Tuesday, 22 November 2016

መካሪ ልቦናስ አለ ! ተመካሪ ሰዉ ግን ከወዴት አለ?


መካሪ ልቦናስ አለ ! ተመካሪ ሰዉ ግን ከወዴት አለ?
ሸንቁጥ አየለ
-------------------------------------
ሸዋ ዉስጥ ደብር ዜና ማርቆስ የሚባል ገዳም አለ::በ1986 ዓም የ12ኛ ክፍል ፈተኛ ስጨርስ ወደ አንድ መለኩሴ አጎቴ ካንድ ጓደኛዬ ጋር ወደ እዚህ ገዳም ሄድን::ይሄን ጓደኛዬን ለማስመከር መሆኑ ነዉ::በወቅቱ ይሄ ጓደኛዬ ነገር ክርስቶስ ላይ ጥርጣሬ ቢያበዛ እስኪ ከኝህ አጎቴ ምክር ስማ ብዬ ነበር ይዤዉ የሄድኩት::እናም መለኩሴዉ አጎቴ ልንጠይቃቸዉ እንደመጣን ሲያዉቁ ደስ አላቸዉ:: ፈገግ ብለዉም ተቀበሉን::

ሆኖም በቤታቸዉ ያለዉንም የሚበላ ነገር አቀራርበዉልን በትንሿ ቤታቸዉ ትተዉን "በሉ ተጨዋቱ:: እኔ ወደ ጸሎት መሄዴ ነዉ" ብለዉን ሄዱ::ቢጠበቁ አልመጡም::እኛም ስለደከመን ቁጭ ባልንበት መደብ ላይ እንቅፍል ይዞን ሄዶ ኗሯል::እሳቸዉ ግን በጣም ከመሸ መጡ::ጥቂት አርፈዉ እንደገና ተነስተዉ ሌሊትም ለጸሎት ብለዉ ሄዱ::ጠዋት ቅዳሴ ቆይተዉ መጡ::አሁንም ያላቸዉን ነገር አዘገጃጅተዉ አቀራርበዉልን የተሰዓት ጸሎት ደርሷል ብለዉ ሊሄዱ ተነሱ::

ነገር ክርስቶስ ላይ ጥርጣሬ የገባዉ ጓደኛዬም የመለኩሴዉ ለጸሎት እያሉ ጥፍት ማለት ገርሞታል እና አንድ ጥያቄ ጠዬቃቸዉ:: "ለመሆኑ ጸሎት የሚበቃዎት መቼ ነዉ? የሚጸልዩትስ ምን እያሉ ነዉ?" ሲል ጠዬቀ::እርሳቸዉም ፈገግ እያሉ " የምድር ጸሎቱ ስሞት ነዉ የሚበቃኝ::ሆኖም በሰማይም ክርስቶስን ማወደሱና እና ማመስገኑ ይቀጥላል::የምጸልዬዉም "አምላኬ : ጌታዬ : ፈጣሪዬ: ንጉሴ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ምስጋና ይገባሃል" እያልኩ ነዉ" ሲሉ መለሱለት::

ልቡ በክርስቶስ ነገር ላይ የሸፈተዉ ወጣትም "ክርስቶስ እኮ ፈጣሪ አይደለም::ለምንድን ነዉ ፈጣሪ የሚሉት?" ሲል ሳያፍር መለኩሴዉ አጎቴን ጠዬቃቸዉ::እኔም አመዴ ቡን አለ::በፍርሃትም ተሸማቀቅሁ:;እንዴት አንድን መለኩሴ እንዲህ በብልግና ይጠይቃል ብዬ መሆኑ ነዉ::እርሳቸዉም ፈገግ አሉ::"ክርስቶስን ፈጣሪ አይደለም ብለህ ታስባለህ? ማለት ነዉ?" ሲሉ::

"አዎን!" አለ ምንም ቅር ሳይለዉ::

"እዴት?" በድጋሚ ጠዬቁ::

"ምክንያቱም መጽሀፍ ቅዱስ እንደሚያብራራዉ..." ብሎ የሚያዉቃትን ጥቂት ጥቅስ ጠቃቀሰ::ድንገትም የዮሀንስ ወንጌል ምዕራፍ አንድን መናገር ጀመረ::ድምጹን ከፍ አድርጎም እየተናገር የነበረዉ መለኩሴዉን ክርስቶስ ኢየሱስ አምላክ አይደለም ብሎ ለማሳመን ነበር::ድንገት ግን ቀጥ ብሎ ቆመና መናገር አቆመ::"እንዴ ቆይ ? " ብሎ መንጎራደድ ጀመረ::"እንዴ ...ቆይ ይሄ ምዕራፍ እኮ ስለክርስቶስ አምላክነት እና ፈጣሪነት የሚያስረዳ ነዉ::እንዴ?..." እንደገና እራሱን አርሞ ምዕራፉን ደግሞ በቃሉ ለበለበዉ:: እራሱ እየተናገረ እራሱ ደግሞ እያብራራ "እንዴ ? እንዴ? ! ..." ማለቱን ቀጠለ::

