Thursday 9 September 2010

ዘመነ ወያኔ - ዘመነ ጨለማ

ከወንድሙ መኰንን፣ በኪንግሀም፣ ጷጉሜን 4 ቀን 2002 ዓ. ም

ወያኔ ኢትዮጵያን ከዘመነ መሳፍንት ወደ ከፋው ዘመነ ዘረኝነት ከወረወራት 19 ዓመት አልፎት ግንቦት ሲመጣ 20ኛውን ሊደፍን እየግሠገሠ ነው። አይ ግንቦት! የማታመጣው ተስቦና ኮሌራ የለ መቸም! ግንቦት 1983 ደኅና አልተገበረም መሰል እንዲህ የከፋብን። በእነዚህ 19 አመታት የደረሰብን እርግማን ጣሊያን ሲወረንም አልደረሰብንም። አንድ የውስጥ መረብ ገጣሚ (internet) ኢትዮጵያዊ አንዴ እንዲህ ብሎ ሲቀኝ አንበብኩ።

እንጀራ በመሶብ፣ ይቀርብ ነበረ
አባሽ በሳህን፣ ትበላው ጀመረ።

ዘመነ ወያኔ ከታሪካዊ ክፋት ሁሉ የከፋ የክፉ-ክፉ ዘመን ነው። የነጻነት ብርሀን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የደበዘዘበት ዘመን ነው። የአገሪቱ ሉዓላዊነት ከመቼውም በበለጠ አደጋ ላይ የወደቀበት ዘመን ነው። ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የድኅነት አርንቋ ውስጥ የተዘፈቀበት፣ ከሥቃዩ ማምለጫ ጠፍቶት የሚዋዥቅበት፣ አበሳውን ያየበት፣ ተስፋ የቆረጠበት ዘመን ነው። ሕዝባችን በደዌ የተመረዘበት፣ ሕይወት የረከሰበት ዘመን ነው። የወባ ማጥፊያ ድርጅትን፣ ልክ እንደ የአዲስ አበባው የሲሚንቶ ፋብርካ፣ ተነቅሎ ሲዘረፍ፣ የወባ ትንኝ እንኳን ነፍስ እንደገና ዘርታ በአቅሟ ሕዝባችንን እየረፈረፍቸው ነው። ዘመኑ፣ ዘመነ አበሳ ነው። የወያኔ ዘመን “ዘመነ ጨለማ” ነው። ይኸን “አሌ” ብሎ የሚከራከር አዳሜ ካጋጠማችሁ፣ ወይ ከአሰቃዮቹ ፍርፋሪ ለቀማ የደለበ ቅልብ ነው፣ ካልሆነ በጤናው አይደለምና አማኑኤል ውሰዱት። ሆዱ ልቦናውን ያልደፈነበት፣ ጥቅም የሒሊና ዓይኑን ያላሳወረበት ሁሉ ይኸንን በግልጽ እያየ በቁጭት ቆሽቱ ይደብናል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሥቃይ መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ትልቅ የልማት ግብ እንዳስቆጠሩ ያለምንም ሀፍርት ያወሩናል። አንድ ጊዜ ኢትዮጵያ ከዓለም አምስተኛ ፈጣን ዕድገት አስመዘገበች ብለው በየከተማው በገጠገጡአቸው ሙቲቻ (zombie) ኤምባሲዎቻቸው በኩል ውሸታቸውን ረጩት ። ሰሞኑን ሀፍርተ-ቢሱ ዋሾ እንዲሁ ኢትዮጵያ ከ10% በላይ ዕድገት እንዳስመዘገበች በመወትወት አድረቁን። ሀቁ ግን፡ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ጠበብት፣ ኢትዮጵያ ከኒዠር ቀጥላ ሁለተኛዋ የመጨረሻ ድኃ መሆኗን የሚያመለክት የምርምር ውጤት ዓለምን አስነብበዋል። ሶማሌ እንኳን ሳትቀር ዘርራን አልፋናለች። 6ኛ ደረጃ ላይ ናት። ጠቅላይ ስቃያችን በ5 ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በቴሌፎን እና በኢንተርቴት (የውስጥ መረብ) ከአገሪቱን ማዳረስ አልፈው፣ ወደ ውጪም (export) እንዲሚልኩ ተመጻድቀውብን ነበር። ሰሞኑን ዓለም አቀፍ የውስጥ መረብ ተጠቃሚዎች ማኅበር (International Telecommunications Union (ITU)) መረጃ መሠረት፣ ኢትዮጵያ ከዓለም በኢንተርኔት ስርጭት ከመጨረሻ ሁለተኛዋ ፣ ብሮድ ባንድ የተባለውን ተክኖሎጂ ለማግኘት እጅና እገር የምታስክፍል ናት በማለት እንዴት ወድ እንደሆነ አረጋግጠዋል። ጠቅላይ ስቃያችን እንዳሉት እንኳን አገሩቱን በኢንተርነት ቴክኖሎጂ ማንበሽበሽና፣ ሌሎቹ የፈጥሩትንም የውስጥ መረብ ሕዝባችን እንዳይጠቅም አገደውታል (block አድርገዋል)። ኢቲዮ ሜዲያ፣ ኢትዮሜዲያ ፎረም፣ አዲስ ቮይስ፣ አባይ ሜዲያ፣ ኢትዮጵያን ሪቪው የተባሉ ድረ-ገጾች ኢትዮጵያ ውስጥ አይነበቡም። ኤዲያ! ምናለ እኚህ ግብዝ ሰው ባይመጻደቁብን!

