Monday 12 September 2011

ሲሉ ሰምታ ዶሮ ታንቃ ሞተች በገና!

ወንድሙ መኰንን፣ ሎንደን፣ ታኅሣሥ 6 ቀን 2002 ዓ.ም
መቸም የወያኔ ትርዒት ማለቂያ የለውም። በየዕለቷ ይከይኗታል። “ፍርድ” ቤታቸውና “ምክር ቤታቸው/ፓርላማቸው”፣ ዋናዎች የትርዒት መድረክ ስለሆኑ፣ የታወቁቱ ቲያትር ቤቶች ደንበኛ አጥተው ከሰሩ። ወያኔ በየቀኑ ገጽ ባህርይ እየሳለ፣ ድራማ ሲሠራ ማን ገንዘብ ክፍሎ ቲያትር ቤት ሊገባ! ሞኝህን ፈልግ! ያውም ዋናው ተዋናይ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሥቃይ መለስ ዜናዊ እያለ! “ዓይን አውጣ ለይ” ቢባል፣ አዕምሮ ቶሎ ብሎ መለስን ነው የሚቀርጸው። ታዲያ መለስ ብዙ ካድሬዎችን በአውሻሸት ስልት ስለኮተኮተኮተ፣ የዋሾዎች ድራማ በየመንደሩ እንደ አሸን ፈልቷል። የወያኔ ሥርዓት እንዳለ በማጭበርበር ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ከላይ እስከ ታች በአጭበርባሪ ገጽ ባህርያት ተገጥግጧል። ምን ቢያወሩ፣ ምን ቢወሸክቱ አገር ቤት ያለው ሕዝባችን ማዳመጡን ስላቆመ የውሸት ዲሪያቸውን ውጭ ድረስ ዘርግተዋል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ አገር ውስጥ አድማጭ ሲያጡ፣ የቴሌቪዢን ፕሮግራማቸውን ወደ ውጭ ማሠራጨት አምጥተዋል። አገር የናፈቀው ስደተኛና እነሱ በተንኮል አቀነባብረው የላኩት አስመሳይ ተሰዳጅ ያይላቸዋል። ያ አልበቃ ብሎ ያንን የገማ የገለማውን ውዳቂ ፕሮፓጋንዳ፣ በየድህረ ገጹ የውስጥ መረብ (ኢንተርነት) በትነው አካባቢውን እየበከሉት ይገኛሉ።
አንድ ቀልድ ሰሞኑን አምባሳደር እምሩ ዘለቀ አጫወቱን። ቀልዱም እንዲህ ነበር።
አንድ፣ ለብዙ ዓመት ውጪ የኖረ አንድ ኢትዮጵያዊ ወደ አገሩ ተመለሰ። እዚያ እንዳለ አንድ ቆንጆ 42 ኢንች ጠፍጣፋ ስክሪን ተለቪዢን ገዝቶ ለናቱ ሰጥቶ ወደ መጣበት አገር ተመለሰ። ብዙ ጊዜ ውጭ አገር ቆይቶ እናቱን ለሁለተኛ ጊዜ ሊጎበኛቸው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ ያ ሰፊ ስክሪን የነበረው ቴለቪዥን ከቦታው ተነስቶ በምትኩ አንዲት ትንሽ ተለቪዢን ተተክታ ብልጭ ድርግም ስትል ያገኛታል። ግርም ብሎት፣ “እማዬ የገዛሁልሽ ቆንጆና ሰፊ ስክሪን ተሌቪዢን የተ ገባ?” ብሎ ጠየቃቸው። እናትዮዋም “አይ ልጄ የገዛኽልኝ ቴሌቪዢን ጉደኛ ነው። መንግሥት በዋሸ ቁጥር እየተሸማቀቀ፣ ያውልኽ ይኸችን አክሏል” አሉት።

