“እየየ ሲዳላ ነው”
ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 28/05/2021
መግቢያ
አባቶች/እናቶች ሲተርቱ፣ “እየየ ሲዳላ ነው” ይላሉ። ዕውነት ሲደላ ነው እየየ የሚባለው? እየየ ተብሎ የሚጮኸው የምር
ድሎት ላይ ሁኖ ሳይሆን፣ የበለጠ አደጋ እያለ፣ ያንን አደጋ ማምከን ትቶ ቁጭ ብሎ ከማልቀስ አደጋውን ለመቀነሰ መጀመሪያ መፍትሄ
መሻት ያሻል ለማለት ይመስላል። ከጀምሩ እየየ የሐዘን ጩኸት ወይም የለቅሶ ዜማ
መሆኑ ጠፍቶአቸው አይደለም እንዲህ የሚሉት። ይኸ አባባል በጣም ጥልቅ ትርጉም አለው። እየየ የሐዘን እንጉርጉሮ ነው። አንዳንዴ
ለማዘንም ጊዜ እንዳለ ያመለክታል። ለምሳሌ፣ አያድርስና፣ ቤት መቃጠል ይጀምራል እንበል። አሰቃቂ ነው። ሕይወትም ጠፍቶ ሊሆን ይችላል።
እሳቱ እየተንቀለቀለ ተወዝፎ የለቅሶ እንጉርጎሮ ማውረድ አይታሰብም። እሳት አደጋ ጠርቶ፣ እስከዚያው ጎረቤት ተጠራርቶ ተባብሮ ወይ እሳቱን ቁጥጥር ሥር ማዋል፣ ወይም ማትረፍ የሚችለውን
ህይወትም ሆነ ንብረትን ማዳን ነው ቅድሚያ የሚሰጠው። ለሞተው ለማልቀስም፣ ለማዘንም እየየውን ለማቅለጠም ጊዜና ቦታ ይጠይቃል።
ኢትዮጵያ በጠላቶቿ ዛሬ ላይ ከውስጥም በእናት ጡት ነካሾች ተወጥራለች፣ ከውጭም በታሪካዊ ጠላቶቿ ተከባለች። አሁን ያለንበት ሁኔታ
ከተደቀነባት አደጋ እንዴት እንድምንታደጋት የምክክርና የትብብር ጊዜ እንጂ የንትርክ ጊዜ ከቶም ሊሆን አይገባም። ሂሳብ በኋላ እንደልማዳችን
እናወራርዳለን። እየየ ሲዳላ ነው!
እኛና የጥቁሩ ዓለም
ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝብ ነጻነት ተምሳሌት ናት። አፍሪካ ውስጥ የሁሉም ፈር ቀዳጆች እኛ ነን። ነጭን አሸንፎ ነጻነትን
ማስጠበቅ፣ ከተነጠቅን ማስመለስ እንደምንችል ያሳየን ከጥቁር ዓለም እኛ ብቻ ነበርን። በኛ ምክንያት ዛሬ 54 ነጻ የአፍሪካ አገሮች
አሉ። በኦሎምፒክ ሜዳ ላይ እንኳን ነጭን በሴቶችም በወንዶችም ለመጀመሪያ ጊዜ በሩጫ ማሸነፍ እንደሚቻል ያሳየን እኛ ኢትዮጵያውያን
ነን። ዛሬ ኬኒያ የሩጫን ነገሥታትን አፍርተው ወርቁን ያግበሰብሱታል። ታዲያ ይኽ ለጥቁር ህዝብ ተምሳሌታችን በአንጻሩ በነጩ ዓለም
ቂም አትርፎልን ጥርስ ውስጥ አስገብቶናል። ሲሹ ይፈልጉናል። ስንፈልጋቸው የሉም። "ሥራችሁ ያውጣቸሁ" ብለው ከሚጎዱን ጠላቶቻች ጎን
ይሰልፋሉ። ነገ ድል ስንነሳ ደሞ “ተወዳጁን” እያሉ እየተንቀረፈፉ ይመለሳሉ።
ይህቺን አገር ለማጥፋት ያልተሸረበ ሸርና ሴራ አልነበረምም የለምም። ሲወጓት፣ ሲያጠቋት፣ ሲቆርሷት፣ እያነሰች እያነሰች፣ አላልቅ ያለች አገር
ናት። በኛ ዕድሜ እንኳን በስንት መስዋዕትነት የተመለሰችውን ኤርትራን ዓይናችን እያየ አስቆርሰው ከመሄዷ ባሻገር አሰብንም ይዛ ሂዳ
ወደብ አልባ አገር አድርገዉናል። ከዚያ ቀደም ብሎ ጂቡቲም ተቆርሳለች። የሚገርመው ጨርስናቸው ሲሉ፣ እንደገና እንበዛለን። አናልቅም።
በምግብ ዕርዳት ምጽዋት ይይዙናል። አሁን ግድብ ለመሥራት በመጀመራችን ነው ይኸ ሁሉ በደል የደረሰብን። ዛሬ ያለነበት ሁኔታ ይኽን ይመስላል።
ፍቱን መድኃኒታችን ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ህብረታችን ነው። መለያየት
ሞት ነው። መከፋፈል ለገዳዮች ምቹ ዒላማ መሆን ነው። በታሪካችን አባቶቻችን ጠላት ሊያጠቃ ሲነሳ፣ የግል ቁርሾአችውን ቁጭ አድርገው፣
