Tuesday, 20 September 2011

ሰራዊቱ፤ ከምድር ጦር እስከ አየር ሀይል

ሰራዊቱ፤ ከምድር ጦር እስከ አየር ሀይል

ተሾመ ተንኮሉ፡ አየር ኃይል


ባለፈው ሰሞን፡ የአንጋፋው የኢትዮጵያ ስፖርት ፎደሬሽን በሰሜን አሜሪካ፡ በአረብ/አበሻው ቱጃር ሰበብ ታምሷል መባሉን ሰምቼ፤ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ አነስ ያለች ፅሁፍ ለዘወትር ወዳጄ ብሰድለት፤ በሃሳቤ መለስለስ ነው መሰለኝ ብዙም ሳይደሰት፤ “ወያኔን እየደጋገሙ ነጋ ጠባ መውቀስ ብቻውን ጠላት ከማብዛት በስተቀረ ማንንም አይጠቅምም” ብሎ ጽሁፌን ገፋብኝ። የወዳጄ የትችት መንፈስ፡ እንደ ጥቂት የዘመኑ ወገኖቻችን ከወያኔ የጥቅም በረከት መግዣ፡ ጭራ መቁላት ሆኖ አልተሰማኝም የእሱ አቋምወሬው ይቁምና የወያኔ እሳት ሁላችንንም አቃጥሎ ሳይጨርሰን ሰደዱን ወደ እራሱ ወደ ወያኔ መንደር እንመልሰውነው። እውነት ብሏል!
እንግዲህ ማን ቀረ ? አለቅን እኰ ጐበዝ !! በዛ፡ በጣም በዛ። ሰዎቹ ልክ አጡ።

ሕወሀት/ወያኔ እንደሆነ የእያንዳንዳችንን ቀዬና ጓዳ በሰደድ እሳቱ እያዳረሰው ነው እኔን አይንካኝ እንጂ ረሃቡም እየጠበሰኝ ቢሆን ይህችን ከሙታን መንደር የገባች እስትንፋሴን ባቆያት ይሻላል” የምንል ካለን ይህም መንገድ የሚያዋጣ አልሆነም አያ ጅቦ  ቋሚውን እንደጨረሰ ወደ ሙታን ሰፈር መዝመቱ እንደማይቀር አያያዙ ያስታውቃል

በሰሞኑ የአዲስ አመት እስራት የተነሳ ልብ ብዬ ነገሮችን ሳስተውል፡ የአንዳንዶቻችን የዋህነት ይገርመኛል። ስለዚህ ስለወያኔ ተፈጥሮ ከራሴ ተሞክሮ አንዳንድ ነገር ማለት ፈለግኩ። ወያኔነት የደምና የዝርያ ማደሪያ እንጂ በታማኝ አገልጋይነት ብቻ ዘላለማዊ መጠለያ እንደማያስገኝ ዛሬም ከሃያ አመታት በኋላ እንኳ ለመረዳት ያለመፈለጋችን ነው ለዚህ ደግሞ ትላልቆቹ እነ አቶ ታምራት ላይኔም ሆኑ / ነጋሶወዘተ ቋሚ ምስክሮች ናቸው

ሞቶ መነሳት በሚለው አጭር የሰቆቃ ትረካዬ፡ http://www.ethiopianreview.com/2007/aug/moto_menesat_sene1999.pdf የወያኔን የአፈናና በሚስጢራዊ የምድር ስር የጨለማ ማጐሪያው ለሁለት አመታት ያደረሰብኝን መከራና ስቃይ በህያው ምስክርነት ማቅረቤ የታወሳል ግርም የሚለኝ ግን ከአፈናው በፊት ወያኔ ያለኝን ሙያ ለመጠቀም በማደርያው በምቾት አቆይቶኝ እንደነበረ ነው ለአገሬ ነው የምሰራው በሚል እምነት፡ በብቃትም ያለብቃትም የመለመላቸውን የአንድ ዘር ምልምል ተማሪዎችን፡ በበረራ ሙያ በማሰልጠን በአየር ኃይል በበረራ አስተማሪነት እስከ ግንቦት 1998 መዝለቄ ይታወቃል በኋላ ግን የተከፈለኝ ወሮታ ለሰብዓዊ ፍጡር የሚገባ አልነበረም ዳሩ አያጅቦ ደግ ስለሰራህለት ብቻ  ወዳጁ አያደርግህም ወያኔ መንግስት ሳይሆን የደምና የዘር ማደሪያ ነው ብዬ አልነበር ! ልክ ነኝ ማለት ነው …. ዘሩ ካልሆንክ መቼም የሱ አትሆንም። ይሄ አባባሌ ከላይ ካልኩት በላይ ተለጥጦ እንዳይተረጎም። በመጨረሻ ወያኔ ለራሱም ዘር የሚበጅ አይደለምና።

