የሆሳዕና በዓል ለረዥም ዘመናት እየተመላለሰ በተከበረበት ዘመን ያልተከሰቱ
በዘንድሮው ሆሳዕና ብቻ በወያኔ መንግሥት የተደረጉ አሰቃቂ ክስተቶች
nigatuasteraye@gmail.com
ሚያዝያ ፳፻፭ ዓ.ም.
መግቢያ
በኢትዮጵያ ታሪክ በዓላቶቻችን፤ የገባር ወንዞችን ውሀ እያግበሰበሰ
እንደሚጓዘው ዓባይ ወንዛችን፤ በወራት
ታዝለው የኡደታቸውን ሂደት በመፈጸም ላይ ሳሉ የሚገጥሟቸውን ክስተቶች እየሰበሰቡ የሚቀጥሉ ናቸው። ክስተቶችም ደስታችንና ሀዘናችንን
የምንገልጽባቸው ናቸው። ድርብ በዓላት የሚባል ስምም ተሰጥቷቸውል። ታሪካችንን ሰፊና ጥልቅ ያደረጉት፤ ስነ ጽሑፋችንንም ያዳበሩት
አገራችን በዚህ መንገድ በመጓዝ የሰበሰሰበቻቸው ክስተቶች ናቸው። ከውጭ የሚመጣ ጠላትና ከውስጥም የጠላት ወኪል (የባንዳነት ውርስ
የተሸከመ የባንዳ ልጅ) ሆኖ የሚሰለፈው መጀመሪያ የሚጋጭ ቀደም ብለው
ከነበሩት ክስተቶችን ከተሸከሙት በዓላት
ጋራ ነው።
ከነዚህም ታላላቅ በዓላት አንዱ የሆሳዕና በዓል ነው።
ይህ በዓል ክርስቶስ በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም የገባበት ቀን ነው። ሸፍጠኞች ባለሥልጣናትንም ገስጾ ከቤተ ምራኩብ ያባረረበት
ታላቅ የሞራል ምሳሌ ሆኖ የሚታወስበት ቀን ነው። ያዘለው መልእክት የክርስትና ህይወት በመዋረድ በትህትና የሚኖረውን ጊዜአዊ ኑሮ ሲሆን፤ በውስጡ የተሸከመው
ኃይልና ድል ግን በመጨረሻ ሞትንና መቃብርን አሸንፎ ለዘላለም መኖርን የሚያሳይ ነው።
ክርስትናን ተቀብሎ በክርስቶ የሚያምን ሁሉ እንደኛ ስርአተ ቤተ
ክርስቲያን በነገረ መለኮቱ ተቀርጾ ቅዳሴውንና ቁርባኑን የሚያከናውንበት መጽሐፍ ባይኖረውም፤ መጽሐፍ ቅዱስን እንደየባህሉ በመተርጎም
ያስታውሰዋል። በተዋህዶው ነገረ መለኮት የሚገለጸውን እምነት የምንከተል በየዕለቱ ሥጋውንና ደሙን ስንቀበል የክርስቶስን ሆሳዕናነት
ብንመሰክረውም፤ በያመቱ የምትመጣዋን ዕለተ ሆሳዕናን ግን ክርስቶስ በተግባር በፈጸመባት ቀን በተከሰቱት ምልክቶች እያጀብናት የቅዱስ
ጎርጎርዮስን መጽሐፍ እንጠቀማለን።
ቅዱስ ጎርጎርዮስ ለቅዳሴ ከምንገለገልበት መጽሐፍ ሌላም ለተዋህዶ
ሃይማኖት ነገረ መለኮት ምስክር የሆነ መጽሐፍ አለው። አባ ማትያስ ከንሳስ ላይ መጥተው “በመጻሕፍት ላይ መጻሕፍት ተተክተዋል፤
በሊቃውንትም ሊቃውንት ተተክተዋል” ብለው ነበር።እንዳሉትም ይህ የጎርጎርጎርዮስ መጽሐፍ ተሰርዞ ሌላ የእነሱን ኑፋቄና ክህደት የተሸከመ
መጽሐፍ ካልተተካበት በቀር፤ከቁርባኑ በፊት ከሚነበቡት መጻህፍት አንዱ ነበር። አቡነ ማትያስ “በመጻህፍት ላይ መጻህፍት ተተክተዋል፤ በሊቃውንትም ሊቃውንት ተተክተዋል” ያሉበትን
ወቅትና ምክንያት በሌላ ጊዜ እንመለከተዋለን።
ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ወንጌልን ተንተርሶ የደረሳቸው መጻሕፍት
የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ነገረ መለኮቱን አብራርተው እየገለጹ እግዚአብሔር አክብሮ በአርያው የፈጠረው ፤
ክርስቶስም በሞቱ ያከበረው ሰው፤ በዚህ ዓለም የሚገጥመውን ውጣ ውረድ ያንጸባርቃሉ። በየዘመኑ የተነሱት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንቱም በሌሎች በዓላት እንደሚያደርጉት
በሆሳዕናው ዙሪያ ባጋጣሚ የተከሰቱትን እያንጸባረቁ የወደፊቱን ህብረተ ሰብ ሁኔታ በትንቢት መልክ ይዳስሱታል። ከዚህ ቀደም
ለረዥም ዘመናት እየተመላለሱ በተከበሩት የሆሳዕና በዓል ያልተከሰቱ በዘንድሮው ሆሳዕና ብቻ በወያኔ መንግሥት የተከሰቱ አሰቃቂ ክስተቶች
ብቅ ብለዋል። በጥቅሏ አገራችን፤ ወያኔ በቤተ ክርስቲያናችን
እና በሌሎችም የእምነት ተቋማት ላይ፤ እንዲሁም በአማራውና በተለያዩ የአገሪቱ ዜጎች ላይ የፈጸመውን ግፍና መከራ በዘንድሮው አከባበር ላይ ደርቦበታል። እንደ ቀድሞው ሁሉ በሊቃውንት