በአንድነት ከመከላክል ውጪ ምርጫ አልነበራቸውም። ይኸን ገድል ነበር ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችን አባቶቻችን ያሳዩት። ታዲያ እኛ ተማርን አወቅን የምንለው ልጆቻቸው ያንን ታሪክ ያንን የአይበገሬነት
ያንን አገራችንን አናስነካም የሚለውን ወኔ ሳንወርስ ነበር የተወለድነው? ባዶ ቀፎዎች ነን፡፡
ከታሪካችን ማኅደር
Berlin Conference |
መስከረም ፯ ቀን ፲፰፹፰ ዓ.ም እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ ፡፡ እንግዲህ ግን ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ለኔ ሞት አላዝንም ፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም ፤ እንግዲህም ያሳፍረኛል ብየ አልጠረጥረውም።
አሁንም አገር የሚያጠፋ ፣ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር በር አልፎ መጥቷልና እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ ፣ የሰውንም መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር ። አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጥውም ። ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም አሁንም ጉልበት ያለህ በጉልበት እርዳኝ ፤ጉልበትም የሌለህ ለልጅ ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በኀዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ አልተውኸም ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም ፡፡ ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረኢሉ ከትተህ ላግኝህ።
ከአድዋ ድል በኋላ ብዙም ርቀን አልሄድንም። ከአጤ ምኒልክ ዕረፍት በኋላ ወደተለመደው ሽኩቻ አባቶቻችን ገቡ። በልጅ እያሱና በአጤ ኃይለሥላሴ መሀል
በነበረው የሥልጣን ፍልሚያ እንደገና ራሶችና ደጃዝማቾች ተቧድነው አገር ተከፋፈለች። ያኔ ያከበረን ዓለም እንደገና ለውርደት አሳልፎ
ሰጠን። ለምን?
መልሱን ባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ (Baron Roman
Prochàzka) የተባለው የኢትዮጵያ ጠላት በ1935 ዓ.ም. ከጻፈው "አቢሲኒያ: የባሩድ በርሜል" (Abyssinia: The Poweder Barrel) ከሚለው
እናገኛለን። ኢትዮጵያን የመበታተን እቅዱ ሲያስረዳ፣ ትልቁ ስትራተጂ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ጎሳዎች እርስበርስ እንዲተላለቁ ማድረግ
ነው ይላል። በተለይ አንድ አማራ የሚባል ነገድ አለ። ያ ሕዝብ ለነጮችም አደገኛ የሆነ ዘር እንደሆነ ያትታል። የኸንን ወገን ሎሎችን
በማነሳሳት ካጠፋነው፣ ኢትዮጵያ የምትባል አገር በቀላሉ ልናጠፋት እንችላለን ይላል። እንደዚያ ተከፋፍላ እያለች ነው ይኸችን አገር
ነጥቆ በቅኝ መያዝ የሚቻለው በማለት ይመክራል።
