Emperor Menelik |
Empress Taitu |
አድዋ
02/03/14 ከመራሹ
ሞፈሩን ቀምበሩን ምሰሶ አስደግፎ
የሃገሩን ፍቅር በልቦናው አቅፎ
ከምኒሊክ ጦር ጋር ጀግናው ተሰልፎ
ምሽትና ልጆቹን ጣፋጯ ጎጆውን
ወደኋላው ትቶ ቋጠረና ስንቁን
ወድሮ ጦሩን አንግቦ ጋሻውን
አሳዶ ሊቀጣ ጣሊያን ወራሪውን
እመር እመር አለው ጋራ ሸንተረሩን
ባዶ እግሩም ደፈረው ቋጥኝ አረንቋውን
ንዳድ በረሃውን
ብርድና ቁርፋዱን
ተቋቁሞ ወጥቶ ሊደቁስ ጠላቱን።
ኦ !! እናት
ሃገሬ የነፃነትና የፍትህ መረዋ
ደሙንም አፍሦ
አጥንቱን ከስክሶ ላንቺ የተሰዋ
በታሪክ መኩሪያችን
በድል አምባ አድዋ
ለቅኝ ገዥዎች
የሽንፈትን ፅዋ
በጥብጦ የጋተው
ምኒልክ እምዋ
ስንኩል ስራቸውን
ግብዓቱን ፈፅሞ
በታሪክ መዛግብት
ተከትቦ ታትሞ
ሲወሳ ይኖራል
ዛሬም ዘወትርም
ተምሳሌው ላፍሪካ
ተምሳሌው ለዓለም።
Ras Mekonnen |
ሐገር ብቻ ሳይሆን ጦሩንም የመራ
እምዬ ምኒሊክ አሞተ ኮስታራ
የጦር መሪም ሆኖ አዛኝ እንደ እናቱ
ውሳኔን ከቴዎድሮስ መላን ከጣይቱ
አጣምሮ አዋሕዶ ለድል ያደረሳት
እምዬ ምኒሊክ ከወራሪ ፋሽስት ከሶላቶ አዳናት።
ኦ !! እናት
ሃገሬ የነፃነት ደወል የፍትህ መረዋ
ከአፅናፍ እስከአፅናፍ
ተዛምቶ ዝናዋ
በታሪክ ክስተቱ
በመኩሪያዋ አድዋ
ቅኝ ገዢን ሁሉ
ተስፋ ያስቆረጠ
ጭራን አስቆልፎ
ዱር ያስፈረጠጠ
የነፃነት ብርሃን
ድል ያስቆነጠጠ
የምኒልክ ሐገር
በኩራት ናጠጠ።
ምን ይልክ እያለ ሲጨነቅ ሶላቶ
ጦሩ ሲቁነጠነጥ ከውጊያ ዘግይቶ
እራሱ መጣበት እየበላ አንኩቶ
ጭለማው ደቅድቆ እረዝሞ ለሊቱ
ሰማይ ተገለጠ ብቅ አለች ጣይቱ
ምንጩን አደረቀች ዘጋች ከብልቱ
እጃቸውን ሰጡ በውሃ ጥማቱ
እንግዲህ ፈረንጆች ምንም ቢዶልቱ
አልቀረላቸውም ውርደቱ ሽንፈቱ
ላንዴም ለሁለዜም ተሰነባበቱ
አልገዙም አገሬን እንደተመኙቱ።
ዘመን ተቆጠረ
ይህ በእንዲህ አልፈ
ክብረ በዓል ሆኖ
ጀግና ተሰለፈ
ግጥም ተነበበ
ቅኔም ተዘረፈ
የጀግና ደርት
ላይ ሜዳል ተለጠፈ።
ግና መች አበቃ
ቂመኛው ሶላቶ
አርባ አመት ተኝቶ
አርባ አመት አስልቶ
እንደገና መጣ
ጦሩን አደራጅቶ
ጥይት አበራክቶ
የጭስ መርዝ ሰርቶ
Ras Mengesha |
በመድፍ በአውሮፕላን በባንዳ ተመርቶ።
ኦ !! እናት ሀገሬ ጀመረ ስቃይዋ
ተሰራጨ ውስጧ በመላ ገላዋ
በቅኝ ገዥዎች ሊፈተን ጤናዋ
በነገስታት ዘመን
ጣልያን ያልተኛላት
አምስት ዓመት
ሙሉ ከረመ ሲወጋት።
ጀግናው በየፈፋው
ጀግናው በየጫካው
ጀግናው በከተማ
ባደባባይ ጀግናው
የጣልያንን አንገት
በካራ ሲቀላው
አምስት ዓመት
ሙሉ መቀመጫ አሳጣው።
ያድዋው ድል ታሪክ ድጋሜ ተሰርቶ
በእነ አባ ገስጥ አቤ አንገቱ ተቀልቶ
ካገራችን ወጣ ወራሪው ሶላቶ።
ኢትዮጵያ ሃገሬን መግዛት አቅቷቸው
ድጋሜ ሽንፈቱ ያልተዋጠላቸው
አልጠፋም እስካሁን ቁስል ጠባሳቸው
እድሜልክ ይኖራል ሲመዘምዛቸው ።
ያቆረዘዘው ቂም
ዘንድሮ ገንፍሎ
በጣሊያን አፊሊ
(Affile) ትዝታው አብቅሎ
ለፋሽስቱ ግራዚያኒ
ሐውልት ተተክሎ
በጦር ያጡትን
ድል በአእምሮ ሊተኩት
ሕዝብን ለፈጀ
ስው ሐውልት ሰሩለት።
Ras Alula |
ሐበሻው ተናጠ
ተቃውሞው ቀለጠ
ምነው መንግስታችን ክፉኛ አለመጠ ?
ተቃውሞ የወጣን ወጣትና አዛውንት
በሽመል ቀጥቅጦ ዘብጥያ ማስገባት
ምን በደለ ሐበሻ ጥፋቱ የፋሽስት
ሕዝብን ለፈጀ ስው ሐውልት የሰራለት።
እንደው ለመሆኑ
ምንድን ቸገራቸው ?
በሐገር ሲላገጥ
ዝም ማለታቸው
ለጣሊያን ሶላቶ
መድረክ መልቀቃቸው
የድሮው ባንዳነት
አገረሸባቸው ?
ወይንስ ሊሬ ገባ
በከረጢታቸው
ልጓም የሚጎትት
ቶሽ እሚል የላቸው
እንደ ዱር አጋሰስ
መረን መውጣታቸው።
ኦ !! እናት ሃገሬ የነፃነት ደወል የፍትህ መረዋ
ደሙንም አፍሦ አጥንቱን ከስክሶ ላንቺ ለተሰዋ
ለታሪክ መኩሪያችን ለድል አምባ አድዋ
ክብር እንሰጣለን
ለወደቁ አባቶች እንፀልያለን
መታሰቢያ ሐውልት በወርቅ እንቀርፃለን
በእምዬ ምኒልክ
ስም እንሰይማለን
ያራዳው ጊዮርጊስን
ፒያሳ ከተማውን
እንጦጦ ጋራውን
ምኒልክ ጦር ሰፈር
ምኒሊክ ከተማ የምኒልክ ጋራ እናሰኘዋልን።
No comments:
Post a Comment