"እውነት፡እልኻለኹ፥በዚች፡ሌሊት፡ዶሮ፡ሳይጮኽ፡ሦስት፡ጊዜ፡ትክደኛለኽ፡አለው።"
ማቴዎስ 26 ቁጥር 34
ከወንድሙ መኰንን፥ ኢንግላድ 11 January, 2022
መግቢያ
ጥቅምት 24 ቀን 2013 በውድቅት ሌሊት በትዕቢት የተወጠሩ የጦርነት ከበሮ ደላቂ የሕወሀት ባለሥልጣናት፥ ለዘመናት በገነቡት የጦር ኃይላቸው የትግራይን ሕዝብ ደሙንና አጥንቱን መስዋዕት እየከፈለ ሲጠብቃቸው የነበረውን የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን፥ የጭካኔ ጥግ በሚሆን አኳኋን፥ በተኙበት ጦራቸውን አምዘግዝገው ወጉት፥ ሳንጃቸውን ወድረው አረዱት። የሞቱትንም ሬሳቸውን ታይቶ በማይታወቅ ሆኔታ ልብሳቸውን ገፈው እርቃናቸውን ሜዳ ላይ ደርድረው የትግራይን ህዝብ አስጨፈሩት። በሕይወት የተያዙትን ፥ ጥይት ላለማባከን በማለት አስተኝተው ሲኖ ትራክ ነዱበት።
ይኸ በወገናችን ላይ የደረሰው ግፍ አንገሽግሾን፣ በመንግሥት ላይ የየራሳችንን ቁርሾ፣ ለምሳሌ አማራው ላይ በአጣዬ፣ በሸዋ ሮቢት፣ በወለጋ፣ በጋሞው ላይ በቡራዩ፣ ኦሮሞ ባልሆነው ሕብረተሰብ ላይ በሻሻማኔ፣ በዘዋይ፣ በአርሲ የተፈጸመውን ግፍ በማየት፣ ለህዛባችን የመኖር ዋስትና ላልሰጠ መንግሥት ላይ ጥርሳችንን ነክሰንበት የነበረው ሁሉ ለጊዜው ልዩነታችንን ወደጎን ገፍተን ከመንግሥት ጎን ተሰለፍን። የሕወሀት ጭካኔ ያንን አስጥሎን በአንድ ላይ አቆሞን ነበር። በየጊዜው ከመንግሥት በኩል የሚደረጉት አንዳንድ አስደንጋጭ ውሳኔዎች ግን ይኸንን አንደነታችንን እይሸረሸረ መሄዱ አልቀረም። በየጊዜው ለሚፈጠረው ቅሬታ መንግሥት ብቻ ነው ተጠያቂው!
የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጣ
ወራሪውና ጨፍጫፊው የትግራይ አሸባሪ ቡድን ይኸን አሳፋሪ ድርጊት የፈጸሙት ለ27 ዓመታት ዓይን ባወጣ ዘረፋ፥ በታጠቁት የጦር መሣሪያ፥ በዘረኝነት ጠበል አጥምቀው፣ ከሰውነት ወደ አውሬነት በቀየሯቸው የትግራይ ተዋጊና ባካበቱት ኃብት ተማምነው ነበር "ጦር አውርድልን" እያሉ መሬቱን ሲገርፉት የነበሩት። ዓላማቸውንም ለማሳካት የያንን የመሰለ እኵይ የጦር ወንጀል ከፈጸሙ በኋል፣ ወደ አዲስ አበባ ገስግሰው ገብተው መንግሥት ገልብጠው ኢትዮጵያን በመበታተንና ታላቋን ትግራይን የመመሥረት ዓላማቸውን አንግበው ፎክረው ዘመቻቸውን ጀመሩ። ነግር ግን በመንገዳቸው ላይ ለ27 ዓመታት ረግጠው የገዙት፣ መሬቱን ቀምተው፥ መብቱን ገፈው፥ ሀብቱን ዘርፈው የጨቆኑት የአማራ ሕዝብ በጀግንነት በልዩ ኃይል ሚሊሺያውና በፋኖው ተደራጅቶ ከፊታቸው ተጋረጠባቸው። አዲስ አበባ ለመግባት ይኽን ልበ ሙሉ ጀግና ሕዝብ፥ ዳሽቆ ማለፍ ቀላል አልሆነላቸውም።
