ደመራ
(በሃይማኖታችን፥ በታሪካችንና በባሕላችን አንጻር)
ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ
nigatuasteraye@yahoo.com
መስከረም ፳፻፬ ዓ.ም.
‘ደመራ’ ደመረ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተወሰደ ነው:: ትርጉሙ ጭመራ
ማለት እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው:: ጥሪት (ካፒታል) እንዳይጎድል እንዳይቀነስ ይልቁንም እየበዛና እያደገ እንዲቀጥል ጠብቆ መያዝ
የሚያስችል ደመራ ነው:: ስሙ እንደሚያመለክተው ማስታወሻነቱ
ለተጠራቀመ፥ ለተሰበሰበና ለተጨመረ ነገር ነው:: በዓሉ አካቶ የያዛቸዉ
ሥርዓቱ የሚከናወንባቸው ቁሳቁሶች፥ የደመራው እንጨቶች፥ ችቦዎች፥ አሽክቶችና፥
ሌሎችም በበዓሉ ዙሪያ የሚታዩት፥ የሕዝቡን ስሜት አንድ ላይ ሰብስቦ ስለያዘ
ደመራ ተባለ:: የደመራ ተቃራኒው ‘ቅነሳና ከፈላ’ ነው::
በአገራችን በተፈጠረው ታሪካዊ ክስተት ምክንያት፥ በነገረ መለኮት ከኛ ጋራ አንድ ከሆኑት አኀት አብያተ
ክርስቲያናት በማይካፈሉት ሁኔታ በተለየና በደመቀ ሥርዓት በመላ ኢትዮጵያ ይከበራል:: ካህኑ የመጀመሪያዋን የደመራ መብራት “ደምረነ ምስለ እለ ይድኅኑ” በሚለው በሊጦኑ ቃለ ቡራኬ ባርኮ፥ ከደመራው እንጨት ጋራ
እንዲደምራት ሕዝቡን በአስተዳደር ለሚመራው ሰው ያቀብለውና የደመራውን እንጨት
ይለኩሰዋል:: ከዚያ በኋላ በተዋረድ ያገር ሽማግሌ ሁሉ ችቦውን እያቀጣጠለ በደመራው ላይ ይጨምረዋል:: በዚህ ሥርዓት የሚከበረውን
የደመራ በዓል በሃይማኖታችን፥ በታሪካችንና በባህላችን አንጸር በመጠኑ እገልጻለሁ:: ዛሬ ባለንበት ዘመን ይህችን እሳት ባርኮ
ሰጭው መንፈሳዊው ካህን ማነው? እሳቷን ከካህኑ ተቀብሎ በደመራው ላይ የሚለኩሳትስ ብቃት ያለው የአገር መሪ ማነው? ከዚያስ በተዋረድ
እየለኮሰ ደመራውን የሚያቃጥል ሽማግሌ ማነው? በማለት ከሊቃውንት አበው የተማርኩትንና የሰማሁትን
· በሃይማኖታችን፥
· በታሪካችንና በባሕላችን
አንጻር
በመዳሰስ ይሕችን ጦማር እደመድማለሁ:: በመጀመሪያ በሃይማኖታችን አንጻር እነሆ!
ደመራ በሃይማኖታችን አንጻር
የአምልኮታችንን ሥርዓት ተንተርሶ “The Wisdom Compass to Eternal Life” በሚል
ርእስ አቤል ጋሼ ጌታችን ያስተማረውን ጸሎት መሠረት በማድረግ በቀመር መልክ ብቅርቡ ባቀረበው መጽሐፍ ብዙውን ዳሶታል:: አቤል
ጋሼ በገጽ ምዕ 10 ገጽ 135 ላይ “While we keep
reciting ‘Have mercy on us’ twelve times corresponding the name of the Father,
the son and the Holy Spirit” ብሎ የጠቆመውን ከደመራ
ጋራ ያለንን መንፈሳዊና ባሕላዊ ግንዛቤ ለመግለጽ እሞክራለሁ::
አምልኮታችንን ጀምረን የምንፈጽመው ነቢዩ ኢሳይያስ በምዕራፍ ፮ ከቁጥር ፪-፭ እንደገለጸው፥ ቅዱስ
ዮሐንስም በራዕዩ አይቶ እንደነገረን፥ (ምዕራፍ ፬ እና ፭) የእግዚአብሔርን ዙፋን በተሸከሙት ኪሩቤል የአምልኮት ዘይቤ ነው::
እነዚህ ኪሩቤሎች በላያቸው ላለው ፈጣሪ አምልኮት ሲያቀርቡ ሶስት ጊዜ “ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥
የነበርክ ያለህ፥ ወደፊትም የምትኖር” እያሉ ነው:: የቀደሙ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንትም ይህን መሠረት በማድረግ “ንሕነሰ ነአምን ከመዝ እስመ ሥሉስ ቅዱስ እሩያን እሙንቱ በተዋሕዶተ መለኮት ወፍጹማን በ፫ቱ አካላት
ዘውእቶሙ ፩ዱ አብ ቅዱስ፥ ወ፩ዱ ወልድ ቅዱስ፥ ወ፩ዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” (ሃይ ምዕ፷፪፡፲፭):: እያሉ የነገረ መለኮቱን
መሠረት አስተማሩ:: ማለትም፥ “እኛም እንደ ሱራፌልና ኪሩቤል፥ ኢሳይያስ ባየው፥ ዮሐንስም
በገለጸው መንገድ በአካል ሶስት፥ በመለኮት አንድ እያልን እናምናለን፥ አምነንም እናመልከዋለን፥ እናስተምረዋለን”::
በኪዳን ተጀምሮ በቅዳሴው የሚፈጸመው አምልኮታችን የሚከናወነው በዚህ መሠረት አንድም
ሶስትም እያልን ነው::
ቅዱስ ጳውሎስ “ሕጻን ሳለሁ፥ እንደ ሕጻን አስብ ነበር እንደ
ሕጻንም እቆጥር ነበር” እንዳለው ሕጻናት ነገሮችን ማጤን የሚጀምሩት የራሳቸውን ጣቶች በማየት፥ የሚዳስሱትንም ለመቅመስ
ጣቶቻቸውን በመጉረስ ነው:: ቁጥር መማር የምንጀምረው በጣቶቻችን ነው:: በጸሎታችን የሰማዩንና የምድሩን ሁኔታ ከዳሰስን በኋላ
የምንደመድመው በጣቶቻችን ላይ ባሉት አጽቆች (phalanxes) ቀመር ነው:: Mutation (የተፈጥሮ ባሕርይን መቀየር) ከሚባለው
አጋጣሚ በቀር ያንዱ እጅ ጣቶቻችን ከአምስት አይጎሉም፥ አይተርፉም::
አውራ ጣታችንን ቆጣሪ በማድረግ በአራቱ ጣቶቻችን ላይ ያሉትን አጽቆች እንቆጥራለን:: አራቱ ጣቶቻችን
እያንዳንዳቸው ሶስት አጽቆች አሏቸው:: በያንዳንዷ ጣት ላይ ያሉት አጽቆች ስብስብ መጠን ለማግኘት ስንደምራቸው ፲፪ ቁጥር እናገኛለን::
እኒህ በጣቶቻችን ላይ ያሉት ፲፪ አዕጹቅ ቁጥሮች ለአምልኮታችን ሥርዓትና የባሕላችን መሠረቶች ናቸው:: ዛሬ በየብስ፥ በባሕርና
