Monday 10 November 2014

እርም (ሐራም)

እርም (ሐራም) 1

ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

nigatuasteraye@gmail.com
ጥቅምት ፳፻፯ ዓ.ም.

በባህላችን የሰው ስም በትርጉም አልባነት እንደማይለጠፍ፤ ከሰውነታችን ጋራ የሚገናኙ ነገሮችም ስማቸው ከመነሻቸው ጋራ የተያያዘ ነው። “እንጀራ” ከምድራዊ ህይወታችን ጋራ ከተገናኙት መሠረታውያን ነገሮች አንዱ ነው። እንጀራ እስካሁን ድረስ የተነሳበትን የታሪክ ትዝታ ተሸክሞ ብዙ ዘመን ተጉዟል። እንጀራ ከወላጅ እናቱ ከጤፍ ጋራ በመተባበር ከኢትዮጵያና ከህዝቧ ጋራ ያላቸው ግንኙነት ሩቅና ጥልቅ ትስስር እንዳለው ሁሉ፤ ከመብላት ስሜትና ሱስ ጋራ ተዋህዶ በሰውነታችን ስለጋባ፤ ዝንት ዓለም የኖረ ይህን ጥብቅ ግንኙነት የሚያስለቅቅ፤ ጥብቅ ምክንያት መቅረብ ያለበት ይመስለኛል። ከኢትዮጵያ እየተጫነ የሚመጣውን እንጀራ አትብሉ ወደሚለው ሀሳብ ምን እንደወሰደን በግልጽ ለማቅረብና፤ እንዴትስ እናቁም ወደ ሚለው ውይይት ለመግባት፤ ከጉባዔ ትምህርት ቤት መምህራን የሰማሁትን ለውይይታችን መንደርደሪያ ብናድርገው የሚጠቅም ይመስለኛል።

በቅድሚያ እንጀራ እንዴት ወደ ህልውና መጣ?የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርምና፤ መመለስ የሚችሉት የጉባዔ ሊቃውንት አበው የሚሉትን እንመልከት። የእንጀራ እናት ጤፍ እንደሆነ የታወቀ ነገር ነው። “ጤፍ ሰው ቀደም ብሎ ለብዙ ዘመን ከኖረበት በኋላ፤ ለቆ በተወዎ ጠፍ በሆነበት ቦታ በመገኘቱ የተገኘበትን ስም በመውሰድ ጠፍ ተባለ። የረዥም ዘመን ዳህጸ ልሳን ጠን ወደ ጤ በመለወጥ ጤፍ ተባለ እንጅ፤ የቀደመ ስም አጠራሩ ጠፍ ነበር” ይላሉ። “ከጠፍ እየተሰራ የምንበላው እንጀራ ደግሞ፤ እንጀራ የተባለበት ምክንያት፤ ባንድ ወቅት ታውቆ ወደ ጠፍነት ከተለወጠ ቦታ ከጠፍ በመገኘቱ ስሙ እንጀራ ሆነ።

እንጀራ የሚለው ቃል መና ከሚለው ቃል ጋራ በሀሳብ የተገናኘ ነው” ይላሉ። የ መና መሰረተ ታሪክ “ወርእየ ወይቤ ብእሲ ለካልዑ ምንት ውእቱ ዝንቱ እስመ ኢያእምሩ“ (ዘጸ 16፡ 15) ተብሎ የተጻፈው ነው። ይህም ማለት፦ መናው በወረደ ጊዜ ሰዎች እርስ በርሳቸው “ይህ ነገር ምንድነው? ኧረ እኛ አናውቅም” እተበባሉ ተነጋገሩ። እንዲበሉት ተዘጋጅቶ የቀረበላቸውን ምግብ ምንድነው ለማለት “መኑ” አሉት። በኑኀ ዘመን ዳህጸ ልሳን፤ “መና” ተባለ። በባህላችን “መኖ” ስንል ቀለብ ማለታችን እንደሆነ ማለት ነው። በግእዝ ኢያእምሩ (እንዳኢ) ባማረኛ እንጀራ ማለት ነው። እንጀራ ከሁለት ቃላት ማለትም “እንጃ” ከምትለው አፍራሽ ግስ እና “ኧረ” ከምትባለው ቃለ አጋኖ ጋራ ተደምሮ የተገናኘ ቃል ነው። ጤፍና እንጀራ ከኢትዮጵያ ጋራ ያላቸው ግንኙነት በዓለም ያለ ሌላ ኅብረተ ሰብ የማይጋራው የዘመን ርቀትና የግንኙነት ጥልቅ አለው ። ከመብላት ስሜትና ሱስ ጋራ ተዋህዶ በሰውነታችን ስለጋባ፤
ይህንን ጥብቅን ጥልቅ ግንኙነት የሚያስለቅቅ ጥብቅ ምክንያት መቅረብ ያለበት ይመስለኛል።2

በዘመናችን በውጭ ተበትኖ የሚኖረውን ህዝባችንን ከኢትዮጵያ እየተጫነ የሚመጣውን እንጀራ ላለመብላት፤ ፍላጎቱን እንዲዘጋ ስሜቱን ቆርጦ እንዲተው ዳዊትን የረዳው አይነት ምክንያት በበቂ ጥናት ተደገፎ ቢቀርብለት የሚያቆም ይመስለኛል።

ለምሳሌ፦ ዳዊት በተራበና በተጠማ ጊዜ፤ መብላት የማይገባውን እንዲበላና፤ መጠጣት የማይገባው እንዳይጠጣ ያደረጉትን፤ ፍላጎቱንና ስሜቱን እንዲገታ የረዱትን ምክንያቶች ብንመለከት ምሳሌ ሊሆነን የሚችል ይመስለኛል።

ዳዊት በተራበ ጊዜ፤ እንዳይበላ ባህልና ህግ የሚከለክለውን ቁርባኑን በላ። በተጠማ ጊዜ እንዳይጠጣ ህግና ባህል የማይከለክለውን ውሀ አልጠጣም አለ። ምክንያቶች ነበሩት። ቁርባኑን መብላት ባይገባውም፤ በላው። ውሀ መጠጣት የሚከለክለው ባህልና ህግ ባይኖርም አልጠጣም። ቁርባኑ የበላበት ውሀውን ያልጠጣበት ጥብቅ ምክንያት ነበረው።

ዳዊት “የቤተ ልሄም ውሀ ጠማኝ” ባለ ጊዜ ፤ ሶስት ሰዎች ለነፍሳቸው ሳይሳሱ የፍልስጥኤምን ሠራዊት ሰንጥቀው ሄደው፤ በበሩ ካለችው ምንጭ ቀድተው አመጡለት። ውሀውን ያመጡለት ሰዎች ባይሞቱም ህይወታቸውን ሰውተውበታል (2 ሳሙ 23፡15_17)። ይህም “አልቦ ዘየዓቢ እምዝ ፍቅር ከመዘይሜጡ ነፍሶ ቤዛ ቢጹ” ብሎ ክርስቶስ ከተናገረው ጋራ የሚገጥም ነው። የዳዊት ሰዎች ወገናቸው ዳዊት ሲጠማው ከማየት ይልቅ ህይወታቸውን ሰውተው ውሀውን በማምጣት ጥሙን ለመቁረጥ የወሰዱት
ውሳኔ፤ ውሀውን መጠጣት ደማቸውን እንደመጠጣት ቆጠረውና ላለመጠጣ እንዲወስን ረዳው። የጥሙን ስሜት ቆረጠለት። ዳዊት ከዚህ ውሳኔ የደረሰው ለሰዎቹ የነበረው ፍቅርና ክብር ግልጽ ሆኖ ስለታየው ነበር። ስሜቱን ፍላጎቱን ለወገኑ ፍቅርና ክብር ሰዋ።

ቁርባኑን መብላት ህጉ ባይፈቅድለትም፤ ዳዊት በተራበ ጊዜ ከህግ ውጭ ቁርባኑን በላው። ህግ የተሰራው፤ ለሰው ህይወት ቤዛነት ነውና፤ ህግ ለሚያከብረው እግዚአብሔር በአምሳሉ ለፈጠረው ለሰባዊነት ክብር ቁርባኑ ክብሩን ለቀቀ። ስለዚህ ዳዊት በተራበ ጊዜ የማይፈቀድልነት ቁርባን በላ (ማቴ 12፡ 4)። ውሀው ግን፤ ክቡር የሆነው የሰው ህይወት ተላልፎ የተሰጠበት በመሆኑ፤ ህግ ባይከለክለውም፤ በሰው ክብር፤ ልዕልና እና በወገን ፍቅር ግዳጅ እርምነው ብሎ አልጠጣም አለ።

በባህላችን አንድ ነገር ላለማድረግ ስንወስን፤ “ያባቴን ሥጋ፤ የናቴን ደም ያስጠጣኝ፤ ወይም “ያንተን ያንችን ሥጋ” በማለት ሀሳባችንን እንዘጋለን። ቢሆንም ለብዙ ሰው እንጀራ ከመተው አውቆም ሆነ ሳያውቅ ኢትዮጵያዊነክ የሆኑትን ነገሮች መተው የሚቀለው ይመስላል። ብርሃኑ ድንቄ የሚባሉ ታላቅ ክቡር ሰው በጽሑፍ ያስቀመጡት ትዝ ይለኛል።

