Friday 9 December 2011


የጐንቻው !

ወዮላቹህ፤የቀን ጅቦች ሳታስቡት፤መሸባቹህ፤             

ሕዝብ መሽጓል በዋሻቹህ፤መሸሸጊያም የላቹህ፤

አጥንት ነካሽ ‘የቄራ ውሾች’፤ተራብታቹህ፤

ስትጮሁ ለከርሳቹህ፤የሕዝብ እሮሮ ነቅፋቹህ፤

ምንደኞቹ፤ሕዝብ-አገር በቅርጫ ያረዳቹህ፤                       

ምረነኛ፤ጉጅሌዎች ‘ስጋ-በስጋ’ የደለባቹህ፤

እርም እምነት የበላቹህ፤በዘር በደም ተሳክራቹህ፤

የወየናቹህ፤በእብሪት በጥጋብ ተወጥራቹህ፤

ጎኁ ቀዷል፤ሊያባራ ነው ምጣችን፤ምጣታቹህ፤

በዓለም መስትዋት የበቀል ቁና ፍዳቹህ፤

ተቆልሏል፤አበሳቹህ፤ልክ ያለፈ ስንክሳራቹህ            

እንዳይነቱ ግብራቹሁ፤የአደባባይ ፍጻሜያቹህ፤

እንደ ቱኒዙ፤ግብጽ፤ሊብያ፤ ነው እጣ ፋንታቹህ።



በቁስላችን እሾህ የምትሰዱ፤የወያኔ፤ቁንጮዎች፤

እሾሁ ሲነጣጠር ወደ አይናቹህ በሚሊዎኖች፤

በሞተ ሰዓት የሟርት ሽብር ከበሮ ደላቂዎች፤

ስንቱን ክቡር ዜጋ ጭቃ ቀቢ፤የአገር ጉድፎች፤

የምታስሩ፤የምትገርፉ፤ወንድም፤ እህት፤ወላጆች፤

ቴሬሪስት፤ድራጊስት፤አልካኢዳ፤አልሸባብ ’ ክሶች፤

የወንበዴ ታርጋ ለጣፊዎች፤ምህረት የማትሹ፤ቂሎች፤

‘ዝና-ስሙ’ ለናንተ እንጂ እድራችሁ አጥፍቶ-አጥፊዎች፤

በፓርላማ፤በ‘አረንጓዴው አደባባይ’፤ባዶ አኬልዳማዎች፤

አይሰሩምና የ‘ጋዳፊ’ መፈክሮች፤የቅጥፈት ስልቶች፤

ወዮላቹህ! ፍጻሜያቹህ፤ለምህረትም-ለተረትም አይመች።



በግንባራችን የደቀናቹህ የወያኔ ‘ጠብ-አንጋቾች’፤

ቃታ ከሳበ ጣታቹህ ዛሬም ልትገድሉ የሕዝብ ልጆች፤

ቅጽፈት ናቹህ፤የሰማይ የምድር ዘላለም ሙቶች፤ 

በህግና በፍትህ ስም የምትቀልዱ ዳኛ ጠበቆች፤

የምታንገላቷቸው፤የትውልድ የሰላም አንኳሮች፤

የአገር-ሕዝብ አውራ፤ንግሥት ናቸውና እስረኞች፤

ዛሬ አስተውሉ፤እንዳይነድፏቹህ ኋላ ‘ሆ!ብለው ንቦች።                  

የኔሰው ገብሬ፤ የዳውሮ ዋርካው፤ ምሁሩ ሻማ፤በራሱ ለቆ፤

የጋረደንን የፍርሃት ድባብ በኃይዎቱ፤ውጋገን ለኛ፤ፈንጥቆ፤

አይሆንምና ደመ-ከልብ ቃል በምድር፤ቃል በሰማይ፤ተሰንቆ፤

እንዲጧጧፍ ትግላችን በየጉልቻው፤አናዳጆችን ማግዶ፤አስጨንቆ።



ወዮላቹህ! ወያኔዎች፤‘ሙባረክን’፤‘ጋዳፌን’ ያዬ፤

እዝነ-ልቦናቹህ፤ካልፈራ፤ዓይነ-ህሊናቹህ፤ካላዬ፤

