Tuesday 11 July 2023

“ኩሽ!” እያላችሁ ምን ያንኮሻኩሻችኋል?

“ኩሽ! እያላችሁ ምን ያንኮሻኩሻችኋል?

ወንድሙ መኰንን
England: 11 July 2023

ሰው ሲበድላችሁ፣ እስቲ አትናደዱ፤
ጠላትን አትጥሉ፣ ክፉን ሰው ውደዱ።
የክፉ ሰው ክፋት፣ ጠቃሚ ነው ትርፉ፤
ያነቃቃችኋል፣ እንዳታንቀላፉ።
የልቦናው ስሜት፣ እየተራቀቀ፣
ሁልጉዜ ወደ ላይ፣ በጣም እየላቀ፤
በሥራ በጥበብ፣ ግሎ ለመነሳት
ቆስቋሽ የፈልጋል፣ የሰው ልጅ እንደ እሳት
                                                                        ከበደ ሚካኤል፣ የዕውቅት ብልጭታ ገጽ 163

1)   1)   መግቢያ

ዳማ የተባለ ዳንግላ ፈረስ፣ ዋርዲት የተባለች ሽቅርቅር በቅሎ ጋር ሜዳ ውስጥ ሣር ሲግጡ ይተዋወቃሉ። መሽቶ ሊለያዩ ሲሉ፣ ዳማ በጣም ስለወደዳት ዋርዲትን “አባትሽ ማናቸው” ብሎ፣ ጠየቃት። ዋርዲት እየተሽኮረመመች፣ “አጎቴ ጥሪኝ የሚባል ፈረስ ነው” ብላ መለሰችለት ይባላል። ፊየል ወዲህ፣ ቅዝምዝም ወዲያ። ምን ለመደበቅ ነው?

ድንቁርና፣ ያጀግናል። ደፋር ያደርጋል። አንድ ሰው ባነበበ፣ በተመራመረ፣ ባወቀ ቁጥር ነው፣ አለማወቁን እየተረዳ ሲመጣ ነው ቁጥብ የሚሆነው። ያልበሰለው ጥራዝ ነጠቅማ፣ ጫፍ ይዞ እንደባዶ ቆርቆሮ ሲንጣጣ ነው የሚውለው። ከሠርቪስ ኮሊጅ ይሁን፣ ወይም ከነጻ ገቢያ ድግሪ እየገዙ፣ ያልበሰሉ የእፍ እፍ ባለ ዶክትሬት ዲግሪዎች፣ ታሪክቱን በጭንቅላቷ እያቆሙ ሲደፏት እያየን፣ አንዳንዴም በዝምታ፣ ካልሆነም በፈገግታ እያሳለፍናቸው ነው። በዝምታችን ምክንያት ምድሪቱ አልበቃ እያለቻቸው ነው። እንደልባቸው ይቀባጥራሉ። ፕሮፌሰሩ ዓይኑን በጨው አጥቦ፣ አንዳችም ሳያመነታ፣ “የመጀመሪያው ሰው ኦሮሞ ይባላል፣ ከውሀ ነበር የወጣው፣ ጾታ አልነበረውም፣ ዋቃ እንዲህ በጎን አይቶት ለሁለት ሰነተጠቀው” [i] እያለ ሲያወጋን ስቀን ወደሌላ መመልከት ግድ ሆነብን። ምንጩ ደሞ የኦሮሞ አፈ-ታሪክ ነው። የትም ተጽፎ የማይገኝ! ይኸው ፕሮፌሰር፣ ለብዙ ሺ ዓመታት በግዕዝ ተጽፎ የተቀመጠውን ታሪክ፣ የደብተራዎች ፈጠራ ነው እያለ ሲያጣጥል ሰምተነዋል። አባቶቻችን ፊደል ቀርጸው፣ ቀለም በጥብጠው፣ ብራና ዳምጠው፣ ጽፈው ያስረከቡን ታሪክ፣ ተረት ሁኖ ከተገኘ፣ በነዚህ የዘረኞች ሊሂቃን ከተጣጣለ፣ የማይመስል አፈ-ታሪክ ዕውነትነት ሲኖረው ይታያችሁ! ወይ አለማፈር!

2)  2)  ሌሎች ምን ይላሉ፣ ስለኢትዮጵያ?

የኢትዮጵያን ታሪክ ብዙ የአውሮፓና የአሜሪካ ተመራማሪዎች ጽፈውታል። ከነዚህም ፐከንሀም (Thomas Francis Dermot Pakenham)፣ ኡላንዶርፍ (Edward Ullendorff) ፣ ክራሚ (Donald Crummey)ሳልቫዶሬ (Matteo Salvadore)፣ ፓንክረስት (Richard Keir Pethick Pankhurst)፣ ፓየዝ (Pedro Páez)፣ ማርኩስ (Harold Marcus) እና ብዙ ሌሎችም የጻፉትን የኛ ዘመናዮች ያጣጥሏቸዋል። “እኛን ኮሎኒ አድርገው ለመግዛት ስለሚፈልጉ፣ ኦሮሞን ዝቅ አድርገውና አንቋሸው ጽፈዋል” ይሉናል። እነ ፓየስ እኮ ያዩትን ነው የጻፉት። ፓይዝ የተባለው ፖርቱጋላዊ፣ የኢትዮጵያ ታርክ (História da Ethiópia) በተባለው በ1622 ዓ.ም በጻፈው መጽሐፉ፣ የኦሮሞ ተዋጊዎችን ጭካኔ በዓይኑ ያየውን መዝግቧል። እና እንዲደብቁላቸው ነው የሚመኙት? ኢትዮጵያን በጣም የሚጠላው ባውም (James Edwin Baum) እንኳን፡ “አረመኔዋ ኢትዮጵያ (Savage Abyssinia) ብሎ በጻፈው ዘረኛ መጽሐፉ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ኦሮሞውንም፣ አማራውንም ቢስድብም፣ ታሪኳን ግን እየመረረውንም ቢሆን እንዳለች እንዲህ ሲል ለማስቀመጥ ተገዷል።

Yemen, the Red Sea province of Arabia, was conquered by the Abyssinians who ruled that turbulent country until 570 A.D. About the year of Mohamet’s birth, they were defeated before Mecca and driven, bag and baggage for ever from the continent of Asia”[ii]