መለኩሴዉ አጎቴ በዚህ ሁሉ የጓደኛዬ ንግግር መሃከል ጣልቃ አልገቡም::እራሱ ክርስቶስ ፈጣሪ አይደለም ብሎ ጥቅስ ማብራራት ጀምሮ እራሱ ደግሞ መዞ ባመጣዉ ጥቅስ ክርስቶስ ፈጣሪ ነዉ ብሎ እራሱን ማስረዳት ጀመረ:: መለኩሴዉ አጎቴም በመጨረሻ ጓደኛዬን እያስተዋሉ እንዲህ አሉ:: "አንተ ጎበዝ ልጅ ነህ::መካሪ ልብ ያለህ::ተመካሪ ልብም ያለህ:: አሳስተዉ ያስተማሩህን ነገር በየዋህነት ሰምተህ በልብህ ብታስቀምጠዉም ልቦናህ ግን እዉነትን የማድመጥ ጸጋን የተሰጠህ ሰዉ ነህና እዉነት እና ሀሰትን አብላልተህ በራስህ መለዬት ቻልክ::"

መለኩሴዉ አጎቴ ይሄችን ብቻ ከተናገሩ ብኋላ "በሉ እርስ በርሳችሁ ተማማሩ" ብለዉን ጥለዉን ወደ ጸሎታቸዉ ሄዱ:: የልጁ ክህደትም ሆነ እራሱን አርሞ ወደ ትክክለኛ ሀሳብ መምጣቱ ድንቅም አላላቸዉ::ሲጀምር እኝህ መለኩሴ ምንም ነገር የሚደንቃቸዉ ነገር ያለ አልመሰለኝም::ከመመልኮሳቸዉ በፊት አላቃቸዉም:: እንዲህ ምንም ነገር የማይደንቀዉ ያደረጋቸዉ ምልኩስናዉ ይሁን ወይም አይሁን ግን አላቅም::

በሶስተኛዉ ቀን ከትንሿ ቤታቸዉ ተሰናብተን እዬሄድን ሳለ ድንገት አንድ ሀሳብ መጣልኝ::ለዘለአለም ስንቅ የሚሆን ምክር ከኝህ ሰዉ ማግኘት:: እናም ዞር ብዬ እያስተዋልኳቸዉ "አባ ! በህይወታችን ሙሉ የምንመራበት ምክር ቢለግሱንስ?" ስል ጠዬቅኋቸዉ::እንደለመዱት ፈገግ አሉ::ከስዉ ልጅ ባህሪ ዉስጥ ፈግግ ማለት ጥልቅ የሰዉነት ህሳቤ ሚስጥር ይመስለኛል::ገና ህጻን ሆኜ::እናም እኝህ አባት ዉስጥ ይሄን ጥልቅ የሰዉነት ሚስጥረ ሀሳብ ያነበብኩት መስለኝ::እናም የሚናገሩትን ለማድመጥ በጥንቃቄ አቆበቆብን:: ሌላዉ ቀርቶ በነገር ክርስቶስ ላይ ልቡ ሲዋዥቅ የነበረዉ ጓደኛዬም በሶስት ቀን ዉስጥ የሆነ የማይታመን የአስተሳሰብ ለዉጥ አምጥቶ አባ የሚናገሩትን በአክብሮት እያደመጠ ነዉ::

አባ ምክር ስጠይቃቸዉ ፈገግ ብለዉ ሲያበቁ እንዳልሰማ ሆነዉ ግን "በሉ ሰላም ግቡ::ቆላማዉን ሀገር እስክትወጡ ቀስ እያላችሁ::" ብለዉን እንድንሄድ ገፋፉን:: እኔም "ምክሩን እኮ አልነገሩንም !" ስል በድጋሜ ጠዬቅሁ::አባ እንደገና ፈገግ አሉ:: እናም "እዉነተኛዉ ምክር እያንዳንዱ ሰዉ ልብ ዉስጥ አለ::ሰዉ የልቡን እዉነተኛ ምክር ለመስማት ከፈቀደ ከልቡ ዉጭ መካሪ አያስፈልገዉም::ለዚህ አባባሌም ምስክር የሚሆነዉ ይሄ ወጣት ነዉ" ብለዉ ወደ ጓደኛዬ በአገጫቸዉ አመለከቱ:: "ተመካሪ ሰዉ ካለ መካሪ ልቦናንስ እግዚአብሄር በየሰዉ ዉስጥ አኑሯል:: ሰዉ ከልቦናዉ ዉጭ መካሪ አያስፈልገዉም" በማለት አባ አብራሩ:: አጭር ግን ቆፍጠን ያለ ማብራሪያ ነበር::

