Friday, 26 April 2013

ፊየል ከመድረሷ ቅጠል መበጠሷ


ፊየል ከመድረሷ ቅጠል መበጠሷ

ወንድሙ መኰንን፣ ሎንደን፣ እንግላንድ 25 April 2013

“ኢሳታዊ ሐረት???” ምን? ጉድ ፈላ። ግዕዙን አረብኛ ተካው ልበል?! ቅዱስ ሚካኤል ወይም ቅዱስ ገብርኤል ሳይሆን፣ ወያኔ ሰሞኑን ክንፉን የዘረጋላቸው የሎንደን ደብረጽዮን ቅድስት ማርያም ጥቂት “ካህናት” በየውሸት መነኲሴው አመራር፣ ጭራሹኑ ሐፍረታቸውን ጥለው፣ ቤተክርስቲያኒቱን በዚህ ዓቢይ ጾም ጥርቅም አድርገው መዝጋታቸው ሳያንስ ወያኔ ብብት ውስጥ ለመሸሸግ ተጥግተው ገና የእግራቸው ጢዛ ንእንኳን ጠፈፍ ሳይል፣ ቋንቋውን አቀላጥፈው መናገር ጀመሩ። “ሐረካት! ሐረካት!” ብለውን አረታ! ይሻላቸዋል። “እየመጣሽ ተኚ” አሉ አባ!



ነገሩ እንዲህ ነው። ሐሙስ ዕለት ከጠዋቱ 5 ሰዓት ከ44 ደቂቃ ላይ “ግርማ” ከሚባል ስም “ESAT HAREKAT.pdf” የተላከ ኢ-ሜይል ደረሰኝ። በቅጡ ሳላነበው፣ አየት አደረግኩትና በሥራ ተወጥሬ ስለነበር፣ የአሜሪካው ጓደኛዬ ግርማ በቀለ ይሆናል፣ “በኋላ አነበዋለሁ” ብዬ ችላ አልኩት። እንደገና ያው ኢሜል በዚያው ስም 6 ሰዓት ከ8 ደቂቃ እንደገና ከቸች አለ። “ሆሆይ! ግርማ ለቀቅ አርግኝ! እኔ ለራሴ መጨረስ የነበረብኝን  ሥራ መጨረስ አቅቶኝ እየተሯሯጥኩ ነው! አትነዝንዘኝ!” ብዬ ሥራዬ ላይ ድፍት አልኩኝ። እንደገና ከ8 ደቂቃ በኋላ ለሶስተኛ ጊዜ ከዚያ ግርማ ያው ኢሜል አቃጨለብኝ። “እዲያ! ችኮ! አልለቀቅከኝም ማለት ነው”  ብዬ ንጭንጭ እያልኩኝና፣ ከፈትኩት! የ-የካው ሚካኤል! “ዓይኔ ነው - ባሌ ነው” አለች አሉ ሴትዮዋ፤ እሱም ሲሰርቅ እሷም ስትሰርቅ በመስመር ተጋጭተው! ሰዎቹ ብሶባቸዋል ማለት ነው! ፈጠጠብኝን ጉድ እዩ!

ይኸ በሕብረቀለማት ያሸበረቀ ጽሑፍ፣ (ሙሉውን ለሚፈልግ በግሉ እልክለታለሁ) እዬዬውን የሚያቀልጠው፣ “ኢሳት ጋዜጣዊ ሐረካት አፋፋመብን” እያለ ነው።  ወይ መከራና ጣጣ! በቃ ወያኔ ከብብቱ እየመዘዘ አዲስ ቃል እየፈበረከ በአቀረሸብን ቁጥር፣ ጀሌዎቹ እየተቀባባሉ ደጋግመው ጆሮአችንን ጭው ማድረጋቸው  ሳያንስ፣ እኛም እንገራረፍበት ገባን ልበል! አንዴ መለስ ዜናዊ ያስቸገረውን ወጣቱን ትውልድ ሊሰድብ ፍልጎ፣ “ወጣቱ ሥራ ፈት ፍንዳታ ነው አለ።” አባባሉ ስሜት እኮ አይሰጥም! በቃ ካድሬዎቹ ተቀባበሉና፣ “ፍንዳታ! ፍንዳታ!” ማለት አመጡብን። ወጣቶቹም ነገሩ ግራ ቢገባቸው “ይኽች ነገር ጥሩ ሳትሆን አትቀርም ብለው ነው መሰለኝ፣ እርስ በርሱ “ወጣት ናት፣ ቆንጆ ናት፣ ወጣት ነው፤ ቆንጆ ነው” ማለት ሲፈልጉ “ፍንዳታ ናት፤ ፍንዳታ ነው” ማለትን አመጡብን! እሺ እሱስ ይሁን አማርኛ ነው፣ ግን ይኽቺ የወያኔ “ሐረካት” ምንድናት! ወያኔ ብዙ ብዙ ቃላት አስተምሮናል። ለምሳሌ፣ “እንተርሀምዌ” የሚባል ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ስሰማ፣ ተርበትብቼ “የድክሺነሪ ያለህ!” (መዘገበ ቃላት) ፍለጋ ገባኹ። እሱም አልረዳኝም። ወንድም ታማኝ በየነ፣ “በጀኖሳይድ” ተከሶ በነበረበት ወቅት ሎንደን ብቅ ብሎ ነበር። ቃሉን ባለማወቁ የተሰማውን ስሜት ነግሮን በሳቅ አፈነዳን። “ምንድነው ‘ጄኖሳይድ’ ብዬ ጓደኛየን ጠየቅኩት” አለ ታማኝ። “‘የሰው ዘር ማጥፋት’ ነው ብሎ ነገረኝ!” ታማኝ፣ እራሱን እንደማከክ እያረገ ቀጠለ። “እንዴ፣ በገንዘብ ማጥፋት ብከሰስ እንኳን ይሁን፣  የሰው ዘር ማጥፋት ግን እምኑ ጋ ቁሜ! ታዲያ አንዳንዴ እራስ ምታቴ ሲነሳብኝ፤ እየተሳሳትኩ ‘ጄኖሳይዴ ተነሳብኝ’ ማለት አመጣሁ” አለ። “ሐረካት!” አሉን የኛ ዘመናዮች! ዕውራን እህቶች ወንድሞቼ! ይቅርታ፣ ይቅርታ! ዕውነት መነገር አለበት። ግን ዕውርን ዕውር ሲመራው መጨረሻው ተያያዞ ገደል ነው። በቀቀኖች!

ስለበቀቀን (parrot) ካነሳን፣ አንድ ነገር ትዝ አለኝ። አንዲት ከበቀቀኗ ጋር ብቻዋን ሎንደን የምትኖር ወይዘሮ ነበረች። ሰው በአንኳኳ ቁጥር ከመክፈቷ በፊት “ማነው” ስትል የሰማ ፓሮት፣ በሩ በተንኳኳ ቁጥር “ማነው” ማለትን ተማረ። ታዲያ አንድ ቀን ጠዋት ወይዘሮዋ ተንስታ ለሥራ ወጣች። አንድ ፖስተኛ መጥቶ በሩን አንኳኳ። “ማነው!” አለ በቀቀን ሆዬ ከውስጥ። “ፖስተኛ ነኝ። በሪኮማንዴ የተላከለዎት ደብዳቤ አለዎት። ፈርመው ይቀበሉኝ።” አለ ፖስተኛ ውጭ ብርድ ውስጥ ቁሞ! በር አልተከፈተለትም! አሁንም አንኳኳ! አሁንም “ማነው” የሚል ጥያቄ ከውስጥ ቀረበለት! ፖስተኛው አሁንም ያንኑ መልስ ሰጠ። በሩ አልተከፈተም። ፖስተኛውና በቀቀኑ እንዲቹ ሲባባሉ ዋሉ። በመጨረሻ ፖስተኛው ላንቃው ደርቆ እራሱን ስቶ ተዝለፍልፎ ወደቀ። ወይዘሮዋ ሥራዋን ጨርሳ ወደቤቷ ስትመለስ አንድ ሰው በሯ ላይ ወድቆ አይታ ደነገጠችና “ማነው!” ብላ ጮኸች! በቀቀኑ ከውስጥ “ፖስተኛ ነኝ። በሪኮማንዴ የተላከለዎት ደብዳቤ አለዎት። ፈርመው ይቀበሉኝ።” አለ። የኛዎቹም በቀቀኖችም ያው ናቸው። “ሐረካት” አሉን? ለዛው ሙጥጦች! ሲያናድዱ!

