Monday 12 March 2012

የአንዱአለም አራጌ ቃል - ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት - ፍትህ ጋዜጣ

አንዱአለም አራጌ ቃል - ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት - ፍትህ ጋዜጣ

  በዚህ በቃሊቲ ወህኒ ቤት በእኔ ላይ የደረሰውን የግድያ ሙከራ አስመልክቶ በተከበረው ጋዜጣዎ መዘገቡን ሰማሁ፡፡ በቅድሚያ ጋዜጣዎ እውነቱን ለማሳወቅ ስለአደረገችው ጥረት ከልብ እንዳመሰግን እንዲፈቀድልኝ እጠይቃለሁ፡፡ እነሆም ፍቃድ ከጠየቁኝ ዘንዳ ምስጋናዬን አቀርባለሁ!
በዚህ ለኑሮም ሆነ ለማሰብ ፍፁም በማይመች ሁኔታ ለዛውም ከተፈፀመብኝ አሰቃቂ ድብደባ ሳላገግም ብዕርና ወረቀት እንዳገናኝ የጐተጐተኝን ጉዳይ ከዚህ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡ ባለሁበት ወህኒ ቤት ጋዜጦችን ቀርቶ መፃህፍትንም ማስገባት ባለመቻሌ እናንተ የምትኖሩበት ‹‹ዓለም›› ከሚያቀርበው የመረጃ ማዕድ መቋደስ አልችልም፡፡ ሆኖም እንደሌላው እስረኛ ሁሉ በህገ-መንግስቱ መሰረት እንዳልጠየቅ አሳሪዎቼ ቢከለክሉም እንዲጠይቁኝ ከተፈቀደላቸው ሁለትና ሶስት ቅርብ የቤተሰብ አባሎች አልፎ አልፎ ወሬ መቃመሴ ግን አልቀረም፡፡ እናም ይህን በመሰለው ሁኔታ ውስጥ ወህኒ ቤቱ በእኔ የደረሰውን የግድያ ሙከራ አስመልክቶ የሰጠውን ምላሽ ይዘት በመስማቴ ቀደም ሲል በጉዳዩ ላይ የመናገር ፍላጐት ባይኖረኝም በቀጥታና በዝርዝር ማስረዳት እንደሚገባኝ ከራሴ ጋር ስምምነት ላይ ደረስኩ፡፡
ስለሆነም አሁን ካለሁበት የእስር ሁኔታና ከገጠመኝ የጤና መቃወስ አንፃር ሃሳቤን በወጉ ለማደራጀት መቸገሬን ግንዛቤ ውስጥ አስገብተው ሃሳቤን በሚከተለው አኳኋን እንዳቀርብ መልካም ፍቃድዎ እንዲሆን በአክብሮት በድጋሚ ጠይቄ ወደ ዋናው ጉዳይ እገባለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብና አለም እንደሚያውቀው ለሁለት ወራት ገደማ በማዕከላዊ እስር ቤት ከቆየው በኋላ ወደ ቃሊቲ ወህኒ ቤት መዛወሬ ይታወሳል፡፡ ቃሊቲም እንደገባው ከሌሎች በአንድ መዝገብ ከተከሰስን ሰዎች ተነጥዬ፣ አሰቃቂ ወንጀል ፈፅመው የታሰሩና በተደጋጋሚ እያመለጡ ያስቸገሩ እስረኞች ወደሚታሰሩበት (የቅጣት ቤት) ተወሰድኩ፡፡ እናም ለምን ወደዚህ አይነት ቦታ እንደተወሰድኩ ለሰሚው ግራ እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡ መቼም በወህኒ ቤቱ ውስጥ ግማሽ ቀን እንኳን ባልቆየሁበት ሁኔታ ‹‹ለአያያዝ አስቸግሮኝ ልዩ ጥበቃ (Maximum security zone) ውስጥ አስገባሁት›› ሊል አይችልም፡፡ ይህ ውሳኔ ቀደም ሲል መከሰስ እንዳለብኝ ከወሰኑት አሳሪዎች እንደተላለፉ መገመት የሚከብድ ጉዳይ አይደለም፡፡
አሳዛኙ ጉዳይ ግን በዚች እጅግ በጣም ጠባብና አራት ማዕዘን ሰማይ ብቻ በሚታይባት እስር ቤት ተወርውሬም የአሳሪዎቼ የበቀል በትር ያልታለየኝ መሆኑ ነው፡፡ በዚች የጭንቅ ማማ ሁለት ወራትን እያገባደድኩ በነበርኩበት አንድ ምሽት ድብደባውን የፈፀሙብኝ አቶ ይባስ አስፋው እንዲቀላቀሉኝ ተደረገ፡፡ አብረውኝ ከነበሩት ከኦፌዴኑ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ጋር በመሆኑ እንደሁላችን ጐናቸውን ያሳርፉበት ዘንድ ወለሉን ካመቻቸንላቸው በኋላ፣ ቤት ያፈራው ቀማምሰን የእስር ህይወታችን ቀጠልን፡ ፡ በመታሰሪያ ክፍላችንም የተከሰስንበትን ሁናቴ ጨምሮ ቀደም ሲል ያለንን የእስር ተሞክሮና አንዳንዴም ግለታሪካችንን መጨዋወታችን አልቀረም፡፡ እናም ከአንደበታቸው በተደጋጋሚ እንደሰማነው በበርካታ የነፍስ ማጥፋትና ከባድ የዘረፋ ወንጀል ምክንያት እንደታሰሩ ገለፁልን፡፡ አክለውም ከዶ/ር ታዬ ወልደሰማያት፣ ከአቶ ታምራት ላይኔና ከአቶ ስዬ አብርሃ ጋር እንደታሰሩ አጫወቱን፡፡ ‹‹ለምን እኒህ ሰው ተለይተው ከእነዚህ ፖለቲከኞች ጋር ታሰሩ?›› የሚለውን ጥያቄ ግን መመለስ አልቻልንም፡፡ በሂደት ለረጅም ጊዜ የሚያውቋቸው እስረኞች የማረሚያ ቤቱ ሰላይ በእነርሱ አገላለፅ ‹‹ወሬ አቀባይ›› መሆናቸውን አስረዱን፡፡ እርሳቸው ግን ሌላውን ታሪክ ባይነግሩንም አሁን ያለንባት ጠባብ ክፍል ውስጥ ከታሰሩ የመጀመሪያ እስረኞች አንዱ ስለመሆናቸው ገለፁልን፡፡
ቃሊቲ ውስጥም ሆነ ውጭ ትክክል ነው ብዬ የማምንበትን ነገር ፊት ለፊት መናገር ወይንም መተግበር ከጉዳቱ ጥቅሙ እንደሚያመዝን አምናለሁ፡፡ ከ1998-1999 ባለው ጊዜ በአብዛኛዎቹ የቃሊቲ ወህኒ ቤት ዞኖችና በከርቸሌ ጨለማ ቤት ድረስም ስታሰር የተከተልኩት ዘይቤ ይኽኑ ነው፡፡ በሂደቱም ከአንድም እስረኛ ጋር የሃይል ነገር ቀርቶ፣ ሃይለ-ቃልም ተለዋውጬ አላውቅም፡፡ ‹‹ቦዘኔ›› ክልል ተብሎ ይታወቅ በነበረው ዞን እንኳን ይኽንን የመሰለ ነገር አልፈፀምኩም፡፡ በጊዜው አብረውኝ የታሰሩ ጓደኞቼ እንደሚያስታውሱት አልፎ አልፎ ፀቤ ከፖሊስ ጋር ነበር፡፡ ከፖሊስም ጋር ቢሆን የነበረኝ አለመግባባት ‹‹ለምን የእስረኛ መብት አይከበርም? ለምንስ እስረኛ ይደበደባል?