በአየር ውስጥ ተቆልፎ የኖረበትን የፍጥረት ምሥጢር የሰው ልጅ እየበረገደ የገባውና በመግባት ላይ ያለው በደመራ በተጀመረ ቁጥር
ነው::
12 ን አጽቆች ለ4 ጣቶቻችን ብናካፍላቸው
የምናገኘው ውጤት ሥላሴ ማለትም 3
ነው:: 12 ን አጽቆች ባንዷ ጣት ላይ ላሉት ለ3 አጽቆች ብናካፍላቸው የምናገኘው ጸወርት መንበር የሚባሉትን 4ቱን ኪሩቤል ነው::
እንደገና 3 እና 4 ብንደምር የሳምንቱን ዕለታት ልክ ቁጥር 7 ን እናገኛለን:: ፊደሎቻችንም የተዋቀሩት በሳምንቱ ዕለታት ላይ
ነው:: በግዕዝ (፩) ተጀምራው የሚያልቁት በሳብእ (፯) ቁጥር ነው:: ፩፥ ፫፥ ፬፥ ፯
ና ፲፪ ቁጥሮች ለብዙ ነገሮች ምልክቶች ናቸው::
በአራቱ ጣቶቻችን ያሉት ፲፪ አጽቆች፥ አንድ ቀን
የተባለው ብርሃን የያዛቸውን አስራ ሁለት ሰዓቶች ያስታውሱናል:: አንድ
አመት የሚሰጡንን የአስራ ሁለት ወራት ጥርቅም ይሰጡናል:: የክርስቶስን ምድራዊ አካል ምንጭ ለማግኘት የምንቆጥራቸውን የ፲፪ቱን
ነገደ ፳ኤል ቁጥር ይሰጡናል:: በመቀጠልም ከክርስቶስ ቀጥለው ክርስትናን ያስፋፉትን የሐዋርያትን ፲፪ ቁጥር ይጠቁሙናል::
የቤተ ክርስቲያናችን የጸዋዕ ማኅበራት፥ በስላሴ፥ በመድኃኔዓለም፥ በእመቤታችን፥ በመላእክት በጻድቃንና
በሰማእታት ስም የሚመሰረቱት በ ፲፪ ቁጥር ነው:: በራዕየ ዮሐንስ ላይ
እንደተገለጸው፥ የያንዳድዱ አጥቢያ (ሰበካ) ቁጥር በአስራ ሁለቱ ነገደ
እስራኤል፥ በ፲፪ ሐዋርያት፥ በ፲፪ ወራትና በ፲፪ ሰዓተ መአልት (ቀን) ልክ ነው:: አካለ መጠን የደረሰ ሁሉ በያለበት አጥቢያ
(ሰበካ) በ ፲፪ እየተመደበ ይደመራል:: ሁሉም የጽዋዕ ማኅበራት ለያንዳንዳቸው
መምሕር ይመደብላቸዋል:: እያንዳንዱ አባል ከዓመቱ ውስጥ ካሉት ወራት አንዱን ይወክላል:: ከነገዶች ውስጥ አንዱን፥ ከሐዋርያትም
አንዱን ይወክላል:: በዚህ መንገድ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት አባል የሆነ ሁሉ በዚህ ቁጥር እየተካተተ (እየተደመረ) የጽዋው
ተካፋይ ይሆናል::
እያንዳንዷ በ፲፪ ቁጥር የተዋቀረችው የጽዋዕ ማኅበር
አባላት ከመካከላቸው በእምነትና በመንፈስ ላቅ ያለውን መርጠው ሙሴ
የሚባል ለማኅበሩ መሪ ይሰይማሉ:: እያንዳንዷ የጽዋዕ ማኅበር የመረጠችው ሙሴ
(መሪ) ደግሞ፥ የሚመራትን የጽዋዕ ማኅበር በመወከል አንድላይ ተሰብስበው ይደመሩና የራሳቸውን የጽዋዕ ማሕበር፦
ማሕበረ በኩር ብለው ይሰይማሉ:: ለማሕበረ በኩሩ መምሕር ሆኖ የሚሰየመው በሙያና በችሎታ ከሊቃውንቱ መካከል ተመርጦ
የደብሩ አለቃ ነው:: የደብሩ አለቃ ዋና ኃላፊነት እየዞሩ የጽዋዕ ማኅበራቱን አባላት የሚያስተምሩትንና የማኅበረ በኩሩን አባላትና
ሙሴዎች አንድላይ እየሰበሰበ ማስተማር ስለሆነ በጥንቃቄ ይመረጣል:: የመሳፍንቱ ሥርዓት ተጽእኖ ቤተ ክርስቲያኒቱን ባያዘናጋት
ኖሮ የያንዳንዷን አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መምራት የነበረበት ይህ ማኅበረ በኩር የተባለው ጉባዔ ነበር::
በተራ በየቤቱ በሚደረገው ጉባዔ ተረኛው ቄጠማውን ጎዝጉዞ፥ ውሐውን ቀድቶ ይጠብቃል:: የአምልኮቱ ማዕከል
ዮሐንስ የታረደው በግ እያለ የገለጸው ክርስቶስ ነው:: ሁሉም ነጭ ልብስ ለብሰው ስለታረደው በግ ፍቅር፥ ክብር ውዳሴና አምልኮ
ለማቅረብ ይሰበሰባሉ:: በሙሴያቸው አስተናባሪነት ካህኑ በራዕየ ዮሐንስ ላይ የተመሠረተውን ሥርዓት በመጠበቅ ጉባዔውን ይመራል::
ከዚያም የማኅበሩ ሙሴ ባለወር፥ ባለሳምንት ብሎ ጉባዔው የተሰየመበትን ስም እየጠራ “የጉባዔው
ወዳጅ ማነህ እኔነ ነኝ የምትል” ብሎ ያውጃል::ተረኛው ተዘጋጅቶ በመጠበቅ ላይ ነውና እኔ ነኝ ብሎ ወደ መሐል ይቀርብና
ይቆማል:: “እኔ አለሁ ብለህ እንደቆምክ መድኃኔለም ይቁምልህ” ይለዋል:: ጽዋውን
በመቀባበል በጽዋዕ ውስጥ ያለውን ጠበል ሁሉም ይካፈለዋል:: ከዚህ በኋላ ጽዋውን የተቀባበሉ አካላት በጉባዔው ፊት ይወድቃሉ::
መምሕሩ “እንደዚህ እንደወደቃችሁ ኃይለ አጋንንትን ያውደቅላችሁ” ብሎ አቤል ጓሼ
እንደገለጸልን ሰዓታቱን፥ ወራቱን ነገደ እስራኤልን፥ ሐዋርያትን በመጨረሻም ስላሴን አራቱ ኪሩቤልን አጠቃሉ ደምሮ በያዘው ፲፪ ቁጥር
“እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ” ይልና ያለፈውን ይቅር ይበለን ከሚመጣውም ጠብቆ በሚቀጥለው
ጉባዔያችን ያገናኘን ብሎ የአምልኮቱን ሥርዓት ይዘጋዋል:: ነፍሳቸውን ይማርና ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የሰበካ ጉባዔውን ሲነድፉት፥ በዚህ ቅዱስ ታሪክና ባሕል
የቤተ ክርስቲያናችንን አስተዳደር ለማዋቀር ነበር፡፡
ደመራ በታሪክችንና በባህላችን አንጻር
ደመራውን የጀመረችው በሶስተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ እሌኒ የምትባለው የቆስጠንጢኖስ እናት ክርስቲያን
ንግሥት ናት:: የጀመረችበት ምክንያትም የክርስቶስ ተቃራኒዎች፥ የክርስትና ንክኪ ያለውን ፍንጭ ሁሉ ለማጥፋት ባደረጉት ጥረት፥ ከክርስትና ፍንጮች አንዱና ዋናው የክርስቶስ
