ወንድሙ መኰንን
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ስቃይ መለስ ዜናዊ ከምንጊዜውም በበለጠ የማጭበርበር አክሮባት ሠርተው የኛው አባ ጉልቤ “በእንከን የለሹ” ብሔራዊ ምርጫ “ተቃዋሚውን አፈር ድሜ አስግጬው አሸንፍኩ” ብለውን አቅራሩብን! ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችም ከዚህ በፊት አይተው የማያውቁት ትርዒት በዝምታ እንዲመለከቱ ተገደዱ። አሜሪካኖቹ ሳይቀሩ በየኤምባሲአቸው እንዲቀረቀሩ ታዘዙ። እንዲህም አርጎ ምርጫ የለም። አባ ጉልቤ ማንን ከመጤፍ ቆጥረው! በአሁኑ ጊዜ እንኳን ለሌላው እና ለታማኙ ተቃዋሚአቸው ለአቶ ልደቱም አልራሩ። ሁሉንም ጠቀለሉት ጃል! አቶ ልደቱ ትንሽ ተዳፈሩ መሰለኝ። በቴሌቪዥን ክርክሩ ጊዜ ምን ያህል መንጠራራት እንደነበረባቸው አቅማቸውን ባለመገምታቸው ገደብ አለፍ አሉ መሰል። ሊቀ መኳሳቸው ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሰሐቅ መክረኛውን ኃይሌ ገብረሥላሴን ይዘው አንድ ነገር እንዲፈጽሙ ተነግሮአቸዋል። ምን ይታወቃል፣ አቶ ልደቱ አቅማቸውን ካወቁ በኋላ፣ በድርድር ሚኒስቴር ሊሆኑ ይችላሉ። ኢሕአዴግ እንደ እግዚአብሔር መሐሪ ሆኖ የለ? በሌላ በኵል ደግሞ፣ በረከት ስምኦን ጋር ፎቶአቸውን እንደባንዲራ እያውለበለቡ፣ ከአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ያላተሙአቸውንም እንጂኒየሩም ሳይቀሩ በዘሮ ዘረሩአቸው። አሁን እንጂነየሩ እንደተቀየሙ እንዳይቀሩ፣ ምናልባት ፕሮፌሰር ኤፍሬም አሁንም ተዓምር ሊሠሩ ይችላሉ። ክፍት የአማካሪ ቦታ አለ የሚል ፍንጭ እየሰጡን ነው። እርስ በርስ ያናኮሩትም አንድነት ምንም አልበጀው። ብርቱካን እስር ቤት እንደተዘጋች እንዳትሞት እና የሕዝቡን ቁጣ እንዳታነሳ፣ ምናልባት አሁንም ኤፍርም የሚሠሩት ተአምር ሊኖር ይችላል። አቶ መለስ፣ ዋናውን ተፎካካሪአቸው አቶ ስዬ አብራሀን በዚህኛውም መስክ ያለርህራሔ በባዶ ረቱአቸው፡፡ የሕዝቡን እጅ በግድ ጠምዝዘው 99.4% (0.6ቷ የተገባች) ድምጽ ለወያኔ አስመዝግበዋል። የኢሰፓ/ደርግ ፖሊቲካ ጊዜዋን ጠብቃ በሾርኒ ብቅ አለች አይደል? በወያኔ የብሔራዊ ክደት ባለሟሎች ጥቅም ላይ ዋለች እንደገና? ደርጎች ነብሳችሁ አይማርም። አንድ ተጨማሪ ተንኰል አስተምራችሁ ሄዳችሁ። ሰሎሞን ተካልኝ የተባለ ገንዘብ እየተከፈለው የሚዘፍን የአገራችን የጠጅ ቤት አዝማሪ ቢጤ እበላ ባይ ሰው፣ ስንት ብር ግንባሩ ላይ እንደለጠፉለት አይታወቅም፣ ጋንጩሩን አስቀየሚ መለስ ዜናዊ፣ “ቅንድቡ ያማረለት ቆንጆ፣ ምሑር የምሑራን ቁንጮ” እያለ እንዲዘፍንላቸው ግጥም አቀበሉት። ይኸም አልበቃ ብሎአቸው፣ መስቀል አደባባይ በስሜት ገንፍለው ወጥተው ፈንጭተዋል። ግን የፈነጩት ጥይት ከማይበሳው መስታወት በስተጀርባ ነው። ፈሪ ጨካኝ ነው።