አሁን በሞቴ “ሐረካትን” በግልጽ ኢሳት ላይ መጠቀማቸው አዲሱን ጌታቸው የወያኔን አንጀት ለመብላት ነው? ለመሆኑ፣ ይኸ “ሐረካት” የተባለውን ቃል ወያኔ ከየት መነተፈችው? እንደመሰለኝ ከሆነ እነዚያ “አል ሀባሽ” (al-Ahbash Islamic sect ) የሚሉት ተለጣፊ እስላሞች (ወያኔ መም “አናሳ” የተባለ ሁሉ እያደንደነች ትለጥፍባቸዋለች) አውሰዋት መሆን አለበት። ወያኔ እንዚህን ተለጣፊዎች ተጠቅ፣ አብዛኛውን የአገራችን የእስልምና ሀይማኖት ተከታዩን ሕዝብ ለመደፍጠጥ ሞክረችእስከአሁን አልተሳካለትም! ወዲፊትም አላህ አይቀናትም! ወያኔ ይኸን ጥራዝ ነጠቅ የአረብኛ ቃል ተውሳ፣ ድራማ ስትሠራ ያዩ የሎንደኑ የውሸት መነኲሴና ደንገጡሮቻቸው እነሱም መወያናቸውን ሊያረጋግጡላት፣ “ኢሳት ቴሌቪዢን ጋዜጣዊ ሐረካት አፋፋመብን” ብለው ኢሪታቸውን ማቀለጣቸው፣ በአንድም ብኩል ያሳዝናል በሌላውም ያስቃል። “ሐረካት” አረብኛ ቃል ሁና ሳለች፣እንግዲህ የበግ ለምድ በለበሱ የወሸት መነኲሴ ተቀደሳ፣ ቤተክርስቲያናችን ስተት ብላ ልተገባ ነው መሰለኝ። ወያኔ፣ ድሮውንም እርጉም የተረገመች እምነት ቢስ ስለሆነ “ሐረካት” ብትለን ያምርባታል። የሚያሳዝነው፣ የእስላም አል-ሀበሾች አባዛኛውን አማኝ ማወናበዳቸው ሳያንስ፣  የኛዎቹ የክርስቲያን አል-ሀበሾች ደግመውለነሱ ካልሆነ ሰርዶው አይብቀል ሆንባቸው ክርስቲያናችንን ለማስነጠቅ “ሐርከውብን (ትርጉሙ ምንም ይሁን ምን) ማረፋቸው ነው።

ለቋንቋው ክብር ቢኖረኝም፣ ቤተክርስቲያናችን፣ በግብጽ ፓትሪያርካት ሥር በነበረችበት ጊዜ እንኳን “አረብኛ” ተጠቅማ አታውቅም ነበር። ያው ግዕዟን ይዛ ስትንገዳገድ ኖረች። ዛሬ ግን፣ ዓይና አዎጣዎቹ የወያኔ አዲስ ፍቅረኞች፣ ታማኝነታችውን ለወያኔ ለማረጋገጥ (ወያኔን እምፕሬስ ለማድረግ)፣ “ሐረካት! ” ብለውን አረፉት!

ይገርማል! ዓይጥ ሞቷን ስትሻ፣ የድመት አፍንጫ ታሸታለች ነው የሚባለው? ኢሳት እንዲያውም አባ ትብዬውንና ደንገጦሮቻቸውን እንተርቪው ለማድረግ ያልቧጠጠው ቋጥኝ አልነበረም።

ተከራከሩና ሀሳባችሁን ግለጡ!” “እምቢዮው”!
እንተርቪው ስጡ!” “እምቢዮው!”

ሌቦች ናቸዋ! በኋላም፣ በስንት መከራና ልመና አይደል፣ ስቱዲዮ ሳይሆን ቤተክርስቲያን  ለዚያውም ሞገደኛውን “አባ” ሳይሆን፣ አለብላቢት ደንገጦሮቻቸውን፣ ያ ሁሉ ጊዜ ሰጥተዋቸው፣ ኢንተርቪው የተደረጉት? አሁን “ሐረካት! ሐረካት!” እያሉ እሳት ላይ ማላዘን፣ ምን ይባላል? አዲስ አበባ ቢሆን እሺ! ግዛታቸው ነው! እዚህ ሕግ አለ።እናንተ ጉደኞች! ይኸ ለሞታችሁ መሆን አለበት! ስትሞቱ እናንተን አያርድርገኝ። ከታጋይ ጳውሎስ ጋር ገሀነም በሯን ወለለ አርጋ ከፍታ እሳቷን አንድዳ ትጠብቃችኋለች። መቼም በጾም ምድር አሰናካላችሁን፣ ቤተክርስቲያናችንን ጥርቅም አድርጋችሁ ዘግታችሁብን፣ መንግሥተ ሰማያት መግባት አታስቡም! ታስባላችሁ እንዴ? “ሊቀ-ሊቃውንታችሁ” የመንገሥተ ሰማያትን ሳያሆን የገሀነምን ቁልፍ ይዞ ነው የሚያሽከረክራችሁ።

የኛዎቹ አዲሶቹ ሐረካውያን፣ “ሐረካትን” ደርሰው ለኢሳት ከመላካቸው ጎን ለጎን፣ የቤተክርስቲያናችንን እንጻ ለወያኔ ሹመኞች የማስረከቡን ሩጫ አጧጡፈዋል። አንድ በምዕራብ አውሮጳ የቤተክርስቲያን አለቃ ነኝ ባይ የቤት መለቅለቂያ፣ ለዚሁ ጉዳይ፣ አዲስ አበባ ሂዶ፣ ወሸታሙን መነኲሴ ካቆመሱት ከአዲሱ ፓትሪያርክ ከአባ ማቲያስ ጋር ተነጋግሮ ተመልሷል። “አቡነ ገብርልና አቡነ ቆስቶስ የተባሉ፣ ለሰማዩም ለምድሪቷም የከበዱ፣ ለሰውም ለመላእክክቱም የገዘፉ፣ ሁለት ተዋጊ አቡናት ታዘው ወደ ሎንደን ጉዞ ጀምረዋል። ፉከራቸው፣ እንሱና የሰኩሪቲ ጥበቃ በተገኘበት፣ ለንደን ደብረጽዮን ቅድስት ማርያምን ለመቆጣጠር ነው። ለመሆኑ እነዚህ አቡናት፣ መስቀል ነው ወይስ መትረየስ ደግነው ነው የሚመጡት? ድንበር ላይ ይፈተሹ! እንግዲህ ለሆሳዕና ቤተክርስትያን ሊክፍቱ እዚህ ያለው ሹመኛቸው የዛተው ዛቻ ለኔም ልትንሹ በግሌ ደርሶኛልእንተያያለን። ታጋይ ጳውሎስ የቀመሷትን ዱላ ሳይቀምሱ እነዚህ አባቶች ቤታቸው አርፈው ቢቀመጡ ለነሱም ለኛም የተሻለ አማራጭ ነበር! ከመጡም፣ ሸቀጣ-ሸቀጣቸውን ሸምተው በሰላም ቢመለሱ መላካም ነገር ነው። አንጡራ ሀብታችንን አንጠፍጥፈን የገዛናትን ቤተክርስቲያን በሕይወት ቁመን እያለን መውሰድ የማይታለም ነው። ዕውን እነዚህ አባቶች የሚመጡት፣ የውሸቱን አባ ለማትረፍ ነው ወይስ ለሌላ? ግሩም! ወገናቸው የሆኑትን ጳጳሳት፣ ከታጋይ ጳውሎስ ደብዳቢዎችና አባ እጅጋየሁ መቸ አዳኗቸው? የዋልድባ ገዳም መነኰሳት “ድረሱልን” እያሉ እሪታ ሲያስተጋቡ፣ መች ደረሱላቸው? ለንደን ወይስ ዋልድባ ይቀርባል? ወይስ ሎንደን ብር ስላለች ነው?

