Saturday 1 May 2010

ቀደዱ እንጂ አልዋሹም!

ከወንድሙ መኰንን

የወያኔ የሹመት ክፍታ የሚለካው በሚዋሽ ምላስ ርዝመት መሆን አለበት። ለዚህ ይሆናል የወያኔ ተሿሚዎች ዓይናቸውን በጨው ሙልጭ አድርገው ታጥበው ሽምጥጥ አድርገው በውሸት እርስ በርስ የሚወዳደሩት። መቸም እራሳቸውን ካልሆነ ማንንም እንደማያሞኙ ግልጽ ነው። በተላይ ዛሬ - ዛሬ ላይ የውሸት ችሎታቸው ኢየታየ መስል ለዲፕሎማሲ ከፍተኛ ሹመት የሚታጩት። ኧረ እባካችሁ ባህልና ጨዋነት ገደል ገብቷል፣ የሕሊና ያለህ!!!!

ከዚህ በፊት፣ ረቡዕ ሐምሌ ፲፩ ቀን ፩፱፻፺፱ ዓ. ም. ወያኔ ወገኖቻችንን ጨፍጭፎ ካበቃ በኋላ የተቃዋሚ መሪዎችን ሰብስቦ እስር ቤት አጉሮ፣ “ሕገ-መንግሥቴን ስላላከበራችሁልኝ፣ እኔን በድምጽ ብልጫ ከዙፋኔ ልታነሱኝ ስለተነሳችሁ ዕድሜ ይፍታችሁ!” ብሎ በሚቆጣጠረው ፍርድ ቤቱ በመፍረዱ የተናደዱ ፲፪ ኢትዮጵያውያን በቀጥታ ገስግሠው የሎንደኑን ኤምባሲ ቁጥጥር ሥር አዋሉት። አንድ ሰዓት ሙሉ ኤምባሲውን ተቆጣጥረው እንግዳ መቀበያ አዳራሹ ውስጥ ያሉት ግድግዳዎች በተጨፈጨፉት ወገኖቻችን ፎቶግራፎች ለጣጥፈው ጥርት ባለ ሰማይ ላይ ርጭት ያሉ ክዋክብት አስመሰሉአቸው። የሚገባውን ሁሉ ተስተናጋጅ ተቀብለው፣ ወያኔ የሚፈጽመውን ወንጀል አንድ በአንድ አስረዱ።

የጀርመን ሬዲዮ በቀጥታ በስልክ ከቦታው ይደረግ የነበርውን ቀድቶ ለሕዝባችን አሰማ። የወያኔ ተላላኪና ጉዳይ አስፈጻሚ ብርሀኑ ከበደ በቦታው አልነበሩም። ሠራተኞቹ ተደናግጠው እንግዳ መቀቢያውን ለተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ጥለውላቸው አንደኛው ፎቅ ላይ ዘግተው ፖሊስ ጠሩ። ፖሊስ ደርሶ ወንድሞቻችን ምን እያደረጉ እንደሆነ ጠየቁአቸው። እነሱም አምባሳደሩን ለማነጋገርና ለምን እንዲህ ዓይነት ወንጀል በአገራቸው እንደሚፈጸም ለመጠየቅ መጥተው እንዳጡአቸው አስረዱ። ፖሊሶቹም “በቃ አሁን መልዕክታችሁን በሚገባ ሁኔታ አስረድታችኋል። አሁን ሂዱ” በለው ተማጽነዋቸው ኢትዮጵያውያን ወደየቤታቸው ከአንድ ሰዓት ቆይታ በኋላ አሰናበቱአቸው። ማታ የጀረመን ሬዲዮ ያቀናበረውን አስተላለፈ። የተቃጠለው የሕዝባችን አንጀት ትንሽም ብትሆን በነዚህ ቆራጥ ወገኖች በወሰዱት እርምጃ ራሰ።

