Thursday 27 May 2010

ሆ ሆ ይ! ጥጃ ለጅብ?

ወንድሙ መኰንን

“አይሰማ ጆሮ፣ አይውጥ ጉሮሮ” ይሉታል አበው ሲተርቱ። ሌላው የምወደው አባባአል “ጆሮ ምነው አታድግም?” ቢሉት “ይኸን ሁሉ ጉድ እየሰማሁ እንዴት ልደግ?” ብሎ ያለው ነው። አንዳንዴ አንድን አስዳናቂ ነገር በቀጥተኛ አማርኛ ቢሉት አንጀት ስለማያርስ ዘይቤዎች በበለጠ ያብራሩታል። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሥቃይ መለስ፣ ዜናዊ ሕዝቡ በነገር እየጎነተላቸው ሲያስቸግሩአቸው አንዴ ንድድ ብሎአቸው “እኔስ የሰለቸኝ፣ የአማርኛ ተረትና የአፋር ባጄት ነው።” ሲሉ ተደምጠዋል። የአማርኛ ተረትና ምሳሌ እርቃናቸውን ያስቀራቸዋላ!
ወያኔ በመባል የሚታወቀው የዘራፊ ቡድን በሚያስደንቅ አኳኋን የስልጣን ልጓም ከጨበጠ ወዲህ ብዙ ብሔራዊ ጥቅሞችን አሳልፎ እንደሸጠ ጸሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ገንዘብ ካየ ይኸ የወንበዴዎቹ መንጋ የእናትንም ሬሳ ከመሸጥ የማይመለስ የሼክስፒሩ ሻይሎክ ነው። በረሀ እያለ ያካሄድ የነበረውን ተራ ውንብድና አቶ ገብረመድኅን አርአያ ቁልጭ አድርገው አንድም ሳያስቀሩ እንደመስታወት አሳይተውናል። ኢግላን፣ አሊጤና፣ ባድሜን፣ ጾሮናን፣ ዛላ አንበሳንና መላውን የኢሮብን መሬት እንዳለ ለሌብነት አስተማሪው፣ ለሻዕቢያ በዱቤ እንደቸበቸበው በታላቁ ሴራ መጽሐፋቸው አስተምረውናል። ነገሩ፣ “ማን ይናገር የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ” ነዋ! የትግራይ ሕዝብ መሬቴን አላስረክብም ብሎ ባነሳው ግርግር፣ ሌላው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ደርሶለት የደም ዋጋ ከፍሎ ውሉን አፈር ድሜ ቢያስግጠውም፣ መዘዙ እስከዛሬ ድርስ ተምዞ አላልቅ ብሎአል። ኢትዮጵያውያን በደማቸው የተቤዡትን መሬት መለስ ዜናዊ በቅልጥፍናቸው አልጄርስ ድረስ ሂድው አስረክበው መጡ። አባ ግድየልሽን ማን ጠይቆአቸው? የትግራይ ሕዝብ ግን ወይ ፍንክች! ወደፊት ከአቶ ገብረመድኅን አርአያ ጋር አንዳንድ ጉዶችን በሰፊው ልንዳስስ በዕቅድ አሳድረነዋል። ዛሬም ይኸ የወንበዴ ቡድን በተአምር መንግሥት ሆኖም ያንኑ የበረሀ ውንብድብናውን በሰፊው ቀጥሎበታል። ሊትወው ክቶ አልሆነለትም። ሌባ ላመሉ ዳቦ ይልስ የለ! ሲልከሰከስ የተጠናውተው ሰይጣን መቸ በቀላሉ ይለቀውና! ጠብልም እዚህ ላይ ዱልዱም ነው። ዛሬ ወያኔ አገሪቷን ያለ ባሕር በር አስቀርቷታል፡፡ ወልቃይት ጠገዴን ከጎንደር አውጥቶ ወደ ትግራይ ከቶታል። ነገሩ ካንዱ ክፍለ ሀገር መሬት ቆሮሶ ወደሌላው ማሸጋሸግ ይኸን ያህል ባላስመረረን ነበር። ትግራይም የኛ ናት። አገራችን ናት። ግን ትግራይን እንደገንዘቡ ስለሚቆጥራት (ትግሬዎች ኡ! ኡ በሉ! ተዋርዳችኋምል!) ነገ ትርፍ ካገኘ ከመቸበችባት ወደ ኋላ እንደማይል ስለተረዳን ጥሩ ዋጋ እንድታወጣለት አቅዶ ኢያሰባትና እያደለባት መሆኑ ታይቶን ነው እንልፍ የሚነሳን። ጠርጥር! “አለማታለሁ” አለ? “አደልባታለሁ” ቢለን ግልጽ ይሆን ነበር። ከዚያም አልፎ የአጼ ቴዎድሮስን የትውልድ ስፍራ፣ ሁመራንና መተማን ለሱዳን ሽጦታል። በአገሪቱ ያሉትን ለም መሬቶች ለሳውዲ አረቢያ እየቸበቸበ ነው። ትንሺቱ ጅቡቲ ሳትቀር ከዚሁ ወንበዴ አማካይነት ከኢትዮጵያ ከምትገፈው የወደብ ክፍያ መልሳ የኢትዮጵያ መሬት በርካሽ እየገዛች ባለርስት ሁናለች። “ትንሽ ቆሎ ይዘህ ከአሻሮ ተጠጋ” ይሉሀል ይኸ ነው። ሱልጣን ኢብራሂም እብን አህመድ ትንጥዬ ቦታ አሰብ ሰላጤ ውስጥ ለመርከብ ማረፊያ ለሩባቲኖ ኩባንያ (Rubattino company) ሽጦ አልነበር ጣሊያን ኤርትራ የምትባል ቅኝ አገር ለመፍጠር በቅታ ዛሬ ወደብ አልባ ያረገችን? ጂቡቲ ታሪክ ላትደግም ምን ያግዳታል፣ ከሀዲዎች ኢትዮጵያን እስካስተዳድሩአት ድረስ? ዕድሜ ለወያኔ፣ አሁንም የወደብ ጥገኛዋ ሁነናል። አንድ ሰሞን መርካቶ ለአንድ የሩቅ ምሥራቅ ቱጃር ሊቸበቸብ ነበር ሲባል ሰምተን ነበር። ውሉ የት ደረሰ? መርካቶ እስከዛሬ ካልተሸጠች፣ አይቀርላትም። አንድ ቀን ጆሮ ግንዷን ብሏት ኢትዮጵያዊነቷ ተሰርዞ እርፍ ትላታለች።
ወያኔ ገንዘብ ከሸተተው ይሉኝታ አያውቅም። ድሮውንስ ቢሆን ኢትዮጵያዊ ይሉኝታ መቸ ተፈጠረበትና? እንኳ ኢትዮጵያዊ ይሉኝታና ሽታውም ባጠገቡ ዝር ብሎበት አያውቅም። አባሎቹ ሲሰርቁ ቢያዙ “ምን አባክ አገባህ/አገባሽ?” ብለው መልሰው የሚያፈጡ ዓይን አውጣዎች ናቸው። “የሌባ ዓይነ-ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ” ይሉታል ይኸ አይደል? ወያኔን በአስታውስኩ ቁጥር አንድ የዛሬ 22 ዓመት ገደማ ያጋጠመኝ ሌባ ትዝ ይለኛል። ከጓደኛዬ ጋር ከፕያሳ ስድስት ኪሎ ለመሄድ ታክሲ ልንሳፈር በሩን ስከፍት አንድ ሰው ተንደርድሮ መጥቶ ገፍቶሮኝ ሾፌሩን “ማርካቶ” ይለዋል። መገፋቴ ሲደንቀኝ እጁ የውስጥ ደረቴ ኪስ ገብቶ ሲበረብረኝ አገኘሁት። በደመ-ነፍስ ያዝኩት። በሰውነት ከኔ የማይሽል ነበረና እጁን ከኪሴ ፈልቅቄ አውጥቼው ሳላውቀው በኃይል ጠመዘዝኩት። አቶ ሌቦ ሆዬ በሱው ብሶበርት በጣም ተቆጣኝ። ኩስትር ብሎ ዓይን ዓይኔን እያየ “በቃ ነቅተሀል! ምን ሙዝዝ ትልብኛለህ። ልቀቀኝ! የማነው ሞዛዛ! ፋራ!” ብሎ እንድብራቅ ሲጮኽብኝ ግራ ተገባሁና ያጠፋሁ መስሎኝ ለቀቅኩት። ከመደናገጤ የተነሳ የተተኮሰባት ድኵላ መስልኩ። በኋላ ነገሩ ገርም አለኝና ሳላስበው ሳቄን አወካሁት። እጁን እያሻሸ፣ “ገና ሳምንት ትስቃለህ! ጀዝባ!” ብሎኝ ምንም እፍረት ሳያሳይ እየተጀነነ አንዳንዴም ዞር እያለ እየተገላመጠኝ መንገዱን ቀጠለ። ያ ዓይን አውጣ ሌባና ወያኔዎች አንድ ናቸው። ወያኔዎቹ ባይብሱ! በነገራችን ላይ ወያኔና ዱሩየዎች አብረው እንደሚሠሩ ታውቃላችሁ? እጅና ጓንት ሁነዋል። ሰም ማጥፋት እንዳይመስላችሁ። ዕውነቴን ነው። በሌቦች ተባባሪዎቻቸው አማካኝነት ነበር የፕሮፌሰር አስራትን (ነብሳቸውን በገነት ያኑርልን) ቦርሳ አስነጥቀው በውስጡ የተገኘውን ሰነድ ምንም ሳያፍሩ በጋዜጣቸው ያስወጡት። የጋዜጠኛው ማስታወሻ ደራሲ ተስፋዬ ገብር አብ ይጠየቅ። የኢሰመጉን ቢሮ በዱሩዬዎች አሠብረው ንብረትና ሰነድ እንዳሰረቁ አንድ የኮበለለ የፓሊስ መኰንን ከነመረጃው ለዓለም አጋልጧል።
አገር ቤት ያጧጧፉትን ማጭበርበር ውጭ አገርም ተያይዘውታል። ማጭበርበሪያ ዘዴአቸው በየጊዜው ይለዋወጣል። አንድ ሰሞን በየኤምባሰው የቅጥረኛ ወኪሎቹ አማካይነት ስደተኛውን ሁሉ አዲስ አበባ ውስጥ የከተማ መሬት እንሰጣችሁአለን፣ ኑ ተደራጁ ብለው ልባቸው ውልቅ እስኪል ስበኩአቸው። ይኸን የጠላት ቅጥረኛ ለመታገል ቆርጠን የተነሳን ስደተኞች ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ለማስጠንቀቅ ያደረግነው መሯሯጥ በወያኔ አፍዝ አደንግዝ ድግምት ከሸፈብን። አባሻ ሆዬ ተንጋግቶ ገባለት። የከተማ መሬት በአቋራጭ ተግኝቶ! የወያኔ ባለሟሎች ያንን ሁሉ የስደተኛ አድራሻ ሰብስው፣ “ያውላችሁ፣ ኢትዮጵያውያን ተበደልን ብለው ጥገኝነት ይጠይቃሉ፣ ዳሩ ግን ከአንዳንድ ጽንፈኞች በስተቀር አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከኛ ጋር ተባብሮ ይሠራል” በማለት የብዙ ሺ ሰዎች ስምና አድራሻ ለየመንግሥታቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር መሥሪያ ቤቶች አስረክቡ። ለዕውነትኛው ደጋፊአቸው የተወሰኑ መሬቶችን ሰጥተዋቸው፣ የተቀሩትን፣ “ሥጋ የለም መረቅ ጠጡ” ብለው ሸኙአቸው። ያስያዙትም ገንዘብ እንዳለ ውሀ በላው።
ቀጥለው ሁለተኛ ዙር እቅዳቸውን አንድግበው ብቅ አሉ። “ኑ! ንዋያችሁን አገር ቤት አፍስሱ” (investment) ብለው ውጭ አገር ነዋሪ ኢትዮጵያውያንን ጋበዙ። አንዳንዱ አላዋቂ የዋህ አገሩን የረዳ መስሎት፣ “እምን አካባቢ ንዋዬን ላፍሥ (invest) ብሎ ምክር ጥየቃ ገባ። ለዚሁ ጉዳይ የሰለጠኑ ምላሳቸው ጥሬ ይሚቆላ ካድሬዎች መንግሥት የእርሻ መሬት እንደሚሰጣቸውና፣ አበባ ተክሎ ወደ ውጭ መላክ እንደሚያዋጣና ተወዳዳሪ የማይገኝለት የትርፍ ጥገት መሆኑን አሳመኑአቸው። ተደራጁ ተባሉ። ገንዘብ ሰብስቡ ተባሉ። ጅሎቹ እንደተባሉት አደረጉ። ቱጃር የመሆን ሕልማቸው ግን ወያኔ ገንዘባቸውን እኪሱ ከከተተ በኋላ፣ ደብዛው ጠፋ። መሬቱም አልተሰጣቸው፣ አበባውም አላበበ፣ ገንዘባቸውም አልተመለሰላቸው። እዬዬ ቢሉ ማን አዝኖላቸው?
