Wednesday, 10 June 2026

ታምነን ከማጉደል ይሰውረን!

ከትዝብተ ሰሎሞን  



ታምኖ ከማጉደል፣
አምኖ መበደል
ታምኖ ከመካድ፣
አምኖ መጎዳት አምኖ መሰደድ፣

ሰው አምኖ ሲቀበል ኋላ ቢታለልም
መበለጥ መሞኘት ለጊዜው ቢመስልም፣
አምኖ መገኘቱ ፣
ድጋፉን መስጠቱ፣
አመድ አፋሸ ሲሆን
ምላሽ ቱርፋቱ፣
የአካል ጥቃቱ፣
ጀርባን መወጋቱ
የመንፈስ ጉዳቱ፣
ካገር መገፋቱ፣
በየብስ በባህሩ የመንከራተቱ፣
ወንድም በወንድም ላይ አስታጥቆ ማዝመቱ
እርስ በርስ ማፋጀቱ

አንጀትን ቢያቆስልም
እምነት ያሳደረ ባመነው ቢካድም፣
ጊዜ ይውሰድ እንጂ የተሸፋፈነ መገለጡ አይቀርም።
አዎ ሀቅ አይሸፈንም፣
ዕምነት ያሳደረ፣ለእውነት የሚታገል ማሸነፉ አይቀርም

ታምኖ ከማታለል
እምነት አሳድሮ
መታለል ይሻላል።
ቃል ከባድ ነገር ነው ከምንም ይከብዳል፣
ስሙን እየጠሩ የዋሹትን ያህል
ፈጣሪ ታጋሽ ነው በጊዜው ይፈርዳል።
በእጅጉ፣በእጅጉ ክፉኛ ይቀጣል።

ትንሽ ላሰበበት በደንብ ላስተዋለ፣
በሀገር አንድነት ላይ ልዩነት ከሌለ፣
እኔ እበልጥ እኔ በልጥ ብሎ ካልተባለ፣
በጥቅም በስልጣን ካልተከፋፈለ፣
ለተናገሩት ቃል ታምኖ እንደመገኘት የሚበልጥ የታለ

አንዱን ከአንደኛ ሳያበላልጡ፣
ሁሉን በእንድ አይተው፣እኩል ቢያስቀምጡ፣
በብሄር በጎሳ፣በየጎጣጎጡ፣
ቢቀር መወሸቁ፣ለጠብ መፋጠጡ፣
ለጋራ ቤታቸው በቀና ለመምከር አብረው ቢቀመጡ፣
የአቅም የችሎታን ሃሳብን ቢያፈልቁ፣

ለህዝባችን ቸግር ጦርነት ባይጠምቁ፣
ሰላምን ቢያቀርቡ፣ፍቅርን ቢያዋጡ፣

ለማያበላልጥ አንዱን ከአንደኛው፣
አንዱ ሲመካበት ሌላው እንዳይወቅሰው፣።
ሁሉን በማስማማት
መቆም ላገር ለህዝብ ታሪክ ለማይረሳው፣
በእጅጉ ይበልጣል ከመስራት ላንድ ብሄር ከመስራት ለጎሳው፣

ሌት ተቀን መስራቱ
መድከሙ መልፋቱ
ህዝብ እረፍት ማጣቱ፣
ይህም ያልፋል ብሎ መታረዝ ማጣቱ፣
ከጦርነት ይልቅ ፣ሰላም መመኘቱ፣
የሰላምን እጆች መውጣት መዘርጋቱ፣
ለሁሉም ይበጃል ፀጋ ነው በእውነቱ።

ግና ይሄ ሁሉ ሰሚ አዳማጭ አጥቶ በስራ ካልዋለ፣
ሀገር ትለማለች ብሎ እየማለ፣
ቃልና ተግባሩ ካልተመሳሰለ፣
የወቅታዊ ችግር የማለፊያ ዘዴ ብልጠት ከተባለ፣
ህዝብን አየናቀ በአፉ ያታለለ
የጊዜ ጉዳይ ነው መጣሉስ አይቀርም እያንከባለለ