እኒህ የተከበሩ አባት “የኢትዮጵያ ህዝብ ባህሉን ሃይማኖቱን ሁለንተናውን እርግፍ አድርጎ እየጣለው ነው ። የቀረው እንጀራ ብቻ ነው። እሱንም ያልተወው የሆድ ነገር ስለሆነበት ነው” ብለዋል። ከኢትዮጵያ የሚመጣውን እንጀራ አትብላ ብሎ መንገር ብቻ ሳይሆን፤ ሆዱ እንዲቆርጥ የሚረዳው ነገር ሊቀርብለት ይገባል። ልጅ አድጎ ጡት አልተው ሲል፤ ጡቱን እርግፍ አርጎ፤ እርም ብሎ፤ እንዲተወው የሚረዳ ነገር ጡቱን ይቀቡታል። እንደዚሁ ሁሉ እንጀራውን የሚያስተው የሚመር እሬት ምክንያት መኖር አለበት።3

እንጀራ ከኢትዮጵያ ወደዚህ እየተጫነ የሚመጣው በ greedy commercial system ያበዱ ሰዎች ወሰን በሌለው ትርፍ አግበስባሽ ስሜት በመነዱ ሰዎች ከሆነ፤ ይህን የሚገታና ሚዛኑን የሚጠብቅ መንግሥት ከሌለና፤ ራሱ መንግሥት የሚደግፈው ከሆነ፤ በሥጋ በደም የተቆላለፈው ህዝብ የሚገታበትን መንገድ መፈለግ አለበት።

እዚህ ላይ Peeter the great የሚባለው ሰው የተናገረውን መጥቀስ እፈልጋለሁ። Peeter the great ተሰዶ እንግሊዝ አገር ሲኖር፤ ከፊቱ ደስታ አይታይበትም ነበር። ያፈራቸው እንግሊዛውያን ወደጆቹ “ብላ! ጠጣ! ተደሰት! ከዚህ ከደረስክ በኋላ ደግሞ ምን አጨማደደህ? ” ይሉት ነበር። Peeter ም “በዚህች ፕላኔት ላይ እስካለሁ ድረስ፤ በህዝቤ ላይ የሚነደው መከራ፤ የሚቃጠለው የህዝቤ አካል ሲጤስ ይሸተኛል” የሚል መልስ ሰጠ። በውጭ ተበትኖ ለሚኖረው ህዝባችን ከኢትዮጵያ እየተጫነ የሚቀርብለት እንጀራ ላለመብላት፤ የወገኑ ሥጋ መቃጠል ተሰምቶት፤ የሚጠበሰው የወገኔ ሥጋ ይሸተኛል ብሎ ከተናገረው Peeter ከደረሰበት የሞራል ደረጃ ላይ መድረስ አለበት። ከዚያ ሞራል ላይ ከደረስን፤ በወያኔ የሚጠበሰው የወገናችን መሰቃየት ከመሰማት አልፎ፤ ከሚጠበሰው ሰውነቱ የሚጠሰው ጢስ ሊያፍነን ሊተነፍገንና ሊዘገንነን ይገባል። ከዚህ ደረጃ ላይ ከደረስን መብላት ቀርቶ የምናስብበት መንፈሳችን ፈጽሞ ይቆለፋል።

ሆድ እንደሆነ ሁል ጊዜ እንግዳ ነው። “ሆድ ለመብል ነው። መብልም ለሆድ ነው። ሁለቱም ይጠፋሉ” እንደተባለው ትላንት ስለበላነው፤ ዛሬ ለማይሸልማን ልማድ ከመገዛት ነጻ ለመሆን መታገል ነው። ለመተው የሚከብደን እንጀራውን የሚተካ ምግብ ጠፍቶ ሳይሆን፤ ልምድን መተው ነው። መብላቱን እንዳናቆም ከወያኔዎች ከሚቀርቡልን ምክንያቶች ይልቅ፤ የበለጠ የሚታገለን ልማድ ነው። ልምድን ለመተው ደግሞ በመቃጠል ላያ ካለው ከወገን ሥጋ ከሚነሳው ጢስ የበለጠ የከበደ ምክንያት ያለ አይመስለኝም። ለነገሩ ለመተው የሚከብደን ከእንጀራ ጋራ ያለን የኖረ ልምድ ብቻ አይደለም። ሲጋራና ማነኛውም ነገር ከተለመደ በኌላ፤ እርም ብሎ መተው ቀላል አይደለም። አንድ ነገር ስለሚያስከትለው ጉዳት ከተገለጸ በኋላ እርም ብለው የሚተው ሰዎች ”አገር ከሚገዛ የራሱን ስሜት የሚገዛ የበለጠ ልዑል ነው” ብሎ ሰሎሞን የተናገረውን የተገነዘቡ መንፈሰ ኃያላን የሚባሉ ናቸው ።