ወደ አማርኛ በቀላሉ ስናቀርበው፤ “አቢሲኒያ፣ የአረቢያ ጠቅላይ ግዛት የነበረችውን የተበጠበጠች፣ የመንን ወራ ከያዘች በኋላ፣ እስክ 570 ዓ.ም ድረስ አስተዳደረቻት። ሞሀመት በተወለደ ዘመን አካባቢ፣ ከመካ በፊት፣ ተሸነፈው፣ ጓዛቸውንና ጉዝጓዛቸው ሰብስበው ተባረሩ” ይለናል። የመን ድረስ ዘልቃ ያስተዳደረች ኃያል አገር መሆኗን መደበቅ አልቻለም።

የኛዎቹ የተማሩ መሀይማን ግን መኖሯንም ክደው ያልሆንቺውን “ኩሽ ነበርች” ይሉናል። ኩሽ እኮ ግብጾች ጥቁሮችን ለመስደብ የተጠቀሙበት ቃል ሆኑን እንኳን አያውቁም። መሀይምነት ጀግና ያደርጋል ያልኳችሁ ለዚህ ነው። ድፍረታቸው የሚገርም ነው። ሊያለያዩን፣ ሊበታትኑን፣ “ኩሽ! ኩሽ! ኩሽ ነን እኛ” ይሉናል። ማነው ኩሽ? “ከአቢሲኒያዎች የተለየን ህዝቦች ነን” እያሉ አንዳንድ በኢትዮጵያ ቆሽታቸው የደበነ ነጮች የጻፉትን አንጠልጥለው፣ ልባቸው ውልቅ እስኪል ድረስ ይንጣጣሉ። በዛ! እነሱስ እሺ ይንኮሻኮሹ፣ ሌሎቹን፣ እንደ ካፋ፣ ወላይታ ጋሞ፣ ሲዳማ፣ የመሳሰሉትን የደቡብ ብሔር ብሔርሰቦችን ምን በወጣቸው? ከጎናቸው ለማሰለፍ? ጅሎች እየመሰሏቸው ብዙ ርቀት ሂደዋል። እነዚህ ሰዎች፣ አንድ ቋሚ የታሪክ አሻራ ጥለው ያለፉት የሚታይ ነገር የላቸውም። የመጀመሪያውም ሀውልት ስለነሱ የተቀረጸው በኢትዮጵያ ጠላት የተጻፈ ልቦለድ ገጸ ባህርይ በአኖሌ ስም ነው። ቢሞቱ ይሻላቸዋል! ሲያሳፍሩ!

በዚያም አልተወሰኑም። ሱማሌውንም፣ አፋሩንም “ኩሽ ናችሁ” ብለው፣ የኢትዮጵያን ፊደላት ሳይሆን፣ ላቲንን፣ እንዲጠቀሙ አስታቅፈዋቸዋል። ወደሰሜኑም ብቅ በለው፣ ቅማንቱን፣ አገውን እና ሸናሻውን፣ ኩሾች ናችሁ እያሉ የአንዳንዱን ግልብ፣ ጭንቅላት አዙረዋል።

የአዋቂዎች ዝምታ፣ መሀይሞች እንደፈነጩበት ሰፊ ቦታ ሰጣቸው። ይፈነጩብናል። የታሪክ ተመራማሪ ኢትዮጵያውያን አፍረው ይሆን ወይም ድፍርት አንሷቸው አይታውቅም ዝምታን መርጠዋል። ንጉሡን ራቁታቸውን መሆናቸውን የሚነግራቸው እብድ ያስፈሊጋል። ግፋ ቢል፣ እብድ ቢባል ነው። ራቁታቸውን ናቸው ብሎ በመሸበት ማደር ይመረጣል! እኔ እሱን መሆን መርጫለሁ።

ከላይ ያለው የደራሲ ከበደ ሚካኤልን ግጥም ያስቀመጥኩላችሁ፣ ዝም ብዬ አይደለም። ይነካኩን ይነካኩንና፣ አንድ ቦታ ላይ ስንደርስ፣ ይበቃናል። እነሱ፣ ለተንኮል ያጣመመቱን ለመቃናት ግድ ይለናል። ለመሆኑ፣ ኩሽ ብለው እንዲህ የሚሟሟቱበት አቶ ኩሽ ሆዬ ማን ነበር? እስቲ በሚቀጥለው እንይ።

3)3)  ትክክለኛው የኩሽ ታሪክ

ነገር ከሥሩ፣ ውሀ ከጥሩ ይባል የለ?  እስቲ ወደ መሠሩቱ እንሂድ። መሠረቱ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በከፊል፣ እስራኤላውያን የትውልድ አመጣጣቸውን ጥንታዊ ታሪክ ጽፈው አስቅምጠውልና። ሙሉ ግን አይደለም። የራሳችን ሊቃውንት እጀ የገቡ ብዙ በብራና ላይ የተጻፉ መጽሐፍት፣ መጽሐፈ ኼኖክ ሳይቀር እስከዘመናችን ዘልቀዋል። ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 10 ከቁጥር 1 ጀምሮ፣ ኖኅ 3 ልጆች እንደ ነበሩት ያወራል። እነሱም፣ ሴም፣ ካምና ያፌት ናቸው። ዣንሸዋ ተቀዳሚ የሚባለው ጥንታዊው መጽሐፈ ብሩክ የነዚህን ትውልዶች ከገጽ 261 እስከ 275 ዝንፍ ሳይል፣ የሴምንም፣ የካምንም፣ የያፌትንም ትውልድ ዘርዘሮ ያስቀምጥልናል። ሰረገላ ታቦር የተባለውም፣ በመሪ ራስ አማን በላይ የተተረጎመውም ከገጽ 290 ጀምሮ እስክ 306፣ ይኸንኑ ይተነትናል። ማንበብ የሚወድ፣ የታሪክም ተመራማሪ ሁኖ ከዩኒቨርሲቲ መመረቅ አያሻውም። ታሪኩን እንደወረደ አንብቦ ይረዳል። ማን የማን ልጅ እንደሆነ በተጻፈው መሠርት ማንበብ ነው። የሚያወሩት ስለካም ልጅ፣ ኩሽ ከሆነ፣ የሴም ልጆች ሴማውያን ከተባሉ፣ የያፊት ልጆች፣ ያፌታውያን ከተባሉ፣ የካም ልጆች ካማዊያን “አፍሪካ” ጋ ሲደርስ የማይባሉበት ምስጢር ከቶም አይገባኝም። አንድ መደበቅ ያለበት ታሪክ ከሌለ እንደ ዋርዲት ምን አጎት ድረስ ያወርዳል?

