Friday, 19 December 2014

ድንቄም ጠቅላይ ሚኒሴቴር!

ድንቄም ጠቅላይ ሚኒሴቴር!

ወንድሙ መኰንን፣ ከብሪታኒያ 19 December 2014

ብዙ ተብሏል። እኔም አንድ ነገር ልጨምርና ልገላገለው። “የጊዮርጊስን መገበሪያ የበላ ሲለፈልፍ ይኖራል” ነው የሚባለው? ተናግሮ ከሚያናግር ይሰውራችሁ! ውሀን ምን ነበር የሚያናግረው? ድንጋይ! የሰውም ድንጋይ እራስ አለ! ይቅርታ አንጀቴ አርሮ ነው!

ሦስት መንግስታትን የማየት ዕድል አጋጥሞኛል። ተወልጄ፣ አድጌ፣ ተምሬ ለዩኒበርሲቲ የበቃኹት በንጉሠ ነገሥቱ ዘመነ መንግሥት ነበር። ዕውነቱን እንናገር ከተባለ፣ ንጉሡ ሲናገሩም ሆነ ሲራመዱ፣ የርዕሰ ብሔርነት ግርማ ሞገስ ነበራቸው። “በንጉሥ መገዛቱ ጊዜ ያለፈበት፣ ያረጀ ያፈጀ፣ ገበሬውን በገባርነት ጠፍንጎ የያዘ፣ አገሪቱ በዕድገት ወደፊት እንዳትራመድ ያገዳት፣ ኋላ ቀር የፊውዳል ሥርዓት ነውና ወደሶሻሊዝም እንለውጣት” የሚሉ ድምጾች ከተማረው ክፍል አካባቢ እያየሉ መጡና እኛንም እንደጎርፍ ይዘውን ነጎዱ። ተከተልናቸው። “መሬት ለአራሹ እያልን” ተማሪዎች በጠበጥን። እንዳጋጣሚ ሆኖ በ፲፱፷፮ ዓ/ም የጠና ረሀብ በወሎ በመከሰቱ ሕዝብ በረሀብ እየረገፈ ፹ ዓመታቸውን “ድል” ባለ ድግስ አከበሩ የሚል በተማሪዎች የተጀመረው ርብሻ በመምሕራን (ሴክተር ርቬው)፣ በታክሲዎች እና በሠራተኞች ሥራ ማቆም አድማ ተቀጣጥሎ ለወታደሩ “መንግሥት የመገልበጥ” እድል ተፈተለት። የሥርዓቱ ጠባቂ የነበረው የወታደሩ ክፍል አመጸና የንጉሡን መንግሥት አፈረሰው። አዝጋሚ ዕድገት ላይ የነበረች ኢትዮጵያ የባሰውኑ በወታደራዊ ደርግ ተጠፈነገችና ወደ ኋ ተወረወረች። የንጉሡ ሥርዓት በአምባገነን ወታደሮች ተካ፣ ሶስት መኰንኖች ተፈራረቁባት። ርዕሰ ብሔርነቱም መጀመሪያ ለጥቂት ወራትም ቢሆን (ከመስከረም እስከ ኅዳር ፲፱፻፷፯) ሌፍትናንት ጀኔራል አማን አንዶም፣ ቀጥሎም ትንሽ ውረድ ብሎ ለጥቂት ዓመታት (ከኅዳር ፲፱፻፮፯ - ጥር ፲፱፷፱) ብርጋዴር ጄኔራል ተፈሪ በንቲ፣ ቀጥሎ በጣም ወርዶ-ወርዶ፣ ለብዙ ዓመታት (ጥር ፲፱፻፷፱ - ግንቦት ፲፱፻፹፫) ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም (በኋላ ኮሎኔል) በመጨራረስ ተተካኩ። ሲምሩ በሰደፍ፣ ከፈለጉም በእሥራት፣ ከጨከኑም በጥይት ሕዝቡን በጅምላ እየረሸኑ፣ ለአሥራ ሰባት ዓመታት በወታደር ፌሮ ጭንቅላታችን ላይ ቁመው ወታደሮቹና ጀሌዎቻቸው ቀጠቀጡን።  ግድያው እሥራቱ ያደነዘዘው ሕዝብ፣ “የባሰ አይመጣም” በማለት፣ ገንጣይ አስገንጣይ ዘረኞች ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግሱ፣ ዝም ብሎ አያው። እንዲያውም አንዳንዱ መንገድ እየመራ ወደ አዲስ አበባ አደረሳቸው። ይኸውና በወያኔ የሚመራው የዘረኞች ቡድን ከዚያች ከተረገመች ከግንቦት ፳ ቀን ፲፱፻፹፫ ዓ/ም ጀምሮ፣ ያላንዳች ርኅራሔ፣ ቀጥቅጦ እየገዛን ነው። ያም ብቻ አይደለም። መሬታችንን እየሸነሸነ፣ ነዋሪውን እየፈነቀለ በርካሽ እየቸበቸበው ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ንጉሡ ለደርግ ከአስረከቧት እጅግ አንሳ ትገኛለች። መሪዎቹም፣ ከበፊተኞችም እጅግ ወርደው የወረዱ ቀትረ ቀላሎች ሆኖብን። መጀመሪያ መለስ ዜናዊ ለሀያ አንድ ዓመታት (ከግንቦት ፳ ቀን ፲፱፻፹፫ - ከግንቦት ፳ ቀን ፳፻፬)፣ ፏልለውብን ሞት ገላገለን። መለስ ዜናዊን የተኩት ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ድቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር ናቸው