ይኸን መጽሐፍ ባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ በጻፈ ማግስት ነበር ጣሊያን ጦሯን ሰብቃ የወረረችን። እሷ ስትወረን፣ የኛ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባልነት ዋጋ አጣ። ድሮም “ዶሮን ሲያታልሏት በመጭኛ ጣሏት” ይባል የለ? አጤ ኃይለሥላሴ የክተት አዋጅ አወጁ። የተለመዱት የምዕራብ መንግሥታት ዕርዳታቸውን ስንሻ ጀርባቸውን አዞሮብን። ከግዚአብሔርና ከሕዝባችን በስተቀር ማን አገሪቱን ያደን? እንደገና ሕዝቡ ከጋምቤላ እስከ ሀረር፣ ከጊዶሌ እስከ መቀሌ ማይጨው ላይ ንጉሠ ነገሥቱን ተከትሎ ተመመ። (ለምን ይሆን ሁሌ ነጫጭ ጠላቶቻችን ትግራይ ላይ የሚገጥሙን? እንቆቅልሽ አልሆነባችሁም?) አባቶቻችንን ፋሽስቶችን ታንክ ላይ እየወጡ ጎትተው አንገታቸው በጎራዴ እየቀሉ በጀግንነት ተዋጉ:: ያ ሁሉ ታንክ፣ ያ ሁሉ ከባደ የጦር መሣሪያ እያረዳቸው፣ ያሁሉ የመርዝ ጋዝ እየዘነበባቸው ስባቺ (Sbacchi) እንደጻፈው፣ አባቶቻችን 10,000 የጣሊያን ወታደሮችን ገድለው፣ 44,000 አቁስለዋል[i]። ፋሺስቶች ጊዜያው ድል ቢቀዳጁም ቋሚ ሊያደርጉት አልቻሉም። እነወጣት ጃካማ ኬሎ፣ እነአቢቹ፣ እነገረሱ ዱኪ፣ እነበላይ ዘለቀ, እነደስታ ዳምጠው እነ ኃይለማርያም ማሞ፣ እነ አድምቄ በሻህ፣ እነ አብረሀ ዶቦጭና ሞገስ አስገዶም፣ ምድሪቱን በጣሊያን እግር ሥር የምትፋጅ ረመጥ አደረጉባት። በሸዋ፣ በጎንደር፣ በጎጃም መንቀሳቀሻ አሳጡት።
አክሊሉ ሀብተውልድ ሰልፍ ላይ |
አንበሶች አባቶቻችን ከጣሊያኖች ከቀሙት መሣሪያ ጋር። እዩዋቸው በባዶ እግራቸው
ይኸ ሁሉ የሚያሳየን፣ አባቶቻችን ያቆዩልን፣ አገር እየነደደች ሌላ ሌላውን በይደር የማቆይት ባህላቸውን ነው። ይኸ በዲ ኤን ኤ የተዋሀደን ውርሳችን ነው። ሁሌም ከውጭ ጥቃት ሲሰነዘርብን፣ አንድ ላይ መሆን ልማዳችን ነው። በአንድነት ከውስጥም ከውጪም አባቶቻችን ባደረጉት የአንድነት ተጋድሎ፣ አውርፓ ሁለተኛ የዓለም ጦርነት ሲነሳ፣ ኢትዮጵያ በ1939 ገደማ ጣሊያንን ከምድሩ “ማማ ሚያ!” እያስባለች ጠራርጋ አወጣች። ቢዘገይም፣ ለራሷ ስትል እንግሊዝ እንደረዳችን አልረሳሁም። የአባቶቻችን ሕብረት ወሳኝነት ሳይረሳ ከተውልድ ትውልድ ሲተላለፍ ይኖራል። እኛ ልጆቻችው ተዘናግተን አጽማቸው አጽማቸው እንዳይወጋን እንጠንቀቅ።
ነጉሡ ከሥልጣን ወርደው የደርግ ጊዚያዊ አስተዳደር ሥልጣን ላይ በወጣ ጊዜ፣ የተቃወሙትን
ወጣቶች እየጨፈጨፈ መንግሥቱን ሊያጠነክር ሲሞክር፣ ሕዝብ ተከፋፍሎ ነበርና፣ የአውርፓና የአሜሪካ መንግሥታት ጀርባቸውን ሲያዞሩብንና
እንደታወጋንም ሶማሊያን አስታጥቀዋት “ጃዝ”! አሏት። ወራን አዋሽን ልትሻገር ምንም አልቀራትም ነበር። መከፋፈል ሞት ነው፣ የምንልበት ዋናው
ምክንያት ይኸው ነው። ደርግ አራጅ ቢሆንም፣ ያለው ምርጫ በሱ ዙሪያ ሁኖ አገር ማዳን ነበርና ሚሊሺያው ከአራቱም ማዕዘናት ተምሞ
ሶማሊያን ወደ ሞቃዲሾ መለሳት። እርግጥ ምዕራቦቹ እንደልማዳቸው ለጅብ አሳልፈው ቢሰጡንም፣ የራሻያን፣ የክዩባንና የየመንን ውለታ
መርሳት አደራ በሊታነት ነው። ወሳኙ ግን የሕዝባን አንድነት ነው። እንደነ ዓሊ በርኬ ያሉት ጀግኖች የወጡት በሚሊሺያነት ከወለጋ
ከተመሙት ገበሬዎች መሀል መሆኑን አንርሳ።
ታሪካችንን እናስተውል። ምንጊዜም የምዕራቡን ዓለም፣ ለአላፍታ እንኳን አንመናቸው። ኢትዮጵያ ትንሽ ከተንገዳገደች፣
ብትንትኗን ለማውጣት እንደሚዞሩብን መርሳት የለብንም። ሽብርተኛ ተበሎ ለተፈረጀው ወያኔ አልንበር እንዴ በ1991 ለንደን ላይ ተሰብስበው
እንዲበታትነን ያስረከቡን? ብንረሳ ብንረሳ የእንሊዝንና የአሜሪካን ሚና እንዴት እንርሳ?