መስቀል ስለነበረ፥ በጉርጓድ ቀበረውት ነበረና፥ ፈልጋ ለማግኘት ነው::
እሌኒ ሕይወቷ የተመሠረተው በክርስትና ፍቅር ላይ ስለነበረ መስቀሉን ለማግኘት በብርቱ ጣረች:: መስቀሉን
ለማግኘት የተጠቀመችበት ስልት፥ እሳት አንድዳ ጢሱ እንዲመራት በመጸለይ ነበር:: የሚቃጠል ነገር ሰብስባና ደምራ በማንደድ ጢሱን ተከትላ በመሄድ መስቀሉን አገኘችው:: የታሪኩ መነሻ
እሌኒ እንደሆነች በያመቱ ስንናገረው የኖርነው ነውና፥ በዚህች ጦማርም መሸፈን ስለማልችል በእሌኒ ዙሪያ የሚነገረውን ታሪክ እዚህ
ላይ ገትቼ፥ ከራሳችን ታሪክ ጋራ ወደተያያዘበት መስመር እሻገራለሁ::
የታሪኩ መሠረት ይህ ሆኖ ሳለ ንግሥት እሌኒ በጀመረችበት ቦታ፥ እኛ በምናደርገው ሥርዓት ዓይነት ሊከበር
ቀርቶ የሚያስታውሰውም የለም:: ታዲያ ለምን እኛ ብቻ በዚህ መልክ እናከብረዋለን? የሚል ጥያቄ ማስከተሉ አይቀርም፥ ተገቢም ነው::
መልስ የሚጠበቀው ከዚያ ወዲህ በየዘመኑ ወደ አገራችን ከገቡት ባሕርያቸው ከደመራ
ይልቅ ወደ ከፈላ ካዘነበሉት አብያተ ክርስቲያናት አይደለም:: የደመራውን ታሪክ የማስተማርና በደመራው ዙሪያ ለሚነሱት ጥያቄዎችም የመመለስ እዳ፥ ሸክምና ግዴታ
ያለባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት::
የጥምቀቱን በዓል ከዓለም ክርስቲያኖች ለየት ባለ መንገድ እንደምናስታውሰው፥ በንግሥት እሌኒ ሕሊና
ውስጥ ይነድ የነበረውን የክርስቶስን ፍቅር በያመቱ ደመራ የሚል ስም ሰጥተን በዓለም ያሉ ክርስቲያኖች በማያስቡበት በተለየ መንገድ
እናከብረዋለን:: በዓላት በምክንያት የሚጀመሩ፥ የታሪክ መነሻዎች ናቸው:: ባንድ ወቅት የተጀመሩት ሳይረሱ የሚታረመውን እያረሙ፥
የሚጨመረውን እየጨመሩ ዓለም እስክታልፍ የሚቀጥሉ ሕዝቦች፥ በቅኝ ገዥዎች አዕምሯቸው ሳይዝልና ሳይዘነጋ እስከ መጨረሻ ጠንክረው
የሚጓዙ እንደ ኢትዮጵያውያን ያሉ ኅብረተ ሰቦች ናቸው::
ይህ በዓል ከተጀመረበት ጀምሮ እስከዚህ ዘመን ድረስ በገጠሙን ክፉ ቀናቶች ሁሉ ሳያቋርጥ ከኛ ደርሷል::
በዓላት ሁለት መንገዶች አሏቸው:: ከሁለቱ አንዱ ከጣዖትና ከባዕድ አምልኮት ጋራ
የተያያዘ ቅዱስ መጽሐፍ የሚያወግዘው ነው:: ከሰይጣን አምልኮት በራቀ መንፈስ ባሕልን ታሪክን አዝለው በመመላለስ የሚታወሱ ሁሉ
በዓላት፥ ይዘታቸው እየሰፋ የሚቀጥል መጻሕፍቶች ናቸው::
ይህ አይነት የSocial Memory መጽሐፍ የሌለው ሕብረተ ሰብ በኛ ግንዛቤ እንስሳት ብቻ ናቸው::
ከዚህ ቀደም ቅበላ (http://www.medhanialemeotcks.org/pdf/ISAT.pdf)
በሚል ርእስ እንደገለጽኩት፥ በሐዘንና በደስታ፥ በልቅሶና በሳቅ፥
በመሸበርና በመረጋጋት በምትናወጠው ዓለም የሚኖር ሰው፥ በዓሉን የሚያከብረው በሚገጥመው ሁኔታ ነው:: አንድ ጊዜ የተዘጋጁ መጻሕፍት
በውስጣቸው የያዙትን ምዕራፍ በሚገጥሟቸው ተመሳሳይ አዳዲስ ክስተቶች እያሰፉ በመደጋገም እንደሚታተሙ ሁሉ፥ በዓላትም እንደዚሁ በየአመቱ
የሚገጥማቸውን እየጨመሩ ስለሚሄዱ የሕብረተ ሰቡ ትዝታ ወይም የ
Social Memory መጻሕፍት ናቸው::
ለደመራው በዓል መነሻዋ እሌኒ ብትሆንም፥ እሌኒ ደመራ ብላ አልሰየመችውም:: ይህ በዓል ደመራ ተብሎ
አሁን በምናከብረው ሁኔታና መንፈስ እጅግ ሰፍቶ ከመከበሩ በፊት፥ ወደ እኛ ተሻግሮ መጥቶ ሲከበርና ሲታወስ ቢኖርም፥ የመስቀል በዓል
እንጅ ደመራ እየተባለ አልነበረም:: እሌኒ የሰራችውን ታሪክ በማስታወስ ሲከበር የቆየው የመስቀል በዓል፥ በአጼ ገላውዴዎስ ዘመን አዲስ ታሪካዊ ክስተት ገጠመውና ሊቃውንት አበው፥ ከታሪካችን ጋራ ደምረውና
አስፍተው ደመራ ብለው
ሰየሙት::
ከሊቃውንት አበው መምሕሮቼ እንደሰማሁት፥ ግራኝ መሐመድ ኢትዮጵያን በወረራት ዘመን፥ የአገሪቱ መሪ
አጼ ልብነ ድንግል በዚያ ዘመን ገናና ይባል የነበረውን የፖርቹጋሉን መንግሥት እርዳታ ጠየቁ:: የፖርቹጋሉ መንግሥትም ይህን አጋጣሚ
ተጠቅሞ፦
· ፩ኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሮማ ካቶሊክ ሥር፥
· ፪ኛ ኢትዮጵያንም በራሱ ቅኝ አገዛዝ ሥር ለማድረግ ከሮማው ፓፓ ጋራ ሲሸርብ ዘገየ::
ከዚህም
ጋራ የዘመኑ የጉዞ ሁኔታ ለመዘግየታቸው ተጨማሪ ችግር ነበር ይላሉ:: በዚያም ሆነ በዚህ፥ አጼ ልብነድንግል ከጠየቁበት ወቅት እጅግ
ዘግይተው፥ ጦርነቱ ከበረደ በኋላ መልእክተኞቹ ደረሱ:: አጼ ልብነ ድንግል ሞተው፥ በጦርነቱ የደቀቀው ሕዝብ በአጼ ገላውዴዎስ መሪነት
በመቋቋም ላይ ሳለ፥ በሸርና ሸፍጥ የተላኩት የፖርቹጋል ሰዎች ዘግይተው ከኢትዮጵያ ደረሱ:: ጦርነቱ እንዳለቀና የነሱም እርዳታ
እንደማያስፈልግ ሲረዱ ወደ አገራቸው በመመለስ ፈንታ፥ በኢትዮጵያ ውስጥ በመኖር
በሕዝቡ መካከል እየገቡ፥ አሁን ቻይናዎች በአገራችን ላይ እንደሚያደርጉት
ማለት ነው፥ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን እየተጋቡ በመዋለድ ኑሯቸውን ማስፋፋት ጀመሩ::
በአገሪቱ ባሕል ሃይማኖትና ፖለቲካ እየገቡ የሕዝቡን አንድነት የሚፈታተን ሸርና ደባ መሥራት ጀመሩ::
በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተፈጠረው ሁኔታ በዘመናችን የተደገመ ይመስላል::
ከአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት መወገድ ጀምሮ ደርግ እስኪፈርስ ድረስ በውጭ ጠላት ባይሆንም እርስ በርስ በተካሄደው እልቂት ያለቀው
ሕዝብ አገሪቷ ያመረተችው ምርጥ ዜጋ ነበር:: አገሪቱ እነዚህን ሁሉ አጥታ፥ ህዝቡም
ተዳክሞ ባለበት ወቅት፥ ዘረኛው ያቶ መለሰ መንግስት አገሪቱን በግላጭ ተቆጣጠራት:: እንደዚሁ ሁሉ በግራኝ መሐመድ ካለቀው የተረፈው ሕዝብ ከግራኝ መከራ በኋላ ሳያርፍ
እንደገና ፖርቹጋሎች ከፈጡሩበት መከራ ውስጥ ገባ:: ከኤርትራ ጋራ በንጉሡና በደርግ
ዘመን በተደረገው ግጭት ካለቀው ሕዝብ ይልቅ በአቶ መለሰ መንግሥት ያለቀው ወገን ይበዛል እንደሚባለው መሆኑ ነው::
በፖርቹጋሎችና በኢትዮጵያውያን መካከል ጥላቸውና መናናቁ እጅግ በማየሉ በቅጽል ስምና በተረብ መዘላለፍ
ተጀመረ:: ኢትዮጵያውያን ለፖርቱጋሎች ትኋን የሚል ስም ሰጧቸው:: ፖርቱጋሎች ደግሞ ለኢትዮጵያውያን ቁንጫ የሚል ስም ሰጧቸው:: በመናናቅ እርስ በርስ የተሰጣጧቸው የቅጽል መግለጫዎች
ትርጉም አላቸው:: ኢትዮጵያውያን ፖርቹጋሎችን በትኋን ጠባይ የገለጿቸው፥ ትኋን የሰው ደም መምጠጥ የምትጀምረው ጨለማ ተንተርሳ፥
ቀስ ብላ እየተጠራራች ከየስርቻ በመውጣት ነው:: ደሙን የመጠጠችው ሰው ካያት ሮጣ አታመልጥም:: የመጠጠችውን ደም ተሸክማ ስትንገዳደገድ
ትደፈጠጣላች:: ጥላው የምትሔደው ክርፋት በቶሎ የሚለቅ አይደለም:: ፖርቹጋሎችን እንዲህ ናችሁ ለማለት ኢትዮጵያውያን ትኋኖች
ብለዋቸዋል::
ቁንጫ ለመባላት ቀንም ሌትም አትመርጥም:: ይዞ ለመግደልም የማትጨበጥ ፈጣን ናት:: የሚሸት ነገር የላትም::
ኢትዮጵያውያኖችንም አይያዙም፥ አይጨበጡም፥ ጠላታቸውን ለማጥቃት ቀንና ሌሊት አይመርጡም ለማለት ፖርቹጋሎቹ ኢትዮጵያውያንን ቁንጫዎች
ብለዋቸዋል:: በዚህ መልክ መሰዳደቡና መተራረቡ አድጎ ጸቡና ጥላቻው እየከረረ
ሄደ:: እንዲያውም በአድዋ አካባቢ
የነበሩት ፖርቹጋሎች ድርጅታቸውን የበለጠ አጠናክረው “መንግሥታችሁ በፖርቹጋል ምንግሥት
ሥር ካልሆነ ተቆርጣችሁ የቀራችሁ ናችሁ” እያሉ በመስበክ በሌላው ክፍለ አገር ሕዝብ ላይ ከፈጸሙት የመከፋፈልና
እርስ በርሱ የማገዳደል ደባ በአድዋ ሕዝብ ላይ የፈጸሙት እጅግ የከፋ ነበር ይባላል::
ይህንም ለማስታወስ በአድዋ
አካባቢ ያሉ ኢትዮጵያውያን እስካሁን ድረስ “ዓኾ ዓኾኋይ ሆይ ሆያዬ ንጎናይ በርሆ”
በማለት ደመራውን በመዞር በያመቱ ያስታውሱታል:: ይህም ማለት፥ “እናንተ
ተቆርጣችሁ የቀራችሁ እያሉ ይዘልፏቸው ስለነበረ፥ እኛ ኢትዮጵያውያን የተቆረጣችሁ እየተባልን በገዛ አገራችን ስንሰደብ ብንኖርም፥
ዛሬ በዚህ ችቦ የነጻነት ብርሃን በራለን” እንደ ማለት ነው ብለው ሲናገሩ ሰምቻለሁ:: የትግርኛውን ቋንቋ ስለማላውቀው
አበላሽቼ እጽፈውና እተረጉመው ይሆናል:: ይቅርታ እየጠየቁ የማቃናቱን ኃላፊነት ባካባቢው ለተወለዳችሁ ወገኖቼ እተወዋለሁ:: ንጎናይ ማለት ቆራጣ ማለት ነው ሲሉ ሰምቻለሁ:: ከዚህም ጋራ ለአገራቸውና ላንድነታቸው
ጸንተው የቆሙ የትግራይ ሰዎች በአማረኛ አሽከት በትግርኛ ጸጎጎት የምትባለውን የመጣበቅ ባሕርይ ያላትን ሐርግ በራሳቸው ላይ ያስራሉ::
ሐረጓን ያንድነታቸውና የጽኑ መተማመናቸው ምልክት አርገው ተጠቅመውባትል:: በአሽክቷ የተጠቀሙበትን ምሥጢር መስከረም ፲፮ በያመቱ
ጽንዒ እያሉ ያስታውሱታል::
የፖርቹጋሎች ሁኔታና አዝማሚያ ኢትዮጵያውያንን እያሳሰባቸው መጣ:: ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ይህን ነገር
ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሕዝባቸው ሳይጎዳ እነዚህን ትኋኖች እንዴት እንደሚገላገሏቸው አጠኑና የመስቀሉን በዓል እንዴት እንደሚጠቀሙበት
ዘዴ አመነጩ::
ምሥጢር ማደላደል
በሚባለው ጉባዔ ላይ በየኔታ ፍስሐ መሪነት፥ ነፍሶቻቸውን ይማርና የኔታ አንዳርጌና የኔታ አምዴ የቅኔ መምሕራን ሲነጋገሩ
እንደሰማሁት፥ በዚያ ዘመን የነበሩ ሊቃውንት እንዴትና በምን መንገድ ፖርቹጋሎችን ላንድ ጊዜና ለመጨረሻ ጠራርገው ለማጥፋት ሲያስቡ፤ በመጽሐፈ መሳፍንት ምዕ ፱ ከቁጥር ፳ ላይ ተመዝግቦ እንደምናነበው “ለትጻዕ እሳት እምቤተ አቤሜሌክ፥ ከመ ትብላእ አብያተ ሴኬም፡ ወትሜሎም:: ወለእመ አኮ እሳት ትጻእ
እምቤተ ሴኬም ወትሜሎም ከመ ትብላዕ ቤተ አቤሜሌክ” የሚለው ንባብ ትዝ አላቸው:: ይህም ማለት “እኛ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራችን የተደጋገመ ግፍ እየተፈጸመብን ነው:: ይህች ከኢትዮጵያውያን
ቤት እየተጫረች የምትወጣ የዘንድሮው የመስቀል በዓል እሳት፥ በሸርና በሸፍጥ በእርዳታ ስም መጥተው የወረሩንን ፖርቹጋሎችን ትብላ፥ ለአገራችን ለነጻነታችን መታገላችን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አጥቶ ረድኤቱን
ከነፈገንም፥ ለዘላለም በፖርቹጋሎች ሥር ተጠቅተን ከመኖርና ለልጆቻችንም የተገዥነትን ውርስ ከማውረስ ይሕች
ከየቤታችን የጫርናት እሳት እኛኑ ትብላን” ብለው ቆርጠው ተነሱ::
“የመስቀል
