል፣ ስፔን እና ቡልጋሪያ ይገኙበታል። የእስራኤሉ ጉዞአችን መንፈሳዊ ስለሆነ፣ የዓለምዬ የጌታችን የመድኃኒታችን ሥጋ ከመስቀል ወርዶ የተገንዘበትን ጠፍጣፋ ድንጋይ፣ አስቀደማ ባዘጋጀችው ንጹህ እራፊ ጨርቅ ስትፈትግ ያነሳኹዋት ፎቶግራ እዚህ ላይ ይታያል።



የዓለምዬ በዓለም ሁሉ ዙራ፣ አገር መጎብኘትን የማትጠግበው ሕልሟ ነበር። የሚከተለው ፎቶግራም ደግሞ፣ ስፔን ውስጥ፣ ቴርሞሊኖስ በሚባል የዕረፍት ቦታ ስትዝናና ያነሳኋት ፍቶግራፍ ነው።




በዚህ አጋጣሚ በዚህ የጭንቅ ጌዜዬ ላልተለያችሁኝ ወዳጅና ዘመዶቼ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ የዛሬ ሁለት ዓመት ከ8 ወር ያልታሰበ አደጋ የዓለም ላይ ሲደርስ ሩጠው ለደረሱልኝና መንፈሳዊ ብርታት ለሰጡኝ፣ ለቀሲስ መስፍን ምስጋና አቀርባለሁ።

ከሞተችብኝ በኋላ ከለንደንና ከሌሎች ከተሞች ሳይቀር በብዙ መቶ የምትቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኛ ወገኖቼ፣ ረቀቱ ሳይገድባችሁ ኤይልስበሪ ድረስ እየተጓዛችሁ ያጽናናችሁኝን ወገኖቼን ምን ብዬ፣ በምን ቋንቋ እንደማመሰግናችሁ ግራ ይገባኛል። በደፈናው እግዚአብሔር ይኸንን ልፋታችሁን ከጽድቅ ይቁጠርላችሁ። በዕምነት ወንድሞቼና እህቶቼ የሆናችሁት፣ ገንዘባችሁን አውጥታችሁ ከገዛችሁት ቤተክርስቲያናችሁ ተገፍታችሁ በድንኳን እግዚአብሔርን የምታመልኩት የደብረ-ጽዮን ቅደስት ማርያም ወታደሮች፣ አኮራችሁኝ። እግዚአብሔር ከጎኔ እንደ አንድ ሰው እንደቆማችሁ ከየአንዳንዳችሁ ጋር ሰየፈ ሥላሴን መዝዞ ይቁም! የነጌታቸው በሻህ ውረድ ቤተሰብ በሙሉ ቤተሰቤ ቢሆንም ስለአንድ ሰው መናገር እፈልጋለሁ። እኔም እንደነሱው ወንድም ጋሻ ልበለው። ስለአቶ ተሾመ ሰይፉ! አቶ ተሾመ ይኸ አደጋ በደረሰብኝ ዕለት ሥራ አድሮ ለመተኛት ቤቱ ሊገባ ሲል ነበር ዜናውን የሰማው። በቀጥታ ወደኔ ቤት መጥቶ ሲያስተዛዝነኝ፣ ሲያስተባበር፣ ሲያስተናግድ ነበር የዋለው። ሳይተኛ በቀጥታ ሥራ ገብቶ ሲሠራ አደረ። 36 ሰዓት ቁጠሩልኝ። ሲነጋ ሊተኛ አልሄደም። ዳሩ ግን፣ ትሑቱንና ተወዳጁን አባታችንን፣ ጀኔራል ኃይሉን ይዞ ቀኑን በሙሉ የቀብሩን ቦታ አብረው መርጠው፣ ተዋውለው፣ ከቀብር ባለሙያዎች (Funeral Directors) ተዋውለው፣ ተፈራርመው ካበቁ በኋላ ጄኔራል ወደቤታቸው ሲመለሱ ወንድም ጋሻ ተሾመ አሁንም ሳይተኛ ወደ ማታ ሥራው ተመልሶ ሲሠራ አደረ። በጠቅላላው ከ72 ሰዓት በላይ ባለመተኛቱ እኔን ከመታኝ ኃዘን ይበልጥ የሱ የእንቅልፍ እጦት ጤንነቱ አደጋ ላይ እንዳይወድቅብኝ የበለጠ አሳስቦኝ ነበር። ዳሩ ግን እግዚአብሔር ከለላውን አደረገለት። አሁን ለዚህ ሰው ምን ምስጋና ይበቃዋል? እንዲያው ዝም ነው!

