Sunday, 16 June 2013

አባ ማትያስ




አባ ማትያስ
አይተን አናውቅም


ሰውንም ሆነ ሌላ ነገር በነበረ ወይም ባለ መለኪያ አንዱን ከሌላው አወዳድሮ በተወዳደረበት መሥፈርት ልቆ የተገኘውን በማክበር፤ ዝቅ ብሎ የተገኘውን ደግሞ በመናቅ እንዲህ የመሰለ አይተን አናውቅም ይባላል። ይህን የሚል ሰውም መጀመሪያ የሚለካበትንና የሚለካውን ነገር መርምሮ መዝኖና ለይቶ ማወቅ አለበት። የሚመዝነውን ነገርና  የሚመዝንበትን መስፈርት ሳያውቅ እንዲህ ያለ ሰው ወይም ነገር አይተን አናውቅም የሚል ሰው ጤነኛ አይደለምና አትቀበለው” የሚለው ምክር መመሪያችን ”ወኩሎ ቃለ ዘይሜህር ይደልዎ ሎቱ ከመ ያእምር ወይዝክር ከመ ውእቱ ገብሮ ቀዳሚ እምቅድመ ይምሀሮ ከመ ያእምር ዘይብሎ በኩሉ ሐተታ” ብሎ ባሰፈረው ሐረግ ላይ ይጠቀሳል (ፍ አ ፭፡ ፻፲፪) ።



nigatuasteraye@gmail.com
ሰኔ ፳፻፭ ዓ.ም.           

 



መግቢያ


ከዚህ ቀደም ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፪ሽ ፪ ዓ/ም ኢትዮጵያ በሶስቱ ፍካሬዎች በሚል ርእስ ባቀረብኳት ጦማር በአቡነ ጳውሎስ ዘመን በህዝብና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን ላይ የደረሰውን ቀውስ ጠቁሜ ነበር። [ሙሉ ሀሳቡን ለማግኘት ይህን ሰንሰለት ይጫኑ ፍልሰታ: “እኛም ማየት አለብን"] በአባ ማትያስ ምን እንደሚከሰት የሚያውቀው “ሩጫችሁን ፈጽማችኋል” ብሎ አቡነ ጳውሎስንና አቶ መለሰን በፈቀደው ጊዜ የጠራ አምላክ ብቻ ነው። የበልአምን አህያ የተጠቀመ አምላክ በአርያው የፈጠራቸውን አባ ማትያስን ብቻ ሳይሆን እነ አቶ ስብሀት ነጋንም ለውጦ ለበጎ ነገር  አይጠቀምባቸውም ማለት የሱን ኃያልነት መካድ ነው። 
“ዘይቀድም ተናግሮ  እምቅደመ ይስማዕ ወይጤይቅ ዐብድ ውእቱ ወይከውኖ  ነውረ (ፍአ ፱፡፫፻፩)” የሚለው መመሪያችን እንደሚያስጠንቅቀኝ ስለ አባ ማትያስ የምናገረው እስካሁን ባሳዩኝ እንጅ ወደፊት የሚሆነውን ለመናገር የትንቢት ጸጋ የለኝም። ነገር ግን እሳቸው ራሳቸው ከናቋቸው ከአቡነ ተክለ ሃይማኖትና ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ ሳንጸጻራቸው የሚታየኝ “እንዲህ ያለ ፓትርያርክ አይተን አናውቅም” የማያሰኝ አይደለም ማለት ደግሞ በሀላፊው ላይ ቆሞ ግራና ቀኝ በመመልከት የሚከተለውን እንድንቃኝ የተሰጠንን ሰባዊ ጸጋ ክዶ እንስሳ መሆን ነው።
የሰውን ስህተት እየተከታተለ ይመዘግባል እየተባለ የሚወቀሰው እኩይ ፍልስጣ ይባላል። እኩይ የሚል ቅጽል የተሰጠው በመመዝገቡ አይደለም። የመዘገበውን እንደመስታዋት እያሳየ አትድገሙ ከማለት ይልቅ፤ ስህተቱን ከስሜት ጋራ በማስማማት ወደ ቀዋሚ ባህርይነት ቀይሮ መጎተቻ ሰንሰለት በማድረጉ ነው።  ይህማ ከሆነ የአቤልን ታሪክ የመዘገበው ቅዱስ መጽሐፍ የቃኤልን በዘለለው ነበር። ሰዎች በተከሰሱበት በተወቀሱበት  ስህተት ተጸጽተው “አበስኩ በሰማይኒ ወበምድር በቅድሜከ ኢይደለወኒ እንከ እሰመይ ወልደ”( ሉቃ ፲፭፡፳፩) ብለው በራሳቸው መስክረው ንስሀ ለገቡበት ወይም በህግ ለተቀጡበት ስህተታቸው  ሊወቀሱ ሊከሰሱ ቀርቶ መወሳት የለበትም።
ነገር ግን በቀደመው ስህተታቸው ንስሀ ከመግባት ይልቅ  ከነሱ የተሻሉትን እየወቀሱ፤ ከስህተት ወደ ከፋ ስህተት እየናሩ ህዝብ  እያየው እየተናገረው የህዝብን ድምጽ እና የራሳቸውን ህሊና ሰብረው ጥሰው በመሄዳቸው በህሊናችን የታዝብነውን ባንደበታችም የማንመሰክረው ከሆነ፤ እነሱ የለቀቁብንን የስህተት እስትንፋስና ጨረር ውጠን አፋችንን ማፈን፤ በነሱ ኃጢአት ራስን አፍኖ እንደ ፊኛ መነፋት እንጅ፤እምነትን ወይም ጥሩ ሰውነትን አያሳይም። በክርስቲያኖች መካከል ይህ እንዳይፈጸም ክርስቶስ “ሑሩ በልዋ ለዛቲ ቁንጽል”(ሉቃ ፲፫፡፴፪) ብሎ አስተምሮናል። ስለዚህ  በቀደመ ስህተታቸው ንስሀ ያልገቡትን አሁንም ያሉበትን ለማሳየት በማደርገው ጥረት ሰው የጎዱ አገር የበደሉ በሸፍጥ የሚጔዘ ሰዎች በዚህች ጦማር  ቢጠቀሱ  እኩይ ፍልስጣ አያስብለኝም።
ከዚህ ቀደም የነ ፋሌቅ ወጥመድ በሚል ርእስ ባቀረብኳት ጦማር እንደገለጽኩት [ሙሉ ሀሳቡን ለማግኘት ይህን ሰንሰለት ይጫኑ የነ ፋሌቅ ወጥመድ  ] ወያኔወች አገሪቱን በተቆጣጠሩበት ወቅት ዘርፎ ለመክበር በነበራቸው እሽቅድምድም የወርቅ ጥርስ ከሰው አካል ሳይቀር የኢትዮጵያን ንብረት ከመላ ኢትዮጵያ እየነቀሉ ለመዝረፍ በሽሚያ ላይ ነበሩ። ያገሪቱን ሀብት ተካፍለው በብርና በወርቅ መተኛት ከጀመሩ በኋላ፤ደካማ የስግብግብነት ባህርይ የሚያጠቃቸውን ከእየ ጎሳው እየመለመሉ አመንኩሰውና አቅስሰው በራሱ ወገን በአገሩና በቤተ ክርስቲያኑ ላይ እንዲዘመት ሲየደርጉ የነበሩትን፤ አሁን ደግሞ ለንደን ላይ ባለችው ርእሰ አድባራት ደብረ ጽዮን ላይ በተረዋ የሚያደርጉትን ደባ በመመልከት ላይ ነን።
  ስለታሪክ እና ዳር ድንበር በሚመሰክሩት በገጠር በሚኖሩት አዛውንቶች ሊቃውንት አበው ላይ እስካሁን የፈጸሙትን ዘመቻ፤ በዓይን የሚታዩትን የታሪክና የቅርስ መድበል የነበሩትን መካናት ላይ የሚፈጽሙትን ማፍረስና ማፍለስ በጥሞና ስናየው፤የማይታዩትን እንደ ሞራል፤ እምነት፤ ብሄራዊ ወገናዊ ፍቅርና ስሜት፤ እንደ ነገረ መለኮት የመሳሰሉትን መንፈሳውያን ቅርሶች፤ ከስር መንግለው ለመደምሰስ ያደረጉትንና በማድረግ ያሉትን መገመት የሚከብድ አይደለም።
በአቡነ ጳውሎስ ሲካሄ የነበረው ይህ የጥፋት ተልእኮ የውስጥና የውጭ ትምህርት በሌላቸው ባባ ማትያስ የሚካሄደው የባሰ እንደሚሆን እሳቸውን ለማስገባት የተደረገውን የነ አባይ ጸሀየን ርብርቦሽና እሳቸውም መመሪያችንን እና እንዳይገቡ የተሰነዘረውን ህዝባዊ ተቃውሞ ጥሰው፤ የነ አቶ ዓባይን ጥሪ ብቻ ተቀብለውት እንዴት በደስታ እንደገቡ በታዘብነው ተረድተናል። “ሰላምና እርቅ የሚፈልጉ ካህናት ይሰቀሉ” እያሉ በድፍረት የተናገሩት እነ አቶ ስብሀት ነጋ ለህዝብ ለቤተ ክርስቲያን ይጠቅማሉ ብለው አባ ማትያስን እንዳላስገቧቸው የታወቀ ነው። 
አባ ማትያስን በመንበሩ ላይ ካስቀመጧቸው በኋላ ሲነገርላቸው የምንሰማው ታሪክ፤ ከሳቸው ጋራ የማይገናኝ የተለመደ የወያኔ ሸፍጥ ነው። አባ ማትያስን ለማያውቃቸው አዘናጊ ስለሆነ በቅርብ የሚያውቃቸው ሁሉ የሚውቀውን እውነት ለማያውቃቸው የማስረዳት ሀላፊነት አለበት። አባ ማትያስ እነ አቡነ ገብርኤልን የመሰሉ ይሉኝታ የለሽ መሳዮችን በማዝመት ህዝቡን በመከፋፈል ለመፈጸም የተሰየሙለትን ደባ ለንደን ላይ ጀምረዋል። በለንደን የሚኖረው ህዝበ ክርስቲያን አምላኩን ለማምለክ፤ ፊደሉንን ታሪኩንና በለንደን ለሚወለዱት ልጆቹ ለማስተማር የገዛውን ህንጻ፤ የሰበሰበሰበውን ገንዘብ፤ ያፈራውን ንብረት በነ አባ ግርማ መሳሪያነት ለመንጠቅ በነ አባ ገብርኤል የተዘረጋውን መስገርት ለመስበር በትንቅንቅ ላይ ነው። በለንደን የሚኖረው ወገን የጀመረውን ትግል በተገቢው መንገድ እና በትምህርት ሰጭ፤ ታሪካዊ አምድ ላይ የሚቀመጥ ሥራ ይፈጽም ዘንድ በአገር ውስጥ እና በውጭ ለምንኖረው ወገኖቹ ያቀረበልንን የድጋፍ ጥሪ በጸሎት በሞራል እንድንቀበል ለማሳሰብ ይህች ጦማር ተዘጋጅታ ቀርባለች።አባ ማትያስ ከዚህ ቀደም ለነበሩበት መስመር ብቃት እምነትና መንፈሳዊ ህይወት እንደሌላቸው ራሳቸው “ወደ ሰማይ ተኩሰው” ካሉባት ቅጽበት ጀምሮ ያቀረብኳቸውን ቅኔዎች እና ጦማሮችን አንባቢ እንዲቃኛቸው እያሳሰብኩ እንዲህ ያለ ፓትርያርክ አይተን አናውቅም” በሚል ርእስ ያዘጋጀኋትን በ ፰ አበይት ክፍሎች ከፋፍዬ በገጽና በቁጥር አመልክቼ ይህችን ጦማር አቀርባለሁ። ለዝርዝሩ ማዉጫዉን ይመልከቱ።






ዉጫ


 




መቅድም

እንዲህ ያለ ሰው አይተን አናውቅም የሚለው ንግግር አንዱን ከሌላው ጋራ በተመሳሳይ መስፈርት አነጻጽሮ ልቆ የተገኘውን ከፍ አርጎ ለማቅረብ ነው። ይህን ቃል ካፋቸው አውጥተው የተናገሩት አባ ማትያስ ናቸው። የተናገሩትም ለብጹዕ አባታችን ፓትርያርክ ተክለ ሃይማኖት ነው። ምን ጊዜና እንዴት ተናገሩት? አቅራቢውስ ይህን ምስክረነት ለመግለጽ ያስቻለው በዚህ ወቅት የት ነበር? የሚሉ ጥያቄዎች ባንባቢ ህሊና ላይ መፈጠራቸው አይቀርም።
ለምስክርነት ያበቃኝን ዝርዝር በዚህች ጦማር ለማቅረብ ሰአት ወስኖኛል። አስፈላጊ ከሆነ ዝርዝር ሀተታውን ከዚህች ጦማር ቀጥየ ማቅረብ እችላለሁ። ሆኖም “አባ ማትያስ ማናቸው? በሚል ርእስ በEthiopian Review ቀርቦ ለተነበበው ጦማር [ሙሉ ሀሳቡን ለማግኘት ይህን ሰንሰለት ይጫኑ አቡነ ማትያስ (አባ ተክለማርያም አስራት) ማናቸው?  ] ውጥን ጨራሽ በማድረግ አንባቢ አባ ማትያስን የበለጠ ተረድቶ እንዲህ ያለ ፓትርያርክ አይተን አናውቅም” ለማለት ያስችለው ዘንድ ይህች ጦማር ቀርባለች።
“አባ ማትያስ ማናቸው?” በሚል ርእስ ተዘጋጅቶ የቀረበውንና ይህችን ጦማር ያነበበ ሁሉ፡ እንዲህ ናቸው እንዴ? በማለት ብቻ ታዝቦ ሳያልፍ የግሉን ድርሻ እንዲወጣ የቀረበ ነው።አባ ማትያስ ብጹዕ ፓትርያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በምን መለኪያና ከማን ጋራ አነጻጽረው እንዲህ ያለ ፓትርያርክ አይተን አናውቅም” ያሉበትን ምክንያት በህይወት ስላሉ ራሳቸው ሊናገሩት ይችላሉ። ብጹዕ አባታችን ፓትርያርክ ተክለ ሃይማኖትን እንዲህ ያለ ፓትርያርክ አይተን አናውቅም” እንዳሏቸው፤አባ ማትያስ አቡነ ጳውሎስንም “እግዚአብሄርን የማይፈሩ ሰውን የማያፍሩ ከፋፋይ” ናቸው ብለዋቸው ነበር። አንባቢ የራሱን ግንዛቤ ይወስድ ዘንድ ራሳቸው ከነቀፏቸው ከሁለቱ ፓትርያርኮች ጋራ አባ ማትያስን እናነጻጽራቸው።

ክፍል አንድ


ንጽጽር

ክፍል ፩.አቡነ ተክለ ሃይማኖት


አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሚታወቁበት ባህርያቸው ጥቂቶች እነሆ!
o   ፩ኛ፦ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በብህትውናቸው፤ በአጽንኦ በአታቸው፤ በምንኩስናቸው፤ ከፍተኛነት እጅግ የተከበሩ ነበሩ። ለምሳሌ፦ ፓትርያርክ ተክለ ሃይማኖት አባ መላኩ እተባሉ በገዳማቸው በሚኖሩበት ጊዜ ላንዳንድ ጉዳይ ወደ ቤተ ክህነት የሚልኳቸውን መልእክተኞች አቡነ ቴዎፍሎስ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት (የቀድሞው አባ መላኩ) ያሳዩት በነበረው አክብሮት  ከመንበራቸው ተንስተው ይቀበሏቸው ነበር።

o   ፪ኛ፦አቡነ ተክለ ሃይማኖት ወደ ፓትርያርክነት የገቡበት መንገድ አህያ ፍለጋ ሄዶ ንግሥና ከገጠመው ከሳኦል ጋራ የሚመሳሰል ነው።(፩ኛ ሳሙ ፱፡፫_ምዕ ፲፡፩) በወላይት አውራጃ እያስተማሩ ያሳድጓቸው የነበሩትን ህጻናት የሚመግቡበት መንገድ በአብዮቱ ምክንያት ተቋርጦባቸው፤ ለአቤቱታ ከበአታቸው ወጥተው በመንበረ ፓትርያርኩ ቅጽር ግቢ በአባ ኃይለ ማርያም ቤት ታዛ ኩርትም ብለው ተቀምጠው በሚተክዙበት ወቅት ነበር።

o   ፫ኛ፦አቡነ ተክለ ሃይማኖት፤ ቃላቸውን እምነታቸውንና ተልእኳቸውን የሚክዱ ማንንም በማውገዝ እና ከማንም ጋራ በመወጋገዝ “እመሰ በበይናቲክሙ ትትባልኡ፡ወትትናሰኩ ተኀልቆ ተረፍክሙ(ገላ ፭፡፲፭) የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስን ማስጠንቀቂያ ያፈረሱ አልነበሩም።

ክፍል ፩.አቡነ ጳውሎስ


“እግዚአብሄርን የማይፈሩ ሰውን የማያፍሩ ከፋፋይ” ብለው እራሳቸው አባ ማትያስ የዘልፏቸውን አቡነ ጳውሎስንም እንመልከት።
o    ፩ኛ፦ ስምንት አመታት ከታስሩበት ተፈተው ወደ ነጻው አገር (አሜሪካ) ከመጡ በኋላ እንደ አባ ማትያስ ደርግንም ሆነ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ሲያወግዙም ሆነ እሳቸውም ሲወገዙ አልተሰሙም።

o    ፪ኛ፦በመንበሩ ላይ ከተቀመጡ በኋላ በሠሯቸው ነገሮች እየተጋለጡ መጡ እንጅ፤ በዚያ ወቅት ቀኖና ጥሰው ከግለ ሰብ ጋራ ተነጋግረው ገቡ ተብሎ ሲነገርባቸው አልተሰማም። እንዳይገቡ የተሰጣቸው ማስጠንቀቂያም የለም። በዚህ ጉዳይ አቡነ ጳውሎስን ታሪክ የሚወቅሳቸው፤ ታመው በፈቃዳቸው ወረዱ የተባሉትን አቡነ መርቆርዮስን፤ ታመው ከሆነም ምንህን አመመህ? በምን ልርዳህ ሳይሉ ምርጫውን በመቀበላቸው ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ግን መወቀሰ ያለባቸው አቡነ ጳውሎስ አይደሉም። ከአቶ ታምራት ላይኔ ጋራ ተባብረው አቡነ መርቆርዮስን ያወረዱና ሲኖዶሱን እየመሩ የቆዩ ለአቡነ ጳውሌስም ሆኑ ለሌላ ሰው እንዲመረጥ መንገዱን ከፍተው በማስተካከል የተባበሩና የመረጡ ጳጳሳት ናቸው። ይህን ያደረጉትን ጳጳሳት መመሪያችን  “ወአኮ ዘተዐዱ ውስተ ሥርአታት ድልዋት። ወለሰብአ ኅርየት ይደልዎሙ ከመ የሀብዋ ለዛቲ ሢመት ለዘድልው ላቲ። ወእመሰ አበዩ ይከውኖሙ አበሳ (ፍ አ ፬፡ቁ ፷፱) ይላቸዋል። ይህም ማለት ለቤተ ክርስቲያን መሪ የሚሆነውን ሰው ስትመርጥ ተልእኮውን ለማከናወን ብቃት ያለውን ሰው ተጠንቅቀህ ምረጥ። ይህን ባታደርግ ተወቃሹና ተከሳሹ አንተነህ” ከራሳቸው አንደበት እንደሰማሁት ይህን ደባ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የፈጸሙት እነ አቡነ ገብርኤል ናቸው። ታዲያ በዚህ ጉዳይ አቡነ ጳውሎስን ከመውቀስ በፊት፤ ይህን ስህተት የፈጸሙት ጳጳሳት እነ አባ ገብርኤል ተወግዘው የቀረውን ዘመናቸውን በንስሀ እንዲፈጽሙ መደረግ ነበረበት።
አቡነ ጳውሎስን እንዲወቀሱ ያደረጋቸው ዓበይት ነገሮች የሚከተሉት ናቸው። አቡነ ጳውሎስ ነገረ መለኮት እንዳይዛባ የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን ሰርዘው ለፖለቲካ ሸፋን ማድረጋቸው ነው። 
ለምሳሌ
ሀ).   ስለ እመቤታችን ትክለኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን የጻፉ መጋቤ ብሉይ ሰይፈ ናቸው። ራሳቸው አቡነ ጳውሎስም በPrinceton Theological Seminary በተመረቁበት dessertation ላይ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ  ቤተ ክርስቲያናችን ከአኀት እና ከመላው ምሥራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት ጋራ እንጅ፤ ከሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋራ እንደማትስማማም አረጋግጠው ጽፈዋል።  [አቡነ ጳውሎስ የተመረቁበትን መጽሐፍ ለማንበብ ይህን ሰንሰለት ይጫኑ:- Abune Paulos Dissertationይህን ጽፈው ሳለ፤ በተቃራኒዉ የጻፉበትን መጽሐፍ የከንሳስ ኪደነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ከደበቁበት ቆፍራ በማውጣት እስካጋለጠቻቸው ድረስ፤ በዚህ ጉዳይ ምንም ያልጻፉትን አቡነ መልከጼድቅን ጠልተው ለማስጠላትእና ተሰሚነትንም ለማሳጣት  እንደ ፕሮፓጋንዳ አድርገው ተጠቅመውበታል።
).    አቡነ ጳውሎስ ለዘር እና ለፖለቲካ ቅድሚያ በመስጠት ነገረ መለኮቱን እና ቤተ ክርስቲያናችንን ለወያኔ ሽፋን በማድረግ አዋርደዋል።
ለምሳሌ፦አባ ማትያስ ባልዋልቡትና ባልገባቸው በነገረ መለኮት ጉዳይ ገብተው በመዘባረቃቸው ያፈላውን ጉድ የከንሳስ ህዝበ ክርስቲያንና የዋሽንግተን ዲሲ ማህበረ ካህናት እንዲታረም ለራሳቸው ለአቡን ጳውሎስ ጥያቄ አቅርበውላቸው ነበር። አባ ማትያስን ገስጸው ስህተቱን ከማረም ይልቅ፤ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ምንም ግንዛቤ በሌላቸው በእነ ዳንዔል ክብረት አማካይነት በአቡነ መልከ ጼዴቅ ላይ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት የሸፍጥ መንገዶች ዘመቻ ሲያካሂዱ ነበር።
·        አቡነ መልከ ጼዴቅ ስለ ጥንተ አብሶ  አልጻፉም።
·        ስለ ጥንተ አብሶ የጻፉት እራሳቸው አቡነ ጳውሎስ ናቸው።
·        አቡነ መልከ ጼዴቅ አልጻፉትም እንጅ ቢጽፉትም ራሳቸው አቡነ ጳውሎስ ትክክል እንደሆነ መስክረው ጽፈውት ስለነበረ ስህተት አልነበረም።
·        አቡነ ጳውሎስ አባ ማትያስን ሸፍነው፤ ሌላውን ለመምታት ማህበረ ቅዱሳንን እንደመሳሪያ አርገው ለብዙ  አመታት ሲጠቀሙበት ከኖሩ በኋላ፤ አባ ሰረቀንም ከማህበረ ቅዱሳን ክስ ለማዳን ሲሉ ተነፈሱ።
·        አባ ሰረቀን ለማዳን ሲሉ እንዳልተሳሳቱ የሚገልጽ ለአባ ሠረቀ የምስክር ወረቀት  እንዲጻፍላቸው ማድረጋቸው፤ ለታላቋ ቤተ ክርስቲያን ከመጠንቀቅ ይልቅ ለግለ ሰቡ ባደረጉት ጥንቃቄ ዘረኛ ያደርጋቸዋል።
).  አቡነ ጳውሎስ የወያኔ መንግስት የጉዲፈቻ ልጅ ሲሆኑ፤ አባ ማትያስ ደግሞ የበኩር ልጅ ናቸው። ሁለቱም የወያኔ ግራና ቀኝ እጆች በመሆናቸው ወያኔ አንድ እጁን እንዳያጣ አቡነ ጳውሎስ ባደረጉት ጥንቃቄ ስለ አባ ማትያስ “ያልተማረ፤ የኮምኒስት ጳጳስ፤ ያውም ደግሞ የተወገዘ” እያሉ በግል ለጠየቃቸው ከመናገር አልፈው የወሰዱባቸው ርምጃ የለም።
እንዲህ ያለ ፓትርያርክ አይተን አናውቅም” ብለው ከነቀፏቸው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋራ፤ እግዚአብሄርን የማይፈሩ ሰውን የማያፍሩ ከፋፋይ ናቸው” ብለው ካጥላሏቸው ከአቡነ ጳውሎስም ጋራ አባ ማትያስን ለማነጻጸር አሁን ወደ አባ ማትያስ እንሻገር።