አባቶቻችን ቅኔዎች አንጻር የዘንድሮውን ሆሳዕና ስናስታውስ የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት በአገር፣ በህዝብ እና በእምነታችን ላይ የፈጸማቸውን የማይረሱ መታሰቢያዎች
ለምሳሌ፦ ምቱር ፓትርያርክ፡ (“ጭንጋፍ (ምቱር) ፓትርያርክ” እዚህ ላይ በመጫን
ያንብቡ) የዘር ማጥፋት ዘመቻና የመሳሰሉትን አስከፊና ዘግናኝ ትዝታዎችን በዘንድሮዋ ሆሳዕና በአላችን
ላይ ደርቦ አውርሶናል። ይህንንም ከዚህ በታች በተዘረዘሩት አንቀጾች አቀርባለሁ።
፩ኛ፡የቅዱስ
ጎርጎርዮስ መጽሐፈ ቅዳሴ
፪
ኛ፡የሊቃውንቱ እይታ
፫ኛ፡
የህዝቡ እይታ
ለሆሳዕናው ቅዳሴ የምንጠቀምበት መጽሐፈ ቅዳሴ፤ ወያኔ በአገር በእምነት ተቋማት እና በህዝብ
ላያ የሚፈጽመውን አረመኔ ስራ የሚያሳይ ብቻ አይደለም:: ህዝባዊውን የተቃውሞ እንቅስቃሴንም ጭምር ስለሚያሳየን የሆሳዕና ዕለት
የተጠቀምነውን ዓመታዊውን የመጽሐፈ ቅዳሴያችንን ይዘት ለመቃኘት እንሞክር።
፩ኛ፦በሆሳዕና ዕለት የምንጠቀመው የቅዱስ
ጎርጎርዮስ መጽሐፈ ቅዳሴ
መቀበል የለብንም ብሎ በድፍረት ካወጀበት ከዋሸንግተኑ ቅድስት
ማርያም ደፍተራ በቀር፤ ቅዱስ ጎርጎርዮስ የደረሰውን መጽሐፍ በመጠቀም የሆሳዕናን በዓል ያላከበረ ካህን የለም። ይህ የሆሳዕናው
መጽሐፈ ቅዳሴ ኢትዮጵያ አገራችን ቤተ ክርስቲያናችን እና በመፈናቀል ላይ ያሉትን ሁሉ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ የሚያሳይ ተራዛሚ
መነጸር ነው። ይህ መጽሐፍ ነገረ መለኮቱን መሰረት አድርጎ በዓለም ዙሪያ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ዜጋ፤ ወያኔ የሚፈጽመውን
ግፍ የገሰጸበትን መንፈስና ስሜት የተሸከመ መጽሐፍ ነው።
ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት የሚታያቸውን የአካባቢ ችግር ለመግለጽ
የሚነሱት እምነታቸው የተመሰረተበትን ነገረ መለኮት መሰረት፤መነሻና
መንደርደሪያ በማድረግ ነው። በዚህ መርኋቸው በሆሳዕና ዕለት የምንጠቀምበትን መጽሐፍ ያዘጋጀው ቅዱስ ጎርጎርዮስ፤ ክርስቶስን “ክርስቶስ ኢፍጡር ወፍጡር ውእቱ።
ዘሰ ንቤ ፍጡር ውእቱ በእንተ ዘተሳተፈ ሥጋ ድካምነ በሥርአት ዘገብሮ በእንቲአነ። ወንቤ ኢፍጡር እስመ ውእቱ ቀዳማዊ እምቅድም
ዓለም ወውቱ ፈጣሬ ኩሉ ዘሀሎ” ማለትም፦“ክርስቶስ ፈጣሪና ፍጡር ነው።
ፈጣሪ ነው የምንለው፤ ቅድመ ዓለም የነበረ መለኮት ሁሉን የፈጠረና የሚቆጣጠር በመሆኑ ነው። ፍጡር ነው የምንለው ደግሞ ራሱ መለኮት
የፈጠረውን ደካማ ሰውነት በመልበሱ ነው እያለ የመሰከረ ሊቅ ነው። (ሃይ ፴፭፡፪_፰)።”
የሆሳዕና ዕለት የምንጠቀመውን መጽሐ ቅዳሴውንም “ነአኲቶ ለገባሬ ሠናያት ላዕሌነ እግዚአ መሐሪ”(፬) ማለትም፦“መለኮት የፈጠረውን
ሥጋ ተዋህዶ ስላደረገልን ታላቅ ቸርነት እናመስግን” ብሎ በምስጋና
በመጀመር፤“አልቦ አድልዎ በሃቤሁ ወኢነሢአ ገጽ ለአውስኦተ ቃሉ ኢይሐፍሮ ለባዕል እንበይነ
ብዕሉ ወኢይሰድዶ ለነዳይ መንገለ ገጽ ዘአፍአ”(፯) እያለ ሚዛናዊ ፍርዱን ይተነትናል። ማለትም፦ “ይህ ሊቅ የክርስቶስን
መለኮታዊና ሰባዊ ባህርያት በተዋህዶ የገለጸውን ነገረ መለኮት እና ሚዛናዊ ፍርዱን ከገለጸ በኋላ፤ አጥብቆ የሚጠላቸው አስከፊ ነገሮች፤
በሱ እና እሱን በመሰሉ ሰዎች ላይ እንዳይደርሱ ከዚህ በታች በጠቀስኩለት ቃሉ በአጽንኦ ተናገረ።”
“ወኢይቅንየነ
ስህተት አላ አድኅነነ እም ኩሉ ምግባረ እኩይ ወእምህሊናሁ ወጽርአታቲሁ ወመናግንቲሁ ወአብጥሎ
ለዘያሜክረነ። ወስድዶ እምኔነ ከመካከላችንም አውጥተህ አርቀው። ወገስጽ ሁከታቲሁ ዘተከለ ዲቤነ። ወብትክ
እምኔነ ምክንያተ እንተ ትወስደነ”(ገጽ ፪፻፹፫ ቁ፹፬᎗፭) አለ። ይህም ማለት፦ “የቆሻሻ
ረግረግ የተሸከመ ምንጭ፣ የደፈረሰና የቆሸሸ ጎርፍ እንደሚያመነጭ፤ ህሊናቸው በጥላቻ፣ በቂምና በሸፍጥ በቆሸሸባቸው ገዥዎች ከመገዛት
አድነን። የስህተት ረግረግ ከሆነው ሕሊናቸው በሚጎርፈው ጽቡረ ኃጢአት ከመለቅለቅም ሰውረን” ይህች አረፍተ ነገር ያዘለቻቸው