የመለስ ቡድን አዲስ አባባን ከተቆጣጠራት ጊዜ ጀምሮ ድኅነት ድባቡን በአገሪቱ ዘርግቶባታል። ሕዝባችን ከምን ጊዜውም የበለጠ ተራቧል፣ ተጠማቷል፣ ታረዟል፣ ደኽይቷል! እርስብርስ አናቁረውት አነካክሰውታል፣ አበጣብጠውታል። ሰላሙን ነስተውታል። ሕዝባችንን ከፋፍለውት እያፋጁት ነው። አጸደ አምልኮዎቻችን ሳይቀሩ፣ በዘረኞች ካድሬዎች ቁጥጥር ሥር ውለዋል። አገራችን ላይ ዘረኞች ነገሡ። ከሀዲዎች ፈነጩባት። ብሔራዊ ውርደትን አከናነቧት። ሁለቱን ወደቦችዋን ዘጉባት። ግዛቶችዋን ከአንዷ አካል ቆርሰው ያልነበረ አገር ሲፈጥሩ፣ የተቀረውን ለጎረቤት አገር ሸጠውባታል። ሱዳን ለከሀዲዎች ለዋለችላቸው ውለታ ለም መሬታችንን በችሮታ መልክ ተለግሷታል። ምን ይደረግ! ከሀዲዎች አዲስ አበባን ሲቆጣጠሯት እኛ ቤት ለቅሶ ሲሆን፣ ካርቱም ላይ አሸሻ ገዳሜ አልነበር የተደለቀው! ሱዳኖች ይኸ እንደሚሆን ገና ከጠዋቱ ስለተረዱ መጨፍር ይነሳቸው? ወያኔዎች የአገሪቱን ለም የእርሻ መሬቶች ሸንሽነው፣ ባለርስቶቹን ከቄያቸው መንግለው ለባዕድ ቱጃሮች ቸበችበውባታል። ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር በታሪኳ ዘመን ሁሉ የተዋደቀች ግብጽ እንኳን ሳትቀር፣ ባለ ሰፊ ቀላድ፣ ባለ ብዙ ጋሻ፣ ባለ ርስት ሆነለች። እናት ኢትዮጵያ ለጠላቶቿ ተመቻችታ፣ ደረቷን ለሞት እንደትገልጥ ተገዳለች! ምነው ታዲያ ይኸ ሁሉ ግፍ ሲፈጸምበት ጀግናውና ቆራጡ ሕዝባችን ግፍን ለመከላከል ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲህ ወኔ ራቀው? ነገሩ ወዲህ ነው። ዘዴው በጣም ረቂቅ ነው። አገሪቱን እንዴት አድርገው፡ እንደጠፈሩአት ምርጫ 2002 አካባቢ የተሸረብቱን ተንኰሎች ብቻ በመዳሰሰ መረዳት ይቻላል።

ቁጥጥር በአገር ቤት

ወያኔዎች ሁለት የመቆጣጠሪያ መሣሪያ አላቸው። ፍርንጆቹ አንዱን ካሮት፣ ሌላውን ዱላ ይሉታሉ። ከሆነ በጥቅማ ጥቅም ማባበል፣ ካልሆን በመጠለዝ ልክ ማስገባት!