ክፍል .አባ ማትያስ


አባ ማትያስ ለፓትርያርክነት ብቃት የላቸውም ከሚያስብላቸው ባህርይዎቻቸው ጥቂቶች የሚከተሉት ናቸው።
o    ፩ኛ፦አባ ማትያስ በኢየሩሳሌም ገዳም የኢ... ቤተ ክርስቲያናችን የሰጠቻቸውን ኃላፊነት የካዱ ናቸው።

o    ፪ኛ፦አባ ማትያስ ታማኝነትን በማጉደል በሰየሟቸው በአቡነ ተክለ ሃይማኖት የተወገዙ ናቸው።

o    ፦አባ ማትያስ በስህተታቸው የደረሰባቸውን ውግዘት በዘመኑ የነበረውን የፖለቲካ ግርግር እነደ መጋረጃ በመጠቅም ዋሽተዋል።

o    ኛ፦ለራሳቸው ሽፋን ሲሉ ያወገዙት የደርግ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመው ስህተት የወያኔ መንግስት ከፈጸመው ስህተት ጋራ ሲነጻጸር፤ የእሳቸውን ቢጤዎች  እነ አቶ ስብሀት ነጋናን ዓባይ ጸሐዬን ከመሰሉ ሰዎች በቀር፤ ማንም ኢትዮጵያዊ የወያኔን መንግስት ከደርግ መንግስት የባሰ እንጅ የተሻለ አርጎ ሲናገር ሰምቼ አላውቅም። አባ ማትያስ ከወያኔ መንግስት የተሻለውን  የደርግን መንግስት ሳያሰልሱ ሲያወግዙ የነበሩ ሲሆኑ፤  በአገር በዘርና በሃይማኖት አጥፊነት  በመከሰስ ላይ ያለውን የወያኔን መንግስት አንዲት ቃል ሲናገሩ አለመሰማታቸው፤ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የጣሊያንን ወታደር ባርኮ ከለው ጣሊያናዊው ጳጳስ እጅግ የከፉ ጨካኝና ዘረኛ አድርጓቸዋል።

o    ኛ፦አባ ማትያስ በነዋየ ቅድሳት ጉዳይ የዋሽንግተን ዲሲ የደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም  ምእመናንን በዓለማዊ ዳኛ በመክሰሳቸው የቤተ ክርስቲያናችንን ህግ ጥሰዋል። በዚህም ተግባራቸው መካሰስ ይቅርና ለሞራል ልዕልና መወራረጃ በማድረግ ለኖረው ህዝበ ክርስቲያን ንዋየ ቅድሳቱን የእርስ በርስ መካሰሻ ያደርገው ዘንድ መጥፎ ምሳሌ ሆነዋል።
መጽሀፋችን “ወአእምሩ እንከ ከመ እምጥንቱ ኀሳረ  ይከውነክሙ እምከመ ጋእዝ ወተስናን ብክሙ። ለምንት ኢትትገፍኡ ወለምንትኑ ኢትትሀየዱ ። ወዓዲ አንትሙ ትገፍኡ ወተሀይዱ ወከመዝኑ ትኤብሱ ላእለ ቢጽክሙ(፩ኛ ቆሮ ፮፡፯) ብሎ እንደ ሚያዝዘው ከነገረ መለኮቱ ውጭ በሆነ ነገር ቆሳቁስ ነክ በሆኑ ምክንያቶች በቤተ ክርስቲያን ሙግት ቢፈጠር ንብረቱን ካህናት ለብዙሀኑ መልቀቅ አለባቸው። ካህናት በገንዘብ ላይ በተመሰረተ ውዝግብ ዓላማዊ ዳኛ ፊት መቆም የተከለከለ ነው። (፩ኛ ቆሮ ፮፡፩_፮) አባ ማትያስ ይህን መመሪያ ጥሰው ሲያቆርቧቸው የነበሩትን የዋሸንግተን መድኃኔዓላምን ህዝበ ክርስቲያን እና ወንድማቸውን አቡነ ይስሀቅን በዓለማዊ አደባባይ ከሰው የቆሙ የመጀመሪያው አስመሳይ መነኩሴ ናቸው።
o    ኛ፡የጳጳስ ስራ በፍ አ ፬ ቊ ፸፫ መሰረት ብሉያትን ሀዲሳትን ሊቃውንትን ተረድቶ አውቆ ሃይማኖትን መጠበቅ ነው። አባ ማትያስ  እንኳን ሊጠብቁት ሊያስተምሩ እራሳቸው ባለማወቃቸው፤ ከንሳስ ላይ ባወጁት  እምነት የሮማ ካቶሊክ እና  የኢ.ኦ.ተ. ቤተ ክርስቲያን አንድ ናቸው ብለዋል። [አቡነ ማትያስ ደባዳቤ ለማንበብ ይህን ሰንሰለት ይጫኑ:-Abba Mathias Letter to Abba Paulos about Kesis Asteraye Tsige]

o    ኛ፦የክርስትናችን መመሪያ “ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው። ነፍሰ ገዳይ የሆነ ሁሉ የዘላለም ህይወት የለውም” (፩ኛ ዮሐ ፫፡፲፭) ይላል። ሰው መውደድ ይቅርና “ሰላምና እርቅ የሚፈልጉ ካህናት ይሰቀሉ” እያለ ግድያን የሚያውጅውን አቶ ስብሀት ነጋን አባ ማትያስ አልገሰጹም። ሊገስጹ ይቅርና የሱን የጥፋት ተግባር ለመፈጸም በሱ ትእዛዝ ወደ መንበረ ፓትርያርክ የገቡ ናቸው።

o    ፰ኛ፦አባ ማትያስ  በመንግሥት ድጋፍ የገባ “ምቱር” ነው አትቀበሉት የሚለውን የቤተ ክርስቲያናችንን መመሪያ ጥሰው የካህናቱንና የህዝበ ክርስቲያኑን ተቃውሞ ሰብረው የገቡ ናቸው።

o    ኛ፦ ወይደልዎሙ ለህዝብ ከመ ያእምሩ ተሠያሚሃ በስሙ ወአርያሁ ወግዕዙ።ወኢይደል ከመያጠይቆ  በዓይኑ.ለእመ ተረክቡ ሃቤሁ ፭ቱግብራት”(ፍ አ ፬፡ ቁ ፸፪) ማለትም፦ ህዝብ የሚሰየመውን በስሙ በአካሉ በግብሩ ለይቶ ማወቅ ይገባዋል። ያ ነው እየተባለ  በዓይን ጥቅሻ በጣት ጥቆማ መምረጥ የለበትም” አባ ማትያስን የኢትዮጵያ ህዝብ አያውቃቸውም። የሚያውቃቸው የአሜሪካ ህዝብ ነው። ያውም በማተራመስ በመዝጋት በመክሰስ ነው። “በኅርየተ  ኩሎሙ ህዝብ ኪያሁ ዘከመ ሥምረተ መንፈስ ቅዱስ ፭፡፺” በሚለው ህጋችን የተመረጡ እንደሆኑ አድርገው “በእግዚአብሄር ፈቃድ ህዝብ መረጠኝ” በማለት ዋሽተዋል። በዚህም “ዳእሙ ስም ሕስው ሀሎ ላዕሌሁ  አኮ ውእቱ እምሀበ እግዚ ዳእሙ እምሀበ ሰብእ”(፭፡፻፶) የሚለው መመሪያችን ዋሾ ቀጣፊ ይላቸዋል።

o    ኛ፦አባ ማትያስ ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ እየነደፈ በመግደል ከተወለደበት ምንደርም እያሳደደ በመበተን የሚጠቀምበትን አይነት ፓርላማ እንደ ምሳሌ ወስደዋል። በብቃት የለሽነታቸው ተቀባይነት እንደማይኖራቸው ስለተገነዘቡ እና በመርዛቸው እየነደፉ ለማፍዘዝ ባላቸው እቅድ፤ ሲኖዶሱን ዲያብሎስ አዳምንና ሄዋንን እየነደፈ ከገነት ያስወጣበትን የገነቱን እባብ አድርገውታል።

o    ፲፩ኛ፦ አባ ማትያስ ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ብቅ ባሉባት ቀን ስለ ዋልድባ ገዳም ሳይሆን የተናገሩት ስለ አባይ ግድብ ነው። ስለ ዓባይ ግድብ በሙያው የሰለጠኑ የሀገሪቱ ልጆች ኢትዮጵያውያን መገደቡን ሳይቃወሙ “ጥናት የጎደለው አቶ መለሰ ለፖለቲካ ሽፋን ህዳሴ በሚል ስም ያመነጩት ሊሆን ስለሚችል በጥንቃቄና በማስተዋል እንመልከተው” በማለት ላይ እንዳሉ የታወቀ ነው። ነገር ግን አባ ማትያስ እውነተኛ መነኩሴ ቢሆኑ እና ለተሰየሙበት ፓትርያርክነት ብቃት ቢኖራቸው ኖሮ ስለ ዓባይ ግድብ ከማውራት ይልቅ፤ መነኮሳቱ ለሚጮሁለት ህዝቡም ለተጨነቀለት ለዋልድባ ገዳም ቅድሚያ በሰጡ ነበር። ከወያኔ አባላት ከነ አቶ ዓባይ ጸሐዬ ውጭ እና ገለልተኛ የሆነ ቡድን ይዘው በገዳሙ በመገኘት የተደረሰበትን እውነት በውስጥና በውጭ ሆኖ ለሚጨነቀው ህዝብ ሪፖርት ባደረጉ ነበር። እንኳን ገለልተኛ ታዛቢ ይዘው ወደ ገዳሙ ሊሄዱ ቀርቶ፤ በገዳሙ ምንም ነገር እንዳልተከሰተና ምንም እንዳልሰሙ ለማስመሰል ባንደበታቸው ሊነኩት እንኴ አልሞከሩም።ይህም የሚያመለክተው የመነኮሳቱን ድምጽ አፍኖ ገዳሙን ለመደምሰስ እቅድ ካለው ወያኔ ጋራ ያላቸውን ህብረት  ነው። 

o    ፲፪፦አባ ማትያስ የ... ቤተ ክርስቲያናችንን የውግዘት መመሪያ ጥሰዋል። ስለውግዘት መመሪያችን የሚነግረንን እንመልከት።

ክፍል . ውግዘት ባጭሩ ሲብራራ


ውግዘት ሕጻናት እርስ በርስ እየተራጩ የሚጫወቱበት መራጫ ውሀ አይደለም። መደፈር መነካት ለማይገባቸው እንደነገረ መለኮት ላለ ዓቢይ ነገር፤ ወይም እግዚአብሄር በአርያው የፈጠረው ክርስቶስ በደሙ ያከበረው የሰው ህይወት እንዳይገሰስ መጠበቂያ ቅዱስ ሥርዓት ነው።እንኳን ውግዘት እገዳም ቢሆን አንድ ሰው ቀድሞ ከተወገዘ ወይም ከታገደ መልሶ ከማውገዙ በፊት የታገደውን የክህነቱን ስራ አቁሞ፤ የተወገዘበትን ወይም የታገደበትን ምክንያት ስህተት መሆኑን ቢያንስ በሶስት ማስረጃዎች አስደግፎ ለሚመለከተው በማቅረብ ውግዘቱን ወይም እገዳውን ከራሱ ላይ ማስወረድ አለበት።
የታሰረበትን የውግዘት ሰንሰለት ከእጁ ሳያወልቅ፤ የተሸከመውን ውግዘት ከራሱ ሳያወርድ፤ መልሶ ማውገዝ አንተ እንትን ነህ ሲሉት፡መልሶ አንተም ያው ነህማለት የውግዘትን ዓላማ ማቃወስ ነው። የታገደም ሆነ የተወገዘ ሰው ውግዘቱ በስህተትም ቢሆን ተሸክሞ መቅረት የለበትም። በስህተት የሚያወግዝ ሰው ቅዱሱን ውግዘት ያለ አግባቡ በመጠቀሙ፤ ራሱንም ያወገዘውንም ውግዘቱንም ያረክሳል። በስህተት የተወገዘውም ሰው ባይሳሳትም እንኳ ውግዘቱን ተቀብሎ ዝም ብሎ ከተቀመጠ፤ በስህተት ባወገዘው ሰው ላይ የሚሰነዘረው በደል እሱንም ይጨምረዋል። ይህ እንዳይሆን መመሪያችን “ወለእመ ተዐውቀ ግብር ላእሌሁ ግብር ዘይከልእበውስተ ቀኖናት እምተሰይሞቱ ይትከላእ።ወእመ አኮስ ለይሰየም ወዕድውኒ ዘያስተዋድዮ  ወኢያቀመ ላዕሁ ዘዘክሮ ለእመ ኮነ ለይሰደድ እምቤተ ክርስቲያን”(ፍአ ፭፡ቁ ፺፱) ብሎ ያስጠነቅቃል።
ለምሳሌ፦አባ ማትያስ ከንሳስ ላይ መጥተው እኔን ለስድስት ወራት አገድኩ ባሉ ጊዜ፤ እዚያው ላይ ትክክል አለመሆናቸውን ለራሳቸውና ለህዝብ ብገልጽም፤ የቤተ ክርስቲያናችንን መመሪያ በመከተል ምንም ሳላደርግ እግዳቸውን አክብሬ፤ መታገድና መወገዝ ያለባቸው እራሳቸው እንጅ እኔ እንዳልሆንኩ ለማሳየት ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ማስረጃዎች ያደረኩትን እጠቅሳለሁ
*    በቅዱሳት መጻህፍት
*    በማህበረ ካህናት
*    በአኀት አብያተ ክርስቲያናት
ራሳቸው አቡነ ጳውሎስ በጻፉትየአባ ማትያስ እምነት የሮማ ካቶሊክ ብቻ መሆኑን በሚያረጋጠው በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በተመዘገበው በማረጋገጥ አቅርቤአለሁ። ይህን ለማረጋገጥ የሚፈልግ ሁሉ በጉጉል ፈልጎ ሊደርስበት ይችላል።
የአባ ማትያስ ስህተትና የኔን ትክክለኛነት በእነዚህ ማስረጃዎች አስደግፌ በማቅረብ እኔ ሳልሆን የተሳሳቱት አባ ማትያስ መሆናቸውን ማህበረ ካህናቱ አራጋግጦ እንዲታረም ለአቡነ ጳውሎስ ሲልክ ለአቡነ ይስሐቅም ስላቀረበላቸው አቡነ ይስሀቅ በጻፉት ደብዳቤ ያባ ማትያስ እገዳ ተሰረዘ። [የአቡነ ይስሐቅን ደብዳቤ ለማግኘት ይህን ሰንሰለት ይጫኑ፦ Archbishop-Abuna-Yesehaq Letter]:: በዚህ መንገድ እገዳው ከላየ ላይ ሳይነሳ እንኳን ቅዳሴ ኪዳን አላደረስኩም የወረወሩብኝን እገዳ ተሸክሜ እርሰዎ ማነዎት? በሚል ስሜት አገልግሎቱን ብቀጥል፤እርሰዎም እኔም እኩል በእገዳ የተሳሰርን ነን በማለት፤ እሳቸው ባዘጋጁት በስህተት ቀንበር መጥመድ እራሴን ከትቼ ከሳቸው ጋር እራሴን እኩል ማድረግ ነበር። ይህም ማለት ራሴ ቀኖናውን እየጣስኩ ሌላውን ጣሰ ብየ መክሰስ ኢትስርቁ ትብል ወለሊከ ትሰርቅ የሚለውን ማስጠንቀቂያ መርሳት ነው። አባ ማትያስ በኔ ላይ በወረወሩት እገዳ ትክክለኛ ሲኖዶስ ቢኖር ተዋርደው ራቁታቸውን ቆመዋል።
በስህተታቸው ቀድመው ያወገዟቸውን አቡነ ተክለ ሃይማኖትን መልሶ ማውገዝ ይቅርና የደርግን መንግሥት ለማውገዝ እንኳ የሞራል አቅማቸው በሁለት ምክንያቶች አይፈቅድላቸውም።
ü  . የደርግን መንግስት እያወደሱ በካድሬነት አገልግለዋል።
ü  . የኢ... ቤተ ክርስቲያናችን የሰጠቻቸውን አደራ በልተዋል። ይህን ህሊናቸው እያወቀው ቀኖናውን ጥሰው ከመንበሩ ላይ ከተቀመጡ በኋላአቡነ ዜና ጠርተው እስኪነግሩኝ ድረስ መወገዜን አላውቅምውግዘቱንም አንስተውልኛል በማለት ዋሽተዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ጊዜ አቡነ ዜናን፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ኤርትራዊውን አቡነ ያዕቆብን በመጥቀስ ሌላም የተምታታ ነገር ተናግረዋል።
እግዚአብሄርን የማይፈሩ ሰውን የማያፍሩ ከፋፋይእያሉ የወያኔ ጎዲፈቻ ልጅ የነበሩትን አቡነ ጳውሎስንእንዲህ ያለ ፓትርያርክ አይተን አናውቅም እያሉ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን የከሰሱት የኢሀደግ የበኩር ልጅ አባ ማትያስ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋራ በቆዩበት ጊዜ በነበራቸው ባህርይ ሲመዘኑ። ወይ ከሁለቱም በላይ ልቀው፤ ወይም ከሁለቱም በታች ወድቀውእንዲህ ያለ ፓትርያርክ አይተን አናውቅምሊባሉ ይገባቸዋል። 

ክፍል ሁለት

በጠቅላይ ቤተክህነት በነበርንበት ጊዜ የተፈጸሙ ክስተቶች

 

ክፍል ፪.እንዲህ ያለ ፓትርያርክ

አይተን አናውቅም

 