ከሀዲው ወያኔ ሥልጣን ላይ ወጥቶ ኢርትራን ረድቶ ሲያስገነጥል ሕዝባችን አንጀቱ ቆስሎ ነበር። ዓይናችን እያየ ኢርትራ
ሌላ አገር ሆነች። እንደ ሶማሊያና እንደ ጅቡቲ ባዕድ አገር ሆነች ማለት ነው። ቢሆንም በዘረፉት ንብረት ክፍፍል ላይ ሁለቱ በመጣላታቸው፣
በድንበር በማሳበብ ጦርነት ተጀመረ። ብልጣብልጧ ወያኔ፣ የኢትዮጵያዊነትን የአንድነት ወኔ ተረድታ፣ “አገርህ በባዕድ አገር ተወረረች”
(እርትራ ባዕድ ሁና!) ብላ የጦርነት ከበሮ አስጎሰመች። “ተነስተህ ተከላከል” ስትል ሕዝቡን ቀሰቀሰች። ሕዝባችን ንዴቱን አምቆ ግር ብሎ ወጥቶ፣ ሻዕቢያን መክቶ ማስቆም ብቻ ሳይሆን፣ አሥመራንም ለመያዝ ጥርጊያ መንገዱን
ወለል አድርጎ አስከፍቶ ነበር። ክህደት ልማዷ የሆነው ወያኔ፣ ድሉን ወድሽንፈት ቀያራው፣ እንድመንግስት ጦርነቱን አስቁማ፣ አልጄርስ
ላይ ሂዳ ተፈራርማ፣ በጦርነት ያጣችውን መሬት፣ በስምምነት አሳልፋ ለኤርትራ ሰጠች። ወያኔ ኢትዮጵያን ለማጥፋት አሻንጉሊታቸው ስለነበረች፣ ምዕራባውያን
ግን ከጎኗ ቆሙ። ወያኔ ለምታደርሰው ሰባዊ መብት ትንፍሽም አላሉም። አማረው በያለበት ሲታረድ ዝም ጭጭ ነበር ያሉት። ወያኔ መገልገያ
መሣሪያቸው ናታ! ለምሳሌ፣ አሜሪካን ከሶማሊያ ተወርዳ ስትወጣ፣ ብርና መሣሪያ አስታጥቀው ወደሶማሊያ ያስዘመቷት የወያኔን ጦር ነበር።
ኢትዮጵያ ሳትሆን የተፈለገችው፣ ከሀዲዋ ወያኔ ነበረች።
ዛሬ ላይ
ይኸንን ሁሉ የታሪክ ጭብጥ የዳሰስነው፣ የአሁኑን ሁኔታችንን ለመረዳት ነው። ወያኔ የጠላቶቻችን ቅጥረኛ ነበረች። ዛሬም ሙትቻ ሁና ጻድቃን ገብረተንሳይ ገና አልተያዘምና ከመቃብር ሊያወጧት የሯሯጣሉ። ሥልጣን ላይ በነበረችበት 27 ዓመታት በሙሉ ያደረገችው ከህደት ተመዝግቦ ቁጭ ብሏል። በሕዝባዊ ግፊት ከሥልጣን የወረደችው የከሀዲዎቹ ቡድን ወያኔ፣ መቀሌ ገብታ ለሁለት ዓመታት፣ ያልጠነከረውን የዐብይን መንግሥት ስታተረማምስ ኖረች። ነገሩ አወቅኩሽ ናቅኩሽ ሆነና ለሽምግልና ሁሉ አስቸገረች። ሰማንያ ከመቶው የአገሪቱ የጦር መሣሪያ በትግራይ ነበረ። ያንን ከያዘች፣ በምድር ላይ የሚያቆማት ኃይል ያለ አልመሰላትም። አንድ ሙሉ ክፍለጦር ትግራይ ውስጥ ነበረ። ያንን በጊዜ ለማውጣት ተሞክሮ፣ ሕዝቡ መንገድ ላይ እየተኛ አናሳልፍም ብሎ እንዳይወጣ አገደች። ምክንያቷን