በዓለም ዙሪያ የተበተናቸው የኦርቶዶክ ዕመነት ተከታዮች መዕምናን በሙሉ! በሆሳዕና ዕለት ሎንደን ላለነው ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ምሕላ አድርጉልን። ሰልፉም ውጊያውም የእግዚአብሔር ነው።

Saturday, 20 April 2013

“እግዚአብሔር የቀባው”


“እግዚአብሔር የቀባው” 





nigatuasteraye@gmail.com

፳፻፭ ዓ.ም.


ማሳሰቢያ አቡነ ማትያስ  ባሜሪካ ራዲዮ  አማካይነት የኢትዮጵያ ህዝበ ክርስቲያን በ፭፻ ድምጽ መርጦ ፓትርያርኩ አደረገኝ ማለት ጀምረዋል። እውነት እንደሚሉት ባገር ውስጥና በውጭ ካሉት ሁሉ ሰዎች በሙያቸው በቅድስናቸው በምንኩስናቸውና ባገልግሎታቸው ከሳቸው የተሻለ ሰው ጠፍቶ እሳቸው ልቀው ተገኝተው የኢትዮጵያ ህዝበ ክርስቲያን ትምህርታቸውን በረከታቸውንና ቅድስናቸውን ፈልጎ በ፭፻ ድምጹ መረጣቸው?
አባ ማትያስ ተመረጥኩ የሚሉበት ወቅትና አፈጻጸሙ በቤተ ክርስቲያናችን መመሪያ ሲለኩ የእምነት የእውቀትና የሞራል ጉድለት ያለባቸውንና የማያውቃቸውን አባ ማትያስን የመሰለ ሰው የኢትዮጵያ ህዝበ ክርስቲያን ሊመርጥ ይቅርና ብቃት ያለው እንከን የማይገኝለት ሰው እንኳ በዚህ ወቅት አይመርጥም።   ይህንን የመሰለ አጥፊ መንግስት ጥፋቱን የሚፈጽመበት መሳሪያ የሚሆን ሰው ለማግኘት ያለውን ሁሉ ኃይል በመጠቀም ለማጭበርበሪያ ምርጫ ከ፭፻ ሰውም በላይ መሰብሰብ ይችላል:: ይህን የተረዳ ብቃት ያለው ሰው ይሸሻል እንጅ፤ አባ ማትያስን የመሰለ የጥፋት ተባባሪ ካልሆነ በቀር አይገባበትም። የተጀመረው እርቅ ሳይፈጸም ምርጫ እንዳይታሰብ እያለ ህዝቡ የሚያስተጋባውን ድምጽ ደምስሶ ተመረጥኩ ካለ፤ መመሪያችን ምቱር ነህ ይለዋል እንጅ ቅዱስ ብጹዕ ፓትርያርክ ነህ በማለት አይቀበለውም።
አባ ማትያስ በዚህ አይነት ግርግር ወደ መንበረ ፓትርያርኩ እንደመጡ እራሳቸው እያወቁ ሳያስቡትና ሳያልሙት ድንገት በተአምር እንደወደቀባቸው ለማስመሰል “በፈቃደ እግዚአብሄር ተመረጥኩ” ማለታቸው የእግዚአብሄርን ስም በከንቱ የሚጠቀሙ “ቢጽ ሀሳዊ” (ወገን መስሎ የገባ አታላይ ዋሾ) ነበማለት መልስ ልንሰጣቸው የሚገባን እንጅ “እግዚአብሄር የቀባህ” ብለን መቀበል የውሸቱ ተካፋይ መሆን ነው።
አባ ማትያስ “በ፭፻ ድምጽ ተመረጥኩላችሁ” የሚል የእንኳን ደስ አላችሁ! መሳይ መልእክት ከማሰማታቸው በፊት እሳቸው በመጡበት መንገድ የሚመጣውን ፓትርያርያርክ መመሪያችን “እግዚአብሄር የቀባው” ብለን እንዳንቀበለውና ይልቁንም ምቱር “ጭንጋፍ (ምቱር) ፓትርያርክ” እዚህ ላይ በመን ያንብቡ) ነህ እንድንለው የሚጠቁመንን ጦማር እና “እግዚአብሔ የቀባው” በሚል ለህዝብ ቀርበው ተነበው ነበርዚህ ጦማሮች በዚህ መንገድ የሚመጣውን ፓትርያርያርክ እንዳንቀበለው የሚያዝዘንን የቤተክርስቲያናችን መመሪያ ስለሚያብራሩ  እንደገና ብንቃኛቸው ከዚህ ቀጥ “እንዲህ ያለ ፓትርያርክ አይተን አናውቅም” በሚል ርእስ የማቀርበውን ጦማር በተብራራ ሁኔታ መረዳት ያስችላል።:  