ዛሬ አቴንስ የሚገኙት ንቡረ ዕድ ኃይለ ልዑል ገሪማና እኔ በሰበካ ጉባኤ መመሪያ ተመድበን በተዘዋዋሪ ልዑካንነት ስንሰራ፤ ግንቦት ፬ቀን ፸ ዓ.. በደብረ ኃይል ቅ/ ራጐዔል ቤተ ክርስቲያን  ደብር ችግር ተፈጠረና ህዝቡ ጉዳዩን ለቡነ ተክለ ሃይማኖትና  ለቤተ ክህነቱ ስራ አስጂያጅ ለቀሲስ ዶ ክተር ምክረ ሥላሴ አቀርበ።  ንቡረ ዕድ ኃይለ ልዑል ገሪማና እኔ ተልከን በቦታው ተገኝተን አጣርተን እንደምናቀርብ ለፓትርያርኩ የቤተ ክህነቱ ጠቅላይ ስራ አስኪያጅ ነግረዋቸው ኖሮ ማታ እራት ላይ የሚከተለው ቃለ ምልልስ ተደረገ።
አቡነ ተክለ ሃይማኖት፦
“አንተና ቀሲስ ኃይለ ልዑል ገሪማ በቦታው ተገኝታችሁ ነገሩን ለማጥናት እንደምትላኩ ስራ አስኪያጁ ነግረውኝ ነበር። ሄዳችሁ ነበር? ከሄዳችሁስ ምን ተረድታችሁ መጣችሁ?” ብለው ጠየቁኝ። 
እኔም፦  “ችግሩ ባለቃውና በህዝቡ መካከል ነው” አልኳቸው።
አቡነ ተክለ ሃይማኖት፦  “ህዝቡን ስሙት”  አሉ።
አባ ተክለ ማርያም (አባ ማትያስ)፦  “ዝም ብሎ መንጫጫት ነው እንጅ ህዝቡ ምን ያውቃል!” አሉ። 
አቡነ ተክለ ሃይማኖትም፦ በቁጣ “እንዲህማ አይባልም” አሉና “ዛሬ ህዝቡ ነቅቷልና መጀመሪያ የህዝቡ ድምጽ መሰማት አለበት። የፈቀደውን ይምረጥ” አሉ።
አባ ተክለ ማርያም፦  መለሱና “ገና አልነቃም” አሉ።
አቡነ ተክለሃይማኖት፦  መለስ አደረጉና “ኧኽ ኧኽ ቢነቃማ ነው እኛን ፓትርያርክ እንድንሆን   የመረጠን!” ብለው በቁጣ ቃል መለሱላቸው።
አባ ተክለ ማርያምም ለአቡነ ተክለሃይማኖት መለሱና “እንዲህ ያለ ፓትርያርክ አይተን አናውቅም!” ብለው እርፍ!
አባ ተክለ ማርያም ይህ ከባድ ቃል ካንደበታቸው ከወጣ በኋላ ከኛ በባሰ ሁኔታ ደነገጡ። ልንጎርሰው በጣቶቻችን የያዝነው ምግብ ከገበታው ላይ ወደቀ። አባ ተክለ ማርያምም ደንግጠው እየተንቀጠቀጡ ከፎቅ ወርደው ሄዱ። ብርሃኑ የጎደለ ምግብ ለማምጣት ከታች ከወጥ ቤት ወርዶ ስለነበረ ይህ ፍጥጫ ተካሂዶ አባ ማትያስ ደንግጠው ሲሄዱ  አቡነ ተክለ ሃይማኖትም አዝነው ከመኝታ ቤታቸው ገብተው ሲዘጉ አልነበረምና ምግብ ይዞ  ሲመለስ ሁለቱንም ከተቀመጡበት አጣቸው።
 የት ሄዱ ብሎ ጠየቀ። አባ መስቀሌም ቀለብ አደረጉና “ሁለት ጥጋበኛ እርስ በራሳቸው ሲታገሉ እኛ ድሆች ጦማችንን አናድርም! ምግቡን ጨምርልን አንተም ቁጭ በልና ራትህን ብላ! ብለው ቁጣ ባለው ድምጽ ለብርሃኑ መለሱለት። አባ መስቀሌ ቀጠሉና “ ፈቃዱ አስተርአየ ብሉ እንብላ” አሉ። ካባ ተክለ ማርያም አንደበት የፈለቀው ከባድ ንግግር በ አዕምሮየ ላይ የጨነው መርግ፤ ካባ መስቀሌ ንግግር ጋራ ተጋጨብኝና በመሳቅ እና በመደንገጥ መካከል ተቀርቅሬ ቀስ ብየ ከፎቅ ወርጄ ወደ ቤት ስሄድ፤ አባ ተክለ ማርያም ሻንጣቸውን ይዘው ከግቢ ወጥተው ሊሄዱ በሩን ሲቆልፉ ደረስኩ። የት ነው የሚሄዱት? ብየ ስጠይቃቸው፤ ወደ መጣሁበት እመለሳለሁ” ብለውኝ ወጥተው አደሩ። እኔም ነገሩ እጅግ እየገረመኝ ብቻየን አደርኩ።
በበነጋው ሰኞ ባቶ  ጸጋየ በርሄ ይመራ የነበረው የህጻናት አስተዳደግ ጉባኤ በኤርትራ ስለ ነበረው ድርጅት ከፓትርያርኩ ጋራ የሚነጋገሩት ጉዳይ ስለነበራቸው በአባ ተክለ ማርያም አማካይነት ቀጠሮ ኖሯቸው፤ የጉባኤው አባላት የነበሩት እነ ንቡረ እድ ዲሜጥሮስ እነ አባ ሀብተ ስላሴ ያሁኑ አቡነ ጢሞቴዎስ ማለቴ ነው ፋይል ከተሸከሙት ከአቶ ጸጋየ በርሄ ጋራ መጡ። ቀጠሮ የተያዘው በአባ ተክለ ማርያም በኩል ስለሆነ ወደ ፓትርያርኩ ቢሮ እንዲያስገቧቸው አባ ተክለ ማርያምን ሲፈልጓቸው አጧቸው። አባ መስቀሌን  አባ ተክለ ማርያም የት አሉ ብለው ጠየቋቸው። አባ መስቀሌም ትላንት ማታ በፓትርያርኩና በሳቸው መካከል ችግር ተፈጥሮ በቤታቸው እንዳላደሩ ነገሯቸው። “የት የሄዱ ይመስለወታል? “ብለው ጠየቋቸው። አባ መስቀሌም “በቤታቸው እና ባካባቢው በሌሉበት ወቅት ሲፈለጉ የምናገኛቸው ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ወይም ከእህታቸው ቤት ስለሆነ ከሁለቱ ባንዱ ነው የሚገኙት። ስለዚህ ወይ መርካቶ አካባቢ ወደ ምትኖረው እህቴ ወደሚሏት ቤት ሄደዋል ወይም ወደ ካቶሊኩ አቡን ወደ አባ አስራት ዘንድ ይሆናሉ” አሏቸው።
ንቡረ ዲሜጥሮስ አባ ተክለ ማርያምን ካሉበት ለማምጣት የፓትርያርኩን ሹፌር አቶ ታደሰን  እንዲተባበራቸው ለመኑና አባ መስቀሌ እና እኔ አብረን ከንቡረ እድ ዲሜጥሮስ ጋራ ወደ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሄድን። አባ ተክለ ማርያም ቁመናቸው እሳቸውን ከመሳሰሉ በቅላታቸው ክልሶች ትግርኛ እንጅ አማረኛ መናገር የሚከብዳቸው ሰዎች ጋራ ሆነው ከአቡነ አስራት ጋራ ተቀምጠው አገኘናቸው
ንቡረ ዲሜጥሮስ ሁሉንም ያውቁ ስለነበረ ገና ከደጃፍ ላይ ደርሰው ሲዩዋቸው ሁሉም ከመቀመጫቸው ተነስተው በክብር ተቀበሏቸው። ንቡረ እድ ዲሜጥሮስ “የመጣነው ላስቸኳይ ጉዳይ አባ ተክለ ማርያምን ፈልገን ነው። ብዙ አልቆይም በሌላ ጊዜ እመለሳለሁ” ብለው ካቡነ አስራትና አብረዋቸው ከነበሩት ሰዎች ተሰናብተው፤ አባ ተክለ ማርያም አስከትለው ሲወጡ ከላይ የጠቀስኳቸው በቅላታቸው ክልሶች ትግርኛ እንጅ አማረኛ መናገር የሚከብዳቸው ሰዎች መኪናችን እስከቆመበት ቦታ ድረስ አጅበዋቸው ወጡና ወደ ፓትርኩ ተመለስን።
ከፓትርያርኩ ቢሮ እንደ ደረስን ንቡረ እድ ዲሜጥሮስ አባ ተክለ ማርያምን “በቀጠሯችን ተገኝተናልና ለፓትርያርኩ ይንገሩልን” አሏቸው። አባ ተክለ ማርያም ሄደው ለመንገርም ፈሩ። የፈሩበትንም ምክንያት ለነንቡረ እድ ዲሜጥሮስ ለመንገር አፈሩና ቆመው ቀሩ። አባ መስቀሌ ወደ አባ ተክለ ማርያም እያመለከቱ “ኧረ ወዲያ ፋይዳ የለዎትም። ተላንት ማታ የሰሩትን ስህተት አይናገሩም! አሉና ፊታቸውን ወደ ንቡረ እድ አዙረው “ትላንትና ማታ ለፓትርያርኩ ተገቢ ያልሆነ ከባድ ቃል ካፋቸው አምልጧቸው ተጋጭተው ተለያይተዋል። በዚህ ምክንያት በገቢው አላደሩምና አስታርቋቸው” አሉ።
በዶ ክተር ክነፈ ርግብ ዘለቀ ይመራ የነበረው በደርግ የተቋቋመው የጊዜአዊ ተሀድሶ ጉባዔ  ቡድን  በዚያ ወቅት አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ከአቡነ ቴዎፍሎስ የበለጡ አስመስለው  ለማቅረብ ቢጫ አልብሰው “ብቸኛው ፓትርያርክ” በሚል ቅጽል ከፍተኛ ፕሮፓጋንዳ የሚያሰራጩበት ነበር። እነ ዶክተር ክነፈርግብ አባ ተክለ ማርያም ከፓትርያርኩ የተጋጩበትን ምክንያት “በአባ በትረ መወገድ የተቀየሙ አድሀርያን አባ ተክለ ማርያምን ካቡነ ተክለ ሃይማኖት ለማራቅ ያደረጉት ተንኮል ነው” ተብሎ እንዲወራ አደረጉ።
ይሁን እንጅ፤ በይቅርታ እንዲስማሙ ተደረገና በንቡረ እድ መሪነት ከፓትርያርኩ ጋራ  ለማስታረቅ አባ ተክለ ማርያምን ይዘን ገባን። ነገሩ ከየት እንደሚጀመር ሁሉም ግራ ገባው። አባ መስቀሌ “ጥፋተኛው አቡነ ቀሲስ አባ ተክለ ማርያም ናቸውና ይቅርታ ይጠይቁ! ለፓትርያርኩም እሰዎም ይቅርታውን ይቀበሉ” አሉ። አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቅንድባቸውን ወደ ላይ ሰኩና አባ ተክለ ማርያምን አተኩረው ተመለከቷቸው። አባ ተክለ ማርያምም በፍርሀት መንፈስ ፈዘው ለጥቂት ደቂቃ ቆመው ቀሩ።
ንቡረ ዕድ ሜጥሮስ በቁጣ “አባ መስቀሌ የነገሩዎትን ለማድረግ ለምን ተቸገሩ ? የሚለው ካፋቸው ሲወጣ፤ አቡነ ተክለ ሃይማኖት “ተዋቸው የፈቀዱትን ይሁኑ! በዚያውስ ላይ በደለኛ ማን ሆኖ ነው? የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ!” አሉና ዝም አሉ። ሁሉም አባ ማትያስን “ይሂዱ እግራቸው ላይ ይውደቁና ይቅርታ ይጠይቁ” አላቸውና፤ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ይቅርታ ጠይቀው  ይሂዱ እንጅ !እርሰዎ ጀግና አይደሉም እንዴ? ባሉት ንግግራቸው አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለካድሬነት ተልእኮ ወደ ጎንደር እስካሰነበቷቸው ድረስ፤ “እንዲህ ያለ ፓትርያርክ አይተን አናውቅም!” ላሉት ይቅርታ ተደርጎላቸው ወደ ቦታቸው ተመለሱ።
     

ክፍል ፪ ለ“ይሂዱ እንጅ! እርሰዎ  ጀግና አይደሉም እንዴ?


ደርግና ኢ.... በትንቅንቅ ላይ ሆነው አዲስ አበባ በተናወጠች ጊዜ የጨነቀው ሁሉ “ደም እንደውሀ  ሲፈስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዝም ብለው ያያሉ” የሚል ጉርምርምታ ነበር። ከእለታት አንድ ቀን አባ ተክለ ማርያም እህት የሚሏት ሴት ዘመዷ የሆነ ሰው በኢ.... ተገደለና ከሀዘኑ ቆይተው “ህዝብ ለምን አታወግዙም እያለ በመጠየቅ አሰለቼኝ ወይ ያስታርቁ ወይ ያውግዙ” አሏቸው። አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ግራ ገብቷቸው ሲጨነቁ አየኋቸው። “ማንና ማንን ነው የማስታርቀው የቱንስ ነው የማወግዘው” ብለው ይጠይቋቸው አልኳቸው።  እንዳልኳቸውም “አስታርቁን ብሎ የላከዎ አካል አለ? ላስታርቅ ብልስ ከይትና ከማን ነው የሚጀመረው? አሏቸው። አባ ተክለ ማርያም “በመንግሥት ላይ አምጾ ህዝብ እየፈጀ ያለውን ኢሃፓ የተባለውን አመጸኛ ነዋ! አሏቸው። ኢ.... የሚባለውን መሪ ካወቁት ይጥሩና ያገናኙኝና ለምን ይህን ታደርጋላችሁ? ብየ ልጠይቃቸው? አሏቸው። አባ ተክለ ማርያምም “ፍርሀት ካልሆነ በቀር እነሱን በአካል መፈለግ አያስፈልግም  የለየላቸው ፈጣሪ አልባወች ናቸው” ብለው ነገሩ ቆመ።
ኢዲዩ የተባለው ድርጅት በዚያው ሰሞን በወሎ በጎንደር በጎጃምና በትግሬ “እግዚአብሄር አልባ ጉግ ማንጉግ መንግሥት መጣብህ እያለ በመስበኩ ፤ ህዝብ በመንግሥት ላይ ማመጽ ጀምሯል። ስለዚህ ይህን የሚያስተባብሉ ለአብዮቱ ታማኝ ቄሶች ይዘጋጁ ተባለ እና አባ ተክለ ማርያምና በኋላ በዚያው በጎንደር ቀርቶ ጓድ ቀለመ ወርቅ ተብሎ የህዝብ ድርጅት ክፍል የነበረው ባህታዊ ቀለመ ወርቅ ካሣሁን ተጠቆሙ። ጥሪውን በደስታ ተቀብለው በሻለቃ ካሳየ አራጋው ይመራ በነበረው ቡድን ወደጎንድር በካድሬነት ሊሄዱ ዝግጅታቸውን አጠናቀው ሳለ፤ በዚያው ሰሞን ወደ ወሎ የተላኩት በኢዲዩ  ተገደሉ ተብሎ ወሬው ደረሰ። አባ ተክለ ማርያም እሞታለሁ ብለው ደነገጡና  ሀሳባቸውን ቀይረው “እፈልገዋለሁ ብለው ያስቀሩኝ ከሄድኩ እሞታለሁ” ብለው አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ተመጸኗቸው።
አቡነ ተክለ ሃይማኖትም የሚቀጥለውን መለሱላቸው። “ይሂዱ እንጅ !እርሰዎ ጀግና አይደሉም እንዴ? ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር ሲይዙት ይደናገር፤ እኔን አስታርቁን ብሎ የጠየቀ ሳይኖር ማንን ከማን ጋራ ማስታረቅ በማላውቀው ነገር ያስታርቁ ወይም ኢሀፓ የተባለውን ያውግዙ እያሉ ሲጨቀጭቁኝ አልነበረም? አሁን በቀጥታ ወደረስዎ ሲመጣ ለምን ይፈራሉ? ሞትንስ ለምን ፈሩ ? መነኩሴ አይደሉም? ይህን ያህል ሞት የሚፈሩ ከሆነ ማን አስገደደዎ? እርሰዎና ባህታዊ ቀለመ ወርቅ ለአብዮቱ ተሰልፈን እንሞትለታለን ብላችሁ በለፈለፋችሁት ነው ከዚህ ሁሉ ካህን እናንተ ላይ ይህ ሃላፊነት የመጣ። መጀመሪያ  እታይ እታይ ምን አሰኘዎ? ያስታርቁን ብሎ ወደኔ የመጣብኝ ሳይኖር ወይ ያስታርቁ ወይ የመንግስትን ተቃዋሚ ያውግዙ እያሉ እኔን ያስገድዱበት የነበረው ጀግንነት አሁን የት ጥሎዎት ሄደ? የርሰዎ ፍርሀት እንድዋሽ ሊያደርገኝ አይችልም ይሂዱ” ብለው በቁጣ ተነገሯቸው። አባ ተክለ ማርያምም “ከሞት ከተርፍኩ ፊተዎውን አላይም” ብለዋቸው ተናደው ሲሄዱ። አቡነ ተክለ ሃይማኖትም “ሳይሞቱ ከተመለሱም እንመክርበታለን። በዚያው ከቀሩም በሰማይ ያገናኘን” ብለዋቸው አባ ተክለ ማርያምን አሰናበቷቸው።
ብዙ ሳይቆዩ ከጎንደር በደህና እንደተመለሱ ተሰማ። ወደ ቤተ ክህነት ግቢ ግን አልመጡም። መመለሳቸው ከተሰማ ከሳምት በኋላ ከንቡረ ዲሜጥሮስ ጋራ ወደ ቤተ ክህነት ግቢ መጡ። አባ ተክለ ማርያም “ከሞት ከተርፍኩ ፊተዎውን አላይም” ብለዋቸው ተናደው ሲሄዱ። አቡነ ተክለ ሃይማኖትም “ሳይሞቱ ከተመለሱም እንመክርበታለን። በዚያው ቀሩም በሰማይ ያገናኘን” በመባባል ተለያይተው ስለነበረ፤ በዚህ የከረረ መሰነባበቻ ቃል ሲለያዩ የተዘረጋውን መጋረጃ ቀዶ መግባት ለአባ ተክለ ማርያም ካቅማቸው በላይ ሆነባቸው። ይሁን እንጅ በንቡረ ዲሜጥሮስ አስታራቂነት የጸቡን መጋረጃ ቀደው ተመልሰው እንደገቡ ከአባ መስቀሌና ከራሳቸው ከአባ ተክለ ማርያም ሰማሁ።
ወደ ጵጵስና የገቡትም በንቡረ እድ ዲሜጥሮስን እና ያን ጊዜ አባ ሀብተ ሥላሴ የዛሬው አባ ጢሞቴዎስን አማላጅነትና አግባቢነት ነው። አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ጳጳስ እንዲያደርጓቸው ወደ ጵጵስናው ሹመት እንዲያቀረቧቸው ሁለቱን አማላጅ አድርገው ላኩባቸው። በመጀመሪ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አልተቀበሉትም፤ እነ ንቡረ እድ “ጳጳስናውን ተቀብለው የእርሰዎን አርዌ ብርት ይዘው ከጀርባዎ ቢቆሙ ለቤተ ክርስቲያን ክብር ነው ብለው እግባቧቸው አቡነ ተክለ ሃይማኖትም “እንዳላችሁ ይሁንላችሁ እንጅ ለኔ ክብር የምትሉት እንኴን ተውት”  ብለው በራሳቸው ትእዛዝ ወደ ጵጵስናው ጎራ አቀረቧቸው። አባ ተክለ ማርያም አባ ማትያስ ተብለው ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄዱ እኔም የነጻ ትምህርት እድል በእንግሊዝ ቤተክርስቲያን አግኜቼ ወደ ኬንያ ሄድኩ። አባ ማትያስ ከኢየሩሳሌም ለቀው በወጡበት ወቅት እኔ ኬንያ ነበርኩ። ከዚያ በኋላ ወደ ዋሸንግተን መጥቼ እስክንገናኝ ድረስ ስለሳቸው አላውቅም።