በዓል ፖርቹጋሎችን
የማይደምር የግላችን ነው:: የምናከብረው ሌሊት ነው:: በበዓላችን የማይደመሩት ፖርቹጋሎች እንቅልፍ ላይ ይሆናሉ:: እናንተ ቱኋኖች ከአገራችን ውጡ፥ እያልን በምናበራው ችቦ ቤታቸውን እያቃጠልን
በኛ ላይ የሚያደርጉትን ግፍና፥ በቅኝ ግዛት ለመቀጠል ያላቸውን ረዥም እቅድ ይህችን የመስቀል በዓል በመጠቀም ላንድና ለመጨረሻ
ጊዜ መግታት አለብን” ብለው ያቀዱትን በየደብሩ ለሚኖረው አካለ መጠን ለደረሰ ወንድ ልጅ ሁሉ ትድረስ ብለው ካህናቱ በቆራጥ
መንፈስ አሰራጩት:: መልእክቱ የደረሳቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉም በመተባበርም ተግባራዊ አድርገውት አደሩ:: ካህናቱ ለወገን መጎሳቆል ተቆርቁረው ወስነው ባንድ ልብ እንሙት
ብለው መነሳታቸው ያስደነቀው አንድ ሰው፥፥
“ካህን ሞተ ተብሎ
አይነግሩም አዋጂ
እንዲህ በየደብሩ
መላክ ነበር እንጂ” ብሎ እንደገጠመ ይነገራል::
በነገራችን ላይ የኔታ አንዳርጌ ከላይ የጠቀስኩትን
ታሪክ መሠረት በማድረግ በደመራ ሌሊት መወድስ ዘርፈውበት፥ እኛ ተማሪዎችም የሳቸውን ቅኔ እንደ ምሳሌ (ሞዴል) በመጠቀም የሳምንቱ
የቅኔ መቁጠሪያችን ሆኖ መሰንበቱን አስታውሳለሁ::
ኢትዮጵያውያን ከወገኖቻቸው አንድ ሰው ሳይጎዳ በመስቀሉ የችቦ እሳት አገራቸውንና
ነጻነታቸውን ከፖርቱጋሎች ነጥቀው መለሱ:: ይህንም ለማስታወስ በደመራው በዓል
“ትኋን ውጪ ቁንጫ ግቢ” ይባላል::
ኢትዮጵያውያን የፖርቹጋሉን መሪና የሮማውን ፓፓ ሸፍጥ አከርካሪውን የሰበሩበት ጥበብና ጀግንነት ፖርቹጋሎችንና ሮማውያን አሳፍሯል፥
አስቆጥቷል፥ ቂምም አትርፏል::
የትኋኗ አለማምለጥና ስትደፈጠጥም የምታስከትለው ክርፋት፥ ለኢትዮጵያውያን ሊቃውንት
ቅኔ ሰምና ወርቅ ሆኗል:: የማይለቅ ክርፋት የተባለው የትኋኗ ሽታ፥ በዚያን ጊዜ የደረሰባቸው ጉዳት፥ በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን
መሪዎች ልብ የቀረጸው ቂምና በቀል ነው ይላሉ:: “ጥንተ አብሶ” ይሉሐል ይህ
ነው::
እያንዳንዱ ዜጋ ለወገንና ለጋራ ጥቅም ለሰባዊ ልዕልና ቅድሚያ በመስጠት የሚቀርብለትን ጊዜያዊ ጥቅም
ንቆና ተጸይፎ በመተው ፍላጎቱን ካልገታ፥ አገር እየበደለ ሕዝቡን እያስለቀሰ ለመኖር ከውጭም ይምጣ ከውስጥም ይፈጠር በጥቃቅን ነገር
በሹመት በገንዘብ መፈተኑ አይቀርም:: ይህ አይነት ፈተና ሁለት ሰዎች [አዳምና
ሔዋን] ብቻ በሚኖሩባት ገነት ከተከሰተ፥ በየተለያዩ የጎሳ ስሞችና ቋንቋዎች
በምንኖርበት ባሁኑ ወቅትማ፥ እንደ ፖርቹጋሎች ለሚከፋፍል ለሚለያይ መንግሥት፤ ድኅረ ገጾችን፥ የመገናኛ መስመሮችን እያፈነ
በጨለማ ዘግቶና አፍኖ ለመግዛት ምን ያህል ምቹ እንደሚሆንለት በአጼ ገላውዴወስ ዘመን ከነበሩት ወገኖቻችን የበለጠ መገንዘብ ይኖርብናል::
ኢትዮጵያውያን ካህናት ከፖርቹጋሎች ጋራ ወግነው ያስቸግሩ ስለነበሩ ወገኖች “ስማዕ እግዚኦ እለ ኪያከ ይስእሉ:: እግዚኦ እለ ዘንስእለከ ኢንሰተት አላ በስክየት ዲበ ጸላኢነ
ነሀሉ:: ሀበነ ዘወትር ጸሎተነ እምኂጠተ ጸላኢ ንትአቀብ:: . . . . ተወከፍ ሲሩያነ በምሕረትከ አንጽሕ አብዳነ አጥብብ ወኅጉላነ”(ዘነግሕ)::
በማለት ጸለዩ:: ማለትም፥ “አቤቱ በቅን ሕሊና የሚለምኑህ ስማ፥ የምንለምንህ እኛም
ተሸንፈን እንዳንወድቅ እርዳን:: በወቀሳም በከሰሳም የምንከሰስበት እንዳይኖር ብንከሰስም እንድንረታ እርዳን:: ከጠላት ሸፍጥና
ማታለል ነቅተን እንድንጸልይ እርዳን:: በስሕተታቸው ተጸጽተው የተመለሱትን ወገኖች ተቀበላቸው:: አርቆ የማሰብ ችሎታ ያጠራቸውንም
ወገኖች ሕሊናቸውን ብሩህ አርግላቸው:: ወደ ጠላት ጎራ በመግባት ከመካከላችን የጠፉትንም ወገኖች ንቃቱንና ማስተዋሉን ስጣቸው”
በሚለው ላይ አስምረውበታል::
ሊቃውንቱ ሰዓቱንና ወቅቱን ከታሪኩ ጋራ በማገናኘትም “መዝገበ
ጽልመት እንተ ብነ በሥምረተ አቡከ አብራህከ ለነ ዘአውጻእከነ እማዕምቅ ውስተ ብርሃን:: ወወሀብከነ ሕይወተ እሞት:: ወጸጎከነ
እምግብርናት ግዕዛነ:: ዘበመስቀልከ አቅረብከነ አምላክ:: አላ ብርሃነ ሀበነ”(መንፈቀ ሌሊት):: እያሉ አምላካቸውን አመሰገኑ::
ማለትም፥ “በጨለማ ውስጥ ለነበርን ለኛ ባባትህ በጎ ፈቃድ የደኅንነት ብርሃን አበራሕልን::
ከጨለማ አዘቅት አውጥተህ ወደ ብርሃን አፋፍ አወጣህን:: ከሞት አድነህ ሕይወትን ሰጠኸን:: ከመገዛትም ነጻ አወጠሀን:: በመሰቀልህ
ያቀረብከን አምላክ ሆይ ብርሃንህን ስጠን”::
በግራኝ መሐመድ የተጎዳውና የተጎሳቆለው ወገን፥ እንደገና ከፖርቹጋሎች ጋራ ፊት ለፊት በመጋፈጥ እንዳይሞትባቸው፥
“ዕቀብ ኩልነ ዘእንበለ ጻሕብ ወዘእንበለ ተመውዖ ወዘእንበለ ማዕቀፍ:: አድኅን አእጋሪነ
እምዳህጽ ወአዕይንቲነ እምአንብእ ወነፍስተነ እሞተ ኃጢአት ወደምረነ ምስለ እለ ድኅኑ ብከ
በጸሎተ ኩሎሙ እለ እምዓለም አሥመሩከ” የሚለውን ንባብ ያቀፈውን
ሊጦን ጸለዩ:: (ሊጦን ዘሠርክ)
ይህም ማለት፥ “አምላካችን ሆይ! በፍልሚያ ውስጥ ገብተን ስንዋጋ ተደናቅፈን ከመሸነፍ
ጠብቀን:: ጠላቶቻችንን ስናሳድድ አንዳልጦን ከመውደቅ አድነን:: እንባ ከማፍሰስም ተዋርዶ ከመሞት አድነን:: ባንተ ታምነው ባንተ
