Tuesday, 20 September 2011

ሰራዊቱ፤ ከምድር ጦር እስከ አየር ሀይል

ሰራዊቱ፤ ከምድር ጦር እስከ አየር ሀይል

ተሾመ ተንኮሉ፡ አየር ኃይል


ባለፈው ሰሞን፡ የአንጋፋው የኢትዮጵያ ስፖርት ፎደሬሽን በሰሜን አሜሪካ፡ በአረብ/አበሻው ቱጃር ሰበብ ታምሷል መባሉን ሰምቼ፤ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ አነስ ያለች ፅሁፍ ለዘወትር ወዳጄ ብሰድለት፤ በሃሳቤ መለስለስ ነው መሰለኝ ብዙም ሳይደሰት፤ “ወያኔን እየደጋገሙ ነጋ ጠባ መውቀስ ብቻውን ጠላት ከማብዛት በስተቀረ ማንንም አይጠቅምም” ብሎ ጽሁፌን ገፋብኝ። የወዳጄ የትችት መንፈስ፡ እንደ ጥቂት የዘመኑ ወገኖቻችን ከወያኔ የጥቅም በረከት መግዣ፡ ጭራ መቁላት ሆኖ አልተሰማኝም ። የእሱ አቋም “ወሬው ይቁምና የወያኔ እሳት ሁላችንንም አቃጥሎ ሳይጨርሰን ሰደዱን ወደ እራሱ ወደ ወያኔ መንደር እንመልሰው” ነው። እውነት ብሏል!
እንግዲህ ማን ቀረ ? አለቅን እኰ ጐበዝ !! በዛ፡ በጣም በዛ። ሰዎቹ ልክ አጡ።

ሕወሀት/ወያኔ እንደሆነ የእያንዳንዳችንን ቀዬና ጓዳ በሰደድ እሳቱ እያዳረሰው ነው ። “እኔን አይንካኝ እንጂ ረሃቡም እየጠበሰኝ ቢሆን ይህችን ከሙታን መንደር የገባች እስትንፋሴን ባቆያት ይሻላል” የምንል ካለን ይህም መንገድ የሚያዋጣ አልሆነም ። አያ ጅቦ  ቋሚውን እንደጨረሰ ወደ ሙታን ሰፈር መዝመቱ እንደማይቀር አያያዙ ያስታውቃል ።

በሰሞኑ የአዲስ አመት እስራት የተነሳ ልብ ብዬ ነገሮችን ሳስተውል፡ የአንዳንዶቻችን የዋህነት ይገርመኛል። ስለዚህ ስለወያኔ ተፈጥሮ ከራሴ ተሞክሮ አንዳንድ ነገር ማለት ፈለግኩ። ወያኔነት የደምና የዝርያ ማደሪያ እንጂ በታማኝ አገልጋይነት ብቻ ዘላለማዊ መጠለያ እንደማያስገኝ ዛሬም ከሃያ አመታት በኋላ እንኳ ለመረዳት ያለመፈለጋችን ነው ። ለዚህ ደግሞ ትላልቆቹ እነ አቶ ታምራት ላይኔም ሆኑ ዶ/ር ነጋሶ … ወዘተ ቋሚ ምስክሮች ናቸው ።

ሞቶ መነሳት በሚለው አጭር የሰቆቃ ትረካዬ፡ http://www.ethiopianreview.com/2007/aug/moto_menesat_sene1999.pdf የወያኔን የአፈናና በሚስጢራዊ የምድር ስር የጨለማ ማጐሪያው ለሁለት አመታት ያደረሰብኝን መከራና ስቃይ በህያው ምስክርነት ማቅረቤ የታወሳል ። ግርም የሚለኝ ግን ከአፈናው በፊት ወያኔ ያለኝን ሙያ ለመጠቀም በማደርያው በምቾት አቆይቶኝ እንደነበረ ነው ። ለአገሬ ነው የምሰራው በሚል እምነት፡ በብቃትም ያለብቃትም የመለመላቸውን የአንድ ዘር ምልምል ተማሪዎችን፡ በበረራ ሙያ በማሰልጠን በአየር ኃይል በበረራ አስተማሪነት እስከ ግንቦት 1998 መዝለቄ ይታወቃል ። በኋላ ግን የተከፈለኝ ወሮታ ለሰብዓዊ ፍጡር የሚገባ አልነበረም ። ዳሩ አያጅቦ ደግ ስለሰራህለት ብቻ  ወዳጁ አያደርግህም ። ወያኔ መንግስት ሳይሆን የደምና የዘር ማደሪያ ነው ብዬ አልነበር ! ልክ ነኝ ማለት ነው …. ዘሩ ካልሆንክ መቼም የሱ አትሆንም። ይሄ አባባሌ ከላይ ካልኩት በላይ ተለጥጦ እንዳይተረጎም። በመጨረሻ ወያኔ ለራሱም ዘር የሚበጅ አይደለምና።

ወያኔ እንደ ጅብ ነው ። እንደ አውሬ። አንድ ቀን የፈራ እለት ይበላሃል ። ሲበላህም በጭካኔ ነው ….. በስቃይህ ይፈነድቃል። የእራሱ ደምና ዝርያ አይኑርብህ እንጂ ከእነ እውቀትህና ከእነ ሙያህም ቢያጠፋህ ፀፀት አይገባውም ። ለእሱ መንደሩ እንጂ ኢትዮጵያ እንደ አገር ሚዛን አትደፋም ። ለነገሩ የራሱንስ ሰዎች እየበላ አይደል እንዴ እዚህ የደረሰው ?!

አያ ጅቦ  አፍኖ ከደበቀህና አንደበትህን ከለጐመህ በኋላ ስም ያወጣልሃል ። እራስህን መከላከል በማትችልበት ሁኔታ ላይ ከህዝብ ሊያጣላህ ይሞክራል ። ብዕር ጨብጠህ ውለህ እንደምታድር በአደባባይ እየታወቀ እንኳ ሽብርተኛ እያለ ስም ይለጥፍልሃል …… አለም ላይ ያለን ሰው ሁሉ  በድርቅና ሊያሳምን ይጥራል ። ምናምኒት ይሉኝታ አልፈጠረበትም ። የሚያስገርመው ግን ዛሬም ከሃያ አመታት በኋላ፡ አንዳንድ ሰዎች ከጅብ ተርታ ተሰልፈው የራሳቸውን የወገኖቻቸውን ሥጋ ሊበሉ ሲሻሙ ማስተዋል  ያስተዛዝባል ። ስለዚህም ለሰራዊቱም ትንሽ መልእክት መስደድ ወደድኩ።

ይህ መልእክቴ በተለይ ለሰራዊቱ ነው። ሰራዊቱ ማን ላይ እንደሚተኩስ ደግሞ ደጋግሞ ሊያስብበት ይገባል ። በችጋር እየተጠበሱ ያሉትን ዘመዶቹን … ወገኖቹን … እናቱን … አባቱን … ወንድምና እህቱን …. ልጆቹን …… ጓደኞቹንና የአደገበትን ቄዬና የሰፈር አዛውንቶችን ሊታደግ ይገባዋል ። የእኔን የአስተማሪያቸውን የግፍ የአፈና ሰቆቃ የሰሙና የተገነዘቡ የበረራ ተማሪዎቼ አምፀዋል ። እልም ብለውም ስርዓቱን ጥለው ተሰደዋል ። እነዚህ በራሪዎች፡ ከፍተኛ የአገሪቱ አንጡራ ሃብት የፈሰሰባቸው ናቸው …. አንድ ሁለት አይደሉም ፤ ከሃያ በላይ ወጣት ተዋጊ በራሪዎች …. ኪሳራው ምን ያክል ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም ። ግን የህዝብ ነን ያሉ ቁርጠኛ ወጣቶች ናቸው ። የህዝባቸውና የአገራቸው ፍቅር እንጂ፡ ዘራቸው አላሸነፋቸውም። በአያ ጅቦ መንደር መቦረቁ ጊዚያዊ ደስታ እንጂ ዘላለማዊ እንዳልሆነ ተገንዝበዋል ። አያ ጅቦ የፈራ ዕለት እንደማይለቃቸውም አውቀዋል ። በእኔ የደረሰው ስቃይ በእነሱ እንደማይደርስ ማረጋጋጫ አጥተዋል ።

የቅንጅትን ድል ተከትሎ በአዲስ አበባ ጐዳና ላይ የተከሰተውን የጅምላ ግድያ ተባባሪ ላለመሆን  መ/አ በኃይሉ ገብሬና መ/አ አብዮት ማን ጉዳይ የጦር ሄሊኮፕተራቸውን ይዘው ስደትን መርጠዋል ። በዚህ አድራጎታቸውም የህዝቡንና የሰራዊቱን አንድነትና ዝምድና አስመስክረዋል ፤ ለተቀሩትም የሰራዊቱ አባላት ትልቅ ምሳሌ ሆነዋል ።