ከሎስ አንጀለስ ድረስ የመጣው ወንድማችን እንጂነር ታደሰ በዛብህና፣ ከካናዳ ድረስ በርሮ የመጣው ወንድማችን ተሰማ ቢተው የዓለም መከታን ከሕጻንነቷ ጀምረው ያሳደጓትን የፊታውራሪ በዛብህንና የወይዘሮ ዳሞትላንቺን ቤተሰብ በሚገባ ወክለዋል። ተሰማን ከአዲስ አበባ ጀምሮ ባውቀውም፣ የታደሰን ማወቅ፣ የዓለም መከታ ኃብት እንደጨመረችልኝ እቆጥረዋለሁ። የዓለምዬ እንኳን በቁምሽ በሞትሽም እንዳስከበርሽኝ ነውና ከልቤ እወድሽአለሁ!

ወንድሜ፣ ጓደኛዬ እና የጭንቅ ቀን ደራሼ፣ ደራሲ አበራ ለማ፣ የዓለምዬ ታማ ለመጠየቅ ከኖርዌይ መምጣቱ እንዳለ ሁኖ፣ ስትቀበርም ከኦስሎ ድረስ በርሮ መምጣቱ በሀዘን የቆሰለውን ልቤን አሽሎታል። አመሰግናለሁ ከማለት በስተቀር ምን ማለት እችላለሁ? በዓለምዬ አማርኛ፣ “የዘመድ አውራ ያድርግልኝ!”

ሰንቱን አመስግኜ እዘልቀዋለሁ። ምግብ ሲያበስሉ፣ ቢቱን ሲያጸዱ፣ እግንዳ ሲያስትናግዱ፣ ቤታቸው ልጆቻቸውን ጥለው እዚሁ ከኔ ጋር ወለው ያደሩ፣ እነ ብርሀን፣ እነወይንሸት፣ እነ ዘገየ፣ ግርማ፣ ትዕግስት፣ አገኘኹ፣ አቢዩ፣ ፍሬሕይወት፣ ታደለች፣ ዶክተር ዮሕንስ፣ ዶር ብርሀኑ፣ ገረመው፣ ሰላም፣ ምስራቅ፣ ወንድሜ ግርማ ተመስገንና ብለቤቱ ትዕግስት ... ኧረ ስንቱ! በደፈናው ልሂድበት እንጂ! አመስግናለሁ።


የየዓለምዬ ቀብር የተፈጸመው ዓርብ ዕለት 16th February 2015 ነበር። የሞተችውም ዓርብ፣ የተቀበረችውም ዓርብ! ይኽች ውብ አባባ፣ ሞቷን ከጌታዋ ጋር ያመሳሰለችው ትመስላለች። ታዲያ ዕለቱ የሥራ ቀን ቢሆንም፣ ቤቱ የረም ሰው ያለ አይመስልም። ማጋነን ባይሆንብኝ፣ ለኢትዮጵያዊ ቀብር ቀርቶ ለሀገሩም ሰው ቀብር ይኸንን የሚያክል ሕዝብ ሲወጣ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም! የመጣው ደግሞ ዘር፣ ቀለም፣ ሀይማኖት ሳይለይ ነው። ፍረንጆቹ በጣም ነበር የተደናገጡት! የመጣው ሰው ሁሉ ጥቁር ልብሶ ወንዱም ሲቱም ዕንባውን እንደጎርፍ ነበር ሲያወርደው የነበረው። እኔን ጓደኛዬና ወንድሜ አገኘሁ፣ እንደምንም ገፋፍቶኝ የአሥራት መኪና ውስጥ አስገብቶኝ፣ ዕንባዬን ጠራርጌ አካባቢዬን ሳየው የቀብር ግቢው ሕዝብ በሕዝብ ተጥለቅልቆ ሲጨናነቅ ለመጀምርያ ጊዜ ሳይ፣ “ዛሬ ስንት ቀብር ነው ያለው?” ብዬ ስጠይቅ፣ “አንድ ነው! ይኸ ሁሉ የወጣው የዓለምዬን ሊሰናበት ነው” የሚል መልስ ሳገኝ፣ ማልቀስ ማቆም እንደነበረብኝ ወዲያ ነበር የተረዳኹት። በዕውነት ተጽናናኹ! ሠርጓ ነበር እንጂ ቀብሯ አይመስልም ነበር።




ተአምረኛዋ የፍቅርተ ካሜራ፣ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ማናችንም ያላየነውን የብርሀን ጮራ ቀርጻ አስቀርታዋለች። እህታችን ፍቅርተ እግዚአብሔር ይስጥልኝ።







ዓለምዬን ተሰናብቶ ሕዝቡ እንዲሁ አልተበተነም። የማርያም ወታደሮች ገንዘብ አዋጥተው፣ አደራሽ ተከራይተው፣ ምግብና ለስላሳ መጠጥ፣ ከ500 በላይ ለሚሆን ሐዘንተኛ አዘጋጅተው ጋብዘው ሸኝተውልኛል። እነሰላም፣ እነከበደ፣ እነ ሶስና፣ እነ ሒሩት፣ ... እንደ ንብ ወዲህ ወዲያ ሲምዘገዘጉና ሲያስተናግዱ ሳያቸው ኮራኹባችሁ፣ እህቶቼና ወንድሞቼ! ኮራኹባችሁ!