ወያኔ እንደ ጅብ ነው እንደ አውሬ። አንድ ቀን የፈራ እለት ይበላሃል ሲበላህም በጭካኔ ነው ….. በስቃይህ ይፈነድቃል። የእራሱ ደምና ዝርያ አይኑርብህ እንጂ ከእነ እውቀትህና ከእነ ሙያህም ቢያጠፋህ ፀፀት አይገባውም ለእሱ መንደሩ እንጂ ኢትዮጵያ እንደ አገር ሚዛን አትደፋም ። ለነገሩ የራሱንስ ሰዎች እየበላ አይደል እንዴ እዚህ የደረሰው ?!

አያ ጅቦ  አፍኖ ከደበቀህና አንደበትህን ከለጐመህ በኋላ ስም ያወጣልሃል እራስህን መከላከል በማትችልበት ሁኔታ ላይ ከህዝብ ሊያጣላህ ይሞክራል ብዕር ጨብጠህ ውለህ እንደምታድር በአደባባይ እየታወቀ እንኳ ሽብርተኛ እያለ ስም ይለጥፍልሃል …… አለም ላይ ያለን ሰው ሁሉ  በድርቅና ሊያሳምን ይጥራል ምናምኒት ይሉኝታ አልፈጠረበትም ። የሚያስገርመው ግን ዛሬም ከሃያ አመታት በኋላ፡ አንዳንድ ሰዎች ከጅብ ተርታ ተሰልፈው የራሳቸውን የወገኖቻቸውን ሥጋ ሊበሉ ሲሻሙ ማስተዋል  ያስተዛዝባል ስለዚህም ለሰራዊቱም ትንሽ መልእክት መስደድ ወደድኩ።

ይህ መልእክቴ በተለይ ለሰራዊቱ ነው። ሰራዊቱ ማን ላይ እንደሚተኩስ ደግሞ ደጋግሞ ሊያስብበት ይገባል በችጋር እየተጠበሱ ያሉትን ዘመዶቹንወገኖቹንእናቱንአባቱንወንድምና እህቱን …. ልጆቹን …… ጓደኞቹንና የአደገበትን ቄዬና የሰፈር አዛውንቶችን ሊታደግ ይገባዋል ። የእኔን የአስተማሪያቸውን የግፍ የአፈና ሰቆቃ የሰሙና የተገነዘቡ የበረራ ተማሪዎቼ አምፀዋል እልም ብለውም ስርዓቱን ጥለው ተሰደዋል እነዚህ በራሪዎች፡ ከፍተኛ የአገሪቱ አንጡራ ሃብት የፈሰሰባቸው ናቸው …. አንድ ሁለት አይደሉም ከሃያ በላይ ወጣት ተዋጊ በራሪዎች …. ኪሳራው ምን ያክል ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም ግን የህዝብ ነን ያሉ ቁርጠኛ ወጣቶች ናቸው የህዝባቸውና የአገራቸው ፍቅር እንጂ፡ ዘራቸው አላሸነፋቸውም። በአያ ጅቦ መንደር መቦረቁ ጊዚያዊ ደስታ እንጂ ዘላለማዊ እንዳልሆነ ተገንዝበዋል አያ ጅቦ የፈራ ዕለት እንደማይለቃቸውም አውቀዋል በእኔ የደረሰው ስቃይ በእነሱ እንደማይደርስ ማረጋጋጫ አጥተዋል

የቅንጅትን ድል ተከትሎ በአዲስ አበባ ጐዳና ላይ የተከሰተውን የጅምላ ግድያ ተባባሪ ላለመሆን  / በኃይሉ ገብሬና / አብዮት ማን ጉዳይ የጦር ሄሊኮፕተራቸውን ይዘው ስደትን መርጠዋል በዚህ አድራጎታቸውም የህዝቡንና የሰራዊቱን አንድነትና ዝምድና አስመስክረዋል ለተቀሩትም የሰራዊቱ አባላት ትልቅ ምሳሌ ሆነዋል

