ሰሞኑን አንድ ቀልድ ከኢትዮጵያ መጥቶ በየድረ-ግጹ እየተዘዋወረ ነው። ቀልዱም እንዲህ ይላል።
ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! ባለፈው ዓመት፡ ዘጠና ዘጠኙ ከመቶ ሕዝባችን የሚወዳቸውን፡
1ኛ. ዝነኛውን ዘፋኛችንን፣ ጥላሁን ገሠሠን ወሰድክብን
2ኛ. ዝኘኛውን ተዋናይ፣ ሲራክ ታደሰን ወሰድክብን
3ኛ. ዝነኛውን ቀልደኛ አዝናኝ፣ተስፋዬ ካሳን ወሰድክብን
የዘንደሮው ዝነኛው ተወደጁ ፖሊቲከኛችን ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ናቸው።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሥቃይ፣ መለስ ዜናዊ 99.6% በምርጫ አሸነፍኩ የሚለውን አዋጃቸውን ተከትሎ ነበር ይኸ በአዲስ አበባዎቹ የአራዳ ልጆች የተፌዘው። ተወዳጅ ተወዳጁን እየመረጠ ጌታ ከወሰደ አሁንም ፈቃዱ ይፈጸም። አሜን እንበል። አሜን!
የወያኔ እጅ፣ አገር ቤት ያለውን ሕዝብና ተቋሙን ተቆጣጥሮ የመደምሰስ ስትራተጂው (የረጅም ግብ ዕቅዱ) ቀፍድዶ ይዞ ዓላማው ሙሉ በሙሉ የተሳካለት ይመስላል። ያልተቆጣጠረው አንዳችም ነገር የለም። ያ ሁሉ ሚሊዮን ሕዝብ በክልል፣ በአውራጃ፣ በወረዳ፣ በቀበሌ፣ በመንደር እያለ ወርዶ እስከቤተሰብ ድረስ ተጠፍሯል። ኦሮሞው “ኦሕዴድ” በሚባል ቀልቀሎ ተሞጅሯል፣ አማራው ብአዴን በሚሉት ስልቻ ተወጥቋል። ደቡቡም፣ ሲሜንም እንዲሁ በየዘንቢሉ ታሥሮ ተንጠልጥሏል። ዘዴው ከራሺያው ስታሊን የተወረሰ ነበር። ዛሬ፣ ቤተሰቡ ለወያኔ ካላደረ፣ ልጅ ትምሕርት ቤት አይገባለትም። ለወያኔ ያልተገዛ ወጣት ሥራ አይገኝለትም። ዩኒቨርሲት የመግባት ዕድልማ “ኢሕአዴግ” ካልሆኑ አይታሰብም። ለወያኔ የፖሊቲካ ካባ ፓርቲ፣ “ለኢሕዴግ” (እነሱ ሲያቆላምጡት “አድጊ” ይሉታል) ያላደረ ሠራተኛ የሥራ መተማመኛ የለውም። ነገ እንደውዳቂ ዕቃ ተሽቀንጥሮ ይጣላል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔን (ኢሰመጉን) አዳክመው ገድለውታል። የኢትዮጵያ መምሕራን ማኅበርን (ኢመማን) በሕገ አራዊት ወጥሮት በዚያ ስም እንዳይንቀሳቀስ ሲያግድ አባላቱ ሌላ ስም ፈጥረው “የኢትዮጵያ ብሔራዊ መምሕራን ማኅበር” እንኳ ብለው ለመንቀሳቀስ ማመልከቻ ቢያስገቡ፣ “የኢትዮጵያን ስም መጠቀም አትችሉም” ተብለው ተሽመድምደው ተቀምጠዋል። ከውጭ ዕርዳታ እንዳያገኙ “በሕግ” ተከልክሏል። አስተማሪው አፉን ተለጉሞ፣ ተተብትቦ በመቀመጡ ትምሕርቱ እራሱ ታሥሯል። የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞችን ማኅበር ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ሥር አውለውታል። የሠራተኛውን ማኅበርማ ገና ከጠዋቱ ነበር