ክፍል ሦስት


ክፍል ከኬንያ ወደ ዋሸንግተን ዲሲ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ጣጥ


 ኢየሩሳሌም ነዋሪ ዐይናለም ግዛው የተባሉ ዜጋአቡነ ማትያስ (አባ ተክለማርያም አስራት) ማናቸው? በሚል ርእስ May 23. 2013 በኢትዮጵያ ሪቪው ቀርቦ በተነበበው ጦማር ገጽ 6 ላይ የኔን ስም ጠቅሰው “አባ ትክለ ማርያም አስራት የዋሺንግተኑን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ከኒው ዮርክ በየሣምንቱ እየተመላለሱ ያገለግሉ በነበሩት መልአከ ገነት ውቡ ላይ ያሳድሩት የንበረውን አግባብ የለሽ ተፅእኖና እራሳቸው ከኬንያ ድረስ አስመጥተዋቸው ከነበሩት ዲያቆን አስትርአየ ጽጌ ጋር የነበራቸውን አለመግባባት” በማለት የተንጠለጠ ውጥኑን ባለጨረሰ ሀረግ ጠቅሰውኛል።[ሙሉ ሀሳቡን ለማግኘት ይህን ሰንሰለት ይጫኑ አቡነ ማትያስ (አባ ተክለማርያም አስራት) ማናቸው? ]  
ዐይናለም ግዛው የተባሉ ዜጋ በደረሳቸው ብጣሽ እንፎርሜሼን ውጥን ጨራሽ በሌለው ንግግራቸው ባቀረቡት ጦማር እኔን ከአባ ማትያስ ጋራ በተያያዘ ሰንሰለት ዲያቆን በሚል ቅጽል ጠቅሰውኛል። ይህን ስል ዲያቆን በሚል ቅጽል ዝቅ አደረጉኝ በሚል ስሜት አይደለም። የሰንበት ተማሪው ሁሉ መላከ እገሌ፤ መምህር እገሌ፤ ቄስ እገሌ፤ ቆሞስ እገሌ፤ ሊቀ ጳጳስ እገሌ፤ እያለ ቤተ ክርስቲያናችንን በሚታራምስበት ወቅት ዲያያቆን መባሉን እመርጣለሁ። ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ  ቤተ ክርስቲያን ቀኖና ነገረ መለኮት አሁንም ዲያቆን ነኝ።
ይሁን እንጅ ቅስናውን እንድቀበል ያመነጩትን የነአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ትእዛዝ ለመጠበቅ  አቡነ አብርሃምም ከቅስናው ጋራ የጫኑብኝን አሁንም በጆሮየ በመጮህ ላይ ያለውን አደራ ላለመሰወር ከዲቁና ወደ ቅስና በራሳቸው በእባ ተክለ ማርያም አዘጋጅነት በ፷፱ ዓ/ምህረት የተሻገርኩ መሆኔን ሳልገልጸው ማለፍ ትክክል መስሎ አልተሰማኝም። ይቅርታ እየጠየኩ ወደ ወደ ጀመርኩት ርእስ  እመለሳለሁ።
የመጀመሪያ ምኞቴና ምርጫየ በወቅቱ በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጽ/ቤት የስደተኞ መርጃ ክፍል ኀላፊ ሆነው ያገለግሉ ከነበሩት ከአቶ መላኩ ክፍሌና እና በናይሮቢም ሆነው ይሰሩ የነበሩት Re ሙሩ ጋንዲ ጋራ በመነጋገር ወደ እንግሊዝ አገር ለመሄድ ነበር።
አባ ማትያስ ለንደን ላይ ሆነው መሰደዴን ሰምተው ሀሳቤን ቀይሬ ወደ አሜሪካ እንድመጣ ጠየቁኝ። ለቤተ ሰብም የሚመቸው አሜሪካ መሆኑን ስለነገሩኝ ሀሳቤን በመቀየር እነ አቶ መላኩ ክፍሌ በቸርች ወርልድ ሰርቭስ አማካይነት ካፒታል ሂል ላይ ያለውን የሉትራን ሬፎርሜሽን ሞግዚት እንዲሆነኝ ተነጋግረው ወደ ዋሸንግተን እንድመጣ ጨረሱልኝ።
የሉትራን ሬፎ ርሜሽን ቤተ ክርስቲናም አገር የሚያለማምደው CO SPONSER ከተገኘ ቤት አለን እንቀበለዋለን በማለታቸው ይህንኑ ላቡነ ማትያስ ነግሬያቸው፤ አቡነ ማትያስ ለዋሸንግተን መድኃኔ ዓለም ህዝብ አቀረቡት። የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደር ቦርድም በወቅቱ የቦርዱ ጸሀፊና የሳቸው የቅርብ ረዳት የነበረችው ለወይዘሪት ሀረገ ወይን ምስባኩ ሀላፊነቱን በመስጠት ነገሩ ተፈጽሞ ወደዲስ መጥቻለሁ። ሁሉንም እያመሰገንኩ ወደ ዲሲ ከመጣሁ በኋላ በገጠመኝ ሁኔታ ዋሽንግተን ዲሲ ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ራሴን እንዴት እንዳገለልኩ ከዚህ በታች አገልጻለሁ  

ክፍል ከዋሸንግተን ዲሲ ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ራሴንገለልኩበት ምክንያት


ከዋሸንግተን መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ራሴን ያገለልኩበት ሁኔታ በህይወቴ ከገጠሙኝ ለመወስን አስቸጋሪና ፈታኝ ከሆኑት አጋጣሚወች በላይ አንዱ ነበር። ማንም ግለ ሰብ ተመሳሳይ ፈተና ላይ ሲወድቅ ነገሮችን አመዛዝኖ  እውነቱን ከተገነዘበ በኋላ ወስኖ የሚወስደው ርምጃ በጔደኝነት፤ ብግል ውለታና ጥቅም፤ በመንደር ልጅነት ወይም በድርጅት አንጻር ከወሰነ ውሎ አድሮ  የራስን ህሊና ይጎዳል። አገራችንን እና ቤተ ክርስቲያናችንን ከገቡበት አዘቅት ለማውጣት ይህን ያህል ዘመን የወሰደው ከዚህ አይነት ሰንሰለት በጥሰን ራሳችንን ነጻ ማድረግ አለመቻለችን እንደሆነ አረጋግጫለሁ።  
በዚያ ወቅት ላሜሪካ እንግዳ ለህዝቡ ባእዳ ነበርኩ። ስፖንሰር ካደረጉኝ ፈረንጆች ይልቅ የማውቃቸው ያመንኳቸው አቡነ ማትያስን ነው። በሁለተኛ ደረጃ በሳቸው አማክየነት ያወኳትን በወቅቱ የረዳችኝን ወይዘሪት ሐረገ ወይን ምስባኩን ነው። ዲሲ በደረስኩበት ወቅት አቡነ ማትያስ እና ወይዘሪት ሐረገወይን ምስባኩ ባንድ ጎራ ተሰልፈው፤ ነፍሳቸውን ይማርና ከነ ኮረኔል አስፋው አንዳርጌ እና ከነ ዶ ክተር አክሊሉ ጋራ በመፋለጥ ላይ ነበሩ። በወቅቱ የደርግ ወኪል ሆነው በተባበሩት መንግስታት ይሰሩ የነበሩት ዶ ክተር አክሊሉ ሀብቴ እነ ኮረኔልን ደግፈው ስለነበረ ጸቡ ተጋግሎ ነበር። የደርግን መንግስት ይቃወም በነበረው የዲስ ነዋሪ ኢትዮጵያዊ ሁሉ  በጃንሆይ ዘመነ መንግስት የፈጸሙት በደል ሳያንስ ከደርግ ጋራ በመወገን አገርን በደሉ እየተባሉ እነ ዶክተር አክሊሉ ይወቀሱ ነበር።
በዚህ ሁኔታ ላይ የነበሩት የእነ ዶክተር አክሊሉ ቡድን ሁለት ነገሮች እያነሳ አቡነ ማትያስን ይቃወም ነበር።
o   ፩ኛ፦  አባ ማትያስ ደርግን የተቃወሙ ኢየሩሳሌም ላይ ለፈጸሙት ስህተት ሽፋን ይሆንላቸው ዘንድ የፖለቲካውን ግርግር በመጠቀም ተሰደድኩ አሉ እንጅ ስደታቸው ለቤተ ክርስቲያንና ለአገር ብለው አይደለም።

o   ፪ኛ የሞራል ድሀ ስለሆኑ ልንከተላቸው ተገቢ ያልሆኑ ናቸው ስለዚህ ልንቀበላቸው አይገባም በማለት ነበር።
የአባ ማትያስ ቡድን ደግሞ የሚከተሉትን እያሰራጩ እነ ዶክተር አክሊሉን ይቃወሟቸው ነበር።
o   ፩ኛ አባ ማትያስ የሸዋ ተወላጅ ባለመሆናቸው እነ ዶክተር አክሊሉ አይፈልጓቸውም።

o   ፪ኛ ዶ ክተር አክሊሉ ደርግን ወክለው ከተባበሩት መንግስታት ጋራ ስለሚሰሩ አቡነ ማትያስን የሚቃወሙት ደርግን ለማስደሰት ነው። በዚህ ምክንያት ካቡነ ተክለ ሃይማኖት ተቀብለው ያመጡትን ንዋየ ቅድሳት በቤታቸው ይዘውታል እየተባለ በሰፊው ይወራባቸው ነበር።
አባ ማትያስ በነ ዶክተር አክሊሉ ይወቀሱባቸው የነበሩት ጉዳዮች ከመላከ ገነት ውቡ ጋራ ከነበራቸው ከባድ ግጭት ጋራ ተዳምሮ ጸቡ ከሯል። መላከ ገነት ውቡ ቀደም ብለው ለትምህርት ወደ ውጭ ከተላኩት ከነመላከ ሰላም ሳሙኤል ተረፈ እና ከነ አቶ ዓለማየሁ ሞገስ ጋራ ለትምህርት ወጥተው ሳይመለሱ የቀሩ እየተባለ በቤተ ክህነቱ አካባቢ ሲነግርላቸው እሰማ ነበረ። በአካል አግኝቻቸው እውነትም ስለሳቸው ቀደም ብየ ሲነገርላቸው ከሰማሁት መልካም ዝናቸው ሳይናወጹ አገኘኋቸው። ሁሉንም መስማት ትቼ በአባ ማትያስና በነ ዶክተር አክሊሉ መካከል ያለውን ውዝግብ መላከ ገነት እንዲነግሩኝ ጠየኳቸውና በጥንቃቄ ሰማኋቸው።
ያባ ማትያስ ተቃዋሚዎች እነ ዶክተር አክሊሉ በአባ ማትያስ ላይ ያደረጉባቸው ዘመቻ የክፍለ አገራቸው ሰው ባለመሆናቸው ብቻ ለመሆኑ  ማረጋገጫ ባላገኝም፤ አባ ማትያስ ከሚወቀሱባቸው ነገሮች ታላቁና ሊያራምድ የማያስችለው በሰፊው ይወራባቸውና ይታይባቸው የነበረው የሞራል ውድቀት ነበር።
የነበረብኝ ተጽእኖ ይህም ብቻ አልነበረም። በወቅቱ የነበረው ዋሸንግተን ዲሲ ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያንኑ አስተዳደር ኮሚቲ:
“አቡነ ማትያስ ከመላከ ገነት ጋራ በመጋጨታቸው ያሉት ብቻቸውን ነው። እኛም በሳቸው ላይ የምናየውንና የምንሰማውን በግልጽ ለምንገር ቦታችን ባለመሆኑ እስካሁን ስንታመስ ቆይተናል። አሁን ግን ራሳቸው “የተማረ ነው አምነዋለሁ በብዙ መንገድ ይረዳኛል ለቤተ ክርስቲያኑም ይጠቅማል” ብለው በነገሩን መሰረት co-sponsor በመሆን መጥተሀል። ከመጣህ ጀምሮ ምን ታያለህ? ምን ተረዳህ? የታየህን ምከራቸው። በደርግንና በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ላይ የሚሰነዘሩት ነቀፌታና ውግዘት የግላቸው ስለሆነ አንቃወማቸውም። እኛን የቸገረን በሳቸው ጎልቶ የሚታየው የሞራል ውድቀት ነው። ከማይመጥናቸው ሰው ጋራ እስካሁን ያሳዩትን ጥብቅ ግንኙነት እንዲቀንሱ ንገራቸው” አሉኝ።
ሰው በነገረኝ ሳይሆን ራሴ አይቼ የተረዳሁትን ለብቻቸው ነግሬአቸው ለጊዜው ድንጋጤ በተመላበት አንክሮ ከተቀበሉኝ በኋላ ከገቡበት ልማዳቸው ሊላቀቁ ባለመቻላቸው በኮሚቴው ፊት በራሳቸው መኖሪያ ቤት ለራሳቸው፡ለወይዘሪት ሀረገ ወይን በግልጽ ነግሬ ከዲሲ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን እራሴን አገለልኩ።  



ክፍል .እራሴን ከዲሲ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያባገለልኩት ወቅት የተናገርኩትን ለማስታወስ


በኮሚቴዎቹ ፊት የተናገርኩትን አባ ማትያስና ወይዘሪት ሀረገወይን   በህወት ስላሉ አንደበታቸው ባይደፍረውም ማምለጥ ለማይችሉት ህሊናቸው እተወዋለሁ። በወቅቱ በመድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የቦርድ አባላት ከነበሩት ጋራ ለረዥም አመታት አብረን በመቆየት በጋራ ያሳለፍነው ሌላ ፈተኛ ነገር ባይኖረንም፤ ያች ወቅትና የተነጋገርንበት ቦታ አገናኝታን በጋራ ያሳለፍናትን ፈተና ክርስቲያኖች ከሆኑና ሞራሉ ካላቸው በዚህ ወቅት ሊመሰክሩት ይገባቸውል ብየ አምናለሁ።
ሆኖም በወቅቱ የነበሩት የዲሲ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የቦሮድ አባላት የነ ዶክተር አክሊሉንም ሆነ የእነ አባ ማትያስን የርስበርስ ግጭት እየነቀፉ ከሁለቱም ቡድኖች ሳይወግኑ፡ እኔም ነገሮችን ያላንዳች ተጽእኖ ራሴን አግልየ በጥሞና እንድመለከታቸው በሚያስችለኝ መንገድ ስለቀረቡኝ፤ በወቅቱ በሚሰራጨው ወሬ ግራ ተጋብቼ ውሎ አድሮ በሚያጸጽተኝ መንገድ እንዳልሄድ ረድተውኛልና ወደኔ የቀረቡበትን ጥበባቸውን አደንቃለሁ።
ሆኖም ባደባባይ ደፍረው መናገር ያልደፈሩትን፤ አንድ ሰውና ሁለት ሰው በግል ሲጠይቃቸው ብቻ የሚናገሩ ከሆነ፤ ነገሩን ወደ አሉባልታነት መቀየር ነውና ከክርስትና ውጭ ያደርቸዋል። ስለዚህ “አባ ማትያስ ማናቸው?” በማለት ከመሰከሩትና ከለንደን ህዝበ ክርስቲያን ጋራ አባ ማትያስን በመፋለም ላይ ያለውን ህዝበ ክርስቲያን ሊደግፉ እንደሚገባቸው ላሳስባቸው እወዳለሁ።
አባ ማትያስ ወደ ዋሸንግተን ዲሲ እንድመጣ ያደረጉበት ምክንያት ፤እሳቸው በሚያምኑበት እኔ በማላምንበት ድርጅት ከሳቸው ጋራ ተሰለፌ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ላይ በየወሩ ለሚያሰራጩት የውግዘትና የዘለፋ ፕሮፓጋንዳ ተበባሪ ለማድረግ እንደነበረ መሆኑንንም ስገነዘበው ደግሞ አባ ማትያስን አመሰግናለሁ ለማለት ይከብደኛል።
በዚህ መሳይ ውዝግብ ማንንም ሳልጎዳ የራሴን ሞራል ለመጠበቅ ከጊዜአዊ እና ግላዊ ወዳጅነት ተጽእኖ ተላቅቄ ለመወሰን የገጠመኝ ፈተና ግን ቀላል አልነበረም።
እዚህ ላይ አንባቢን ላስገነዝበው የምወደው ይህችን ዓለም መቼ እንደምንሰናበታት በለበስነው ሥጋዊ ብዥታ ባናውቅም፤ ዘላለማዊት መኖሪያችን እንዳልሆነች ግን አረጋግጠኞች በመሆን እናውቃለን። በህወታችን የምንወስናቸው ውሳኔዎች፤ በሥጋዊ ብዥታ እንደምናውቃት ዕለተ ሞታችን በብዥታ ላይ በተመሰረተ ሀሳብ ላይ መመስረት የለባቸውም። ውሳኔወቻችን ይህች ዓለም ዘላለማዊት ቤታችን አለመሆኗን  በምናውቅበት እርግጥ ላይ መመስረት አለበቻው።
ከኬንያ ወደ ዋሸንግተን እንድመጣ ላደረጉልኝ ላንዲት ውለታ ብቻ ስል፤
*                ፩ኛ፡ህዝቡ በገሀድ እያየው እኔም ደርሸበት የተረደኋቸውን የሞራል ውድቀት ሸፍኘ ከሳቸው ጋራ መቆም።
*                ፪ኛ፦እሳቸው በሚያምኑበት እኔ በማላምንበት ድርጅት ከሳቸው ጋራ ተሰለፌ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ላይ በየወሩ ለሚያሰራጩት የውግዘትና የዘለፋ ፕሮፓጋንዳ ተበባሪ መሆን
*                ፫ኛ፦መላከ ገነት ውቡን ከዚያ በፊት ባላውቃቸውም፤ ከነ መላከ ሰላም ሳሙኤል ተረፈና አቶ ዓለማየሁ ሞገስ ጋራ ለትምህርት ወጥተው ሳይመለሱ የቀሩ እየተባለ በጥሩ ዝና በቤተ ክህነቱ አካባቢ ሲነግርላቸው እሰማ ስለነበረ ስለሳቸውም የሰማሁት መልካም ነገር እውነት ሆኖ ስላገኘሁት፤ ባካባቢው የሚካሄደውን ሁሉ ከሳቸው ተረዳሁ። እውነቱን ከተረዳሁ በኋላ ግን አባ ማትያስ ላደረጉልኝ አንዲት ውለታ ብቻ ያውም እኔ በማላውቀው ለተዘጋጀ ውለታ ለበስ ወጥመድ ላላመንኩበት ድርጅት መሰለፍ ተገቢ እንዳልሆነ አዕምሮየ ስላስገደደን ቅር እያለኝ እራሴን አግልያለሁ።
እራሴን በማግለሌም ለእነ ወይዘሪት ሀረገ ወይን ክህደት መስሎ ታያቷቸው በከሀዲነት ሲፈርጁኝ። አባ ማትያስን ለማጥቃት ይታገሏቸው የነበሩት እነ ዶክተር አክሊሉ ደግሞ ከአባ ማትያስ የኔን እራሴን ማግለል ከማስረጃዎቻቸው አንዱ አድርገው ባሰራጩት ፕሮፓጋንዳ አባ ማትያስን ለመታት ተጠቅመውባተል።
በገለጽኩት ችግር ምክንያት ከሳቸው መለየቴን አባ ማትያስ እና ወይዘሪት ሀረገ ወይን  እንደ ክህደት ቢቆጥሩትም፤ በበኩሌ ራሴን አገለልኩ እንጅ እሳቸውን ለመጉዳት ብየ በደል የፈጸምኩባቸው ስላልመሰለኝ “የወያኔ መንግሥት ኢትዮጵያን አፈራረሳት እጁን የሰጠውን ወታደር ከወገናዊነት ስሜ በራቀ ጭካኔ ፈጁት። በኤርትራም እጁን የሰጠውን ወታደር የወርቅ ጥርሱን እየወለቀ ለመውሰድ ከሰባዊ አድራጎት ውጭ ግፍ ተፈጸመበት” የሚል ዜና ተሰምቶ በስያትል ያለ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ተበሳጭቶ ወገናዊ ስሜቱን በሰላማዊ ሰልፍ  በገለጸበት ወቅት ስያትል ነበርኩ።

ሲያትል በነበርኩበት ወቅት የተፈፀመ


አቡነ ማትያስ “ምን መጣ ብላችሁ ነው የምትንጫጩ? በማለታቸው ከዋሸንግተን ህዝብ ጋራ በግጭት እንዳሉ ሰማሁ። ምንም እንኴ ዲሲ ላይ በተፈጠረው ችግር በሃሳብ ሳንግባባ ቀርተን ብንለያይም፤ አልፌ አልፌ በስልክ መነጋገሬን አላቋረጥክሙ ነበርና ከራሳቸው ለመስማት ደውየ አነጋገርኳቸው። የሰጡኝ መልስ “ኤርትራ ላይ አለቀ የምትሉት ኢትዮጵያዊ ሁሉ መጀመሪያውንስ በሰው አገር ምን ለማድረግ ሄደ? እንኳን አሰብ ኤርትራ ቀድሞውንም የኢትዮጵያ አካል አልነበረችም። እንኳን አስብ የአክሱም ታሪክም የናንተ አይደለም። ገና እናንተ የማትወዱትና የማትቀበሉት ብዙ ነገር ሲደረግ ታያላችሁ” የሚል የቁጣ ቃል መለሱልኝ።
ይህችን ጦማር ሳዘጋጅ መንፈሴን ለማሳረፍ ምናለሽ መቲ የሚለውን የኢሳት ቴሌቪዥን ስመለከት በመቲና በወይዘሮ ኤልሳቤጥ መካከል ስለ ህጻናት አምባ የተፈጸመውን ግፍ ሲነጋገር ተመለከትኩ። በዚህ ውይይት ላይ የወያኔ ባለስልጣናት ህጻናቱን ሲበትኑ ህጻናቱ “የት ነው የምንሄደው ያደግንበት ቤታችን ይህ ነው? እያሉ ሲያለቅሱ። የወያኔ ባለስልጣናት “የጠላት ልጆች የማሳደግ ግዴታ የለብንም” ብለው መለሱላቸው ሲሉ ወይዘሮ  ኤልሳቤጥ የተናገሩት ንግግር አባ ማትያስ ከተናገሩት ጋር ገጠመብኝ።
ወይዘሮ ኤልሳቤጥ “ይህ የወያኔወች አነጋገር ያደረሰው ጉዳት መቼውንም ሊጠገን የማይቻል የአዕምሮ ቀውስ ነው” ብለውታል። አባ ማትያስና እነ ስብሀት ነጋ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያስከተሉት የሞራል የነገረ መለኮትና የቀኖና ቀውስ ለማስወገድ ህዝቡ ተገንዝቦ የሚያርመው ስለሆነ “ሊጠገን የማይቻል የአዕምሮ ቀውስ ነው” ባልለውም ቀላል ነው ማለት አይቻልም።  
በደርግ ዘመንና ከዚያም በፊት በአገር በወግንና በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ተፈጽሞ በማያውቅ ሁኔታ አገር ሲቃወስ ድንበር ሲፈርስ ህዝብ ሲጎዳ አስችሏቸው ዝም አይሉም የሚለው አዝጋሚ ግምቴ ደርግን በየወሩ ይዘልፉ ስለነበረና የወያኔን ድርጊት ከደርግ ጋራ ሳነጻጽረው የከፋ ስለመሰለኝ፤ በዚያ ግንዛቤ የከፋ መጣ ይላሉ በሚል ከጠቅላላው ህዝብ ጋራ ይቆማሉ የሚል ደካማ ግምት ነበር። ለካ አባ ማትያስ ገብረ ኪዳን ደስታና ስብሀት ነጋ በዓለም ዙሪያ ያሉትን ሰዎቻችውን ካዘጋጇቸው አንዱ በመሆን በስልክ ንግግራችን በሰጡኝ መልስ መቶ በመቶ ኢትዮጵያዊ እንዳልሆኑ አረጋገጥኩ። የሳቸው ተከታይ የሆኑት ማህበረ ቅዱሳኖች ከንሳስ ላይ ለተሳሳተው ለሮማ ካቶሊክ እምነት ድጋፍ ለመስጠት በመጡ ጊዜ በአካል ተገናኘን።