ወያኔዎች አንድ አዲስ የተሳካለት ድራማ ሰሞኑን ሠርተው በዩ-ትዩብ (youtube) እንደ አዲስ አበባው ስንዴ “ረጭተዋል”። አይታችሁታል? ካላያችሁት እዩት እንጂ! እያዩ አንጀት እያረረ መሳቅ ነው።  ማሽላስ እያረረ ይንከተከት የለ! ትርዒቱ አምስት ክፍል አሉት። አምስቱም ክፍል በመገረምና በመደነቅ ዓይን የሚያስፈጥጡ ናቸው። “ቅደድ” ይሉሀል፣ እንዲህ ነው ኢንጂ!
በክፍል አንድ የሌለ ሴራ “ሴራ” ተብሎ “Failed Terrorist Plot in Ethiopia: Part 1”[1] ርዕስ ለብሶ ቀረበልን። ማንም አልሞተም። ምንም ንብረት አልወደመም። ምንም ሙከራ አልተደረገም። ግን፣ “ሽብርና እልቂት ሲሸረቡ ደረስንባቸው” ብለው የማይመስል ትርዒት አቀረቡልን። ዶሮዋ ጫር ጫር፣ ፎከት ፎከት ማድረጓን ትታ፣ የሰማችውን ሥራ ላይ ልታውል ባደረገችው ሙከራ የገባችበቱ ጣጣ መሰል ትርዒት መሆኑ ነው።

መንታ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች (The twin tower) ሲደረመሱ፣ ሕዝብ ሲተረማመስ ይታያል። እኛ እስከምናውቀው ያ ጉድ የተከሰተው በኒው ዮርክ ከተማ ነበር። ቆየት ቢልም ዜናውን እናስታውሳለን። በተዓምር ያ ጉድ አዲስ አበባ እንደተፈጸመ አድርገው ወያኔዎች ሊያጃጅሉን ሞክሩ። ሕዝብ ይተራመሳል። ተተራማሹ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ይመስላል። የአዲስ አበባ የከተማ አውቶቡስም ተጨራምቶ ተደንቅሯል። አቧራው ጨሰ። ድብልቅልቁ ወጣ። የዖሳማ ቢንላዲን ፎቶግራፍ ብቅ አለ። ምን መዓት መጣ! አልቃይዳ አዲስ አበባን አጋያት እንዴ የሚል የስነ-ልቦና ቡካት በተመላክቹ አዕምሮ ተዘራ። ግን ያ እኮ ዝነኛው ቱዊን ታወርስ በመባል የሚታወቀው፣ ሽብርተኞች ኒው ዮርክ ውስጥ ያወደሙት ንብረት ነው እንጂ ነቅለው አዲስ አበባ አላመጡትም። አስተናጋጅ የሚያወራው ስለኢትዮጵያ ነው። ቅጠል ይዘው ትናንሽ ኢትዮጵያውያን እሳት ሊያጠፉ ይሯራጣሉ። ትረካው፣ በቅርቡ በስለላ ሙያ የተካኑ (“የብሔራዊ መረጃና ድኅንነት አገልግሎት” ያሉአቸው) የጆርጅ ኦርዌል የናፖሊዮን ዓይነቱቹ ውሾች፣ የወያኔ ጆሮ ጠቢዎች እንዴት አድርገው ኢትዮጵያን ከአርማጌዶን እንደታደጓት የሚያወሳ ትዕይንት መሆኑ ነው። ዲንቄም! ተባለ እንዴ! የቁንጫ ቁንጥጫ ከአንበሳ ቡትረፋ አይወዳደረም። አቅራቢው፣ ባለ በሌለ ኃይሉ ድምጹን የአዲስ አበባን ሞልቃቃ የአራዳ ልጅ ለማስመሰል ጥሯል። “ም-መሰልህ” የሚል ለመምሰል ሞክሯል። ላደመጠው ግን የአዲስ አበባ ጠርንም ያሸተተው ከደደቢት በርሀ ከወጣ በኋል መሆኑ ይነቃበታል። ለምሳሌ “ሊቀቡት” እያለ ሲናገር የአዲስ አበባ ልጅ አለምሆኑ ይነቃበታል። አፉን አሞጥሙጦ፣ ጉሮሮውን አጥብቦ፣ የሰለለችውን ድምጹን እንድምንም አጎርንኖ እንዲህ በማለት በዜማ ቀጠለ።

