Tuesday 19 June 2018

በቅሎ ቢጠፋው ኮርቻ ገልቦ አየ!!


በቅሎ ቢጠፋው ኮርቻ ገልቦ አየ!!

ከአበባ ይመር

ውድ አንባቢዎቼ ሆይ

በመጀመሪያ ደረጃ ይኸን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ አንዱና ዋናው ምክያት፣ ያለንበት የሀገራችን ሁኔታና የተዘበራረቀው በመገናኛ ብዙሃኖች የሚሰራጨው ህዝቡን ግራ የሚያጋባ ሽብር አዘል ወሬ ነው፡፡

ሀገር ወዳድነት፟

ሀገር መውደድ ማለት እኔ እንደሚመስለኝ አንድ ሰው ሲፈጠር አብሮት ሠርጾ የሚያድግና ጊዜና ሁኔታን ጠብቆ የሚጥለው ወይም የሚያነሳው ሳይሆን ተጣብቆት እስከ መቃብር የሚወርድ ፍቅር ነው፡፡

ስለሆነም ፣ በውስጤ ያለው የሀገር ፍቅር ስሜት ሀገሬን፣ ሕዝቤን፣ ባህሌን ከማፍቀርና እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊነት ከመኩራት ታሪክን ከመዘከር ያለፈ በማንኛውም እንቅስቃሴ ውስጥ አልሳተፍም። አቅምን ማወቅ ታላቅ ችሎታ ነው እንዲሉ።
ማንኛውንም እንቅስቃሴ ለመሳተፍ የአይምሮ ብስለትና የሞራል ጥንካሬ ያስፈልጋል። ከዚህም በላይ በሀገራችን የሚደረጉት ማንኛቸውም ፖለቲካም ይሁን ሌሎች እንቅስቃሴዎች ሴቶችን ለማሳተፍም ሆነ ያላቸውን ተቀባይነት ለማሳየት የሚያደርጉት ጥረት እንብዛም ጎልቶ የሚታይ ሳይሆን ጭራሽ የለም የሚያስብልም ነው ። ዓለም ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ሲነጻጸር ማለት ነው። ከሚሊዮን አንድ ብትገኝም በተለያዩ መንገድ ጥላልፈውና አዳክመው ከጨዋታ ውጭ ማድረግ፣ በዘመናችን ብቅ ብለው ከነበሩት እህቶቻችን ያየነው ነው። ጭራሽ ከተነሱለት ዓላማ አውጥተው ከህዝብ ዓይን እና ጆሮ እንዲጠፉ ከተደረጉት ውስጥ ወ/ሮ ብርቱካን ሚዴቃሳን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።

እኛ ኢትዮጵያውያን ሴቶች፣ ካለው የባህልና የሀይማኖት ትስስርም ጭምር ቶሎ ብቅ ብንልም ፣ የሚደርሱብንን ችግሮችም ሆነ ተቃውሞዎች ተቋቁሞ ለማለፍ የሞራል ብቃት ያንሰናል። ‘’ዝም በይ አንቺ! ደሞ ምን የሚሉ አይናውጣነት ነው? ወደ ጉዋዳ ጊቢ !’’ የሚለው የቤተሰቦቻችን ቁጣና ከቁንጥጫ ጋር ስንቀምሰው ያደግነው፣ ሥነ ስርዓት የማስከበር ወጉ ዛሬም እንደ ጥላ የሚከተለን ነው። በደል ባይሆንም ከዘመኑ ጋር ለመራመድ ግን  በትንሹም ቢሆን ልጓም መሆኑ አልቀረም።
ስለዚህ ይህ ሁሉ ተደማምሮ ሴቶች በፖለቲካው ዓለም አሉን? ቢባል በሙሉ አፍ የሉም ነው መልሱ።