›› በሚል እንጂ በሌላ ምክንያት እና በግል ጉዳዬ አልነበረም፡፡ ይኽንንም በግልጽና በአክብሮት ከመግለፅ ውጭ የተለየ አቀራረብ ኑሮኝ አያውቅም፡፡ አቶ ይባስ አስፋውም ለረጅም ዓመታት የታሰሩና የኤች አይ ቪ ታማሚ በመሆናቸው ከማክበርና ከመንከባከብ ውጭ አንዳች ቅር የሚያሰኝ ነገር ተናግሬያቸው ወይንም ፈፅሜ አላውቅም፡፡
ነገር ግን ገና አንድ ሳምንት ሳይሞላቸው ጀምሮ በጋዜጣ ላይ ሊገለፁ የማይችሉ አያሌ ፈታኝ ነገሮችን ያደርሱብኝ ጀመር፡፡ መዘለፍ የእለት ተእለት ህይወቴ ሆነ፡፡ እንደ ድመት በጥፍሬ ቆሜ መውጣት መግባት የዘወትር የአኗኗር ዘይቤዬ ሆነ፡፡ ከአለፈው የእስር ተሞክሮዬ በመነሳት ያረጋጋቸዋል ብዬ የማስበውን ነገር ሁሉ ባደርግም አልተሳካልኝም፡፡ ያለአንዳች ማጋነን ክብራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከተናካሽ ውሻ ጋር ከመታሰር ፈፅሞ የተለየ አልነበረም፡፡ ጊዜው እየገፋ ሲሄድ ተራ ስድብ እየተሰደብኩም ሁሉንም በፀጋ ከመቀበል ባለፈ ሌላ አማራጭ አላገኘሁም፡፡ አስቀድሜ እንደገለፅኩት ያለሁበት እስር ቤት ከወህኒ ቤቱ አቅም በላይ የሆኑ እስረኞችና በሌሎች የወህኒ ቤቱ ዞኖችም አደገኛ የተባሉ እስረኞች ለቅጣት የሚመጡበት ቤት ነች፡፡
ታዲያ ሰውየው እኔና ሌሎች በእጣት የምንቆጠር እስረኞች ወዳለንበት ቅጥር ለምን መጡ? ከቀደመው የእስር ቤት ቆይታዬ እንደተረዳሁት እስረኞችን እንዲሰልሉ የሚመደቡ እስረኞች አሉ፡፡ ስለደብዳቢዬ ከታሳሪዎች ከተረዳሁትም በላይ በተለያየ ወቅት ከተለያዩ ፖለቲከኞች ጋር መታሰራቸው ለምን ይሆን? የሚለው ጥያቄ እየተመላለሰ ሳያሳስበኝ አልቀረም፡፡ መጀመሪያ ሞት፣ ከዛም በኋላ በይገባኝም እድሜ ልክ የተረደባቸው እስረኛ በመሆናቸው ለ16 ዓመታትም እንደሚሉት የታሰሩ በመሆናቸው ክፍለ ሀገር በዝውውር ቢሄዱ ኑሮ እስከአሁን ሊፈቱ ይችሉ እንደነበር በማንሳት ይቆጫሉ፡፡ የወህኒ ቤቱን ሃላፊዎች ከረጅም ቆይታቸው የተነሳ እስከ ቤተሰብ ድረስ እንደሚያውቋቸውና የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሊያስረዱን ሞክረዋል፡፡ ከድብደባው 10 ቀናት በፊት ወደ ዋናው የወህኒ ቤቱ ኃላፊ ቢሮ እያሉ በየቀኑ ማለት በሚቻል ሁኔታ በጥበቃ ፖሊሶች አማካኝነት ይመላለሱ ነበር፡፡ ሁኔታው ለሁላችንም ግልፅ ነበር፡፡ የስለላ ስራ እየሰሩ እንደሆነ፡፡ እናም በዚያ ወቅት በእኔ በኩል በወንጀለኛ መቅጫ አንቀጽ 148 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት ለፍርድ ቤት ለማቅረብ በመፃፍ ላይ ነበርኩ፡፡ ወረቀቱንም ልነጠቅ እንደምችል የራሴን ግምት ወስጀጃለሁ፡፡ የተለየ አማራጭም ሆነ የሚደበቅ ጉዳይ ባለመኖሩ የመጣው ይምጣ ብዬ መፃፌን ቀጠልኩ፡፡ የኔ ሀሳብ የነበረው ወህኒ ቤቱ በፍተሻ ሰበብ ይወስድብኛል የሚል ነበር፡፡ የተፈጠረው ግን ከዚህ ፈፅሞ የተለየ ነበር፡፡
ግለሰቡ በ6/6/2004 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ እንደተለመደው ዋና አስተዳዳሪው ቢሮ ውለው መጡ፡፡ እንደመጡም ፍራሻቸውን አሁን ወዳሉበት ዞን ለመላክ ሲሞክሩ ግራ ከመጋባት በዘለለ የተለየ ሀሳብ አልያዝኩም፡፡ መፃፌን ግን ቀጥያለሁ፡፡ በዚያው እለት ማታ ሽንት ቤት ገብተው ሲወጡኩ ‹‹ቧንቧ ባለመዝጋታችሁ ውሃ ፈሰሰብኝ›› በማለት ‹‹እናንተ ትንንሾች›› ሲሉ ሶስታችንንም በጅምላ ሰደቡን፡፡ አሰዳደባቸውና ሁናቴአቸው ከሌላ ጊዜ የከረረና እንደምንም ምክንያት ፈልገው አካላዊ ግጭት ውስጥ ለመግባት የመፈለግ ፍላጐት ይነበብባቸው ነበር፡፡ ሶስታችንም ለመሃላ እንኳን አንዳች ሳንተነፍስ ምሽቱም እየገፋ ነበርና እንደተገረፉ ህፃናት ትንፋሻችንን ውጠን ወለሉ ላይ እንደ አስከሬን ተገግጠን አንቀላፋን፡፡ በማግስቱ የግድያ ሙከራ ባደረጉብኝ ቀን አርፍደው ከእንቅልፍ ነቁ፡፡ አቶ በቀለ ገርባ ያነባል፡፡ እኔ አሁንም እየፃፍኩ ነው፡፡ አቶ ይባስ እንደተነሱ በመጮህ ያዘጋጁትን በሶ ‹‹ትጠጣላችሁ አትጠጡም›› አሉ፡፡ ሁለቱ የእንርሱን ድርሻ መጠጣታቸውን ሲገልፁ እኔ መጠጣት እንደማልፈልግ ገለፅኩላቸው፡፡ ይኽ የሆነው ከቀኑ 5 ሰዓት ገደማ ነው፡፡ ስምንት ሰዓት ተኩል ሲሆን በፀጥታ የተቀመጥንባት ክፍል በር በሃይል ተከፈተ፡፡ ደብዳቢዬ ለረጅም ሰዓት ከቤት ውጭ ቆይተዋል፡፡ ሃሳባቸው ሌሎቹ እስረኞች ሲወጡ ጠብቀው ውሳኔያቸውን ለመፈፀም እየተጠባበቁ እንደነበር ነው ከድርጊታቸው በኋላ የተረዳሁት፡፡ በአጋጣሚ ሁላችንም በስራ በመጠመዳችን ከተቀመጥንበት