እንግዲህ እኔ እስካሁን የኖርኩት ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እስከ ኃይለማርያም ደሳለኝ መሆኑን ተገንዘቡልኝ። ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በ፲፱፻፳፰ ዓ/ም በሊግ ኦፍ ኔሺን ላይ ያደረጉትን[i] ንግግር፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ፣ ሰኔ ፳፪ ቀን ፲፱፻፺፱ ዓ/ም ካደረጉት አሳፋሪ ንግግር[ii] እና የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ሰሞኑን የስልጤ ዞን ዋና ከተማ፣ ወራቤ የተመሠረተችበትን አሥረኛ ዓመት ለማክበር ተግኝተው ከተናገሩት አሳፋሪ ንግግር[iii] ብናወዳድር፣ “እንዴት ወርደን እዚህ ደረሰን” ያስብላል

መለስ ዜናዊ ለሰው ስሜት የማይጨነቁ፣ በአራዳ አነጋገር ሁሉንም የሚዘረጥጡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ስቃይ ነበሩ። ሙት ወቃሽ ላለመባል፣ ያሉትን አስነዋሪ አባባሎች “ሾላ ብድፍን” ብለን እናልፈዋለን። አሽቃባጮችም ነበሯቸው። ብልግና በተናገሩ ቁጥር፣ መላው የፓርላማ አባላቸው፣ የሚያቅለሸልሽ ታሪክ እንኳን ቢሆን፣ ከት ብሎ የሚስቅላቸው ቷቸው ነበር። እሳቸውን የተኩት ጉድ እንደሳቸው መሆን ቢያምራቸውም፣ የተለዩ ፍጡር ናቸው። ወላጆቻቸው፣ “ኃይለ ማርያም”ብለው ስም ሲያወጡላቸው፣ ለመሆኑ ምን ታይቶአቸው ነው? በዚህ ስማቸው መጨረሻ ላይ እደምደማለሁ መልካም ንባብ

ኃይለማርያም፣ ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሳይሆኑ፣ የወያኔ ባለአደራ ሁነው የጠቅላይ ሚኒስቴርነቱ ቦታ ጠባቂ ናቸው። አልጋ ጠባቂ እንበል?! አልመሆናቸውን ገና በጠዋቱ፣ የሟቹ የመለስ ሚስት፣ ደፋሯ አዜብ ጎላ (መስፍን) አስመስክራለች። “የምኒልክን ቤተ መንግሥት አልለቅለትም” ብላ ጎዳና ተዳዳሪ ልታደርጋቸው ምንም አልቀራትም ነበር። ደንቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር!

ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የራሳቸው ሰው ባለመሆናቸው፣ የወያኔ መሣሪያ መሆናቸውን ለማስመስከር፣ አራዳው መለስ የተናገሩትን አነጋገር ቃል በቃል፣ አንዲት ቃል ሳይጨምሩ - ሳይቀንሱ፣ እንደበቀቀን ሲደግሙት ተሰምተዋል። የእነ አቤ ቶኪቻው መሳቂያ መሳለቂያም ሁነዋል። ከኦሪጂናሌው መለስ ላለማነስ፣ ብዙ ነውሮችን ካፋቸው ዘርግፈዋል። አዪዪ! ምናለ በተማሩት የውሀ ማጣራት ሙያ ቢሰማሩ ኑሮ! ከሰውም ሞገስን፣ ከእግዚአብሔርም በረከቱን ባገኙ ነበር። ለጠማው ንጹሕ ውሀ ማቅረብ በሰማይም ባጸደቃቸው በምድርም ባስከበራቸው!
ያለቦታው ገብቶ፣ ያለ ሰገባው
አሳዛኙ ልቤ፣ የተንገላታው

ነበር ያለው አፍቃሪ! ያለቦታቸው ገብተው፣ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ አገር የመምራቱን ኃላፊነት አምቦጫረቁት የቢቢስን እና የሲኤንኤንን ገዜጠኞች በሽብርተኝነት ሊያስሯቸው እንደሚችሉ አስፈራርተዋል። አራዳ ሳይሆኑ፣ እንደመለስ ጮጋ ለመሆን የሚያደርጉት መፍጨርጨር የመጨረሻው ፋራ መሆናቸውን፣ አጋልጦባቸዋል። አይ የኛ ነገር። ወርደን ወርደን እዚህ ደረስን? እንዲያው ኢትዮጵያውያን ፈጣሪን ምን ያኽል ብንበድለው ነው፣ ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ ጉዶች አሳልፎ የሰጠን? ነገራችን ሁሉ፣ከድጡ ወደ ማጡሆኖብናል። ሕዝባችን መገድሉ፣ መታሰሩ፣ መሰደዱ፣ መራቡ፣ መጠማቱ፣ መታረዙ ሳያንስ፣ እነዚህ መዥገሮች በየቀኑ እየተነሱ የሚመርጉበት ስድብ፣ የባሰ የሚያስመርር ደረጃ ላይ አድርሶታል።ጠቅላይ ሚኒስቴርኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ድንቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር!

የታኅሣሥ ፪ቱን (11 December 2014) ኢሳት ሬዲዮ ፕሮግራም እንደኔ ያደመጠ ሁሉ መቼም ሆዱ በንዴት ድብን እንደሚልበት አልጠራጠርም። ጨጓራ የሚልጥ የአልሰርን በሽታ ያስንቃል። ከአንደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቀርቶ፣ አንድ እራሱን ከሚያከብር፣ አባትና የቤተሰብ ኃላፊ ነኝ የሚል ሰው፣ እንዲህ የወረደ ንግግር አያደርግም። ምን አለ አሁን እንዲህ ዓይነት ቅሌት ቢቀርባቸው? ዲያ! ዲያል ወዲያ! ምን ዓይነቱ ለዛው ሙጥጥ ናቸው? እኔ ስለሳቸው አፈርኩ። ሰውዬው ያልበላቸውን ነበር የሚያኩት። ወራቤ፣ የስልጤዋ ዋና ከተማ፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር መስለዋት አሥረኛ ዓመቷን ልታከበር፣ የወያኔ ባላደራውን ጠርታ፣ መከበሯ ቀርቶ ተዋረደች። ጠቅላይ ሚኒስቴር ተብዬው፣ እንዲህ ነበር ያሉት፣ ዲንቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር!