እንደ ደመራ ልትሞቁን ከዳዳቹህ፤ሕዝብ ሲቃጠል እየታዬ፤

ኢትዪጵያዊ በግፋቹሁ እየጋዬ፤ንስሃቹህ፤ከዘገዬ፤

ወዮላቹህ፤ወገን ጥዶ ያብስላቹህ መስቀል ከቦ እያጋዬ።





እነሆ፤የተዳፈነው እሳት፤ተቀጣጥሏል፤ሰደዱ፤

የተቆጡት፤የቆረጡት፤በየማዕዘኑ፤ሊነጉዱ፤

‘የፎጡን’፤ግንብ፤ሊንዱ፤ቅቦችን ሊያስርዱ፤

ወዩላቹህ!፤ሕዝብ ሃያል ነውና የቁጣ ክንዱ፤

መውረጃቹህ ይኸኔ ነው፤ብትሰሙ፤ብትዱ፤

በግብጽ ‘ሙባረክ’፤ሕዝብ የናቁት፤ ‘አንበሳ’፤

እንደ ጨርቅ አልቀው ሲጓጓዙ በሳንሳ፤

አልጋ ወራሾች፤ተሳስረው ከንጉሱ፤የቁም እሬሳ፤

የሊቢያው ‘ጋዳፊ’፤ሕዝብን በስድብ አርክሰው፤

ተያዙ፤አይጥ ጉድጉድ ተወትፈው፤በቆሻሻ ማኩሰው፤

የሞት-ሞት፤ ሞቱ፤ያልማሩትን ሕዝብ ምህረት ለምነው፤

ወዮላቹህ! ወያኔዎች፤በደመ ነፍስ፤ያላቹህ፤

ቅንጣት እምነት ካላቹህ፤በደል ጥፋታቹሁን፤አምናቹህ፤ 

ግቡ ንስሃ ፤ባለቀ ሰዓት ሽብር አሳሩን ትታቹሁ።


 





ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት መስዋዕቱ፤ ሰማዕታቱ የኔሰው ገብሬ!  ዳውሮ-ዋርካ
በወያኔ በደልና ግፍ ተንገብግቦ ሕይዎቱን በአደባባይ ለወገኑና ለሐገሩ መስዋዕትነት በቁሙ እሳት አጋይቶ የመጨርሻውን የሕይዎት ዋጋ ለከፈለው ጀግናው ወጣት ምሁር የኔሰው ገብሬ መታሰቢያ ትሁንልኝ።

እነሆ አምላካችን ነፍሱን ይማርልን፤ ለወላጅ ቤተሰቦችም ጽናትን ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ቆራጥነትን፤ እሻለሁ፡ ወንድማችን ደመ-ከልብ ሆኖ እንዳይቀር መልዕክቱን፤ተቀብለን መስዋዕትነቱን ግብ እናድርስ፡ የትግሉን ሰደድ አቀጣጥለን፤ለድል እንብቃ፤የሰማዕታቶቻችንን ነፍስ ይማር።

የወጣቱ ምሁር የኔሰው ገብሬ እንደ ቱኒዚያው መሐመድ ቡዋዚዚ ለዓረብ ሕዝብ ተምሳሌ ሆኖ በርካታ ህሕዝቦንችንና አገራትን ከዘመናት ከባርነት ያልተለየ አገዛዝ ነፃነት እንዳቀዳጀና እያቀዳጀም እንዳለው ሁሉ፤ የቆራጡ ወንድማችን ገድልም ለኛ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን እንደኛ በጨካኝ፤ገዥዎቻቸው ስር ለሚማቅቁ፤ ጥቁር አፍሪቃዊያን ወገኖቻችን ሁሉ፤የነጻነት ቀንዲል ይሆናል።

የጐንቻው!      yegonchaw@yahoo.co.uk










No comments:

Post a Comment