አልወጣንም፡፡ ጊዜ እየመሸባቸው ስለነበር ያላቸው አማራጭ ባለው ሁኔታ እርምጃውን መውሰድ ነበርና በሩን እንደከፈቱ ተንደርድረው በመግባት አሳልፈው ይሰጡብኛል ብዬ የሰጋዋቸውን ወረቀቶች ከሌሎች ወረቀቶች እየለዩ ጉዳዩን ይከታተሉ ስለነበር ከያሉበት ለቀሟቸው፡፡ ከማስታወሻ ደብተሮቼም በተጨማሪ 40 ገጽ ወጥ ፅሁፍና ሌሎችንም ሰነዶችን በእጄ ላይ የነበረውን ጨምረው ነጠቁኝ፡፡ ይኼ ነገር እንደሚመጣ በተወሰነ መልኩም ቢሆን እጠብቀው ነበርና ዝምታን መረጥኩ፡፡ በበኩሌ ከማንም ሰው ጋር ቢሆን ግብግብ መግጠም አልፈልግም፡፡ ስለዚህም ዝም አልኩ፤ ሆኖም ዝምታዬ መፍትሄ አልሆነም፡፡ እናም ከተቀመጥኩበት ተንደርድረው ከኮንክሪት ግድግዳ ጋር አጣብቀው ጭንቅላቴን ረገጡኝ፡፡ ተንሸራትቼ በቀኝ ጐኔ የሲሚንቶው ወለል ላይ ተነጠፍኩ፡፡ አሁንም አልበረዱም፡፡ ከወለሉ ላይ ጭንቅላቴን ሶስት ጊዜ እንደረገጡኝ አቶ በቀለ መሃል በመግባት ለማስጣል ሲሞክሩ በሰመመን ውስጥ ሆኜ እሰማለሁ፡፡ ‹‹እገለዋለሁ! ብገለው 6 ወር ብቻ ነው ካቴና የሚገባልኝ›› ይላሉ፡፡ አቶ በቀለንም ዘወር ካላለ እንደሚደበድቡት ይዝታሉ፡፡ ነገር ግን አቶ በቀለ ‹‹ደብድበኝ እንጂ ስትጨርሰው ዝም ብዬ አላይህም፡፡›› እያለ ግብግብ ገጥሟል፡፡ ከዚህ በኋላ ሌሎች እስረኞችም በመጨመራቸው ወለሉ ላይ እንደወደኩ ደብዳቢዬን ገፋፍተው አስወጧቸው፡፡ ትንሽ ራሴን ማወቅ ስጀምር ጭንቅላቴ ላይ ድብደባ ስለተፈፀመብኝ ህክምና የማገኝበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹልኝ ፖሊሶችን ጠየኩ፡፡ የተከበሩ የጋዜጣው አዘጋጅ እስካሁን የገለፅኩልዎ ሁሉ እውነት ስለመሆኑ በፈጣሪ ስም አረጋግጥልዎታለሁ፡፡
ከፍ ብዬ አጠቃላይ ሂደቱን ልገልፅልዎ ሞክሬያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ የወህኒ ቤቱ አስተዳዳሪ ሁኔታውን አስመልክቶ በጋዜጣዎ ባወጣው ምላሽ ላይ የእኔን እምነት እንድገልፅ ፈቃደዎንና ትግስትዎን በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ እውነቱን ለመናገር የእኔ ጉዳይ በአሳሪዎቼ በእነአቶ መለስ እጅ እንጂ በወህኒ ቤቱ አሊያም በፍርድ ቤቱ እጅ ነው የሚል አንዳች ብዥታ ኑሮኝ አያውቅም፡፡
