Thursday, 8 December 2011

የብሶት ምጥ!


የጐንቻው!

ሃያ ዘመን ሕዝብ ያረገዘው፤ውል እድሩ፤ የብሶት-ምጥ፤

የተጣባ ከውስጣችን፤ሕመማችን ሥር የሰደደ አለቅጥ፤

ሲያስጨንቅ ፤ሲያስጠብበን፤የኖረ፤ሲያንቆራጥጥ፤

ስንድህ በእንብርክክ ‘ሽል’ በውስጣችን  ሲገላበጥ፤

የሁለንተናችን ግልግል ውስጠ-ደማሚት እበጥ፤

አልፈነዳ፤ አልወለድ፤ ብሎ፤ወገን በሕቡ፤ሲናጥ፤

በቁርኝት አሳስሮን፤እጅ መዳፉችን፤ሲላጥ፤

ግፍ፤ቆሰቆሰው፤ሊያቀጣጥሉን፤‘የቀኑ ሰዎች’ በፈሊጥ፤

ስም እያዋሱን ‘ሞግሸነት’ መዘባበቻ፤ሽብር ስላጥ፤             

ባጐረስን እየተነከስን፤ሲገፉን፤ኖረው፤ከድጥ ወደ ማጥ፤

‘ብሶት ወለደን’ ብለው፤ያነገሱት፤የእንግዴ-ልጅ ምጥማጥ፤

የትውልድ ተስፋ የምያመክኑ፤ለእሳት ዳረገውን ለረመጥ፤

በስለን አረናል፤በየጐጇችን፤እየተቃጠለን፤ሳንገላበጥ።

Wednesday, 7 December 2011

አሻቅበው ቢተፉ፣ ተመልሶ ባፉ!

ወንድሙ መኰንን

አኬልዳማ (חקל דמא)ጥሬ ቃሉ የተገኘው ከአርማያክ ቋንቋ ነው። አርማያክ ጌታ እየሱስ ክርስቶስ በዚህች ግፍ በሞላባት ምድር ላይ ሲኖር ይናገርበት የነበረ ቋንቋ ነው። ዓለም ይኸን ቃል የወሰደው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው። የሐዋሪያት ሥራ ም. ፩ ቁ. ፲፱ እና የማቴዎስ ወንጌል ም፡ 27 ቁ፡ 8 ላይ ቃሉ ተጽፎ እናገኘዋለን። ነገሩ እንዲህ ነበር። ያኔ ይሑዳ የተባለ ከሀዲ ጌታን በ30 ብር (30 pieces of silver) አሳልፎ ሽጦት ነበር። ልክ የኢትይጵያን መሬት፣ ዛሬ ለባዕዳን እንደሚቸበችበው፣ ከሀዲ የወያኔ መንጋ እንደማለት ነው። ጌታ በግፍ ከተሰቀለ በኋላ፣ ታዲያ ይሑዳ ተጸጽቶ 30 ብሯን መልሶ “ተቀበሉኝ” አለ። ቀጣፊ! ከፋዮቹ፣ የደሙ ዋጋ ወደ እነሱ እንዳይመጣ ሰግተው፣ በዚያ ገንዘብ የአንድ ሸክላ ሠሪ መሬት ለእንግዶች መቃብር ይሆን ዘንድ ገዙበት። መሬቱንም አኬልዳማ ተባለ። ትርጉሙም፡ “የደም ምሬት” ማለት ነው። ጸረ እግዚአብሔር የሆነ ሌባ ወያኔ ቃሉን ከማያምንበት መጽሐፍ ቅዱስ እንደልማዱ ዘርፎ፣ ተጨማለቀበት! ለነገሩስ፣ “ሰይጣን ሀጃውን ለሟሟላት ሲከጅል፣ አንዳንድ የሚበጁትን ቃላት ከመጽሐፍ ቅዱስ ይጠቃቅሳል” ማለት ይኸው አይደል!

ወንጀል ፈጻሚው፣ ሰላማዊውን ሰው መልሶ ወንጀለኛ አድርጎ ድራማ ወይም ትርዒት መሥራትን ወያኔ የተካነበት ዘዴ ነው። አሳሪው ዕብሪተኛ የወያኔ መንጋ፣ ሕዛባችንና ወገናችን ላይ የሚያደርሰው ሰቆቃ አንሶት፣ አሁን ደግሞ የግፍ ግፉን፣ ሰው አስሮ እያሰቃየ፣ በስቃይ ብዛት ተገደው መሣሪያ በግንባራቸው ላይ ተደግኖ ሰለባዎቹ ስቃዩ እንዲቀልላቸው በሚለፈልፉት ላይ እየተመሠረተ እራሱ ሊዝናናበት (ተሳስቶ ዕውነትም ቢናገር የሚያምነው መቸም የለምና) ትርዒት መሥራት ከጀመረ ውሎ አድሯል። አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ “አኬልዳማ ” የሚል ሶስት ክፍል ድራማ ሠርቶ ቅስማችንን ሊሰብር፣ በኢትዮጵያ ተሌቪዥን ለቀቀው። “እንደልማደህ ቅደድ” በሉት እንግዲህ! ትንሹን ውሸት ወያኔ እንዲሸፍነው፣ ሌላ ያንን የሚያሳንስ ትልቅ ውሸት መዋሸት ነበረበት። ትንሹን ወንጀሉን ወያኔ የሚያቀለው ሌላ ግዙፍ ወንጀል ፍጽሞ የበፊተኛውን ወንጅሉን በማደንከይ ነው።



ክፍል ፩፡ የእምዬን ወደ አብዬ

በክፍል ፩ ድራማ ወያኔ ከዚህ በፊት እራሱ በደኖ ላይ በፈጸመው የወገናችንን ጭፍጨፋ ወንጀል ያላንዳች እፍረት በሚያመቸው መንገድ እንደገና ከልሶ (ኤዲት አድርጎ) አቀረበ። አንድ ጥሩ ማስጠንቀቂያ ግን በአንድ ቆንጆ ድምጽ ባላት ሴት ንባብ ይጀምራል። እሱም፤ “ይኸ ፕሮግራም ከ13 ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት እንዲያዩት አይመከርም” የሚል ነው። ደግ ብላለች። ይኽች ብቻ ናት ከዚያ ሁሉ ቆሻሻ የምትለቀም ደግ ነገር። ለዚያውም ቆሻሻ ውስጥ ለቅመው በልተው ሊሚያድሩ ሕጻናት ከታሰበ ባለት ነው። ለታሪክ ተመዝግቦ መቀመጥ አለበት። http://www.diretube.com/ethiopian-documentary/akeldama-part-1-video_25cf45af1.html ጉድ በሉ ጃል! ገደል ውስጥ እጃቸው ከኋላ ታስሮ ከነነፍሳቸው ተወርውሮ የተፈጠፈጡት ሕጻናት፣ ሴቶች፣ ወንዶች ሬሳ በገመድ እየተንጠለጠለ ሲወጣ ይታያል። ከተንቀሳቃሽ ስዕሉ በታች የተጻፈው “ኦነግ የፈጸመው ወንጀል” የሚል ነው። እ?? አይ አንተ አምላክ! አይ አንተ ፈጣሪ! ኦነግ በዚያን ጊዜ ከወያኔ ጋር የጊዜያዊ መንግሥት አካል አልነበር? ታዲያ ወያኔ ያኔ ምነው ሕግ አላስከበረ? የያኔው የወያኔ ጠቅላይ ሚኒስቴር፣ የአሁኑ ጴንጤ፣ ታምራት ላይኔ አልነበር፣ “ሽርጣም እያለ ይሰድብህ የነበርዉን አሁን በለው” እያለ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ሲያነሳሳ የነበረው? የአዛኝ ቅቤ አንጓች! የነዚያን ንጹሀን ሰዎች ደም ደመ-ከልብ ሁኖ እንዲቀር ማን ነበር አድበስብሶት ያስቀረበት!? ያኔ አንዲት ቃል ያልተነፈሰው ይኸ የገዳዮች መንጋ፣ ዛሬ ያንን እራሱ የፈጸመውን ወንጀል ሌላ አካል እንደፈጸመው አቀነባብሮ ሲያቀርብ፣ ማንን ለማታለል ነው? ለነገሩ፣ አቶ ዲማ ነገዎ የተባሉ የኦነግ የአመራር አካል በኢሳት ቀርበው እንዳስረዱን ከሆነ፣ በጊዜው ነገሩ በነጻ አካል እንዲጣራ ኦነጎች ጠይቀው፣ ወያኔ እንዳዳፈነው ነው።ታዲያ ዛሬ ወያኔ እራሱ የፈጸመውን የአረመኔነት ወንጀል፣ እንደመሣሪያ መልሶ ሲጠቀም ማንን ለማታለል ፈልጎ ነው። ምነው እኛን ቤተሰብ አልቆባቸው የሚያለቅሱትን ንግግር ሙሉ በሙል አላውጣም ይኸ ጋጠ-ወጥ ቀጣፊ! “ቤተሰቤን ያስጨረሰው መለስ ዜናዊ ነው” አልነበር ያሉት? ያንን ቆርጦ ማውጣትን ምን አመጣው? ይኽ ሁል ሸንካላ ዝባዝንኬ፣ እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን፣ ርዕዮት ዓለሙን፣ የአንድነቱን ወጣት መሪ አንዱዓለም አራጌን ... ወዘተ በግፍ ማሠሩን ለመሸፈን መሆኑ ነው? ትልቅ ውሸት ተብሎ ካልተተረጎመ፣ ምን ፋይዳ ሊፈይድለት ነው? ይኸን ጉዳይ፣ አርቲስት ታማኝ በየነ በጥሩ ሁኔታ በኢሳት ቴለቢሽን ላይ ሂዶበታልና፣ እዚህ ላይ ገታ አድርጌ እንድታዳምጡ አንባቢን እጋብዛለሁ። አምላካችን ይባርክኽ፣ ታማኝ!