የኖኅ ልጆችን የትውልድ ሐረግ (Family Tree) ሲመዘዝ እንዴት ማመን ይቻላል? መልሱ ቀላል ነው።  ጥንታዊውያን ማንበብና መጽሐፍ የሚችሉ አባቶቻችን፣ ልጆች ሲወለዱላቸው፣ ቀኑና ዓመተ ዓለሙን/ምህረቱን ወይም በየአገሩ የዘመን አቆጣጠር ባህል መዝግቦ ማስቀመጥ ልማዳቸው ነው። ያልተማሩት ይኸ ዕድል የላቸውም። ለምሳሌ፣ ወላጅ አባቴ፣ አቶ መኰንን አየነው፣ ነፍሳቸውን ፈጣሪ በገነት ያኑርልኝና፣ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ውርስ ባህላቸው መሠረት፣  የኔን ልደት ከነ ሰዓቷ፣ ቀኗ፣ ወሯንና ዓመተ ምሕረቷን፣ ከደረታቸው በማትለየው ዳዊታቸው የውስጥ ሽፋኗ ላይ ጽፈው ቁጭ አድርጎልውኛል። ያ ብቻም አይደለም። የደብረ ኤሊያስ ካህናት ትውልድ በመሆናቸው ወደ ኋላ በትንሹ እስከ ሰባት ቤት አባቶቻችን እነማን እንደነበሩ፣ ተመዝግቦ ከተቀመጠው ስሞቻችውን በቃሌ ቆጥሬ እንድይዝ አስጠንተውኛል። ቁም-ነገሩ፣ በአፈ ታሪክ ሳይሆን፣ የሥነጽሑፍ ባህል ያዳበረ ሕብረተሰብ ነገሮችን በቅደም ተከተሉ፣ በጽሑፍ መዝግቦ መያዝ፣ የዕድገት ደረጃውን ያመለክታል። እስከነ ተረቱ፣ በአፍ የተነገረ ይረሳል፣ የተጻፈ ይወሳል ይባል የለ? በአፈ ታሪክ የሚወራው፣ ምንም ዓይነት ማረጋገጫ ስለማይገኝለት፣ ተረት ሁኖ ይቀራል። አንዳንዴም የጎደለውን ለማሸብረቅ ያልነበረው ገብቶበት ይቦካዋል።

በሴም በኩል፣ አንዷን ዘለላ መዘን እስክ አብርሃም ያለውን ትውልድ እንይ[iii]። ምክንያት አለን። ኖኅ ሴምን ወለደ፣ ሴም አርፍክስድን ወለደ። አርፍክስድ ሳላን ወለደ። ሳላ ኤቦርን ወልደ። ኤቦር ፋሌቅን ወለደ። ፋሌቅ ራግውን ወለደ። ራግው ሴሮሕን ወለደ። ሴሮሕ ናኮርን ወለደ። ናኮር ታራን ወለደ። ታራ አብርሃምን ወለደ። ይበቃል[1]። ከሴም እስክ አብርሀም 10 ትውልድ መሆኑን ልብ በሉልኝ።

አሁን ደሞ በሌላ በኩል፣ ከሴም ታናሽ ወንድም፣ ከካም እስከ ካህኑ አበመሌክ ያለውን የትውልድ የሐረግ ዘለላ መዘን ከመጽሐፍ ቅዱስና ከተለያዩ ምንጮች እንመልከት።  

ኖኅ ካምን ወልደ። ካም ኩሽን ወለደ። ኩሽ ሳባን ወለደ፣ ሳባ ኑባን ወለደ። ኑባ አጋናን ወለደ። አጋና ኤታን ወለደ። ኤታን ናምሩድን ወለደ። ናምሩድ አዳማን ወለደ። አዳማ ራፌልብን ወለደ። ራፌልብን ቄናን ወለደ። ቄና መልክጸዴቅን ወለደ[iv]ከካም እስከመልከጸዴቅ 11 ትውልድ ነው። ኩሽ የት እንደቀረ አያችሁ? ከከነዓን ምድር እግሩም አልተቃነቀም

ኩሽ ናምሩድን ወለደ የሚል የተሳሳተ  ነገር አንብቤ፡ “ታላቁ ዶቦ ሊጥ ሆነ ብያለሁ።” ኩሽ ለናምሩድ ቅማንቱ[2] ነበር። አምስተኛ ትውልድ መሆኑ ነው። የነገሮች ውል ሲጠፋ እንዲህ መሳሳት ያመጣል። እንዲያው ዝም ነው። ምነው ኢትዮጵያውያንን ሊቃውንትን በጠየቁ!

ችግሩ ከየት እንደመጣ ላስረዳችሁ። ቫን ሰተር (Van Seter)[v] የተባለው ጸሐፊ እንደዘገበው ከሆነ፣ ኦሪት ዘፍጥረት፣ ኦሪት ዘጸአት፣ ኦሪት ዘሌዋውያንና ኦሪት ዘኁልቁ የተጻፉት በ6ኛው እና በ5ኛው መቶ ዓመት ዓለም፣ ዕብራውያን ከግብጽ ባርነት ነጻ ከወጡ በኋላ ነበር። የራሳቸውን ታሪክ በአብዛኛው መዛግብቱ ቢኖራቸውም፣ በስደት ዘመን የካምን መዝገበ ታሪክ አልነበራቸውም። የናምሩድ ትውልድ ስሀተት ከዚህ ነው የተፈጠረው። እንዲህ ነው የሆነው። መጽሐፈ ኼኖክና፣ ሌሎች መጻፍትን፣ ኖኅ የሰጠው ለካም ነበር። ካም ደሞ ለታላቅ ልጁ፣ ለኩሽ ሰጠው። መጻፍቶቹ፣ ካህን ለሚሆኑት ለታላላቆቹ እየተወረሱ እስከ መልከጸዴክ ደረሱ። መልከጸዴቅ ለታላቅ ልጁ፣ ለኢትዮጵ (ሌላ ስሙ ኢትኤል) አወረሰው። ኢትዮጵ መጻሕፍቱን ይዞ፣ ዛሬ አፍሪካ ወደምትባለው መሬት ተሻገረ። እንዲህ እያለ ኢትዮጳውያን ሊቃውንት እጅ ገቡ። እስራኤላውያን፣ በዚያን ጊዜ የካምን ታሪክ የሚክታተሉበት መንገድ አልነበራቸውም። ታላቁን ናምሩድ የካም ዘር ቢሆንም፣ ውሉ ስለጠፋቸው የኩሽ ልጅ ብለውት አረፉ።