ለትልቅ አላማ ለህዝብ እኩልነት መሆኑ ከቀረ፣
በድብቅ የጎሳ ስሌት ካስቆጠረ፣
በሰውነት ሳይሆን በዘር ከመተረ፣
መፅሀፍ ቅዱስ ቁራን እየጠቃቀሱ ምን አስቀባጠረ
ለግፍ ለሀጢያቱ
የአለማዊው መንገድ መዋሸት መቅጠፉ ይበቃ ነበረ
ህዝብ ምን አጠፋ አምኖ ባከበረ
ወገኑ ሲታረድ አገር ሰላም ይሁን ብሎ በመከረ
እርሙን እየበላ አንጀቱን ባሰረ፣
እውን በግፍ ላይ ግፍ መደረብ መቆለል ይገባው ነበረ?

አዎ እንደተባለው ሁሉም አላፊ ነው፣
ቃል ግን ክብር አለው፣
የሰው ልክ ቃሉና ተግባር መገናኛው፣
ውሃ ልክ መለኪያው፣
በቃሉ መታመን ለቃሉ መሞት ነው።

ከተራ እረኛ ለማኝ የኔ ብጤም፣
እጅግ የከበሩ የናጠጡ ሃብታም፣
ልዑልና ልዕልት ንጉሰ ነገስትም
የእውቀት ጠበብቶች ፣የአለም መሪዎችም፣
ሞኛሞኝ ቂልና ብልጥ ነን ባዮችም፣
ጊዜ የሰጣቸው ፈርጣማ ጉልበታም፣
ሌሎችም ፣ሌሎችም።

ባለበት የቀረ፣
የያዘውን ይዞ ዝንተ አለም የኖረ
አንዳች ፍጡር የለም።
ሁሉም አላፊ ነው ወደድንም ጠላንም።

ሀብታም ይደኸያል፣
ደሀ ሀብት ያገኛል፣
ደካማው ይነሳል
የነጣው ይወዛል ፣
የወዛው ይነጣል፣
የቀላው ይጠቁራል፣
ወጣትም ያረጃል
ጉልበትም ይደክማል፣
ቂም በቀል ይወልዳል፣
የዛሬ አሸናፊ ነገ ይሸነፋል
የዛሬ ብልጣብልጥ ነገ ይሸወዳል፣
ጊዜም እንዳነሳ መልሶ ይጥላል።
ፍቅርን መዝራት ግን ፣
በቃል ፀንቶ መቆም ለቃልም መታመን፣
ፍቅር ያሳጭዳል፣።
መንፈስን ያድሳል።
በፈጣሪ ዘንድም ገነትን ያወርሳል።

አምኖ እንዳከበረው፣
ዘር ጎሳ ሳይለየው ፣
ማንም የማይሽረው
በቃሉ የፀና
ወሮታው ፍቅር ነው፣
ለሚስት ለልጆቹ ቀጣይ ትውልዶቹ፣
ኩራት የሚሆነው፣
ብሩህ ተስፋ ያለው።

ለትውልድ ይሰራል
ህዝብን ያከበረ ቃሉን ይጠብቃል፣
የንፀሀንን ደም ከመፍሰስ ያድናል፣
ሁሉንም `ሚያስማማ ታሪክን ይጽፋል፣
በሰላም ይተኛል፣
በሰላም ይነሳል፣
ህሊናው ከፀፀት የፀዳ ይሆናል፣
እምነት ታላቅ ዕዳ መሆኑን ያስታውሷል።

ታምኖ ከሚያጎድለው፣
አምኖ የተካደው፣
ምንም እንኳን ንብረት፣ወገኑን ቢያሳጣው ፣
ከሁሉም ከሁሉም ነፃ ነው ኅሊናው፣
በሴራ ያመነው
ብልጠት የመሰለው፣
በቃሉ ያልጸናው፣
የዘራውን ያጭዳል የጊዜ ጉዳይ ነው፣
ዕምነት ታላቅ ዕዳ! መሆኑን ይወቀው።

ታምነን ከማጉደል ይሰውረን!

ሀገራችንና ህዝባችንን ከክፉ ነገር  ይጠብቅልን!
05.05.2023።።።።።
ትዝብተ ሰሎሞን

No comments:

Post a Comment