የወያኔ ባለሥልጣናት፣ የአገር ቤቱን ሕዝብ አንዴ በክንዳቸው ካዳሸቁት በኋላ፣ ዓይናቸውን በጨው ሙልጭ አድርገው አጥበው፣ ምንም ሳያፍሩ (ድሮስ ማፈር መች ተፈጥሮባቸው?) ውጭ አገር ተበትኖ ወደሚኖረው ስደተኛ ኢትዮጵያዊ በአንድ ልብ ፊታቸውን አዙረዋል። ቢሳካም ባይሳካም ሁሉንም መሞክራቸው መቸም አይቀርም። አዳሜ፣ እየመጡብህ ነውና ስደተኛ ሁሉ ጥግ ያዝ! ወያኔዎች ያንን የቀልድና የልጆች የዕቅ-ቃ ጨዋታ መሰል ምርጫ ላይ ድል ሲቀናጁ፣ ውጭ አገር የተነሰነሱት አሽክሮቻቸውም ጌቶቻቸውን ለማስደሰት አልተኙም። አማራውን በአሞሌ ጨው እያባባሉ በጠነዛው ጉሮኖአቸው ሊሞጅሩት ሰሞኑን አንድ ዘግጀት ለንዶን ውስጥ ደግሰዋል። ሆዳሞቹ ከርሳቸውን ለመሙላት ይሄዳሉ። ሆድን የሚያክል ክፉ አውሬ! ወጥመዱ ውስጥ የሚገቡላቸው አይታጡም። ኢትዮጵያውያን ግን ለሌላ ዙር ትግል እየተደራጁ ነው።
ከዚህ በፊት “ጥጃ ለጅብ?” በሚል አርዕስት አንድ መልዕክት ሞጫጭሬ ነበር። ካላዩት፣ የሚከተለውን የግሌን ድረ-ገጽ ወይም ብሎግ ይመልከቱ። http://wondimumekonnen.blogspot.com/
በዚያ ርዕስ እንድጽፍ ያኔ ያስገደደኝ ምክንያት በዚያን ሰሞን ወያኔ እንደዛሬው ወጥምድ ጠምዶ ስደተኛውን ሊመዝብር ደርሰንበት ነበር። በጊዜው የለንዶኖች የወያኔ ጥቅም አስጠባቂዎች በኤምባሲው አማካኝነት በአካባቢው ኗሪ ስደተኛውን ኢትዮጵያዊ ሕብረተሰብ በየሬስቶራንቱና በየመጠጥ ቤቱ እያደኑ፣ “አገራችሁ በጣም ተሻሽላለችና፣ ገንዘባችሁን በፓውንድ ኢትዮጵያ ባንኮች ውስጥ አስቀምጡ። ወለድ ይወልድላችሁአል። በፈለጋችሁ ጊዜም ልታወጡት ትችላላችሁ፤” እያሉ በተለመደው የቁጭ-በሉ ታክቲካቸው ሊያታልሉ ስሞክሩ ነበር “ጅብን ጥጃ ጠብቅ ብለው አምነው አይተውለትም” ብዬ ወገኔን ያስጠነቀቅኩበት። ወያኔ የውጭ ምንዛሪ ባገኘው መንገድ ለመመዝበር አስቦ አልሰሜን አባብሎ አስግበቶ ለመሞጭለፍ የነደፈው ታክቲክ ውሀ በላው። አይታሰብም! ወገናችን ነቃ። ዕቅዳቸው ከሸፈ። ጎበዝ!! አሁን ደግሞ ሌላ የባሰ ተንኰል እየመጣብህ ነውና፣ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እጂጌህን ሰብስብ። በያለህበት ንቃ! ለወያኔ አትታለል። ለነዚህ የቀን ጅቦች እራስህን አትሰዋ። ኦሮሞን፣ አማራን፣ ወላይታን፣ ሲዳማን፣ ጉራጌን እየነጠሉ፣ በልማት ማኅበር ስም እየከፋፈሉ ዲያስፖራውን ሊያዳክሙ በአጭሩ ታጥቀው ተነስተዋልና ተዘጋጅተን እንጠብቅ። ከዚህ በፊት በፍረንጆቹ አቆጣጠር 2006 ዓመተ ምሕረት ላይ፣ በያለንበት ሊያኮላሹን የነደፉቱትን 52 ገጽ የፈጀ እቅዳቸውን አግኝተን ይፋ አድረግን ነበር። ካላዩት፤ የሚከተለውን ድረ-ግጽ በአስሊ መኪናዎ አመልካች ጠቁመው ያንብቡ።
http://www.ethiomedia.com/carepress/attack_on_diaspora.html
የወያኔ አሽከሮች፣ ያንን ሰነድ ሥራ ላይ ለማዋል ዛሬም ሌት ተቅን ይባዝናሉ። እንቅልፍም አይተኙም። ተኝተውም አያድሩም። ነገር ሲጎነጉኑ ውለው ነገር ሲጎነንጉኑ ያድራሉ። ሰሞኑን በጉያቸው ሸጉጠው ብቅ ብቅ ያሉባት ታክቲክ በጎን ሲታይ አያ ጅቦ ሆዬ ጥጃውን እራሱን “ና! ለምለም ሳር ያለበትን አውቃለሁ። ንጹህ ውሀ የሚፈስበትን ምንጭ አሳይሀለሁ፣ ደግ እረኛህ እኔ ነኝ። ና ላሰማራህ!” የሚል አባባይ ደም የጠማው ተንኰለኛ ተኵላ ይመስላል። ይኸ የወያኔዎቹ እንቅስቃሴ፣ ከወጥመድነቱም ባሻገር፣ አማራው ላይ የወረደ ስድብ ነው። ወያኔ አማራን ሊያደራጅ! ጉድ ነው!