በምድር ላይ፡ ሰው አንድ ብቻውን አይደለም። ወያኔ አንድን ሰው በግፍ ሲያስር እና ሲገድል የሰውየውን እናት ፣ አባት ፣ ወንድም ፣ እህት ፣ ልጅ፣ ጓደኛ …. በአጠቃላይ ወገኖቹን ሁሉ እንደሚያስከፋ ልብ ሊል ይገባል ። ለዚህም ነው አየር ኃይሎቹ መ/አ በኃይሉ እና መ/አ አብዮት ያልታጠቀ ህዝባችን ላይ አንተኩስም ብለው እራሳቸውን ለመስዋዕትነት አሳልፈው የሰጡት ። ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ወጣት በራሪዎችም ለስርዓቱ አንገዛም ብለው መኰብለላቸውም የዚሁ ምሳሌ አካል ነው ። እንደ እነዚህ ያሉ ለህዝብ ዘብ የቆሙ የታጠቁ ወታደሮች ዛሬም በሰራዊቱ ውስጥ መኖራቸው በፍፁም አጠራጣሪ ሊሆን አይችልም ።

በወያኔ መንደር ተተክለው ፍሬ ሣያፈሩ እንደጠወለጉ ከጠፉት መካከል ታምራት ላይኔን የመሰለ የለም ። ዛሬ ፊታቸውን ከሞት በኋላ ላለችው ህይወታቸው ንሰሃንና ፅድቅን ፍለጋ ቢያዞሩም፡ የገዛ ህዝባቸውን ፣ ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ እንደ ወያኔዎች ቀመር እንኳ ቢሆን፡ እወክልሀለሁ ያሉትን የመንደራቸውን ሰው፡ አማራውን፡ ሳይታደጉ የስልጣን ዘመናቸው እንደ ንፋስ ማለፉ ሳይፀፅታቸው እንደማይቀር የታወቀ ነው ። ስለዚህ እነሆ ባለተራ “አርቲፊሻል” ባለስልጣናት፡ የዛሬዎቹ ታምራት ላይኔዎች፡ እነ ሀይለማሪያም ደሳለኝ፡ እነ አዲሱ ለገሰ፡ እነ ሬድዋን ሁሴን፡ እነ ሽመልስ ከማል፡ ሳይመሽ ከአሁኑ የህዝባችሁ ተገን እንድትሆኑ እንደሚገባ ከቀድሞው ባለስልጣን ትምህርት መውሰዱ አማራጭ የማይገኝለት ይሆናል ።

የወያኔ ባህርይ ትንተና ይቀጥላል። ወያኔ ሊጠቀምብህ ሲፈልግ እንደ ድመት ፀጉሩን አለስልሶ ስርህ ይነጠፋል ። ረዥም መወጣጫ መሰላልም ያቀርብልሃል፤ በመሰላሉም ተጠቅመህ እጅግ ወደ ላይ እንድትወጣና ከፍ ብለህ እንድትታይ ያደርግሃል ። እንዲመችህም ይጥራል …. እናት እና አባትህን ፤ ሚስትና ልጆችህንም ጭምር እልም አድርገህ እስክትረሳቸው ድረስ ይስፈነድቅሃል፤ በሀብት ላይ ሀብት፡ በሚስት ላይ ሚስት፡ በስልጣን ላይ ስልጣን ይሰጥሀል፤ ግና ቡረቃው ብዙ አይዘልቅም ….  የአገልግሎት ዘመንህም ማለቁን  ከወያኔ በቀር  እራስህም አታውቀውም ። ወደ ላይ የወጣህበትን መሰላል ቀስ ብሎ  ከስርህ ዞር ሲያደርግብህ ትባንናለህ ፤ በከበሮና በጭፈራ ከፍ ብለህ የወጣሃውን ያክል አሁን በተቃራኒው በሰላም መውረጃ ታጣለህ … ። ከፍ ብለህ እንድትታይ የወጣህበት ከፍታ ላይ ሆነህ በሽብር ፣ በጭንቀትና ብፍርሃት ስትርድ ሁሉም ሰው እንዲያይህ ያደርግሃል ፤ ከዚያም ገፍትሮ ይጥልሃል ። ወይም ዞር ብለህ ስታይ፡ የወጣህበት መሰላል ተነስቶብሀል። አበቃ ማለት ነው ያንተ ነገር ።

ማነው እሱ “የወያኔ ስልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው” ያለው? ስልጣንህ የዛፍ ላይ እንቅልፍ አይነት ናት ፤ ሸለብ ካደረገህ  ከዛፉ ላይ መውደቅህ አይቀርም …. ከወደቅበት መነሳት ከቻልክ የታደልክ ነህ …. ብዙዎቻችን ግን አልቻልንም ! ይህንን ሁሉ የማወራው ለዘመኑ ባለተራ ባለስልጣናት ነው … ለሰራዊቱም አባላት ጭምር ። ቤተሰብ .. ህዝብና ወገንን ከመታደግ የበለጠ ነገር የለም ።

ያ ነው የወያኔ ተፈጥሮ። የወያኔን ሀጢያት ታውቁታላችሁ። እንግዲህ ሃያ አመታት ሙሉ ለአገር የሚጠቅሙ ፣ የሃገር ሃብት የሆኑ ዜጐችን አጥተናል ። ወያኔ እነ ፕሮፌሰር አስራትን የመሳሰሉ እውቅ ባለሙያ፡ እነአሰፋ ማሩን የመሳሰሉ ጎበዝ መምህራን አይናችን ፊት ቆረጣጥሞ ሲበላ ተመልክተናል ። ፍርሃት ይሁን ትዕግስት ብዞዎቻችን ዝምታን መርጠናል ። አንዳንዶቻችን፡ ሻማ ከማብራት ያለፈ የወሰድነው እርምጃ የለም ። እነ ፕሮፌሰር መስፍንን የመሳሰሉ ለምድር የከበዱ አዛውንት በጠመንጃ ሰደፍ አስደብድበናል …… ኢንጅነር ኃይሉ ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ፤ ዶ/ር ሀይሉ አርአያ፡ ያዕቆብ ኃ/ማርያም …… ወዘተ  የመሳሰሉትን ወያኔ በፈለገው ጊዜ አስሮ በአሰኘው ጊዜ ለቋል …. ብቸኛዋን መንፈሰ ጠንካራ ታጋይ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ከጨቅላ ልጇ እና ከአዛውት እናቷ ቀምቶ በጨለማ ጉድጓዱ ከነነፍሷ ቀብሯት ተመልክተናል። አሁኑም ከሻማ ማብራት የዘለለ ማድረግ ነበረብን ……… በቅንጅት ድል ዘመን የታየው የህብረት ክንድ ግን ለኢትዮጵያ አይደለም ለሌላውም ይተርፍ ነበር ። ስለዚህ የያዘን ፍርሃት ነው የሚል እምነት የለኝም ።

እነሆ ያ ሁሉ ሆነና፡ ወያኔ ዛሬም ብዕር ያነገቡ ጋዜጠኞችንና በሰላማዊ መንገድ ትግል የመረጡትን የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችን እያፈነ ወደ ጉድጓዱ ሰዷቸዋል …. እንደኔ ልምድ ከሆነ፡ እነሆ በዚህ ሰዓት የነጻነት ታጋዮቻችን፡ በእስር፡ በማእከላዊ ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው ይሆናል። ጎበዝ፡ በኢትዮጵያ ምድር ሰው በረሀብ እየተቀጣ፡ የእርዳታ ምግብ እየተከለከለ፡ ሕዝብ ለዘመናት ከኖረበት መሬቱ እየተፈናቀለ፡ እያለቀሰ ነው። እንባ፡ አንዳንዴም ደም እንደጐርፍ እየፈሰሰ ነው …. የህዝባችንን ሰቆቃና ግድያ ማቆም ያለብን በህብረት ነው ። ሰራዊቱም የህዝቡ አጋር መሆኑን ደግሞ ማረጋገጥ ይኖርበታል ….. የዓአማ አንድነት ያስፈልጋል። የድርጅት ጋጋታ ግን አያስፈልግም ….። የቅንጅት ዘመኑ የህዝብ ማዕበል ለኢትዮጵያ አይደለም ለሌላውም ይተርፋል ። መቁረጥ ነው። ድርጅቶችም የናቴ መቀነት ጠለፈኝ ሰበባችሁን አቁሙና ወደተስፋይቱ ምድር ምሩን።


ቸር እንሰንብት

ተሾመ ተንኮሉ፡ አየር ኃይል፡ መስከረም፡ 2004/2011

Tuesday, 13 September 2011

ሊበሏት ያስቡአትን አሞራ …

ሊበሏት ያስቡአትን አሞራ …

ወንድሙ መኰንን፣ መሰክረም 1 ቀን 2004 ዓ.ም.