የተቆጣጠሩት። ሁሉ በጃቸው ሁሉ በደጃቸው ሁኖላቸዋል። መሬቱ በጃቸው (እንደፈለጉ፣ ይሸጡታል፣ ይለውጡታል፣ ይለገሱታል)፣ እርሻው በጃቸው፣ ንግዱ በጃቸው፣ ሕክምናው በጃቸው፣ ጦሩ በጃቸው፣ ፍርድ ቤቱ በጃቸው፣ አስመራጩ ድርጅት በጃቸው ... ምን ቀራቸው? በአጠቃላይ አገር ውስጥ ኗሪ ሕዝባችን ሕይወቱ ሙሉ በሙሉ በወያኔ ቁጥጥር ሥር ወድቋል። አንድ ጊዜ አንድ የነደደው ኢትዮጵይዊ ሠራተኛ፣ ወርቃማው አለቃው ጠርቶት የስለላ ሥራ በባልደረቦቹ ላይ እንዲሠራ በግልጽ ሲያዘው፣ ንድድ ብሎት፣ “ይኸንንስ ከማደርግ ለምኜ ባድር ይሻለኛል” ብሎ በድፍረት ተናገረው። ወርቃማው አለቃ እየሳቀ መልሶ፣ “ያንንም እኛ ስንፈቅድልህ ነው” ብሎት አረፈ። ሕዝባችን እስከዚህ ተዋርዷል።
በመዳፉ ሥር ያለው ሕዝባችን አማራጭ በማጣቱ፣ 99.6% ድምጽ እንዲሰጠው ያለምንም ዕፍረት በግድም ሆነ በውድ አስፈጽሞታል። የሚገርመው ባሕር ተሻግሮ ኢትዮጵያዊውን ዝርያ በሙሉ ለመቆጣጠር የነደፈው የረዥም ጊዘ ዕቅዱ ነበር። እኛ ደግሞ ለእንደዚህ ዓይነቱ ዓይን ያወጣ ድፍረት፣ ምቹ ነን። ዕቅዱን አውጥቶ አሠራሩን ነድፎ “የኮንስቲትወንሲ ግንባታ መሪ ዕቅድ” ብሎ ለየኢምባሲው የበተነው በ1998 ዓመተ ምሕረት ነበር። በየኤምባሰው የተኮለኮሉትም ጉዳይ አስፈጻሚዎች ሥራውን በሰፈው ተያይዘውታል። አምባሳደር ካሳሁን አየለ የፈረሙባቸው 21 ደበዳቤዎች ዛሬም አዲስ ቮይስ በሚባል ድረ ገጽ ለሕዝቡ ጥቅም እንዲውሉ ተቀምጠዋል ። ቢንያም ከደር የተባሉ የቀደሞ በኩዌት የኢትዮጵያ እምፓሲ ዋና ጸሐፊ ይኸንኑ በኢትዮሜዲያ ድረ-ገጽ አረጋግጠውልናል።
ውጪ ኗሪ ኢትዮጵያዊ ሳይወድ በግድ ተሰዶ ነው የተበተነው። ያኔ ከቤቱ ከዘመዱ ከአዝማዱ ሲሰደድ አሳዳጁን ያውቀው ነበር። ከሞት የተረፈው ዛሬ ለዚያ የዳረገውን ረስቶት ይሆን? የበረሀውን ሐሩር ተቋቁም፣ የሞተው ሙቶ፣ ባሕሩን ደፍሮ፣ የሰጠመው ሰጥሞ የተረፈው የደረሰበት ደርሷል። አንድ ሰሞን አንዲት ዘመዳችን በሱዳን ሰሐራ በረሀን አቋርጣ፣ በሊቢያ አድርጋ ሜዲቴራኒያን ባሕር በአልባሌ ታንኳ ስትሻገር ብዙ ወገናችን ስምጦ በዓሳ ሲበላ በዓይኗ አይታለች። እሷ በተአምር ተርፋ ማልታ ደረሰች የሚል ዜና ሰማን። ከሎንደን ከቤተሰቤ አንድ ሰው ማልታ ድረስ ሂዶ እንዲጎበኛት ወስንን። አማራው፣ ኦሮሞው፣ ትግሬው ጉራጌው፣ ኤርትራዊው በዘር መከፋፈሉን ወደ ጎን ትቶ “በአብሻ” ስም ተሰብስቦ ተጋግዞ ተጠጋግቶ የማልታ የስደት መተላለፊያ ኑሮውን በመጠለያ ይገፋታል። ታዲያ እነዚህ “አበሾች” ዓሳ አንበላም ብለው እርፍ። ምነው ቢባሉ፣ ዓሳው ወንድምና እህታቸውን ሲባላ ስላዩት እሱን መብላት ወገናቸውን የሆነውን የሰው ሥጋ የበሉትን ያህል ስለሚሰቀጥጣቸው እንደሆነ አስረዱ። በዚህ ሁኔታ ለንዶን፣ አምስተርዳም፣ ኮፐንሀገን፣ ኦስሎ፣ ኢየሩሳሌም፣ ኩዌት ... ኒው