ቃላት ከወያኔ ጋራ በጥቅም የተሳሰረ ሆዳም ካልሆነ በቀር ማንም ኢትዮጵያዊ የሚቀበለው አይደለም። እንዲያውም ይህች አረፍተ
ነገረ የሸከመቻቸውን ኃይለ ቃላት በዓለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያን
እንደመፈክር አርገው እየተጠቀሙባቸው ነው።
·
‘ወጽርአታቲሁ ወመናግንቲሁ’ ለስህተቱ መርሆ ታዛዦች ሆነው የማይተባበሩለትን እያሰረና እየገረፈ ከሚያሰቃይበት ጠማማ ፍርዱም አድነን።
·
‘ሁከታቲሁ’ እርስ በርሳችን
እንዳንተማመን እንድንጠላላ እና በራሳችን አገር ‘ተሰዳጅ’ና ‘ተሳዳጅ’ እንድንሆን የሚያደርግበትን፡ በመካከላችን የዘረጋውን ስርአቱን
·
‘ብትክ እምኔነ’ ‘ነቃቅለህና አፈራርሰህ አስወግድልን’ ይላል።
ቅዱስ ጎርጎርዮስ ግፈኛው ገዥ
የሚፈጽመውን ግፍና የዘረጋውን የሸፍጥ የተሞላውን መርሆ ነቃቅልልን
ብሎ በጸሎት ብቻአላለፈም። የበዳዩ የግፍ ጽዋዕ ቶሎ ሞልቶ የመከራው
ዘመን እንዲያጥር፤ የተበደለው ክፍልም በበኩሉ ሊያደርገው የሚገባውን ነገር እንዲህ ሲል ገለጸ።
በተበዳዩ ላይ የሚፈሰው የበደል ጎርፍ ጽዋው
ሞልቶ የመከራው ዘመን እንዲያጥር
ቅዱስ ጎርጎርዮስ “ወጽርአታቲሁ ወመናግንቲሁ
ሁከታቲሁ” እያለ ግፈኛው ገዥ በተገፊዎች
መካከል የዘረጋው መርሆ ተነቃቅሎ የሚወገድበትን፤ የመከራውም ዘምን ሊያጥር የሚችልበትን ጠቆመ። ማነኛውም ዜጋ በሀገር፤ በህዝብና
በእምነት ተቋማት ላይ የሚሰነዘረውን ግፍና መከራ ከህዝብ ጋራ መካፈል እንጅ ከበደለኛው የሚጎርፈው የኃጢአት ንክኪ እንዳያረክሰው
መጠንቀቅ ሲችል መሆኑን እንዲህ ሲል ያስጠነቅቃል።
“ወናእትት ጽልመተ ኃጢአት እምሥጋነ ወነፍስነ ወመንፈስነ ዘከመ የአትት ጽልመተ ዛህል እምነ አረር ወሐጺን
ወብርት በእሳት ወአቃቂር ውዑያት ዘውእቶሙ ጾም ወጸሎት ወንጽህና ወፍቅር ወትህትና ወሃይማኖት ርትዕት በሥላሴሁ ለእግዚአብሔር”
(ቅ፹፪)ማለትም፦ “በዝገት የጎደፈ እርሳስ ብረት በእሳትና በኬሚካል እንደሚጠራ በተለያዩ የኃጢአት አይነቶች ነፍሳችን ሰውነታችንንና
መንፈሳችንን በጾም በጸሎት በንጽህና፡ በፍቅር በእግዚአብሄር ላይ በተመሰረተው እምነት መጽዳት አለበት።”
በጽርአታት፤ በመናግንንት፤ በሁከታት
መርሆ በሚመራ መንግስት ጭነት ስር ወድቆ በመቃተት ላይ ያለ
ህብረተሰብ የጭነት ዘመኑን አሳጥርልን በሚል ጸሎትና ምኞት ሳይወሰን፤ የመከራው ጽዋ ሞልቶ ከተጫነበት መርግ ድንጋይ
ፈንቅሎ ሊወጣ ይችል ዘንድ፤ በፈጣሪው በራሱ እና በጥጉ ከተሰለፈው ወገኑ ላይ ያለውን እምነት ሊመረምር፡ ሊገነዘብና ሊረዳ ይገባዋል። “ቡሩኩ ለእግዚአብሄር ልዑል
ዘፈጠረ ሰማየ ወምድረ” (ዘፍ ፲፬፡፲፰) እያለ መጠራቱን በማረጋገጥ ለአብራም
የመሰከረለትን መልከ ጼዴቅን የመሰለ ካህን እንደሚያስፈልገው ያመለክታል። ይህንንም ባጭሩ እንመልከተው።
መልከ ጼዴቅና አብራም
መልከ ጼዴቅ በምድር ላይ የሥጋ ዘመድ አልነበረውም። የተወለደበት አድራሻውም አይታወቅም። የትውልድ ሀረግ የለውም።ከዘር፣
ከጎሳ፣ ከግል ክብርና ልክስክስ ነገር የጸዳ ነበር።
·
የሰው ልጅ የዳነበት የክርስቶስ ክህነት የተገለጸበት ምሳሌ መልከ ጼዴቅ ነው።
·
“ዘሩን ያያል ዕድሜውም ይረዝማል(ኢሳ
፶፫፡፲) እንዲል በክርስቶስ የሚያምን ሁሉ የህይወት መነሻ የዘር ግንድ አድርጎ እንዲቆጥር
የተደረገውም ከዚሁ ክህነታዊ ተልዕኮ ነው። (ገላ ፫፡፲፮_፳፪)
ቅዱስ ጎርጎርዮስ ወደ ኋላ ታሪክን
በመቃኘት መጽሐፍ ቅዱሱን ተንተርሶ ያዘጋጀው መጽሐፍ፤ እኛ (ካህናት) ዜማ አልብሰን በቤተ መቅደስ እንጉርጉሮ ብቻ ተወስኖ ከብዙኃኑ
ጆር እንዳይደርስ፤ ወይም ከተግባር ለይተን የመተዳደሪያ ሙያ አድርገን እንድንጠቀምበት አልነበረም። እራሱ ደራሲው ቅዱስ ጎርጎርዮስም
የባህሉን ዜማ አልብሶ እኛ በምንጠቀምበት መንገድ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ያንጎራጎረው አልነበረም። (ለልማድ በልማድ ብቻ አይወሰን ለማለት እንጅ ለቅዳሴ አገልግሎት የሚደረገው ይቁም ማለት አይደለም) የቅዱስ ጎርጎርዮስ