ይኸን ሁሉ ሥራ ለሠራችኹና፣ በየዓለምዬ ቀበር ላይ ለተገኛችሁ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በሙሉ፣ በወንድሟ በኃይሌ፣ በእህቷ በጽዳለ እና በራሴ ስም ምስጋናችንን አቀርባለሁ። እግዚአብሔር ይባርካችሁ!

የዓለምዬን 40 ቀን መታሰቢያ የደገሱት እስካአሁን ከእኔ ጋር ጥቁር ለብሰው የሚያዝኑላት መንትዮቹ እግዚአብሔር የሰጠኝ እህቶቼ ፈሰወርቅና እጥፍ ዓለም ናቸው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ የዓለምዬን የተዋወቅኳት፣ የእጥፍ ዓለምንና የዶክተር ዮሐንስን የጋብቻ መልስ ከነሱ ጋር እየዞርኩ ስስተናገድ በአንዱ ላይ ነበር። የዓለምዬን ውድድ አድርጌ ሳገባትም የታፌን ይኹንታ እንደወላጅ እናቴ ጠይቄና አግኝቼ ነው። ይኸ ቤተሰብ፣ የዓለምዬና እኔ ስንጋባ ከጉኔ እንዳልተለየ ኹሉ አሁንም በሞቷ ከጎኔ ያልትለየ ቤተሰቤ ነው። 40ዋን የተዋጡት እኔ አንዲት ሰባራ ስንጥ ስላነሳ እነሱው ናቸው። ውዷን ፍቅሬን ባጣትም የናንተ እንክብካቤ ኃዘኔን አቅልሎልኛል፣ ታፌ! ኑሪልኝ የኔ እህት!








እንግዲህ ለመጨረሻ ያቆየኹአቸው የነፍስ አባታችንን መልአከ ብርሀን ቀሲስ ብርሀኑ ናቸው። አባታችን የዓለም መከታና እኔ ስንጋባ በክብርና በተክሊል የዳሩን አባታችን ናቸው። ታማ ተመላልሰው ጠይቀዋታል። ስታርፍም ጸሎተ ፍታቱንም ሆነ 40ውን በሚገባ አድርሰውላታል። የሥልጣንና የገንዘብ ጥመኞች ከወያኔ ጋር ተባብረው፣ ሕዝቡን ገፍተው ሜዳ ላይ ሲበትኑት፣ አባታችን ከሕዝብ ጋር ድንኳን ውስጥ የቀሩ ብቸኛ ቄስ ናቸው። እግዚአብሔር ብቻ ውለታቸውን ይመልስ። ሐመልማለ ድንግልን (የዓለም መከታን) ወደ ጌታ ዕቅፍ እንድትገባ ስለለመኑልኝ፣ አባቴ አመሰግንዎታለሁ። መሪ ጌታ ሀዲስ (ቃለ ሕይወት ያሰማልን)፣ ዲያቆን ደረጀ፣ ዲያቆን እንግዳ፣ ዲያቆን ማኅደር፣ ዲያቆን እስራኤል ዲያቆን ትንሳኤንና ዲያቆን ለይኵንን እጅጉን አመሰግናለሁ። ጸሎታችሁን እግዚአብሔር ይስማልኝ። 

አፍቃሪ ባለቤቷ ወንድሙ መኰንን

2) የወይዘሮ የዓለም-መከታ ጋርዳቸው አጭር ሕይወት ታሪክ


ወይዘሮ የዓለም ከታ ከአባቷ ከአቶ ጋርዳቸው ወጤ እና ከእናቷ ከወይዘሮ ጥሩወርቅ ሽፈራው በኢትዮጵያ አቆጣጠር፣ ሐምሌ 5ቀን 1955 በጎጃም ክፍለ ሀገር፣ በባሕር ዳር ከተማ ተወለደች። ዕድሜዋ ለትምሕርት እንደደረሰ፣ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዳንግላ ጀምራ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባሕር ዳር ጨረሰች። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ተዘዋውራ፣ ግብርና ሚኒስቴር ተቀጥራ ስትሠራ የማታ ትምሕርቷን በተፈሪ መኰንን ተምሕርት ቤት ቀጠለችና በሒሳብ መዝገብ አያያዝ በ1978 ዓ. ም በዲፕሎማ ተመረቀች። ዲፖሎማዋን እንደያዘች፣ በዕርዳታማስተባበሪያና መምሪያ ተቀጥራ በማገልገል እስከ የትራንስፖርት ስምሪት ኃላፊ መሆን በቃች። የአሁኖቹ የአገራችን ገዢዎች ሥልጣን እንደያዙ፣ ብዙ ሠራተኞችን ከዕርዳታ ማስተባበሪያ መምሪያ1983 ዓ.ም ሲያባሩሩ፣ የዓለም መከታን ደሞዟን ከ600 ብር ወደ 285 ብር አውርደው ሥሪ አሏት። እንሱን ፍርድ ቤት ከሳ፣ ጠበቃ ቀጥራ እየተሟገተች እያለ፣ ወደ እንግላንድ የመምጣት ዕድል አጋጠማትና አገር ጥላላቸው እንደወጣች ቀረች። እዚህ እያለች ተከራክራ፣ ደሞዟ ያለአግባብ እንድተቀነሰባት አስፈርዳ፣ የሚገባትን በወኪሎቿ በኵል ከተቀበለች በኋላ፣ ሥራዋን በገዛፈቃድዋ ለቀቀች።