“... ይኸ የፊልም መረጃ እንደሚያሳየን ገና ከጅምሩ የብሔራዊ መረጃና ድኅንነት አገልግሎት ይኸንን የጥፋት ተልዕኮ ከጥንስሱ ድርሶበት በቅርበት ሲከታተለው እንደነበረና እንዲሁም፣ በፎቶግራፍና በቪዲዮ ሳይቀር ይቀርጽ እንደነበረ እንመለከታለን።”
ዎዎዎዎ!!!  እንዴት ተቀለደ በል! ምስኪን ዕንቁራሪት ነበረች ዝሆንን ለማከል ብላ ተንጠራርታ፣ ተወጣጥራ፣ ተነፋፍታ ፈንድታ የሞተችው? አቶ አሳምነው ጽጌና ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ የገጸ ባህርይዎቹ ዋና መሪ ተዋናይ ሁነው ተስለዋል። ተከሳሾቹ እንዳይደበደቡ ፈርተው “በሉ” የተባሉትን ለማለት ይንተባተባሉ። ከለፍላፊዎቹ መሀል ሌተና ኮሎሌል የሺዋስ አጥናፈ፣ “የቡድኑ ሥራ አስፈጻሚ” አባልና፣ ሌተና ኮሎኔል አስቻለው አምባቸው እንዲሁ “የቡድኑ ሥራ አስፈጻሚ” አባል ይገኙበታል። የየትኛው ቡድን? የወያኔ ይሥለላ ቡድን? ካልሆነ ሁለቱም ለፍላፊዎች የሥራ “አስፈጻሚ አባል” ሲሆኑ ምነው ምንም ዓይነት ቅጣት አልተበየነባችውም? የአቃቤ ሕጉ ምስክር ናቸው። ሌሎቹ ተደብድበው መሆን አለበት በጤናቸው እንደዚያ የሚወከውኩበት ጉዳይ አይታይም። እንቁራሪት ወያኔ እንደዝሆኑ አሜሪካ ለመከየን ስትነፋፋ፣ ዋ! ፈንድታ እንዳታርፈው!

መቸም  ወያኔ አንድ እንደሞት የሚፈራው ግንቦት ሰባት የተባለ ቡድን ውጭ አገር አለና፣ እንደምንም - እንድምንም ትሪዒቱን ለጥጦት “ሽብር ሲሸርቡብኝ፣ ሕገ-መንግሥቴን ሊያፈርሱብኝ ሲዶልቱ ያዝኳቸው” ካላቸው የቡድኑ አባላት ጋር በማይዛመድ መልኩ አያይዞታል። ባለማፈርም አንዳርጋቸውን ጎዳሁ ብሎ የ80 ዓመቱን አዛውንት አባቱን ሊያነካካ የተደነቀረ የማይመስል ታሪክ ነው። የቅንጂት መሪዎችን ሲያስር ያሳየውን የጠንባ ታሪክ በሌላ መልኩ እንደገና ደገመው። አገር ቤት የሚሰማው ስለማይገኝ ብዙ ሚሊዮን ብር ፈጅቶ አቀናጅቶ በዩ-ትዩብ የውሸት ስልቻውን ተረተረው። የካንጋሩ ፍርድ ቤቱን ተጠቅሞ ለምን ግማሹን በሞት፣ ግማሹን በዕድሜ-ልክ እሥራት እንደፈረደበት ይተርካል። “የጊዮርግስን መገበሪየ የበላ፣ ‘ለፍልፍ ለፍልፍ’ ይለዋል ነው የሚባለው? የሰሩትን ካካ ሰርተው ዝም ብሉስ!
የወያኔ ደናቁርት ትረካቸው ውስጥ አንዲት የማትቀር ተደጋግማ ተበላ የማታልቅ አነጋገር አለቻቸው። “ባንክ መዝረፍ”! እና የፖሊስ ጣቢያ ወርሮ መሳሪያ መንጠቅ። ምክንያት አለቀባቸው መሰል! ከብት መዝረፍም አለ። እህል መዝረፍም አል። ከጓሮ ጎመንም ይዘረፋል። ነጋ ባንክ መዝረፍ! ጠባ ባንክ መዝረፍ! ያለ ባንክ አንዳችም ነገር አያታያቸውም እንበል? ኤዲያ! የሰለቸ ነገር! እንዲያ ነገሩ ዕውነት ቢሆን እንኳን ባንክ ዘራፊዎች ሌቦች እንጂ ከመቼ ወዲህ ነው “ሽብርተኞች” የሆኑት? እራሳቸውን ያሞኙ እንደሆነ እንጂ፣ ኢትዮጵያዊውን ትተን የዓለም አቀፉንም ሕብረተሰብ  ብነውስድ ወያኔ የለየለት የሽብርተኛ ቡድን መሆኑን ጥርት አድርጎ ያውቀዋል። ፍሰሐ ተክሌ የተባሉ ጸሐፊ ያንን ግልጥ አድርገው አስረደተውናል። ተመራማሪው በሰንጠረዥ የወንጀሉ ዓይነት፣ ቀኑና ቦታው ልቅም አደርው መረጃውን ከግርጌ በተጠቁመው አመልካች አስቅምጠውታል።[2]