እኔም ዛሬ ይህን ጽሁፍ ሳዘጋጅ፦

በመጀመሪያ ወደ አይምሮዬ የመጣው ነገር ቢኖር ‘’ይሰድቡኝ ይሆን’’ የሚለው ፍርሀት ነበር። ግን
ባለቤቴ ከጎኔ ነው። ‘’አይዞሽ በርቺ ‘’ ይለኛል። እግዚአብሔር ይባርክህ።
ለማንኛውም ለመጻፍ የተነሳሳሁበት ዋናው ምክንያት በመገናኛ ብዙሀን ላይ አንድ ሰው እንዲህ የሚል መልዕክት አስተላልፏል፣
‘’ዶ/ር ዓብይን ለመደገፍ ህውሀት ወድቆ ማየት የፖለቲካ ቀብዴ ነው’’ ይላል።

በጣም ስለገረመኝና ታዝቤ ማለፍ ስላልቻልኩ እኔም የበኩሌን ድርሻ ለምን አላበረክትም አስባለኝ።

‘’እንስራና ገንቦ የለም ወይ ከቤትሽ፤
ትንሽና ትልቅ ያለመለየትሽ’’

ይሉ ነበር ውዷ አያቴ እንዲህ አይነት ነገር ሲገጥማቸው። እኔም ለዛሬ ልጠቀምበት።

ዶ/ር ዓብይን ስንደግፍኮ ነው ህውሀት ሊወድቅ የሚችለው። ይኽን ለሀያ ሰባት ዓመት ሥር ስዶ ሲያደማን የኖረና የተደራጀ የማፊያ ቡድን አንድ ዓብይ እንዴት ይጥለዋል ተብሎ ይታሰባል? አንተ ቀብድህን ጠብቅ! አስባለኝ።

እኛ ኢትዮጵያዊያን እና እስራኤላዊያን ያለን የታሪክ መመሳሰል አስደመመኝ!!

በግብጽ ምድር ዕብራዊያን በግዞት ሳሉ እየበዙ የወንዶችም ቁጥር እየጨመረ በመጣ ቁጥር የግብጹ ንጉሥ፣ አዋላጆች ዕብራዊያንን ሲያዋልዱ ፣ ወንድ ከተወለደ እያነቁ እንዲገድሉ በማስጠንቀቂያ ትዕዛዝ ወጥቶ ነበር። በእኛም በኢትዮጵያኖች ላይ በዚህ በሀያ ሰባት ዓመት ውስጥ አማሮችን ዘራቸውን ከምድረ ገጽ እንደ ዕብራዊያን እንዲጠፉ ስለተፈለገ፣ እህቶቻችን እንዳይወልዱ የሚያመክን መርፌ በጨካኝ ገዢዎቻችን ትዕዛዝ ይወጉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ሙሴ በዚህ አስጨናቂ እና አሰቃቂ ጊዜ ቢወለድም፣ በቤተሰብ እጅ ማደግ ባለመቻሉ የተነሳ ከባህር ውስጥ ተጥሎ በእግዚአብሔር እርዳታ በግብጻዊቷ ልዕልት ከባህር ውስጥ ተገኝቶ በፈርዖን ቤት በድንቅ ተዓምር የናቱን ጡት እየጠባ እንዳደገ በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ እናነባለን። ካደገም በኋላ በንጉሡ ቤት ከፍተኛ ሥልጣንና ከንጉሡ ቀጥሎ ሁለተኛ ሰው እንደነበር መጽሀፉ ይነግረናል። ሆኖም ግን የወገኖቹ ስቃይና መከራ ያንገበግበው ስለነበር አንድ ቀን አንዱ ግብጻዊ አንዱን ዕብራዊ ሲደበድበው አይቶ በንደት ግብጻዊውን ገደለው። በሚቀጥለው ሁለት ዕብራዊያን ሲጣሉ አይቶ ሊገላግልና ወንድማማች ስለሆኑ መጣላት እንደሌለባቸው ሲመክራቸው ከሁለቱ አመጸኛው ፦ ‘’እንደ ግብጻዊው ልትገድለን ነው ‘’? ሲለው ደንግጦ እንደ ተሰደደ መጽሀፍ ቅዱስ ይነግረናል።ይህ በመሆኑ ዕብራዊያን የመጣላቸውን አዳኝ ባለማወቃቸው እና እርስበርስ ባለመስማማታቸው የግዞትና የመከራ ዘመናቸውን አስረዘሙ።

