Tuesday 8 January 2013

‹‹በፍቅርና በመተሳሰብ የምንኖርባት ኢትዮጵያ ትናፍቀኛለች

Andualem Aragie, vice-chairman UDJ
 
‹‹በፍቅርና በመተሳሰብ የምንኖርባት ኢትዮጵያ ትናፍቀኛለች››

‹‹ከእስረኞች ሁሉ ህገ-መንግስታዊ መብቴ ተጥሶ ዘመድ አዝማድ እና ጓደኛ እንዳይጠይቀኝ የተደረኩት እኔ ነኝ››

አንዷለም አራጌ

የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የነበረውንና በሽብርተኝነት ሰበብ ለእስር ተዳርጎ የሚገኘውን ወጣቱን ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌን ከአንድነት ከፍተኛ አመራሮችና አባላት የተውጣጡ ሰዎች ጠይቀውት መመለሳቸውን የሕዝብ ግንኙነት መረጃ ይጠቁማል፡፡ በዋናው መጠየቂያ በር አትገቡም ከተባለ በኋላ ወደ ማረሚያ ቤቱ አስተዳዳሪ የቀረቡት ጠያቂዎቹ ስም ዝርዝራቸው ከተመዘገበ በሁዋላ ሊፈቀድላቸው የቻለ ሲሆን ከወጣቱ ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌ ጋር የማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎች አጠገብ ቢኖሩም ውይይት አካሂደዋል፡፡

ከአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች መካከል ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ፣ አቶ ተመስጌን ዘውዴ፣ አቶ ዘካርያስ የማነብርሃን፣ አቶ ዳንኤል ተፈራ እና አቶ ሙላት ጣሰው እና ከአስር በላይ የሚሆኑ አባላትም በመገኘት የአንዷለም የጤና ሁኔታና የእስር አያያዝ ምን እንደሚመስል ጠይቀዋል፡፡

አቶ አንዷለም በበኩሉ ከራሱ ይልቅ የገዥው ፓርቲ አፈናና ጭቆና እንዲሁም በዚህ ሁኔታ እየታገሉ ያሉ ባልደረቦቹ ጉዳይ እንደሚያሳስበው ገልጦ በእሱ በኩል እንደቀረበበት ክስ በማንም ላይ በክፋት ባለመነሳቱ የህሊና ሰላም እንደሚሰማው ተናግሯል፡፡ አሁንም ግን ኢትዮጵያና ፖለቲከኞቿ ስለፍቅርና መተሳሰብ ሊገባቸው እንዳልቻለና በፍቅር ተሳስቦ መኖር የሚባለውን እንደሚፈሩት ይሄም ነገር ክፉኛ እንደሚያሳስበው ተናግሯል፡፡

በተያያዘም በቃሊቲ ከሚገኙ እስረኞች በተለየ 6 ሰው በሚያድርባት ጠባብ ክፍል የታሰረና እንደማንኛውም እስረኛ ዘመድ አዝማድ ጓደኛ እንዳይጠይቀው የተደረገ ብቸኛ ግለሰብ መሆኑን የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ በተገኙበት ፊት ለፊት ተናግሯል፡፡

ለእኛ ቀርቶብን ለልጆቻችን እንኳን የተሻለ ማረሚያ ቤት ማስተላለፍ አለብን ያለው አንዷለም እሱ ላይ ብቻ ያነጣጠረው የመብት ገፈፋ ተገቢ እንዳልሆነ ፊት ለፊት ገልጧል፡፡ በዚህ ሃቅ የተበሳጩት ኃላፊው ‹‹ተነስ ግባ!› የሚል ዘለፋ የአንድነት አመራር አባላት በተገኙበት ፊት በብስጭት ተናግረዋል፡፡

የአንድነት አመራርና አባላትም የተጀመረው ትግል ግቡን እስኪመታና በፍቅርና መተሳሰብ የምንኖርባት ኢትዮጵያ እስከምትፈጠር ከትግሉ ሜዳ እንደማያፈገፍጉ አረጋግጠውለታል፡፡

Taken from
http://www.fnotenetsanet.com/?p=2925#comment-102

No comments:

Post a Comment