ቀጣሪ ጌቶቻቸው ከአዲስ አበባ ደውለው ወረደውባቸው ነው መሰል፣ አባሳደር ብርሀኑ ከበደ ምንም ሳያፍሩ፣ ወደ ጀርመን ሬዲዮ ቢሮ ደውለው “ውሸትን ዕውነት አስመስላችሁ እንዴት ታስተላልፍላችሁ። አንድ ሁለት ቦዘኔዎች ከሕዝቡ ተቅላቅለው እምባሲ ውስጥ ገብተው ነበር። አምስት ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተገፍትረው ወጥተዋል። እንዴት ያንን ወሬ ብላችሁ ታወራላችሁ ብለው” አምባረቁቸው። የጀረመን ሬዲዮም ዕድሉን ሰጥቶአቸው በሚቀጥለው ቀን ውሸታቸውን እንዲቀዱት ፈቀደላቸው። መቸም ጆር አይሰማ በዚህ ዕድሜአቸው ሲቀዱ ሰማንላቸው። “ስጥ እንግዲህ!” ይላል አራዳ ልጅ። ይኸ ጸሐፊ ወንድሞቻችን ኤምባሲውን ከተቆጣጠሩት ሰዓት ጀምሮ እስከለቀቁ ደረስ ሁኔታውን ይከታትል ነበር። ልጆቹ የሠሩት ጅግንነት ከምንም በላይ ሊዘገብ ቢችልም ዝም ብሎ አልፎት ነበር። የአምባሳደሩን ቀደዳ ከሰማ በኋላ ግን “የምጣዱ እያለ የዕንቅቡ ተንጣጣ” በሚል ርዕስ በዕውነት የሆነውን በቪዲዮ “መቅረጸ-ስዕል” ተጨባጭ መረጃ አሰደግፎ አምባሳደር ተብዬው ያሉት በሙሉ ውሸት መሆኑና ሂሊናቸውን ሽጠው የሆነውን አልሆንም እንዳሉ አስቀመጠላቸው። ጽሑፍ አንብበው፣ ቪዲዮውን አይተው ካበቁ በኋላ አምባሳደር ሆዬ እዬዬአቸውን አቀለጡት። ሎንዶን ሜትሮፖሊታን ፖሊስ ጣቢያ ሩጠው ሂደው “እሪ አለቅን! ሕግ ባለበት አገር ሕገ-ወጥ ቦዜኔዎች በጉልበት ኤምባሲአችንን ያን ሁሉ ሰዓት ሲቆጣጠሩት አንድ ሰው እንኳን እንዴት አላሰራችሁም። የዲፕሎማቲክ ጥበቃችሁ ተጓደለብን፣ የኢትዮጵያና የእንግልዝ ወዳጅነት በዚሁ ጉዳይ ሊያከትም ነው። አንድ ነገር አድርጉ። ይኸው ከአንድ ሰዓት በላይ በሰላም ለመሥራት ዋስትና የለንም። ዛሬ ያለምንም ችግር ኤምባሲውን ተቆጣጥረውት ከሄዱ ነገ መጥ|ተው ላይገድሉን ምን ዋስትና አለን ... “ ገለመሌ አሉ!! “ቪዲዮውን እዩት!! አልቀናል! እንዴት ዝም ትላላችሁ!” በማለት በዚያው በጀርመን ሬዲዮ “ሁለት ሰዎች፣ አምስት ደቂቃ” ባሏት አፋቸው መልሰው ፖሎሶች ላይ አለቀሱባቸው። ፖሊሶቹም ይሄንን ድርገት መርቷል ያሉትን አንዱን ወንድም ጠርተው፣ የውያኔውን አምባሳደር ዕንባ ለመጥረግ ያህል፣ አስጠነቀቁት።

የወያኔው ተላላኪ፣ አምባሳደር “ብርሀኑ ከበደ” ከዚያ ትምህርት ወስደው “ሳይገድሉ ጎፈሬ፣ ሳያረጋግጡ ወሬ” እንደማይደግማቸው ተስፋ አድርገን ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል አሁንም ደገሙት። ያሁኑ ይባስ!!! ያሁኑ ይባስ!!! ወይ ቅሌት!!