ለመሆኑ ሽብርተኛ ማለት ምን ማለት ነው። ሽብርተኛ መኖሪያ ሕንጻ፣ የንግድ ሕንጻ፣ የምንግሥት ተቋማት እና ድልድይ ሳይቀር አፍራሽ ነው። ወያኔ ያንን አድርጎታል። ከነጭራሹ “ድልድይ አፍራሽ” የሚል የቅጽል ስም ተጎናጽፏል። ሽብረተኛ ሆስፒታል የሚያቃጥል ጨካኝ ወሮበላ ነው። ወያኔ ያንን ወንጀል በግልጽ ፈጽሟል። ሽብርተኛ ትምሕርት ቤት በቦምብ እያጋየ ሕጻናትን ገዳይ ነው። ወያኔ ድሮ በዚያው መንገድ አልፎ ለመንግሥትነት በቅቶ ዛሬም መንግሥት ከሆነ በኋላ የቀጠለበት ሕጻን ገዳይ ጨካን መንጋ ነው። ሽብርተኛ ሰው ጠላፊ ቡድን ነው። ወያኔ ስንት የውጭ ዜጋ ጥልፎ አሰቃይቷል። ግማሹ ጋዜጠኛ ነበር። ሌሎች የዓለም አቅፍ የዕርዳታ ሠራተኞች ነበሩ። የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ መልቀቂይ ፈተና (ESLCE) ሊፈትኑ ትግራይ ድረሰ ሂደው የታፈኑ የዚህ ጸሐፊ የቅርብ የሥራ ባልደረቦችና ጓደኞች ዛሬም በተአምር ከዚያ ጭካኔ ተርፈው በሕይወት ይገኛሉ። ሽብርተኛ አይሮፕላን ጠላፊ ነው። ወያኔ ያንን ፈጽሟል። ለምሳሌ የካቲቲ 23 ቀን 1977 ዓ. ም (2nd March 1985) ላሊበላ ላይ የጠለፉት የዕርዳት ማጓጓዣ የፈረንሳይ አይሮፕላን እስከዛሬ ቁስሉ ያልሻረለት ጠባሳ የሽብርተኛ ድርጊት ምልክት ነው። ሽበርተኛ ቦምብና መተረይስ አንግቶ ሕዝብ መሐል ገብቶ አራጅ ነው። ወያኔ የወጣለት ነበሰ ገዳይ ነው። ትላንትም ገድሏል፣ ዛሬም እየገደለ ነው። በማንኛውም መለኪያ ወያኔ የሽብርተኞች ቡድን ነው። ለወያኔ ሽብርተኝነት መረጃ ለመፈለግ ሩቅ መሐድ የለብንም።
በመሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘው የሽብርተኛ ቡድን የጥናት ማዕከል፣ በተለይ  National Consortium for the Study of Terrorism and Responses to Terrorism – START – A centre of excellence for the US Department of Homeland Security Based at the University of Maryland”[3] ወያኔ ትላንትም ሽብርተኛ እንደነበር፣ ዛሬም ሽብርተኛ መሆኑን በደንብ አጥንቶ ቁልጭ አድርጎ ለአሜሪካን መንግሥት ጥቅም አስቅምጦለታል። ታዲያ ግርም አድርጎ ሰውን ቁዝም የሚያደርገው ወያኔ የሽብርተኛ ድርጊቱን በግልጽ እየፈጸመ፣ ሰላምዊውን ሰው ሽብርተኛ እያስመሰለ የሚያቀርበው ቀፋፊና አስልቺ ትርዒቱ ነው።