ለመረዳት ቀላል ነበር። ከ20 ዓመት በላይ እዚያ አካባቢ ከጠላት ክልሉን ሲጠብቅ የኖረ ኃይል በመሆኑ፣ ያንን በሰላም ከለቀቀችው፣ የትግራይን መልክአ ምድር፣ አባጣ ጎባጣዋን፣ ጓዳ ጎድጓዳዋን ጠንቅቆ የሚያውቅ ኃይል በመሆኑ፣ ጦርነት ስትጀምር መንግሥትን ማሸነፍ የሚቀል እንደማይሆን ስለተረዳች፣ እዚያችው ሁኖ ለእርድ እንደሚዘጋጅ ከብት ማስቀመጥ ነበረባት። ወታደሩ ካምፕ ሲሆን፣ ጦር ማሣሪያ ግምጃ ቤት (store) አኑሮ ተጎልቶ እንዲቀመጥ አደረገችው። በለመደችው በአንድ ኅዳር ሌሊት የክህደት “መብረቃዊ” ጥቃቷን አደረሰችባቸው። “ጦርነት ከተጀመረ፣ ቁርሳችንን ባሕር ዳር እራታችንን አዲስ አበባ እንበላለን” የምትለዋን ትዕቢቷን ጀመረች። ያን ሁሉ ካዘጋጅች በኋላ ነው እንግዲህ ለእርድ ያዘጋጀችውን የሰሜን እዝ ክፍለጦሩን ወታደሮች በተኙበት በማረድ ጦርነት የጀመረችው። በነገራችን ላይ አንድ የጦር መሪ የነበሩ ሰው እንደነገሩን፣ አንድ ክፍለ ጦር የሚባለው 48,000 ገደማ ተዋጊ ኃይል ያለው ነው። ከዚያ ውስጥ ከኤርትራ የተመለሱት፣ በየበረሀው ጥለዋቸው የሸሹት፣ ከመቀሌ የተሰበሰቡት አንድ ላይ ተደምረው፣ 12,000 ብቻ ነበር የተረፉት። 36,000 በተኙበት ፈጇቸው ማለት ነው። ይኸ የጦር ወንጀል በዓለም ፍርድ ቤት አስከስሶ የሚያስቀጣ ነበር። ዳሩ ምን ይደረግ! አባቱ ዳኛ! ልጁ ቀማኛ! ማን ላይ ቁመሽ ማንን ተክሺያለሽ ነው ነገሩ!
አሸንፌ እገባለሁ ብላ ነበር
ወያኔ በእርግጠኝነት ጦርነቱን የጫረቸው። አሸነፋ አዲስ አበባ ስትገባም ዲፕሎማሲያዊ
መከላከልን ለማድረግ፣ በተባበሩት መንግሥታት የዓለም አቀፍ የምግብ ድርጅት ሹም አድርጋ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ የነበረውን ቴውድሮስ
አድሀኖምን በብዙ ጉቦ አስገባች። በሰብአዊ መብት እንዳትወቀስ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ውስጥ የራሷን ካድሬዋን ፍሰሐ ተክሌን አስቀመጠች፣
በተባበሩት መንግስታት የዓለም አቀፍ የምግብ ድርጀት ውስጥ እንዲሁ በርሀ ገብረእግዚአብሔር ተኮላ የተባለውን አስቀምጣለች። በሺ
የሚቆጦሩ ዲጂታል ወያኔዎችን በማኅበራዊው ሚዲያውን አጥለቅልቃ ነበር። በተረፈ፣ አሜሪካን አገር እነሱዛን ራይስ ቅምጥ