በጭካኔና ከዱር አውሬነት በባሰ ወንጀል የተደፈረው የኢትዮጵያ ህዝብም ተቆጣ። ከዳር እስከዳር ከወንድሙ የአማራው ሕዝብ ጎን ለመቆም ሆ ብሎ ወጣ።። በየቦታው ተሠማርቶ የነበረ የመከላከያ ሠራዊትም ከያለበት ተሰበሰበ። ሕይወቱን አትርፎ አምልጦ ወደ ኤርትራ ተሻግሮ የነበረውም የመከላከያ ሠራዊት ተደራጅቶ ተመለሰ። የአማራው ሕዝብ ገትሮ የያዘለትን አውሬ ለመምታት፣ ደረሰለት። የአማራው ልዩ ኃይልና ፋኖው አላሳልፍ ከማለቱም ባሻጋር ገስግሶ ከጎንደር የተቀማውን ርስቱን ተዋግቶ ወልቃይትንና ሁመራን ነጻ አወጣቸው። የወያኔ ገዳይ ቡድን መሸነፉን ሲያውቅ በማይካድራ 1,100 ንጹህ ምስኪን አማሮችን ጥቅምት 29 ቀን ላይ ጨፍጭፎ ወደ ሱዳን ፈረጠጠ። በሂደት ራያም ነጻ ወጣች። የአማራን ምድር ረግጦ ማለፍ ቀረበትና በሦስት ሳምንት ውስጥ ዕብሪተኛው የሕወሀት አመራር የጥጋብ ፊኛው ተነፈሰ። የራሱን ህዝብ እንደጅል ቆጥሮ፥ "ባጫ ደበሌን ማረኩልህ ደስ ይበልህ፥ አበባው ታደሰን ገደልኩልህ እልል በል፥ 180,000 ጦር ደመሰስክልህ" እያለው "ደቂሴ ንሬን" አንከስ እያለ አስጨፈረው። የማታ የማታ ዕውነትና ንጋት እያደር ይጠራል ሆነና፥ ዋና ከተማውን ጥሎ ወደ ተንቤን ተራራ እግሬ አውጩኝ አለ። "አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው፣ ታላቅ ቾሎታ ነው" አለ ዘፋኙ! ተዋጊዎቹም ልብሳቸውንና መለዮአቸውን አውልቀው ከሲቪሉ ከሕዝብ ተቀላቅለው ተመሳሰሉ። ኢትዮጵያም ለመጀመሪያ ጊዜ ከተሰነቀረባትን የሕወሀት እሾህን ነቅላ ከስቃይ የምትገላገልበት ቀን የደረሰላት መሰላት። ህዝቡ ደስ አለው። የአንድነት ጡሩምባ ከዳር እስከ ዳር ተነፋ። አኩርፎ የነበረው ውጪ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ሁሉ በአንድነት ቆመ። የኢትዮጵያ ትንሳኤ የደረሱላት መሰለው። መከላከያው፣ ልዩ ኃይሉ፣ አመራሩን እያሳደደ የገባበት ግብቶ፥ ከተቻለ ከነሕይወቱ ይዞ፥ እምቢ ያለውን እስከወዲያኛው ሸኝቶ ሕወሀትን ታሪክ ለማድረግ ተጋድሎውን ተያያዘው።
ጉድና ጀራት ከወደ ኋላ