http://www.youtube.com/watch?v=PUMRnjrKL0c

የመለስ ዜናዊ አገዛዝ የፋሽስት አገዛዝ መሆኑ ጸሞቀው ሀቅ እኮ ነው። መለስ ዜናዊ እኮ በዘር ማጥፋት ተወንጅሏል። በጋምቤላ፣ በዚሁ አሁን ሊያታለለን በሚሞክረው በበደኖ እልቂት፣ የአርባ ጉጉ ጭፍጭፋ፣ የወተር፣ የእንዳየሱስ፣ የኦጋደን የአንድ መንደር መንደደድ በመሳሰሉት ዓለም-አቀፍ ፍርድ ቤት፣ ፋይል እንዲከፍት የጀኖሳይድ ዎትች ፕረዝደንት ዶክተር ግሪጎሪ ስታንተን አመልክተው ውጤቱን እየተጠበቀ እኮ ነው። ያውላችኋ! http://redsea1.websitetoolbox.com/post/Tigray-The-Looming-Genocide-By-Dr.Gregory-Stanton-5558857

አሁን ወያኔ የእምዬን ወደ አብዬ ማዞሩ፣ ያ እንዲደመሰስለት ይኾን? መለስ ዜናዊን የሚጠብቀው የሊቢያው ጋዳፊ ዕጣ ፈንታ እንደሆነ ማወቅ አለበት። አንድ “ውኒጥ-ዝኒጥ” የለም! “በነጻ ገቢያ ተሽጦ ገንዘብ የሚያወጣ” የተባለለት ጭንቅላት፣ እንደጋዳፊ የተፋትን መልሶ በአፉ እስኪውጣት ድረስ አያስቀርለትም።

ክፍል ፪፡ የሌባ ዓይነ-ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ

የወያኔን ቅጥፈት ባየሁ ቁጥር፣ ሁሌ ትዝ የሚለኝ፣ አንድ ፒያሳ ያጋጠመኝ፣ ከዚህ በፊት የተረኩላችሁ የሌባ ገጠመኝ ነው። ልድገምላችሁ። ከጓደኛዬ ጋር ወደ አራት ኪሎ ለመሄድ ታክሲ አቁሜ ልሳፈር ስል፣ አንዱ ጎረምሳ ገፍትሮኝ፣ “ታክሲ፣ መርካቶ!” ብሎ ጮኸ። መገፍተሬ ሳያንሰኝ፣ አንደኛው እጁ እኪሴ ውስጥ ግብቶ ሲበረብኝ አገኘሁት። በደመ-ነፍስ፣ ባለኝ በሌለኝ ኃይሌ ተጠቅሜ የሞት ሞቴን እጁን ከኪሴ አውጥቼ ሳይታወቀኝ ጠመዘዝኩት። ታዲያ የወያኔው ብጤ፣ ዓይን-አውጣ ሌቦ ትኩር ብሎ ዓይኔን እያየ በንቀት ፌዝ፣ “በቃህ ነቅተሀል! ልቀቀኝ! የማነው ገገማ!” ብሎኝ አረፈው። ትልቅ ጥፋት ያጠፋሁ መስሎኝ ተደናብሬ ለቅቅኩት። እየሰደበኝ ሄደ። ወያኔ ማለት ከዚያ ሌባ የባሰ ዓይን አውጣ ነው። አያድርስባችሁ! እስቲ ይኸኛው የውሸት ቋጠሮውን በሁልተኛው ክፍል አብረን እናፍተልትለው። http://www.diretube.com/ethiopian-documentary/akeldama-part-2-video_30d42597c.html

ኤዲያ! “ዕድሜ ዘልዛላው” አሉ እኚያ አሮጊት! “የሞኝ ለቅሶ መልሶ መልሶ” ይባላል። ይኸ ሁለተኛው ክፍል፣ ከዚህ በፊት “ሲሉ ሰምታ ...” በሚል ርዕስ የተቸሁበትን ትርዒት ነው የተደገመብን። የያኔው ትችቴ ኢትዮሜዲያ፣ በአዲስ ቮይስ፣ በኢኤመኤፍ እና በዓባይ ሜዲያ ቁጥሩን የማላውቀው ሕዝብ ሲያነበው በራሴ ብሎግ ብቻ ከ10 ሺ ሰው በላይ አንብቦታል

 (http://wondimumekonnen.blogspot.com/2011/09/blog-post.html)።

ብዙ ስድብም ከወያኔ ቡችሎች ቀምሼአለሁ። እዚያ ላይ መጨመር የምፈልገው አለኝ። ወያኔ በሻዕቢያ ተጠፍጥፎ ተሠርቶ፣ ተዘርቶ፤ ተኮትኵቶ አድጎ፣ ለሥልጣን የበቃ ድረጅት ነው። ሻዕቢያ አባቱም እናቱም ነው። ዛሬ ከሻዕቢያ ጋር ተነጋገራችሁ ብሎ ሌሎችን መኰነኑ፣ የሌብነት ሌብነት ነው። እነዚህ፣ በአንድ አልጋ ካልተኛን፣ ባንድ ማዕድ ካልበላን፣ በአንድ ጉድጓድ ካልሸናን ብለው ሥቃያችንን ያበሉን የኢትዮጵያ ጥንድ ጠላቶች አልነበሩምን? ለመሆኑ፣ ከዚህ በፊት ማን ነበር፣ ከሻዕቢያ ጋር ኢትዮጵያን የወጋት! ያደማት! ያለባሕር በር ያስቀራት! ማን አባቱ ነበር፣ ኢትዮጵያን አኬልዳማ ያደረጋት! ከሀዲ የወያኔ መንጋ አልነበረም ወይ! የማን እናት ናት ለምሆኑ አሥመራ ድረስ ሂዳ ለኤርትራ ነጻነት ድምጽ የሰጠችው? ሰሞንን ከዳዊት ከበደ መጣጥፍ አንድ ነገር ተማርኩ። ምን ይላል መሰላችሁ?