ምኞት አቅራቢው ካህን ተረድቶ የሰሰሚውን አዕምሮ ቀይሮ አንባቢውም፡ ሰሚውም የሆሳዕናውን ምስጢር እየተገነዘበ አካባቢውንና የራሱን
ህልውና መመርመር እንዲችል የሰጠው ትምህርት ነበር።
ሊቁ ጎርጎርዮስ በመልከ ጼዴቅና በአብራም መካከል የተከናወነውን
ሲገልጽ “ቡሩኩ አብራም ለእግዚአብሄር ልዑል ዘፈጠረ ሰማየ ወምድረ” (ዘፍ ፲፬፡፲፰)
ማለትም፦ “ሰማይንና ምድርን ለፈጠረ አምላክ ተለይተህ ጸጋና ሞገስ የተቀዳጀህ”
እያለ ቀደም ብለው የነበሩትን መልከ ጼዴቅንና የተባረከውን አብራምን
ጠቀሰ።
አብራም መልከ ጼዴቅን ከማግኝቱ በፊት “ለሌሎች በረከት ትሆናለህ”( ፲፪፡፪) ተብሎ ተጠርቷል። መልከ ጼዴቅ ይህን በመመልከት
“ወመልከ ጼዴቅ ካህኑ ለእግዚ ወንጉሠ ሳሌም አውጽአ ህብስተ ወወይነ ወባረኮ ለአብራም
እንዘ ይብል ቡሩኩ አብራም ለእግዚአብሄር ልዑል ዘፈጠረ ሰማየ ወምድረ”
(ዘፍ ፲፬፡፲፰) ማለትም፦ የእግዚአብሔር ካህን የጽድቅና የሰላም ንጉሥ
ህብስትና ወይን ይዞ አብራምን ተቀበለው ሰማይንና ምድር ለፈጠረ አምላክ
የተለየህ እያለ ከፍ አድርጎ አከበረው። ከዚያ በኋላ “ወይቤሎ አብራም ለንጉሠ ሰዶም አሌዕል እዴየ ሃበ እግዚአብሄር ልዑል ዘገብረ ሰማየ ወምድረ
(፳፪) ማለትም፦አብራም ሰማይንና ምድርን ለፈጠረ ለእግዚአብሄር እጄን አስማርኬያለሁ
እያለ ለሰዶም ንጉሥ ተናገረ።
ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ቀጠለና “አብራም ነስአ መቅረጸ ወቀረጸ አጽፋረ እደዊሁ ወእገሪሁ ወስእርተ ርእሱ”(፹፪) ማለትም፦
አብራም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ የሆነ ሰውን የሚጎዳ የአራዊት ባህርዩን ከራሱ ለማስወገድ ያደረገውን ውሳኔ ገለጸ። ጎርጎርዮስ
በመልከ ጼዴቅና በአብራም መካከል የተከናወነውን እንደ ምሳሌ በመጠቀም ከገለጸ በኋላ፤ እራሱንም በመጨመር የሆሳዕናውን ቅዳሴ ያነበበና
ያዳመጠ ሁሉ የአብራምን ምሳሌ ይጠቀም ዘንድ “አንጽሀነ በፍጹም ነፍስ ወሥጋ ወመንፈስ
ወሕሊና ከመ በልብ ንጹህ ወበፍርሀተ ነፍስ ንንብብ ዘእንበለ ጽርአት ወኢፍርሃት ከመ ንበል ኦ እግዚአብሔር አብ ቅዱስ
አቡነ ዘበሰማያት(ቅ ፹፫) እያለ ሁሉም ከሞራል ውድቀት እንዲጠነቀቅ አሳሰበ። ማለትም፦ “በአምላካችን ፊት ቆመን ቅዳሴውን ለማንበብና ለማዳመጥ በድፍረት እውነትን ለመመስከር የበቃን
እንሆን ዘንድ መጀመሪያ እራሳችን የወደቅንበትን የሞራል ዝቅጠት መመልከት እንዳለብን ሰበከ።”
ጎርጎርዮስ እንደገለጸው ለተገቢ
ፓትርያርክ ጥሪና የክብር አስራት ማቅረብ የሚገባው ሰው፤ መጀመሪያ በእግዚአብሄር የተጠራ ሰው መሆን አለበት። ይህን ጥሪ ማሰማትና
ከጠራው ሰው የበረከት አስራት መቀበል የሚችል ካህንም ከዘር፤ ከጎሳ፣ ከአድለወና ከገንዘብ የተላቀቀ መሆን አለበት። ከዚህ አይነት ካህን በረከት ለመቀበል የአክብሮት አስራት ማበርከት የሚችልም
ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ “ወነሥአ መቅረጸ ወቀረጸ አጽፋረ እደዊሁ ወእገሪሁ ወሥእርተ ርእሱ”(፹፪) “አብራም የእጅና የእግሩን ጥፍር ቆረጠ።” እንዳለው፤ በውስጡ የነበረውን
የአራዊት ባህርይ ስሜት ማስወገድ ይኖርበታል። ይህ ቅዱስ ጎርጎርዮስ የደረሰው የሆሳዕናውን በዓል ያከበረንበት መጽሐፈ ቅዳሴያችን፤
በዕለተ ሆሳዕና አንባቢው ክህንና ሰሚው ህዝብ በተግባር ንዲያውለው የተነበበ ነው።
በጎርጎርዮስ መነጽር ዛሬ አገራችን ቤተ ክርስቲያናችን ያሉበትን እና
ምን አይነት ክህናት እንደገጠማቸው ለመመልከት እዚህ ላይ ላቁምና፤ በሆሳዕናው በዓል ዙሪያ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት በትንቢት መልክ
ወደ ተናገሯቸውን ቅኔዎች እንሻገር።
፪ኛ፦ ጥንታዊያን ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት
በሆሳዕናው አካባቢ ምን አሉ?