ክፍል .መ፦አባ ማትያስ ከንሳስ ላይ የፈጸሙት ደባ


የከንሳስ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን የተመሰረተችው ሀሳቡን ካመነጩት ጥቂት ሰዎች ጋራ በመተባበር በአቡነ ይስሀቅ እና በራሴ ነበር። ህንጻውን ከፕሮ ቴስታንቶች ገዝተው ኢርቶዶክሳዊ መልክ ያስያዙት፤ አባ ማትያስን ተፋልመው ያባረሩና አሁንም ያንድነታቸውን ስም በመድኃኔዓልም ስም ሰይመው ክርስቲያናዊ የህወት ጉዟቸውን ከንሳስ ላይ በመቀጠል ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
አባ ማትያስ የወደቁበትን የተሳሳተ እምነት በመካከላችን የዘሩብን ሰዎች ስለ ነገረ መለኮት ሊመሰክሩ የሚችሉት አባ ማትያስ ብቻ ናቸው ብለው ያቀረቡትን ጥያቄ ተቀበለው አባ ማትያስን የጋበዙ ሰዎች በኪዳነ ምህረት ስም የተመሰረተውን ቤተ ክርስቲያን ሲመሩ የነበሩት አሁን በመድኃኔ ዓልም ስም ያንድነታቸውን ስም ሰይመው ክርስቲያናዊ የህወት ጉዟቸውን ከንሳስ ላይ በመቀጠል ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው።  
አባ ማትያስ ግብዣውን ተቀብለው ሊመጡ ፈቃደኛ መሆናቸውን ስሰማ ስልክ ደውየ “የሚመጡበት ምክንያት እጅግ አወዛጋቢ በሆንም በአካል ከተለያየን አመታት በኋላ ለመገናኘት ያበቃንን አምላክ አመስግኘ፤ ጉዳዩ የመላ ህዝበ ክርስቲያኑና አኀት አብያተ ክርስቲያናት የሚሳተፉበት በጉባዔ የተማርነውም ስለሆነ፤ ነገረ መለኮቱን የተረዳ ልዩነቱን መግለጽ ከቻለ እንኴን እርሰዎ ማንም ቢመጣ አልቃወምም” አልኳቸው።
እሳቸውም “የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሊቃውንት የሚሉትን የተማርከውንና የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በጥቅሉ የምዕራቡ ክርስትና በዚህ ጉዳይ የሚለያዩበትን ጽፈህ ላክልኝ” ብለውኝ፤ ስለ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ጠልቀው ያልተረዱ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ የሚጠቅሷቸውን ሳይቀር ገልጬ (ጥቅምት 15 ቀን 2002 ዓ.. . . .) የተጻፈውን 21 ገጽ ጽፌ ላኩላቸው። መድረሱን በስልክ ስጠይቃቸው “መድረሱን ደርሶኛል ግን አንተ የምትለውን ፈጽሞ ሰምቼው አላውቅም” አሉኝ።
 ቀጠሉና “እመቤታችንን በተመለከተ በኛና በካቶሊኮች መካከል ይህን ያህል ልዩነት ያለ አይመሰለኝም ነበር“ አሉኝ። እኔም መልሸ “ ከንሳስ ላይ ጥያቄውን ያነሱት ሰዎች ከሮማ ካቶሊክ አባባል ጋራ አቆላለፈው ወደ ህዝቡ ስለከተቱ ባስረጅነት ስጋበዝ ተናገርኩት እንጅ “በሐና እና በኢያቄም ሩካቤ ሥጋ በተፈጥሮ ህግ ተወለደች፤ ከሴቶች ተፈጥሯዊ ልማድ ንጽህት ቅድስት ናት። በሰውነቷ የሰራቸው ነገር የለም” እንላለን እንጅ፤ እንደ ሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በ“ Immaculate Conception”ተጸንሳ ተወለደች አንልም።  በዚህ መንገድ ተጸንሶ ተወለደ የምንለው ያለወንድ ዘር ከሷ የተወለደውን ጌታችንን ብቻ ነው ይህ ነገር የሚነሳው በሊቃውንቱ ደረጃ በከፍተኛ አብነት ትምህርት ቤቶች ነው። ወይም comparative theological studies በሚሰጥባቸው ዘመናውያን ሰሚናሮች ነው። ስላቸው “እንዲህ ነው እንዴ ለካ” አሉኝ። እንደ ከበዳቸው ገባኝ እና “ይህ ነገር ይዘው የመጡ ሰዎች ወደ ህዝቡ ከተውታልና አዋቂ ሰው ሳያነጋግሩ እንዳይመጡ። ከዚህ ከመጡ በኋላ ግን ያልሆነ ነገር ተናግረው ችግር ቢፈጥር፤ እኔ ከተማርኩትና በካህናት ማስልጠኛም ውስጥ ሳስተምረው ከኖርኩት ፈቀቅ አልልም በኔና በእርሰዎ መካከል ችግር ይፈጠራል”ብያቸው ተለያየንና መጡ።
የላኩላቸውን አንብበው ተረድተው፤ ከአዋቂ ሰው ጋራም ተነጋግረው፤ የኛ የኦሬንታል እና ምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ይህን ይላሉ፤ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን  እናንተ በስህተት የምትከተሉን ይላሉ፤ፕሮቴስንታንቱ ደግሞ ይህን ይላል ብለው የተሳሳቱትን አስተምረው ይመለሳሉ ብየ ስጠብቅ፤ እራሳቸው ጭራሽ ብሰው አንድ ጊዜ ወደ ሮማ ካቶሊክ ሌላ ጊዜ ወደ ሂንዱ ይትብሀል እየዘለሉ በመዘባረቅ ራሳቸውን ፈራጅ ዳኛ፤ የሰንበት ተማሪዎችን ለነገረ መለኮቱ ጠበቃ፤ ከሳሽ እና ምስክር፤ እኔን ተከሳሽ አድርገው ለመፍረድ የፍርድ ዙፋናቸውን ዘረጉ።
ችሎታቸውን የማውቅው አባ ማትያስ  ፈራጅ ሆነው፤ አንድ እና ብዙ፤ ሩቅና ቅርብ፤ ትንቢትና ሀላፊ፤ ለይተው የማይናገሩ ሰዎች  ከሳሽና ምስክር ሆነው፤  በኔ ላይ ለመፍረድ በከፈቱት ስብሰባ ተሰብስበው በኔ ላይ እየተጠቃቀሱ የሚመላለሱትን ስሰማ   የደረቤ የከብት እረኞች ጋማውን ይዘው የሚጋልቡት ሌጣ ፈረስ መስለው ታዩኝና እሳቸውንና ከእሳቸው ጋራ የተሰበሰቡትን ጥያቸው ወጣሁ። ኮሚቴዎቹ ከውጭ ነበሩና አዝኘ መውጣቴን ከፊቴ ተረድተው ተደናገጡ። ለምን ጥየ እንደወጣሁ ጠየቁኝ። በሚቀጥለው ጦማር  የምገልጸውን  ከአባ ተክለ ማርያም ጋራ ማን እንዳስተዋወቀን በጋራ ያሳለፍነውን ደግና ክፉ ትዝታ  ክደው እንደማያውቁኝ በመምሰል ራሳቸውን ዳኛ   የሰንበት ተማሪዎችን ከሳችና ምስክር  በማድረጋቸው “ጊዜ የገጠመው ቅል ድንጋይ ይሰብራል” የሚለው ትዝታ ትውስ ብሎኝ  እየተገረምኩ ኮሚቴዎች ለጠየቁኝ ምንም መልስ ሳልመልስ መጽሀፍ ወደ ማነብባት ክፍል ተመለስኩ።
አባ ማትያስ ቀጠሉና “ህዝቡ ይሰብሰብና የደረስኩበትን ውሳኔ አውጃለሁ” በማለታቸው አዋጃቸውን ለመስማት ወደ ስብሰባው ከገባው ህዝብ ጋራ ተመልሼ ገባሁ። አባ ማትያስ በህዝብ ፊት ቆሙና፤ የሰንበት ተማሪዎች ትክክል እንደሆኑ፤ እኔንም በመሳሳቴ እንዳገዱኝ የሚገልጽ ከቤታቸው ጽፈው ይዘው የመጠቱን ከኪሳቸው አውጥተው አነበቡ። የጻፉትን ወረቀት ስመለከተው ግርም ብሎኝ “ጽፈህ ላክልኝ ባሉኝ መሰረት ደክሜ በመጻፍ የላኩለዎትን ወረቀት ከምን አደረሱት? ብየ ስጠይቃቸው፤ የጽሑፉን ይዘት ከመናገር ይልቅ “ያን ደቃቃ ጽሑፍ! ብለው የፊደሉን መጠን በመናገር ቁም ነገሩን ሊሰውሩት ሞከሩ። ይህ የተደራረበ ሸፍጣቸው ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት እንዲህ ያለ ፓትርያርክ አይተን አናውቅም” ባሉባት ቅጽበት የተሰማኝ የሳቅና የልቅሶ አይነት መሳይ ስሜት ወረረኝ። ዲሲ ላይም በኮሚቴወችና በወይዘሪት ሀረገ ወይን ፊት የሞራል ምስክርነት የሰጠሁባት ቅጽበት በኔና በእሳቸው መካከል የታሪክ ቀለበትነቷን ከንሳስ ላይ ጠቀለለች። በዚያች ወቅት  የተናገርኩትን በቦታው የነበረ ህዝብ ይናገረው።
ይህንም አድርገው ወደ ዲስ ከተመለሱ በኋላ። “እኔንም ሆነ አቡነ ይስሀቅን ያጠቁ መስለዎት ተሳስተዋል፤ የወደቁት ራሰዎ ነዎ ያስቡበት” ስላቸው፤ መልሰው ከነገሩኝ ከተለያዩ ነገሮች ውስጥ በጣም ያናደደኝ “ብትፈልግ ወደ ሰማይ ተኩሰው! የሚለው ትዝህርትና ባዶ ትእቢት የተሞላበት ንግግራቸው ነበር። ይህን አይነት ንግግር ባህላችን “የስድ አደግነት ንግግር” ሲለው፤  የቤተ ክርስቲያናችን መርሆ  ደግሞ  “ወኢይደቅ ውስተ ሥቃየ  ሰይጣን ወይደሉ ከመ ይኩንዎ ሎቱ ሰማዕተ  በሠናይ እምአላውያን ዚአነ በሃይማኖት ከመ ኢይደቅ ውስተ ትዕይርት ወውስተ አሕበለ ሰይጣን ፍ; አ; ፭፡፹፫)  ይለዋል። “ብትፈልግ ወደ ሰማይ ተኩሰው! የሚለውን  ንግራቸውን በወቅቱ  ያካፈልኳቸው ሰዎች የሳቸውን ስም እየጠቀስኩ የማቀርበውን ጦማር ባነበቡ ቁጥር አባ ማትያስ “ብትፈልግ ወደ ሰማይ ተኩሰው! ብለው ያዘዙህን ለመፈጸም ወደ ሰማይ በመተኮስ ጥይትህን አልጨረስክም? ይሉኛል።
“ሌባ ሲሰርቅ ይስማማል። የሰረቀውን ሲካፈል ይጣላል” እንደተባለው፤ በአቡነ  ጳውሎ ስና በአባ ማትያስ መካከል የነበረው አለመግባባት ከኢትዮጵያ ህዝብ የሚሰርቁትን ሲካፈሉ እንጅ፤ አገር በማጥፋቱ በሀሰቱ በሸፍጡ የወያኔን መንግሥት ለመርዳት በሚያስችላቸው ነገር ሁሉ ተባብረዋል። አባ ማትያስና አቡነ ጳውሎስ ይጋጩ የነበረ የወያኔን ቀልቦ ስቦ ባለሟልነታቸው ለማሳየት በሚያደርጉት ውድድር እንጅ ለአገርና ለቤተ ክርስቲያን በሚጠቅም ስራ ላይ የተሻለ ለማምጣት  ሲሉ አልነበረም። ይልቁንም እነ አቶ ስብሀት ነጋ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ለዘረጉት ተልእኮ ደቀ መዛብርት መሆናቸውን ያረጋገጡበት ነው። የአባ ማትያስና የአቡነ ጳውሎስ የእርስ በርሳቸው ግጭትና ፍጭት ወያኔ ኢትዮጵያን እና ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ገና ጫካ ሳለ ለቀመረው ሙስና ስለሚሰጡት የተሻለ ድጋፍ  ነበርየሚገርመው ግን  የነ አባ ገብርኤል አቋምና ባህርይ ነው። መልካቸውን እየለዋወጡ “ከዲቁና እስከ ጵጵስና በክህደት ጎዳና” በመጔዝ ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ በመተባበር በህዝባቸው ላይ የፈጸሙት ደባ ሳያንሳቸው፤ አሁን ደግሞ  ለአባ ማትያስ የጥፋት ጉዳይ አዲስ ተላላኪ በመሆን አባ ገብርኤል ከአቡነ ቀውስጦስ ጋራ በለንደን በሚኖረው ህዝበ ክርስቲያን ላይ የፈጸሙት የጥፋት ተልእኮ ነው። ያደረጉትን እንመልከት።

ክፍል አራት

የአባ ማትያስ ልዑካን እነ አባ ገብርኤል ለንደን ላይ የፈጸሙት ከቤተ ክርስቲያናችን መመሪያ ጋራ ይጋጫል።


ክፍል . አባ ገብርኤል


  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ህዝበ ክርስቲያን “ወነሀሊ በእንተ ኤጲስቆጶሳት ከመ እሙንቱ አፉሁ ለእግዚአብሔር” (አን ፱፡፫፻፲፩) ተብሎ የተነገረውን ባለመልቀቅ ጳጳስ አይዋሽም ይልቁንም አንደበቱን የሸፍጥና የነገረ ዘርቅ መፈሰሻ ቦይ ከማድረግ ቆጥቦ የእግዚአብሔርን ቃል የሚናገር አድርጎ ለመንፈሳውያን አባቶች የሚሰጠው የክብር ግምት ከፍ ያለ ነው። እነ አባ ገብርኤል ህዝቡ የሚሰጠውን ክብር እንዳላዋቂነት በመቁጠር ንቀውታል። “ሥዩማነ ቤተ ክርስቲያን ኢይሐስው ግሙራ” (አን ፱፡፫፻፪) የሚለውንም ረስተውታል። እምነቱንማ ጨርሰው ሰርዘውታል። ይህንን ባህርያቸውንም  “ከዲቁና እስከ ጵጵስና በክህደት ጎዳና” ብሎ የቤተ ክህነቱ ጋዜጣ ገልጾታል።
፩ኛ፦ አባ ገብርኤል በእምነቱ ዙሪያም በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመን ተወግዘው የተገለሉ ነበሩ። ከንሳስ ላይ አባ ማትያስ ለፈጠሩት ክህደት ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህንና መጋቤ አዕላፍ መክብብን አስከትለው ወደ አቡነ ማትያስ በመሄድ መሳሳታቸውን ገልጸው እንዲያስተካክሉ ነግረዋቸው፤ አባ ማትያስም “የተሳሳተውማ አስተርአየ ነው” ብለው ጥያቄቸውን አልቀበልም ሲሏቸው፤ ተመልሰው መጥተው እሳቸው የሚለውን ቃል ገፈው እሱ እያሉ የሚከተለውን የዘለፋ ቃል በዓባ ማትያስ ላይ ሰንዝረው ነበር። “አባ ማትያስ ምንም የማይገባው ጸጉር ብቻ ነው። ይህን በተመለከተ መጻፍ የምታስብ ከሆነ፤ አባ ማትያስን ለይተህ ከሀዲ ነው እያልክ ጻፍ እንጅ ሲኖዶስ ተሳሳተች ብለህ አትጻፍ፤ እኔንም አደራህን አትጥቀሰኝ” በማለት በማህበረ ካህናቱ ስብሰባ ላይ ተናግረው ነበር።
*    ፪ኛ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ታሟል። በሽተኛ ነው” እያሉ በመጀመሪያ  የነገሩን እራሳቸው አባ ገብርኤል ናቸው።አባ ጳውሎስንም ሲኖዶሱ በምልአተ ድምጹ መርጧቸዋል። ይሁን እንጅ ሲኖዶስን ክደው ከትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት ጋራ የሚሰሩ ነጭ አሞራ ናቸው እያለ የሰበኩ ናቸው። በኋላ ግን ሲለፈልፉ የነበረውን ሁሉ ክደው በዲሲ የነበረውን ማህበረ ካህናት አፍርሰው ቅዱስነታቸው አቡነ ጳውሎስ ጠሩኝ በማለት ወደ አቡነ ጳውሎስ ከገቡት አንዱ ናቸው።

*    ፫ኛ በገንዘብ ላይ ባላቸው የስግብግብነት ባርይ ከቀድሞው አባ መላኩ ጋራ በምእመናን ንብረት እኔ ልዘዝ በሚል መንፈስ እርስ በርስ በተጣሉበት ጊዜ፤ በዲሲ  ከተማ ዙሪያ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት  ሳሉ ቤተ ክርስቲያን ይመስርቱልን ብሎ የጠየቃቸው ሰው ሳይኖር፤ ለራሳቸው መተዳደሪያ ሲሉ ከሲኖዶሱ ፈቃድ ውጭ ልደታ ብለው ቤተ ክርስቲያን የመሰረቱ ለራሳቸው ጥቅም የቆሙ ናቸው።
አባ ገብርኤል ተነግሮ በማያልቀው ሸፍጣቸው የጵጵስናውን ተልእኮ ሙዝ፤ ስብና ሞራ ከቅቤ ጋራ ቀላቅሎ ንጹህ ቅቤ እያስመስለ በመሸጥ ህዝብ ከሚያታልል ሸፍጥ ከተመላበት ንግድ  የባሰ ማድረጋቸውን ሁሉም ስለሚውቀው የሳቸውን ጵጵስና እዚህ ላይ እናቁምና አቡነ ቀውስጦስ ከአባ ገብርኤል ጋራ በመተባበር ለንደን ላይ ያሳዩትን ውድቀት እንመልከት።

ክፍል . አቡነ ቀውስጦስ


ስለ አባ ማትያስ ስናገር፤ማንም ግለ ሰብ ተመሳሳይ ፈተና ላይ ሲወድቅ ነገሮችን አመዛዝኖ  እውነቱን ከተገነዘበ በኋላ ወስኖ የሚወስደው ርምጃ በጔደኝነት፤ ብግል ውለታና ጥቅም፤ በመንደር ልጅነት ወይም በድርጅት አንጻር ከወሰነ ውሎ አድሮ  የራሱን ህሊና ይጎዳልያልኩትን ስለ አቡነ ቀውስጦስ ስናገር፤“አአምር በዝንቱ ከመ ውእቱ ይእዜ ይትሀሠሥ እምኔከ በብዙኅ አውስኦ ፈድፋደ ለዘአማኅጸንዎ  ብዙህ ይትሀሠሥ ብዙኀ” ፭፡፻፲፱) የሚለው በወንጌሉ ላይየ ተመሰረተው መመሪያችን በበለጠ መንፈስና ስሜት እንድናገረው ያስገድደኛል።
ከአባ ማትያስ እና ከአባ ገብርኤል ጋራ የተዋወቅነው በገዳም አይደለም። በትምህርት ቤት አይደለም። ከአቡነ ቀውስጦስ ጋራ የተዋወቅነው ግን በቅዱሳን አበው በነ የኔታ ብርሃኑ ጉባዔ  በደብረ ሊባኖስ ገዳም ነው። በእድሜ ቢበልጡኝም ያንድ መምህርና ያንድ ጉባዔ ልጆች ነን። እሳቸው ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ለቀው ወደ ሰቃ ገዳም በመምህርነት ሲሄዱ፤ እኔ በዕድሜ ልጅ ስለነበርኩ ለዘመናዊ ትምህርት ወደ አዲስ አበባ ስመጣ ነው የተለያየነው። አቡነ ቀውስጦስ ሊቃውንት አበው “እስመ አነ ወለድኩክሙ በትምህርተ መንፈስ ቅዱስ” እያሉ በመንገር ካስተማሩን መስመር ከወጡ በተቀብኦ ያገኙትን ክብር ከላያቸው ገፈው ጥለዋል። ያን ከለቀቁ ለጥቅም ብለው ወደ ጵጵስናው ከገቡ ሰዎች ለይቼ የማይበት ዓይን ሊኖረኝ አይገባም።
  ወደ ሲኖዶሱ ከገቡ በኋላ  በዚያ ዙሪያ ከተሰበሰቡት ከነ አባ ገብርኤል  የሸመቱትን አቋም የለሽ ባህርይ የመቀበል ግዴታ የለብኝም። የማልቀበለበትንም ምክንያት አባ ማትያስ ከንሳስ ላይ የሰሩትን አንስተን ስንነጋገር ዝም ብሎ ማለፍ ነው ባሉኝ ጊዜ በግልጽ ነግሬያቸዋለሁ። ስለ አቡነ ቀውስጦስ  ስናገር “ወይደሉ ለክሙ ኦ ኤጲስቆጶስ ከመ ትኩኑ ሰብአ ዓይን ልሕዝብ።  እስመ አዕይንቲሁ አንትሙ ለክርስቶስ”( ፍ አ ፭፡ቁ፻፲፯) የሚለውን መመሪያ ጥሰው ዓይናቸውን ለአባ ማትያስ መነጸር አንደበታቸውን ለነ አቶ አባይ ጸሀዬ ማይክሮፎን በማድረጋቸው  ልቤ እየደማ ነው። ቢሆንም የምትወደውና የምታከብረው ወንድም ሲሳሳት ገልጾ አለመንገር ልክ አለመሆኑን በተናገርኩት ላለመጠለፍ፤ ከምቃወማቸው ሰዎች የህሊና ትዝብትም ለመዳን፤ አቡነ ቀውስጦስ ለንደን ላይ የሰሩትን ለመግለጽ  ከዚያ በፊት በሳቸው ካይ ከነበረኝ ትዝብት እጀምራለሁ።