በምድር ላይ፡ ሰው አንድ ብቻውን አይደለም። ወያኔ አንድን ሰው በግፍ ሲያስር እና ሲገድል የሰውየውን እናት አባት ወንድም እህት ልጅ፣ ጓደኛ …. በአጠቃላይ ወገኖቹን ሁሉ እንደሚያስከፋ ልብ ሊል ይገባል ለዚህም ነው አየር ኃይሎቹ / በኃይሉ እና / አብዮት ያልታጠቀ ህዝባችን ላይ አንተኩስም ብለው እራሳቸውን ለመስዋዕትነት አሳልፈው የሰጡት ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ወጣት በራሪዎችም ለስርዓቱ አንገዛም ብለው መኰብለላቸውም የዚሁ ምሳሌ አካል ነው እንደ እነዚህ ያሉ ለህዝብ ዘብ የቆሙ የታጠቁ ወታደሮች ዛሬም በሰራዊቱ ውስጥ መኖራቸው በፍፁም አጠራጣሪ ሊሆን አይችልም

በወያኔ መንደር ተተክለው ፍሬ ሣያፈሩ እንደጠወለጉ ከጠፉት መካከል ታምራት ላይኔን የመሰለ የለም ዛሬ ፊታቸውን ከሞት በኋላ ላለችው ህይወታቸው ንሰሃንና ፅድቅን ፍለጋ ቢያዞሩም፡ የገዛ ህዝባቸውን ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ እንደ ወያኔዎች ቀመር እንኳ ቢሆን፡ እወክልሀለሁ ያሉትን የመንደራቸውን ሰው፡ አማራውን፡ ሳይታደጉ የስልጣን ዘመናቸው እንደ ንፋስ ማለፉ ሳይፀፅታቸው እንደማይቀር የታወቀ ነው ስለዚህ እነሆ ባለተራአርቲፊሻልባለስልጣናት፡ የዛሬዎቹ ታምራት ላይኔዎች፡ እነ ሀይለማሪያም ደሳለኝ፡ እነ አዲሱ ለገሰ፡ እነ ሬድዋን ሁሴን፡ እነ ሽመልስ ከማል፡ ሳይመሽ ከአሁኑ የህዝባችሁ ተገን እንድትሆኑ እንደሚገባ ከቀድሞው ባለስልጣን ትምህርት መውሰዱ አማራጭ የማይገኝለት ይሆናል

የወያኔ ባህርይ ትንተና ይቀጥላል። ወያኔ ሊጠቀምብህ ሲፈልግ እንደ ድመት ፀጉሩን አለስልሶ ስርህ ይነጠፋል ረዥም መወጣጫ መሰላልም ያቀርብልሃል፤ በመሰላሉም ተጠቅመህ እጅግ ወደ ላይ እንድትወጣና ከፍ ብለህ እንድትታይ ያደርግሃል እንዲመችህም ይጥራል …. እናት እና አባትህን ሚስትና ልጆችህንም ጭምር እልም አድርገህ እስክትረሳቸው ድረስ ይስፈነድቅሃልበሀብት ላይ ሀብት፡ በሚስት ላይ ሚስት፡ በስልጣን ላይ ስልጣን ይሰጥሀል፤ ግና ቡረቃው ብዙ አይዘልቅም ….  የአገልግሎት ዘመንህም ማለቁን  ከወያኔ በቀር  እራስህም አታውቀውም ወደ ላይ የወጣህበትን መሰላል ቀስ ብሎ  ከስርህ ዞር ሲያደርግብህ ትባንናለህ በከበሮና በጭፈራ ከፍ ብለህ የወጣሃውን ያክል አሁን በተቃራኒው በሰላም መውረጃ ታጣለህ ከፍ ብለህ እንድትታይ የወጣህበት ከፍታ ላይ ሆነህ በሽብር በጭንቀትና ብፍርሃት ስትርድ ሁሉም ሰው እንዲያይህ ያደርግሃል ከዚያም ገፍትሮ ይጥልሃል ወይም ዞር ብለህ ስታይ፡ የወጣህበት መሰላል ተነስቶብሀል። አበቃ ማለት ነው ያንተ ነገር