ዓበይት በዓላት እየተቀበባሉ ዓመትን በሚደፍኑት ወራት ላይ ተጭነው
በአካባቢው የሚፈጠሩትን አጋጣሚ ክስተቶች እየተሸከሙ ነው ብለናል። ክስተቶችን በየአካባቢ የሚኖረው ህዝቡ በሚችለው ቋንቋ
ሊቃውንቱም በስነ ጽሁፍ ሁሉም በየደረጃቸው ለሚቀጥለው ትውልድ ያንጸባርቃሉ። በሆሳዕናው በዓልም ከኛ በፊት የነበሩት ሊቃውንቱ ሁሉ
አካባቢያቸውን ተመልከተውበታል። ከብዙ ኢእትዮጵያውያን ሊቃውንት ሁለት መጋቢ መርሻንና አቶ የተሻ ወርቅ የተባሉት የቤተ
ክርስቲያናችን ሊቃውንት ያፈለቌቸውን ቅኔዎች ለምሳሌ ያህል እጠቅሳለሁ።
፩ኛ፦መጋቢ መርሻ የተባሉ ሊቅ፦በሆሳዕና
ዕለት በድንጋዩና በሕጻናት ላይ የተከሰቱትን እየጠቀሱ፤ የህብረተ ሰቡን ድካም አንጸባርቀዋል። መጋቢ መርሻ የሆሳዕናው ምስጢር ያልማረካቸውን
ፈሪሳውያንን ባንድ ድግስ ላይ ሳይጋበዝ እንደተገኘ ወይም ለዝግጅቱ ባእድ እንደሆነ ለማሳየት በሆሳዕናው ዕለት የተጠቀሱትን ድንጋዮች
ምሳሌ አድርገው ገልጸዋቸዋል። ይህም ብቻ አይደለም። ባለ ቅኔው “ሰው ትላንት የተመገብኩት በቃኝ ብሎ ምግብ ቢያቋርጥ በሰውነት
ላይ የሚያስከትለውን ድካም እየገለጹ፤ በአንጻሩ ሰው ፈጣሪውን ከማሰብ ቢያቋርጥ የሚያስከትለውን የመንፈስና የሞራል ድካም በመግለጽ
አታቋርጡ ይላሉ።
እግር የጣላቸው ድንገት ደራሾች የሆሳዕናን መልዕክት ባለመረዳታቸው
ለነፍስና ለመንፈስ ጠቃሚ የሆነውን ቋሚ ምግብ ትተው ለሥጋቸው በሚጠቅመው ምግብ ላይ ብቻ አተኮሩ። የዛሬ ሰዎች የነገ አፈሮች ነንና
ሞት ሳይቀድመን እንብላ እንጠጣ ይላሉ”።
“ይቤሎሙ ሆሳዕና ለአዕባነ ደብር ሀለፍት፤
ኢትበሉ
ለጌሰም ቅዳሴ ምግበ ዕለት።
ወለሆሳዕና ይብልዎ ህብስተ ሕይወት፤
ንብላእ ወንስተይ ጌሰመ ንመውት።
አምጣነ
ዘዮም ሰብእ ወእንተ ጌሰም መሬት።
ንብልአ ወንስተይ ጌሰመ ንመውት።”
፪ኛ፦ አቶ የተሻ ወርቅየተባሉት ኢትዮጵያዊ ሊቅም፦ በምቀኝነትና በበቀል በሽታ የተመረዘው ልባቸው በመላ ሰውነታቸው
የሚያሰራጨው ደም መላ ሰውነታቸውን መርዞታል። እነዚህን ሰዎች ከያዛቸው አባዜ ለመፈወስ በተመሳሳይ በሽታ ለተለከፉ ሰዎች የሚሰጠውን
መድኃኒት ቢሰጣቸው በቀላሉ ሊፈውሳቸው ይቅርና፤ በአህያ የተጫነ መድኃኒት ቢሰጣቸውም አይፈውሳቸውም። እስከ መቼውም የሚፈወሱ አይደሉም”አሉ።
“ለአይሁድሂ እለ ሀሙ በደዌ ቅንአት ዘቁስል፤
ኢይበቁኦሙ ሆሳዕና ዘተጽእነ በእዋል፤
አኮኑ ጽኑዕ ደዌ ልቦሙ በቀል፤
ወእስከ ማዕዜ ኢይትነስኡ በማየ ገቦ ወዘመስቀል”
የአቶ የተሻ ወርቅን
ቅኔ የበለጠ ግልጽ ለማድረግ፦ ሆሳዕና (መድኃኒት) የተባለው ክርስቶስ በአህያዋ ላይ ተቀምጦ ወደ ፈሪሳውያን መጥቷል። ግን
አምነው ስላልተቀበሉት ሊድኑ አልቻሉም። አንድ የመድኃኒት አይነት በተመሳሳይ በሽታ የታመመውን ሁሉ ሰው ሲፈውስ፤ እንዳጋጣሚ አንድ
ሰው በተመሳሳይ በሽታ ተለክፎ መድኃኒቱ ቢሰጠው ሊፈውሰው ይቅርና፤ የአህያ አቅም የሚሸከመው መድኃኒት ቢሰጠውም ሊፈሰው አልቻለም”ብለው
ፈሪሳውያንን ገለጿቸው።
የመጋቢ መርሻ እና የአቶ የተሻ ወርቅ ቅኔዎች ባጭሩ ሲቀርቡ፦
“ህዝባዊ ዝምድና የሌላቸው፤ አልፎ ሀጆች፤ የዛሬውን ሆድ መሙላት እንጅ የነገውን የማያስቡ አውዳሜዎች፤ መሆናቸውን ይገልጻል። አቶ
የተሻ ወርቅም እምነትና ማስተዋል ያቃታቸው ከሀዲዎች በምቀኝነት በቅናትና በተንኮል የተመረዘ ደም ልባቸው በማሰራጨት መላ ሰውነታቸው