አፓረታይዱ የወያኔ ዘርኛ ሥርዓት ቅጣምባሩ እየጠፋበት መጥቷል። የወሮባላ ሥርዓት መሆኑ እየተነቃበት በሄደ ቁጥር ዓይን-አውጣነቱ ብሶበታል። ዓይኑን በጨው ሙለጭ አደርጎ አጥቦ፣ በደረቁ ሊላጨን ይሞክራል። ኤዲያ! ለሚፈጽመው ወንጀል ሁሉ፣ ወንጀለኛነቱ በግልጽ እየተነበበበት ምን ምክኒያት ያስደረድረዋል? ብልጥ ነኝ ማልቱ ይሆን? ድንቄም! “ውሸት ሲደጋገም ዕውነት ይሆናል” የሚባለውን አባባል ከነጠሬ ቃሉ ወስዶት ይመስል፣ ውሸቱን በየዕለቱ ይተረትረዋል። አሁን አሁንማ፣ ወያኔ ተሳሰቶ ዕውነት ቢናገር፣ ዜጎቻችን “መንገስታችን ታሟል ማለት ነው” እሚሉበት ደረጃ ደርሰዋል። ለምሳሌ አሥራ አምስት ሺ ሕዘብ በረሀብ እየረገፈ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ነግረውን የሰው አጥንት በቴሌቪዢን እያስቆጠሩን ለወገን ድረሱ እየተባለ፣ በረሀብ የተጠቁት የቦረና ከብት አርቢዎች ቀርበው “እኛም ከብቶቻቸንም እያለቅን ነው የወገን ያለህ ደረስልን!” እያሉ ሲማጠኑን፣ “ገንዘቡን ሁሉ የት አደረሱት” እንዳይባል ነው መሰል መቀባዠሩ! የኛ ዘመናዊ ጠቅላይ ሥቃይ መለሰ ዜናዊ አንደለመደው፣ “የለም! ነገሩ አልገባችሁም! አኛ አገር፣ ዕድሜ ለኢህአዴግ፣ ድርቅ እንጂ፣ ወይ እንደ ንጉሡ ዘመን፣ ወይ እንደ ደርጉ ዘመን ረሀብ የለም” በማለት አቀርሸብን። ቅርሻቱን ተቀባብለው ሕዘባችንን ማደንቆር ሥራቸው የሆነው ካደሬዎቹም ያንኑ አስጠሊታ ማደንቆራቸዉን ያራገቡብን ገቡ። ይባስ ብለውም፣ የወያኔ ሬዲዮና ቴሌቪዢን አልበቃ ብሎአቸው፣ ያንኑ የገማና የገለማ የመለስን ቅረሻት ያለወትሮአቸው ቪ ኦ ኤ የአማርኛው አገለግሎት ላይ በእርሻ ሚኒስቴር ዲኤታው  በኩል ብቅ ብለው እንዳለ ዘረገፉብን። ቪ ኦ ኤ ዎች! እግዚአብሔር ይይላችሁ። ሕዘባችንማ ለእንቁጣጣሸ፤
“አበባ አየሸ ወይ? ለምለም!
ዶሮ ወጥ አለሽ ወይ? የለም!
በግ ወጥ አለሽ ወይ? የለም!
ትንሽ ጥበስ አለሸ ወይ? የለም!
ገነዘብ እስኪመጣ፣ ለምለም!
ቀኑ እሰኪወጣ፣ ለምለም!
ልምከርሽ ወይ? ለምለም!
አዴይ - የብር ሙዳይ ኮለል በይ!
አዴይ - ውሀሸን ጠጥተሽ ጋደም በይ!”

እያለ እየቀለደ ርሀቡን ለመረሳሳት የሞከራል። በዚያን ሰሞን “ፈረቃ” የምትል ድራማ ሠረተው እንዳዝናኑን ማልት ነው።

ሰሞኑን ደግሞ ወያኔ የሕዳሴ ግድብ እያለ ሕዝባችንን መዋጮ በመዋጮ ኪሱን እያራቆተው ነው። ያለው አንጡራውን አርከፈክፎ፣ የሌለው ተበደሮ እያዋጣ ነው። የቸገረው ወገናችን በራሱ ስቃይ እያፌዘ ለመዝናናት የሞክራል። “አይ አባይ፣ ለበዙ መቶ ሺሕ ዓመታት አፈራችንን እየሸረሸርክ ያጋዝከው አንሶህ፣ አሁን ደገሞ ኪሳችንን እየበረበርክ ማራቆት ገባህ?” እየተባባለ ይሳሳቃል። ምን ይደርግ?

የወያኔ ሥርዓት የሚተነፍሰው በጠቅላይ ሥቃዩ መለስ ሳምባ ነው። ያ በሲጋራና በጫት የተበከለ ሳምባ ነው እስከአሁን በመጨረሻዋ ደቂቃ ላይ እየደረሰላቸው ነብስ የሚዘራላቸው። እነ ሰዬና ገበሩ ከወንበሩ ሲያነቃነቁት አንዲት ሌሊት ሲያምጥ አድሮ፣ “ቦናፓርቲዝም” የሚል ቅርሻት ተፋባቸው። የ”ቦናፓርቲዝምን” ምንነት ለማወቅ ሲደናበሩ፣ ውሾቹ ተቀርማመቱአቸውና ግሟሹን አሥር ቤት ሲከቱት (በሙስና! ጉድ ነው!)፣ ሌሎቹን አስቦክተው የበላይነትን ተቀዳጁ። እንደዚሁ ወያኔ ተዘናገቶ ሲቀላምድ፣ ቅንጅት ደርሶ ከሥሩ ሲነቀንቀው፣ ጀሌዎቹ ተደናብረው የሚይዙትንና የሚጨብጡትን አጥተው ሲደናብሩ፣ አሁንም መለስ ሆዬ ሲቃዥ አድሮ፣ አንድ ጠዋት “ኢንተርሐምዌ” የምትለውን ቃል አግኝቶ ከብብቱ ሥር አውጠቶ አቀረሸብን። ካድሬዎቹም ያቺን ተቀባብለው ተንጫጩብን። ብዙዎቻችን ግራ ተጋብትን “የድክሺነሪ ያለህ! የኢንሳይክሎፒዲያ ያለህ” እያልን መሯሯጥ ገባን።ነገርዮውን ለማወቅ ስንሯሯጥ ምረጫው ደረሰና በአፍ ጢሙ ደፋው። ኢነተርሐመዌ እንደቦናፓርቲዝሟ ሳትሠራ ቀረች። አሁን መለስ ያፈጠጠ ወንጀል መሥራት ነበረበት። እሱ ወንጀለኛ ሁኖ ሳለ፣ እሱ ከሀዲ ሁኖ ሳለ፣ ነጹሐንን በወንጀልና በሀገር ከሕደት ከሰሰ። ዓለም “ጉድ” እያለም “ዕድሜ ይፍታህ” አሰፈረደባቸው። ከዚያ በሁዋላማ የሚገድለውን ገደሎ፣ የሚያሥረውን አሥሮ፣ ሥልጣኑን ካረጋጋ በሁዋላ “ምሬአቸዋለሁ” በማለት ዓይኑን በጨው አጠቦ ለቀቃቸው። የተወናበዱት የቅንጅት መሪዎችም አዚም እንደዞረባቸው ዋናውን የሀገር ጠላት መለስንና ግብረአበሮቹን ተትው እርስበርስ ሲናቆሩ ብትንትናቸው ወጣ። ያ ዓይን ያወጣ አሠራር በተመጻዋች አገሮች ዘንድ በዙም ጉዳት ሳያስከትል ማለፉ ስለተሳካለት፣ አሁን ዐይን ያወጣ ማጭበርብሩን በጠራራው ፀሐይ በሰፊው ተክኖት ያላንዳች ማወላወልና ማመንታት የማይመስሉ ሰንካላ ምክኒያቶች እየደረደረ ተቀናቃኞቹን አየገደላቸውና፣በዓለም ሕብረተሰብ ዘንድ የሚታወቁትንም እንደ ደበበ እሸቱ ያሉትን በእሥራት እያስወገዳቸው ነው።