ወዳጆችዋ አሉላት። የኦባማ ሰዎች እንዳሉ፣ ባይደንንም ጨምሮ፣ ወገኖቿ ናቸው። ከአማራው ወልቃይትንና ሑመራ እንዲሁም ራያን ቀምታ
አማሮችን ስትጨፈጭፍ እያዩ፣ እየሰሙ ጭጭ ያሉት አሜሪካና እግሊዝ ምንም እንደማይሏት ታውቅ ነበር። ኦሮሚያ ውስጥ በአርባ ጉጉ፣
በበደኖ፣ በወተር በመሳሰሉት ቦታ አማሮች ታርደው ገደል ሲጣሉ፣ አሜሪካ መቸ ድምጽ አሰማች? እንግሊዝ አገር፣ ሌበር እንዳለ ከበረሀ ጊዜ ጀምሮ ወገኗ አድርግዋአለች። ለምሳሌ የኒል ኪኖክ ሚስት፣ ግለኒስ ኪኖክ
በረሀ ድረስ ትግራይ ገብታ ሲዋጉ አይታ መጥታ እርዳታ አሰባስባላቸዋለች። እነቶኒ ብሌር ወያኔ ህዝቡ ላይ የምታደርሰውን ሰቆቃ ወደጎን
ትተው አልነበር መለስን የአፍሪካ ባለሟላቸው አድርገው የሾሙት? እነ ሎርድ አልተን የመሰሉ ቅልብ አፈቀላጤዎች አሏቸው። ከጋዜጠኞች፣ እነ ማርቲን ፕላውት፣
ዊሊያም ዴቪድሰን፣ አለክስ ዲ ዋል የተባሉት በገንዘብ ተገዝተው ቅልብ ተቀማጮች ሁነው ተዘጋተው ነበር። የትርግራይ ሪፓብሊክ ሊመሠረቱ! ነገሩ ሌላ ሆነና፣ አሁን ከሞት ሊያድኗት ይሯሯጣሉ፡፡
የወያኔ የድል ብሥራት ሊሰሙ አሰፍስፈው ሲጠባበቁ የነበሩት ምዕራባውያን፣ ያልጠበቁት ነገር ያልጠበቁት ነገር ሲከሰት ዕጢአቸው ዱብ አለች። ። በቀናት አዲስ አባባ ትገባለች የተባለች ወያኔ በ15 ቀን ብትንትኗ ወጣት። በጦር ሜዳ ሽንፈት ሲያጋጥማት፣ በሽሽት ላይ እያለች የጨፈጨፈቻቸው የማይካድራ ምስኪን የአማራ እዝብ ነው። ይኸ በጦር ወንጀል ብቻ ሳይሆን፣ በሰብዓዊ መብትም ጥሰት የሚያስጠይቅ ነበር። እነዚህ ሁለቱ ወንጀሎች፣ በአሜራካን ሦስት ባለሥልጣናት በጊዜው የተወገዙ ነበሩ። እነዚህ ባለሥልጣናትም፣ ረዳት ዋና ጸሓፊው የአፍሪካ ጉዳይ ተጠሪ ሚስተር ቶቦር ናጊ (Tobor P Nagy)፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር ሚስተር ማይክል ሬይነር (Michael A Raynor) እና በሰክሬታሪ ኦፍ ስቴት ማይክል ፖምፔዮ (Michael Pompeo ) ነበሩ። ዛሬ ላይ የእነዚህ ባለሥልጣናት ድምጽ አይሰማም። በነሱዛን ራይስ አቀንቃኝነት፣ የጆ ባይደን መንግሥት ወያኔን ሊያድናት ይሯሯጣል። የመቶ ዓመትን ሽርክና በመቶ ቀን ባይደን አወደመው። ድሮም አሜሪካ ብሎ ወዳጅ! ለማንም አይበጅ!