፩ኛ፡ አሜሪካ ተሰደው ስለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን

“አንዳንድ ጌዜ አሜሪካን አገር ውስጥ የሆነ መርቸዲስ፣ ማለት፣ መኪና ተደርድሮ ባለበት ፎቶግራፍ ይነሱና ከዚያ በኋላ ወደቤተሰብ ይልኩና፣ ይኼ የኔ መኪና ነው ይላሉ። ማንን እንድሚያታልሉ ግን አይገባም።”

ያጣ ወሬ! እንዴ! ጠቅላይ ሚኒስቴር ተበዬው እኮ በሥፍራው የተገኙት የወራቤን ከተማን አሥረኛ ዓመት ምስረታ ለማክበር ነበር። አሜሪካ የሚኖሩት ስደተኞችናና የወራቤ ከተማ ምን አገናኛቸው? ከተደረደሩት መኪናዎች ጋር ተደግፈው የተነሱትን ፎቶ የት ቁመው ያዩት? ሰውዬ ለምን ያልበላቸው ቦታ ያካሉ? ለመሆኑ፣ አሜርካን ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንቱ የተባሉ ስንት ኢትዮጵያውያን ምሑራን እንዳሉ ያውቁ ይሆን? አሜሪካን ሆስፒታሎች ውስጥ ስንት እውቅ ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች እንዳሉ ማን በነገራቸው። አሜሪካ የምርምር ማዕከላት ውስጥ፣ ናሳ ሳይቀር፣ ስንት ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶች እንዳሉ የሚያስብ ጭንቅላት አላቸው ልበል? ኢትዮጵያን ለማንቋሸሽ እራሳቸው ቆሽሸው አረፉት! ይሁን! ይህ ቀን እኮ ታልፋለች። ማርቸዲስ ለኃይለማርያም ብርቅ ይሆን ይሆናል እንጂ፣ ወጪ አገር ማርቸዲስ ታክሲ ነው። ፈራሪም፣ ሎተስም፣ ቤንትሌይም፣ ሮልስ ሮይም ማለት እኮ አንድ ነገር ነበር። ድንቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር!

፪ኛ፤ በጀርመን ተሰደው ስለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ

“... ለልጆቼ ዶሮ ይዘህ ሂድ አሉኝ። እሺ ብዬ ጀርመን አገር ዶሮ ወጥ ተሸክሜ ሄድኩኝ። ከሄድኩ በኋላ፣ በተሰጠኝ ስልክ ብደውል፣ ብደውል፣ ልጆቹን ማግኘት አቃተኝ። ምንድነው ሲባል፣ ስልኩን ለጓደኞቼ፣ ለጀርመናዊ ለጓደኞቼ አሳየኹዋችወ፣ ኧረ! ይኸማ ሀይም(?) ውስጥ እኮ ነው አሉኝ። ምንድነው ሀይም አልኳቸው። ሰው የሚሰቃይበት እስር ቤት ዓይነት ነገር ነው አሉኝ። ዶሮ ወጡን ይዤ እዚያ ሀይም ሄድኩ። ስደርስ ኮንቴነር ውስጥ ነው ያሉት። እዚያ ዱቄት ይሰጣሉ፣ ዱቄቱን እያቦኩ፣ ዱቄት ብቻ ነው የሚበሉት። እቃውን አስረከብኩላውና፥ “ታዲያ ያ ሁሉ ፎቶግራፍ የላካችሁት፣ ከየት የመጣ ነው?” አልኳቸው። ብዙዎቻችን እናውቃለን፣ ውጭ አገር ሰው እንዴት እንደሚኖር።“