ሶስተኛው ዙር ዕቅዱ በሚሌኒየም ሳቢያ ሚልዩን በሚሊዮን ዶላር ሐይቅ ሊዋኙ የነደፉት ነበር። ከየአንዳንዱ ሚሌኒየም ኢትዮጵያዊ ቱሪስት ቢያንስ ቢያንስ አንዳንድ ሺ ዶላር ሊመነትፉ ተመን አውጡ። የለየላቸው ቁጭ በሉዎች ከሎንዶን ኢምፖርት አደረጉ (ወደ አገር አስገቡ)። ይኽ ዝግጅት የ፲፱፻፺፯ ምርጫን ተከትሎ የጨፈጨፉት የንጹሐን ደም ገና ቀለሙ ከአስፋልቱ ላይ ሳይለቅ ነበር። የቅንጅት መሪዎች “በአገር ክህደት ወንጀል” ተከሰው ወህኒ ታጉረዋል። አንዳንድ ሞኛሞኝ ወገናችን በአፍዝ አድንግዞቹ ድግምት ተታሎ ሊቀላቀላቸው ስንቅ ሲሰንቅ ደርሰንበት፣ ኡ ኡ ብለን ጮኽንበት። “ጥቁር ውሻ ውለድ” ተብሎ ተገጠመበት። አብዛኝው ኡኡታችንን ሰምቶ ጉዞውን ቢሰርዝም፣ ሌሎቹ፣ ገንዘባቸውን ቋጥረው፣ በብዙ ዋጋ የአይሮፕላን ቲኬት ገዝተው “አፍንጫችሁን ላሱ” ብለውን ገቡ። መለስ ዜናዊ ከነሚስታቸው (ውይ ምስኪን!! ሲያሳዝኑ! ኑሮ “ቀዳማይ” እመቤት አዜብ መስፍንን እንደሚያገላታቸው አያችሁ?) በሱዳንኛ ሲደንሱ በቴለቪዢን መስኮት ከማየት በስተቀር ያገኙት አንዳችም ፋይዳ አልነበረም። ለንዶን ላይ ያደረግነው አከባበር እትዮጵያ ውስጥ ከተደረገው ይበልጥ ኢትዮጵያዊ ደርዝ (style) ነበረው።
እኔ የሚገርመኝ፣ የሚታለል ሕዝብ ብዛቱ! ተታሎ! ተታሎ! ተታሎ አለማለቁ! አንዱ ተሞሽልቆ ሲውጣ በብረት ዓይኑ እያየ ሌላው ሊላጭ መግባቱ! ሰሞኑን ጆሮን ጭው ከሚያድረጉት ውስጥ ለውስጥ ከሚሽሎከሎኩት ዓበይት ጉዳዮች መሐል፣ የይሉኝታ ሽታ (DNA) ዝር ያላለበት የዘመናችን ዓይን-አውጣ ቡድን በየትላልቅ የዓለም ከተሞች በወኪሎቹ አማካይነት የሚያደርገው የገንዘብ ፍለጋ መልከስከስ ነው። አሁንስ ብሶበታል። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ የሙያ ማኅበራት፣ ተቃዋሚ የፖሊቲካ ድርጅቶች ምንም ዓይነት የገንዘብ ዕርዳታ ከውጭ እንዳይደርሳቸው ሕገ-አራዊት ነድፎ አንቀጽ ቋጥሮ ጥርቅም አድርጎ በሩን ዘግቶባቸዋል። ይኸን ካደረገ በኋላ የራሱን የልመና ኮሮጆ አንጠልጥሎ፣ ያለምንም ሀፍረት በዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ድርጅቶች ድጃፍ “ስለ-እመብርሀን” መጽውቱኝ፡ኢያለ ልመናውን በሞኖፖል ተያያዘው። ታዲያ ምን ያረጋል፣ ቢሯሯጥም ቋቱ ጠብ አላለለትም። በሌላ በኩል ደግሞ፣ “አሁን በሌሎች በሩን ሰለጠረቀምኩት፣ ወጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ለሎችን