መከላከል ከሚድኑት ጋራ ደምረን”
“እግዚኦ ገደፍከነ ወነሠትከነ፥
ቀሰፍከነሂ ወተሣሀልከነ
አድለቅለቃ ለምድር ወሆካ
ወፈወስካ ቁስላ እስመ አንቀልቀለት
አርአይኮሙ ዕጹባተ ለሕዝብከ
ወአስተይከነ ወይነ መደንግጸ” የሚለውን በክስተት
መልክ ከተቀባበሉ በኋላ ከዚያ ቀጥሎ ያለው ንባብ
“ወወሐብኮመ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ
ከመ ያምሥጡ እምገጸ ቅስት
ወይድኀኑ ፍቁራኒከ” የሚለውን ዲያቆኑ መስቀሉን ይዞ ከፍ ባለ ድምጽ አሰምቶ እንዲያዜም አደረጉ:: ይህም ማለት የችቦውን
ዘዴ እንደመከላክያ ጋሻ አርገን እንድንጠቀምበት አስተማርከን:: ከጣላቶቻችንም ጋራ ፊት ለፊት ተጋጥመን ጠላት ከሚወረወርብን ጦር
እናመልጥ ዘንድ የችቦውን መብራትና የምንጠቀምበት ሰአት ገለጽክልን የሚለውን መንፈስ የያዘ ነው:: የታሪኩ መነሻ በተብራራ
ሁኔታ ለሕዝብ አልተነገረም እንጅ ይህ እስከ ዚህ የገለጽኩት ሁሉ በያመቱ በየደመራው በዓል ላይ አመታዊ ሥርዓት ሆኖ ይካሄዳል::
አምና ለዘመነ ሉቃስ “የተወደደችውን
የጌታን ዓመት እንስበክ” በሚል ርዕስ ባቀረብኳት
ጦማር (http://www.medhanialemeotcks.org/pdf/ethiopian_new_year_zemene_lukas.pdf) ስለ መንፈሳዊው አባት ሚና ስገልጽ፥ “አምላኩን
ወዶ ለማስወደድ፥ ሃይማኖቱን አክብሮ ለማስከበር፡ በህዝባዊ ፍቅር ልቡ የነደደ፥ ቅዱስ ተብሎ የተሰየመ አባት፡ የምሕረት ምንጭ በሆነው
አምላክ ስም፡ በሚያቀርበው የምሥራች ቃል:: ዘመኑን ባርኮ ለሥጋውያን መሪዎች አውደ ምህረቱ ይለቅ ነበር” እንዳልኩት፥
በደመራው በዓልም፥ የሚቃጠልበት የእሳት ምንጭ በካህኑ እጅ ያለው ችቦ ነው:: መጀመሪያ “ደምረነ
ምስለ እለ ይድኅኑ” ብሎ የሚጸልየው ያካባቢው ካህን የመጀመሪያዋን እሳት በእጁ ባለው ችቦ ላይ ይጭራታል:: ካህኑ ካቃጣላት
ችቦ ላይ የአገሪቱ ሥጋዊ መሪ በራሱ ችቦ እሳቱን እንዲለኩስ ይፈቅድለታል::
የአገሪቱ መሪም እሳቱን በካህኑ እጅ ላይ ካለው ችቦ በችቦው ለኩሶ በደመራው ላይ መለኮሱን ይመራል:: በተዋረድ የተከበሩ የአገር
ሽማግሌዎች ይቀጥላሉ:: ከዚያ ጎረምሳው፥ ኮበሌው ወጣቱ እሳቱን በችቦው እየተቀባበለ ወደ ደመራው እየወረወረ የጀግንነት ምልክቱን
ብትር ከፍ አድርጎ ይዞ ሆ! እያለ ደመራውን ይዞራል::
ቁርጥ የሚባል ስም ተሰጥቶት ጥሬ ሥጋ መብላት የተጀመረውም በዚሁ ዘመን ነው:: በሌሎች ክፍላተ ሐገሮች የሚደረገው
ተመሳሳይ መሆኑንና አለመሆኑን ባላውቅም፥ ባደግኩበት አካባቢ ቁርጥ ሥጋ ወንዶች ብቻ ሲበሉ እንዳየሁ ሁሉ፥ በደመራው በዓልም ዳቦት(ችቦ)
አብርተው ከቤት የሚወጡት ወንዶች ብቻ ናቸው:: ወንዶች ብቻ የሆኑበትን አባቶች ሲናገሩ እንደሰማሁት፥ “ብርሃን ዘበ አማን ዘያበርህ ለኩሉ ሰብዕ” የተባለው በጨለማ ለነበረው ዓለም ያበራው፥
ያለ ወንድ ዘር ወንድ ሆኖ የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው::
እመቤታችን “እመ ብርሃን (የብርሃን እናት) ምሥራቅ (መውጫ)” እንጅ ብርሃን አይደለችም:: ይሁን እንጅ በማሕጸኗ
አድሮ ወልዳው በሄደችበት ሁሉ ታቅፋ ያቋረጠችውን ዘመን በደመራው በዓል ይታወሳል:: በደመራው በዓል አጋጣሚ ሆኖ የቤቱ ባለቤት በሞት ወይም በሆነ ነገር በቤት ውስጥ ከሌለ፥ በእናቱ እቅፍ ያለ
ወንድ ሕጻን በእናቱ እጅ ችቦውን (ዳቦቱን) እያበራ ከቤት ይወጣል:: ሴት ብቻ ከሚኖሩበት ቤትም፥ ከጎረቤት ወንዶች ልጆች አንዱ
አብርቶ እንዲወጣ የሚደረገውም ይህን ለማስታወስ ነው::
ከፖርቹጋሎች ጋራ በተፈጠረው ታሪካዊ ክስተት ላይ፥ በዚያች ሌሊት ችቦ እያበራ ወጥቶ ፖርቱጋሎችን የደመሰሱት
ወንዶች ብቻ ስለሆኑ፥ የመታሰቢያነቱ ገጽታ ተለጥጦ መልኩን እንዳይለውጥ ሴቶች ችቦ አብርተው ከመውጣት ተቆጥበዋል:: ይህ በእሌኒ የተጀመረ በዓል፥ በኢትዮጵያውያን ከትውልድ ወደ ትውልድ እንደሐረግ እየዘመተ በቅኝ
ገዥዎች ሳይቆራረጥ በደማችን በምግባችን በስሜታችን ሳይቀር ተቀርጾ ለረዥም ዘመን በመቀጠሉ፥ የታሪክና የባሕላችንን ምዕራፍ እያሰፋ እስከኛ ዘመን ደርሷል::
ትውልድ በውጭም ሆነ ባገር በቀል ወራሪዎች ተወሮ፥ ተበታትኖና ቋንቋውን ታሪኩንና ባሕሉን እንዲረሳው
ካልተደረገ፥ ታሪኩ በግልጽ እየተነገረው በያመቱ የደመራው ሥርዓት ከቀጠለ፥ እየተፈራረቀ የሚገጥመውን ሁሉ እያባዛና እየደመረ ባህሉንና ታሪኩ
እየሰፋ ይሄዳል:: ይህ የደመራው በዓል ይዘቱን ሳይለቅ፥ ከታሪካችን ጋራ ያለው ጥምረት ለትውልዱ በግልጽ እየተነገረ እንዲቀጥል፥
ጠንካራ መመሪያ የመስጠቱ ኃላፊነት የመንፈሳዊና የፖለቲካ መሪዎች ቢሆንም፥ ከመንግሥት ይልቅ በላቀ ሁኔታ ኃላፊነቱ የሚመለከታቸው
ወላጆችንና፥ ሽማጎሌዎችን ነው::
የመጀመሪያዋን የደመራውን እሳት የሚለኩሳት ማነው?
“ደምረነ ምስለ እለ ይድኅኑ” የሚለውን
ሊጦን ጸልዮ ባርኮ የደመራዋን እሳት ለአገሪቱ መሪ የሚያቀብላት ካህን ማነው? ከካህኑ
ተቀብሎስ የደመራውን እሳት በማቃጠል የሚመራው የአገሪቱ መሪስ የትኛው ነው? ሥርዓቱን ተከትለው በእጃቸው ያለውን የደመራ ችቦ እያቀጣጠሉ
ወደ ደመራው መጨመር የሚችሉትስ ሽማግሌዎች የትኞቹ ናቸው?