ወያኔዎች፣ የአገራችንን ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ ዘርፈው ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ እንዲሁ የሕዝባችንን ሕልውና ተቆጣጥረውታል። ኑሮውን፣ ውሎውን አዳሩን ሙሉ በሙሉ አንቀው ይዘውታል። ድምጽ እንዳያሰማ ጎሮሮውን አንቀውታል። እንዳይሰማ ጆሮውን ድፍነውበታል። አንድ ሰሞን ሬዲዮአቸውን የሚያዳምጥ አልነበረም። የአሜሪካና የጀርመን ድምጽ ሬዶዮዎችን ብቻ ነበር የሚደመጡት። የቻለ “ዲሽ” የሚባል የሳቴላይት ጠላፊ ሳህን ዘርግቶ የውጭ ቴለቪዥን ነበር የሚያየው። በዚህ የተነሳ፣ የወያኔ ጋዜጠኛ የጠነባ መርሀ ግብራቸው ማየት ሕዝቡ እንደትጸየፈባቸውው ገብቶት፣ ዜና ሊያነብ ብቅ ሲል፣ “እንደምን አመሻችሁ፣ ዲሽ የሌላችሁ” ይላል እየተባለ ተቀልዶ ነበር። ዛሬ ያ ቀልድ ቀርቷል። በአገር ቤት፣ ነጻ ሬዲዮ ድሮም አልተፈጠርም ! ነጻ ቴሌቪዢንማ ከቶ ማን አስቦት! ነጻ ጋዜጣን ድራሹን አጥፍተውታል! የተመጣጠን ዕውነተኛ መረጃ ከውጭ ለሕዝባችን እንዳይደርሰው፣ ቪኦኤ (የአሜሪካን ድምጽ ሬዲዮ) ዛሬ የለ! ጀርመን ድምጽ ዛሬ የለ! ኢሳት ቴሌቪዥንማ፣ ሳተላየት እንዴት ማፈን እንደሚቻል የአፋኝ ተክኖሎጂ መለማመጃ ሁኗል። “የቻይናን” የፍቅር ዕድሜ ያሳጥርልንና በአጭሩ ተሰምቶ በማይታወቅ ቴክኖሎጂ ከአየር ላይ ቀልበውታል። ይኸ ማለት ሕዝባችን መጮህ ቀርቶ ከውጭ የምንጮለትን እንኳን እንዳይሰማ ምንም ዓይነት መረጃ እንዳይደርሰው ቀፍድደው ይዘውታል። እእንዳይዘዋውር፣ እግሮችን ጠፍረው አስረውታል። በአገሩ እንደድሮው ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ አርሶ አምርቶ፣ ነግዶ አትርፎ እንዳይበላ ከልክለውታል።
ሕዝቡን በወረዳና በቀበሌ ከፋፍለው ከመቆጣጠር አልፈው፣ ጎጥና ጋሬ በመባል ሥርዓት (system) ታች ወርደው እስከ አምስት ሰው ድረስ የሚቆጣጠሩበት ሕዋስ ፈጥረዋል። በዚህ ክትትል መሠረት፣ ማንም ዜጋ፣ ለምሳሌ ገብሬ፣ ከተወሰነለት ሁኔታ የማፈንገጥ ምልክት ካሳየ፣ ለዘር ብድር ከባንክ አያገኝም፣ ማዳበሪያ በብድር አይሸጥለትም፣ ከውጭ በልመና የመጣውን የዕርዳታ እህል እንኳን አያገኝም። ማንኛውም ዜጋ ጥቅም ማገኘት ከፈለገ፣ የአባልነት ፎርም መሞላት አለበት።