ስለዚህ ከወህኒ ቤቱ አስተዳዳሪዎችም ሆነ ከፖሊሶች ጋር ከወንድማማችነትና ከአክብሮት ውጭ ሌላ የተከልኩት መንገድ ኑሮ አያውቅም፡፡ ደብዳቢዬ አስተዳዳሪው ቢሮ ሲመላለሱ ግን ምን እየተነጋገሩ እንደነበር ለማሽተት ብዙ አስቸጋሪ አልነበረም፡፡ የግድያ ሙከራውም ቢሆን አሳሪዎቼ የወህኒ ቤት አስተዳደሩን በመጠቀም ሊወስዱብኝ ያሰቡት እርምጃ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስለዚህም ከዚህ በታች የማነሳቸው ነጥቦች የግድያ ሙከራው በአሳሪዎቼ እንጅ በደብዳቢዬ የግል ፍላጐት ላለመፈፀሙ አስረጅ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡
1ኛ. ከሌሎች እስረኞች ተነጥዬ ከመጀመሪያውም እንዲህ አይነት ቦታ የገባሁት ይኽን መሰል እርምጃ ለመውሰድ ያመች ዘንድ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
2ኛ. እስከአሁን በነበረው የወህኒ ቤቱ አሰራር በእስረኛ ላይ የግድያ ሙከራ የሚያደርግ ቀርቶ ግጭት እንኳን ቢፈጥር አስተዳደሩ በአፋጣኝ በካቴና አስሮ ማማ ስር በማስገባት ቅጣት ይፈፅም ነበር፡፡ እኔን ለመግደል የሞከሩት እስረኛ ግን ሊቀጡ ቀርቶ ከሶስት ሳምንታት በላይ አንዳች ተግሳፅ እንኳን ሳይደርስባቸው እኛ ካለንበት በእጅጉ በተሻለ ቦታ ታስረው ይገኛሉ፡፡
3ኛ. ችግሩ እንደተፈጠረ ተጠርተው የመጡት የአስተዳደሩ አባላት ለአቶ ይባስ የጀግና አቀባበል ነበር ያደረጉላቸው ማለት ይቻላል፡፡ ‹‹አንተ ፖሊስ ወይንም የአስተዳደሩ አባል ባለመሆን ቀድሞውንም መንጠቅ አልነበረብህም፣ አሁንም በአስቸኳይ መልስ›› ማለት ሲገባቸው፣ ሰነዶቹን በፈገግታ ተቀብለው ሰውየውን ወደ ተሻለ ማረፊያ ቤት እኔን ደግሞ ባለሁበት ቅጣት ቤት እንድቀጥል አድርገዋል፡፡
4ኛ. ተጐድቼ ወደ ህክምና እንዲወስዱኝ በምጠይቅበት ሰዓትም ቢሮ አስገብተው ወረቀቱን የነጠቁኝ የእርሃብ አድማ ለማድረግ ሃሳብ ላይ መሆኔን ስለደረሱብኝ መሆኑንና የወህኒ ቤቱ አስተዳደርም ይኽኑ እንደሚጠረጥሩ ገለፁልኝ፡፡ በእኔ በኩል የሚባለው ነገር ፍፁም ሀሰትና ነገሩን ለማድበስበስ ተብሎ የቀረበ መሆኑን ገልጬ የግድያ ሙከራው ባለቤቶች እነርሱ መሆናቸውንና ንብረቴን ከእነርሱ እንደምጠብቅ አስረዳሁ፡፡