  መግቢያ

            
ነቢዩ ዳዊት በአንድ ወቅት “እግዚአብሔርም በቀባው ላይ እጄን እዘረጋ ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቅልኝ” (፩ኛ ሳሙ ፳፮፡ ፲፩) ብሎ ተናግሮ ነበር። በእውነት ይህ ቃል በሥልጣን በተለይም በክህነት አገልግሎት ያሉትን ሰዎች እግዚአብሔር የቀባቸው ናቸውና ቢሳሳቱም “እግዚአብሔር ይቅጣቸው” ብሎ ህዝብ እንዳይናገራቸው፤ እንዳይወቅሳቸውና እንዳይከሳቸው የሚከለክልና የሚያግድ ነውን?
 ዳዊት “እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን አልዘረጋም” ያለው፤ “አማልክተ ኢትህሚ ወለመኮንነ ህዝብከ ኢትበሎ እኪተ” (ዘፍ ፳፪፡፳፰) ማለትም፦ “መሪህን አትንቀፍ አትተችም” የሚለው ህግ ያለ ምንም ገደብ እንዲጠበቅ አልነበረም። ስልጣኑን ወይም ክህነቱን መጋረጃ አድርጎ የፈለገውን ስህተት በህዝብ ላይ የሚፈጽም ማንም ሰው በዝምታ እንዲታለፍም አልነበረም።
ታሪኩ ባጭሩ እንደዚህ ነው። ሳኦል ዳዊትን አሳዶ ለመግደል ቀንና ሌሊት ይጥር ነበር። ከእለታት አንድ ቀን አቢሳና ዳዊት ሳኦልን እንቅልፍ ጥሎት አገኙት። አቢሳ “ዛሬ እግዚአብሔር ጠላትህን በእጅህ ላይ ጥሎታልና እንደተኛ ባንድ ውግ ብቻ ገድየው ልገላግልህ? ብሎ ዳዊትን ፈቃድ ጠየቀው (ሳሙ ፳፮፡፰)። ዳዊት ግን “ሕያው እግዚአብሔር ይመታዋል። ወይም ቀኑ ደርሶ ይሞታል። ወደ ሰልፍ ወርዶ ይገደላል” የሚል የትንቢት ቃል ተናገረ።
ዳዊት እንዳለውም፤ ሳኦል ከሌላ ሰራዊት ጋራ ለመዋጋት በተሰለፈበት ድል ተነስቶ ራሱን በራሱ ገደለ (፩ኛ ሳሙ ፴፩፡፩-፲፫)። ዳዊት በሳኦል ላይ እጄን አልዘረጋም ያለው የሳኦልን ስልጣን ከመረከቡ በፊት የሳኦል ህይወት እንዴት እንደሚቆም በእግዚአብሔር መንፈስ አስቀድሞ ስለተረዳ ነበር።
 “እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን አልዘረጋም” ያለው ዳዊት፤ አስመሳዮችና በወሬ የሚተዳደሩ ሰዎች ደፍረው የማይናገሩት፤ የማይታለፍ ሊገለጽ የሚገባ የፈጸመው የተቀደሰ ነገር አለ። ሳኦል ከሌላ አቅጣከመጣበት ሰራዊት ጋራ ሲዋጋ ተሸንፎ ተስፋ ቆረጠና “በጣላቶቼ እጅ ከመውደቅ ግደለኝ” ብሎ የራሱን ጋሻ ጃግሬ ለመነው። ጋሻ ጃግሬውም አልገደለውም። ሳኦል እራሱን በራሱ ገደለ። ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል ራሱን በገደለበት መንገድ እዜያው ላይ ራሱን ገድሏል” (፩ኛ ሳሙ ፴፩፡፭)። የተፈጸመው ታሪክ ይህ ሆኖ ሳለ፤ ግርግሩን በመጠቀም ሹመት ሽልማት የፈለገ፤ ባካባቢ ሆኖ ይህንን የተመለከተ ወሬኛ፤ ዳዊት ያለምንም ተቀናቃኝ እንደሚነግሥ ተረድቶ፤ ይህን ይዤ ወደ ዳዊት ብቀርብ ጥቅም አገኛለሁ ብሎ በመገመት ያልገደለውን “እኔ ሳኦልን ገደልኩልህ” እያለ ዳዊትን ቀረበው።    ዳዊት በከንቱ ውዳሴ ህሊናውን ያላስጎነበሰ፤ በወሬ ሹመትና ሽልማት ለማግኘት የተቅነዘነዘውን ወሬኛ ሰው ለነገር አቀባይነት ይጠቅመኛል ሳይል መቀጣ ይሆን ዘንድ በሚመራው ህዝብ ፊት ቀጣው (፪ኛ ሳሙ ፩፡፲፮)። ይህ የዳዊትን ማንነት የሚገልጽና ጊዜ ላነሰው ባለ ስልጣን ነገር በማቀበል ለሚኖሩት ወሬኞች ተግሳጽን ያዘለ ትልቅ ትምህርት ነው።
ጥልቅና ምጡቅ በሆነ ምክንያትና ግንዛቤ “እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን እዘረጋ ዘንድ እግዚአብሔር ከኔ ያርቅ” (፩ኛ ሳሙ ፳፮፡ ፲፩) ብሎ ዳዊት የተነገረውን ያልተረዱ ብዙ የዋሀን ሰዎች ሸፍጠኞችን ቢቃወሙ የሚቀሰፉ እየመሰላቸው፤ ጳጳስ ሰረቀ፤ ዘረፈ፤ ዋሸ፤ ዘሞተ፤ ወለደ የሚል ነገር ሲሰሙ መቃወማቸው ይቅርና “ኧረ ኧረረረረ... መስማቱም ኃጢአት ነው!” ይላሉ። ሸፍጠኞችም ይህንን ጥቅስ እንደ ማስፈራሪያ አድርገው በመጠቀም መጋረጃ አድርገውታል። ይህ አይነት መንፈስ ከዳዊት አባባል ጋራ ፈጽሞ የሚገናኝ አይደለም። ሊቃውንቶቻችንም አይቀበሉትም። ጥቂቶችን ለምሳሌ እንመልከት::

የኢ..... ሊቃውንት በደብረ ሊባኖስ

ገዳም የነ የኔታ አንዳርጌ ግንዛቤ


ከዕለታት አንድቀን አንድ በሰው ፊት የተከበሩ፤ ውስጣቸው ግን የተበላሸ ሰው፡ ውሻ ገደል ከሚባለው ቦታ ላይ ስህተት ፈጸሙ። “ስህተቱ ቢገለጽ እግዚአብሔር የቀባቸውን ክብር መንካት ነውና ዝም በሉ ሰውየውንም ሸፍኗቸው” ተባለ። ሰውዬው ግን ይህንን ሽፋን በመጠቀም ወደ ጫጋልና ደብረ ጽጌ እየተዘዋወሩ በስህተቱ ቀጠሉ። በመጽሐፋዊው ቅኔያቸው የተደነቁት የደብረ ሊባኖሱ ገዳም የቅኔ መምህር የነበሩት፤ በኋላ ወደ ተወለዱበት አገር ብቸና ጊዮርጊስ ተመልሰው ያረፉት መሪጌታ አንዳርጌ ካሳ። “ካህን ቢሳሳት እግዚአብሔር የቀባው ነውና አትናገረው” የሚባለው ነገር ወደ ተሳሳተ ባህል ተለውጦ ህዝብ በመጉዳት ላይ መሆኑን በመግለጽ በመጻሕፍት ላይ መስርተው ሙሉ ቤት ዘረፉ። ቅኔው የገዳሙን ሊቃውንት አንቀሳቀሰ። ተመሳሳይ ችግር የነበረባቸው በሳቸው ላይ እያጉረመረሙ ተነሱባቸው።
 በዚያው በውሻ ገደል ይኖሩ የነበሩት፡ የስመ ጥሩው የስሬው ቅኔ መምህር የኔታ ጥበቡ ደቀ መዝሙር የነበሩት፡ ሌላው የገዳሙ የቅኔ መምህር የኔታ አምዴ፡ የሳምንቱ የቅኔ ባለተራ ስለነበሩ በእጣነ ሞገር ቅኔያቸው የእለቱን ቅዱስ ካወሱ በኋላ፡ በአሰረ ንጉሡ ላይ የየኔታ አንዳርጌን ቅኔን የሚደግፍ በሊቃውንቱ ፊት ተቀኙ። በብህትውናቸው በቅድስናቸው የሚደነቁ የኔታ ላእከም፤ ግርማ በተሞላበት ድምጻቸው “ይበል” ብለው ከቀመጡበት ብድግ አሉ።
የኔታ አንዳርጌም “ስህተቱ ቢገለጽ እግዚአብሔር የቀባቸውን ክብር መንካት ነውና ዝም በሉ ሰውየውንም ሸፍኑት” እያሉ የሚያስተምሩ ሰዎች የሚቀጥሉና፤ ሕዝቡም ትምህርቱን አምኖ የሚቀበለው ከሆነ፤ ነውር ነው ተብሎ ሊታፈርበት የሚገባው ሁሉ ኃጢአት ባህል ይሆናል። መዋረድና ማፈር የሚገባቸው መልካም እንደሰሩ ሆነው ይሸለሙበታል። የሞራል፤ የስነ ምግባር ሰዎች፤ አንገታቸውን እንዲደፉ፡ እንዲናቁ፡ እንዲዋረዱና እንዲያፍሩ ይደረግበታል ብለው ከሳቸው በፊት የነበሩት አለቃ ንጉሤ የሚባሉት ሊቅም በዚህ ላይ የተቀኙትን ነግረውናል። ቅኔውም እንደሚከተለው ነው።
አይቴኑ ለነውር ብሔረ ሙላዱ፤ በውስተ ኩሉ ብሔር እስመ ከመነግድ ይሄሉ።
ትምህርተ ዝኒ ነገር ከመ ይትግሀድ ለኩሉ።
ኀጥዕ ይሳለቅ ላዕለ ጻድቅ፤ ከመ ዘንጹህ ወሠናይ ባህሉ።