ደግሞ “ጀርምናዊ ጉደኞቼ ይላሉ! አያፍሩም? ለመሆኑ፣ የማን ደፋር እናት ናት፣ እንደተራ ሰው፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒቴራችንን ዶሮ አሸከማ ጀርመን አገር ድረስ የምትልክ? “የማይመስል ወሬ፣ ለሚስትህ አትንገር” ነው የሚባለው? እንዴ! የወራቤ ነዋሪ ላለፉት አሥር ዓመታት ያደረገውን ጉዞ እንዲገመግሙለት እንጂ፣ ጀርመን ውስጥ ስለሚኖ ስደተኛ ወሬ ጠምቶአቸው ነው እንዴ የጋበዟቸው? በነገራችን ላይ፣ ጀርመን አገር አዲስ የመጡት ስደተኞቹ፣ ምናልባት ጉዳያቸው እስከሚጠናቀቅ በዚያ ዓይነት አኗኗር ለጊዜው ይኖሩ ይሆናል፣ ለመሆኑ፣ አዲስ አባባ ስንት የጎዳና ተዳዳሪዎች እንዳሉ የሚያይ አይን ተተክሎላቸው ይሆን?

፫ኛ፣ በአረብ አገር ተሰደው ስለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ

“እኛ እህቶቻችንን ለማየት አቻልንም። ሳውዲ ሂደን፣ ማየት አልቻልንም።... ይኸ የዚያ አካባቢ የሀይማኖትዊ ሥነ ሥርአት ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ሂጄ ማየት ስላልተቻለኝ፣ የፈቀዱልኝስ እንድሄድ ነበር። ለምንድነው፣ ማየት የማይፈቀድልኝ፣ የሀይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ሊሆን ይችል ይሆናል ግን በእዚያ ደግሞ ቦታ ስንሄድ፣ መንገድ ላይ እንደአበደ ውሻ የሚኖሩ እህቶቻችን አየን። ከዚያ ቦታ ስንሄድ፤ በምባሲ በራፍ፣ ወደ ሺ የሚጥጉ፣ አንድ ላይ ተኰልኵለው  በዚያ ሙቀት ውስጥ ኤር ኮንዲሺነር በሌለበት ታጭቀው ሲሰቃዩ አየሁ። ከዚያ በኋል ግን፣ ምን ትዝ ይለኛል፣ ቢያንስ እዚህ ገጠር ውስጥ በእግራቸው ተጉዘው በልተው ጠግበው እኮ ይኖራሉ።

ድንቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር! ወያኔ አገሪቱን መቀመቅ ውስጥ በመጨመሩ፣ ኢኮኖሚዋን ማድቀቁ፣ እና እንደ ኃይለማርያም ደሳለኝ ያሉ አሽከሮቻቸው በልተው በልተው ሆዳቸው ተወጥሮ ሲነፋፋ፣ ቤተሰቦች የሚበላ የሚቀመስ ሲያጡ፣ ወጣት ሴቶቻችን ገና በሎጋ ዕድሜአቸው፣ትምሕርታቸውን አቋርጠው፣ ሴተኛ አዳሪ ከመሆን፣ በጉልበታቸው ሠርተው ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት የሚያደርጉትን መፍጨርጨር፣ ከእብድ ውሾች ቆጥረዋቸው አረፉ? ደግሞ ሰለ አረቦች ግርድና አፋቸውን ሞልተው ተናግረዋል። ለመሆኑ የግርድና ንግዱን የሚያካሄዱት የሕወሀት አባላት መሆናቸውን የሚረዳ ጭንቅልታ ማን ባዋሳቸው! አፋቸው ተበላሽቷል። ታዲያ ምን ያደርጋል! በቅቤ አሽተው አይመልሱት ነገር። ድንቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር!