ክፍል . አቡነ ቀውስጦስ ለንደን ላይ የፈጸሙት ስህተት የቀሰቀሰብኝዝብት


አባ ማትያስና እኔ ከንሳስ ላይ በተጋጨንበት ወቅት አቡነ ቀውስጦስ ኢየሩሳሌም ላይ ሆነው ካቡነ ጳውሎስ ጋራ ከኢየሩሳሌም ተነስ አልነሳም በመባባል በፍጥጫ  ላይ ነበሩ። አባ ማትያስ የሰሩትን ስህተት በስልክ ስነግራቸውያለ ችሎታቸው ለምን እዚህ ውስጥ ገቡበማለት አዝነው ነበር። በራሳቸው ጉዳይ ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ በፍጥጫ ላይ እንደሆኑና  አሁን በሲኖዶሱ ዙሪያ የተሰበሰቡት ሰዎች ከድህነት ለማምለጥ ጵጵስናውን እየገዙ የገቡ እንደሆኑ፤ ስለ ነገረ መለኮቱ ባላቸው እውቀት ከሰንበት ተማሪዎች  በታች የወደቁ መሆናቸውን ተነጋገርን። በንግግራችን ላይባሁኑ ወቅት ይህን ከባድ ነገር ለማቃናት ስለሚከብድ ዝም ብሎ መተው ይሻላልአሉኝ።
ዝም ብየ ማለፍማ አልችልም! ይልቁንም በሲኖዶስ ዙሪያ የተሰበሰቡት በዚህ ለመነጋገር ካቅማቸው በላይ ከሆነና መጽሀፍ ዘርግተው ሲያሷዩዋቸውም  መረዳት ካቃታቸውበኢየሩሳሌም አካባቢ የአኀት አብያተ ክርስቲያናትና ምስራቃውያን ኦርቶዶክሶች ስላሉ ሰው ይዘው ሄደው የሚሉትን ተረድተው ከነሱ ይለየናል ብለው ይንገሯቸው። በመጽሀፍ ላይ ያለውን ባያውቁት ከመላው ኦርቶዶክስ ይለየናል ብለው ካከፈሏቸው ምናልባት ይነቁ ይሆናልብያቸው ተለያየን። እንደተነጋገርነውም ባካባቢው ያሉትን ጠይቀው እነሱምእናንተ ደግሞ ይህን መሳይ ስህተት ከየት አመጣችሁት?” ብለው መልሰው እንደ ጠየቋቸውና እሳቸውምለራሴ ግንዛቤ እንጅ ቤተ ክርስቲያናችንማ እናንተ ከምትሉት የተለየ የላትምብለው እንደመለሱላቸውና ይህንኑ ማስረጃ አድርገው  ጉዳዩን እንደሚያቀርቡት ተነጋግረን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ነበር።
ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ፤ አቡነ ጳውሎስ አቡነ ማትያስን በላያቸው ሲልኩ፤ እሳቸውን ወደዲሲ ልከዋቸው በመጡ። የተነጋገርነው ከምን አደረሱት ? ብየ ጠየኳቸው። አቡነ ጳውሎስ ዘግተው ይዘው እንድንነጋገርበት አልፈቀዱምአሉ። ለምን መጡ? ስላቸው ተለኬ መጣሁ? አሉ።ለእምነቱ አቋም ለሌላቸው ሰው ተልከው እንዴት ይመጣሉ? ስላቸው አቡነ ጳውሎስ ላኩኝ የሚለውን ለውጠውሲኖዶሱ ነው የላከኝአሉ።
በጣም አዝኘእንደ እናንተ ያላችሁ በፍርሀትና በግል ጥቅም ታስራችኋል።  ጵጵስናውን እየገዙ ከየአቅጣጫው የገቡት ደግሞ በዝሙትና በዘረፋ ይህችን ቤተ ክርስቲያን ለማጥፋት ተነስታችኋል ? ስላቸው፤አሁን በጊዜአዊነትም ቢሆን በሙሉ ውክልና መጥቻለሁና አባ ማትያስ ስለሰሩት ስህተት ብቻ ሳይሆን አለ የምትለውን ጉድለት ዘርዝረህ ጻፍልኝና ለሲኖዶሱ አቀርበዋለሁብለውኝ ባማረኛ ጽፌ አቀበልኳቸው።ይህማ ከባድ ነው እንዴት ይህን አቀርባለሁ በረድ አርገህ ጻፈውብለውኝ፤ የበረደ ምጣድ እንጀራ አያወጣምና ግእዙን በማልበስ ካልሆነ የጽሁፉን ይዘት አላበርደውምብያቸው በግእዝ ጽፌ ሰጠኋቸው። ምንም አላደረጉም። [ሙሉ ሀሳቡን በግዕዝ አቡነ ቀውስጦስ የጻፍትን ደብዳቤ ለማንበብ ይህን ሰንሰለት ይጫኑ የቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ደብዳቤ ለአቡነ ቀውስጦስ]
ገንዘብ ሊሰበሰስቡ ተመልሰው በመጡ ጊዜ፤ ስጠይቃቸው መልስ አልነበራቸውም። በኋላ  እሳቸውን የታዘቡ ሰዎችበነ ዳንኤልክብረት በማህበረ ቅዱሳን ስም እየታተሙ የተሰራጩት መጻህፍት ሁሉ ይህንን ስህተት አንጸባርቀዋል። በሳቸው እየተባረኩ  ስለተሰራጩ ይህን ካነሱ እራሳቸ ይዋረዳሉ ስለዚህ ለራሳቸው ክብርና ጥቅም የቆሙ ስለኑ ለቤተ ክርስቲያን ብለው መስዋዕት መክፈል አይፈልጉምአሉኝ። ከዚያ ወዲህ ታዝቤ ተውኳቸው።
በዚህ ድካማቸው እያዘንኩ እያለሁ፤ በቅርቡየመለሰ አምልኮበሚል ርእስ የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ የተባለ ሰው ባሳተመው መጽሐፍ ከገጽ 82 እስከ ገጽ 87 ላይ የሚናገረው ስለ አቡነ ቀውስጦስ ነው።ምነው አባታችን እያወቁ!” በሚል አንቀጽእኔ መሀይሙ ለእርስዎ ቅዱስ ቃሉን መስበክ ምን እንደሆነ ልነግረዎ እንደ ማልችል እና እንደ ማይገባኝ  ባውቅም ማስታወሱን ግን አስፈላጊ ሆኖ አገኘሁትእያለ ስለ እርሳቸው ለራሳቸው ገልጾ የጻፈውን ተመለከትኩ።
እኔ እያለ ራሱን የገለጸው ተመስገንመሀይሙእያለ ነው። መሀይም የምትለው ቅጽልአምነወይምሀይመነከሚባሉት ቃላት የፈለቀች ናት። ከሁለቱም ቃላት የሚፈልቁት ሀሳቦች ማመን ወይም ማሰመን ነው። ተመስገን ራሱን ዝቅ አድርጎ ባቀረበው ልማዳዊ አነጋገር የመሀይም ትርጉም፤ በተመስገን ትህትና ላይ የሚቆም አይደለም። የግእዙ ትርጉም አምኖ ለማሰመን የተሰለፉትን አቡነ ቀውስጦስን ራቁታቸውን አቁሟቸዋል።
ተመስገንይድረስ ለአቡነ ቀውስጦስብሎ ባቀረባት ጽሁፉበአዲስ አበባ አስተዳደር አዳራሽ ሊገኙ የቻሉት ጵጵስናዎ ወደ ዓለማዊ ሲመነዘር ከከንቲባ ጋራ አቻ ሆኖ ይሆን?  እያለ እራሳቸውን እንዲመለከቱ የምክር መስተዋት አቅርቦላቸው ነበር። ባለመታደላቸው ለንደን ላይ በሚኖሩት ምእመናን ፊት ያንኑ ስህተት በመድገም፤ ራሳቸውን እንዲመለከቱበት ተመስገን ያቀረበላቸውን መስተዋት ሰበሩት!

ክፍል አምስ

በርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረጽዮን ቅድስት ማርያም የኢ.. . .. ምእመናን ላይ የተፈጸመው በደል  


ኢይደልዎ ለኤጲስ ቆጶስ ከመ ይህድግ መንበሮ ወይሑር ሃበ ካልዕ ሀገር ዘእንበለ ከመ ይዕርቅ ዘቦሙ በቁዔት ለሰብአ ይእቲ ብሄር በውስተ ህጎሙ (. . ፭፡ ፻፶፮)” ማለትም፦ በአንዲት አገር የሚኖሩ ክርስቲያኖች ነገረ መለኮት የሚያቃውስ፤ ሞራል የሚጥስ፤ ነገር ሳይጨምሩ ከሚኖሩበት አገር ህግና ባህል ጋራ አጣጥመው የሚያዘጋጁት መመሪያ በቤተ ክርስቲያናችን መርሆ ተቀባይነት አለው። ለነሱ የሚጠቅማቸው ከሆነ፤ ይህን እየተቃወመ የሚነሳውን ቡድን ገስጾ እና ይቅርታ እንዲጠይቅ አርጎ  ለማስማማት ካልሆነ በቀር አንድ ጳጳስ ሀገረ ስብከቱን ለቆ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ አይችልም
በሄደበት ቦታ ችግር የተፈጠረው ብዙሀኑ ነገረ መለኮት ሳያቃውሱ ለአምልኮቱ የሚሰበስቡትን  ቆሳቁስ ለማስተዳደር ይጠቅመናል ብለው በዘረጉት መመሪያ ከሆነ ኢያከብድ ቃልየ ላዕሌክሙ ተአክሎ ለዘከመዝ ዛቲ ተግሳጽ እንተ ረከበቶ እምቡዙሐን። ወዓዲ ይደሉ ከመ ትስረዩ  ሎቱ ወታስተፍስህዎ (፪ኛ ቆሮ ፪፡፮) ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ ባዘዘው መመሪያ መሰረት ይህም ማለትከነገረ መለኮቱ ውጭ በሆነ በቆሳቁስ ምክያት ያለመግባባት ተፈጥሮ በቤተ ክርስቲያን ሙግት ቢነሳ፤  ነዋየ ቅድሳቱ ለብዙ ህዝብ መለቀቅ አለበት። ብዙሀኑ የገሰጸው ሰው ይቅርታ እንዲጠይቅ ህዝቡም በይቅርታ እንዲቀበለው ትምህርት መሰጠት አለበት።
እነ አቡነ ቀውስጦስ የሰሩት ተቃራኒውን ነው። የለንደን ህዝበ ክርስቲያን ቀኖናውን አናውቅም፣ ዓለም አቀፋዊነቷን ብሄራዊትነት ታሪካዊትነትና ጥንታዊትነትንም አናምንም ያስተምሩን ያላቸው ይመስል፤ ሲኖዶሱም ቅዱስ አይደለም፤ የአባ ማትያስን ፓትርያርክነት አንቀበልም እንዳሉም አስመስለው፤ ነገረ መለኮቱን ቀኖናውን እና ቃለ ዓዋዲው ራሳቸው ባፈረሱብት መርሆዋቸው ንቅንቅ ያለ በለንደን ህግ እንደሚከሰስ ተናገሩ። ቤተ ክርስቲያኑ (ህዝቡ) ንብረታችን ሰፍቷልና ንብረታችንን ለመቆጣጠር የምንኖርበት አገር ህግ በሚሰጠን እድል ከዚህ በታች በተዘርዝሩት በሀገሩ ህግ መሰረት
፩ኛ Trust
 ፪ኛ፡Trustees
 ፫ኛ፡Trusty of deeds
 ፬ኛ፡Charity Company Limited Guarantee
፭ኛ፡Land registery  በሚለው መስርተው መተዳደሪያችን ይሻሻል አሉ አንጅ ቀኖናውን አልካዱም፤ ስለ አባ ማትያስን ፓትርያርክነት እንኳን አንስተው ስለመቀበላቸውና ላለመቀበላቸው አንዲት ቃል  አልተናገሩም። በዚህ ዙሪያ ምእመናኑ ያነሱት ጥያቄ ሳይኖር  ያለ ህዝብ ታዛቢነት ባቋራጭ ዘርፎ ለመክበር የፈለገ ግለሰብ Theocrasy ብሎ የነገራቸውን ብቻ ሰምተው በህዝበ ክርስቲያኑ ላይ ከባድ ሸክም ጭነው መሄዳቸው ራሳቸውን ከቤተ ክርስቲያናችን መመሪያ ውጭ አድርገዋል።
በለንደን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ለንደን ላይ እንንገሥ ያሉ እያስመሰሉቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለንደን በስደት በቆዩበት ዘመን ልንገስ አላሉምእያሉ መናገር በህዝብ አዕምሮ ላይ መቀለድና ታሪክ ማዛባት ሸፍጥ ነው። የተላኩት ስለቤ ተክርስቲያን ከሆነ ህዝቡ ያቀረበውን መመሪያ ከቃለ ዓዋዲው ጋራ ይጋጫል ወይስ አይጋጭም? በሚል ውይይት ላይ ብቻ መሆን ሲገባ የተነሳውን ጥያቄ ለመሸፈን “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለንደን በስደት በቆዩበት ዘመን ልንገስ አላሉምየሚል ነገረ ዘርቅ መናገር ከፍተኛ ደባና ሸፍጥ ነው።
ከዚያ ቦታ ላይ ስለ ቀዳማዊ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ለመናገር እንኳ ቢፈልጉ፤ ከአጼ ይኩኖ አምላክ እስከ እሳቸው ዘመን ድረስ  በቤተ ክርስቲያንና በፊውዳሉ ስርአት መካከል የነበረውን የመሬት ይዞታ ግንኙነት በጥሶ  የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር ህዝባዊ ያደረገውን ቃለ ዓዋዲ በነጋሪት ጋዜጣ ባወጁት መልካም ፈቃዳቸው ለቤተ ክርስቲያን ያደረጉት ውለታ ብቻ መሆን ነበረበት።
በዚያ ቦታና  ወቅት እነሱን ወደ ለንደን እንዲመጡ ያደረጋቸው በለንደን የሚኖረው ህዝበ  ርስቲያን አባ ግርማ  የምንኩስናቸውን ቅናተ አዲም እረሱ፤ የመታመን ማተባቸውን በጠሱ ብሎ በመጮሁ  ነው። እነ አባ ቀውስጦስ ዓይኖቻቸውን ለአባ ማትያስ መነጽር አንደበታቸውን ለነ አቶ ስብሀት ነጋ ማይክሮፎን ባያደርጉት ኖሮ፤  በለንደን የሚኖረው ህዝበ  ክርስቲያን ከሚናገረው ጋራ የተያያዘ ለነ አባ ግርማ የሚጠቅም ሌላም የሚመሰከሩት ነበራቸው። ያም  እነ እያዩ በሌ በሙዚቃቸውማተብ ያጣችሁ፤ የዓለማየሁ አለላችሁእያሉ ለእምነተ ጎደሎዎች ምሳሌ አርገው የሚጠቅሱት የአጼ ቴወድሮስን ልጅ ለንደን ላይ የተቀበረውን የዓለማየሁ ማተብ ነበር። ግን የራሳቸውን ማተብ በጥሰው ያለ ህዝቡ ታዛቢነት ባቋራጭ ዘርፎ ለመክበር Theocrasy እያለ ህዝቡን በማስቸገር ላይ ያለውን ግለሰብ ደግፈው፤ ከሰጠነው ትእዛዝ ንቅንቅ የሚል ካለዓለማዊ ህግ አለብለው ህዝቡን አስፈራርተው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። ለመሆኑ Theocrasy የሚለውን መርሆ  ከጥንት ጀምሮ የነበረው የቤተ ክርስቲያናችን እይታ ምን ብሎ እንደሚገልጸው ያውቃሉ? ይህንም በዚህ አጋጣሚ እንመልከተው።

ክፍል ስድስት

Theocracy


ህዝቡን ከፋፍሎ እርስ በርሱ ለማደባደብ በነ ስብሀት ነጋና ዓባይ ጸሐዬ የተቀመረ እኩይ ዘዴ ካልሆነ በቀር በቤተ ክርስቲያናችን ይህ ቃል ተሰምቶ አያውቅም።  ቃለ ዓዋዲው የተመሰረተው በኦሪቱ ትምህርት፤ በሐዋርያት ስብከት፤ በሊቃውንት ስርአት ትውፊት ላይ ነው። ይህ ትውፊት በህዝባዊ አስተዳደር ላይ እንጅ እነሱ እንደሚሉት በTheocrasy አስተዳደር ላይ የተመሰረተ አይደለም። የብሉይ የሀዲስ እና የመጻህፍተ ሊቃውንት ምሁራን ይቃወሙታል። በኦሪቱ፤ በሀዲሱ፤ በሊቃውንቱ መጽሕፍት እንመልከተው።

ክፍል ፮.ሀ Theocracy በኦሪት


ለ Theocrasy አስተዳደር እንደምሳሌ የሚወሰደው እግዚአብሄር ያነጋገረውን የሙሴን  አመራር ነው። ሙሴ ህዝቡን በቴወክራሲ ለተወሰነ ጊዜ ለመምራት ቢሞክርም ለራሱ ውድቀት ለህዝቡ በሽታ ሆኖበት ወደ ህዝባዊ አስተዳደር ለወጠው። በTheocrasy አመራር አልገፋበትም። ከሱ በላይ በእውቀት በልምድ የላቀ ዮቶር የተባለ ሰው “ስምአኒ ወአነ አመክረከ ወእግዚአብሔር የሀሉ ምስሌከ”  (ዘጸ ፲፰፡፲፱) ሙሴ ሆይ ምክሬን ብትሰማ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ይሆናል”   “አኮ ርቱዕ ዝ ነገር ዘአንተ ትገብር” አንተ ወኩሉ ህዝብ ዘሀሎ ምስሌከ ዓቢየ ህማመ ተሀምም። ይከብደከ ወኢትክል ባህቲተከ ገቢሮቶ”( ዘጸ ፲፰፡፲፯_፳፯) ማለትም፦ ራስህ ሰብስበህ ይዘህ የምታካሄደው አስተዳደር ትክክል አይደለም። በዚህ የምትቀጥል ከሆነ ለህዝቡም ለራስህም መልካም አይደለም ትታወካላችሁ። ብቻህን ሸክሙ ይከብድሀል። “ወቃለ ዘየአጽቦሙ ያምጽኡ ሃቤከ። ወቀሊለ ኩነኔ እሙንቱ ይኮንኑ” ለአስቸጋሪውና ለከባዱ ስራ ራስህን አዘጋጅ። ለቀላሉ ስራ ደግሞ ህዝቡን አዘጋጅ ብሎ መከረው። ለሙሴ የተሰጠውን አስቸጋሪ ስራና፤ ለህዝብ እንዲለቅ የተነገረውን ቀላል ስራ፤ ሐዋርያት ወደ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አምጥተው እንዴት እንደገለጹት በቦታው እናየዋለን።
ሙሴ ለህዝቡ ሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ የሰጠ ቡሩክ ስለነበረ የራሱን ዝናና ሳባዊ ስሜት ሳያስቀድም፤ የመከረውን ሊቅ አንተ ማነህ ሳይል፤ ምክሩን ተቀበለ። በማይችለው ነገር ራሱን  ጠልፎ ከመውደቅ አዳነ። ህዝቡንም በህሊና ዝለት ላይ ከመውደቅ አተረፈ። “ወዘንተ ቃልየ ለእመ ገበርከ ይሄይለከ እግዚ ወትክል ኮንኖ ወህዝብ ይግብእ ውስተ ምግባሪሁ በፍስሐ” ፳፫” አስተዳደሩን ከቴወክራሲ አውጥተህ ህዝባዊ ብታደርግ አንተም ህዝቡም ያለ መታወክ ያለ ሀሜት በደስታ በመተማመን እንዲኖር ታደርጋለህ ያለውን ተቀብሎ አመራሩን ህዝባዊ አደረገው።