ዮርክ፣ ዋሽንግተን፣ ሎስ አንጀለስ፣ ... ኦቶዋ፣ ቶሮንቶ፣ ኦንታሪዮ፣ ... የገባውን ስደተኛ ነው ወያኔ መልሶ ቁጥጥሩ ሥር ለማግባት በሰፊው የተሰማራው። ትንሽም ቢሆን እየተሳካለት ነው። ሆዳም ሞልቷላ። የትላንትና ስቃዩን እንዲረሳ ሆድ አስገድዶት አንዳንድ ወገናችንን ከወያኔ ጋር መወገን ጀምሯል። በጣሊያን ወረራ ጊዜስ ባንዶች አልነበሩ ሕዝባችንን ያስጨረሱት? ዛሬም የባንዳው የልጅ ልጅ ነግሶብን ከወገናችን ደካማ ደካማውን በሆዱ እየገባ እየመለመለ እያበነደደው ነው።
የወያኔን ዘዴ በተለያዩ ጊዜያት አጋልጠናል። ይኸችን ሰሞን እንኳን፣ “እሳት ቢያንቀላፋ ገልባ ጎበኘው” በሚል ርዕስ ወያኔ “የአማራ ልማት ማኅበር ሊያቋቁም” እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ሜይ 29 ቀን 2010 ዓ ም (29 May 2010) መጥራቱን በየድረ-ገጹ አጋልጠናል ። በአጭሩ ወያኔ አማራውን ሊያለማ ከቶ ፍላጎትም ሆነ የሞራል ብቃትም እንደሌለው ጸሐይ የሞቀው ሐቅ ነው። ዋናው ቁም-ነገር እና ልፋቱ ሁሉ ስደተኛ አማራውን ተቆጣጥሮት ሊያጠፋው ነው። ወያኔ ኦሮሞውን ሊያለማ ፍላጎት የለውም። ዓላማው ሌላ ነው። ሕዝባችን በዚህ ተታሎ እንዳይሄድ ብንነግረውም፣ የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል ሆኖበት መሰል 200 የሚድርስ ስደተኛ ሂዶለታል የሚል መረጃ ደርሶናል። ወያኔ ከሌሎቻችን የሚለየው በአንዲት ነገር ነው። የማይቻል መስሎ የሚታየውን ሁሉ ከመሞከር ወደ ኋላ አይላትም።
“የከተማ መሬት ይሰጠሀል” እየተባለ እራሱ ሰው መረማመጃ መሬት እየሆነ የሚነጠፍለት ሆድ አደር እየበዛ መጥቷል። “ግባ ወደ አገርህ። መኖሪያ ቤትህን ሥራ” እየተባለ ተሸውዶ በየወያኔ ኤምባሲው ወዶ እየገባ እጁን የሚሰጥ ሆድ አደርን ያው ከርሳሙ ሆዱ ይቁጠረው። ሲሄድ ታድያ ሙሉ ስሙን፣ አድራሻውን ስጥቶ፣ ስልኩን አስረክቦ ነው የሚመለሰው። በአጭሩ ሒሊናውን ሽጦ ነው የሚመጣው። የወያኔን ወንጀል ለዓለም ሕዝብ ለማጋለጥ ሰላማዊ ሰልፍ በወጣንባቸው ማግስት የወያኔ አምባሳደሮች፣ ያንን በአሥር ሺህ የሚቆጠር ስም ዝርዝር ይዘው በየአገሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ መኮልኮል ዓይነተኛ ልማዳቸው አድርገውታል። ምነው ቢባል፤ “እዚህ ሰላማዊ ሰልፍ የሚሰለፉብን፣ በአብዛኛው የደርግ ርዝራዦች ናቸው። በመቶ ሺ የሚቆጠር የኢኮኖሚ ስደተኛ ይኸውና እኛ ጋ ተመዝግቦ ኢሕአዴግ አገር ውስጥ የሚሠራውን የልማት ሥራ በሞራልም በገንዘብም ይድግፍልናል” እያሉ የወያኔ ልዩ መልዕክተኞች ያጭበረብሩበታል። ሒሊና-ቢስነት ይሉሐል ይኸ ነው። ለወገን ደንታ-ብስነት ይሉሀል ይኸ ነው። ለሆድ ሲሉ ወገንን ማስጠቃት፣ ወገንን አሳልፎ መስጥት ማለት ይኸ ነው። ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ዛሬ ሁለት ነገር እንቃኛለን።