የዓለም መከታ፣ ለትምሕርት ባላት ጉጉት ምክንያት፣ እስከ  ሕይወትዋ መጨረሻ ድረስ ስትማር ነበር።  በፈረጆቹ አቆጣጠር፣ 1995 እስከ 1996 .. ድረስ  South Thames Collegeገብታ  AAT Foundation (Association of Accounting Technicians) ተምራ አጠናቃለች፣ 1996 እስከ 1997  ድረስ South Thames College ገብታ፣ Certificate Computer Studies (Advanced Excel & PowerPoint) አግኝታለች፣ 1998 እስከ 2002 .  Thames Valley University (አሁን University of West Londonገብታ ለሶስት ዓመት ተምራ፣ BA (Hons)  Accounting & Business Finance – Degree  ተመርቃለች፣ 



2002 – 2003 ACCA Certificate Professional Part 1 ከወሰደች በኋላ፣ ከዚህ ዓለም ለመለየት አንድ ቀን ሲቀራት የከፍተኛ ዲፕሎማ የምታገኝበትን ወረቀት ጽፋ፣ ጨርሳ፣ አስረክባ ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ፈቃድ፤ ሌላ ስለነበር ዲፕሎማዋን ሳታገኝ  ተለይታናለች።

የዓለም መከታ፣ በእንግሊዝ አገር በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ተቀጥራ አገልግላለች። Hammersmith & Fulham Council – Education Finance Department Finance Assistantነት December 2001 እስከ March 2004 ሠርታለች። Islington Council – Housing Department Payment and Rent Arrears Officer/Finance Officer በመሆን March 2004 እስከ March 2005 . አገልግላለች፤ The City Of Westminster Council (Social and Community Service) ተቀጥራ Finance Officerነት (Adult Social Care Department, Older people and Disability Team) 2005 እስከ 2011 ድረስ በቀና መንፈስ አገልግላለች። የዓለም መከታ የጤንነቷ ነገር ቢያስቸግራትም፣አልተቀመጠችም። በበጎ ፈቃድ ብርቲሽ ሐርት ፋውንዴሽን ውስጥ በነጻ ስታገልግል ነበር፤ ያረፈችው።

ዓለም መከታ፤ ከወንድሙ መኮንን ጋር፤  ሰኔ 8 ቀን  1994 .. ( 15th June 2002) ተጋብተው፤ አስራ ሁለት አመታት በላይ፤አንድ ላይ በፍቅር፤ በመከባበር በመተዛዘን ኖረዋል። 


ዓለምንና ወንድሙን፤ አንድ ላይ ሆኖ ላያቸው ሰው ሁሉ፤ በቅርብ ጊዜ የተዋወቁ ጓደኛሞች፣ ወይም በጣም የሚዋደዱ እህትና ወንድም እን ባልና ሚስት አይመስሉም ነበር። በጣም ነበር የሚፋቀሩት፤ በጣም ነበር የሚተሳሰቡት።
የዓለም መከታ በፈረጆቹ አቆጣጠር በሜይ 2012 በደረሰባት አሳዛኝና ድንገተኛ አደጋ ለሁለት ዓመት ያህል ታማ በስቶክማንዴቪል እናበኦክስፎርድ ቸርቺል ሆስፒታሎች ስትታከም ቆይታ ለአስራ አንድ ወራት ተሽሎአት እቤቷ ተመልሳ ገብታ ነበር፤ አጋጣሚ ሁኖ የምግብ መመረዝ (ፉድ ፖይዝኒንግአግኝቷት በድንገት ሳይታሰብ ዓርብ ጃኑዋሪ 16 ቀን 2015 . ኤይልበሪ በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ አርፋለች። በህመሟ፤ ጊዜ ሁሉ ባለቤቷ ወንድሙ መኮንን፤ ከጎኗ ሳይለይ፤ በሚገባ አስታሟታል፤ ተንከባክቧታል።

 የዓለም መከታ እንደ ስሟ ለዓለም ሕዝብ ሁሉ አዛኝና ፈጥኖ ደራሽ ናት። የታመመን ጠያቂ፣ የተቸገርን ረጂ፣ የአዘነውን ሁሉ አጽናኝ፣ ሥራ ላጣ ወገኗ ሁሉ እንደራሷ አድርጋ ሥራ ፍለጋስትንከራተት ዕድሜዋን ሙሉ ለሰው የኖረች ርኅሩህ የሁሉም እህት ነበረች። ዓለም፤ መከታ ፈሪሐ እግዚአብሔር ያደረባት፤ በጣም ጥሩ ክርስቲያን ነበረች። ባለቤቷ፤ ወንድሙ መኰንንም አንደረሷው፤ ለዕምነቱ ጠንካራ በመሆኑ ለሰርጋቸው ከጋበዙት  እንግዶች መካከል ዋና ሠርገኞች ቅዱስ ገብረኤልና ቅዱስ ሚካኤል ነበሩ።  የጥሪ ካርዳቸውም እነሆ!