ክፍል ሁልት፣ ሶስትና አራት እንቶ ፈንቶ የሞላበት ግብስብስ ነው። ገቢያው አይችሌ (አይ ስም አወጣጥ) የተባለ የባንክ ሠራተኛ ለትምህርት ጣሊያን አገር እንደሄደና አንዳርጋቸው ጸጌን እንዳገኘ ነገሩን። ታዲያ ምን ይጠበስ? አንዳርጋቸውን በየጊዜው በየስብሰባው፣ ወይም በየሰላማዊ ሰልፉ እናገኘው የለ? ከባንክ እንዴት ገንዘብ መዘረፍ እንደሚቻል ለመነጋገር ነበር ለማለት ሞከሩ። ከየት? ከጣሊያን ወይስ ከአዲስ አበባ? የማይመስል ወሬ። የአቃቤ ሕግ ምስክር ሁኖ እንደ የሺዋስ እና አስቻለው፣ የተመረጠ፣ የተዋናይነት አኪር ጨረሶ የራቀው ዘላባጅ ነው።
ወደ ዱባይ እንዴት አንድ ቡደን ከወያኔ “የብሔራዊ መረጃና ድኅንነት አገልግሎት” አባል ከሆነች ሴት ጋር እንደሂደ ይደሰኩራሉ። አብራቸው ተኛች አለማለታቸው ገላገለን። ፍተወትን እንደ ቅመም “ጠብ” ቢያደርጉባት ኑሮ የልቦለድ ፊልማቸው ትንሽ በጣመች ነበር። የግንቦት 7ቶቹን ዶር ብርሀኑ ነጋንና አንዳርጋቸውን እንዳገኙት ይናገራሉ። አራቱ ግን አንድ ላይ አይታዩም። የሉማ! ጀነራል ተፈራ ማሞ ትንሽዋን ቡድናቸው (ቲማቸውን) አግዝፈው ለነዶክተር ብርሀኑ ማቅረብ ነበረባቸው ተብሎ ተነገረን። “ምነው” ቢባል፣ “ጠቀም ያለ ገንዘብ ከነአንዳርጋቸው ለማግኘት ነው” አሉን። እንግዲህ ይኸ ጥቂት ቡደን ነበር የወያኔን መንታ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ ሊያደረማምስ የነበረው! ታላቁን የዘረኞችን ባይብል “ሕገ-መንግሥት” ሊንድ የተነሳው! የሕዝብ እልቂት ሊያመጣ ነበር ተብሎ የተሟረተው!! ወያኔ በባዶ ሜዳ፣ “ያዙኝ! ለቀቁኝ! ቡራ ከረይ! ፋሲካ ነጩ! የኦሳማ ቢንላዲንን ተከተአዮች ጨፈለቅኩ” እያለ ሲደነፋ የልጅነታችንን “ሰባት ገዳይ!” ተረት-ተረት አስታወሰን። ገጽ ባህርይ የተላበሱት ተዋናዮቹ እርስ በርስ የሚቀረን ትያትር ሲሠሩ አየን። በአንድ በኵል ገዝፎ ሲቀርብ፣ በሌላ በኵል አንሶ ቁንጫ አከለ። የቱን እንያዘው! ምነዋ ይህ ሁል ቡካት!