ወያኔ የዘመኑን ቴክኖሎጂም ያላገባብ እየተጠቀመ፣ ቅረሻቱን ዩ-ቲዩብ በሚባልው ዜዴ ውጭ ኗሪ ኢተዮጵያውንን ሊበክል ድራማ እየሠራ እየረጨብን ነው። ከነዚህ ድራማዎች መሀል፣ ግንቦት 7 ሊገለብጠኝ ሲሞክር ተከታትዬ እንዴት እንደደረስኩበት እዩልኝ ብሎ የበተነብን የገማ፣ የገለማ የውሸት ዝግንትል የቅርብ ትዝታ ነው። በወቅቱ መልስ ተሰጥቶታል። በጊዜው ያላያችሁ፣ የሚከተለውነ ደረ-ገጽ ይጫኑ። http://wondimumekonnen.blogspot.com/2011/09/blog-post.html። ብሎጌ ነው።

ይኸ ብልግናው በዓለም አቀፍ ሕብረተሰብ ዘንድ ተበልቶበታል። ለምሳሌም ሰሞኑን የወጣው ዊኪ ሊክ እንደሚያስረዳን ከሆነ፣ የአሜሪካን ኤመባሲ ለመንግሥቱ ባስተላለፋቸው የምሰጢር የቴሌግራም መልዕክቶች አዲስ አበባ ውሰጥ በየጊዜው ይፈነዱ የነብሩት ፈንጂዎች፣ ሆን ተበለው የተፈጸሙ “የመንግሥት ሥራዎች” ናቸው ብሎ ደምድሞታል። እንዲያውም አንዱ ጋ ሲያትት ምን አለ መሰላችሁ! “ሁለት ሰዎቸ ከሁለት ቀን በፊት ይያዛሉ። ከሁለት ቀናት በሀዋላ፣  ቦምብ በተጠመደበት፣ ቤት ወሰጥ ከሁዋላ ይቆለፍባቸዋል። የጸጥታ አባሎች፣ ቦምቡን በርቀት ያፈነዱትና (remote control detonation) ያጋዩአቸዋል።” ይታያችሁ። ምስኪኖቹ የወያኔ ጥቃት ሰለባዎች እዚአችው ቤት ወሰጥ ገላቸው በግፍ ተበጣጠቆ ሕይወታቸው አለፈች። ልብ በሉ፣ ይኸንን ጉድ የሚዘከዘኩት፣ የአሜሪካን ዲፕሎማቶች ናቸው። ከዚያ በሁዋላማ የተሠራው ድራማ አሰገራሚ ነበር። “ሸዕቢያ አዲስ አበባን ባግዳድ ለማደረግ የላከቻቸው የኦነግ አባላት ቦምብ ለማፈንዳት ሲገጣጠሙ በድንገት ፈንድቶባቸው ፈጃቸው” ተበሎ ቲያትር ተሠራበት። ወያኔ ውሸት ሀጢአት መሆኑ ጨርሶ አያውአወም። “ሰው ምን ይለኛል”ማ ደሮም በአባሎቹ ህዋስ (DNA) ውሰጥ አልተፈጠረባቸውም። በነሱ ዕይታ ሁሉ ነገር፣ የተገላቢጦሽ ነው። ዕውነትና ውሸት ቦታ ተቀያይረዋል። ወንጀልና ንጽህና ቦታ ተደበላለቆባቸዋል። ከፋትና ደግነት ተምታቶባቸዋል። እነሱ ግን ገራ ግራውን ያዙ።
ይህቺ የተበላባት ዕቁብ ለመሆኑ ከየት መጣች? የመጣቺውማ ከ1997 ነበር። አንደኛውን እንደ ወትሮው ፊትለፊት ተኩሶ መግደል በዓለምአቀፍ ርዳታ ለጋሾች ዘንድ አስወቃሽ  እየሆነ ስለመጣ፣ መለሰ ከብብቱ ስር የመዘዛት “ትሪክ” ናት። ዘዴይቱም “ማስብ” ትባላለች። ከእንገሊዝኛ የተገኘች ቃል  Minimize Accusations and save bullets – MASB ብሎ ነው ለክ እንደቦናፓርቲዝሙ የፈበረካት። በዚህች ዘዴ ሕዝባችንን ቁም ስቅሉን እያሳየውና አበሳውን እያበላው ነው። ሀሳቧን አመጦ የወለዳት መለስ ነበር። በፈረንጆቹ አቆጣጠር ሜይ 8 ቀን 1997 ዓ. ም. አቶ አሰፋ ማሩን በጠራራ ጸሐይ በአውላላ ሜዳ ላይ ተኩሶ ከገደላቸው በሀዋላ ዓለም ከዳር እስከዳር “ዓይንህን ላፈር” አለው። መለ  አምጦ አምጦ "ማስብን" ወለደ።“ማስብ” ብሎም ሰየማት። “ማስብ” የምትባለዋ ኮድ ሥራ ላይ ከዋለች ወዲህ ሕጉንም እነዳሰፈላጊነቱ በመጠመዘዝ ማሰር፣ እንደማጅራት መቺ አደፍጦ መግደል፣ ከተጋለጡም ሽምጥጥ አድረጎ መካድና ፊሸካ ነፊዎቸ ካሉም ማሰፍራራት፣ ሆድ-አደሮችን በጥቅም እየደለሉ ወራዳ ሥራ ማሠራትና ወንጀል ማስፈጸም፣ የመሳስሉን በሰፊው ተያያዙት። ለምሳሌም የመርካቶ  ኪስ አውላቂ የነበሩ ሌቦች አሁን የወያኔ ግብረ አበሮች ናቸው። ሥራ አግኘተው አለፎላቸዋል። ወያኔ ማጅራት ለማሰምታት ይልካቸዋል። የተቃዊሚ አባላትን ቢሮ ሆነ በሎ ሠብሮ ለማዘረፍ፣ ያሠማራቸዋል። የኸንን ጉድ የከዱአቸው የድሮ አባሎቻቸው በመጽሐፍ ሳይቀር አወጥተው እያጋልጡት ይገኛሉ። ተስፋዬ ገበረ አብን ለዋቢነት መጥራት ይቻላል። በዚህም መሠረት በመቶ ሺ ሚቆጠሩተን ዜጎቻቸንን ያለ ጥፋት ጥፋት  እየተፈበረከላቸው ወይ ወህኒ ታጉረል፣ አለበለዚያም ሕየወታቸው ጠፍቶ ደማቸው ደመ-ከልብ ሁኗል። ሰሞኑን ወንድማችንን ተወዳጁንና ታዋቂውን ተዋናይ ደበበ አሸቱን ያጋጠመው የሰበዓዊ መብት ጥሰት የዚሁ የወያኔ ድር ዝግንትል ውጤት ነው።
http://www.ethiotube.net/video/15485/Breaking-News-ETV-News--Artist-Debebe-Eshetu-arrested-for-allegedly-conspiring-with-Ginbot-7

ሁለት ነገሮችን እናስረግጥ። በመጀሪያ ደረጃ፣ ወያኔ የሰበሰባቸው ሙትቻ አሻንጉሊቶች በቀላቢ ጌታቸው በመለስ ትዕዛዝ ግንቦት ሰባትን “አሸባሪ” ብለው ስለፈረጁት ግንቦት ሰባት አሸባሪ ሊሆን አይችልም። እንደዚያማ ቢሆን ሞት የተፈረደበት፣ ዶር ብርሀኑ ነጋ በሰላም አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ወስጥ ባላስተማረም ነበር። ቀጣሪውም በርከሌይ ዩኒቨርሲቲሰ ለምን አይከስም? ሌላው ወያኔ ሞት የፈረደበት፣ አንዳረጋቸውም በሰላም እንገሊዝ አገር እንዴት መኖር ቻለ? ይልቅስ የለየለት አሸባሪ፣ ሕወሀት ነው። ጫካ እያለ የውጭ ዜጎችን በማፈን በአሜሪካን መንግሥት የወንጀል ተመራማሪ መሑራን ከአሸባሪዎች መፈረጁን ዛሬም በሚከተለው ደረ-ገጽ ይነበባል። ወያኔ ሥልጣን ላይ ፈጥ ካለ 20 ዓመት አስቆጠሯል። የዩኤስኤም አንቲ ቴረሪዝም ጓድንት ደረጃም በቀቷል። ምነው እስከዛሬ የህቺ መረጃ አልተሠረዘችለትም?

http://www.start.umd.edu/start/data_collections/tops/terrorist_organization_profile.asp?id=4287

ወያኔ አሸባሪነቱን፣ ዛሬም “መንግሥት” ተበሎም አልተወም። ጎረቤት አገር ደረስ ነብሰ ገዳዮችን ልኮ መቶ አለቃ ጃታኔ አሊን ኬኒያ ውስጥ አሰገደሏል። ሰዎቸን ከጂቡቲ አሳፍኖ ኢትዮጵያ ድረስ አሰውሰዷል። አገር ውሰጥ ከሕግ ውጪ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩትን በሰበብ በአሰባቡ ፈጀቷል፣ አሰፈጀቷል። ያለበቂ ምክኒያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አሰሮ አንገላቷል። ለመሆኑ እነጸጋዬ ገብረመድህንን፣ እነስጦታው ሁሴንን፣ እነአበራሽ በርታን እምን መቃብር ወሸቃቸው?