ክፍል፮ Theocracy በሐዲስ ኪዳን


 ቤተ ክርስቲያናችን በዓለም አሉ ከሚባሉት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ወደ ሙሴ ትምህርት የምትቀርብ ናት።  በጽላቱ በሰንበቱና በማይበሉ ሁሉ ኦሪታዊ ባህል አላት። ይህ ልንክደው የማይገባንና ጥንታዊነታችንን የምናረጋግጥበት እውነት ይሁን እንጅ ባተረጓጎም ስልታችን ቤተ ክርስቲያናችን እንከን የሌለባት ናት። ለምሳሌ፤ ቤተ ክርስቲያናችን  ለቅዳሚት ሰንበት ያላት ክብር ከፍያለ ቢመስልም “ወአውጽእዎ አፍአ ኩሉ ተዓይን እምትእይንት ወወገርዎ “(ዘኁ ፲፭፡፴_ ፴፭) እንዲል፤ በሷ ምክንያት ሰው ስለተገደለ። ለክርስቶስም መከሰስ ምክንያት ስለሆነች ( ዮሐ ፭፡ ፲፮)  ቅዳሚት ስእርት (የተሻረች) ከመባል አላመለጠችም። “ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ ኔ እኔም አሳርፋችኋለሁ እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝና ዕረፍት ታገኛላችሁ”(ማቴ ፲፩፡፳፰) ብሎ በተናገረው መሰረት ሰንበት በሸክምነት በመፈረጇ በሰው ላይ የነበራት ክብር ተሽሮ ለሰው ልጅ በሚደረግ መልካም ስራ ተተክታለች”(ማቴ ፲፪፡፲፪)።
ዮቶር ለሙሴ በዚህ መሳይ አስተዳደር ራስህን ጠቅለህ ይዘህ  የምትቀጥል ከሆነ ለህዝቡም ለራስህም መልካም አይደለም ትታወካላችሁ። ብቻህን ሸክሙ ይከብድሀል። “ወቃለ ዘየአጽቦሙ ያምጽኡ ሃቤከ። ወቀሊለ ኩነኔ እሙንቱ ይኮንኑ” ራስህን አስቸጋሪው ስራ አዘጋጅ፤ ለቀላሉ ስራ ደግሞ ህዝቡን አዘጋጅ ብሎ የመከረውን ምክር፤ የመጀመሪያዎቹ  ክርስቲያኖች ሐዋርያት ተጠቅመውበታል። ለሙሴ የተሰጠውን አስቸጋሪ ስራና፤ ለህዝብ እንዲለቅ የተነገረውን ቀላል ስራ ሐዋርያት ወደ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አምጥተው እንዴት እንደገለጹት በቦታው እናየዋለን ብየ ያለፍኩትን እዚህ ላይ እንመልከተው።
ሐዋርያት “ወንህነሰ ኢንጸመድ ማእዳተ አላ ለመልእክተ ቃሉ፤ የሐዋ ፮፡፪_፮)  ማለትም፦ እኛ ከማእድ ስራ እራሳችንን እናውጣ። እራሳችንን ለቃሉ ተልእኮ እናዘጋጅ እናሰለፍ” እያሉ፤ ቀላሉን ስራ ግን ለህዝቡ ለቀቁ። ዮቶር አስቸጋሪ ብሎ የገለጸውን የስራ ዓይነት፤ ሀዋርያት “መልእክተ ቃሉ” ብለውታል።። ቀሊል ኩነኔ የተባለውን ደግሞ  ሀዋርያት ማእድ ብለውታል። ሊቃውንት አበው ሲተነትኑት ዮቶር አስቸጋሪ ከባድ ያለውን የረቀቀው ነገረ መለኮት፤ ሞራል፤ እምነት፤ ታማኝነትና የቅድስና ምሳሌ ለመሆን በቅቶ መገኘት ያለበት ካህኑ ነው። ይህ ለካህኑ መለቀቅ አለበት። ቀላል ወይም ማእድ የተባለው ደግሞ ከህዝቡ የሚቀርብ ስለሆነ ከሥጋ ጋራ የተያያዘ ቆሳቁስ ነገር (ንዋየ ቅድስት) ነው። ይህን በተመከተ የሚከናወነው አስተዳደር ለህዝቡ የተሰጠ ህዝባዊ ሚና ነው።
በነ ስብሀተ ነጋ እና በአባይ ጸሀይ በሚሽከረከረው ሲኖዶስ የሚታዘዙ ካህናት በተለይም መነኮሳት የቤተ ክርስቲያናችንን መርሆ ስተዋል። ከባድ የተባለውን ነገረ መለኮት፤ እምነት ሞራል፤ በጥቅሉ የቅድስናን ምሳሌነት ርግፍ አርገው ትተው፤ ህዝቡ የሚሰበስበውን ንዋየ ቅድሳት ለነ አቶ ስብሀ ት ነጋ ለማስረከብ ከንብረቱ ባለቤት ከህዝበ ክርስቲያኑ ጋራ  በትንቅንቅ ላይ ናቸው።
ቅዱስ ጴጥሮ ስም “መጥፎውን ረብ በመመኘት ምእመናንን በግድ ለመምራት አትሞክሩ”(፩ኛ ጴ ፭፡፪) የሚለውን ረስተው ህዝቡን በራሱ ገንዘብ በየአደባባዩ  እየጎተቱት  ነው። “ህዝቡን በማስገደድ ሳይሆን በበጎ ፈቃዱ የሚያቀርበውን መባ ተቀበል” ብሎ መሴ ያዘዘውን (ዘጽ፳፭፡፪)፤ መሰረት በማድረግ የህግ ሊቅ የሚባለው ቅዱስ ጳውሎስም  “እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ በሀዘን ወይም በግድ አይሁን”(፪ ቆሮ ፱፡፯) ብሎ ለቤተ ክርስቲያን መመሪያ እንዲሆን ያስተማረውን ሰረዙት። የቀኖና መመሪያችንም ፍ አ ፮፡፪፻፲፮ ላይ በሰፊው አብራርቶ  በብሉና በሀዲስ የተመሰረተው ፍት ሀነገስቱም ከነገረ መለኮቱ እና  ከቀኖና ጋራ  የማይጋጩ መመሪያወችን  በየዘመኑ የሚነሱት ሊቃውንት ዘመኑንና ትውልዱንና ቦታውን እየቃኙ ያሻሽሉ “ዘይበቁዕ ለሰብአ ዝንቱ መዋዕል ወዘይሄይስ ለሕግ ወምርሀቶሙ ዘያቀውም ወይኤምር”(ፍ አ ፬፡ ፷፮) ብሎ የሰጠውን ትእዛዝ  ሰረዙት። ቤተ ክርስቲያናችን መጠንቀቅ  ያለባት ክርስቶስ አክብሮ ወዶ ደሙን ላፈሰለት ህዝብ ነው። ለህዝብ ሸክምና እንቅፋት የሆነ ነገር ሁሉ ነገረ መለኮቱንና መንፈሳዊ ህይወቱን የማያቃውስ የሞራሉን ልዕልና የማይንድ ከሆነ ላለመቀበል መሞከር፤ አባ ማትያስ በኢየሩሳሌም ባጠፉት ጥፋት ምክንያት በአቡነ ተክለ ሃይማኖት የተሰነዘረባቸውን ውግዘት ለመሸፈን የወቅቱን ግርግር እንደተጠቀሙበት የራስን ደካማ ባህርይ ለመሸፈን የሚደረግ ፈጠራ ነው። በቤተ ክርስቲያናችን መመሪያ ቃለ ዓዋዲው  ተቀባይነት የለውም። ስለዚህ Theocracy የሚባለው መርሆ ለመሪውም ለተመሪውም የማይበጅ የማይታሰብ  ነው።

ክፍል ሰባት

ቃለ አዋዲ የፓትርያርክ ቴዎፍሎስና የዓጼ ኃይለ ሥላሴ ታሪካዊ ውርስ ነው


እነ አባ ገብርኤል በለንደን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ለንደን ላይ እንንገሥ ያሉስመስለው  “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለንደን በስደት በቆዩበት ዘመን ልንገስ አላሉምእያሉ የተናገሩት ሸፍጥ የአጼ ኃይለ ስላሴን ታሪካዊ ውርስ እንድናነሳው ያስገድደናል።
በዚያ ቦታና ሰአት  ስለ ቀዳማዊ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ መናገር አልነበረባቸውም። ለመናገር እንኳ ቢፈልጉ፤ ከአጼ ይኩኖ አምላክ እስከ እሳቸው ዘመን ድረስ  በቤተ ክርስቲያንና በፊውዳሉ ስርአት መካከል የነበረውን የመሬት ይዞታ ግንኙነት በጥሶ  የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር ህዝባዊ ያደረገውን ቃለ ዓዋዲ በነጋሪት ጋዜጣ ባወጁት መልካም ፈቃዳቸው ለቤተ ክርስቲያን ያደረጉት ውለታ ብቻ መሆን ነበረበት።
ከዚህ ቀደም በነሐሴ ወር ፪ሽ ፫ ዓ.ም. ፍልሰታ በሚል ርእስ ስለ ቃለ ዓዋዲው አንስቼ ከጋሼ አበራ፥ (ሊቀ ትጉሀን አባ አበራ)  ከቀሲስ ኃይለ ልዑል ገሪማና ከነ አቶ ቄርሎስ ጋራ ባደረኩት ተሳትፎ፥ የቃለ ዓዋዲውን መዋቅር ሥልት አብራርቼ   ስላቀረብኩት በጥልቅ ለመረዳት የፈለገ ይህን ሰንሰለት በመንካት ሊያነብ ይችላል። [ፍልሰታ: “እኛም ማየት አለብን"] እዚህ ላይ ለመግለጽ የፈለግኩት ግን ዛሬ ለንደን ላይ ቃለ ዓዋዲውን በtheocrasy መመሪያ ለመተካት ሰዎች በመነሳታቸው ቃለ ዓዋዲውን በተግባር ለማዋል ያለፉት አባቶች የከፈሉትን መስዋዕትነት ለመግለጽ ነው
በሰማእትነት የተገደሉት ኢትዮጵያዊው ሊቅ ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ቃለ ዓዋዲውን ባወጁበት ወቅት፤ ጥቂት የደብር አለቆች ጥቂት የመሬት ከበርቴዎችን አሳድመው መንግስትዎን  የሚጻረር ነው አንቀበልም” በማለት በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዙፋን ፊት ከሰው ባቀረቧቸው ጊዜ ደብረ ሊባኖስ በጉባዔ ትምህርት ላይ ነበርኩ።
ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ በቀዳማዊ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ፊት በቃለ ዓዋዲው ምክንያት ተከሰው በቀረቡ ጊዜ የሰጡን መልስ እና፤  ጃንሆይም በዚህ መልክ የቀረበላቸውን ሰምተው የወሰዱትን ርምጃ ሊቃውንት እያወሱ በማድነቅ በሰፊው ሲናገሩት የሰማሁትን በዚህ አጋጣሚ ሳልጠቅሰው ባልፍ ክህደት ይሆንብኛል። 
 አቡነ ቴዎፍሎስ ለተከሰሱበት የሚከተለውን የመልስ ቃል ተናገሩ። “ቃለ ዓዋዲ ብየ በመሰየም ለቤተ ክርስቲያናችን የዘረጋሁላት መመሪያ በኦሪት፤ በሐዲሳት እና በሊቃውንት ትምህርት ላይ ብቻ የተመሰረተ አይደለም። “ይልቁንም” ብለው “ገአረ ኢየሱስ በሕማሙ  ወጸርሀ ሃበ አቡሁ አድነነ ርእሶ ወወጽአት መንፈሱ ሶቤሃ” . . .  ወእንዘ ሀሎ ህየ ጸርሀ  ኀበ አዳም ገብሩ ወኀበ ኩሎሙ ደቂቁ”( ሰለስቱ ቅ ገጽ ፪፻፭፡ ቁ ፺፯  ገጽ ፪፻፮፡፺፱) ማለትም፦“ክርስቶስ በመስቀል ላይ በነበረበት ሰአት በመለኮታዊ እሪናው ለሚተካከለው ለባህርይ አባቱ  ያሰማውን ድምጽ ፤ በሰብአዊ እሪናው ለሚተካከለውም ደቂቀ አደም ያንኑ ድምጽ አሰምቷል።ንዋየ ቅድሳት የመለኮት ክብሩ የሚገልጽባቸው በመሆናቸው ከስሙ ጋራ የተያያዙ ቢሆኑም፤ ከህዝቡ የመጡና ህዝቡን መልሰው የሚያገለግሉ ስለሆኑ ህዝባዊነት ባህርይ አላቸው። ስለዚህ ህዝበ ክርስቲያኑ እግዚአብሔርን ለማምለክ  በበጎ ፈቃድ የሚሰጠውን ንዋየ ቅድሳት ሊጠብቅበት የሚያስችለውን መተዳደሪያ ደንብ ቃለ ዓዋዲ ብየ ያዘጋጀሁት ከክርስቶስ  መለኮታዊና ሰባዊ ባህርይ ውህደት በፈለቀው ድምጹ ላይ ነው።”
አቡነ ቴዎፍሎስ ቀጠሉና ጃንሆይ! ብለው፤ “ግርማዊነተዎ  እንዲማሩ የፈቀዱላቸው ኢትዮጵያውያን ልጆቸዎ “በጠቅል ጊዜ ያልተማረ ማዘን አይቀርም እያደረ” እያሉ ከዘረጉላቸው ትምህርት ገበታ በቀሰሙት እውቀት፤ ለወደፊቱ የሚጠቅማቸውን በተመልክቱበት ዓይናቸው፤ በቤተ ክርስቲያናቸው ላይ ያለውንም መሻሻል የሚገባውን ቀኖናዊ ስህተት “መሬት ላራሹ” በሚለው ቋንቋቸው እየተናገሩ ነው። ጥቂት ከበርቴዎች በቤተ ክርስቲያናችን ስም በያዙት መሬት ወጣቶች ቤተ ክርስቲያናቸውን እየወቀሱ ናቸው። የከሰሱኝ የመሬት ተጠቃሚዎች እና ጥቂት የደብር አለቆች “በርስዎ ዘመን ከደሮ ወተት በቀር የኢትዮጵያ ህዝብ ያጣው የለም” እያሉ የሚደልለዎትን  አይስሙ! ብለው ለጃንሆይ ከተናገሩ በኋላ፤ ፊታቸውን ወደ ከሳሾቻቸው  አዙረው “ይቤ መጽሐፍ ምልሑ እከየ እማእከሌክሙ ወኢትኩን ዘታፈጥን ለመቲር ወኢደፋሬ ወኢረዋጼ ለወሢር በሞሰርት ነዊኀ አስናን”( ፭፡፻፴፫) የሚለውን ቁጣና ግርማ በተመላው ድምጻቸው ጠቀሱ።
ይህም ማለት፤ ለህዝብ ለአገር ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ ነገር ሲቀርብ መታየት ያለበት የቀረበው  ሀሳብ ጎጅና ጠቃሚነቱ እንጅ ነገሩን ያፈለቀውን ሰው በምናይበት ማየት ተገቢ አይደለም።  እንዲህ ያለ መንፈስ ከመካከላችን መወገድ አለበት።  ከሥነ ምግባር ውጭ በሆነ መንፈስ እርስበርሳችን አንጠላለፍ፤  የግርማዊነታቸውን ክቡር ሰአትም አናባክን፤ በህሊናቸውም ላይ ሸክም አናክብድ!” ብለው ከተናገሩ በኋላ፤ ፊታቸውን ወደ ጃንሆይ መልሰው “ከሥራ ፈቶች አሉባልታ ርቀን፤ ህሊናችን የነገረንን፤ አቅማችንና ጊዜያችን የፈቀደልንን ጠቃሚ ነገር ለህዝባችን ሰርተን የማለፍ ግዴታ አለብን” ብለው ተናገሩ። በተጽእኖ አቡነ ቴዎፍሎስን ፓትርያርክ  አደረጉብን እያሉ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴን ያሙና ይከሱ የነበሩ ሰዎች በከሳሾች መካክል  ስለነበሩ፤ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ  ፊት ታቸውን ወደ ሰዎች አዙረው “ላባትነት ባጨነዎ ጊዜ ለከፈልንለት መስዋዕት ዛሬ ፍሬውን ለማየት ያበቃንን አምላክ እናመስግናለ” ብለው በመናገር ከሳሾችን ገሰጹ እየተባለ ይነገር ነበር።
አንባቢ እንዲያጤነው የማሳስበው፤ ቀዳማዊ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ የቤተ ክርስቲያኗ የበላይ ጠባቂ ነበሩ። በህገ መንግሥቱም የታወቀ ስለነበረ እሳቸውን በዓለም ያልነበረ ስርአት እንዳመጡ ተደርገው የሚያስከስሳቸው አይደለም። ይህም ደግሞ አስቀድመው በሰለጠኑት ህብረተ ሰቦች በክርስቲያኑም ሆነ በእስልምናው የነበረ ስርአት ነው። እስካሁንም ባለበት አለ። ትውልድ በማለፍ እና በመተካት ቅብብሎሽ ላይ ሲደርስ የተሻለ ያስተዳደር ዘይቤ ለመፍጠር የቆመበትን መተቼት ተገቢ ነው።
 ይሁን እንጅ  በአገር በምነት ተቋማት ላይ የሰራውን ደባ ንጉሥ ኃይለ ስላሴ ከሰሩት ጋራ እስቲ እናነጻጽረው። ቃለ ዓዋዲው የመንግስተዎ ተቃራኒ ነው እያሉ  የከሰሱትን ሰዎች ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ  ሳይሰሙ፤ የቃለ ዓዋዲውን  ጠቃሚነቱንና ዘላቂነቱን ተረድተው ቃለ ዓዋዲው እንዲታወጅ ያደረጉትን በጎ ፈቃድ፤ እነ አባ ማትያስን እየመለመለ ከላከብን  ከወያኔን መንግሥት  ዓላማና ተግባር ጋራ ስናነጻጽረው፤ ከቀዳማዊ ንጉሥ ኃይለ ስላሴ ጋራ ሊወዳደር ይቅርና፤ እስከዚህች ቅጽበት ድረስ የራሱን አገር የወጋ፤ የራሱን አገር ዳር ድንበር ያፈረሰ፤  የራሱን ህዝብ እያሳደደ መሬቱን ለባእድ የሰጠ መንግሥት በዓለም ላይ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ በክፋት በጥፋትና በሙስና ተወዳዳሪ የሌለው እንደሆነ እንረዳለን።
 ለመንግስታቸው ቅድሚያ በመስጠት ቃለ ዓዋዲውን ሳይቃወሙ፤ በነጋሪት ጋዜጣ እንዲወጣ በማድረጋቸው  ከፓትርያርክ ቴዎፍሎስ ጋራ የሚጋሩትን ለቤተ ክርስቲያን ያደረጉትን የቃለ ዓዋዲውን ታሪክ እነ አባ ገብርኤል መናገር ሲገባቸው፤ እነ አቶ ስብሀት ነጋ በአባ ማትያስ በኩል የወነጨፉትን ተቀብለው፤ ሲኖዶሱ ቅዱስ ነው፤ ፓትርያርካችን አባ ማትያስ ቅዱስ ናቸው፤ የሚለውን ወደ ህዝቡ ወረወሩት።
ገዳማቱን እየደመሰሰ ንብረቷን እየዘረፈ እና እነ አባ ግርማን  በመሰሉ   ሰዎች  ህዝብ  ለመጉዳት ለመበታተን በሚያደርገው እጅግ የከፋ ደባው፤ የወያኔ መንግስት ከቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ጋራ ሊነጻጸር ቀርቶ ከጣሊያን ጋራ የማይነጻጸር በክፋቱ እጅግ ከሁሉም የከፋ ጠላት መሆኑን እያወቁ፤ በተለይ በተለይ አቡነ ቀውስጦስ በህዝብ መካከል ይህን ተናግረው መሄዳቸው ታሪክ በማይረሳው ትዝብት ላይ ወደቁ።
በወያኔ ዘመን እንደ አሸን የፈሉ እንደነ አባ ግርማ ያሉ መነኩሴዎች ምንኩስናውን የገቢ ምንጭ በማድረግ የተሰለፉ እንጅ ቤተ ክርስቲያናችንን የሚያውቋት አይደሉም።  በሻርያ ህግ በመመራት ላይ ያለው የኢራን መንግስት የሚጠቀምበትን theocracy የሚባለውን የግሪክ ቃል ለንደን ላይ ይዘው ብቅ በማለት ከዚህ በታች የተጠቀሰውን “የላቀ ማእረገ ክህነት ያለው፤ገዳማዊና ሥርአተ ምንኩስና የተቀበለ” የሚለውን ስርአት በህዝቡ ላይ ጫኑበት። እነ አባ ግርማ ካቀረቡት የመተዳደሪያ ቃለ ዓዋዲ ማሻሻያ ሃሳብ ቀጥሎ ይገኛል።
አንቀጽ 40(39)

ቁጥር 1

የቤተ/ክኑ አስተዳዳሪ የሚከተሉት መመዘኛዎች የሚያሟላ ይሆናል።

የርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ካቴድራል በአውሮጳ ቀደምትና መንበረ ሊቀ ጵጵስና ሆና ከመቆየቷ አንጻር የደብሩ አስተዳዳሪ ፦