ሰኔ ፱ ቀን ፪ሺ፩ ዓ. ም. ኢትዮጵያውያን የወያኔ መንግሥት የሚያደርሰውን ጭፍጨፋ፣ ጠቅላላ የሰባዓዊ መብት ገፈፋ፣ እና ዓይን ያወጣ ንቅዘት ወይም ሙስና፣ ብርቲሽ የተመራጮች ምክር ቤት አባላት፣ ለበጎ አድራጎት ድርጅት አባላት፣ ለትብብር ከውሦስተኛው ዓልም ሕዝብ ጋር (Solidarity with the Third World) አባላት እና ለጋዜጠኞች ሶስት ሰዓት የፈጀ ገለጻ በሀውስ ኦፍ ኮመንስ በሚባለው የተመራጮች ምክር ቤት (House of Commons) አቅረበው ነበር። ገለጻው የብዙዎችን ዓይን የከፈተ እና ብዙዎቹ ጉድ ያሉበት ነበር። ይኸንን ከፍተኛ ስብሰባ በዓይነቱ ልዩና የመጀመሪያው በመሆኑ፣ አዘጋጆቹን ቪኦኤ በመባል የሚታውቀው የአሜሪካን ድምጽ ሬድዮ እና የጀርመን ሬዲዮ አዘጋጆቹን አፈላልገው ቃለ መጠይቅ (interview) አድርገው ነበር። ይኸ ሁኔታ ውያኔን ከምንም በላይ አስደነገጠው። የሚይዙትን የሚጨብጡትን ያጡት ለማጁ የወያኔ ተላላኪ ቦቦታው ሳይኖሩ፣ ለአሜሪካን ድምጽ ሬዲዮ ዓይን ያወጣ የውሸት ስልቻቸውን እንደገና ደገሞው ቀደዱት።

“በመጀመሪያ ደረጃ፣ እንዲህ ዓይነት ስብሰባ አልነበረም፣ የነበረው ትብብር ከሶስተኛው ዓልም ሕዝብ ጋር (Solidarity with the Third World) በቅርቡ ገንዘብ ለማሰባሰብ ያደረገው ቅደመ ስብስብ ነበር። አንዲት ሳብራ የምትባል ሴት እነዚህ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ሰዎች በጎን ጠራርታ አመቻችታላቸው ነው የገቡት”

በማለት አጥላልተው፣ አወዳድቀውና አቃለው ለማለፍ ሞክረው ነበር። ጋዜጠኛው “እንደስዚህ ዓይነት ስብሰባ አልተደረገም ነው የሚሉኝ?”ብሎ ሲያፋጥጣቸው፣
“አይ አልተደረገም አላልኩም። የኢትዮጵያን ጉዳይ ለመነጋገር የተጠራ ስብሰባ አልነበረም። እኛ አልተጋብዝንም። ስብሰባው ተደርጓል ግን በትንሽ ክፍል 14 ቁጥር ውስጥ የተደረገ አነስተኛ ስብስባ ነበር። አንድም የፓርላማ አባል አልነበረም”

በማለት ዘባርቀዋል። ውሸታቸው ያሳፈረው ጋዜጠኛ አዲሱ አበበም ግርም ብሎት፣ “የተከበሩ ብሩስ ጆርጅ አልነበሩም ነው የሚሉኝ” ሲላቸው፣ ድንግጥ ብለው “አይ ለትንሽ ደቂቃዎች ነበሩ። ትንሽ ካዳመጡ በኋል ውልቅ ብለው ወጥተዋል” በማለት ሽምጥጥ አድረገው ሳያፍሩ ክደዋል። “አይነጋ መስሏት” ነው አበው የሚሉት?