ተመርዟል:: ይህ በሽታ በቀላል መድኃኒት ሊፈወስ ይቅርና በአህያ የተጫነ መድኃኒት ሊፈውሰው አይችልም” ሲሉ የገለጹት የዘመናችን
መሪዎች የተመረዙበትን ቂም፡ጥላቻ ሊፈውሰው የሚችል መድሃኒት በ፳፪ ዓመት እንኳን ለማግኘት አለመቻሉን ይጠቁማል።
ቅዱስ ጎርጎርዮስ በድረሰቱ ያዘጋጀውን መጽሐፈ ቅዳሴያችንና የሊቃውንቱን
ቅኔዎች እንደ ጧፍ መብራት ይዘን በጨለማ ውስጥ ወደ አለው ህብረተሰባችን በመግባት ያለበትን ጠቅላላ ሁኔታ የዘንድሮውን ሆሳዕና
ያከበረበትን ሁኔታ ስንመለከተው፤ አባ ማትያስና የሳቸው ተከታዮች ካከናወኑት ቅዳሴ ጋራ ይጋጫል።ከዚህ በታች የምገልጸው በኖሮዌ
በደቡብ አፍሪቃና በአሜሪካ ውስጥ በተለያዩ አገሮች ተበትነው የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ከፈጸሙት ተልእኮ ጋራ ግን በሚገባ ተስማምቷል።
፫ኛ፦ከሆሳዕናው በዓልጋራየተስማማው
የኢትዮጵያውያን እንቅስቃሴ
በዚህ ዘመን ያለን ካህናት የሆሳዕና ዕለት ያነበብነውን የመጽሐፈ ቅዳሴ ይዘት በሊቃውንት አበው
ትርጓሜ ስልት ብንረዳው፤ ቀኖና የሚለውንም ብንገነዘበው፤ ሊቃውንቱም በቅኔያቸው የገለጹት ቢገባን፤ በህዝባችን፤ ባገራችን፤ በየገዳማቱና
ማምለኪያ መካናት ዘመቻ በማድረግ ላይ ያለውን የወያኔን መንግሥት ከማውገዝ ባላፈገግንም ነበር። ከዚያም አልፈን ከሆሳዕናው መጽሐፈ
ቅዳሴያችን ጋራ በመጋጨት ላይ ያለውን “የነ አባ ማትያስን እኩይ ተግባር መቃወም ማለት ፖለቲካ ነው” እያልን ለሆዳችንና
ለጌጣችን ከህዝብ የምንዘርፈው ገንዘብ እንዳይቋረጥብን ብቻ ቅዳሴውን ከተግባር ገንጥለን ቀድሰናል፡ ሰብከናል እያልን ገንዘቡንም
በመዝረፍ በህዝብ ላይ ተደራራቢ በደል ባልፈጸምንም ነበር። [በቤተክርስቲያናችን ላይ የተደገዉን የማጥፋት ዘመቻ የሚከተሉትን
አንባቢ ይመልከት፦
በህዝባውያን መገናኛዎች እንደሰማነው
በተለያየ ቦታ ተበትኖ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ዜጋ የወያኔ መንግሥት የሚፈጽመው መከራ እንዲያቆም ያሳየው ተቃውሞ፡ ያሰማው ድምጽ አምላክን
የቀደስንበት መጽሐፈ ጎርጎርዮስ የገለጸውን ክርስቶስ በሆሳዕናው በዓል የፈጸመውን ተግባር ተርጉሞታል።
በኖሮዌ ከተማ በተካሄደው ትእይንት (እዚህ ላይ በመጫን
ያንብቡ)
የወያኔ መንግስት ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረበት ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎችና ወቅቶች በህዝብ ላይ የፈጸማቸውን ግፍና መከራ ከዚህ
በታች የተዘረዘሩትን
፩ኛ፡ በ85 በአርባ ጉጉና በበደኖ
፪ኛ፡ በ93 በመላ ኦሮምያ ክልል
፫ኛ፡ በ97 ምርጫ የተጨፈጨው
፬ኛ፡ በ2ሽ በጋምቤላ
፭ኛ፡ በ2ሽ1 በኦጋዴን
፮ኛ፡ በ2ሽ3 በአፋር
፯ኛ፡ በ2ሽ4 በሲዳማ
፰ኛ፡ በ2ሽ5 ቤኒሻንጉል ጉምዝና ባካባቢዋ የፈሰሰውን ደም እየገለጸ
ጸሎት እናድርግ። ከዚያም ስለ አባይ ግድብ ከመነጋገራችን በፊት፡ በናንተ የሚጎርፈው የኢትዮጵያውያን ደምና እንባ የሚገደብበት
መንገድ እንነጋገር ብሎ አንድ ዜጋ የተናገረው ሊቁን ቅዱስ ጎርጎርዮስን ይመስል ነበር።
ይህ ዜጋ በቤተ መቅደስ ሲነበብ ያረፈደውን የጥንት ሊቃውንት
በቅኔያቸው የገለጹትን በራሱ አማረኛ ገልጾታል።አንድ ወጣትም የወያኔን
መንግስት ወክሎ ወደ ተቀመጠው ሰው በጣቱ እያመለከተ “ተነሰ አንተ! አንተንም ይመለከትሀል!”