የዓለም መከታ ከማለፏ በፊት፣ አሜሪካን አገር ሂዳ፣ ያሳደጉአትን አክስቷን ወይዘሮ ዳሞትላንቺንና የአክስቷን ልጆችና የልጅ ልጆች፣ ከነበቤተሰባቸው በሙሉ ጎብኝታ ትሰናብታቸዋለች። ወደ ሳንዲያጎም ጎራ ብላ ሌላውን የአክስቷን ልጅ፣ ደራሲ ወጋየኹን ተሰናብታለች። እዚህ ለንደን ቤተክርስቲያኗ ስለተዘጋባት፣ ሥጋ ወደሙን የምትቀበልበት የክርስቶስ ቤት ጠፍቷት ስትጨነቅ ነበር። ሎስ አንጀለስ የነበሩትን አባቶች ጠጋ ብላ፣ ንሰሐ ገብታ፣ ሥጋ ወደሙን ተቀብላ በንጽሕና ነበር ያረፈችው።


 የዓለም መከታ 11 ወንድምና እህቶች ነበሩአት። የተሟላ ቤትና ነብረት ጥላ ነው ይኽችን ዓለም የተሰናበተችው። የዓለም መከታ ይኽችን ዓለም ትታ ወደ ጌታዋና ፈጣሪዋብትሄድም፣ ፍቅሯና ትዝታዋ እንደነፍሱ በሚወዳት ባሏ፣ በወንድሞቿ፣ በእህቶቿ፣ ኮትኩተው በአሳደጓት በእናቶቿ እና በጓደኞቿ ልብ ውስጥ ተቀብሮ ይኖራል።

 በዚህ የሀዛን ሰዓት፣ ለወንድሞቿ ለኃይለ ሚካኤል ጋርዳቸው፣ ለጸሐዩ ጋርዳቸው፣ ለእህቶቿ፣ ለጸዳለ ጋርዳቸው፣ ለእምዩ ጋርዳቸው፣ የውልሰው ጋርዳቸው፣ ለኤልሳቤጥ ጋርዳቸው፣ ትበርህ ጋርዳቸውና የሺጥላ ጋርዳቸው፣  እንዲሁም ለእናቶቿ ለእማሆይ አስካለ ቤዛ እና እማማ ጽጌ ወንድማገኝ፣ እንዲሁም እህታቸውን ተክተው እንደናት ጡት አጥብተው ለአሳደጓት ለእማሆይ ዳሞትላንቺ ሺፈረው፣ አብራቸው ላዳገች ለፊታውራሪ በዛብህ ቤተሰቦች ብሙሉ ለዶክተር አድማሱ በዛብህና ዶክተር ይሳለሙሽ ሰንደቅ፣ ለእንጂነር ታደሰ በዛብና ለወይዘሮ ጸለ ከነልጆቻቸው፣  ለወይዘሮ የሻሽወርቅ በዛብህ ከነቤተሶቿ፣ ለወይዘሮ ዝማምወርቅ በዛብህ፣ ለወንድም አበራ ከነቤተሰቦቻቸው፣ ለሥነጸሐይ እና ለአፈወርቅ ከነቤተሰቦቻቸው፣ ለሲስተር አሳመነች በዛብህ እና ለአቶ ተሰማ ቢተው ከነቤተሰቦቹ እግዚአብሔር መጽናናትን ይስጣቸው።

ነፍስ ይማር!

ቤተሰቦቿና ጓደኞቿ

3)   የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ መልዕክት (ኒው ዮርክ)