፩ኛ - የሎንደኑ የኢትዮጵያውያን የእግር ኳስ ጨዋታ ቡድን
ወጣትነት የእሳት ዘመን ነው። ወጣቱ ስደተኛ የእግር ኳስ ጨዋታ፣ የኢትዮጵያ ዘፈንና ጭፈራ ይወዳል። ወያኔ ሁሉም ቦታ አለ። የወያኔ ባለሥልጣኖች ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ የአጎት የአክስታቸውን ልጆች በስደተኛ ስም በገፍ ወደ ሎንደን አግዘዋቸዋል። ሥራ ፈጥረውለት መሆኑ ነው። ታዲይ እነዚህ አስመሳዮች ከዕውነተኛ ስደተኞች መሐል በጓደኝነት መልክ፣ በኳሱ ሜዳ፣ በጫቱ በርጫ፣ በየጭፈራው ክበብ ተሰግስግው ሰይጣናዊ የወያኔ ተግባራቸውን በሰፊው ተያይዘውታል። ልብ ማኮላሸቱን ቀጥለውበታል።
እንግዲህ አንዱና ዋነኛው በሎንደን የስፖርት ፍቅር የሳባቸውን ወጣቶች አድብቶ የሚያጠምድ ወያኔ፣ የአቶ አባይ ጸሐይ ቤተሰብ አባል በመሪነት ተሰማርቷል። እያንዳንዱ የዚህ ቡድን አባል ማን ማን እንደሆነ ያውቃል። አላሙዲም ብቅ ሲል ስኳር እንደሚያቅማቸው እናውቃለን። ልጆቹ በተለያዩ ድለላ እንደተያዙም ሳይታለም የተፈታ ሐቅ ነው። ከተለያዩ አገሮች የመጡት ስደተኞች የሚገናኙበት “የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ጨዋታ ውድድር” በሚል ሰበብ ሰሞኑን በወያኔ ካድሬዎች አነሳሽነት የታቀደ ተግባር ሥራ ላይ በመዋል ላይ ይገኛል። ከየአገሩ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የሚኖሩትን ስደተኞች አስተባብረውም ጨዋታ ጀምረዋል። ታዲያ አንዱ አስገራሚ ነገር፣ የድፍረታቸው ድፍረት ወያኔዎች አንዳንዱን የዋኅ ኢትዮጵያዊ ወጣት አግባብተው፣ እነሱ ያዘጋጁለትን፣ መለያ ልብስ ወይም በተለምዶ ማላያ እንዲልብስ አድርገውታል። ማላያውም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የተዋረደባት ጠባሳ አምባሻ መሳይ ኮከብ ምልክት ደረቱ ላይ ደረተውበታል። “ይኸ ቡደን የኔ ቡድን ነው” እያለን ነው ወያኔ! በዚህ የተነሳ ወጣቶቹ እስከመበጣበጥ ደርሰው ግማሾቹ “ይኸንን ሰንደቅ ዓላማችን ብለን ለብሰን አንጫውትም” ብለው እራሳቸውን ሲያግልሉ ሌሎቹ የዋኾች ግን “የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ምንም ኖረበት ምን ያው የኢትዮጵያ ሰንደ ዓላማ ነው፣ ሁሉንም በፖሊቲካ አትተርጉሙት” በማለት ቀጥለውበታል። ባለፈው ሁለት ሳምንት ቻልፎንት ስታዲየም አካባቢ ባደረጉት ግጥሚያ መሸነፍ ደርሶባቸው ተመልሰዋል። ድሮውንም ጎበዝ-ጎበዝ ተጫዋቾች የማይካፈሉብትና፣ ሁለት ልብ ሆነው የሚጫውቱትም ተጫዋቾች ከወገን የሚደርስባቸውን ወቀሳ እያሰላሰሉ መቼ አትኩረው ተጫውተው ውጤት ያገኛሉ? ወያኔ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ያግበሰበሰውና በኢትዮጵያ ስም ለምኖ ያካበተው ገንዝብ አለው። እንደልቡ ሊረጨው ይችላል። ያ ሁሉ ግን የእምቧይ ካብ ነው። ዛሬ ለሆዱ የተሰለፈለት የዋኅ ሕዝብ ነገ ለሕሊናው ይሰለፍበታል። እንዲያ አልነበር በቅንጅት ጊዘ የተፈጸመው? አሁንም ያ ይደገማል።
ሰንደቅአላማችንን በተመለከተ አንጀቴ አርሮ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ኖቨምበር 6 ቀን 2000 ዓ.ም በእንግሊዝኛ ቋንቋ የጻፍኩት ግጥም አለ። ከፈለጉ የግል ብሎጌ ውስጥ ገብተው ማንበብ ይችላሉ።
http://wondimumekonnen.blogspot.com/2010/06/scar.html
ሰንደቅ ዓላማችን ተዋርዷል። የተዋረደ ሰንደቅ ዓላማችን ከነአምባሻ ምልክቱ ለብሶ የተጫውተ እያወቀም ይኹን ሳያውቅ፣ ያው እርሱም ወይኗል። የወያኔ ካባ ውስጡ ዳባ ነው። ወያኔ ማላያውን ሲያለብስህ፣ “ተቆጣጥሬህአለሁ፣ የት አባትክ ልትገባ!” እያለህ ነው። አንዱን ሰው አንዴ ማኖ ካስነኩት አለቀለት ብለው ይገምታሉ። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ስቃይ አንዴ ለአዲስ ተሿሚ ካድሬዎች ላይ ሲፎክሩ ምን አሉ መሰላቸሁ። “የእሕአዴግ ሥልጣን፣ የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው። ሽልብ ካደረገ ዱብ ነው”። እንደሸረሪቷ ደምን ምጥጥ አድረገው ይተፉታል። ሁለተኛው ጉዳያችን የሚከተለው ነው።
፪ኛ፡ ዲያስፖራው አገር ቤት ገብቶ ንዋዩን እንዲያፈስ ወይም ኢንቭስት (invest) ኢንዲያደርግ የሚደረገው የጠልፋ ሙከራ
አንድ ጓደኛዬ የሚከተለውን ጥሪ “ተመልከት” ብሎ አስተላለፈልኝ።
Dear Ethiopia Investor,
As you know, Precise Consult International has been at the forefront of promoting Diaspora business in Ethiopia. Accordingly, we have been a part of four Ethiopian Diaspora Business Conferences, held in Addis Ababa, Washington DC, and Los Angeles, either as lead organizer or as a major sponsor. This year, on the fifth anniversary of the event, we have once again partnered with the Ethiopian American LLC and USAID Vega Ethiopia to put together what promises to be a historic milestone in Ethiopian business.