ሲል ለጸሎት ሰውነቱ የዛለውን ሰው ለመቀስቀስ “ተንስኡ ለጸሎት” የሚል
ዲያቆን ይመስል ነበር። ባዳራሹ የተሰበሰበው ሁሉ ዜጋ ተሰጥኦውን ለመመለስ ባንድ ድምጽ ተቃውሞውን እያስተጋባ ከተቀመጠበት ተነሳ።
በዚያ ቦታ ያልታየው ዘንባባ ብቻ ነበር። ስድስት ሆነው የመጡ የኖሮዌ ፖሊሶችም የህዝቡንና የወያኔ ወኪሎችን ከቃኙ በኋላ እምነተ
ጎደሎ የሆኑትን የወያኔን ወኪሎች እነ ወይዘሮ መብራት በየነን “ጻኡ”
ብለው ለማስወጣት እራሳቸውን ወደ ዲቁና አገልግሎት ለወጡ። በጅራፍ እየገረፈ ከምኩራብ ያባረረውን የክርስቶስን ተልእኮ በተግባር ከፈጸሙት ኢትዮጵያውያንም ጋራ በመስማማት የወያኔን
ልኡካን ካዳራሹ ለማስወጣት ክህዝቡ ጋራ ተሰለፉ። “አጋንንት ገረሩ ለነ” ያሉት የሐዋርያት አድናቆት ትዝ አለኝ። ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ “የዘራፊዎች ዋሻ አደረጋችሁት”(ማቴ ፳፩፡፲፫) እያለ እንዳበረራቸው፤ ኢትዮጵያውያንም የወያኔ ወኪሎችን ሌባ!
ሌባ! ሌባ! በሚል ግርማ በተመላው እንቅስቃሴ ከተቀመጡበት ወንበር ገልብጠው አበረሯቸው። ይህም ህዝባዊ እንቅስቃሴ በቅዱስ ጎርጎርዮስ
መጽሐፍ እና በሊቃውንቱ ቅኔ የተገለጸውን ክንውን ገልጾታል።
እኛ ካህናቱ የቅዱስ ጎርጎርዮስን መጽሐፍ በዜማ ሸፍነን ህዝቡን
ካደነቆርንበት ቅዳሴያችን ይልቅ፤ (ይህን ስል እኛ ካህናት ቅዳሴውን ከተግባር አንለየው ለማለት እንጅ ለመንቀፍ አይደለም) የህዝቡ
እንቅስቃሴ ትክለኛውን ትርጉም እንደተከተለ
“እምክህነትሂ ወእምቅዳሴ አመ ሆሳዕና በዓል፤
ምሁራነ ኦሪት ካህናት ለእመ ተከልኡ በወንጌል።
ዘኢተምህሩ አዕባን ግብረ ቅዳሴ በቃል፤
ተደለው ለቅዳሴ ቅዳሴ እምይትኀጎል” ሲሉ ጥላሁን ገብረ መድኅን የሚባሉ
የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ የደረሱት ቅኔ ገልጾታል።
በሆሳዕናው ዕለት ህጻናት ሳይቀሩ የሚደረገውን ሲያንጸባርቁ፤
ተሽሞንሟኞች ፈሪሳውያን ሊተባበሩ ይቅርና ዝም አሰኛቸው ብለው ክርስቶስን ጠየቁት። ክርስቶስም መልሶ “እነሱ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮሀሉ አላቸው።”(ሉቃ ፲፱፡፵) ያለውን መሰረት
በማድረግ ጥላሁን ገብረ መድኅን የሚባሉ ሰው ከላይ የጠቀስኩትን የተቀኙት በወያኔ ዘመን ያለው ህዝባዊ እንቅስቃሴ የካህናቱን ቦታ
እንደወሰደ ይገልጸልናል።
በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በወይዘሮ መሰረት ቢተው የሚመራውን ግብረ ኃይል ፈጥሮ “ታሪክ በመበረዝ ሃይማኖትን በማናናቅ ህዝቡን በማፈን
በህዝብ ላይ ያነጣጠረውን ፖለቲካ ከሥር ነቅሎ ለመጣል እና ይህን እኩይ መርሆ በመጠቀም ወገንና አገርን በማጥፋት ላይ ያለውን የወያኔን
መሪዎች ለፍርድ ለማቅረብ እንተባበር” እያለ የተማህጽኖውን
ድምጽ አሰማ። በተቃራኒ ግን የሲኖዶሱ ጸሐፊ ነኝ የሚሉት አባ
ሕዝቅኤል በቅድስት ድንግል ማርያም ስም እየማሉ “ስለዋልድባ ካንተ መስማቴ ነው” እያሉ ሲናገሩ ሰማናቸው። (ለመስማት እዚህ ላይ በመጫን ያዳጡ ESAT_Radio_Tue_30_Apr_2013) እናንተ ባትናገሩ
ሕጻናት ወይም ድንጋዮች ይናገራሉ” ብሎ ክርስቶስ የተናገረው ተግባራዊ ሆነ። (15 መነኮሳት የተናገሩትንም ለመስማት እዚህ ላይ በመጫን ያዳጡ ESAT_Radio_Mon_22_Apr_2013)
ከነ አባ ሕዝቅኤል ይልቅ የሆሳዕነውን መጽሐፈ ቅዳሴያችንን ክብርት
ወይዘሮ መሰረት ቢተው “በህዝብ ላይ ያነጣጠረውን ፖለቲካ ከሥር ነቅሎ ለመጣል” እያሉ ያቀረቡት ጥሪ፤ “ወአብጥሎ ለዘያሜክረነ።
ወስድዶ እምኔነ ወገስጽ ሁከታቲሁ ዘተከለ ዲቤነ። ወብትክ እምኔነ ምክንያተ እንተ ትወስደነ”(ገጽ
፪፻፹፫ ቁ፹፬-፭) ማለት፦ እርስ በርሳችን እንዳንተማመን እንድንጠላላ እና ተሰዳጅና ተሳዳጅ እንድንሆን የሚያደርግበትን