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ፥ ልዩ ኃይሉና የአማራው ወዶ ዘማች ፋኖው፥ እንዲሁም በወያኔ ርኬት ድብደባ ተጋብዘው ወደ ውጊያው የተቀላቅሉ ኤርትራውያን ተዋጊዎች ፥ በአየር ኃይሉ ተዋጊ ጄቶችና ሰው አልባ በራሪዎች (ድሮናች) በታጀበው ውጊያ የተንቤን ተራራ ጋየች። በዚያ እልህ አስጨራሽ ውጊያ 15 ገደማ የሚሆኑ፥ ስብሀት ነጋን ጨምሮ ከዋሻ እየተጎተቱ ወጡ። ወደ ዘብጥያም ወረዱ። እነ ሥዩም መስፍንና ዐባይ ጸሀይ የተባሉት የወያኔ አመራሮች ግን እጅ አንስጥም ብለው ወደማይቀርላቸው ሲኦል ተሸኙ። የኢትዮጵያ ህዝብ በከፊልም ቢሆን አንጀቱ ራሰ። የውጭ ጠላቶቻችን ቢጮሁ፥ ቢያላዝኑ፥ ኢትዮጵያ ፍንክች አላለችም። የተቀሩትን የሕወሀት አመራሮችን ማደኑ ቀጠለ። እነደብረጽዮን፥ ጻድቃን፥ ታደሰ ወረደ፥ ... የመሳሰሉት በየጢሻው እየተሽሎከሎኩ እስከ ሰኔ ድረስ ከመያዝ አመለጡ።
የዓለም አቀፉ ጫና ቢበዛ፥ የምዕራቡ ዓለም ጋዜጦች፥ ቴሌቪዥኖች እና ማህበራዊ ሚዲያዎች የውሸት መረጃዎችን ቢለቁም ኢትዮጵያውያን በአንድነት ቁመው መከቱት። የአባቶቻችን የጀግንነት ወኔ የተመለሰ መሰለ። እኛም የመንግሥት ቃል አቀባዮች በጊዜው እየወጡ፣ ይኸን ያህል ተደመሰሰ፣ ይኸን ያህል ተማረከ እያሉ ሲያስረዱን፣ በኩራት ተዝናንተን፣ የቀሩትን አመራሮች የሚያዙበትን ወይም የሚወገዱብትን ዜና ስንጥብቅ በድንገት ወሽመጣችን ተቆረጠ።
ሰኔ 21 ቀን ደረሰ። የኢትዮጵያ መንግሥት ጆሮ ጭው የሚያደርግ መርዶ ተነገረን። ማንም ያልጠበቀ በጣም የከፋ ዋጋ የሚያስከፍል፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕምነቱን የጣለበት የሚሸረሽር: መንግሥት እርምጃ ወሰደ። የያዘውን ይዞ፥ የቀረውን ታንኩን፥ መድፉን፥ ዲሽቃውን፥ ብሬሉን ጥሎላቸው፥ ከትግራይ ከወጣ በኋላ ልክ ወያኔዎች እንደሚያደርጉት፣ "አሸንፌ ተመለኩ፥ ደስ ይበላችሁ ብሎ" ሊያስጨፍረን ሞከረ። "ሕወሀት ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያን የሚያሰጋ ደረጃ ላይ እንደሌለች አውጆ አርፋችሁ ተኙ ተባልን። ክው አልን። ባለንበት ኩምሽሽ አልን። መንግሥት "የምንፈልገውን እያሳየን ወደበረሀ ወስዶን እዚያው ጥሎን ተመለሰ" ጉድና ጅራት ድሮም ከወደ ኋላ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ዶሮ ጮኸ።
የወሎው፥ የሰሜን ሸዋና የአፋሩ ሕዝብ ከነከብቶቹ እልቂትና መፈናቀል የማን ስህተት ነው?