እነዚህን የሁለቱን የወንድማማቾችን ሐረጎች ምን አስመዘዘን? መክንያቱም የሴምና የካም 10ኛና 11ኛ ትውልድ በአንድ ጊዜ እንደኖሩና እንደሚገናኙም፣ ዝምድናቸውንም እንደሚያውቁ ለማመልከት ነው። መጽሕፍ ቅዱስ፣ ኦሪት ዘፍጥረት፣ ምዕራፍ 14 ከቁጥር 17 እስክ 21 እንዲህ ይላል።

“ኮሎዶጎምርና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ነገሥታት ወግቶ ከተመልሰ በኋላም፣ የሰዶም ንጉሥ የንጉሥ ሸለቆ በሆነ በሊዊ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ። የሳሌም ንጉሥ መልከጽዴቅም እንጀራንና የወይን ጠጅን አወጣ። እርሱም የእግዚአብሔር ካህን ነበረ። ባረከውም፦ አብራም ሰማይንና ምድርን ለሚገዛ ለልዑል እግዚብሔር የተባረከ ነው። ጠላቶችህን በእጅህ ተጣለልህ ልዑል እግዚአብሔርም የተባረከ ነው አለውም። አብርሃምም ከሁሉ አሥራትን ሰጠው።”

አውሮፓውያንና አሜሪካውያን ተመራማሪዎች፣ ግዕዝን ለመማር የሚሟሟቱበት ምክንያት ብዙ የነገሮችን ግንኝነት ውል በፍጹም ሊያገኙት ባለመቻላቸው ነው ወደ ኢትዮጵያ የሚያንጋጥጡት። የአብርሃምንና የመልክጸዴቅን ግንኙነት (relationship) ጨርሶ ያልገባቸው፣ ፈረንጆች እንዲ ሲሉ ይናገራሉ።

Abraham encounters a mysterious figure named Melchizedek. So, who exactly is this mysterious Melchizedek? As Abraham is returning victorious from a risky battle, he passes by the city of Salem, and the king comes out to meet him. We're told that this king is also a priest who serves the same God as Abraham.[vi]

በቀላሉ ወደ አማርኛ ስንመልሰው፡ አብርሃም ምስጢራዊ የሆነ መልከጸዴቅ የተባለ ሰው ያጋጥመዋል። እና፣ ይኸ ምስጢራዊ የሆነ ሰው ማነው? አብርሃም አደገኛ (risky) የሆነ ጦርነት ተዋግቶ ድል ነስቶ በሳሌም ከተማ ውስጥ ሲመለስ ይኸን የሳሌምን ንጉሥ ያገኘዋል። እንደነገሩን ከሆነ፣ ይኸ ንጉሥ፣ አብርሃም የሚያመልከውን እግዚአብሔር የሚያገለግል ካህን ነው። 

እንደዚህ ዓይነት ብዙ ነገሮች ከኢትዮጵያ ምንጮች ካልሆነ በስተቀር ሌላ ቦታ ድርና ማጉን ማገናኘት የማይቻሉ ነገሮች አሉ።[3]

እንግዲህ ዕውነተኛው ኩሽ የኖረው ወደ 5,000 ዓመተ ዓለም አካባቢ ነው። ወዲያው ከታላቁ ውሀ መጥለቅለቅ በኋላ ብዙ ህዝብ አልነበረም። የከነዓን ምድር ሁሉ ለኖኅ ልጆች የምትበቃ ሰፊ ነበርች። ኩሽ ከከነዓንም ምድር ወጥቶ አያውቅም። አፍሪካ የት እንዳለችም አያውቅም። ይኸ ጥቁር ህዝብን በደፈናው ነጮቹ ኩሽ የሚሉት ከግብጽ ተውሰው በዘረኝነት ላይ የተመሠረተ ታሪካዊ ጭብጥ የሌለው መላ ምት ነው። ቀላ ቀላ ባሉት ወራሪ ዘሮች ድቅልቅል ያሉት ግብጾች ወደደቡብ የገፏቸውን፣ ጥቆርቆር ያሉትን ኑቢያዎች የሰደቧቸው መስላኡቸው ኩሽ አሉቸው። የድንቁርና ጥግ ይሉሀል ይኸ ነው።

በ440 ዓመተ ዓለም ገደማ የኖረው ታላቁ የግሪክ የታሪክ ሰው፣ ሔሮዶቱስ (Herodotus) ስለኩሽ ሳይሆን ስለ አእትዮጵያ ("Αἰθιοπία - Aethiopia") ነበር እንዲህ እያለ የተርከው።

“... this country produces great quantities of gold, has an abundance of elephants and all the woodland trees, and ebony; and its men are the tallest, the most handsome, and the longest lived."[vii]

ወደ አማርኛ ስንመልሰው፡ “አገሪቱ ብዙ ወርቅ የምታመርት፣ ብዙ ዝሆኖች የሚገኙባት፣ በጫካ የተከበበች፣ ብዙ ለአናጢ ሥራ የሚመቹ ግንዶች ያሏት፣ ህዝቧ በጣም ረጃጅም የሆኑ፣ በጣም የሚያማምሩ፣ እና በዙ ዓመታት መኖር የሚችሉ ናቸው” ይላል። ሔሮዶቱስ ማለት የዓለም ታሪክ አባት ተብሎ የተሰየመ ነው። የተቃጠለ ፊት የሚለው ትርክት ሰዎች እንደልማዳቸው የግሪክ ቃል ፈልገው አጠጋግተው ካልሆነ እንጂ፣ በሔሮዶቱስ ገለጻ አንድም ቦታ የተቃጠለ ፊት የሚል አናገኝም። ከየት ፈበረኩት? እንዲያው የተቃጠለ ፊት በግሪክኛ Kaméno Prósopo (Καμένο πρόσωπο) ነው። ምኑን ከምን አገናኙት?