“ሆኖም በኣዲ ቛላ፣ ኤርትራ ውስጥ ተወልደው ያደጉት የመለስ ዜናዊ እናት ወ/ሮ አለማሽ ገብረልዑል፤ በምኒልክ ቤተ መንግስት ውስጥ ሲደበቁ፤ ሌሎች ኤርትራዊያን ግን “የአይናቸው ቀለም አላማረንም” ተብለው ተባረሩ። ከነዚህ ተባራሪዎችም መካከል አድዋ ውስጥ የነመለስ ዜናዊ ጎረቤት የነበሩት ሴትዮ፤ “እኔ ለኤርትራ ድምፅ የሰጠሁት ከአለማሽ ጋር አብረን ሄደን ነው። እሷ ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖረች እኔ መባረር የለብኝም።” ብለው እያለቀሱ ቢለምኑም የአይናቸው ቀለም አላማረምና እያለቀሱ የአድዋ ከተማን ተሰናበቱ።”

ለመሆኑ ከወያኔ የበለጠ፣ የሻዕቢያ ደንገጡር በዚህ ምድር ላይ አለ? ከመለስ ዜናዊ የበለጠ፣ የሻዕቢያ ጠበቃ ከየት ሊመጣ ነው? እኛም እናውቃለን። እነሱም ያውቁታል። እኛ እንደምንውቅባቸሁ እነሱም ያውቁታል። ለመሆኑ ማንን ለማደናገር ነው? ለምንኛውም፣ የሚከተሉትን ከህደቶች ለታሪክ መዝግባችሁ አኑሩት! አቦይ ሰበሀት የተባለው ወያኔ፣ “የኤርትራ ነጻነት አደጋ ላይ የሚወድቅ ከሆነ፣ ኢትዮጵያን ብትንትኗን አውጥተን ለኤርትራ ነጻነት እንደገና በረሀ እንግባለን” ያለበት ከነድምጹ ያውላችሁ! http://www.aigaforum.com/audiovideo.html። የካሀዲ የልጅ-ልጅ ከሀዲ መለስ ዜናዊ በኤርትራ የ“ናጽነት” ቀን ተግኝቶ፣ “የጠላቶቻችሁን አከርካሪ ላንዴና ለመሸረሻ ጊዜ ሰብረነዋል” ብሎ ሲቃ እየተናነቀው የተናገረው ከነድምጹ ያውላችሁ። http://www.fettan.com/Documents/Harvesting_of_Planted_Ethnic_Discord.pdf.

ትግርኛ ከሆነ የሚቀናችሁ ትግርኛውም ይኸውላችሁ!

http://www.fettan.com/Documents/Harvesting_of_Planted_Ethnic_Discord.pdf

እና የሻዕቢያ የጓዳ ገረድ ማን ሁኖ ነው እኛኑ መልሶ ልብ የሚያደርቀው? በየትኛው ሞራሉ ነው ማንንም በሻዕቢያ አሸክርነት ሊኮንን የሚችለው? ከወያኔ የበለጠ የሻዕቢያ ተላላኪ ነበረ ወይ?! አይኖርም! አለቀ! ደቀቀ! ዕውነቷ ይኽቺ ናት! በነገራችን ላይ ወያኔ፣ እኔ ከተጣላሁት ሰው ጋር ለምን ተነጋገራችሁ ብሎ የሚኮርፍ አባ ጉልቤ ታዳጊ ሞልቃቃ (bully boy) አይመስላችሁም? ስለአሸባሪነት ከተነሳም፣ ከወያኔ የበለጠ አሸባሪ ከቶ ከየት ሊመጣ ነው?። ዛሬ የሽብርተኝነትን ሕግ የቀዳሁት ከአሜሪኖቹ ነው የሚለን አሸባሪ፣ ስለሱ አሸባሪነትስ፣ በአሜሪካኖቹ የሚሉትን ያውቅ ይሆን? ይኸውላችሁ ሀቁ!

http://www.start.umd.edu/start/data/tops/terrorist_organization_profile.asp?id=4287

ወያኔ ጭርሶ ተጨማልቋል። ጭምልቅ ብሏል! አንድ ወራዳ ሥራ ይሠራና ሰው “ግድ! ጉድ!” ሲል ከዚያ የባሰ ወራዳ ሥራ ሠርቶ ነው ነው የመጀመሪያውን ግዙፍ ውራዳውን ሥራ በቀጣዩ ሱፐር ግዙፍ የቀድሞውን ውርደት የሚያደንከው። “ኢህአዴግ መስማትና ማየት የተሳነው መንግሥት አይደለም!” እያለ መልስ ሲቀባዥር ሰምተነዋል ትርዒቱ እዚህም ይደግማል። አንደኛ መስማትና ማየት የተሳናቸው እዚህ ላይ “እሪ” ማለት አለባቸው። ሰብአዊ መብታቸው በአንድ አባ ጉልቤ ጠቅላይ ስቃይ ተደፍሮባቸዋል። ሁለተኛ፣ እነ እስክንድርናና የአንደነትን መሪዎች ለማሰር ሲነሳሳ ያደረገው የፓራላም ድንፋታው ገና ለግና ሕግን ያለቦታው እንደሚጠቀም (abuse of power) እየነገረን ነበር። የሕግ ያለህ! መቼም የጊዜ ጉዳይ ነው። “የሽሮ ድንፋታ እንጀራ እስኪቀርብ” ነበር የተባለው? ይኸቺ ጊዜ ታልፋለች! እያንዳንዱ ምድረ-ወያኔ መንጋ ኢትዮጵያና ሕዝቧ ላይ ለፈጸመው የክህደትና የወንጀል ሥራ እንደ አጎቱ፣ እንደ ኃይለሥላሴ ጉግሳ ይጠይቅባታል። ወያኔዎቹ ብቻ ሳይሆኑ፣ ጀሌዎቹም ጭምር የሚጠይቁበት ጉዳይ ነው። ግፍ በዝቷል። ጽዋው ሞልቶ ፈሷል! ይቅርታ የሚባልበት ጊዘ አልፏል። አንገሽግሾናል!

እንዲያው በሞቴ፣ እነአንዳርጋቸውና ብርሀኑ ነጋ ምንኛ የወያኔን ካምፕ እንቅልፍ ነስተውታል ጃል! እኛ እኮ እዚህ እንሱን የምናያቸው እንደማንኛውም ተራ ዜጎች ነው። ጉድ እኮ ነው! እኔ እንዳርጋቸውን በመጠኑም ቢሆን አውቀዋለሁ። የምንገናኝበትም ሁኔታ አለ። በወያኔ የሽብርተኝነት ሕግ፣ እኔም እንደ እነስክንድር ሽብርተኛ ነኝ ማለት ነዋ! ቆይ እንጂ! በአንድ ወቅት አንዳርጋቸው፣ የወያኔ ማዘጋጃ ቤት ሹም አልነበር እንዴ! ታዲያ ከአንዳርጋቸው ጋር የተነካካ ሁሉ ሽብርተኛ ከሆነ፣ ከዚህ በፊት ቀጥሮት ሲያሰራው የነበረ ወያኔስ ምን ሊባል ነው? አንዳርጋቸው ሳያውቅ ምናልባት ከሽብርትኞች ጎራ በገባበት ዘመን ሳይከሰስ፣ ዛሬ ከሕዝብ ወገን ሲሆን ነው “አሸባሪ” ሲሆን ነጉር ሁሉ የተገለቢጦሽ ነው። ለመሆኑ አንዳርጋቸው ማንን ነው የሚያሸብረው! ወያኔን ከሆነ እያሸበረ ዕንቅልፍ የሚነሳው፣ ነገሩ ሌላ ነው። እንደኔ ያለው ተራው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን፣ አንዳርጋቸው የወያኔ ስለባ ከመሆኑና የሕዝብን ብሶት ከማጋባቱ በስተቀር ሽብርተኛ አድርጎ አያየውም። ለመሆኑ ለ17 ዓመታት ሙሉ ሕዝቡን በጠብመንጃ፣ በቦምብ ሲያጋዩት በርሀ ከርመው፣ ላለፉት 20 ዓመታት ደግሞ ስልጣን ላይ ፊጥ ብለው ሕዝቡን የሚያሸብሩት፣ አሸባሪዎች ምን ሊባሉ ነው? አሸባሪዎቹስ የምኒልክን ቤተመንግሥት በጉልበት የያዙ የኢትዮጵያ ጠላቶች፤ የተገንጣይዋ ኤርትራ ጠበቃዎች፣ እነመለስና ግብረአበሮቹ ናቸው። ይኸንን የምንለው እኛ የወያኔ ስለባዎች ብቻ አይደለንም። የዓለም ታዛቢዎችም ብለው ጨርሰውታል። ከፈለጋቸውሁ ይኸውላችሁ! http://www.youtube.com/watch?v=4WsV6fJJ51Q።

ክፍል ፫፡ ወያኔያዊ እኵይ ከፋፋይ ድርጊት በትርዒት

ወያኔ እስካሁን ከሠራው የወራዶች ትርዒት ሁሉ ሶስተኛው ከፍል የሚግለማ ነው።

http://www.ethiotube.net/video/16614/Must-Watch-ETV-Documentary--Akeldama--Part-3--The-case-for-Ginbot-7

ኤጭ! የፊተኞቹን ሁለቱን ርሷችው! ይኸን ትርዒት ነው ልብን ብግን የሚያደርገው። ሰው ሁሉ ልብ ብሎ አድምጦት ወስኖ ከነዚህ መዥገሮች ለመላቀቅ ቆርጦ መነሳት ያለበት።