በመጄሪያ ደረጃ፣ ስብሰባው የተደረገው፣ ኢትዮጵያው ውስጥ ለሚደረገው አፈናና ጭቆና ለአገሪቱ ፓርላማ፣ በጎ አድራጎት ድረጅቶች፣ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ ትብብር ከሦስተኛው ሕዝብ ጋር እና ለጋዜጠኞች ታስቦ የተደረገ እንጂ ለገንዘብ ማሰባሰቢያ ቅደመ ዝግጅት አልነበረም። “ወሸት ቁጥር አንድ” በሉ! ፲፬ ቁጥር ክፍል አነስተኛ በመሆኑና የሚመጡት እንግዶች ከሦስት መቶ በላይ በመሆናቸው፣ ከዚያ ባሻገር ወያኔ የፈጸማቸው የዘር ማጥፋት ቪዲዮና በሙስና የተዘፈቀበት መረጃ በፕሮጀክተር ስለሚቀርብ ስብሰባው የተደረገው በታላቁ የኪሚቲ ስብሰባ አዳራሽል (The Grand Committee Room) ነበር። ውሸት ቁጥር ሁለት በሉ። አንድም የፓርላማ አባል የለም ብለው ዓይናቸውን በጨው አጥበው ለሸመጠጡት፣ ጉባዔውን የከፍቱት በክብር እንግድነት የሁሉም ፓርቲዎች የምክር ቤት ሊቀመንበር፣ የተከበሩ ዴቪድ አንደርሰን (The Chairman of All Party Parliamentary Group on Third World Solidarity, MP David Anderson) ነበሩ። ውሸት ቁጥር ሦስት በሉ! አምባሳደር ተቢዬው ሲወጠሩ ተውናብደው አንደርሰን ብቻ ተገኝተው ነበር። ውሸት ቁጥር አራት! አንደርሰን ብቻ አለነበሩም። ከመኖርም አልፈው የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የተከበሩ ብሩስ ጆርጅ ነበሩ። ውሸት ቁጥር አምስት። አንድም ጋዜጠኛ አልነበርም ላሉት፣ “ተመክሮና የአሁኑ የሜዲያ ሽፋን በኢትዮጵያ (Exeprience and The Current Media Coverage in Ethiopia) በሚል ርዕስ ንግግር ያደረገችው ታዋቂዋ የጋርዲያን (The Guardian) ጋዜጣ ዘጋቢ ሳውንድራ ሳተርሊ (Saundra Satterlee) ነበረች። ውሸት ቁጥር ስድስት! በስንት ፍጥጫ የተከበሩ ብሩስ ጆርጅን መገኘት ያመኑት አማሳደር ብርሀኑ (ምኑን ብርሀን ሆኑ)፣ ብሩስ ጆርጅ አቋርጠው ሂደዋል ላሉት፣ የመዝጊያ ንግግራቸውን ሲያደርጉ፣ “If there were a contest in the severity of corruption the rulers of Ethiopia, who have redefined the word, would undoubtedly win the gold prize.” (በሙስና ዝቅጠት ውድድር ቢደረግ፣ የቃሉን አዲስ ፍቺ ያገኙልን የኢትዮጵያ መንግሥት መሪዎች፣ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሁነው ባጠለቁ ነበር) በማለት ተሰብሳቢውን አስቀውታል። ከዚያም አልፈው ተርፈው በመጨረሻ የዚህን ጽሑፍ አቅራቢ ውጪ ጠብቀው ወደ ጎን ወስደውት አንዳንድ ነገሮቻን ካወያዩት በኋላ ወደፊት ተገናኝተው በሰፊው መረጃ መሰብሰብ ላይ አብረው ለመሥራት ወስነዋል።

ተወካይ አልላኩም ላልቱ ጭልጥ ላለ ቅጥፈት፣ በመጀመሪያ ደረጃ እሳቸው በቦታው አልነበሩም፣ ታዲያ ማን መረጃውን አጥናቀረላቸው? እልፍኝ አስክልካያቸው ሆድ-አደር ያለው ከበድ እዚያ ጉጉት መስሎ ጉልት ብሎ አላመሸም? እንዲያውም አይታው ብግን ያለች አንድኛዋ እህታችን፣ “እምባሲ በር ይዞ አትገቡም እያለ ዘበኛ ይመስል ፍርፋሪ ለቃሚ የወያኔ እልፍኝ አስከልካይ ምንድነኝ ብሎ ነው እዚህ የተጎለተው? ወይ አያምር ወይ አያፍር!” ብላ የዚህን ጽሑፍ አቅራቢ አስቃዋለች። ያስ ሌላው ተላላኪአቸው? ዓለማየሁ ነኝ ያለው (ዓለሙ ጥፍት ትበልበትና)! አንዷ እህታችን “ዶማ” ያለችው! ስለወያኔ ሙስና በቀረበው በዚያው መድርክ፣ “ይኸ መንግሥት ብዙ ለውጥ አምጥቷል። ብዙ ወጣቶችን ባለመኪና አድርጓል” ብሎ ሲናገር ሕዝቡስ ጮሆበት አፉን አላስዘጋውም? ሚዛናዊ አይደላችሁም ብሎ ለመናገር ሲሞክር፣ አንዳዶቹ በጣም ከመናደዳቸው የተነሳ “የት ያለህ መሰለህ? የኢትዮጵያ ፓርላማ?” እያሉ ይጮኹብት የማን መልዕክተኛ ነበር?