ሀ/ ገዳማዊና ሥርዓተ ምንኩስናን የተቀበለ
ለ/ የላቀ ማዕርገ ክህነት ያለው

አባ ግርማ ይህን ደፍረው ሲናገሩ ከምእመናኑ ይልቅ “የላቀ ማእረገ ክህነት ያለው” ሲሉ የክህነትን ትልቅና ትንሽ ይንገሩን ብለው መጠየቅ የነበረባቸው በህግ ተወስነው በማገልገላይ የተሰለፉ ካህናት መሆን ነበረባቸው።እኛ መአስባን እንጅ መነኮሳት አይደለንም። ቦታውም የቀለጠ ከተማ እንጅ ለገዳም ምቹ አይደለም ስርአተ ገዳሙም አይፈቅድም። ገዳም ለማህበረ መነኮሳት ነው፤ ገዳማዊና ሥርዓተ ምንኩስናን የተቀበለ የሚሉት ለምንድነው? ብለው በምእመናኑ ፊት ቢጠይቋቸው ኑሮ፤ በሚሰጡት መልስ በተለያየ መስክ አዕምሯቸውን ያበለጸጉ ክርስቲያኖች የሚያሸንፉበትን ትጥቅ በመስጠት እዚህ ከመድረሱ በፊት ችግሩ በተቀጨ ነበር። ካህናቱ በህዝብ ፊት አፋጠው መጠየቅ ነበረባቸው።
ማህበረ ምእመናኑ በክህነት ትልቅነትና ትንሽነት ያለውን ሙግት ባካባቢው ላሉት ካህናት ትቶ፤ በታሪክ የሚታወቀውን በዓለም አቀፋዊነት ባህርዩ የሚንጸባረቀውን theocracy የሚለውን መርሆ ላለመቀበል፤ እውቀቱን እየተጠቀመ ሃላፊነቱን ለመወጣት ወስኖ በህብረት መንቀሳቀሱ የሚያስገርም ነው። ህዝቡ  በተሰማራበት የእውቀት መስክ ስለ theocracy ምንንተ የደረሰበት  ግንዛቤ የቀደሙ ሊቃውንት አባቶቻችን ከሰሩልን መመሪያ ጋራ መስማማቱ እጅግ የሚያስገርም ነው። የመማር ትርጉምም ይህ ነው።
theocracy የሚለውን መርሆ በንጽጽር ነገረ መለኮት ጥናት እንደተረዳነው፤ ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን እነ አባ ግርማ ይዘው የተነሱትን የእስልምና ነገረ መለኮት ሊቃውንት “When the Koran and the Islamic tradition mention wholesome deeds, what is meant activity that represents obedience to God’s command. The primary wholesome deeds are the Five Pillars, but every sort of good deeds is included in the category, that is, all those deeds that the Shariah recognizes as good. In addition the authorities of the second and third dimensions of Islam often broaden the term to include a wider definition of good.” The Vision of Islam pp27) ሉ ገልጸውታል። ሻለቃ ማሞ ለማ ስለዚህ ጉዳይ  አንስተው ሲናገሩ በቪዲዮ በተዘጋጀው ውይታቸው እንዳየነው “በለንደን ከታማ ያሉ ኢትዮጵያውያን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አካላት፤ ይህችን ለንደን ላይ የመሰረትናትን ቤተ ክርስቲያን መምራትና ማስተዳደር ይቅርና ዓለምን መምራት የሚችል እውቀት የተሞሉ ናቸው ላሉት ከላይ የጠቀስኩትን አብራርተው እንዲነጋገሩበት ለነሱ እተወዋለሁ።
እነ አባ ግርማ  theocracy በሚሉት መርሆ እንስማማ ቢባል እንኳ እራሳቸው መውጫ ወደ ሌለው አዘቅት እየገቡ ናቸው። እንኳን እነሱ ከእግዚአብሄር ጋራ ቃል በቃል የተነጋገረው ሙሴም ሊሸከመው አልቻለውም። ሐዋርያትም አልቻሉትም። ይህ መመሪያ በዘመናችን አለ የሚባለው በስልምና እምነት በሚኖሩት ሰዎች ነው። ለእነሱም ይህ መመሪያ “The Five Pillares are the basic practice of Islam.” እንዲል የእስልምና ሃይማኖት አዕማድ ከሚባሉት መሰረታውያን መመሪያወቹ ጋራ በመቆላለፉ ዘመኑን ዋጅቶ ለማለፍ አቅቶት እየተንገዳገደ  ነው።  “The Shariah sets down rules  for right activity. These are God’s rules as specified in the Koran and explained by the Prophet.) The Vision of Islam chapter 1 pp 9-25)  ተመልከቱ።
ወደ ክርስትና ስንሻገር ደግሞ በዚህ መሳይ መመሪያ ስትመራ የኖረችው በ1854 የ immaculation conception ነገረ ማርያም ያወጀችው አከታትላም የአይገሰስ ጵጵስናን ህግ አዋጅ ያስከተለችው  የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያ ናት። ይህንኑ ነገረ ማርያም ከንሳስ ላይ ያወጁት አባ ማትያስ በመንበሩ ላይ ከተቀመጡ አመት ሳይሞላቸው አባ ግርማ በተባሉት መነኩሴ አማካይነት በአባ ማትያስ ደቀ መዛብርቶች በነ አባ ገብርኤል ለንደን ላይ እንዲታወጅ መደረጉ እጅግ የሚያስገርም ነው።
ለንደ ላይ የተፈጸመው ደባ፤ሻለቃ ማሞ እንዳለቱ  በለንደን የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ምሁራን የሚበዙበት ከሆነ እራሱ ያፈራውን ንብረት ይቅርና እነ አቡነ ቀውስጦስ  ማስፈራሪያ ወደ አደረጉት ነገረ መለኮት ቀኖና እና ሞራል ተሻግሮ እናንተ እነማናችሁ እንዲል ያስገደዱት ይመስላል። የኢትዮጵያን ህዝብ ማሸነፍ የሚቻለው በፍቅርና በትህትና እንጅ በንቀትና በሸፍጥ ከሆነ ታናሽነቱን ወደ ታላቅነት ይለውጠዋል። አባ ግርማ ሩቅ ረዥም ጥልቅና ምጡቅ የሆነውን ኢትዮጵያዊነት ሁለንተና መገንዘብ ቢያቅታቸው፤
 “ታናሽ ነው ይሉታል እጅጉ ዘለቀን፤
ከበላይ እኩል ነው እሱም የከፋው ቀን”

ብሎ ህዝባችን የሚያንጎራጉረውን ማስታወስ በተገባቸው ነበር።በነ አባ ማትያስ የሚካሄደው ደባ “አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ አዋጣ” እንደሚባለው ለንደን ላይ የሚኖረውን ህዝብ ወደ ቀኖና፤ ነገረ መለኮትና ሞራል ተሻግሮ ኧረ ለመሆኑ እናንተ እነማናችሁ? ብሎ እንዲጠይቃቸው እየገፉት ነው።
እነ አቡነ ቀውስጦስ እውነት የቤተ ክርስቲያናችን ልኡካን ቢሆኑ ኖሮ  “ኢያከብድ ቃልየ ላዕሌክሙ ተአክሎ ለዘከመዝ ዛቲ ተግሳጽ እንተ ረከበቶ እምቡዙሐን። ወዓዲ ይደሉ ከመ ትስረዩ  ሎቱ ወታስተፍስህዎ(፪ኛ ቆሮ ፪፡፮) ሲል ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን መርሆ በመከተል የምእመናኑን ታዛቢነት አስወግዶ ባቋራጭ ለመክበር አስቦ የTheocrasyን መርሆ መመሪያው  በማድረግ ብዙሀኑን የበጠበጠውን ግለ ሰብ ይቅርታ እንዲጠይቅና ህዝቡ ይቅርታ አድርጎ እንዲቀበለው ማድረግ ነበረባቸው። ይህን ከማድረግ ይልቅ ከግለ ሰቡ የተቀበሉትን ስህተት በህዝቡ ላይ ጭነው መሄዳቸው  ህዝቡን ተቋቁሞ በሚያሸንፍበት መስመር ላይ አሰልፈውታል። አባ ግርማን ግን እጅግ ጎድተዋል። 
 ይህ ክፉ ዘመን አልፎ በመልካም ዘመን ሲተካ ይህን ችግር ከፈጠሩት ከአባ ግርማ ይልቅ ጥርሳቸውን ነክሰው ደማቸውን አፍልተው አይናቸውን አፍጥጠው በዓለማዊው ህግ በመመካት በህዝብ ክርስቲያኑ ላይ ፎክረው የተናገሩት ጳጳስ ናቸው። በዚህ ንግግራቸው በለንደን የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ባላሉትና ባላሰቡት ነገር እልክ ውስጥ በመክተት ሲኖዶስ ከሚሉትና ቅዱስ ፓትርያርክ ከሚሏቸው ከአባ ማትያስ ጋራ ቅራኔ ውስጥ እንዲገባ አስገድደውታል። ይህም ብቻ አይደለም “ወኢይሤኒ ይሰየም ህዝባዊ ዘእንበለ  እምድኅረ ዐጸባ ወእምድህረ  አቀመ ላዕለ ነፍሱ ዐቂበ ቀኖናት ቅዱሳት”(ፍ አ ፭፡፹፱)  ወደ ሚለው ቀኖናችን እንዲሻገር አርገውታል። ይህም ማለት፦ዘመኑ ምንኩስና የረከሰበት፤ ተምሮ ተወዳድሮ መኖር ያቃተው ሰነፍ ጎረምሳ ባቋራጭ ዘርፎ ለመክበር መነኩሴ ነኝ እያለ ከመጣ፤ ጳጳስ ሁሉ ቀጣፊ ከሆነ ህዝቡ እውነተኛውን ታማኙን ከመካከሉ ሊሰይም ይችላል”። 
 “ወኢይኩን ገብረ ለአሐዱሂ እምሰብዕ እስመ  እግዚአብሔር ዘወሀቦሙ ግእዛነ ኢይደሉ ከመ ይመንንዋ ለግእዛኖሙ”( ፍ አ ፱፡ ፫፻፩) ማለትም፦ ክርስቲያኖች እግዚአብሄር የሰጣቸውን ነጻነት በማንም ማስረገጥ የለባቸውም” ብላ ቤተ ክርስቲያናችን የምታስተምረውን ሰውረው  ህዝቡን በማፍዘዝ ላይ ያሉትን ጳጳሳት መነኮሳት  እና የሰንበት አስተማሪዎችን አወቅንባችሁ ብሎ በቁጣ እንዲነሳ አድርገውታል።
  ከቀኖናችን፤ ከነገረ መለኮቱ እና ከታሪካችን ውጭ በነ አባ ማትያስ ግፊት  የሚንቀሳቀሱትን  ሁሉ የሚፈጽሙትን የጥፋትና የማበጣበጥ ተልእኮ  ለማስቆምና ጨርሶም ከቤተ ክርስቲያናችን ለማስወገድ ኀላፊነቱ የለንደን ህዝበ ክርስቲያን  ብቻ መሆን የለበትም። ቅዱስ ሲኖዶሳችን ከነ ስብሀት ነጋ ተላቆ ለነገረ መለኮቱ ለህዝብ እና ለአገር በሚቆሙ ተገቢ ሰዎች እስኪተካ ድረስ፤ በየቦታው በተመሳሳይ ችግር የተፈተነውና ወደፊትም በመፈተን ላይ ያለው ሁሉ ህዝበ ክርስቲያን  ተባብሮ  የመቆም ምሳሌ ይሆነን ዘንድ በአባ ካሳ መፈክርና እንጉርጉሮ ይህችን ጦማር እደመድማለሁ።



ክፍል ስምንት

የአባ ካሣ እንጉርጉሮ


በተወለድኩበት ደብር አባ ካሣ የሚባሉ አባት ነበሩ። እኒህ አባት ያልተማረ ዲያቆን ያልተማረ ቄስ የክርስቲያኖች ነቀርሳ ነው ማለት ልማዳቸው ነው። ጥሩ ድምጽ ያለው ዲያቆን የቅዳሴውን ዜማ ብቻ ከድምጹ ጋራ አስታርቆ ይቀድሳል። የሚያዜመውን አያውቀውም ዳዊት መድገምም መልእክታት ማንበብም አይችልም። ከእለታት አንድ ቀን አባ ካሣ “ካልረሳሀው ዲቁናውን የሰጡህ አቡን ተማር ሳይሉህ አይቀሩም፡ ለምን ዘነጋሀት? ትዝ ይበልህ” ብለው በሰው ፊት በመናገር አሳፈሩት። ምክራቸውን ተቀብሎ ከመማር ይልቅ፤ በምክራቸው ተቀይሞ አቅሙ በሚፈቅድለት መንገድ ሊጎዳቸው አሰበ። አባ ካሳ በመቃብር ቤት ስለሚኖሩ የሰበካው ህዝብ ሲደገስ መጀመሪያ የሚታሰቡት እሳቸው ናቸው። ደጋሾች ከድግሱ ምግብ በአገልግል አርገው ይልኩላቸዋል። ከእለታት አንድ ቀን አባ ካሣ“አቡኑ ተማር ያሉህን አትርሳ” ያሉት ዲያቆን  በአገልግል አሸዋ ሞልቶ ከድግስ ቦታ በምግብ የተሞላ አስመስሎ አቀረበላቸው። ከፍተው ሲያዩት አሸዋ ሆኖ አገኙት። በጣም ተበሳጭተው ደብሩን ጥሎ መሄድን ተመኙና የሚቀጥለውን አቅራርተው ፎከሩ።
“አባ በዝብዝ ካሣ ገፍ የተጫነህ 
አባይን መሻገር ከፈራ ልብህ
የብቸና ውርጋጥ ይጫወትብህ”

አባ ካሳ “ተማር” ብለው ለዲያቆኑ የሰጡት ምክር እና Commander Aseffa ለአባ ግርማ “በመነኮሱ ጊዜ የገቧቸውን ቃላት በጥልቅ ያስታውሱ። እርሰዎም ጳጳስም ንጉሥም አንድ ሰው ነው። ህሊናወን ይመርምሩ! ብለው የመከሯቸው ምክር፤ ዮቶር ለሙሴ ከለገሰው ምክር ጋራ ይመሳሰላል። አባ ግርማ እንደ ሙሴ ተግሳጹንና ምክሩን ተቀብለው ከላይ የተገለጸውን የቤተ ክርስቲያናችንን ያስተዳደር መርሆ ተምረው ቲወክራሲ የሚሉትን መርሆ የኛ አለመሆኑን ተረድተው፤ በቀለጠው ከተማ ባለችው ደብር ላይ የጫኑትን ገዳማዊ የቁምስና አስተዳደር  ትተው አስተዳደሩን በእድሜና በችሎታ ለሚልቃቸው በህግ ተወሰኖ ለሚያገለግል ካህን ቢለቁ ዘላቂ ክብራቸውን ባተረፉ ነበር።
ነገር ግን  የሙሴ መንፈስ በውስጣቸው ባለመኖቱ የCommander Aseffa ምክር አባ ግርማን አባስጭቶ በቀለጠው በለንደን ከተማ የሚኖረው ህዝብ ለራሱ በመሰረተው ቤተ ክርስቲያን ገብተው የቁምስና አስተዳደር  ጫኑበት። ከዚያም ርቀው ንብረቱም የኔ ነው አይመለከትህም ብለውት አረፉ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምእመናን ሆይ! ከእለት ጉርስህ እና ከልጆችህ አፍ እየተሻማህ ለቤተ ክርስቲያን የምታቀርበው መባ በተገቢ ቦታ እንዲውል ማድርግ የሚቻለው የዘመኑ ሲኖዶስ ምን አለ? ጳጳስ እገሌስ ምን አለ? መላከ እገሌስ ምን አለ? ቆሞስ እገሌስ ምን አለ? ከማለ ወጥታሁ፤ በእግዚአብሄር ቃል መሰረት ላይ ሊቃውንት አበው ጽፈው ደጉሰው ባስረከቡን ነገረ መለኮት ቀኖና ታሪክና ትውፊት ተረድተን አጥርና ሚዛን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው።
ባለንበት ዘመን የገጠመን ችግር አቶ ስብሀት ነጋና ገብረ ኪዳን ደስታ ጫካ ላይ ሳሉ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የዘረጉት የጥፋት እቅድ ብቻ አይደለም። ህዝበ ክርስቲያኑ ሊያውቀውና ሊረዳው የሚገባውን ሥርአተ ገዳም፤ ስርአተ ደብር፤ ስርአተ ምንኩስና፤ እና ቁምስና የሚለውን ከመረዳት ይልቅ፤  “እኔ ምን አገባኝ የካህን ስራ ነው” እያለ ሁሉንም እርግፍ አርጎ ለካህናቱ በመልቀቁ ነው።የክህነትን ተልእኮ ወደ ንግድ ሥራ በተለወጠበት ዘመን ይቅርና አምላክ ባነጋገራቸው በእነ ሙሴና በሐዋርያት ዘመን እንኳ የነዋየ ቅድሳት አስተዳደር ለካህናት አልተለቀቀም። ስራው በሚገባ እንዲከናወን የቆሳቁሱ አገልግሎት ለምእመናን ቢለቀቅም፤ በካህናት በኩል የሚካሄደው መንፈሳዊ አገልግሎት ቢጓደልና ካህናት ማካሄድ ካቃታቸው ምእመናኑ ሊገቡባት ይገባል።
ለምሳሌ፦ እስጢፋኖስ የተመረጠው በምእመናን ለምእመናን ቆሳቁስን ለተመለከተ ማእድ ለተባለው ነገር ነው። ይሁን እንጅ እስጢፋኖስ የተገደለው ለተሰየመለት ቆሳቁስ አይደለም። በወቅቱ ለነገረ መለኮቱ የሚቆም ባለመኖሩ በነገረ መለኮት ራሱን በማሰለፉ ነው። “ወኢይሤኒ ይሰየም ህዝባዊ ዘእንበለ  እምድኅረ ዐጸባ ወእምድህረ  አቀመ ላዕለ ነፍሱ ዐቂበ ቀኖናት ቅዱሳት”(ፍ አ ፭፡፹፱) መመሪያችን  የጵጵስና ተልእኮ በትዳር ባልታሰረ ሰው እንዲከናወን የታዘዘው ልጄ ቤቴ በሚል ስሜት አገልግሎቱ እንዳይጎዳ እንጅ ምንኩስና ከጋብቻ የበለጠ ቅዱስ በመሆኑ አይደለም።
ምንኩስና ገዳማዊ ሕይወቱን ለቆ  ዓላማውን ስቶ በዓለም ውስጥ ተሰማርቶ በመኖር በንብረት በገንዘብ በሥጋዊ ጥቅም ከህዝብ ጋራ ግጭትና ክስ ውስጥ ከገባ በትዳር ላይ ካሉት ከ(መአስባን)  ህዝቡ በታማኝነቱ በምሳሌ ነቱ ይጠቅመናል ብሎ ያመነውን መርጦ ማስቀመጥ እንደሚችል ይጠቁማል።
 በታሪካችን በቤተ ክርስቲያኑ መቅደስ እሳት ተነስቶ ጽላቱን የሚያተርፍ ካህን ከጠፋ፤ እሳቱ ያቃጥለናል ሳይሉ ወይምየካህን ስራ ነውም ሳይሉ ከቤተ መቅደስ በመግባት ጽላት ከመቃጠል ያተረፉ ምእመናን አሉ። ህዝበ ክርስቲያንን ይህን የመሰለ ፈተና ሲገጥመው ቆሞ  ከመልከት ይልቅ ቤተ ክርስቲያንን ለማዳን መሞከር በኦርት እና በክርስቶስ ትምህርት የተደገፈ ነው።
ዳዊትና ከርሱ ጋራ የነበሩት ሰዎች ወደ ቤተ መቅደስ መግባትና ተረፈ መስዋእት መብላት የማይገባቸውን ባደረጉ ጊዜ  ስህተት ሆኖ እንዳልተ ቆጠረባቸው። ምእመናንም ያልተጠበቀ ግዳጅ ቢገጥማቸው ያንግዳጅ ከካህናቱ የሚሸፍን ቢያጡ፤ ካህናቱ ሊያደርጉት የሚገባቸውን ምእመናን ቢያደርግ ስህተት ሆኖ አይቆጠርባቸውም ” (ማቴ፲፪፡፪ -፭) በሚለው በክርስቶስ ቃል ሊቃውንት ያስማሙታል።
ከላይ በኦሪት ዘመን ሙሴ ታላቁን ስራ ሃላፊነት ወስዶ ቀላሉን ለህዝብ እንደተዎ እና ሐዋርያትም መልእክተ ቃሉን ወስደው የምእድ አገልግሎቱን ለምእመናን እንደተው አይተናል። አሁን እንደምንመለከተው ከሆነ ካህናቱ ይህን ምሳሌ ለቀው ንብረት ውስጥ ገብተዋል። የካህናት ተልእኮ ለነገረ መለኮት ለሞራል ለታሪክ ለህዝብ ለአገር መስዋዕት የሚጠይቀውን ስራቸውን ለቀው ለማእድ ለምግብ ለገንዘብ አስተዳደር ተሰልፈዋል። ህዝቡ እንደ አባ ካሣ በሁሉም እየተጎዳ ነው። አባ ካሣ ምግብ ከመነፈጋቸው ባሻገር ድንጋይ እንዲሸከሙ እንደተደረጉ፤ ህዝቡም ለሞራል ለእምነት ለህይወት ምሳሌ የሚሆን ከማጣቱ ባሻገር ስርአተ ቁምስንና ተሸከመ። በመነኮሳት ንብረቱን ተዘረፈ፤ ተከሶ በአደባባይ ቆመ ።ይህም የነ አቶ ስብሀት ነጋ ፓትርያርክ ዲሲ ላይ የፈጸሙት ቤተክርስቲያናችን የምታወግዘው መጥፎ  ምሳሌ ነው። አባ ማትያስ በዚህ ጦማር የተገለጹት ከሆኑና ሌላ ማትያስ ካልሆኑ “እንዲህ ያለ ፓትርያርክ አይተን አናውቅም” ብንል ተገቢ ነው።  
ይህን ምስክርነት ለመስጠት እችል ዘንድ ከአባ ማትያስ ጋራ ምን እንዳገናኘን በማቀርባት ጦማር እንገናኝ።
ይቆየን

ለሌሎች ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ጦማሮች የሚከተለዉን ድህረ-ገጽ ይመልከቱ:: http://www.medhanialemeotcks.org/

No comments:

Post a Comment