፬ኛ፣ ድንጋይ ይወረውራሉ ስለሚሏቸው የስልጤ ወጣቶች

“አንድ እኛ እዚህ ግድም የሚያሳዝነን፣ አብዛኛው እዚያ መርካቶ አካባቢ ደንጋይ የሚወረውረው ወጣት የዚህ ዞን ወጣት መሆኑ ነው። በሙስሊምነት ከሆነ፣ ትልቁ ሙስሊም፣ ኦሮሞ ነው፣ ኦሮሚያ ነው። ነገር ግን ድንጋይ የሚወረውረው ግን የሥልጤ ወጣት ነው። ምን ማለት ነው ይኼ? ምን ማለት ነው? አባቶች በተለይ እስቲ ይታያችሁ የናንተ ልጆች ድንጋይ ሲወረውሩ፣ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ መስኮት ሲሰብሩ፣ መኪና ሲሰብሩ፣ እናንተ እዚህ ሁናችሁ ሲታዩ እንዲያው በአጠቃላይ፣ ይኸ ምን ማለት ነው? ይኸ አደብ መግዛት አለበት። ትላንት ከዚህ ሞባይል ገዝቶ፣ መርካቶ የገባ ሰው ድንጋይ እያነሳ ንብረትና ኃብት ማውደም ማለት፣ ይኽ ንቀት ነው። በምንም ምልኩ! ድንጋይ ወርውሮ መስኮት ሰበረና መኪና ከሰበረ በኋላ ሲታሰር ደግሞ በኃይማኖት ምክንያት ታሰርኩ ካለ፣ ድንጋይ የሚያስወረውር ሀይማኖት የለም። እንደዚያ ነገር ድንጋይ የሚያስወረውር ሀይማኖት የለም ...።”

ለዛው ሙጥጥ! ወይ ጉድ! ከክብር እንግዳ ተሳዳቢ እግዚአብሔር ይሰውራችሁ። የሥልጤ ሕዝብ የጋበዛቸው፣ የወራቤን ከተማ መቆርቆር አሥራኛ ዓመት ሲያከብሩ፣ ከጠቅላይ ሚኒስቴራቸው ጋር አብረው በክብር ተደስተው ቀኑን ለማሳለፍ ነበር እንጂ፣ ሊሰደቡ፣ ሊዋረዱ፣ ልጆቻቸው ላይ የሚቃጣውን ማስፈራሪያ ሊያዳምጡ ነበር እንዴ! የስልጤን ሕዝብ አዋረዱት! ምንኛ ሕዝቡ ልቡ ይቁሰል! ድንቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር! 

፭ኛ፣ ስለሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሞቴ

አፋጣኝ የፍርድ ውሳኔ ለምን አይሰጥም ተብሎ የተጥየቁ ግለሰቦችን በተመለከተ በመጀመሪያ ደረጃ እኛ ሰዎቹ የሙስሊሙ ኮሚቴ ተወካዮች ነን ሊሉ ይችላሉ። ይኸ መብታቸው ነው። ማንም አይከለክላቸውም።  ግን መንግሥት ተወካይ ለመሆናቸው ምንም ማስረጃ የለውም። ሙስሊሙን እነሱን እንዴት እንደወከለ አናውቅም። ስለዚህ ስለማናውቅ ጉሕጋዊ ወኪሎች ስለመሆናቸው ማስረጃ የለንም ነው የምንለው። ሕጋዊ ወኪሎች አይደሉም። እነዚህ ግለሰቦች ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው በሀማኖታቸው ምክንያት ወይም ዕምነታቸው ምክንያት ወይም በሚያራምዱበት ዕምነት ምክንያት አይደለም የታሰሩት። የታሠሩት ሀይማኖታቸውን እና እምነታቸውን ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ከማካሄድ አልፈው ሂደው ከምንግሥትና ከሕዝብ ጉዳዮች ላይ ወንጀል በመፈጸማቸው ነው የታሰሩት።