በቦታው የነበሩ አንድ የቀድሞ የዲፕሎማቲክ ከፍተኛ ባለሥልጣን የቪኦኤውን ትርተራ እንዳዳመጡ፣ ለዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ደውለው፣
“ብርሀኑ ከበደ፣ የዲፕሎማሲን ሙያ አዋረደ። ሁላችንም ድፕሎማት ነበርን። የአገርን ጥቅም ለማስከበር የስብዕናን ክብር ሳያዋርዱ መሥራት ምንም ነውር የለበትም። ግን እንዲዚህ መቀደድ ያሳፍራል። ቤልጀይም ጁኒየር ድፕሎማት ሁኖ ሲሠራ ደህና ወጣትና ወደፊት ጥሩ ባለሟል ይኾናል ብዬ ስጥብቅ ነበር። እንዲህ ዓይነት ወራዳ ሥራ ሲሠራ በማየቴ አዘንኩ”
ብለዋል።

አምባሳደር ብርሀኑ ከበደ፣ ቤልጀየም በነበሩብት ጊዜ የደርግ ጥቅም አስጠባቂ ነበሩ። እሱስ ይኹን፣ ያን ጊዜ የደርግን መንግሥት ያገለግሉ የነበሩ፣ ሥርዓቱ ሲወድቅ፣ መጪው መንግሥት አገር ጎጂ በመሆኑ እንዳለ ተሰደዋል። ክፍተት ሲገኝላቸው ሰልፋቸውን አስተካክለው አምባሳደር ተባሉ፣ ያውም የወያኔ! አምባሳደር ብርሀኑ! ሞኝ አይሁኑ! ትንሽ እንኳን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅር እንዲልዎት እንዲህ ዓይነቱን የወራዳ ሥራ እራስዎ አይስሩ። የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ የለዎትም? እሱ ወጥቶ ይቀላምድ። እርስዎ ምን በወጣዎት! እንዲይ ዓይነቱን መቅደድ ለቦታው የተዘጋጀ ሰው ይቀደደው። ልብ ይበሉ። ይኸ ምክር የወዳጅ ምክር ነው። ይልቅ እስዎ ወያኔ አይታመንም እና ልክ እንደ ፍሰሀ አዱኛ በጊዜ ሹልክ ብለው ያምልጡ። ይሻልዎታል። ለምን ቢሉኝ፣ ጌታዎ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሥቃይ፣ መለስ ዜናዊ ብለው ጨርሰውታል። ጠቅላይ ሥቅዩ ምን አሉ መሰሰዎት!

“የወያኔ ሹመት የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው። ሽልብ ካሉ ዱብ ነው።”

ማንም አምባ ገነን መንግሥት ሥልጣንን ሙጭጭ ብሎ ለዘልዓለም ጨብጦ የኖረበት ታሪክ በአገራችንም ሆነ በሌላው ዓለም ታይቶ አይታወቅም። ሁሉም አምባገነን ሌሎቹን እንዳዋረደ እሱም በተራው ተዋርዶ ከሥልጣን ይወርዳታል። አብዛኛው የአምባገነን ከነግሳንግሱ ለሌሎች ባዘጋጃት ወጥመድ እራሱ ይገባባታል። ከቀናውም ለስደት ይዳረጋል። እንደርስዎ ላሉት ለጀሌዎቹ ወይውላቸው። ወያኔ የኢትዮጵያውያንን ቆሽት አሳርሮ አይኖራትም። አምባሳደር ብርሀኑ! በሰፈርዎ የዕውነት ብርሀን ደብዛዋ እንደ አዲስ አበባው መብራት ጠፍታለች። አሁንስ ጨለማው ከበደ።

No comments:

Post a Comment