Thursday 28 November 2013

እጅ-ለጅ!

እጅ-ለጅ!
ወንድሙ መኰንን፣ ከብሪታኒያ

የፊት ጉዱን ረስቶ፣ ከረሀብ መትረፉን፣ የሙሴን ውለታ
የእናት ጡት ነካሽ ልጅ፣ ፈርዖን በእስራኤል፣ ክንዱን አበረታ!

መሄጃ ያጣህ ዕለት፣ ኢትዮጵያ አትርፋልህ፣ ዕምነትህ እንዳትጠፋ!
ስማን እንጂ ሳውዲ፣ አንተም እንደፈርዖን፣ ታዋርዳት ገባህ፣  አገሬን በይፋ?

ደግ እናት ነበረች፣ አንጀቷ የሚራራ፣ እግዚአብሔርን ፈሪ
ኢትዮጵያ አገሬ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ የሰው ልጅ አፍቅሪ
አቅፋ የምትደብቅ፣ የተሰደደውን፣ ላትሰጥ ላባራሪ
ዕድሜለወያኔ፣ ዛሬ ግን ቀን ጥሏት፣ ለጆቿ ተርበው፣ ሆኑ ጦም አዳሪ።

አይ ስምንተኛው ሺ፣ የዘመን ጎዶሎ፣ ያመጣብን ጣጣ
አንተም ቀን አልፎልህ፣ አሽከርና ገረድ፣ ከኢትዮጵያ ታስመጣ?

እሱስ እሺ ይሁን፣ ምነዋ መርሳትህ፣ ያቺን ክፉ ዘመን
ጌዜው ተለዋውጦ፣ እኛም ለአንድ እንጀራ፣ በእጅህ ላይ ሲጥለን።
ዕምነትክን ረስተኸው፣ ትዕዛዙን ጥሰህ፣ እግዚአብሔርን መፍራት
እንዳንተው ተሰደው፣ ወደ አንተ ቢሚጡ፣ ወንድሜን ገድለኸው፣ እህቴን ደፈርካት?

አገር ሻጭ ወንበዴ፣ ፔትሮ ዶላር ታጥቆ፣ ከሀዲ ቢመጣ
ወይኔ እንዲህ እንዋረድ፣ እግዚአብሔር የት ሄደ፣ ከአዘቅጥ እንዳንወጣ?

ይነጋል ሌሊቱ፣ እንደጨለመ አይቀር፣ በርታ አይዞህ ተጋገዝ
ከወረደት ለመውጣት፣ ማንም አይደርስልህ፣ ኢትዮጵያዊ ሁሉ፣ እጅ-ለጅ ተያያዝ::
----------------------------------------------------------------
ምስጋና ለአለባቸው ደሳለኝ፣ መቅረጸ-ምስል ድምጹን እንድጠቀም ለፈቀደልኝ

No comments:

Post a Comment