ከ9ኛው እስከ 8ኛው ዓመተ ዓለም የኖረው ሆሜርም፣ ኤሊያድ ( Iliad)  በተባለው ድርሰቱ ሁለት ጊዜ፣ በኦዲሰይ (Odyssey) 3 ጊዜ ኢትዮጵያን በስሟ ጠርቶ ያሽሞነሙናታል። ግሪኮች በነበረው ስሟ፣ ኢትዮጵያ ብለው ጠሯት እንጂ፣ አዲስ ስም አላውጡላትም። ኢትዮጵያ ስለምትባለውና ስለህዝቧ ነው የተናገሩት። እነሱ ማን ናቸውና ነው ለኢትዮጵያ ስም የሚያወጡላት? በስሟ ጠርተው ነው ያደነቋት። የዘመኑ ታርክ አጥኚ ነን ባዮች እንዴት “የተቃጠለ ፊት” ሊሉት ቻሉ? እንዴት አጠጋጉት? ምናልባት፣ አዲግራትን “አዳ ጋራ” እንዳሉት አጠጋግተው ይሆን? ግሪኮች የሚያወሩት ስላጋጠመቻቸው “ኢትዮጵያ” ነበር እንጂ ስም አላወጡላትም። እነሱ በግልጽ ሲናገሩ የነበሩት፣ ስለ ኢትዮጵያን ልብ የሚሠርቅ ውበታቸው ነው እንጂ ስለተቃጠለው ፊታቸው አልንበረም። እስቲ ይታያችው፣ የግሪክ አፈታሪክ (mythology) ክዋክብትን በኢትዮጵያ ንግሥት ካሶፒያ (Cassiopeia) እና ንጉሥ ሲፊየስ (Cepheus) እያሉ ሲሰይሙ ስለተቃጠለው ፊት፣ ወይም ስለ ኩሽ እያወሩ ነበር? ስለ ልዕልቲቱ የካሶፒያና የሲፍየስ ልጅ፣ ስለ አንድሮሜዳ ሲያወሩ፣ ስለኩሽ ነበር ያወሩት? ከየት ነው ኩሽ መጥቶ በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ የተደነቀረው? ኩሽ መጥፎ ስም ሁኖ ሳይሆን፣ የታሪክ መሠረት ስለሌለው ነው። ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ይሉሀል ይኸ ነው። “ኢትዮጵያ” የሚለው መጠሪያ ስም ግን የተረጋገጠ የታሪክ መሠረት አለው። ለመሆኑ ይኽቺን ኩሽ የምትለዋን ቃል ማን ነበር መጀመሪያ አምጥቶ የደነቀራት? ከላይ እንደተገለጸው ግብጾች ነበሩ። ጢሞቲዎስ ኬንዳል (Timothy Kendal) የተባለ ሰው፣ እንዲህ ጉዱን ይነግረናል።

Kush, the Egyptian name for ancient Nubia, was the site of a highly advanced, ancient black African civilization that rivaled ancient Egypt in wealth, power and cultural development. The first capital of Kush lay at Kerma just south of the Third Cataract of the Nile.[viii]

“ኩሽ፡ ግምጾች፣ ለጥንታዊ ኑቢያውያን የሰጡት ስም ነው። አካባቢውም በጣም በሥልጣኔ የመጠቀና ከግብጽ ሥስልጣኔ፣ ሀብትና ኃያለነት ያላነሰ የጥቁር አፍሪካውያን አገር ነበር። የመጀመሪያው ዋና ከተማቸው ኬርማ ይባል ነበር። የሚገኛውም ከሦስተኛው የአባይ ካታራክት (ዓባይን እንደ የዓይን ሞራ የሸፈነ መሬት) ትንሽ ወደ ደቡብ ወረድ ብሎ ነው”። ግብጽን ከኢትዮጵ ዘሮች ከቀሟት በኋላ ማን ያልተፈራረቀባት አለ? ግሪክ፣ ሮማዎች፣ ቱርኮች፣ አረቦች ... ወዘተርፈ።

የአውሮፓ ቅኝ ግዥ ነጮች፣ ያቺን ከግብጽ ተዋሱና ትርጉሙን አጣመው ጥቁሩን ህዝብ በሙሉ ኩሽ አሉት። ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ስም ማውጣት አቅቷቸው ነው፣ ነጮቹ ግሪኮች አዲስ ስም የሚያወጡላቸው? ለነገሩ፣ አልተሳካላቸውም እንጂ፣ አቢሲናያስ ሊሉን ምን ያልፈነቀሉት ድንጋይ ነበር?

4)  ኢትዮጵያ - ምድረ ኢትዮጵ

የካምን ትውልድ ሀረግ ስንመዝ፣ 11ኛው ትውልድ ላይ ነበር የቆምነው። እሱም ካህኑ መልከጸዴቅ ነበር። ካህኑ መልክጸዴቅ ምሥጢራዊ ሰው ሳይሆን በቀጥታ ዘር ሐረጉ ሳይዛነፍ ከካም፣ የወረደ 11ኛ ትውልድ ነው። አብርሃምና መልከጸዴቅ ፈረንጆቹ distance cousin (የሩቅ የአጎት ልጆች) የሚሏቸው ናቸው።