እስመ እንዘ ሠርዌ በውስተ ዓይኑ፤ እምዓይነ ቢጹ ብሩህ አውጽኦተ ሠርዌ ዘያስተዴሉ።
አይሁድሂ ሐዋርያት በጽእለቶሙ ጸአሉ።
አብዳነ ዝንጉአነ ወሐሳውያነ እንዘ ይብሉ።
እስመ እንዘ ብእሴ ጻድቀ ዘሀለዎሙ ይስቅሉ።
ውጹአን እምነ ጽድቅ በጽድቅ ርእሶሙ ተለአሉ

የቅኔው ይዘት ባጭሩ “አይቴኑ ለነውር ብሔረ ሙላዱ” ነውር ሊታፈርበት ሲገባ እንደሙያ ሆኖ እንደ ቅኔ የሚፈልቀው ኧረ ከየት ነው? እያሉ በመደነቅ ምንጩን ከጠየቁ በኋላ፤ “በውስተ ኩሉ ብሔር እስመ ከመነግድ ይሄሉ” ማለት “አሁንማ አገሩን ሁሉ ወሮት ያልደረሰበት ምን ቦታ አለና፡ የነውርን መነሻ አጠያየቀኝ” ይሉና፤ ኀጥዕ ይሳለቅ ላዕለ ጻድቅ፤ ከመ ዘንጹህ ወሠናይ ባህሉ ማለትም ይህን ነገር ባጭር ካልቀጨነው ማፈር የሚገባው ነውረኛ፤ ንጹህ ባህል እንደሚከተል ሆኖ ደህነኛውን እንደሞኝ እንዳልተማረ በማየት ያጃጅለዋል ካሉ ባኋላ ቀጠሉና ውጹአን እምነ ጽድቅ በጽድቅ ርእሶሙ ተለአሉ” በማለት ቅኔውን ደመደሙ። ማለትም፦ ከመስመር የወጡት ነውረኞች በነውራቸው ይኩራራሉ ያልገባው ህዝብም ያከብራቸዋል። ወጣቱም እንደምሳሌ ይወስደውና መመለሻ ከሌለው ሞራል ውድቀት ውስጥ መውደቅ ይመጣል”
 የኔታ አንዳርጌ ይህን ያለቃ ንጉሤን ቅኔ አስታውሰው የነገሩን፤ “እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጂን አልዘረጋም” የሚለው አነጋገር ህዝቡን አፈዘዘው። ሞራለ ቢሶችንም መረን ለቀቃቸው ብለው በዘረፉት ቅኔ የተነኩ ሁሉ በወቀሷቸው ጊዜ፤ የተሰለፉበት ሙያ እንዳስገደዳቸው ባያደርጉት ግን ከሳቸው በፊት ከነበሩት መምህሮቻቸው የተረከቡትን የሞራል ሃላፊነት ለመወጣት እንዳደረጉት ለማሳየት ነበር።
እኔም ያለቃ ንጉሤንና የመምህሮቼን የየኔታ አንዳርጌንና የነ የኔታ አምዴ ብቃትና ችሎታው ባይኖረኝም። ጳጳሱ ወለደ፤ ከመንግስትና ከነጋዴ ጋራ የጥቅም ተሻሚ ሆነ፤ “ዋልድባ የገባ አይወጣ፡ ከል የገባ አይነጣ” እየተባለ ይነገርለት የነበረው መነኩሴ ሁሉ ዋልድባን እየለቀቀ ወደ ከተማ በመገስገስ ከህዝብ ጋራ እየተጎራበተ ማህበራዊ ኑሮ ጀመረ ሲባል እሰማለሁ፤ አያለሁም። በሌላ በኩል ደግሞ “እግዚአብሔር በቀባው ላይ መናገር ልክ አይደለም” የሚሉ ሰዎችም ገጥመውኛል። ታዲያ ከመምህሮቼ የሰማሁትን የዘረፉትንም ተቀብየ፤ እራሴ ሙሉ ቤት ቆጥሬ ነግሬበት እንዴት ሳልመሰክር ልለፈው?
ዳዊት በእግዚአብሔር ተመርቶ “እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጂን አልዘረጋም” ያለበትንም ምክንያት ተረድቶ የተፈጸመውን ቅዱስ ተግባር፤ ለጥፋት ለኃጢአትና ለበደል መጋረጃ ማድረግ፤ በበደል ላይ በደል፤ በኩነኔ ላይ ኩነኔ፤ መፈጸምና ተያይዞ መጥፋትን የሚያስከትል እንጅ፤ ትህትናን ወይም ጻድቅነትን አያተርፍም። እነ ቅዱስ ጳውሎስም “እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጂን አልዘረጋም” የሚለውን በዚህ አይነት ሽባ በሆነ መንፈሰ አልተረጎሙትም። የቅዱስ ጳውሎስን አቋም እንመልከት።

የቅዱስ ጳውሎስ አቋም

ባንድ ወቅት “የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን”(የሐዋ.ሥ.፳፫፡፬-፭)። ብሎ አንድ ያልተረዳ ሰው ለቅዱስ ጳውሎስ ጥያቄ አቀረበ። ቅዱስ ጳውሎስም “ሊቀ ካህን መሆኑን ባላውቅ ነው” ብሎ መለሰለት። ይህንን ለይተው ያልተረዱ ሰዎች፤ አንድ ጊዜ ካህን ነህ፤ ወይም ሹም ነህ ከተባለ በኋላ፤ ካህንን ወይም ጳጳስን መዝለፍ ትክክል አይደለም ይላሉ። ይህ የቅዱስ ጳውሎስ ንግግርም ለጥፋተኞች መጋረጃ በመሆን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ከከፍተኛ ጉዳት ላይ ከጣሏት አስተሳሰቦች አንዱ እንደሆነ ለማየት እንሞክር።
ቅዱስ ጳውሎስ “ወኢያድሉ ለገጽ ወኢይንስኡ ሕልያን ፡እስመ ሕልያን ያዐውሮ ለጠቢባን ወያሴስሎ ለቃለ ጽድቅ“(ዘዳ ፲፮፡፲፱) የሚለውን፤ ማለትም፦ ዳኛ መዛኝ እንደሆነ፤ ዳኝነት መመዘን ሲሆን፤ ህግ ደግሞ ሚዛን እንደሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ያውቃል። መማለጃ (ጉቦ) ዳኝነትንና ሚዛናው ፍትሕን ነቃቅሎ በመጣል ህብረተ ሰብን በድቅድቅ ጨለማ የሚጥል እንደሆነ ተምሮ የተረዳ የህግ ምሩቅ ነው። ህግ ተምሮ ማወቁ ብቻ ሳይሆን “እግዚአብሔር ቆመ ውስተ ውስተ ማኅበረ አማልክት። ወይኴንን በምእከለ አማልክት . . . ፍትሑ ለነዳይ.. ወአጽድቁ ግፉዐ ወምስኪን” (መዝ ፹፩፡፩_፬) ማለትምእግዚአብሔር በፈራጆች መካከል ቆሞ ይፈርዳል። ስለዚህ ለተበደለው ለተገፋው ፍረዱ” ብሎ ዳዊት የተናገረውን ደጋሚ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ፦
·       ፍርድ ቤትን፡ ከቤተ መቅደስ፤
·       ፈራጅን ከካህን፤
·       ፍርድን ከቅዳሴ