ዛሬም በዶ/ር ዓብይ እና በሙሴ መካከል የተቀራረበ መመሳሰል ይታያል። አዎ! ዶ/ር ዓብይ ላለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት፣ እንደ ፈርዖን አደንዝዞ ሲያርደን እና ሲያደማን በኖረው በራሳችን ናዚ ውስጥ ጎልብተው ያደጉ ናቸው። ግን ማን ያውቃል ፣ በናዚው ገበታ ለሥጋቸው ማጎልበቻ የተመገቡ ቢሆንም ለዓይምሯቸው ንቃትና ለህሊናቸው ብስለት ግን ፣ ሙሴ በስውር እናቱን ቤተመንግስት አስገብቶ መግባ እንድታሳድግ ያደረገ አምላክ ዶ/ር ዓብይንስ የሀገር ወዳድነትን ስሜት፣ የወገንን ፍቅር፣ የሰውን ክቡርነት ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነትና ታላቅነት እየተመገቡ ላለማደጋቸው ምን ማስረጃ አለን?።
ከዚህ ይልቅ፣ የዛሬ አራት አመት ገደማ ለጉብኝት እስራኤል ሀገር በነበሩበት ጊዜ ያደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ሙሴ ያለ ጊዜው በመነሳት ግብጻዊዉን ገሎ፣ በገዛ ወገኖቹ በዕብራዊያን የተሰደደበትን የመከራ ዘመን ዓይነት ይገጥማቸው ነበር። ግን እግዚአብሔር ለዚህ ቀን ጠብቆ ከክፉ ናዚዎች ሰውሮ ያመጣልን ዘመን አሻጋሪው ሙሴ ቢሆኑስ!! ሊንኩን ይመልከቱ ……….


ታዲያ ዛሬም በሙሴ እንዳላገጡት ዕብራዊያኖች የምንመስል ብዙ ኢትዮጵያኖች በዶ/ ዓብይ ላይ የምንሰጠው አስተያዬትም ሆነ አመለካከት በተቻለ መጠን ያልተዛባና ዕውነትን ያለቀቀ ቢሆን ይመረጣል።

ይህንንም በማድረጋችን ስንጓጓለት የነበረውን ሰላም እና መረጋጋት ለህዝባችንም አንድነትን ለማምጣት ዶክተሩ የጀመሩትን ውጥን ከግቡ ለማድረስ የየአንዳንዳችን ትብብርና አንድነት እንደሚያስፈልጋቸው ከወዲሁ ተገንዝበን ከጎናቸው ልንቆም እና ድርሻችንን ልንወጣ ይገባል።

ካልሆነ ግን ሀያ ሰባት ዓመት ሙሉ በሥልጣን ላይ የነበረን እና የተደራጀን የማፊያ ቡድን በአንድ ሌሊት ጥለህ አሳዬን ማለት፣ በጽሁፌ አርዕስት ላይ እንዳሰፈርኩት የጠፋችውን በቅሎ ልትደበቅበት ከማትችለው ኮርቻ ውስጥ ገልቦ እንደመፈለግ ይቆጠራል።
የዶ/ር ዓብይ ዓላማ እኛ ከምንመኘው ዓላማ ጋር ከተመሳሰለ ጅምሩ እንዲሳካና ከምናልመው ግብ እንድንደርስ ትንሿን ኮርቻ ገልቦ ትልቁን በቅሎ ከመፈለግ፣ ትንንሾቹን ልዩነቶች አስወግደን አንድ የሚያደርገንን ኢትዮጵያዊነት እና ለህዝባችን ሰላም እግዚአብሔርን ይዘን እንቁም።

ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር።

No comments:

Post a Comment