ሀቁ፣ በብርሀኑም እጅ፤ ሆነ በአነዳረጋቸው እጅ ግን እስካሁን አንዲትም ሕይወት አልጠፋችም። ስለዚህ የለየለት ቴረሪስት የወያኔ መንጋ እንጂ የግነቦት 7 አባላት አይደሉም። ወያኔ የማይመስል ደራማ እየሠራ ባያደነቁረን ምናለበት! ሳታመካኝ፣ ብላኝ ነበር ያለቺው ያቺ ምስኪን እንስሳ? “ዘረፋዬን ሊያሰቆሙበኝ፣ ዘረኝነቴን ሊየስጥሉኝ የሚሞክሩትን ሁሉ አሳድዳቸዋለሁ” ቢል ያምርበታል። ደርግ አንድ የሚያስመሰግነው ነገር ቢኖር፣ የሚፈጽመውን ወንጀል ለመቀባባት አለመሞከሩ ነው። አገር ከሀዲም አልነበረም። ወያኔ ግን፣ ከገዳይነቱም ባሻገር የ’አገር ከሕደት ወንጀሉን፣ ተጠምቆበታል።
ወያኔን ሻዕቢያ እዳንልፈጠርው፣ እንዳልኮተኮተው፣ እንዳላሳደገው፣ ዛሬ ከሻዕቢያ ጋር የተነጋገረውን ሁሉ ከአሸባሪነት እየፈረጀው ያደነቁረናል። የሚገርመው እሱ ትላንት ከሻዕቢያ ጋር “በአንድ አለጋ ካልተኛን፣ በአንድ ጉደጓድ ካለሸናን” እያለ ሲያሰቃየን እነዳልነበረ፣ የሞራሉን ብቃት ከየት አባቱ አምጠቶ ነው ዛሬ ከሻዕቢያ ጋር አትነጋግሩ ሊለን የደፈረው? ለመሆኑ አንቀጽ 37 ሕገ መንግሥቴ የሚለው ውስጥ የተጠነቀረው የማንን ጎፈሬ ለማበጠር ኑሯል? ሻዕቢያ ሁለት የባሕር በሮቻችንን እንደያዘች ኤርትራን እንድትገነጠል ማን ነበር የረዳት? ተገነጣይዋን ጠቅላይ ገዛቴን ዕወቁልኝ እያለ በተባበሩት መንግሥታትና በአፈሪካ አንድነት ኮሪዶሮች ላይ ማን ነበር ኩስኩሰ እያለ ሲለማመጥ የነበረው? ዛሬስ ቢሆን ያ ሰብህት ነጋ የሚሉት ጉደኛ ኤርትራ ከተጠቃች "አለንላት" እያለ ሲፎክርብን ምን ተብሎ ሊተረጎም ይሆን? “ኢትዮጵያ ትበታተናለች እነጂ የ’ኤርትራ ናፅነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ አንፈቅድም” አልነበር ያለን?

ብዙ ብዙ ነገር ማለት ይቻላል። ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ፣ የት ቦታ ነው ከግንቦት ሰባት አባላት ጋር ተገናኝታ የተሰባጠረችው? ጋዜጠኛ እንደመሆኗ፣ የመሰላትን ብትጽፍ “ሕገ መንግሥት” በተባለው የወያኔ ሰንክሳረስ የተፈቀደም አይደል? ዘርይሁን ገበረ እግዚአብሔርና ውብሸት ታዬስ ከሙያቸው ባሻገር ምን ወንጀል ፈጸሙ? የሚገርመው የኤሊያስ ክፈሌ ነገር ነው። አሱን ሊደርሱበትም፣ ሊያንበረክኩትም ስለማይችሉ ቢተውት ይሻላቸው ነበር። መካሪም የላቸው ልበል እነዚህ ጋጠ-ወጦች? ኤልያስን ባያባብሱበት ይበጃቸው ነበር።
አሁን ደበበ እሸቱን ማሰራቸው ወያኔዎች የፈሩትን ሕዝባዊ አመጽ ሊያስቀርላቸው መስሏቸው ይሆን? በግፍ ላይ ግፍ በጨመሩ ቁጥር የኢትዮጵያውያን ንዴትና ቁጭት እየበዛ ነው የሚሄደው።

እንዲህ ዳመኖ ዳምኖ የዘነበ እንደሆን
የጎረፉ መውርጃ፣ በየት በኵል ይሆን?
እንዲህ ጢሶ ጢሶ፣ የነደደ እንደሆን?
የአመዱ ማፍሰሻ በየት በኵል ይሆን?

የተዳፈነ እሳት፤ ጢሶ ጢሶ መንደዱ አየቀርም። ዳመኖ ዳመኖ መዝነቡ አይቀርም። ሰሜን አፍሪካ የዘነመው የሕዝብ አመጽ ዶፍ ኢትዮጵያም የወርዳል። የወያኔ መፈጨረጨር ከጎረፉ አያድነውም። ጠራርጎ ከነዝግንትሉ ይዞት መሄዱ አየቀሬ ነው። ይለቅ ሊበላት የከጀላትን አሞራ ሁሉ ጅግራ ባይላት ከትዝበቱ በተረፈ!!!
በ2004፣ ይደመሰስ የወያኔ ሥርዓት!

Monday, 12 September 2011

ሲሉ ሰምታ ዶሮ ታንቃ ሞተች በገና!

ወንድሙ መኰንን፣ ሎንደን፣ ታኅሣሥ 6 ቀን 2002 ዓ.ም
መቸም የወያኔ ትርዒት ማለቂያ የለውም። በየዕለቷ ይከይኗታል። “ፍርድ” ቤታቸውና “ምክር ቤታቸው/ፓርላማቸው”፣ ዋናዎች የትርዒት መድረክ ስለሆኑ፣ የታወቁቱ ቲያትር ቤቶች ደንበኛ አጥተው ከሰሩ። ወያኔ በየቀኑ ገጽ ባህርይ እየሳለ፣ ድራማ ሲሠራ ማን ገንዘብ ክፍሎ ቲያትር ቤት ሊገባ! ሞኝህን ፈልግ! ያውም ዋናው ተዋናይ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሥቃይ መለስ ዜናዊ እያለ! “ዓይን አውጣ ለይ” ቢባል፣ አዕምሮ ቶሎ ብሎ መለስን ነው የሚቀርጸው። ታዲያ መለስ ብዙ ካድሬዎችን በአውሻሸት ስልት ስለኮተኮተኮተ፣ የዋሾዎች ድራማ በየመንደሩ እንደ አሸን ፈልቷል። የወያኔ ሥርዓት እንዳለ በማጭበርበር ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ከላይ እስከ ታች በአጭበርባሪ ገጽ ባህርያት ተገጥግጧል። ምን ቢያወሩ፣ ምን ቢወሸክቱ አገር ቤት ያለው ሕዝባችን ማዳመጡን ስላቆመ የውሸት ዲሪያቸውን ውጭ ድረስ ዘርግተዋል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ አገር ውስጥ አድማጭ ሲያጡ፣ የቴሌቪዢን ፕሮግራማቸውን ወደ ውጭ ማሠራጨት አምጥተዋል። አገር የናፈቀው ስደተኛና እነሱ በተንኮል አቀነባብረው የላኩት አስመሳይ ተሰዳጅ ያይላቸዋል። ያ አልበቃ ብሎ ያንን የገማ የገለማውን ውዳቂ ፕሮፓጋንዳ፣ በየድህረ ገጹ የውስጥ መረብ (ኢንተርነት) በትነው አካባቢውን እየበከሉት ይገኛሉ።
አንድ ቀልድ ሰሞኑን አምባሳደር እምሩ ዘለቀ አጫወቱን። ቀልዱም እንዲህ ነበር።
አንድ፣ ለብዙ ዓመት ውጪ የኖረ አንድ ኢትዮጵያዊ ወደ አገሩ ተመለሰ። እዚያ እንዳለ አንድ ቆንጆ 42 ኢንች ጠፍጣፋ ስክሪን ተለቪዢን ገዝቶ ለናቱ ሰጥቶ ወደ መጣበት አገር ተመለሰ። ብዙ ጊዜ ውጭ አገር ቆይቶ እናቱን ለሁለተኛ ጊዜ ሊጎበኛቸው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ ያ ሰፊ ስክሪን የነበረው ቴለቪዥን ከቦታው ተነስቶ በምትኩ አንዲት ትንሽ ተለቪዢን ተተክታ ብልጭ ድርግም ስትል ያገኛታል። ግርም ብሎት፣ “እማዬ የገዛሁልሽ ቆንጆና ሰፊ ስክሪን ተሌቪዢን የተ ገባ?” ብሎ ጠየቃቸው። እናትዮዋም “አይ ልጄ የገዛኽልኝ ቴሌቪዢን ጉደኛ ነው። መንግሥት በዋሸ ቁጥር እየተሸማቀቀ፣ ያውልኽ ይኸችን አክሏል” አሉት።