መተርጉማን አባቶች በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፪ ቁጥር ፮
ላይ “ስድስቱ መሳብክት እለ እብን በዘ ያጥህሩ ቦቶን” ተብሎ በሚነበበው አረፍተ
ነገር፥ ታሪክን ሃይማኖትንና ባህልን ይገልጹበታል:: ክርስቶስ የቃናውን ውሐ ወደ ወይን የለወጠባቸው ጋኖች የተሠሩት “ዕብነ አልማስ” በሚባል ማዕድን ከቀለጠ ድጋይ ነው:: ይህ የከበረ ማዕድን ድንጋዩን ሰብስበው
ሲያቀርቡለት ያቀልጠዋል:: በሱም ድንጋዩን እያነጡጡ፥ እየላጉ፥ በፈለጉት ቅርጽ ይሠሩታል::
ሰውም ከምንቼትነትና፥ ከቶፋነት እየተላቀቀ ወደ ጋንነት ለመድረስ ማንጠጫ፥ መላጊያና መቅረጫ “ዕብነ አልማስ” አለው:: ለተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ የመጀመሪያውና ቀዳሚው “ዕብነ አልማስ”፥ መለኮቱን ከሥጋችን የደመረው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: ተከታዮቹም
ቅዱስ አትናቴዎስ “ቅትራተ ሐጺን ዘኢያንቀለቅል” ብሎ የገለጻቸው ሕዝቡ በእምነታቸው
በሞራላቸው አምኖ የሚሰማቸው ካህናት ናቸው:: ቀጥሎም “በሃይማኖት በታሪክና ባባሕል ምስክርነታቸው በእውቀትና በሞራላቸው በቤተ
ክርስቲያን ዙርያ የተሰለፉ ያገር ሽማግሌዎች ናቸው” ይላሉ ሊቃውንት አበው:: ሲያብራሩትም፥ ሕጻን ሃይማኖት ታሪክና
ባህል ይዞ አውቆና ተምሮ ከናቱ ማህጸን አይወጣም:: ክርስቶስ እንዳለውም በሥጋ አልሚ ምግብ በዳቦ ብቻ ሰው አያድግም::
Fast Food Nation እንዳይሆን ማለት ነው:: ትውልድ ሃይማኖቱን፥ ታሪኩንና ባህሉን ለይተው በተረዱ ባባትና እናት፥ በሐገር
ሽማግሌዎችና በመንፈሳዊውያን መሪዎች እየተነጠጠ፥ እየተላገና እየተቀረጸ ማደግ አለበት::
ከካህናትና ከፖለቲካ መሪዎች በመቀጠለ የነ አብርሃምን የነ ይስሐቅንና የነ ያዕቆብን
ምሳሌ የያዙ ዕብነ አልማሶች የሚባሉት ያገር ሽማግሌዎች
ነበሩ::
በፖርቹጋሎች ምክንያት ምዕራፉን አስፍቶ ከኛ ዘንድ የደረሰው የመስቀሉ በዓል፥ እምነትና ሞራል ተንተርሰው፥ እውነትን እየፈለጉ ያለፉትን
ከእሌኒ በፊት የነበሩትንና በዓለም ያሉትን ሁሉ አርበኞች ዕብነ አልማሶች እያልን እንድናስታውሳቸው አድርጎናል:: ለምሳሌ “ተዘከሮሙ እግዚኦ ለኩሎሙ አበዊነ ወአኀዊነ ወአኃቲነ እለ ኖሙ ወአዕረፉ በርትዕት ሃይማኖት ወደምር ነፍሳቲሆሙ ውስተ ሕጽነ አብርሃም ይስሐቅ ወያዕቆብ”
ማለትም፥ “ሳይወላውሉ በቀናች እምነት ጸንተው ለወገናቸው ለነጻነታቸው መስዋዕት እየከፈሉ
ያለፉትን አባቶቻችንን፥ ወንድሞቻችንን እናቶቻችንና እኅቶቻችንን በአብርሃም በይስሐቅና በያዕቆብ ሕጽን አንድ ላይ ሰብስብልን” እያልን በቅዳሴያችን
እንጸልያለን::
እነ አብርሃምን ዕብነ አልማሶች
የምንልበትን ምክንያት፥ በኢትዮጵያ መንበር ላይ ቆሞ የሚቀድስ ካህን ሁሉ ክህነቱን ከመቀበሉ በፊት ከሊቃውንት ሊማረውና ጠልቆ ሊረዳው
ይገባዋል::
“በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ” ተብሎ ለአብርሃም ወንጌል የተሰበከለት፥ “ወበጽሖሙ ሌሊተ ምስለ ደቂቁ ወቀተሎሙ ወዴገኖሙ እስከ ባኮር እንተ እምጸጋማ ለደማስቆ”( ዘፍ ፲፬፡
፲፭) ማለትም፥ “አብርሃም አርበኞቹን አሰልፎ በእምነት ተሰልፎ ድልን ከተጎናጸፈ
በኋላ ነው:: እነ ያዕቆብንም ቅዳሴው የሚያነሳሳቸው “ወለዛቲ ምድር እንተ ወሀብኩ
ለአብርሃም ወለይስሐቅ ለከ እሁበከ ወለዘርእከ እምድኅሬከ” (ዘፍ ፴፭፡፲፪-፲፬):: ከሚለው ባሻገር “ወአቀመ ያዕቆብ ሐውልተ ውስተ ውእቱ ብሔር ኀበ ተናገሮ”(፴፭፡፲፬) ማለትም፥ “ያዕቆብ እግዚአብሔርን ባናገረበት
ቦታ ላይ የድንጋይ ሐውልት አቆመ” የሚለውን ገጸ ንባብ መሠረት በማድረግ ነው::
ያዕቆብ እግዚአብሔርን ባናገረበት ቦታ ሐውልት ያቆመበት ምክንያት፥ ቦታውን ቤተ-ኤል (የእግዚአብሔር
ቤት) ለማለት እንጅ፥ እንደ ዘመናችን ፓትርያርክ፥ እንደ ማክዶናል ፋስት ፉድ እየተገላበጡ ትላንት ሌላ ዛሬ ሌላ ከሚናገሩትና ከሚያደርጉት ጋራ በመገለባበጥ የራስን ቅርጽና ዝና በህዝቡ ልቡና
ለማስረጽ አይደለም:: ያዕቆብ የተከለው ድንጋይ ያነበበውን ሁሉ እስከኛ ዘመን ድረስ እየናጠጠና እየላገ ያለና የሚቀጥል ነው::
በዚህ ታሪካዊ ባሕርያቸው እነ ያዕቆብን መጽሐፈ ቅዳሴያችን ይጠቃቅሳቸዋል:: ቅዳሴያችን “ወለነኒ
አድኅነነ እምኩሉ አበሳ ወመርገም ወእምኩሉ ጌጋይ ወእምኩሉ ክሕደት ወእምኩሉ መሐላ በሐሰት ወእምኩሉ ግዘት ወእምተደምሮ በዕልወት ወርኩስ ምስለ ዓላውያን ወአረማውያን” በማለት ከከሐዲዎች ከሸፍጠኞችና ከአስመሳዮች
ጋራ ከመደመር እራሳችንን እንድንጠብቅም በጽኑዕ ያሳስበናል::
ይሁን እንጅ ያገር ሽማግሌዎች በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት እራሳቸው እየተነጠጡ ካላደጉ፥ የሰውነታቸው
እርጅና የጸጉራቸው መሸበት ብቻ የአገር ዕብነ አልማስ ሊያደርጋቸው አይችልም:: ይልቁንም በእርጅናቸውና በሽበታቸው ጎጠኝነትን፣መንደርተኛነትንና፣ ሸፍጠኛነትን በመስበክ የሚከተላቸውን
ትውልድ ፈጣን ምግብ (Fast Food Nation) የሚያደርጉ የሕብረተሰብ ነቀርሳዎች ስለሆኑ፥ ትውልዱ የሚያደርጉትንና የሚናገሩትን
በጥንቃቄ ሊያጤነው ይገባል:: “ፍልሰታ” በሚል ርዕስ ያቀረብኳት ጦማር ይመልከቱ::(http://www.medhanialemeotcks.org/pdf/Filseta%20Final.pdf)
ጊዜ ሲበላሽ የሀገር ሽማግሌዎች ከደመራ
ሆታ ባሻገር የደመራውን ምሥጢር ለመረዳት የተሳናቸው ሕጻናት ይሆናሉ:: ይህን ሳያስተውሉ ስለደመራው በዓል የሚሰብኩ፤ የደመራውን
ችቦ ባርከው እሳቱን የሚለኩሱ ካህናትም፥ ከሆታው ባሻገር ያለውን የደመራውን ምሥጢር ከሊቃውንት አበው ሰምተውት ካላወቁ፥ ከሕጻነ
አዕምሮ ገና ያልተላቀቁ ይሆናሉ:: ለደመራው ምሥጢር ተቃራኒ የሆኑትን ቅነሳንና
ከፈላን ለሚያርምዱ አጫፋሪ በመሆንም ሆባዮች ይሆናሉ:: (በግዕዝ ሆባይ ማለት ዝንጀሮ ማለት ነው)
ችቦ አብርቶ ትኋንን ውጪ፥ ቁንጫን ግቢ