ቦምብ፣ መትረየስ፣ የሳተላይት ሬዲዮ፣ ከየክፍለ ጦሩ ተሰብስቦ፣ አንድ ሥራ ፈት ወጣት እንዲያገለባብጥ ተቀጠረ። ወጣቱ አልተከሰሰም። አሁንም የአቃቤ ሕጉ ምስክር ነው። ምን ማድረግ እንዳለበት ብቻ ተነግሮት ከይኬሻው፣ ከየጆኒያው፣ ከየማዳበሪያ ፌስታሉ ጠመንጃውን፣ ጥይቱን እየመዘዘ መሬት ላይ ሲደረድር ታየ። አይ ቅነበር!! ከዶኵመንታሪ ፊልም ይልቅ፣ የሕጻናት የዕቃ-ዕቃ ጨዋታ አስመሰሉት። ተደብድበው፣ ተንገላተው፣ ፊታቸው አብጦ ፍርድ ቤት የቀረቡትን ዓለም እያየ፣ የኛ የውሸት ቋቶች “ምንም ዓይነት ኃይል መገደድ ወይንም መደለያ ሳይደረግባቸው ለዳኛ ያቀረቡት የዕምነት ቃላቸው ላይ እንደምናየው ዓላማቸው ሽበር መፍጠር፣ ሕገ-መንግሥትን ማፍረስ፣ የመንግሥትን ተቋማትን ማፍረስ፣ ብሎም ከሌሎች የሽብር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በአመጽ መንግሥትን ለመጣል ነበር።” እያሉ የውሸት አተላቸውን ደፉብን። ይድፋቸው!
የወያኔ ሕገ አራዊት በሚክየነብት ቲያትር ፍርድ ቤትም ተከሳሾቹ በውሸት ተከሰው የሞትና የዕድሜ ልክ እሥራት ሲፈረድባችው፣ የቅጥፈት ድርሰት አንባቢው “ሊንዱት የተነሱት ሕግ-መንግሥት፣ መብታቸውን ጠበቀላቸው” እያለ ሲመጻደቅብን ይስማል። የፊልሙ አቀናባሪ እና ደረሲ አቃቤ ሕግ በሪሁ ተ/ብርሀን (ስሙን ልብ ብላችሁ ያዙት። እንድ ቀን ዕውነት ትፋረደዋለች) ቀርቦ፣ ቅርሻቱን ተፋብን። ለምን 5 ሰዎች እንዲገደሉ፣ 33 ሰዎች ዕድሜ ልክ ጽኑ እሥራት፣ 2 ሰዎች በአሥር ዓመት እሥራት እንደተፈረደባቸው፣ የተቀረው ደግሞ ምስክር ሁኖ በነጻ እንዲለቀቁ  እንደተደረገ እየተንተባተ ሊያሳምነን ሞከረ። ወይ መጨማለቅ!

የሚገርመው በአምስተኛውና በመጨረሻው ክፍል፣ የታዩት የአንዳርጋቸው ጽጌ መኖሪያ ቤቶች ናቸው የተባሉ ሁለት በረቶች ናቸው። አንዱ ዙሪያውን በግንብ የታጠረ፣ ፎቅ ቤት ነው። መቸም አውሮፓ ውስጥ ሊሆን አይችልም። ሌላው ግዙፍ የሆነ ቤት ነው። እንግሊዝ አገር ኗሪዎች እንዲህ ዓይነቱን ሕንጻ ያውቁታል። የአንድ ሰው ሳይሆን ከሶስት መቶ እስከ-አምስት መቶ ሰዎች የሚኖሩበት የቀበሌ የወል ቤት (Council House) እንጂ የአንድ ሰው ተብሎ ሊታይ አይችልም። ምናልባት፣ አቶ አንዳርጋቸው እዚያች ሕንጻ ውስጥ ከኖረ፣ የአንድ መኝታ ክፍል ያላት የቁጠባ ቤት መሆን አለባት እንጂ ያንን ሕንጻ በሙሉ መኖሪያ ቤቱ ሊያደርገው የሚችል ከቶም ተአምር አይኖርም። መቸም ነገርን ማጋነን ልማዳቸው ነውና ጠቅላላውን የወል ሕንጻ (building complex) የአንዳርጋቸው መኖሪያ ቤት አስመስለው ያለ አንዳች ሀፍረት አቀረቡት። ዱርውንስ መች ሀፍረት ተፈጠረባቸውና!
የተመልካቹን ሥነ-ልቦና ለማኮላሸት፣ በመጀመሪያ ክፍል የታየው አሰቃቂ እልቂት የመጨረሻው ክፍል፣ ይደግመዋል። እሳት ትምሕርት ቤትን ያጋያል። ሕጻናት እርጥብ ቅጠል ይዘው የሚጨሰውን እሳት በዚያ ቅጠል ይጠበጥቡታል። አዎቶቡስ ተጋጭቶ ይሁን ምን እንደነካው አይታውቀም ተጭረማምቶ ቁሟል። እንዲሁ ጭርምትምቱ የወጣ፣ ምናልባትም ሰሜን ጦር ግንባር ላይ ሻዕቢያና ወያኔ ሲፋለሙ የደረሰ አደጋ ሊሆን ይችላል፣ መኪናዎች ከጥቅም ውጩ ሁነው ይታያሉ። ሆቴል አይሉት ትምሕርት ቤት ውስጥ፣ በእሳት ጋይተው የተጨረማመቱ ጠርጴዛዎችና ወንበሮች ይታያሉ።