*So what’s in store this year?*
For the first time in the history of the event, this year’s conference will be held over two days and will be open to the wider Ethiopian Diaspora public in North America. It will also have a business exhibition from Ethiopia with the aim of helping to establish market linkages between Ethiopian business and the U.S market via the Diaspora. As ever, the topic of doing business in Ethiopia will be thoroughly covered by guests’ speakers already doing business in Ethiopia. This year’s event will also be presided over by a surprise high profile speaker.
*What’s in it for you?*
If you are a business in Ethiopia looking to penetrate the U.S market and would like to participate in the business exhibition, there are still openings left so contact us immediately to arrange the details. If you live in North America and you are looking to connect with Ethiopian businesses or would like to be informed about doing business in Ethiopia, do not miss this historic event. Please feel free to forward this message to all those you know who may be interested in doing business in Ethiopia. The fifth Ethiopian Diaspora Business Conference will be held in Washington, DC, July 11-12, 2010. For more information, please visit www.ethiopiainvestor.com
ይኸንን ጥሪ ሳነብ ከትከት ብዬ ነበር የሳቅኩት። የሸረሪቷ ነገር እንደገና ታየኛ! ሸረሪት ሆዬ ድሯን አድርታ ካበቃች በኋላ ከአካባቢው ራቅ ብላ ለሆዷ ካንዱ ጥንብ ወደ ሌላው ጥንብ የምትክለፈለፈውን ዝንብ ትጠብቃለች። ሆዷን እንጂ የተደራላትን አሽክላ ያላስተዋለችው ዝንብ በሸረሪቷ ድር ትያዛልች። ሸረሪት ተመልሳ ዝንቧ ገና በሕይወቷ እያለች ድሟን ምጥጥ አድርጋ ከጨረሰች በኋላ፣ ሌላ ራት ለማጥመድ የደረቀችውን ዝንብ ገፍታ ጥላ፣ ድሪዋን ጠጋግና እንደገና ትጠብቃለች። የወያኔም ስልት ይኸው ነው። ገና ከመጀመሪያው እኮ ንግዱንም እንደተቆጣጠረው ከላይ አመልክተናል። ዛሬ በነጻነት የሚነገድ ነጋዴ ወይም የቢዝነስ ሰው የት አለና? በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሁሉም ነገር ሊፈጽም የሚችለው ወያኔ ሲፈቅድለት ቢቻ ነው። እንዳነበብነው ልመናም ቢሆን! ሸክ አላሙዲ የወያኔን ካናቴራ ለብሶ የወጣው በጤናው ነው? ንብረቱን ለመጠበቅ እርሱ ሰውዬው የወያኔ ንብረት መሆን ነበረበት። ነገሩ ግልጽ ነው። “ገንዘብህ ባለበት እዚያ ልብህ አለ።”
ለመሆኑ ይኸ ሚሺን ወይም ተልዕኮ የተሰጣቸው እነማን ናቸው? የሚከተለውን የወያኔ ኤምባሲ ድረ-ገጽ የመልከቱ።
http://www.ethiopianembassy.org/pdf/ADM%20Award.pdf
የሚገርመው ግን የዋሁ ሰደተኛ ማትረፉን እንጂ መዘረፉን ወይም እራሱ መጠቀሚያ መሆኑን አለመገንዘቡ ነው። ንብረት ኢትዮጵያ ውስጥ ማፍሰስ የቻለ ስደተኛ፣ ለምን ውጭ አገር እንደሚኖር በመጀመሪያ ደረጃ አይገባኝም። የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አንተም አብረህ ዝረፍ የሚባለውን አባባል ተከትሎ ከወያኔ ጋራ ተባብሮ ሊመዘበራት ከሆነ፣ ያው እሱም ሌባ ነው። ከወያኔ ጋራ ካልተባበሩ ምንም ዓይነት ሥራ ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት አይቻልም። አገሩን የወደደ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ የወያኔ እሳት እራት ከሚሆን፣ በመጀመሪያ ደረጃ ቀንደኛውን የኢትዮጵያን ጠቅላይ ሥቃይ ለመገላገል ገንዘቡንም፣ ጉልበቱንም እዚያ ላይ ቢያውል የሕሊናም ዕረፍት ያገኛል፣ ከታሪክም ወቀሳ ይተርፋል።
አንዳንዶቹ ያጋጠሙኝ እበላ ባዮች፣ “ሁሉንም በፖሊቲካ ዓይን አትየው። ጽንፈኛ አትሁን።” ይሉኛል። ፖሊቲከኛም አይደለሁም። ጽንፈኛም አይደለሁም። ዳሩ ግን ወያኔ ላለፉት 19 ዓመታት አገራችንን ሲመዘብራት፣ ሕዝባችንን ቁም ስቅል ስቃዩን ሲያሳየው ዝም ብዬ የምመለከትበት አንጀት የለኝም። ሆድ አደርማ ብሆን፣ ምን ችግር አለ። መኖር እችላለሁ። ወገኔንም ሽጬ ብሆን ተንቀባርሬ መኖር እችላለሁ። እኔነቴን እስካሁን አልሸጥኩትም፣ ወደፊትም አልሸጠውም። እንዲሁ እንደሌሎቹ መሰሎቼ ዕውነቷን ተናግሬ እመሸብኝ አድራለሁ። ለጊዜው እንግሊዝ አገር ተሰደጄ ውዬ ተሰድጄ በማደር ላይ እገኛለሁ።
ወያኔ አሁን አሁን የልብ ልብ ተሰምቶት የሚሠራውን ሁሉ በግልጽ ማድረግ ጀምሯል። የአሜሪካንን ድምጽ ሬድዮ አፍኜአለሁ ብሎ እኮ በግልጽ የተናገረ፣ ትከሻው ያበጠበት ወንጀለኛ ነው። “አገር ቤት ንዋይ አፍስሰን ሕዝባችንን ልንረዳ ነው” እያላችሁ የምትሞዳሞዱት ሆዳሞችም ሆይ፣ አዙሮ ማየት አቅቶአቸው ከወያኔ ጋር የየምትሽኮረመሙ ወገኖቼ፣ ወያኔ ያዘጋጀላችሁን አሽክላ የማሳያችሁ፣ አንዱም ሀቁን ነገሬአችሁ ከምትሄዱበት ገድላማ መንገድ እንደትመለሱ፣ ካልሆነም እኔ ከደማችሁ ንጹሕ መሆኔን ልነግራችሁ ነውና፣ አንዲያው አትናደዱብኝ። የተዘጋጀላችሁን ወጥመድ፣ የሚከተለውን ድረ-ገጽ አንብባችሁ ተረዱ።