ስርአቱን በመካከላችን የዘረጋውን መርሆ ነቃቅለህ አፈራርሰህ አስወግድልን” ከሚለው ከቅዱስ ጎርጎርዮስ መጽሐፈ ቅዳሴ ጋራ ተስማማ።
ከዋልድባ ገዳም የተባረሩት አባት ሲናገሩ እንደተሰሙት “ስለቤተ
ክህነቱ ስታነሳብኝ ደሜ ይጎሻል። እነሱ ከሆዳቸው በቀር ስለሃይማኖት ስለ ቤተ ክርስቲያን ስሜቱም የላቸውም” (ለመስማት እዚህ ላይ በመጫን ያዳጡ ESAT_Radio_Tue_30_Apr_2013) ቀጠሉና “ኩታ መልበስ
መቌሜ ተደግፎ መቆም ከበሮ መደብደብ አማኝነትን አይገልጥም ሃይማኖትን አገርንና ቅርስን አያስጠብቅም” እያሉ የተናገሩት ክርስቶስ
ህጻናትን ዝም አሰኛቸው ብለው የተናገሩትን ፈሪሳውያንን በገሰጸበት ቋንቋ ዛሬ ካህናት ንነ፤ ሰባኪዎች ነን፤ ጳጳሳት ነን የሚለውን
ሁሉ ገሰጹት።
ጎርጎርዮስ በመጽሐፈ ቅዳሴው እንደገለጸው፤ መጀመሪያ በእግዚአብሄር
ከተጠራ ከአብራም አስራት የተቀበለው የዘርና የጎስ ችግር የሌለበት መልከ ጼዴቅ ነው። በዘመናችን ያሉት ሰዎች በዘር በሽታ ያበዱ
በመሆናቸው ዘረፋ እንጅ አስራት መስጠትና መቀበል የበቁ አይደሉም።
የደርግን መንግስት በየሳምንቱ ሲያወግዙ የነበሩት አባ ማትያስ፤
አገርን፤ ቤተ ክርስቲያንን፤ ህዝብን የገደለውንና እየገደለ ያለውን የወያኔ መንግስት በጎሰኝነት ስሜታቸው ምክንያት አጠፋ ሲሉ አንዲት
ቀን እንኴ ተሰምተው አያውቁም። ጎርጎርዮስ “ወነሥአ መቅረጸ ወቀረጸ አጽፋረ እደዊሁ ወእገሪሁ ወሥእርተ ርእሱ”(፹፪) “አብራም የእጅና የእግሩን ጥፍር ቆረጠ።” ሲል ጎርጎርዮስ ለተናገረው
በተቃራኒው የተሰለፉ ናቸው። ወደ መንበሩ ፓትርያርኩ ጎትተው ያስቀመጧቸውም ሰዎች ገና ከአራዊትነት ባህርያቸው የተላቀቁ አይደሉም።
ሰላም የሚፈልጉ ሁሉ ይሰቀሉ የሚሉ በውስጣቸው ያለው የአራዊት ባህርይ ስሜት የሰው ደም ከመጠጣትና ሥጋ ከመብላት ገና ያልበረደላቸው
እነ አባይ ጸሐይዬ: እነ ስብሀት ነጋ ናቸው።
አባ ማትያስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ “ንዑ አኃውየ እነግረክሙ ፈሪሃ
እግዚ እለ ትፈቅዱ ትርአዩ መዋዕለ ሠናያተ ንክላእ ልሳነነ እምእኩይ ወከናፍሪነ ከመ ኢይንብብ ጉሕሉት” (ቅ ፲፮) ማለትም፦
ወንድሞቻቸውን ካንደበታቸው ጽርፈትን በትዕቢት ቅፈተ ሥጋቸውን ያሳበጡትን የምንሰራው ስራ መልካም አይደለም ትውልድ የማይዘነጋው
ኃጢአት ነው ብለው ገስጸው የሚመልሱ አይደሉም። ለክርስቶስ ክህነታዊ ተልእኮ ምሳሌ በተጠቀሰው በመልከጼዴቅ መስመር የመጡ ፓትርያርክ
አይደሉምና፤ በደም የተነከሩትን በዘርና በጎሳ መካከል ዘላለማዊ በቀል በመትከል ላይ ያሉትን መክረው እምቢ ካሏቸው አውግዘው የሚመልሱ
አይደሉም። ይልቁንም የሚያባብሱ እንጅ።
ታዲያ የትኛው ነው የሆሳዕናን በዓል አንድም ብሎ በተግባር የተረጎመው? የቤተ ክርስቲያናችንን መመሪያ ሰብረው በመግባታቸው
መመሪያችን ምቱር የሚላቸው አባ ማትያስ? ወይስ የእመቤታችንን ስም እየጠራ ስለዋልባ አልሰማሁም እያለ በሀሰት የሚምል አባ ህዝቅኤልን
የመሰለ ሰውየ መሳይ የተሰበሰበበት ሲኖዶስ? ወይስ ለደመወዝ ለመተዳደሪያ
በቤተ መቅደስ ተስግስጎ ህዝብ እየተሰቃየ እየተፈናቀለ አንዲት ነገር ሳይተነፍስ የጎርጎርዮስን መጽሐፍ አነብንቦ
ህዝብ ያሰናበተው ካህን ነኝ ባይ? ወይስ ወያኔ በአገር በህዝብና በሃይማኖት የሚያደርሰውን በግልጽ በመቃወም በተግባር የተረጎመው
ዜጋ? የዘንድሮው የሆሳዕና በዓል ይህን ክስተት ተሸክሞ አለፈ።
“እንዲህ ያለ ፓትርያርክ አይተን አናውቅም” በምትለው ጦማር
እንገናኝ እያልኩ እሰናበታችኌለሁ።
ይቆየን።
ለሌሎች ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ጦማሮች የሚከተለዉን
ድረ-ገጽ ይመልከቱ::
No comments:
Post a Comment