እናም ሰሞኑን የመለኩሴዉ አጎቴ ጥልቅ ምክር ታስቦኝ እንደ እርሳቸዉ ብቻዬን ፈገግ አልኩ:: በኢትዮጵያዉያን ፖለቲከኞች መሃከል እየተከናወነ ያለዉን የእርስ በርስ መጠፋፋት ጉዳይ ሊያስቀር የሚችል አንድ ግሩም ምክር አዘል ጽሁፍ ማዘጋጀት አለብኝ ብዬ ሰሞኑን አስቤ ተነስቼ ነበር::የኢትዮጵያ ነገር ለልቤ ጭንቅ : ለመንፈሴ ህመም: ለህሳቤዬ እሩቅ ሲሆን በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች መሃከል እኮ አብሮነት ቢፈጠር "አንዲት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን" በፍጥነት እዉን ማድረግ ይቻል ነበር ብዬ እንደ ሞኝ እፈላሰፋለሁ::

እንደ ሞኝ ያልኩት ያለምክንያት አይደለም:: በጥልቅ ምክንያት ነዉ::እንኳን የማይተዋወቁ : በነገድ የሚለያዩ: በፖለቲካ ህሳቤ እና ርዕዮት አለም የተነጣጠሉ ሀይሎች አንድ ሊሆኑ ይቅር እና በእዉቀት ኮትኩተን እና አጀግነን ለጋራ ትግል ይሆናሉ ብለን የምናዘጋጃቸዉ ሰዎች በጣም በፍጥነት ሲገለባበጡ እና ሲከረባበቱ ብሎም ወደ ሌላ ጎራ ሲሰለፉ በተደጋጋሚ ላስተዋለ ሰዉ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ለምን አንድ አልሆኑም ብሎ ማሰቡ በራሱ ሞኝነት ነዉ::አንድ ባይሆኑ ግን ለምን ተከባብረዉ አይታገሉም? ብሎ መጠዬቅ ግን ጤናማ ጥያቄ ይመስላል:: ግን ይሄም የኢትዮጵያን ፖለቲካ ቀርቦ በደንብ ለሚያጠናዉ ሰዉ የሞኝ ጥያቄ ነዉ::

እናም ማዘጋጀት የጀመርኩትን የምክር ጽሁፍ አጥፍቼ ስለ መለኩሴዉ አጎቴ ምክር ማንሰላሰል ጀመርኩ:: "ተመካሪ ሰዉ ካለ መካሪ ልቦናንስ እግዚአብሄር በየሰዉ ዉስጥ አኑሯል:: ሰዉ ከልቦናዉ ዉጭ መካሪ አያስፈልገዉም" የሚገርም እና የተራቀቀ አባባል ነዉ::ኢትዮጵያዉያን ይሄን ያህል ጥልቅ ህዝብ ሆነዉ ሳለ ለምን ጥልቅ መሰረት ላይ የቆመ ሀገር መመስረት አቃታቸዉ?
"መካሪ ልቦናስ አለ ! ተመካሪ ፖለቲከኛ ግን ከወዴት አለ?" የሚል ጥያቄ ሲቀርብም ይሰማኛል::እናም በክፉ መንፈስ የተጠለፈዉን: ዘረኛ እና አንባገነን ስርዓት ለማስወገድ በተጋድሎ ላይ ያለዉ ህዝባችን የተባበረ እርዳታ የሚፈልግበት ወቅት አሁን ነበር::ፖለቲከኞች ግን በመርዛማ የመጠላላት እና የመጠላለፍ ሀሳብ ዉስጥ ወድቀዋል:: ይሄ ዛሬ አልተጀመረም:: ቅንጅት የተበታተነዉ የተንኮል ፖለቲካ ማጥ ዉስጥ ተቀርቅሮ ጭምር ነዉ:: ከቅንጅት በፊት የነበሩትን አቢዮታዊ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ወደ መርዛማ አዘቅት ዉስጥ የጣላቸዉም ይሄዉ በሸፍጥ እና በአሉታዊ እንቅስቃሴ የተሞላዉ የፖለቲካ ህሳቤ ነዉ:: የፖለቲከኞቻችን ልቦና እዉነትን ሳይሆን ሸፍጥን ለማፍልቅ ፈጣን ነዉ::

እናም ምክር ፖለቲካን አቅጣጫ አያሲዘዉም::በተለይም እንደ ኢትዮጵያ አይነት ፖለቲካዊ ምህዳር ዉስጥ የሚተራመስ የፖለቲከኛ ህዝነ ልቦናም እራሱን ለመምከር የሚያስችለዉን እዉነተኛ ምክር ለማፍለቅ ልቦናዉን ጸጥ የሚያደርግበት ሁኔታ ዉስጥ አይደለም::በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት ፖለቲከኛነት በልብ ዉስጥ ትርምስ እና በዉጭም ትርምስ የሰፈነበት ከባቢ ህይወት ዉስጥ መመላለስ ይመስላላል::

እናም "እዉነተኛዉን እና ትክክለኛዉን ሁኔታ ለመለዬት እና ለማወቅ የሚያስችል መካሪ ልቦና በያንዳንዱ ዉስጥ አለ:: ተመካሪ ፖለቲከኛ ግን ከወዴት አለ?" ብሎ ዝም ማለት የቀለለዉ መፍተሄ ባይሆንም አንዱ አማራጭ ግን ይመስላል:: "መካሪ ልቦናስ አለ ! ተመካሪ ሰዉ ግን ከወዴት አለ?"