ማነው እሱ “የወያኔ ስልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው” ያለው? ስልጣንህ የዛፍ ላይ እንቅልፍ አይነት ናት ሸለብ ካደረገህ  ከዛፉ ላይ መውደቅህ አይቀርም …. ከወደቅበት መነሳት ከቻልክ የታደልክ ነህ …. ብዙዎቻችን ግን አልቻልንም ! ይህንን ሁሉ የማወራው ለዘመኑ ባለተራ ባለስልጣናት ነውለሰራዊቱም አባላት ጭምር ቤተሰብ .. ህዝብና ወገንን ከመታደግ የበለጠ ነገር የለም

ያ ነው የወያኔ ተፈጥሮ። የወያኔን ሀጢያት ታውቁታላችሁ። እንግዲህ ሃያ አመታት ሙሉ ለአገር የሚጠቅሙ የሃገር ሃብት የሆኑ ዜጐችን አጥተናል ወያኔ እነ ፕሮፌሰር አስራትን የመሳሰሉ እውቅ ባለሙያ፡ እነአሰፋ ማሩን የመሳሰሉ ጎበዝ መምህራን አይናችን ፊት ቆረጣጥሞ ሲበላ ተመልክተናል ፍርሃት ይሁን ትዕግስት ብዞዎቻችን ዝምታን መርጠናል አንዳንዶቻችን፡ ሻማ ከማብራት ያለፈ የወሰድነው እርምጃ የለም እነ ፕሮፌሰር መስፍንን የመሳሰሉ ለምድር የከበዱ አዛውንት በጠመንጃ ሰደፍ አስደብድበናል …… ኢንጅነር ኃይሉ / ብርሃኑ ነጋ / ሀይሉ አርአያ፡ ያዕቆብ /ማርያም …… ወዘተ  የመሳሰሉትን ወያኔ በፈለገው ጊዜ አስሮ በአሰኘው ጊዜ ለቋል …. ብቸኛዋን መንፈሰ ጠንካራ ታጋይ / ብርቱካን ሚደቅሳን ከጨቅላ ልጇ እና ከአዛውት እናቷ ቀምቶ በጨለማ ጉድጓዱ ከነነፍሷ ቀብሯት ተመልክተናል። አሁኑም ከሻማ ማብራት የዘለለ ማድረግ ነበረብን ……… በቅንጅት ድል ዘመን የታየው የህብረት ክንድ ግን ለኢትዮጵያ አይደለም ለሌላውም ይተርፍ ነበር ስለዚህ የያዘን ፍርሃት ነው የሚል እምነት የለኝም

እነሆ ያ ሁሉ ሆነና፡ ወያኔ ዛሬም ብዕር ያነገቡ ጋዜጠኞችንና በሰላማዊ መንገድ ትግል የመረጡትን የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችን እያፈነ ወደ ጉድጓዱ ሰዷቸዋል …. እንደኔ ልምድ ከሆነ፡ እነሆ በዚህ ሰዓት የነጻነት ታጋዮቻችን፡ በእስር፡ በማእከላዊ ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው ይሆናል። ጎበዝ፡ በኢትዮጵያ ምድር ሰው በረሀብ እየተቀጣ፡ የእርዳታ ምግብ እየተከለከለ፡ ሕዝብ ለዘመናት ከኖረበት መሬቱ እየተፈናቀለ፡ እያለቀሰ ነው። እንባ፡ አንዳንዴም ደም እንደጐርፍ እየፈሰሰ ነው …. የህዝባችንን ሰቆቃና ግድያ ማቆም ያለብን በህብረት ነው ሰራዊቱም የህዝቡ አጋር መሆኑን ደግሞ ማረጋገጥ ይኖርበታል ….. የዓአማ አንድነት ያስፈልጋል። የድርጅት ጋጋታ ግን አያስፈልግም …. የቅንጅት ዘመኑ የህዝብ ማዕበል ለኢትዮጵያ አይደለም ለሌላውም ይተርፋል መቁረጥ ነው። ድርጅቶችም የናቴ መቀነት ጠለፈኝ ሰበባችሁን አቁሙና ወደተስፋይቱ ምድር ምሩን።


ቸር እንሰንብት

ተሾመ ተንኮሉ፡ አየር ኃይል፡ መስከረም፡ 2004/2011

No comments:

Post a Comment