የምን ወንጀል? ሰው ገደሉ? ዕቃ ሰበሩ? በቃ ወያኔ አስተዳዳሪአቸው “ወንጀለኞች” ናቸው ካለ እንደበቀቀን ተከትለው፣ የኛ “ጠቅላይ ሚኒስቴር” ረዱባቸው ማለት ነው? ወያኔ ከሳሽም፣ ምስክርም፣ ዳኛም ነው። አገሪቱን ጠፍንጎ ይዞአል። ምን ዓይነት ጭንቅላት ቢኖራቸው ነው፣ ወያኔ እንዲህ የሚጫወትባቸው? አይ ሆድ! ለሆዱ ያደ አንጎሉ አይሠራም። ይህቺን አጥብቃችሁ ያዙልኝ! ሕግ የሚሠራው ሁሉም ሲገዛለት ነው። ወያኔ ሕግን የሚጠቀመው ሌላውን ጠፍንጎ ለመያዝ ነው። ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ዕውቀታቸው ወሀ ማጣራት ነው አንጂ ሕግ አይደልምና የተማሩት፣ የሕጉን ነገር ባያጨማልቁት ጥሩ ነበር።  ከዚያ አልፈው ተርፈው፣ እስካሁ ፍርድ ያልተሰጠበትንም ምክያት ሲደረድሩ፣ የተከሳሾቹ ጥፋት እንደሆነ ሊነግሩን ከጅሎአቸዋል። ኧረ ምን ከጀላቸው፣ ወጀሏቸው እንጂ! ጥፋተኛ ላለመሆናቸው፣ አራት መቶ ገደማ ምስክሮች በማቅረባቸው፣ ያንን ለማዳመጥ የዘገየ ፍርድ ነው ብለውን አርፍዋል። ድንቁርና አንዳንዴ ጡሩ ነው። ከሒሊና ቀሳ ያድናል።በድፍኑ፣ ወያኔ ወንጀለኛ ነው ብሎ የፈረጀው ሁሉ ወንጀለኛ መሆን ስላለበት፣ እራሱን መከላከል የለበትም ሊሉን ምንም አልቀራቸውም! በቃ! ወያኔ ከእግዚአብሔር በታች ትልቁ አማላካቸው ነው። ድንቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር።

፮ኛ፣ ወላይታን ሕዝብ በጅምላ ሰድቡ

“እኔ የተወለድኩበት ብሔር፣ ብዙ ሰው ነው እዚህ ጋ የሚያሰፋው። ያኛውን ለመምሰል ሲል ነ። ትንሽ ቀላ ካለ፣ ያኛውን እመስላለሁ ለማለት ይኸንን አሰፍቶ፣ እራሱን ለውጦ፣ እራሱን ለመሸ የምንሸቃቀጥበት ነው የኛ ትውልድ።

ኧረ በሕግ አምላክ! እኚህን ሰው አንድ በሉልን! የወላይታ ሕዝብስ እራሱን እንደሸቀጥ አልሸጠም። ይልቁንስ ከኩሩውና ከርህሩሁ የወለይታ ሕብረተሰብ ተፈጥሮ ሒሊናውን ለቁራሽ እንጀራ የሸጠ ማን እንደሆነ እናውቃለን። የሥነ አዕምሮ ሐኪም ጋ የሚወስዳቸው ዘድ የላቸውም? ወያኔ ምን ጭንቅላታቸውን ብታዞራቸው ነው ጃል፣ እራሳቸውን እንዲሰድቡ የለወጠቻቸው? ደግሞ የወላይታን ባላዊ ጠባሳ ለመሸፈን መሰፋትን፣ ከወራቤ አሥረኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ጋር ምን አገናኛቸው? ስድብ ርቦአቸዋል? ስድብ ጠምቶአቸዋል? የእሳቸውን አዕምሮ ነው ወያኔ ግጥም አድርጋ የሰፋችባቸው እንጂ፣ እኔ የማውቀው የወላይታስ ሕዝብ ባሕሉን አክባሪ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ነው። ድንቄም ጠቅላይ ሚኒስቴር!

በመጨረሻ፣ ጠቃላይ ሚኒስትሩ፣ ለምንድነው ዲያስፖራውን የሚጠሉት? ምክንያት አላቸው! በፈረጆቹ አቆጣጠር፣ 2011 ላይ ወያኔ ገንዘብ ከዲያስፖራው ለመለምን ወሰነች። እሳቸው የአሜርካውን ልክ እንዲመሩ ተላኩ። ሁሉም በሄዱበት ተመሳሳይ ዕድል ገጠማቸው። ከሄዱበት ሁሉ ዲያስፖራው ምድረ ወያኔን ባዶ እጃቸውን ስደዳቸው። ለንደን ላይ ለምሳሌ፣ ከኢምፔሪያ ኮሎጅ አሳደናቸው አባረን፣ እምባሲ ከተናቸዋል[iv]፣ አንዲት ሳንቲም ሳይሰበስቡ ተመለሱ። አሜርካ ላይ እንዲሁ አዳራሻቸው ተረሾባቸው፣ ኪሳራ በኪሳራ ሆነው፣ ቤሳ ቤሲትን ሳይሰብበሰቡ ተመለሱ ታዲያ በዚህ የበሸቁት ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ሚያዝያ ፲፭ ቀን ፳፻፫ (23 April 2011) በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ፣ እንዲህ እያሉ ነበር የተሳደቡት!