አሁንም እንደገና ተከበናል
ሰሞኑን፣ የጆ ባይደን መንግሥት ለአሻንጉሊቶቹ፣ ለወያኔ የሚብጁ ውሳኔዎችን
አሳልፏል። የወያኔን ባለሥልጣናት በዘዴ፣ በዕርዳታ መኪኖዎች ደብቆ ለማስወጣት ያቀዳት ትልም ተባኖበት ከሽፎበታል። በተባበሩት መንግሥታት
አስወስኖ በጉልበት ገብቶ ለማስወጣት የሞከራት ትልምም በራሺያና በቻይና አፈር ድሜ ግጦባታል። ስለዚህ፣ በመጀመሪያ መስጠንቀቂያ የራሷን ሕግ በኢትዮጵያ ላይ አተላልፋለች። ሳንቲሟንም ለመከልከል ወስናለች። አልፋ ተርፋ፣ ልክ ያኔ ሊግ ኦፍ ኒሺን ለኢትዮጵያና ለጣሊያን ጦር መሣሪያ
እንዳይሸጥ ብሎ እንደከለከለው (ዕውነቱ ግን ለኢትዮጵያ እንዳይሸጥ ነበር፣ ምክንያቱም፣ ጣሊያንም ጦር መሣሪያ ተመርት ነበር፣ ጀርመንም
የፈለገችውን ጦር መሣሪያ ትለግሳት ነበር)፣ ዛሬም የአሜሪካን መንግሥት ለኢትዮጵያው ባለሥልጣናት ቪዛ እገዳ ጥላለች። ምነው ያኔ
ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሥልጣን ላይ ሁና ያን ሁሉ ደም ስታፈስ ዕገዳ አልጣለችባት? ይኽ ሁሉ የአሜሪካና የአውሮፓ ግፊት እንዳለ
ሁኖ በሌላም በኩል ተከበናል። ኢትዮጵያ በግብጽና በሱዳን በሕዳሴው ግድብ ምክንያት ልተወጋን እየተዘጋጀች ነው። ማይካድራ ላይ አማራውን
ጨፍጭፈው ያመለጡ፣ ወደ ሀምሳ ሺ የሚጠጉ የወያኔ ተዋጊዎችን በስድተኛ ስም ስብስባ ሱዳንና ገብጽ እያሰለጠኑና እየላኩብን ነው::
ሱዳን ድንበሩ ክፍት ሲሆንላት ገብታ መሬት መያዟ ሳይቀር፣ ግድቡ ያለበት ቤኒሻንጉልም የኔ ነው እያለችን
ነው። ከፈለገችም ጎንደር የመያዝ ዝታለች። የወያኔ ደጋፊ ሰልፈኞችም፣ “ጎንደር
ጎንደር የሱዳን” አገር ሲሉ ስመተናቸዋል። ግብጽና
አሜርካ የጦር ሽርኮች ናቸው። አብረው ይለማመዳሉ። ለምን? መቼም እስራኤል ሊወጉ አይደለም። ያው የፈረደባት ኢትዮጵያን ሊወጉ ነው
እንጂ! እኛ ግን “አሜሪአካ ከግብጽ ውጪ ልንላት አልተፈቀደልንም። እሷ ግን አማራና ኤርትራ ከትግራይ ይወጡ እያለችን ነው! ድፍረት! ለምን? የተበታትንን መስሏት! ኢትዮጵያ በዘር ወያኔ ከፋፍላ ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብ ቀብራብን
በመሄዷ አየድለም? "ተከፋፍለዋል፣ ጊዜአችን አሁን ነው" ብለው አይደል የኢትዮጵያ ጠላቶች የተረባረቡብን? የኢትዮጵያ ጠላቶች በሁሉ
አቅጣጫ ተነስተውባታል። አሁን የተያዘው ዘዴ፣ ኦሮሞውን አማራው ላይ ማስነሳት ነው። ኦነግ ሸኔ ያንን ተግባር እየፈጸመላቸው ነው።
ይኸ መንግሥት ገና አልጠነከረም። ጊዜ አሁን ነው ባዮች ናቸው። በተለይ አማራውን መምታት አንዱ ትልቁ የያዙት ዘዴ ነው።
ዛሬም ያ ነባር ሁኔታ እንዳለ ነው። ኦነግ ሸኔ፣ አማሮችን ጨፍጭፎ የሻሻማኔን ከተማ ዶጋመድ አድርጓታል። ዝዋይ ውስጥ
አማሮችንና ክርስቲያኖችን እያደነ በግፍ ጨፍጭፏቸውል። ባለፉት ወራት፣ አጣየን እንዲሁ ዶጋመድ አድርገዋት ሕዝቡን አፈናቅለዋል።
ከሚሴንና ሸዋ ሮቢትን እንዲሁ አቃጥለዋል። የዕቢይ መንግሥት በጊዜ ለነዚህ ምስኪኖች ባለመድረሱ በጣም ተናደንበታል። እያንዳንዱን
“ብልጽግና” ውስጥ የተሰገሰጉትን የኦነግ የውስጥ አርበኞችን እንዴት መንጥሮ አላወጣም ብለንም ተንገብግበናል። መተከል ትላንትና
የጎጃም አካል ነበረች። በአባዛኛው የሚኖረውም የአማራ ሕዝብ ነው። ቀጥሎ ግሙዞች ነበሩ። ሸናሻም፣ አገውም ኦሮሞም ይኖርበት ነበር።