ወይዘሮ የዓለም መከታ

የወይዘሮ የዓለም መከታ ዜና ዕረፍት ሲሰማ፥ ሞት ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አብሮን እንዳልኖረ ሁሉ አዲስ ነገር ሆኖብን ነበረ። ምክንያቱም ግልጽ ነው፤ ወይዘሮ የዓለም የሰውን ልጅ ከሕፃንነት እስከ ጉልምስና ዘመን የሚያጠቃውን ድንገተኛ ሞት ሁሉ አልፋ ሰው ሙሉ ጤነኛ በሚሆንበት ጊዜ ስለነበረች በወጣትነቷ የምትለየን እኅት አልነበረችም። ከሦስት ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ሳያት፡ ሙሉ ጤና ያላት ጎልማሳ ሴት ወይዘሮ ነበረች። ታዲያ ድንገተኛውን ሐዘን እንዴት እንመነው? ተደናገጥን፤ ሐዘኑ ከበደን።
የዓለም ስለተለየችን ብናዝንም መጽናኛ የሚሆነንን መልካም ትዝታዋን ትታልን ስለሄደ እናመሰግናታለን። በመልካሙ ትዝታዋ አብራን ትኖራለች። እንደማውቃት ሰው ትወዳለች፤ ለሰው ታዝናለች። የጨዋ ኢትዮጵያዊ አስተዳደግ ምን እንደሚመስል ለማወቅ የሚፈልግ ከየዓለም ጋር የጥቂት ሰዓት ቆይታ ማድረግ ይበቃዋል። ንግግሯ ሁሉ የተመጠነ፡ የተቆጠበ፥ ቃላቷ ጣፋጭ ፍሬ የያዙ፡ ነበሩ። ሰው ተናግሮ ሳይጨርስና አስተሳሰቡን በሚገባ ሳትረዳ፥ ቃል ከአፏ አይወጣም ነበር።
ከባለቤቷ ጋር ያላትን ግንኙነት ሳስታውስ ሰሎሞን ስለመልካም ሚስት ሲጽፍ፡ የዓለምን ባሕርይ እየተከታተለ  የጻፈው ይመስለኛል።

ጠባየ መልካምን ሚስት ማን ሊያገኛት ይችላል? እርስዋ ከዕንቍ ይልቅ የከበረች ናት። ባልዋ ይተማመንባታል፤ የሚፈልገውን ነገር ሁሉ አያጣም። በምትኖርበት ዘመን ሁሉ መልካም ነገር ታደርግለታለች . . . ለድሆችና ለችግረኞች ትለግሳለች። ባልዋ የአገር ሽማግሌዎች በሚሰበስቡበት ሸንጎ የተከበረ ነው። በጥበብ ትናገራለች፤ በቅን መንፈስ ትመክራለች።ጥሩ ሚስቶች የሆኑ ብዙ ሴቶች አሉ፡ አንቺ ግን ከሁ ትበልጫለሽይላታል። ቍንጅና ከንቱ ነው፤ ውበትም ይጠፋል፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን ልትመሰገን ይገባታል። እርስዋ ለምታደርገው ነገር ሁሉ አመስግኗት፤ ስለ መልካም ሥራዋ በሰዎች ሁሉ ዘንድ ልትከበር ይገባታል።

የዛሬ ሦስት ዓመት ሎስ አንጀለስ ላይ ስንገናኝ፥የዓለም፥ አሜሪካ ድረስ መጥተሽ እንዴት ዋል አደር ብለሽ ታሪካዊና ብርቃብርቅ ቦታዎችን ሳታይ ትመለሻለሽብየ ብጠይቃት፥ወንድሙ ብቻውን ነው፤ ይኸን ያህል መቆየቴም የሚገባ አልነበረም፤ መሄድ አለብኝአለችን። ይኸን አስተያየቷን የሚያውቅ ሕመሟ እየጸናባት ሲሄድ ምን ትልና ስለማን ታስብ እንደነበረ ለማወቅ አጠገቧ መገኘት አያስፈልገውም።

ዶክተር ወንድሙም ሕይወቱን ለእሷ እንደቀደሰው፥ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በፊት ኦክስፎርድ ከተማ ሁለቱን ያገኘኋቸው ጊዜ በቅርቡ ተመልክቻለሁ። የሚያያት እንደ አዲስ ፍቅርቱ፥ የሚያገለግላት እንደ እመቤቱ ነበረ። መልእክት ስንለዋወጥ ስለ የዓለም በሰፊው ሳይጽፍ አይደመድምም ነበረ። የዓለም ስለተለየችው ቢያዝንም፥ምነው ይኸንን ሳላደርግላት ተለያየንየሚለው ጉዳይ ያለ አይመስለኝም። የሚወዱት ሲለይ ከዚህ የበለጠ መጽናኛ አይኖርም።

የዓለም  በማህላችን በአካል አለመገኘቷ የሚያሳዝነን እኛን ነው እንጂ እሷስ በልጅ እግሯ፥ በቅን ሕሊናዋ፥ በሩኅሩኅ ልቧ መንፈሳዊ ሩጫዋን በአሸናፊነት ስለፈጸመች፥ ዓይን ያላየውን፥ ጆሮ ያልሰማውን፥ በሰው ልቡና ያልታሰበውን፥ ቅዱስ ስሙን ለሚወዱ ያዘጋጀውን ቦታ ወርሳ፥ ከነሳራ፥ ከነርብቃ፥ ከነክርስቶስ ሠምራ፥ ከነመስቀል ክብራ ጋር ማኅበረተኛ ሆናለች። ሁላችንንም እግዚአብሔር ያጽናን። ዶክተር ወንድሙ፥ ዘመዶቿ  እግዚአብሔር ያጽናችሁ። እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔር ነሣ። የእግዚአብሔር ስም የተቀደሰ ይሁን።

ጌታቸው ኃይሌ

 ኒው ዮርክ፥ ጥር 15 ቀን 2007 . .        