ወያኔ ትላንትና “አማራ ጠላታችን ነው። አማራ ጨቋኝ ነው። አምራ ነፍጠኛ ነው” እንዳላለ፣ አሁን ደግሞ “አማራውን በልማት ማኅበር ላደራጅ” ብሎ “ተቆጣጢርና ደምሲስናውን” ስትራተጂ ነድፎላችሁ በአጭሩ ታጥቆ በድፍረት ተነስቷል። ጅል አማራ-አማራው እየተመረጠ ይጃጃልለት እንዶሆነ እንጂ፣ መቸም በጤናው ስድቡን እየጠጣ ከወያኔ በታኝ ቡድን ጋ በደኅና አዕምሮው የሚተባበር ይኖራል ብዬ አልገምትም። ይኸ አባባሌ ታዲያ ሆድሞችን አይጨምርም። ሒሊና ቢሶችን ቁጥር ውስጥ አይገቡም። ሆዳሞቹማ አይደሉም እስከዛሬ ያስጠቁን? ወያኔዎች እንዲህ የሚል ድብዳቤ ለጥቁር (ተለጣፊ) አማሮች፣ ለአስመሳዮችና እንዲሁ ለየዋሆች ልከዋል!።
“አልማ (አማራ ልማት ማኅበር መሆኑ ነው) 2002 ... በቅርቡ አዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ በተካኼደ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት 1.2 ሚሊዮን ብር ገቢ ማሰባሰብ ችሏል።
በዚህም መሰረት በእንግሊዝ አገር አልማ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ ሜይ 29 ቀን 2010 አቶ ሕላዊ ዮሴፍ የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) የቦርድ ሊ/መንበር በተገኙበት ታላቅ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጀት ይደረጋል።
ስለሆነም በዚህ ታላቅ ዝግጀት ላይ ተገኝተው የበኩልዎን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪአችንን እናቀርባለን።”
“አልማ” አሉት? “አጥፋ” ባሉት ባማረላቸው። “የአማራ ጥፋት ማኅበር”!!! ገሩምና ደግም ልክ ነው። የግብዣ ደብዳቤው ላይ የኢትዮጵያን ኤምባሲ ማኅተም ጉብ ብሎበታል። አምባሳደር ብርሀኑ ጥሩ ግልጋሎት እየሰጡ መሆን አለበት። ቦታውም እዚያው “ኢትዮጵያ ኤምባሲ ነው”። ጃንሆይን ያመስግኑ። ምን የመሰለ የተንጣለለ ቤት ለነዚህ ጉዶች ጥለውላቸው አለፉ። ወያኔዎች አንዴ ቤቱን ሊሸጡት ሲያስማሙ ነበር። ንጉሡ አንድ ያሠሩት ሕግ ነገሩን አፈረሰባቸው መስል መሸጥ አቃታቸው። ጉድ ነው። እንግዲህ በዚሁ አዳራሽ ነው የአማራ ጥፋት ማኅበር ሊደራጅ የተደገሰለት። ወያኔ አማራን ሊያደራጅ!!! ያውም በልማት ማኅበር አደራጅቶ እንደከብት ሊነዳ! እኔ ልንገራችሁ ቁርጡን! ወያኔ ያደራጀው አማራ፣ ዝናብ ያጨቀየው አቧራ!!! የጨቀየ ጭቃ ልብስና ጫማ ከማቆሸሽ ባሻገር ለምን ይጠቅማል? ጭቃን እያነሱ የሆን ነገር ላይ፣ ከመልደፍ፣ ከመደፍደፍ፣ ከመለጠፍ፣ ከመመረግ በስተቀር ምን ይደርግበታል? ከወያኔ የሚተባበር፣ ያው ተለጣፊ ጭቃ አይደል? የጭቃም ጭቃ! አንድ የምወዳቸው አዛውንት አንዴ የሆነ ነገር ግርም ብሎአቸው በአንድ ስብሰባ ላይ፡ “የቸገረው ዱቄት ከነፋስ ይጠጋል” ብለው