ወያኔዎች አንድ አዲስ የተሳካለት ድራማ ሰሞኑን ሠርተው በዩ-ትዩብ (youtube) እንደ አዲስ አበባው ስንዴ “ረጭተዋል”። አይታችሁታል? ካላያችሁት እዩት እንጂ! እያዩ አንጀት እያረረ መሳቅ ነው።  ማሽላስ እያረረ ይንከተከት የለ! ትርዒቱ አምስት ክፍል አሉት። አምስቱም ክፍል በመገረምና በመደነቅ ዓይን የሚያስፈጥጡ ናቸው። “ቅደድ” ይሉሀል፣ እንዲህ ነው ኢንጂ!
በክፍል አንድ የሌለ ሴራ “ሴራ” ተብሎ “Failed Terrorist Plot in Ethiopia: Part 1”[1] ርዕስ ለብሶ ቀረበልን። ማንም አልሞተም። ምንም ንብረት አልወደመም። ምንም ሙከራ አልተደረገም። ግን፣ “ሽብርና እልቂት ሲሸረቡ ደረስንባቸው” ብለው የማይመስል ትርዒት አቀረቡልን። ዶሮዋ ጫር ጫር፣ ፎከት ፎከት ማድረጓን ትታ፣ የሰማችውን ሥራ ላይ ልታውል ባደረገችው ሙከራ የገባችበቱ ጣጣ መሰል ትርዒት መሆኑ ነው።

መንታ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች (The twin tower) ሲደረመሱ፣ ሕዝብ ሲተረማመስ ይታያል። እኛ እስከምናውቀው ያ ጉድ የተከሰተው በኒው ዮርክ ከተማ ነበር። ቆየት ቢልም ዜናውን እናስታውሳለን። በተዓምር ያ ጉድ አዲስ አበባ እንደተፈጸመ አድርገው ወያኔዎች ሊያጃጅሉን ሞክሩ። ሕዝብ ይተራመሳል። ተተራማሹ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ይመስላል። የአዲስ አበባ የከተማ አውቶቡስም ተጨራምቶ ተደንቅሯል። አቧራው ጨሰ። ድብልቅልቁ ወጣ። የዖሳማ ቢንላዲን ፎቶግራፍ ብቅ አለ። ምን መዓት መጣ! አልቃይዳ አዲስ አበባን አጋያት እንዴ የሚል የስነ-ልቦና ቡካት በተመላክቹ አዕምሮ ተዘራ። ግን ያ እኮ ዝነኛው ቱዊን ታወርስ በመባል የሚታወቀው፣ ሽብርተኞች ኒው ዮርክ ውስጥ ያወደሙት ንብረት ነው እንጂ ነቅለው አዲስ አበባ አላመጡትም። አስተናጋጅ የሚያወራው ስለኢትዮጵያ ነው። ቅጠል ይዘው ትናንሽ ኢትዮጵያውያን እሳት ሊያጠፉ ይሯራጣሉ። ትረካው፣ በቅርቡ በስለላ ሙያ የተካኑ (“የብሔራዊ መረጃና ድኅንነት አገልግሎት” ያሉአቸው) የጆርጅ ኦርዌል የናፖሊዮን ዓይነቱቹ ውሾች፣ የወያኔ ጆሮ ጠቢዎች እንዴት አድርገው ኢትዮጵያን ከአርማጌዶን እንደታደጓት የሚያወሳ ትዕይንት መሆኑ ነው። ዲንቄም! ተባለ እንዴ! የቁንጫ ቁንጥጫ ከአንበሳ ቡትረፋ አይወዳደረም። አቅራቢው፣ ባለ በሌለ ኃይሉ ድምጹን የአዲስ አበባን ሞልቃቃ የአራዳ ልጅ ለማስመሰል ጥሯል። “ም-መሰልህ” የሚል ለመምሰል ሞክሯል። ላደመጠው ግን የአዲስ አበባ ጠርንም ያሸተተው ከደደቢት በርሀ ከወጣ በኋል መሆኑ ይነቃበታል። ለምሳሌ “ሊቀቡት” እያለ ሲናገር የአዲስ አበባ ልጅ አለምሆኑ ይነቃበታል። አፉን አሞጥሙጦ፣ ጉሮሮውን አጥብቦ፣ የሰለለችውን ድምጹን እንድምንም አጎርንኖ እንዲህ በማለት በዜማ ቀጠለ።

“... ይኸ የፊልም መረጃ እንደሚያሳየን ገና ከጅምሩ የብሔራዊ መረጃና ድኅንነት አገልግሎት ይኸንን የጥፋት ተልዕኮ ከጥንስሱ ድርሶበት በቅርበት ሲከታተለው እንደነበረና እንዲሁም፣ በፎቶግራፍና በቪዲዮ ሳይቀር ይቀርጽ እንደነበረ እንመለከታለን።”
ዎዎዎዎ!!!  እንዴት ተቀለደ በል! ምስኪን ዕንቁራሪት ነበረች ዝሆንን ለማከል ብላ ተንጠራርታ፣ ተወጣጥራ፣ ተነፋፍታ ፈንድታ የሞተችው? አቶ አሳምነው ጽጌና ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ የገጸ ባህርይዎቹ ዋና መሪ ተዋናይ ሁነው ተስለዋል። ተከሳሾቹ እንዳይደበደቡ ፈርተው “በሉ” የተባሉትን ለማለት ይንተባተባሉ። ከለፍላፊዎቹ መሀል ሌተና ኮሎሌል የሺዋስ አጥናፈ፣ “የቡድኑ ሥራ አስፈጻሚ” አባልና፣ ሌተና ኮሎኔል አስቻለው አምባቸው እንዲሁ “የቡድኑ ሥራ አስፈጻሚ” አባል ይገኙበታል። የየትኛው ቡድን? የወያኔ ይሥለላ ቡድን? ካልሆነ ሁለቱም ለፍላፊዎች የሥራ “አስፈጻሚ አባል” ሲሆኑ ምነው ምንም ዓይነት ቅጣት አልተበየነባችውም? የአቃቤ ሕጉ ምስክር ናቸው። ሌሎቹ ተደብድበው መሆን አለበት በጤናቸው እንደዚያ የሚወከውኩበት ጉዳይ አይታይም። እንቁራሪት ወያኔ እንደዝሆኑ አሜሪካ ለመከየን ስትነፋፋ፣ ዋ! ፈንድታ እንዳታርፈው!

መቸም  ወያኔ አንድ እንደሞት የሚፈራው ግንቦት ሰባት የተባለ ቡድን ውጭ አገር አለና፣ እንደምንም - እንድምንም ትሪዒቱን ለጥጦት “ሽብር ሲሸርቡብኝ፣ ሕገ-መንግሥቴን ሊያፈርሱብኝ ሲዶልቱ ያዝኳቸው” ካላቸው የቡድኑ አባላት ጋር በማይዛመድ መልኩ አያይዞታል። ባለማፈርም አንዳርጋቸውን ጎዳሁ ብሎ የ80 ዓመቱን አዛውንት አባቱን ሊያነካካ የተደነቀረ የማይመስል ታሪክ ነው። የቅንጂት መሪዎችን ሲያስር ያሳየውን የጠንባ ታሪክ በሌላ መልኩ እንደገና ደገመው። አገር ቤት የሚሰማው ስለማይገኝ ብዙ ሚሊዮን ብር ፈጅቶ አቀናጅቶ በዩ-ትዩብ የውሸት ስልቻውን ተረተረው። የካንጋሩ ፍርድ ቤቱን ተጠቅሞ ለምን ግማሹን በሞት፣ ግማሹን በዕድሜ-ልክ እሥራት እንደፈረደበት ይተርካል። “የጊዮርግስን መገበሪየ የበላ፣ ‘ለፍልፍ ለፍልፍ’ ይለዋል ነው የሚባለው? የሰሩትን ካካ ሰርተው ዝም ብሉስ!
የወያኔ ደናቁርት ትረካቸው ውስጥ አንዲት የማትቀር ተደጋግማ ተበላ የማታልቅ አነጋገር አለቻቸው። “ባንክ መዝረፍ”! እና የፖሊስ ጣቢያ ወርሮ መሳሪያ መንጠቅ። ምክንያት አለቀባቸው መሰል! ከብት መዝረፍም አለ። እህል መዝረፍም አል። ከጓሮ ጎመንም ይዘረፋል። ነጋ ባንክ መዝረፍ! ጠባ ባንክ መዝረፍ! ያለ ባንክ አንዳችም ነገር አያታያቸውም እንበል? ኤዲያ! የሰለቸ ነገር! እንዲያ ነገሩ ዕውነት ቢሆን እንኳን ባንክ ዘራፊዎች ሌቦች እንጂ ከመቼ ወዲህ ነው “ሽብርተኞች” የሆኑት? እራሳቸውን ያሞኙ እንደሆነ እንጂ፣ ኢትዮጵያዊውን ትተን የዓለም አቀፉንም ሕብረተሰብ  ብነውስድ ወያኔ የለየለት የሽብርተኛ ቡድን መሆኑን ጥርት አድርጎ ያውቀዋል። ፍሰሐ ተክሌ የተባሉ ጸሐፊ ያንን ግልጥ አድርገው አስረደተውናል። ተመራማሪው በሰንጠረዥ የወንጀሉ ዓይነት፣ ቀኑና ቦታው ልቅም አደርው መረጃውን ከግርጌ በተጠቁመው አመልካች አስቅምጠውታል።[2]