ይኸን ፎርም ያልሞላ ተማሪ፣ ዩኒቨርሰቲ የመግባት ዕድል የለውም። ይኸን ፎርም ያለሞላ ተመራቂ የሥራ ዕድል የለውም። ይኸን ፎርም ጎጡና ጋሬው በሚያዘው መሰረት ያልሞላ ዜጋ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕይወት የለውም። ያለው ምርጫ መሰደድ ነው። ለዚህ ነው ወጣቶቻችንን በርሀ የሚበላቸው። ባሕር የሚያሰምጣቸው። የሶማሌ መንገድ መሪዎች የሚያርዱአቸው። አንድ ሰው ይኸን ፎርም ሞላ ማለት ደግሞ፣ እሱም እንደነሱ ወየነ ማለት ነው። ምርጫ 2002ን በ99.6% አሸነፍን የሚሉት አንዱ ዜዴአቸው እንዲህ ዓይነቱን ፎርም በማስሞላት ነበር። እዚህ ቦታ ስለሚያጠብብን ነው እንጂ ሌላም ለምርጫው የተጠቀሙበት ፎርም አለ። እነሱ ምርጫውን እጃቸው አስገብተው ያበቁት ገና በ2000 ዓ ም የክልል ምርጫ ብቻቸውን ሩጠው ብቻቸው ያሸነፉ ጊዜ ነበር። “ኢህአዴግን እመርጣለሁ” የሚል ፎርም እያንዳንዱን ተራ ዜጋ አስፈርመው ይዘው 2002ን ይጠባበቁ ነበር። አልፈርምም የሚል ዜጋ ያው ከተቃዋሚው ጎራ ተፈርጆ ይቀመጣል። ተወዳዳሪ ከሆንም አርፎ እንዲቀመጥ በጋሬው በኵል መልዕክት ይደርሰውል፣ እምቢ ካለም እስከመገደል ይደርሳል። ሲገደል ደግሞ ታፔላ ይለጠፍለታል። ለምሳሌ የደቡቧን ተወዳዳሪ ባለትዳር ወይዘሮ ከገደሏት በኋላ፣ የድብቅ ፍቅረኛዋ እንደገደላት በቪኦኤ ሳይሰቀጥጣቸው ተናግረዋል። የኦብኮውን ተወዳዳሪ ከገደሉ በኋላ “አባላችን ነበረ። ኮሌራ ገደለው” ብለው ዐይናቸውን በጨው አጥበው ድርቅ ብለው ዋሽተውናል። ኮሌራ ማለታቸውስ ባልከፋ፣ ከነሱ የባሰ ኮሌራ የለምና፣ አባላችን ነበር ማለታቸው ግን አብጋኝ ውሸት ነበር። ይኸ እንግዲህ ዱላው መሆኑ ነው።

ምርጫ 2002 ሲደርስ ወያኔ በሚያስገርም ሁኔታ ገንዘብ ይረጭ ነበር። ገንዘቡን እንደ አቧራ አብንነውታል። የሚገርመው ነገር፣ በየደቦው (በየወንፈሉ)፣ በየዕድሩ፣ በየዕቁቡ፣ በየለቅሶው፣ በየገቢያው እየተዘዋወሩ፣ የሰውን የግል መርሀግብር ወይም ዝግጀት (programme) ሳይስፈቅዱ፣ እየረገጡ፣ “ኢሕአዴግን ምረጡ” እያሉ ከመደስኮርም አልፈው፣ ብር፣ ካናቴራ፣ ሹራብ እና ሰዓት ድረስ ለየአንዳንዱ ለተገኘ ሕዝብ በስጦታ መልክ ችረውታል።

በጄ የገባው ሰዓት የተቸረው በአንድ ሠርግ ላይ ነው። ሶስት መቶ ዕድምተኞችና 5 ያልታጋበዙ የወያኔ በር ሰባሪዎች (gate crushers) ነበሩ:: እንግዶቹ እየበሉና እየጠጡ እየተዝናኑ፣ ሙዚቀኞቹ እየዘፈኑ፣ ሚዜዎቹ እስክስታ እየመቱ ሳለ፣ ባለጌዎቹ የወያኔ ካድሬዎች በቀጥታ ወደ መድረኩ ወጥተው ድምጽ ማጉያውን ነጥቀው ተቆጣጠሩት። ነገሩ በጣም የሚያናድድ ቢሆንም፣ የሙሽርቹ ወላጆችም ሆኑ፣ ሚዜዎች፣ ወይም እድምተኛው፣ ባለጊዜዎች መሆናቸውን እንደተረዱ ጸጥ ብሎ ከማዳመጥ ባሻገር አንዳችም ምርጫ አልነበራቸውም። እጅ እጅ የሚለውን የቆረፈደ የ“ኢሕአዴግ” መጪው የ5 ዓመት መመሪያ (Policy) ያሉታን አብራሩ። በደሞክራሲ ዕደገት፣ በኢኮኖሚ ምጥቀት፣ በሳይንስ ብስለት፣ በቴክኖሎጂ እምርታ፣ ተቅደጀ የሚሉቱን ወሬ ዘበዘቡ። እድምተኛው ችክ እያለው ሰማቸው። በኋላም ላይ፣ ይኸንን ሰዓት አውጥተው ለያንዳኑ ዕድምተኛ በተኑት። ሳዓቱን ትኵር ብላችሁ ብታዩት፣ ወርቃማ ነው። ከመክበዱ በስተቀር በጥሩ እጅ የተሰራ ነው። ወርቃማ ወለሉ ላይ (dashboard) “መጪው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ብሩሕ ነው” የሚል ዐርፍተ ነገር ተጽፎበታል። ድንቄም! እንዲህ አድርጎ ብሩህ ጊዜ ሰመጣ አይተንም ሰምተንም አናውቅም! ለማንኛውም፣ ዕድምተኛው ወርቁን ተቀብሎ “ኢሕአዴግን እመርጣለሁ” ብሎ ፈርሞ ሸኛቸው። ግልግል!
ምርጫ 2002 እንግዲህ በዝህ ሁኔታ ነበር 99.6% ድል ለወያኔ ያመቻቸው። ይኽቺ ናት ዲሞክራሲ! ይኽቺ ናት ጨዋታ! መጪው አምስት ዓመትም ሆነ፣ ከእንግዲህ ወዲያ ወያኔ ሥልጣን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚቆይባት ግዜ ዘመንም ይሁን አመታት፣ ወራትም ይሁኑ ሳምንታት፣ ቀናትም ይሁኑ ሰዓታት፣ ዲቂቃም ይሁን ሰኮንድ፣ ለሕዝባችን የድቅድቅ የጨለማ ዘመን ነው። የጨላማ ዘመንነቱ ድግሞ፣ የብሒል ብቻ ሳይሆን የጥሬ ቃሉም ጭምር ነው። አዲስ አበባ ኢሌክትርክ አጥታ በወያኔ ዘመን ጨላማ ውስጥ ተዱላ አበሳዋን እየገፋች አይደል!