4) የወንድም ደጀን አንሳ ግጥም

የእህታችን ያለም መታሰቢያ


ያለም ፈጣሪዋን ስምህን ስትጠራ
እናትህን ማርያምን ከልቧ አፍቅራ
ምስጋና ስታቀርብ ገድልህን ዘርዝራ
ካንተ ቅድስናን ፅድቅን ልታፈራ
ምነው ወሰድክብን ከማናያት ስፍራ።
የእውነት ጠበቃ ነች የፍቅር ጎተራ
ለተከፋው አዝና ላጣው ተቸግራ
ስትሸፍን ነበረ ገንዘቧን ዘርዝራ
ዝም ያለን አናግራ ሑሉንም አክብራ
ላገሯም ነጻነት ላንድነት ዘምራ
በልበሙሉነት ሳትሰለች ሳትፈራ
በእየአደባባዩ ስትታገል ኖራ
ተምሳሊት ነበረች አቋመ ጠንካራ።
ሰጥተህን ነበረ እህት ባልንጀራ
ደግነት ቅንነት ስትለግሰን ኖራ
መልሰህ ወስድካት ሆኖ የሷ ተራ
እውቀቷን ከፍ አርጋ ትምህርቷን ተምራ
እህት ወንድሞቿን ባሏን ስታኮራ
የመመረቂያዋን ጽፋ ወረቀቱን
መጨረሻው ደርሶ ሳትጭነው ማረጉን
ምነው እንዲህ ባጭር የሄደችው ጥላን።
ያንችን ሕመምሽን ትተሽው ወደጎን
አቀናለሁ ብለሽ አስበሽ የሰውን
ምናለ ባትገዥው ባትበይው ምግቡን።
ይሄ ደግነትሽ ፈተና ሆነና ወሰደው ስጋሽን
ለማን አደራ አልሽው ደጋፊሽ ወንድሙን
አንጀታችን ቢያርር ቢቆስል ልባችን
ሐዘንም ብናጠብቅ ሞትሽም ቢመረን
አንቺ እንደሁ ሄደሻል ወደ አምልክ ጌታችን
ከጎኑ እንዲያኖራት ደጓ ነፍስሽን
ዛሬም ዘወትርም እንፀልያለን።
ምስጥረኛዬ ነሽ ጓዳዬ ይሉሻል
ችግር ፈችዬ ነሽ ደራሿ ይሉሻል
ታዲያ ጓደኝነት እንዴት ይጠፋሻል
ሳትሰናበችን መሄድሽ ይበጃል?
በተስኪያን ስናጠሽ አርፈን ከድንኳን
ከቶም በልባችን ሞት አልጠረጠርን
ድንገተኛ ሆኖ የቀጠፈብን
በይ አፈር ይቅለልሽ እኛም እንመጣለን
የኮንትራት ዓለም አይበርደን አይሞቀን
እግዚአብሔር እጅ ነሽ ፅድቁን ያላብስልን።

5)  የወይዘሮ ሒሩት መስፍን መልዕክት ከሎንደን
    
Yalem,

I met yalem some 22 years ago when she first arrived in London.  That very night, I could tell what an inspirational and ambitious woman she was.  She told me she wanted to work hard and she wanted to further her education.   I could feel the hunger to succeed in her.    She achieved them all, if not more-   which is why I want my eulogy of Yalem to be a chronological order of her tragically short yet purposeful and extraordinary life I have witnessed since I first met her.     

Yalem stayed about three weeks with me and my siblings before we knew it, she had found a job and put herself to college.  Within a year or so, her brother and sister have joined her.  She worked really hard.  Putting up long hours, at times she held two jobs. She was unbelievably focused.      In such a short space of time, she bought her own flat by herself. 

She went to University got her Degree in Accounting. She was bright as a button, highly intelligent; a cut above from the rest. She such energy, and desire to know, succeed and   upon   becoming a British citizen she made a solo and adventurous journey to Morocco which is a testimony to her fun loving and fearless personality!  She loved Britain and   was very mindful of the opportunities it provided her.

When she met her husband Wendemu, she was happy and content with the concept of being a couple. She adored him. 

She was a unique person.  She was always helpful to others.  She gets out of her way to assist those often in her community without jobs and housing.  She would not just tell people how to get help but she would travel with them to these offices and introduce them with the employers there who typically would be Yalem’s friends too.  She had great ability to network.   That was not just it, back in our homeland Ethiopia she would have so many people who would rely on her for their rent, medical bill, educational bill and other necessities.