ለይቶ ለማያት ህሊናው፤ ትምህርቱና እምነቱ አልፈቅዱለትም። ከእለታት አንድ ቀን በፍርድ አደባባይ ተከሶ ቆመ።
“ወንድሞቼ ሆይ እኔ እስከዚህች ቀን ድረስ በመልካም ሕሊና ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኖሬአለሁ”(የሐዋ. ፳፫፡፩) በህግ ፍረዱብኝ እያለ ራሱን ለትክክለኛ ፍርድ አዘጋጅቶ አቀረበ። ዳኛው ሚዛናዊ ፍርዱን ጥሎ፤ ጳውሎስን አፉን በጥፊ እንዲመቱት ሰዎችን አዘዘ(፪)። ጳውሎስ የህግና የሞራል ሰው ስለነበረና ህግ ሲጣስ ሞራል ሲደመሰስ አላስችለው አለ። “አንተ በኖራ የተለሰንክ ግድግዳ! እግዚአብሔር ይምታህ! በህግ ልትፈርድብኝ በህግ ወንበር ላይ ተቀምጠህ ሳለህ፤ ያለ ሕግ እንድመታ እንዴት ታዝዛለህ? (የሐዋ ፳፫) ብሎ ዳኛውን ገሰጸው። አንድ አድርባይ “የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን”(፳፫፡፬-፭) ብሎ ጳውሎስን በፍርዱ አደባባይ ላይ አፋጦ ያዘው።
“ስሜን በማያምኑ ህብረተ ሰብ መካከል ያንጸባርቅ ዘንድ አገልጋይ እንዲሆነኝ መርጨዋለሁ” (የሐዋ ፱፡ ፲፭) ብሎ ክርስቶስ የመረጠለትን ሐዋርያዊ አገልግሎት በዝምታ፤ በይሉኝታና፤ በፍርሀት ረግጦት ማለፍ ለጳውሎስ ትልቅ ክህደት ሆነበት።
 “የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን” ሲባል በመስማት ብቻ፤ ውስጡን ጠልቆ ሳይረዳ ያፈጠጠበትን ግለ ሰብ፤ ዳኛውንና ባደባባይ የተሰበሰውን ህዝብ ለማስተማር ቅዱስ ጳውሎስ እድል አገኘ። ቅዱስ ጳውሎስ ህጉን ከዳኛውና ከግለ ሰቡ ይልቅ የበለጠ እንደሚያውቅና ለህጉ እንደቆመለት ለመግለጽ ሲል “አማልክተ ኢትህሚ ወለመኮንነ ህዝብከ ኢትበሎ እኪተ (ዘፍ ፳፪፡፳፰) ማለትም፦ በህዝብህ አለቃ ላይ ክፉ አትናገር” የሚለውን ከህግ ጠቅሶ “ሊቀ ካህን መሆኑን ባላውቅ ነው” ብሎ የጥብቅና አመላለስ በአደባባይ መለሰ።
የኢትዮጵያው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከዚህ በላይ የተገለጸውን እንዴት እንደሚገነዘቡት ከዚህ በታች እንመልከት። ቅዱስ ጳውሎስ “ሊቀ ካህን መሆኑን ባላውቅ ነው” ያለበት ምክንያት፦ ካህኑና ህጉ አልተዋወቁም። መዛኝነቱንም አላወቀም። ባለማወቁም የህጉን ሚዛንነት ሰበረው። ለቅዱስ ጳውሎስ ይህ በህዝብ ፊት የተፈጸመውን የተደራረበ ስህተት ሳይቃወም ማለፍ መስማማትና ማጽደቅ ስለሆነ ከራሱ ህሊና ጋራ መጋጨት አልፈለገም። “ወንድሞቼ ሆይ እኔ እስከዚህች ቀን ድረስ በመልካም ሕሊና ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኖሬአለሁ”(የሐዋ ፳፫፡፩) እያለ የመሰከረለትን የራሱን ህሊና መካድ ሆነበት።
ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን”(፳፫፡፬-፭)። ተብሎ ሲጠየቅ “ሊቀ ካህን መሆኑን ባላውቅ ነው” ብሎ የመለሰው፤ ለተሳሳተው ዳኛና: ለስህተት መጠቀሚያ ሆኖ ለቀረበው ህግ እውቅና በመስጠት የራሱን ህሊና እንዳያጎድፍ እንጅ ለተሳሳተው ካህን ወይም ዳኛ ክብር ለመስጠ አይደለም። ምክንያቱም ጳውሎስ “በሕግ ለመፍረድ በህግ ወንበር ላይ ተቀምጠህ ሳለህ ያለ ህግ እመታ ዘንድ ታዝዛለህን”(፫) በማለቱ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ እንዲመታ ያዘዘው ካህንና ዳኛ እንደሆነ ያውቃል። ይሁን እንጅ በፍርድ ወንበር ላይ የተቀመጠው የሚሰራውንና ያለበትን ህላፊነት ሳያውቅ፤ ያለ ቦታውና ያል አቅሙ ተቀምጦ፤ ያለበትን ቦታና ፍርድን እያረከሰ ስለሆነ የጳውሎስ ሕሊና ሊቀበለው ይቅርና “አንተ በኖራ የተለሰንክ ግድግዳ እግዚአብሔር ይምታህ። በህግ ልትፈርድብኝ በህግ ወንበር ላይ ተቀምጠህ ሳለህ ያለ ሕግ እንድመታ እንዴት ታዝዘለህ? (የሐዋ ፳፫)  ብሎ በአደባባይ በህዝብ ፊት ዳኛውን ከዳኝነቱ አውርዶ ጣለው
ቅዱስ ጳውሎስ ይህን የመሰለ ደካማ ባህርይ ያለውን ሰው እውቅና ሰጥቶ ከሚደርስበት ጊዜአዊ ችግር ከማምለጥ ይልቅ፤ እውቅናውን ነፍጎ የሚደርስበትን ስቃይ መቀበሉን መረጠ” ይላሉ የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ. የአብነቱ ጉባኤ ሊቃውንት።
 እነዚህን የመሳሰሉ ጥልቅ ግንዛቤና ማስተዋል የሚጠይቁ ነገሮች ተብራርተው ለህዝብ ባለመነገራቸው፤ ለአድር ባዮች ወይም ግንዛቤ ለሌላቸው ሰዎች “ሹም ዳኛ(ካህን) እግዚአብሔር የቀባው ወይም በእግዚአብሔር ፈቃድ የተሰየመ ነውና አትናገረው” እንዲሉ ምክንያት ሆኗቸዋል። ለብዙ ዘመን ሲነገሩ በመኖራቸው ወደ ባህል በመለወጥ ለህዝብ መጉጃም ሆነዋል።
ማንም ግለሰብ ይህንን ጥልቅ ግንዛቤ ሳይረዳ “የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን”(፳፫፡፬-፭) ብሎ የተሳሳተውን ለመጋረድ መሞክር፤ ያለህግ ለተቀመጠ የኖራ ልስን ዳኛ (ካህን) ጀሌ መሆንን ያስከትላል። ይህን የተናገሩ እነ ነቢዩ ዳዊትና እነ ቅዱስ ጳውሎስ ናቸው። ሲናገሩትም መስዋዕትነትን በሚጠይቁ ጊዜዎች ትምህርት ለመስጠት እንጅ ለሸፍጠኞች ሽፋን ለመስጠት አልነበረም።