መርዳት ስለማይችል፣ ገንዘቡን ለኔ የሚያስረክብበትን ዘዴ ልቀይስ” ብሎ የተነሳ ይመስላል። ጨዋ ለመምሰል መጀመሪያ በዓይጋና በዋልታ የመረጃ ማዛቢያ ድረ-ገጾች ላይ ኢትዮጵያውን “ዶለራችሁን፣ ፓወንዳችሁን፣ የናችሁን እንዳለ በአገራችሁ ባንክ ማስቀመጥ ትችላላችሁ” ብሎ አወጀ። የሰማውም የለ። መልሳችሁ መውሰደም ብትፈልጉ በዚያው ባስቀመጣችሁት አገር ገንዘብ (currency) ይሰጣችሁአል” እያለ ወተወተ። ማን ሰምቶት! እነዚያን ድረ-ገጾች የሚያነብ ኢትዮጵያዊ በቁጥር ኢምንት ነበርና አመርቂ ውጤት አልተገኘም። ለ ዲ ኤል ኤ ፓይፐር በየወሩ 50 ሺ ዶላር ከየት መጥቶ ይከፈል? ጉድ ፈላ። ወያኔ ኤምባሲ ለተለያየ ጉዳይ የሚሄዱትን “ጠቃሚ መረጃ” እያለ ይጠቁማቸው ገባ። አልሆነም። አሁን ግን ነገሩ ዓይኑን አፍጦ መጣ። በታወቁት የወያኔ ቅጥረኛ አውደልዳዮች (ካድሬ) እና ለንዶን ውስጥ ከሚኖሩት፣ እነዚያ ዓባይ ሜዲያ ድረ-ገጽ “ወያኔ! ወያኔ! ወያኔ” እያለ ታርጋቸውን ግምባራቸው ላይ በለጠፈባቸው ሆድ አደር ከርሳሞች አማካይነት ያንኑ ዓይጋ ድረ-ገጽ ላይ ያያችሁትን ፎርም በገፍ እያባዛ በየሬስቶራንቱና በየመሸታ ቤቱ እያስዞረ መከፋፍል ጀምሯል። አልሰሜን ግባ በልው!! ሆ ሆ ይ! ጥጃ ለጅብ አደራ ይሰጣል እንዴ! ገንዘቡን መጣያ ያጣ ኃብታም ካለ ደግ።
እንግዲህ ወያኔ የማጭበርበር መሣሪያውን ወልውሎ በመጣ ቁጥር ከማስጠንቀቅ በሻገር የምናደርገው ነገር አይኖርም። ከዚህ በፊት ተናግረናል። አስጠንቅቀናል። “እምብየው!” ብለው ሂደው ተበሉ። አሁንም ይኸውና አዲስ ዘዴ አንግቦ ሊያጭበረብራችሁ ተነስቷል። አሁንም አዳሜ፣ “እምቢ” ብለሽ ሂደሽ የእሳት ዕራት ከሆንሽ፣ እኛ የምንለው፤ “ወደሽ ከተደፋሽ ቢረግጡሽም አይክፋሽ” ነው። እሰየው ከማለት ባሻገር ከንፈር የሚመጥላችሁ እንደማይኖር ከወዲሁ ዕወቁትና ጥጃችሁን ለጅብ በአደራ ከማስረከብ ታቀቡ።

2 comments:

  1. Dear Dr. Wondimu God bless you and your family. Your persistent contribution to justice and democracy is great. Presence of individuals like you is a big hope for many of us.

    Mulu..

    ReplyDelete
  2. Thank you Susana! God bless you too.

    ReplyDelete