ያን ዓይኑ እንደጉርጥ የተጎረጠረጠ ሞጋጋ ዝግጀት አቅራቢን፣ ከየት አገኙት? አስጠሊታ! ጻረ-ሞት (gohst) የመስላል። የካድሬነት እንጂ የጋዜጠኝነት ሙያ የማይታይበት የወያኔ ዕቃ! እዚህም ክፍል ውስጥ አንዳርጋቸው ጽጌና፣ እነዶክተር ብርሀኑ ነጋን በመኮነን በማላዘኑ ይቀጥላል። በዚህ አቀራርብ፣ የግንቦት ሰባትን አባላት የሆኑትንም ያልሆኑትንም እየጨፈለቀ ይዘባርቃል። ጽሑፉ፣ ወይም ስክሪፕቱ፣ በመለስ ዜናዊ የተደረሰ የዘረኞች ድርሰት መሆን አለበት። ለዛው ሙጥጥ! ትልቁ ኢሰብዓዊ የሆነው ድርጊቱ፣ በእስር ቤት ይዞ የሚያሰቃያቸውን ሰለባዎቹን (victims) በዱላና በመሣሪያ እያስፈራራ እያቀርበ ማናዘዝ ነው። በነገራችን ላይ በደርግ ዘመን እንደዚህ ስቃይ የበዛበት ወጣት፣ ዱላው እንዲቆምለት “ታንክ ከወላጆቼ ቤት ጓሮ ቀብሬአለሁ” ብሎ መርቶአቸው ጉድጓድ እንዳስቅፈረ ይተረካል። ቀለደብን ብለው እዚያው ገድለዉት በቆፈሩት ጉድጓድ ቀብረውት ሄዱ። “Under duress” ወይም “በሥቃይ ተይዞ” የሚባል ሕጋዊ አንቀጽ በዓለም ሕግ እንዳለ የወያኔ ቦዘኔ መንጋ ያውቅ ይሆን? መንግሥቴን ሊገለብጡብኝ ነው ብሎ አስሮ ደብድቦ እነ አቶ አሳምነው ጽጌና ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ፣ ሌተና ኮሎሌል የሺዋስ አጥናፈ፣ ሌተና ኮሎኔል አስቻለው አምባቸው ላይ የፈበረከባቸውን ሸር እዚህም ደገመው። እነ ደበበ እሸቱ ላይ ተጠቀመ። እነዚያ ላይ የተጠቀመው ዘዴ፣ ከሥቃይ ብዛት አንደኛው በሌላው ላይ መስካሪ አንድርጎ ማስለፍልፍ ነበር። አሁንም ያንኑ አደረገው። ኤሊያስ ክፍሌ የግንቦት ሰባት አባሉ ሁኖ ቀርቧል። የውሸት ውሸት! ሀፍረተ ቢሶች! ኤሊያስ የወያኔን እርኩስ ሥራ ከማጋለጥ በስተቀር የማንም ፓርት አባል ሁኖ አያውቅም። ሲያስፈልገውም፣ ግንቦት ሰባትን ሲያብጠለጠለው እናነበዋለን። እሺ የኤሊያስስ ይሑን፣ አበበ ገላውን መክሰሳቸው፣ በደኅና ሕሊናቸው ነው? “የአራት ኪሎው ማም ቂሎ” ብሎት አልፈው ጓደኛዬ!

ከሁሉ ከሁሉ የሚገርመኝ፣ ወያኔ በደል በፈጸመ ቁጥር ዓይኑን ብልጥጥ አድርጎ “ይቅርታ ጠይቁኝ” ማለቱ ነው። ዓይኑ ይጥፋና! አንድ “ታዲዮስ አንተነህ” በሚል ስም የሚጽፍ የወያኔ ቡችላ ሰሞኑን ምን ያለኝ መሰላችሁ። የስድብ ጋጋታዉን ካዥጎደጎደው በኋላ፡ “ይልቅ ይቅርታ ጠይቀህ፣ ከሕዝብ ወግን ተቀላቀል” ነበር ያለኝ። በጣም ስለገረመኝ፣ ለብዙ ደቂቃዎች እዚያ ዐረፍተ-ነገር ላይ ፍዝዝ ብዬ ቀረሁ! ይገርማል! ይኸ የባንዳ ልጅ ባንዳ አገር ሻጮችን “ይቅርታ ጠይቅ” ይበለኝ!!! እኔን ነጻውን ስደተኛ ዜጋ ከማይደርሱበት የስደት ቤቴ “ይቅርታ ጠይቅ” ሊሉኝ የደፈሩ ወራዶች፣ እነዚያ በቁጥጥሩ ሥር ያሉትንማ እንዴት ያሰቃዩአቸው? መለስ ዜናዊ አንዴ ሲጨማለቅ የሰማሁት ትዝ አለኝ። “ከኦነግ የበለጠ የጎዳን የለም። ዳሩ ግን መሪዎቹ ይቅርታ ስለጠይቁን በሰላም በቦሌ በኵል አገር ለቀው እንዲሄዱ ፈቅደንላቸዋል ሸኘናቸው። ፕሮፌሰር አሥራት፣ ከሆነግ የበለጠ በደል እኮ መንግሥታችን ላይ አላደረሱም። ይቅርታ ቢጠይቁን ልንለቃችሁ እንችላለን” ነበር ያለው ለጥያቄ አቅራቢው የውጭ ጋዜጠኛ! ወይኔ የሰውዬው ልጅ! በኋላስ! የቅንቅጅት መሪዎችን አፍሶ በአሰረ ማግስት፣ ተላላኪዎችን “ሽማግሌ” ተባዮቹን ጉዶች ልኮ ምን ነበር ለማግኘት የተሟሟተው? “ይቅርታ ይጠይቁኝ” ነበር ያለው። ከብዙ ውትወታ በኋላ “ይቅርታዋን” እንደፈለጋት አገኛት። ለመሆኑ “ይቅርታዪቱ” ከልባቸው መስሎት ይኾን? ዳሩ ግን፣ ከፋፍሎአቸው የሚፍልገውን አግኝቷል። ከተለቁቁም በኋላ፣ ብትንትናቸውን አውጥቶ እንዳይነሱ አደረጓቸዋል። “አከርካሪአቸውን መታን!” ብሎም ፎከሯል!

በእስር እንግልትም ቅስም መስበር ልማዱ ነው። ቅስም ለመስበር ደግሞ የማይጠቀመው ወራዳ ሥራ የለም። ለምሳሌ አንዷ የኦሮሞ ብሔራዊ ጎንግሬስ አባል ላይ ያደረሰውን በደል የቀድሞ ባለሥልጣናቸው የነበረ ሰው ሲነግረኝ፣ ሰውነቴን ሰቀጠጠኝ። አንድ የነሱ፣ ሰላይ አድናቂዋ መስሎ ቀረባት። እሥሯም ጉዳይ አስፈጻሚ መስሎ ጉድ-ጉድ እያለ አመኔታዋን አገኘ። በኋላ፣ እንዴት አድርጎ እንደመረዛት፣ እራሷን እንድሰት እንዳደረጋት፣ ከዚያ በኋላ እሷ ሳታውቅ ወራዳ ፎቶዎች እንዳነሳት፣ ወደ ልቧ ስትመለስ የወያኔ መንጋ ያንን ፎቶግራፍ አሳይቷት በወገኖቿ ላይ እንደትዘምት እንዳስገደዳት (blackmail)፣ ቅስሟን እንደሰበረና ከትግል ውጪ እንዳደረጋት አጫወተኝ። ከዚያ በኋላ ያች ጀግና ልጅ ሰው አልሆነችም። “አንቀጽ 39 ለነሱ ለአናሳዎቹ ይረዳቸው እንደሆነ እንጂ ለኛ ለብዙኃኑ ኢትዮጵያውያን ኦሮሞዎች ምናችንም አይደለም” ያለችው ጀግና ስነ-ልቦናዋ ተሰልቦ ከጨዋታ ውጭ ሆነች። አገር ጥላም በረረች። ያለችበትም አይታወቅም። ጭጭ ምጭጭ አደርጋት!