ሽብርተኛው ወያኔ፣ እራሱን ለጥፋት ሳይሆን ለልማት እንደቆመ፣ እነብርጋዴር ተፈራ ማሞንና ሌሎችን በሀሰት የተከሰሱትን ተጎጂዎች ግን፣ አንዲት ጥይት እንኳን ሳይተኩሱ፣ ሕዝብ እንደፈጁ፣ የፈሰሰ የእንስሣ ይሁን የሰው አይታወቅ-ደም ወለሉን እንዳስጨቀዩት፣ ንብረትን ውደም እንዳደረጉ አሳይተው ሊያሞኙን ሞክረዋል።
ወየኔ እራሱ ሽብረተኛ ሁኖ ሰላማዊውን ሽብርተኛ አድርጎ ማቅረቡ ለራሱ መጽናኛ ይሆን እንደሆነ እንጂ አንድ ሰው እንኳን አታሎ ማምለጥ የማይችልበት ድረጃ ላይ ይገኛል። ይኽ ያፋኝ ቡድን ማወቅ ያለበት አንድ ነገር አለ። ታኅሳስ 4 ቀን 1960 ዓ.ም እነ ጄነራል መንግሥቱ ነዋይ፣ ጃንሆይ ላይ አመጹና ተገደሉ። የንጉሱን ዙፋን ግን ለክፈውት አነቃነቁት። የተነቃነቀው ዙፋን ወዲያው ባይወድቅም መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ ም ተገልበጠና ንጉሡ እንደማይሆን ሁነው ተገደሉ። ወተደራዊ ደርግ ሥልጣን ያዘ። የዚያ መሪ ጨካኙ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ሕዝቡን አመሱት፣ ጨፈጭፉት፣ ፈላጭ ቆራጭ ሁነው ተዘባነኑ። እነ ጄነራል ፋንታ በላይን ላከባቸው። ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ. ም ሊገለብጡአቸው ተነኮሱአቸው። ያኔ የመንግሥቱ ወታደሮች የበላይነቱን ይዘው ቢያተርፉትም የተነቃነቀው ጥርስ መነቀሉ አይቀርምና የኮሎኔል መንግስቱ ሥልጣን ግንቦት 20 ቀን 1983 ተፈንቅሎ በምትኩ ወያኔ ስልጣን ያዘ። የምኒሊክ ቤተ መንግስት ሟርተኛ ነው። ዛሬ እነ ጄነራል ተፈራ ማሞ መለስን ለመገልበጥ ሞክራችሁአል ተብለው የሞትና የእድሜ ልክ እሥራት ተፈርዶባቸዋል። ነገሩ ሟርት ነውና የመለስ ዜናዊም መንግሥት ማጠሩን ማብሰሪያ ንገርት ነው። ምንም ዓይነት ድራማ ቢደርቱ ያቺን ጽዋ ሳይጠጡአት አያልፉአትም። ታላቋ አገር አሜሪካ የምታደርገውን ጸረ-ሽብር ወታደራዊ እርምጃ እኛም እንወስዳለን ብሉ መንጠራራት ትርፉ መላላጥ ብቻ ነው። ኦሮሞ ወንድሞቼ ሲተርቱ፡ “እንደ እከሌ ልዝፈን ማለት ማጅራት ይቆለምማል” ይላሉ። ወያኔ ድራማ ሠርታ ለጊዜው ለስሟ ቁና ሰፍታለች። ቁናው ግን በቅርቡ በእሳት ይጋያል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የወያኔ ግፍ አንገሽግሾት አንገቱ ደርሷል። የለውጥ ሽታ ከአድማስ ባሻገር ይሸታል!



[1] http://www.youtube.com/watch?v=dQlXBKZXOzs
[2] http://www.ethiomedia.com/fastpress/tplf_vs_violence.pdf
[3] http://www.start.umd.edu/start/data/tops/terrorist_organization_profile.asp?id=4287

No comments:

Post a Comment