ዘርን፤ እምነትን፤ ታሪክን፤ ገዳማትን በጥቅሉ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችንን ለማጥፋት ተዘጋጅቶ በመጣው ወያኔ እየተረዱ፤ ስስታም ነጋዴወች በውስጥ ከሚኖረው ህዝብ አፍ እየተሻሙ ወደኛ የሚያመጡትን እንጀራ መብላት፤ ቅዱስ ጳውሎስ “ለወገኑ የማያስብ ሰው እምነት ከሌለው አረመኔ ይልቅ እጅግ የባሰ ጨካኝ ነው” ብሎ የገለጸውን አይነት መሆን ይመስለኛል። በእርግጥ ከኢትዮጵያ የሚመጣውን እንጀራ እርም ብለን ማቆማችን የውስጡን ወገን በረሀብ ከመቃጠል ፋታ የሚሰጠው ከሆነ፤ ማቆሙ የሞራል፤ የዜግነትና የሃይማኖትም ግዴታችን ይመስለኛል።

እናስብ! በወያኔ ተሸላልታ የቀረበችልን አገራችን ከሀምሳ አመት በፊት የነበሩ ወገኖቻችን የሚያውቌት፤ የሞቱላትና የተሰውላት ኢትዮጵያ አይደለችም። በህይወት ያለው ህዝባችንም እንጀራ ሊበላ ይቅርና ወያኔ ምጣዱን ሰብሮበታል። የጤፉንም ምድር ዘርፎታል። ህዝቡን ወደ ምጣድነት ለውጦ የፍግ እሳት እያነደደበት ነው። ጎሳወችንም እየለያየ ተራ በተራ ዘራቸውን እያጠፋ ነው።4

የእንጀራን ስረ ነገር ለማግኘት ወደ ኋላ መለስ ብለን ታሪካችንን ስንቃኝ የምንቆመው ከጠፍ ላይ ነው። የስም አጠራሩን የተሸከመው በዚያ ወቅት የነበረው ጠፍነት፤ አሁን ወያኔ ከሚያካሂደው ጠፍነት ጋራ ስናነጻጽረው ክንውኑ የተለያየ ቢሆንም ግብሩ ያው ተመሳሳይ ጠፍነት ነው። ሁሉችንም ከተስማማንና የዳዊት ውሳኔ ከገባን፤ የተከበሩ ብርሃኑ ድንቄ የተናገሩትንም ካስተዋልን፤ ታላቁ ጴጥሮስ ከተናገረው ጋራ ካገናዝበንና አሁን ህዝባችን ያለበትን ኑሮ በጥልቅ ከተረዳን፤ ወያኔ ከንግዱ ከዘረፋውና ከጥፋቱ እስኪታገድ ድረስ ከኢትዮጵያ እየተጫነ የሚመጣውን እንጀራ ለማቆም ሰውነታን ዜግነታችን የሚያስገድደን የሚስለኛል።

ወያኔ በልማት ስም ኢትዮጵያን ወደ ጠፍነት ለሚጎተትበት ለሸፍጠኛ ታሪኩ መታሰቢያ ይሆነው ዘንድ፤ ከኢትዮጵያውያን አፍ እየተነጠቀ ለሚያቀርብልን እንጀራ እርም የሚል ቅጽል ሰጥተነው ወያኔ ከንግዱ፤ ከግድያው፤ ከዘረፋውና ከድብደባው እጁን እስኪያነሳ ድረስ፤ ተጭኖ የሚመጣውን እንጀራ ከመብላት ብንቆጠብ ድርሻችንን በመወጣት ላይ መሆናችንን አንርሳ። “ሆድ ለመብል ነው። መብልም ለሆድ ነው” ሁለቱም ይጠፋሉ። ወያኔም ይጠፋል። የጣለብን ታሪካዊ ጠባሳ ግን በታሪክ ተጽፎ ለዘላለም
ይኖራል።

ከመብላት ሱስ በቀላሉ መላቀቅ የማይችል ሆዳችን “ሊበላት የፈለጋትን እርኩም ጅግራ ናት” ይለናል። ላለመተው የሚያስገድደን ልማዳችን እንጀራን ከመብላት ላለማስተው ብዙ ምክንያቶች ያስፈጥረናል። ቢሆንም፤ ከመብላት ወደ አለመብላቱ በማዘንበል ከአገራችን ተጭኖ የሚቀርብልን እንጀራ መብላት፤ የወገንን ሥጋ መብላትና ደሙን መጠጣት እርም (ሐራም) ነው ብለን ለተወሰነ ጊዜ ለመተው ራሳችንን እንፈትነው።

በተረፈ እግዚአብሔር ይርዳን።
http://www.medhanialemeotcks.org

1 comment:

  1. Here is a video of the March I was describing!
    https://www.youtube.com/watch?v=INTXqbvP35M&list=UUdWafskwgGzNgceUQzsU3Cg
    Video, courtsey of Anteneh

    ReplyDelete