መጽሐፈ ብሩክ ዣንሸዋ ቀዳማዊና ቀጥሎ ሰረገላ ታቦርን ስናነብ፣ ካህኑ መልከጸዴቅ ሦስት ወንዶችና አራት ሴቶች ልጆች እንደነበሩት እናገኛለን። ከሦስቱ ወንዶች፣ አንዱ ኢትኤል፣ በኋላ፣ ኢትዮጵዮ የተባለ የበኩር ልጁ እንዳለ እንገነዘበለን። በዚህን ጊዜ የከነዓን ምድር በሰው ተጨናንቃ ነበር። የሴም ልጆችም በዝተው ነበር። የካም ልጆችም እንደ የምድር አሸዋ በዝተው ነበር። በየጊዜው ለከብቶቻቸው ግጦሽና ውሀ፣ ለሚያርሱት መሬት፣ ከሴም፣ ከያፌትና ከወንድሞቻቸው ጋርም እየተጋፉ ይጣሉ ነበር። በዚህ የተነሳ፣ ኢትዮጵ ከብቶቹንና ቤተሰቡን ይዞ ወደ ሲን (Sinai) በረሀ ወረደ ይለናል ሰረገላ ታቦር ገጽ 307። ከሲና ተንስቶ ወደ ደቡብ የዓባይን ወንዝ ተከትሎ እንደሰፈረ እንረዳለን። በዚህ መሠረት፣ ኢትዮጵ ግብጽን፣ ሱዳንን እና የዓባይ ምንጭ የሚፈልቅባትን መሬት የራሱ ርስት አድርጎ በራሱና በልጅ፣ በልጅልጆቹ ማንም ሳይጋፋው ማስተዳደር ቀጠለ። የያዛቸውም መሬቶች እንዳሉ የኢትዮጵ ምድር ወይም ግዛት እንደተባለ ጥንታዊ መዛግብት ላይ ተጽፏል። ሌላም ቦታ፣ የያፌትም ልጆቹ ሆኑ የሴም ልጆች በሄዱበት በራሳቸው አባቶች ስም የያዙትን መሬት መሰየም የተለመደ ነው። ለመሳሌ እንግላንድ የኢንተርኔት ምድር ናት። ስኮትላንድ፣ የስኮቲሾች ምድር ግዛት ናት። አየርላንድ፣ የአይሪሽች ምድር ናት። ምድርን ወይም ግዛትን አንዳንድ ቦታ በ..”ያ” (..ia) ተቀጽላ ይተኩታል። አረቢያ የአረብ ምድር ናት። ኢንዲያ የህንዶች የሚኖሩባት ምድር ናት። ዩጎስላቪያ፣ የዩግስላቮች አገር ነበርች። ራሺያ የሩስኪዎች አገር ናት። ሶማሊያ፣ የሶማሌዎች ምድር ናት። እንደዚሁም የኢትዮጵ ግዛት የነበረችው ጠቅላላ አህጉር ኢትዮጵያ ትባል ነበረ። ውቂያኖሷም፣ የኢትዮጵያ ውቂያኖስ ነበረ። 



በኋላ ላይ ግሪኮችም፣ ሮማውያንም፣ ሌሎችም ቅኝ ገዢዎች ኢትዮጵያን ወይም የኢትዮጵ ምድር ወረሯት። የአህጉሩንም ስም 17ኛ መቶ አጋማሽ ክፍለዘመን ላይ ሮማውያን “አፍሪካ” ብለው እንደሰየሟት ከተለያዩ ምንጮች እንረዳለን[ix] የጥንት ነባር ካርታዎችን ስናይ፣ የትም ቦታ ኢትዮጵያ የሚል እንጂ ኩሽ የሚል አገር አታገኙም። የሆኑ፣ የኋላ ታሪክ ተመራማሪዎች ነን የሚሉ ሰዎች ናቸው ጥቁሮቹን አፍሪካውያንን ግብጽን ተከትለው “ኩሽ” ብለው ያረፉት። ከየት አመጡት? የኛዎቹ ጉዶች ያንን ይዘው ይንኮሻኮሻሉ። እግዚአብሔር ይማራቸው።

የሆነ ሁኖ፣ የኢትዮጵ 10 ትውልድ ዛሬ አፍሪካ የተባለችውን፣ የኢትዮጵን ምድር እስከዮቶር ድረስ ተራ በተራ እንዳስተዳደሯት እናገኛለን። ዮቶር ማለት፣ የሲጳራ አባት፣ የግብጻዊው ሙሴ አማት ነበር። ስማቸውን ስንዘረዝር፣ ኢትዮጵ አዜብን ይወልዳል። አዜብ ሞሪን ይወልዳል። ሞሪ ልብናን ይወልዳል። ልብናም መላክን ይወልዳል። መላክም ጋቢናን ይወልዳል። ጋቢናም አዲያምን ይወልዳል። አዲያምም ኖርኑስን ይወልዳል። ኖርኑስም ዮቶርን ይወልዳል። አንባቢን ላለማሰልቸት፣ እዚህ ላይ ቆም እንበልና ትውልዱ፣ እያለ እስከ ንጉሥ አክሱም ይኸዳል። አክሱም ማለት፣ የኛ ዘመናዮች ያለ ምንም ተጨባጭ መረጃ፣ “አካሱማ” ከሚለው የኦሮሚኛ ቋንቋ የመጣ ሳይሆን፣ ነግሥተ ሳባ የተባለችው ንግሥት አያት ነበር። አክሱምን አካሱማ ያሉን “ሁንዱማ ኬኛዎች” ነገ ሚኒስቶታ የተባለ የአሚሪካ ከተማ ውስጥ እየበዙ መጥቷልና፣ “ማና ሶታ” ነበር እንዳይሉን፣ ምን ይገድባቸዋል?

ስለዚህ ኩሽ ብሎ ነገር አፍሪካ ውስጥ አልነበረም። ባይሆን እንኳን የካም ልጆች ነን ቢሉ ያምርባቸዋል። ከሴምና ከያፌት እኩል ሚዛናዊነቱን የጠበቀ ነዋ። የሴም ልጆች ሴማውያን ናቸው። የያፌት ልጆች እነ ጋሜር፣ ማጎግ፣ ማዴ፣ ያዋን፣ ይልሳ፣ ቶቤል፣ ሞሳሕ፣  ቴራስና የልጅ ልጆቻቸው በሙሉ ያፌታውያን ነው የሚባሉት። የካም ልጆች ካማውያን (Hamites) እንዳይባሉ ጥራዝ ነጠቅ የኦሮሞ ልሂቃን ያንኮሻኮሹት ምን ተአምር ተፈጥሮ ነው? ምን ለመደበቅ ታስቦ ነው ከጊዜ በኋላ ኩሽ የተባሉበት ምክንያት?

ታዲያ እኛ ኢትዮጵያውያን ማን ነን? የሚቀጥለው ክፍል ያብራራዋል።

5)   ማጠቃለያ - እኛ ማን ነን?