5ኛ. በደረሰብኝ ከፍተኛ ድብደባ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ብሆንም ተገቢውን የህክምና ክትትል ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ሌሊትም ሆነ ቀን ከፍተኛ የስቃይ ስሜት ሲሰማኝ በጥበቃ ላይ የሚገኙ ፖሊሶችና በጤና ጣቢያው ያሉ የህክምና ባለሙያዎች የቻሉትን ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉም ግልፅ በሆነ የአቅም ውስንነት ምክንያት ጊዜያዊ ማስታገሻዎችን ከማድረግ ባለፈ ከስቃዬ ሊታደጉኝ አልቻሉም፡፡ ይህም ሁኔታ በውል እየታወቀ የተሻለ የህክምና ክትትል በድንገተኛ እንኳን እንዳገኝ አለመደረጉ ያልተፈለገው ህይወቴ ይቀጥል ዘንድ ባይፈለግ ነው የሚል ከፍተኛ ስጋት አለኝ፡፡
6ኛ. ክስ የምመሰርት ከሆነ በአስተዳደሪዎቹ ተጠይቄ ነበር፡፡ ግለሰቡ በራሳቸው ተነሳሽነት አደረጉት ብዬ እንደማላምን በመግለፅ ፈቃደኛ አለመሆኔን ገለፅኩ፡፡ አክለውም ምስክሮች እንዳሉኝ ጠይቀው እነርሱ የራሳቸውን እርምጃ እንደሚወስዱ ገልፀው ቢሄዱም፡፡ በጉዳዩ ላይ እዚህ ግባ የሚባል ነገር ሳያደርጉ አያሌ ቀናት አልፈዋል፡፡ ይኽም የእውነት በግለሰቡ የተፈፀመ ቢሆን ኑሮ ጉዳዩ በዚህ ሁኔታ በቸልተኝነት እንደማይያዝ መረዳት አያስቸግርም፡፡
7ኛ. የወህኒ ቤቱ አስተዳደሮች የተወሰዱብኝን ሰነዶች ሙሉ በሙሉ እንዲመልሱልኝ ብጠይቅም ቀደም ብለው በጋራ እያየን የሚመለስ ካለ እንደሚመለስ የማይመለስም ካለ ለምን እንደማይመለስልኝ እንደሚገልፁልኝ ነግረውኝ ነበር፡፡ በአጋጣሚ አደጋው ከተፈጠረ በኋላ ተቀይረው የመጡት አስተዳደሮችም በተገለፀው መሰረት ይፈፅሙልኛል ብዬ ባስብም አልተሳካም፡፡ ከወሰዷቸው ሰነዶች የፍርድ ቤት የክስ ወረቀቴንና አንድ የተገነጠለ የደብተር ሽፋንና የተቀደዱ አንዳች ነገር ያልተፃፈባቸው የተቀደዱ ወረቀቶችን መለሱልኝ፡፡ ብዙ የደከምኩባቸው ፅሁፎች የውሃ ሽታ ሆኑ፡፡ በሁኔታው ማዘኔንና አዲስ እንደመሆናቸውም ከእነርሱ ጋር እሰጣ- ገባ ውስጥ መግባት እንደማልፈልግ ገልጬ መብቴን እየገፈፉ ግን በዝምታ እንደማልቀጥል ስገልፅላቸው ደብዳቢዬ ወረቀቶቹን ከሰጡአቸው እንደሚጠይቋቸው ካልመለሱላቸው ግን ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ገለፁልኝ፡፡ ‹‹ዶሮን ሲያታልሏት…›› የሚባለው በእንዲህ ያለ ጊዜ ነው፡፡ አንድ እስረኛ ከወህኒ ቤቱ አቅም በላይ እንደሆነ ማን ሊያምን ይችላል? ሰነዱንስ ቀደም ብለው ሊመልሱልኝ፣ የማይመለስም ካለ ለምን የሚለውን እንደሚያስረዱኝ ተገልፆልኝ እንደነበር ዘንግተውት ወይንስ…?