ውጭ-አገር ኗሪውን ለመቆጣጠር የተየቀሰ ዘዴ

ከዚህ በፊት ብዙ ብለናል። አዲስ ነገር ስላለ አሁንም እንላለን። ወያኔ የአገር ቤቱን ሕዝብ ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮ አብቅቶለታል። አሁን አንደኛውን ፊቱን ወደ ውጭ አገር አዙሯል። በ2006 የዘረጋውን 52 ገጽ መመሪያ አሁን አሻሽሎት እንደድሮው አምባሳደሮቹ የሚመሩት ሳይሆን በቀጥታ ከአዲስ አበባ “በደኅንነት እና በስለላ መሥሪያ ቤት” የሚመራ ቡድን ተቋቁመዋል። ዕቅዱንም ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ አውሏል።
ሥራቸው መረጃ መሰብሰብ ብቻ አይደለም። ከዚያ የላቀ ነው። ብዙ ሃላፊነት ተጥሎበታል። አምባሳደሩ አፍንጫው ሥር የሚደረገውን እንዲህ ዓይነቱን ሥራ ጨርሶ የማወቅ መብት የለውም። የስደተኞችን እንቅስቃሴ ከመከታተል ባሻገር፣ በተለያየ የቁጥጥር ዘዴ ፈልስፎ ደንበኛ መመሪያ ወጥቶ መጠቀም ጀምረዋል። ልዩ ስውር ካሜራ ይዘው በተልያዩ የሕብረተሰቡ ስብሰባ ላይ በመገኘት ይቀዳሉ። በሕብረተሰብ ማኅበራት አመራር ውስጥ የራሳቸውን ሰዎች አሰርገው ማስግባት ይሞክራሉ።

ባለፈው ዓመት ከተጀመሩት ዜዴዎች አንዱ፣ የስደተኛውን ኪስ የሚያራቁቱበትን ብልሀት መፍጠር ነበር። ስደተኛው አገር ቤት ንዋይ እንዲያፈስ የሚደረገው ጥረት በተለያየ መንገድ ይቀጥላል። አሁን ገንዘብ በውጭ ምንዛሪ አገር ቤት ባንኮች ውስጥ ማስቀመጥ እንደሚቻል፣ ለማግባባት ፎርሙን ካድሬዎቹ እየበተኑት ደርሰንበት ከዚህ በፊት ኅብረተሰባችንን አስጠንቅቀናል ። አገር ቤት ሂዶ መኖሪያ ቤቱን እንዲሠራ የሚሰጠው የመሬት ምሪት ድልላ አሁንም በተሻሻለ መንገድ ይቀጥላል። መሬት እመራለሁ ብሎ መረባቸው ውስጥ ጥልቅ ይልላቸዋል። ይኸንን የስለላ መረብ እንዲመራ ከኢትዮጵያ ታዞ የመጣ በለሥጣን ወይንም በሚኒስተር ደረጃ፣ ካውንስለር ተብሎ በየአገሩ ትሹሟል። ካልሆነም በአንደኛ ጸሐፊንት ደርጃ ይቀመጣል። ለምሳሌ በሎንደን የሚከተሉትን ሦስት ስሞች ልብ ብላችሁ አስተውሉ። ሰላዩን እናንተው አውጥታችሁ አውርዳችሁ አሰላስላችሁ ድረሱበት። (ስሙም ሰላይ ነኝ እያለ ይናገራል።)