ይኸን መጠየቅ ጊዜው አሁን አይደለም ልትሉኝ ትችላላችው። ለመሿሿምና ለመሸላለም ጊዜው ካመቸ፣ ዋጋ የሚይስከፍሉ ስህተቶችማ ሲሠሩ ዝም ማለት አድር ባይነት ነው። እንዳይደገም! እንዲህ ዓይነት ጥቆማ መንግሥትን ቢጠቅመው እንጂ አይጎዳውምና፣ ካድሬዎች አደብ ግዙ። ጃንሆይንም መግሥቱንም ገደል የከተታችሁት የእናንተ ዓይነቶቹ ናችሁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግሥታቸው ሊነገራቸው ይገባል።
መከላከያችን መቀሌን በድንገት ጥሎላቸው ሲወጣ፣ ባይሆን ደጀኑ የሆነውን የአማራና የአፋር ድንበር ላይ እንደመቆየት ዕድላችሁ ያውጣችሁ ብሎ ሁለቱን ሕዝብ አጋፍጦ ዞር ማለት ምን ይባላል! በዚህ ላይ አማራው እንዳይታጠቅ ላለፉት 30 ዓመታት ተፈርዶበታል። ቆይ እንጂ! ልክ አሜሪካና እንግሊዝ ናዚ ጀርመኒና ኮሙዩኒስት ራሺያ ሲተላለቁ በራሳቸው እስከሚመጣ ድረስ ዝም እንዳሉት መንግሥታችን አማራውና ትግሬው እንዲተላለቅለት አውቆ የተዋቸው አስመስሎበታል። የሕወሀት አመመራሮች በወርቅ መሶብ የቀረበላቸውን ድል ሳያስቡት ተቀብለው፣ መቀሌን በከበሮ ድለቃ ቀውጡት። እግዚአብሔር ዘፈን ሲያምረው ማንን ነበር ያጠግባል የተባለው? ረሳሁት። የሕወሀት አመራሮች ከተሸሸጉበት ጎሬ ወጥተው፥ መሣሪያቸውን ከደበቀቡት ጉድጓድ ቆፍረው አውጥተው፥ መከላከያውም ትቶላቸው የወጣውን ዘመናዊ መሣሪያ "እናመሰግናለን" ብለው ተቀብለው፥ እንደ እባብ አፈር ልሰው ነፍስ ዘርተው፣ ወደ የዕዝ ማዕከላቸው ተመለሰሱ። የምዕራቡ ዓለም አደነቋቸው። የጦር ታክቲክና ስትራተጂአቸውንም ዕጹብ-ድንቅ አሉላቸው። የጻድቃን የጦር አመራር ብቃት በአፍሪካ ታይቶ የማይታውቅ ተብሎ ተጨበጨበለት። እነ ጌታቸው ረዳ የምዕራቢያውያን ሜዲያ ኮከብ ሁነው የጋዜጦቹን ገጽ ሞሉት። የቴሌቪዥኑንና የሬዲዮውን ሜዲያ ተቆጣጠሩት። በዚያ አላበቁም።
"ከአማራው ጋር የምናወራርደው ሂሳብ አለን" በማለት፥ ሕወሀቶች አማራው ላይ ዘመቱ! ጎንደርን በከፊል፥ ወሎን መሉ በሙሉ፥ ሰሜን ሸዋ ተቆጣጥረው የደም መሬት አደረጉት። ወንዶቹ ታረዱ፥ ሴቶቹ፥ ሕጻናቱና አሮጊቶች ሳይቀሩ በተፈራራቂ የሕወህት መንጋ ተደፈሩ። ከመንግሥት ተቋም እስከ የግለሰብ ንብረት ዘረፉ፥ የቀረውን አወደሙት። ከብቶቹም ተረሸኑ። የአማራው ሚሊሺያና ፋኖ አንዳንንዴ ብቻውን ሌላ ጊዜም በመከላከያው እየታገዘ ቢዋጋም እንድ በአንድ የወሎን ትላልቅ ከተሞች፥ ላሊበላ፥ ደሴና ኮምቤልቻ ሳይቀሩ በሕወህት ቁጥጥር ሥር ወደቁ። ወያኔዎች ሸዋም ዘለቁ። ተሰምቶ የማይታወቅ ግፍና ጭፍጨፋ አደረሱ። የአንድ ቀን መዘዝ በዘጠኝ ወር ይመዘዝ ይሉሀል ይኸ ነው። ይኸ ጉድ ተሸፋፍኖ መታለፍ የሌለበት ግፍ ነው። ተመዝግቦ ይቀመጥ። የስህተቱ ምንጭ ከመቀሌ መውጣቱ ብቻ ሳይሆን ደጀኑንም ለቆ ማፈግፈግ፣ አማራና አፋርን ዋጋ አስከፍሏል።