ለመሆኑ ሽብርተኛ ማለት ምን ማለት ነው። ሽብርተኛ መኖሪያ ሕንጻ፣ የንግድ ሕንጻ፣ የምንግሥት ተቋማት እና ድልድይ ሳይቀር አፍራሽ ነው። ወያኔ ያንን አድርጎታል። ከነጭራሹ “ድልድይ አፍራሽ” የሚል የቅጽል ስም ተጎናጽፏል። ሽብረተኛ ሆስፒታል የሚያቃጥል ጨካኝ ወሮበላ ነው። ወያኔ ያንን ወንጀል በግልጽ ፈጽሟል። ሽብርተኛ ትምሕርት ቤት በቦምብ እያጋየ ሕጻናትን ገዳይ ነው። ወያኔ ድሮ በዚያው መንገድ አልፎ ለመንግሥትነት በቅቶ ዛሬም መንግሥት ከሆነ በኋላ የቀጠለበት ሕጻን ገዳይ ጨካን መንጋ ነው። ሽብርተኛ ሰው ጠላፊ ቡድን ነው። ወያኔ ስንት የውጭ ዜጋ ጥልፎ አሰቃይቷል። ግማሹ ጋዜጠኛ ነበር። ሌሎች የዓለም አቅፍ የዕርዳታ ሠራተኞች ነበሩ። የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ መልቀቂይ ፈተና (ESLCE) ሊፈትኑ ትግራይ ድረሰ ሂደው የታፈኑ የዚህ ጸሐፊ የቅርብ የሥራ ባልደረቦችና ጓደኞች ዛሬም በተአምር ከዚያ ጭካኔ ተርፈው በሕይወት ይገኛሉ። ሽብርተኛ አይሮፕላን ጠላፊ ነው። ወያኔ ያንን ፈጽሟል። ለምሳሌ የካቲቲ 23 ቀን 1977 ዓ. ም (2nd March 1985) ላሊበላ ላይ የጠለፉት የዕርዳት ማጓጓዣ የፈረንሳይ አይሮፕላን እስከዛሬ ቁስሉ ያልሻረለት ጠባሳ የሽብርተኛ ድርጊት ምልክት ነው። ሽበርተኛ ቦምብና መተረይስ አንግቶ ሕዝብ መሐል ገብቶ አራጅ ነው። ወያኔ የወጣለት ነበሰ ገዳይ ነው። ትላንትም ገድሏል፣ ዛሬም እየገደለ ነው። በማንኛውም መለኪያ ወያኔ የሽብርተኞች ቡድን ነው። ለወያኔ ሽብርተኝነት መረጃ ለመፈለግ ሩቅ መሐድ የለብንም።
በመሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘው የሽብርተኛ ቡድን የጥናት ማዕከል፣ በተለይ  “National Consortium for the Study of Terrorism and Responses to Terrorism – START – A centre of excellence for the US Department of Homeland Security Based at the University of Maryland”[3] ወያኔ ትላንትም ሽብርተኛ እንደነበር፣ ዛሬም ሽብርተኛ መሆኑን በደንብ አጥንቶ ቁልጭ አድርጎ ለአሜሪካን መንግሥት ጥቅም አስቅምጦለታል። ታዲያ ግርም አድርጎ ሰውን ቁዝም የሚያደርገው ወያኔ የሽብርተኛ ድርጊቱን በግልጽ እየፈጸመ፣ ሰላምዊውን ሰው ሽብርተኛ እያስመሰለ የሚያቀርበው ቀፋፊና አስልቺ ትርዒቱ ነው።

ክፍል ሁልት፣ ሶስትና አራት እንቶ ፈንቶ የሞላበት ግብስብስ ነው። ገቢያው አይችሌ (አይ ስም አወጣጥ) የተባለ የባንክ ሠራተኛ ለትምህርት ጣሊያን አገር እንደሄደና አንዳርጋቸው ጸጌን እንዳገኘ ነገሩን። ታዲያ ምን ይጠበስ? አንዳርጋቸውን በየጊዜው በየስብሰባው፣ ወይም በየሰላማዊ ሰልፉ እናገኘው የለ? ከባንክ እንዴት ገንዘብ መዘረፍ እንደሚቻል ለመነጋገር ነበር ለማለት ሞከሩ። ከየት? ከጣሊያን ወይስ ከአዲስ አበባ? የማይመስል ወሬ። የአቃቤ ሕግ ምስክር ሁኖ እንደ የሺዋስ እና አስቻለው፣ የተመረጠ፣ የተዋናይነት አኪር ጨረሶ የራቀው ዘላባጅ ነው።
ወደ ዱባይ እንዴት አንድ ቡደን ከወያኔ “የብሔራዊ መረጃና ድኅንነት አገልግሎት” አባል ከሆነች ሴት ጋር እንደሂደ ይደሰኩራሉ። አብራቸው ተኛች አለማለታቸው ገላገለን። ፍተወትን እንደ ቅመም “ጠብ” ቢያደርጉባት ኑሮ የልቦለድ ፊልማቸው ትንሽ በጣመች ነበር። የግንቦት 7ቶቹን ዶር ብርሀኑ ነጋንና አንዳርጋቸውን እንዳገኙት ይናገራሉ። አራቱ ግን አንድ ላይ አይታዩም። የሉማ! ጀነራል ተፈራ ማሞ ትንሽዋን ቡድናቸው (ቲማቸውን) አግዝፈው ለነዶክተር ብርሀኑ ማቅረብ ነበረባቸው ተብሎ ተነገረን። “ምነው” ቢባል፣ “ጠቀም ያለ ገንዘብ ከነአንዳርጋቸው ለማግኘት ነው” አሉን። እንግዲህ ይኸ ጥቂት ቡደን ነበር የወያኔን መንታ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ ሊያደረማምስ የነበረው! ታላቁን የዘረኞችን ባይብል “ሕገ-መንግሥት” ሊንድ የተነሳው! የሕዝብ እልቂት ሊያመጣ ነበር ተብሎ የተሟረተው!! ወያኔ በባዶ ሜዳ፣ “ያዙኝ! ለቀቁኝ! ቡራ ከረይ! ፋሲካ ነጩ! የኦሳማ ቢንላዲንን ተከተአዮች ጨፈለቅኩ” እያለ ሲደነፋ የልጅነታችንን “ሰባት ገዳይ!” ተረት-ተረት አስታወሰን። ገጽ ባህርይ የተላበሱት ተዋናዮቹ እርስ በርስ የሚቀረን ትያትር ሲሠሩ አየን። በአንድ በኵል ገዝፎ ሲቀርብ፣ በሌላ በኵል አንሶ ቁንጫ አከለ። የቱን እንያዘው! ምነዋ ይህ ሁል ቡካት!

ቦምብ፣ መትረየስ፣ የሳተላይት ሬዲዮ፣ ከየክፍለ ጦሩ ተሰብስቦ፣ አንድ ሥራ ፈት ወጣት እንዲያገለባብጥ ተቀጠረ። ወጣቱ አልተከሰሰም። አሁንም የአቃቤ ሕጉ ምስክር ነው። ምን ማድረግ እንዳለበት ብቻ ተነግሮት ከይኬሻው፣ ከየጆኒያው፣ ከየማዳበሪያ ፌስታሉ ጠመንጃውን፣ ጥይቱን እየመዘዘ መሬት ላይ ሲደረድር ታየ። አይ ቅነበር!! ከዶኵመንታሪ ፊልም ይልቅ፣ የሕጻናት የዕቃ-ዕቃ ጨዋታ አስመሰሉት። ተደብድበው፣ ተንገላተው፣ ፊታቸው አብጦ ፍርድ ቤት የቀረቡትን ዓለም እያየ፣ የኛ የውሸት ቋቶች “ምንም ዓይነት ኃይል መገደድ ወይንም መደለያ ሳይደረግባቸው ለዳኛ ያቀረቡት የዕምነት ቃላቸው ላይ እንደምናየው ዓላማቸው ሽበር መፍጠር፣ ሕገ-መንግሥትን ማፍረስ፣ የመንግሥትን ተቋማትን ማፍረስ፣ ብሎም ከሌሎች የሽብር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በአመጽ መንግሥትን ለመጣል ነበር።” እያሉ የውሸት አተላቸውን ደፉብን። ይድፋቸው!
የወያኔ ሕገ አራዊት በሚክየነብት ቲያትር ፍርድ ቤትም ተከሳሾቹ በውሸት ተከሰው የሞትና የዕድሜ ልክ እሥራት ሲፈረድባችው፣ የቅጥፈት ድርሰት አንባቢው “ሊንዱት የተነሱት ሕግ-መንግሥት፣ መብታቸውን ጠበቀላቸው” እያለ ሲመጻደቅብን ይስማል። የፊልሙ አቀናባሪ እና ደረሲ አቃቤ ሕግ በሪሁ ተ/ብርሀን (ስሙን ልብ ብላችሁ ያዙት። እንድ ቀን ዕውነት ትፋረደዋለች) ቀርቦ፣ ቅርሻቱን ተፋብን። ለምን 5 ሰዎች እንዲገደሉ፣ 33 ሰዎች ዕድሜ ልክ ጽኑ እሥራት፣ 2 ሰዎች በአሥር ዓመት እሥራት እንደተፈረደባቸው፣ የተቀረው ደግሞ ምስክር ሁኖ በነጻ እንዲለቀቁ  እንደተደረገ እየተንተባተ ሊያሳምነን ሞከረ። ወይ መጨማለቅ!

የሚገርመው በአምስተኛውና በመጨረሻው ክፍል፣ የታዩት የአንዳርጋቸው ጽጌ መኖሪያ ቤቶች ናቸው የተባሉ ሁለት በረቶች ናቸው። አንዱ ዙሪያውን በግንብ የታጠረ፣ ፎቅ ቤት ነው። መቸም አውሮፓ ውስጥ ሊሆን አይችልም። ሌላው ግዙፍ የሆነ ቤት ነው። እንግሊዝ አገር ኗሪዎች እንዲህ ዓይነቱን ሕንጻ ያውቁታል። የአንድ ሰው ሳይሆን ከሶስት መቶ እስከ-አምስት መቶ ሰዎች የሚኖሩበት የቀበሌ የወል ቤት (Council House) እንጂ የአንድ ሰው ተብሎ ሊታይ አይችልም። ምናልባት፣ አቶ አንዳርጋቸው እዚያች ሕንጻ ውስጥ ከኖረ፣ የአንድ መኝታ ክፍል ያላት የቁጠባ ቤት መሆን አለባት እንጂ ያንን ሕንጻ በሙሉ መኖሪያ ቤቱ ሊያደርገው የሚችል ከቶም ተአምር አይኖርም። መቸም ነገርን ማጋነን ልማዳቸው ነውና ጠቅላላውን የወል ሕንጻ (building complex) የአንዳርጋቸው መኖሪያ ቤት አስመስለው ያለ አንዳች ሀፍረት አቀረቡት። ዱርውንስ መች ሀፍረት ተፈጠረባቸውና!
የተመልካቹን ሥነ-ልቦና ለማኮላሸት፣ በመጀመሪያ ክፍል የታየው አሰቃቂ እልቂት የመጨረሻው ክፍል፣ ይደግመዋል። እሳት ትምሕርት ቤትን ያጋያል። ሕጻናት እርጥብ ቅጠል ይዘው የሚጨሰውን እሳት በዚያ ቅጠል ይጠበጥቡታል። አዎቶቡስ ተጋጭቶ ይሁን ምን እንደነካው አይታውቀም ተጭረማምቶ ቁሟል። እንዲሁ ጭርምትምቱ የወጣ፣ ምናልባትም ሰሜን ጦር ግንባር ላይ ሻዕቢያና ወያኔ ሲፋለሙ የደረሰ አደጋ ሊሆን ይችላል፣ መኪናዎች ከጥቅም ውጩ ሁነው ይታያሉ። ሆቴል አይሉት ትምሕርት ቤት ውስጥ፣ በእሳት ጋይተው የተጨረማመቱ ጠርጴዛዎችና ወንበሮች ይታያሉ።

ሽብርተኛው ወያኔ፣ እራሱን ለጥፋት ሳይሆን ለልማት እንደቆመ፣ እነብርጋዴር ተፈራ ማሞንና ሌሎችን በሀሰት የተከሰሱትን ተጎጂዎች ግን፣ አንዲት ጥይት እንኳን ሳይተኩሱ፣ ሕዝብ እንደፈጁ፣ የፈሰሰ የእንስሣ ይሁን የሰው አይታወቅ-ደም ወለሉን እንዳስጨቀዩት፣ ንብረትን ውደም እንዳደረጉ አሳይተው ሊያሞኙን ሞክረዋል።
ወየኔ እራሱ ሽብረተኛ ሁኖ ሰላማዊውን ሽብርተኛ አድርጎ ማቅረቡ ለራሱ መጽናኛ ይሆን እንደሆነ እንጂ አንድ ሰው እንኳን አታሎ ማምለጥ የማይችልበት ድረጃ ላይ ይገኛል። ይኽ ያፋኝ ቡድን ማወቅ ያለበት አንድ ነገር አለ። ታኅሳስ 4 ቀን 1960 ዓ.ም እነ ጄነራል መንግሥቱ ነዋይ፣ ጃንሆይ ላይ አመጹና ተገደሉ። የንጉሱን ዙፋን ግን ለክፈውት አነቃነቁት። የተነቃነቀው ዙፋን ወዲያው ባይወድቅም መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ ም ተገልበጠና ንጉሡ እንደማይሆን ሁነው ተገደሉ። ወተደራዊ ደርግ ሥልጣን ያዘ። የዚያ መሪ ጨካኙ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ሕዝቡን አመሱት፣ ጨፈጭፉት፣ ፈላጭ ቆራጭ ሁነው ተዘባነኑ። እነ ጄነራል ፋንታ በላይን ላከባቸው። ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ. ም ሊገለብጡአቸው ተነኮሱአቸው። ያኔ የመንግሥቱ ወታደሮች የበላይነቱን ይዘው ቢያተርፉትም የተነቃነቀው ጥርስ መነቀሉ አይቀርምና የኮሎኔል መንግስቱ ሥልጣን ግንቦት 20 ቀን 1983 ተፈንቅሎ በምትኩ ወያኔ ስልጣን ያዘ። የምኒሊክ ቤተ መንግስት ሟርተኛ ነው። ዛሬ እነ ጄነራል ተፈራ ማሞ መለስን ለመገልበጥ ሞክራችሁአል ተብለው የሞትና የእድሜ ልክ እሥራት ተፈርዶባቸዋል። ነገሩ ሟርት ነውና የመለስ ዜናዊም መንግሥት ማጠሩን ማብሰሪያ ንገርት ነው። ምንም ዓይነት ድራማ ቢደርቱ ያቺን ጽዋ ሳይጠጡአት አያልፉአትም። ታላቋ አገር አሜሪካ የምታደርገውን ጸረ-ሽብር ወታደራዊ እርምጃ እኛም እንወስዳለን ብሉ መንጠራራት ትርፉ መላላጥ ብቻ ነው። ኦሮሞ ወንድሞቼ ሲተርቱ፡ “እንደ እከሌ ልዝፈን ማለት ማጅራት ይቆለምማል” ይላሉ። ወያኔ ድራማ ሠርታ ለጊዜው ለስሟ ቁና ሰፍታለች። ቁናው ግን በቅርቡ በእሳት ይጋያል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የወያኔ ግፍ አንገሽግሾት አንገቱ ደርሷል። የለውጥ ሽታ ከአድማስ ባሻገር ይሸታል!



[1] http://www.youtube.com/watch?v=dQlXBKZXOzs
[2] http://www.ethiomedia.com/fastpress/tplf_vs_violence.pdf
[3] http://www.start.umd.edu/start/data/tops/terrorist_organization_profile.asp?id=4287