አስደመሙን። ዱቄቱስ መጠጊያ አጥቶ ነው ከበታኙ የሚጠጋው፣ ስደተኛው አማራ ምን ቸግሮት ነው ከአራጁ ጋር የሚውለው? የወያኔስ ድፍረት አላበገናችሁም? “እሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጎበኘው” ይሉሀል ይኸ ነው። አማራው ያለወትሮው ተኝቶ ሲገዛላቸው የወያኔዎች ድፍረት ድንበሩን ጣሰ። ማፈር ቀረ። መፍራት ቀረ። ጎበዝ አንድ በሉ!!
እስቲ ከድሮው የወያኔ ካድሬ፣ አሁን እራሱን ነጻ ካወጣው፣ ከተስፋዬ ገብረአብ መጽሐፍ ትንሽ እንመልከት። (ነገሩን ያገኘሁት ከ”ደራሲው ማስታወሻ” ተስፋዬና አንዳርጋቸው ካደረጉት ውይይት፣ በ125 ገጽ ላይ ነው)።
“በኢህአዴግ የድርጅት ኮሚቴ ደረጃ ውይይት ከተደረገበት በኋላም፣ ኢሕዴንን ወደ አማራ ድርጅትነት ለመለውጥ ጥናት ይደረግ ተባለ። ጥናቱ “አማራነት ምንድነው?’ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥ መመሪያ ተሰጠ። ክዚህ በሁዋላ ቀጣዩ ጥያቄ፣ ጥናቱን ማን ይስራው?’ የሚል ነበር።
አንዳርጋቸው ትረካውን አቋርጦ መሳቅ ጀመረ።
ምንድነው የሚያስቅህ?’ አልኩ
‘ጥርናቱን ማን እንዲያካሄድ እንደተወሰነ ታውቃለሁ?’
‘ማን ሆነ?’
‘በረከት ስምኦን”
በረከት እኮ ማለት አማራን በጣም የሚጠላ፣ አማርኛን መናገር የሚጸየፍ፣ የዞረበት ዘረኛ ዜጋ ነው። ለምሳሌ በቪኦኤ ትግርኛው ፕሮግራም ቃለ መጠይቅ በደስታ በትግርኛ ሲሰጥ፣ እንግሊዝኛው ፕሮግራም ላይ ቀርቦ በእንግሊዝኛ ሲንተባተብ፣ በአማርኛው መርሀ ግብር ላይ ግን አማርኛ ላለመናገር ጨርሶ የማይካፈል፣ ጸረ አማራ ስሜት የተጠናወተው ጠብራራ ፍጡር ነው” ሲፈጠር ክፋትና ውሸት አብሮት ተፈጥሮ አብሮት ያደገ ያጨካኖች ቁንጮ ሲሆን፣ ወያኔ በመልኩ የጠፈጠፈው የአማራው፣ ድርጅት መሪ ነው። ምን እሱ ብቻ፣ ተፈራ ዋልዋ የተባለ ዘረኛ፣ አንዲት ጠብታ የአማራ ዘር በማይስክሮስኮ ሥር ቢመረመር የማይገኝበት ፣ (ተስፋዬ ገብረአብና አንዳርጋቸው የጊሚራ ተወላጅ ተወላጅ ነው ይሉታል መጽሐፉ ውስጥ)፣ የአማራውን ድርጅትን ቀፍድዶ ይዞ አመራር ላይ ጉብ ብሎ የወያኔን ጉዳይ ያስፈጽማል። እነዚህ ሁልቱ መርዘኞች ነበሩ፣ ዲላና አዋሳ በተካሄደው ስብሰባ “የኢህአዴግም፣ የደቡብ ሕዝብም ጠላቶች አማራና ጉራጌ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ናቸው” ብለው መርዝ ሊረጩ ሲሞክሩ፣ የወላይታና የሲዳማ ብሔረሰብ አባሎች አዋርደዋቸው የመለሱአቸው። ተፈራ ሲናገር፣ “የአማራ ብሔረስብ አይታመንም። ዝም ብሎ አድፍጦ ጠብቆን በካርዱ አደባየን” ብሎ ስሞታ አሰማ። እስቲ ይታያችሁ፣ እነዚህ አማራ ላይ በቂም በቀል የተመረዙ ነበሩ እንግዲህ የተለጣፊው አማራ ብሔረሰብ ድርጅት መሪዎች የሆኑት። ተወልደና አለምሰገድስ ቢሆኑ ትግሬ ሆነው ሳሉ፣ የአማራው ድርጅት ፈላጭና ቆራጭ ሆነው መሰየማቸው ምን ይባላል?