ሚሌ የምትባለዋን መተላለፊያ ዘግተው የኢትዮጵያን ጉሮሮ እንዘጋለን ብለው ዝተው ማንንም አስቀይሞ በማያውቀው አፋር ህዝብ ላይ ዘመቱበት። አፋሮች ተጨፈጨፉ። ሕዝባቸው አለቀ፥ ንብረታቸው ወደመ። ጭፍራ የምትባለው ከተማቸው ወደመች። አፋሮች ግን ታይቶ በማይታወቅ ጀግንነት ሚሌን ላለማስነካት በታላቅ ጀብዱ ታሪክ ሠሩ። ሕወሀቶች ሚሌን ለመያዝ እንደቋመጡ ዓላማቸው በአፋር አናብስት ከሸፈባቸው። ኪሳራ!
በወሎ ግንባር ግን ታሪኩ ሌላ ነበር። ደሴንና ኮምቦልቻን በብዙ መስዋትነት ከጨበጡ በኋላ፥ ሕወህቶች ደብረሲና ደረሱ። አዲስ አበባን ለመያዝ ቀናት ሲቀራቸው፥ የኢትዮጵያ መንግሥት የምር ሰይፉን መዘዘ። በራሱ ደረሰአ! ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀሩ ከተኙበት ባነኑ። ልክ ናዚ ጀርመኒ ፖላንድን መውረራቸው ሳያንስ ፓሪስን ተቆጣጥረው የእንግሊዝ ወደቦችና ከተሞችን መደብደብ ሲጀምሩ እንግሊዝ እንደባነነችው ማለት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እራሳቸው ታጥቀው ጦሩን ሊመሩ እንደቀድሞዎቹ መሪዎች ግንባር ገቡ። በራሳቸው መምጣቱ በጀ ልበል?! ቢዘገይም የሚደነቅ እርምጃ ነበር። የሰው ወኔው ተመለሰ። ሕዝቡ እንደገና ሆ ብሎ ወጣ። መከላከያው፥ ልዩ ኃይሉ፥ ፋኖውና አፋሩ ልዩ ኃይልና ሕዝብ በተቀናጀ መልኩ በጀግንነት፥ በቆራጥነትና በወሳኝነት፥ ወራሪ፥ ጨፍጫፊ እና ዘራፊ የወያኔ፥ ሪፍራፍ ተዋጊን መክቶ፥ ለአራት ወራት ሙሉ እየገደሉም እየሞቱም፣ ተንፏቅቀው ተንፏቅቀው ደብረሲና የደረሱትን ጉዶች፥ በሁለት ሳምንት ከሰሜን ሸዋና ወሎ ጠራርገው፥ እንዲፈረጥጡና ሬሳቸውን እንኳን ሳያነሱ ኮረም እንዲገቡ አደረጓቸው። አፋርም ሙሉ በሙሉ ተለቀቀ። ይኸ ምንድነው የሚያሳየው? ቀድሞውኑ መንግሥት ችላ በማለት የውሎ፥ የሰሜን ሸዋና የአፋር ምድርን እንዲይዙ ዕድል ሰጥቷቸው ነው እንጂ፣ የነዚህን መሬቶች የመርገጥ አቅም ወያኔዎች ባልነበራቸው ነበር ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግባቸውን በከፊል ፈጽመው በኋላ ወደ አዲስ አዲስ አበባው ቢሮዋቸው ተመለሱ።
ጦሩ በሽሽት ላይ ያሉትን የወያኔ "እውር ድንብር" ተዋጊዎችን አባርሮ ኮሩም ደረሰ። የመቀሌ ባለሥልጣኖች ተደናብረው፣ ጓዝና ጉዝጓዛቸውን ቀርቅበው፣ ተስፋ በመቁረጥ፣ የዓለም አቀፉን ሕብረተሰብ "አድኑን" እያሉ እየተማጸኑ፣ ወደተምቤን ተራሮች መጓጓዝ ሲጀምሩ እንደገና "ደጉ" መንግሥታቸው ነፍስ ዘራላቸው። የኢትዮጵያ ጦር አሳዶ የወያኔን አመራር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አከርካሪ ይሰብራል ብለን ስንጠብቅ፣ ዋጃን እንደተቆጣጠሩ፣ አላማጣን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አንድ ቀን ሲቀራቸው፣ "ባለህበት እርጋ" የሚል ትዕዛዝ መንግሥት አስተላለፈ። እንደገና ወሽመጣችን ተቆረጠ። ወያኔ እንዳትጠፋ አልተፈለገም ማለት ነው? አውላላ ሜዳ ላይ እንደገና ተጣልን! ዶሮው ለሁለተኛ ጊዜ ጮኸ!
ሦስኛው ዶሮ!
ለሁለተኛ ጊዜ የመኖር ዕድል የተሰጣቸው የወያኔ ተዋጊዎች፥ መፈርጠጣቸውን አቁሙው አፈሙዛቸውን ወደኋላ አዞሩ። በወልቃይት ጠገዴ በኩልም ያለ የሌለውን ጦራቸው ሰብቀው ውጊያ ጀምሩ። እስካሁን አዲ አርቃይን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ተቆጣጥረው፣ ጎንደሬ አማራውን እያፈናቀሉት ነው። በአፋር በኩል የአባላ ከተማን በመድፍ አያወደሙት ነው። በአላማጣ በኩል ውጊያቸውን አጧጡፈው ዋጃና፥ ጥሙጋ የተባሉትን ከተሞች ተቆጣጥረው ወደቆቦ የምድር ክላስተር ቦምብ እይተኮሱ እየገሰገሱ ነው። ቆቦን በመድፍ ከርቀት ማጋየታቸውን ቀጥልዋል። ምስኪኑ ህዝብ፣ ከዋጃ ወደ ቆቦ ተፈናቀለ። ቆቦም መደብደብ ሲጀምር፥ ከቆቦ ወደወልዲያ እየተመሙ ነው። ከወልቃይት ጠገዴም አማራው እንደገና ተክዷል እየተባለ ሽብር እየተነዛ ነው፥ መካላከያም፥ ልዩ ኃይሉም፥ ፋኖውም ይውጣ የሚባል መመሪያ እንደተሰጠ ሹክሹታው ቀጥላል። ጭስ ካለ እሳት አለ። ከዚህ በፊት የተንሾከሾከው በሙሉ ዕውን ሁኖ የእለ? የኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ የቁጣ ንግግርም ይኸንኑ አመላካች ይመስላል። አማራው እንደገና በጎንደር ቅስሙ እስኪሰበር ከተተወ ሥራ ለሠሪው እሾህ ላጣሪው እንደሚባለው ለመንግሥትም ጦስ ይዞ ይመጣል። አለባበሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ይባል የለ? የሱዳን ኮሪዶር ሕወሀቶች ማስከፈት ከቻሉና እንደገና መታጠቅ ከቻሉ፣ መንግሥትንም የመግልበጥ ሕልማቸው ሊሳካ ይችላል። ጦር መሣሪያቸው አልቆ ያልጨረስናቸው፣ ሌላ አውዳሚ መሣሪያማ ከታጠቁ ሕዝባችንን ይጭርሱና ኢትዮጵያን ወደመበታተናቸው ሁለተኛ ደረጃ እቅዳቸው ይራምደሉ። ለኃጢአን የመጣ ለጻድቃን ይተርፋል ይባላል።
ጦርነቱ ገና አላላቀም። የምን አሸሻ ገዳሜ ነው? መንግሥት ሆይ! የጦር አማራሮቹን ጠርተህ ከምትሾምና ከምትሸልም ይልቅ፣ መጀመሪያ ጦርነቱን በድል ፈጽም! ለመሆኑ፣ መቼና ለማን ነው የማርሻልነት ማዕረግ የሚሰጠው? ጦርነቱ እስኪጠናቀቅ ፌሽታው መቆየት አይችልም ነበር? የልጅ ነገር አደረጋችሁት። የምታቦኩት ሁሉ ለራት አልበቃም!