8ኛ. እየተፈፀመብኝ ያለው ግፍ ሳያንስና ጥዋትና ማታ ከሞት ጋር ግብግብ በገጠምኩበት ሁኔታ የወህኒ ቤቱ አስተዳደር በጋዜጣዎ ላይ ነገሩን ተራ ጉዳይ ተራ ግጭት አስመስሎ ለማቅረብ መሞከሩ ሀዘኔን አክብዶታል፡፡ ስቃዬንም አብዝቶታል፡፡ ከፍ ሲል እንኳ ለመከላከል እጄን እንዳላነሳው በሚገባ እየተረዱ ጉዳዩን የግድያ ሙከራ ሳይሆን ግጭት ለማስመሰል መሞከራቸው ከበደል ሁሉ የከፋ በደል ነው፡፡ በሰውነት ከተቸረኝ ክብር ውጭ የምጠቅሰው ሌላ ክብር የለኝም፡፡ ነገር ግን የወህኒ ቤቱ እርምጃ እኔን ተራ አምባጓሮ ፈጣሪ በማስመሰል ለማብጠልጠል የታቀደ እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡ ለመሆኑ ምንስ የሀሳብ ልዩነት ቢኖረኝ ሰውነቴን ይጠራጠራሉ? ወይንስ ኢትዮጵያዊነቴን? ከእስር አያያዜ ጀምሮ ከፍ ብዬ እስከ 7ኛ ተራ ቁጥር የገለፅኳቸው በደሎች ሳያንሱ እኔን እንደ ምግባረ-ብልሹ አድርገው ለአንባቢ ለማቅረብ ይመቻቸው ዘንድ ‹‹ጉዳዩ ተጣርቶ ጥፋተኛው ተለይቶ እርምጃ እንወስዳለን፡፡›› የሚል ምላሽ መስጠታቸው እውነት ልጅ ያወጣላቸው ይሆን? ወይንስ ክብር ያጐናፅፋቸው ይሆን? በአጠቃላይ ወህኒ ቤቱ በጉዳዩ ዙሪያ እያሳየ ያለው ነገር በገሃድ የሚያሳየው የጉዳዩ ባለቤት አሳሪዎቼ መሆናቸውንና ያንንም ለመሸፈን ሲል ከፍ ያለ ውጥረት ውስጥ መግባቱን ነው፡፡ ነገር ግን ይኼን መሰሉ ተግባር ለተቋም ግንባታም ሆነ ለወንድማማችነት መልካም ሁኔታዎችን ሲፈጥር አይታየኝም፡፡ የፓርቲዬ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህም ዓላማም፣ እንዲህ አይነት የሸፍጥና የመጠፋፋት አዙሪት ቆሞ ፍትህ፣ ዴሞክራሲ፣ ነፃነትና ወንድማማችነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ማየት ነው፡፡
ክቡርነትዎ እንዲረዱልኝ የምፈልገው ይኽንን የመሰለ ደብዳቤ ስፅፍ ማንንም ለመበቀል ወይንም ለማንቋሸሽ ሳይሆን እውነቱ ፍንትው ብሎ እንዲወጣ፣ ወህኒ ቤቱም እንደተቋም ህዝብ የሚያምነውና የሚያከብረው እንዲሆን ከማሰብና ጉዳቴንና ስቃዬንም ህዝብ እንዲያውቅልኝ ከመሻት የተነሳ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ባነገብኩት እውነት ደስተኛ ነኝ፡፡ ለዚህ እውነት ደግሞ ግራና ቀኛቸውን ለይተው ከማያውቁ ልጆቼ ተለይቼ ዘመኔን በሙሉ በውርደት ለመጨረስ ብቻ ሳይሆን፣ ለመሞትም ዝግጁ መሆኔን አሳዳጆቼም እንዲያውቁት እወዳለሁ፡፡
መቼን እኔ ባለሁበት ሁኔታ ያለ ሰው ነገር ቢያበዛ ቅር እንደማይሰኙ በተመተማመኔ ነገሬን ዘለግ ማድረጌን ይረዱልኝ፡፡
ስለትብብርዎ በቅድሚያ እያመሰገንኩ እውነቱን የማሳወቅ ጥረትዎ እንዲሳካ እምኛለሁ!!
አክባሪዎ!
(የማይነበብ ፊርማ)
አንዱዓለም አራጌ
የህሊና እስረኛ
የካቲት 25/2004 ዓ.ም.
ከቃሊቲ ወህኒ ቤት

1 comment:

  1. This is outrageous. Injustice is ruling Ethiopia. This account of Andualem is an evidence how far the rights of individuals detriorated in Ethiopia!

    ReplyDelete