ለማለት መጀመሪያ በደመራው እንጨት ውስጥ መወከልን ይጠይቃል:: ቀጥሎም የሚያበራው ችቦና የሚያቃጥለው የደመራው እሳት፥ ተቃራኒ
በመሆን ለመክፈልና ለመቀነስ የመጣውን የፖርቱጋሎች ስሜት የተሸከመውን የሚያቃጥል፥ ከሰልና አመድ የሚያደር፥ በእምነታቸው በሞራላቸው
ጸንተው ለቆሙት ኢትዮጵያውያ ግን የሚያበራ፥ የሚያሞቅና የሚያደምቅ እሳት መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል::
ከችቦውና ከደመራው ጋራ አብራ የገባች በአጥርና በዛፍ ስር የምትበቅል በአማርኛ አሽክት (ትድምርት ዘእንበለ ፍልጠት) በትግርኛ
ጸጎጎት
የምትባል ጥልቅ ትርጉም ያላት ሐረግ አለች:: ይሕች ሐረግ መረሳት የሌለባት በዚያ ዘመን ትልቅ ሚና የተጫወተች ናት:: ፓርቹጋሎች
አንድነታችንን አፍርሰው ሊለያዩን አይችሉም በሚል ጽኑዕ ውሳኔ የተስስማማ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ዘመቻው ከመጀመሩ በፊት እንደ ልዩ መግባቢያ
ሆና አገልግላለች:: እኔ ካገር ቤት የመጨረሻውን ደመራ አክብሬ ወደ ደብረ ሊባኖስ እስከሄድኩበት ዘመን ድረስ ልጆች ሆነነ በራሳችን
እናደርጋት ነበር:: እናቶችና ሽማግሌዎች ደግሞ ለቁርጥማት መድኃኒትነት አላት እያሉ በደመራው አመድ ላይ ጎዝጉዘው ይቆሙባት ነበር:: የደመራው
እንጨት እርጥብና ደረቅ ነው:: “በርጡብ እጽ ለእመ ኮነ ከመዝ እፎ በይቡስ”
እንዳለው ክርስቶስ፥ ርጥቡ እንጨት ባሕርዩን፥ እሱነቱን ያልቀየረ፥ በቀላሉ ለእሳት ያልተጋለጠ ወገን ነው:: ቢጎዳም ለወገን ነው::
የሚወክለው ቁርጠኛውን ዜጋ ነው:: ደረቁ እንጨት ባሕርዩን የቀየረውን፥ እራሱን ከወገኑና ከታሪኩ አግልሎ አድር ባይና ወላዋይ የሆነውን፥
በአስመሳይና በሸፍጠኛ ባሕርዩ ከፖርቹጋሎች ጋራ የወገነውን ዜጋ ይወክላል::
“አጓጉረውና እርጥቡን
ከደረቅ፥
እዚያው ጤሶ ጤሶ እዚያው ነዶ ይለቅ” የሚለው ሽለላ (ቅራርቶ) የመነጨውም ከዚህ
ነው
ይባላል::
የደመራው በዓል ይህን አስደናቂ ምሥጢር ያዘለ ከሆነ፥ “ደምረነ ምስለ እለ ይድኅኑ” ብሎ ይህን ምሥጢር በቃሉ ያስተማረ፥ በተግባሩ ያከናወነ የደመራዋን
እሳት ችቦ የሚባርካት በዘመናችን የትኛው ካህን ነው? ከካህኑ ለኩሶ ደመራውን በመጀመሪያ የሚያቀጣጥለው መሪስ የትኛው ነው? ወጣቱንስ
በየመንደሩና በየቤቱ በዚህ ኢትዮጵያዊ እምነት ታሪክና ባሕል የሚቀርጽ፥ የሚልግና የሚያስተካከል የትኘው ያገር ሽማግሌና የቤተ ሰብ
ሐላፊ ነው?
ዛሬ ከመቸውም ዘመን በከፋ ሁኔታ የተዋሕዶውን ሃይማኖት አፍርሰው፥ በፖርቹጋላዊ ከፈፋይ መንፈስ ለመተካት
የሚታገሉ አስመሳዮች ደፍረው ወደ ቤተ መቅደሳችን የገቡበት ዘመን አይደለምን? ከሃይማኖቱ፥ ከታሪኩና ከባሕሉ ይልቅ ለመንደርተኝነት
ቅድሚያ በመስጠት ከሀዲዎች መሆናቸውን እያወቁ ድጋፍ ለመስጠት ሽንጣቸውን ገትረው የተነሱ ሽማግሌዎች የተከሰቱበት ዘመን አይደለምን?
በአገሩቱ ላይ የሚካሄደውንስ የፖለቲካ ዘይቤ ስንመለከተው በአድዋ ላይ ሥር ሰዶ የነበረው
“ዓኾ ዓኾኋይ ሆይ ሆያዬ ንጎናይ በርሆ” በማለት ኢትዮጵያውያን ያባረሩት
ፖርቹጋላዊ የፖለቲካ መርሆ፥ ዛሬ መልኩን ለውጦ በነ አቶ መለሰ አማካይነት ኢትዮጵያን የተቆጣጠረበት ዘምን አይደለምን?
እነዚህ ካላይ በጥያቄ ያቀረብኳቸው መጠይቆች፥ እውነትም የወቅቱ መጠይቆች ናቸው ብለን ተስማምተን ከተቀበልናቸው::
የቀደሙ ሊቃውንት አበው በመጽሐፈ መሳፍንት ምዕ ፱ ከቁጥር ፳ ላይ የሰፈረውን “ለትጻዕ እሳት እምቤተ አቤሜሌክ፥ ከመ ትብላእ አብያተ
ሴኬም፡ ወትሜሎም:: ወለእመ አኮ እሳት ትጻእ እምቤተ ሴኬም ወትሜሎም ከመ ትብላዕ ቤተ አቤሜሌክ” የሚለውን ተመርኩዘው፥ ማለትም
“እኛ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራችን የተደጋገመ ግፍ እየተፈጸመብን ነው:: ይህች ከኢትዮጵያውያን ቤት እየተጫረች የምትወጣ የዘንድሮው
መስቀሉ በዓል እሳት፥ በሸርና በሸፍጥ በእርዳታ ስም መጥተው የወረሩንን ፖርቱጋሎችን ትብላ፥ ለአገራችን ለነጻነታችን መታገላችን
በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አጥቶ ረድኤቱን ከነፈገንም፥ ለዘላለም በፖርቱጋሎች ሥር ተጠቅተን ከመኖርና ለልጆቻችንም የተገዥነትን
ውርስ ከማውረስ ይሕች ከየቤታችን የጫርናት እሳት እኛኑ ትብላን” ብለው ቆርጠው የተነሱበትን ያባቶችን መንፈስ ልንቃኘው ይገባናል::
የጥንት ኢትዮጵያውን ችቦውን አንድ ላይ አስረው፥ እንጨቱን አንድ ላይ ደምረው ያቃጠሉት፥ ዛሬ እኛ
እንደምናደርገው በጎሳ በቋንቋ፥ በሃይማኖት፥ ከውጭ ሠርሥሮ በገባ ሃይማኖትና በተለያዩ የፖለቲካ ትርጓሜ በመለያየት አልነበረም::
ደመራውን ችቦውን ትንሿን አሽክት እንኳ ሳይቀር ላንድነታቸው ምልክት በመጠቀም ነበር:: እግዚአብሔር “ደምረነ ምስለ እለ ይድኅኑ” እያሉ የደመራውን እሳት የሚያበሩ ካህነት፥ “ትኋን ውጭ፡ ቁንጫ ግቢ” እያሉ የደመራውን ችቦ የሚያበሩ ሽማግሌዎች፥ የካህኑንና የሽማግሌዎችን ምኞት በሆታ የሚያስተጋባ ትውልድ
እንዲፈጠር እንጸልይ::
ለዚህ ዓመት የደመራ በዓል ያደረሰን አምላክ፥ ለከርሞውም በሰላምና በጤና ጠብቆ ያድረሰን::
ለሌሎች ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ጦማሮች የሚከተለዉን ድህረ-ገጽ ይመልከቱ::
ሚስተር ቤንጃሚን የኢሜል ዝርዝሮችን እነሆ ፣ Lfdsloans@outlook.com ፡፡ / ወይም ደግሞ ንግዴን ለመጀመር በ 90,000.00 ዩሮ ብድር የረዳኝ WhatsApp + 1-989-394-3740 እና እኔ በጣም አመስጋኝ ነኝ ፣ እዚህ አንድ ነጠላ እናት ነገሮች እንዳላደረጉ መንገድ ለመፍጠር እየሞከርኩ ነው ፡፡ ከእኔ ጋር ቀላል ይሁኑ ግን ንግዴ እየጠነከረ ሲመጣ እና እያሰፋ ሲሄድ እያየሁ በሚስተር ሚስተር እርዳታ ፊቴ ላይ ፈገግታ አሳየኝ ፡፡ የገንዘብ ድጋፍን መፈለግ ወይም በዚያ ንግድ ውስጥ መከራን ማለፍ ወይም የመነሻ የንግድ ሥራ ፕሮጀክት መጀመር መፈለግ ይህንን ማየት እና ከችግራቸው ለመውጣት ተስፋ ሊኖረው ይችላል ... እናመሰግናለን ፡፡
ReplyDelete