ብርሀኑ ከበደ - አምባሳደርና (ለስሙ) ባለሙሉ ሥልጣን (His Excellency Ambassador Berhanu Kebede)
ሀብቶም አብራሀ - ሚኒስቴር ካውንስለር (እ-እ-እ-ም! ይቅርታ ጉሮሮየን ከርክሮኝ ነው) (Habtom Abraha - Minister Counsellor)
ተስፋየ ይታይኽ - አንደኛ ጸሐፊ (Tesfaye Yetayeh - 1st Secretary - Community Affairs)

ለመሆኑ የኮምዩኒቲ ጉዳይ ተከታታዩ የትኛውን ኮሙኒቲ ጉዳይ ሊያስፈጽም ነው እዚያ የተጎለተው? ለመሆኑ ከራሱ ኮሙዩኒቲ ወይም ማኅበርሰብ ጋር የተጣላ ኤምባሲ፣ ምን ዓይነት ኮሙይኒቲ አለኝ ብሎ ያወራል? ለማንኛውም ምለመላው ቀጥሏል። ዓላማቸው ብዙ ነው። ዋናው ንጹህ ዜጋ በመምሰል ኢትዮጵያዊ የሆነውን ተቋም ሠርገው በመግባት ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ነው። እዚህ ላይ ቤተክርስቲያናችንም ዒላማቸው ውስጥ አለችበት። የኢትዮጵያ ማኅበረሰባት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ዒላማ ውስጥ ናቸው። እንግዲህ ፍርጀ ብዙውን በጥቅሉ በሁለት መክፈል እንችላለን። እንሱም ማደራጀትና መንጠቅ ናቸው። ማደራጀቱን ቀጥለውበታል። ማደራጀትን በተመለከተ ወያኔ የሚመራው “የኢትዮጵያ ማኅበረስብ” በየኤምባሰው ቅጥር ገቢ ይቋቋማል። በሎንደን፣ ለምሳሌ ሆዳደር “ያለው” የሚመራው “ይሁንታ” በመባል የሚታወቀው ዓይነት ማለት ነው። የየብሔረሰቡ የልማት ማኅበር እየተባለም የስለላ መዋቀሩ በተለየ መልኩ አደረጅቶ ሊቆጣጠረው እየሞከረ ነው። ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ሜይ 29 ቀን 2010 በሎንደን “አማራ ልማት ማኅበር ” ብለው የጠሩት ነው። መልማዮቹ ወይ ለዚሁ ጉዳይ ከአዲስ አበባ፣ አዲስ የተሰደዱ አስመሳይ ስደተኞች ሊሆኑ ይችላሉ፣ ካልሆነም ነባር የባሰባቸው ሆዳሞች አሉበት። ወጣቱን “ስፖርት ከበብ አቋቋመንልሀል፣ እናደራጅህ” በማለት ይቀርቡታል። ምግብ፣ ለስላሳ መጠጥ፣ አንዳንዴም ሙዚቃና ዳንኪራ በነጻ ያቀርቡለታል። ዋናው ነገር፣ የወያኔ አምባሻ ምልክት ባንዲራ ያለበት ካናቴራ ልብስ/ልብሺ ማለት ደረጃ ላይ ሲደርሱ ይነቃባቸዋል። ባለንግድ ድርቶችም፣ በተለያየ ጥቅማ ጥቅም ሊያዙ ዕቅድ ውስጥ ናቸው። ውጭ ለምንኖረው ለያንዳንዳችን አንዳንድ ዕቅድ ነድፈውልናል።

በተለያየ ምክንያት ኤምባሲ የረገጠ ማንኛውም ሰው አድራሻውን፣ ስልክ ቁጥሩ፣ ኢሜሉ ይወሰዳል። ያ ዳታ ቤዝ (database) ውስጥ ይገባል። ወያኔ ያንን መረጃ እንደሁኔታው ጥቅም ላይ ያውለዋል። ለምሳሌ፣ ስማችሁን፣ አድራሻችሁን እና ኢሜላችሁን ለወያኔ የሰጣችሁ ካላችሁ እንደሚከተለው ዓይነት መልዕክት ይደርሳችሁአል። ቀጥሎ የምታነቡት ዕውነተኛ ከወያኔ የደረሰ መልዕክት ነው።

Date: Jul 14, 2010 10:47 AM
Subject: Opportunities in Ethiopia
To: " >
Representatives from capacity building minister will be coming to US in less than a month.
They will be looking for skillful and professional Ethiopians willing to work in Ethiopia.
Specific areas of interest include Agriculture, Medicine, IT, Law, Finance, and Economics.