እህታችንን ብርቱካን ሚዴቅሳን እሥር ቤት ምን እንዳደረሰባት እስካሁን በግልጽ የተነገረ ነገር የለም። ብቻ ያደረገውን አድርጎ ያችን የአንበሳ ግልገል፣ “አጥፍቸአለሁ! ይቅርታ!” አሰኝቷት ለቀቃት! ይቅርታውን አግኝቷል። ብርትኳን ከስነ-ልቦናዋ ቁስል እያገገምች ነው። ብርቱካን! እንወድሻለን! አይዞሽ! በርቺ! ባለሽበት፣ አምላካችን ካንቺ ጋር ይኹን። እልባችን ቀርጸነሽ ይዘንሻል! የኛዋ ኦንግ ሳን ሱኪ!

ወያኔ ምን ጊዜም ቢሆን አስገደዶ ይቅርታ ቢያስብል፣ ልባዊ ይቅርታ ከማንም ኢትዮጵያዊ አያገኛትም! ሰው በድሎ ይቅርታ ጠይቁኝ የሚል አምባገነን ምናልባት ወያኔ ብቻ መሆን አለበት። ይኸ እንከፍ ቡድን ሰው አሰቃይቶ ይቅርታ ቢያሰኝ ዕውነት ያስገበረ ይመስለው ይኾን? እንዚህ መንጋዎች ከጫካ ከወጡ ሀያ ዓመት ቢደፍኑም፣ አሁንም እንደ ዱር አውሬ ነው የሚቅበዘበዙት። ከሁሉ ከሁሉ የሚያሳዝነው፣ በጁ ይዞ ካስለፈለፋቸው ሰዎች ሁሉ፣ የደበበ እሸቱ ቅስም መሰበር ነው። ጀግናው ደበበ፣ ተሰበረላቸው! ጀግናው ደበበ ግንቦት ሰባትን አወገዘላቸው። ብርሀኑ ነጋን ሰደበላቸው! ሲናገር የሰከረ እንጂ በብሩህ ልቦናው እንዳለ አይመስልም። ጸጉሩ ተንጨባሯል። ያበደ ነው የሚመስለው። “መንግሥት እኮ በግልጽ አስቅምጧል” ይላል ደበበ ዕንባ እየተናነቀው። “ግንቦት ሰባት አሸባሪ ድርጅት ነው ብሎ አስቀምጧል። እዚህ አገር ሁኜ፣ በየዕለቱ የሚሰጠውን መረጃ እያየሁ፣ አሸባሪ ነው ተብሎ ከተፈረጀ ድርጅት ጋር ለምንድነው፣ በምንም መልኩ ይኹን ግንኙነት ያደረግኩት! ይኸ ነው የሚያስጸጽተኝ” እያለ በራሱ ላይ የፈርዳል! በቤታቸው አዋርደውታል! ቅስሙን ሰበረውታል! ወንድሜን!!! የሚፈልጉትን ብሎላቸው ከእስር ቤት ወጣ። በነሱ ቤት አብቅቶለታል! ከዚህ በኋላ ሰው የሚሆን አይመስላቸውም። እኛ ግን እነሱ እንደፈለጉት አናወግዘውም። ማንም ሰው በጠላት እጅ ሲወድቅ፣ ጠላት የሚፈልገውን ተናግሮ ስቃዩ እንዲቀርለት የሚያደርገውን መለፍለፍ የሥነ-ልቦና ሊቃዉንት በግልጽ አብራርተውታል። ፒ ኤ ዲ (ዶክተሬት ድግሪ) ተሠርቶበታል። ነጻ ሲወጣ ዕውነቱን ይናገራል።

ስለእስክንድር ማለት የምፈልገው ነገር አለ። ወያኔ ያን ሁሉ ማስፈራራት ካደረሰበት በኋላ፣ መጽሐፉን እንዳይታትም ከለከለው። ያንን መጽሐፍ ጓደኞቼና እኔ ልናሳትምለት ታጥቀን ተነስተን። አንድ እስክንድር ያስጠነቀቀኝ ጉዳይ ቢኖር፣ ያንን መጽሐፍ ለማሳተም ከተሰብሰብን ቡድን መሀል አንድም የፖሊቲካ ድርጅት አባል እንዳይኖር ነበር ያለኝ። የትኛው ፍርድ ቤት ቀርቤ ዕውነቱን ልመስክር! ወይኔ የአቶ ሰውዬው ልጅ! በዚህ የተነሳ፣ ሌሎች ፈቃደኛ የሆኑቱን ሶዎች ሁሉ ነበር አይሆንም ብዬ ያስቀርሁት። መጨረሻ ላይ አንዳንድ ነገሮች ስላሳሰቡኝ፣ “እኔ የወያኔ ነቃፊ ስለሆንኩኝ፣ ምናልባት በኔ ምክንያት እንዳያጠቁህ፣ ሌላ ሰው ልወክልና ጀርባ ልሰለፍ” አልኩት! “የለም! አንተማ ወደ ጀርባ መሰለፍ አያስፈልገህም! ጓደኞቼን ሁሉ ወያኔ ሊመርጥልኝ አይችለም። የፖሊቲካ ድርጅቶችን ብቻ አስወግድ። ወያኔ ሊያጠፋኝ ሲነሳ ምንም ዓይነት ተጨባጭ ምክኒያት ሊኖረው አያገባም። ሳያመካኝ ይብላኝ!” ነበር ያለኝ። ይኸ ሰው ነው እንግዲህ፣ ከሻዕቢያና ከግንቦት ሰባት ጋር ግኑኝነት አለህ ተብሎ ለእስር የተዳረገው። ቢኖረውሳ! የአሜሪካን፣ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ ጋዜጠኞች አፍጋኒስታን ተራራ ድረስ ሂደው ታሊባንን ያነጋግሩ የለም እንዴ! የሕሊና ደንቆሮ!

ወያኔ የመሀይም ጥርቅም ነው። ከጫካ እንደውጧት አንድም ያልተለውጡ የወንበዴ መንጋ የተጠራቀሙበት ዋሻ ነው። የሰላጠነ አገርማ፣ የሕግንና የሚዲያን ልዩነት ጠንቅቆ ያውቃል። ለፍዳዳው የወያኔ አፈ-ቀላጤ “ይኸ አገር እኮ በሕግና ሥነ-ስርዓት የሚመራ ነው ብሎ ሲመጻደቅ” ስሰማ ሊያመኝ ተናነቀኝ። በሕግና በሥነ-ሥርዓት የሚመራ አገርማ ውስጥ፣ በመጀመሪያ ደረጃ፣ በፍርድ ቤት የተያዘውን ጉዳይ በሜድያ ላይ፣ ያዉም በከሳሹ በመንግሥት ቴሌቪዥን ወጥቶ አይዝረከረክም። ነጻ ፍርድ ቤት ቢኖርማ እንዲህ ዓይነት ብልግና መንግሥት ሲፈጽም ሲያይ ጉዳዩን ወርውሮት ተከሳሾችን በነጻ ይልቅ ነበር።

በዚህ ፊልም፣ በጣም አስቂኝና አሰልቺ የግንባታ መንግስሥት ተረት-ተረት ሲተላለፍ እንሰማለን። ይገርማል! የጥፋቱ ገዥ የልማት መንግስት ነኝ ለማለት ይጣጣራል! ሰው ጦሙን ማደሩን ማን በነገረው! በልማት አመካኝቶ ገንዘብ ለመሰብሰብ እንዳበደ ውሻ ይሯሯጣል። ያ ቀላባጅ ፕሮግራም አቅራቢ እንዲ ሲል ፕሮግራሙን ይደመድማል።

“ለአሸባሪዎቹና ለዕኵይ ተግባራቸው ቀዳዳ ከፍተን ዕድል ከፈጠርንላቸው አንድ ቀን ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት ሁሉ፣ አባት፣ እናት፣ እህት፣ ወንድም ወይንም እጅግ የምንወዳትን ሕይወታችንን ሊነጥቁን እንድሚችሉ መርሳት የለብንም። አሁንም፣ ሽብርተኝነት የመኖራችን ሕልውና ሥጋት እየሆነ መጥቶብናል። በመሆኑም እያንዳንዱ ዜጋ አካባቢውን በንቃት መጠበቅ ይኖርበታል። ለሀገሩ ሰልምና ልማትም ዘብ መቆም ይጠበቅበታል። እኛ ኢትዮጵያውያን ከሰላማንና ከልማታችን በላይ የሚበልጥብን ምንም ነገር የለም። አሸባሪዎቹ፣ በጥፋት መንገዳችው ሲዳክሩ፣ እኛ በሕዳሴ መንገዳችን እንቀጥላለን።”