“ከሁለት ሺ በላይ ሕዝብ በሚሰበሰብበት አካባቢ፣ ከ20 እስከ 150 ሰዎች፣ የተቃውሞ ሰልፍ ቢወጡ፣ ምንም የሚገርም አይደለም። እነሱም፣ የቀደሞ የደርግ ሥርዓት ርዝርዦችና፣ በሽብር ተግባር ላይ የተሰማሩ የአማጺ ቡድኖች አባላት ናቸው። እነዚህ ሰዎች፣ በበርካታ ዓመታት ሲጮሁ ኑረዋል። ኢትዮጵያ ግን ወደፊት እየገሰገሰች ትገኛለች። እነሱ እየጮሁ ይኖራሉ፣ ምናልባትም፣ አርጅተው እስኪሞቱ ድረስ የሚጮሁ ይኖራሉ። ሬሳቸው አገር ቤት ሊቀበር ይመጣል... እኛም እንቀጥላለን። ይልቁንስ፣ በዚህ ታሪካዊ ወቅት እራሳቸውን በእሳት ባያስለበልቡ የሚሻል ይሆናል”።

አርጅተው እስኪሞቱ ድረስ የሚጮሁ ይኖራሉ። ሬሳቸው አገር ቤት ሊቀበር ይመጣል” ነበር ያሉት? ይኸንን የተናገሩት ሚያዚያ ፲፭ ነበር። ከነዚያ ሰላማዊ ሰልፈኞች እስከአሁን ሙቶ ወደ አገር ቤት የተመለሰ ሬሳ የለም። እግዚአብሔር ይመስገን። ዳሩ ግን እንደ ጣዖት የሚያመልኳቸው አሳዳሪ ጌታቸው፣ መለስ ዜናዊ፣ ነሐሴ ፲፭ ቀን 2004 ዓ/ም ብራሴልስ ሆስፒታል ሙተው ወራት ከከረሙ በኋላ ለቀበር፣ አዲስ አበባ ሬሳቸው ገብተውላቸዋል። በእግዚአብሔር የሚያምን ሰው ግፍ አይናገርም። አንዳንዴ እግዚአብሔር ቅርብ ነው። ስሙ የተመሰገነ ይሁን!

ሰውዬው የዞረባቸው ናቸው። ጠቅላላ ሰብዕናቸው፣ ውጥንቅጡ የወጣባቸው የሚናገሩትንም ሆነ የሚያደርጉትን የማያውቁ ጉድ ናቸው። ወይ አያምሩ ወይ አያፍሩ! እንኳን ለጠቅላይ ሚኒስቴርነት፣ የአንድ መስሪያ ቤት ዴፓርትመንት እንኳን ለመምራት ብቃት ያንሳቸዋል። እንኳን ሠርተው፣ ተናግረው ስሜት የማይሰጡ አሳፋሪ ሰው ናቸው። ለወያኔ መሣሪያነት ያበቃቸው ይኸው ቅደመ ሁኔታ ነው።

አንድ ለብዙ ጊዜ አምቄው እስከዛሬ ያቆየሁትን ልበልና ልሰናበታችሁ።

ደንታ-ቢስ ከሀዲ፣ አድር-ባይ ሆድ-አደር
ወገኑን የሸጠ፣ የወያኔ አሽከር፣
ስብዕናውን ገድሎ፣ ከሒሊናው የራቀ
ስሙ ኃይለ-ማርያም፣ እሱ ጸረ-ማርያም፣ የተዘባርቀNo comments:

Post a Comment