እስቲ ቆም ብለን እናስብ! ያስቀመጥነውን ከቦታው ስናጣው ትዕግስት የሌለን። ቤታችን ሲዘረፍ፤ ገንዘባችን ሲወሰድ፤ የልብሳችን ፍ ስትነካ፡ ባንዲት ሳንቲም ስንበለጥ ለመብታችን የምንታገል ሰዎች ስንሆን፤ ዳኛ የእውነት ሚዛንነቱን ሲሰብር፤ የተቀደሰውን ፍርድ ሲያረክስ፤ ለእምነት ለመንፈሳዊነት ለቅድስና ለሞራል ለታማኝነት ምንጭና መለኪያ ናት በምንላት ቤተ መቅደስ ይህ ሁሉ የሞራል ድቀት ጎርፍ ሲያጥለቀልቅ “እግዚአብሔር የቀባውን መናገር ኃጢአት ነው” እያልን ዝም ማለት ተገቢ ነውን? ለመሆኑ የእግዚአብሔር ቅባት ምንድነው? የእግዚአብሔር ቅባት በዚህ መንገድ የምንጠቀምበት ከሆነ እያረከስነው መሆናችንን አናስተውልምን?
እዚህ በምኖርበት አሜሪካን አገር የሚኖረው ሕዝብ  የሚያደርገውን እንመልከት! ዓለማውያን የሕዝብ መሪዎች ሲባልጉ “ለዓለማዊ ህይወታችን ምሳሌ ልትሆኑን አትችሉም” ብለው ከስልጣን ሲያባርሯቸው እየተመለከትን ነው። “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም እንደ እኔ ቅዱሳን ሁኑ” የሚለውን ትእዛዝ ለማክበር ከተቀደሰው ቤተ መቅደስ ውስጥ ገብተው አ፩ዱ አብ ቅዱስ የሚሉ አይደሉም። “ቅዱስ” ብለው ኪዳኑንም የሚመሩ አይደሉም። ይሁን እንጅ ህጸጽ የተገኘባቸውን “እግዚአብሔር ይይላቸው እንጅ እኛ ምን አገባን” ብለው አይሸከሟቸውም።
በዚህ መንገድ የኛን የኢትዮጵያንን ስንመለከተው ከሁሉም እራቀ። ወንጌሉ የሚነገርበትን ፈረንጆች stage ብለው ከሚጠሩት አብልጠን ቅዱስ ለማድረግ ስንል “አውደ ምህረት” እንላለን። ፈረንጆች መታሰቢያ ያሉትን፤ እኛ “ሥጋውና ደሙ” እንለዋለን። የሚከናወንበትን “ቤተ መቅደስ” ብለን በማክበር ቅዱሳን ሕጻናት እንኳ እንዳይደርሱበት እንከላከላለን። ካህናትን በተፈጥሮ ህግና በወንጌል በተደነገገው ቁዱስ ጋብቻ የተወሰኑና የእግዚአብሔር ዓይኖች፤ የንስሀ አባቶች ናቸው እንላለን። ጳጳሶቻችን ሴት የማያዩ፥ ገንዘብ የማይወዱ፥ ዓለምን የናቁ ብጹአን ቅዱሳን ናቸው እንላለን። መነኮሳት በገንዘብና በሴት መከሰስ ይቅርና ከየገዳም መውጣት የለባቸውም የሚል ስርአትም ያለን ሰዎች ስንሆን፤ እንደኛ ይህን ያህል የተደራረበ የቅድስና ስርአት በሌላቸው ላይ ይህን ያህል መዘርክረክ ሳይታይባቸው፤ ለምንድነው በዚህ ዘመን በእኛ ይህን ያህል የተዝረከረከ ነገር የተከሰተው? “እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን አልዘረጋም” የሚለው የተቀደሰ ቃል በተሳሳተ መንፈስ ሲነገር በመኖሩ አይደለምን? ሌላ ምክንያት አለ?
 በቤተ ክህነቱ ላይ ቀጣፊ አታላይ ዋሾ ዘራፊ ከሀዲ አድርባይና ቀላማጅ ተሰብስቦ ሲን  ጫጫ  በት “እግዚአብሔር ይውጉዳው እኔ ምን አገባኝ” ብለን ተስማምተንና ተቀብለን ለመኖር እንዴት እንወስናለን? ምን አይነት አዚም ዞረብን?
በቤተ ክህነቱ ላይ ቀጣፊ አታላይ ዋሾ ዘራፊ ከሀዲ አድርባይና ቀላማጅ ተሰብስቦ ሲን  ጫጫ  በት “እግዚአብሔር ይውጉዳው እኔ ምን አገባኝ” ብለን ተስማምተንና ተቀብለን ለመኖር እንዴት እንወስናለን? ምን አይነት አዚም ዞረብን? በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን በዋሸንግተን ዲሲ ቅድስት ማርያም የተከሰተውን መልካም ምሳሌ ሳልጠቅሰው አላልፍም።
ደፍተራ፤ ባንድ ወቅት “እጀን ከአፍአዊ እድፍ ጉድፍ ንጹህ እንዳደረኩ ንጹሀን ሆናችሁ ለመቀበል ባትቀርቡ እኔ ከበደላችሁ ንጹህ ነኝ” (ቅ ገ ፹፫ ቁ ፵፫) የሚለውን ቃል ከተናገረ በኋላ። እንደገና በዚያችው ቅጽበት ገልብጦ “እኛ ካህናቱ ብንሳሳት አትዩን ዝም ብላችሁ የምንነግራችሁን ስሙን” ብሎ ተናገረ ተብሎ፤ በይፋ በተነገረ ጊዜ፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ያሉትን አስመሳይ መነኩሴዎች ጳጳሳትና ካህናት ከያሉበት እየመነጠሩ ለማውጣት ለሚሞክሩ ቅዱስ ሞራል ላላቸው ክርስቲያኖች ቅዱስ ምሳሌ እንደሚሆን በሰፊው ተነገረ። ይህ በየቦታው ቢቀጥል ቤተ ክርስቲያናችንን ካማስተካከልም አልፈን፤ ኢትዮጵያን ካለችበት ማጥ ማውጣት እንደምንችል አልጠራጠርም
ሸፍጠኞች የሚጠቀሷት እነሱን የምትደግፍ የምትመስል ምእመናንን የምታስፈራራ አንዲት ሐረግ አለችንና እሷንም አንመልከታት። “አንተሰ ሕዝባዊ አልብከ ሥልጣን ከመ ትኮንኖ ለካህን በእንተ መሥዋዕት አላ ሶበ ትሬእዮ ለካህን ይገብር ከመዝ ጉየይ ኀበ ክልእ መካን ወኢትኮንኖ”(ሃ. . . ፳፪፡ ፲፪) በማለት ሰለስቱ ምእት የተናገሯት ናት። ይህም ማለት “ክህነቱ የሌለህ አንተ ምእመን ሆይ! ካህኑ የምትነቅፍበትን ነገር ፈጽሞ፤ ለአምልኮት ህሊናህን የሚያውከው ከሆነ፤ እየታዘብከው ካህን በሚቀድስበት ጊዜ እራስህን አግልል እንጅ፤ ስለመስዋዕቱ ክብር ስትል ካህኑን መስዋእቱን በሚያቀርብበት ወቅት አትንቀፈው” ይህ ትእዛዝ የተሰጠው የካህኑ አገልግሎትና የመስዋዕቱ ክብር ተቆላልፎ ግለሰቡ ያየውን ያላዩ በንጹህ ህሊና በተመሰጦ አምልኮት ላይ ላሉ ሰዎች እንቅፋት ላለመሆን ነው። ብዙ ሰው በማስረጃ ያረጋገጠውን ስህተት የፈጸመውን ካህን ጳጳስ መነኩሴ በዝምድና በጓደኝነትና በመንደር ልጅነት ወይም በድርጅት ምክንያት ጋርደው ማለት አይደለም።
“ከማሽላ አዝመራ ሲያባርሩት፡ ወደ ዘንጋዳ ክምር፤ ከዚያ ሲያባርሩት፤ ወደ ስንዴና ጤፍ ክምር፡ እየዘለለ እንደ እሚያስቸግር የቆላ ዝንጀሮ፤ ካንዱ አገር፡ ወደ ሌላ አገር፤ ካንድ ሰባካ፡ ወደ ሌላ ሰባካ ፤ ካንድ ደብር፡ ወደ ሌላ ደብር እየተዘዋወረ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የሚያውከውን ዝም በለው፤ ተባበረው፤ ተከተለው፤ ወይም በሀሜት እለፈው ማለት አይደለም። የምነትና የሞራል ሰዎች ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይቃወሙታል።

የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አቋም

“እመሰ ወደቅነ ውስተ ግበ ፍትወት፤ ወነበርነ ውስተ ጽልመት ዘግብረ ዓለም። ይደልወነ ናንቃዕዱ ላዕለ ገዓር። ወንስጥጥ ልብሰ ጽልመት ዘየአውደነ ወይከልአነ ነጽሮ”( ተግ ገጽ ፪፻፵፩_፵፪) ማለትም፦ በስግብግብ ባህርይ ፈተና ተጠልፈን ጨለማው ጥቅጥቅ ካለበት ጉድጔድ ብንወድቅ፤ ከወደቅንበት ወጥተን ከጨለማው ለመላቀቅ እንጣር። የጋረደንን የሸፈንን ነገር ሁሉ ሰንጥቀን እንውጣ” እያለ ሸክሙ የከበዳቸውን ሰዎች ቅዱስ ዮሐንስ አበረታታ።
የምዕራቡ ክርስትና ቅዱስ የሚለው፤ በኋላ ተጸጽቶና ንስሀ ገብቶ ብዙ መጻህፍት ጽፎ ያለፈው አውግስቲን የሚባለው፤ በአንድ ወቅት የሮማ መንግስት ባደረሰባቸው መን አንገዛም ያሉትን ሰዎች ለማስገዛት ሲል፤ ከፖለቲከኞች ጋራ በማበር በፈጠረው የፖለቲካ ዘዴ “ሰው በውርስ ኃጢአት የተወለደ ስለሆነ መገዛት አለበት” ብሎ በግልጽ ሰበክ። ኦርቶዶክሳዊው ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፤ በተናቸው ጭቆና ተንገሽግሸው “በቃን ከላያችን ውረድ” የሚሉትን ድሆች “በኃጢአት ውርስ የመጣባችሁ መርገም ነውና ተገዙ የምትል ከሆነ። አንተና እንዲገዙ የምትሰብክላቸው ሰዎች እንዴት ተወልዳችሁ ወደ ዚህ ዓለም ልትመጡ ቻላችሁ?” በሚል ንግግሩ የገዥዎችንና ያውግስቲንን ቀልብ ገፈፈው። የአውግስቲን ሸፍጥ አንደ አዚም አፍዞት የነበረውን ህዝብ የዮሐንስ ትምህርት ከተኛበት ቀሰቀሰው። የተቀሰቀሰው ህዝብ ዮሐንስን “አፈወርቅ” የሚለውን የክብር ቅጽል አቀዳጀው። ከዚህ ቀደም፦
፩ኛ የዘመናችንን ጳጳሳት ከአርቶዶክስ ትምህርትና ትውፊት ምን ያህል እንደራቁ ለማሳየት “የዘመናችን ጳጳሳት በዮሐንስ አፈወርቅ ዐይን ሲታዩ” ( http:/medhanialemeotcks.org/wp-content/uploads/2011/01/yezare_sinodos.pdf ) የተጻፈውን ይመልከቱ::

፪ኛ የኦርቶዶክሱን ነገረ መለኮት አመሰራረትና ግንዛቤ ከሮማ ካቶሊክና ከፕሮቴስንታንት ለመየት፤ መስከረም ፲፯ ቀን ፪ሺ ፪ ዓም “ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም በሮማ ካቶሊክና በፕሮቴስታንት የሚሰጣት አክብሮትና ግንዛቤ” በሚል ርዕስ  የተጻፈውን ( ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም በሮማ ካቶሊክና በፕሮቴስታንት የሚሰጣት አክብሮትና ግንዛቤ) ይመልከቱ::
የተሳሳተና ያለቦታው የተቀመጠ መሪ “እግዚአብሔር የቀባው” ነውና መንቀፍና መተቸት ኃጢአት ነው እያሰኙ የሚኖሩና ይህንንም የሚሰብኩ ሰዎች የሞራል ውድቀት የተጠናወታቸው እንደሆኑ ለማሳየት “ የእምነትና የሞራል ግዴት በሚል ርእስ ማቅረቤ ይታወሳል። “እግዚአብሔር የቀባው” በሚል ርእስ ያዘጋጀኋትን ይህችን ጦማር ያስከተልኩበት ምክንያት፤ ብቃት እውቀትና ሞራል ሳይኖራቸው የተሰየሙትንና ወደፊት ለሚሰየሙ ሁሉ አለመቃወም ትህትናንና ቅድስናን የሚገልጽ ሳይሆን ከውድቀት እጅግ ወደ ባሰ ውድቀት የሚከት መሆኑን ተገንዝበን የምንከላከልበትን መንገድ እንድንፈልግ ነው።  
ማንም እነዚህን ተከታታይ ጦማሮች አንብቦ ከተረዳና፤ ወደፊት አከታትየ የማቀርባቸውን ጦማሮች ካነበበ፤ ለካ እንዲህ ነው እንዴ! ብሎ ባለጌውን አስመሳዩን ቀጣፊውን ጳጳስ ቄስ መነኩሴ፡ ባዲስ ፋሽን እራሱን መምህር እያለ በመሰየም የተነሳውንም መምህሬ እገሌ፤ ወይም ድርጅቴ በማለት ከመከተል ይልቅ ከነሱ አሉባልታ ተላቆ ምጻሕፍት ምን ይላሉ? ወደ ሚለው ደረጃ በመድረስ ለቤተ ክርስቲያናችን ቅድስና ቅድሚያ እንዲሰጥ ዓይኑን ይከፍትለታል። ለመቃወምም የሞራል ድፍረቱ ይዳብርለታል። የማይረቡ የማይጠቅሙ ሰዎች በተቀደሰው መንበር ተሰይመው በተራቸው ግልቢያቸውን እንዳይጀምሩ አሁኑን ተቃውሞውን ማሰማት እንዲችልም ይረዳዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን አካል የሆነ ሁሉ መጽሐፍ እያነበበ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የጉባኤ ሊቃውንት አተረጓጎምና አገላለጽ ተረድቶ ስህተቱን ልይቶ እየገለጸ አታላዩን ሁሉ አንቀበልም ወደሚለው የሞራል ብቃት ካልደረሰ፤ ዶክተረ አረጋዊ በርሄ ገልጸው በመጽሐፋቸው እንዳቀረቡልን፤ አቶ ስብሀት ነጋና ገብረ ኪዳን ደስታ በቤተ ክርስቲያናችን የጫኑብንን መርግ በቀላሉና ባጭር ጊዜ ፈንቅለን ከላያችን የምናስወግደው አይደለም። እንዲያውም አሁን ፓትርያርክ ለመሆን በጩነት ቀረቡ የተባሉት ሰዎች በቤተ ክርስቲያናችን ላያ ተጭነው ሸክሙ እየከበደ የሚሄድ ይመስላል

ይቆየን
እላይ በተቀስኩጦማር እንገናኝ።
ለሌሎች ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ጦማሮች የሚከተለዉን ድህረ-ገጽ ይመልከቱ::