I am planning to set up a meeting with these representatives. If you are interested, please fill out the below information and send it to me.

Name::__________________________________________________________
Residence City/Country:____________________________________________
Phone: __________________________________________________________
E-mail: __________________________________________________________
Citizenship: ______________________________________________________
Education: ______________________________________________________
Qualification (Knowledge/Skill/Ability): _______________________________
Specialization: ___________________________________________________
Experience: _____________________________________________________
Desired Position/Service: __________________________________________
Availability Type: ________________________________________________
(permanent employment, temporary/term employment, consulting, volunteer, etc..)
Availability Period: _______________________________________________
Desired Location: ________________________________________________
Desired Salary/Compensation: ______________________________________
Desired Benefit: _________________________________________________
Supplemental Documents (Resume, CV, etc..): ________________________
Additional Information: __________________________________________
________________________________________________________________
ዕውነት ኤክስፐርት ፈለገው እንዳይመስላችሁ። ኢትዮጵያ በሥራ አጦች ተጨናንቃለች። ዓላማው “አገሬን እረዳለሁ” ብላችሁ ስትቀርቡት፣ ሕይወታችሁን ቁጥጥር ሥር ሊያውላችሁ ነው። ቀጥሎ የጠነባ ፖሊቲካውን ሳትወዱ በግዱ ሊግታችሁ!
ሌላው ሥራ የሚከተለው ነው። ጠቅላይ ሥቃይ መለስ ዜናዊ ውጭ አገር በጎበኙ ቁጥር፣ ስደተኛው ሰላማዊ ሰልፍ እየወጣ ቁም ስቅላቸውን ሲያሳያቸው ኑሯል። ያ መቆም አለበት። ለምሳሌ ጂ-20 በተባለው ስብስባ ላይ ሊገኙ ሎንዶን ሲመጡ ከአውሮፓ ተሰባስበው በመጡት ኢትዮጵያውያን ቆሌአቸው ተገፎ የርእስ በሔሮች መሳለቂያ መሆናቸው አናዶአቸዋል። መኪና ውስጥ ገብተው የተተኮሶባት ድኩላ መስለው ተደናግጠው ሹክክ ሲሉ አንዱ ወንድማችን ፎት አንስቶአቸው እነሆ እስከዛሬ ምስላቸው እንደጉድ፣ ለጉድ ይታያል። መሬት ያደሉት፣ የሁለተኛ ዜግነት መብት ልዩ ምልክት የሆነውን የኢትዮጵያዊነት ካርድ በ£400 ያስገዙአቸው ስደተኞች እንዳሸን በፈሉባት ሎንዶን ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ውርደት ለመመከት ብርሀኑ ከበደ ደጋፊዎቻችውን ባለማሰማራታቸው ቁጣ ብጤ እንዳወረዱባቸው ሰምተናል። ዴንማርክም፣ እንዲሁ ዘምተንባቸው ነበር። ኦቶዋም ተመሳሳይ ዕድል ገጥሞአቸዋል። ዋሽንገንም አልቀረላቸውም። ታዲያ ለዚህ ዓይነቱ ተግባር አንድ ነገር መደረግ እንዳለበት በማምን በየአገሩ ያንን የሚከታተል ግብረ ሀይል ተቋቅሟል። ሥራም ጀምሯል። መፍትሔው ቀላል ነው። የወያኔ የድጋፍ ኮሚቴ በየአገሩ በገንዘብም ሆነ ባገኙት ዕድል አቋቁመው በየጊዜው አጽፋ ሰላማዊ ሰልፍ እያደረጉ “ኢሕአዴግ ለዘልዓለም የኑር” የሚሉ በቀቀኖችን (parrots) መፍጠር ነው። ይኸንን ኦታዋ ካናዳ ላይ ለማድረግ ሞክረው ነበር። አሁን በነሐሴ ሆድ-አደር ጋዜጠኛ ንጉሤ ወ/ማርያምና፣ ግንባሩ ላይ ብር ከተለጠፉለት መላጣውን “ጸጉሩ ሞላ ያለ” ብሎ ከማሞገስ ያማይመለስ ሒሊና ቢስ ዘፋኝ ሰሎሞን ተካልኝ ጋር ያዘጋጁት የወያኔ ድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ የዚያ እንቅስቃሴ አንዱ አካል መሆኑ ነው ። ዓባይን አስታከው “ከመለስ ጋር ወደፊት! ወያኔ የልጅ ልጅህን ይገዛል።” ብለው ላንቃቸው እስኪደርቅ ጩኸው ተመለሱ። ሰሎሞን ተከልኝም “ቅንድቡ ያማረው” የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሥቃይ “ለዘልዓለም ይግዛን” ብሎ ዘፍነላቸው። ምን ችግር አለው፣ አላሙድ የተባለው ቱጃር ትንሽ ቀርሺ ድግሞ ቢለጥፍለት፣ ድንክየውን ጠቅላይ ሥቃይ “መለሎው መለስ” ብሎ ቢዘፍን ሊደንቀን አይችልም።