አንዳርጋቸው ንግግሩን ቀጥሎ ተስፋዬን እንዲህ ይላል መጽሐፉ ውስጥ።
“የአማራ ማንነት በረከት ስምኦን እንዲያጠና ታዘዘ። አያይዞ በረከት ቀጠለ። በረከት ስምኦን ጥናቱን ኣጥንቶ ጨርሶ ይዞ መጣ። የሚደንቅ ጥናት ነበር። ፅሑፉ ገና ሲጀምር አማራውን ያወግዛል። አማራው ሌሎች ብሄርብ-ሄረሶቦችን እንዴት እንደጨቆነ ይተነትናል። የአማራው ነፍጠኛ ሌሎች ላይ አደረሰ የሚለውን በደልም ያብራራል። አማራው ሌሎች ሕዝቦች ላይ ፈጸመ የሚባለውን ግፍ አንድ በአንድ ለቅሞ ጽፎአል። በረከት ይሔን ሁሉ አንብቦ ሲያበቃ፣ ‘አማራነት ምንድነው ለሚለው ጥያቄ ምላሽ እንደሰጠ ተማምኖ ወረቀቱን አጣጠፈ።”
እንግዲህ እንዲህ ዓይነት ዓይኑን ያፈጠጠ፣ ጥርሱን ያገጠጠ ጥላቻ የተፈጸመው አገር ቤት ባሉት አማሮች ላይ ነበር። ያም የሆነው አማራ ነን የሚሉ እንደጉልቻ የተጎለቱ፣ እንደ ጉቶ ግማጅ የተተከሉ ባሉበት መድረክ ነበር። በጠመንጃ አፈሙዝ አስገድደው ኣማራው ስድቡን ጠጥቶ፣ ውርደቱኝ ችሎ አገር ቤት አፍዝ አድንግዝ የደገሙበት ይመስላል። ግን ለንዶን ድረስ በድፍረት መጥተው የአማራ ልማት ድርጅት እናቋቁማለን ብለው ሲወዛወዙ ማየት፣ “እውነትም አማራ ተቀልዶበታል” ያሰኛል።
አማራ ነን እያሉ፣ አማራውን ለመቅበር ጎድጓድ የሚቆፍሩ የወያኔ ቅጥረኛ ኩሊዎች፣ ኦሮሞ ነን እያሉ ለሚበደለው ኦሮሞ መቃብር የሚምሱ ሆዳሞች ሞልተዋል። እዚህም ቤት እዚያም ቤት ሞልተው ተርፈዋል። የወያኔ ዓላማ እነዚህን ሆዳሞችን ተጠቅሞ በዘር ከፋፍሎን ኢትዮጵያን ብትንትኗን ሊያወጣት ነው። የዚህ ወይም የዚያ ብሔር ልማት እያለ ገንዘብ ይሰበስባል። ዳሩ ግን የአማራውም ሆነ የኦሮሞው ሕይወት ግን ከድጡ ወደ ማጡ ሲዘቅጥ እንጂ ሲሻሻል አልታየም። ለሆዳሞቹ፣ አንድ መልዕክት አለኝ። መልዕክቱም ሲወርድ ሲዋረድ ከአባቶቻችን የመጣ ነው። በሱው ልዝጋው ጦማሬን።
እዚያም ሂዴሽ በላሽ፣ እዚህም መጥተሽ በላሽ
ሰው ታዘበሽ እንጂ፣ ሆድሽን አልሞላሽ!
No comments:
Post a Comment