ውይ! ተባለ እንዴ! ይኸን ሁሉ ሲለፈልፍ ታዲያ፣ አሜሪካ ውስጥ፣ በመንታ ሕንጻዎች ላይ የደረሰውን አደጋ ፊልም እያሳየ ነው። እሱ ስለሌለው ልማቱ ሲደሰኩር፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደነቃበት ከዚህ በታች ባለው የጸሎት መርዶ እናርዳውና እኛም በበኩላችን ቅስሙን እንስበረው። አሁንም ከሩቁ ወዳጄ ከጋዜጠኛ ከዳዊት ከበደ ያገኘሁት፣ ወያኔን “ሕዳሴ” እያለ “የአባይ መገደቤ ነው፣ ገንዘብ አምጡ” እያለ ሲይስጨንቅቸው፣ የአዲስ አበባ አራዳ ወጣቶች የደረሱት ጸሎት ነው።

የአባይ ህዳሴ ፀሎት

አባያችን ሆይ፣
በበርሃ የምትኖር፤
ስምህ ይመዝገብ፣ ግብርህም ይምጣ።
ማረፊያህ በግብፅ እንደሆነ፤ እንዲሁም በህዳሴው ላይ ይሁን።
የእለት ውሃችንን ስጠን ዛሬ፤
ደሞዛችንን ይቅር በለን፤
እኛም የጠየቁንን እንደምንሰጥ።
አቤቱ ወደ ቦንብ ግዢ አታግባን፤
ከብድር አድነን እንጂ።
ቦንድ ያንተ ነውና፤
አይ መብራት ኃይል፤
ለዘለአለሙ፤
አሜን።

ወያኔን ለማስወገድ ሁላችንም ከመተባብር ሌላ ምርጫ የለንም። ታስረው የሚንገላቱትን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ከጎናቸው ከመቆም ሌላ አማራጭ የለንም። ወያኔ ሺህ ጊዜ ትርዒት ቢያቀነባብር፣ ለራሱ ይዝናናበት እንደሆን እንጂ ሀቋን አይቀይራትም። እስከዘልዓለም ልባችንን አያገኛትም! ውጭ ያለነው፤ ወያኔ ላይ ማመጽ አለብን! እያንዳንድህ! እያንዳድሽ ወግኔ ታጥቀህ ተነስ! ታጥቀሽ ተነሺ! ወያኔ ላይ፣ ጥርስህን ንከስ! ጥርስሽን ንከሺ! ልብህን ዝጋበት! ልብሽን ዝጊበት! አበቃ!|

Wednesday, 2 November 2011


Aninet's Organ -

Wednesday, 5 October 2011


ሰንደቅ ዓላማችን
ከወንድሙ መኰንን፣ ኤልስበሪ፤ ኢንግላንድ፣ መስከረም ፳፬ ቀን ፪፼፬ ዓ. ም
ወያኔ ወደ ሥልጣን የመጣው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እያጋየ ነበር። የጨው መቋጠሪያ ጨርቅም አድርጎት ነበር፡፡ በመጣም በነጋታው ሕገ-መንግሥቴ የሚለውን መጨቆኛ መሣሪያ ለማጽደቁ ኑ ብሎ በጠራቸው የሱ ብጤ ዘረኞች ስብሰባ ላይ ሰንደቅ ዓላማችን፣ ሲዋረድ፣ ሲብጠረጠር እንደነበር ለታሪክ ዩ-ትዩብ በተባለው የዘመኑ የድምጽና የተንቀሳቃሽ ስዕል ማሳያ የድረ ገጽ ማሳያ ላይ ለሕብረተሰቡ ለዕይታ በቅቶ ይገኛል።
ያንን ጉድ ስንሰማ ስንቶቻችን በገንን።
ሰንደቅ ዓላማችን እንዳገራችን እራሷ ባለታሪክ ናት። ሰንደቅ ዓላማችን፣ እነሱ እንዳሏት “ጨርቅ” ብቻ ሳትሆን ስንት ደም የፈሰሰባት ወድቃ የተነሳች ልዩ የታሪካችን መዘክርና የማንነታችን ማብሰሪያ ሰንደቅ ናት። በነገራችን ላይ በተለምዶ “ባንዲራ” ትባል እንጂ ትክክለኛው አጠራሯ “ሰንደቅ ዓላማ” ነው። ባንዲራ በጠላት ወረራ ጊዜ እንድንቀበለው ወራሪዎች የዶሉብን ወይም የተበከልንበት “አልለቅ” ያለን የጣሊያን ቃል ነው። ጠላት ወርሮን አራዳን “ፒያሳ”፣ አዲስ ከተማን “መርካቶ” እንዳላትና ለሌሎቹም ካክዛንቺስ፣ ፖፖላሬ፣ ባምቢስ ብሎ ሰይሞ ተጣብቀውብን እንደቀሩት የቦታ ስሞች እንደማለት ነው። ባህር ምድርንስ ኤርትራ ብሎ ሰይሞ አይደል ጉድ ያፈላብን!
ከአምስቱ ዓመታት የጠላት ወረራ በስተቀር ይኽች ሰንደቅ ዓላማ ለብዙ መቶ ዓመታት ዓርማችን ሁና አገልግላለች። ቀይና አርንጓዴው ቦታ ቢቀያየሩም፣ ብጫው ከመሀል ሁኖ ከኛ ጋር የኖረች አርማችን ናት።
ሰንደቅ ዓላማችን ከ ፲፰፻፸፫ (1881)[1]  እስከ ፲፰፻፹ (1887) ዓ.ም. ድረስ ይኸን ስዕል እንደምተመስል ከታሪክ መዘክር ማውቅ ችለናል።










በአጼ ምኒልክና በንግሥተ ነገስታት ዘውዲቱ ምኒልክ ዘመን መንግስታት ከ፲፰፻፹ (1887) እስከ ፲፱፳፰ (1936) ዓ. ም. ሰንደቅ ዓላማችን፣ ምንም ዓይነት ምልክት ያልተለጠፈባት ሁና እንደሚከተለው ተሽሞንሙና እናገኛታለን።













ይኸች ሰንደቅ ዓላማ ነበረች፤ አደዋ ድረስ ዘምታ በአሸናፊነት ወደ አዲስ አበባ የተመለሰችው። ይኽችን ሰንደቅ ዓላማ መሆን ነበረባት ዘርዓይ ድረስ በጁ ጨብጦ የብዙ ጣሊያኖችን አንገት በጎራዴ ሮም ላይ የቀላው። መሰረቷ ሶስቱ ቀለማት ናቸው።
መቸም ታሪካችን ውጣ ውረድ የሞላበት ነው። ጠላት በ፲፱፳፰ (1936) ዓ.ም. ሲወረን፣ ሰንደቅ ዓላማችንን እንደወያኔዎቹ አብጠልጥሎ ሳይሆን በክብር አውሮዶ አታጥፎ ካስቀመጠ በኋላ፣ የራሱን፣ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ እና የሶማሌ ውሁድ የምስራቅ አፍሪካ ጣሊያን ኤምፓየር ብሎ ሰይሞ “ባንዲራ” ሠርቶ አንጠለጠለላት። የኛ ሰንደቅ ዓላማ “ወደቀች” የሚባለው በዚህ የአምስት ዓመት የጠላት ወረራ ነበር። ዕውነቱ ግን ጠላት ሰንደቅ ዓላማዋን ከጃንሆይ ግቢ አውረዳት እንጂ አልወደቀችም። ሰንደቅ ዓላማዋ አርበኞችን ተከትላ በረሀ ገባታ ተዋጋች እንጂ አልተጣለችም። ሰንደቅ ዓላማችንም እንዳባቶቻችን እራሷን ችላ አርበኛ ናት! ያችን ሰንደቅ ዓላማ ያከበረና የያዛት ሁሉ በአሸናፊነት እንደሚወጣ የተመሰከረላት በዚህን የችግር ጊዜ ብሩህ ተስፋ ነበረች። የሚከተለውን የምሥራቅ አፍሪካና “ባንዲራ” የነመለስ አያት እና መሰሎቻቸው ባንዳዎች ያጎበድዱላት ይሆን ይሆናል እንጂ የኛዋስ በየዱር ገደሉ ስትውለበለብ ነበር። "ባንዲራ" ማለት ይኽች ናት። በቃሉም ውስጥ “ባንዳ” ይገኝበታል። ሌላም አስጸያፊ ቃል በውስጧ ይገኝባታል።። አልለውም ግን። 
-