http://ethiopolitics.com/news_1/200908241000.html
በዚህ ጥሪ መሠረት እያንዳንዱ ኢትዮጵያ ውስጥ ንዋይ ያፈሰሰ፣ አሻራ መስጠት ይኖርበታል። አሻራ ከሰጠ ቁጥጥር ሥር ዋለ ማለት ነው። እናቱ፣ አባቱ፣ እህቱ፣ ወንድሙ ወይም የቅርብ ዘመዱ እንኳን ቢረሸን በሚኖርበት አገር ሰላማዊ ሰልፍ መውጣት አይችልም። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሥቃይ መለስ ዘናዊ ለጉብኝት በመጡ ቁጥር እንደ ጭራቅ እንኳን ቢጠላቸው ተሰልፎ እጅ መንሳት ሊኖርበት ነው። ወያኔ ስሙን መዝግባ ይዛለቻ። የሚኖርበትን አድራሻ ታውቃለች፣ ስልኩን ታውቃለች፣ ኢ-ሜሉን ታውቃለች፣ አሻራውን በእጅዋ ጨብጣለች። ያ ማለት ንዋዩን ኢትዮጵያ ውስጥ ያፈሰሰ ስደተኛ ከነዘር ማንዘሩ የወያኔ አገልጋይ ሆኖ እንዲቀመጥ የተደራለት ድር መሆኑን ይገንዘበው። አንዴ ወያኔ ከነጀሰህ በኋላ፣ ከሕዝቡ ካላተመህ በኋላ፣ ውኒጥ-ውኒጥ ማለት ትርፉ ለመላላጥ ብቻ ነው። በመጀመሪያ አትለከፍ። አንዴ ከተለክፍክ፣ ዘልዓለም ጠባሳው ይከተልሀል። ታርጋው ተለጥፎልህ፣ ከተገላገልከውም በኋላ “የወያኔ አሽከር” እንደተባልክ ትኖራለህ። ወገኔ ከዚህ መዓት እራስህን አድን። አይድረስባችሁ!
ባለፈው ግንቦት አንድ የወያኔ አሽከር እዚህ ሎንደን ውስጥ ሊበራል ዲሞክራትን ወክሎ ለፓርላማ ተወዳደረ። ይኸ ሰው በሄድንበት እየተከታተለን፣ የወያኔን ወንጀል በአጋለጥን ቁጥር ሽንጡን ገትሮ፣ አይኑን በጨው አጥቦ፣ ወሸት አንግቦ የሚከራከረን ሰው ነበር። ታዲያ ይኸ አጭበርባሪ በዚህ ዲሞክራሲ በሰፈነበት አገር፣ በሱው ብሶ እንግሊዝ ፓርላማ ገብቶ ለወያኔ ወኪል ሆኖ ሊያገለግል ሲጥር ደርሰንበት “አይሆንም” ብለን ተቃወምን። ታዲያ አንዳንድ የዋሆች፣ “ምን አለበት። እናንተ ማድረግ ያቃታችሁን ትልቅ ነገር እሱ ዕድሉን ቢሞክር። እናንተ ምቀኝነት ይዞአችሁ ካልሆነ ወገናችሁን እንዴት ትቃወሙታላችሁ” ብለው ሊጋፈጡን ሞከሩ። ወገናችን? እንዲህም አድርጎ ወገን አላየነም! ከዚህ በፊት ወያኔን ደግፎ ሲነታረከን የተነሳውን ፎቶራፍ እያሳየናቸው ለማሳመን ሞክረን። እርግጥ ብዙ ሰው አሳምንናል። ስንቱ ግን ያልነቃ አለ! ሰንቱ ገና ይነጫል። ስንቱ ገና ይሞሸለቃል! ስንቱ ገና ይበላል! ስንቱ ገና ይታለላል! አሁንም የሚገርመኝ፣ ይኸንን ሁሉ የማጋለጥ ሥራ እየሠራን፣ “ወያኔ ሊሞጨልፋችሁ ነው ተጥንቀቁ” እያልን ተታልሎ፣ ተታልሎ የወያኔ እሳት እራስት እየሆነ ያማያልቅ ሕዝብ እንደ አሸን መፍላቱ ነው። ተስፋ የማትቆርጠዋ የወያኔ ሸረሪት ሳትቦዝን ነጋ ጠባ ድሯን አድርታ ትጠብቀናለች። ልንበላ ገበተን እንበላ ጎብዝ! ተደግሞብናል ልበል? ጋግርቱ ይለቀን እንደሆን እሲቲ ወደ ፈጣሪ ኢግዚዖ እንበል! ኢግዞዖ!
Although I didn't really understand Amharic .But anyway,welcome to my blog.
ReplyDeletehttp://b2322858.blogspot.com/