የኢትዮጵያ ፈርስቱ (Ethiopia First postmaster) ብንያም፣ “ለጋዜጠኛ” ንጉሤ ወ/ማርያም ደርሶ ያነበበውን የፍቅር ደብዳቤ ሰምታችሁአል። እንዲያው ካልሰማችሁ፣ በሞቴ በግርጌው በተጠቀሰው አድራሽ ጠንቁላችሁ ስሙት ። እኔ መቸም ኢትዮጵያ ውስጥ የወንድ ለወንድ ፍቅር ግሎ እንዲህ አደባባይ ሲወጣ ገና ማየቴ ነው። ሴትና ወንዱም ቢሆን በድብቅ ነበር።

ወይ ፍቅር እያለ ሰው ያወካል
ግን አንድም ሰው አላየው ቁሞ በአካል

በሎ ዘፈነ መሀሙድ! ብንያም ንጉሤን እንዴት መጥራት እንዳለበት ግራ ተጋብቶ አንዴ ንጉሥዬ እያለ ሊያቆላምጠው (ንጉሤ ድግሞ ለማቆአላመጥ አያመች ጣጣ) ሲሞክር፣ በሌላ ጊዜ ንግስቲየ እያለ ፍቅሩን ለገልጥለት ሲሞክር ለሰማ “ይኸስ ብሶበታል! ጾታም መለየት አቅቶታል” ያሰኛል። ብንያም ከመጀመሪያም የወያኔ ቫይረስ ተሸካሚ ሆኖ አሁን እንደአላሙዲ የባነነበት ዜጋ ሊሆን ይችላል። ንጉሤ ወልደማርያም ግን፣ ለሆዱ ያደረ ሆዳም ነው። እንደሰማነው ከሆነ፣ ወያኔ ገርፎት ሲያባርረው፣ ዘረኞቹን ይኮነነን እንደነበረ ጓደኞቹ ይነግሩናል። ዛሬ 180% ድግሬ ዙሮ የወያኔ አንድ ቁጥር አፈቀላጤ ያደረገው ያው ከርሱ መሆን አለበት። ቆይ ብቻ! ወያኔ የንጉሤ ወልደማሪያምን ጎተራ ሆድ ከሞላ፣ የወያኔ ሰልፍ ድጋፍ ቢያዘጋጅ፣ ምን ያስደንቃል? ብዙ ንጉሤዎች በየከተማው ሞልተዋል። እንዲሁ እንደጨለመብን የምንቀር መስሎአቸዋል ይዘባነኑብናል። አይነጋ መስሏቸዋል።

እንዲህ ዳምኖ ዳምኖ የዘነበ እንደሆን
የጎርፉ መሄጃ በየት በኩል ይሆን
እንዲ ጢሶ ጢሶ የነደደ እንደሆን
ያመዱ ማፍሰሻ በየት በኵል ይሆን?

ስደተኛው ጓዴ! ይኽች ክፉ ዘመን እንደከፋችብን አትቀርም፡ ታልፋለች! በነዚህ የወያኔ ልክፍተኞች በሰደት በምትኖርበት አገር ተሳስተህ ትቀርባቸውና፣ ዋ! በወያኔ ልክፍት እንዳትለከፍ ሁልጊዜ እራስህን ጠብቅ። እስካሁን መድኀኒት አልተገኘለትም። አንድ ቀን ለነዚህ ኃጢአተኞች የሚመጣው መዐት አንተንም ይዞ እንዳይነጉድ አንተነትህን አድን። ዘመነ ጨለማን በዘዴ ዕለፈው! በተረፈ እግዚአብሐር፣ የኢትዮጵያ አምላክ፣ ሁላችንንም በያለንበት ጠብቆን ብርሀኑን ያብራልን።

No comments:

Post a Comment