በየአደባባዩ ከሞቅዲሾ እስከ አሥመራ ይኸንን “ባንዲራ” ብላ ጣሊያን ብታውለበልበውም፣ የኛ ዕውነተኛ ሰንደቅ ዓላማ ግን አርበኞቹ ባሉበት ሁሉ፣ ሲንቀሳቅሱ ከፍ አድርገው ተራ በተራ ሲሸከሟት፣ ሲያርፉ፣ በየእንጨቱ እያውለበለቧት በየዱር በየገደሉ ተሟሟቱባት። በቆላ በደጋ ለአምስት ዓመታት ተዋግተው ነጻነታቸውን ሲያስመልሱ፣ ኦሜዴላ ላይ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተወለበለበች ሰንደቅ አሸናፊዋ ዓላማችን አረንጓዴ፣ ብጫ፣ ቀይ የሆነች ሌጣ መለያችን ይኽች ነበረች። ቀዩና አረንጓዴው ቦታ እንዴት እንደተቀያየሩ ለታሪክ ባለሙያዎች ትቼዋለሁ።



















በኋላ ላይ ግን ያው ዘውዱን የጫነ አንበሳ ተቀምጦበት ኦፊሴላዊ በሆነ ቦታ ላይ ሲውለበለብ፣ በየመሥሪያ ቤቱ፣ በየትምሕርት ቤቱ ይወጣና ይወርድ የነበረው የግድ ዘውድ ያያዘ አንበሳ ያለበት ሳይሆን መሠረታዊው አርንጓዴ ብጫና ቀይ ሰንደቅ ነበር። መሠረቱ ምንጊዜም ሶስቱ ቀለማት ናቸው። ንጉሡም ሆኑ ባለሟሎቻቸው የሚያውቋት ያችኑ በአረንጓዴ ብጫ ቀላማት ያንቆጠቆጠችውን ሰንደቅ ዓላማችንን ነበር። ትርጉሙም፣ አርንጓዴ ልምላሜንና ዕድገትን፣ ብጫው ዕምነትን (በእግዚአብሔር ማመንን) እና ቀዩ ኢትዮጵያዊው ሁሉ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ጉራጌ ጊሚራ፣ ወላይታ፣ አደሬ፣ ሲዳማ ትግሬ፣ እስላም ክርስቲያን ሳይል በአንደነት ደሙን አፍሦ፣ አጥንቱን ከስክሶ የወጃትን አገራችንን የሚያወሳ መሰዋዕትነትና ጀግንነትን ነው። አንድም ሰው፣ “ወድቆ በተነሳቸው ሰንደቅ ዓላማችን” ሲባል፣ ቀጥ ያላል። ሰንደቅ ዓላማችን የራሷ የሆነ ልዩ ክብርና ልዩ ፍቅር ሕዝባችን ዘንድ ነበራት።

እያንዳንዱ ሕብረተሰብና እያንዳንዱ ቤተሰብ ጋ ይኸች ሰንደቅ ዓላማ የየበተሰቡ እንደ አንድ አባል ሁና ነበር የኖረችው። ዛሬም አለች። በትግራይ፣ አንድ ትልቅ ሰው ሲሞት ክብሩ የሚለካበት፣ ሬሳው ሰንደቅ ዓላማ ለብሶ ወደ ቤትክርስቲያን ሲሄድ ነው። ያንን እንኳ ወያኔዎች አልተገነዘቡትም! ታዲያ ዘውድ የግድ ያለበት አልነበረም፣ አይደለም። ዘውድ ያለበት የሚውልበለበው ኦፊሴል በሆነ ንጉሡ ወይም እንደራሴአቸው ባለበት ብቻ ነው። ይኸች ሰንደቅ ዓላማ ከ፲፱፳፰ (1936) እስከ ፲፱፻፷፮ (1974) ኦፊሴላዊ በሆነ ቦታ ብቻ ከነዘውዱ ተውለበለበች። በየትምሕርት ቤቱ ሲትወጣ፣
ደሙን ያፈሰሰ ልቡ የነደደ፣
ባርበኝነት ታጥቆ ጠላት ያስወገደ፣
ንጉሡን አገሩን ክብሩን የወደደ
ነጻነቱን ይዞ መልካም ተራመደ፡፡
ገናናው ክብራችን ሰንደቅ ዓላማችን፣
ያኮራሻል አርበኝነታችን፡፡

እየተባለ እየተዘመረ ትወጣ ነበር። የሚሄድ ሁሉ በያለበት ይቆማል።
ሲትወርድ ደግሞ

ተጣማጅ አርበኛ በአገር መውደድ ቀንበር፣
ገዳይ ድል አድራጊ ደም አፍሳሽ ወታደር፣
አንቺን እያሰበ ይጓዛል ሲፎክር፣
ሰንደቅ ዓላማችን የነጻነት አገር

እየተባለ ሲዘመር አሁንም የሚንቀሳቀስ ሰው ቀጥ ይላል፣ የተቀመጠ ተንስቶ ቀጥ በተጠንቀቅ ይቆማል።

በ፲፱፻፷፮ (1974) ደርግ ሥልጣን ስይዝ፣ እስከ ፲፱፻፷፯ (1975) ዘውዱን አውርዶለት በኦፊሴል ሲጠቅም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ግን ሌጣው እንዳለ ሕዝቡ ይጠቀምበት ነበር። ትንሽ ቆይቶ ደርግ ኦፊሴሊያዊ በሆነ ቦታም ጭምር በየስብሰባው ያለ ዘውዱ አንበሳውን ያስቀምጥበት ጀመር


ከመሠረታዊውን አረንጓዴ ብጫ ቀዩን ግን ማንም ሊደፍር አልሞከረም። እንዲያውም መስከረም ፪ ቀን ፲፱፻፷፯ (1975) አምበሳውንም እስካናካቴው አነሳውና ሌጣ አርንጓዴ ብጫ ቀይ ኦፌሰሊያዊ ለሆነ ስብሰባ ሁሉ ሳይቀር የሚውለበለብ ተደርጎ መጠቀም ተጅምሮ ነበር።


ወዲያው፣ ትንሽ ቆይቶ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት፣ "የሕብረሰብዓዊት ኢትዮጵያ ጊዚያዊ ወታደራዊ መንግሥት" አርማ ቀርጾ መህል አስቀመጠና ኢፊሴሊያዊ በሆኑ ቦታዎች ይጠቅም ነበር፡፡ ሕዝቡም ሆነ መሥሪያ ቢቶች ግ ን ልሙጡን ከመጠቀም የሚያስገድዳቸው ሕግ አልነበረም፡፡



በኋላ ላይ ደርግ “ሕብረተሰባዊት ኢትዮጵያ”ን ሲያውጅ አንድ ያንን የሚያንጸባርቅ አርማ አስቀምጦበት ነበር። ልብም ያለው የለም። እነሱም ሆኑ ሕዝቡ ግን ያው ምንም ዓርማ ያልነበረበትን ነበር ይጥቀሙ የነበሩት።
በኋላ ላይ በ፲፱፻፸፯ (1985) ዓ.ም ላይ “የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት” መሰረትኩ ሲል አርማውን ቀየረ።


ሌጣው ግን ምንጊዜም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማነቱን እንኳን መከራከርና የጠየቀም አልነበረም። እንዴት ተደርጎ! ሁሉም አረንጓዴ ብጫውን አቅፎ በየቤቱ በየበዓላቱ ያውለበልብ ነበር።

በታሪካችን ሰንደቃላማችን የተዋረደችው ከወራሪው ጣሊያን በበለጠ በዚህ በወያኔ ዘመነ ፍዳ፣ ዘመን ኩነኔ ነው። አንደኛ፣ ከበረሀ ጀምሮ ቤተመንግሥት እስኪደረስ ድረስ ሰንደቅ ዓላማችን ወያኔ እንዳቀጠለና፥ እንደቀደደ፥ እንደረገጠ ነበር። አዲስ አበባን ሲቆጣጠር በሰላም የመከላከያ ሚኒስቴርን ሲረከብ እንደወራሪ ሰንደቅ ዓላማዋን ወዲያው እንደማይሆን አድርጎ አውርዶ የወያኔን ሰንደቅ ዓላማ በቦታው ተካ። ሰው እሪ ብሎ ሲጮኽበት ተገዶ በቦታው መለሰው። ይኸ ከሀዲ ቡድን ሕዝባችንን ልብ አያውቀውም እንበል? ከዚያ በኋላ ሰንደቅ ዓላማውን ለመቀየር ያልሸረበው ደባ፣ ያልፈተለው ተንኰል አልነበረም። በብዙ ሰው ትግል አረንጓዴ ብጫ ቀዩ ተረፈ። በ፲፱፻፹፬ (1992) የዘረኞች መንጋ ተሰብሰቦ ከመጀመሪያ በዩቲዩቡ ፊልም ላይ እንደታየው ዶልቶ፣ “የብሔር-ብሔረሰብነትን እኵልነት የሚያበስር” ብሎ በ፲፱፻፹፰ (1996) ላይ በክብ ሰማያዊ ኣምባሻ መሰል ዙሪያ ውስጥ የተሠራ ኮከብን ለጠፎበት “ህንካችሁ ትክክለኛው ባንዲራችሁ ይኽች ናት” ሊለን ሞከረ። የሆዳችንን በሆዳችን ይዘን ዘግተነው ትክክለኛውን መጠቀሙን ሕዝቡ ቀጠለ።