እኛማ ዓለም ያወቀን ጸሐይ የሞቀን ከጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ስንቀነስ፣ ስንቆረጥ የተረፍን፣ የአባታችንን፣ የኢትዮጵን ስም ወርስን የቀረን ኢትዮጵያውያን ነን። እየቆረሱን አናልቅ ብለን ያስቸገርናቸው ህዝብና አገር ነን። አጼ ዘርዓ ያቆብ እንኳን 15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከዛሬው በእጅጉ የሰፋች አገርን ሲያስተዳድሯት ነበር። ትላንት፣ ዓይናችን እያየ ጂቡቲና ኤርትራ ሌላ አገር ሁነዋል። ዛሬ፣ ዘረኞች 83 ቦታ በቋንቋ ሸንሽነውን፣ የፈለገ መገንጠል ይችላል የሚል “ሕገ መንግሥት” ቀርጸው፣ ሊለያዩንና የኢትዮጵያን ስም ከምድረ ገጽ አጥፍተው በኩሽ ሊቀይሩ ሲታትሩ እናያለን። በተለይ ኩሽ ኩሽ እያሉ የሚጮኹ የኦሮሞ ልሂቃን በሚያስፍር ሁኔታ ህዝቡን በሴምና በኩሽ ከፍለው ደም ለማፋሰስ ሌት ተቀን ይጥራሉ። ነገሩ፣ ጸረ ሴማዊነት (antisemitic)(x) ፕሮፌሰር ግርማ ብርሀኑ ቢጠቁምንም፣ ቦታውን የሳተ ነው። እዚህ ሴማውያን የሉም። እስራኤልና፣ አንዳንድ የተሰደዱብት አገር ነው የሚኖሩት። እዚህ የነበሩትም ሂደዋል። "ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ" ይሉሀል ይኸ ነው።

ኩሽ ኩሽ ባዮችን እረፉ እንላለን! አታንኮሻኩሹብን! ኩሽ ብሎ ነገር የለም። ካምና ሴም የሚባል የተከፈለ ህዝብ የለንም። የዘመናችን ታልቁ የቤተክርስቲያናችን በሕይወት የሚገኙ ሊቅ፣ አባታችን ቀሲስ አስተራዬ ጽጌ፣ “ሕብረ ሐመልሚል” በሚል ርዕስ “የአቶ መላኩ አስፋ የሕይወት” በሚል ርዕስ በሚያዝያ 1 ቀን 2006  ዓ.ም. ባበረከቱት ጽሑፍ እንዲህ ብለው ነበር።

የመላኩ ሰውነት   አርአያ ኮሰኮስ ዘብሩር የተባለውን  የሁላችንን ሰውነት  የምንመለከትበት መስተዋታችን ነው።   በሌላ  አገላለጽኢትዮጵያዊነታችን በለመለመ መስክ በቅለው፤ አብበው፤  በሩቅ የሚታዩ  የጽጌ ረዳ፤ የአደይ አበባ፤ የሶሪት አበባ፤ የሱፍ አበባ መሳይ ይህ ቀረሽ የማይባል የውበት ውጥንቅጥ ማለት ነው። ከዚህ ውጭ ነኝ የሚል ኢትዮጵያዊ ካለ፤ ወፍ ዘራሽነትህን ተቀብለህ ቦታህን ፈልግ ሊባል ይገባዋልእያሉ ሊቃውንት አበው አስተምረውናል።

ይኸ አባባል ዝም ብሎ ነገር ለማሳመር የተነገረ፣ ሳይሆን ሀቅ ላይ ተመሥርቶ የተነገረን፣ ዕውንተን ያዘለ ጥልቅ መልዕክት ነበር። ምሑራዊ ትንተና ነው። አባታችንን “ቃለ ሕይወት ያሰማልን” እያልኩ፣ ወደሌላው የመጨረሻ የኩሽ ትርክት የቀብር ሳጥን ላይ የሚመታ 12 ቁጥር ሚስማር ልለፍ። ይኸውም ኩሽ ወይም ሴም የምባል ዘር አለመኖሩን የሚነግረን ሳይናስዊ ቀመር ነው። አረቦች ሐባሽ ያሉን ምክንያት ነበራቸው።

በአገራችን፣ ጥርት ያለ ኩሽ የለም፣ ሴምም የለም ስንል በታሪክ በሳይንሱም ላይ ተመርኩዘን ነው። ኢትዮጵያዊያን ነን። የምንናገረው ቁንቋ፣ የማን ልጆች መሆናችንን፣ ማንነታችንን ሊያሳየን አይችልም። ቋንቋ የሕብረሰብ መግባቢያ እንጂ፣ የዘር ሀረግ መምዘዢያ አይደለም። ዕረፉ አትንኩሻኮሹብን! በታሪካችን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በ20ኛው መቶ መጨረሻ ክፍለ ዘመንና በ21ኛ መቶ መጀመሪያ ኢትይጵያውያን በዓለም በስደት እንደጉድ ተዘርተናል። ልጆቻችን እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ስዊዲሽኛ፣ ኖርዊይጅኛ፣ ጀርመኒኛ፣ ግሪክኛ ጣሊያንኛ፣ ስፓኒሽ፣ ... ወላጆቻቸው እንደተሰደዱብት አገር አፍ መፍቻ ቋንቋቸው አድርገው ያድጉበታል። ታዲያ ያ አይደለም ማንነታቸውን የሚውስነው። ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ሲሰደዱ፣ ኢትዮጵያን በልባቸው ይዘው ነው በዓለም የተዘሩት። በሂዱበት፣ የራሳቸውን ባህልና አኗኗር ይዘው ነው የሚንከራተቱት። እንዲያውም፣ የኢትዮጵያዊነት ስሜት የሚብስባቸው፣ አገራቸው እየኖሩ ሳይሆን ከአገር ሲወጡ ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። ምግባቸው እንኳን በተቻለ መጠን አትለውጥም። የኢትዮጵያ በረበሬ ጣዕም ሌላ ቦታ የለችም። ምጥን ሽሮአቸው እንኳን አትለያቸውም። በሔዱብት ሬስቶራንታቸው፣ ትከተላቸዋለች። በዓላቶቻቸውን ልክ እንደ ኢትዮጵያ ነው የሚያክበሩት። ቤተ ዕምነታቸውም፣ አብራቸው ተሰዳለች። ልጆቻቸውንም፣ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ለማሳደግ ነው የሚጥሩት። ሕጻናቱ፣ ኢንደሌላው ሕብረተሰብ፣ የማንነት ጥያቄ (identity crisis) ጭንቀት አይታይባቸውም። በኩራት ኢትዮጵያዊነታቸውን ይናገራሉ። ኤርሚያስ በትንቢቱ (13:23) በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን፣ ወይስ ነበር ዝንጉርጉርነቱን ይለውጥ ይችላልን?” ያለበት ምክንያት ነበረው። ቂሲስ አስተራየን የሚሉትም ይኸንኑ ውበት ነው። አንድ የሚያደርግን፣ በውስጣችን የሚዘዋወረው የደማችን አንድነት ነው እንጂ፣ የምንናገረው 83 ቋንቋዎች አይደለም።

እስቲ አንድ ከዚህ በታች የአለውን የዘረመል (DNA) ምርመራ ውጤት ከልብ ተመልክቱ። ወደ ሌላ አትዩ! አትኩራችሁ ተመልከቱ፡ አጥኑ! አገናዝቡ! ምን ይታያችኋል?