I remember clearly, one early morning she phoned me to ask if I knew anybody in the Sahara Dessert flabbergasted by the question, I just teased her back by saying yes, I said; “call Colonel Gaddafi”, as usual, she busted out into her infectious laughter and told me off for making a joke at her expense.  She said her sister is stranded there.   To my surprise though she has managed to send the money to her sister at the Sahara Dessert and as a result of which she had reached to Switzerland safely!

Yalem   has an incredible ability to love and trust everyone that crosses her path and she loved everyone without prejudice.

Nationality, ethnicity, race, gender, culture – none of these things have any meaning to Yalem.  She was almost childlike in her innocence. Because of which, she was often misunderstood, often people wonder why she is so kind asking what is she after. The truth is, Yalem was after nothing.  She did not want anything from anybody-but she wanted something from everybody; and that was, to love and be loved in return.

A shining light has gone out of our community.   Every day I reach to the phone as if she is still on the other end then, I quickly get filled with the bitter realization that she is no more.  Somehow though, I drew great comfort from knowing that, my sister, friend and confidant is in a place with the almighty God, where nothing and no one can hurt her anymore. 

I love you Yalem, you will be sorely missed.



Hirut Mesfi

6) የጎንደርጌጥ መዝገቡ ግጥም

የዓለምዬ

አቤት ልብልሽ፣ ስትደውይ ስልኩን
ሆዴ ተረበሸ፣ ሳጣው ድምጽሽን
እንቢ አለኝ አንጀቴ፣ ሆዴም ቢድልለው
እንቢ አለኝ መርሳት፣ ልቤም ቢያታልለው
አትርሽኝ የሚለኝ፣ ዕውንት አንደበትሽ ነው

ያለምዬ

ያላስለመድሽኝ ያለጸባይሽ
ሰው ቀጥሮ መጥፋትን ማን ነው ያስተማረሽ
ወዳጅ ጓደኞችሽ፣ ስትወጅ ስታከብሪ አይ ነበር ህልጊዜ
በጣም ተንስፈሰፍኩ፣ ስትሄጅ ያለ ጊዜ
በቃ ተለየሽኝ፣ ፍቅር ነበር ለእኔ ደኅና ሁኝ ምርኩዜ
እግዚአብሔር ሆይ! አቤቱ ነፍሷን ተቀብላት፣ በጻድቃንም ቦታ በቀኝህ አቁማት!

አሜን

ጓደኛሽና እህትሽ
የጎንደርጌጥ መዝገቡ

7) የወንድም ደረጀ በጋሻው ግጥም




8)የወንድማችን ሳሙኤል አድማሱ እና የእህታችን የወይዘሮ ዙርያሽወርቅ ለየዓለምዬ ማስታወሻ
ለመጨረሻ ጊዜ የዓለምና ወንድሙ የክርስቶስን ልደት፣ አብረው ሲያከብሩ


                  ዋ!! እኔን
  ሞታለች ይሉኛል የዓለም መከታን
   የሞትኩት እኔ ነኝ የሆንኩት በድን።
    ትህትና ደግነት አሟልቶ የሰጠሽ
     ውበትን ከሀይማኖት አብዝቶ ያደለሽ
     የወንድሙ እህት፣እናትም ሚስትም ነሽ።
      የዓለምዬ እርቀሽ በአያሌው ሄደሻል
      ወንድዬ ማን አለው አሁን ጨክነሻል።
     እሱም  አይሆንለት ካንቺ መለየት
     ተፅናንቶ አየሁት ወይ ክርስቲያንነት።
     ለቅሶሽ ለቅሶ ሆኖ እንደዚያ ያማረ
     አንቺ  ግን የለሽም  ደግነትሽ ቀረ።
     ወገን አለቀሰ ባልሽም አነባ
     ምርኩዙን ተነጥቆ እንዴት ቤቱ ይግባ?
     ጣራና ግርግዳው ለሱ ምንድነው
      ምሰሷዋ አንቺ ነሽ ቤቱ ባዶ ነው።
     ልንገርሽ የአለሜ ያለ እድሜሸ ሄደሻል
     ሁላችን እንምጣ ለብቻሽ ይከብዳል::
    

የዓለም መከታ ለመጨረሻ ጊዜ ቤተክርስቲያን ለማስቀድሰ በባቡር ስትሄድ የተነሳችው።
የዓለምም ዓለም ነሽ መከታም መከታ 
    የሁላችን ድጋፍ መጠጊያ አለኝታ።
    ወንድዬ በርታልኝ አንተ የኔ አንበሳ
     አለምን ስታጣ እንዳትሆን ኮሳሳ
     አለብህ አደራ ኢትዮጵያን አትርሳ
     ነፍስሽን ያኑራት ከርብቃ ከሳራ
     ዘላለም ይኖራል ስራሽ እንዳበራ!!!!!!!!!

ተፃፈ 22/04/2015
ሀገረ አሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት
መታሰቢያነቱ ለእህታችን ለወይዘሮ አለም መከተ

እህትሽ ዙሪያሽወርቅ መኮንን
ወንድምሽ ሳሙኤል አለባቸ