ቆዩኝማ! ማን ነበር ያ ስም አይጠሬ ይኸን ኮከብ ግንባሩ ላይ የለጠፈው? 
ማንም ክፍል ሥልጣን ሲይዝ የራሱን አርማ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ መለጠፉ የተለመደ እየሆነ መጥቷልና እሱስ መሆኑ ባላስገረመም ነበር። የነሱ አምባሻ አሽታሮት ብዙም ባልደነቀን ነበር። ዳሩ ግን፣ እየቆዩ በሄዱ ቁጥር ሌጣውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የያዘ ሁሉ የነሱን ኮከብ ካላስቀመጠበት ለነሱ ሰጥ ለጥ ብሎ አለመገዛቱ እየመሰላቸው መወንጀላቸው ነው።
ይኸ ሰንደቅ ዓላማ የአባቶቻችን ደም የፈሰሰበት፣ አጥንታቸው የተከሰከሰበት ነው። ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎበታል። በዚህ ምክንያት ማንም ሰው ተነስቶ የሚቀልድበት ወይም የፈለገውን ለጥፎበት ሊያርክሰው አይችልም። ወያኔ ሰንደቅ ዓላማችንን እንዳጎደፋት፣ መጥቶ ዛሬም በጉልበት ሥልጣን ጨብጦም እንዳዋረዳት ይገኛል። የሱ አሽታሮት የሌለበትንም “ባንዲራ” ሳይሆን አርንጓዴ ብጫ የያዘውን ሁሉ ወንጀለኛ በማድረግና በማሰር ሕዝባችንን ማሰቃየት ጀምሯል። ይኸንንም ከሚከተለው የአሜሪካን ድምጽ ሬዲዮ ቃለ መጠይቅ በመኢአዱ መሪ በእንጅነር ኃይሉ ሻውልና በአንድ የወየነ በወያኔ አፈቀቀላጤ ኃብታሙ ሚሚ በሚባለው መሀል የተካሄዱትን ክርክሮች በመስማት መረዳት ይቻላል።
ኮከብ የሌለው ባንዲራ ከዚህ ሥርዓት ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ባንዲራ ነው። ያ ሥርዓት ፈርሷል። በብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ትግል ፈርሷል! በሚገባ ለመስቀመጥም የጨቋኝ ሥርዐት ምልክት ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችና ወደዘር ጭቆና ዳግም ላለመግባት በጋራ ቃል ገብተው ነው ... አንድነታቸውን ለማጠናከር እየሠሩ ያሉት። ... ስለዚህ ከዚህ አንጻር ስናይ አንደኛ ባንዲራ እንደሚታወቀው ሰንደቅ ዓላማ ከስሙ እንደሚገለጸው የአንድን ሥራዓት አላማ ነው የሚገልጸው። የኛ የፌዴራል ሥራዐታችን ዓላማ የፌዴራሉ መንግሥት ባንዲራ ኮከብ ያለው ነው። ያኛው ሥርዓት የራሱ ዓላማ የነበረውና የወደቀ ሥርዓት ነው። ዳግመኛም የማይመለስ ሥርዐት ነው። ... እንግዲህ ያንን ሰንደቅ ዓላማ አውለበልባለሁ ብሎ ማለት ጸረ-ሕዝብነት በወንጀልም የሚያስጠይቅ ነው። ከዚያም ባሻገር በኢትዮጵያ ብሔር ብሐረ ሰቦች መበቶች እንደማመጽ የሚቆጠር ነው። ያንን ለመስቀል መሞከር ሕገ-ወጥነት ነው። ሕገ መንግሥቱንም መተላለፍ ነው።
ኃብታሙ ሚሚ እንደዛተውም የወያኔ ኮኮብ የሌለበትን ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልበውን ሁሉ የጨቋኝ ሥርዐት አራማጆች እያለ ማሳደዱን ቀጥሏል። ወያኔ ታሪካችንን እያጎደፈ፣ ባሕላችንን እያቆሸሸ፣ አንድነታችንን እያፈረሰ፣ አገራችንን እየሸጠ ይኽ ምልክት ያለበትን ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብና “የባንዲራ ቀን እያለ” ማሾፍ ጅምሯል።

በቅርብ ቀን የወያኔ ቅልቦች ውጭ አገር ድረስ እጃቸውን አስረዝመው የተረገመችውን “ባንዲራቸውን” ስደተኛው እንዲቀበለው ማስገደድ ጅምረዋል። የወያኔ ተንኰል ያልገባቸው ወጣት ኢትዮጵያውን የስደተኛ ሊጆች ወያኔ በረሀብ ለሚፈጀው ሕዝባችን ገንዘብ ለማሰባሰብ፣ አባቶችን፣ እናቶችን፣ ወንድሞችን፣ እህቶችንና ጓደኞቻቸውን ለንዶን ውስጥ ለማሰባሰብ ሞክረው ነበር። የወያኔ ሰዎች በራሪ ወረቆቶቹ ላይ የነበረውን ሰንደቅ ዓላማ አይተው “ያ ትክክለኛ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ሳይሆን የቅንጅት ሰንደቅ ዓላም ነውና በኢትዮጵያ ስም ይኸን ሰንደቅ ዓላማ መጠቀም አትችሉምና ትክክለኛው ይኸ ነው” ብለው አስፈራርተው እንዳይስቀየሩአቸው ደርሰንበት በግነናል።
ስደተኛው ኢትዮጵያዊ ሕብረተሰብ ይኸን ድፍረት መመከት ይገባዋል። ወያኔ ለአረንጓዴ፣ ብጫ ቀዮ ሌጣ ቀለም ተገቢውን ክብርና ቦታ እስካልሰጠው ድረስ ማንም ይኸንን የዘረኝነት ዓላማ የተንጸባረቀበትን የግድ መቀበል የለበትም። ወጣቶቹስ ምንም አያውቁምና አይፈረድባቸውም። ለትላልቆቹ ግን ትልቅ መልዕክት ማስተላለፍ ይጠበቅብናል። እሱም፣ ይኸንንም “ባንዲራ” ይዞ የተገኘ አዋቂ፣ የሟቾቹ አባቶቹና እናቶቹ አጥንት ይውጋው ብለን መርገም አለብን። እርጉም የተረገመ ይኹን! አሜን።[2] ወያኔ መሠረታዊውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ እስካላከበረ ድረስ ከሱ ጋር ያበረ፣ ከሱ ጋር የተባበረ፣ ከሚተባበረውም ጋር የዋለ፣ የፕሮፌሰር ጌታቸውን ቃል ልዋስና፣ እሱም እራሱ ወያኔ ስለሆነ የተረገመ ይሁን። ይኸን የወያኔ የዘረኛ አርማ “ባንዲራ” የያዘ ሁሉ ጥቁር ውሻ ይውለድ በሉና ርግሙት። ዕውነተኛው ሰንደቅ ዓላማችን፣ ያልተበረዘች፣ ያልተለወጠች፣ በድል አድራጊነት ዛሬ ላይ የደረሰች አርንጓዴ ብጭ ቀይ አርማችንን ከፍ አድርገን እናውለብልባት።





[1] በቅንፍ ውስጥ የሚታዩት የአውሮፓ ወይም የግሪጎራውያንን አቆጣጠር ነው።
[2] ነሐሴ ፴ ቀን ፲፱፻፩ ዓ. ይኸንን በተመለክተ የተጻፈችውን የእንግሊዝኛ ግጥሜን ብሎጌ ላይ ማንበብ ይችላሉ። http://wondimumekonnen.blogspot.com/2010_06_01_archive.html