አንድ ንጹህ ኦሮሞ ፈልጋችሁ አታገኙም። አንድ ንጽህ አማራም ፈልጋችሁ አታግኙም። ኩሽ እየተባለ የሚንኮሻኮሽበት ኦሮሞ የኦሮሞ ልሂቅ፣ ከአማራው፣ ከአፋሩ፣ ከትግሬው፣ ከወላይታው ተደባልቋል። ለመድኃኒት እንኳን ንጹህ ኦሮሞ አይገኝም። እምኑ ጋ ነው ኩሽነቱ? እንድገመው! ቋንቋው? ቋንቋንማ ማንም ሊናገረው ይችላል። ስንት ኦሮሚያ ውስጥ የተወለዱ አማሮች ተብለው የተፈረጁ ኦሮሚኛ የመጀመሪያ ቋንቋቸው እንደሆነ እነዚህ የተማሩ መሀይማን ይረዱ ይሆን?

አማራውም ቢሆን፣ ከኦሮሞው፣ ከአፋሩ፣ ከትግሬው፣ ተደበላልቋል። ደሙ ሲመረመር አንድ ንጹህ አማራ በአጉሊ መነጽርም (microscope) ተፈልጎ አይገኝም። እምኑ ጋ ነው ሴማዊነቱ? ቋንቋውን ስለተናገረ? እንዳልነው ቋንቋማ መግባቢያ ነው። ስንቱ አማራ ያልሆነ ይራቀቅበታል።

እናንተ የተማራችሁ መሀይማን! ኩሽ አገራችንን ረግጦም አያውቅም። የኖረው ክ7023 ዓመት በፊት በከነዓን ምድር ነው። ወደዚህ የመጣው ከኩሽ 12ኛው ትውልድ ኢትዮጵና ቤተሰቡ ነበሩ። በዝተው ተባዝተው አህጉሯን ስለሞሏት ግዛቱም ኢትዮጵያ ይባል ነበር። ኢትዮጵያ በታሪኳ ስደተኞችን ስትቀበል የኖረች ናት። በተለያየ መንገድ በአረቢያም ይሁን በሱዳን በኩል በተለያየ ጊዜ የሴም ልጆች ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡም ከካም ልጆች ጋር ተጋብተው ተዋልደው ቀሲስ አስተራየ እንዳሉት “ህብረ ሐመልሚል” ፈጥረዋል። የተለየ ሴም ወይም ኩሽ የምትሉት ነገር የለም። እኛ ኢትዮጵያውያን ነን። አትንኮሻኮሹብን።

ትላንት ያልነበራችሁትን፣ ዛሬም ያልሆናችሁትን፣ ነገም ልትሆኑ የማትችሉትን ኩሽ እያላችሁ አታንኮሻኩሽብን! በሀሰት ተርክት ህዝባችንን አታምሱት። ስላም ስጡን።

አበቃሁ።




End Note - የመጨረሻ ግርጌ ማስታውሻ


[1] ከሴም እስከ አብርሀም ያለው ትውልድ በደረገጹ ላይ ክ10ኛው ተራ ቁጥር ጀምሮ ተደርድሯል። የተወሰደውም፣ ከዘፍጥረት ምዕራፍ 11 ነው።

[2] ትውልድ ሲተነተን እንዲህ ነው፡ ልጅ አባት አያት ቅድመ-አያት ቅም-አያት ቅማንት፣ ሽማት ፣ምንዥላት አንጅላት፣ ፍናጅ፣ ቅናጅ ፣አስልጥ አምስጥ ማንትቤ፣ ደርባቴ

[3] ለምሳሌ፤ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 26 ቁጥር 18 ላይ “እርሱም ፦ ወደ ከተማ እገሌ ዘንድ ሂዳችሁ ፦ መምህር፦ ጊዜዬ ተቃርባል። ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ከአንተ ዘንድ ፋሲካን አደርጋለሁ ይላል በሉት።” ማነው እገሌ? መልሱን ከሐሙሱ ሰይፈ ሥላሴ፣ ተአምሩ ላይ 318ቱ ሊቃውንት ከአሪዮስ ጋር በኒቅያ ጉባኤ ሲከራከሩ፣ በቁጥር 18 ላይ፣ ይኽ እገሌ፣ ወዳጁ አልዓዛር መሆኑን እንረዳለን።



[ii] Baum, James E.: Savage Abyssinia, J.H Sears & Company, Inc. Publishers, New York, 1928, P. XVii

[iv] መጽሐፈ ብሩክ፣ ዣንሸዋ ቀዳማዊ ገጽ 269 እና ሰረገላ ታቦር ገጽ 290 (ትርጉም፣ መሪ ራስ በላይ አማን)።

[v] Van Seters, John (2004). The Pentateuch: A Social-science Commentary. Continuum International Publishing Group. ISBN 978-0567080882

[vii] https://stockton.edu/hellenic-studies/documents/chs-summaries/kantzios96.pd

[viii]f

[viii]https://www.pbs.org/wonders/Episodes/Epi1/1_wondr2.htm#:~:text=Kush%2C%20the%20Egyptian%20name%20for,Third%20Cataract%20of%20the%20Nile.

[ix] https://youtube.com/shorts/kdMNA-szyKk?feature=share

x Girma Berhanu: The New Frontier Of Antisemitism: Racial Discourse And Oromo Extremism In Ethiopia – Analysis, https://www.eurasiareview.com/29062023-the-new-frontier-of-antisemitism-racial-discourse-and-oromo-extremism-in-ethiopia-analysis/?fbclid=IwAR2qRe-3GyGWSQgqMLmaeKkaFJLltxbr7LTFOEkDiqO5m5GNtMDHcFZ_RTc

No comments:

Post a Comment