ከወለጋ አሶሳን ወያኔ ቀረፈችና ለጠፋ አካባቢውን በርታን ከወለጋ አስገብታ ቤኒ ሻንጉል አለች። በርታና ጉሙዞች መሆናቸው ነው ባለንብረቶቹ። እንዲያም ሁኖ አማሮች ዛሬም በቁጥር አንደኛ ናቸው። የ2007 ህዝብ ቆጠራ እንደሚያሳየው፣ አማራው 25.41%፣ በርታን፣
21.69%፣ ግሙዝ 20.88%፣ ኦሮሞ 13.55%፣ ሺናሻ 7.73% እና አገው 4.22% ያሳያል። የሌሎቹን ዕጣ ፈንታ ወሳኞቹ ግን በርታና ጉሙዞች ብቻ ናቸው። በመተከል አማራው ለሺህ ዓመታት የኖረበት አገሩ ነው። የኢትዮጵያ ጠላቶች ግን ያንን ሕዝብ ዓድምውበት እንዲፈናቀል
በግሙዝ ቀስትና መትረየስ በታጠቁ ይረሸናሉ። መንግሥት ያንን ማቆም ባለመቻሉ ተናደንበታል። የተፈለገውም ያ ነበር። ግቡን እየመታላቸው
ነው። በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ ነው እንግዲህ የውጪ ጠላት የከበበን። ተከበናል። ኢትዮጵያን የመበታተን ጊዜ አሁን ነው ብለው አሰፍስፈው
ተነስተዋል። እኔም እንድ አንድ ግለሰብ ስላለቁት ወገኖቼ የዶክተር ዐብይን መንግሥት የምጠይቀው ሺ ጥያቄዎች አሉኝ። አገሬን የሚባላ
ድራጎን ክንፉን ዘርግቶ እሳት እየተፋ ሊያቃጥላት ሲያንዣንብብ ግን ያንን ጥያቄን የሙጥኝ ብዬ ልሟዘዝ ወይስ በይደር ላቆየው የሚል
ሙግት ከራሴ ጋር ብዙ ጊዜ ነበር የተያያዝኩት። ተባብረን የመጣብንን አደጋ ካልተከላከን ተያይዘን ልንጠፋ ነው። እየየ ሲዳላ ነው
ይሉሀል የኸ ነው።
ዛሬም ላይ፣ አገር ልትጠፋ ገመድ ተሽርቦላታልና፣ የአባቶቻችንን፣ የወንድሞቻችንን፣ የእናቶቻችንን፣ የእህቶቻችንን መገድል ያንገበግበናል። ግን ገዳዮቹን ለመፋረድ ስንተጋ፣ አገራችንን አደጋ ላይ የሚጥል የኢትዮጵያ ጠላቶች ሴይፍ ተመዞብናል። ሁለት ምርጫ ነው ያለን። ከጠላት ጋር ተባብረን በባንዳነት አገራችንን እናጥፋት ወይስ በመንግሥት ላይ ያለንን ንዴት ለጊዜው ገታ አድርገን የተቃጣብንን መዓት በአንድነት እንደአባቶቻችን ተባብረን እንመክት? ምርጫው የራሳችሁ ነው። ወያኔ እንደሆነች፣ “እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል” ያለችው እንስሳ ብጤ ናት። አንዴ ባንዳ ሁናለችና እዚያው ትበንድድ። እኛ ግን ባንዳ አንሆንም። አገራችንን ለመከላከል፣ ቁርሾአችንን ቁጭ አድርገን ታሪካዊ አደራችንን እነወጣ። እየየ ሲዳላ ነው።
ተስፋ አንቁረጥ። እኛ አንድ ላይ ከሆን፣ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ከዚህ በፊት ያልተወን እግዚአብሔር ከኛ ጋር ነው። ቀጥሎ፣ ሕዝባችን እርስ በርሱ ይነታረክ እንጂ፣ ጠላት ከውጪ ሲመጣብን አንድ ላይ ማበሩን ከጥንት ሲወርድ ሲዋራረድ የመጣ ደማችን ውስጥ ያለ ፍረንጆቹ ዲ ኤን ኤ ነው። ቀጥሎ፣ በክፉ ጊዜ ትታን የማታውቅ ራሺይ ዛሬም አለችልን። ቻይናም "እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ" እያለች ነው። ከዚያ እግዚአብሔር ይመስገን፣ አንዱም በአድዋ እና በ1939ኙ ድል ተነሳስተው ነጻ የወጡት አባዝኞቹ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን፣ እንደ ጥቁር አሜሪካኖቹ፣ ከጎናችን እንደሚቆሙ እንገምታለን። በዚህን ጊዜ የመጣብንን መዓት የመመክት ጉልበታችን ከምንጊዜውም የተሻለ ነው። ስለዚህ ላለመጥፋት እንተባበር። እየየ ሲዳላ ነው።
ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው።
(መዝሙረ ዳዊት መዕራፍ
133 ቁጥር 1)