ውጪ ኗሪው ኢትዮጵያዊ (ዲያስፖራው) ተጋብዞ በገፍ ወደ አገር ገብቷል። ለምን ጋበዛችሁት? በስሜት የተዘጋጀለትን ሁሉ እየጎበኘ በደስታና በጉጉት አገሩን እንዴት እንደሚረዳ፥ የወደሙትን መልሶ እንዴት አድርጎ እንደምያቋቋምለት በታላቅ ተነሳሽነት እየተመካከረበት ባለበት በዚህ ጊዜ ሌላ ዱብ ዕዳ ለምን አወረዳችሁበት? ብዙዎቻችሁን ሕወሀት ለዚህ ደረጃ አሰልጥና አሳድጋ እንዳደረሰቻችሁ እናውቃለን። ለምን ከዚያ አስተሳስብ ሰብራችሁ አትወጡም? ለምን አገራችንን ዋጋ ታስከፍሏታላችሁ? ለኢትዮጵያ እንደምታወሩት ከቆማችሁ ብሰሉ እንጂ! ከጎናችሁ የምንቆመው ስንተማመንባችሁ ነው። ስንት ጊዜ በእናንተ ላይ ያለንን እምነት ትሸረሽራላችሁ? የምነፍልገውን እያሳያችሁን ወስዳችሁ በረሀ የምትጥሉን ደነዞች አድርጋችሁ አትቁጠሩን።
እኛ የቀሩትንም የሕዋህት ባለሥልጣናት የተከፈለው መስዋዕትነት ተክፈሎ ተይዘው ለፍርድ ይቅርባሉ ብላን ስንጠብቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዕለተ ዓርብ፣ ያውም በጌታችን የመድኃኒታችን የእየሱስን ክርስቶስ በአለ ልደት በሚከበርበት ቀን፥ ተስፋችንን አጨለሟት። በስንት መስዋዕትነት የተያዙት የወያኔ ቁንጮ መሪዎችን፣ አቶ ስብሀት ነጋን፥ ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋን፥ አቶ አባይ ወልዱን፥ እቶ አባዲ ዘሙን፥ ወይዘሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔርን እና አቶ ኪሮስ ሀጎስን በይቅርታ ፈትቼአቸዋልሁ፥ ብለውን እርፍ! ምን? ይኸን ሲያውጁ፣ ለ3ኛ ጊዜ ዶሮው ጮኸ! በደም የተበከለችው፣ በጣዕር በስቃይ ላይ ያለችው ምስኪኗ እናት ኢትዮጵያም ዕንባ ባቀረሩ ዓይኖቿ ጠቅላይ ሚኒስትሯን አየች።
4
"...ኢትዮጵያ ዕንባ ባቀረሩ ዓይኖቿ ጠቅላይ ሚንስትሯን አየች"። "ጠቅላይ ሚንስትሯን"??? በወያኔ አገዛዝ ተጸንሶና ተገንብቶ ዛሬ ኦነጋዊያን በአብይ እየተመሩ እንደተመቻቸውና እንደፈለጉት በሚጠመዝዙት አገር ጎጂ/ከጂ የጎሣ አገዛዝ መንኮራኩር እየተነዳች በሃቅ የኔ የምትለው የፖለቲካ መሪ አላት? በሙሉ ልብ አብይ "ጠቅላይ ሚንስትሯ" ሊባል የሚችል ሰው ነው?!
ReplyDelete